ሰሕድ ቁ. 20

የሰፊው ሕዝብ ድምፅ

 ቁጥር 20፣          ጥር 5፣ 1967 

የፅሁፉ ፍሬ ሀሳብ

መኢሶን በዚህ የሰፊው ሕዝብ ድምፅ እትሙ፣ ቀደም ሲል “የኢትዮጵያ ሶሻሊዝም” በወታደራዊ ደርግ መታወጁ  የሕዝቡን ፍላጎት ለማሟላት የታሰበ ቢመስልም እንኳን፤በኢትዮጵያ ውስጥ መሠረታዊ የፖለቲካ ለውጥ ለማምጣት ያሉትን በርካታ ውስብስብ ችግሮችና እንቅፋቶችን መፍታት እንደማይችልና ከይዘቱ ውሱን መሆኑን ያትታል። ከጠቀሳቸውም ከእነዚህ ችግሮች አንዱ፤ ለውጡን የሚመራ የፖለቲካ ድርጅት የመመሥረት ጉዳይ ነው። “የኢትዮጵያ ሶሻሊዝም” አዋጅ፣ አንድ ብቸኛ የፖለቲካ ህብረት ይቋቋም!” እና “ሶሻሊዝም በኢትዮጵያ ይስፈን!” ምኞታዊ የይስማ በለው አዋጅ ተጨባጭ ፖለቲካዊ ለውጥ እንደማያመጣ ያስገነዝባል። “ሰዎች ታሪክን መሥራት ይችላሉ” ቢባልም፤ ሆኖም ግን “እንደተመኙትና እንደ ስሜታዊ ፍላጎታቸው አይደለም” የሚባለውን ማርክሳዊ የፍልስፍና ምክር ማዳመጡ አግባብ አለው ይላል።በተጨማሪም፣ እንደወታደራዊ ደርግ ምኞት፤ አንድ ብቸኛ የፖለቲካ ድርጅት፣ የኢትዮጵያን በርካታና ውስብስብ ችግሮች ለመፍታት ችሎታም አቅምም የለውም ሲል ያረጋግጣል።        

የሰፊው ሕዝብ ድምፅ

ለሰፊው ሕዝብ ሰራተኛ ገበሬ፣ ነጋዴ፣ ወታደር፣ ምሁር መብትና ጥቅም የሚታገል ጋዜጣ

የኢትዮጵያ ሰፊ ሕዝብ ይቅደም

 
ቁጥር 20                                                                        ቀን 5/5/67

 

ምን አይነት የፖለቲካ ድርጅት?

ከታላቁ ፈላስፋ ከካርል ማርክስ አያሌ ጽሑፎች ውስጥ ብዙ ጊዜ የሚጠቀስ አንድ መሠረታዊ ነገር አለ፣ ይኸውም፡ ቃል በቃል ሳይሆን፡ ፍሬ ሃሳቡ እንዲህ ነው፣ ሰዎች ታሪካቸውን ይሠራሉ፣ ነገር ግን ይህን የሚያደርጉት እንደ አሰኛቸው፣ እንደ አሻቸው፣ እነርሱ በመረጡትና ባዘጋጁት ሁኔታ ውስጥ ሳይሆን፣ በአለና በተሰጠ አንፃራዊ ሁኔታ ውስጥ እንጂ። ማርክስ ይህን ጥልቅና ሰፊ ሃሳብ በጥቂት ቃላት አጠቃለለው፣ ግን ብዙዎች ይህን አብነት – ሰው ታሪኩን እንዴት እንደሚሠራ – ባለመገንዘብ ይህ ነው ከማይባል ትልቅ ስህተትና ጥፋት ውስጥ ይሰጥማሉ።

ከእኛ ከራሳችን፤ ማለት ከህሊናችን ውጭ በአንፃራችን፣ በዙሪያችን ነገሮችና ሁኔታዎች አሉ፣ እነዚህ ራሳቸውን የቻሉ በራሳቸው የሚኖሩ ወይም ያሉ ናቸው እንጂ፤ እኛ በአእምሮአችን ወይም በሀሳባችን የፈጠርናቸው አይደሉም። እንደፈለግን በዘፈቀደ ከመቅፅበት ከእመአልቦ ወደቦ፣ ከቦ ወደ እመአልቦ/ ካለመኖር ወደ መኖር ከመኖር ወደ አለመኖር/ የምንለዋውጣቸው፤ የሀሳብችን ሥራዎች ወይም ፍጥረቶች አይደሉም። ከእኛ ውጭ የራሳቸው ህልውና ያላቸው ነገሮች ወይም ሁኔታዎች ናቸው።

