የሰፊው ሕዝብ ድምፅ
ቁጥር 12፣ ጥቅምት 26፣ 1967
የፅሁፉ ፍሬ ሀሳብ
መኢሶን በዚህ የሰፊው ሕዝብ ድምፅ እትሙ፣ ከአጼ ኃይለ ሥላሴ ከዙፋን መውረድ በኋላ፤ ወታደራዊ መንግሥት መደበኛ የስም ለውጦች እንዳካሄደ ይገልጻል። በዚህም የይስሙላ ስያሜዎች፣ በንጉሠ ነገሥት መንግሥት ይልቅ የኢትዮጵያ መንግሥት፤ በጠቅላይ ግዛት ምትክ ክፍለ ሃገር አስተዳደር፤ በጸጥታ መሥሪያ ቤት ፋንታ የሕዝብ ደህንነት በሚል እንደተቀየሩ ይገልጻል።ሆኖም፣ እነዚህ የስም ለውጦች፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ ለሚያነሳቸው መሠረታዊ ጥያቄዎችና ችግሮች ዘላቂ መፍትሄ ሊሰጡ እንደማይችሉ፣ መሸፋፈኛና ማድበስበሻ እንደሆኑ ያጠያይቃል። የንጉሠ ነገሥቱ መንግሥት በርካታ የቀድሞ ባልሥልጣኖች በአስተዳደር ሃላፊነት ላይ እንደቀጠሉ ሆነው፤ አዳዲስ ስያሜዎች መስጠቱ በራሳቸው መሠረታዊ ለውጦች እንደማያመጡ ያሳስባል። እውነተኛ ለውጥ ስምና ግብርን ማጠቃለል እንደሚገባውና እንዲያውም ግብር ስምን መቅደም እንደሚኖርበት ያስገነዝባል።
የኢትዮጵያ ንጉሰ ነገስት መንግሥት ይባል የነበረው ዛሬ የኢትዮጵያ መንግሥት ብቻ ተብሎ እንዲጠራ ታውጇል፤ እንደዚሁም ጠቅላይ ግዛት የሚለው የክፍለ ሃገር አስተዳደር ተብሎ ተሰይሟል፤ ሌሎችም የስም ለውጦች ተደርገዋል። ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ላይ በ22/2/67 ደግሞ ‘የሕዝብ ፀጥታ መጠበቂያ መ/ቤት’ በመባል ይታወቅ የነበረው ከዚህ ቀን ጀምሮ ‘የሕዝብ ደህንነት መጠበቂያ መ/ቤት’ እንዲባል በወታደራዊ መንግሥት ተወስኗል። ይህ የስም መለዋወጥ እዚያና እዚህ አልፎ አልፎ ከሚወሰዱት ተነጣላ እርምጃዎች ጋር ዘላቂ መፍትሄ ሊሆን ይችላል ወይ?
ያለውን እውነቱንና ሃቁን ነገር እንመልከት፤ ዛሬ በስልጣን ላይ ያሉት እነማን ናቸው? የመንግሥቱን ከባድ መኪና ከላይ ሆነው የሚያንቀሳቅሱት ሚኒስቴሮች፣ እንደራሴዎች፣ አፈንጉሶች፣ የጦርና የፖሊስ አለቆች፣ የኃይለሥላሴ ፍጡሮች፣መሳሪያዎች ቡችሎች የጭቆናና የግብ ተባባሪዎችና ግብረበሮች አይደሉም ወይ?
አንዳንዶቹ የጌስታፖ አለቆችና ቀንደኞቹ ቦታ ቀያይረዋል፣ አንዳንዶቹ ከአዲስ አበባ ወደ ክፍለሃገር ተዛውረዋል፣ በርከት ያሉትን የቀድሞ አለቃቸው ኮሎኔል በላቸው ጀማነህ ወደ አገርግዛት ወስዶ ከፍተኛ ሥራ ላይ አሰማርቷቸዋል። ብዙዎቹ ግን የበለጠ ስልጣን ተቀዳጅተው በቀድሞው አስቀያሚ ተግባራቸው ላይ እንደተሰማሩ አይደሉምን? የሰፊውን ሕዝብ ወገኖች፣ ግንባር ቀደም ታጋዮቹን፣ እነዋለልኝ መኮንንን፣ እነጥላሁን ግዛውን፣ እነማርታ መብራህቱንና ሌሎችንም ያለምንም ሰብአዊ ርህራሄ የረሸኑት፣ አጋድመው ያረዱት ዛሬ የት ናቸው? የሻምበል ባሻ ገብረፃድቅ ተወልደን እንደዚያ አሰቃይተው አካላተጎደሎ ሆኖ ዘወትር፣ ምነው በሞትኩትና ባረፍኩት፣ ስለበለስ አሳረፉኝ እያለ ሲማጠናቸው በሲኦል ውስጥ እንዲኖር ያደረጉት አረመኔዎች ዛሬ ምን ይሰራሉ? አንድ እንኳን ከሥራው የተወገደ አለ ይሆን? አንድ የተያዘና የታሰረስ አለ? በሰራው የጭካኔ ወንጀል በዚያ ሁሉ ግፉ ተጠይቆ የተቀጣ አንድ እንኳን እገሌ የሚባል ሰው አለ ይሆን? ታዲያ እነዚህ ሁሉ አረመኔ ወንጀለኞች ምንም ሳይነኩ፣ እንዲያውም ሹመትና እድገት እየተሰጣቸው፣ ፀጥታን ደህንነት ብለነዋል ማለቱ ምን ትርጉም ሊኖረው ይችላል? ማን ሊያምንበት ይችላል?
