የሰፊው ሕዝብ ድምፅ
ቁጥር 36፣ ጥር 10፣ 1968
የፅሁፉ ፍሬ ሀሳብ
መኢሶን በዚህ የሰፊው ሕዝብ ድምፅ እትሙ፣ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ትግል ይበልጥ እየተደራጀና እየተቀነባበረ ሲሄድ፤ ድልን ለመጎናጸፍና አዲሲቷን ኢትዮጵያ ለመመሥረት የሚያስችል ተስፋ እንደሚሰጥ ያረጋግጣል። ወደፊትም በሕዝቦች ጽኑ ትግል የምትመሠረተው ኢትዮጵያ፣ ሕዝባዊ ዲሞክራቲክ ሪፑብሊክ እንደምትሆን ይጠቁማል። በፊውዳሊዝምና በኢምፔሪያሊዝም ላይ ሕዝባዊ ድል የሚገኘው በነቃ፣ በተደራጀና በታጠቀ የረጅም ጊዜ ትግል መሆኑ እንደማያጠያይቅ ይገልጻል።
የኢትዮጵያ ሕዝቦች ለነፃነት፣ ለእኩልነት፣ ለእድገትና ለሰላም በሚያደርጉት መራራ ተጋድሎ ብዙ ድሎችን እንደተጎናፀፉ እሙን ነው። ለወደፊቱም ገና ብዙ ተጋድሎ፣ ገና ብዙ ውጣ ውረድ የሞላበትና እጅግ የተወሳሰበ ትግል ይጠብቃቸው እንጂ፣ ትግላቸው በበለጠ እየተደራጀ፣ በበለጠ እየተቀነባበረና በበለጠ እየተጠናከረ በሄደ መጠን ደግሞ፣ በድል ላይ ድልን እየተጎናፀፉ እውነተኛ ነፃነትና እኩልነት የሚሰፍንትን አዲሲቱን ኢትዮጵያ መመስረታቸውና መገንባታቸው የማይቀር ነው። ይህች፣ ዛሬም ሆነ ለወደፊቱ ገና ለረጅም ጊዜ የኢትዮጵያ ጭቁን ሕዝቦች በመላ የሚታገሉላት አዲሲቱ ኢትዮጵያ ከሕዝባዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሌላ ልትሆን አትችልም።
በዛሬው ወቅት የኢትዮጵያ ሕዝቦች ዋና ጠላቶች ፊውዳሊዝም፣ ኢምፔሪያለዝምና ቢሮክራሲያዊ ካፒታሊዝም ናቸው። ጊዜ ይፈጃል እንጂ፣ ከአቢዮታዊው የትግል ማዕበል ውስጥ የገቡት ተራማጅ መደቦችና ኃይሎች ሁሉ፣ ዛሬ የተበታተነ የሚመስለውን ትግላቸውን አቀነባበረው በዋና ጠላቶቻቸው ላይ በሕብረት መነሳሳታቸው ከቶ የማይቀር ነው። የኢትዮጵያን ጭቁን ሕዝቦች ሙሉ ድልን የሚጎነፀፉት ጠንካራ ክንዳቸውን አቀናጅተው ሲነሱና በነቃ፣ በተደራጀና በታተቀ ትግላቸው አማካይነት ብቻ እንደሆነ ከትግላቸው መማራቸው፣ በትግላቸው መረዳተቸው ከቶም አይቀርም። ይሁን እንጂ፣ የኢትዮጵያን ጭቁን ሕዝቦች አብታዊ ትግል ከነጭራሹ ለመቅጨት ወይም በየምክንያቱ ለማሳበር ከተነሳሱት አድሃሪና ተራማጅ-መሰል ኃይሎች ጋር በየእለቱ መራራ ትግል ካላካሄድን ደግሞ፣ በበለጠ የመደራጀቱ፣ በበለጠ የመቀነባበሩና በበለጠ የመጠናከሩ ጥያቄ እጅግ ሊራዘም እንደሚችልም ከሁኑ መረዳት ይኖርብናል።
