የሰፊው ሕዝብ ድምፅ
ቁጥር 16፣ ታህሣሥ 4፣ 1967
የፅሁፉ ፍሬ ሀሳብ
መኢሶን በዚህ የሰፊው ሕዝብ ድምፅ እትሙ፣ በመካሄድ ላይ ያለው የለውጥ ጉዞ በቅድሚያ የሚታሰብበት ዋና ጥያቄ፣ “ወዴት ነው የምናመራው?” እና “የጊዜው ሁኔታ ከቀድሞው በምን ይሻላል?” እንደሆነ አስገንዝቦ ዘርዘር ያለ ትንታኔ ይሰጣል። በጊዜው ሁኔታ ላይ ሕዝቡ፣ የጉዞ አቅጣቻችን ወዴት ነው? በሚል ጥርጣሬና ስጋት ውስጥ እንዳለ ያስረዳል። የኑሮም ዋስትናውም እንዲረጋገጥለት ይጠይቃል። ህዳር 14፣ 1967 ዓ.ም. ወታደራዊ መንግሥት በእስራት ላይ ጥፋታቸው በሕግ ተመርምሮ ፍርዳቸውን እየተጠባበቁ በነበሩት ስድሳ ሰዎች ላይ የወሰደው ድንገተኛና ጭካኔ የተሞላበት ግድያ መፈጸሙ ደግሞ ይህንን የሕዝብ ስጋት እንዳባባሰው ያሰረዳል። የግድያ እርምጃውንም፣ “የእብደት ምሽት እርሸና” ሲል ይገልጸዋል። በዚያው ስሞን ደግሞ፣ ወታደራዊ ደርግ በተለይ በኤርትራ ተወላጆች ላይ በሰፊው የአፈሳና የእስራት ዘመቻ እየፈጸመ እንደነበር ዘግቦ፤ ዜጎች ተፈቃቅረውና ተከባብረው በሰላም አብረው የመኖራቸውን እድል እንደሚያመነምነው ያስጠነቅቃል። በኤርትራ ክፍለ ሃገር የተነሳው ፖለቲካዊና ታሪካው ችግር፣ የሽፍቶችና የአጋሚዶ ወንበዴዎች ሥራ እንደሆነ እያቃለሉ ማየት ስህተት እንደሆነና ከመፍትሄው ጎዳናም የሚያደናቅፍ እንደሆነ ያሳሰባል። ከአስራ አራት አመታት ያላነሰ ጊዜ በሚካሄደው ጦርነት፣ ከታሪክም አለመማር እንደሆነ ያስረዳል። በዚህ ጊዜ ውስጥ ሁሉ የችግሩን መንሰኤና ከባድነት ከታሪክ ሳይማሩ፤ ችግሩን በጦርና በጉልበት ለመፍታት መሞከሩ ለምን ያስፈልጋል? ሲለ በብርቱ ያጠያይቃል። የኤርትራ ችግር በመሠረቱ የፖለቲካ ችግር በመሆኑ፤በዲሞክራሲያዊ መንገድ መፍታት የሚቻልበትን አላማ መተለም ተገቢ እንደሆነ ይጠቁማል።
ዛሬ ሰፊው ሕዝብ ራሱን የሚጠይቀው ወዴት ነው የምናመራው? ግባችን ምን ይሆን? ዛሬ ምን ተደረገ? ነገስ ምን ይመጣ ይሆን? የዛሬውስ ሁኔታ ከቀድሞው በምን ይሻላል እያለ ነው።
በከተማና በገጠር፡ በአገር ውስጥና በውጭ አገር ያሉት ኢትዮጵያውያንና የሌሎችም አገሮች ሕዝቦች ዛሬ በአገራችን ውስጥ የስልጣን ጉጉት ያሳበዳቸው እፍኝ የማይሞሉት ሴረኛ መኮንኖች የሚፈጽሙትን ፋሽስታዊ ድርጊት በጥልቅ ሃዘኔታ ይመለከታሉ። በሁሉም ገጽ ላይ ስጋት ጥርጣሬ ብስጭት ቁጣ የጠወለገ ተስፋ ተጽፎ ይታያል፣ ፈገግታ ሳቅ መዝናናት በተስፋ ማንፀባረቅ ከአገራችን ሸሽተው ሄደዋል። አሁን ምን ይደርስብኝ ይሆን? ምን ይመጣብን ይሆን የሚለው ሥጋት ከምን ጊዜውም ይበልጥ እየሰፋና እየጐላ ሄዷል።
ባሁኑ ጊዜ የማናችንም ደህንነት ህልውና ሕይወት አንዳችም ዋስትና የለውም፤ በፋሽዝም የወይን ጠጅ ሰክሮ የጠነበዘ የእብደት ዳንኪራ ይደልቃል። እርግጠኛ አለመሆን፡ አለመተማመን፡ የመኖር ዋስትና ማጣት ወረርሽኝ በአገሪቷና በሕዝቦቿ ላይ ሰፍኗል።
