የሰፊው ሕዝብ ድምፅ
ቁጥር 13፣ ህዳር 3፣ 1967
የፅሁፉ ፍሬ ሀሳብ
መኢሶን በዚህ የሰፊው ሕዝብ ድምፅ እትሙ፣ ለአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች መልእክት ያስተላልፋል።በዚህም ግልጽ መልእክቱ፣ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ሕዝባዊ መንግሥት ሳይቁቋም በገጠሪቱ ኢትዮጵያ እድገት በህብረት የእውቀትና የሥራ ዘመቻ አንሳተፍም ብለው የወሰኑትን እየጠቀሰ፤ አንደኛ፣ተማሪዎች በገጠር ከሕዝቡ ጋር በመዋሃድ ትግሉን ከመቀጠል ይልቅ (ትምሕርት ቤቶች በመዘጋታቸውም) በከተማዎች ሥራ ፈትተው መንከራተታቸው ለቤተስቦቻቸው አላስፈላጊ ሽክምና ለተራማጅ ዓላማዎች አጉዳፊ ስም የሚያሰጥ እንደሆነ ያሳስባል። ሁለተኛም፣ በገጠርና በከተማ ከሕዝቡ ጋር በሚደረጉት ትግሎች እየተደራጁ ማቀነባበር እንድሚኖርባቸው ፖለቲካዊ ምክር ይሰጣል። ስለዚህም የዩኒቨርስቲ የተማሪዎች ማኅበር ሥራዎችና ጋዜጦቻቸው፣ ተማሪዎች በየዘመቱባቸው መቀጠል እንደሚያስፍልግ ያሳስባል። ተማሪዎች፣ በዘመቻው “እንዝመት አንዝመት” እያሉ ከመከፋፈል ይልቅ፣ ጊዜው በሚጠይቀው በጸረ-ፊውዳልና በጸረ-ኢምፔሪያሊስት ትግል ዙሪያ በአንድነት መታገልና ማታገልን እንደሆነ ያስታውሳል።
ሕዝባዊ መንግሥት ተቋቁሞ ዲሞክራሲያዊ መብቶችና ነፃነቶች ሥራ ላይ ሳይውሉ ከትግሉ ሜዳ ፈቀቅ አንልም፣ እድገት በህብረት የእውቀትና የሥራ ዘመቻ በተሰኘውም የወታደራዊው ፈላጭ ቆራጭ መንግሥት ኘሮግራም አንሳተፍም ከሚል ውሳኔ ላይ መድረሳችሁና ከመካከላችሁም ብዙዎቹ በየብሄራቸውና በየክፍለሀገራቸው በመካሄድ ላይ ካሉት የነፃነት እንቅስቃሴዎች ጋር በመቀላቀል አብሮ በመሰለፍ ለሙሉና ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ለመታገል መቁረጣቸው በመሰረቱ የሚደገፍና የሰፊውን ሕዝብ የትግል እንቅስቃሴ ወደፊት የሚያራምድ ነው። ሆኖም ትግሉን በሚገባ ለመቀጠል የወሰዳችሁት እርምጃ ወደ ትክክለኛ ግቡ እንዲያመራ ተማሪዎችም ሆኑ ሌሎች ተራማጆች ሊያስቡባቸው የሚገቡ አንዳንድ ጉዳዩች መኖራቸውን ልናስታውስ እንወዳለን።
በመጀመሪያ ነገር ለመታገል ብላችሁ ከተነሳችሁ ሁላችሁም ጊዜያችሁን በትግል ላይ ማዋል ይገባችኋል። አንዳንዶቻችሁ ወደየገጠሩ ተሰማርታችሁ የትግል ግዴታችሁን ስትፈጽሙ ብዙዎቹ ያለምንም ሥራ በየከተማው ውስጥ ዝም ብለው ሲንከራተቱ ተራማጆችን በጠቅላላው ከማስወቀሱም ሌላ ለወላጆችና ለህብረተሰቡም ምህረት የሌለው ሸክም ይሆናል። ስለዚህ በየገጠሩ ሄደው ከሰፊው ሕዝብ ጋር ለመሰለፍ የማይቻላቸው ተማሪዎች በየከተማው ከሠራተኛውና ከሌላው የሰፊው ሕዝብ ክፍል ጋር ለመዋሃድና ለመደራጀት መሞከር ይገባቸዋል። በጠቅላላውም በየከተማውና በየገጠሩ የምትፈጽሟቸው የትግል ተግባሮች ተፈላጊውን ውጤት እንዲያስገኙ በአጠቃላይና በተቀናበረ መንገድ መመራት ይኖርባቸዋል፣ በግለሰብ ወይንም በትናንሽ ቡድኖች ደረጃ ተወስነው መቅረት አይገባቸውም።
ሁለተኛ፣ በየከተማውና በየገጠሩ የምታካሄዱትን ትግል ለማቀነባበር ድርጅታዊ አንድነታችሁን መጠበቅ ያስፈልጋል። ይህም ማለት በምስጢር ብቻ እንኳን ቢሆን ማህበራችሁ ሥራውን መቀጠል አለበት፣ጋዜጣችሁም በየጊዜው መውጣት አለበት ማለት ነው። ማህበራችሁ ሥራውን ከቀጠለና ጋዜጣችሁም መውጣቱን ከቀጠለ በልዩ ልዩ ክፍለሃገሮች የሚታገሉትን ተማሪዎች እርምጃ ለማቀነባበር የትግል ዜናዎችን በመለዋወጥ የታጋዮችን ሞራል ለማጠናከር፣ ጠቅላላ የትግል መስመራችሁንና የትግል አንድነታችሁን ለመጠበቅ ይረዳችኋል። በግለሰቡና በጥቃቅን ቡድን ደረጃ መታገልን ከመረጣችሁ ሃይላችሁ ተበታትኖ ተውጣችሁ ልትቀሩ እንደምትችሉ ማስታወስ ይጠቅማል። ከሁሉ አስቀድሞ ትግላችሁ ፀረፊውዳል ፀረኢምፔሪያሊስት ፀረጭቆና /ሰብአዊና ብሄራዊ/ መሆኑን ሁል ጊዜ ማስታወስ ያስፈልጋል። ይህ ከሆነ ምንም እንኳን ብዙ የሃሳብ ልዩነት በመካከላችሁ ቢኖር የአንድነታችሁን መሰረት በግልጥ ለመወሰንና ድርጅታዊ አንድነታችሁንና ጥንካሬያችሁን ለመጠበቅ ትችላላችሁ።