ነገሩ በሌላውም በኩል ያው ነው፤ እንዲያውም ይብሳል። ‘ኢትዮጵያ ትቅደም’ የሚለውን አዲሱን ፍልስፍና እንዲያስተምሩና እንዲያሰራጩ፣ የሰፊውን ሕዝብ የመንግሥቱን ጉዳይ ማወቅ መብት ሥራ ላይ አውሉ የተባሉትን የጋዜጠኞች ጉዳይ እስቲ እንመልከት። እነበአሉ ግርማ፣ ጳውሎስ ኞኞ፣ አጥናፍሰገድ ይልማ፣ ተስፋዬ ኃብትህይመር /ጥቂቶቹን ለመጥቀስ ያህል/ አጤ ኃይለሥላሴ የኢትዮጵያ አባት እናት ተወዳዳሪ የሌላቸው መሪ፣ ፈጣሪዋ ናቸው፣ የዘመናችን የዓለም ታላቅ የፖለቲካ ሰው ናቸው፣ የኢትዮጵያ ፀሀይ አፍሪካ ብርሃን የዓለም አንፀባራቂ ኮከብ፣ በምድር ክንፍ ያወጡ ጻድቅ ወዘተ. ናቸው እያሉ ለብዙ ዓመታት ሲያወድሱ ሲያኮፍሱ አልነበሩምን? ከትላንተ በስቲያ እነአክሊሉን እነራስ መስፍንን እነጀኔራል ይልማን፣ትናንትና እንዳልካቸውን እነጄኔራል አቢይን እነሚካኤልን ሲያነፍሱ ሲያኮፍሱ ሲያሽሞነሙኑ፣ ጭራቸውን ሲቆሉላቸው፣ ጎንበስ ብለው እግራቸውን ሲልሱ የነበሩ እስስቶች አይደሉም ወይ?
እንግዲህ እነዚህ ርካሾች፣ ህሊና ቢሶች፣ ፍፁም የሰውነት ጠባይ የሌለባቸው፣ ስልጣን ለጨበጠ ሁሉ አጎብድደው መሬት ለሚልሱ ወራዳ አድርባዎች እንዴት እንደዚህ አይነት ከባድ ኃላፊነት ያለው ሥራ ይሰጣል? እነዚህ የቀድሞ መንግሥት አባሪ ተባባሪ ወንጀለኞች ዛሬ አይናቸውን በጨው ታጥበው የሰፊውን ሕዝብ ወገኖች ለመወንጀልና ለማሳጣት ይሽቀዳደማሉ። እንዲህም አድርጎ ለውጥ የለ! ግሩም ድንቅ ነው፤ ፍሬውን ብቻ ያሳየና።
የአድሃሪው መንግሥት አቋም፣ ሰዎቹ፣ አስተሳሰባቸው፣ አሰራራቸው ያው ነው፣ ምንም አልተነካም፣ ‘ኢትዮጵያ ትቅደም’ የሚለውን መዝሙር በነበዓሉ ግርማና በነአለማየሁ ሞገስ የሚዘመረው እንዲያው ከአንገት በላይ መሆኑ ለማንም ግልጽ ነው። እውነተኛ ለውጥ ስምና ግብርን ያጠቃልላል፤ እንዲያውም ግብር መቅደም ይኖርበታል፤ ስም ይከተላል እንጂ አይቀድምም። በንፁህ ኢትዮጵያን ሕይወት የቀለዱት ጌስታፖዎቹ ሳይነሱና ቅጣታቸውን ሳይቀበሉ፣ አስተሳሰባቸው አቀራረባቸው አሰራራቸው በሰፊው ሕዝብ መብትና ጥቅም መጠበቅ የታነፀ ቅን ሰዎች በስፍራው ሳይመደቡ፣ ማናቸውም ነገር እንዳለ ሆኖ ‘ፀጥታ ጥበቃ’ የሚለውን በ‘ደህንነት ጥበቃ’ ቢለውጡት ምንም አይነት መሻሻል ወይንም እርምጃ እንዳልሆነ መገንዘብ ያስፈልጋል። አለበለዚያማ ማወናበድ አይደለም ወይ?
ከዚህ በላይ በተጠቀሰው መግለጫ ውስጥ ደርጉ ‘የግል ጥቅም አይግባበት እንጂ ለአገሪቱና ለሰፊው ሕዝብ የጋራ ጥቅም ሲባል፣ ለኢትዮጵያ ሕዝብ አንድነት ሲባል ኢትዮጵያዊያን እርስ በርሳቸው መወያየት መከባበር አሳብ ለአሳብ መለዋወጥና ለጋራ ችግራችን መፍትሄ እንዲሹ እንፈልጋለን /መስመር የተጨመረ/ ብሎአል። ከልብ በእውነት በሃቅ ከሆነ አባባሉ ወይም ነገሩ ጥሩ ነው። የሰፊው ሕዝብ ወገኖች፣ ተራማጆችስ የሚሉት ይህንኑ አይደል? እስካሁን ድረስ ሲወተውቱና ሲታገሉ የቆዩት ለሰፊው ሕዝብ መብት፣ ለሰፊው ሕዝብ ደህንነት እንደሆነ ግልጽ ነው፤ ዛሬም ቢሆን የሚታገሉት፣ ህይወታቸውን የሚሰውት ለዚሁ ለተቀደሰ አላማ እንጂ ለሌላ አይደለም። ይህም ወረቀት ቢሆን ‘ሰፊው የኢትዮጵያ ሕዝብ ይቅደም’ በማለት ነው ተጋድሎውን ሲያካሄድ የቆየው፤ አሁንም በዚሁ ተግባር ላይ ነው።
ተማሪው፣ ሠራተኛው፣ ጭሰኛው ገበሬ፣ ወታደሩ፣ መምህሩ፣ ምሁሩ መሬት ላራሹ፣ ለሥራአጡ ሥራ፣ ሥራ ለሠራተኛው ተገቢ የሥራ ዋጋና ዋስትና፣ ትምህርት ጤና ዲሞክራሲ ለሁሉ፣ ከወታደርና ከሲቪል በምርጫ የተውጣጣ ጊዜያዊ መንግሥት አሁኑኑ ይቋቋም፤ ሙሉና ደንበኛው ሕዝባዊ መንግሥት ከ6 ወር እስከ አንድ አመት ድረስ ይቋቋም፣ ወዘተ. በማለት ሲጠይቅ የግል ጉዳይ፣ የግል ጥቅም አግብቶበታል ወይ? ሹመት ስልጣን ገንዘብ ወይም ሌላ ነገር ለግሉ የጠየቀ አለ ወይ? የት ላይነው የግሉስ ጥቅም?
