ሰሕድ ቁ. 37

የሰፊው ሕዝብ ድምፅ

ቁጥር 37፣    ጥር 25፣ 1968

የፅሁፉ ፍሬ ሀሳብ

መኢሶን በዚህ የሰፊው ሕዝብ ድምፅ እትሙ፣ ከሁለት ዓመታት በፊት በ1966 የተጀመረው ሕዝባዊ አብዮታዊ እንቅስቃሴ በብቃት የተደራጀ መሪ ፓርቲ እንደሌለው ይገልጻል። በዚህም ምክንያት ሕዝባዊው እንቅስቃሴ በተለያዩ የንዑሰ ከበርቴ መደብ ክፍሎች ሲመራ እንደቆየ ይጠቁማል። የአገሪቱ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ሁኔታዎች ለአብዮታዊ ትግል የበሰሉ የነበሩትን ያህል፤ የእንቅስቃሴው ፖለቲካዊ አደረጃጀትና ህሊናዊ ሁኔታ ዝቅተኛ ደረጃ ላይ እንደነበሩ ያስገነዝባል። በዚህም ልዩ ታሪካዊ ወቅት በሕዝብ ስምና “በጊዜያዊነት” ስም  “ጨባጭ ያጣችውን” የመንግሥት ሥልጣን ወታደራዊ ደርግ እንደያዛት ያስታውሳል። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ  ሥልጣን የጨበጠው ደርግ አንዳንድ ጊዜ ወደግራ እያዘመመ ከሰፊው ሕዝብ ጋር ሲቆም፣  ሌላ ጊዜ ደግሞ ወደቀኝ እያደላ የሕዝቦችን ጥቅም የሚጎዳ እርምጃዎችን እየወሰደ እዚህ መድረሱን ያብራራል።

 

የሰፊው ሕዝብ ድምፅ

ለሰፊው ሕዝብ ሰራተኛ ገበሬ፣ ነጋዴ፣ ወታደር፣ ምሁር መብትና ጥቅም የሚታገል ጋዜጣ

የኢትዮጵያ ሰፊ ሕዝብ ይቅደም

ቁጥር 37                                                                      ቀን 25/5/68

​​​​

የ ት   ደ ር ሰ ና ል ?

መግቢያ

የዛሬ ሁለት አመት፣ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ፈጽሞ ታይቶ የማይታወቅ አይነት ሰፊ ሕዝባዊ አብዮታዊ እንቅስቃሴ ፈንድቶ አገሪትዋን ከዳር እስከ ዳር አጥለቀለቃት። ይህ እንቅስቃሴ መሪ መደብ ቢኖረውም መሪ ፖርቲ አልነበረውም። ይህም የሆነው ካገሪትዋ የታሪክ እድገት የተነሳ ነበር።  ያገሪቷ ነባራዊ  /ኦብጀክቲቭ/  ሁኔታ- ማለትም የሰፊው ሕዝብ የኑሮ ሁኔታ፣ ቁስአካላዊ መሰረቱ- ለአብዮት የበሰለ ሆኖ ሳለ፣ የእንቅስቃሴው ደረጃ ግን በዚያው መጠን ወደኋላ የቀረ ስለነበር ነው።

የእንቅስቃሴው መሪ መደብ የነበረው የንኡስ ከበርቴው መደብ ነው። አሁንም እንደዚያው ነው። የዚህ መደብ የግራ ክንፍ፣ ይህ፣ ዛሬ በስልጣን ላይ ያለውን መንግሥት “ፋሽስታዊ” የሚለው ክፍል እራሱ ጭምር፣ በዚያን ጊዜ ይህንኑ ዛሬ የሚያወግዘውን ወታደር የመንግሥትን ስልጣን እንዲይዝ በተቻለው ሁሉ መንገድና ቋንቋ ገፋፍቶት እንደነበር ይታወሳል። ለማንኛውም፣ ሰፊው ሕዝብ በትግሉ ያለፈውን ሥርዓት መሰረት ሲያናጋ በሕዝብ ስምና ለሕዝብ የቆመ ምንም አይነት ድርጅት አልነበረውም። በዚህም ምክንያት፣ ከገዥ መደብ እጅ የተፈለቀቀችው ስልጣን ለትንሽ ጊዜ በአየር ላይ ከተንሳፈፈች በኋላ፣ በዚያን ጊዜ ታጥቆ የነበረው ወታደር መጀመሪያ ለሕዝብ የቆመ መስሎ ብቅ በማለት፣ በኋላም የሰፊውን ሕዝብ መሰረታዊ መብቶች በመግፈፍ ለጊዜው “ጨባጭ” ያጣቸውን ስልጣን ያዘ። በዚያን ጊዜ ይህን ሊቋቋም የሚችል ሌላ የተደራጀ ኃይል አልነበረም። የወታደሩ ስልጣን መያዝ በዚያን ጊዜ ከነበረው የሰፊው ሕዝብ አለመደራጀትና አለመታጠቅ የመጣ አጋጣሚ ነበር።

የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ እንቅስቃሴ እየወደቀና እየተነሳ፣  የዚህን እንቅስቃሴ መሪነትም በሞላ ጐደል የያዘው ወታደራዊ ደርግ እየተደናበረ፣ አንዴ ወደቀኝ አንዴ ወደግራ እያጋደለ፣ ይኸው እስከዚህ መጥተናል። ለሰፊው ሕዝብ ትግል ሰፋፊ ጐዳናዎችን የሚከፍቱ እርምጃዎች የተወሰዱባቸው ወቅቶች ነበሩ፤ የሰፊው ሕዝብ ትግል በየቦታው በፀረአብዮት አመጽ የተደመሰሰበትና በሕዝብ ላይ አሰቃቂ ወንጀሎች የተፈፀሙባቸውም ወቅቶች ነበሩ። ሆኖም፣ ማንም ሃቀኛ ተራማጅ በቀላሉ ሊገምት እንደሚችለው ሁሉ፣ የነዚህ ሁለት ዓመቶች አጠቃላይ ውጤት ሲታይ፣ አዝማሚያው ወደ ግስጋሴ፣ ወደ ብሄራዊ ዲሞክራሲያዊ አብዮቱ አቅጣጫ የሚያመራ ሆኗል።

የተነሳሳነው የየካቲትን እንቅስቃሴ እድገቶችና ውድቀቶች በዝርዝር አቅርበን ሚዛኑን ለማሳየት አይደለም። ይህ ወደፊት መደረግ የሚገባው ነገር ነው። አሁን ግን አንድን ጥያቄ መመለስ ይኖርብናል። በብሄራዊ ዲሞክራሲያዊ አብዮቱ ጐዳና ላይ የት ደርሰናል? በዚህ አብዮት ጐዳና ላይ አሁን ዛሬ የተደቀኑት ችግሮች ምን ምን ናቸው? የቅርብ ጊዜውስ አዝማሚያ ወዴት ነው? እነዚህንና ሌሎችንም መሰል ጥያቄዎች በሚገባ ካልመለስን የእለቱን ተግባራችንንም በሚገባ ለመወሰንና ለመፈፀም አይቻልም። ስለዚህም፣ ከዚህ በታች ባጭር ባጭሩ ያገሪትዋን ሁኔታና የኢትዮጵያን ተራማጆች ተግባር ለማቅረብ ሞክረናል። በነዚህ ነጥቦች ላይ ሰፊ ውይይት እንደሚደረግና ሂሶች እንደሚቀርቡለት ሰሕድ ምኞቱን ይገልፃል። 

1.የኢትዮጵያ ገጠር ሁኔታ

በገጠር ያለው ሁኔታ ባሁኑ ሰአት በሰሜንም ሆነ በደቡብ፣ የአድሃሪ ኃይሎችን መጠናከር ያሳያል። በሰሜን፣ በቤጌምድርና በጐጃም የቀድሞዎቹ ጭቃሹሞችና ነጭለባሾች በነጋ ተገኝ ሰዎች ተገፋፍተው ገበሬውን አሳምፀውታል። ስለዚህም በአሁኑ ወቅት ወታደራዊው መንግሥት ከገበሬው ከራሱ ጋር ለመዋጋት ተገዷል። በትግራይም የመንገሻ ሥዩምና ሌሎችም ከኤርትራ ግንባሮች ጋር የተያያዙ ጥቂት ቡድኖች እንዳስቸገሩት ናቸው። ከዚያም የሀንፍሬ አሊ ሚራህ አድሃሪ “የአፋር ነፃ አውጭ ግንባር” አለ። እላይ በጠቆምነው መሰረት፣ እነዚህ አድሃሪ ኃይሎች አሁን እንደሚሞክሩት ሁሉ ከተባበሩና አንድ ፀረአብዮታዊ ግንባር ከፈጠሩ፣ የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ እንቅስቃሴም የነርሱንም ፈተና ማለፍ ይኖርበታል። ጥያቄው እንግዲህ ሰፊውን ሕዝብ እንቀሳቅሶ በዚህ ትግሉ የሚመራው ኃይል በቅርቡ ሊፈጠር ይችላል ወይ ነው።

በሰሜን ብቻ ሳይሆን በደቡብ ኢትዮጵያም በሲዳሞ፣ በባሌ፣ በከፋ አድሃሪ ኃይሎች እየተጠናከሩ ናቸው። የነአበራ ሞልቶትና የሲዳሞው ፖሊስ ዋና አዛዥ አሁን ባሉበት ቦታ መቆየት በኬንያ ያሉትን የነመንገሻ ሥዩምን ደጋፊዎች ያግዛል። የመገናኛ መስመር ይፈጥርላቸዋል። እነዚህ ሁለት አድሃሪዎች በሕዝቡ ላይ የፈፀሟቸው አሰቃቂ ፍጅቶች እየታወቁ፣ በዚያው ሆነው የደቡቡን ነፍጠኛ ፀረአብዮታዊ ድርጅት እንዲያጠናክሩ መደረጋቸው፣ ሰዎቹ ከራሱ ከደርጉ ውስጥ ደጋፊዎችና አበረታቾች እንዳሏቸው ያሳያል። በባሌም ሁኔታው ከሲዳሞው የተለየ አይደለም። አስተዳዳሪው ከሶማሊያ ሰርገው የገቡትን ቡድኖች ለማቋቋም ደሃውን ገበሬ በማስታጠቅ ፈንታ ከቀድሞ የመሬት ከበርቴዎች ጋር ይዶልታል። አንዳንዶች እንደሚሉትማ ከሆነ ኃይለማርያም ሌንጮ የራሱን መንግሥት በባሌ እንዳቋቋመ ሊቆጠር ይችላል።  አድሃሪ፣ ፈላጭ ቆራጭ፣ በብዙ ዘማቾችና በሌሎችም ተራማጆች ላይ ወሰን የሌለው ወንጀል የፈፀመ ሰው እንደሆነ ይነገርለታል። የከፋ አስተዳዳሪና ቢሮክራሲም እንደዚሁ በክፍለ ሃገሩ አደሃሪ ፈላጭ ቆራጭነትን መስርቷል።

የደቡቡን ፀረአብዮት እንቅስቃሴ አድሃሪ የደርግ አባሎች እራሳቸው ከጥቂት ወራት በፊት አጠናክረውት ተመልሰዋል። የተባሉት የደርግ አባሎች በሃረርጌ፣ በሲዳሞና በሌሎችም ቦታዎች ከመሬት ከበርቴውና ከፖሊስ ጋር በመሻረክ ብዙ የገበሬ ማህበራትን አፍርሰው ነበር። እነዚህ አድሃሪዎች ያጠናከሩት ፀረአብዮት አሁን አለ።

በዚያ በኩል ያለው ሁኔታ ትንሽ የተሻሻለ የሚመስለው “የገበሬዎች ማህበር ማደራጃና ማጠናከሪያ አዋጅ” ከወጣ በኋላ ነው። የዚህ አዋጅ አጠቃላይ ይዘት አብዮታዊ ሆኖ ሳለ፣ ባንዳንድ አንቀጾቹ፣ በተለይም የፍርድ ሸንጐዎችን ስልጣን በሚመለከተው በኩል፣ ግልጽ ስላልሆነ፣ ፖሊስና ጠቅላላው የገጠር ቢሮክራሲ አዋጁን እንዳሻቸው እየተረጐሙ አሁንም ሰፊውን ሕዝብ በመጨቆን ላይ ናቸው። የገጠርን መሬት የሕዝብ ያደረገው አዋጅ ከሥራ ላይ ሊውል በሚሞከርበት ጊዜ ብዙ መሰናክሎችን እንዳገኘ ሁሉ፣ ይህኛውም አዋጅ ካሁኑ በብዙ ገጠሮች ብዙ ችግሮች አጋጥመውታል። 

