የሰፊው ሕዝብ ድምፅ
ቁጥር 38፣ የካቲት 15፣ 1968
የፅሁፉ ፍሬ ሀሳብ
መኢሶን በዚህ የሰፊው ሕዝብ ድምፅ እትሙ፣ በዲሞክራሲያ፣ በላብ አደርና በአብዮታዊ ወጣት ጋዜጦች ዙሪያ የተሰባሰቡት ደንፊና አወናባጅ ኃይሎች የኢትዮጵያን ወዛደሮች ትግል ለማደናቀፍ በተለያዩ አስመሳይ መልኮች ጥረት እንደሚያደርጉ ያጋልጣል። በዚህም አሳሳችና አደናቃፊ የፖለቲካ አቋማቸው ከጸረ-ወዛደር አድኃሪ ኃይሎች ጎን እንደተሰለፉ በሰፊው ያባራራል።አያይዞም፣ የጊዜ ጉዳይ እንጂ ወዛደሮች ለይተው አስመሳይነታቸውን አጋልጠው እንደሚታገሏቸው ይገልጻል።
መግቢያ
ያገራችንን የፖለቲካ ሁኔታ በየዕለቱ በአንክሮ እየተከታተሉ የሚመረምሩ እውነተኛ ተራማጆች ሁሉ፣ በተለይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአንድነት ሆነው የመዘገቡት መሠረታዊ ጉዳይ፣ በዛሬው ወቅት የኢትዮጵያን ሕዝቦች ትጥቅ ለማስፈታት ያሰፈሰፉት ኃይሎች የለየላቸው አድሃሪዎች ብቻ እንዳልሆኑ ነው። እንደሚታወቀው፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መሳፍንቶቹም በመሳፍንት ወጋቸው ገና “ክርስትና ባላነሱት” ጋዜጣቸው አማካይነት፣ በኢትዮጵያ ወዛደሮች ስም መናገር ጀምረዋል። ዴሞክራሲያ፣ ላብአደር እና አብዮታዊው ወጣት በሚባሉት ጋዜጦች አካባቢ የተቆላለፈው የንኡስ ከበርቴ ደንፊ ቡድንም ከረጅም ጊዜ ጀምሮ ሲያወናብድና ሲያምታታ እንደቆየ የሚታወቅ ጉዳይ ነው።
እነዚህ የተለያዩ የሚመስሉት ኃይሎች ልዩ ልዩ ቀለሞችን እየተቀባቡ ከየኣቅባባው ብቅ ይበሉ እንጂ መሰረታቸው አንድ መሆኑን በብዙ ተጨባጭ ማስረጃዎች ለማረጋገጥ ይቻላል። የአድሃሪዎቹ ጥርቅሞች ዋና ጥረት የወዛደሩን መደብ ትግል ማጨናገፍ፣ ወዛደሩን በየምክንያቱ ማጋፈጥ፣ ማስመታት፣ መበተንና ማዳከም እንደሆነ ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ዛሬ በጣሙን ግልጽ እየሆነ በመሄድ ላይ ነው። በዚህ ጽሁፍ ውስጥ ወደፊት እንደምንደርስበት፣ ለፀረወዛደርነታቸው ምስክር ሆነው የሚቆሙት እነርሱ ራሳቸው በመሆናቸው፣ ባህሪያቸውን ማሳየቱ እጅግም አድካሚ አይሆንብንም። የዚህ ቁጥራችንም አንደኛው ኢላማ ይህው ነው።
በዚህ ቁጥራችን ውስጥ፣ በመጀመሪያ በኢትዮጵያ ሠራተⶉች ታሪክ እናትታለን። ከኢትዮጵያ ሠራተኞች የትግል ታሪክ ውስጥ የምንገነባው እስከዚህም ዝርዝር ሃተታ ለማቅረብ ሳይሆን፣ አንደኛ፣ ዋና ዋናዎቹን ወቅቶች (ፌዝስ) ለመለየትና የየምእራፎቹንም አይነተኛ ጠባዮች በመጠኑም ቢሆን ለመጠቆም ስንል ነው። ሁለተኛ፣ ከትግሉ ታሪክ በምንቀስመው ትምህርት በበለጠ የነቃና የተደራጀ ትግልን አስፈላጊነት በበለጠ ለማብሰር ስንል ነው። በመጨረሻም፣ዛሬ በወዛደሩ ስም ለመናገር ያኮረኮሩትን “መሳፍንት ማርክሲስቶች” እና የንኡስ ከበርቴ ደንፊዎች በቅጡ ለማጋለጥ የሚቻለው በእነደዚህ አይነቱ የትንተና ዘዴ ብቻ እንደሆነም አጥብቀን ስለምናምን ነው።
የኢትዮጵያ ሠራተኞች በየካቲቱ ሕዝባዊ አብዮታዊ እንቅስቃሴ ወቅትም ሆነ ከዚያን ጊዜ በፊትና በኋላ፣ ለመብታቸውና ለጥቅማቸው ሲሉ ከፍተኛ ተጋድሎዎችን እንዳካሄዱ ታሪካቸው ራሱ ይመሰክርላቸዋል። ከኢትዮጵያ ሠራተⶉችም ታሪክ የምንቀስመው የመጀመሪያው ታላቅ ትምህርት፣ የኢትዮጵያ ሠራተኞች ከሞላ ጎደል በወጉ ተሰልፈው ለመታገል የበቁትና “ብዙ” ድሎችንም ለመቀዳጀት የቻሉት፣ የመጀመሪያውን የሠራተኛ ድርጅታቸውን ጥንስስ ከጣሉበት ጊዜ አንስቶ እንደሆነ ነው። ለወደፊቱም ቢሆን፣ ብዙ ውጣ ውረድ የሞላበትን አብዮታዊ ትግል ሊመሩ የሚችሉትና በድል አድራጊነትም የፖለቲካውን ስልጣን ሊጨብጡ የሚችሉት፣ በነቃና በተደራጀ ትግላቸው አማካይነት ብቻ እንጂ፣ በሌላ በምንም አይነት ተአምር ሊሆን አይችልም። ይህንን እውነት መካድ ወይንም ደግሞ ችላ በማለት ወደሥራ አለመተርጎም፣ በወዛደሩ መራራ ሕይወት ላይ መሳለቅና ማላገጥ ነው።
ነገር ግን በዚህም ብቻ አናበቃም። ዛሬም ሆነ ለወደፊቱ፥ የተራማጅ ለምድ የለበሱ የሚያወናብዱትን አድሃሪዎች ሁሉ መቋቋምና ማጋለጥ አንደኛው አብዮታዊ ተግባራችን እንደሆነ እናምናለን። በዚሁ ትክክለኛ መስመር በመግፋትም፥ ዛሬ የወዛደሩን መደብ ለመበታተንና ለማደከም የተነሳሱትን “መሳፍንት ማርክሲስቶች” እና የወዛደሩን መደብ ትግል ለማክሸፍና በዲሞክራሲያ አካባቢ ያከለኮሉትን የንኡስ ከበርቴ ደንፊዎች ባለን አቅም ሁሉ እናጋልጣቸዋለን፣ እንታገላቸዋለን። የወዛደሩ መደብ እየመነጠረ እንዲያወጣቸው በገሃድ እናመለክተዋለን። ለነቃና በወጉ ለተደራጀ ትግል እንጠራዋለን።
የኢትዮጵያ ሠራተኞች የትግል ታሪክ ባጭሩ
እንደሚታወቀው የኢትዮጵያ ወዛደር መደብ የተወለደው በእድገቱና በአስተሳሰቡ እጅግ ወደኋላ በቀረ የፊውዳል ህብረተሰብ ውስጥ ነው። ዘመኑም፣ በተለይም “ነቃ ያለው” የፊውዳል መደብ ክፍል፣ ጥቅሙንና ሕይወቱን በመላ ከኢምፔሪያሊስት ዓለም ጋር ለማስተባበር ሲል ለኢምፔሪያሊስቶች እየሰገደ ጭራውን የሚቆላበት ዘመን ነበር። ስለሆነም፣ የኢትዮጵያ ወዛደር መደብ ገና ከተወለደ ጊዜ አንስቶ፣ ከሁለት አበይት ጠላቶች ጋር (ከፊውዳሊዝምና ከኢምፔሪያሊዝም ጋር) ፊት ለፊት እንዲጋጠምና የሞት ወይንም የሽረት ትግል እንዲያካሂድ ተገድዶ ነበር። የኢትዮጵያ ወዛደር መደብ ገና በጨቅላነቱ የተናነቃቸው እነዚህ ጠላቶቹ፣ ዛሬም ቢሆን የኢትዮጵያ ሕዝብ ዋና ጠላቶች ናቸው።
የስከዛሬውን የኢትዮጵያ ወዛደሮች የትግል ታሪክ በአጠቃላይ በሰባት (7) ወቅቶች በመክፈል ለማጥናት እንችላለን። የትግሉን ዘመን በወቅቶች የምንከፍለው፣ እስከዚህም በመሰረታዊ ባህሪያዎች (የመደብ ትግል ነውና) የተለያዩ ትግሎች ታካሄደዋል ለማለት ሳይሆን፣ የእድገት ደረጃዎችን በቅጡ በመለየት እንድንችል በማለት ነው። የመጀመሪያው ወቅት ከ1939-1953 ዓ.ም ድረስ ያለው ጊዜ ነው።
I
የኢትዮጵያ ሠራተኞች ቀደም ሲሉም ቢሆን፣ በእድርና በመረዳጃ መልክ እየተረዳዱ የየእለት ችግሮቻቸውን ለመወጣት ይሞክሩ ነበር። ይሁንናም፣ ከጊዜ በኋላ ደግሞ፣ በእነዚህ ማህበሮች፣ አማካይነት ብቻ እርስበርስ መጠጋጋት የማያዛልቃቸው መሆኑንም መረዳታቸው አልቀረም። እንደዚሁም፣ ይዋል ይደር እንጂ፣ የኢትዮጵያ ወዛደሮች በተደራጀ መልክ ከመደብ ትግል ውስት መግባታቸው አልቀረም ነበር።
በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ የመጀመሪያው የሠራተኞች ማህበር የተመሰረተውና፣ ሠራተኞቹም በራሳቸውም ድርጅት አመራር ስር ተሰልፈው የመጀመሪያውን የሠራተኛ እርምጃ የወሰዱት በ1939 ዓ.ም. ላይ ነበር። ከኢትዮጵያ ሠራተኞች የታሪክ መዛግብት እንደምንረዳው፣ የሠራተኞችን መደብ በግንባር ቀደምነት የመሰረቱት ሠራተኞች የፍራንኮ- ኢትዮጵያ የምድር ባቡር ሠራተኞች ናቸው። ማህበራቸውም 10/12/ አባላት በሚገኙበት አንድ የሠራተⶉች ኮሚቴ አማካይነት የሚመራ ነበር። ማህበሩ ከተቋቋመበት ጊዜ አንስቶ፣ የአባላቱን መብቶችና ጥቅሞች ለማስከበር ከፍተኛ ተጋድሎ አካሂዷል። በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ የመጀመሪያው የሥራ ማቆም እርምጃም የተወሰደው በዚሁ ማህበር ነው።
ካንዳንድ መረጃዎች እንደሚታየው በጊዜው ትግሉን የቀሰቀሱት ጥያቄዎች የሠራተኛውን የእለት ከእለት ችግሮች የሚመለከቱ ነበሩ። ዋና ዋናዎቹም የሚከተሉት ናቸው፦ 1/ የማህበራቸው በሕግ መታወቅ፣ 2/ አላግባብ ከሥራ መባረር እንዲቀር፣ 3/ ለተመሳሳይ ሥራ ተመሳሳይ ክፍያ፣ 4/ በሥራ ስምሪትም እንደፈረንጆቹ ችሎታ ላላቸው ኢትዮጵያን ሁሉ የሥራ እድሎች ክፍት እንዲሆኑ፣ 5/ አሰቃቂና አደገኛ የሥራ ሁኔታዎች እንዲሻሻሉ፣ 6/ የጡረታ መብት… ወዘተ።
ነገር ግን፣ ፊውዳሊዝምና ኢምፔሪያሊዝም ለሠራተኛው ሕዝብ ከቶም ደንታ የሌላቸው የበዝባዥ ሥርአቶች በመሆናቸው፣ ሠራተኞቹ ለጥያቄዎቻቸው አንዳችም መልስ ሳያገኙ ቀሩ። የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ሠራተኞች ማህበር ከጥያቄዎች መደርደር አልፎ ወደሠራተኞች እርምጃ የተሻገረውም በዚህም ወቅት ነው። በ1939 ዓ.ም. ላይ ቁጥጥራቸው 7000 የሚደርስ የኩባንያው ሠራተኞች በአንድነት ሆነው ለሁለት ወራት ሙሉ ሥራ በማቆም ታገሉ። ለኢምፔሪያሊስቶች ያደረው የኃይለሥላሴ መንግሥት፣ በመጀመሪያ በሃረርጌ ገዥው፣ በኋላም በየተራ ባቋቋቸው ኮሚቴዎች አማካይነት የሠራተኛቹን ተገቢ እርምጃ ለማዳፈን ሞክሮ ነበር። ኩባንያውም “ሃበሻ ምግቡ ማሸላ፣ ልብሱ ዶንያ፣ መኝታው ኬሻ” በሚለው የቅኝ ገዥ ዘረኛ ፍልስፍናው በመመራት፣ ታጋይ ሠራተኞችን እያስወጣና በገንዘብ እየቀጣ ልዩ ልዩ ተጽእኖዎችን ለማድረግ ሞክሮ ነበር።
ይሁን እንጂ፣ ሠራተኞቹ በየጊዜው በወሰዷቸው ቆራጥ እርምጃዎች የሚወርድባቸውን ግፍና አመጽ ሁሉ በትክክል የተቋቋሙት እንደነበር ደግሞ፣ ታሪካቸው ራሱ በቅጡ ያስረዳናል። የዚህ ድርጅት ሠራተኞት በዘረኝነት የተጨማለቀው ኢምፔሪያሊዝም በስድብ ያከናነባቸውን ውርደት በዱላ ተበቀሉት። እንደገና በ1941 ዓ.ም. ላይ ለአንድ ወር ተኩል የቆየውን የሥራ ማቆም እርምጃ በወሰዱበትም ጊዜ፣ ከጥያቄዎቻቸው መካከል አንዳንዶቹን ለማስፈፀም ችለው ነበር። “የኢትዮጵያና የፈርንሳይ የምድር ባቡር ኩባንያ ሠራተኞች ማህበር መጽሄት” በሚል ስም ይታተም ከነበረው መጽሄታቸው እንደምንረዳው፣ የዚህ ድርጅት ሰራተኞች በ1943 ዓ.ም. ላይ ሌላ የሥራ ማቆም እርምጃ ወስደው ነበር።
“በአሰሪው ጭቆና” ይላል ሠራተኞች በዚሁ መጽሄታቸው ውስጥ፣ “በአሠሪው ጭቆና ምክንያት ችግሩን ለማስታገስ ባለመቻሉ ካንድ ሁለት ሦስት ጊዜ ያደረጋቸው ንቅናቄዎች በህገወጥነት ተገምተዋል” (ገጽ 2፣ መጽሄቱ ዓ.ም. ስለሌለው ዓ.ምቱን ልናቀርብ አልቻልንም-ሰህድ)።
የፍራንኮ-ኢትዮጵያ የምድር ባቡር ሠራተኞች እንደዚህ በለሰለሰ አነጋገር ያስተላለፉልን ሃቅ፣ በጊዜው የነበረውን የኢትዮጵያ ሠራተኞች መራራ ጩኸት በግልጽ ያበስርልናል። የኢትዮጵያ ሠራተኞች ይህንን መራራ ጩኸት ካሰሙበት ጊዜ አንስቶ፣ በህግ የታወቀ ድርጅት እንዲኖራቸው ያደረጉት ተጋድሎ በዚህች ባጭር ጽሁፍ ውስጥ ሊገለጽ የሚችል አይደለም። በዓመታት እንኳን ቢቆጠር ከመጀመሪያው በ“ሕገ-ወጥ” መንገድ ከተመሰረተው የሠራተኞች ማህበር አንስቶ፣ እስከሕጋዊው ማህበራቸው መቋቋም ድረስ (ከ1939-1955) ያለው ጊዜ እንኳን የአንድ ጎልማሳ እድሜ ነው። የኢትዮጵያ ሠራተኞች በእነዚህ ዓመታት ውስጥ ሰብአዊ መብቶቻቸውን ለማስከበር ብዙ ተጋድሎዎችን አድርገዋል። ብዙ ኢሰብአዊ ግፍና አመጽ ተፈጽሞባቸዋል።
ከ40ኛው ዓ.ም. መግቢያ እስከ 50ኛው ዓ.ም አጋማሽ ድረስ የነበረውን የኢትዮጵያ ሠራተኞች እንቅስቃሴ አይነተኛ የሚያደርጉት ባህሪዎችም ሁለት ናቸው። አንደኛው በርከት ያሉ የሠራተኞች ማህበሮች መቋቋማቸው ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ የተበታተነው የሠራተኛው ትግል ነበር።
በ50ኛው ዓ.ም መግቢያ ላይ ተቋቁመው ከነበሩት ማህበራት መካከል፣ ከአዲስ አበባ የወንጂ ሱኳር ፋብሪካ፣ የሞዝቮልድ፣ የቃጫ ፋብሪካ፣ የሕዝብ ማመላለሻ፣ የዲያባኮ ጥጥ ፋብሪካ፣ የፎግስታድና ቫስኪን እና ከድሬዳዋ የሲሚንቶና የጥጥ ፋብሪካ ሠራተኞች ማህበራት ይገኙባቸዋል። በኤርትራ ቀደም ሲልም ጀምሮ ብዙ የሠራተኛ ማህበሮች ተቋቁመው ነበር። ይሁን እንጂ፣እነዚህና/ምናልባትም ሌሎችም ማህበራት ጭምር) በነዚህ ዓመታት ውስጥ ምንም እንኳን በየጊዜው እየተነሱ ቢታገሉም፣ ትግላቸው በዚያው በሚሰሩበት ቦታ ተወስኖ ይቀር ነበር እንጂ ከዚያ ውጭ የሚዘልቅና የሚያስተጋባ አልነበረም። ለምሳሌም ያህል፣ በ1953 ዓ.ም. ላይ የአየር መንገድ፣ የወንጂ ስኳር ፋብሪካ፣ የዳርማር ጫማ ፋብሪካ፣ የጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካና የከባድ መኪና ሾፌሮችና ታክሲ ነጂዎች ወዘተ. . . የወሰዷቸውን ሥራ ማቆም እርምጃዎች ልንጠቅስ እንችላለን።
ሆኖም፣ የኢትዮጵያ ወዛደሮች ከጊዜ ጋር፣ በአንድነት መደራጀቱና መታገሉ የበለጠ እንደሚያጠናክራቸው መረዳታቸው አልቀረም ነበርና፣ የ50ኛው ዓ.ም. መግቢያ በሌላ በኩል ደግሞ፣ የአንድ የአጠቃላይ የሠራተኞች ማህበር መመስረት ዋዜማም ነበር። የጊዜውም የአካባቢ ሁኔታ ለእንደዚህ አይነቱ እርምጃ አመቺ እንደነበር አንዳንድ እውነቶችን ብቻ በማውሳት ለመረዳት ይቻላል።
አመቺ የአካባቢ ሁኔታዎች የምንላቸው፦ አንደኛ፣ አዳዲስ የሥራ ዘርፎች መከፈታቸውንና የሠራተኞች ቁጥር መጨመሩን፣ ሁለተኛም፣ የኤርትራንና የኢትዮጵያን ፌደሬሽን፣ ሶስተኛም፣ የኃይለሥላሴ ፊውዶፋሽስት መንግሥት የአፍሪካ አንድነት ድርጅት መሥራች አባልና አስተናጋጅ ሆኖ መቅረቡንና አራተኛም፣ ኢትዮጵያ ረዘም ላለ ጊዜ የዓለም ሠራተኞ ማህበር (አይ.ኤል.አ.) አባል ሆና ማቆየቷን ነው። እነዚህ የአካባቢ ሁኔታዎች፣ የኢትዮጵያን ሠራተኞች ወደ ተቀነባበረ ትግል እንዲያመሩ ይርዷቸው እንጂ፣ ዋናው ምክንያት እያደገ የመጣውን ብዝበዛና ጭቆና ተበታትነው ለመቋቋም አለመቻላቸውን ከትግላቸው በመረዳታቸው እንደሆነ ለመካድ አይቻልም። የሁለተኛው ወቅት መክፈቻም ይኸው የታሪክ እድገት ነው። ሁለተኛው ወቅት ከ1953-1955 ዓ.ም. ድረስ ያለው ጊዜ ነው።
II
በዚህን ጊዜ ውስጥ የነበረውን የኢትዮጵያ ሠራተኞች እንቅስቃሴ አይነተኛ የሚያደርጉት ዋና ባህሪዎች ሁለት ናቸው። ምን እንኳን ለጊዜው ካሉን መረጃዎች እንደምነረዳው፣ ጠቅላላው የትግል አቅጣጫ አንድ አጠቃላይ ማህበር በመመስረት ላይ ያተኮረ ቢሆንም፣ ይኸው እንቅስቃሴ በሌላ በኩል ደግሞ፣ የኢትዮጵያ ሠራተኞች ማህበራት በህግ የታወቀ እንዲሆኑ ከፍተኛ ተጋድሎ ማድረግ እንደነበረበት ልንጠራጠር አንችልም። ይህንን ከፍተኛ የትግል እርምጃ በግንባር ቀደምነት ያንቀሳቀስ የነበረው የሠራተኛ ማህበር፣ በአቶ አበራ ገሙ ይመራ የነበረው የኢትዮጵያ ቃጫ ፋብሪካ ሠራተኞች ማህበር ነበር።
“የምናሳስባችሁ” ይላሉ አቶ አበራ ገሙ፣ ግንቦት 18 ቀን 1953 ዓ.ም. በጊዜው ለነበሩት የኢትዮጵያ ሠራተኞች ማህበራት በፃፉት ደብዳቤ ውስጥ፣ “የምናሳስባችሁ፣ ለኑሯችን መልካም ግብረገብነት ሰላማዊ ድርጅት ለማቋቋም ስላሰብን፣ የሚቋቋመው ማህበር ተካፋይ ትሆኑ ዘንድ ነው። ሙሉ እምነታችንን በናንተ ላይ አድርገን የምንጠራችሁ፣ ይህ ከዚህ በላይ የተፃፈው ለኛ ለሠራተኞች ለወደፊት ደንበኛ እርምጃ የሚሰጠን ስለሆነ ነው።” (ስርዝ የተጨመረ- ሰህድ) ጥሪው የተደረገው ለግንቦት 20 ቀን 1953 ዓ.ም. ሲሆን፣ የስብሰባውም ቦታ ደጃዝማች ባልቻ ፎቅ ፊት ለፊት ከሚገኘው ሜዳ ላይ ነበር።
“በዚያን እለት” ይላሉ የሞዝቮልድ ሠራተኞች ስለስብሰባው ባቀረቡት ራፖርት ውስጥ፣ “በዚያን እለት ስብሰባ፣ ከጠሪው ክፍል ጋር የአራት ፋብሪካ ሠራተኞች (የቃጫ ፋብሪካ፣ የሕዝብ ማመላለሻ፣ የዲያባኮ የጥጥ ፋብሪካ፣ የፎግስታድና ቫስኪን) ብቻ ነበርን። . . . በአቶ አበራ ገሙ የቀረበው ሃሳብ፣ በአንድነት ሆነን ማህበር እናቋቁም የሚል ነበር። ይህንን ሃሳባቸውን በፀጥታ ካዳመጥናቸው በኋላ፣ ከኛ ክፍልም አቶ ገብረሚካኤል ወልደመድህን. . . ንግግር ሲያደርጉ እንዲህ አሉ “ስለዓለም የሠራተኞች ማህበር ሁኔታ ቀደም ብሎ በሬዲዮና በጋዜጣ እሰማና አነብ ነበር። ዛሬ ደግሞ ይህን በመስማቴ በጣም ደስ ብሎኛል። ቅዱስ በሆነው በዛሬው ቀን የተሰበሰብነው የአራት ፋብሪካ ሠራተኞች ብቻ የምናቋቁመው ማህበር በቂ ሆኖ ሊጠቅመን ስለማይችል፣ እንደዓለም የሠራተኞች ማህበር (እኛም) አንድ የኢትዮጵያ ሠራተኞች ማህበር የሚል እንድናቋቁም” . . . (ሰረዝ የተጨመረ)
የአቶ ገብረሚካኤል ንግግር ተጨማሪ ሃተታ የሚያስፈልገው አይደለም። የእቅድ ጥራት ያለው ከመሆኑም በላይ፣ የዓለምአቀፋዊነት ስሜት እንደሚታይበትም ግልጽ ነው። ሳናስታውሰው የማናልፈው ቁም ነገር ግን፣ ግንቦት 20 ቀን 1953 በኢትዮጵያ ሠራተⶉች የትግል ታሪክ ውስጥ ከፍተኛ ቦታን የሚያዝ ቀን እንደሆነ ነው። የኢትዮጵያ ሠራተኞች ይህንን ቀን ለዘላለም ሲያስታውሱት ይኖራሉ።
አሁንም ከሞዝቮልድ ሠራተኞች ማህበር እንደምንረዳው፣ የኢትዮጵያ ሠራተኞች “ቀን በሥራ ላይ፣ ማታ በእረፍት ጊዜያቸው፣ ደብዳቤ በመፃፃፍና በመላላክ ብዙ ከደከሙ በኋላ” በሰኔ ወር 1953 ዓ.ም. ላይ የ22 ፋብሪካ ሠራተኞችን በአንድነት ለመሰብሰብ ችለው ነበር። ለኢምፔሪያሊስቶች ያደረው የኃይለሥላሴ መንግሥት፣ እየገፋ የመጣውን የሠራተኞች እንቅስቃሴና የሠራተኞችን መደራጀት በምንም አይነት ኃይል ሊቋቋመው እንደማይችል የተረዳውም በዚህ ጊዜ ነበር።
