ሰሕድ ቁ. 6

የሰፊው ሕዝብ ድምፅ

ቁጥር 6፣    መስከረም 14፣ 1967

የፅሁፉ ፍሬ ሀሳብ

መኢሶን በዚህ የሰፊው ሕዝብ ድምፅ እትሙ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ በየካቲትt 1966ቱ እንቅስቃሴ ዋና ዋና የመብት ጥያቄዎቹን በግልጽ ማቅረቡን ያስታውሳል። ከእነዚህም የሕዝብ ፍላጎቶች ውስጥ የዲሞክራሲያዊ አስተዳደር ጉዳይ ቅደሚያውን እንደያዘ ይገልጻል። ሆኖም፣ “ከሕዝብ አብራክ የተገኘን ነን” የሚሉትና የሕዝቡን ጥያቄዎች እንረዳለን የሚሉ ጥቂት የጦር መኮንኖች፣ “ጊዜያዊ” በሚል አሳሳች ስያሜ ከሕዝቡ ተነጥለው ወታደራዊ መንግሥት አቋቁመዋል። በዚህም፣ የወታደሮች የስልጣን አያያዝ ዝግጅት ውስጥ የአሜሪካን ስለላ ድርጅት (ሲ አይ ኤ) ጣልቃ ገብነት አለበት ተብሎ እንደሚጠረጠር ይጠቁማል። በመስከረም 1967 ዓ.ም. መባቻ ላይ፤ በተማሪዎች፣ በሠራተኞች፣ በወታደሮች እና በመምህራን ላይ ወታደራዊ ደርግ የወስዳቸው ጸረ-ሕዝብ እርምጃዎች፣ ይህንን የጣልቃ ገብነት ጥርጣሬ የሚያረጋግጡ ማስረጃዎች እንደሆኑ ያስገነዝባል።     

የሰፊው ሕዝብ ድምፅ

ለሰፊው ሕዝብ ሰራተኛ ገበሬ፣ ነጋዴ፣ ወታደር፣ ምሁር መብትና ጥቅም የሚታገል ጋዜጣ

የኢትዮጵያ ሰፊ ሕዝብ ይቅደም

ቁጥር 6                                                                        ቀን 14/1/67

 

የሚያዋጣው

የኢትዮጵያ ሰፊ ሕዝብ በየካቲት ወር የትግሉን እንቅስቃሴ በይፋ ማካሄድ ሲጀምር ዋና ዋናዎቹን ፍላጎቶቹን በልዩ ልዩ መንገድ ገልጧል። ሰብአዊ መብቶቹን ለመጎናፀፍና ኑሮውን ለማሻሻል ነው በቆራጥነት የተነሳው። ሠርቶአደሩ አርሶአደሩ ወዘተ ይበልጥ የአተኮረው በዲሞክራሲያዊ አስተዳደር ላይ መሆኑ ግልጽ ነው።

የሰፊው ሕዝብ ፍላጎትና ጥያቄ ይህ መሆኑ በማያጠራጥር መንገድ ተደጋግሞ የተገለጸ ሲሆን ወታደራዊ መንግሥት ማቋቋሙ ምን ትርጉም ሊሰጠው ይችላል? ከሕዝብ ወጣሁ፣ የሕዝብ ወኪል ነኝ፣ ሕዝቡን ለማዳን መጣሁ፣ ወዘተ… የሚለውን ደርግ እንዴት እንደዚህ ዓይነት ፀረሕዝብ ፀረዴሞክራሲ ነገር ያደርጋል?

ይህ ሊሆን የቻለው አብዛኞቹ የደርጉ አባሎች ከመሠረታቸው ፀረሕዝብ ሆነው አይመስለንም፤ ሰፊውን ሕዝብ ወጥሮ ሰንጎ በመያዝ ይበዘብዘው የነበረውን የኃይለሥላሴን መንግሥት አሽቀንጥሮ በቆራጥነት ያስወገደው፤ የሕዝቡን ጥያቄና ፍላጎት ተከትሎ ነው ለማለት ይቻላል።

ስለሆነም፣ ሌላው ጠንቀኛው የኢትዮጵያ ለፍቶአደር ዋና ጠላት የአሜሪካ ኢምፔሪያሊዝም በደርጉ ውስጥ ሰዎቹን ያስገባ መሆኑ ዛሬ የአደባባይ ምስጢር ነው። ሕዝቡ ሲታገልለት የቆየውን ሕዝባዊ መንግሥት ወደዚያ ብሎ የወታደር መንግሥት እንዲታወጅ ያደረገው የአሜሪካ ኢምፔሪያሊዝም ለመሆኑ አንድና ሁለት የለውም። ጥቅሙን ሊጠብቅለት የሚችል እንደዚህ ያለ መንግሥት ነውና አሁንም ቡችሎቹንና ጥገኞችን መራርጦ በጥቂት ‘ምርጥ’ መኮንኖች የሚመራ ፋሽስታዊ መንግሥት በማቋቋም ላይ መሆኑ ተደርሶበታል። እቅዱን የሚያወጡትና የሚመሩት ምርጦቹ የሲአይኤ ባልደረቦች ዲን ፖልና ጓደኞቹ መሆናቸውም በግልጽ ታውቋል። ‘ምርጦቹ’ መሪዎች መካከል ትልቅ አለመግባባት ሰሞኑን ተፈጥሮ ዲን ፖልና የአሜሪካን አምባሳደር እንዳስታረቋቸው ተደርሶበታል፤ ማታ ማታ በየሆቴሉና በየቪላው እንደሚሰበስቧቸውና እንደሚመክሯቸው ተረጋግጧል። አሁን እርስበርሳቸው ተመራርጠው፣ ጁንታውን አቁመው ሌሎቹን ለመበታተን የተነሱት፤ ‘ምርጦቹ’ በሲኤይኤ መዳፍ ውስጥ ያሉ የአሜሪካ ኢምፔሪያሊዝም ቡችሎች መሆናቸው የማያጠራጥር ነው።