አዋጁ ባጠቃላይ ይዘቱ አብዮታዊ ነው ብለናል። ይሁንናም እንደማንኛውም ይህ መንግሥት እንደሚያወጣው አዋጅ ሁሉ፣ አብዮታዊም ቢሆን፣ ከሥራ ላይ በትክክል የመዋሉ ጉዳይ አጠራጣሪ ነው። አዋጁ የገበሬዎች ማህበር ተግባርና ስልጣን በሚለው አንቀፁ፣ “የፊውዳሊዝምን ሥርዓትና የኢምፔሪያሊዝምን ተጽእኖ ለመደምሰስ በሚደረገው ትግል እንዲሳተፍ የአርሶአደሩን ርእዩተ አለም የህብረተሰባዊነት ፍልስፍና ለማነጽ” ይላል። የአገልግሎትና የአምራቾ የህብረት ሥራ ማህበራት “አላማ፣ ችሎታና ተግባር” የሚሉት አንቀጾች በያዟቸው ነጥቦች ውስጥ፣ “ለማያቋርጥ መሻሻል፣ ለአንድነትና ለዴሞክራሲያዊ መብቶች መታገል፣. . . ማናቸውንም የብዝበዛ አይነቶች ቀስ በቀስ ከገጠር ለማጥፋት የመታገልና ከማንኛውም አይነት ብዝበዛ የመግታት፣ የማህበራቱን የፖለቲካ ንቃት ከፍ ለማድረግ የማያቋርጥ የፖለቲካ እንቅስቃሴ የማካሄድ፣ ወዘተ” የሚሉ አሉ። እነዚህና የመሳሰሉት አንቀጾች ያዋጅ አውጭዎቹን ቀና ምኞት ከማሳየት በስተቀር፣ ባሁኑ ሰአት፣ አንድም ሰፊውን ሕዝብ የሚያንቀሳቅስ አብዮታዊ ፖርቲ በሌለበት ጊዜ፣ በትክክል ከሥራ ላይ ሊውሉ አይችሉም። እንዲያውም፣ ከላይ እንደተጠቆመው ሁሉ፣ የገጠር ቢሮክራሲና ፖሊሱ በተቻለው መንገድ ሁሉ አዋጁን በማደናቀፍ ላይ ይገኛል።

ከአዋጁ ተስፋ ሊጣልባቸው የሚችሉ አንቀጾች “አብዮታዊ የአስተዳደርና የልማት ኮሚቴዎችን” የሚመለከቱት ናቸው። የነዚህን ውጤት የሚወስነው የዘማቾች፣ የአዝማቾች፣ የገበሬ ማህበራት መሪዎችና የመሬት ይዞታ ሠራተኞች ተባብሮና ተግባብቶ መሥራት ነው። እንደዚያም ሆኖ ግን የገበሬዎች የደህንነት ጥበቃ ቡድኖች እስካልታጠቁ ድረስ የነዚህም ኮሚቴዎች ሥራ አስቸጋሪ እንደሚሆን ለመገመት ይቻላል።

የሆነው አይነት መሰናክል ቢኖርባቸውም የኢትዮጵያ ገበሬዎች በነዚህ አዋጆች መሰረት እንዲደራጁና እንዲጠናከሩ ለማድረግ መታገል ያስፈልጋል። ስለዚህም፣ አሁንም የገበሬውን የፖለቲካ ንቃት ከፍ በማድረግ በኩል ሊረዱ የሚችሉት ዘማቾች ናቸው። አንዳንድ የግራ ለምድ የለበሱ አድሃሪዎች አዋጁ በገጠር “ፋሽዝምን ያስፋፋል” በማለትና ዋናው ተግባራችን ደርጉን ገልብጦ “ጊዜያዊ ሕዝባዊ መንግሥትን ማቋቋም ነው” በማለት፣ ዘማቹ ወደ ገጠር እንዳይመለስና ማንኛውንም መስዋእት ሳይፈራ ከሰፊው ሕዝብ ጐን ተሰልፎ እንዳይታገል ለማድረግ ሲሞክሩ ይታያሉ። እነዚህ የገጠሬው ሕዝብ ትግል እንዳይገፋ፣ ገበሬው ከቢሮክሲውና ከፖሊሱ ጋር በሚያደርገው የእለት በእለት ተጋድሎ አጋርና መሪ እንዲያጣ፣ እጅ እግሩን ታስሮ ለአድሃሪዎች እንዲሰጥና ትግሉ እንዲደመሰስ የሚያግዙ፣ አወቁም አላወቁም፣ የነመንገሻ ሥዩም- ነጋ ተገኝ አጋዦች ናቸው። የሽሙጥ ደራሲ በትክክል እንዳመለከተው ሁሉ እዚሁ በየከተማው “ፋሽስት፣ ፋሽስት” እያሉ እነአልጋወራሽን በተጨበጠ መንገድ የሚረዱ አድሃሪዎች ናቸው።

በዘማችነት በገጠር ተሰልፈው የነበሩትና አሁንም የተሰለፉት የኢትዮጵያ ወጣቶች ለሰፊው ሕዝብ ደህንነት ሲሉ ብዙ ስቃይን ተቀብለዋል። የተረሸኑ፣ የተገረፉ፣ ኢሰብአዊ ስቃይ የተቀበሉ ብዙዎች ናቸው። ነገር ግን በማንኛውም ህብረተሰብ ውስጥ ምንም መስዋአት የሌለበት “ንፁህ አብዮት” ተደርጐ አያውቅም። እነዚያን ሕይወታቸውን ለሰፊው ሕዝብ የሰጡትን ወጣት ሰማእታት የኢትዮጵያ ሰፊ ሕዝብ ሲያስታውሳቸው ይኖራል። ደማቸውንም ሳይበቀልላቸው እንደማይቀር ጥርጥር የለውም። ስለሆነም፣ በኛ አስተያየት፣ የጊዜው የዘማች ተግባር እነዚያ ወንድሞቹ ይዘውት የወደቁበትን የአብዮት ባንዲራ አንስተው ትግላቸውን መቀጠል፣ ማንኛውንም መስዋእትነት ሳይፈሩ ቆርጦ ወደፊት መራመድ ነው እንጂ፣ ያለአብዮታዊ ትግል ሊመጣ የማይችለውን የ“ጊዜያዊ ሕዝባዊ መንግሥትን” ተአምር መጠበቅ አይደለም።

የገበሬ ማህበራትን ለማደራጀትና ለማጠናከር የወጣው አዋጅ ብዙ ጉድለቶች ቢኖሩበትም፣ አብዮታዊ የሆነ ፖርቲ በሌለበት በኢትዮጵያ ሁኔታ የአዋጁን አብዮታዊ ይዘት ሙሉ በሙሉ ከሥራ ላይ ለማዋል እንዳማይቻል የታወቀ ነገር ቢሆንም፣ ሰፊው ሕዝብ ከቀድሞዉ ሥርዓት አውታሮች ጋር በሚያደርገው ተጋድሎ የሚያግዙት አንፃሮች አሉት። ስለዚህም የሃቀኛ ተራማጆች ትግል እነዚህን አንፃሮች ማጠንከርና የገጠሩን ሕዝብ ደረጃ በደረጃ ወደብሄራዊ ዲሞክራሲያዊ አብዮቱ ግብ ለማቅረብ መሆን አለበት።

2. የከተሞቹ ሁኔታ

በከተማ ያለው ዋናው ፀረአብዮታዊ ኃይል የቢሮና አቀባባይ ከበርቴው ነው። በተለይ፣ የቢሮ ከበርቴው ባሁኑ ሰአት የልብ ልብ ተሰምቶት በፊት ይንቀጠቀጥለት የነበረውን ደርግ አሁን ከመጤፍ አይቆጥረውም፤ያሾፍበታል፤ ያወናብደዋል። በተረፈ ደግሞ ከነመንገሻ ሥዩም ድርጅት ጋር፣ ከኢምፔሪያሊዝምና በደርግ ውስጥም ካሉ አድሃሪዎች ጋር ውስጥ ውስጡን ይደራጃል፣ ያሴራል።

ደርግ የፈለገውን ያህል ተራማጅ አዋጅ ቢያወጣ፣ የመንግሥቱን አውታሮች ከላይ የጨበጠው ከፍተኛ የቢሮ ከበርቴ በቦታው እስካለ ድረስ፣ አብዮታዊ እንቅስቃሴው ምንም ያህል አይራመድም። የቢሮ ከበርቴው ሻጥር /ሳቦታዥ/ የሚሰራበት ብዙ መንገድ አለው። እነዚህን መንገዶች የመንግሥቱ ጋዜጦች ጭምር ሰሞኑን በሰፊው ሲያብራሩ ስለነበር እዚህ ላይ አንመለስባቸውም። ይልቁንስ ከሁሉ አደገኛ የሆነው የቢሮ ከበርቴው ፀረአብዮታዊ ድርጊት ከኢ.ዲ.ዩና( የነመንገሻ ሥዩም ፖርቲ) ከኢምፔሪያሊዝም ጋር መዶለቱና ከማሴር ፀረአብዮታዊ ሁኔታን በድርጊት ወደማዘጋጀት ማለፉ ነው። ኢምፔሪያሊዝም በድርቅ እርዳታ፣ በኤኮኖሚ እርዳታ፣ በብድር፣ ኤክስፐርት በማቅረብ፣ ወዘተ. አሁንም ቢሆን የሚሰራው ከቀድሞው የቢሮ ከበርቴ ጋር ነው። ይህኛው በተቻለው ዘዴ ሁሉ ያንኪዎችና ሌሎችም ኢምፔሪያሊስት አገሮች በሰፊው፣ ከቀድሞው በበለጠ ሁኔታ ወዳገሪትዋ እንዲገቡ ያደርጋል።

የቢሮ ከበርቴው አንድ አይናውጣ ሻጥር የሚታየው በሥራና ቤቶች ሚኒስቴር ድርጊቶች ነው። የከተማ ቦታና ትርፍ ቤቶች አዋጅ ብዙ ጉድለቶች እንዳሉት ይታወቃል። ቢሮክራሲው በነዚህ ጉድለቶች በሚገባ ይጠቀማል። ለተወረሱት አድሃሪዎች እርዳታ የሚሆኑና ሰፊውን ጭቁን ሕዝብ ደግሞ በደርጉ ላይ የሚያስነሱ ውሳኔዎችን ያስተላልፋል። በሕብረት ሥራ ማህበራት ትግበራ ውስጥ እየገባ ከላይ እንደየሁኔታው ፀረዲሞክራቲክ ትእዛዞችን ያስተላልፋል። በዚህ መንገድ የየቀበሌው ነዋሪዎች የኃይለስላሴ ዘመን ይሻለን ነበር ከሚሉበት ደረጃ ያደርሳቸዋል። በአዋጁ ምክንያት የቤት እጥረት እንዳለ፣ እንደዚሁም ብዙ ወዛደሮች በዚሁ ምክንያት ሥራ እንዳጡ እያወቀ፣ ለቤቶች ሥራ የተመደበው ገንዘብ ካሁኑ ከሥራ ላይ መዋል እንዳይጀምር በረቀቁ ጥናቶችና “በችግሮች” ትንተና ጊዜው እንዲያልፍ ያደርጋል። ጊዜው እያለፈና ሁኔታው እየባሰ ሲሄድ፣ አካባቢው ለፀረአብዮት እርምጃ እንዲያመች የቢሮ ከበርቴው በደንብ ያውቃሉ። በተጨበጠ መንገድ እነመንገሻ ሥዩምን ያግዛል ማለት ነው።

የከተሞች የህብረት ሥራ ማህበራት በጠቅላላው ተስፋ ያላቸው ቢሆንም በአንዳንድ ቦታዎች በማይረቡ ሰዎችና በሌቦች አመራር ስር በመሆናቸው፣ ሌሎችም ቦታዎች ጉቦ በለመዱ ወታደሮች ስር በመሆናቸውና የተመረጡት ሃቀኛ የማህበር ሃላፊዎች ሥራዎችን ለማከናወን የማይችሉበት ሁኔታ ስለተፈጠረ፣ በመፈራረስ ላይ ያሉ አሉ። ደህና ተራማጆችም ያሉባቸው ማህበራት የሚኒስቴሩን አድሃሪ ተፅእኖ በመታገል ብቻ ተወስነዋል። የነዚህ ማህበራት ዋና  ችግር ከገበሬ ማህበራት ችግር የተለየ አይደለም። የሕዝቡን እንቅስቃሴ አቀናብሮ የሚመራ አብዮታዊ ፓርቲ እስከሌለ ድረስ የማህበራቱ የትግል ውጤት ምንጊዜም ቢሆን አጥጋቢ ሊሆን አይችልም። በተረፈም ዴሞክራሲያዊ መብቶች እስካሁን አለመኖራቸው ይህንን ትግል ክፉኛ እንዳደናቀፈው በቀላሉ ለመገመት ይቻላል።