ብዙም አልቆየ፣ በነሃሴ ወር 1954 ዓ.ም. ላይ “የአሠሪና የሠራተኛ ጉዳይ” አዋጁን አውጆ፣ በሕዝባዊ ኑሮ እድገት ሚኒስቴር ውስጥ የአሠሪና የሠራተኛ ጉዳይ መ/ቤቱን አቋቁሞ ነበር። “ከዚህ በኋላ” ይላል የሞዝቮልድ ሠራተኞች ማህበር፣ ከዚህ በኋላ እያንዳንዱ የፋብሪካ የሠራተኞች ማህበር በህግ መፈቀዱ በሬዲዎና በጋዜጣ በተሰማ ጊዜ፣ ወደማህበሩ ለመግባት ፈቃደኞች ያልነበሩ ሁሉ፣ እኛ እንሰበሰብበት ወደነበረው ስፍራ በብዛት መጉረፍ ጀመሩ” ከዚህ በኋላ የነበረውም ትግል “አንድ የኢትዮጵያ ሠራተኞች ማህበር” የሚል ማቋቋምና ማህበሩን ማሳወቅ ነበር። የነጋሲው መንግሥት፣ በሠራተኞች ትግል ተገዶ በሚያዚያ ወር 1955 ዓ.ም. ላይ “የኢትዮጵያ ሠራተኞች አንድነት ማህበርን (ኢ.ሠ.አ.ማ)”ን በሕግ ሲያውቅ፣ ከ15000 የሚያንሱ የኢትዮጵያ ሠራተኞች በ29 ማህበራት ሥር ተደራጅተው ነበር።
ማህበሩ በህግ ታውቆ ሲመሰረት ለመሪነት የተመረጡት ሹማምንት የኢትዮጵያን ሠራተኞች አፈላልገውና ሰብስበው “ለወደፊቱም ደንበኛ እርምጃ የሚሰጣቸውን” የሠራተኞች የአንድነት ማህበር ለማቋቋም የደከሙትና የታገሉት ወዛደሮች ነበሩ። እነሱም፣ አቶ አበራ ገሙ (ከቃጣ ፋብሪካ፣ የክብር ፕሬዚዳንት)፣ አቶ አብርሃም መኮንን( ከወንጂና ሱካር ፋብሪካ፣ ፕሬዚዳንት)፣ አቶ ዘለቀ ወልደማሪያም (ከድሬዳዋ ጥጥ ፋብሪካ፣ ም. ፕሬዚዳንት)፣ አቶ በየነ ሰለሞን (ምንም አይነት ማህበር ሳይወክሉ፣ ዋና ፀሃፊ)፣ አቶ አለሙ ቦጋለ (ከቃጫ ፋብሪካ፣ ም. ፀሃፊ)፣ አቶ ኃይሉ ኢጋ (ከአየር መንገድ፣ ም.ፀሃፊ)፣ አቶ ደጀኔ መኮንን (ከፎግስታድና ከቫስኪን፣ ገንዘብ ያዥ) ናቸው። አንዳችም ማህበር ሳይወክል ሰርጎ የገባው በየነ ሰለሞን፣ የኋላ ኋላ ጠንቅ እንደሆነባቸው ወደፊት እንመለስበታለን።
ለኢትዮጵያ ሠራተኞች አንድነት ማህበር መቋቋም የጊዜውም የአካባቢ ሁኔታ አመቺ እንደነበር ቀደም ስንል አመልክተናል። ይሁን እንጂ፣ የኢትዮጵያ ሠራተኞች እርስ በርስ መፈላለጋቸውና በድርጅት ሥር በአንድነት መቀነባበራቸው የጊዜው የታሪክ ግዴታም እንደነበር ወዲያውኑ ገልፀናል። አቶ አበራ ገሙ በጊዜው እንዳሳሰቡት፣ በዚያን ወቅትና “ለወደፉቱም ደንበኛ እርምጃ ሊወስዱ የሚችሉት በአንድነት ሆነው በማህበር ለመደራጀት ሲችሉ ብቻ ነበረ።” ሆኖም፣ ከአካባቢያቸው ሁኔታ ውስጥ፣ በተለይም የኤርትራና የኢትዮጵያ ፌደሬሽን መመስረትና የአፍሪካ አንድነት ድርጅት መቋቋም ደግሞ ለዚሁ እርምጃቸው በጣሙን ረድቷቸዋል።
የኤርትራ ሠራተኞች፣ ከፌደሬሽኑም በፊት ቢሆን በሕግ የታወቁ የሠራተኛ ማህበሮችና የትግል ልምድ ያላቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች እንደነበሯቸው ይታወቃል። እንደሚታወሰውም፣ በ40ኛው ዓ.ም. መጨረሻ ላይ፣ የሠራተኞች እንቅስቃሴ ብርክ ያስያዘው የኃይለሥላሴ መንግሥት በየህግ ማውጫው ምክር ቤት (በኤርትራም ጭምር) የሠራተኞችን መብት የሚፃረሩ ሕጎቹን ማውጣት ጀምሮ ነበር። በ1950 ዓ.ም. ላይ የኤርትራ የሕግ ምክር ቤት፣ ፀረ ሠራተኛ የሆነ ሕግ ባሳለፈበት ጊዜ በአስመራ ከተማ ከ5000 የሚበልጡ ሠራተኞች የተቃውሞ ሰልፍ በማድረግ ከወታደሮች ጋር ከፍተኛ ግጭት አድርገዋል፤ በብዙ መስዋአትነት ለመብታቸው ታግለዋል። ስለሆነም፣ በ“አንድነቱ” ግርግር ሰሞን፣ የነጋሲው መንግሥት፦ አንደኛ፣ በኤርትራ የነበሩትን የሠራተኞች ማህበራት እንዲያውቅ ተገድዶ ነበር። ሁለተኛም፣ ለዓለም ሕዝቦች “ዲሞክራሲያዊ” መስሎ መታየቱ የግዴታ ሆኖበት ነበርና፣ በ1948 ዓ.ም. ላይ ሕገመንግሥቱን “አሻሽሎ” ቀርቦ ነበር።
በዚያኑ ጊዜ የተፈጠረው ሌላ አመቺ ሁኔታ ደግሞ፣ የኃይለሥላሴም መንግሥት የአፍሪካ አንድነት ድርጅት መሥራች አባልና አስተናጋጅም ሆኖ መቅረቡ ነበር። የኃይለሥላሴ መንግሥት ለዚሁ “ብቁ እንዲሆን”፣ በኢትዮጵያም ውስጥ በሕግ የታወቁ የሠራተኞች ማህበራት መኖራቸውን “ማሳየት” እና ራሱን አጋጊጦ መታየት ነበረበት። በጊዜው፣ የኢትዮጵያን ሠራተኞች በአንድነት ለመበስበስ የታገሉት ወዛደሮች፣ የኢትዮጵያን ሠራተኞች ያደራጁትና ማህበራቸውንም በሕግ ለማሳወቅ የበቁት በእነዚህም አመቺ ሁኔታዎች በትክክል በመጠቀም ነው።
እንደገለጽነው፣ ኢ.ሠ.አ.ማ. በተቋቋመ በአራተኛው ወር ላይ (ሃምሌ 1955) የመጀመሪያውን የመልእክተኞች ጉባኤ ሲጠራ፣ 15000 አባላት ያሏቸው 29 የሠራተኛ ማህበራት ተመስርተው ነበር። ካንዳንድ መዛግብት እንደምናየው፣ የኢ.ሠ.አ.ማ. የመጀመሪያው ጉባኤ በብዙ አቅጣጫዎች የተደራጁትን ሠራተኞች ጥንካሬ ቢያሳይም፣ በሌላ በኩል ደግሞ፣ በትግል ልምዱ ገና ያልበሰለ መሆኑን የሚያመለክቱ አንዳንድ እርምጃዎች እንዳልታጡበትም ለመካድ አይቻልም።
ጉባኤው ወደ ውሳኔዎች ያመራው በቅድሚያ የየማህበራቱ ተወካዮች ስለሥራቸው ሁኔታ ያቀረቧቸውን ብሶቶችና ምሬቶች በጥሞና ካዳመጠ በኋላ ነበር። በውሳኔው ውስጥ ካቀረባቸው ጥያቄዎች መካከል፦ የአሠሪና የሠራተኛ ህግ በአስቸኳይ እንዲወጣ፣ 2/ ለሕይወት ጠንቅ የሆኑት የሥራ ሁኔታዎች እንዲሻሻሉ፣ 3/ የመንግሥቱ ፖሊስና ፍርድ ቤቶች በሠራተኛ ላይ የሚፈጸሙት በደልና ግፍ ባስቸኳይ እንዲታገድ፣ 4/ አላግባብ ከሥራ ማባረር እንዲቆይም፣ 5/ የጡረታ መብት ወዘተ. . . የሚሉት ይገኙባቸዋል። ጉባኤው የተነሳው፣ ላቀረባቸው ጥያቄዎች በ60 ቀናት ውስጥ መልስ ካላገኘ፣ ጠቅላላ የሥራ ማቆም እርምጃ እንደሚወስድ ጥብቅ ማስጠንቀቂያ ሰጥቶ ነበር።
ከሚነገረው እንደሚሰማው፣ ይህ የርምጃ ውሳኔ በሚወስድበት ወቅት፣ በሁለት ወገኖች በኩል የከረረ ክርክር ተካሂዶ ነበር። አንድኛው ወገን “ገና አልተጠናከርንም፤ አሁን የሥራ ማቆም እርምጃ በመውሰድ መጋፈጥና መመታት ነው፤ ጊዜው አይደለም. . .” በማለት ሲከራከር፣ ሌላው ወገን ደግሞ፣ “የማህበሩን ማንነት ለማሳወቅና የተረገጠውን የሠራተኞች መብት ለማስከበር መውሰድ ያለበት እርምጃ እንደሆነ” ደጋግሞ ይገልጽ ነበር። የሆነው ሆኖ፣ ለሁለት ቀንና ሌሊት የጋለ ክርክር ከተካሄድ በኋላ፣ “በጊዜው ማህበር ያቋቋሙና ያላቋቋሙ ሠራተኞች ሁሉ በአንድነት ሥራ እንዲያቆሙ ተወሰነ።” እንደእውነቱም ከሆነ፣ የጊዜው ሁኔታ ከዚህ የተለየ እርምጃ እንዲወስድ የማይፈቅድ ነበር። በአንድ ወገን ከመንግሥቱ ተጽእኖ የተነሳ የማህበሩ ህልውና ከጥያቄ ውስጥ ገብቶ ነበር። የሠራተኛ ማህበር መሪዎች በገፍ ይታሰሩና ከሥራ ይባረሩ ነበር። የነጋሲውም መንግሥት፣ ለአፍሪካ አንድነት ድርጅት ክብረ በዓል “ካሳያቸው” በኋላ፣ የልቡን ሊያደርስ አይኑን አያሽም ነበር። በሌላ ወገን ደግሞ፣ በኢትዮጵያ ሠራተኞች ጫንቃ ላይ ለዓመታት የተጠራቀመው ግፍና አመጽ የያንዳንዱን ሠራተኛ ሕይወት ከሞት አፋፍ ላይ አድርሶት ነበር።
ውሳኔው እንዳለፈ የሚቀጥለው ውይይት ያተኮረው በእርምጃው ዝግጅት ላይ ነበር። ካንዳንድ ምንጮች እንደሚሰማውም፣ የጊዜው መሪዎች ለሚወስደው እርምጃ ከፍተኛ ዝግጅቶችን አድርገዋል። አንደኛው ዝግጅት የስንቅን ጉዳይ የሚመለከት ሲሆን፣ ለዚሁም የየፋብሪካው ሠራተኞች ለእድር፣ ለእቁብ፣ ወይንም ደግሞ ለእዳ የሚከፍሉትን ክፍያ አቁመው፣ ቢያንስ ለወር ያህል የሚያበቃቸውን ቀለብ እንዲሸምቱ መምሪያ ተላልፎ ነበር። ሁለተኛው ዝግጅት ከፖሊስ ኃይል ጋር የሚገጥማቸውን የከረረ ግጭትና መከላከያቸውን የሚመለከት ነበር።
ነገር ግን፣ የነጋሲው መንግሥት ብዙም አልቆየ፣ የኢምፔሪያሊስቶች ጌቶቹንና የራሱን ጥቅም ለማስጠበቅ ሲል፣ መላውን የቢሮክራሲ፣ የዜና ማሰራጫ፣ የፖሊስና የፀጥታ ኃይሉን አሰልፎ በኢ.ሠ.አ.ማ. ላይ ዘመተበት። ከጥቂት ቀናትም በኋላ፣ የማህበሩ ፕሬዝዳንት አቶ አብርሃም መኮንን ሥራቸውን “በፈቃዳቸው” ለቀቁ ተባለ። እኚህ ሥራቸውን “በፍቃዳቸው” የለቀቁትት መሪ፣ በመጀመሪያ ለሦስት ወራት ያህል ከቤታቸው ሌላ ላያምራቸውና፣ ከዚያም ለሦስት አመት ሙሉ ከአዲስ አበባ ላይወጡ “ፈቃደኛ” ሆነው “ተቀምጠው” ነበር። ም.ፕሬዚዳንቱ አቶ ዘለቀ ወ/ማርያምም ካንዴም ሁለት ሦስቴ የድሬዳዋን ወህኒ ቤት “በፈቃዳቸው” እየተመላለሱ ጎብኝተዋል። ቀደም ሲልም፣ ኢ.ሠ.አ.ማን ለማቋቋም ከፍተኛ ተጋድሎ ያደረጉት አቶ አበራ ገሙ የራሳቸውን ሕይወት “በፈቃዳቸው” እንዳሰለፉ፣ ለኢትዮጵያ ሠራተኞች በመላ መርዶ ተልኮባቸው ነበር። ሌላው ትልቅ መርዶ፣ የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ሠራተኞች ጠቅላላ የሥራ ማቆም እርምጃ አለመሳካት ነው።
በኢ.ሠ.አ.ማ. ላይ እንደዚህ ያለው አመጽ የወረደው ያለምክንያት እንዳልሆነ ግልጽ ነው። ደንቆሮው የነጋሲ መንግሥት፣ ላበላው ኢምፔሪያሊስት ካፒታል መጮህ እስከዚህም አያስደንቀንም። “ውሻ በበላበት ይጮሃል” ይባል የለ እስከነ ተረቱ! የኢምፔሪያሊስቶቹም አያስደንቀንም። ኢምፔሪያሊስቶችም ቢሆኑ፣ የሠራተኛውን ትግል የወዛደሩን መደብ ማንነት ጠንቅቀው ያውቃሉ። ከዚህ ሁኔታ ማንም ተመልካች ወዲያውኑ ሊገነዘበው እንደሚችለው፣ የነጋሲው መንግሥትና የኢምፔሪያሊስቶች ዋና ጥረት፣ ያንሰራራውን የኢትዮጵያ ሠራተኞች እንቅስቃሴ በለጋነቱ መቅጨትና ኢ.ሠ.አ.ማን የቡችላ ድርጅት ማድረግ ነበር። ይህ ፀረወዛደር ጥረታቸው ደግሞ ለጊዜውም ቢሆን ተሳክቶላቸው ነበር።
በዚያን ወቅት፣ ምናልባትም የሠራተኛውን ማህበር በለጋነቱ ለመደቆስ እንዲያመቻቸው በማለት፣ የሥራ ማቆም ውሳኔ እንዲወሰድ የገፋፋ ፀረወዛደር ኃይሎች እንዳልጠፉ ብንጠረጥር ከእውነቱ ብዙ የምንርቅ አይመስለንም። በጊዜው የኢምፔሪያሊስት አሜሪካ ኢምባሲ ዋና ፀሃፊ የነበረው ሚስተር ማክዶናልድ የኢ.ሠ.አ.ማ. ዋና ፀሃፊ ከነበረው ከአቶ በየነ ሰለሞን ጋር የጠበቀ ወዳጅነት እንደነበረው የአደባባይ ሚስጢር ነው። በተጨማሪም፣ አ.ሠ.አ.ማ. ሊመሠረት አካባቢ በዙሪያው ይሽከረከሩ የነበሩት ፕሮፌሰር መስፍንና ዶክተር በረከተአብ የተጫወቱት ሚና እስከዚህ በግልጽ የሚታወቅ አይደለም። የሆነ ሆኖ፣ በኋላ በግልጽ እንደታየው፣ ኢ.ሠ.አ.ማን የመሠረቱት ወዛደሮች “በፈቃዳቸው” ሲሰናበቱና ሲንገላቱ፣ የሲ.አይ.ኤው ማክዶናልድ ቡችላ የሆኑት አቶ በየነ ስለምን ደግሞ “በፈቃዳቸው” የኢ.ሠ.ኣ.ማ ፕሬዝዳንት ሆነዋል። (በነገራችን ላይ! ሲ.አይ.ኤው ማክዶናልድ፣ ባለፉት ዓመታት በርግጥ ለተራብነው የኢትዮጵያ ሕዝቦች የኢምፔሪያሊስት አሜሪካ እርዳታ ይዘውልን መጥተው በቅጡ ጎብኝተውን ሄደዋል።
“በዚያን ጊዜ” ይላል፣ በአቶ በየነ ሰለሞን የፕሬዘዳንትነት ዘመን የኢ.ሠ.ኣ.ማን 10ኛ ዓመት ለማክበር የታተመው “የሠራተኛ ድምጽ”፣ “በዚያን ጊዜ (1955 ዓ.ም) የተነሳሳው የሥራ ማቆም ዝግጅት ሊገታና የተፋጠጠው ሁኔታ ሊበርድ የቻለው፣ በጊዜው የኢ.ሠ.አ.ማ. ፕሬዚደንት የነበሩት አቶ አብርሃም መኮንን ስልጣናቸውን በመልቀቃቸው ነበር” (ገጽ 12)። ይህ በውስጠ ‘ዘ’ የተላለፈልን ዜና፣ አቶ በየነ ሰለሞን ወደስልጣን በመጠጋታቸው ምክንያት ነበር ማለትም እንደሆነ አንባቢው ይረዳዋል።
“የኢትዮጵያን ሠራተኞች ማህበራዊ እንቅስቃሴ ከተቃወሙት ብዙዎቹ” ይላል ይኸው ጉደኛ መጽሄት ለጠቅ አድርጎ፣ “ከጥንቱ አስተሳሰባቸው ጋር በአዲሱ የኢንዱስተሪና የንግድ ሥራ የተሰማሩት ኢትዮጵያውያን አሰሪዎችና በኢትዮጵያ ለረጅም ዘመን የተቀመጡ የውጭ አገር ሰዎች ናቸው። ሆኖም፣ ይህንን ሁሉ የምናስታውሰው (በአቶ በየነ ሰለሞን ዘመን ማለት ነው-ሰህድ)፣ ለቂምና ለወቀሳ ሳይሆን፣ በትዝብት፣ ለትዝብት ያህል ብቻ ነው” (ከተጠቀሰው መጽሄት፣ገጽ 12)።
ይህንን “የሠራተኛ ድምጽ” ያነበበ ሰው የባሰውን የሚደነቀውና ግር የሚለው (ግር የሚለው እንበል እንጂ!)፣ ይኸው መጽሄት “ለባለውለታዎቹ” ለአቶ አበራ ገሙና ለአቶ አብርሃም መኮንን የሚደርስላቸውን ዝክር ሲመለከት ነው። “የኢ.ሠ.ኣ.ማ ባለውለታዎች” ይላል የምሁሩ ርእስ፣ በስተግራ ፎቶግራፋቸውን፣ በስተቀኝ ውለታቸውን ተንተኖ ለመድረስ ሲነሳሳ፦
“አቶ አበራ ገሙ. . . ማህበሩ እንዲፈቀድ ለአገር ግዛት ሚንስቴር ደንቡን አስገብተው እንደነበር ይታወሳል። ሆኖም፣ ኢ.ሠ.ኣ.ማን ለማቋቋም የሚቻልበት ሕግ ነሃሴ 30 ቀን 1954 ዓ.ም. በመውጣቱ፣ የሠራተኛን ማህበር የማቋቋም ሃሳባቸው ተቀይሮ፣ኢ.ሠ.አ.ማ. በተቋቋመበት ጊዜ የክብር ፕሬዝዳንት ሆነው ተመርጠው፣ እስከ እለተሞታቸው ድረስ ታላቅ ድጋፍና አገልግሎት ሰጥተዋል።
“አቶ አብርሃም መኮንን. . .ምንም እንኳ ከተመረጡ ከአምስት ወራት በኋላ ከስልጣናቸው ቢለቁም፣ ኢ.ሠ.አ.ማ. ሳይቋቋምም ሆነ ከተቋቋመ በኋላ ያሳዩት ትጋት በጣም የሚያስደንቅ እንደነበረ የቅርብ የሥራ ጓደኞቻቸው የኢ.ሠ.አ.ማ. ሹማምንት ይመሰክራሉ። አቶ አብርሃም መኮንን ሰርተው የማይደክሙ ከመሆናቸው ሌላ፣ በስብሰባ ላይ ለማስረዳትና ስሜትን ለመማረክ ከፍተኛ የንግግር ችሎታ ነበራቸው።” (ገጽ 22-23፣ ስርዞች የተጨመሩ-ሰህድ)
አንባቢው የጠቀስናቸውን አረፍተ ነገሮች ተመልሶ ያንብባቸው ከማለት በስተቀር የምንጨምርበት ነገር የለንም። ምንም አይነት የሰማያት ምስጢር የለውም። የኢትዮጵያ ሠራተኛ እንቅስቃሴ ‘አዲስ’ ምዕራፍ የሚጀመረውና የሚያከትመውም ከ “ታዛቢው” ከአቶ በየነ ሰለሞን ዘመን ጋር ነው። ይህንን ምእራፍ በሁለት ወቅቶች ከፍሎ መመልከት ያስፈልጋል። አንደኛው ከ1955-1966 ዓ.ም. ያለው ወቅት ነው። ሁለተኛው ደግሞ ከየካቲት 1966 – መስከረም 1967 ዓ.ም. ድረስ ያለው ታሪካዊ ጊዜ ነው። በኛ አከፋፈል በኢትዮጵያ ሠራተኞች የትግል ታሪክ ውስጥ፣ የመጀመሪያው ሦስተኛው፣ የኋለኛው ደግሞ አራተኛው ወቅት መሆናቸው ነው።
III
“ታዛቢው” ፕሬዚዳንት፣ በ1955 ዓ.ም. ላይ በእነአክሊሉ ኃብተወልድ- ጌታውን ተሰማ – ሙላቱ ደበበ- የም/አለቃ ሚካኤል አመዴ ቡድንና በሲአይኤው ማክዶናልድ እርዳታ ታጋዮችን ወዛደሮችን ካስወገዱበት ጊዜ አንስቶ፣ እስከ የካቲት 1966 ዓ.ም. ድረስ፣ በአሠሪዎች ላይ ምንም አይነት የረባ “ቂምና ወቀሳ” እንዳልነበራቸው ተነግሮለት ያለቀ ጉዳይ ነው። እኚሁ ሰው፣ ለኢ.ሠ.አ.ማ. 7ኛ ዓመት በወጣው “የሠራተኛ ድምጽ” መጽሄት አማካይነት፣ ለኢትዮጵያ ሠራተኞች ባስተላለፉት መልእክት ውስጥ እንዳሉት፣ “አሠሪዎች እስካሁንም ድረስ የማህበር መሪዎችን ያለምክንያት ከሥራ በማስወጣት የሚፈጽሙት ተግባር አሳዛኝ አድራጎት ብቻ ነበር።” (“የሠራተኛ ድምጽ”፣ ሚያዚያ 1 ቀን 1962 ዓ.ም. ገጽ 8)
ይህ “ጠሊቅ ዘሊቅ” የሆነው ሚስጢር የሚገልጽልን ወደጠቀስነው መጽሄት ርእስ አንቀጽ ተመልሰን የሚከተለውን ስናነብ ነው። “ባለፉት ዓመታት” ይላል ርእስ አንቀፁ፣ “ባለፉት ዓመታት የኢ.ሠ.አ.ማ. ዋና ተግባሩ ከቀን ቀን በእያንዳንዱ ሠራተኛ የሚመጣውን ቅሬታ ማስፈፀም ነበር። አሁን ግን ይህ (ተግባሩ) ተለውጧል። ኢ.ሠ.አ.ማ. በየእለቱ የሚፈፀመውን ቅሬታ አፈጻጸም ለያንዳንዱ ማህበር ትቶ፣ (ሁን [የማይነበብ – አዘጋጆቹ] አጠቃቀላይ ብሄራዊ ጉዳዮቹን በመከታተል ላይ ነው።” (ገጽ 6፣ ስርዝ የተጨመረ-ሰህድ)
ከኃይለሥላሴ ዘመን “አጠቃላይ ብሄራዊ ጉዳዮች” የሚባሉትን መዘርዘሩ እስከዚህም አስፈላጊ አይመስለንም። ለማንኛውም፣ አንባቢው ሳይሰለቸን የሚከተሉትን ጥቅሶች ይወጣቸውና የኢትዮጵያን ሠራተኞች “ብሄራዊ ጉዳዮች” ልብ ይበልልን። ጥቅሶች በሙሉ የተወሰዱት ከጠቀስነው የሚያዚያ 1 ቀን 1962 ዓ.ም. “የሠራተኞች ድምጽ” መጽሄት ውስጥ ነው።
“ኢ.ሠ.አ.ማ. ከአሠሪና ከሠራተኛ ጉዳይ ጽ/ቤት ባለሥልጣኖች ጋር መልካም የሥራ ግንኙነት አለው። ችግር በገጠመውም ጊዜ የነዚህ ባለሥልጣኖች ትብብር አይነፈገውም።” (ገጽ 20)
“ኢ.ሠ.አ.ማ. ከኢትዮጵያ የአሠሪዎች ፌደሬሲዮን ጋርም መልካም ግንኙነት አለው። ሆኖም፣ ሁለቱን ድርጅቶች በበለጠ ለማቀራረብ ብዙ መፈፀም ያለባቸው (ብሄራዊ) ጉዳዮች አሉ።” (ገጽ 21)
“ግርማዊ ንጉሠ ነገሥትም፣ ለሠራተኞች እንቅስቃሴ እድገትና መደራጀት አባታዊ ድጋፋቸውን ከመስጠት ምንጊዜም አልተቆጠቡም። መልካም ፈቃዳቸው ሆኖ፣ የኢ.ሠ.አ.ማ. ህንፃ የተቋቋመበት መሬት ለሠራተኞቻቸው ሰጥተዋል።” (ገጽ 21)