በዛሬው ወቀት በተለይም ከተራማጅ-መሰል ኃይሎች ጋር የሚያደርገው ትግል ለጠቅላላው እንቅስቃሴ የበለጠ ጥራትን ለመስጠት የሚደረግ ትግል እንጂ፣ አንዳንዶች እንደሚያስቡት ለንትርክ፣ ለጭቅጭቅ ወይንም ደግሞ ለፀጉር ፈለጣ የሚደረግ ትግል አይደለም። ሌኒን “የግራ ክንፍ ኮሙኒዝም- የጨቅላነት በሽታ” በሚለው መጽሃፉ ውስጥ ስለቦልሼሺክ ፓርቲ መጠናከር አንስቶ ሲናገር፣ እንደገለፀው “በውጭ አገሮች ዘንድ ስለቦልሼሽክ ፓርቲ የማይታወቅ መሠረታዊ ጉዳይ ቢኖር፣ የቦልሼሽክ ፓርቲ ያደገውና እንደብረት ሊጠነክር የቻለው አንድ አናርኪዝም-አናርኪዝም ከሚገማው የንጉስ ከበርቴ ሪቮሉሺንዝም ጋር ለብዙ አመታት ባደረጋቸው ትግሎች ምክንያት ነው ይላል። (ሌኒን፣ ምርጥ ፅሁፎች፣ ቅፅ 3፣ ቅፅ 358)። እኛም ሌኒንን ተከትለን፣ በተለይም ዛሬ የወጣቱን ትውልድ በማርክስና በሌኒን ስም የተደባለቀውን የንጉስ ከበርቴ ደንፊ ቡድን ከዛሬው ካልጋለጥነውና [የአዘጋጆች እርማት] ካልታገልነው የጨለማውን ዘመን ለማራዘም ብቻ የምንረዳ “ፍጡራን” መሆናችንን በትክክል ማመን ይኖርብናል።
ከየካቲት 1966 ዓ.ም በፊትም ሆነ በየካቲቱ ሕዝባዊ አብዮታዊ እንቅስቃሴ ወቅት፣ የኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ቁልጭ አድርጎ ያሳየው ሀቅ ቢኖር፣ ለእንቅስቃሴው የፖለቲካና የእርዮተ አለም አመራር ሊሰጥ የሚችል አብዮታዊ ድርጅት ወይንም ፓርቲ እንዳልነበረ ነው። የየካቲቱ ሕዝባዊ አብዮታዊ እንቅስቃሴ ዛሬም ሆነ ለወደፊቱ በሀቀኛ አብዮታዊያን ዘንድ ሺህ ጊዜ ተደግሞ የሚነሳው አብይ ጥያቄ፣ የአብዮታዊ ድርጅትን አመራር ጥያቄ መሆኑን በቅጡ አስተምሮናል። በተጨማሪ ግን፣ መልክና ሥርዓት ያለው አብዮታዊ ትግል ያለ አብዮታዊ ድርጅት እንደማይኖር ሁሉ፣ አብዮታዊ ድርጅት ደግሞ ያለአብዮታዊ ትግል የማይገኝ መሆኑንም ገና በቅጡ መረዳት ይኖርብናል። በተለይም የተራማጁ ሰፈር፣ ዛሬ ሰርጎ ከገባበት “የንጉስ ከበርቴ ሪቮሉሽኒዝም” ነፃ ሆኖ፣ ኃይሉን አስተባብሮና ባለው አቅም ሁሉ ተጋግዞ በፊውዳሊዝም፣ በኢምፔሪያሊዝምና በዲሞክራሲያዊ ካፒታሊዝም ላይ እንዲረባረብ የምንታገል አብዮታዊያን ሁሉ፣ ለአብዮታዊ ድርጅት አብዮታዊ ትግል ማካሄድ እንዳለብን ካሁኑ በቅጡ መረዳትና ይህንኑ በተግባር መገለጽ አለብን።
በተለይም ዛሬ የኢትዮጵያን ወጣቶች የተራማጅ ለምድ ለብሶ የተደባለቃቸው የንኡስ ከበርቴ ደንፊ ቡድን የመረጠው የትግል ዘዴ፣ አንገብጋቢ በሆኑት ለፖለቲካ ጥያቄዎች ላይ መወያየትና መስመርን ማጣራት የሚለውን አብዮታዊ የትግል ዘዴ ሳይሆን፣ በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ “ውዠንብርን መንዛት” የሚለውን የአድሃሪዎች የትግል ዘዴ እንደሆነ በገሀድ እየታየ ነው።[1] ይህ የንኡስ ከበርቴ ደንፊ ቡድን ከረጅም ጊዜ ጀምሮ ስራዬ ብሎ የትግል ዘዴ የተራማጅ ግለሰቦችን ስም ማጥፋት፣ ተራማጅ ግለሰቦችን መጠቆምና የፈጠራ ወሬዎችን በመንዛት ማወናበድና የተራማጁን ሰፈር በሆነ ባልሆነው ምክንያት መከፋፈል እንደሆነ አገር እያወቀለት ሄዷል። በዚህ ተግባሩም መላው የአድሃሪ ሰፈርና ሲ.አይ.ኤ. አብረውት ያሽቃብጣሉ።