ወታደራዊው መንግሥት ሰሞኑን በተማሪዎች፣ በሠራተኞች፣ በመምህራን፣ በተራማጆች፣ በምሁራን፣ በወታደሮች፣ በሥራ አጦች፣ ወዘተ. የወሰዳቸውና በመውሰድ ላይ ያለው ፀረሕዝብ እርምጃዎች/ የተማሪዎች መደብደብና መታሰር፣ አሥር የሚሆኑ የመንግሥት ሠራተኞች መያዝና መታሰር፣ በኢሠአማ ላይ የተደረገው ዛቻና ማስፈራራት፤ በመጨረሻ ደግሞ የመሪዎቹ መያዝና መታሰር፣ በዩንቨርስቲ መምህራንና በተራማጅ ምሁራን ላይ የተሰነዘረ ዛቻና ማስፈራራት፣ በጠቅላላው ሕዝብ ላይ የሚደረገው የማወናበድና የማስፈራራት ድርጊቶች/ በቀጥታ የቪየትናምን፣ የሳንቶ ዶሚኒጎን፣ ወዘተ. ሕዝቦች ካስጨፈጨፈው ከሲአይኤ፤ ከአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም የመነጨ ነው። ይህ በፍጹም አያጠራጥርም፤ አገር ወዳድ ኢትዮጵያዊያን ይህን የመሰለ አረመኔ ድርጊት ይፈጸማሉ ብሎ እንዴት ለማመን ይቻላል።

ሰፊው ሕዝብ፤ የሕዝብ መንግሥት እንዲቋቋም አፋጦ ስለያዛቸው ትላንትና 12/1/67/ ለጁንታው ሃሳብ የሚያቀርቡ አንዳንድ ሰዎች መርጣችሁ ቶሎ ላኩ፤ የተባለውም በችኮላ በቂምበቀል በአድሎና ለማወናበድ የተወረወረ ትእዛዝ፤ ከዚያው ከፀረሕዝብ ከሲአይኤ የሰረፀ መሆን አለበት፣ ያለበለዚያ ሕዝቡ ከራሱ ባመነጨው ስልጣን ደንበኛ ወኪሎቹን መርጦ ራሱን በራሱ ለማስተዳደር ሲጠይቅ እንዴት እንደዚህ አይነት ወራዳና ርካሽ ማጭበርበሪያ ይጣልለታል?

ደርጉን የሚመራው ‘የምርጥ’ መኮንኖች ቡድን ፍሬቢስ፣ ፀረሕዝብ፣ የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም ቡችላ መሆኑን በብዙ አይነት መንገድ አሳይቷል። ይህ ቡድን የኢትዮጵያ ሰፊ ሕዝብ ዋና ጠላት መሆኑን በማያዳግም መንገድ ገልጧል። የሕዝቡ የትግል እንቅስቃሴ ማፋፋምና ወደፊት መራመድ፣ እነዚህን የኢምፔሪያሊዝም ቡችሎች ማስወገድና ድምጥማጣቸውን ማጥፋት አለበት።

አሁን ቆሞ ማየት ‘የምርጦቹ’ ቡድን ሲለፈልፍ እና ሲያወናብድ ዝም ብሎ ማየት አይገባም፤ በቃ፣ የሶስተኛው ዙር ደርግ ጉዳይ አልቋል፤ አክትሟል። ሰፊው ሕዝብ በተጠንቀቅ ላይ ብቻ ሳይሆን ትግሉ ውስጥ በቀጥታ መግባት አለበት፤ በየበኩሉ በየሙያውና በየሰፈሩ በዝቅተኛና በከፍተኛ ደረጃ ከዚያም በአጠቃላይ ባንድነት መደራጀትና የገጠመውን ትግል ማካሄድ አለበት፤ እነዚህን ወንበዴ ከሃዲዎች እንደአንድ ሰው ሆኖ በመነሳት ድምጥማጣቸውን በማጥፋት የሰፊውን ሕዝብ መንግሥት ማቋቋም አለበት።

የኢትዮጵያ ተማሪዎች፣ ኢሠአማ፣ ተራማጅ መምህራንና ምሁራን፣ ተራማጅ ወታደሮች፣ አርሶበሌው፣ ሁሉም ጠላቶቹን ለይቶ አውቆ ተቋቁሟቸዋል፣ ሁላችንም ባንድነት እንነሳ፣ በግንባር ቀደሞቹ ዙሪያ እንሰለፍ። እናሸንፋለን።

 

 

 