ህዳር 14/67 ሳይታሰብ ሳይጠረጠር ስድሳ ሰዎች በድንገት ተረሽነው በአንድ ጉድባ ውስጥ ዓለምበቃኝ አጥር ሥር ተቀበሩ። ከእነዚህ ውስጥ አብዛኛዎቹ ለ30 ዓመታት ያህል በስልጣን ካርቻ ላይ አንሰራፍተው በመቀመጥ ሰፊውን ‘ሰርቶ አደር’ ሕዝብ ስጋውን በልተው ደሙን ጠጥተው በአጥንቱ ያስቀሩት የኃይለሥላሴ ፍጡሮች ናቸው። ሌሎቹ ደግሞ ያለፈውን የጭቆና መንግሥት በመቋቋም በማንበርከክና በመጣል ከሰፊው ሕዝብ ወገን ተሰልፈው የነበሩ ናቸው። በሰፊው ሕዝብ ላይ ሲያላግጡ የኖሩት የቀድሞ መሳፍንትና ባለስልጣኖች ቅጣታቸውን መቀበል የሚገባቸው ቀደም ብሎ ሲሆን ለብዙ ወራት በእስር ቤት ቆይተው፡ ሕግ ወጥቶ፡ ፍርድ ቤት ተቁቁሞ፡ ፍርዳችሁን ትቀበላላችሁ በመባል ሲጠባበቁ ቆይተው በድንገት ያለምንም በቂ ምክንያት ተደበደቡ።
ለመሆኑ የርሸናው ውሳኔ የተወሰደው፡ የሚረሸኑትስ ምርጫ የተከናወነው በእንዴት ያለ መንገድ ይሆን? እነእንቶኔ እነእንቶኔ ሁሉም ሚኒስትሮች ወይም እንደራሴዎች ወይም…. ሆነው ሳለ በምን ምክንያት ይሆን እነዚያ ሲረሽኑ እነዚህ የቀሩት? ምንም መልስ የለም፤ በደፈናው ‘ጥፋታቸው ተመርምሮ’ ይላል፤ ከዚህ ሌላ ምንም የለም። መሞት አይገባቸውም ነበር ለማለት ሳይሆን የቀድሞዎቹ ባለስልጣኖች ለአሰቸኳይ ፍርድ ቀርበው፡ ጥፋታቸው ተዘርዝሮ እንደ የጥፋታቸው ወዲያውኑ መቀጣት ሲገባቸው ሰባትና ስምንት ወር አስቀምጦ በድንገት መረሸን ምን ትምህርት ይሰጣል ነው። ደግሞስ የሰፊው ሕዝብ ወገን የሆኑ ታጋዮችን ከበዝባዦች ጋር በአንድነት መረሸን ከስልጣን ጥማት የመነጨ እብደትን እንጂ ሌላ ምንን ያሳያል?
በነሻምበል በላይ ፀጋዬ፡ ሻምበል ወልደ ዮሀንስ ዘርጋው በነም/አሥር አለቃ ተክሌ ኃይሌና በሌሎቹም የሰፊው ሕዝብ ወገኖች ላይ የተወሰደው የጭካኔ እርምጃ ሰፊው ሕዝብ እነሻለቃ መንግሥቱ ኃይለማርያምን እነሻምበል ሲሳይ ኃብቴን ወደፈት ይፋረዳቸዋል። የእነዚህና የሌሎችም የምድር ጦር መሃንዲስ ባልደረቦች ደም በራሳቸው ላይ ይጮሃል።
ከህዳር 14 ቀኑ የእብደት ምሽት ርሽናና ከፀረ ሕዝቡ ህግ መታወጅ ወዲህ ወታደራዊው መንግሥት ሥራዬ ብሎ የያዘው ንፁህ አገር ወዳድ ኢትዮጵያውያንን የማፈኑን ጉዳይ ነው። ‘የዘጠና ቀን እሥራት’ የሚባለውን የደቡብ አፍሪቃን ፋሽስታዊ ህግ ገልብጠው ያወጁት እነሻለቃ መንግሥቱ ህግ ያወጁ እንጂ ራሳቸው ህግንና የሰውን መብት ማክበርን ጨርሶ አያውቁም። ‘የሚቃወመንን ሁሉ እንደጐርፍ እናጥለቀልቀዋለን’ እንዳሉት ሁሉ የማያጐበድድላቸውን ማንኛውንም ሰው ለማጥፋት ታጥቀው ተነስተዋል።
ለይስሙላ ፋሽስታዊ ህግ ታወጀ፣ አከታትለው ሰውን በገፍ ማፈስ ጀመሩ፣ አፈሳው አሁንም እንደቀጠለ ነው። ለስሙ ያህል እነደጃዝማች አሉላ፡ እነፍስሃዬ ሃረጐት ወዘተ. ተጠርተው አሥራ ስድስት አሥራሰባት ተባለ እንጂ በአዲስ አበባ እስካሁን የታፈሰው በትክክል ይህን ያህል ነው ለማለት፡ በቀላሉ ለመገመት አይቻልም። ሰው እንደድሮ ከየትም እየታነቀ በመወሰድ ላይ ነው። የአሜሪካን ኢምፔርያሊዝም ውራጅ የለበሱ ወታደሮች /አብዛኞቹ የኃይለሥላሴ ጠባቂዎች የነበሩ ክብር ዘበኞች/ በአሜሪካን አሮጌ ጅፕ ላይ ሆነው በየሰፈሩ እየዞሩ ያፍሳሉ።