ባሁኑ ጊዜ ኢትዮጵያችንን- ሰፊውን ሕዝብ- የገጠማት ከባድ ችግር መፍትሄ ሊያገኝ የሚችለው የኢትዮጵያን ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ /የሕዝብ መንግሥት/ በመመስረት ነው። ለጊዜው ግን ከወታደርና ከሲቪል በምርጫ የተውጣጣ መንግሥት ይቋቋም፣ ፈላጭ ቆራጭ አምባገነን ወታደራዊ መንግሥት የባሰ ችግር ውስጥ የመቀምቀናል፣ ወዘተ. ማለት የግል ጥቅም ፍላጎት አለበት ወይ? አገር የጋራ ናት ሁሉና እያንዳንዱ ዜጋ ለአገሩ እኩል የማሰብና ትክክል የሚመስለውን መንገድ የማመልከት፣ ለሃሳቡ የመከራከር መብት እንደአለው የታወቀና የታመነ ከሆነ፣ እኛም በዚሁ መብታችን ነው ለመጠቀም የሞከርነው። ደርጉ ግን ይህንን እንደሃጢአትና እንደወንጀል በመቁጠር የብዙ ንፁሃን ኢትዮጵያውያንን ደም አፍሰሶአል፣ ብዙዎች ተደብድበዋል፤አካላተጎደሎ ሆነዋል፣ ታስረዋል፣ ከቀድሞ አሳሪዎቻቸው ጋር ሆነው ‘ፍርድ’ በመጠባበቅ ላይ ይገኛሉ። በዚሁ ምክንያት በተራማጅ የሰፊው ሕዝብ ወገኖች ላይ ከባድ የማጥላላትና የማርከስ የማሳደድና የማጥቃት ዘመቻ በመካሄድ ላይ ነው። ታዲያ ይህ ድርጊት ከዚህ በላይ ከተጠቀሰው ሃሳብ ጋር አይጋጭም ወይ? በፍፁም አያፈርሰውም ወይ? በአፍ የሚነገረው ሌላ ነገር በግብር የሚታየው ደግሞ ፍጹም የተለየ ተቃራኒ ነው። የትኛውን እንመን ታዲያ?
ቃልና ሥራ አብረው መሄድ አለባቸው፤ ሰው ሆነ ድርጅት ሊታመን የሚችለው የሚናገረውና የሚያደርገው አንድ ሲሆኑና ሲስማሙ ብቻ ነው። በደርጉ ዘንድ ግን አብዛኛውን ጊዜ የሚለፈፈውና የሚደረገው በጣም ይለያያሉ፤ ታዲያ ሰፊው ሕዝብ እንዴት ሊያምነው ይችላል?
የአባቶች ምሳሌ፣ ‘የሚያድግ ጥጃ ከገመዱ፣ የሚያጠግብ እንጀራ ከምጣዱ’ እንደሚለው ማናቸውም ነገር የውኃ ሽታ አይነት ቢሆንም ደርጉ በ22ና በ23/2/67 ስለ ንግግር እና ጽሁፍ ነፃነትና ስለሰፊው ሕዝብ የመንግሥቱን ጉዳይ የማወቅ መብት በሰጠው መግለጫ መሰረት የሚከተሉት መፈፀም ይኖርባቸዋል።
- የዜና ማሰራጫ መሳሪያዎች የሕዝብ ንብረት እንደመሆናቸው መጠን በሞኖፖል መያዛቸውና የወታደራዊውን መንግሥት አጉል ዝና ማስተጋባታቸው ቀርቶ ስለአገር ጉዳይ የተለየና ተቃዋሚ ሃሳብ ያላቸው ሁሉ ይህንኑ አስተያየታቸውን ለሰፊው ሕዝብ እንዲገልፁ እንዲደረግ፤
- አሁን በሥራ ላይ ያሉት ቱልቱላ አድርባይ ጋዜጠኞች ቶሎ ብለው ከጋዜጣ ሥራ እንዲገለሉና ሁኔታቸው እየተመረመረ ጥፋተኞቹ ለፍርድ ሸንጎ ቀርበው ተገቢ ቅጣታቸውን እንዲቀበሉ፤
- ዲሞክራሲያዊ መብቶች ሥራ ላይ ይዋሉ፤ ጊዜያዊ ሕዝባዊ መንግሥት ይቋቋም፣ በማለታቸው የተያዙትና የታሰሩት የሰፊው ሕዝብ ወገኖች በፍጥነት እንዲለቀቁ፤
- የእነጥላሁን ግዛውና የነዋለልኝ መኮንን ገዳዮች፣ የሻምበል ባሻ ግብረፃድቅ ተወልደን በማሰቃየት አካላተጎደሎ ያደረጉት ሌሎችንም አገርወዳዶች ያሰቃዩትና ሕይወት ያጠቁት ጌስታፖዎች ተይዘው ለፍርድ እንዲቀርቡና ቅጣታቸውን እንዲቀበሉ፤
- ሌሎችም የኃይለሥላሴ ፍጡሮችና የግፍ ግብረአበሮች ከስልጣን እንዲወርዱና ምርመራቸው ተጣርቶ ጥፋተኞቹ ፍርዳቸውን እንዲቀበሉ፤
- መሰረታዊ መብቶችና ነፃነቶች፣ የንግግርና የጽሁፍ የመሰብሰብ የማህበርና የመደራጀት ነፃነቶች አሁኑኑ ሥራ ላይ እንዲውሉ፤
ደርጉ እነዚህንና የመሳሰሉትን ጥያቄዎች የተቀበለ መሆኑን በይፋ ለሰፊው ሕዝብ እንዲያስታውቅ አስፈልጋል