የወዛደሩን መደብና ዝቅተኛ የቢሮ ሠራተኞችን ሁኔታ በሚመለከተው በኩል፣ ኢሰአማ ባለፈው መስከረም ከመንግሥቱ ጋር ከተጋጩ በኃላ ማህበሩ እንደፈራረሰ ይታወቃል። የመምህራን ማህበርም እንደዚያው ነው። ባሁኑ ሰአት የወዛዳሩ መደብና የንኡስ ከበርቴው መደብ የግራ ክንፍ አብዮቱን በተለያዩ መንገዶች ይመለከቱታል። የፊተኛው ባጠቃላይ ገለልተኛነት ውስጥ የወደቀ ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ አኩርፏል ለማለት ይቻላል። ባለፈው መስከረም ወታደራዊው መንግሥት ደንብሮ የወሰዳቸው እርምጃዎች የለየላቸው ፋሽስታዊ ወንጀሎች ነበሩ። ይሁንናም፣ የወዝአደሩና የንኡስ ከበርቴው ማህበራት መሪዎች የተባሉትም ንኡስ ከበርቴዎች በቃል ተራማጅ፣ በድርጊት አድሃሪ በሆኑት በኢ.ህ.አ.ፖ. እና በተመሳሳይ ቡድኖች ድንፋታ ብቻ፣ የሚወክሏቸውን ድርጅቶች ወደማያዋጣ አጉል ድፍረት (አድቬንቸሪዝም) አስገብተዋቸው እንደነበር ዛሬ ለሁሉም ግልጽ የሆነ ይመስለናል። ካለፈው መስከረም ድርጊቶች የወዛደሩ መደብና ሌሎችም ሠራተኞች የነበረውን ሁኔታ በደንብ አጥንተው ተገቢውን ትምህርት የሚቀስሙበት ጊዜ የግድ መመጣቱ አይቀርም። ባጭሩ ብቻ፣ ማንም ሰው ሊክድ የማይችለው አንድ የማህበራቱ ጥፋት ነበር፡፡  ይኸውም በጉባኤዎቹ ላይ የተደረሱባቸው ውሳኔዎች ለሰፊው አባል ቀርበው በነሱ ላይ ዲሞክራሲያዊ ክርክር ሳይደረግባቸው፣ መሪዎቹ በፈላጭ ቆራጭነት ከላይ ትእዛዝ መስጠታቸው ነበር። ደርግን “አንበርክኮ” ዲሞክራሲያዊ መብቶችን የመንጠቅና “ጊዜያዊ ሕዝባዊ መንግሥትን” ለማቆም የመንግሥት ግልበጣን ማድረግን የመሰሉ የሞትና የሕይወት ጥያቄዎች እንደዚሁ ከላይ በትእዛዝ መልክ መወርወር የማይገባቸው ነገሮች ነበሩ። የሙከራው ውጤት በግልጽ እንዳሳየው ሁሉ፣ ይህ ድርጊት የማህበራቱን ጊዜያዊ መዳከም አስከትሏል። በዚህም መጥፎነቱ በኛ ግምት ለወዝአደሩ መደብ በተለይ ትምህርት አትርፏል። ለማንኛውም የወዝአደሩን መደብ ጊዜያዊ ገለልተኛነትና የንኡስ ከበርቴውን የግራ ክንፍ ኩርፊያ በዚህ አንፃር ለመረዳት ይቻላል።

አዲሱ “የሠራተኛ ድርጅት አዋጅ” ይህንን ሁኔታ ለጊዜው ምንም ያህል አልለወጠውም። እንደገበሬ ማህበራት ማጠናከሪያ አዋጅ ሁሉ፣ ምናልባትም በበለጠ ደረጃ፣ ይህኛውም አዋጅ ሊታለፉ የማይችሉ ብዙ ጉድለቶች አሉት። ከነዚህ ውስጥ ዋነኞቹ በአንቀጽ 106፣ ሠራተኛ ክርክር ተጀምሮ ከ50 ቀን በፊት ሥራን ሊያቆም እንደማይችል የሚያስታውቀው- በኃይለስላሴ ዘመን 60 ቀን ነበር! – እና የከፍተኛ ፍርድ ቤትን ውሳኔ በመቃወም ሥራን ለማቆም አይቻልም የሚለው ነው። ሥራን ማቆም የሠራተኛው የመጨረሻ መሳሪያ መሆኑ እየታወቀ፣ ይህንን መሳሪያ በሞላ ጐደል መቀማቱ በፍፁም ትክክል አይደለም። እንዲያውም በዛሬይቱ ኢትዮጵያ ሠራተኛው የሥራ ማቆም መብት እንዳለው በቀጥታና በማያሻማ ቋንቋ ማስፈር ያስፈልግ ነበር። በተረፈ፣ በአንቀጽ 9 መሰረት፣ እንደኢትዮጵያ ባለችው የሰው የሥራ ጉልበት ርካሽ በሆነባት አገር፣ አሰሪው እግዜርን ካልፈራ “በየሶስት ወሩ ሠራተኛን የመቀያየር መንገድ አለው። ሠራተኛው ከሥራው የሚታገድበትን ሁኔታ የሚዘረዝረው አንቀጽ 14 ባንዳንድ ንኡስ አንቀጾች ሠራተኛውን ለአሰሪው አሳልፎ ይሰጣል።. . . 

ዋናው ቁምነገር ግን አሁንም እንደዚያው እንደገበሬ ማህበራት ማጠናከሪያ አዋጅ ነው። አዋጁ ጉድለቶችን ያዘለ ቢሆንም፣ የኢትዮጵያ ወዛደርና ሌሎችም ሠራተኞች በአዋጁ አማካይነት ሊደራጁ ይችላሉ። በዚህ በተወሰነ መብትም በመጠቀም ወዛደሩ ድርጅቱንና ንቃተህሊናውን ሊያጠናክር ይችላል። እነዚህ ደግሞ በበኩላቸው ለመጭው የመደብ ትግል በይበልጥ እንዲዘጋጅ ያደርጉታል።

አንዳንድ የግራን ለምድ የለበሱ አድሃሪዎች የአዋጁን ጉድለቶች ብቻ በመመልከትና እነዚህን አለመጠን በማጋነን፣ ሠራተኛው እንዳይደራጅ መሞከር መያዛቸው ታውቋል። በማንኛውም ሁኔታ ቢሆን፣ ሰርቶአደሩ ሕዝብ በገዛ እራሱ የመደራጀትን እድል ካገኘ መደራጀት አለበት። አትደራጅ ብሎ መምከር ፍፁም አድሃሪነት ነው።

እንግዲህ ለማጠቃለል ያህል፣ የከተማውንም ሁኔታ አይነተኛ የሚያደርገው የቢሮክራሲው ሻጥርና ሴራ፣ ከኢምፔሪያሊዝምና ከነመንገሻ ሥዩም ጋር መመሳጠሩ፣ የንኡስ ከበርቴው የግራ ክንፍ ማኩረፍና የወዛደሩ መደብ ገለልተኛ አቋም መውሰድ ነው። ዲሞክራሲያዊ መብቶች ተሰጥተው ቢሮክራሲው ካልተጋለጠና ካልተመታ፣ የንኡስ ከበርቴውም መደብ በየፊናው በመደራጀትና ድምፁን በማሰማት ፊቱን ወደ አብዮቱ እንዲመልስ ካልተደረገ፣ የወዛደሩም መደብ በፍጥነት ነቅቶና ተደራጅቶ ያለበትን ታሪካዊ ኃላፊነት እንዲገነዘበውና በዚያም መሰረት ትግሉን እንዲያፋፍም ካልተደረገ፣ ከነዚሁ ጋር ተያይዞም የሥራአጡ ችግር በቶሎ ካልተፈታ፣ የኤኮኖሚ ምግባሮች ካልተስፋፉ፣ የከተሞቻችንም ሁኔታ ለፀረአብዮታዊ ቅልበሳ፣ ለነመንገሻ ሥዩምና ለኢምፔሪያሊዝም ሴራ እጅግ አመቺ ይሆናሉ።

3. ኤርትራ፣ ጐረቤት አገሮችና ኢምፔሪያሊዝም

በኤርትራ ጦርነቱ ቀጥሏል። በኤርትራ ተዋጊዎች፣ በወታደሩና በተለይም በሰላማዊው ሕዝብ በኩል ብዙ እልቂት አለ። እንደ ኃይለሥላሴ  ዘመን ሳይሆን፣ ዛሬ በርግጥ የወንድማማች ደም በከንቱ ይፈስሳል ከሚባልበት ደረጃ ተደርሷል። ጦርነቱ ባንድ በኩል በሁለቱ ሕዝቦች መካከል ቂምና ጥላቻን ይበልጥ እየፈጠረ ሲሄድ፣ በሌላ በኩል ደግሞ እዚህ በሚካሄደው አብዮታዊ እንቅስቃሴ ላይ ተጽእኖ ይኖረዋል፣ ያገሪትዋን ኃብት በከንቱ ያባክናል። ይህ ሁኔታ ለኤርትራና ለኢትዮጵያ ሕዝቦች የማይበጅ መሆኑን ሰፊው ሕዝብ በደንብ ቢያውቀውም፣ “የኢትዮጵያ አንድነት ፍፁምነት” ያሳወረው ወታደራዊ ደርግና የግንባሮቹ አድሃሪ መሪዎች ለሰፊው ሕዝብ ጭንቀት ደንታ ያላቸው አይመስሉም። ስለዚህም፣ በውይይትና በመተማመን፣ በመቀራረብ ወደመፍትሄ ሊያመራ ይችል የነበረው የኤርትራ ጦርነት ዛሬ እየተባባሰ፣ ከኢትዮጵያ ውጭ ያሉትን ኃይሎችም እየሳበና በነገሩ እንዲገቡበት እያደረገ፣ ይበልጡን አደገኛ እየሆነ ሄዷል።

የዛሬ አመት ተደርጐ የነበረው የግንባሮቹ ትልቅ ጥቃት የተመሰረተው በማይረባ ግምት ላይ እንደነበረ ውጤቱ አሳይቷል። ኃይለሥላሴ  ከወደቀ በኋላና በተለይም በኢትዮጵያ ውስጥ አንዳንድ የግራ እንቅስቃሴዎች ወዲያውኑ በደርጉ ላይ ሲነሱ፣ ለኤርትራ ግንባሮች መሪዎች ደርግ አንድ ሃሙስ የቀረው መንግሥት መስሏቸው ነበር። ምናልባት የአረብ አገሮችም እርዳታ ከዚያ ጥቃት በፊት እንደዚያ እጥፍ ድርብ ሆኖ የመጣው በዚሁ በተሳሳተ ግምት ላይ በመመስረት ሳይሆን አልቀረም። የኤርትራ ግንባሮች ለታገሉባቸው በርከት ያሉ አመታት አመራሩን የያዘው የአድሃሪው ክፍል ነው።

የዚህ ክፍል ግምትና ጥረት፣ ከቀድሞውም በውጭ አገር ያሳትሟቸው የነበሩ ጽሁፎች እንደሚያሳዩት ሁሉ፣ ኃይለሥላሴ ከወደቀ ኢትዮጵያ ትበታተናለች፣ ስለዚህም ኤርትራ ነፃ ወጥታ የራስዋን ባንዲራ የምትሰቅልበት ሁኔታ ይፈጠራል በሚል ትንተና የተወሰነ ነበር። ይህ የሰፊውን ሕዝብ ትግልና ፍላጐት የሚንቅ የተሳሳተ ትንተና ባለፈው አመት በጥር ወር በተግባር ተሞክሮ በሁለቱም ኃይሎች በኩል ትልቅ ፍጅትን እንዳስከተለ ይታወሳል። ድርጊቱ ለማንም አልጠቀመም። የኤርትራ ግንባሮች ባንዲራቸውን አልሰቀሉም። የኢትዮጵያ መንግሥትም የኤርትራን ተዋጊዎች አልደመሰሰም። በመሃከል ግን የብዙ ሰላማዊ ሰው ንፁህ ደም በግፍ ፈሰሰ።

በዚህ ባለፈዉ ባንድ አመት ውስጥ እንደመሬት ላራሹ ያሉ፣ እንደኩባንያዎች መወረስ፣ ወዘተ. ያሉ እርምጃዎች በተወሰዱ ቁጥር፣ የኤርትራ ግንባሮች አድሃሪ መሪዎችን ይበልጡኑ ወደቀኝ እየተገፉ ሄደዋል። በሰህድ ቀደም ብለን እንዳመለከትነው ሁሉ፣ እነኦስማን ሳላህ ሳቤ ከአረብ አድሃሪ አገሮች፣ ከነመንገሻ ሥዩም- ነጋ ተገኝና ከነአሊ ሚራህ ጋር “ወዳጅነት”ን ፈጥረዋል፤ በመፍጠርም ላይ ናቸው። በነዚህ አድሃሪ መሪዎች በኩል ባሁኑ ሰአት አንድ አይነት ትንተና አለ ቢባል፣ ምናልባት የሚከተለው ይሆናል፡- የመሬት አዋጅ፣ የኩባንያዎች መወረስ፣ የከተማ ቦታና ትርፍ ቤት መወሰድና ሌሎችም ተራማጅ አዋጆች በደርጉ ላይ ጠላትን ያበዙበታል፤ የኢትዮጵያ ኤኮኖሚ ይሰባበራል፤ በዚህ ላይ የወጣቱ ትውልድና የሠራተኛው ተቃውሞ አለ፤ ስለዚህም ደርግ እየተዳከመ ሄዶ መውደቁ አይቀርም፤ ስለዚህም ባገሪትዋ ጠቅላላ ትርምስ ይኖራል፤ ጊዜ የሚሰራው ለኛ ነው፤ የኤርትራን ሕዝቦች አሰልፈን፣ በዚህ አጋጣሚ “ነፃ እንወጣለን” ።