ያሁኑ የኢትዮጵያ ሁኔታ የተማሪውን ድርጅታዊና የትግል አንድነት ይጠይቃል። እስካሁን ድረስ ተማሪዎች በኢትዮጵያ ሕዝብ ትግል ውስጥ ትልቅ ኃይል መሆናቸውን በተግባር ገልፀዋል። ከዚህ በፊት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ለማድረግ ያበቃችሁ ድርጅታዊ አንድነታችሁ አሁን በጣም የተዳከመ ይመስላል። እዚህ ላይ ልናስታውሳችሁ የምንፈቅደው የጨቋኝ መደቦች መሳሪያ የነበረው ሰራዊት እንኳን በመካከሉ ያለውን ልዩነት ለጊዜው ጋብ አድርጐ የመንግሥትን ስልጣን ጨብጦ ፀረሕዝብ አስተዳደርን ለመመስረት ሲፍጨረጨር፣ እናንተ ፀረኢምፔሪያሊስትና ፀረፊውዳል የሆናችሁ ምሁራን ደግሞ ከዚህ የበለጠና የተቀደሰ የአንድነት መሰረት እንዳላችሁ መሳት አይቻልም። ልትጠቀሙበት ይገባችኋል። በመካከላችሁ የሃሳብ ልዩነት አሁንም አለ፣ ወደፊትም ይኖራል። ነገር ግን የዚህ ልዩነት መሰረት ከአንድነታችሁ መሰረት ማነሱን ጠንቅቆ ማወቅ ይገባል።
አሁን ለጊዜው በመካከላችሁ ልዩነት ካመጡት ጥያቄዎች አንዱ የብሄሮች ጥያቄ መሆኑ ይታመናል። የብሄሮች ጉዳይ በመሰረቱ ከባድና አጨቃጫቂ ለመሆኑ በታሪክ ተደጋግሞ የተመሰከረ ነው። ስለዚህ ይህ ጥያቄ በጥንቃቄና በረጋ መንፈስ መቅረብ ያስፈልገዋል። የብሄሮች ጥያቄ ክርክር ብዙ ጊዜ ስሜት የመቀስቀስ ዝንባሌ ስላለው ተከራካሪዎቹ በስሜታቸው ብቻ እንዳይመሩ መጠንቀቅ ያሻል። በመሰረቱ አሁን ባገራችን እንደሚታየው በእውነተኛ እኩልነት አብሮ ለመኖር በመፈቃቀድና በወንድማማችነት ስሜት ላይ ያልተመሰረተ በኃይል የተገሃባ ‘የብሄሮች አንድነት’ የስሙ ተቃራኒ የሆነ የፌዝ አንድነት መሆኑን ታውቁታላችሁ። ይህ የፌዝ አንድነት ፈርሶ እውነተኛ የብሄሮች አንድነት እንዲገነባ እያንዳንዱ ተራማጅ ኢትዮጵያዊ ጥረት ለማድረግ ግዴታ አለበት። ይህም ጥረት በትክክል በተግባር ሊገለጽ የሚችለው የገዥው ብሄር አባሎች የብሄራቸውን የበላይነት ስሜት /ሾቪኒዝም/ በመቃወም፣ የተጨቋኝ ብሄሮችም አባሎች የየብሄራቸው ጠባብ ብሄረተኝነት ዝንባሌ /ናሮ ናሽናሊዝም/ በመቃወም፣ ሁለቱም ወገኖች ባንድነት ለብሄሮች እኩልነትና እያንዳንዱ ብሄር የራሱን እድል በራሱ የመወሰን መብቱ እንዲከበር ሲታገሉ ነው።
የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችም ይህን ትክክለኛ አቋም በመውሰድ በተግባር መግለጽ ይኖርባቸዋል። የተጨቋኝ ብሄሮች አባሎች በየብሄራቸው የትግል አንቅስቃሴ መስማታቸው የኢትዮጵያን ሕዝቦች የነፃነት እንቅስቃሴ የሚያፋፍምና ወደፊት የሚያራምድ ነው። ነገር ግን ድርጊታቸው ሁሉ የተሻለ ውጤት ሊሰጥ የሚችለው የየተጨቋኙ ብሄር ትግል ሲጠቃለልና ከጠቅላላው የሰፊው ሕዝብ ፀረ ኢምፔሪያሊስትና ፀረፊውዳል ትግል ጋር ሲቀነባበር መሆኑን አጥብቆ ማሰብ ያስፈልጋል።
በመጨረሻም በድጋሚ ልናስታውሳቸሁ የምንፈልገው የፖለቲካ ድርጅቶች ባልጠነከሩበት በአሁኑ ጊዜ ፋሽስታዊ አገዛዝን ለመቃወም የተማሪዎች የትግልና የድርጅት አንድነት አስፈላጊ መሆኑን ነው። ያንድነታችሁን መሰረት በትክክል ባለመረዳት ድርጅታችሁ ቢፈርስና ኃይላችሁ ቢደክም የሚጠቀመው ‘የተማሪ ነገር ድሮውንስ የልጅ ነገር አይደል’ እያለ የሚያፌዝባችሁ የጠላት ወገን ብቻ ነው። ስለዚህ የትግል አንድነታችሁንና ድርጅታችሁን ማጠንከር ያስፈልጋል። በውስጥ ብቻ ሳይሆን በውጭ ከሚገኙትም ማህበራትና ኢትዮጵያውያን ተራማጆች ጋር አንድነታችሁን በማጠናከር ትግሉን መቀጠልና ማፋፋም ነው።
የተማሪ ማህበራት ከሰፊው ሕዝብ ጋር ይጠንክሩ
የትግልና የድርጅት አንድነት ይዳብር።
መሰረታዊ ለውጥ፡ ምን? መቼ? እንዴት?