በሌላ በኩል ግን፣ እንደዚህ ያለው አፀያፊ የትግል ዘዴ በእውነተኞቹ ተራማጆች ዘንድ ከቀን ቀን በበለጠ እየተነቃበትና እየተወገዘ በመሄድ ላይ ነው። እውነተኛ ተራማጆች ሁሉ የሚሹት የትግል ዘዴ በተጨባጭ ጥናቶች ላይ የተመረኮዘ፣ ግልፅና ሃቀኛ ውይይት፣ አብዮታዊ ሂስና ግለ-ሂስ፣ ቅን ነቀፌታዎችንና መተራረምን፣ ከዚያም እንደብረት የጠነከረ አንድነታቸውን እንጂ፣ የንኡስ ከበርቴው ደንፊ ቡድን በየጓዳው እየፈተለ የሚረጫቸውን የፈጠራ ወሬዎች አይደለም። እውነተኞቹ ተራማጆች የሚያምኑት “በፖለቲካ ጥያቄዎች ላይ ብቻ በመከራከርና በመወያየት የፖለቲካ መስመርን ማጣራት” በሚለው አብዮታዊ መመሪያ እንጂ፣ በሃሜት፣ በፈጠራ ወሬ፣ በስም ማጥፋትና በጥቆማ ዘመቻ ወይንም ደግሞ ከናካቴው በበትር መዘዛ አይደለም። የንኡስ ከበርቴው ቡድን አንዴ እየሸሸ፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ ከቃላቶች፣ ከቅጽሎች፣ ከአሳሳች መፈክሮችና ከአወናባጅ ጥቅሶች በስተጀርባ እየመሸገ፣ በሌላ ጊዜም ዱላ ዱላ እያለው ይቁነጠነጣል እንጂ፣ ከፖለቲካ ክርክር ውስጥ እንዲገባና እውነተኛ መልኩን እንዲያሳይ መገደዱ እንዲሁ ከቶም የማይቀር ነው።
የዛሬውን የፖለቲካ አካባቢ በአንክሮ የሚከታተል ሰው ሁሉ በግልጽ የሚረዳው አንድ ነገር አለ። ይኸውም በተራማጁ ሰፈር ውስጥ ያሉት የፖለቲካ መስመር ልዩነቶች በተለይም በብዙሃኑ ወጣትና በተራማጅ ምሁራን ዘንድ ከሞላ ጎደል እየታወቁ በመሄድ ላይ መሆናቸውን ነው። እነዚህ የመስመር ልዩነቶች በትግል እሳት እየተፈተኑ፣ በበለጠ እየተብራሩ፣ እየተብላሉና እየተጣሩ በሄዱ መጠን ደግሞ፣ የተራማጁ ሰፈር በመላ ዛሬ “አለሁ! አለሁ!” እያለ በኢትዮጵያ ሕዝቦች መራራ ትግል ላይ ክፉኛ የሚያላግጠውን የንኡስ ከበርቴ ደንፊ ቡድን አንቅሮ እንደሚተፋውና ለትክክለኛው አብዮታዊ መስመር እንደሚሰለፍ ከቶም ለመጠራጠር አይቻልም። ነገር ግን፣ አሁንም ሌኒን እንደሚያስተምረን “የተጀመረው የፖለቲካ መስመር (የፖሌሚክስ) ክርክር ፍሬ ሊሰጥ እንዲችል፣ ወደ ግለሰቦች ሽኩቻ እንዳያመራ፣ የውዠንብር መንዣ መሳሪያ እንዳይሆንና ወዳጅና ጠላቱ በወጉ የሚለይበት ክርክር እንዲሆን ደግሞ ቅን ጥረቶችን ማድረግ እጅግ አስፈላጊ ነው። ፖሌሚክስ ጥቅም የሚሰጠው የልዩነቶቹን አርእስት ግልጽ ሊያደርግልን ሲችል ብቻ ነው። እንደዚሁም፣ የልዩነቶቹ ስፋት እስከምን ድረስ እንደሆነ ሊያመለክተን ሲችልና መሰረታዊዎቹን ልዩነቶች በአንዳንድ በከፊል ጥያቄዎች ላይ ያሉትን ልዩነቶች በግልጽ ሊያበስርልን ሲችል ነው።” /ሌኒን፣ ኤ ድራፍት ኘሮግራም ኦፍ አወር ፖርቲ፣ ከሙሉ ስራዎቹ፣ ቅጽ 4፣ ገጽ 231/
እኛም ግልጽና ሃቀኛ ውይይቶች እንዲካሄዱ ከፈለግን፣ የተራማጁ ሰፈር በዛሬው ወቅት የሚከራከርባቸውን የፖለቲካ መስመር ጥያቄዎች በግልጽ ማቅረብ ይኖርብናል። በኛ ግምት ዋና ዋናዎቹ የልዩነት አርእስቶች የሚከተሉት ናቸው።