የሰሞኑ ፋሽስታዊ እርምጃ ይበልጥ ያተኮረው በኤርትራውያን ወንድሞቻችን ላይ በመሆኑ የሰፊውን ሠርቶአደር ሕዝብ ተፈቃቅዶ በእኩልነትና በወንድማማችነት አብሮ የመኖር እድል በኃይል ሳያመነምነው አይቀርም። ቁጥራቸው በርከት ያለ የነቁ የኤርትራ ተወላጆች— ምሁራን፡ የመንግሥት ሠራተኞች፡ በንግድ ሥራ የተሰማሩ፡ በልዩ ልዩ ሙያ የሚተዳደሩ፡ ሠራተኞችና ሥራአጦች እየተያዙ ወዳልታወቀ ሥፍራ በመወሰድ ላይ ናቸው።
እንደዚህ አይነቱ ድርጊት ምን ትርጉም አለው? የኤርትራ ሕዝብ የራሱን እድል በገዛ ራሱ ለመወሰን ያለውን መሰረታዊ መብት ገፍፎ በኃይል ለመግዛት ከሆነ ከንቱ ድካም ነው። ይህ ከቶ የማይሆንና የማያዋጣ መሆኑን እንዴት ከታሪክ፡ በተለይም ዛሬ ወደአሰራአራት ዓመት ከሆነው የዚሁ ክፍለ ሃገር የትግል ታሪክ ለመረዳት ተሳናቸው?
የኤርትራ ሕዝብ ንቅናቄ በመጀመሪያ ላይ የጥቂት ሽፍቶች፡ የወንበዴዎች ሥራ ነው እየተባለ ቆየ፤ ቀስበቀስ እየጠነከረ ሲሄድ፡ በአረቦች የተገዙ የኢትዮጵያን አንድነት ለማደፍረስ የተነሱ እስላሞች የክህደትና የተንኮል ድርጊት ነው ተብሎ በመሰየም ቀጠለ። ዳሩ ግን የኤርትራ ሕዝብ ትግል እየተስፋፋ ሄደ፤ ከቆላ ወደወይና ደጋ፡ ከዚያም ወደደጋውና ወደመሃል አገር መጣ። የነፃአውጭው ግንባር ከእነኢድሪስ ሞሃመድ፡ ከነኦስማን ሳላህ ሳቢህ አልፎ እነደጃዝማች ተድላ ባይሩን፡ እነኢድሪስ ገላውዴዎስን፡ እነወልደአብን፡ እነአፈወርቅ ኢሳያስን ወዘተ. በመጨመር እስላሙንና ክርስቲያኑን ባንድነት አቅፎ ወደፊት ገሰገሰ።
አሁንም ነገሩን በማጭበርበር የአጋሚዶዎች፡ አገር ለማከፋፈል የተነሱ ጥቂት ወንበዴዎች፣ የራሳቸውን ጥቅምና ክብር የሚሹ፣ የኢትዮጵያ ጠላቶች መሳሪያዎች፣ በእነጋዳፊ እየተረዱ አገራችንን ለአረቦች ለመሸጥ የሚያስማሙ ደላላዎች ወዘተ. እየተባሉ ተወገዙ፣ የጦር አስተዳደር የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታወጀ፤ ነገሩ እየገፉ መጣ። በዛሬው ጊዜ ወታደር ከሰፈረባቸው ቀበሌዎች በስተቀር አብዛኛው አገር በነፃ አውጭው ግንባር ቁጥጥር ስር መሆኑ የታወቀ ነው።
ኃይል የማያዋጣ መሆኑን፡ ጉዳዩ መፍትሄ ሊያገኝ የሚችለው በዲሞክራሲያዊ መንገድ፡ በውይይት በእኩልነት ወዘተ. መሆኑን እንዴት ከአለፈው መገንዘብ ያቅታል? እነሻለቃ መንግሥቱ ይህን ቁልጭ ያለ እውነት ማየት አቅቷቸው፡ መሳሪያ በብዛት እናስመጣ፣ ወታደር በብዛት ወደኤርትራ ልከን የነፃአውጭውን ግንባር በኃይል እንደምስሰው፣ በል እንግዲህ አስፈላጊውን ትእዛዝ ስጥ ብለው ጄኔራል አማንን ቢያዙት አይሆንም፡ ይህ አያዋጣም፡ ነገሩ በሰላም እንጂ በኃይል ሊፈታ አይችልም ብሉ ስለመለሳቸው በመካከላቸው መግባባት ጠፍቶ አማን መስዋእት እስከመሆን በቃ። ጉዳዩ አሳዛኝ የተወሰደውም እርምጃ የተሳሳተ ከመሆኑም በላይ ሰሞኑን በአዲስ አበባ የተጀመረው የኤርትራውያን መታፈስና መታሰር በእሳት ላይ ቤንዚን እንደመጨመር የሚቆጠር ነው። ስለሆነም ድርጊቱን መላው የኢትዮጵያ ሰፊ ሕዝብ ሊኮንነው ይገባል።