ታሪካችንን የምንሠራው – ለመኖር የምናደረገው ትግልና መፍጨርጨር በእንደዚህ ያለ ከሙሉ ቁጥጥራችን ውጭ በሆነ ሁኔታ ውስጥ ሆነን ከፍጥረት አካባቢያችን- ጋር በመታገል ነው። እንዲህም ሲባል ያለንበት አንፃራዊ ሁኔታና በአካባቢያችን ያለውን ፍጥረት – መሬት አየርና ሌሎችም ነገሮች ለመለወጥ አንችልም ማለት እንዳልሆነ ግልፅ ነው። የሰው ልጅ፣ ፍጥረትን፣ አካባቢውን የመለወጥ ችሎታ ያለው መሆኑ ለማመን ግልጽ ነው። ስለሆነም የሰው ልጅ ያለበትን ሁኔታና አካባቢ ሊለወጥ የሚችለው እንዲያው እንደ አሻውና ድንገት ከመሬት ተነስቶ፡ ይህ ይሁን፣ አይሁን፣ ይሄኛው እንደዚህ ይሁን ብያለሁና እንደዚያ ይሁን ወዘተ. በማለት አይደለም። ሰዎች ታሪካቸውን የሚሠሩት፡ አካባቢያቸውን የሚለውጡት የፍጥረትን የለውጥ ሕግጋት በመከተል ብቻ ነው

አላዲን ፋኖሱን ነካ አድርጎ በባዶ በረሃ፣ በለመለመ ዛፎች የተዋበ ቤተመንግሥት ሠራ፣ ማርና ወተት ከሰማይ አስዘነበ፣ የተመኘውንና የፈለገውን ሁሉ ፋኖሱን በመንካትና ይህን እፈልጋለሁ፣ ያ ይምጣ ወዘተ. በማለት ምኞቱ ሁሉ ከመቅጽበት ይሟላለት ነበረ የሚለው የልጆች ተረት በእውነተኛ ሕይወት ውስጥ ስፍራ የለውም። አካባቢያችን፣ ያለንበት ሁኔታ ምን እንደሆነ እንዴት ልንለውጠው እንደምንችል፣ አስቀድመን ደህና አድርገን በጥልቀት እንድናጠናው ያስፈልጋል፤ በትክክል ምንነቱንና የሰጠውን ሕግጋት፣ የደረሰው ለምን ዓይነት ለውጥ መሆኑን ከተረዳን በኋላ ታሪካችንን ልንሠራ፣ አካባቢያችንን ልንለውጥ እንችላለን። ይህ ሁሉ ከባድ ትግልና መፍጨርጨርን የሚጠይቅ እንጂ በነሲብ እንደአላዲን እንዲህ ይሁን በማለት የሚደረግ አይደለም። ባለፈው ቁጥራችን በኢትዮጵያ ውስጥ ሶሻሊዝም መታወጁሰፊውን ሕዝብ ፍላጎት የተከተለ ቢሆንም አዋጁ የሶሻሊዝምን ትክክለኛ ፍች ይሰጣል፣ ደግሞም ጠቅላላ ሁኔታው ለሳይንሳዊ ሶሻሊዝም አሁን ባሁን ሥራ ላይ መዋል የበሰለ ነው ማለት አይደለም፣ ገና ወደፊት ብዙ ትግል ይቀረናል፣ የምርት ኃይሎች- መሳሪያዎችና ባለሞያዎች – ገና አልተጠናከሩም፣ የዕድገታቸው ደረጃ ዝቅተኛ ነው፣ የመንግሥቱን መኪና የሚያንቀሳቅሱት የቀድሞው መንግሥት ባለስልጣኖች ስለሆኑ ለወጡን፡ ሶሻሊዝምን ከማጨናገፍና ከማሰናከል አይመለሱም፣ በሌላም አቅጣጫ የቀደሞው አቋምና ሁኔታ እንዳለ ነው፣ ተራማጆች አሁንም እሥር ቤት ታጉረዋል፣ ፋሽስታዊ ሕጎች አልተሠረዙም ወዘተ.፣ እነዚህ ሁሉ የለውጡ ጠንቆችና እንቅፋቶች አልተነቀሉምና በፍጥነት አስቸኳይ እርምጃዎች ይወሰዱ ወዘተ. በማለት አንዳንድ ነገሮችን ለማመልከት ሞክረን እንደነበረ የሚታወስ ነው። በአዋጁ ውስጥ ስለቀረበውም የፖለቲካ ድርጅት በአጭሩ ነካ አድርገን ወደፊት እንመለስበታለን በማለት አልፈነው ነበረ። ሁኔታው በፈቀደው መሠረት አሁን ወደዚህ ጉዳይ (ድርጅት) ገባ ብለን አስተሳሰባችንን ለማመልከት እንሞክራለን።