ይህ ሊሆን ይችላል። ግን ደግሞ ሌላ ሊሆን የሚችልም ነገር አለ። ይኸውም የኤርትራ (የኢትዮጵያም) ሰፊ ሕዝብ መሰረታዊ ጥያቄዎች መልስ ለማግኘት መቻል ነው። የኤርትራም ሆነ የኢትዮጵያ ሰርቶአደር ሕዝብ የሚፈልገው ፍትህን፣ ሰላምን፣ እኩልነትን፣ ነፃነትን፣ ዲሞክራሲን ነው። ሰርቶአደሩ ሕዝብ የሚፈልገው የመደብ ብዝበዛና ጭቆና የሚደመሰስበትንና የብሄረሰቦች፣ የሃይማኖቶች፣ የጾታዎች እኩልነት በህግና በተግባር የሚከበርበትን፣ ማንኛውም ዜጋ ሰርቶ ለማደር ዋስትና የሚያገኝበትን ሥርዓት ለመፍጠር ነው። እነዚህን ጥያቄዎቹን ጊዜያዊ ወታደራዊ መንግሥት ሊያሟላ ይችላል ለማለት ሳይሆን፣ በኢትዮጵያ በመካሄድ ላይ ያለው አብዮታዊ እንቅስቃሴ በትክክል “ሊመራ” ከቻለ (በተራማጆች ላይ የሚወድቅ ትልቅ ኃላፊነት ነው) ወደነዚህ ጥያቄዎች መፍትሄም ሊያመራ ይችላል። ይህ ከሆነ ደግሞ አድሃሪዎቹን የግንባሮቹን መሪዎች የኤርትራ ሰፊ ሕዝብ እራሱ አጋልጦና ለብቻ ነጥሎ፣ የአብዮቱን መቅረዝ እራሱ  በመያዝ፣ ትግሉን በትክክለኛው አቅጣጫ አፋፍሞ፣ መብቶቹን ወደማስመለስ፣ ወደእውነተኛ እኩልነትና አንድነት፣ ወደፍትህና ወደእድገት፣ ወደሰፊው ሕዝብ ደህንነት ማምራት ከሚችልበት ሁኔታ ሊያደርሰው ይችላል። የዚህ አይነቱ ሁኔታ ሊፈጠር አይችልም ተብሎ የሚተው ነገር አይመስለንም። ያም ሆነ ይህ፣ የኤርትራ ጦርነት በአሁኑ አኳኋን ከቀጠለ፣ ሁለቱም ወገኖች ጥያቄውን በሰላም ለመፍታት ካልሞከሩ፣ ሰፊው ሕዝብ በከንቱ የሚሰቃይ መሆኑን የኤርትራና የኢትዮጵያ ተራማጆች በደንብ ሊያውቁት ይገባል። 

በኤርትራ ግንባሮች አድሃሪ መሪዎች በኩል ያለው “ትንተና” ከላይ የጠቀስነው ጠባብ ብሄርተኝነትን የሚያንፀባርቅ አስተሳሰብ ሲሆን፣ በደርጉ በኩል ያለው ደግሞ የዚያኑ ያህል በትምክህት ላይ የተመረኮዘ “ኢትዮጵያዊ ብሄርተኝነትን” ያፀባርቃል። ከዚህ በፊት ተደጋግሞ እንደተነገረው ሁሉ፣ ከመደብ ይዘቱ የተነሳ፣ ደርጉ ከዚህ ከ“ብሄርተኛ” ርእዮተአለም ሌላ፣ ለምሳሌም የወዛደሩን መደብ አለምአቀፋዊነት /ኢንተርናሽናሊዝም/ ሊያንፀባርቅ አይችልም። ስለዚህም “በኢትዮጵያ አንድነት ፍፁምነት” በጥብቅ ያምናል። ከስሮ ቢገለበጥ ይገለበጣታል እንጂ ይህችን እምነቱን እስከመቼውም የሚለቃት አይመስልም። ከዚህም የተነሳ፣ ኤርትራን በሚመለከተው በኩል፣ እስካሁን ደርጉ በፖለቲካ ፈንታ የጉልበትን መፍትሄ መርጧል። ይሁንናም፣ አገሪትዋ ባለችበት በዛሬው ሁኔታ፣ ዋናው መፍትሄ ፖለቲካዊ መሆን ነበረበት።

ይህንን መፍትሄ በሚመለከተው በኩል፣ የሰህድ አቋም የታወቀ ነው። መጀመሪያ ነገር፣ የኢትዮጵያ መንግሥት የብሄረሰቦችን የራስን እድል ሰራስ የመወሰን መብት በይፋ ማወቅ አለበት። ይህንን መብት ማወቁን በገቢር ለማሳየት የሚያስችሉትን አንዳንድ እርምጃዎችንም ካሁኑ መውሰድ ይኖርበታል። ሁለተኛ ነገር፣ በትግሉ ሜዳ ለሚገኙት ተራማጅ ኤርትራውያን ካሁኑ የሰላም ጥሪ በይፋ አድርጐ ጦርነቱ የሚቆምበትን ሁኔታ ከነርሱ ጋር መወያየት አለበት። የዚህ አይነቱ ውይይት የመጀመሪያ ተግባር ሰላምን ማግኘት ነው። ሶስተኛ ነገር፣ የሰላም ሁኔታ ከተፈጠረ ወዲያ የኤርትራና የኢትዮጵያ ሕዝቦች ስለኤርትራ ጥያቄ ሰፊ ዲሞክራሲያዊ ክርክር  አድርገው፣ የኤርትራ ብሄረሰቦች የወደፊት እድል በራሳቸው በኤርትራውያን መወሰን ይኖርበታል። ለማንኛውም፣ የመወያያ ነጥቦቹ የሆኑትን ቢሆኑም፣ ጊዜያዊው ወታደራዊ መንግሥት በፍጥነት የሰላምን ጥሪ በትግሉ ሜዳ ለሚገኙት ተራማጅ ኤርትራውያን በይፋ ማቅረብ ይኖርበታል። በኛ አስተያየት የፖለቲካው መፍትሄ ቁልፍ ይህ ስለሆነ በዚያ መጀመር ያስፈልጋል።

ይህ እንግዲህ የኤርትራንና የኢትዮጵያን የውስጥ ሁኔታዎች ስንመለከት ነው። ይሁን እንጂ፣ ባሁኑ ጊዜ የኤርትራን ጥያቄ ከነዚህ ሁኔታዎች አንፃር ብቻ መመልከት ትክክል አይሆንም። በተለይም ኢትዮጵያ ባጠቃላይ ሲታይ ወደግራ ማዘንበልን ከጀመረች ወዲህ፣ በዚህ ጥያቄ ውስጥ አያሌ የውጭ ኃይሎችም ገብተውበታል። የነዚህ ኃይሎች በነገሩ መግባትም ጥያቄውን ይበልጥ ውስብስብ አድርጐታል።

አድሃሪ የአረብ አገሮች፣ እንደሳውዲ አረቢያ ያሉት፣ የቀይ ባህርን አካባቢ የአድሃሪዎች ሰፈር ለማድረግ እንደሚፈልጉና፣ ለዚህም፣ በአንድ ጋዜጣ አባባል “የኤርትራን አረብ ሕዝብ” ትግል ከመቼውም ይበልጥ እንደሚደግፉ በግልጽ ተናግረዋል። ቀድሞ ከኃይለሥላሴ ጋር ስምምነት የነበረውና ተራማጆችን የሚጨፈጭፈው የሱዳኑ ኑሜሪም እንደዚሁ የኤርትራን ግንባሮች ይደግፋል፤ እነመንገሻ ሥዩምንም ይረዳል። ሶማሊያ ጂቢቲን ለመያዝና ውጋዴንንም ለመውሰድ ስለምትፈልግ፣ የኤርትራን ግንባሮች ብቻ ሳይሆን ሃንፍሬ አሊሚራህንም የምታበረታታ ይመስላል። በዚያው አካባቢ በውጋዴንና በተለይም በባሌ ኘሮቮኬሽን -ተንኮል- በመፈም ላይ የሚገኙ የታጠቁ ቡድኖች እንዳሉ ይታወቃል። በኬንያ የነመንገሻ ሥዩም ደጋፊዎች በመደራጀትና በመጠናከር ላይ እንዳሉ ይነገራል። 

የኃይለሥላሴ መንግሥት ቀድሞ የኢትዮጵያን ሕዝቦች ለማወናበድ “ተከበናል” እያለ ሲያስወራና ሲለፍፍ የነበረው ሃሰት ዛሬ በርግጥም በተጨባጭ መልክ የሚታይ ይመስላል። ይህ ሁሉ ሁኔታ የኤርትራን ግንባሮች አድሃሪ መሪዎች የሚያበረታታ ለመሆኑ ምንም ጥርጥር የለውም። መታወቅ ያለበት ግን የዚህ ጠቅላላ “ርኩስ ወዳጅነት” አላማ የኤርትራን ሕዝብ ከተባለው “የኢትዮጵያ ኮሎኒያሊዝም” ነፃ ለማውጣት ሳይሆን፣ የኢትዮጵያ ሕዝቦች የጀመሩትን አብዮታዊ እንቅስቃሴ ለመደምሰስ መሆኑ ነው።

ከዚህ ሁሉ ጋር የሁለቱ ሃያላን መንግሥታት ውድድር አለ። ማንም እንደሚያውቀው ኢትዮጵያ እስከቅርብ ጊዜ ድረስ በአፍሪካ ያሜሪካ ኢምፔሪያሊዝም ዋና ምሽግ ነበረች። አሁንም ቢሆን ደግሞ ያሜሪካ ኢምፔሪያሊዝም ባገሪትዋ የኤኮኖሚ፣ የፖለቲካ፣ የባህልና ወታደራዊ አቋም ላይ ፈጽሞ የማይናቅ ተጽእኖ አለው። ከኛ ዝቅ ብሎ ደግሞ ሶቭየት ህብረት በሶማልያ ውስጥ በሰፊው ገብታለች። ያሜሪካ ኢምፔሪያሊዝም በኢትዮጵያ ላይ የነበረውን ያህል ቁጥጥር ይህኛው ሃያል መንግሥትም በሶማሊያ ላይ ተጽእኖ አለው። በሌላ በኩል ደግሞ ይኸው ኃያል መንግሥት በኢትዮጵያ ላይ ከተሰለፉት አንዳንድ የአረብ አገሮች ጋር የጠበቀ “ወዳጅነት” አለው። የሁለቱ ኃያላን መንግሥታት ውድድር የሚያተኩረው በአፍሪቃ፣ በቀይ ባህርና በህንድ ውቅያኖስ ላይ በመሆኑና ኢትዮጵያም በዚህ ያፍሪቃ ክፍል የያዘችው የስትራቴጂ ቦታ ከፍተኛ የኤርትራም ጥያቄ በዚህ ውስብስብ ሁኔታ ውስጥ መታየት ይኖርበታል። አሁን እንግዲህ በደረስንበት ሁኔታ አሜሪካኖችም አልወጡ፣ ሶቭየቶችም አልገቡ፤ ውስጥ ውስጡን እነርሱ የተስማሙበትን ነገር ለማወቅ ያስቸግራል።….

የኢትዮጵያና የኤርትራ ሕዝቦች የራሳቸውን ችግር በራሳቸው ለመፍታት መቻል አለባቸው። ከዚህ በላይ ስለመፍትሄ ስንናገር ቁልፉ የሚገኘው በትግሉ ሜዳ ላይ ባሉት ተራማጅ ኤርትራውያን ዘንድ ነው ያልነው በዚህ ምክንያት ነው። እንኳንስ እንደነዚህ በብዙ ክር የተሳሰሩ ሁለት ሕዝቦች ቀርተው፣ ሌሎችም አፍሪካውያን ቢሆኑ፣ በመካከላቸው የሚነሱትን ችግሮች የውጭ እጅ ሳያስገቡ እራሳቸው በውይይትና በሰላም መፍታት አለባቸው። ይህ ሆኖ ሳለ፣ ወንድማማች ሕዝቦችን እርስ በርስ ማስጨፍጨፍ፣ ማራራቅ፣ ለበላይነትም ሲባል የዚህኛው ወይም የዚያኛው ባእድ ኃይል ጥገኛ መሆን አሳፋሪ ብቻ ሳይሆን በሰፊው ሕዝብ ላይም የሚፈፀም ትልቅ ወንጀል ነው። ለዚህም ሃላፊዎቹ አንድ ቀን የግድ ይጠየቁበታል።

በበኩላችን የኤርትራና የኢትዮጵያ ሰርቶአደር ሕዝቦች ጥቅም አንድ ነው እንላለን። ሰፊው ሕዝብ የርስ በርስን መቀራረብና በማንኛውም ነገር የመደጋገፍን፣ የመተባበርና የመተሳሰርን ጠቃሚነት ያውቃል። ስለዚህም፣ በእኩልነት ላይ የተመሰረተ አንድነትን ይፈልጋል። ይህንን ሃቅ ስለምናውቅ፣ ባሁኑ ሰአት የኤርትራም ተራማጆች አብረውን እንዲሰለፉ ጥሪ እናደርግላቸዋለን። ለኤርትራም ሆነ ለኢትዮጵያ ሕዝቦች ለእኩልነት፣ ለነፃነት፣ ለሰላምና ለእድገት ለሚያደርጉት ትግልና ለሚጠቅማቸው ዘላቂ አንድነት ዋስትና ሊሆን የሚችለው የልዩ ልዩ ብሄረሰቦች ተራማጆች በመደብ ደረጃና በአለምአቀፋዊነት መተሳሰር ብቻ ነው።