ዲሞክራሲ ያሸንፋል
ድሉ የሰፊው ሕዝብ ነው።
ከ መ ጥ ፎ ወ ደ ባ ሰ
የወታደር መንግሥት ሥራ ያቀላጥፋል፣ ያፋጥናል፣ በቶሎ ይቆርጣል፤ የቢሮክራሲ ፀር ነው እያሉ የደርጉ መሪዎችና ቱልቱላዎቻቸው ሲናገሩ እንሰማለን፣ ሲጽፉም እናነባለን፣ ምን እንደተሰራና ከየት ወደየት እንደመጣን ዞር ብለን ስንመለከት ግን የምንረዳው ከዚህ አባባል በጣም የተለየ ሁኔታ ነው። አስተዳደሩ በጣም ተጨማልቋል፤ ኢኮኖሚው ከቀን ቀን ወደአዘቅት እየወረደ ነው።የሰፊው ሕዝብ ችግር ከቀን ቀን እየተባባሰ በመሄድ ላይ ነው። የእንቅስቃሴው ተስፋ የውኃ ሽታ ሊሆን ነው ወይ? የደረስንበት ሁኔታ ደብዛዛ ስእል ባጭሩ የሚከተለውን ይመስላል።
የአስተዳደሩ ጉዳይ፣
እንዳልካቸው መኮንን ያጨማልቀውን ያስተዳደር ጉዳይ ደርጉ አባብሶታል። ልጅ፣ ሚኒስቴር እየተባሉ ሲቀለቡ የነበሩትን የንጉሡን ዝርያዎችና የእንዳልካቸውን ጭፍራዎች እስካሁን ድረስ በሚኒስቴርነት አቆይቶአቸዋል። እነበላቸው ጀማነህን፣ እነበለጠ ገ/ፃድቅን፣ እነበላቸው አሥራትን የመሳሰሉትን እልም ያሉ አድሃሪዎች ለውጥ ለውጥ እያለ የሚጮኽው ደርግ ጠንካራ፣ ተራማጅና ቅን አስተዳዳሪዎች በሚያስፈልጉበት በዛሬው ጊዜ ባለስልጣኖች አድርጎአቸዋል። የመሳፍንትን አገዛዝ አጠፋለሁ የሚለው ደርግ ጥቂት መሳፍንትን በእስር ቤት ከማቆየቱ በስተቀር የመሳፍንቱን ሥርዓት ጨርሶ አልነካውም። ግማሾቹም ከላይ እንደጠቀስነው ሚኒስትሮችና እንደራሴዎች ናቸው። ለነርሱ ቁንጮ ንጉሱ ያሳደገውን፣ የፖለቲካ ብስለት የሌለውን፣ የኢምፔሪያሊስቶች አሻንጉሊት የሆነውን አማንን አድርጎአል።
ሚንስተር ተብለው የተሾሙትም ቢሆኑ ከአማካሪነት ደረጃ አልፈው ምንም የሚረባ ነገር መሥራት አልቻሉም። ዛሬ ትላልቅ ውሳኔዎች በፍጥነትና በተቀላጠፈ ሁኔታ መውሰድ ሲገባቸው ሚኒስቴሮቹ ምንም አይነት ውሳኔ ያላደረጉ ፈቃድ ሳያስተላልፉ ቢሮ ታቅፈው ይውላሉ። አነስተኛዋ አሉታዊ ውሳኔ ከክፍል ሹም ወደዴሬክተር፣ ከዴሬክተር ወደመምሪያ ሹም ወደ ሚኒስቴር ሄዳ ለደርጉ ትቀርባለች፤ ተመልሳ ወደታች እስክትወርድ ሕዝቡ ይጨነቃል፣ ይቸገራል፣ይጉላላል። ደርጉ ግን ለዚህ አብይ ችግር ያገኘው መፍትሄ ስም መለዋወጥ፣ ግዛቱን አስተዳደር ማለት፣ መስሪያ ቤቶችን እዚህም እዚያም መቆለል፣ ላንዳንድ ግለሰቦች ትከሻ የሚያጎብጥ ስልጣን ማሸከም፣ ብዙዎቹን ያለ ሥራ ቁጭ አድርጎ የሕዝቡን አንጡራ ገንዘብ በከንቱ ማባከን፤ ሁሉን ነገር እኔ ካላየሁ በማለት ሥራውን መጎተትና ማራዘም ነው።
የድርቁ ጉዳይ፣
ሽመልስ አዱኛ በቴሌቪዥን እየቀረበ ሲደሰኩር ተሰማ አባደራሽ ደቂቃ የማይቋረጠውን ባዶ ልፍለፋውን ያምቦለቡላል። ሁለቱም ባለስልጣኖች በየቦታው እየዞሩ፣ ቼክ እየሰበሰቡ እግዜር ይስጥልን፣ ስለተራበው የኢትዮጵያ ሕዝብ እናመሰግናለን፤ እርዳታው ከፍ ያለ ቢሆንም ችግሩ ደግሞ በጣም ከባድ ነው፤ ወደፊትም በለጥና ጠቀም አድርገው እንደሚሰጡ ተስፋ አደርጋለሁ ወዘተ….