“የኢ.ሠ.አ.ማ. ተግባር ባገር ውስጥ ብቻ የተወሰነ አይደለም። በዓለም አቀፍ የሠራተኛ ማህበር ድርጅቶችም ትጉህ ተካፋይነቱን በማሳየት ባለሥልጣኖቹ ከፍ ካለ ቦታ ለመመረጥ በቅተዋል. . . ።”( ከአቶ በየነ ሰለሞን መልእክት፣ ገጽ 8/ አንባቢውን እናስታውሰውና፣ የኢ.ሠ.ኣ.ማ. ባለሥልጣኖች “ትጉህ ተካፋይ” የሆኑባቸውና “ከፍ ካለም ቦታ ለመመረጥ የበቁባቸው” ዓለም አቀፍ የሠራተኛ ማህበር ድርጅቶች፣ የኢትዮጵያ ሠራተኞች በግንቦት ወር 1967 የተገላገሏቸው የሲ.አይ.ኤ. ድርጅቶች ናቸው። እነሱም “ዓለም አቀፍ ነፃ (?) የሠራተኞች አንድነት ማህበር” (አይ.ሲ.ኤፍ.ቲ.ዩ.)፣ “አፍሪካን አሜሪካን ሌበር ሴንተር” (ኤ.ኤ.ኤል.ሲ.) እና የጀርመኑ የ“ፍሬድሪክ ኤበርት እስቲፍቱንግ”. . .ወዘተ ናቸው።
“አጠቃላይ ብሄራዊ ጉዳዮች” በኢ.ሠ.አ.ማ. መሪዎች በወጉ የተያዙለትን ኢትዮጵያዊ፣ አሁን ደግሞ የጊዜውን እውነተኛ የሠራተኞች ድምጽ እናቀርብለትና በርጋታ እንዲያነብልን እንጠይቀው። የምናሰፍረው ጥቅስ በዳቦ ጋጋሪዎች ማህበር የተፃፈ ሲሆን፣ የተገኘውም ቀደም ስንል ካየነው ጉደኛ መጽሄት ውስጥ ነው።
“የሠራተኞች አንድነት ማህበር በሚል ስያሜ ያቋቋማችሁልን ማህበር እጆቻችንንና እግሮቻችንን ጥፍር አድርጎ አስሮናል። ማህበራችን ከመቋቋሙ በፊት ያቀረብነው ጥያቄ መፍትሄ ካለገኘ ሥራውን ዘግተን እንወጣለን በማለትና በአሠሪዎቻችን ላይ በመዛት ብቻ አያሌ ጥቅሞችን እናገኝ ነበር።. . . የሠራተኞች አንድነት ማህበር ካቋቋምን በኋላ ግን፣ ‘ችግራችሁን በማህበር መሪዎቻችሁ አማካኝነት ተወያዩ’ ብላችሁ ትመክሩናላችሁ። ከአሠሪዎች ጋር በምናደርገው ውይይት አጥጋቢ መፍትሄ ካላገኘን፣ ቅሬታዎቻችንን ለኢ.ን.ነ መንግሥት የሕዝባዊ ኑሮ እድገትና የማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ለአሰሪና ሠራተኛ ጉዳይ ጽ/ቤት መመልከት ይኖርብናል። በጽ/ቤት አማካኝነት ለመታረቅ ካልበቃን፣ ለክቡር የአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ ወሳኝ ቦርድ ቅሬታችንን ማቅረብ አለብን።. . . የቦርዱን ውሳኔ በመቃወም፣ አሠሪም ሆነ ሠራተኛ ለጠቅላይ ን.ነ. ፍርድ ቤት ይግባኝ ይል ይሆናል። ቅሬታው በዚህም አልፎ ለግርማዊ ን.ነ. ችሎትም በአቤቱታ መልክ የሚቀርብበት ጊዜም አለ። ስለዚህ ያቋቋማችሁልን የሠራተኞች አንድነት ማህበር በእርግጥ አንድነታችንን( ትብብራችንን) አዳክሞታል። ከላይ የተገለፀውን ስነስርዓት እስከመጨረሻው ተከትለን ችግራችንን ለመውጣት የገንዘብ፣ የጊዜና የሰው ጉልበት ችሎታ ያጥረናል። ስለዚህ፣ ያቋቋማችሁልን የሠራተኞች አንድነት ማህበር ለአሠሪዎቻችን ጥቅም ያሰረን መሆኑ ግልጽ ነው።” (ገጽ 11፣ ስርዝ የተጨመረ-ሰህድ)
ከዚህ በላይ ያቀረብናቸውን ጥቅሶች በትዕግሥት ያነበበ ሰው ሊያልፈው የማይችለው ሃቅ ቢኖር፣ የኢ.ሠ.አ.ማ. ጽ/ቤት የነጋሲው መንግሥትና የኢምፔሪያሊስቶች መ/ቤት እንጂ፣ የኢትዮጵያ ሠራተⶉች ድርጅት እንዳልነበር ነው። እንደውነቱ ከሆነ፣ የጊዜውን የኢ.ሠ.አ.ማ. ጽ/ቤት ከበጅሮንዱ ወይንም ከንጉሠ ነገሥቱ የልዩ ካቢኔ ጽ/ቤት የምንለይበት ምንም አይነት ሚዛን የለንም። የኢትዮጵያ ሠራተⶉች እነዚህን ሁሉ ዓመታት ያሳለፉት በአንድ ወገን ከአሰሪዎቻቸው-ከበዝባዦቻቸው- ጋር ሲታገሉና፣ በሌላ ወገን ደግሞ “እጅና እግራቸውን ጥፍር አድርጎ በማሰር ለአሰሪዎች ጥቅም” ካጋፈጣቸው የኢ.ሠ.አ.ማ. ጽ/ቤት ጋር ሲዋጉ ነው።
ኢ.ሠ.አ.ማ. እንደተቋቋመ ተነስቶ የነበረውን የሥራ ማቆም እርምጃ ቀደም ስንል አውስተነዋል። የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ሠራተኞች የሥራ ማቆም እርምጃ፣ በነጋሲው መንግሥትና በኢምፔሪያሊስቶች ሴራ ይክሸፍ እንጂ፣ እርምጃው ለኢትዮጵያ ሠራተኞች በመላ የመጀመሪያው የሠራተኞች ትግል ልምምድ እንደነበርም ለመጠራጠር አይቻልም። እኛ እስከምናውቀው ድረስ፣ ከዚህ ጊዜ አንስቶ እስከ የካቲት 1966 ዓ.ም. ድረስ፣ በኢትዮጵያ ሠራተⶉች አንድም ጠቅላላ የሥራ ማቆም እርምጃ አልተወሰደም። ሆኖም፣ የኢትዮጵያ ሠራተኞች መብታቸውንና ጥቅማጥቅማቸውን ለማስከበር የሚያካሂዱት ትግል ደግሞ ለአፍታም ያህል እንኳ ተቋርጦ አያውቅም።
ለምሳሌ ያህል፣ በጥቅምት ወር በ1957 ዓ.ም. ላይ የተካሄደውን የአየር መንገድ ሠራተኞች የሥራ ማቆም እርምጃ ልንጠቅስ እንችላለን። እንደዚሁም በታህሳስ ወር 1958 ዓ.ም. ላይ የከተማ አውቶብስ ነጂዎች ያካሄዱትን ትግልና የሰላማዊ ሰልፍ እንቅስቃሴ ለማስታወስ እንችላለን። ከዚሁ በመከታተል በሚያዚያ ወር ላይ፣ የማተሚያ ቤቶች ሠራተⶉች ለ5 ቀናት ያህል ሥራ በማቆም ከፍተኛ ትግል አካሂደዋል። በ1959 ዓ.ም. በነሃሴ ወር ላይ፣ ላይ፣ የአየር መንገድ ሠራተኞች ለ4 ቀናት ያህል ሥራ በማቆም ቀደም ሲሉ ላቀረቧቸው ጥያቄዎች መታገላቸውን ቀጥለው ነበር።
ለጊዜው ከመረጃዎች እጥረት የተነሳ፣ ብዙዎቹን የሠራተⶉች እንቅስቃሴ ለመዘርዘር አንቻል እንጂ፣ የኢትዮጵያ ሠራተኞች በየጊዜውና በየቦታው ብዙ መራራ ትግሎችን እንዳካሄዱ የማይካድ እውነት ነው። ለምሳሌም ያህል፣ በ1955 ዓ.ም. ደግሞ፣776 የሠራተⶉች ክርክሮች ነበሩ።
የኢትዮጵያ ሠራተኞች ሌላው ትግል፣ የዳቦ ጋጋሪዎች ሠራተኞች “ያቋቋማችሁልን ማህበር” እያሉ ከሚጠሩት “ማህበራቸው” ነበር። አቶ አብርሃም መኮንን ከሥራቸው እንደተወገዱ፣ በኢ.ሠ.አ.ማ. ጽ/ቤት ውስጥ የተቀሰቀሰው የመጀመሪያው ትግል በአቶ በየነ ሰለሞንና በም/ዋና ፀሃፊው በአቶ አለሙ ቦጋለ በሚመሩ ሁለት ወገኖች መካከል ነበር። “የአቶ በየነ የአመራር ጉድለትና የችሎታ ማነስ የሚያውቁት አቶ አለሙ ቦጋለ በ1957 ዓ.ም. ካንዳንድ ጠንካራ የማህበሩ መሪዎች ጋር በመመካከር በአቶ በየነ ምትክ ሌላ ሰው እንዲመረጥ ጥረት አድርገው ነበር። ሆኖም አቶ በየነ ሰለሞን ይህ ውጥን መኖሩን እንደሰሙ፣ አቶ አለሙ ቦጋለንና በጊዜው የድርጅቱ ሹፌር የነበረውን አቶ ወርቅነህ ተስፋዬን ያለአንዳች ክፍያ ከሥራ አሰናበቷቸው። ሾፌሩ ከሥራ የተባረረው “አቶ አለሙን በመኪና ታዘዋውር ነበር” በሚል ምክንያት እንደሆነ ታውቋል!!” (ገጽ 9 – ይህንን ጥቅስ ያገኘነው ካንድ የደብዳቤዎች ፋይል ውስጥ ነው። ካሁን ወዲያ “ፋይል” በማለት እንጠቅሰዋለን- ሰህድ)
ይኸው “ፋይል” ለጥቆ እንደሚለው፣ አቶ አለሙና ሌሎችም የማህበር መሪዎች በተለሙት እቅድ መሰረት በ1958 አጋማሽ ላይ የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ የወንጂና ስኳር ፋብሪካዎች፣ የኢ.ኢ ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ፣ የእንጨት ሥራዎችና የሌሎች ድርጅቶች ሠራተኞች ማህበር መሪዎች እየተገኛኙ ባደረጉት ውይይት፣ የድርጅቱ ሹማምንት ለመለወጥና ከሠራተኛ ማህበር የወጡ ሰዎች በየቦታው ለማስቀመጥ ተሞክሮ ሳይሳካ ቀርቷል።
“አቶ በየነና ተከታዮቻቸው እነዓለም አብዲ፣ በዚያን ጊዜ ከዩንቨርስቲ ወጥተው በድርጅቱ ውስጥ ተቀጣሪ ሆነው ይሰሩ የነበሩትን እነፍስሃ ጽዮን ተክኤን አስከትለው ከፍተኛ ጥረት ካደረጉ በኋላ፣ የድርጅቱ ሹማምንት ሆነው ተመረጡ። አቶ በየነ ሰለሞን (ማንኛውንም ማህበር ሳይወክሉ፣ ፕሬዚዳንት)፣ አቶ ፍስሃ ጽዮን ተክኤ (ማህበር ሳይወክሉ፣ ዋና ፀሃፊ)፣ አቶ ፍስሃ ገብረማርያም (ማህበር ሳይወክሉ፣ ተቀዳሚ ምክትል ዋና ፀሃፊ) . . .” ሆነው ነው የተመረጡት። (ፋይል ገጽ 9- ስርዞች የተጨመሩ- ሰህድ)
የነጋሲው መንግሥትና የኢ.አይ.ኤ. ተጠሪ የነበሩትን የኢ.ሠ.አ.ማ. ሹማምንት ለመለወጥ የተደረገው የመጀመሪያው ትግል በነአቶ በየነ ሰለሞን አሸናፊነት ቢያከትም፣ የዚያ ትግል ውጤት ለኢትዮጵያ ሠራተኛ በመላ መራራ መርዶ ነበር። ይኸው ሁኔታ በ1961 ዓ.ም. በተደረገው ምርጫ ላይ ተመልሶ ሲደርስ፣ “የአቶ በየነ ወገን (በውነትም) በልዩ ዘዴ ሥልጣኔን ለመያዝ ችሎ” (ፋይል 10) እነደነበር ለመጠራጠር አይቻልም።
ፋይሉ እንደሚያስረዳን፣ “በ1961 ዓ.ም. ሚያዚያ ወር ላይ በተደረገው የኢ.ሠ.ኣ.ማ. ሹማምንት ምርጫ ጊዜ ሁለት ተቃራኒ ፓርቲዎች (ወገኖች ቢላቸው የተሻለ ነው – ሰህድ) ተፈጥረው ነበር። የነዚህም ተቃራኒ ወገኖች አላማና ፍላጎት ለሥልጣን ሽሚያ መሆኑን የሚያስረዳዉ የድርጅቱ ም/ፕሬዝዳንት የነበረው ዓለም አብዲ የአንደኛው (ፓርቲ) መሪ ሲሆን፣ አቶ በየነ ሰለሞን ደግሞ፣ ፕሬዝዳንትነቱን እንደያዙ የሌላው (ፓርቲ) መሪ ሆነው መቅረባቸው ነበር። . . . ያም ሆነ ይህ፣ የአቶ በየነ ወገን በልዩ ዘዴ ሥልጣኑን ለመያዝ ችሏል።”
“በዚያን ጊዜ በተደረገው ምርጫ” ይላል ይኸው መከረኛ ፋይል፣ “አከራካሪ ነጥቦች ከነበሩት ውስጥ መዋጯቸውን በትክክል ያልከፈሉ ማህበሮች ድምጽ ይኑራቸው አይኑራቸው የሚለውና በየጽ/ቤት ውስጥ ተቀጣሪዎች የሆኑት ሰዎች መምረጥና መመረጥ አይገባቸውም የሚለው ነበር። ውዝፍ ስላለባቸው ማህበሮች ድምጽ አሰጣጥ ሁኔታ በንኡስ ኮሚቴ ተጠንቶ የተወሰነ መሆኑን የኮሚቴው ውሳኔ ሲያስረዳ፣ በውሳኔው መጨረሻ የገባቸው አጭር አረፍተ ነገር፣ የኢ.ሠ.አ.ማ. ጽ/ቤት ተቀጣሪዎች የነበሩት ሰዎች ለመምረጥና ለመመረጥ አብቅቷቸዋል። ይህች አረፍተ ነገር የገባቸው፣ ከኮሚቴው አባሎች የመጨረሻ ስብሰባና ፊርማ በኋላም እንደሆነም ይነገራል።” (ፋይል ገጽ 10፣ ስርዝ የተጨመረ- ሰህድ)
በጊዜው የዛች የኮሚቴ ሊቀመንበር የነበሩት አቶ ጌታቸው አማረ የተጫወቱትን ሚና አናውቅም። ይሁን እንጂ፣ የአቶ በየነ ሰለሞንን “ልዩ ዘዴ” ተረድተነዋል። ከዚህም በተጨማሪ፣ በተለይም “ይህች አረፍተ ነገር” የኋላ ኋላ ኢ.ሠ.አ.ማን ለተደባለቀው የንኡስ ከበርቴ ደንፊ ቡድን የቱን ያህል እንደጠቀመችው መረዳቱ እጅግም አያዳግተንም። እንደርስበታለን።
የሆነ ሆኖ፣ በ1961 ዓ.ም. ምረጫ አቶ በየነ ሰለሞን እነደገና አሸናፊወ ፕሬዚዳንት ሆኑ። አቶ ዓለም አብዲ የም/ፕሬዚዳንቱንም ቦታ አጡ። ብቻ “አህያ ላህያ ቢራገጥ ጥርስ አይሳበር” ነውና፣ በ1964 ዓ.ም. ምርጫ አቶ ዓለም አብዲ ተመልሰውም ም.ፕሬዚዳንት ሆነው ነበር። ካሁኑ የምናስታውሰው ቁም ነገር ቢኖር ግን፣ የ1961 ዓ.ምን ምርጫ በመቃወም “አያሌ ማህበሮችና በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ሠራተኞች” ከፍተኛ ትግል አካሂደው እንደነበር ነው። ለዚሁም፣ የኢትዮጵያ ሠራተⶉች ማህበራት፣ “ምርጫው” ካለቀበት ጊዜ አንስቶ የፃፏቸውን መአት ደብዳቤዎች ብቻ መመልከቱ በቂ ነው። ለዚች መግቢያ በአሥር (10/ የሠራተኞች ማህበራት ተፈርሞ፣ ለሕዝባዊ ኑሮ እድገትና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የተላከውን ደብዳቤ ብቻ ብንጠቅስ በቂ ነው። ደብዳቤው የተፃፈው ሐምሌ 3 ቀን 1961 ነው።
“ኢ.ሠ.አ.ማ. ሚያዚያ 27 ቀን 1961 ዓ.ም ያደረገው የመሪዎች ምርጫ በትክክል አይደለም በማለት ከሚያዚያ 29 ቀን 1961 ጀምሮ ላቀረብነው የተቃውሞ ድምፅ እስካሁን ድረስ መልስና ውሳኔ ካለማግኘታቸውም በላይ፣ ሁኔታው ከእለት ወደእለት እየተፋፋመ ከመሄዱ የተነሳ፣ አያሌ ማህበሮችንና በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ሠራተኞችን አሳዝኗቸዋል።
“ሀ/ ምርጫው በሚስጢር መፈፀም ሲገባው (ኢ.ሠ.አ.ማ. ደንብ፣ አ. 6 ከ. 9)፣ መራጮች ከአዳራሹ ውስጥ እየወጡ፣ ምርጫው በሌሎች ድምፅ በማይሰጡ ሰዎች ተከናውኗል።
“ለ/ . . . ‘ኢ.ሠ.አ.ማ ጠቅላይ ምክር ቤት አባል ለመሆንና ለእጩነት ብቁ የሚሆኑት፣ በምርጫው ጊዜ በኢትዮጵያ ሠራተኞች ማህበሮች ውስጥ ከሁለት ዓመት ላላነሰ ጊዜ ትክክለኛ ማህበርተኞች ሆነው ሲገኙ ነው’ የሚለው ደንባችን ( አ̇.8 ከ .18) እያለ፣ የተመረጡት ግን ተቀጣሪዎች እንጂ በመህበርተኝነት የተመዘገቡ አይደሉም። በወቅቱም ተቃውሟችንን በማሰማት ላይ እንደነበርን ለመናገር እድል ባለማግኘታችን በሽፍንፍን አልፏል። “(ፋይል፣ገጽ 21)
“በሽፍንፍን ያለፈውን” ምርጫ የኢትዮጵያ ሠራተኞች ይኸው ግልጥልጥ አድርገውልናል።
የአቶ በየነን ወገንም “ልዩ ዘዴ” ተጨማሪ ማስረጃ የሚጠይቅ አይደለም። “የ1961 ምርጫ በተነገረው ሁኔታ ተድበስብሶ” ይላል ይኸው መልሰን መላልሰን የምንጠቅሰው ፋይል፣ “በኢ.ሠ.አ.ማ. ሹማምንት ታቅዶ የነበረው ማደናገሪያ ለወዛደሩ ሠራተኛ ተቆርቋሪ ለመምሰል፣ በ1962 ዓ.ም. በታህሳስ ወር ላይ ሠራተኞች በያሉበት ሰላማዊ ሰልፍ እንዲያደርጉ ማነሳሳት ነበር። . . . ሠራተኛው የተሻሻለ ህግ የሚያገኝ መስሎት፣ እንደተነገረው በያለበት ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግና ቅሬታውን ለመግለጽ ሲዘጋጅ፣ ሁኔታውን ያነሳሱት እነዚያው የኢ.ሠ.አ.ማ. መሪዎች፣ ‘ቅሬታችን ተፈጽሟልና ሰልፉ ቀርቷል’ ሲሉ፣ በአስቸኳይ ዘዋሪ ደብዳቤ አስታወቁ። በመንግሥት ጋዜጦችም አስነገሩ።” (ፋይል፣ ገጽ 25- ስርዝ የተጨመረ- ሰህድ)። የአንባቢው አንጀት እርር የሚለው ሰላማዊውን ሰልፍ ለማዘጋጀት፣ “ለአባል ድርጅቶች በሙሉ” የተላከውን የኢ.ሠ.አ.ማ. ዘዋሪ ደብዳቤ ሲያነብ ነው።
በደብዳቤው ውስጥ በ17 ነጥቦች የተዘረዘረው የጊዜው የሠራተኞች መሰረታዊ ጥያቄዎች ሰፍረዋል። “በዚህ መሰረት” ይላል ይህ ጉደኛ ደብዳቤ፣ “በዚህ መሰረት” ኢኮኖሚው እንዳይበደል ሲባል፣ ሰላማዊው ሰልፍ በበአል ቀን እንዲሆን ተወስኗል።” (ፋይል፣ ገጽ 28) የበአል ቀን የተባለው ታህሳስ 29 ቀን 1962 ዓ.ም. የገና ልደት በአል መሆኑ ነው።
አንጀቱ ያረረው አንባቢ፣ አሁን ደግሞ ቆሽቱ ሲደብን እያዳመጠ የሚከተለውን የኢ.ሠ.አ.ማ. ደብዳቤ ያንብብ፦
“ለታህሳስ 29 ቀን 1962 ዓ.ም. ሰላማዊ ሰልፍ እንዲደረግ ታህሳስ 15. 62 በዝዋሪ ደብዳቤ ቁጥር 109/62 ያስተላለፍነውን ውሳኔ እናስታውሳለን። . . . የሰላማዊው ሰልፍ ጉዳይ ላልተወሰነ ጊዜ መተላለፉን እናስታውቃለን። የሠራተኛውን መብት ለማሳደግና ለማስከበር ላሳያችሁት መተባበርና ቆራጥነት እናመሰግናለን። በዚህም አቅጣጫ ለሁሉም ወዛደር ወንድሞቻችን፣ እህቶቻችንና ቤተሰቦቻቸው መልካም የልደት በዓል እንዲሆንላቸው የላቀ ምኞታችንን እናቀርባለን” (ፋይል፣ገጽ 30-31። ወይንም የኢ.ሠ.አ.ማ. ደብዳቤ ቁ.113) 62 ታህሳስ 27 ቀን 1962 ዓ.ም. – ስርዝ የተጨመረ-ሰህድ)
አንባቢው እስካሁን ባገኛቸው ተጨባጭ መረጃዎች ላይ በመመርኮዝ፣ የኢ.ሠ.አ.ማን ጽ/ቤት አንቅሮ እንደተፋው አንጠራጠርም። የኢትዮጵያ ወዛደሮች ግን፣ ከላያቸው ላይ የተዘፈዘፉትን የንጉሥ ኃይለሥላሴና የኢምፔሪያሊስት ቡችሎች አሽቀንጥረው ለመጣልና እውነተኛ የሠራተኛ እንቅስቃሴ ለመጀመር ገና ብዙ መታገል ነበረባቸው። ዛሬም እየታገሉ ናቸው። ለወደፊቱም ገና ብዙ ትግል ይጠብቃቸዋል።
የኢትዮጵያ ወዛደሮች የንጉሥ ኃይለሥላሴን – የኢምፔሪያሊስቶችንና – የበየነ ሰለሞንን “ርኩስ አንድነት” ለመጣል የሚያደርጉት ሦስተኛ ዙር የሚጀምረው በ1963 ዓ.ም. ላይ ነው። በኢ.ሠ.አ.ማ. ላይ ፍፁም እምነት ያጡት የሠራተኛ ማህበራት፣ ከዚህ ዓመተ ምህረት ጀምሮ የአካባቢ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ለማቋቋም ይነሳሉ። ከዚህ ጊዜ በኋላ የነበረውም ዋና ትግል በኢ.ሠ.አ.ማ. ጽ/ቤት በአንድ በኩልና በአዲስ አበባና በአካባቢው ሠራተኞች ማህበራት መካከል ነበር። በተጨማሪም፣ ወደፊት እንደምንደርስበት በኢ.ሠ.አ.ማ. ጽ/ቤትና በኤርትራ ሠራተኞች ማህበር መካከል ከፍተኛ ትግል ነበር።
ኢ.ሠ.አ.ማ. ቀደም ሲልም ቢሆን፣ በድሬዳዋና በአስመራ ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች ነበሩት። የአዲስ አበባና የአካባቢው ሠራተኞች የላቸውም ነበር። የአዲስ አበባና የአካባቢ የሠራተኞች ማህበራት በ1963 ዓ.ም. ላይ የቅርንጫፍ ጽ/ቤት ለማቋቋም ትግላቸውን አፋፍመው ሲነሱ እንደ ድሬዳዋና አስመራ ሠራተኞች የቅርንጫፍ ጽ/ቤት እንዲኖራቸው ነበር። የኢ.ሠ.አ.ማ. ምክር ቤት ታህሳስ 23 ቀን 1963 ዓ.ም. ባደረገው ስብሰባ ላይ ይህንኑ ጥያቄቸውን ተቀብሎ በአዎንታ ያፀድቀዋል። ሆኖም፣ አምባገነኑ የኢ.ሠ.አ.ማ. ጽ/ቤት ደግሞ ውሳኔውን ለማጣመምና ቢቻለውም በገዛ ሥልጣኑ ለመሻር ያላገላበጠው ድንጋይ አልነበረም። በዚያን ጊዜ “የኢ.ሠ.አ.ማ. ጠቅላይ ምክር ቤት የፈቀደልንን የአካባቢ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት፣ የኢ.ሠ.አ.ማ. ጽ/ቤት ሥራ አስኪያጅ ሊነፍገው አይገባውም. . .” (ፋይል፣ ገጽ 32) በማለት፣ የተፃፉት ደብዳቤዎች እጅግ ብዙ ከመሆናቸው የተነሳ ልንጠቀምባቸው እንኳ አልቻልንም። የሆነው ሆኖ፣ የኢ.ሠ.አ.ማ. አምባገነን አመራር፣ በተለመደው “ልዩ ዘዴው” በሐምሌ ወር 1964 ዓ.ም. ላይ፣ የቅርንጫፍና ጽ/ቤቱን ሥራ ለማገድ ችሎ እንደነበር ይታወቃል።