ለውጥ ዛሬ በሁላችንም ዘንድ የተለመደ ቃል ነው፣ ረዘም ላለ ጊዜ የብዙዎቻችን ምኞት እንደነበር ባለፈው የካቲትና ከዚያም ወዲህ ተደጋግሞ ታይቷል። ለውጥን ፊት ለፊት መቃወም የሚፈልጉት በጣም ጥቂቶች ሲሆኑ የቀረው ሁሉ የለውጥ ደጋፊ ነው። ብዙዎቻችን እምንለያየው ግን ምን አይነት ለውጥ እሚለው ጥያቄ ላይ ነው።
መሰረታዊ ለውጥ በርከት ካሉ ዓመታት ጀምሮ በኢትዮጵያ ተማሪዎች ማህበራትና ባንዳንድ የሰፊው ሕዝብ ወገኖች አካባቢ ሲሰማ ቆይቷል። በሌላ በኩል ደግሞ መጠነኛ ጥገና ቢደረግ አስተዳደሩ ቢሻሻል የሰፊው ሕዝብ መብት ሊከበርና ኑሮውም ሊሻሻል ይችላል የሚል ነፋስ ሲነፍስ ነበር።
በአገሪቱ ላይ አንሰራፍቶ መላውን ሕዝብ ሲጨቁንና ሲበዘበዝ የኖረው በኢምፔሪያሊዝም ስር የነበረው የመሳፍንት ስርአት የአገሪቱን የኤኮኖሚ አቋም ጨርሶ አበላሸ፣ የጥቂት ሃብታሞችን ጥቅምና ደህንነት ብቻ በመጠበቅ ሰፊውን ሕዝብ በረሃብ መቅሰፍት አስመታው። ከየካቲት 66 ወዲህ የመሰረታዊ ለውጥ ጥያቄ በመላ ኢትዮጵያ እንዳስታጋባ ነው። መሰረታዊ ለውጥ ዋና የጊዜው ጥሪ ነው ለማለት ይቻላል።
ታዲያ መሰረታዊ ለውጥ በርግጥ ምንድነው? መሠረታዊ ለውጥ ምን እንደሆን በትክክል መረዳት ያስፈልጋል። መሰረታዊ ለውጥ ሲባል አንድን አምባገነን የጭቆና አገዛዝ በሌላ አምባገነን የጭቆና አገዛዝ መተካት አይደለም፣ ጌታ የመቀያየር ጉዳይ ሊሆን አይችልም። በአጠቃላይ አነጋገር መሰረታዊ ለውጥ ሲባል በጨቋኝና በተጨቋኝ በበዝባዥና በተበዝባዥ መደቦች መካከል ያለውን የኢኮኖሚና የፖለቲካ ግንኙነት ሙልጭ አድርጐ አፍርሶ ሌላ አዲስ ግንኙነት መመስረት ማለት ነው፣ የተለመዱት የብዝበዛና የጭቆና መሳሪያዎች መፍረስና መንኮታኮት ማለት ነው፣ በባለመሬትና በጭሰኛ በላብአደሩና በከበርቴው መካከል ያለውን የተዛባና አድሃሪ ግንኙነት መፋቅና የሰፊውን ሕዝብ መብትና ጥቅም የሚያስከብርና የሚጠብቅ አዲስ ግንኙነት መመስረት ማለት ነው፣ የፖለቲካ ስልጣንን ከጥቂት መሳፍንትና መኳንንት እጅ ማስገባት ማለት ነው። መሰረታዊ ለውጥ የሁሉም ዜጋ እኩልነት መደብ ብሄር፣ ጾታና እምነት ሳይለይ በትክክል የሚጠበቅበት የፖለቲካና የኤኮኖሚ አቋም መመስረት ማለት ነው። መሰረታዊ ለውጥ ከዚህ ያነሰ ሊሆን አይችልም።
በቁጥር በጣም ያነሱ የገዥ መደብ አባሎች በብዙ ሚልዮን የሚቆጠረውን ሕዝብ የሥራ ፍሬ በመግፈፍ የራሳቸውን ጥቅም ያካብታሉ፣ በርካታው ለፍቶአደር ሕዝብ ሰርቶ ያመረተውን እየተገፈፈ በችግር አለንጋ ይገረፋል። ገበሬው – የገጠር ሕዝብ – በጣም ወደኋላ በቀሩ የእርሻ መሳሪያዎች አርሶ ያመረተውን ሰብል ግማሹን ያህል ለባለመሬቱ አሳልፎ እንዲሰጥ ይገደዳል። ላብአደሩም ለፍቶ የሚያፈራውን የጉልበቱን ፍሬ አይጠቀምበትም፣ አብዛኛው እጅ ለከበርቴው ይሄዳል፣ ላብአደሩ እንዳይሞት ያህል ብቻ ከጉልበቱ ፍሬ በደመወዝ መልክ ጥቂት ይወረወርለታል።
በአነስተኛ ንግድና በልዩ ልዩ የእጅ ሥራ ዘርፎች የሚተዳደረው ንኡስ ከበርቴና ከተማዎቹን ያስጨነቀው የሥራአጥ ሰራዊትም በዚህ በተዳፈነ ኢኮኖሚ ውስጥ ያለአንዳች መተማመኛ የሚንገላወድ ሕዝብ ነው። የነዚህ ሁሉ በዝባዥ የስርአተማህበሩ የበላይ ተጠቃሚዎች የሆኑት መሳፍንት መኳንንት ጥገኛ ከበርቴዎችና የውጭ ከበርቴዎች ናቸው። ስለዚህ የለውጡ ዋና አላማ በነዚህ ተጠቃሚዎችና በተበዝባዡ ሰፊ ሕዝብ መካከል ያለውን የኤኮኖሚ ግንኙነት መቀየር ነው፣ አሁን በሰፊው ሕዝብ ጫንቃ ላይ የተጫነውን የጭቆና ቀንበር አውዘግዝጐ መጣል ነው።