እያሉ የኮክቴል ብርጭቆ ሲያጋጩ ይውላሉ። ዋናው ሥራቸው እየዞሩ ገንዘብ መልቀምና ዲስኩር ማፍሰስ ነው። ሕዝቡ ግን አሁንም በረሃብ እንደቅጠል ይረግፋል፤ ቢሮክራሲው እየጨመረ፣ ሥራው እየተጎተተ ድርቁ በመስፋፋት ላይ ይገኛል። ኦጋዴን ሌላው ወሎ ሆኖአል። እነሽመልስ ችግሩን የሚገልጡት በብዙ ሺህ የሚቆጠር ሕዝብ ካለቀ፣ ሰማንያ በመቶ የሚሆነው ከብት ከወደመ በኋላ ነው። ታዲያ ነገሩ ከበፊቱ ምን ያህል ተለየ? እንደራሴው፣ አውራጃ ገዥው /ስሙም ቢለወጥ/ ወረዳ ገዢው፣ እያንዳንዱ ሚኒስቴር ሚሲዮኖቹና የአሜሪካ፤ የእንግሊዝ፤ የጀርመን ሰላዮች የየራሳቸው የልማት፣ የማቋቋሚያ፣ የዚህ የዚያ ፕላን እያሉ በተዘበራረቀ ሁኔታ ውርውር ይላሉ። ተሰማ አባደራሽ ከኪሱ የሚያወጣውን እስታትስቲክስ እንደውዳሴማርያም አንባቢ ወይም እንደ ሰይጣን ጎታች ያወርደዋል። ድርቅ ግን በጸሎት ወይም በምትሀት የሚጠፋ ሳይሆን በተቀላጠፈ ሥራ ብቻ የሚለወጥ በመሆኑ ፈቅ አላለም፤ እንዳውም ብሷል። ችግረኛውም መጠለያ ጣቢያው እየተጣበበ በዋናው ከተማ በኮሚሲዮኑ አካባቢ ጭምር ውጭ ወድቆ ይታያል። ደርጉ ከነቅጥልጥሎቹ በኦጋዴን በኤርትራ በጎሙጎፋ በቦረና ለሚያልቀው ሕዝብ ተጠያቂ መሆኑን የዘነጋው ይመስላል። እነአክሊሉ በወሎ ጉዳይ እንደ ተጠየቁት ደርጉም በእነዚህ ክፍለሃገሮች ጉዳይ ተጠያቂ መሆኑ አይቀርም። ድርቅ መስፋፋቱን ስለአመነ፣ መሪዎቹ ሄደው ስለጎበኙት፣ እርዳታ እርዳታ ብሎ ስለአስተጋባ ብቻ ድርቁ እንዳይስፋፋ የመከላከሉ ኃላፊነት ከራሱ ላይ የሚወርድለት መስሎታል።
የመርማሪ ኮሚሲዮን ጉዳይ፣
በአድሃሪው ፕሮፌሰር መስፍን የሚመራው መርማሪ ኮሚሲዮን የወሎን ጉዳይ ብቻ እንኳን ለማጠናቀቅ ብዙ ወራት ሲፈጅ፣ የአስተዳደርና የፍርድ በደልን፣ ያላግባብ መበልፀግ ምርመራ ለማገባደድ ስንት አመት እንደሚፈጅ ለመገመት ይቻላል። ኃይለሥላሴ ባወጀውና ከሁኔታው ጋር በማይሄድ በተመሰቃቀለ ሁኔታ በወጣ ህግ ላይ ተመስርቶ እየሰራ ምንም ውጤት እንደማያመጣ ሳይታለም የተፈታ ነው። ታዲያ ደርጉ በተለመደው አመንችነቱ ለምርመራ ኮሚሲኑ ከፍተኛ ገንዘብ እየከፈለ በሌላ በኩል ደግሞ የጦር ፍርድ ቤት ያቋቁማል። አቤቱታውን ለምርመራ ኮሚሽኑ ሲያቀርብ የነበረው ሕዝብ እንደገና ለጦር ፍርድ ቤቱ እንዲያቀርብ ታዟል። ልክ የአጼንና የአክሊሉ ኃብተወልድን ተደራራቢ መስሪያ ቤቶች ማቋቋም አይነት አሰራር መሆኑ ነው። ግፈኛውን አፄ ኃይለሥላሴን፣ ሌባውን ልጁን አስፋወሰንን፣ ዘራፊዋን ተናኘወርቅንና ሌሎቹ የንጉሱን ወላጆች እንዳይመረምር ደርጉ ኮሚሲዮኑን ከልክሎአል፤ አንዴ ሲያባብል አንዴ ሲሳደብ እያመቀመቀ የንጉሳዊ ደም ጠባቂ ሆኖአል። ፍርዱ ከተፋጠነና ትክክለኛ ፍርድ ከተሰጠ አድሃሪ ኃይሎችን ለማባበያ፣ ሕዝቡን ለመወናበጃ በመያዣ መልክ ያስቀመጣቸውን መኳንንት ስለሚያጣ የተያዙትን ባለስልጣኖች በቶሎ ለፍርድ ለማቅረብ አይፈልግም። መርማሪ ኮሚሲዮኑ ውስጥም ቢሆን ሥራውን ለማፋጠንና በቶሎ ለማገባደድ የሚፈልጉትን ለሕዝብ ተቆርቋሪ የሆኑ ጥቂት አባሎች ሥራ በወታደሩ ተመራጮችና በአንዳንድ አድሃሪዎች እንዲጎተትባቸው ያደርጋል። እንዲያውም፣ የጉድ ጉድ፣ ያላግባብ የያዛቸውን ተራማጆች እነዶክተር እሸቱ ጮሌንና ኮሎኔል እምሩ ወንዴን፣ የምድር ጦር መሐንዲስና የአርሚአቬሽን አባሎችን: እንዲሁም ሌሎች የሕዝብ ወገኖችን በቅድሚያ ያለ ምርመራ በአወናባጆቹ የጦር ፍርድ ቤት አግብቶ ለማስቀጣት በመዘጋጀት ላይ መሆኑ ተደርሶበታል። ይህም የሚያሳየው ደርጉ ቆርጦ የተነሳው ሥራአጦችን በጥይት ለመደብደብና ተራማጆችን ለማጥፋት ብቻ መሆኑን ነው። ታዲያ ሰፊው ሕዝብ በደርጉ ላይ እንዴት እምነት ሊኖረው ይችላል?