1ኛ/ ለጊዜያዊ ሕዝባዊ መንግስት ወይንስ ለነቃ፣ ለተደራጀና ለታጠቀ የሕዝብ ትግል
2ኛ/ የዛሬይቱ ኢትዮጵያ ዋና ቅራኔ
3ኛ/ ደርጉና የተራማጆች አቋም
4ኛ/ ዘመቻውና የዘማቾች አብዮታዊ ተግባር
5ኛ/ እስካሁን የወጡት አዋጆችና የተራማጆች አቋም
6ኛ/ አብዮታዊ ድርጅትና አብዮታዊ የትግል ዘዴ
ጥያቄዎቹን ተራ በተራ የዘረዘርነው ለአቀራረብ እንዲያመች እንጂ፣ የተያያዙ ለመሆናቸው አንድና ሁለት የለውም።
የሰፊው ሕዝብ ድምጽ በተለያዩ ጊዚያት በነዚህ ሁሉ ጥያቄዎች ላይ ያሉትን አቋሞች በየጊዜው ገልጿል። (ቁጥር . . . . 30፣ 31፣ 33፣ 34፣ 35 ተመልከት)። ለወደፊቱም እንደዚሁ ይቀጥላል። እርግጥ ከዚህ ላይ መወሳት የሚገባው የሰፊው ሕዝብ ድምጽ ቀደም ሲል “ጊዜያዊ ሕዝባዊ መንግስት” የሚለውን መፈክር ይደግፍ እንደነበረ ነው። ይህ ጋዜጣ ይህንን መፈክር በአንድ በተወሰነ ጊዜ ይዞ ተነስቷል፣ ታግሎበታልም። በአንድ በተወሰነ ወቅት ትክክል ነው፣ ለትግሉ መግፋት ይጠቅማል ብሎ የወሰደውን መፈክር ዛሬ ፍፁም አድሃሪ መፈክር በሆነበት ወቅት እኝኝ ብሎ መያዙ ከፀረአብዮት ኃይሎች ጋር እንደሚያስፈልገው በመገንዘብ ትቶታል፤ እንዲያውም ይታገለዋል። የየጊዜውን ተጨባጭ ሁኔታ እያጠኑ ለተጨባጭ ሁኔታው ተስማሚ የሚሆነውን የትግል መስመር መቀየስ ደግሞ፣ አብዮታዊ የአሰራር ዘዴ እንጂ፣ የንኡስ ከበርቴው ደንፊ ቡድን ሊያምን እንደሚፈልገው አላማን መተው አይደለም። ዛሬ በመሳሳትም ሆነ በመወናበድ በዚህ ጥያቄ ላይም ሆነ በሌሎች ጥያቄዎች ላይ የተሳሳተ አቋም ይዘው የሚኳትኑ ሃቀኛ ተራማጆች ስህተታቸው የሚያስከትለውን ጉዳት አጥብቀው በመገንዘብ ስህተታቸውን የማያርሙበት ምክንያት አይታየንም። ለዚህም ሌኒን ጥሩ ምክር ይሰጠናል። ሌኒን “የግራ-ክንፍ ኮሙኒዝም የጨቅላነት በሽታ” በሚለው መጽሃፉ ውስጥ እንዳለው፡
“አስፈላጊዎቹን ማሻሻያዎች አድርገን ብናነፃጽር፣ የፖለቲካ መስመር ክርክር /ፖለሚክስ/ የጠቅላላው እንቅስቃሴ መልእክት መሆኑን ካስረዳ በኋላ ስለግለሰቦች ያለን አስተሳሰብ ለፖለቲካና ለፖርቲዎችም ጭምር ሊያገለግለን ይችላል። (እንደሚታወቀው) ብልሁ ሰው ጨርሶም የማይሳሳተው ሰው አይደለም። ሊኖርም አይችልም። ብልሁ ሰው እጅግ ከፍተኛ ስህትቶችን የማይፈጽመው ሰው ነው። እንደዚሁም ስህተቶቹን በቀላሉና ወዲያውኑ ሊያርም የሚችለው ሰው ነው።” (ሌኒን፣ ምርጥ ስራዎች፣ ቅጽ 3፣ ገጽ 361)።
ወደ ትግል ዘዴው እንመለስና፣ የንኡስ ከበርቴው ደንፊ ቡድን አምርሮ የያዘው የትግል ዘዴ በትርኪ ምርኪው ማወናበድን እንጂ፣ በፖለቲካ ጥያቄዎች ላይ በግልጽ መከራከሩን፣ መወያየቱንና አቋሙን ማጣራቱን እንዲሁ አልደፍር ብሏል። በዚህ አያያዙ፣ የፖለቲካ ጥያቄዎች በተነሱበት ቁጥር እንደአላቂ ሳሙና እየተሙለጨለጨ ቢያስቸግር ከቶም የሚያስደንቀን ነገር አይሆንም።