የኢ.ሠ.አ.ማ.ጽ/ቤት፣ በዚሁ ወቅት የሞከረው ሌላ አድሃሪ ሴራ የአስመራ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት በሆነ ባልሆነ ምክንያት እያወናበደ ለመበታተን ነበር። ስለዚሁ ጉዳይ፣ በአንድ ወገን በአስመራው ቅርንጫፍ ጽ/ቤትና በኢ.ሠ.አ.ማ. ጽ/ቤት መካከል፣ በሌላ ወገን ደግሞ በአስመራው ቅ/ጽ/ቤትና በሕዝባዊ ኑሮ እድገትና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር መካከል ብዙ የደብዳቤ ለውውጦች ተካሄደዋል። አሁንም ጠቅሰን ስለማንጨርሳቸው፣ አቶ በየነ ሰለሞን የፃፉዋትን አንዲት ደብዳቤ ብቻ ጠቅሰን እንለፍ።
“ብዙ ጊዜ” ይላል አቶ በየነ ሰለሞን፣ ነሃሴ 11 ቀን 1964፣ በኢ.ሠ.አ.ማ. አመራር ላይ ቅሬታቸውን ላሰሙት የኤርትራ ወዛደሮች በፃፈላቸው ደብዳቤ ውስጥ፣ “ብዙ ጊዜ፣ መብታችን ተነክቷል ብላቹ የምትጽፉት ደብዳቤ ሁሉ ያለማወቅ ነው፣ ከአጉል አማካሪዎች ከመስማት ብትጠነቀቁ የተሻለ ይመስለናል” (ፋይል፣ ገጽ 59)።
በአቶ በየነ ሰለሞን አነጋገር፣ ባለማወቅና አጉል አማካሪዎችን እየሰሙ፣ መብታችን ተነክቷል በማለት ብዙ ጊዜ ደብዳቤ የፃፉትን አንዳንድ ማህበሮች ስም ብቻ እንኳ ብንዘረዝር፣ የኢትዮጵያ ወዛደሮች በኢ.ሠ.አ.ማ. አመራር ላይ የቱን ያህል ተነስተውበት እንደነበር እንረዳለን። የአቃቂ በሰቃ ኢ.ኢ. ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ ሠራተኞች፣ የሴፌሪያን ኩባንያ፣ የኤች.ቪ.ኤ.፣ ነሃሴ 30 /1964 ዓ.ም. 14 ማህበሮች በአንድነት ያቀረቡት የቅሬታ ደብዳቤ የባህርዳር ጥጥ ፋብሪካ፣ የቢስ ሠራተኞች. . ወዘተ መጥቀስ ይቻላል።
እንደሚታወቀው፣ የኢትዮጵያ ወዛደሮች በአንድ ወገን ከበዝባዦቻቸው ጋር፣ በሌላው ወገን ደግሞ፣ እጅና እግራቸውን ጠፍሮ በማሰር ለበዝባዦቻቸው “ካጋፈጣቸው ከኢ.ሠ.አ.ማ. አመራር ጋር ያደረጉት ረጅም ትግል መልኩን የሚቀይረው በየካቲቱ 1966 ዓ.ም. ሕዝባዊ አቢዮታዊ እንቅስቃሴ ወቅት ነው። ይህኛው የታሪካችን ክፍል እራሱን የቻለ በመሆኑ፣ በሠራተኞችም እንቅስቃሴ ውሰጥ እንደ አንድ ወቅት መወሰድ አለበት። በኛ አከፋፈል መሰረት አራተኛው ወቅት መሆኑ ነው። ከየካቲት 1966- መስከረም 1967 ዓ.ም. ድረስ ያለው ጊዜ መሆኑ ነው።
IV
የኢትዮጵያ ወዛደሮች ከ1955 ዓ.ም. በኋላ፣ አንደ አንድ ሰው ተነስተው በታላቅ አብዮታዊ ስሜት ከትግል ማእበል ውስጥ የገቡት በየካቲት ወር 1966 ዓ.ም. ላይ ነው። እንደተመለከትነው፣ ከዚህን ጊዜ በፊት፣ እያንዳንዱ የሠራተኛ ማህበር በየሚገኝበት ፋብሪካና የሥራ ድርጅት ውስጥ ፣ለአባሎቹ ጥቅምና መብት የየበኩሉን ትግል ያካሄድ ነበር እንጂ፣ ጠቅላላ የሥራ ማቆም እርምጃ ተውስዶ አያውቅም። የ1962 ዓ.ምን. የሥራ ማቆም እርምጃ ውጤት ቀደም ስንል አውስተናል።
የኢትዮጵያ ወዛደሮች በነዚህ ዓመታት ውስጥ በሙሉ ተንቀሳቅሰው ጠቅላላ የሠራተኛ እርምጃዎችን ለመውሰድ ያልቻሉት ከሁለት ዋና ምክንያቶች የተነሳ ነው። አንደኛው ምክንያት፣ በኢትዮጵያ ወዛደሮች ጫንቃ ላይ እንደከባድ ሸክም ተዘፍዝፎ የነበረው የፊውዳሊስቶች፣ የቢሮ ከበርቴዎች፣ የአሰሪዎች፣ የኢምፔሪያሊስቶችና የኢ.ሠ.አ.ማ. ቡችሎች ጽ/ቤት “ርኩስ አንድነት” ነው። ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ፣ ጠንካራ የሆነ የወዛደሩ የፖለቲካ ድርጅት (ፓርቲ) አለመኖር ነው።
በዚህ አጋጣሚ፣ በተለይም ሁለተኛውን ምክንያት በሚመለከተው በኩል፣ የኢትዮጵያን ተራማጆች ሰፈር አፍኣዊነት፣ ጨቅላነትና ዳተኝነት ሳናወሳ ማለፍ፣ እንደጲላጦስ “የጣት ውሃ አቅርቡልኝ” የማለት ያህል ይሆንብናል። ጨርሶ ልናልፈው የማንችለው ሃቅ ነው።
የኢትዮጵያ ተማሪዎችና ተራማጅ ምሁራን፣ የወዛደሩ መደብ የታሪክ ሚና ከተረዱት ዓመታት አልፈዋል። ይሁን እንጂ፣ በእምነታቸውና በገቢራቸው መካከል የሰማይንና የምድርን ያህል ርቀት እንደነበረና እንዳለም ደግሞ፣ የዚያኑ ያህል እውነት ነው። እነዚህ ወገኖች ምንም እንኳን ብዙ ቢያወሩና ቢጽፉም፣ እስካሁን ድረስ በግልጽ እንደታየባቸው፣ በተግባር የወሰዷቸው እርምጃዎች እጅግ የሚያሳፍሩና የሚያሳዝኑ ናቸው።
አንዳንዶቹ የወዛደሩን መደብ እንኳን ተዋህደውት ሊመሩት ቀርቶ፣ ካጠገቡም ዝር አይሉም። እነዚህ አፍአዊያን፣ ዛሬም ቢሆን፣ የወዛደሩን መደብ በአንጎላቸው ውስጥ እያንጓለሉ ስቃዩን ያሳዩታል እንጂ፣ ከርሱ ጋር ሆነው አንዲት እርምጃ እንኳን አይራመዱም። ሌሎቹ ደግሞ፣ የወዛደሩን መደብ የተዋሃዱት ሳይሆኑ፣ ዘው ብለው የተደባለቁት “ተራማጅ መሳይ በገበያ” ናቸው። የነዚህ ሚና ራሱን የቻለ ስለሆነ ወደፊት እንመለስበታለን። ለጊዜው ግን ይሄኛው ክፍል የንኡስ ከበርቴ ደንፊዎች ጥርቅም እንደሆነ ብቻ አመልክተን እንለፍ። በመጨረሻ መወሳት ያለበት የተራማጆች ክፍል ዳተኛውና ድንጉጡ ክፍል ነው። ይህኛው ክፍል፣ ምናልባት(.) የቲኦሪ ጥራት አለው፤ ለትግሉም የቆረጠ ነው። ነገር ግን ዳተኛ ከመሆንም አልፎ፣ በሆነ ባልሆነው እየበረገገ ምሶ ከተቀበረበት ጉድጓድ ውስጥ እንኳ ሊወጣ አልቻለም። ይህ ክፍል፣ በዛሬው ወቅት የሚታየው በአንድ ወገን ፀረዲሞክራቲኩን ደርግ ሲያወግዝና፣ በሌላ በኩል ደግሞ በንኡስ ከበርቴው ደንፊ ቡድን ቅብዝብዝነት ሲነጫነጭ ነው።
ከዚህ በላይ ከተነገረው የምንረዳው እውነት፣ የኢትዮጵያ ሠራተኞች ዛሬም ቢሆን፣ ሊያነቃቸው፣ ሊያደራጃቸው፣ ሊመራቸውና ሊያታግላቸው የሚችል ጠንካራና የበሰለ በወዛደሩ ርዮተዓለም የሚመራ የፖለቲካ ድርጅት እንደሌለው ነው። ይህ፣ ብንወድም ብንጠላም መራራ እውነት ነው። እርግጥ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ፣ ነፃነት፣ ሬቮሉሽን፣ ወዝ የተሰኙ ተራማጅ ጋዜጣዎች መውጣት ጀምረዋል። የሰፊው ሕዝብ ድምጽ ባለፉት ቁጥሮቹ /36 ና 37/ እንዳመለከተው፣ የርሱና የነዚህ ጋዜጦች አንድነት ወደትክክለኛው ግብ ሊመራን የሚችል ነው። ወዝ የተባለው ጋዜጣ ይህንኑ ሃሳብ አቅርቧል። እኛም፣ እነዚህ ወገኖች በአስቸኳይ ወደ ውይይት ማምራት አለባቸው እንላለን።
ወደርእሳችን እንመለስና፣ የኢትዮጵያ ወዛደሮች ከአሥራ አንድ ዓመታት በኋላ፣ ለመጀመሪያ ጊዜ የወሰዱት የየካቲቱ ጠቅላላ የሥራ ማቆም እርምጃ፣ እጅግ ታላቅና የታሪክን አቅጣጫ የጠቆመን እርምጃ እንደነበር ሁላችንም እናስታውሳለን። ከየካቲት 28- መጋቢት 2 ቀን የቆየው የኢትዮጵያ ወዛደሮች እንቅስቃሴ 120,000 ሠራተኞች የተሳተፉበት እርምጃ ነበር። ይህ የመጀመሪያው ጠቅላላ የሥራ ማቆም እርምጃ፣ በጊዜው በአንድ በራሪ ጽሁፍ ውስጥ እንደተገለፀው፣ የወዛደሩን መደብ ማንነት ለገዢው ክፍል ብቻ ሳይሆን፣ ለጠቅላላው የኢትዮጵያ ሕዝብም በገሃድ አሳይቷል። የየካቲት ጠቅላላ የሥራ ማቆም እርምጃ የመሰከረው ሌላ እውነት ደግሞ፣ የኢትዮጵያ ወዛደሮች በጫንቃቸው ላይ በተሸከሙት የፊውዳሊስቶች፣ የቢሮ ከበርቴዎች፣ የአሠሪዎች፣ የኢምፔሪያሊስቶችና የኢ.ሠ.አ.ማ. ጽ/ቤት “ርኩስ አንድነት” የቱን ያህል ይጨቆኑና ይበዘበዙ እንደነበር ነው። ለዚሁም፣ በጊዜው የተገለፁትን የሠራተኞች ጥያቄዎችና በሠራተኞች ይበተኑ የነበሩትን በራሪ ወረቀቶች ልብ ብሎ ማጥናቱ ብቻ በቂ ነው።
ነገር ግን አሁንም ቢሆን፣ የኢትዮጵያ ወዛደሮች በየካቲቱ እንቅስቃሴ ወቅት የወሰዳቸውን ከፍተኛ እርምጃዎች በሁለት ከፍለን ለማየት እንገደዳለን። አንደኛው ክፍል፣ በኢ.ሠ.አ.ማ. አማካይነት የተወሰዱትን እርምጃዎች የሚያጠቃልል ሲሆን፣ ሁለተኛው ክፍል ደግሞ፣ እያንዳንዳቸው የሠራተኛ ማህበራት ያካሄዷቸውን ትግሎች የሚያጠቃልል ነው።
የኢ.ሠ.አ.ማ. ጽ/ቤት የየካቲቱን ጠቅላላ የሥራ ማቆም እርምጃ የተቀበለው የግዴታ ሆኖበት እንጂ፣ ወዶትና አምኖበት እንዳልሆነ መገንዘቡ እስከዚህም አዳጋች አይደለም። “ምክር ቤቱ /የኢ.ሠ.አ.ማ./” ይላል አቶ በየነ ሰለሞን፣ በጊዜው “አፍሪካ” ለተባለው መጽሄት በሰጠው ቃለ መጠይቅ ውስጥ፣ “ይህንን ውሳኔ ያሳለፈው እንደሚወራው አጋጣሚ ጊዜ ጠብቆ ሳይሆን፣ቀደምሲል በነሃሴ ወር 1965 ዓ.ም. እና በጥር ወር 1966 ዓ.ም. ተሰብስቦ በነበረበት ወቅት ባዘጋጀው እቅድ መሰረት ነው።”
አንባቢው ይህን አረፍተ ነገር መለስ ብሎ ቢያጠናው፣ “አጋጣሚ ጊዜ ጠብቆ” መነሳቱ ምን ነውር ይኖርበት ይሆን? በማለት ራሱን መጠየቁ አይቀርም። ሁለተኛም፣ በነሃሴ ወር 1965 የተላለፈ ውሳኔ እያለ፣ የጥር ወር 1966 ዓ.ም. ስብሰባ ለምን አስፈለገ ብሎ ለመጠየቅ ይገደዳል። በመጨረሻም፣ ከየካቲት ወር በፊትና በየካቲት ወር ውስጥ ብዙ የሠራተኛ ማህበሮች (የአየር መንገድ፣ የባንክ፣ ወዘተ. . .)፣ አስተማሪዎች፣ ታክሲ ነጂዎችና ተማሪዎች ያንን ሁሉ እንቅስቃሴ ባካሄዱበት ወቅትና ከፖሊስ ጋር ኃይለኛ ግጭት በገጠሙበት ወቅት፣ የኢ.ሠ.አ.ማን ጽ/ቤት የዋጠው ነገር ምንድን ነበር? . . . . ለጥያቄዎቹ መልስ ለመስጠት መነሳሳት ጠቃሚ ገጾችን ማባከን ይሆንብናል። ስለሆነም፣ በመጋቢት ወር መጨረሻ ላይ የወጣውን “የሠራተኛው ድምጽ” ርእስ አንቀጽ ብቻ አናግረን እናልፋለን።
“ከዚህ በፊት እንደተደረገው ሁሉ፣ ወደፊትም በሃገሪቱ ውስጥ ሊደረግ የሚገባውን የፖለቲካ፣ የሶሻል እና የኢኮኖሚ አቋም፣ በሰላማዊ መንገድ ለማስገኘት እንደማንኛውም ህብረተሰብ ኃላፊነት እነዳለብን እናምናለን። . . . የሠራተኛው ንቅናቄ . . . ለሃያኛው ክፍለ ዘመን ኢትዮጵያ የሚያስፈልጓትን ለውጦች ለማምጣት መታገል አለበት። ሆኖም፣ ያለንን ጥሩ ልምድና ባህል በሙሉ ፈንቅሎ መጣል አለበት ማለታችን አይደለም። ካዲሲቷ ኢትዮጵያ አቋም ጋር. . . ያገራችንን ታሪክ የሚጠበቅ ልምድና ባህል ሊጠበቅ ይገባዋል።” (ስርዝ የተጨመረ- ሰህድ)
የኢ.ሠ.አ.ማ. አመራር “ከዚህ በፊት እንደተደረገው ሁሉ የአገራችንን ታሪክ /የነጋሲዎችን ታሪክ) ለመጠበቅ ኃላፊነት እነዳለበት ይመን” እንጂ፣ በየካቲት ገንፍሎ እንደሰደድ እሳት ከተቀጣጠለው ሕዝባዊ አብዮታዊ እንቅስቃሴ ውስጥ የገቡት የኢትዮጵያ ሠራተኞች፣ “ከዚህ በፊት እንደተደረገው ሁሉ” የነጋሲዎች ባሪያ ሆነው ለመቆየት አልቻሉምም፣ አልፈለጉምም ነበር። ለዚሁም፣ ከየካቲቱ ጠቅላላ የሥራ ማቆም እርምጃ በኋላ፣ የተካሄዱትን “የአያሌ ማህበራትና በሺህ የሚቆጠሩ ሠራተኞች” ትግሎች ማውሳት ብቻ በቂ ማስረጃ ነው። ለመዘርዘር ብንነሳሳ፣ አንጀምረው እንደው እንጂ፣ ከዳርስ የምናዘልቀው ጉዳይ አይደለም። መጋቢት 5 ቀን 350 የትንባሆ ሞኖፖል ሠራተኞች፣ በዚሁ እለት 350 ቡና የሚለቅሙ ሴቶች፣ መጋቢት 8 ቀን 1500 የሰለሞን ማህተመሥላሴ አስመጪና ላኪ ተቀጣሪ ሴቶች ሠራተኞች፣ በዚሁ ቀን በአዲስ አበባ አከባቢ ከሚገኙ ፋብሪካዎች የተወጣጡ 3000 ሴቶች፣ መጋቢት 9 ቀን 86 ግንበⶉችና 100 የፋርማሲ ሠራተኞች፣ መጋቢት 11 ቀን 800 የአስመራ ማዘጋጃ ቤት ሠራተኞችን ወዘተ. . . መጥቀስ ይቻላል።
የየካቲቱ ሕዝባዊ አብዮታዊ እንቅስቃሴ የነጋሲውን ዙፉን እንዳራደው ሁሉ፣ የኢሠአማውን የነበየነ ሰለሞንን የሥልጣን ወንበርም አዋዥቆት እንደነበር እሙን ነው። የመደብ ትግል ነውና፣ ንጉሥ ኃይለሥላሴ ዙፋኑን ለማሰንበት ሲል እየተጠናበረ ብቅ ማለቱ እስከዚህም አያስደንቀንም። እንዳልካቸው፣ “ያገሪቱን ትላልቅ ሰዎች” ተቀብሎ ማነጋገር፣ የህገመንግሥት ጉባኤ፣ የፀጥታ ኮሚቴ፣ ሚካኤል እምሩ. . . ሁሉ ትዝ ይሉናል። በየነ ሰለሞንም “ከዚህ በፊት እነደተደረገው ሁሉ” መዋዠቅ የጀመረውን ወንበሩን መሬት ለማስያዝ “ልዩ ልዩ ዘዴዎቹን” ሲፈትል ይታየናል።
ከየካቲት 1966 – መስከረም 1967 ድረስ በኢ.ሠ.አ.ማ. ውስጥ የተካሄደው ትግል በሦስት ወገኖች መካከል ነበር። የአንደኛው ወገን መሪ በየነ ሰለሞን ሲሆን፣ የሌላው ወገን መሪ ደግሞ፣ ዓለም አብዲ ነበር። ሦስተኛው ወገን የተወከለው በየካቲት ወቅት ኢ.ሠ.አ.ማን ዘው ብሎ የተቀላቅለውና ከኢትዮጵያ ሠራተኞች እንቅስቃሴ አናት ላይ ቂቢብ ባለው የንኡስ ከበርቴ ደንፊ ቡድን ነበር። ይህ ደንፊ ቡድን ወደ ኢ.ሠ.አ.ማ. አመራር እጁን ሊዘረጋና በዚያም አካባቢ ተጽእኖውን ሊያሳርፍ የቻለው የአዲስ አበባና አካባቢው ቅርንጫፍ ማህበር እንዲቋቋም ከረጅም ጊዜ ጀምሮ ከሚታገሉትና የነበየነ ሰለሞን ዋና ተቀናቃኞች ከነበሩት፣ ጠንከር ካሉት የማህበራት መሪዎችና የቢሮ ሠራተኞች መካከል አንዳንዶቹን በእጁ በማስገባቱ ነው። ወደ ዝርዝር ሁኔታው በኋላ እንመለሳለን። ይህ ቁንጥንጥ ቡድን በዚያን ወቅት በኢ.ሠ.አ.ማ. በተጨማሪ በአንዳንድ ሕዝባዊ ድርጅቶች አናት ላይም (አስተማሪዎች፣ ተማሪዎች) ዘሎ ቁጢጥ ለማለት ብዙ ጥረት አድርጓል። ወደፊት እንመለስበታለን። (የንኡስ ከብርቴ ደንፊ ቡድን ቀደም ሲል “ዲሞክራሲያ” በተባለው ልሳኑ የታወቀ ሲሆን፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ፣ “የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ” አቋቋምኩ ብሎ፣ “ላብአደር” እና “አብዮታዊው ወጣት” የተባሉትን ጋዜጦች ማውጣት ጀምሯል።)
እነዚህ ሦስት ወገኖች በመጀመሪያ ላይ በአንድነት ሆነው ለ“ጊዜያዊ ሕዝባዊ መንግሥት” መፈክራቸው ተሰልፈው ነበር። በቅርቡ የወጣች አንዲት ሽሙጥ የምትባል ጋዜጣ እንዳለችው ያ“ክረምትና በጋን አንድ ወገን የሚያደርግ፣ ሳይዘንብ ካመት አመት የእህል በረከት የሚያወርድ፣ ቅቤና ማሩ ጣእሙ የሚጨምርበት፣ ወርቅ፣ . . . . ወርቅ ወርቅ የምታፈስበት፣ አመቱን ሙሉ ሳይሰራ፣ ሳይታጨድ፣ ሳይወቃ፣ የሚበላበት፣ መቼም ድረስ ያልፋል፣ ይጠፋል፣ ያልቃል፣ ይደቃል የማይባልበት” (ሽሙጥ፣ ጥር 5/ 1968፣ ቁጥር 1፣ ገጽ 2)
ጊዜያዊ ሕዝባዊ መንግሥት በወቅቱ ብዙ ሠራተኞችንና እውነተኛ ተራማጆችን ያወናበደና ያባከነ የትግል ጥሪ ነበር። እንደ ሽሙጥ አነጋገር፣ ዛሬ ስለ“ጊዜያዊ መንግሥት” ሲሰሙ ምራቃቸው ጠብ ጠብ እያለ መሰብሰቡ የሚያስቸግራቸው “የልዑል ጌታዬ” ተወካዮች፣ ኢምፔሪያሊስቶችና የንኡስ ከበርቴው ደንፊ ቡድን ብቻ ይሁን እንጂ፣ በጊዜው ጉዳዩ የገባቸው እነበየነ ሰለሞንም በመፈክሩ ሥር ተሰልፈው እንደነበር ለመካድ አይቻልም። ነገር ግን አንዳንድ መረጃዎችን ብንጠቅስ የመስከረም 1967 ዓ.ም. ጠቅላላ ጉባኤ በሴራና በተንኮል የተበከለ እንደነበረም ወዲያው እንረዳለን።
የመስከረሙ ጉባኤ ከመደረጉ በፊት ብዙ በኢ.ሠ.አ.ማ. ላይ ቅሬታ ያላቸው ማህበራት፣ በመጀመሪያ የቅሬታ አቅራቢ ኮሚቴ እንዲቋቋም ጠይቀው ነበር። በዚህም መሰረት አንድ የቅሬታ አቅራቢ ኮሚቴ ተመርጦ የማህበራትን ቅሬታዎች በአራት ነጥቦች ዘርዝሮ አቀረበ። ቅሬታዎቹም፦
1ኛ/ በሠራተኞች ላይ የተዘፈዘፉት አድሃሪ መሪዎች በአስቸኳይ እንዲነሱ፣
2ኛ/ የኢ.ሠ.አ.ማ. ህገማህበርና ደንብ እንዲሻሻል፣
3ኛ/ የሠራተኞች ጉዳይ ህግ ተረቅቆ እንዲቀርብ “የህግ አጥኚ ቡድን” ይመረጥ፣
4ኛ/ ጠቅላላ የኢ.ሠ.አ.ማ. ጉባኤ ከአራት ወራት በኋላ እንዲጠራ፣ የሚሉ ነበሩ።
ሆኖም፣ አሁንም “በከፍተኛ ብሄራዊ ጉዳይ ላይ ያተኮረው” የኢ.ሠ.አ.ማ. አመራር በሸረበው ተንኮልና ባካሄደው “የጦፈ” የቅስቀሳ፣ የቅሬታ አቅራቢው ኮሚቴ ነጥቦች መና ቀሩ። ነገሩ ሁሉ ተገልብጦ፣ “ቅሬታቸው ሊሰማ የሚችለው በመጀመሪያ ለኢ.ሠ.አ.ማ. መክፈል የሚገባቸውን የብዙ ጊዜ ውዝፍ ሲከፍሉ ብቻ ነው” የሚልም ክርክር ተነሳ። የመጨረሻ መጨረሻም፣ “ከቅሬታ መስማቱ ጉዳይ የሚበልጠው ሃገሪቱ ዛሬ የወደቀችበት ከፍተኛ የፖለቲካ ውዝግብ ነው” ተባለና፣ በነበየነ ሰለሞንና በንኡስ ከበርቴው ደንፊ ቡድን የተደገፈው ታሪካዊው የመስከረም 1967 ዓ.ም. የፖለቲካ ውሳኔ ተላለፈ።
“በኢትዮጵያ ሠራተኞች አንድነት ማህበር ጠቅላላ ጉባኤ (?)” ይላል በበየነ ሰለሞን፣ በዓለም አብዲና በሌሎች 15 ሰዎች የተፈረመው የመስከረም 6 ቀን 1967 ዓ.ም. ወረቀት፣ “በወሰነው በዚህ መሰረታዊና (?) ዲሞክራሲያዊ (?) ውሳኔ ሳብያ፣እንዲሁም የወዛደሩን ችግር በቅንነት በሚመለከቱ ርእሶች /አርእስት) ረገድ በወሰደው አቋም ምክንያት ለሚፈጠረው ችግር፣ የኢትዮጵያ ሠራተኞች ከዳር እስከዳር አስቸኳይ እርምጃ ለመውሰድ በንቃትና በተጠንቀቅ እንዲጠብቁ አዟል” (ስርዝና የጥያቄ ምልክቶች- ሰህድ)