‘ኢትዮጵያ ትቅደም’ በደርጉ ሲፈታ

ተደጋግሞ በደርጉ አካባቢና በመሪዎች ነን ባዮች፤ በግልና በስውር ለሚያገኟቸው የማህበርና የድርጅት መሪዎች የሚነገር ነገር አለ። ይኽውም ‘ኢትዮጵያ ትቅደም’ የሚለው ዓላማ በምንም አይነት የውጭ ሀገር ርዕዮተዓለም መሰየሚያ ቃል የማይፈታ መሆኑን፤ ካፒታሊዝም፣ ሶሻሊዝም፣ ወይም ሌላ ‘ኢዝም’ ን የማይከተል፣ በኢትዮጵያውያን /ጥቂቶቹ የደርጉ አባሎች/ ለኢትዮጵያ በታላቅ ጀግንነት እና በረቂቅ ብልሃት የተነደፈ ዓላማ መሆኑን ነው። ‘መሠረታዊ ለውጥን’ ለማምጣት ዋናው ግቡ ነው ይላሉ። ነገር ግን አንድ ቡድን ወይም ግለሰብ የሚከተለውን ርዕዮተዓለም /አይዲዮሎጂ/፡ እርሱ ነኝ ወይም አይደለሁም ባለው የሚወሰንና የሚረጋ ሳይሆን፣ በአድራጎቱ የሚገለጽ ስለሆነ ‘ኢትዮጵያ ትቅደም’ ሲል ደርጉ ምን አይነት ርዕዮተዓለም እንዳለው ለመመርመር እንሞክራለን።

ይህንን ለመመልከት ደርጉ ከተፈጠረ ጀምሮ ለሕዝብ ያሰማቸውን መግለጫዎች፤ ያስፋፋቸውን ዘይቤዎችና መዝሙሮች፤ በቴሌቪዥን እየተዘጋጁ የምናያቸውን ትያትሮች፤ በራዲዮና በጋዜጣ የሚወጡትን ግጥሞች፣ ወዘተ መመርመር ያስፈልጋል። ይህንን ስናደርግ በመጀመሪያ የምናየው የደርጉ አፈቀላጤዎች /እፍኝ የማይሞሉ/ ኢትዮጵያን የሚያዩዋት 25 ሚሊዮን ልጆች እንዳሏት ችግረኛ እናት ነው። እነዚህ ልጆችዋ፣ አንዱ ጥቁር አንዱ ጠይም፣ አንዱ ቀይ፣ አንዱ ከበርቴ፣ አንዱ ድሃ /የእናት ሆድ ዥጉርጉር፡ እንደሚባለው/ ሆነው በወንድማማችነት ለዘላለም ሊኖሩ የሚችሉ ሲሆን፤ አንዳንዶቹ ድርጉ እንዳለው ‘ሰብአዊ ርህራሄና ብሔራዊ ሰሜት የሌላቸው የግል ጥቅም አጋባሾች ጨቋኞች’ የሆኑና ሌሎቹን ያራቁቷቸዋል። ባለጌዎቹ ልጆች ከየዋሆቹ ጋር አብረው የተከናነቡትን ጋቢ ይገፏቸዋል። እናንተ አስተዳዳሪ ሁኑ ብላ እናት ኢትዮጵያ ብትሾማቸው፤ እነኝህ ‘የገዥ ቡድንና አጫፋሪዎቻቸው’ በወሳሰቡት ምስቅልቅል አስተዳደር ስር ሌሎቻችን ተረግጠን ስንማቅቅና ስናለቅስ ብዙ የቀን ጨለማ ዘመን ገፍተናል። እኛም ደርጉ ‘የዋህ ሕዝብ’ እያለ የሚጠራን ሲቪል የሆነው ልጆች፤ እናታችን ‘3000 ዓመት አርግዛ ስድስት ወር አምጣ ደርጉን እስክትወልድ’ ድረስ የዋህ ስለሆንን ዝም ብለን ተገዝተን ነበር። አሁን ግን ‘ጀግናውና ብልሁ’ ወንድማችን አቶ ደርጉ ስለደረሰ፣ እኛንም እናታችንንም በቴሌቭዥን ትርኢት እንደታየው እፍኝ የማይሞሉትን ጨቋኝ ወንድሞቻችንን 4ኛ ክፍል ጦር አሥሮ፡ የታሰርንበት የረሃብና የድንቁርና ሰንሰለት ፈትቶ ወታደር ሆስፒታል አስገብቶ ‘አንድነትን፣ ለሥራ ትጉህነትንና መፈቃቀርን’ በመርፌ እየሰጠን በመሻር ላይ እንገኛለን።