የሌሎቹም ብሄሮች አባሎች፡ ለምሳሌ ኦሮሞዎች ትግራዮች በሰሞኑ ፋሽስታዊ ድርጊቶች መነካታቸው እሙን ነው። ከሌሎቹም ክፍሎች የነቁት፡ ለወገን ለሃገር ለሰፊው ሕዝብ ተቆርቋሪ የሆኑት፡ በርከት ያሉ ተራማጆች መታፈሳቸውና ወደአልታወቀ ስፍራ መወሰዳቸው የታወቀ ነው። ብዙ ሰዎች የደረሱበት ጠፍቷል።
በወታደራዊው መንግሥት ስም ስልጣን ኮረቻ ላይ ወጥተው ሰማይ ምድር ለዞረባቸው ߵለምርጦቹߴ ጥቂት መኮንኖች፡ ለነሻለቃ መንግሥቱ ኃይለማርያም፡ ለነሻምበል ሲሳይ ኃብቴ፡ ለነሻለቃ አጥናፉ አባተ፡ ለነሻለቃ አሥራት፡ ለነሻለቃ ኪሮስ፡ ለነመቶአለቃ መንገሻ፡ ለነመቶአለቃ ስለሺና ለስልጣን ጓደኞቻቸው ሁሉ አንድ መልእክት አለን፣ ትክክለኛውን መንገድ አልያዛችሁትም፣ የያዛችሁት መንገድ፡ የምትከተሉት መመሪያ በፍፁም አያዋጣም፣ የኢትዮጵያን አንድነት እንጠብቃለን ስትሉ እንዳታፈራርሱትና አገሪትዋን እንዳትገነጣጥልዋት፡ ስፊውን ሕዝብ አቃቅራቸሁ ሆድና ጀርባ እንዳታደርጉትና ለብዙ ዓመታት እንዳትለያዩ ያሰጋል እንላለን። የምትከተሉት መንገድ ወደጥፋት እንጂ ወደ ልማት፡ ወደማነጣጠል እንጂ ወደእውነተኛ አንድነት ከቶ አይመራም እንላለን። እንደ ኢትዮጵያ ያሉ፡ በውስጣቸው በቋንቋ በባህል በሃይማኖት የተለያዩ ብሄሮች ነገዶች ጎሳዎች የሚኖሩባቸው አገሮች ዘላቂና ቋሚ የሆነውን አንድነታቸውን ለመገንባት የሚችሉት በኃይልና በጭቆና ሳይሆን፡እያንዳንዱ ብሄርና ነገድ የራሱን እድል በገዛ ራሱ እንዲወስን ያለውን መሰረታዊ መብት በማወቅና በማክበር ብቻ ነው። በእውነተኛ እኩልነት፡ በመፈቃቀድና በጋራ ጥቅም ላይ የተመሰረተ አንድነት መሰረቱ የፀና፡ ዘላቂነት ያለው አንድነት ነው። ያለዲሞክራሲ፡ ያለእኩልነት፡ ያለመብት እንድነት ሊኖር አይችልም። እውነተኛ አንድነት የሚመነጨው ከዲሞክርሲ፡ ከእኩልነትና ከመፈቃቀድ እንጂ ከጭቆና አይደለም። በእውነተኛ እኩልነትና በጋራ ጥቅም ላይ የተመሰረተውን እውነተኛ አንድነት የሚቃወም የሚጠላ ሕዝብ አለ ለማለት በጣም አስቸጋሪ ነው። በአንድነት ለመኖርም ሆነ ላለመኖር መወሰን ያለበት እያንዳንዱ ብሄር ራሱ ነው።
ዛሬ ኢትዮጵያን ሰንጎ የያዛት ችግር የብሄሮች ጥያቄ ብቻ እንዳልሆነ ከዚህ በፊት በዚህ ጋዜጣ ውስጥ በመደጋገም እንዳመለከትን የሚታወስ ነው። ለብሄሮች ጥያቄም ሆነ ለሌሎቹ ችግሮች ምንጩና መሰረቱ በአገሪቱ ባላባታዊ ሥርዓት በማንሰራፋቱ የተፈጠረው የእውነተኛ እኩልንት መጥፋት፡ የጭቆናና የብዝበዛ መስፋፋት፡ በጠቅላላውም የዲሞክራሲ መደምሰስ ነው።
እስከ መስከረም 2/67 ድረስ ለደረሰብን በደልና ችግር፡ ውድቀትና መቆርቆዝ- ለረሃቡ ለቸነፈሩ ለእልቂቱ- በቅድሚያ ተጠያቂው አጤ ኃይለሥላሴና ግበረአበሮቻቸው ነበሩ። ከተጠቀሰው ጊዜ በኋላ ግን በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ለሆነው መባባስና የበለጠ ውድቀት ማነው ሃላፊው? ተጠያቂው ማን ይሆን?