የንኡስ ከበርቴው ደንፊ ቡድን አድሃሪ የትግል ዘዴ እርቃኑን የሚቆመው “ተከታዩቼ እንደሆኑ ሳይታለም(!) የተፈታ (!)ነው” /ሰርዝና ቃለ አጋኖ ከሰህድ/ የሚላቸው የህብረተሰባችን ክፍሎች /ማለትም አስተማሪ፣ ተማሪ፣ ምሁር፣…/ ጥያቄዎችን ሲያነሱበትና ጐትተው ከፖለቲካ ክርክር ውስጥ ሲያስገቡት ነው። አንዴ የፖለቲካ አቋሙንና መስመሩን ከቁጥር ቁጥር እንደሸሚዝ እያቀያየረ አጋጊጦ ይቀርባቸዋል። ሲሻው ደግሞ “ከኔም ወዲያ አብዮታዊ ላሳር ነው” በሚል ጉራ ተነፋፍቶ ብቅ ይላል። ነገር ግን፣ በአንዲት በራሪ ወረቀት ሲጋለጥ ደግሞ፣ እንደሱም ሽሽት ሽሽት የሚለው፣ እንደሱም የሽምጡን የሚፈረጥጥ “አብዮታዊ” ከቶም አይገኝም።
“ሳይታለም የሚከተሉት” አብዮታዊ ኃይሎች “በጽሁፎች ላይ እንከራከር፣ እንወያይ፣ መስመራችንን እናጣራ . . . ወዘተ” ሲሉት፣ ለንኡስ ከበርቴው ደንፊ ቡድን የተከሰተለት “አብዮታዊ” የትግል ዘዴ “አታንቡ፣ አቃጥሎ፣ ከኔም ወዲያ . . .” የሚለው አድሃሪ የትግል ዘዴ ነው። በበኩላችን የንኡስ ከበርቴው ደንፊ ቡድን ዛሬ በጥቂት በራሪ ወረቀቶች አማካይነት በመጠኑ ስለተጋለጠ፣ የሚያጋልጡኝን ጽሁፎች ሁሉ “አጥፉ፣ አቃጥሉ” እያለ ቢዘምት እስከዚህም አንደነቅም። ከዚህም አልፎ ነገ ጥዋት በነሌኒን ጽሁፎች በበለጠ ሲጋለጥ ደግሞ፣ እነሱንም “አቃጥሏቸው” ቢለን እንኳን እስከዚህም አንደነቅም። ምክንያቱም፣ ለመጀመሪያው “በመደብ ትግል ይሉኝታ እንደሌለ” እናውቃለን። ሁለተኛም፣ ከበርቴው ደንፊ ቡድን የሚታገለው ለነቁና ለተደራጁ ታጋዩች ሳይሆን፣ ለ“ጀሌዎች” እንደሆነ ታሪክ ደጋግሞ አስተምሮናል። ይህንን የታሪክ እውነት የኛዎቹ የንኡስ ከበርቴ ደንፊዎች ቢደግሙት እናዝን እንደሁ እንጂ፣ አሁንም በበለጠ መታገል እንዳለብን በበለጠ እንረዳ እንደሁ እንጂ፣ አንደነቅም። ይኸው ቡድን ዛሬ ስራዬ ብሎ ለያዘው የስም ማጥፋትና የጥቆማ ዘመቻም ያለን አቋም ከዚሁ የተለየ አይደለም።
የሰፊው ሕዝብ ድምጽ የጊዜው ዋና ጠላቶች ፊውዳሊዝም፣ ቢሮክራሲያዊ ካፒታሊዝምና ኢምፔሪያሊዝም እንደሆኑ ደጋግሞ አመልክቷል። በነዚህ ዋና ጠላቶችና በኢትዮጵያ ሰፊ ሕዝብ መካከል ያሉት ቅራኔዎች ጨርሰው ሊታረቁ የማይችሉ ናቸው። ስለሆነም፣ እነዚህን ዋና ጠላቶች ለመደምሰስ የሚተጋገዙት አብዮታዊ መደቦችና ኃይሎች በሙሉ ባላቸው አቅም ሁሉ በዋና ጠላቶቻቸው ላይ መረባረብ ይኖርባቸዋል። የሰፊው ሕዝብ የፈላጭ ቆራጭነት አገዛዝ የሚነግሰው በዋና ጠላቶቻችን መቃብር ላይ ብቻ እንደሆነ ሳይሰለቹ ማስተማር ይኖርባቸዋል። ለዚሁም፣ ሰፊውን ሕዝብ ለነቃ፣ ለተደራጀና ለታጠቀ ሕዝባዊ ትግል በትእግስት ማዘጋጀትና መምራት ይኖርባቸዋል። በሌላ በኩል ግን፣ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ለማይቀረው መራራ ትግል በየእለቱ በበለጠ ለመዘጋጀት እንዲችሉ ደግሞ፣ ሰፊውን ሕዝብ በጊዜያዊ ጥያቄዎች አካባቢ እየቀሰቀሱ በአንድነት መሰብሰብና ማሰለፍ የያንዳንዱ ተራማጅ ተግባር ነው። የጊዜው ዋና ጥያቄዎች ዲሞክራሲያዊ መብቶችና የሰፊው ሕዝብ መታጠቅ እንደሆኑ የሰፊው ሕዝብ ድምጽ ደጋግሞ አመልክቷል።