እንግዲህ ለደርጉ በኢትዮጵያውያን መካካል ያለው ልዩነት የየዋህና የክፉ፣ የሞኝና የብልህ፣ የሥራ ወዳድና የአልማጭ፣ ወዘተ… ብቻ ነው። ደርጉም ዋና ጠላት አድርጎ የሚያየው የቀድሞውን አስተዳዳሪዎች ብቻ ነው። ስለዚህም ነው ደጋግሞ ኃይለሥላሴንና ሚኒስትሮቻቸውን ‘የሕዝቡ በደል ምንጭ’ ናቸው የሚላቸው። ስለዚህ ነው እነርሱን ካሰረ በኋላ ‘ያለ ምንም ደም መፍሰስ ለውጥ አመጣለሁ’ የሚለው። ይህ መቼም አህያ ልትሸከመው የማትችለው ትልቅ ስህተት ነው። ሕዝብ የሚከፋፈለው በመደብ መሆኑ በህብረተሰብ ሳይንስ የተረጋገጠ ሲሆን፡ በኢትዮጵያም ህብረተሰብ ውስጥ መደቦች መኖራቸው የሚያጠራጥር አይደለም። እነዚህም በአንድ በኩል የታላላቅ ባለመሬቶች /ፈውዳሎች/ መደብና የኢምፔሪያሊዝም አቀባባይ ከበርቴ መደብ፤ በሌላ በኩል የንዑስ ከበርቴ /አነስተኛ ነጋዴ፣ አስተማሪ፣ የመንግሥት ዝቅተኛ ሠራተኛ፣ ምሁራን፣ ዝቅተኛ መኮንኖች/ መደብ፣ የሠራተኛ መደብ፣ የጢሰኛና ደሃ ገበሬ መደብ፣ ወዘተ… ናቸው። እንግዲህ የደርጉ አስተሳሰብ የመደቦችን መኖር ሰለሚክድ የአንዳንዶቹን መደቦች መኖር አልፎ አልፎ ለማመን ቢገደድም በመደቦች መካካል ዝንተዓለም የሆነ ትግል መኖሩን ይክዳል። ስለዚህም በሰላም ያለ ‘ምንም ደም ለውጥ ማድረግ ይቻላል’ ይላል።  ለምሳሌ ስለመሬት ይዞታ፤ ጢሰኛንና ባለ መሬትን ሁለቱንም አስደስቶ መሰረታዊ ለውጥ ለማድረግ የሚቻል ያስመስላል። እንዲሁም በጥገኛው ከበርቴና በወዝአደሩ መካከል ያለውን ቅራኔ ዘንግቶ ‘ሥሩ፣ በርቱ፣ ሀገር ለመገንባት’ ይላል። ‘የልማትና የዕውቀት ዘመቻ’ የተባለውን ዝግጅትም የሚመለከተው ኢትዮጵያዊያንን እንዲሁ መደብ የለሽ በማድረግና ችግር የሃብት አፍሪ መደቦች መመዝበር ሳይሆን ‘የድንቁርናና የስንፍና’ አድርጎ ነው።

ከዚሁ አስተሳሰብ የሚቃረብ የዚሁ የመደቦችን መዘንጋት የሚመስል ሌላ በደርጉ የሚሰነዝር አሳብ አለ። ይኸውም ስለ ‘ጎሣና ሀይማኖት’ ያለው አስተሳሰብ ነው። የወደቁት ገዢዎች ሕዝቡን በልዩ ልዩ ተንኮልና ዘዴ በሀይማኖት በጎሣና ዘለቄታ በማይኖረው ጊዜያዊ ጥቅም ከፋፍለውታል፤ ለደርጉ ሃይማኖቶችና ብሄሮች በፈላጭ ቆራጩ ኃይለሥላሴ በዘፈቀደ የተፈጠሩ ነገሮች ናቸው። ኃይለሥላሴ ከወደቀ ብሔሮች አንድ ሆነው ይኖራሉ። የደርጉ አፈቀላጤ፣ ጀ. አማን፣ ይህንን አስተሳሰብ በኤርትራ ሲሰብክ ሰንብቷል። እርግጥ አድሃሪው አገዛዝ ብሔሮች ይበልጥ እንዲራራቁ አድርጓል። ነገር ግን ለብሔሮች ጉዳይ መፍትሄ ሊገኝ የሚቻለው፤ በቅድሚያ ብሔሮች መኖራቸው ታምኖ፣ እያንዳንዱ ብሄር የራሱን እድል በገዛ ራሱ የመወሰን መብቱ ሲታወቅና ሲከበር፤ ከዚያም በኋላ የእያንዳንዳቸው ፈቃድ በእኩልነት ታይቶ፡ እርስ በርስ የሚያጋጩአቸው የገዢው ብሔር ጨቋኝ መደቦችና የተጨቋኝ ብሔሮች ባላባቶችና ጥገኛ ከበርቴዎች ተወግደው፣ የልዩ ልዩ ብሄሮች ተበዝባዥ መደቦች በፈቃዳቸው አንድነታቸውን ሲገነቡ ነው። ይህንን ዕውነት የማያምን ደርግ የብሔሮችን ህልውና የማይገነዘብ ደርግ፣ ለዚህ ችግር መፍትሄ ሊሰጥ እንደማይችል የታወቀ ነው።