እነዚህንም የሰፊው ሕዝብ ጠላቶች በጠቅላላ መልስ ፊውዳሊዝምና ኢምፔሪያሊዝም ብለን እናቀርባቸዋለን። የፊውዳሊዝም /ባላባታዊ ስርአት/ ዋናው መሰረቱ መሬት ሲሆን የባለርስትና የጭሰኛ ግንኙነት ካልተወገደና የመሬት ይዞታ ከስርመሰረቱ ካልተለወጠ በስተቀር በቀላሉ ሊጠፋ የሚችል አይደለም። ፊውዳሊዝም ለረጅም ጊዜ አንሰራፍቶ በቆየበት እንደኢትዮጵያ ባለው አገር ውስጥ ከንጉሱና ከመሳፍንቱ እጅ ስልጣንን በመውሰድ ብቻ ፊውዳሊዝምን /የባላባታዊ ስርአትን/ እንደመስሳለን ማለቱ ዘበት ነው።
የስርአቱ መጠበቂያ መሳሪያ የሆነው የቅጥር ወታደር ለጊዜው ቢከዳቸውም የኤኮኖሚ ሃይላቸው እስካልተደመሰሰ ድረስ ባለመሬቶች ጽኑ ትግል ማድረጋቸውና መልሰው ስልጣን መጨበጣቸው አይቀርም። በእነርሱ ላይ የሚነሳው የሕዝብ አመጽ የከበርቴውንም ክፍል ስለሚያሰጋው በተለይም በጥቅምና በልዩ ልዩ ዘዴ የተዛመዷቸው የውጭ ከበርቴዎች በሰፊው ሕዝብ ላይ ጦርነት ማወጃቸው እሙን ነው።
ስለዚህ ማናቸውም የሰፊው ሕዝብ ወገን የሆነ ለውጥ ፈላጊ እነዚህን ሁለት የሕዝብ ጠላቶች ፊውዳሊዝምና ኢምፔሪያሊዝም – ከሚፈልገው ለውጥ ጋር አያይዞ መመልከት ይኖርበታል፣ የነርሱን ብርታትና ድካም ከሰፊው ሕዝብ ብርታትና ድካም ጋር በትክክል ማመዛዘን ይኖርበታል።
አገራችን ያለችበት ሁኔታ ሲታይ ለሰፊው ሕዝብ የሚጠቅም እውነተኛ ለውጥ በባላባታዊ ስርአትና በኤምፔሪያሊዝም ላይ የሚደረግ ቁርጠኛ ዘመቻ ነው። በሰፊው ሕዝብ ኃይል እነዚህን ሁለት ጠላቶች በአንድነት መምታት አለበት፣ ሁለቱንም በኃይል በመደምሰስ በሕዝቡ ላይ ያላቸውን የኤኮኖሚና የፖለቲካ ተጽእኖ ጨርሶ ማጥፋት አለበት፣ መሬትን ወደ ሕዝብ መልሶ በአገሪቱ ውስጥ ያሉትን ዋና ዋና የኢንዱስትሪና የንግድ ድርጅቶች ወርሶ ከኢምፔሪያሊስት ተጽእኖ ነፃ የሆነ ብሄራዊ ኤኮኖሚ መገንባት አለበት። ይህን የማያደርግ ለውጥ ዘላቂነት የለውም፣ ከግቡ አይደርስም፣ተመልሶ እነርሱ እጅ መግባት ይሆናል።
ከየካቲት ወር ጀምሮ በተፋፋመው የሕዝብ እንቅስቃሴ የተገኘውን የለውጥ ፍሬ የቀማው በጥቂት ሴረኞች መኮንኖች የሚመራው ወታደራዊ ደርግ መሰረታዊ ለውጥ እንዳመጣ አድርጐ ራሱን በመቁጠር በየእለቱ የሚያደርገውን ፍሬቢስ ድንፋታ እንሰማለን። የወታደራዊውን ደርግ የሥራ ክንውን ስንመለከት አንዳንድ ተነጣላ ድርጊቶችን ከመፈፀምና ውጤቱ አጠራጣሪ የሆነውን ዘመቻ ከማወጅ በስተቀር ምንም የሚጨበጥ ፍሬ አይታይም፣ ይህንንም አተኩሮ ለተመለከተው ምርጦቹ መሰረታዊ ለውጥ እንዳይደረግ የሚከላከሉ የእውነተኛ ለውጥ እንቅፋት መሆናቸውን በግልጥ ያሳያል።
መሠረታዊ ለውጥ ሊያሰኘው የሚችል አንዳችም እርምጃ አልተወሰደ፣ ንጉሱ ጥቂት መሳፍንትና ባለስልጣኖች ከመታሰራቸው በስተቀር ባላባታዊ ስርአቱ እንዳለ ተትቷል። ጭሰኛው ገበሬም ለባለ መሬቱ እንደተለመደው እንዲገብር ታዟል። የውጭ ከበርቴዎችም እንደልባቸው የላብአደሩን ጉልበት እንዲበዘብዙ ተፈቅዶላቸዋል። እንዲያውም በምርጦቹ የሚነዳው ደርግ /የወታደር መንግሥት/ እውነተኛ ለውጥ ፈላጊዎችን የለውጥን አፈቀላጤዎች ትንፋሽና እንቅስቃሴ ለማፈን የሚያደረገው ጥረት ቀላል አይደለም።
ባላባታዊው ስርአት የምርት ሃይሎችና ዘዴዎች እንዳይስፋፉ ወደኋላ በመጐተቱ የእርሻ መሬቶችን በሙሉ በጥቂት ባለመሬቶች እጅ አጠራቅሞ የአርሶበሌውን ገበሬ ጉልበት በመበዝበዝ በአገሪቱ ውስጥ አንዳንድ አነስተኛ ኢንዱስትሪዎች ቢቋቋሙና ንግድ በመጠኑ መንቀሳቀስ ቢጀምርም ከውጭና ከውስጥ ከበርቴዎች ጋር በመሻረክና የፖለቲካ ጥላ በመስጠት ሰፊውን ሕዝብ ምን ያህል ሲበድለው እንደቆየ ከላይ ለመጥቀስ ሞክረናል። ይኸው ባላባታዊ ኤኮኖሚ ዛሬ ተናግቷል፣ በአዲስ ዘዴና በተሻሻለ የምርት ግንኙነት ካልሆነ በስተቀር እንደበፊቱ ሊቀጥል እንደማይችል በግልጥ ይታያል። ልዩ ልዩ ምክንያት ሊሰጠው ቢሞከርም አገሪቱን ያጥለቀለቀው ረሃብ የባላባታዊው ኤኮኖሚ ውድቀት ምልክት ነው፣ የኤኮኖሚው ውድቀት ውጤት ነው። እንደዚህ አይነቱ ሁኔታ ሊፈታ የሚችለው መሰረታዊ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ለውጥ በማድረግ ብቻ ሲሆን ይህን ለውጥ ሊያመጣ የሚችለው የዚህ ለውጥ ባለቤት የሆነው ሰፊው ሕዝብ ብቻ ነው።