 
 ሀ/ አንድ ብቻ የፖለቲካ ማህበር ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል
ጊዜያዊው ወታደራዊ ደርግ በሶሻሊዝም አዋጁ ውስጥ ለፖለቲካ ድርጅት መጠነኛ ስፍራ ሰጥቶታል። መሠረታዊ መመሪያዎች በሚለው ክፍል የፖለቲካ ድርጅትን አስፈላጊነት በጠቅላላው፣ ጥቅምና ጉዳቱ ምን እንደሆኑ፣ አንድ ብሔራዊና ግንባር ቀደም የሆነ የፖለቲካ ማህበር ምን ያህል አስፈላጊና ጠቃሚ እንደሆነ፣ በአንፃሩ ደግሞ አያሌ የፖለቲካ ማህበሮች አደገኛ መሆናቸውን አመልክቶ ባሁኑ ጊዜ የሚያስፈልገን በህብረተሰባዊነት ፍልስፍና የሚመራ መደበኛ የሆነ፤ መላውን ሕዝብ የሚሰበስብና የሚያስተባብር ብሄራዊ የተራማጆች ፖለቲካ ህብረት ነው በማለት ደምድሟል። በዚህ ረገድ የወታደራዊው ደርግ ምርጫ ግልጽ መሆኑን በመገንዘብ ለአሁኑ ሁኔታችን አይስማማም በማለት ባለፈው እትማችን አቋማችንን በመጠኑ ገልጸናል። ከዚህ በላይ ከፍ ብለን የማርክስን መሠረታዊ ሀሳብ በመመርኮዝ፡ እኛ ስለፈለግንና ይሁን ስላልን ማነኛቸውም ነገር ይሆናል፡ ይፈጸማል ማለት እንዳልሆነ ግልጽ ነው። አንፃራዊ ሁኔታ መብሰሉን፣ ምቹ መሆኑ፣ መድረሱን ሳናረጋግጥ፣ ሶሻሊዝም በምድረ ኢትዮጵያ ይስፈን! አንድ የተራማጆች የፖለቲካ ህብረት ይቋቋም! ወዘተ. ብለን ማወጅ ጠቅላላውን ሁኔታ እምብዛም አይለውጠውም። ሁሉ ነገር እነደዚህ በቀላሉ አዋጅ! አዋጅ! በማለት የሚከናወንና የሚፈጸም ወዘተ. ቢሆንማ ኖሮ፤ የሰው ልጅና ዓለማችን ሌላ በሆነ ነበረ። አንድ የተራማጆች የፖለቲካ ማህበር ያስፈልገናልና ይኸው እንዲቋቋም አውጀናል በማለት ተባለውን ድርጅት ለማቋቋም አይቻልም አንልም።የተባለው ድርጅት በቀላሉ ሊቋቋም ይችላል። ግን የኢትዮጵያን መሠረታዊ ችግሮች ሊፈታ አይችልም እንላለን። ዋናው ጥያቄ ለኢትዮጵያ ምን ዓይነት የፖለቲካ ድርጅት ያስፈልጋታል የሚል ነው። በህብረተሰብ የመደብ መከፋፈል የምናምን ከሆነ፣ በኢትዮጵያ ውስጥ መደቦች አሉ ብለን የምንቀበል ከሆነ፣ የምናቋቁመው የተራማጆች የፖለቲካ ህብረት የየትኛውን መደብ ጥቅም የሚጠብቅ፣ የየትኛው መደብ ተወካይ ይሆናል? ካለፈው የካቲት ጀምሮ የትግሉን እንቅስቃሴ ሲያካሂድ የቆዩትን ሦስቱን