4. የኢትዮጵያ ተራማጆች አሰላለፍ

የዛሬይቱ ኢትዮጵያ ተጨባባጭ ሁኔታ የተራማጆችን የጠበቀ ህብረትና የወዛደሩን ፖርቲ በፍጥነት መገንባት በሚጠይቅበት ባሁኑ ሰአት፣ ብዙ የኢትዮጵያ “አብዮታውያን” ተራማጅ አስተሳሰብን በሚያጋጥመው “የህፃንነት በሽታ” ተለክፈዋል። አንዳንድ ቅን ሰዎች የተራማጁን በጥቂት ቡድኖች መከፋፈል እያዩ፣ “እርስበርስ መቦጫጨቁን” እየተመለከቱ ተስፋ ይቆርጣሉ። ነገር ግን ይህ የእድገት ምልክት መሆኑን የግድ ማስታወስ ያስፈልጋል። በማንኛውም አብዮት ውስጥ የዚህ አይነቱ የግራ ኃይል መከፋፈል ደጋግሞ ደርሷል። በግራውም ውስጥ “ግራ” እና ግራ፣ ማለትም በአፋቸው የግራ በድርጅታቸው ግን የቀኝ የሆኑ በአንድ በኩል፣ በአፋቸውም ሆነ በድርጊታቸው በርግጥ የግራ የሆኑ በሌላ በኩል አሉ። በኢትዮጵያም የዚህ አይነቱ ሁኔታ ከእለት ወደእለት ይበልጡን ግልጽ እየሆነ ሄዷል። ይህም የግድ ወደአንድ አቅጣጫ ማምራት ይኖርበታል። ሃቀኛው ግራ እየተጠናከረ፣ የውሸትን ግራ እያጋለጠና እየታገለው ይሄድና የሰፊውን ሕዝብ ተቀባይነት ያገኛል። አድርባዩ “ግራ” ግን በመጨረሻ የጥቂት አድሃሪዎች ፀረአብዮታዊ ቡድን ሆኖ ይቀራል።

ማንም እንደሚገምተው፣ በኢትዮጵያ ግራ ውስጥ ዛሬ ሁለት አዝማሚያዎች እየጠሩ ሄደዋል። እነዚህም በጋዜጣችን በሰህድና በ“ግራው” ጋዜጣ በዲሞክራሲያ ይወከላሉ። በቅርቡ አንዳንድ የአብዮታውያን ቡድኖች ብቅ ብቅ ማለታቸው ይታወቃል። ነፃነት፣ ሪቮሉሽንወዝ፣ ታጋይ ኢትዮጵያዊት እና የአብዮት ፋና በሚባሉ ጋዜጦች የመጡት በነዚህ ግሩፖች ሲሆን፣ ከጋዜጦቹ ይዘት በቀላሉ ለመገመት እንደሚቻለው ሁሉ፣ በሰህድና በነርሱ መካከል ከዝርዝር ነጥቦች ሌላ መሰረታዊ የመስመር ልዩነት የለም። የኢትዮጵያን ሁኔታ ትንተናና የተራማጆችን ጊዜያዊ ተግባር በሚመለከተው በኩል ከነዚህ ጋዜጦች ጋር ከሙሉ ስምምነት ላይ ልንደርስ እንችላለን የሚል ግምት አለን። ለማንኛውም ስህድ ከነዚህ ግሩፖች ጋር ሃቀኛና አብዮታዊ ውይይትን ለመክፈት፣ በግሩኘ ደረጃ በሂስና በግለ ሂስ ከእርስ በርሳችን እንድንማር ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን ባለፈው ቁጥሩ ጠቁሟል።

እንግዲህ በኢትዮጵያ ግራ ውስጥ ያሉት ሁለት አዝማሚያዎች በየትኞቹ ነጥቦች ላይ ነው የሚለያዩት? 

በመጀመሪያ ነገር የምንለያየው “የጊዜያዊ መንግሥት” በሚለው መፈክር ነው። ይህንን መፈክር እንዲያውም ለመጀመሪያ ጊዜ ያቀረበው ሰህድ እንደነበር ይታወሳል። ዛሬ ግን ሰህድ ይህንኑ መፈክር በተቻለው መንገድ ሁሉ ይታገለዋል። ይህንንም ለምን እንደሚያደርግ በዝርዝር ለማወቅ የሚፈልገውን አንባቢ ሰህድ ቁጥር 35ን ፈልጐ እንዲያነብ ከመጋበዝ በስተቀር እዚህ ላይ አንመለስበትም። ባጭሩ ብቻ፣ “ጊዜያዊ ሕዝባዊ መንግሥት” የሚለው መፈክር እራሱ ኃይለኛ ቅራኔን በውስጡ የያዘ ከመሆኑም በላይ፣ ከሥራ ላይ ሊውል ቢችልም እንኳን የንኡስ ከበርቴውን መደብ አንድ ክንፍ ፈላጭ ቆራጭነት በሰፊው ሕዝብ ላይ ከማስፈር ሌላ ምንም ፋይዳ አይኖረውም። ሰህድ የሚያምነው የአለም ብሄራዊ ዲሞክራሲያዊና ሶሻሊስት አብዮቶች ፍቱነቱን ባረጋገጡበት በ“ጊዜያዊ አብዮታዊ መንግሥት” ነው። ይህም የሚመጣው ሰፊው ሕዝብ ነቅቶ፣ ተደራጅቶና ታጥቆ በጉልበት በፊውዳሊዝምና በኢምፔሪያሊዝም፣ እንዲሁም በወኪሎቻቸውና በርዝራዦቻቸው ላይ ድሉን ሲያረጋግጥ ብቻ ነው። የምንታገለውም ለዚህ አይነቱ መንግሥት መመጣት ነው። ምናልባት የኢትዮጵያ አብዮት ጐዳና የተለየና ራሱን የቻለ ሆኖ በርግጥ “ጊዜያዊ አብዮታዊ መንግሥት” አይፈጠር ይሆናል። ለማንኛውም ግን የነዲሞክራሲያ፣ የነመንገሻ ሥዩምም፣ “ጊዜያዊ ሕዝባዊ መንግሥት” በምንም አይነት የአብዮታዊውን መንግሥት ቦታ ሊወስድ አይችልም።

ሁለተኛው የመለያያ ነጥብ የደርግን ባህርይ የሚመለከተው ትንተና ነው። ሰህድ ደጋግሞ እንዳመለከተው ሁሉ፣ ደርጉ የንኡስ ከበርቴውን መደብ የሚወክል፣ በዚህ ምክንያት በጣም ወላዋይ የሆነ፣ ባጠቃላይ ሲታይም አንዴ ወደ ቀኝ አንዴ ወደ ግራ የሚያዘነብል ኃይል ነው። በውስጡም የቀኝና የግራ ቡድኖች አሉ። /ቀኝና ግራ ማለት እዚህ ላይ የተደራጁ፣ በምእራብ አገሮች እንደሚገኙት የፖርላማ ፖርቲዎች ማለት እንዳልሆነ ግልጽ ነው። የደርጉ የቀኝና የግራ ክንፎች ያልተደራጁ ከመሆናቸውም በላይ በአባሎቻቸው ብዙ ጊዜ ተለዋዋጭ ሳይሆኑ አልቀሩም። /ስለዚህም ደርጉ በአንድ ርእዩተአለምና በአንድ የፖለቲካ መስመር ዙሪያ የተሰበሰበ፣ አንድነት ያለው አካል አይደለም። በዚህ ምክንያት ነው አንድ ጊዜ በጣም ተራማጅ፣ አንድ ጊዜ ደግሞ በጣም አድሃሪ ወይም በጣም ግራ ቀደም እርምጃዎችን የሚወስደው።

በዚህ ነጥብ ላይ የዲሞክራሲያ አቋም ይህን ያህልም ግልጽ አልሆነም። ዲሞክራሲያ በደርጉ ላይ አንድ ስም፣ ለምሳሌ “ፋሽስት ደርግ”፣ “ፋሽስት ጁንታ”  ወይንም አሁን በጽሁፎቹ ላይ እየፀደቀ የሄደ የሚመስለውን “የምርጥ መኮንኖች መንግሥት” የሚሉትን ቅጽሎች ከመለጠፍ አልፎ፣ የደርጉን የመደብ ይዘት ለመተንተን የሞከረበት ጊዜ የለም። አልፎ አልፎም የግራና የቀኝ ኃይሎችን የለየበትና የግራው ክንፍ ከርሱ ጋር እንዲተባበር የጋበዘበት ወቅቶች ነበሩ። እንዲያውም ደግሞ በዚያው በአንድ የዲሞክራሲያ ቁጥር ውስጥ እላይ “ፋሽስት ደርግ” ብሎ እታች ደግሞ “በደርጉ ውስጥ የቀኝ ኃይሎች እየተጠናከሩ ናቸው” በማለት በደርጉ ውስጥ ፋሽስቶችንና ሱፐር ፋሽስቶችን ለመለየት የሞከረበት ወቅት ነበር። ባጭሩ፣ ዲሞክራሲያ እራሱ እንደደርጉ ወላዋይ በመሆን፣ ስለደርጉ ባህርይ ውዥንብርን ነዝቷል፤ በመንዛት ላይም ነው።

ሶስተኛ፣ አብዮታውያን ያንድን መንግሥት የመደብ ባህርይ በገጽ መለየት ያለባቸው ለትንተና ቅንጦት ሳይሆን፣ ለትግላቸዉ ይህ አስፈላጊ ስለሆነ ነው። ከዚህ ትንተና በመነሳት፣ ተራማጆች አንድ የተወሰነ አቀራረብ ይኖራቸዋል። ደርግ በርግጥ ፋሽስት ከሆነ፣ ከኢምፔሪያሊዝምም፣ ከነመንገሻ ስዩምም፣ ማለትም ከመሬት ከበርቴዎች ጋር ጭምር የግድ ተባብሮ፣ “ፀረፋሽስት ግንባር” መስርቶ እርሱን መገልበጥ ያስፈልጋል። ደርግ የንኡስ ከበርቴው ወላዋይና ደንባራ ክፍል ከሆነ ደግሞ፣ ተራማጆች በተቻላቸው መንገድ ሁሉ ሊያረጋጉት መጣር፣ የግራውንና የቀኙን ለመለየት፣ የግራው ከሰፊው ሕዝብ ጋር እንዲሰለፍ ለመገፋፋት፣ ጠቅላላው ደርግ ከፊውዳሊዝምና ከኢምፔሪያሊዝም ጋር ያለውን ቅራኔ ለማፋፋም መታገል ይኖርባቸዋል። ደርግ በፀረፊውዳልና /ገና ባይለይለትም/ በፀረኢምፔሪያሊስት አቋሙ፣ ለተወሰነ ጊዜም ቢሆን የሰፊው ሕዝብ ወገን መሆኑን ስለሚረዱት ሃቀኛ ተራማጆች በዚህ ባህርዩ በመጠቀም የሰፊውን ሕዝብ ትግል ያራምዱታል። ደርግና ሰፊው ሕዝብ ባንድነት በዋነኞቹ ጠላቶች በፊውዳሊዝም፣ በኢምፔሪያሊዝምና በቢሮክራሲያዊው ከበርቴ ላይ እንዲረባረቡ ለማድረግ ይታገላሉ እንጂ፣ የመንግሥትን ስልጣን ስለያዘ ብቻ ወታደራዊው ደርግም የሰፊው ሕዝብ ዋና ጠላት ሆኖ ከነዚያ ሶስት ጠላቶች እኩል መወጋት አለበት አይሉም። ሰህድ የፊተኛውን ፖለቲካ አብዮታዊ ሂስ በሚለው አቋም ሲያጠቃልለው፣ ዲሞክራሲያ ግን ሁለተኛውን የተምታታና ዞሮ ዞሮም ፀረአብዮታዊ የሆነውን አቋሙን በአወናባጅነቱ ሲረጨው ቆይቷል፤ በመርጨት ላይም ይገኛል።

አራተኛ፣ ከዚህ በላይ ያነሳነው የደርግ ባህርይ ጉዳይ፣ በግልጽ እንደሚታየው፣ ከዛሬይቱ ኢትዮጵያ ቅራኔዎች ትንተና ጋር የተያያዘ ነው። በዲሞክራሲያ “ትንተና” መሰረት፣ የየካቲት እንቅስቃሴ ያስከተላቸው ታላላቅ ለውጦች፣ ለምሳሌ የዘውድ አገዛዝ መውደም፣ የሶሻሊዝም የመንግሥት መመሪያ ሆኖ መታወጅ፣ የትላልቅ የኢምፔሪያሊስቶች መወረስ፣ በተለይም የገጠር መሬት የሕዝብ መሆን፣ የገበሬ ማህበራት ከነችግሮቻቸውም ቢሆን መቋቋም፣ ወዘተ. ባገሪትዋ የቅራኔዎች ቅደም-ተከተል ውስጥ ምንም አላስከተሉም። ለነርሱ የኢትዮጵያ ሕዝብ ዋና ጠላቶች ፊውዳሊዝም-ኢምፔሪያሊዝም- የደርግ ፋሽዝም ናቸው። ወይንም ደግሞ በፊውዳሊዝም- ኢምፔሪያሊዝምና በሰፊው ሕዝብ መካከል ያለው ቅራኔና በደርግና በሰፊው ሕዝብ መካከል ያለው ቅራኔ በባህርዩ፣ በአይነቱ፣ አንድ ነው። ይህ የቅራኔዎች “ትንተና” ማወናበጃ መሆኑን ሰህድ በጊዜው አሳይቷል። ማንም የአብዮታዊ ቴዎሪን ሀ ሁ የቆጠረ ሰው በቀላሉ ሊገነዘበው እንደሚችለው ሁሉ፣ ደርግ ባሁኑ ሰአት ከኢምፔሪያሊዝም ጋር በብዙ ሰንሰለቶች የተያያዘ ቢሆንም፣ በሁለቱ መካከል ቅራኔ እንዳለ ግልጽ ነው። ይህም ቅራኔ በይዘቱ በኃይለሥላሴ መንግሥትና በኢምፔሪያሊዝም መካከል ከነበረው ይለያል። ይህኛው /የኃይለሥላሴ መንግሥትና የኢምፔሪያሊዝም ግንኙነት/ አይነተኛ ያደርግ የነበረው በሁለቱ መካከል የነበረው አንድነት ወይም መግባባት፣ መቻቻል ሲሆን፣ ያኛውን /ደርግና ኢምፔሪያሊዝም/ ግን አይነተኛ የሚያደርገው የመራራቅ፣ የትግል፣ የመቃቃር አንፃሩ ነው። ስለዚህም፣ ለጊዜውም ቢሆን፣ ይህ ቅራኔ የደርጉንና የሰፊውን ሕዝብ መቀራረብ አስከትሏል፤ ወይም በማስከተል ላይ ነው። ይህም መቀራረብ ነገ ሊፈርስና ወደጠላትነት ሊለወጥ ይችላል፤ ዛሬ ግን አለ። ከዚህም የተነሳ፣ የአብዮታውያን ተግባር በዚህ ጊዜያዊ መቀራረብ በመጠቀም የሰፊውን ሕዝብ ዘላቂ ትግል ማዘጋጀትና ማጠናከር ነው። ይህንን በመሳት ደርግ ባሁኑ ሰአት ከፊውዳሊዝም- ኢምፔሪያሊዝም እኩል አንዋጋ ማለት ሰፊውን ሕዝብ ጊዜያዊ ወዳጁን አሳጥቶ ለአድሃሪዎች አሳልፎ መስጠት ነው።    