ላብአደሩ፣ ጭሰኛውና ድሃው ገበሬ፣ ተማሪው፣ መምህሩ፣ ምሁሩ፣ ወታደሩ፣ ዝቅተኛው ነግዶ አዳሪ ወዘተ. እነዚህ ሁሉ በለውጡ እንቅስቃሴ ውስጥ በሙሉ ልብ መሳተፍ አለባቸው።መሰረታዊ ለውጥ ሊመጣ የሚችለው በዚህ አይነት መንገድ ብቻ ነው እንጂ እፍኝ በማይሞሉ ሴረኞች ወይም በጠመንጃና በሳንጃ በማስፈራራትና በማስገደድ አይደለም። ይህ ደህና ተደርጐ መታወቅ አለበት።
ካለፈው የካቲት ጀምሮ ሲካሄድ የቆየውና አሁንም በመቀጠል ላይ ያለው ሕዝባዊ እንቅስቃሴ የአጠቃላይና የጠንካራ ድርጅትን አስፈላጊነት በጉልህ አሳይቷል። ሰፊው ሕዝብ ልዩ ልዩ የሙያና የመረዳጃ ድርጅቶች አሉት፣ በእነዚህም አማካይነት ውስጥ ውስጡን ሲታገል የቆየ ቢሆንም በእንደዚህ አይነት ድርጅት የመንግሥት ስልጣን መያዝ አለመቻሉን የየካቲቱ እንቅስቃሴ በይፋ አስረድቷል። የትግሉ ፍሬ ሊነጠቅ የቻለው አጠቃላይና ጠንካራ የትግል ድርጅት ሳይኖረው በመቅረቱ ነው። ሴረኞቹ ጥቂት መኮንኖች እስልጣን ኮርቻ ላይ ፊጥ ለማለት የቻሉት በዚህ ምክንያት ነው። ይህ እውነት ብዙ ጊዜ ተደጋግሞ ተገልጧል። ስለሆነም ከላይ እንደተባለው መሰረታዊ ለውጥ ሊመጣ የሚችለው ሰፊው ሕዝብ በደንብ በአጠቃላይ ተደራጅቶ የሚመራው የራሱ የሆነ ከራሱ የወጣ ሰፊና ጠንካራ ተራማጅ ድርጅት ሲኖረው ብቻ ነው። ያለበለዚያ ምርጦች ሴረኞች ለማጭበርበር እንደሚሞክሩት ያለምንም ድርጅት በጠመንጃና በሳንጃ በማስፈራራትና በፍሬቢስ ኘሮፖጋንዳ በማወናበድ አይደለም። ይህ ሆን ብለው የሚፈጥሩት ውዥንብር አንድ ስንዝር እንኳን ወደፊት አያስኬድም፣ እንዲያውም እስካሁን የተደረገውንና የደረሰውን ስንመለከተው ወደኋላ ብዙ ኪሎሜትር ሄደናል።
በጥቂት የተሸጡ መኮንኖች የሚመራው ወታደራዊው መንግሥት የሰፊውን ሕዝብ መደራጀት እንደማይፈልግ ግልጽ ነው። እንዲያውም አጥብቆ የሚቃወም መሆኑን በፋሽስታዊ ድርጊቶቹ በይፋ ገልጧል። ሰፊውን ሕዝብ አግልሎና በጫማው ስር ረግጦ የመንግሥቱን ስልጣን ለብቻው በሞኖፖል የያዘው ዲሞክራሲን አጥብቆ የሚያወግዘው ሰፊው ሕዝብ ጠንካራና አጠቃላይ የፖለቲካ ድርጅት እንዳያቆምና እውነተኛውን መሰረታዊ ለውጥ እንዳያመጣ ነው። የሰፊውን ሕዝብ ጥያቄና ፍላጐት ከምንም ሳይቆጥርና ትክክለኛውን መንገድ ትቶ ጠማማውን መንገድ በመመረጥ ወታደራዊ መንግሥት ያቋቋመው በጥቂት ራስ ወዳጆች የሚመራው ደርግ ወደመሰረታዊ ለውጥ የገሰገሰውን ሕዝባዊ እንቅስቃሴ ለጊዜው ከማጨናገፍ በቀር ሌላ ምንም ፋይዳ ሊሰራ እንደማይችል የታወቀ ነው። በምንም አይነት ከውድቀትና ከመውደም የሚያድነው የለም። መሰረታዊ ለውጥ ግን ለጊዜው ቢዘገይም መምጣቱን ማንም ሊያስቀረው አይችልም።
የሕዝቡ ቀዳማይ ጥያቄ ፊትም አሁንም ሕዝባዊ መንግሥት ነው። ይህም ለቅንጦት ሳይሆን መሰረታዊውን ለውጥ ለማምጣት ጠንካራና አጠቃላይ ድርጅት ለመመስረት ነው። ጊዚያዊ ሕዝባዊ መንግሥት ሕዝቡ ሰብአዊ መብቶቹንና ነፃነቶቹን ተጐናጽፎ በመደራጀት ባላባታዊ ሥርዓትንና ኢምፔሪያሊዝምን እንዲደመስስና እውነተኛውን ዲሞክራሲ እንዲመሰረት ያስችለዋል። በምርጦቹ የሚመራው ደርግ ግን በማጭበርበር የቀድሞውን መንግሥት ባለሟሎች የሰፊውን ሕዝብ ጠላቶች ከፍተኛ ቢሮክራቶችን መርጦ ‘የመማክርት ሸንጐ አቋቁሜላችኋለሁ’ በማለት ዴሞክራሲን ዘቅዝቆ በመስቀል አፌዘባት። በዲሞክራሲ ማፌዝና ሕዝቡ አይኑን አልከፈተም ብሎ መናቅ ራስን ከሁሉ በላይ በማድረግ መለኮታዊ ነኝ ማለት ለአጤ ኃይለሥላሴ እንኳን እንዳልበጀውና በመጨረሻ ከውርደት አዘቅት ውስጥ እንደጣለው መገንዘብ እንዴት ያቅታል? ምርጦቹ ከዚህ ትንሽ ትምህርት እንኳን ለመቅሰም አለመቻላቸው ያስገርማል።