ይህ ውሳኔ ከውጭም ከውስጥም በነበረው “የጦፈ” የቅስቀሳ ውጤት እንጂ፣ የኢትዮጵያ የተዘጋጁበት፣ የተወያዩበት እና በጥሞና ያጤኑት የፖለቲካ ውሳኔ አልነበረም። አቶ ግርማቸው አማረ ከላይ የጠቀስነውን ውሳኔ ለመስከረሙ 1967 ዓ.ም. ሲያቀርቡ፣ እኛን ትዝ የሚለን ሌላው ቁም ነገር የኢ.ሠ.አ.ማ. 1961 ዓ.ም. ጉባኤና “ያቺ አረፍተ ነገር” ናቸው።
እንደሚታወሰው “የኢትዮጵያ ሠራተኞች ከዳር እስከዳር” የወሰዱት (አንድም) አስቸኳይ እርምጃ አልነበረም። በወቅቱ የተፈፀመው ነገር፣ በመስከረም 2 ቀን 1967 ዓ.ም. ፀረዲሞክራቲክ አዋጅ መሰረት “የሠራተኛ” መሪዎች መታሰር ነበር። ዛሬ በግትርነት አንረታም ያሉት የንኡስ ከበርቴ ደንፊዎች ያቺ ‘ጊዜያዊ ሕዝባዊ መንግሥታቸው” ትዝ ባላቻቸው ቁጥር፣ “የኢትዮጵያ ሠራተኞች ከዳር እስከዳር አስቸኳይ እርምጃ ቢወስዱ” ኖሮ እያሉ ለመሸሽ ቢሞከሩ፣ የኢትዮጵያ ፊውዳሊስቶች፣ ኢምፔሪያሊስቶችና እነበየነ ሰለሞንም “ቢወሰዱ ኖሮ” እያሉ ጣሪያ ጣሪያውን እንደሚያማትሩ ከቶም አንጠራጠርም።
የሆነው ሆኖ፣ የአቶ በየነ ሰለሞን ዘመን በዚሁ ያከትምና እኛም ወደ አምስተኛው ወቅት እንገባለን። አምስተኛው ወቅት ከመስከረም 1967 ዓ.ም. እስከ ግንቦት 1967 ዓ.ም. ድረስ ያለው ጊዜ ነው።
V
አምስተኛውን ወቅት አይነተኛ የሚያደርጉት ባህሪዎች እጅግ ብዙና የተወሳሰቡ ናቸው። በዚህን ወቅት በኢ.ሠ.አ.ማ. ውስጥ በሁለት ወገኖች መካከል መራራ ትግል ተካሂዷል። ፀረዲሞክራቲኩ ደርግም “የኢትዮጵያ ህብረተሰባዊነት” የሚለውን መመሪያውን አንግቶ ቀርቧል። የኢ.ሠ.አ.ማ. አንደኛው ወገን የሚመራው፣ ለጊዜው እኛ ባልተረዳነው “ተአምር” (!) ከእሥር “በተረፈው” እና “ጊዜያዊ ሕዝባዊ መንግሥትንም” በተወው በዓለም አብዲ ሲሆን፣ ሌላ ወገን ደግሞ፣ ከመቼውም ጊዜ ይልቅ አሁን፣ በኢ.ሠ.አ.ማ. ዙሪያ ባነፈነፈው የንኡስ ከበርቴ ደንፊ ቡድን ነበር።
በእነዚህ ሁለት ወገኖች መሃከል የተካሄደው ትግል በዝርዝር ባይታወቅም፣ በመካከላቸው ብዙ ሽኩቻዎች እንደነበሩ መረዳቱ እስከዚህም አዳጋች አይደለም። ለማንኛውም በሁለቱ ወገኖች መካከል የሚካሄደው ትግል ከሮና ተፋፍሞ የሚመጣው በሚያዚያ ወር 1967 ዓ.ም. ላይ ነው። የክርክሩ ዋና ርእስ የኢ.ሠ.አ.ማን ጠቅላላ ጉባኤ መጠራት የሚመለከት ሲሆን፣ በመሃል ለፀረዲሞክራቲኩ ደርግ ያደረው ዓለም አብዲ የጉባኤውን መጠራት አጥብቆ ይከላከልና ያደናግር ነበር። ሌላው ወገን ደግሞ፣ የስብሰባውን በአስቸኳይ መጠራት አጥብቆ ይጠይቅና ለዚሁ ትክክለኛ አላማው ይታገል ነበር። አላማው ትክክል ይሁን እንጂ፣ በትግል ዘዴው አምታቺና ትርምስ ነዥ እንደነበር ከቶም ለመካድ አይቻልም።
አዲሱን “በየነ ሰለሞንን” ያገኘው ፀረዲሞክራቲኩ ደርግም፣ ባንድ በኩል ዓለም አብዲን እየደገፈ፣ በሌላ በኩል ደግሞ፣ ጠቅላላው ጉባኤ እንዲጠራ (እንዳይጠራ) የማይሰጠው ተስፋና የማይገባው ቃልኪዳን አልነበረም። እንደሚታወሰው በመጀመሪያ ለጥር 24፣ ከዚያም ለየካቲት 22 እና 23 ቀኖች ተጠርቶ ነበረውን የኢ.ሠ.አ.ማ. ጠቅላላ ጉባኤ፣ ፀረዲሞክራቲኩ ደርግና አድርባዩ ዓለም አብዲ ተባብረው “ላልተወሰነ ጊዜ ሊያስተላልፉት” ችለዋል። የንኡስ ከበርቴው አካል የሆነው ደርግ፣ የታቀፉት የንኡስ ከበርቴ ልቦና እየዋለለችበት ቢቸገር እስከዚህም እይደንቅም ። ዞሮ ዞሮ ከንኡስ ከበርቴው መደብ ውስጥ፣ የወዛደሩን ርእዮተ ዓለም ተቀብለው እስከመጨረሻው ድረስ የሚዘልቁት እጅግም የበዙ እንዳልሆኑ እነሌኒን በብዙ ጽሁፋቸው፣ ብዙ አስተምረውናል።
እንደዚህም ሲል፣ ደርጉ በተለይም ከጥቅምት ወር 1967 ዓ.ም. መጨረሻ ላይ አንስቶ፣ አንዳንድ ተራማጅ እርምጃዎች እየወሰደ፣ በሌላ ጊዜ ደግሞ፣ የወሰዳቸውን ተራማጅ እርምጃዎች በፋሽስታዊ አመፅ እየበከላቸው መጥቶ ነበር። ይህ ሁኔታ ምንም እንኳን በተለይም ለጠቅላላው የአድሃሪዎች ሰፈርና ለንኡስ ከበርቴው ደንፊ ቡድን እጅግ አመቺ ቢሆንም፣ በአንክሮ ሲታይ ደግሞ፣ የኢትዮጵያ ሠራተኞች ለፀረዲሞክራቲኩ ደርግም ሆነ ለንኡስ ከበርቴው ደንፊ ቡድን አንዳችም አይነት ሙሉ ድጋፍ እንዳልሰጧቸው ግልጽ ነው።
ዲሞክራቲኩ ደርግ የኢትዮጵያን ወዛደሮች ሙሉ ድጋፍ እንዳያገኝ አጥብቆ የታገለው ወገን፣ የንኡስ ከበርቴው ደንፊ ቡድን እንደሆነ የማይካድ ነገር ነው። በዚሁ ትግሉ “ሊሞገስ” ይገባዋል። ነገር ግን፣ ይህ የጉዳዩ አንድ አንፃር ብቻ ነው። በሌላ አንፃር፣ ዛሬ የኢትዮጵያን ወዛደሮች የነቃና በወጉ የተደራጀ ትግል የሚከላከለው፣ የሚያተራምሰውና የሚያምታታው ወገን፣ ይኸው የንኡስ ከበርቴ ደጋፊ ቡድን ነው። ይህንንም እውነት ለመካድ አይቻልም። በዚህ ጽሁፍ ውስጥ ደጋግመን የምንመለስበት ጉዳይ ነው። ለጊዜው ግን ከሚነገሩለት ታሪኮች አንደኛውን ብቻ አውስተን እንለፍ።
እንደሚታወሰው የኢ.ሠ.አ.ማ. ጠቅላላ ጉባኤ ለየካቲት 22 እና 23 እንዲጠራ እቅድ ነበር። ሆኖም፣ “የገጠርን መሬት የሕዝብ ያደረገው” የየካቲት 25 ቀን 1967 ዓ.ም. አዋጁ ከመታወጁ በፊት፣ የኢ.ሠ.አ.ማ. “መሪዎች”፣ ለአዋጁ አስፈላጊ የሆነውን የድጋፍ ሰልፍ በማዘጋጀት ላይ ለውይይት እንዲገኙ ሃሳብ ይቀርባል። ውይይቱ የተካሄደው በመሬት ይዞታ ሚኒስቴር ውስጥ ሲሆን፣ የሁለቱም ወገኖች አፈጉባያቸው ለውይይቱ ስብሰባ ተገኝተው ነበር። በዚያን እለት የታየው የንኡስ ከበርቴው ደንፊ ቡድን አቋም እጅግ አሳዛኝ ከመሆኑም በላይ፣ ሌኒን እንዳለው “አናርኪዝም፣አናርኪዝም የሚገማ” ነበር። ውይይቱ እንደተከፈተ፣ እነዳልነው ትክክለኛ አላማ ይዞ የኢ.ሠ.አ.ማ. ጠቅላላ ጉባኤ እንዲጠራ የሚታገለው ወገን፣ በኢትዮጵያ ወዛደሮች ስም በማይታጠፍ ቃሉ የሰጠው መግለጫ የሚከተለው ነበር።
“የኢ.ሠ.አ.ማ. ጠቅላላ ጉባኤ ካልተጠራና ውሳኔ ካልተሰጠበት በስተቀር አዋጁን በመደገፍ ሰላማዊው ሰልፍ ላይ ተካፋይ ለመሆን አይቻልም”። ለጥቆም “ጊዜያዊ ወታደራዊ መንግሥት” ይላል አንድ በዚያው ሰሞን የተበተነ በራሪ ወረቀት፣ “የካቲት 25 ቀን 1967 የሰጠውን (“ያሰበውን”?) የመሬት ይዞታ አዋጅ በመደገፍ ወዛደሮች ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ ፈልገው ስለዝግጅቱ በቅድሚያ ለመወያየት (ጠቅላላ ጉባኤ ተጠርቶ ማለት ነው- ሰህድ) እንዳይችሉ የመሰብሰብ መብት ነፍጓቸዋል።” (ይህ ጥቅስ የተወሰደው “ዓለም አብዲና ግብረ አበሮቹ በወዛደሩ ላይ ከሚፈጽሙት አድራጎቶች በጥቂቱ” በሚል ርእስ ከተበተነ አንድ በራሪ ጽሁፍ ውስጥ ነው። ገጽ 2፣ ጽሁፉ ቀን አልተፃፈበትም። ምናልባት በመጋቢት ወር የተበተነ ነው)
የሰማነው “የማይታጠፍ ቃል” እና የጠቀስነው ጽሁፍ፣ የንኡስ ከበርቴውን ደንፊ ቡድን የአዎንታዊነት ባህሪ በገሃድ የሚያሳዩን እውነቶች ናቸው። የንኡስ ከበርቴው ደንፊ ቡድን፣ ደርጉ በውድም ሆነ በግድ የኢ.ሠ.አ.ማን ጠቅላላ ጉባኤ መጠራት እስካልተቀበለ ድረስ፣ “ለመሬት ላራሹ” አዋጅ ደንታም አልነበረውም። በዚያን ጊዜ ለርሱ የተከሰተለት “አብዮታዊ” (?) ትግል፣ በሁኔታው ተጠቅሞ የኢ.ሠ.አ.ማን ጠቅላላ ጉባኤ ማስጠራቱ ብቻ ነበር። ይህ እንግዲ በኢትዮጵያ ሠራተኞች ዙሪያ ያነፈነፈው የንኡስ ከበርቴ ደንፊ ቡድን፣ በኢትዮጵያ ሠራተኞች ስም ሲናገርና የኢትዮጵያ ሠራተኞች ሲሸልታቸው ነው። መለስ ብለን ስናስተውል፣ በውጪ አገር የሚገኝ “ሌላው የንኡስ ከበርቴ ደንፊ ቡድን፣ “የፌዴሬሽን ቡለቲን” በተሰኘው ጋዜጣው ውስጥ፣ የኢትዮጵያን ሠራተኞች እንደሚከተለው ሸልቷቸው ነበር፦
“የየካቲቱ ሬቮሉሽን በመነሳት ላይ ያለው ላባደር ሠራተኛ ከራሱ የመደብ ጥቅም አልፎ፣ የጠቅላላ ህብረተሰቡን በተለይም ደግሞ፣ የተፈጥሮ (?) የመደብ ጓድ የሆነውን የጭቁን ገበሬውን ዋና ጥያቄ ይዞ የተነሳበትና የታገለበት ነው። የየካቲቱ ሬቮሉሽ ……[የማይነበብ – አዘጋጆቹ] ከፍተኛ ዲሞክራቲክ በሆነው የኢትዮጵያ ላብአደር ሠራተኛ የተጀመረ ግንባር ቀደም መሪነቱም በዚሁ መደብ የተወሰደ ታላቅ ትግል ነው” ( የኢት.ተማ. ፌደሬሽን ቡለቲን፣ ግንቦት 1966፣ ርእስ አንቀፅ፣- ጥያቄ ምልክትና ስርዞች የተጨመሩ- ሰህድ)
አንባቢው ይህንን፣ ከሌሊንም በላይ “ሌኒኒስት” የሆነውን ድርሰት ተመልሶ ያንበበውና፣ የንኡስ ከበርቴው ደንፊ ቡድን የኢትዮጵያ ወዛደሮች እንደምን እንደሚሸነግላቸው ብቻ ይረዳልን። አጠገባችን ያለው የንኡስ ከበርቴ ደንፊ ቡድን፣ በየካቲት 1967 ዓ.ም. ላይ “የማይታጠፍ ቃሉን” ሲሰጠን፣ ከላባደሮችም በላይ “ላብአደር” አድረጎ የሚቆጥረው ሰው ቢኖር ክፉኛ ተሳስቷል ከማለት በስተቀር ምንም የምንጨምርለት ነገር የለንም።
የሆነው ሆኖ፣ የመሬት ላራሹ አዋጅም ታወጀ። የኢትዮጵያም ወዛደሮች፣ ጠቅላላው ጉባኤ ሳያስፈልጋቸው፣ለአዋጁ ያላቸው ድጋፍ በገሃድ ገለፁ። እኛም የንኡስ ከበርቴውን ደንፊ ቡድን ማንነት በገሃድ ልንመሰክር በቃን። የኋላ ኋላም፣ በውጭ አገር የሚገኘው “ሌላው” የንኡስ ከበርቴ ደንፊ ቡድን፣ “የታወጀው መሬት ላራሹ አዋጅ በገጠር ፋሺዝምን የሚያስፋፉ ነው” እያለ ሲያወናብድ፣ አጠገባችን ያለው የንኡስ ከበርቴ ደንፊ ልሳን የሆነ “ዲሞክራሲያ” ደግሞ፣ ቀደም ሲል ጭፍን ፋሺዝም በኢትዮጵያ ነገሠ” በሚል ርእስ ሥር ሰፊ ሃተታ ጽፎለት እንደነበር ትዝ አለን (ዲሞ ቅጽ 1፣ ቁ.17፣ 15.3.67)
ሆኖም፣ በየካቲት ወር የመሬት ላራሹን አዋጅ ከዚሁ ሆኖ ያዳመጠውና ሰፊው ሕዝብ ለአዋጁ የሰጠውን የደመቀ ድጋፍ በዓይኑ የተመለከተው የንኡስ ከበርቴው ደንፊ ቡድን፣ ተሙለጭልጮ “ሊያመልጠን” የሚከተለውን ጽፎልን ነበር። በሰፊው እንጥቀሰውና አንባቢው ማንነቱን ይይበት፦
“ከወዛደሩና ከገበሬው አብራክ የተገኙት ተራ ወታደሮችና የበታች ሹማምንት፣ እንዲሁም ጥቂት ተራማጅ መኮንኖች ይህንን ከፍተኛ ታሪካዊ ቆራጥነት የሚጠይቅ ታሪካዊ እርምጃ በመውሰድ ለመደብ ጓደኛቸው ለሰፊው ሕዝብ ያላቸውን ጽኑ ታማኝነት በተጨባጭ ማስረጃ በማሳየታቸው፣ የቀሩት መሰረታውያን ጥያቄዎች፣ የኢምፔሪያሊዝምና የዲሞክራሲ መብቶች ጉዳይ፣ ተገቢውን መልስ እንዲያገኙ እነዚህ የሕዝብ ወገኖች በደርጉ ውስጥ ሆነው እስከመጨረሻው እንደሚታገሉ ተስፋ እናደርጋለን።
“ይህ የታወጀው አዋጅ፣ በሰፊው የኢትዮጵያ ሕዝብ መካከል፣ አዲስ የህብረተሰብ ግንኙነት፣ ስልተምርት፣ ይትብሃል የሚመሰርት እንደመሆኑ መጠን፣ ገዥነት፣ ጢሰኝነት፣ ገባርነት፣ ሎሌነት፣ ሥራአጠነት፣ ባተሌነት፣ ሴትአዳሪነት፣ ከሰፊው የኢትዮጵያ ሕዝብ ከሰፊው መዝገብ ተፍቀው፣ በአንድ ቃል (?) በወዛደርነት የሚተኩበትን፣ ፍትህና ርትእ የሚሰፍንበት አቅጣጫ ያመለክታል” (ዲሞ.፣ ልዩ እትም፣ 30.6.67- ስርዞች የተጨመረ- ሰህድ)
አምታቺው የንኡስ ከበርቴ ደንፊ ቡድን “በኢትዮጵያ ላይ ፋሺዝም በነገሠ” በሦስት ወር ውስጥ፣ “ፍትህና ርትእ የሚሰፍንበትን አቅጣጫ ተመለከተው” ያቺ መከረኛ የንኡስ ከበርቴ ልቦናው እየተሙለጨለጨችበት በመቸገሩ እንደሆነ ይገባናል። ከዚህም አልፎ፣ “የፋሺስቱ ስርዓት” መሪዎች በሦስት ወር ውስጥ፣ “የሰፊው ሕዝብ የመደብ ጓደኞችና ለሰፊውም ሕዝብ ያላቸውን ጽኑ ታማኝነት በተጨባጭ ማስረጃ ያሳዩ የሕዝብ ወገኖች መሆናቸውን” ሲነግረን “የሚስጥረ ሥላሴን” ምስጢር አላነበብንበትም።
በዚህ አልበቃ ያለው አንባቢ ግን፣ ሲሻው ደግሞ የዲሞክራሲያን ቅጽ 2፣ ቁጥር 26 እና 27 ጎን ለጎን አስቀምጦ ያንብባቸው። ለዲሞክራሲያ በታደለው ተአምር ብቻ፣ እፍታም ሳይቀር “ልክ እንደጀርመንና ኢጣልያን ፋሺዝም ከነገሠባት ኢትዮጵያ” ወጥቶ፣ “የፍትህና የርትኦን አቅጣጫ ይመለከታል።” እኛም፣ “መንገዱን ጨርቅ ያድርግልህ ብለን እንሸኘዋለን።” “ቅዱስ ዲሞክራሲያ” አቅፈውና ደግፈው ይከተሉት።
ልናሳስበው የምንፈልገው ቁም ነገር ቢኖር፣ እሩቅ ከመሄድ በፊት “ዲሞክራሲያ” ቅፅ 2 ቁጥር 28ን እንዲያነብ ነው። በዚህኛው የዲሞክራሲያ እትም ውስጥ የሰፈሩትን ፀረሕዝብ ሃሳቦች ለመተቸት መጀመሩ፣ ይህንን ጽሁፋችንን ያለቅጥ ስለሚያራዝምብን፣ ለጊዜው በማስታወሱ ብቻ ተወስነናል። አርእስቱ “አርሶአደሩን ማን ይምራዉ?” የሚል ሲሆን፣ ይዘቱ ደግሞ “የገበሬዎች ማህበር ለማደራጀትና ለማጠናከር” የወጣው የታህሳስ 1968 ዓ.ም. አዋጅ ነው።
በመሬት ላራሹ ምክንያት የመዘገብነው የንኡስ ከበርቴው ደንፊ ቡድን ወላዋይነትና አምታችነት፣ የሠራተኛ ቀን (ሚያዚያ 23) ክብረ በአል በሚዘጋጅበት ወቅትም ተደግሞ እንደነበር ይታወቃል። ይሁን እንጂ፣ የኢትዮጵያ ወዛደሮች አሁንም ለዓመታት የታገሉለትን የሠራተኛ ቀን ከዓለም ወዛደሮች ጋር ሆነው የሚያከብሩበት ምክንያት አልታያቸውም ነበርና፣ እለቱን በደማቅ ሁኔታ አክብረውት ውለዋል። በእለቱ፣ በኢትዮጵያ ሠራተኞች የተያዙት መፈክሮች ገሃድ እንዳደረጉት፣ ለፀረ ዲሞክራቲኩ ደርግም ሆነ ለቁንጥንጡ የንኡስ ከበርቴ ደንፊ ቡድን ሙሉ ድጋፋቸውን አልሰጡም። በአንድ በኩል የደርጉን ፀረዲሞክራቲክነት አውግዘዋል፤ በሌላው በኩል ደግሞ፣ የጊዜውን የሰፊውን ሕዝብ ጥያቄዎች በትክክል አንስተዋል።
የሆነው ሆኖ፣ ኢ.ሠ.አ.ማ ውስጥ በተመሰጉት በሁለቱ አድርባይ ወገኖች መካከል የተካሄደው ትግል በጣሙን ተጋግሎ የመጣው በሚያዚያና በግንቦት ወራት ውስጥ ነበር። በዚህን ርቀት በነበረው ትግል፣ ከየአቅጣጫው ይወረወር ከነበረው የስም ማጥፋት ዘመቻ በተጨማሪ፣ በዱላ እስከመሻተት ተደርሶም እንደነበር የአደባባይ ሚስጥር ነው።
የንኡስ ከበርቴው ደንፊ ቡድን የበላይነቱን ያገኘው በሚያዚያ/ግንቦት 1967 ዓ.ም. ላይ ነው። ከሁሉ መነገር ያለበት መሰረታዊ ጉዳይ ግን፣ የኢ.ሠ.አ.ማ.ን አድሃሪ አመራር ለማውረድና “ከሠራተኛ ማህበር በወጡ ሰዎች” ለመተካት የሚደረገው ትግል፣ ረጅም ታሪክ እንዳለው ነው። ይህንን ጉዳይ በዚሁ ጽሁፋችን ውስጥ በብዙ ቦታዎች አሳይተናል። በሚያዚያ/ግንቦት 1967 ዓ.ም. ላይም እነዚያ ረጅም ትግል ያደረጉት የሠራተኛ ማህበራት በቅንነትና በእውነተኛ ወዛደርነት ዓለም አብዲን ከሥልጣን ለማውረድ ታግለዋል። የንኡስ ከበርቴውን ደንፊ ቡድን፣ በሚያዝያ/ ግንቦት ላይ ይህንን ረጅምና ቅን የወዛደሮች ትግል ለራሱ ግቦች እንደተጠቀመበት ግን የማይታበል ሃቅ ነው።
ሆኖም፣ በቅንነትና በእውነተኛ ወዛደርነት ረጅም ትግል ያካሄዱት ወዛደሮች በጊዜው የንኡስ ከበርቴ ደንፊ ቡድን እንደሚጠቀምባቸው ሊያውቁም ሊጠረጥሩም አልቻሉም ነበር። አንዳንዶቹ፣ ምንም እንኳ የፖለቲካ ንቃት ተቀዳሚ መሆን እንዳለበት ደጋግመው ቢገልፁም፣ ሊቸረቸርባቸው የተነሳው የንኡስ ከበርቴ ቡድን በብዙ ማወናበጃዎች ይጠቀም እንደነበር የታወቀ ነው። ለምሳሌም ያህል “ለፖለቲካው ኤክስፐርቶቹ ይበቃሉ፤ የናንተ ሥራ መታገል. መታገል. ነው” የሚለውን የፖለቲካ ቅስቀሳውን ብቻ ማውሳቱ ይበቃል።
የሰፊው ሕዝብ ድምጽ በጊዜው፣ “ይህን ሁሉ ፀረዲሞክራሲያዊ ድርጊት የተቃወሙ የወዛደሩ ተራማጅ ክፍሎች ትግላቸውን በማፋፋም ሚያዝያ 11 ቀን ባደረጉት ስብሰባ ዓለም አብዲን ከሥልጣን አውርደው በርሱ ቦታ ኢ.ሠ.አ.ማ በጊዜያዊ የሠራተኞች አስተባባሪ ኮሚቴ እንዲመራ መወሰናቸው ይታወሳል” በማለት የጻፈው “ይህንን ሁሉ” ውስብስብ ሁናቴ በመመልከት ነበር። (ሰህድ- ሚያዝያ 23 /67-ልዩ እትም)
እንደሚታወሰው፣ ዓለም አብዲን ከሥልጣን የወረደው ሚያዝያ 11/18/ ላይ፣ የንኡስ ከበርቴ ደንፊ ቡድን በወሰደው አስደናቂ “አብዮታዊ” እርምጃ ነው። እኛም፣ በጊዜው የተበተኑትን አንዳንድ በራሪ ወረቀቶች በማጥናት፣ ታሪኩን ከሞላ ጎደል ልንረዳ እንችላለን።
“ዓለም አብዲና ግብረ አበሮቹ” ትላለች አንዲት ደራሲና ቀን ያልሰፈረባት በራሪ ወረቀት፣ “በኢትዮጵያ ሠራተኛ ላይ ያደረሱትና የሚያደርሱት ግፍ፣ የግፍ ግፍ ቢዘረዘር መጸሃፍ አይበቃውም” (ገጽ 3)። እኛም እንደዚሁ እንላለን። ይህቺው በራሪ ወረቀት ለጠቅ አድርጋ “እኛስ ከትግሉ የምንቀስመው ትምህርት ምንድነው?” ብላ ስትጠይቅ እኛም አብረን ጠየቅን። መልሳም፣ “ምርጫችን አንድ ብቻ ነው፤ ይኸውም ዓለም አብዲን ከሥልጣን አውርዶ እውነተኛ መሪዎችን መምረጥ ብቻ ነው” (ገጽ 3-4) ስትለን፣ እኛም ትክክለኛ ምርጫ ነው አልን።
ነገሩ መላ ያጣው አንዲት ደራሲና “ያልታወቀን” የሚያዝያ 11/67 በራሪ ወረቀት ስናነብ ነው። የወረቀቱ ርእስ፣ “የመላው የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማህበሮች ውሳኔ” የሚል ነው። ሰፋ አድርገን እንጥቀሳት፦