ዛሬ ߵምርጦቹߴ በረሃብ የሚሰቃየውን ሕዝብ ግብር ክፈል ብለው ሰንገው በመያዝ የተሰበሰበውን ገንዘብ በገፍ እያወጡ ለወታደሩ መደለያና መሸንገያ በማድረግ ገጠሩን ሳይሆን እንደ አዲስ አበባ ያሉትን ከተሞች በቁጥጥራቸው ስር ቢያደርጉም፡ የተማረውንና የነቃውን፡ ተማሪውን ሠራተኛውን፡ ምሁሩን፡ በጠቅላላው ሰላማዊውን ሰፊ ሕዝብ አስቀይመውታል፣ አሳዝነውታል፣ ነጥለውታል፣ የገዛ እንቅስቃሴውን ነጥቀው የበይ ተመልካች አድርገውታል።
በሰፊው ሕዝብ የተጠየቀው አይነት መንግሥት ተቋቁሞ ቢሆን ኖሮ ዛሬ ሁኔታችን ሌላ በሆነ ነበር። የኤርትራ ጉዳይ ዲሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ መፍትሄ ያገኝ ነበር፣ ወይም ለማግኘት ይቃረብ ነበር፣ ከታጋዩም ሕዝብ ሆነ ከወታደሩ ብዙ ሕዝብ አያልቅም፡ ደም እንደውሃ አይፈስም ነበር፣ አንድነታችን የበለጠ ይጠነክር ነበር፣ ለጥፋትና ለእልቂት የሚባክነው ገንዘብ ለልማት፡ የሰፊውን ሕዝብ የኑሮ ደረጃ ከፍ ለማድረግ ይውል ነበር፣ የረሃቡም ሁኔታ ፈጽሞ ባይጠፋም ሌላ መልክ ይይዝ ነበር፣ መስፋፋቱ ቀርቶ እየጠበበ ይሄድ ነበር፣ የመሬት ይዞታም ጉዳይ መፍትሄውን ወደማግኘቱ ይቃረብ ነበር። ኢትዮጵያ የሰው ልጅ መሰረታዊ መብቶችና ነፃነቶች የሚከበሩባት፡ ዲሞክራሲ የሰፈነባት አገር ትሆን ነበረ እንጂ የፋሺዝም ዙፋን አትሆንም ነበር። ተማሪው አስተማሪው ምሁሩ ሠራተኛው ወታደሩ ገበሬው በአንድነት ትግሉን ከፍጥረት ጋር ከመሬትና ካካባቢው ጋር ያደርግ ነበር። የገጠሩ ዘመቻ ፍሬ ሊሰጥ ይችል ነበር።
… ይህ፡ሁሉ እንዳይሆን እንቅፋት የፈጠሩት፡ ሰፊው ሕዝብ የከፋ የችግር ማጥ ውስጥ እንዲወድቅ ያደረጉት፡ ወደዚህ አደገኛ ሁኔታ ያደረሱንና አሁንም ወደባሰ ጥፋት የሚገፉን እነሻለቃ መንግሥቱ ኃይለማርያም መሆናቸውን ደህና አድርገን እንድንገነዘበው ያስፈልጋል። አንድ ቀን እንደ ቀድሞዎቹ በደለኞች እነርሱንም የኢትዮጵያ ሰፊ ሕዝብ እንደሚፋረዳቸው አይጠረጠርም።
የኢትዮጵያ ሰፊ ወታደር ሆይ. ከሰፊው ሕዝብ አብራክ የወጣህ መሆንክን ትዘነጋዋለህን? የታጠቅኸው መሳሪያ ከየት እንደመጣ፡ ማን እንደገዛው፡ ደምወዝህን የምትለብሰውን ልብስ፡ ሰላማዊውን ሕዝብ ለማደን በከተማና በገጠር የምትዘዋወርበትን መኪና፡ ይህንኑ ስታደርግ የሚከፈልህን የውሎ አበል ላቡን አንጠፍጥፎ ያፈራው ሰፊው ሠርቶአደር ሕዝብ መሆኑን ልትዘነጋው አይገባህም። ባስታጠቀህ መሳሪያ መልሰህ ወንድምህን አባትህን ልጅህን ሚስትህን እህትህን ልትመታበት? እንዴት ሊሆን ይችላል? ኃይለሥላሴ ሲጠቀምብህ ነበር፣ አሁን ደግሞ እነሻለቃ መንግሥቱ እነሻምበል ሲሳይ ሊጠቀሙብህ ነው። ከፊተኛው ምንም አልተማርክም ማለት ነው ወይ? ይህማ ታጥቦ ጭቃ መሆኑ አይደለም እንዴ?