ባሁኑ በኢትዮጵያችን ሁኔታ ድርጅትና ዴሞክራሲ የሚለያዩ ነገሮች አለመሆናቸው ግልጽ ነው። ዴሞክራሲን መጠየቅና ለዴሞክራሲ መታገል ያስፈልጋል። ማስፈለግ ብቻ ሳይሆን ግዴታም ነው። ሌላም ምርጫ ሌላው መንገድ ባርነት የፊውዳሊዝምንና የኢምፔሪያሊዝምን እንዲሁም የፋሽዝምን የብዝበዛና የጭቆና ቀንበር ተሸክሞ ማቃሰት ነው። ከሰላማዊው ሕዝብና ከወታደሩ በምርጫ የተውጣጣ ጊዚያዊ ሕዝባዊ መንግሥት ተቋቁሞ ዋና ዋና የሕዝብ መብቶችንና ነፃነቶችን እንዲያስከብርና ሥራ ላይ እንዲያውል ሁሉም ሀሞቱን ኮስተር አድርጐ አስፈላጊውን መስዋአትነት ተቀብሎ መታገል መጋደል አለበት።የሚያዋጣው መታገል መደራጀት ለከፍተኛ ትግል ለመሰረታዊ ለውጥ ከባዱንና መራራውን ትግል አሁኑኑ ወገብን ጠበቅ አድርጐ መጋተር ነው። ይህ ብቻ ነው ዘለቄታ ያለው፣ ይህ ብቻ ነው የሚያዋጣው።
እንግዲህ ባሁኑ ጊዜ ተራማጅ የሰፊው ሕዝብ ወገኖች ለምን ዴሞክራሲ ዴሞክራሲ የሕዝብ መንግሥት የሕዝብ መንግሥት እንደሚሉ፣ ከወታደሩና ከሰላማዊው ሕዝብ የተውጣጣ ጊዜያዊ መንግሥት እንዲቋቋም እንደሚፈልጉና ለዚህም እንደሚታገሉ ላንዳንድ ሁኔታውን በደንብ ላልተረዱና ተረድተው ደግሞ የግል ጥቅማቸውን በመፈለግ ለማወናበድ ለሚፈልጉ ሁሉ ግልጽ ወሆን አለበት።
ይህ ሁሉ የሚያስፈልገው ከዚህ በላይ ከፍ ብሎ የተመለከተውን አይነት መሰረታዊ ለውጥ ለማምጣት መንገድ እንዲጠርግ ነው፣ ወደዚህ ግብ እንዲያቀርበን ነው፣ እውነተኛውን መሰረታዊ ለውጥ ለማምጣት እንድንችል ነው፣ ከሰፊው ሕዝብ አንዳንድ በሚገባ ያልነቁ ሕዝቦች የፖለቲካ ንቃታቸው የበለጠ ከፍ እንዲል ነው።
ሆኖም አንዳንድ አድርባዩች የሰፊውን ሕዝብ ትግል ዋጋቢስ ለማድረግ ይሞክራሉ፣ የፋሺስቶቹ መሳሪያ በመሆን የሰፊውን ሕዝብ ግንባር ቀደም ታጋዩች ስልጣን ፈላጊዎች ናቸው በማለት ያወግዛሉ፣ ክህደታቸውንና አወናባጅነታቸውን በማይጨበጡና በማይዳሰሱ ከንቱ ቃላት ለመሸፈን ይሞክራሉ፣ ግን እንደቢጤዎቻቸው ከታሪክ ፍርድ አያመልጡም፣ አወናባጅነታቸው ይከሰትባቸዋል፣ የክህደታቸውን ጽዋ ፉት ከማለት አያመልጡም፣ ሥራ ለሰሪው እሾህ ላጣሪው ነውና ድርጊታቸውና ተንኮላቸው ያጋልጣቸዋል፣ አደናቅፎ ይጥላቸዋል።
የእውነተኛ ተራማዶች የሃቀኛ የሕዝብ ወገኖች ቦታ ከሰፊው ሕዝብ ጐን ተሰልፎ ባለፈው የካቲት የፈነዳውን የትግል ቋያ ማፋፋም ነው፣ ለዲሞክራሲያዊው ትግል ለእውነተኛው የሕዝብ መንግሥት ትግል መደራጀትና ማደራጀት ነው። በግንባር ቀደምትነት ሲታገሉ የቆዩትና አሁንም ይህንኑ ስፍራቸውን ይዘው የሚገኙት እርስበርሳቸው መፈላለግ አንድነታቸውን ማጠንከርና መደራጀት ይኖርባቸዋል። ሰፊውንም ሕዝብ ለትግሉ መቀስቀስና ማደራጀት፣ የፖለቲካ ንቃቱ የበለጠ ከፍ እንዲል መካከሉ ገብተው አብረው እንዲሰለፉ ያስፈልጋል። የሬቮሉሽናውያን ታሪካዊ ስፍራ ሰፊው ሕዝብ መካከል ነው፣ የትግሉ ሜዳ እዚህ ነው። የጊዜው ታሪካዊ ተግባራቸውም ከሰፊው ሕዝብ ጋር አብረው በመሰለፍና በመደራጀት ለዲሞክራሲ ለሕዝባዊ መንግሥት የሚያረገውን ትግል ማንቀሳቀስና ከግቡ እንዲደርስ ማድረግ ነው። የእውነተኛ ተራማጆችና ሪቮሉሽናውያን ስፍራ የሰፊው ሕዝብ የፊት ደጀን በመሆን ትግሉን ያላአንዳች ማወላወልና ወደ ኋላ ማለት መምራት ነው።
ፊውዳሊዝም ፋሽዝምና ኢምፔሪያሊዝም ይወድማሉ
ሕዝባዊ መንግሥት ይቋቋማል
ዴሞክራሲ ያሸንፋል
ድሉ የሰፊው ሕዝብ ነው።
የበሬን ምስጋና አህያ ወሰደው
ወይም
የወታደር አስተዳደር ደርግ
ፊት ከወጣ ጆሮ ኋላ የወጣ ቀንድ እዩኝ እንዲል ጐልቶ
ልታይ ልታይ አለ ደርጉ ትናንት መጥቶ።
ሕዝቡ በነቀለው በዚያ ጉቶ ፈንታ
ደርጉ ጉቶ ሆነ መች አለው ይሉኝታ።