የመሬት ይዞታው ጉዳይ፣
ስለመሬት ይዞታውም የወታደሮቹ መንግሥት ይህንኑ የማመንታት ጠባዩን፣ ዝርክርክ አሰራሩን ያሳያል። በአንድ በኩል አድሃሪው ሚኒስቴር በለጠ የዘመዶቹንና የወገኖቹን፣ እንዲሁም የነዘውዴ ገብረሥላሴን፣ የነተካልኝ ገዳሙን ሰፋፊ መሬቶች ከውርስ ለማዳን ይታገላል። በሌላ በኩል አንዳንድ የደርጉ አፈቀላጤዎች የፊውዳሉን አገዛዝ መሰረት ለማፍረስ መሬትን የሕዝብ ልናደርግ ነው ይላሉ። በጠቅላላው ግን በየቦታው ደርጉ የጭሰኛውን ንቅናቄ ለመስበር ቆርጦ ከመነሳቱ የተነሳ መሪ ሊሆን ይችላል ብሎ የሚገምተውንና በሕዝቡ ዘንድ ተደማጭነት ያለውን ሁሉ በየክፍለሃገሩ ያስራል፣ ያስፈራራል። የመሬት ይዞታን ኤክስፐርቶች አንዴ አንዱን አይነት እንዴ ሌላውን አይነት ህግ አጥኑ እያለ ያወናብዳል። ስለድርቅ ቀበሌዎች ከሌላው አገር የተለየ የመሬት ይዞታ ልናወጣ ነው እያለ ኮለኔል ተሰማ ይዘባርቃል። የመሬት ይዞታ ለውጥ በኤክስፐርት፣ በቀላድ ጣይ ወይም በወታደር ብቻ ሊሰራ እንደማይቻል እና የመሬት ድልድልንም ሆነ ዘላቂ ለውጥ ለማምጣት የሚቻለው በሰፊው ሕዝብ ድርጅቶች አማካይነት መሆኑን ደርጉ አላምን ብሏል። ባለርስትን ከጭሰኛ የሚያስማማ ህግ ይፈልጋል። እንዲህ አይነት ህግ ስለማይገኝ፣ ገዢ መደብ ከተገዢ መደብ ሊስማማ ስለማይችል የደርጉ ልፋት ጊዜ ለማግኘት፣ ፋታ ለማግኘት፣ ስልጣኑን ለማረጋገጥ እንደሆነ በየቀኑ እየጎላ ይታያል። እነደእንዳልካቸው ፋታ ስጡኝ፣ ስድስት ወር ስጡኝ፣ ጥናት ይጠናል እያለ እንደሚያወናብድ አይጠረጠርም። ታዲያ ይህ ማወናበድ እንደማያዋጣ ከነአጤ ኃይለሥላሴ እንኳን ለመማር አይችልም ማለት ነው ?
የዘመቻው ጉዳይ፣
የእውቀትና የሥራ ዘመቻ የተባለውን ዝግጅት እንደ ሌላው የደርጉ ሥራ ሁሉ ዝብርቅርቅ ያለ፣ በቂ ጥናት የሌለው ለማወናበድና ስልጣን ላይ ለመቆየት የተጠነሰሰ መሆኑ እየተገለጠ በመሄድ ላይ ነው። የመሬት ይዞታውን ህግ ከዘመቻው በፊት እናወጣለን ብለው መለፈፍ ከጀመሩ ወደ ሁለት ወር ያህል ሊሆነው ነው። ህጉም አልወጣ ዘመቻውም አልተዘጋጀ። አንዳንድ አስቂኝ የሆኑ ከምእራብ ስርዓተ ትምህርት የተቀዱ ፕሮግራሞች ለዘማቾቹ በአንዳንድ ትምህርት ቤት ይሰጣሉ። በሌሎቹ ገና ይዘጋጃል እየተባለ ተማሪና አስተማሪ ሥራ ፈትቶ ቁጭ ብሎአል። የተማረ ሰው በጠማት አገር የትምህርት ዘመን ዝም ብሎ ይባክናል። በከፍተኛ ደመወዝ ከውጭ አገር የመጡ መምህራን የዚችን የድሃ አገር ሃብት ሳይሰሩ ይበላሉ። ስለዝግጅቱ፣ ስለማስተማሪያ ቋንቋ፣ በሚመጣው አመት በሃኪምነት በመሃንዲስነት በአስተማሪነት በቴክኒክ ሙያ በንግድ ሙያ ወዘተ. መመረቅ ስለሚገባቸው ተማሪዎች መዝመት ወይም አለመዝመተረ ሳይጠና ደርጉ ስለ ዩኒፎርምና ስለ ጫማ ያጠናል፤ ጨረታ ያወጣል፤ ቀለሙን ስፌቱን፣ ዘማቹ የሚታጎርበትን እስር ቤት /ካምፕ/ ፕላን ያስጠናል፤ የቀን አበል እየከፈለ የዩንቨርስቲ መምህራን ማንትስና ምንትስ ቦታ ስልክ እንዳለ አይታችሁ ኑ እያለ ይልካል።