አምስተኛ፣ ከዚህ ሁሉ የትንተና ልዩነት ጋር ተያይዞ የትግል ዘዴ ልዩነት አለ። ይህንንም ነጥብ ያለፈው አንድ ቁጥራችን በሚገባ ስላብራራው በሰፊው አንመለስበትም። የዲሞክራሲያን የትግል ዘዴ አይነኛ የሚያደርገው፣ ወረቀቱና ደጋፊዎቹ በግለሰቦች ላይ የሚያደርጉት ዘመቻ፣ በፖለቲካ ክርክር አማካኝነት ደጋፊዎችን በማፍንት ፈንታ በሃሜትና በስም ማጥፋት ያዳማጩን ስሜት ቀስቅሶ “ጀሌ” ማድረግ፣ ደጋፊው እንዳያስብ፣ እንዳይመራመር፣ የሚሰጡትን መፈክሮችና መመሪያዎች ያላንዳች ጥያቄ እንዲቀበል ማድረግ ነው።

ይህም በአብዮታዊ ዲሲኘሊን ቦታ ፋሽስታዊ ዲሲኘሊንን መተካት ነው። ሰህድ በበኩሉ በተቻለው መጠን አብዮታዊ ቴዎሪን ለማሰራጨት፣ በውይይትና በክርክር ደጋፊዎችን ለመሳብና እራሱም ለመታረም፣ አስበው፣ አውቀው፣ አሰላስለው፣ የስህድን መስመር የራሳቸው አድርገው የሚታገሉ የነቁ አብዮታውያንን ለመፍጠር ይታገላል። ይህኛው የትግል ዘዴ አድካሚ ነው፤ ረጅም ነው፤ ባንድ ጊዜ ብዙ አጨብጫቢዎችንና ጀሌዎችን የሚያግበሰብስ አይደለም። ነገር ግን እውነተኛ የወዛደር ፖርቲን ለመመስረትና በርሱም አማካይነት የኢትዮጵያን ሕዝቦች ትግል በቅጡ ለመምራት የሚቻለው በዚህ መንገድ ብቻ መሆኑን ያምንበታል። የሰህድ አላማ ጥቂት ጀሌዎችን፣ የቀኝም ሆኑ የግራ፣ አግበስብሶ በነዚህ አማካይነት “ጊዜያዊ ሕዝባዊ መንግሥትን” በማስመረጥ የመንግሥትን ስልጣን በተቻለ ፍጥነት መጨበጥ አይደለም። ቆራጥነትና ትእግስት በተመላበት መንገድ ታግሎ ሰፊው ሕዝብ እራሱ በገዛ አብዮታዊ ትግሉ የመንግሥትን ስልጣን እንዲጨብጥ ማድረግ ነው። በዚህም ምክንያት የሁለታችን የትግል ዘዴዎች እንደሰማይና ምድር የተራራቁ ሆነዋል።

በመጨረሻም፣ በስህድና በዲሞክራሲያ መካከል ያለው መሰረታዊ ልዩነት፣ ከላይ የተጠቀሱትን ሁሉ የሚያጠቃልለው የርእዩተአለም ልዩነት ነው። በኢትዮጵያ ግራ ውስጥ ዲሞክራሲያ የሚወክለው ደንፊውንና አለሁ አለሁ ባዩን ንኡስ ከበርቴ ነው። ይህ ክፍል፣ በሰፊው ሕዝብ ላይ አንዳንድ ጭቆናዎች ሲፈፀሙ ባየ ቁጥር በኃይለኛ ስሜት ይገፋፋና እብድ ይሆናል። በአጉል ድፍረትና ድንፋታም ሕዝቡ ሳይደራጅና ሳይታጠቅ እንዲጋፈጥ ይገፋፋል። ሰፊው ሕዝብ ጥቂት ድሎችን ባገኘ ቁጥር ደግሞ “አብዮቱን መመራት ሊቀርብኝ ነው” በሚል ፍርሃት ተወናብዶ እነዚህን ድሎች ያናንቃል፤ እንዲያውም ድሎቹን በመሸነፍ መተርጐም ይቃጣዋል። በማንኛውም ጊዜ ቢሆን ጠቅላላውን የአብዮቱን ሂደት ለመገምገምና አዝማሚያው ወዴት እንደሆነ ለማየት ሰለማይችል፣ ለማየትም ጥረት ስለማያደርግ፣ “ትንተናዎቹ” ከአፍንጫው ርቀው የማይሄዱና በግላዊነት /ሳብጀክቲቪዝም/ የተሞሉ ናቸው። ከመጠን በላይ የሆነ ተስፋና ከመጠን በላይ የሆነ ተስፋ መቁረጥም ይፈራረቁበታል። በዚህ መልካቸው ሲታዩ ደርግና ዲሞክራሲያ አንድ ናቸው ለማለት ይቻላል።

ሰህድም ቢሆን በድሃው ገበሬና በወዛደሩ፣ በተለይም በዚህኛው ውስጥ ስር እስካልሰደደ ድረስ በንኡስ ከበርቴው ጠባዮች እንደተበከለ ይኖራል። ይሁንናም፣ በተቻለው መጠን በወዛደሩ ርእዩተአለም ለመመራት፣ በትንተናው ሁልጊዜ ከተጨባጭ ሁኔታዎች ለመነሳትና ነገሮችን ከሁሉም ማእዘን ለመመልከት ይጥራል። ማንም ሊክደው እንደማይችልም፣ ሰህድ ባቋራጭ የመንግሥትን ስልጣን ለመያዝ ሳይሆን ለዘላቂው ሕዝባዊ ትግል መቃናት ይታገላል። ለማንኛውም፣ የሚመጡት አመታት በርግጥ በሁለቱ መስመሮች መካከል መለየታቸው እንደማይቀር ፈጽሞ አንጠራጠርም።

5. ደርግ፣ ዲሞክራሲያዊ መብቶች፣ የፖለቲካ ጽ/ቤት

ከዚህ በላይ ባንድ ቦታ እንደጠቀስነው ሁሉ፣ ደርጉ የግራና የቀኝ ክንፎች አሉት። በጠቅላላው፣ ግራ የምንለው የጊዜውን የኢትዮጵያ ሁኔታና የአብዮትዋን አቅጣጫ በሞላ ጐደል ተረድቶ፣ በዚህ አቅጣጫ ግስጋሴ እንዲኖር የሚታገለውን የደርግ አባል ሁሉ የሚይዘውን ክፍል ነው። የቀኝ የምንለው ደግሞ በመደብ ጥቅም፣ ወይንም ከደርግ ውጭ ካሉት ያገርና ባእድ አድሃሪዎች ጋር በመሻረክ፣ ወይንም ደግሞ ሁኔታውን ባለመረዳትና በፍርሃት፣ – ዙሮ ዙሮ እነዚህም ሁሉ የመደብን ጥቅም የሚመለከቱ ነጥቦች መሆናቸውን አንረሳም- በጠቅላላው የኢትዮጵያ ሕዝቦች፣ አብዮታዊ እንቅስቃሴ ወደፊት እንዳይራመድ መሰናከል የሚሆነውን ሁሉ ነው። አንዳንድ ተራማጆች የዚህ አይነቱ የደርግ አከፋፈል መኖሩን ይጠራጠራሉ። ይሁንናም፣ እንኳንስ እንደደርጉ ባለው የሰዎች ቡድን ውስጥ ይቅርና በአንድ ሰው አንጐልም ውስጥ የመደቦችን ትግል የሚያንፀባርቁ የግራና የቀኝ አስተሳሰቦች እንዳሉ ይታወቀ ነገር ነው። እንደዚሁም መደቦች፣ የወዛደሩ መደብ ጭምር፣ የቀኝና የግራ ክንፎች አሉአቸው። ስለዚህም በወዛደሩ እንቅስቃሴ ውስጥ ተደጋግሞ እንደታየው ሁሉ ለምሳሌ የቀኝና “የግራ” አድርባይነት የሚባል ነገር አለ። የደርጉ የግራና የቀኝ ክንፎች አሉ ተባለ እንጂ እነዚህ ክንፎች የለየላቸውና የተደላደሉ ናቸው ማለት አይደለም። ይህ ወደፊት ሊመጣ ይችላል። ለማንኛውም፡ ከጥቂት ወራት ወዲህ የሚወሰዱትን እርምጃዎች ብንመለከት፣ የደርጉ የግራ ክንፍ እንደተጠናከረ ለመገመት ይቻላል።

የሰፊው ሕዝብ የዲሞክራሲ ጥያቄዎች እየገፉ መምጣታቸውና በደርጉም ውስጥ ያለው የኃይል ማዛን ለጊዜው ወደግራው ስለሚያዘነብል፣ ረዘም ላለ ጊዜ ሲጠየቁና ሲጠበቁ የነበሩት ዲሞክራሲያዊ መብቶች በቅርቡ ሳይገኙ አይቀሩም ብለን እንገምታለን። የነዚህ መብቶች መለቀቅ በየካቲቱ አብዮታዊ እንቅስቃሴ ታሪክ ውስጥ፣ ከ“መሬት ላራሹ” በማያንስ መንገድ፣ አዲስ ምዕራፍን ይከፍታል።

ዲሞክራሲያዊ መብቶች በትክክል ከሥራ ላይ የሚውሉበትን ሁኔታ ለመፍጠርና ሰፊው ሕዝብ በፍጥነት የፖለቲካ ንቃትን እንዲያገኝ፣ እንዲደራጅና እንዲታጠቅ ለማድረግ የሚያግዝ የፖለቲካ ጽህፈት ቤት በደርጉ ስር እንደተቋቋመ ያደባባይ ሚስጥር ሆኗል። ይህ ፅህፈት በርግጥ ከላይ የተጠቀሱትን ተግባሮች የሚያከናውን እንጂ በከተማ እንደሚወራው “የደርጉን ፖርቲ” ለማቋቋም የተፈጠረ ካልሆነ፣ ሰህድ አሳቡን በመሰረቱ ይደግፈዋል። ለማንኛውም ግን፣ ጋዜጦችን አቋም ከመውሰዱ በፊት የጽህፈት ቤቱ ተግባሮች በግብር መገለጥ እስኪጀምሩ ድረስ ይጠብቃል።

6. ዲሞክራሲያዊ መብቶች ለዛሬው ትግል ከመቼውም ይበልጥ ያስፈልጋሉ።

የዲሞክራሲያዊ መብቶችን አስፈላጊነት እንደገና ለማጤን፣ ከዚህ በላይ የዘረዘርናቸውን ሁኔታዎች ባንድነት አጣምረን፣ የዛሬይቱ ኢትዮጵያ ያለችበትን ሁኔታና አዝማሚያውም ወዴት እንደሆነ እንጠቁም።

ባንድ በኩል የውስጥና የውጭ ፀረአብዮታዊ ኃይሎች በመጠናከር ላይ ይገኛሉ። በኤርትራና በጐረቤት አገሮች በኩል ያለው ሁኔታ፣ የኢምፔሪያሊዝም ሴራና የሁለቱ ሃያላን መንግሥታት ውድድር፣ የነመንገሻ ሥዩም – አሊ ሚራህ ፀረአብዮታዊ ግንባር መጠናከር፣ በሰሜንም ሆነ በደቡብ ኢትዮጵያ የመሬት ከበርቴዎች፣ የነፍጠኞችና የሌሎችም አድሃሪዎች ማንሰራራት፣ በከተሞች የቢሮክራሲው ሻጥር /ሳቦታዠ/፣ የንኡስ ከበርቴው ኩርፊያ፣ የወዛደሩ ገለልተኝነትና የሥራአጡ መብዛት፣ በተጨማሪም የንዑስ ከበርቴው ደንፊ ቡድን በተራማጁ ውስጥ ውዥንብርን መንዛት፣ እነዚህ ሁሉ ሁኔታዎች ለፀረአብዮታዊ ቅልበሳ አመቺ ሆነው እናያለን። የኢትዮጵያ ሕዝቦች በየካቲት እንቅስቃሴ ሳቢያ ያገኙዋቸው ድሎች ፀድቀዋል ለማለት ፈጽሞ አይቻልም።