“እነዓለም አብዲ በሠራተኛው ቤት ሥልጣን ከያዙበት ጊዜ ጀምሮ የሚካሄደው የሠራተኛ ትግል እነሆ እስከዛሬ ድረስ አደርባይ መሪዎችን አውርዶ እውነተኛ መሪዎችን ለመምረጥ አልቻለም።”
“ይህ በዓለም ታሪክ ውስጥ ሕዝባዊ ትግሎችን በግንባር ቀደምነት መምራቱ በሰፊው የሚተረክለት (“የሚተረክለት”?) የወዛደር መደብ፣ እውነተኛ መሪዎቹን በመምረጥ በተጀመረው ትግል ተገቢውን ድርሻ በመፈፀም ላይ ይገኛል” (ገጽ 3)። በገጽ 4 ላይ ደግሞ የሚከተለው ስፍሯል፦
“እስከዛሬ ድረስ የሠራተኛውን ትግል ሲያፍን የኖረው ዓለም አብዲ ከሥልጣን ወርዶ ወደፊት ምርጫ እስከሚደረግበት ጊዜ ድረስ፣ የኢትዮጵያ ሠራተኞች አንድነት ማህበር በጊዜያዊ የሠራተኞች አስተባባሪ ኮሚቴ እንዲመራ ወስነናል።”
ይህች “የመላውን ኢትዮጵያ ሠራተኛ ማህበሮች ውሳኔ” ያበሰረችልን በራሪ ወረቀት መልካም ዜና አሰምታናለች። እኛም ከዓለም አብዲ የተገላገልን መስሎን ተደስተን ነበር። ሆኖም፣ ከዚህ በራሪ ወረቀት ውስጥ፣ አንደኛ፣ ይህንን ከፍተኛ ውሳኔ ለማሳለፍ የተሰበሰቡትን የሠራተኛ ማህበራት ቁጥር እንኳ ለመረዳት ባለመቻላችን ግር ተሰኘን። ሁለተኛም፣ አሁንም ደራሲዋ “ያልታወቀውን” ሌላ በራሪ ወረቀት ስናነብ ደግሞ፣ ይኽስ “የአፍዝ-አደንግዝ” ነገር አለበት በማለት ተጠራጠርን።
ይህችኛዋ በራሪ ወረቀት የተበተነችው ሚያዝያ 18 ቀን 1967 ዓ.ም ሲሆን፣ ረጅም ርእሷም “የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማህበሮች በፊርማቸውና በማህተማቸው አጽድቀው ሚያዝያ 11/67 ዓ.ም. ባስተላለፉት ውሳኔ መሰረት፣ ዛሬ ሚያዝያ 18/67 ዓ.ም ከኢትዮጵያ ሠራተኞች የተላለፈ [የማይነበብ] ውሳኔ” የሚል ነበር። እንጥቀሳትና እኛም እንማር፦
“ጊዜያዊ ወታደራዊ መንግሥት ካስተማረን ትምህርቶች አንዱ” ትላለች ወረቀታቸው “የትግል ዘዴንና ብልሃትን ነው። በሃገሪቱም ሆነ በዓለም ዙሪያ እንደ አምላክ ይፈራ የነበረው ንጉሥ ያለአንዳች ችግር (?)፣ ያለአንዳች ሁከት(?) ከሥልጣን አውርዶ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብም “አበጃችሁ” አላቸው። ጉዳዩ ከሕዝብ ስሜት የራቀ አልነበረምና ነው (ገጽ 1)
“አሁንም እኛ የወዛደሩ ተወካዮች መሰብሰብ ባንችልም፣ በፊርማችን የዓለም አብዲን መውረድ አረጋግጠን፣ እነሆ ዛሬ፣ ሚያዝያ 18/67 ዓ.ም. አንስተን፣ ኢ.ሠ.አ.ማ በጊዜያዊ የሰራተኛ ኮሚቴ እዲመራ አድርገናል /ገጽ 1/።
“በተጨማሪ በዛሬው እለት፦
“1/ ኢ.ሠ.አ.ማን የሚመሩ አሥራ አንድ ሰዎች የያዘ ኮሚቴ ተቋቁሟል። ኢ.ሠ.አ.ማን ሙሉ ኃላፊነትና ሥልጣኑን ተረክበዋል። የኮሚቴው አባሎች የስም ዝርዝር፦ 1ኛ/ አቶ ማርቆስ ሃጎስ፣ 2ኛ/ አቶ ገብረሚካኤል ወ/መድህን፣ 3ኛ/ አቶ ግርማ ወ/ሰንበት፣ 4ኛ/ አቶ ተሰማ ደሬሳ፣ 5ኛ/ አቶ ሚካኤል ተፈሪ፣ 6ኛ/ አቶ ጌታቸው አማረ፣ 7ኛ/ ወ/ሮ ጎመጀ ሸዋ ለማ፣ 8ኛ/ አቶ አበበ ገ/ፃድቅ፣ 9ኛ/ አቶ መኮንን ተስፋዬ።
“እንዲሁም ከኤርትራ ክ/ሃገርና ከሃረርጌ ክ/ሃገር የኢ.ሠ.አ.ማ ቅርንጫፍ ማህበራት አንዳንድ ተወካዮች መርጠው ከዚሁ ኮሚቴ ጋር እንዲሰራ።
“2/ ምክር ቤት እየተባለ የሚጠራው ግን በሕይወት የሌለ አካል ከዛሬ ጀምሮ ፈርሷል” (ገጽ 2)
በዚህ ጽሁፋችን መግቢያ ውስጥ፣ የንኡስ ከበርቴው ደንፊ ቡድን ለፀረ ወዛደርነት፣ አድርባይነቱ፣ ለአምታቺነቱ፣ ለወላዋይነቱ. . . እሱው ራሱ ምስክር ሆኖ እንደሚቆም ተናግረን ነበር። እንደዚሁም፣ እነዚህን ባህሪዎቹን ለማሳየት እጅግም አድካሚ እንደማይሆንብን ወዲያውኑ ገልፀን ነበር። አንባቢው እንግዲህ ከዚህ በላይ የጠቀስነውን የሚያዚያ 18/67 በራሪ ወረቀት እንደገና ይመለስበትና ይመለከተው ከማለታችን በፊት፣ ከመስከረም 6/67 የኢ.ሠ.አ.ማ “አመታዊ ጠቅላላ ጉባኤ ውሳኔ” ውስጥ የሚከተለውን እንጥቀስለት፦
“የጦር ኃይሉ ደርግ በሰጣቸው ልዩ ልዩ መግለጫዎች ስልጣን ለመያዝ የማይፈለግ መሆኑን በመግለጽ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ እውነተኛ ነፃነት እንዲቀዳጅ፣ የራሱን እድል ራሱ እንዲወስን የሚጥር መሆኑን መግለፁ የሚታወስ ነው። ይሁን እንጂ፣ ጊዜያዊ ሕዝባዊ መንግሥት ሊቋቋም ሲችል፣ ጊዜያዊ ወታደራዊ መንግሥት መቋቋሙ ሕዝቡን ከታላቅ ጥርጣሬ ላይ ከመጣሉም ሌላ፣ የተቀሰቀሰውን ሕዝባዊ ፍላጎት ሁሉ ማቅ አልብሶታል። የጦር ኃይሉ ደርግ . . . እጅግ ፀረዲሞክራሲ አስተሳሰብ የሚያስተናግድ መሆኑን በይፋ ለመግለጽ እንወዳለን” (ገጽ 3)
አንባቢው አሁን ወደኋላ ተመልሶ የሚያዝያ 18/67 ዓ.ምን በራሪ ቀረቀት ሲያነብ፣ “የትግል ዘዴና ብልሃት” መምህር ሆኖ የሚቀርብለት፣ ያ የመስከረሙ 1967 “ጊዜያዊ ወታደራዊ መንግሥት” እንደሆነ ይገነዘባል። ከዚያም “ያለአንዳች ችግር”፣ “ያለአንዳች ሁከት”፣ “አወጃችሁ” የሚሉትን ሃረጎች ሲያነብ ደግሞ፣ የንኡስ ከበርቴው ደንፊ ቡድን አደርባይነትና አምታቺነት እርቃነስጋውን ቆሞ ይታየዋል። የኢትዮጵያን ወዛደሮች በአደርበይነት በማርከስና በሌኒን ስም የተቀላቀላቸው ንኡስ ከበርቴ ደንፊ ቡድን፣ አሁን ደግሞ ማርክስንና ሌኒንን እርግፍ አድርጎ በመተው፣ “የትግል ዘዴውንና ብልሃቱን” “ፋሺስት” ከሚለው ጊዜያዊው ወታደራዊው መንግሥት መማር ይይዘዋል።
እንደሚታወሰው፣ የሚያዝያ ወር የንኡስ ከበርቴ እርምጃ ብዙም አልቆየ። ፀረዲሞክራቲኩ ደርግ ጣልቃ ገብቶ፣ ለርሱ ያደረውን ዓለም አብዲን ከሥልጣን ወንበሩ ላይ መልሶ አስቀምጦታል። በጊዜው በደርጉና በንኡስ ከበርቴው ደንፊ ቡድን መካከል የተደረሰው ስምምነት፣ “የኢ.ሠ.አ.ማ ጠቅላላ ጉባኤ” ከሚያዝያ 23 ቀን በኋላ( ከሠራተኞች ቀን በኋላ) እንዲጠራና አቶ ዓለም አብዲም እስከዚያው ድረስ ሥልጣናቸውን ይዘው እንዲቆዩ” የሚል ነበር።በዚህ ስምምነት፣ ጊዜው የመጣ የመሰለው የንኡስ ከበርቴ ደንፊ ቡድን “የፍትህንና የርትእን አቅጣጫ ሲመለከት”፣ የሠራተኛው ቀን ክብረ በአል “ያለትርምስ ሊከበርልኝ ነው” ያለው ደርግ ደግሞ፣ ጊዜያዊ ፋታ በማግኘቱ ተደስቶ ገብቷል። ነገር ግን የተባለውን ጠቅላላ ጉባኤ በግንቦት ወርም ቢሆን ለመጠራት አልተቻለም። ግንቦት 9/67 እንደገና “የመላው የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማህበሮች ውሳኔ” በሚል ርእስ የተበተነች አንዲት “ሌላ” ደራሲዋ “ያልታወቀ” በራሪ ወረቀት እንዳላቸው፦
“ይህም ሆኖ ዓለም አብዲ ከሥልጣኑ አልወረደም። . . . ትዕግስት ወሰን አላት። . . . ዳግም ላይመለስ ለመጨረሻ ጊዜ የወዛደሩን ጠላት ከወዛደሩ ቤት አሰወጥቷል። ሚያዝያ 11 እና 18 ቀን በተላለፉት ውሳኔዎች መሰረት ምርጫ እስከሚደረግበት ጊዜ ድረስ፣ ኢ.ሠ.አ.ማ በወዛደሩ በተመረጠ ጊዜያዊ የሠራተኛ ኮሚቴ እንዲመራ በማይታጠፍ ቃሉ ወስኗል” /ገጽ 2)።
“ይህም ሆኖ” እንበልና ደግሞ፣ “ዓለም አብዲ ከሥልጣኑ አልወረደም።” እንደሚታወሰው፣ ፀረዲሞክራቲኩ ደርግ በወሰደው የጣልቃገብነትና የሁሉን አውቅላችኋለሁ እርምጃ ግን ግንቦት 11 ቀን 1967 ዓ.ም. የኢ.ሠ.አ.ማ ጽ/ቤት ዘጋው። ብ.ጄ. ተፈሪ ባንቴ ግንቦት 23 ቀን 1967 ዓ.ም. ባደረጉት ንግግር ውስጥ፣ “የሁለት ኃይሎች ትግል ቢሯችሁን እንዲደፈር አድርጎታል” ሲሉ፣ በሊቀ መንበርነታቸው ገለልተኛ ይምሰሉ እንጂ፣ ሁለቱ ኃይሎች፣ በአንድ ወገን ፀረዲሞክራቲክ ደርግና ዓለም አብዲ፣ በሌላው ወገን ደግሞ የንኡስ ከበርቴ ደንፊ ቡድን መሆናቸውን ለመካድ አይቻልም። “የተደፈረው” የኢ.ሠ.አ.ማ. ቢሮ የተከፈተው በዚሁ እለት ነበር።
የኢ.ሠ.አ.ማ. ጽ/ቤት በተከፈተበት እለት፣ ጉባኤውን እንዲመሩ የተመረጡት አቶ ማርቆስ ሃጎስ ባደረጉት “አብዮታዊ” ንግግራቸው ደግሞ፣ ከዚህ በታች የምንጠቅሰውን “መልእክት ለጉባኤው አስተላልፈው” ነበር።
“ከዛሬ ጀምሮ የእኛ መፈክር ቃል ‘ወዛደር ታጠቅ’ የሚል መሆን አለበት። ከእንግዲህ ወዲያ ወዛደር በመለዮ ለባሽ ጎን ተሰልፎ፣ በመካሄድ ላይ የሚገኘውን አብዮታዊ እንቅስቃሴ ከግቡ የማድረስ ኃላፊነት አለበት። ቤታችን ተከፍቷልናል። ከወዛደሩ ጉን የቆመው ጊዜያዊ ወታደራዊ መንግሥት አድሃሪያንን አስወገደልን ጽ/ቤታችንን እንዲከፈት ስላደረገልን በመላው ወዛደሮች ስም ደስታችንን እንገልፃለን” (ኢ.ሠ.አ.ማን በጊዜያዊነት የሚመሩ ሃላፊዎችን ለመምረጥ የተደረገ ስብሰባ ቃለ ጉባኤ፣ ግንቦት 23-24፣ ገጽ 6- ሰርዞች የተጨመሩ)
ሚያዝያ 11/18/ ቀን በተወሰደው “አብዮታዊ” እርምጃ ለሊቀ መንበርነት የበቁት አቶ ማርቆስ ሃጎስ፣ ግንቦት 23 ቀን እንደገና በሊቀ መንበርነት ሲመረጡ፣ ኢ.ሠ.አ.ማን “የደፈረውን” ጊዜያዊ ወታደራዊ መንግሥት ለጊዜው ለኛ ግልጽ ባልሆነልን አብዶ “ከወዛደሩ ጎን” አቁመውት ቁጭ አሉ። እኛም፣ “ጊዜያዊው ወታደራዊ መንግሥት አድሃሪያንን በማስወገድ” ረገድ ከሰማየሰማያት የወረደለት ልዩ ተሰጥዖ ( “የትግል ዘዴና ብልሃት”) ሊገባን አልቻለም። “ያለአንዳች ችግር” እንዳንል፣ ብዙ አየን። “ያለአንዳች ሁከት” እንዳንል፣ ብዙ ሰማን። “አበጃቹ” አንዳንል፣ ይኸው የሊቀመንበር ማርቆስ ሃጎስ “መልእክት” የተቀበለው ጉባኤ ከዚህ በታች የምንጠቅሰው ውሳኔ ግንቦት 26/67 ዓ.ም. አሳልፏል፦
“የኢ.ሠ.አ.ማ. አባል የሆኑ ተጋይ የማህበር መሪዎች ኢ.ሠ.አ.ማን ለወዛደር በሚጠቅም አኳኋን ለማደራጀት ትግላቸውን ከጀመሩ አያሌ ዘመናት አልፈዋል። ትግሉ ተፋፍሞ፣ የወዛደሩ ጠላት የሆኑ አድሃሪዎችን ከቤት በማስወጣት፣ ኢ.ሠ.አ.ማን በወዛደሩ ቁጥጥር ሥር አደረገ። አንድነቱ ይህ ሆኖ ሳለ፣ ያካሄድነው ሃቀኛ ትግል ለስልጣን ሽሚያ ተብሎ መተርጎሙን መላ ወዛደሩን ተቃውሟል።
“ለስልጣን ሽሚያ በሚል ሳቢያ፣ የኢ.ሠ.አ.ማን መዘጋት ወዛደሩ አጥብቆ ተቃውሟል። ለወደፊቱም፣ ትክክለኛ ያልሆነ ተመሳሳይ እርምጃ እንዳይወሰድ በጥብቅ ያሳስባሉ” (ስርዝ የተጨመረ)
ይህንን ግልጽ እንቆቅልሽ አንባቢው ይፍታው እንበልና ወደሚቀጥለው ወቅት እንለፍ። በአከፋፈላችን መሰረት፣ ስድስተኛው ወቅት የሚጀምረው ይኸው ጉባኤ ካለቀ በኋላ ነው። ጊዜውም ከግንቦት 1967 መጨረሻ እስከ መስከረም/ ህዳር 1968 ዓ.ም. ድረስ ያለው ጊዜ ነው ።
VI
በአጠቃላይ ሲታይ፣ ከግንቦት 1967- መስከረም/ህዳር 1968 ዓ.ም. ድረስ ያለው ጊዜ አይነተኛ የሚያደርገው ባህርይ፣ በአንድ በኩል የፀረአብዮት ኃይሎች ማንሰራራት ሲሆን፣ በሌላ በኩል፣ ደግሞ የአብዮት ኃይሎች መዳከምና መመታት ነው ።
በገጠር፣ በአንድ ወገን ገበሬዎች፣ ተራማጅ ዘማቾች፣ የመሬት ይዞታና የነቁ ያስተዳደር ሠራተኞች በሌላ ወገን ደግሞ፣ የታጠቁት አድሃሪዎች፣ የገጠሩ ንዑስ ከበርቴና የመንግሥቱ ማሺነሪ (ፖሊስ፣ ፍርድ ቤቶች፣ አድሃሪ የመንግሥት ባለስልጣኖች- የደርጉም ቀኝ ክንፍ ጭምር) ፊት ለፊት ተፋጥጠው ነበር። የገበሬ ማህበራት መሪዎች፣ ዘማቾችና የመሬት ይዞታ ሠራተኞች ይታሰሩ፣ ይገረፉና ይገደሉ ነበር። በሌላ በኩል ደግሞ፣ የታሰሩት አድሃሪዎች እየተፈቱ ነጻ ይለቀቁ ነበር። የገበሬ ማህበራትም ከአድሃዎች የወረሷቸውን መሳሪያዎች እንዲመልሱ ይታደኑ፣ ይገደዱ ነበር። በሌላ በኩል ደግሞ፣ መሳሪያቸውን በገበሬ ማህበራት የተወረሱት አድሃሪዎች ይታጠቁና ጠመንጃቸውን ይወለውሉ ነበር። ብዙ የገበሬ ማህበራት እንዲፈርሱ ሲደረግ፣ በሌላ በኩል ደግሞ፣ ብዙ አድሃሪዎች “ይቅርታ” እየጠየቁ እንዲገቡና በግላጭ እንዲደራጁ ተደርጓል።
በዚህ ወቅት፣ አውቀውትም ይሁን ሳያውቁት፣ የለየላቸው አድሃሪዎችና የንኡስ ከበርቴው ደንፊ ቡድን ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ በአንድነት ተሰልፈው ነበር። የነዚህ አድሃሪ ኃይሎች የጊዜው የአንድነት መፈክር “ዘማቾች ወደ ከተማ! አድሃሪዎች ወደ ገጠር!” የሚለው ፀረአብዮታዊ መፈክር ነበር ቢባል ከእውነት የራቀ አይደለም።
የሰፊው ሕዝብ ድምጽ በጊዜው፣ “ዘማቾች ለሚያገለግሉት ሕዝብ የተሻለ የሚሰሩበትን፣ ሥራቸው የሚቀላጠፍበትን፣ የሚያጋጥሟቸውን ልዩ ልዩ ችግሮች በህብረትና በውይይት የሚፈቱበትን ብሄራዊ መድረክ ከመነፈጋቸው የተነሳ፣ በአሁኑ ሰዓት ዘመቻው ባልተደራጀ መልክ የመበተንና በዚሁም ላድሃሪዎቹ ሴራና ተንኮል እጅግ ያመቸ አዝማሚያ በመፍጠር ላይ መሆኑን ማንም ሊታዘበው የሚችል ሃቅ ነው። . . . ከዚህ አዋሳኝ መድረክ ላይ ብዙ መቆየት አይቻልም። ወይ እየተቀባበለ እዚህ የደረሰው አብዮት ለጊዜው ክፉኛ የመቀልበስ አደጋ ላይ ይወድቃል። ወይ ደግሞ አብዮቱ አዲስ እስትንፋስ አግኝቶ ግስጋሴውን ይቀጥላል።. . . . እዚህ ላይ መርሳት የማይገባን ቁም ነገር ግን፣ የታወጀውን ከሥራ ላይ ለመዋል ሆነ የጎደለውን ለማሟላት የነቃ፣ የተደራጀና የታጠቀ የሕዝብ ትግል አስፈላጊ መሆኑን ነው” በማለት የፃፈው የጊዜውን ውስብስብና አስጊ ሁኔታ በመመልከት ነበር። (ሰህድ፣ ቁጥር 30፣ 1.13.67)
በከተማም ቢሆን የጊዜው ሁኔታ ሰህድ “አዋሳኝ መድረክ” በማለት ከገለጸው የተለየ አልነበረም።
ለመጀመሪያ በትናንሽ ንግዶች፣ በትራንስፖርት፣ በዝቅተኛ የቢሮ ሥራና በመሳሰሉት መስኮች የተሰማራው ክፍል እጅጉን ተጨንቆ፣ የሚይዝ የሚለቀውን አጥቶ ነበር። የንግድ መዳከም የከተማ ኑሮ መወደድ የደሞዝ መስተካከል እና የከተማ ቦታና ትርፍ ቤቶች መወረስ. . .፣ይህንን ክፍል በጣሙን አደናግጠውት ነበር። በአንድ በኩል መጪዎቹ ቀናት ጨለማ የሆኑበት ተስፋውን ቆርጦ ነበር። በሌላ በኩል ደግሞ፣ የአብዮቱን መቀልበስ አሰፍስፎ ይጠባበቅ ነበር።
በወቅቱ ምን አልባት መጪዎቹ ቀናት ፈካ ብለው የታዩት ክፍል ቢኖር፣ ከፍተኛው የቢሮ ከበርቴ ብቻ ነበር። ይህ ክፍል በእነዚያ ወራት ውስጥ በነበሩት ትርምሶች በመጠቀም ለስልጣን የተቃረበ መስሎት እንደነበረ የሚያስረዱ ብዙ መረጃዎች አሉ። ለዚሁም፣ በተለይም እየተበራከቱ የመጡትን የቢሮክራሲ ሻጥሮች (ሳቦታዦች) በአንክሮ ማጥናት ነው።
የሆነው ሆኖ፣ እነዚህ ክፍሎች በተለይም በሃምሌው “የከተማ ቦታና ትርፍ ቤቶች” አዋጅ አከባቢ፣ በመጠኑም ቢሆን ተደናግጠው ነበር። ያለ የሌለን ሊወሰድብን ነው ብለው ፈርተው ነበር። አዋጁን ከሰሙ በኋላ ግን ሁኔታው እንዳሰቡት አስፈሪ ባለመሆኑ በየጓዳቸው ተመስገን ለማለት በቅተዋል። አብዮቱን የመቀልበስ፣ ወይም ሲቀለበት የማየት ተስፋቸው የመነመነ መስሏቸው ነበር። የኋላ ኋላም አዋጁንም ሸርተት እያሉ ለማምለጥ ልዩ ልዩ ሙከራዎችን አድርገዋል፤ በመጠኑም ችለዋልም።
በዚህ ወቅት፣ በተቀሩት የከተማ ህብረተሰብ ክፍሎች ውስጥ ይታይ የነበረውም ውዥንብር እጅግ ከፍተኛ ነበር።ባጠቃላይ ሲታይ፣ የኢትዮጵያ ሠራተኞች አቋም በመጀመሪያው ላይ ወደ ቅዋሜ እያዘነበለ የሚሄድ የገለልተኝነት አቋም ነበር። ምንም እንኳን ለህብረተሰባዊነትና ስለወዛደሩ መደብ ተደጋግሞ ቢገለጽና “እንግዲህ ፋብሪካ ሁሉ የናንተው ነው” እየተባለ ቢነገርም የኢትዮጵያ ሠራተኞች “ከኢትዮጵያ ህብረተሰባዊነት በቀጥታ ያገኙት ተጨባጭ ጥቅም በጣም የተወሰነ እንደነበር የታወቀ ነው። በተጨማሪም፣ የጠቅላላው ኢኮኖሚ መዋዠቅና እየናረ የሄደው የኑሮ ዋጋ፣ በገጠርም ሆነ በከተማ የአድሃሪዎች ማየልና የንኡስ ከበርቴው ደንፊ ቡድን የሚረጨው “አብዮታዊ” ፕሮፖጋንዳ፣ ሠራተኛው ሕዝብ ጠቅላላውን እንቅስቃሴ በቅዝቃዜ እንዲመለከተው አድርጎት ነበር። የሥራ አጡም ጥያቄዎች እየገፉ የመጡት በዚሁም ወቅት ነው።
እኛ እስከምናቀው ድረስ በዚህን ወቅት ውስጥ ከፍተኛ የሠራተኛ እንቅስቃሴ የታየው፣ በግል በተያያዙ የመመላለሻ ድርጅቶች ውስጥ ነበር። ሠራተኞች በግል የተያዙት የማመላለሻ ድርጅቶች እንዲወረሱ ሲጠይቁ፣ መንግሥቱ ደግሞ በወቅቱ ይህንን እርምጃ ለመውሰድ አልቻለም ወይንም አልፈለገም ነበር። በሃምሌ ወር “የከተማ ቦታና ትርፍ ቤቶች አዋጅ” ሲታወጅ በተደረገው ሰልፍ ላይ በግልጽ እንደታየው፣ ሰልፉ ለአዋጁ ከሰጠው ድጋፍ ይልቅ በግል የተያዙ የማመላለሻ ድርጅቶችን መወረስ የሚጠይቅ እንደነበረ ይታወሳል። በዚህም ጥያቄ ላይ ሲሆን፣ የኢ.ሠ.አ.ማ. “አዲሱ” አመራር አንዳችም የተቀናበረ የሠራተኞች እርምጃ ለማስወሰድ እንዳልቻለም የዚያኑ ያህል የታወቀ ነው።