ሌላ ግዙፍ የሚታይ ነገር የደርጉ ስለታሪክ ያለው የተምታታ እምነት ነው። ተደጋግሞ እንደሚሰማው ለደርጉ ‘የኢትዮጵያ ታሪክ የ3000 ዓመት ጨለማ’ ነው። በዚህ የጨለማ ዘመን አንዳንድ ምርጥ ‘ኢትዮጵያውያን ሀገሪቱን ለማሻሻል’ ሞክረው፣ ሁሉም የተማሩትና የሠለጠኑት ምርጥ የደርጉ አባሎችና አጫፋሪዎቻቸው ከ3 ወራት በፊት ብቅ እስከአሉ ድረስ ከሽፎባቸዋል። የደርጉ ፕሮፓጋንዳ የድሮዎቹን ‘ምርጦች’ ሁኔታው ያስመረራቸውና ያንገፈገፋቸው ጥቂት ኢትዮጲያውያን ሲላቸው ስለዛሬዎቹ ደግሞ “… ጥበብና ችሎታ ባላቸው፣ በራሳቸው በሚተማመኑ ወታደራዊ ሊቃውንት ወጣቶች ተዘጋጅቶልሃል” ይለናል። የባርነትን ሥርዓት የተቋቋሙትና ያፈረሱት አክሱማውያንና የዛጉዌ ለፍቶአደሮች፣ የፊውዳልን ሥርዓት ለብዙ ዘመናት የታገሉት የሃረር፣ የከፋ፣ የወላሞ፣ ወዘተ… ገበሬዎችና ዘላኖች፣ /ኢምፔሪያሊዝምን ሲቋቋሙ ያለቁት የኤርትራና የትግራይ፣ የኡጋዴን፣ የሸዋ፣ የቤጌምድር ሕዝቦች/፣ የጎሣን ትምክህት የሃይማኖትን ጭቆና የተቋቋሙት ኦሮሞዎች፣ ሱማሌዎች፣ ደራሳዎች፣ ወዘተ… ለደርጉ ሰምየለሽ እንደመሆናቸው፤ በሬዲዮና በጋዜጣ በሚጽፈው አዲስ ምዕራፍ ላይ ቦታ የላቸውም። ይህ ምርጣዊነት /ኤሊቲዝም/ ከላይ ከጠቀስነው መደብ የለሽ ርዕዮተዓለም የሠረፀ ነው። የኢትዮጵያ ታሪክ የነገሥታት /ዘርዓ ያዕቆብ፣ ቴዎድሮስ፣ ሚኒልክ/ የመኳንንት /አሉላ፣ ሀብተ ጊዮርጊስ፣ ወዘተ…/ ነው ከተባለ፤ የታሪክን ምእራፎች የሚጽፉት አንዳንድ ጀግኖች ምርጥ ወታደሮች ወይንም ምሁራን ናቸው ከተባለ፤ የታሪክ ፈጣሪ ሕዝብ ነው የሚለውን የተራማጆች እምነት መቃረኑ ግልጽ ነው። ከዚህም ጋር የሚያያይዘውን ፀረዲሞክራሲ የሆነው ሌላ እምነት፤ ሕዝቡ አልበሰለም፣ ሕዝቡ ስላልተማረ የሚበጀውን አያውቅም። ስለዚህም ሰብአዊ መብትና ነፃነት አይገባውም። የፖሊቲካ ማህበር ወይም ፓርቲ አያስፈልገውም፤ አትሰብሰቡ አትደራጁ የሚለው ሰሞኑኑን የሚለፈፈው የማስፈራሪያ ፕሮፓጋንዳው ነው። ሕዝቡ ተመልካች፣ ደርጉ ተዋናይ የሆነበት የዛሬው ቲያትር የመነጨው ከዚህ ከፀረሕዝብና ፀረዲሞክራሲ ከሆነው ምርጣዊነት አስተሳሰብ ነው። አንዳንድ ምሁራን በአማካሪነት እንዲገቡ ይደረጋል የሚለው ዓዋጅ ምሁራኑ ማንንም የተደራጀ ቡድን እንዳይወክሉ ለማድረግና ድርጅት ራሱ አስፈላጊ አለመሆኑን ለማሳመን የታሰበ ነው። ይህን አስተሳሰብ የሚከተሉት የደርጉ ‘ምርጥ አባሎች’ ሲናገሩ ደርጉ ውሰጥ ብዙ ያልተማሩ ዲግሪ የሌላቸው አባሎች ስለአሉ አላሠራ አሉን፣ ደምበኛ /ጁንታ/ የምርጥ መኮንኖች ቡድን ማቋቋም አለብን ሲሉ ይሰማሉ። እንግዲህ ዲሞክራሲውን በጦሩም አባሎች መካከል ብዙ የማይፈቅዱ ናቸው ማለት ነው።

ምናልባት አንዳንድ አንባቢዎች፤ ሰዎች በመደቦች ትብብር ቢያምኑም ምርጠኛም ቢሆኑ ‘ኢትዮጵያ ትቅደም’ ስላሉ ብሄረኛ /ናሽናሊስት/ ርዕዮተ ዓለም አላቸውና አምፔሪያሊስቶችን ይቋቋማሉ ብለው ያምኑ ይሆናል። ነገር ግን ታሪክ እንደሚያሳየን ኢምፔሪያሊስቶች ጭቆናቸውንና ምዝበራቸውን የሚያካሂዱት በራሳቸው ዜጎች ወይም በሌሎች በባዕድ ግለሰቦች ሳይሆን በአገሪቷ ዜጎች ‘በወንድሞቻችን’ አማካይነት በተለይ የተወናበደ ግዑዝ ዓላማ ይዘው በሚነሱ ምርጥ መኮንኖችና አቀባባይ ከበርቴዎች መሆኑን እናውቃለን።

በአጠቃላይ ደርጉ ‘ኢትዮጵያ ትቅደም’ ሲል እስካሁን የታሰረውን እግሯን ሳይፈታላት ከኋላ በመገፍተር ብቻ ለማስሮጥ የሚሞክር ይመስላል። የኢትዮጵያን መቅደም የሚወድ ሲጨቆንና ሲበዘበዝ የኖረው ድሃው ሕዝብ ነው። ሌላውማ ለማን ብሎ፤ ለሰፊው ሕዝብ ኢትዮጵያ ልትቀድምለት የምትችለው ባላባታዊው አገዛዝ ከአናቱ መቀንጠብ ብቻ ሳይሆን፡ ከሥሩ ተመንግሎ ሲወድቅ ነው። ሀቀኛ ፀረኢምፔሪያሊስት አቋም ተወስዶ የጅአዙር ቅኝ ግዛት መሆኑ ተወግዶ ነፃ ብሄራዊ ኢኮኖሚ መገንባት ሲጀመር ብቻ ነው። ኢትዮጵያ በምርጦች አትቀድምም። በሰፊው ሕዝብ እንጂ።