ብዙ ተራማጆች በትክክል እንዳመለከቱት ሁሉ “አዋጅ በአዋጅ ይሻራል”። ሰፊው ሕዝብ ባልተደራጀበትና ባልታጠቀበት ባሁኑ ወቅት፣ ማእከላዊው ስልጣን ተገልብጦ በኢምፔሪያሊስቶች ሎሌዎች ከተያዘ፣ እነዚሁ ኢምፔሪያሊስቶችና ሎሌዎቻቸው ባጭር ጊዜ ውስጥ በሚልዩን የሚቆጠር ፀረአብዮታዊ ሰራዊት አሰልጥነው፣ አስታጥቀው ሊያሰልፉ ይችላሉ። በቪየትናም በዲዩም ጊዜ የሆነው አይነት ፀረአብዮት እዚህም ሊደረግ ይችላል። አሜሪካኖችና ዲዩም የመንግሥት ስልጣን ከጨበጡ ወዲያ፣ የቪየትናም ሕዝብ ከፈረንሳይ ቅኝ ገዥዎችና ከጃፖን ፋሽዝም ጋር ተዋግቶ ያገኛቸውን ድሎች በሁለት አመታት ውስጥ ሙሉ በሙሉ፣ ለጊዜውም ቢሆን፣ ለመደምሰስ ችለዋል። ላራሹ የሆነውን መሬት መልሰው ቀምተዋል፤ ዲሞክራሲን አጥፍተዋል።

የኢትዮጵያ ሰፊ ሕዝብም በፍጥነት እንዲነቃ፣ እንዲደራጅና እንዲታጠቅ ካልተደረገ፣ እስካሁን የተገኙት ድሎቹ ባጭር ጊዜ ውስጥ ሊደመሰሱ እንደሚችሉ ፈጽሞ መጠርጠር የለብንም። ይህ እንግዲህ የኢትዮጵያ የጊዜው ሁኔታ ጥቁር ገጽ ሲሆን ይህን አደጋ ለመቋቋም ዛሬ ከመቼውም ይበልጥ ዲሞክራሲያዊ መብቶች እንዲፈቀዱ፣ ሰፊው ሕዝብም በነርሱ እየተጠቀመ እንዲደራጅና ትግሉን በበለጠ እንዲያፋፍም ያስፈልጋል። ዛሬ የነዚህ የዲሞክራሲያዊ መብቶች መታወጅ ጉዳይ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ትግል በደረሰበት ደረጃ ፈጽሞ ሊቀር የማይችሉ ግዴታ ነው። እነዚህ መብቶች ካልተፈቀዱ የሠራተኛ ማህበራትንና የገሠበሬ ማህበራትን ማጠናከሪያ አዋጆችን ከሥራ ላይ በትክክል ለማዋል አይቻልም። የቢሮክራሲውን፣ የኢምፔሪያሊዝምንና የውስጥና የውጭ አድሃሪዎችን ሴራ አጋልጦ እነርሱንም ለመቋቋም አይቻልም። ስለዚህም፣ ዲሞክራሲያዊ መብቶች የግድ መሰጠት ይኖርባቸዋል። እንደሚሰማው በእርግጥ የሚሰጡ ከሆነ እንግዲህ ጥያቄው የነዚህ መብቶች መሰጠት ምንን ያስከትላል? እኛንስ መብቶቹ በምን ይጠቅሙናል? የሚለው ነው። እነዚህን ጥያቄዎች ከመመለሳችን በፊት ግን አንድ ነገር፡-

አንዳንድ የተሳሳቱ ተራማጆችና የዲሞክራሲያ አይነት አወናባጆች ደርግ በስልጣን ላይ እስካለ ድረስ፣ ወይንም ደግሞ “ጊዜያዊ ሕዝባዊ መንግሥት” የሚባለው ነገር እስካልተፈጠረ ድረስ፣ ወይንም ሰፊው ሕዝብ የመንግሥትን ስልጣን ራሱ እስካልጨበጠ ድረስ ምንም ዲሞክራሲ ሊኖር አይችልም ይላሉ። ይህ መቼስ ከታሪክ ቁስአካልነት የራቀ አስተሳሰብ ነው። በርግጥ የዴሞክራሲ ዋና ጥያቄ፣ “እንብርቱ” የመንግሥት ስልጣን ጉዳይ ነው።

ይህንንም ማለት የመንግሥትን ስልጣን የያዘው መደብ፣ እንደመደቡ አይነት ዲሞክራሲውም ይለያል ማለት ነው። የቡርዧ ዲሞክራሲ የቡርዧው /የከበርቴው/ መደብ ፈላጭ ቆራጭነት ነው፤ አዲሱ ወይንም ብሄራዊ ዲሞክራሲም የሰፊው ሕዝብ ፈላጭ ቆራጭነት ነው። ይሁንናም፣ ሰርቶአደሩ ሕዝብ የራሱን ዲሞክራሲ ለመመስረት በስልጣን ላይ ካሉት መደቦች የመሰብሰብን፣ የመደራጀትን፣ የንግግርንና የጽሁፍን፣ ወዘተ. መብቶች ለማግኘት ይታገላል። እነዚህን አግኝቶም ለመንግሥት ስልጣን ከውድድር ውስጥ ይገባል። ገና ለገና የመንግሥትን ስልጣን አልያዘምና፣ የሚገኘውም ዲሞክራሲ ዘላቂነት አይኖረውምና ይህንን ስልጣን ከያዘው መደብ ወይም ከያዙት መደቦች በትግሉ የሚያገኘው ዲሞክራሲ አይጠቅመውም ማለት አይደለም። ወይንም ደግሞ ስልጣንን እራሱ ካልጨበጠ፣ ታግሎ የሚያገኛቸው እነዚህ መብቶች “ዲሞክራሲ” አይደሉም ለማለት አይቻልም። እነሌኒን፣ ከሁሉ አስቀድሞ ለዲሞክራሲያዊ ሬፐብሊክ የታገሉት፣ በዚህ ሬፐብሊክ ውስጥ የሰፊው ሕዝብ ዲሞክራሲ ይሰፍናል ብለው ስላመኑ ሳይሆን፣ ሬፐብሊኩ ለወዛደሩና ለሰርቶአደሩ ሕዝብ ትግል፣ ሰፊውን ሕዝብ ስልጣን ለማስያዝ፣ አይነተኛ መሳሪያ ነው ብለው ስላመኑ ነው። ይህም ደግሞ ታሪክ በገቢር እንዳረጋገጠው ሁሉ ትክክለኛ አስተሳሰብ ነበር። በዛሬይቱ ኢትዮጵያም የመንግሥት ስልጣን ገና በሰፊው ሕዝብ እጅ አልገባም። ሰፊው ሕዝብ በትግሉ ከደርጉ በሚያገኛቸው ዴሞክራሲያዊ መብቶች በመጠቀም፣ የራሱን መንግሥትና ዲሞክራሲ የሚመሰርትበትን አብዮታዊ ሁኔታ ይፈጥራል። 

እንግዲህ ወደላይኞቹ ጥያቄዎቻችን እንመለስ፡- የዲሞክራሲያዊ መብቶች መገኘት ምንን ያስከትላል? በነዚህ መብቶች እንዴት ልንጠቀምባቸው እንችላለን?

በዚህ ጋዜጣ ተደጋግሞ እንደተጠቀሰው ሁሉ፣ ኢትዮጵያ መቼውንም ቢሆን ግልጽ የፖለቲካ ትግልን አይታ አታውቅም። ህብረተሰባችን በፊውዳሊዝምና በኢምፔሪያሊዝም የታፈነ ስለነበር፣ አሁንም በሞላ ጐደል ሁኔታው እንደዚያው ስለሆነ፣ መደቦች ባደባባይ ወጥተው በጋዜጦች፣ በንግግሮችና በተለይም በየራሳቸው የፖለቲካ ድርጅቶች አማካይነት የታገሉበት ወቅት አልነበረም። ስለዚህም የመደቦች ትግል ይካሄድ የነበረው መደቦቹን በሚወክሉ አንዳንድ ግለሰቦችና የጥቂት ሰዎች ቡድኖች ዙሪያ ሆኖ፣ የትግሉም ዘዴ በወሬ፣ በሃሜት፣ በተንኰል /በኢግትሪግ/ ነበር። የዲሞክራሲያ ሰዎች የወረሱት ፊውዳላዊ የፖለቲካ ትግል ዘዴ መሆኑ ነው። ዲሞክራሲያዊ መብቶች ሲፈቀዱ መደብ ተመደቡ ይሰለፍና ባደባባይ ይወጣል። ባሁኑ ጊዜ በዝቅተኛ ደረጃ ተደራጅተው የሚገኙት የሕዝብ ክፍሎች ሁሉ – ደርግም፣ ሰራዊቱም፣ ተማሪና ዘማቹም፣ ብሄረሰቡም፣ ሴቱም፣ ሠራተኛውም፣ ባጠቃላይ በሕዝባዊ ድርጅቶችም ሆነ በሌላ መልክ የተደራጁት ክፍሎች – ይከፋፈላሉ። ሁሉም በየፖለቲካ መስመሩ፣ ማለትም ዙሮ ዙሮ በየመደቡ ይሰለፋል። የመደቦቻችንም አሰላለፍ ግልጽ ይሆንና ማን ከየትኛው ወገን እንደሆነ ይታወቃል። ይህም ትግሉን ያፋፍመዋል፤ የሰፊው ሕዝብ ወገኖች ባንድነት የሚሰበሰቡበትን ሁኔታ ይፈጥራል። 

ዲሞክራሲያዊ መብቶች ከተፈቀዱ የሰፊው ሕዝብ የመፍጠር ችሎታ /ክሪኤቲቪቲው/ በነፃ ይለቀዋል። ማለትም ሰፊው ሕዝብ አዳዲስ የድርጅት አይነቶችን፣ አዳዲስ የአሰራርና የምርት ዘዴዎችን፣ አብዮታዊ አካባቢዎችን በያለበት ይፈጥራል። በፊውዳላዊው ሥርዓትና በኢምፔሪያሊዝም ተተብትቦ ተይዞ የነበረው ጉልበቱ ይፍታታል። ይህም አብዮቱን በቁስአካላዊም ሆነ በመንፈሳዊ ይዘቱ አሁን ካለው ሁኔታ እጥፍ-ድርብ ወደፊት ይገፈትረዋል።

ሰፊው ሕዝብ ዲሞክራሲያዊ መብቶችን ካገኘ አብዮታዊ አስተሳሰብን ባጭር ጊዜ ውስጥና በሰፊው ለማሰራጨት ይቻለናል። ይህ ጋዜጦችን ወይንም እርሱን የሚመስሉ ጋዜጦች አሁን ያላቸውን ስርጭት በአስር በሃያ እጅ ሊጨምሩ ይችላሉ። በዚህም መንገድ ሰፊው ሕዝብ በሃያ በሰላሳ አመታት ውስጥ ያላገኛቸውን የፖለቲካ ትምህርቶች በወራት ውስጥ ያገኛቸዋል። ስለዚህም፣ አሁንም አብዮታዊ ሁኔታው በፍጥነት ያድጋል።

እንደ ሰህድ ያለው ጋዜጣ አብዮታዊ አስተሳሰብን የሚያሰራጭ ብቻ ሳይሆን፣ አደራጅም ነው። ማለትም ጋዜጣው በያዛቸው አስተሳሰቦችና መፈክሮች ዙሪያ ግለሰቦችና ቡድኖች እንዲሰበሰቡ፣ ጋዜጣው መመሪያቸው እንዲሆን፣ የየእለቱን የትግል ይዘት ሊያስተጋባ የሚችልና የወደፊቱንም አቅጣጫ ሊያሳያቸው የሚችል አይነተኛ መሳሪያ ይሆናል።

ባጭሩ፣ ዲሞክራሲያዊ መብቶች ሲኖሩ፣ ሰፊው ሕዝብ ባጭር ጊዜ ውስጥ ሊማርና ሊደራጅ፣ ፊውዳሊዝምን፣ ኢምፔሪያሊዝምንና ቢሮክራሲያዊ ካፒታሊዝምን በይፋ ሊያጋልጥና ሊዋጋ፣ በጠቅላላው የመደቦች ትግል እንዲፋፋምና ሰልፉ እየለየ እንዲሄድ፣ በዚያውም ህብረተሰባችን በውስጡ የያዛቸው አዳዲስ፣ ወጣትና ገስጋሽ ኃይሎች ብቅ እንዲሉ ጥሩ አካባቢ ይኖራል።