ባንተ ስም፡ አንተን መሳሪያ በማድረጉ ትልቅ ጥፋት በመደረግ ላይ ነው፣ የብዙ ንፁሃን ወንድሞችህና እህቶችህ ደም በመፍሰስ ላይ ነው፣ ብዙዎች ለሃገርና ለወገን ለቆርቋሪዎች እየታረሱ በመሰቃየት ላይ ናቸው። እነዚህ በተንኮልና በሥራ ውስጥ ውስጡን ተመራርጠው ስልጣን የጨበጡት ትእቢተኞች ወዴት እንደሚመሩን ትገነዘበዋለህ ወይ? ታዲያ ከተገነዘብከው፡ በትክክል ወዴት እነደምንጓዝ ከተረዳኸው እንዴት ዝም ብለህ ትመለከተዋለህ? ከዚህ በፊትም ደጋግመን እንዳመለከትነው የምናመራው ወደርስበርስ ጦርነት ነው፣ ወደርስበርስ ፍጀት ነው፣ ደም አናፈስስም የሚሉት ወደደም ውቂያኖስ ሊወረውሩን ነው። አዎን ከገደል አፋፍ ላይ ደርሰናል፤ ግን እስከመቼ ድረስ ነው ዝም ብለህ መሳሪያ የምትሆን? እንዴት ወደጥፋት ስንሮጥ ዝም ብለህ ታያለህ? እንዴትስ አብረህ ጠፊ መሆንክን ዘነጋኸው? እያወቅህ ዝም ካልክ ውሎ አድሮ ከሰፊው ሕዝብ ብዙ ጥያቄ እንደ ሚኖርብህ ልትገነዘበው ይገባሃል። ነገረ ጀንበር ካለ ሩጥ አባት ካለ አጊጥ ነው።
የኢትዮጵያ ሰፊ ሕዝብ ሆይ! ለብዙ ዘመናት ስትበዘበዝና ስትጨቆን ኖርክ፣ የብዝበዛውንና የጭቆናውን ቀንበር ሰባብረህ ራስህን ነፃ ለማውጣት ከባድ ትግል ስታደርግ ቆየህ፣ ካለፈው የካቲት ጀምረህ የትግልህን እንቅስቃሴ በገሃድ ስታካሂድ ቆይተህ በመጨረሻ ላይ ጥቂት ሴረኛ መኮንኖች መጥተው፡ አንተን የትግሉን ባለቤት ገለል አድርገው በኃይለሥላሴ ኮርቻ ላይ ከተገጠበው ትከሻህ ላይ ተቀመጡ። አጤ ኃይለሥላሴ የምንወደውና የሚወደን ሕዝቦችን እያሉ በመሸንገል የላብህን ፍሬ እያለቡ ውጭ አገር ይደበቁ እንደነበር ሁሉ አሁንም ߵምርጦችߴ መኮንኖች የድሃ ልጆች ነን እያሉ ቤሳቤስቲን ሳታገኝ ሰብአዊ መብትህን አጥተህ፡ አይንህን አልከፈትክም በሚል አንሃሳ ምክንያት በሞግዚትነት እየቀጡ ሊያሳድጉህ ይዛበቱብሃል።
ከኢምፔሪያሊዝም ጋር ተሻርከው በአገርና በውጭ አገር ከበርቴዎች ያስግጡሃል፤ ባድርባይ ጋዜጠኞችና ሊሾሙብህ በሚሹ አንዳንድ ፍርፋሪ ለቃሚዎች እምቢልታና ተልቱላ እያስነፉብህ ሊያወናብዱህ እንደተነሱ ሳትነቃባቸው አልቀረህም። ሴረኞቹ ጥቂት መኮንኖች ቀጥቅጠውና ረግጠው ከትከሻህ ላይ ፊጥ ለማለት ከአንተው የወጣውን፡ ፈላጭ ቁራጭህ የሆነውን ሰራዊት፡ አንተን አስጨንቀው የሰበሰቡትን የግብር ገንዘብ በገፍ እያስታቀፉ ባንተ ላይ መሳሪያውን እንዲያዞር በማድረግ ላይ ናቸው፤ ሰብአዊ መብትህን የሚደመስሰውን ፋሽስታዊ አዋጅ አውጥተው በአምባገነንነት ወንድምህን እህትህን ልጅህን በማሰርና ወደአልታወቀ ስፍራ በማጋዝ ላይ ናቸው።
ይህ ሁሉ ለምን ይሆናል? እንዴት ብርሃን አገኛለሁ ስትል እልም ካለው ጨለማ ውስጥ ትጣላለህ? እንዴት ይህን ሁሉ ግፍ ተቀብለህ ለመኖር ትችላለህ? በረሃብ በቸነፈር እንደ ቅጠል ትረግፋለህ፣ ችግርህ እየባሰ ሄደ እንጂ አልተሻሻለም፣ ከለውጡ ወዲህ ለመሆኑ ምንድነው ያገኘኸው? መሬት ላራሹ መቼ ሥራ ላይ ዋለ? ሥራአጡ መቼ ሥራ አገኘ? ረሃብተኛው መቼ እህል ውኃ አገኘ? ከመስከረም ወዲህ ሁሉም ተባባሰ፣ ከአር ዘሎ ቅዘን ሆነ እንጂ ላንተ ምንም አልወደቀልህም፣ የነበረህን አጣህ፣ ቅርስህን አሟጠጥክ እንጂ ሰባራሳንቲም አላገኘህም።