ስለዚህ ‘ኢትዮጵያ ትቅደም’ በማለት ደርጉ /ጥቂት ምርጦች/ ጆሮአችንን የሚበጥስበት ሕብረተሰባዊ ፍልስፍና ወይም ረዕዮተዓለም /አይዲዮሎጂ/ በራሱ ትርጉም የሌለው፤ ቢኖረውም የተድበሰበሰ ወይም የተወናበደ ነው።

 

ተጠቅሞ መጠቀም

ወይንስ

የኢምፔሪያሊስት ብዝበዛ?

 

የኢትዮጵያ ሰፊ ሕዝብ አሁን ባለበት ታሪካዊ የለውጥ ዘመን ጠላቶቹ የሆኑትን ባላባታዊ ሥርዓትና የውጭ ከበርቴ ብዝበዛ አውድሞ በመቃብራቸው ላይ ነፃ የሆነ ብሔራዊ ኢኮኖሚ ለመገንባት በመታገል ላይ ነው። ይህን ከፍተኛ ትግል ለማጨናገፍ፤ ባንድ በኩል የባላባታዊው ሥርዓት ርዝራዦች፣ በሌላ በኩል የኢምፔሪያሊስት ታማኝ አገልጋዮች፣ የቆዩ የሕዝብ ጠላቶች ከየተደበቁበት ዋሻ ሆነው የመጨረሻ ትግላቸውን በማድረግ ላይ ናቸው።

የኢትዮጵያ ቤዛ ነኝ የሚለው በጥቂት ‘ምርጥ’ መኮንኖች የሚመራው መንግሥት ለከበርቴዎቸ በተለይ ለውጭ አገር ሞኖፖሎች ደህንነትና ጥቅም ዋስትና አንደሚሰጥ ደጋግሞ ገልጿል። ይህም ማለት ባጭሩ ‘በምርጥ’ መኮንኖች የሚመራው መንግሥት የባዕድ ሞኖፖሎች በኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት ሲያደርጉ የነበረውን አገሪቱን የመበዝበዝና ወዝአደሩን የመጨቆን ተግባራቸውን ሊቀጥሉ እንደሚችሉ ቃል ገብቶላቸዋል ማለት ነው።

በሦስትና በአራት ቢላዋ መብላት የለመዱት እነ በዓሉ ግርማ መስከረም 7 እና 8 ቀን 67 ዓ.ም በወጣው አዲስ ዘመን ርዕሰ አንቀጽ ውስጥ የማጭበርበሪያ ዘዴ በመጠቀም የውጭ ከበርቴዎች ወዳገራችን ገብተው እንዲበዘብዙ ግብዣ አድርገውላቸዋል። በዓሉ፤ የዉጭ ከበርቴዎች እስካሁን ኢትዮጵያ ውስጥ ገብተው በሚገባ እንዲበዘብዙ የኃይለሥላሴ መንግሥት በሩን በደንብ ስላልከፈተላቸው ካወገዘ በኋላ ባዲሲቱ ኢትዮጵያ ውስጥ ግን ሙሉ ጥበቃና መንከባከብ እየተደረገላቸው የሕዝቡን የላብ ፍሬ ወደአገራቸው ለማዛወር እንደሚችሉ ተስፋ ስጥቷል። ሀተታውንም በመቀጠል የውጭ ከበርቴዎች ወደ አገራችን የሚጋበዙት ‘ተጠቅመው እንዲጠቅሙን’ እንጂ በቁና ሰጥተው በደውላ እንዲቀበሉ ለማድረግ እንዳልሆነ አስታውቋል።

እስቲ የዚህን አባባል ይዘት እውነተኝነት እንመርምር።

የኃይለሥላሴ መንግሥት በዕውነት የውጭ ከበርቴዎች ወደ ኢትዮጵያ እንዳይገቡ ከልክሎ ነበር? መልሱ በአጭሩ አልከለከለም ነበር ነው። እንዲያውም የኃይለሥላሴ መንግሥት የውጭ ከበርቴዎችን ለመሳብ ብዙ ጥረት ያደርግ እንደነበረ ግልፅ ነው። ኃይለሥላሴ ወደ ምዕራብ አገሮች በሄደ ቁጥር ከበርቴዎች ወደ ኢትዮጵያ መጥተው እንዲቋቋሙ ግብዣ ሳያደርግ ተመልሶ አያውቅም ነበር። ከዚያም ሌላ በውጭ አገር የንግድ አታሼዎች አማካይነት ለባዕድ ከበርቴዎች በጋዜጣና በልዩ ልዩ የማስታወቂያ መሳርያዎች ያልተቋረጠ ግብዣ ያደርግላቸው ነበር። በተጨማሪም በአሜሪካኖች ገፋፊነት በተነደፈው የኢንቨስትመንት ሕጉ መሠረት ባዕድ ከበርቴዎችን ለመሳብ የሚከተሉትን ጥቅሞች አበርክቶላቸው ነበር።