በመጨረሻም በመሀከላቸው ያሉትን የሁለተኛ ደረጃ ቅራኔዎች በደረጃቸው ለመያዝና ለማስወገድ እንዲችሉ ግልጽና ቅን ውይይቶችን ማድረግ አለባቸው። ይህንን እውነት በመሸሽ፣ ተራማጆችን በማርክስና በሌኒን ስም ማወናበድ፣ መከፋፈል፣ ወይንም ደግሞ በስም እየጠሩ ለጠላት አሳልፎ መስጠት፣ ያለዚያም በዱላ ጭምር ለማስፈራራት መቁነጥነጥ ግን፣ በምንም አይነት ሃሳብ የተራማጆች የትግል ዘዴ ሊሆን አይችልም። ዛሬ አውቀውም ሆነ ሳያውቁ የንኡስ ከበርቴውን ደንፊ ቡድን የተቀላቀሉት ቅን አብዮታውያንና ከዚህ ቡድን ውጭ ያሉ ተራማጆች ሁሉ የትግል አንድነታቸውን ሊመሰርቱ የሚችሉት የሰዎችን ስም በመነገድ ሳይሆን፣ በግልጽና በቅን ውይይት፣ በአብዮታዊ ሂስና ግለሂስ፣ በቅን ነቀፌታዎችና በመተራረም . . . ብቻ ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ በአንክሮ ማጤን አለባቸው። በሰፊው ሕዝብ ድምጽ ቁጥር 35 ከውስጥ እንደተገለፀው “ዛሬ ይህን ባናደርግ ወደፊት በአብዮቱ ላይ ለሚፈጠረው ተጨማሪ ችግር ተጠያቂዎች መሆናችን አይቀርም።” ሃቀኛ ተራማጆች ድምፃቸውን የማሰማት ግዴታ አለባቸው።
“The Second Congress or the Russian Social-Democratic Labor party welcomes the growing revolutionary initiative among the student youth and calls upon all organizations of the party to give them every possible assistance in their efforts to organize. It recommends that all student groups and study circles should, firstly, make it the prime object of their activities to imbue their members with an integral and consistent world outlook and give them a thorough acquaintance with MARXISM, on the one hand, and with, …. the principal currents among the conflicting advanced trends of today; secondly, that they should beware of these false friends of the youth who divert them from a