የነቃውን የንዑስ ከበርቴ ክፍል በሚመለከተው በኩል ሁለት ዋና የመስመሮች ነበሩ። እንደተመለከትነው፣ አንደኛው ክፍል፣ ጠቅላላው ሁኔታ ለፀረአብዮት ኃይሎች አመቺነት እንዳለውና የፀረአብዮት አደጋም እንዳለ ሲገነዘብ፣ የንኡስ ከበርቴ ደንፊ ቡድን ደግሞ ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ብቸኛ የሆነውን ደርግ “ለማንበርከክ” የሚቻል መስሎ ታይቶት ነበር። የመጀመሪያው ጠቅላላውን የቅልበሳ አዝማሚያ ለመከላከል ዲሞክራሲያዊ መብቶችንና የሰፊውን ሕዝብ መታጠቅ ሲጠይቅ፣ ሁለተኛው (በዲሞክራሲያ አካባቢ የተኮለኮለው የንዑስ ከበርቴ ደንፊ ቡድን) ደግሞ፣ ጊዜው የደረሰ መስሎት ለፖለቲካ ስልጣን ያነፈንፍ ነበር። “ዘማቾች ወደ ከተማ” የሚለው መፈክሩና በነሀሴ 1967 ዓ.ም. የ“ኢ.ህ.አ.ፓ” መታወጅ ከእነዚህ ሁኔታዎች ሁሉ ተነጥሎ ሊታይ አይችልም።
ወደ ርእሳችን እንመለስና፣ ከግንቦት 1967 ዓ.ም፣ ጀምሮ የኢ.ሠ.አ.ማን አመራር የያዘው የንኡስ ከበርቴው ደንፊ ቡድን እንደነበር ተናግረናል። የዚህ የደንፊ ቡድን አመራር ሠራተኛውን የሚያስመታ፣ የሚበታተንና የሚያደክም መሆኑ በገሃድ የታየው መስከረም 1968 ዓ.ም. ላይ ነው።
እንደሚታወሰው ከመስከረም 8-11 ዓ.ም. የኢ.ሠ.አ.ማ. ልዩ ጠቅላላ ጉባኤ ይካሄዳል። መስከረም 14 ቀን የአየር መንገድ ሠራተኞች ማህበር ፀሐፊ የጉባኤውን ውሳኔ ለሰራተኞቹ ሲያድል ይያዛል። በዚህ ምክንያት በተነሳው መፋጠጥ ተኩስ ተከፍቶ ቢያንስ 7 ሠራተኞች ተገድለዋል፤ ከሰላሳ የማያንሱ ቆስለዋል።
“የሰፊው ሕዝብ ድምጽ” በአየር መንገድ ሠራተኞች ላይ የተፈጸመውን ፋሽስታዊ ግፍ በጊዜው አውግዟል። የኢትዮጵያ ወዛደሮች ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ነቅተው እንዲታገሉና በበለጠ እንዲደራጁ አሳስቧል። እንዳለውም፣ “የኢትዮጵያ ወዛደር የአብዮቱ ተስፋ፣ የኢትዮጵያ ግስጋሴና ብልጽግና ምሰሶ እሱው መሆኑን ተገንዝቦ፣ የነፃነቱን ተጋድሎ ያህል ቁም ነገር፣ በአፈ ወዳጆቹ በጥቂት ፀረሕዝብ አፈፃድቆች ተከሻ ላይ ጥሎ እንደማይተኛ በተደጋገመ ትግሉ አስመስክሯል። እያስመሰከረም ነው። በእርግጥ ፀረአብዮት ኃይሎች በሙሉ ከአገራችን ገጽ ድምጥማጣቸው ጠፍቶ፣ አዲስዋ ሕዝባዊት ኢትዮጵያ እስከምትመሰረተበት ጊዜ ድረስ፣ ይህ ተጋድሎ እየተፋፋመ ይሄዳል እንጂ በምንም አይነት አይገታም። ይህንን ለመግታት በወዛደር ወኪሎች፣ በአስተማሪዎች፣ በገበሬዎች፣ በተማሪዎች ላይ የሚዘንበውን ፀረሕዝብ አመጽ ለመቋቋም፣ የኢትዮጵያ ተራማጆች ወዳጁን ከጠላት በመለየት ትክክለኛ ፖለቲካ ተመስርተው አንድነታቸውን ለማጠናከር በትጋት መሥራት አለባቸው” (ሰህድ- ልዩ እትም፣ 16. 1. 68)
የንኡስ ከበርተው ደንፊ ቡድንስ ምን አለ? ለዚህ ጥያቄ መልስ የምናገኘው የእርሱ ልሳን የሆነውን “ዲሞክራሲያ” (ቅጽ 2፣ ቁጥር 19፣ መስከረም 25/1968) በጥሞና ስናነብ ነው።
“የኢትዮጵያ ላብአደሮችም” ይላል ይህ አምታችና አስመቺ “ነፃ” ጋዜጣ፣ “የኢትዮጵያ ላባደሮችም ለአራት ቀናት ያደረጉት አድማ ትክክለኛ ግቡን ባይመታም (?)፣ አንዳንድ መሰረታዊ ትምህርቶችንና ድሎችን (?)አቀናጅቷል። የመንግሥቱን ፍጹም አድሃሪነትና ፀረ ሕዝብነት ለማጋለጥ ረድቷል። (ገጽ 2፣ ስርዞችና ምልክቶች የተጨመሩ- ስህድ)
አንባቢው ይህንን አንቀጽ ተመልሶ ቢያነበው፣ የንኡስ ከበርቴውን ደንፊ ቡድን አድርባይነት እና አስመቺነት እንጂ፣ ከዚሁ የተለየን ነገር ሊረዳ አይችልም። ለመጀመሪያው “የኢትዮጵያ ላባደሮች ለአራት ቀናት ያደረጉት አድማ” ምን አይነት ባህሪዎች እንደነበሩት ቢነግረን በበለጠ ባወቀን ነበር። የሆነው ሆኖ፣ አሁንም ከዲሞክራሲያ እንደሚነግረን፣ ይህ “አዋጅ ትክክለኛ ግቡን አልመታም”። “ባይመታም” ይላል ዲሞክራሲያ ለጠቅ አድርጎ “አንዳንድ መሰረታዊ ድሎችን አቀዳጅቷል።”
የመስከረም 1968 ዓ.ም. የሥራ ማቆም እርምጃ የቱን ያህል የተወዛገበ እና የተተረማመሰ እንደነበር ሁላችንም እናውቃለን። ከዚህም በላይ ደግሞ፣ ብዙ ወዛደሮች በግላጭ የተመቱበትና የተገደሉበት ነበር። “ዲሞክራሲያ” ግን ይህን ሁሉ ረስቶ የሚያወጋን ስለመሰረታዊ ድሎች ነው። ሆኖም፣ የወዛደሩ መደብ በመስከረም 1968 ዓ.ም. ላይ የተቀዳጃቸውን ድሎች የትኞቹ እንደሆኑ እንኳን አይነግረንም። ምኑን ያህል “መሰረታዊ” እንደሆኑም ለመረዳት ተስኖናል።
በበኩላችን “የትኞቹ” ብለን በመጠየቅ የወዛደሮቹ በጥይት መቆላት? በግፍ መታሰር? የፋሽታዊውን አዋጅ መታወጅ?. . . በማለትም ብዙ ጥያቄዎችን ማንሳታችን ላይቀር ነው። የኢትዮጵያ ወዛደሮች “መሰረታዊ ድሎች” እነዚህ ከሆኑም አልቆልናል ለማለት እንደፍራለን።
ለአስመቺው የ“ዲሞክራሲያ” ቡድን የታየው “መሰረታዊ ድል” በእውነትም በወዛደሮች መገደል፣ መታሰርና በፋሽታዊው አዋጅ መታወጅ “የመንግሥቱ ፍጹም አድሃሪነትና ፀረሕዝብነት መጋለጥ” ነው። ዲሞክራሲያ እንደሚለውም “የፈሰሰው የወዛደሮቹ ደም የመንግሥቱን ‘ፋሽሽታዊት’ ለማጋለጥ ረድቷል።”
እንግዲህ አንባቢው ራሱን ይጠይቅ። የንዑስ ከበርቴው ደንፊ ቡድን የሚሰጠውን መመሪያ በትክክል ይረዳውና እርሙን ያውጣ። “የኢትዮጵያ ላባደሮች ሆይ! ጭፍን ፋሺዝም በኢትዮጵያ ላይ ነግሷል (ዲሞ. ቁ. 17፣ 15.3.67) ይህንንም ለመረዳት ከተሳናችሁ በ‘ፋሺስቱ መንግሥት’ ጥይት ተቆሉ። ያኔ ይገለጥላችኋል።”
የኢትዮጵያ ወዛደሮችና ተራማጆች ሁሉ በዚህ መመሪያ ስር ከተሰለፉ በእውነትም ያልቅላቸዋል። እነሱ የስርዓቱ “ፋሽስትነት እንዲገለጥላቸው” ደረታቸውን እየሰጡ ሲቆሉና ሲያልፉ፣ ምድረ አድሃሪዎችና የንኡስ ከበርቴ ደንፊ ቡድን፣ በኢትዮጵያ ሕዝቦች ላይ “መሠረታዊ ድላቸውን ይቀዳጃሉ”። በዚህም “እንቆቅልሽ”፣ አብዮቱ በአድሃሪው ሰፈር አሸናፊነትና በሰፊው የኢትዮጵያን ሕዝብ ተሸናፊነት ወደፊት ሊራመድ ነው ማለት ነው።
ስለሆነም፣ በመስከረም ወር 1968 ዓ.ም. ላይ በቅጡ ያልተደራጁትና ያልተዘጋጁት የኢትዮጵያ ወዛደሮች ለጊዜውም ቢሆን በንኡስ ከበርቴው ደንፊ ቡድን ተታለው በግላጭ ተመቱ። የመስከረሙ ግጭት በፀረዲሞክራቲኩ ደርግ አሸናፊነት፣ በኢትዮጵያ ወዝአደሮች ተሸናፊነት ተፈጸመ። ቢሆንም ይላል ዲሞክራሲያ፣ “የመንግሥቱን ፋሽስትነት ለማጋለጥ ረድቷል።”
በዲሞክራሲያ አካባቢ ያኮለኮለው የንኡስ ከበርቴዎች ደንፊ ቡድን ዓላማ ይህ ብቻ ነበር። በዚያን ወቅት የኢትዮጵያ ወዛደሮች የቀሰሙት ትልቅ ትምህርት ግን፣ የሚያዛልቃቸው የነቃ፣ በወጉ የተደራጀና የተዘጋጀ ትግላቸው እንጂ፣ የንኡስ ከበርቴ ድንፋታ አለመሆኑን ነው። ሌላው በዓይናቸው ያዩት እውነት ደግሞ፣ እነሱ ሲጋፈጡና በግላጭ ሲመቱ፣ አምታቺው ቡድን ለራሱ ብቻ መሽጎ እንደነበር ነው።
ከዚህ በኋላ ይኸው አስመቺና አምታች ቡድን በኢትዮጵያ ሠራተኞች ስም፣ “የኢ.ሠ.አ.ማ. የትግል ጥሪ” (ቀን የሌለበት ጥሪ) ሲል ቆየት ብሎም “ትግላችን ይቀጥላል” (25.2.68) ቢል፣ ለጠቅ አድርጎም “የላብአደር ትግል ትንሳዔ” (26.2.68) ቢልና በመጨረሻም “ድላችን በጣም ቅርብ ነው” /3.3.68/ እያለ ቢደነፋ፣ የኢትዮጵያ ሠራተኞች ደግሞ “ጥሪው” ለአድሃሪዎች፣ “ትንሣኤው እና ድሉም” የአድሃሪዎቹ እንደሆነ በቅጡ እየተገነዘቡለት ሄደዋል።
እኛም ወደ መጨረሻው ወቅት ተሻግረን፣ ይኸው የንኡስ ከበርቴ ደንፊ ቡድን፣ በዛሬው ወቅት ደግሞ፣ የኢትዮጵያን ሠራተኞች ትጥቅ ለማስፈታት “ልዩ ልዩ ዘዴዎች” ሲጠነስስ እንይዘዋለን። እንዳከፋፈላችን ይህ ለጊዜው የመጨረሻው ወቅታችን ሰባተኛው ወቅት መሆኑ ነው። እሱም ከህዳር 26 ቀን 1968 ዓ.ም. ወዲህ ያለው ጊዜ ነው።
VII
እንደሚታወሰው፣ ህዳር 25 ቀን ፋሽስታዊው አዋጅ ይነሳል። ከ100 በላይ የሚሆኑ የሠራተኛ ማህበራት መሪዎች ይፈታሉ። ህዳር 26 ቀን 1968 ዓ.ም. “የሠራተኛ ጉዳይ አዋጅ” ይታወጃል። በተከታታይም ብዙ ተራማጅ አዋጆች ይታወጃሉ። ጠቅላላ አቅጣጫው የአብዮቱን ወደፊት መራመድ የሚያመለክት ሲሆን፣ እውነተኞቹ ተራማጆችም “የተደፋውን አንገታቸውን” ቀና በማድረግ ላይ ነበሩ። በዚሁ አንጻር ግን፣ መሳፍንቶቹም “ማርክሲስቶች” ሁነውና (?) ተኳኩለው ብቅ ብለዋል። አወናባጁ የንኡስ ከበርቴ ደንፊ ቡድንም ከማርክስና ከኤንግሊስ በላይ ማርክሲስት፣ ከሌንንም በላይ ሌኒኒስት ሆኖ ቀርቦናል።
የመሳፍንቶቹ “ማርክሲስቶች” በህዳር ወር ባወጡት ጋዜጣቻው፣ “የሠራተኛ ጉዳይ አዋጅ” የታወጀው “ፋሺዝምን ለማደራጀት ነው” ሲሉን፣ አወናባጁ የንኡስ ከበርቴ ደንፊ ቡድን ደግሞ፣ “ላባደር” በተባለው “ነፃ” ጋዜጣው አማካኝነት “ታገሉ እንጂ አትደራጁ” ይለናል።
ወደነዚህ አወናባጆች ከመነሻገራችን በፊት ግን፣ በመጀመሪያ ረገድ አዋጁ የሥራ ማቆምን መብት በቀጥታና ግልጽ በሆነ ቋንቋ አለመግለጹ፣ የአዋጁ ጉልህ ጉድለት እንደሆነ እንግለጽ። በዚህ አንጻሩ አዋጁ ፀረወዛደር ነው። “ድርጅት” የተባለውም ነገር የተብራራ አይደለም። ለምሳሌ፣ ዛሬ በብሔራዊ ሀብት ልማት ሥር ያሉት ኮርፖሬሽንስ ሁሉም ድርጅት ናቸው። እነዚህ ኮርፖሬሽንስ ደግሞ በውስጣቸው ብዙ ‘ድርጅቶችን’ አቅፈዋል። ዛሬ የኢትዮጵያን ሠራተኞች በኮርፖሬሽንስ አንጻር ተደራጅ ማለት ግን አትደራጁ የማለት ያህል ነው። በዚህ አንጻር ፀረድርጅት መሆኑ ግልጽ ነው።
እንደዚሁም፣ “አንድ ድርጅት. . . ሥራውን ለጊዜው በከፊል ሆነ በሙሉ ለማቆም ወይም ጨርሶ በከፊል ሆነ በሙሉ ለመዝጋት ያሰበ እንደሆነ፣ እርምጃውን ከመውሰዱ ከስድሳ /60/ ቀን በፊት ለሥራተኛ ጉዳይ ጽ/ቤት ማስታወቅ አለበት” የሚለው አንቀጽ ሠራተኛውን ሕዝብ የሚደቁስ፣ አሰሪውን ወገን የሚረዳ አንቀጽ ነው። በመጨረሻም፣ “(የማህበር) ውሳኔዎች በሥራ ላይ በሚሉበት ጊዜ፣ በአፈጻጸሙ ላይ (?) ማንኛውም ሰው ጉድለት ቢያደርስ፣ በኃላፊነት የሚጠየቀው ውሳኔው ያስተላለፈው ጉባኤ ሳይሆን፣ በግል በአፈጻጸሙ ላይ (?) የተካፈሉ (!)ሰዎች ወይም ሰው ነው” የሚለውን አንቀጽ በግልጽ ከፋፋይና ማህበራቱን የሚያክም የሚያስፈራራም አንቀጽ ነው።
እነዚህ አይናቸውን አፍጥጠው የሚታዩት የአዋጁ ፀረ ወዛደር አንቀጾች ሲሆኑ፣ የግላዊነት “ማርክሲስቶች” እና “ላብአደር” ግን ብዙ ብዙ አይተዋል። ስለሆነም፣ ዛሬ ለወዛደሩ ያላቸው የአንድነት ምክር እና “አብዮታዊ” መመሪያ “አትደራጅ” የሚለው ነው።
መሳፍንቶቹ በፖስታ የሚላላኩት “ቅስቀሳ” እንደሚለው ከሆነ፣ በህዳር 26 ቀን 1968 ዓ.ም. አዋጅ መሠረት መደራጀት “ፋሺዝምን ማጠንከር ነው”። ለዚሁም ወንጌላቸውን ትተው ማርክስ እና ሌሊንን እያነሱ ያፈርጧቸዋል። ማርክሲዝም- ሌኒኒዝምን ከመቸው ቀስመው እንዳበቁ ባናውቅም፣ “የማርክሲዝም- ሌኒኒዝም ፍልስፍናን የቀሰሙ በአንድ ራስ ሁለት ምላስ የሌላቸው ተራማጆች ሁሉ የሚያምኑበትን” ሲነግሩን እንደሚከተለው ይላሉ።
“መሰረታዊ ሕዝባዊ አብዮት ሳይፈጸም ኢንዱስትሪና የንግድ ድርጅቶችን ወደ መንግሥት ማዞር ከግላዊ የከበርቴ ሥርዓት ወደ መንግሥታዊ የከበርቴ ስርዓት /እስቴት ካፒታሊዝም/ መሸጋገር ስለሆነ፣ ለአምራቾች ማለት ለሠራተኞች ምንም አይነት ቋሚ ለውጥና ጥቅም ሊያስገኝ አለመቻሉ የተረጋገጠ ነው።”
የመሳፍንቶቹ “ማርክሲስቶች” ምስኪንነት ገሃድ ነው። ለመጀመሪያው፣ መሳፍንቶቹ እንደሚያምኑት ያው ምጽአታቸው ካልደረሰ በስተቀር፣ “አብዮት” ተፈጸመ ማለት የወንጌሉ ስብከት እንዲሁ እንጂ፣ ማርክሲዝም አይደለም። አብዮት የማያቋርጥ ክንውን ነውና። ሁለተኛም፣ እንደሚታወቀው አብዮት የሚጀምረው፣ በመጀመሪያ የኢንዱስትሪና የንግድ ድርጅቶችን ተረክቦ አይደለም። ወይንም ደግሞ፣ አብዮት “የተፈፀመ” እለት ፊሽካ ተነፍቶ “የኢንዱስትሪና የንግድ ድርጅቶችን” በፊርማ በመረካከብ አይደለም። እነዚህ እርምጃዎቹ ሁሉ የአብዮታዊ ትግል አንቀሳቃሽም፣ እሴቶችም ናቸው።
ለመሳፍንቶቹ “ማርክሲስቶች” ይቺ እውነት ልትገለጥላቸው አትችልም። አንጋጠው የሰማያትን ተአምር ይጠብቁ እንዲሁ እንጂ፣ የኢትዮጵያ ሕዝቦች እንደው መሬቱንም ፣እንዱስትሪውንም. . . በትግላቸው የራሳቸው ለማድረግ ተነስተዋል። “አብዮቱ እስኪፈጸም ድረስም” አይጠብቃቸው።
እንግዲህ የመሳፍንቶቹ “ማርክሲስቶች” ይህንን ዲያሌክቲክስ ከወንጌላቸው ውስጥ ባያገኙት ጨርሶ አይደንቀንም። ከዚህም አልፈው “አብዮቱ እስኪፈፀም ድረስ መሬታችንንም፣ኢንዱስትሪያችንንም፣ የንግድ ድርጅቶቻችንንም. . . አትንኩብን” ሲሉን ግን፣ አታወናብዱን፤ ብዝበዛችሁ አንገፍግፎናል፤ አንጠብቅም እንላቸዋለን። ከዚህም አልፈው “አትደራጁ” ሲሉን ደግሞ፣ ለማን እንዲበጅ? እናንተ ተደራርታችሁ የለም ወይ? ብለን እንጠይቃቸዋለን።
የንኡስ ከበርቴው ደንፊ ቡድን አቋምም ከመሳፍንቶቹ የተለየ አይደለም። አሁን የምንመለከትበት “ላብአደር” የተባለውን “ነፃ” ጋዜጣውን ነው። /“ላብአደር”፣ ቁ.27፣ታህሳስ 18. 1968 ዓ.ም. ተመልከት።/
እነዚህ አወናባጆች በዚህ ቁጥራቸው ውስጥ ብዙ “አብዮታዊ” ቃላትን ወርውረዋል። ነገር ግን፣ በጥሞና የሚያነበው ሰው ወዲያውኑ የሚረዳላቸው ፍሬ ነገር፣ “ታገሉ ግን አትደራጁብን” የሚለውን ፀረ ወዛደር መፈክራቸውን ነው።
እንደነርሱ አነጋገር፣ “ፋሽታዊው የ‘ምርጥ’ መኮንኖች መንግሥት. . . እኛን (?) ላብአደሮችን እግር ተወርች ማሰርያ ሰንሰለቱን ባወጣው ህግ አጥብቋል። . . . ላብአደሮች ከትግላችን በስተቀር ሌላ ጋሻ፣ ሌላ መከታ የለንም” (ገጽ 1፣ ስርዞችና ምልክት የተጨመሩ – ሰህድ) ስለሆነም “እንታገል”።
ለመጀመርያው፣ “እኛን” እያሉ ሲናገሩ፣ ምድረ ንኡስ ከበርቴዎች በምን አይነት ተአምር “ላብአደሮች” እንደሆኑ አልገባንም ነበር። ብቻ ታሪክ ደጋግሞ እንዳረጋገጠው፣ እንደዚህ ያለው “ተአምር” ለንኡስ ከበርቴ ደንፊዎች ብቻ የታደለ የማወናበጃ ዘዴ በመሆኑ ብዙም አልተደነቅንም። ሆኖም፣ ለጠቅ አድርገው፣ የኢትዮጵያን ላብአደሮች “ከትግላቸሁ በስተቀር ሌላ ጋሻና መከታ የላችሁም” ሲሏቸው፣ ከንኡስ ከበርቴው ደንፊ ቡድን ጋር እንድንስማማ እንገደዳለን። በጣም ጥሩ እንላለን።
ነገር ግን፣ እኮ እንዴት ነው የምንታገለው? የሚለውን ጥያቄ በማቅረባችን፣ የቃላቶቹን ባዶነት ወዲያውኑ ተረዳን። እነ “ዲሞክራሲያ” በዚህ ጽሁፋቸው ውስጥ በልዩ ልዩ አገላለጽ “ታገሉ፣ ታገሉ. . .” ሲሉን እንጂ፣ ተደራጁ ሲሉን አንሰማቸውም። “ተጋድሎ፣ አብዮታዊ ትግል፣ የትግል ጎዳና፣ ታጋይ፣ የትግል ጥሪ፣ አብዮታዊ ተገድሎ፣ ቆራጥነት፣ ትግላችን፣ መስዋእትነት፣ ታግለን፣ ስንታገል የኖርን፣. . .” የሚሉት ቃላት በየመስመሩ ሰፍረዋል። ዞሮ ዞሮ “ከትግላችሁ በስተቀር ሌላ ጋሻ፣ ሌላ መከታ የለንም” ማለት ነው።
ታላቁ ሌኒን የዓለምን ወዝአደሮች ያስተማራቸው ደግሞ፣ ከድርጅቶቻቸው በስተቀር ሌላ መከታ እንደሌላቸው ነው። ወዛደሮች ተደራጅተው እንዲታገሉ እንጂ፣ ተበታትነው እንዲታገሉ አይደለም። ከዚህ በታች የምንጠቅሰው ሌኒን እንደሚያስተምረን፣ ላብአደሮች በሠራተኛ ማህበሮች ውስጥ መደራጀታቸው ለንቃታቸው የሚያስፈልጋቸው የማይታለፍ ት/ቤት እንደሆነ ነው።
“. . .የላባአደሩ መደብ በየትም ዓለም ቢሆን የሚያድገው በአንድ ወገን በሠራተኛ ማህበራቱ፣ በሌላ ወገን ደግሞ፣ በሠራተኛ ማህበራትና በፓርቲው መካከል ባሉት የመደጋገፍ እርምጃዎች ነው። ከዚህ ውጪ የተከናወነና የሚከናወን አንድም ዓይነት የወዛደር እድገት የለም “(ሌኒን፣” “የግራ ክንፍ ኮሙኒዝም- የጨቅላነት በሽታ”፣ ሙሉ ሥራዎች፣ ቅጽ 31፣ ገጽ 50)
እንግዲህ፣ “ከትግላችን በስተቀር ሌላ ጋሻ” የለንም የሚል “ታጋይ”፣ ለመታገል መደራጀት እንደሚያስፈልግ ወዲያውኑ ካልገለፀ፣ ባዶ ቃላትን ብቻ እንደወረወረ መታወቅ አለበት። የ“ላብአደር” አዘጋጆች የመደራጀቱን ጉዳይ የሚዘሉት፣ እንዲያውም አልፈው ተርፈው የሚቃወሙት የሕዝቡን ትግል መልክ አሳጥተው ለማዘበራረቅ ሲሉ እንጂ፣ ጉዳዩንስ አጥተውት አይደለም። ፀረ ወዛደር ኃይሎች የምንላቸውም ስለዚሁ ምክንያት ነው። የተደራጁ ወዛደሮች ያጠፏቸዋል። ያልተደራጁትን ወዛደሮች ግን በቀላሉ ለማወናበድ ይችላሉና ነው።
እንደተመለከትነው፣ በዚህ ጽሁፋቸው ውስጥ ስለ ትግል ብዙ ብዙ ያወራሉ። ነገር ግን፣ መልሰው ደግሞ “የሠራተኛው ጉዳይ አዋጅ አድሃሪ ነውና፣ ፋሽስታዊ ነውና በሱ መደራጀት የለብንም” ይላሉ። “ሰብአዊ መብቶችን፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጥቅሞችን ከፋሽስቶች እንደምጽዋት አንቀበልም” (ገጽ1) የሚለውን የነዚህን ሰዎች ድንፋታ ያነበበ ሁሉ ብዙ ብዙ እንዲጠይቃቸው መገደዱ የማይቀር ነው። የሚያገኛቸው መልሶች ግን ከአሁኑ ግልጽ ናቸው።
- “የኢትዮጵያ ጭሰኞች! ‘የመሬት ላራሹን’ አዋጅ ከፋሽስቶች እንደምጽዋት አትቀበሉ። ታገሉ!”