ሕዝቡን እናነቃለን እያሉ እስካሁን ያነቁት በማርያም አካባቢ የሚኖረውን ሕዝብ 12 ሰአት ሙሉ የሚያደነቁር ጡረንባቸውን በማስጮህ ብቻ ነው። አጥኑ ብለው በግድ የሰበሰቧቸውን ምሁራን ይዘው በማርሽና በታምቡር አንጎላቸውን አያዛሉ እንኳን በአሥር ወር በእነርሱ አያያዝ በአሥር አመትም የማይፈጽሙትን የሰገራ ዋፈራ፣ የህንጻ አሰራር ዘዴ፣ የአለባበስና የምግብ አመራረጥ ከንቱ ትምህርት ያዘጋጃሉ። በጠቅላላው ዘመቻው ከመብት ጋር፣ ከሕዝባዊ ድርጅቶች ጋር ተያይዞ ቢሆን ኖሮ፣ በቅንነትና በሃቅ የተወጠነ ቢሆን ኖሮ፣ ‘ሂዱና አስተምሩ’ ሳይሆን ‘ሄደን እንማር’ በሚል ኣላማ የታቀደ ቢሆን ኖሮ፣ በደንቆሮና በጭፍን ግዳጅ እንደጋሪ ፈረስ አይኑን ተጋርዶ አፉን ተሸብቦ በጠመንጃና በሳንጃ ፍራቻ መዝመት ሳይሆን ዘመቻው በውዴታና በዘማቾቹ የሀገር ፍቅር የተገፋፋ ቢሆን ኖሮ እንዴት ያለ ጥሩ ዘመቻ፣ ፍሬያማ ዘመቻ በሆነ ነበር? ሰኞ ማታ በማወናበጃ ቴሌቪዥናቸው ስለኪውባ ወጣቶች ዘመቻ አወናባጅ መኮንኖቻችን ያሳዩት ፕሮግራም የሚያሳየው የእነርሱን አይነት የማወናበጃ ትርኪምርኪ ሳይሆን ከላይ የጠቀስነውን አይነት እውነተኛ ሕዝባዊ ዘመቻ ነው።
ስለ ኢኮኖሚ፣
ደርጉ ሥራ ከጀመረ ጀምሮ የአገሪቱን ኢኮኖሚ ለማንኮታኮት በአጭር የታጠቀ ይመስላል። አስቸኳይ እርምጃዎች በሚኒስቴሮቹ አይወሰዱም፣ በገጠሩም ቢሆን ጊዜያዊ እርምጃ እንኳን ባለመወሰዱ በባለመሬቱም ሆነ በጭሰኛው በኩል እርሻን የማሻሻሉ ጉዳይ ተዳክሟል፤ ጭሰኛው በስጋት ላይ ስላለ እርሻውን ማሻሻል ካቆመ ዘመን የለውም። ባለመሬትና ጭሰኛ ተፋጥጠው በብዙ ስፍራ የእርሻው ሥራ በሚገባ አልተሰራም። በዚህ ላይ ደርጉ ባስከበራቸው የከበርቴ እርሻዎች ውስጥ ከቦዘንተኝነቱ የተነሳ የደረሰው ሰብል እየረገፈ ነው። ጠባቂ ያጡ ከብቶች፣ መሳሪያዎች፣ ንብረቶች በመባከን ላይ ይገኛሉ። የመሬቱ ህግ በመዘግየቱ በሚፈጠረው ግጭት ወደፊት ብዙ ሰብል እንደሚባክን አያጠራጥርም። በከተማም ታክቲካዊ መንገድ መከተል የማይችለው ወታደራዊ ደርግ አነስተኛ ነጋዴዎች አስደንግጦአቸዋል። ያዝ ለቀቅ የሚያደርጋቸውም የውጭ ከበርቴዎች ከውጭ እቃ ማስመጣት፣ ከውስጥ ገዝቶ መላክ እየቀነሱ ናቸው። እንዲያውም አብዛኞቹ ገንዘባቸውን ይዘው እየሾለኩ በማውጣት ላይ መሆናቸው ቀደም ብሎ ታውቋል። ወታደራዊው መንግሥት የወረሰውን የመኳንንት ንብረት እንደማንቀሳቀስ ዝምብሎ ስለጉለተው ኢኮኖሚውን ማንቀሳቀስ ሲችል አዳክሞታል፣ የተጀመሩ ሕንፃዎች እንኳን ቆመዋል፣ አዲስ ኢንቨስትመንቶች ተቋርጠዋል፣ ኑሮ ሽቅብ እየናረ ሲሄድ ሠራተኛውና ንዑስ ከበርቴው በጣም ተቸግሯል፤ ይህ ሁሉ ተደማመሮ የስርአጥ ሰራዊት ያለመጠን እየበዛ ሄዷል።ደርጉ ለሁኔታው ያገኘው መልስ አትናገሩ አትሰብስቡ ሥራ አትፈልጉ እያለ ሥራአጡን በጥይት መደብደብ ብቻ ነው።
በጠቅላላው የትም አገር የፋሽስት አገዛዝ ለሰፊው ሕዝብና ለሃገር የማይበጅ መሆኑ ሲታወቅ የኛዎቹ ፋሽስቶች ሲያመነቱ ስልጣን ከእጃችን ያመልጠናል ብለው በመንቀጥቀጥ፣ ጭሰኛውንና ድሃውን ገበሬ፣ ሠራተኛውን ተማሪውን አስተማሪውን ትልቅ የችግር አዘቅት ውስጥ በመጨመር ላይ ናቸው። የተባ የነቃ አስተዳደር ሲያስፈልገን ደርጉ ቀሰስተኛ ዳተኛ ራስወዳድ ለስልጣን ስግብግብ ሆነብን።ሰፊው ሕዝብ መንገዱ ከእንግዲህ ይበልጥ ግልፅ እየሆነለት በመሄድ ላይ ነው። ደርግ የሚባለው ነገር አላዋጣም፤ መሰረታዊ ለውጥ መምጣት አለበት። ለዚህም የአብዮት ኃይሎች የሚዘጋጁበት ዲሞክራሲያዊ የሆነ ጊዜያዊ ሕዝባዊ መንግሥት ይቋቋም ሲባል አመቅማቂው ደርግ የባጡን የቆጡን እየቀባጠረ መንገዱን መምረጥ አቅቶታል። መውደቂያው እሩቅ አይደለም። ሕዝባዊ ኃይሎች ያሸንፋሉ።