  1. ከበርቴዎች ኢትዮጵያ ውስጥ አንድ ሥራ ከጀመሩ አንስቶ ለአምስት ዓመታት ያህል ታክስ እንዳይከፍሉ ልዩ መብት መስጠት፤
  2. ሥራውንም ለመጀመር ከውጭ አገር በሚያስገቡት ዕቃዎች ላይ የጉምሩክ ታክስ ከመክፈል ነፃ እንዲሆኑ፤ ለአንዳንድ እቃዎች እንዲያውም መንግሥት የትራንስፖርት ዋጋ እንዲከፍልላቸው ማድረግ፤
  3. የወዝአደሩን ዝቅተኛ ደመወዝ በሕግ ባለመወሰን ከበርቴው ከረሃብ የማታድን ደመወዝ እየከፈለ እንዲበዘብዝ በማድረግ፤
  4. የወጪና ገቢ መዝገባቸው አያያዝ ዋናቸውን ቶሎ ለማስመለስ በሚያስችል መንገድ እንዲሆን፤
  5. ፍጹም ጨቋኝ የሆኑ የሠራተኛና አሰሪ ግንኙነት ሕጎች በማውጣት /ለምሳሌ የሥራ ማቆም መብት በመከልከል፤ የሥራ የጤና ዋስትና ወዘተ. በመከልከል/ የከበርቴዎችን ትርፍ ማዳበር፤
  6. ከበርቴዎች ትርፋቸውን በሙሉ በፈለጉ ጊዜ ወደ ሀገራቸው እንዲያግዙ መፍቀድ፤
  7. የባዕድ ከበርቴዎች ዝናቸውን ብቻ ዋስትና በማድረግ ምንም ገንዘብ ሳይዙ ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ከኛው ባንኮች የኛኑ ብር ተበድረው ሥራ እንዲጀመሩ መፍቀድ፤
  8. አንዳንድ የሀገራችን ነጋዴዎች የውጭ ከበርቴዎች በጀመሩት የሥራ አቅጣጫ እንዳይሳተፉና እንዳይወዳደሩአቸው በሞኖፖል ሕጎች መከላከል፤ ወዘተ.

በነዚህ መብቶች በመጠቀም ከ1955 ዓም እስከ 1968 ዓም በነበሩት አሥራ ሦስት ዓመታት ውስጥ የውጭ ከበርቴዎች በጠቅላላው ወደ ሁለት ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ገንዘብ በልዩ ልዩ መንገድ በዝብዘው ወደ አገራቸው እንዳጋዙ በአውሮፓ የኢትዮጵያ ተማሪዎች ማህበር ያደረገው ጥናት አረጋግጧል። ያውም ይህ በይፋ የወጣው ገንዘብ ነው። በምሥጢር የወጣው ከዚህ በምንም እንኳን የሚያንስ አይመስለንም።

ታዲያ የኃይለሥላሴ መንግሥት በሩን ከፍቶ አላስበዘበዘንም ተብሎ ሊታማ ይችላል? እንዲያውም የቀድሞ ባለሥልጣኖቻችን ከተወነጀሉበት ዋና ዋና ምክንያቶች አንዱና ዋንኛው ከውጭ ከበርቴዎች እየተመሳጠሩ ስላስበዘበዙን አይደል? የብዝበዛው በር ከዚህ ወዲያ መክፈት ማለት ለነበዓሉ እንጂ ለኛስ አይገባንም።

ሁለተኛው የበዓሉ መርህ ደግሞ ጨርሶ የተወላገደ የመሓይም አነጋገር ነው። የውጭ ከበርቴ ‘በቁና ሰጥቶ በዳውላ ካልተቀበለ’ ለምን ባህር ተሻግሮ ወሰን አልፎ ሕዝቡን አገሩን ቋንቋውን ወደማያውቀው ስፍራ ይመጣል? ከበርቴ ዘወትር በምንም ዘዴ ይሁን በምን፣ የሚፈልገው አንድ ነገር ነው፤ ትርፍ፤ የተቻለውን ያህል ትርፍ። ሌላ ጉዳይ የለውም ለሕዝቡ ሥራ ይከፈታል፤ አገር ያቀናል፤ መንገድ ይጠርጋል የሚለው ኢምፔሪያሊዝም በነበዓሉ ላይ የቀረፀባቸው የከበርቴዎች የምጣኔ ሃብት ሳይንስ /?/ ነው። ለነገሩም የጥቂቶች መክበር የብዙሃን መደህየት ምክንያት ነው። ‘ጠቅሞ መጠቀም’ የሚባል አስተሳሰብ በከበርቴዎች ዘንድ የለም። አይቻልምም። አንዱ ሲጠቀም /ሲበዘብዝ/ ሌሎች ብዙዎች መጉዳት /መበዝበዝ/ አለባቸው። ይህ ነው የከበርቴዎች የምጣኔ ሀብት ፈሊጥ።

የውጭ ከበርቴዎች ወደ አገር ውስጥ በሚጋበዙበት ጊዜ የትኛው የሥራ መስክ ለሕዝቡ ሥራ ይሰጣል? የትኛው ኢንዱስትሪ ለሕዝቡ ተፈላጊውን ዕቃ ያቀርባል? የትኛው አገልግሎት ለሕዝብ ይጠቅማል? ብለው አያስቡም። ምን ገዷቸው? የነሱ ጥያቄ በየትኛው መስክ ብሰማራ የወፈረ ትርፍ እዝቃለሁ? ነው። ለዚህ ነው በአገራችን ውስጥ የገቡት የውጭ ከበርቴዎች ብዙ ትርፍ የማይሰጥ ግን ለሕዝቡ በረከት የሚሆኑ ከባድ ኢንድስትሪዎች እስካሁን ያላቋቋሙት። በሌላ በኩል ብዙ ትርፍ የሚያስገኙትና ከሕዝብ መሰረታዊ አገልግሎቶች ርቀው የሚገኙት እንደ ኢንሹራንስና የአስመጪና ላኪ ሥራዎች በውጭ ከበርቴዎቸ ተወረዋል።