በገጠር ያለኽው ጭሰኛና ድሃ መሬት ገፊ ተነስተሃል፣ በማይቀረውና አሁንም በመጠኑ በሚካሄደው የመደብ እርስበርስ ጦርነት ውስጥ ተሰልፈሃል፣ ውጊያውን ጀምረሃል፣ የሚያዋጣው ይህ ብቻ መሆኑን ደህና ተገንዝበኸዋል፣ ግን እንድትደራጅ ያስፈልጋል፣ አንድነትህን ለማጠንከርና ድልን ለመቀዳጀት የምትችለው ከመደብ ወንድምህ፡ ከቢጤህ ጋር መሬትን ላራሹ ለማስደረግና ሰብአዊ መብትህን ለማስከበር በተጣራ አላማ ታጥቀህ መደራጀት ለዘላቂው መፍትሄ ዋስትና ነው። ድርጅት ኃይል መሆኑን በተግባር መግለጫው ጊዜ አሁን ነው።
በከተማ ያለኸው ሰፊው ሕዝብ፡ የወታደር ፋሽስታዊ አገዛዝ ዛሬ ጡንቻውን የሚፈትነው ባንተ ላይ ነው፣ የጭቆናው ቀንበር የተጫነው፡ ፋሽስዊው ህግ በመሞከር ላይ ያለው ባንተ ላይ ነው፣ በቀላሉ በመጠቃት ላይ ያለኸው አንተ ነህ፣ አሞትህን አኮሳትረህ ታጥቀህ፣ መነሳት ብቻ ነው የሚያዋጣህ፣ የባርነት ኑሮ ከመኖር ታግለህ መሞት ይሻልሃል፤ የተጣለብህን ጠላት ድል ልታደርገው የምትችለው በመደራጀት ብቻ ነው። መሰረታዊ ሰብአዊ መብትና ነፃነት፡ የሙሉ ስብእና ክብር፡ መሬት ላራሹ፡ ትምህርት ጤና ሥራ፡ ሕዝባዊ መንግሥት ሊመጣ የሚችለው በልመና በፀሎት እንዳይደለ ደህና አድርገህ ልትረዳው ይገባሃል፤ ብዙ መስዋአትነት የተቀበልክለት የትግልህ እንቅስቃሴ ፍሬ የተቀማው ለምን ይመስልሃል? በደንብ ስላልተደራጀህ፡ አጠቃላይና ጠንካራ የትግል ድርጅት ሳትፈጥር ስታመነታ በመቆየትህ ብቻ ነው፤ ሌላ ምክንያት የለውም። ለመብቶችህ ዋስትና ሊሰጥ የሚችል በቁጥጥር ስር የሆነ የራስህ መንግሥት ሊኖርህ የሚችለው፡ ኑሮህ ሊሻሻልና ሊሟላ የሚችለው፡ ከየካቲት 1966 ጀምረህ በይፋ ስታስተጋባቸው፡ ፊትለፊ ገጥመህ የታገልክላቸው ጥያቄዎች ደንበኛ መልሳቸውን ለማግኘት የሚችሉት በደንብ ተደራጅተህ ትግልህን በስልት ስታካሄደው ብቻ ነው። ይህን ደህና አድርገህ ልትገነዘበው ይገባል። ለዚህ ውሎ ማደር፡ ማመንታት፡ ጊዜ መፍጀት አስፈላጊ ካለመሆኑም በላይ ትልቅ ጉዳት አለው።
ሰፊው የኢትዮጵያ ሕዝብ ሆይ! ካለፈው የካቲት ጀምረህ ብዙ መንገድ ተጉዘሃል፣ ብዙ ድሎችንም ተቀዳጅተህ ነበር፣ አሁንም ቢሆን ሴረኞቹ የትግልህን ፍሬ ምንጊዜም ቢሆን ቀምተውህ አይቀሩም፣ የትግል እንቅስቃሴ ቋያ ገና አልበረደም፤ እንዲያውም በመፋፋምላይ ነው። በሚገባ ባለመደራጀትህ፡ ትግልህ ለጊዜው እንኳን በከተማ ደከም ያለ ቢመስልም፡ ካብራክህ የወጡት ወጣቶችህ በግንባር ቀደምነት ከመጋፈጥ ወደኋላ ያሉበት ጊዜ ፍፁም የለም። ከዚህ በፊት ለብዙ ዓመታት ኃይሥላሴን እንደታገሉት ሁሉ፡ አሁንም አዲሶቹን ጨቋኝ ፋሽስታዊ ኃይለሥላሴዎች ላንዲት ሴኮንድ እንኳን ሳያመነቱና ወደኋላ ሳይሉ ይጋጠሟቸዋል። ትግላቸው ያንተ ትግል በመሆኑና ትግልህ ትክክለኛና ሃቀኛ መሆኑን በሙሉ ልብ ስለሚያምኑበት ለዚህ ትልቅ አላማ በምንም አኳኋን ከቶ ከጎንህ አይለዩም፤ ባንተ ትግል ባንዲራ ስር ተሰልፈው መሞቱን እንደትልቅ ሰማእትነት ይቆጥሩታልና። ከዚህ ሲኦል