አጫጭር የትግል ዜናዎች
የዘመቻው ተቃውሞ፣
ብዙ በዩኒቨርስቲ የሚገኙ ተማሪዎች ጊዜያዊ ሕዝባዊ መንግሥት እንዳይቋቋም የሚከለክለውን፣ የሰፊውን ሕዝብ መሰረታዊ መብቶች የገፈፈውን፣ የብሔሮችን እኩልነት ትንሽ እንኳን በተግባር ለመግለጽ የማይፈልገውን አጉል ትምክህተኛ ደርግ ትእዛዝ አንቀበልም፤ ‘የእድገት በህብረት’ በሚባለው የእስራት ዘመቻ አንሳተፍም በማለት ወደየቤታቸው ተመልሰዋል። የገጠሩን ሕዝብ እስከ ተቻለ ድረስ በራሱ ቋንቋ ማስተማር ሲገባ አማርኛ ላይ ሙዝዝ በማለቱ ተቆጥተዋል። ወደሰሜን ከሄዱት ተማሪዎች መካከል 150 ያህሉ ከአውቶቡሰ እየወረዱ እንዲመለሱ በወታደሮች መገደዳቸው ተሰምቷል።
በልዩ ልዩ 2ኛ ደረጃ ት/ቤት የሚገኙ ተማሪዎችም የ‘ዘመቻውን’ ፍሬቢስነት በመገንዘብ ተቃውሞአቸውን እያጠነከሩ ነው። መድሃኔዓለም አጠቃላይ 2ኛ ደረጃ ት/ቤት፣ በልኡል መኮንን ት/ቤት በአስፋወሰን አጠቃላይ 2ኛ ደረጃ ት/ቤት ወዘተ. ትልቅ ጥያቄ በዘመቻው ላይ ተነስቷል።
የሕዝባዊ መንግሥት ደጋፊዎች መታደን፣
በተፈሪ መኮንን ት/ቤት የሕዝባዊ መንግሥት ደጋፊዎች ናችሁ በመባል ሁለት መምህራን በቀደም መታሰራቸው ሲገለጥ አንድ አምስት ያህሉ ደግሞ በዚሁ ሰሞን ሳይያዙ እንደማይቀሩ ይነገራል። እነዚህ አገርወዳድ አስተማሪዎች በአንዳንድ አድሀሪና የደርግ ቡችላ በሆኑ የሥራ ጓደኞቻቸው መጠቆማቸው ታውቋል። ጠቋሚዎቹም በፊተኛው የአ.አ. መምህራን ማህበር ሥራ አስኪያጅ ኮሚቴ ውስጥ የነበሩና አሁን በዲሞክራሲያዊ መንገድ መሻራቸውን አንቀበልም ያሉ ናቸው።
የእስረኞች ስቃይ፣
ወታደራዊ አገዛዝን ተቃወማችሁ ተብለው በመታሰር ከሚማቅቁት 11 የገንዘብ ሚኒስቴር ሠራተኞች መካከል ቢያንስ አምስቱ በጥኑ መታመማቸው ተደርሶበታል። ከእስር ቤቱ የተበላሸ አያያዝና ከጠቅላላው ፋሺስታዊ አገዛዝ የተነሳ እነዚህ ወጣት ወንድሞቻችን በትልቅ ስቅይ ላይ ናቸው። የአወናባጁን ደርግ ፋሽስታዊ መልክ ለማየት የነርሱ ሁኔታ በቂ ምስክር ነው።
ንዑስ ደርጉ በጎንደር፣
ባለፈው ሰሞን የጎንደሩ ንዑስ ደርግ ‘ኢትዮጵያ ትቅደም’ የሚለውን ጥሬ ቃል ለማብራራት በጎንደር ቀ.ኃ.ሥ. ት/ቤት ተገኝቶ ነበር። ተማሪዎች መምህራንና የከተማው ሕዝብ ደርጉ ስልጣን ላይ ከመውጣቱ በፊት ጀምሮ የቀረቡት የሕዝብ ጥያቄዎች ለምን መልስ እንዳላገኙ ላቀረቡለት ጥያቄዎች መልስ መስጠት ስላልቻለ እንዳይወጣ ተከልክሎ በብዙ ችግር ለማምለጥ ችሏል።
እንፍራንዝ በተባለችውም አነስተኛ ከተማ የተላኩትን የንኡስ ደርግ አባሎች ሕዝቡ እነዚህማ ከኃይለሥላሴ መንግሥት ጋር ሆነው ሲዘርፉን የነበሩት ወታደሮች ናቸው፤ አሁን ደግሞ መንግሥት ነን እያሉ እንዴት ያታልሉናል በማለት አባርረዋቸዋል።
ማረሚያ፣
ባለፈው እትም/በቁጥር 11/ በትግል ዜናዎች አምድ ላይ ስለ ጳጳሳት ፍቅረነዋይ ስናወሳ ስማቸው ሳይጠቀስ ተዘንግተው የቀሩት የኢሊባቦሩ ሊቀጳጳስ ናቸው።