ሕዝቡ በነቀለው ባንዱ ጉቶ ፋንታ
መቶ ሃያ ጉቶ ተተክቶ አንዳፍታ
ያደናቁረናል በወሬ ቱማታ።
አጤ ኃይሌ ቢሆን አርበኛች አሳዳጅ
ደርጉም አልቦዘነ በማደን በማፈን ያገሩን ተራማጅ፣
ሁለቱ አንድ ናቸው አንዱ ያንዱ ቅዳጅ።
ማሳውን ያረሰው ቀንበር ተሸክሞ
ፈሩን የቀደደው ቀንበር ተሸክሞ
ኋላም ያበራየ አውድማ ላይ ውሎ አፉን ተሸብቦ
እንዲያ በድካሙ አለሙን መግቦ
የዚያን በሬ ትግል የበሬውን ልፋት የበሬን ምስጋና
አህያ ነጠቀው ምርቱን ተሸክሞ እቤት ወሰደና።
ተማሪና ምሁር ወዝአደር ታጋይ
ባመነበት ፀንቶ ላገሩ ለሕዝቡ እንዲያ ሲሰቃይ፣
ፈር እየቀደደ በፖለቲካ ማሳ
ምርቱን ያመረተው ሲወድቅ ሲነሳ፣
ትግሉ ተፋፍሞ አጤን ሲጥለው
ድንገት ደረሰና ከጥንት የነበረው ወታደር ፖሊሱ
አጤ ደጋፊው
ምርቱን ወሰደና
ፊቱን አዞረና
ጀርባውን ሰጠና
ደርግ በሚል ስያሜ ራሱን ሾመና
ባጤ ባዶ መንበር ቁጭ ቂቢብ አለና
አመስግኑኝ አለ በሌሎች ምስጋና።
ዛሬ ለወጉ አሁን ለወጉ
በመንግሥት ስም በሃገራችን ይገኛል ደርጉ።
ደርጉ ደረሰ ደርጉ ደረሰ
እነሆኝ ድርቁ ይልቁን ባሰ።
አጤ ቢሄድ ጊዜ በፊት በር ገባና
ተተካ በቦታው በስርቆሽ በር ገብቶ ደርጉ አጤን ሆነና።
ባጤ ኃይሌ ጊዜ አፈሙዝ ደቅኖ በተማሪ ላይ
በጤ ኃይሌ ጊዜ አፈሙዝ ደቅኖ በወዛደር ላይ
ባጤ ኃይሌ አፈሙዝ ደቅኖ በተራማጅ ላይ
የፈጀው ጨፍጭፎ ሁሉን ያደረገው የጥይት ሲሳይ
አመስግኑኝ ባዩ ደርጉ አይደለም ወይ?
ተመዞ የነበር የወታደር ሳንጃ በተማሪ ላይ
ተመዞ የነበር የወታደር ሳንጃ በወዝአደር ላይ
ተመዞ የነበር የወታደር ሳንጃ በተራማጅ ላይ
እንደተመዘዘ አሁንም ስናይ
ምን እንበለው ደርጉን ባሳየው ጠባይ?
ልክ እንዳጤ ኃይሌ ተማሪ ሃደለ
ልክ እንዳጤ ኃይሌ ወዝአደር ገደለ
ልክ እንዳጤ ኃይሌ ተራማጅ ገደለ
ገና በጅምሩ በደም ተነከረ በደም ተበከለ።
እምን ላይ ነው ብሎ ተራማጅነቱ
አምን ላይ ነው በሉ ተቆርቋሪነቱ
አምን ላይ ነው በሉ የሰው ልጅነቱ
ስልጣን ከመያዙ ሰው ጭዳ ማለቱ።
ልክ እንዳጤ መንግሥት በደም ኃይል ተፀንሶ
ተፋጥኖ የመጣው ደርጉ እንዲያ ገስግሶ
ለካ ለማፈን ነው ተራማጁን ሁሉ ወዝአደሩን ሁሉ በጥይት ጨርሶ።
ባሰሳ የመጣ ይጠይል ባሰሳ
ደርጉ ላገር ሳይሆን ባገር ላይ ተነሳ።
አጤ ኃይሌ ቢሆን አርበኞች አሳዳጅ
ደርጉም አልቦዘነ በማደን በማፈን ያገሩን ተራማጅ፣
ሁለቱ አንድ ናቸው አንዱ ያንዱ ቅዳጅ።
ሰገሌ ተፈሪን በወሎ ደም ወልዳ
በሃምሳ ዓመት በላይ አስፈጀት ኢትዮጵያን በግፍ አስጠምዳ።
አዲሳባም ደርጉን በወሎ ድርቅ ወልዳ
ይኸው ጀምራለች ኢትዩጵያን ልታወድም በኃይል አስጠምዳ።
በመሃል ሰፋሪ አስታካ ተፈሪ ያች ትንሽ ኩዛ
ከሃምሳ ዓመት በላይ ፈላጭ ቆራጭ ሆነች ሃበሻን ስትገዛ።
የተፈሪ መንግሥት ትናንትና አክትሞ
እሱን የመሰለ ተተካ ፈጽሞ ።
በተማሪ ትግል አያ ደርግ አስታኮ
በወዝአደር ትግል አያ ደርግ አስታኮ
በተራማጅ ትግል አያ ደርግ አስታኮ
ፈላጭ ቆራጭ ሆነ የኢትዩጵያን ሕዝብ ሰብኮ።
ለመሳፍንት ሳስቶ ወታደር ገዳይ
ለመኳንንት አዝኖ ወዝአደር ገዳይ
ፍርድ አዋቂ ዳኛ ፍትህ አደላዳይ
አሁን የት ይገኛል ይህን ደርግ መሳይ
አሁን እንደደርጉ አስተዋይ ማን አለ
አሁን እንደደርጉ ብልህስ ማን አለ
ለኳንንት አዝኖ፣ ለመሳፍንት ሳስቶ፣ ደም
አይፍሰሰ የሚል ድሃ እየገደለ።
ደርጉ ተራቀቀ
በጥበበ ጠለቀ
በአእምሮ ደርጅቶ በእውቀት ጐለመሰ
ደም አይፍሰስ ይላል ደም እያፈሰሰ።
ዛሬ ለወጉ አሁን ለወጉ
በመንግሥት ስም በሃገራችን ይገኛል ደርጉ።
ደርጉ ደረሰ ደርጉ ደረሰ
እነሆኝ ድርቁ ይልቁን ባሰ።
ካምስት ዓመት ሽሽት አጤ ተመልሶ
አርበኛውን ፈጀው ባንዳን አቅፎ ለብሶ፣
ደርጉም ስልጣን ሲይዝ ባጤ ስፍራ ገብቶ
አጫጭር የትግል ዜናዎች
4ኛ ዙር ሊያደርጉ ነው እንዴ?