ይሁንናም፣ ይህ ሁሉ ነገር በቀላሉ ከሰማይ እንደ መና ይወርድልናል ብለን መጠበቅ የለብንም። የዲሞክራሲያዊ መብቶች መኖር ለሰፊው ሕዝብ ወገኖች እጅግ አስፈላጊ ነገር ቢሆንም፣ አድሃሪዎችና ኢምፔሪያሊስቶች መብቶቹን ለማክሸፍ መብቶቹ በሚሰጡዋቸው ፍንጮች አይጠቀሙም ማለት አይደለም። በተቻላቸወ መንገድ ሁሉ ልዩ ልዩ ሻጥሮችን ከመፈፀም አይመለሱም። ጥቂት ግለሰቦችንና ቡድኖችን በገንዘብ እየገዙ፣ በርከት ያሉ ድርጅቶችን የግራ ካባ አሰደርበው እያቋቋሙ፣ ተራማጁ እራሱ የበለጠውን እንዲከፋፍልና ትግሉን በነርሱ ላይ በማተኮር ፈንታ እርስ በርሱ እንዲጋጭ እያደረጉ፣ በሰፊው ሕዝብ ውስጥ ጠቅላላ ውዥንብርንና ውካታን ለመፍጠር ይችላሉ። ዛሬ የሚታየውን የኢ.ህ.አ.ፖ. አይነት አወናባጅ ቡድኖች በብዛት ሊፈጥሩ ይችላሉ። በነዚህ ላይ መንቃትና ተገቢውን ማጋለጥ ማከናወን የሃቀኛ ተራማጆችና የሰፊው ሕዝብ ፈንታ ነው። በተረፈም፣ ወታደራዊው መንግሥት እራሱ በዲሞክራሲ የሚያምንና የኢትዮጵያ ሕዝቦች ትግል ወደግቡ እንዲያመራ የሚመኝ ከሆነ፣ በኢምፔሪያሊስት አገሮች ሰላዮችና አወናባጆች ላይ ተገቢውን እርምጃ መውሰድ ይኖርበታል። 

አሁን ባለንበት ሰአት ሰፊ የፖለቲካ ክርክር ካለመደረጉ የተነሳ፣ የመስመር ትግል ይህን ያህልም የተፋፋመ ስላልሆነ፣ ዲሞክራሲያዊ መብቶች በሚመጡበት ጊዜ የግራው ኃይል በብዙ ትናንሽ ቡድኖች የተከፋፈለ ሆኖ ሊወጣ ይችላል። ይህ ሁኔታና ከላይ የተጠቀሰው የአድሃሪዎች ሴራ ደርጉንም፣ ሰራዊቱንም፣ ፖሊሱንም ሊያስበረግግ ይችላል። ስለዚህም፣ ባንድ በኩል ሀቀኛ ተራማጆች ባንድነት እንዲሰበሰቡ መጣር ሲኖርብን፣ በሌላ በኩል ደግሞ የዚህ አይነቱ ሁኔታ የሚጠበቅና ቢኖርም ደግሞ ለመሸጋገሪያ ጊዜ እንጂ ዘላቂ አለመሆኑን በቅስቀሳችን ማስረዳት አለብን።

የዲሞክራሲያዊ መብቶች መታወጅ ለኢትዮጵያ ሕዝቦች አዲስ አብዮታዊ ምዕራፍን ይከፍታል። በነዚህ መብቶች በመጠቀም ለጊዜው የሚታየውን ለአድሃሪዎች መንሰራራት ለማጨናገፍ፣ እንደጥቁር ደመና ባገራችን ላይ የሚያንዣብበውን ፀረአብዮት ለመበታተንና ብሩህ የሆኑ ቀኖች እንዲመጡ ለማድረግ ይቻላል። የኢትዮጵያ ሕዝቦች የወደፊት እድል የጠራ ነው። ለነዲሞክራሲያ፣ ለነመንገሻ ሥዩምና ለሌሎችም አድርባዩችና አድሃሪዎች ያገሪትዋ ሁኔታ ጨለማ ሆኖ ይታያቸዋል። ደርግ አገሪትዋን “ከአዘቅት ውስጥ ጨምሯታል”፣ ስለዚህም ከአዘቅቱ የሚያወጣት የነርሱ ተአምረኛ “ጊዜያዊ ሕዝባዊ መንግሥት” ብቻ ነው ይላሉ። የኢትዮጵያ ሰፊ ሕዝብ ግን በተጨባጭ አኳኋን የነርሱ ብርሃን ለርሱ ጨለማ መሆኑን ያውቃል። በበኩላችን የኢትዮጵያ የወደፊት እድል ከቀን ፀሃይ የጠራ ነው እንላለን። የኢትዮጵያ ሕዝቦች ነቅተው፣ ተደራጅተውና ታጥቀው፣ እንደአንድ ሰው ሆነው መነሳታቸውና ሶስቱን ጠላቶቻቸውን፣ ፊውዳሊዝም- ኢምፔሪያሊዝም- ቢሮክራሲያዊ ካፒታሊዝምን መደምሰሳቸው ፈጽሞ አይቀርም። በነርሱም መቃብር ላይ አዲስ ሕዝባዊት ኢትዮጵያን ይገነባሉ። የሚመጡት ቀናት የሰፊው ሕዝብ ይሆናሉ።

7. መደምደሚያ፡- ተግባራችን

በየካቲት 1966 የተጀመረው የኢትዮጵያ ሕዝቦች ሰፊ አብዮታዊ እንቅስቃሴ እየወደቀ እየተነሳ፣ ብዙ መሰናክሎችን ተራ በተራ፣ ደረጃ በደረጃ እያሸነፈ፣ አሁን በጣም አመቺ ከሆነ ሁኔታ ላይ ደርሷል። በትግሉ ውስጥ ብዙ ተራማጆች፣ ብዙ የሰርቶአደሩ መደብ አባሎችና ወገኖች ሕይወታቸውን ጭምር መስዋእት አድርገዋል። አሁን በደረስንበት ደረጃ ከነርሱ እጅ የወደቀውን ባንዲራ አንስተን፣ አርአያቸውን በመከተል፣ ቆርጠን በመነሳትና ማንኛውንም መስዋእትነት ሳንፈራ፣ የሚመጡትን ችግሮች ሁሉ አንድ ባንድ እያሸነፍን ወደፊት መገስገስ አለብን።

ሰህድ ትክክለኛ የፖለቲካ መስመር አለው። ከአድሃሪዎች፣ ከቀኝና ከግራ አድርባዩች ጋር እየታገለ በሄደ ቁጥር ደግሞ ይህ መስመራችን የበለጠውን እየጠራ ይሄዳል። ነገር ግን፣ የአብዮቶች ታሪክ እንደሚያስተምረን ሁሉ፣ ትክክለኛ መስመርን መያዝ በምንም አይነት ብቻውን አይበቃም። ይህ መስመር በሰፊው ሕዝብ ውስጥ መሰራጨት አለበት። በድርጅትም መተርጐም አለበት። ስለዚህም የሰህድ ሰዎችና ደጋፊዎቹ ሁሉ ተያይዘን መጠንከር፣ መስፋፋት አለብን። በየትምህርት ቤቱ፣ በየፋብሪካው፡ በየመስሪያ ቤቱ፣ በየከተማውና በየገጠሩ፣ በተቻለ ቦታ ሁሉ የጋዜጣችን አንባቢ ቡድኖች መቋቋም አለባቸው። ሰህድን በፊው ማሰራጨትና የያዘውን መልእክት በቃልም ቢሆን ማስተላለፍ ግዴታችን ነው። ያንባቢ ቡድኖችም ጋዜጣውን ባገኙበት መንገድ በኩል እንዲጽፉልን፣ እንዲያርሙን፣ አዳዲስ አሳቦችን እንዲያቀርቡልን መደረግ አለበት። ትክክለኛ መስመራችን በሰፊው ሕዝብ ውስጥ ካልገባ፣ ከሰፊው ሕዝብ እርማትና ትምህርት ካላገኘን፣ ሰፊዉ ሕዝብም ይህንን መስመር የራሱ አድርጐ ካልወሰደ ሥራችን ዋጋ አይኖረውም።

ለዲሞክራሲያዊ ትግል ካሁኑ መዘጋጀት አለብን። ይህ ትግል አሁን የያዝነውን ሥራ እጥፍ ድርብ እንደሚያደርገው መገንዘብና በቁስአካላዊም ሆነ በመንፈሳዊ አቋማችን እንድንጠነክር የተቻለውን ሁሉ ጥረት ማድረግ አለብን። የሰህድ ሚሊታንቶችና ደጋፊዎች በያለበት እንዲበዙ፣ በሥራው እንዲሳተፉ፣ ሰፊ የቅስቀሳና ኘሮፖጋንዳ እንዲያደርጉና የጊዜውን ድካማችንን ወደ ጥንካሬ እንድንለውጠው በኃይል መታገል ያስፈልጋል። እንግዲህ፣ ለዚህ ተግባራችን የቅስቀሳችንና የኘሮፖጋንዳችን ይዘት ምን ይሆናል? 

1ኛ/ ኤርትራንና ጐረቤት አገሮችን በሚመለከተው በኩል፣ ባሁኑ ሰአት ያለውን አደጋ ለሕዝቡ መግለጽ አለብን። ሰህድ ብሄረሰቦች የራሳቸውን እድል የመወሰን መብት እንዳላቸው ያውቃል። የኤርትራ ብሄረሰቦችም ሆኑ ሌሎች ብሄረሰቦች የገዛ እድላቸው እንዳሻቸው ለመወሰን መብት አላቸው። ይሁንናም፣ የኤርትራን ግንባሮች አድርባይነትና በነርሱም ሳቢያ የመጣውን የጐረቤት አገሮችንና የሃያላን መንግሥታትን ጣልቃገብነት ማጋለጥ አለብን። የኤርትራና የኢትዮጵያ ሕዝቦች ችግሮቻቸውን በራሳቸው ለመፍታት ይችላሉ። በኤርትራ በኩል ያለውን አደጋ የኤርትራ ተራማጆች ተገንዝበውት አብረን እንድንሰለፍ ጥሪ እናደርግላቸዋለን። በግለሰብ ደረጃም ሆነ በድርጅት፣ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ አገር፣ የኤርትራንና የሌሎችንም ክፍሎች ብሄረሰቦችን ኢንተርናሽናሊስቶች ለውይይት መጋበዝ አለብን። በወዛደሩ ርእዩተአለም ላይ የቆመ የወዛደሩን ፖርቲ ለማቋቋምና ለመገንባት የምንችልበትን መንገድ ማግኘት ያስፈልገናል። ሰህድ ጠባብ ብሄርተኝነትንና የትልቅ ብሄረሰብ ትምክህትን ይቃወማል፤ ይዋጋል።

2ኛ/ የነኢ.ዲ.ዩንና የሌሎችንም አድሃሪዎች ኘሮፖጋንዳና ከኢምፔሪያሊዝምና ከቢሮክራሲያዊ ከበርቴው ጋር የሚያደርጉትን ሴራ ማጋለጥ አለብን። የነዚህን ፀረአብዮታዊ መፍጨርጨር የሚደመስሰው የሰፊው ሕዝብ መንቃት፣ መደራጀትና መታጠቅ ነው። ሰፊው ሕዝብ ነቅቶ፣ ተደራጅቶ መታጠቅ አለበት። ኢትዮጵያን ከውጭ ወረራና ከፀረአብዮታዊ ቅልበሳ ሊያድናት የሚችል የተደራጀና የታጠቀ የሕዝብ ኃይል ብቻ ነዉ። ሌላ የለም።

3ኛ/ የደርጉን የመደብ አቋምና በውስጡ ያሉትን የቀኝና የግራ ትግሎች፣ ሰፊው ሕዝብ እንዲገነዘባቸው ማድረግ አለብን። ከደርግ ወደገጠር እየተላኩ በሰፊው ሕዝብ ላይ ፋሽስታዊ ወንጀሎችን የሚፈጽሙትን የቀኝ ሰዎች ሕዝቡ ራሱ ያውቃቸዋል። እነዚህን የኢትዮጵያ ሕዝብ ይፋረዳቸዋል። ባጠቃላይ ሲታይ ግን ደርግ ባሁኑ ሰአት የኢትዮጵያ ሕዝቦች ዋና ጠላት አይደለም። ነገ ሊለወጥ የሚችል ጊዜያዊ ወዳጅ ነው። ስለዚህም በርሱና በፊውዳሊዝም- ኢምፔሪያሊዝም-ቢሮክራሲያዊ ካፒታሊዝም መካከል ያሉትን ቅራኔዎች ማባባስና ይበልጠ የደርግ አባል ከሰፊው ሕዝብ ጐን እንዲሰለፍ ቅስቀሳና ኘሮፖጋንዳ ማድረግ አለብን። በማንኛውም መንገድ ፊውዳሊዝም-ኢምፔሪያሊዝምና ደርግ “አንድም-ሶስትም” አይደሉም።

4ኛ/ የተራማጆችን አሰላለፍ በሚመለከተው በኩል፣ ዋናው አላማችን በወዛደሩ ርእዩተአለም ላይ የቆመና ሃቀኛ ተራማጆችን ያቀፈ የወዛደር ፖርቲ መፍጠር ነው። ለዚህም ባንድ በኩል በጥናት ቡድኖች አብዮታዊ ቴዎሪን ማስፋፋትና ጥራዝ-ነጠቅነትን መቋቋም፣ በኛ መስመር ባጠቃላይ ከሚሰማው ሌሎች ቡድኖች ጋር መቀራረብና ያሉትንም ልዩነቶች በሂስና በግለሂስ ማሸነፍ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ከ“ግራ” አድርባዮች ጋር የሃሜት ሳይሆን ጠንካራ የርእዩተአለም ትግል ማካሄድ አለብን። የሕዝቡን መንቃት፣ መደራጀትና መታጠቅ የሚቃረነውንና የንኡስ ከበርቴውን ፈላጭቆራጭነት በኢትዮጵያ በአቋራጭ ለመመስረት የወጣውን “ጊዜያዊ ሕዝባዊ መንግሥት” የሚለውን መፈክር ፉርሽነት በሰፊ-ውይይት ማሳየት ይገባናል።

እንግዲህ፣ ጓዶች፣ ጊዜው ጥሩ ነው! ወደፊት!!​​​​​​​
ሰፊው ሕዝብ ያሸንፋል!!!
Scroll to Top