የውጭ ከበርቴዎች በሰው ዕውቀት ሥልጠናና በቴክኒክ ይረዳሉ እየተባለ የሚወራውም ፍፁም ውሸት ነው። አንድ የውጭ ከበርቴ በአገር ውስጥ ኩባንያ በሚያቆምበት ጊዜ በሥራ መሪነትም ሆነ በጉልበት ሥራ ተቀጥረው የሚሠሩት ኢትዮጵውያን ሲሆኑ የኩባንያውን ተንኮላዊ ተግባር በምሥጢር ለመያዝ እንዲያመች ብቻ አንዳንድ የራሱን ዜጋ ኤክስፐርቶች ወይም ሥራ አስኪያጆች ከላይ ያስቀምጣል። ኩባንያው ትርፉን ለመጨመርና ከወዝአደሩ የዘወትር ትግል ለመዳን ሲል ዘመናዊ አውቶማቲክ መሣሪያዎች በማስመጣትና በሰው ፈንታ በመተካት ብዙ ወዝ አደሮች ከሥራ ያባርራል። ለዚህም ዓይነተኛ ምሳሌ የሚሆነን የወንጂ ስኳር ፋብሪካ ከአራት አመት በፊት የአገዳ ቆረጣ በመኪና ማሠራት ባስጀመረበት ጊዜ ከ5000 የማያንሱ ወዝአደሮች መባረራቸው ነው።

ይህ ነው እንግዲህ የውጭ ከበርቴዎች ‘ተጠቅሞ መጥቀም!’ ይህ ነው እነበዓሉ በሐቅ ሠርቶ መኖር የሚሉት ብዝበዛ! እንዲህ ዐይነቱ ሐቅ ባፍንጫችን ይውጣ።

የኢትዮጵያ ሰፊ ሕዝብ ከማንኛውም የውጭ ከበርቴ እጅ ነፃ የሆነ ኢኮኖሚ ለመገንባት በራሱ መተማመን አለበት። በራሱ ለመተማመን ይችላል። እነበዓሉ የሚረሱት ባለፉት አሥር ዓመታት በውጭ ከበርቴዎች በቀዳማዊ ኃይለሥላሴና በመሳፍንት ወደውጭ የተጋዘው ከአሥራ አምስት ቢሊዮን ብር በላይ የሚሆን ገንዘብ የተፈራው እዚሁ አገራችን ውስጥ መሆኑን ነው።

እንደ ዕውነቱ ከሆነ አገራችን ባለፉት አሥር ዓመታት ውስጥ የካፒታል አበዳሪ ነበረች ለማለት ይቻላል። ኢትዮጵያ ወደኋላ የቀረችው ካፒታል ስላጠራት ሳይሆን ሐብት /ካፒታል/ በሚገባ በሥራ ላይ ባለመዋሉ ነበር።

አሁንም ትክክለኛ የፖለቲካ አስተዳደር ካገኘች አገራችን በራሷ ካፒታል በራሷ የተፈጥሮ ሀብት ልትለማና ልትራመድ ትችላለች። እነበዓሉ ገና ያልገባቸው የኢኮኖሚ ዕድገት ዋና ዓላማው ለጥቂት ከበርቴዎች ትርፍ ማዳበር ሳይሆን የሕዝቡን የኑሮ ሁኔታ ማሻሻል መሆን እንደሚገባው ነው። በኢትዮጵያም ዕውነተኛ ሕዝባዊ መንግሥት ከተቋቋመ ዋና ዋና የኢኮኖሚ ቅርንጫፎች በመንግሥት እጅ ተይዘው ኢንዱስትሪዎች በትርፍ ሳይሆን ለሰፊው ሕዝብ በሚሠጡት ሥራ ጠቃሚ ውጤትና አገልግሎት እየተመዘኑ በመቋቋም አንዱ ሌላውን በመደገፍና ሰፊ ገበያ ባገሩ ውስጥ በመፍጠር የአገሪቱን የኢኮኖሚ እርምጃ ለማፋጠን ይቻላል።

በቅርቡ የደረሰው የዓለም ታሪክ እንደሚያሳየው ከፍተኛ የኢኮኖሚና የሕብረተሰብ ለውጥ ያደረጉት አገሮች በራቸውን ለውጭ ከበርቴዎች ከፍተው የተበዘበዙት ሳይሆኑ እነዚህን የሕዝብ ጠላቶች አንቅረው ተፍተው ነፃ የሆነ ኢኮኖሚ የገነቡት ናቸው። ለዚህም ታምራዊ እርምጃ ሕዝባዊት ቻይና ኗሪ ምስክር ናት። የውጭ ከበርቴዎች ድቀት እንጂ ልማት አየስገኙም።

ለነፃ ብሔራዊ ኢኮኖሚ እንታገል!
ኢምፔሪያሊስቶችና ቡችሎቻቸው ይጥፉ!
Scroll to Top