thorough revolutionary training through recourse to empty revolutionary or idealistic phrase- mongering and philistine complaints about the harm and uselessness of sharp polemics between the revolutionary and the opposition movements, for as a matter of fact those false friends are only spreading an unprincipled and unserious attitude towards revolutionary work…”(LENIN; “Draft Resolution on The Attitude Towards The Student Youth”, Coll .works; vol.6; p.47)
“It is not only by reactionaries that the expression “false friends” is used; we know from the example of the liberals and socialist revolutionaries that such “false friends” do exist. It is these false friends that are trying to persuade the youth that they have no need to distinguish between different trends. We, on the contrary, consider it the main task to develop an integral revolutionary world outlook. . . . ” (LENIN; “Speech on The Attitude Towards the Student Youth”; Coll. Works; Vol.6; p.509)
[1] *
በግልጽ እንደሚታየው በዚህ ውዠንብር በመንዛት የተካኑት የንኡስ ከበርቴ ደንፊዎች ልሳን “ዲሞክራሲያ” እና ተቀጥላዎቿ እነ “ላባደር”፣ እነ “አብዮታዊው ወጣት” ናቸው። ከጥቂት ሳምንታት ወዲህ ሃቀኛ የሆኑ ተራማጆች በሁለት ጋዜጦች አማካይነት ድምፃቸውን ማሰማት እንደጀመሩ ልንገነዘብ ችለናል። አንደኛው “ነፃነት” የተባለው ጋዜጣ በመጀመሪያው ቁጥሩ ላይ ያሰፈረው መለስተኛ ኘሮግራሙን ብቻ ነው። ኘሮግራሙ ምንም እንኳን አንዳንድ ጉድለቶች ቢኖሩበትም በውይይት ሊሻሻሉና ሊሟሉ እንደሚችሉ እምነታችን ነው። ሁለተኛው “ሪቮሉሽን” የተባለው ጋዜጣ ስለጊዚያዊው የኢትዮጵያ ሁኔታ ሀተታ ከማቅረቡ በላይ፣ ዛሬ ጐልተው በሚታዩን ሁለት ጋዜጦች /ዲሞክራሲያ እና የሰፊው ሕዝብ ድምጽ/ ላይ ሂሶችን አቅርቧል። በሰፊው ሕዝብ ድምጽ ላይ የተሰነዘሩት አንዳንድ ሂስ አግባብ ያላቸው ቢሆንም፣ አብዛኛዎቹ ግን በነሲብ የተሰነዘሩ ናቸው እንላለን። ሆኖም፣ ግልጽና ቅን ውይይት ልናደርግባቸው እንደምንችል ደግሞ ሙሉ እምነት አለን።