3ኛ ክፍለጦር 25ኛ ሻለቃ ጄኔራል ጥላሁን ቢሻኔንና ሌሎች መኮንኖችን የንኡስ ደርጉን አባሎችና የአብይ ደርጉን መልእክተኞች አሰሩ። የሚጠይቁት የ7 ብር ጭማሪ መሆኑ ተሰምቷል። የሰሜኑ ንኡስ ደርግ የአቢይ ደርጉን በላይነት አለመቀበሉን አሰምቶአል። የፖሊስ ሰራዊቱም በጌታቸው በኮሎኔል በላቸው ጀማነህ መሪነት ከደርጉ ገሸሽ በማለት ላይ ይገኛል።5ኛ ክፍለጦር እየተባለ የሚጠራው የመሃንዲስ የአርሚ አቬሽን ወዘተ. ሰራዊት ለደርጉ ድጋፉን ከከለከለ ሰንብቷል። እንዲሁም በአየርወለድ በታንከኛ ጦር ውስጥ በልዩ ልዩ ግጭቶች የተነሳ ብዙ ወታደሮች ታስረዋል። የ4ኛ ክፍለጦርና የክብርዘበኛውም ባለሌላ ማእረግ ሕዝቡ በወታደር ላይ በሚያሳየው ጥላቻ ግር ብሎት የደርጉን ነገር ችላ ብሎታል። በጠቅላላው ነገሩ ሲታይ ለ3ኛው ዙር የተደረገውን እንቅስቃሴ ይመስላል። ልዩነቱ ግን ከዚያን ጊዜ ይበልጥ አድሃሪ ሃይሎች መዘጋጀታቸውና አብዩተኞችን ለማጥፋት መቁረጣቸው ነው።ደርጉ በማመንታቱ በመዝረዝረኩ አላስደሰታቸውም፣ አንዳንድ የደርጉ ኘሮፖጋንዳም አልጣማቸውም። የአሜሪካ ኢምፔሪያሊስቶችም ደርጉ ውስጥ ያሉአቸው ቡችሎች ደርጉን በትነው ስልጣን መያዝ ባለመቻላቸው ቅር ተሰኝተዋል። እንግዲህ 4ኛውን ዙር እነርሱም ይፈልጋሉ ማለት ነው። ከሚኒስትሮች አነበላቸው ጀማነህ፣ እነተካልኝ፣ እነሽመልስ እንዲሁም አንዳንደ ቴክኖክራቶችና የዩኒቨርሲቲ አስተማሪዎች በሴራው ውስጥ እንዳሉበት ይገመታል። በጠቅላላው ጊዜው አመቺ ስለመሰላቸው አሜሪካኖችና ቡችሎቻቸው ደርጉን ጥለው ጁንታ ለማቋቋም ተነስተዋል፣ 4ኛው ዙር የነርሱ ይመስላል። ከታሪክ ምንም ጊዜ የማይማሩት አድሃሪዎች የሕዝብን ችግር በማባባስ መቃብራቸውን እንደሚቆፍሩ አልተረዱም።
የገጠሩ ሕዝብ ትግል ተስፋፍቷል፦
በሆሮጉድሩና በጨሊያ ወረዳ ሕዝቡ ተነሳስቶ ለብሄሮች እኩልነትና መሬት ለአራሹ በማለት ትጥቃዊ ትግል ጀምሯል። እንዲሁም በሰላሌ አውራጃ በሚካሄደው ትግል ለጊዜው ከሕዝብ ወገን አራቱ ሰዎች ቢያዙና የሁለቱ – የአቶ ጣቆ ሰኚና የአቶ ሊጄንሶ ወዳጆ- ንብረት በወታደራዊው መንግሥት ቢዘረፍም ትግሉ ቀጥሏል።
ያለአግባብ መበልፀግና ደርጉ፡-
የደርግ አባሎች በየቦታው ሲዘዋወሩ በቀን 25 ብር አበል ያገኛሉ። እንዲሁም ከባለ ስልጣኖች የተወረሱትን መኪናዎች ተከፋፍለው ታርጋቸውን ለውጠው ከተማ ውስጥ ሲዘዋወሩባቸው ይታያሉ።
የስድስት ሰዎች መገደል፡-
ከሻሸመኔ ወደወላሞ ሶዶ መንገድ ላይ ስድስት የሃብታም ገበሬ ተቀጣሪዎች መሬታቸውን በተቀሙ ጭሰኞች ተገደሉ።
የመልካሴዲ ሠራተኞች፡-
የኑሮ መወደድ በመጠኑም ቢሆን ለመቋቋም የደመወዝ ጭማሪ እንዲደረግላቸው ጠይቀው እምቢ የተባሉት የመልካሴዴ ሠራተኞች በጥቂት ቀናት በፊት ጀምሮ ሥራ አቁመው ነበር ። በዚህም ምክንያት በመልካሴዴ የእርሻ ጣቢያ የሰፈረው በመቶ አለቃ አያሌው የሚመራ ፖሊስ የምንሥራ ማቆም ነው እናንት ወመኔዎች እያለ ቀኑን ሙሉ በጉልበታቸው ሲያስቆማቸውና በንብርክክ ሲያስኬዳቸው ውሎአል። እንዲህ ነው የሕዝብ ወገን የሆነ ወታደር እንዲህ ነው የሕዝብ ወገን የሆነ ደርግ።