ከዚህ ባርነት ራስህን የምታወጣ አንተ ብቻ መሆንህን ግን አትዘንጋ፣ ሌላ ቤዛ የለህም፣ አንተው ነህ የራስህ ቤዛ። ድሎችህ ፍሬቢስ እንዳይሆኑ፡ እንዳለፈው አወናባጆችና ሴረኞች ፍሬውን እንዳይቀሙህ ተደራጅ! ተደራጅ! አሁንም ሁል ጊዜ ተደራጅ! ድርጅት በእርግጥ ኃይል ነው። በብዙ አገሮች በብዙ ሕዝቦች ዘንድ የተፈተነ፡ ተወዳዳሪ የሌለው፡ ከአቶሚክ ቦምብ የበለጠ ኃይል ድርጅት ነው፣ ይኸውም በደምብ ወንድማማችነት ላይ የተመሰረተ አጠቃላይና ጠንካራ ድርጅት ነው።
በኤርትርትራውያን ወንድሞቻችንና በሌሎችም ተራማጆች ላይ
በመፈፀም ላይ ያለውን ፋሽስታዊ ድርጊት አጥብቀን እናወግዛለን፣ እንኮንናለን፣
ፋሽስታዊውን የጥቂት ሴረኞች መንግሥት በሙሉ ኃይላችን እንቃወማለን፣
የዴሞክራሲያዊ መብታችን ዋስትና ለሆነው ሕዝባዊ መንግሥት
እንደራጅ፣ በቆራጥነት፡ ያለምንም ማመንታትና ያለማወላወል ባንድነትና
በህብረት እንታገል፣ ወደፊት እንጂ ወደኋላ አንበል፣
ድሉ የሰፊው ሕዝብ ነው።
አ ጫ ጭ ር የ ት ግ ል ዜ ና ዎ ች
የትግራይ ቋንቋ ተናጋሪዎች በገፍ እየታፈሱ ታስረዋል፡-
በአዲስ አበባ ውስጥ በፈነዱት ሦስት ቦንቦች አስታክኮ ፋሽስታዊው መንግሥት የትግራይ ቋንቋ ተናጋሪዎችን/ ትግራይና የኤርትራ ተወላጆችን/ ከየንግድ ቤቱ፣ ከየአደባባዩ፣ ከየአውራጎዳናውና ከየመስሪያ ቤቱ እያፈሰ በገፍ አስሯቸዋል። በስለላ ቡችሎቹም አማካይነት በከተማው ውስጥ ፀረትግራይና ፀረኤርትራ ወሬ በማስነዛት ሕዝቡን ከሕዝብ ለመለያየት እየሞከረ ነው።
ወታደራዊው መንግሥት በዓለምአቀፍ አስተያየት ተነቀፈ፡-
የዓለም ሕዝብ ስለወታደራዊው መንግሥት ፀረዲሞክራሲያዊና ፋሽስታዊ ድርጊቶች ከያቅጣጫው ነቀፌታውን መሰንዘሩን ቀጥሏል። የደርጉ አሻንጉሊት ተፈሪ በንቴ ለውጭ አገር ጋዜጠኞች ህዳር 3 ቀን በሰጠው መግለጫ መሰረት የጦር ፍርድ ቤቱ ለጋዜጠኞችና ለተከሳሽ ዘመድ አዝማድ ክፍት ይሆናል ማለቱ የውጭ ታዛቢዎችን አስተያየት ለማባበል ይመስላል።
ጄኔራል ነጋ ተገኝ ሸፈተ፡-
የቤገምድር ክፍለሃገር ዋና አስተዳዳሪ ሸፍቶ ወዳልታወቀ ስፍራ መጥፋቱ ተረጋገጠ። ጄኔራል ነጋ እስከቅርብ ጊዜ ድረስ የደርጉ ዋና ደጋፊ መስሎ ይደሰኩር ነበር። ከጄኔራሉ ሌላ ከዚሁ ክፍለሃገር ቢትወደድ አዳነና ደጃዝማች ታደሰ /የነጭለባሽ አዛዥ/ መሸፈታቸው ተረጋግጧል።
የደጋ ዳሞት ሕዝብ ሸፈተ፡-
የጎጃም ክፍለሃገር የደጋ ዳሞት ሕዝብ ወታደራዊውን መንግሥት አልቀበልም በማለት ሸፍቷል።
የቲኤልኤፍ መቋቋም፡-
በመንገሻ ስዩም አማካይነት የትግራይ ነፃነት ግንባር /ቲ.ኤል.ኤፍ./ መቋቋሙ ከምእራብ የጋዜጣ ምንጮች ተነገረ። ይህ አዲስ ድርጅት ለጊዜው 600 የሚሆኑ ተዋጊዎች እንዳሉትና ከኤርትራ የነፃነት ተዋጊ ድርጅት ጋር አንዳንድ ስምምነት ላይ ለመድረስ በመጣር ላይ እንዳለ በተጨማሪም ተናግሯል።
የኤርትራ ሕዝብ ትግል ተፋፍሟል፡-
የኤርትራ ሕዝብ ትግል እየተፋፋመ መሄዱ ይነገራል። ኢ.ኤል.ኤፍና ፒ.ኤል.ኤፍ. የተባሉት ተዋጊ ድርጅቶች በመካከላቸው የነበረውን ልዩነት በማስወገድ ስምምነት ላይ እንደደረሱ ከኤርትራ የሚደርስ ዜና ይገልፃል።