- “ዘማቾች! ገበሬዎችን አታደራጁ። ወደ ከተማ መጥታችሁ ታገሉ!”
- “የኢትዮጵያ ወዛደሮች! ‘የሠራተኛን ጉዳይ አዋጅ’ ከፋሽስቶች እንደ ምጽዋት አትቀበሉ። ታገሉ!”
- “የኢትዮጵያ ከተሜዎች! ‘የከተማ ቦታንና የትርፍ ቤቶችን አዋጅ’ ከፋሽስቶች እንደ ምጽዋት አትቀበሉ። ታገሉ!”
- “የኢትዮጵያ ሕዝቦች! ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጥቅሞችን ከፋሺስቶች እንደ ምጽዋት አትቀበሉ። ታገሉ!” . . . . ወዘተ።
“ታገሉ፣ ታገሉ፣ ታገሉ፣. . . ግን አትደራጁብን። የአወናባጆቹ ታክቲክ በአጭሩ ይኸው ነው።
እንግዲህ ከመንገሻ ስዩምና ከኢምፔሪያሊስቶች አንስቶ እስከ “ዲሞክራሲያ”፣ “ላባደር” እና “አብዮታዊ ወጣት” ድረስ ያሉት ምድረ አድሃሪዎች እንደ ጦር የሚፈሩት ትልቁ ጠላታቸው የነቃ፣ የተደራጀና የታጠቀ ሕዝባዊ ትግል እንደሆነ በቅጡ ገብቶናል። እዚህ ወጥመዳቸው ውስጥ መግባት ተበታትኖ ድል መመታት ነው።
እውነተኛ ተራማጆች የሚያምኑት አዋጁ ሺ ጊዜ አድሃሪ ቢሆን እንኳን፣ ይህንኑ አድሃሪነቱን ሊሽረው የሚችለው የነቃው እና የተደራጀ የወዛደር ትግል ብቻ እንደሆነ ነው። ይህ እውነት “ታገሉ” ብቻ እያለ በሚደነፋው የንኡስ ከበርቴ ውር ውር ሊሻር አይችልም። የኛ የንኡስ ከበርቴ ደንፊዎች፣ በአንድ ወገን “የፋሺስቶች አዋጅ ነውና አትደራጅ” እያሉ፣ በሌላ በኩል ደግሞ፣ “ትግልህን አፋፍም” ሲሉ ወዛደሩን ለተደራጁ አድሃሪዎች “ለጭዳ ለማቅረብ” በማዘጋጀት ላይ እንደሆኑ መታወቅ አለበት። “ታገሉ፣ ታገሉ. . .” እያለ የሚጮኸው የንኡስ ከበርቴ ደንፊ ቡድን ዛሬ መለስ ብሎ “የላብአደሮች መሪዎች ለጭዳ የሚቀርቡ ከብቶች አይደሉም” ቢለን፣ በመስከረም ምን ሰራችሁ ብለን መጠየቃችን የማይቀር ነው።
በሌላ በኩል ደግሞ፣ እነዚሁ ደንፊዎችና አወናባጆች የኢትዮጵያን ሕዝቦች መራራ ትግል የቱን ያህል እንደሚያንቋሽሹና እንደሚያጣጥሉ ግልጽ ሊሆንልን ይገባል። ይሁንናም ለመረዳት፣ የኢትዮጵያ ወዛደሮች “የሠራተኛ ጉዳይ አዋጅ” እንዲታወጅ የቱን ያህል እንደታገሉ ብቻ መመልከቱ ይበቃል። እነ “ዲሞክራሲያ” እንደሚሉት ግን አዋጁ “ምጽዋት” እንጂ፣ የትግል ውጤት አይደለም። ይህ ትንተና የንኡስ ከበርቴ ደንፊ ቡድን የተካነው ልዩ የማወናበድ ችሎታ እንጂ፣ ከሰማያት “የተመጸወተው” ልዩ የድንቁርና ማህተሙ እንዳልሆነ ግልጽ ሊሆንልን ይገባል።
“አዋጁ ሺህ ጊዜ አድሃሪ ቢሆን እንኳ” ብለናል። ሌኒን ደግሞ “እንኳን ሳይደራጁ ቀርቶ፣ ተደራጅተውም በእርግጥ አድሃሪ የሠራተኛ ማህበሮች ቢሆኑ እንኳን” ይለናል፣ “የማርክሲስቶች ተግባር እነዚህ አድሃሪ ማህበራት ውስጥ ገብቶ መሥራት ነው።”
“በጣም የተማሩት፣ ጉረኞችና ስለ ኣብዮት ሲናገር ፍርሃት የሚውጣቸው የጀርመን ግራዎች፣ ኮሚኒስቶች በአድሃሪ የሠራተኛ ማበራት ውስጥ ገብተው መታገል የለባቸውም በማለት የሚያካሄዱት ውይይት አስቂኝና በጨቅላዎች ድንቁርና የተጨመላለቀ ውይይት ነው። እነዚህ አድሃሪዎች ከዚህም አልፈው ኮሚኒስቶች እንዲህ አይነቱን ትግል መተው አለባቸው፤ ከአድሃሪ የሠራተኛ ማህበራት መውጣትና የራሳቸውን ፍጹም አዲስ የሆነ የሠራተኞች ማህበር መፍጠር አለባቸው ሲሉን፣ የምንረዳቸው ጉረኝነታቸውን፣ ጨቅላነታቸውንና አስቂኝነታቸውን ብቻ ነው” (ሌሊን፣ “የግራ ክንፍ ኮሚኒዝም- የጨቅላነት በሽታ”፣ ሙሉ ሥራዎች፣ ቅጽ 31፣ ገጽ 49)
የወዛደሩን የትግል አቅጣጫ በሆነ ባልሆነ “ቲዎሪ” ሊያወናብዱ ለተነሳሱት የጀርመን “ግራዎች” ሌኒንን የሰጣቸው መልስ ከዚህ በላይ የተመለከትነውን ነው። ዛሬ የኢትዮጵያን ወዛደሮች ተደባልቀው ሊያወናብዱ ለተነሳሱት ለኛ “ግራዎች” የምንሰጣቸው መልስም ከዚሁ የተለየ ሊሆን አይችልም። የኛዎቹ አወናባጆች ዛሬ የኢትዮጵያን ወዛደሮች የሚመክሩት፣ በተደራጀ ተጋድሏቸው ያገኟቸውን ድሎች በመመርኮዝ፣ ለመጭው ትግል ደግሞ፣ በበለጠ እንዳይደራጁና እንዳይታገሉ ነው። ስለሆነም፣ ዛሬ የኢትዮጵያ ሕዝቦች በበለጠ እንዲደራጁ እንደሕይወት እስትንፋስ የሚያስፈልጉንን ሰብአዊ መብቶች እንኳ፣ በመቃወም፣ “ሰብአዊ መብቶችን. . . . ከፋሺስቶች እንደምጽዋት አንቀበልም” ይሉናል።
የነዚህን አድሃሪ ቡድኖች ያወናባጅነት ታክቲክ አንባቢ ልብ ይበለው። እነሱ “ሰብዓዊ መብቶችም” ባይኖሩ፣ በፓስታ እየተላላኩ ይደራጃሉ። እነሱ “ሰብአዊ መብቶችም” ባይኖሩ፣ በተካኑት የማወናበጃ ዘዴያች እያወናበዱና እያስፈራሩ “ፓርቲም ነን” ብለው ተደራጅተዋል። የኢትዮጵያ ሕዝቦች ግን መታገሉ ብቻ እንጂ፣ መደራጀቱን ለእነሱ ይተዉላቸዋል። ከዚህስ በኋላ? ከዚህ በኋላ እነሱ ተደራጅተው የሚንገበገቡለትን የፖለቲካ ስልጣን ይይዛሉ። የኢትዮጵያ ሕዝቦች ደግሞ፣ ታግለውና ታግለው ባዶ እጃቸውን “ነፃ ይወጣሉ”። ለጊዜውም ቢሆን ያልቅላቸዋል።
ይህንን ያድሃሪዎች የተባበረ ጥሪ ለማክሸፍ የሚቻለው፣ ሌኒን እንዳለው፣ የኢትዮጵያ ወዛደሮች፣ የታወጀው “የሠራተኛ ጉዳይ አዋጅ” አድሃሪ ቢሆንም እንኳ፣ በሱም ስር ቢሆን ተደራጅተው ለመታገል ሲነሳሱ ነው። የኢትዮጵያ እውነተኛ ተራማጆችም፣ በ“አደሃሪው” አዋጅ ስር የሚደራጁት የሠራተኛ ማህበራት ሺ ጊዜ አድሃሪ ቢሆኑ እንኳ፣ ከነገው ውስጥ ገብተው የኢትዮጵያን ወዛደሮች ለማደራጀት ሲያግዙና ሲረዱ ነው። ትክክለኛውና አብዮታዊ የትግል መስመር ይህ ብቻ ነው።
አሁን ደግሞ፣ አወናባጁ የ“ዲሞክራሲያ” ቡድን የሚዋኝበትን ሌላ ማጥ እንመለከትና የአንባቢን ፍርድ እንጠይቅ። አሁንም የምንናገረው ያንኑ “ላብአደር” የተባለው “ነፃ” ጋዜጣ ነው።
በግንቦት ወር 1967 ዓ.ም. “እውነተኛ መሪዎችን በሚገባ መርጠናል” የሚለን “ላባደር” (ገጽ 2) ትንሽ አለፍ ብሎ ደግሞ፣ “የጭቁን መደቦችን ዲሞክራሲያዊ መብቶች ረግጦና አፍኖ ምርጫ አካሂዱ ማለት አሉባልታ ነው” (ገጽ 3) ሲል ይሰማል።
አንባቢው እንደሚረዳው፣ እነዚህ ከ“ላባደር” የወሰድናቸዉ ጥቅሶች ራሳቸውን የቻሉ ታሪኮች ናቸው። ለመጀመሪያው “አሉባልታው” ከየት ላይ እንደሆነ እንኳን ግልጽ አይደለም። ምናልባት “ፌዝ ነው፤ ቀልድ ነው፤ ለማወናበድ ነው . . .” ለማለት ተፈልጎ ይሆናል። ለጠቅ አድርገው፣ በግንቦት ወር 1967 ዓ.ም. ምርጫ ላይ፣ “እውነተኛ መሪዎቻችንን በሚገባ መርጠን ተከትለናል” ሲሉን ግን፣ በዚያን ጊዜ የነበሩንን “ዲሞክራሲያዊ መብቶች” እንድናጠያይቅ እንገደዳለን።
የኢትዮጵያ ሕዝቦች ሁሉ እንደሚያውቁት፣ ፀረዲሞክራቲኩ ደርግ መስከረም 2 ቀን 1967 ያወጀውን ፀረዴሞክራቲክ አዋጅ እስከ ዛሬ ድረስ አላነሳውም። ይህ አዋጅ እንዲነሳ ገና ብዙ መደራጀትና ብዙ መታገል አለብን። ዛሬ “የጭቁን መደቦችን ዲሞክራሲያዊ መብቶች ረግጦና አፍኖ ምርጫ አካሂዱ ማለት አሉባልታ ነው” የሚለን “ላብአደር” ግን፣ በግንቦት ወር 1967 ዓ.ም. ላይ “እውነተኛ መሪዎቹን በሚገባ መርጦ ተክቶ” ነበር።
ከእንግዲህ የግንቦቱን እንቆቅልሽ ለእኛም ግልጽ ሊሆንልን ይገባል። በተነገረን መሰረት ለኢትዮጵያ ሕዝቦች ሁሉ እስከ ዛሬ የተነፈጓችው ዲሞክራሲያዊ መብቶች፣ እኛም በማናውቀው ምስጢር በግንቦት ወር 1967 ዓ. ም. ላይ ለንኡስ ከበርው ደንፊ ቡድን ብቻ ተሰጥቶ ነበር። ስለሆነም፣ በግንቦት ወር 1967 ዓ.ም. ላይ “እውነተኛ መሪዎቹን በሚገባ መርጦ ለመተካት” ችሎ ነበር። የኢትዮጵያ ወዛደሮችም በንኡስ ከበርቴው ደንፊ ቡድን አመራር ስር ወድቀው ነበር። የንጉስ ከበርቴው ደንፊ ቡድን፣ ዛሬ መለስ ብሎ “መሪዎቻችን እስካልተፈቱ. . . ድረስ፣ ምንም አይነት ምርጫ ሊካሄድ አይችልም፤ አናደርግምም” (ገጽ 3) ቢለን፣ እኛ ደግሞ ይህ ሁሉ በተደራጀ ትግል እንጂ፣ “በምጽዋት” አይገኝም በማለት እንመልስለታለን።
ይኸው የንጉስ ከበርቴ ደምፊ ቡድን ለኢትዮጵያ ወዛደሮች የላከላቸው የትግል ጥሪ ግን የሚከተለው ነው :-
“1/ መሪዎቻችን እስካልተፈቱ ድረስ ምርጫ አናደርግም።
2/ ላብአደሩን ያለአንዳች ተጽእኖ ማደራጀት እስካልተቻለ ድረስ ምርጫ እናደርግም።
3/ መሰረታዊ ጥያቄዎቻችን እስካልተፈጸሙ ድረስ ምርጫ እናደርግም። . . .”
ተራማጅ ነኝ የሚል ግለሰብና ድርጅት ሁሉ የታሰሩት ተራማጆች እንዲፈቱ፣ በላባደሮች ላይ የሚደረጉ ተጽዕኖዎች እንዲነሱ፣ የላብአደሩ መሰረታዊ ጥያቄዎች እንዲፈጸሙ ይታገላል። ነገር ግን እውነተኛ ተራማጆች ደግሞ፣ ያልተደራጀ ትግል ዘላቂነት እንደሌለው ያውቃሉ። በዚህ አንጻር “ምርጫ አናደርግም” የሚለው መፈክር፣ አሁንም በግላጭ ለማስመታትና ለመበታተን የታሰበ ፀረወዛደር መፈክር እንጂ፣ አንዳንድ ሰዎች ሊያምኑ እንደሚፈልጉት አብዮታዊ መፈክር አይደለም። የኢትዮጵያ ወዛደሮች አሁንም ወገናቸው መስሎ ባቀረባቸው የንኡስ ከበርቴ ደንፊ ቡድን ተታለው ሳይደራጁ ሲቀሩ ከታላቅ ስህተት ውስጥ እንደወደቁ ካሁኑ መገንዘብ አለባቸው። አሁንም የሚያዛልቃቸው የነቃ፣ የተደራጀና በቅጡ የተዘጋጀ ትግላቸው እንጂ፣ የንኡስ ከበርቴው ደንፊ ቡድን ድንፋታ አይደለም። መደራጀት፣ መታገል፤ በበለጠ መደራጀት፣ በበለጠ መታገል፤ አሁንም በበለጠ መደራጀት፣ አሁንም በበለጠ መታገል. . . . የጊዜው ጥሪ ይህ ነው።
ከንግዲህ አንዲት የመጨረሻ ነጥብ ብቻ እናነሳና ይህንን ሰባተኛ ወቅት ለጊዜው እንደምድመው።
“መሪዎቻችሁን አትምረጡ፤ አትደራጁብን፤ ብቻ ታገሉልን” የሚለው “ላባደር”፣ በጠቀስነው ጽሁፍ የመጨረሻ አንቀጽ ውስጥ ደግሞ፣ “ለሁሉም ዋስትናና አማራጭ የሚሆነንን ከጭቁን መደቦች የሚውጣውን ጊዜያዊ ሕዝባዊ መንግሥት መምረጥ ነው” ብሎናል። ይህ እንግዲህ፣ የሠራተኛ ማህበራችሁን አቋቁማችሁ አትደራጁ፣ እንደተበታተናችሁ እኛን ምረጡ ለማለት ነው።
በዚህ ውስጥ ያለውን ቅራኔ አምባቢው ራሱ ይረዳዋል። በተጨማሪም ስለ ጊዜያዊ ሕዝባዊ መንግሥት ጥያቄ ሰህድ ቁ. 35 ማንበብ ነው። ዛሬ ልናወሳው የምንፈልገው የመጨረሻ ነገር ቢኖር ግን፣ የመንገሻ ስዩም- ነጋ ተገኝ- እያሱ መንገሻ- አሊ ሚራህ ፊውዶፋሺስት ቡድንም፣ የጊዜው ዋና ጥያቄ “የብሄራዊ እርቅ መንግሥት እንዲመረጥ መታገል ነው” እንደሚሉንም ብቻ ነው። ብራቮ! አድሃሪዎች ብራቮ!
ማጠቃለያ
– የኢትዮጵያን ወታደሮች ገና በጨቅላነታቸው የተናነቋቸው አብይት ጠላቶች ፊውዳሊዝም፣ ቢሮክራሲያዊ ካፒታሊዝም እና ኢምፔሪያሊዝም ናቸው። እነዚህ ሦስቱ ዛሬም ቢሆን የኢትዮጵያ ጭቁኖች አበይት ጠላቶች ናቸው።
– የኢትዮጵያ ወዛደሮች፣ ከልጅነት ጊዜያቸው አንስቶ ባላቸው አቅም ሁሉ እየተጋገዙና እየተደጋገፉ መብታቸውንና ጥቅማቸውን ለማስከበር ብዙ መራራ ተጋድሎዎችን አድርገዋል።
– ሆኖም፣ ከሞላ ጎደል የተቀነባበረ ትግል ለማካሄድ የቻሉት የሠራተኛ ማህበራትን መመስረት ከጀመሩበት ጊዜ አንስቶ ነው።
– በተለይም ከ1955 ዓ.ም. ወዲህ /ኢ.ሠ.አ.ማ. ከተመሠረተ ወዲህ/፣ የኢትዮጵያ ሠራተኞች ትግል በሁለት አቅጣጫ የተመራ ነበር። የኢትዮጵያ ሠራተኞች በእነዚህ ዓመታት ሁሉ የታገሉት፣ በአንድ ወገን ከአሰሪዎች ጋር ሲሆን፣ በሌላ በኩል ደግሞ ከኢ.ሠ.አ.ማ. አመራር ጋር ነበር።
– የኢትዮጵያ ሠራተኞች “ከመሪዎቻቸው” ጋር ከሚያደርጉት ትግል እስከ ጊዜያችን ድረስ በሦስት ደረጃዎች አልፈዋል። የመጀመሪያው ለነጋሲው አገዛዝና ለኢምፔሪያሊስቶች ካደረው ከበየነ ሰለሞን ቡድን ጋር ነበር። ሁለተኛው ለፀረ ዲሞክራቲኩ ደርግ ካደረው ከዓለም አብዲ ቡድን ጋር ነበር። ሦስተኛውና ዛሬም የተያዘው ትግል ደግሞ ከንኡስ ከበርቴው ደንፊ ቡድን ጋር ነው።
– በነዚህ የትግል ምዕራፎች ወቅት፣ እስከ ጊዜያችን ድረስ ሃቀኞቹና እውነተኞቹ የወዛደር ወገኖች በየጊዜው ተሸነፈዋል። ወይንም ደግሞ አሁን በመጨረሻ እንደደረሰው፣ የንኡስ ከበርቴው ደንፊ ቡድን በማንነታቸው በመጠቀም ብዙ ቸርችሮባቸዋል።
– የዛሬው ዋና ትግል የንኡስ ከበርቴውን ደንፊ ቡድን ውር ውር ማክሸፍና እውነተኛ የሠራተኛ ማህበር እንቅስቃሴ እንዲወከለድ መታገል ነው። ለዚሁም ሁሉ እድሜያቸውን በሙሉ የታገሉት ሃቀኞቹ ወዛደሮችና እውነተኞቹ ተራማጆች ሁሉ እጅ ለእጅ ተያይዞ መነሳት አለባቸው። የኢትዮጵያን ወዛደሮች ለማይቋረጠው መራራ ትግል በበለጠ ለማደራጀትና ለማዘጋጀት መርዳት አለባቸው።
የኢትዮጵያ ወታደሮች ሆይ !
እነመንገሻ ስዩም- እያሱ መንገሻ- ነጋ ተገኝ- አሊ ሚራህ. . . በኢምፔሪያሊስቶች እየተረዱ “የኢትዮጵያ ዲሞክራቲክ ህብረት” በተሰኘ ድርጅት ስር ተደራጅተውባችኋል።
በሃገር ውስጥ ያሉት ምድረ አድሃኖች ተደራጅተውባችኋል። የኢትዮጵያን አርሶአደሮች ማህበራት በመሳሪያ ጭምር ለመበተን እየታገሏቸው ናቸው።
የመሳፍንቶቹ ርዝራዦች፣ በአንድ በኩል “በአዋጁ መሰረት መደራጀት ፋሺዝምን ማደራጀት ነው” እያሉ፣ በሌላ በኩል ግን ራሳቸውን ለማደራጀት በፖስታ እየተላላኩባችሁ ናቸው።
ዲሞክራሲያ፣ ላባደር፣ አብዮታዊ ወጣት በሚባሉት ጋዜጦች አካባቢ የተኮለኮለው የንኡስ ከበርቴው ደንፊ ቡድን፣ ለራሱ ተደራጅቶ የላከባችሁ ጥሪ፦ “አትምረጡ፤ አትደራጁ፤ ከመረጣችሁም ‘ጊዜያዊ ሕዝባዊ መንግሥቴን’ ምረጡልኝ” የሚለውን ትጥቅ የሚያስፈታት ጥሪ ነው።
እንግዲህ የኢትዮጵያ ወዝአደሮች ዛሬ ከጠላቶቻችሁ በበለጠ ተደራጅታቹ እስካልታገላችሁ ድረስ፣ የተደራጁት ምድረ አድሃሪዎች ተባብረው ሊበታትኗችሁና ሊያጠቋችሁ እንደተነሱባችሁ ግልጽ ይሁን።
ዛሬ እንመርጥም ማለት አንደራጅም ማለት ነው። አንደራጅም ማለት ደግሞ፣ እንደተበታተንን በአድሃዎች እንጨፍጨፍ ማለት ነው።
የኢትዮጵያ ወዛደሮች ካሁኑ ነቅተውና ባላቸው አቅም ሁሉ ተደራጅተው፣ ጠላቶቻቸውን ለመደምሰስ ካልተጠናከሩ በውነትም ምድረ አድሃሪዎች “ለጭዳ ያቀርቧቸዋል”።
ስለሆነም፣ የጊዜው ዋና የወዛደሮች ተግባር ላወናባጆች ጆሯዋቸውን መስጠት ሳይሆን፣ መደራጀትና፣ ተደራጅቶም ለመሠረታዊዎቹ ጥያቄዎች መታገል ነው። “የታሰሩትን ተራማጅ የወዛደር መሪዎች ለማስፈታት የሚቻለው፣ ያለአንዳች ተጽእኖም ለመደራጀት የሚቻለው፣ መሰረታዊዎቹንም ጥያቄዎች ለማስፈፀም የሚቻለው” የበለጠ በተደራጀ ትግልና እንደብረት በጠነከረ አንድነት ብቻ ነው።
አውነተኞቹ ተራማጆች የኢትዮጵያን ወዛደሮች ትግል ለማገዝና ለመርዳት ከፍተኛ ግዴታ አለባቸው። በጊዜውና በየቦታው ለተደራጀ ትግል ቅስቀሳ የማድረግ ግዴታ አለባቸው።
መሳፍንት፣ የቢሮ ከበርቴዎች፣ ኢምፔሪያሊስቶችና አወናባጆች የሚደመስሱት በነቃ፣ በተደራጀና በቅጡ በተዘጋጀ ትግል ብቻ ነው።
የነቃው፣ የተደራጀውና የታጠቀው ሕዝባዊ ትግል ያሸንፋል።
“.. It (the minority) treats pure will as the motive power of revolution instead of actual conditions. While we say to the workers: ‘you have got to go through fifteen, twenty, fifty years of civil wars and national wars not merely in order to change conditions but in order to change yourselves and become qualified for political power’. You on the contrary tell them, ‘we must achieve power immediately, otherwise we may as well lie down Let go to sleep’. … Just as the democrats turned the word ‘people’ into a sacred thing, so you have done with the word ‘proletariat’. Like the democrats you substitute revolutionary phrases for revolutionary development” (C: Marx & F. Engels, “Selected Correspondence, 1846-1895”; International Publishers, 1935, p. 522- 23).