መደቦች፡ ማለትም ወዝአደሩ፣ አርሶአደሩ፣ ንውስ ከበርቴው እነዚህን ብንወስድ ይህ የታሰበው ድርጅት የትኛውን መደብ ነው የሚወክለው? ምንም እንኳን በትግሉ እንቅስቃሴ ውሰጥ ጐን ለጐን በመሰለፍ ተባብረው ጨቋኝና በዝባዥ መደቦችን ድል ቢያደርጉም እነዚህ ሦስት መደቦች ጥቅምና ፍላጎት ሙሉ በሙሉ አንድ አይደሉም፣ ተመሳሳይነት ቢኖርም እስከ ተወሰነ ምዕራፍ ድረስ ነው፣ ከዚያ በኋላ ጥቅማቸውና ፍላጎታቸው ተቃራኒነት አለው። የጥያቄዎቹ አስፈላጊነት ይህንን የመደብ ልዩነትና የጥቅም ግጭት ለይቶና ቁልጭ አድርጎ በማሳየት የታሰበው የፖለቲካ ድርጅት የየትኛው መደብ ተወካይ መሆኑን ለማረጋገጥ ነው። የትግሉ አሸናፊዎች መደቦች ሦስት መሆናቸውና የታቀደው የተራማጆች የፖለቲካ ህብረት በእርግጥ የየትኛው ወኪል ሊሆን እንደሚችል መገመቱ ብቻ አይደለም ችግሩ፤ በዚህ ጊዜ መሠረቱን መያዝ የሚገባው የወዝአደሩ መደብ በፖለቲካ ማህበር በአለመደራጀቱ ታሪካዊ ተግባሩን ለመፈጸም በማይችልበት ደረጃ ላይ መገኘቱ ነው። በእንደዚህ ዓይነት ሁኔታ አንድ የተራማጆች ድርጅት ብቻ ለማቋቋም መሞከር የሳይንሳዊ ሶሻሊዝምን /የማርክሲዝምን/ ሕግጋት አለማወቅና ትልቅ ስህተት ውስጥ መውደቅ ነው፣ ምን ሊያስከትል ይችላል? 
  1. አቆርቋዥ ቢሮክራሲ፡-
ባሁኑ ሁኔታ አንድ የፖለቲካ ፓርቲ ብቻ ማቋቋም አጤ ኃይለሥላሴ የዘረጉትንና ያስፋፉትን አቆርቋዥ ቢሮክራሲ የበለጠ ማስፋፋትና ማባባስ፣ ሰፊውን ሠርቶአደር ሕዝብ ማስጋጥና ማስበዝበዝ ነው። በአዋጁ ውስጥ እንደተገለጠው
“እንዲህ ያለ ማህበር ሲኖር፣ መሪዎች ከመላው ሕዝብ መሀከል የሚመነጩበት፣ ሕዝቡ ስለ ዕለትና ስለዘለቄታው ችግር የሚናገርበትና የሚደመጥበት፣ መሪዎች ለአገር የሚበጅ ነገር ሲወጥኑ ለሕዝብ የሚገልጡበት፣ ሕዝብ የሚደግፈው ለውጥ በየቦታው ያለዕንቅፋት ሊከናወን የሚችልበት፣ሕዝብ መሪዎቹን የሚገታበት፣ አይነተኛ የፖለቲካ መሣሪያ ተፈጠረ ማለት ነው።”
ይህ ሊሆን አይችልም። ይህ ምኞት ነው እንጂ ሌላ ነገር ሊሆን አይችልም። ይልቁንስ የሰፊው ሕዝብና መሪዎቹ መገናኛና መወያያ ባንድነት ሆነው ወደፊት መራመጃ፣ የሶሻሊዝም ማስፋፊያ ወዘተ. መሆኑ ይቅርና የዚህ ተቃራኒ፣ አጤ ኃይለሥላሴ ባወረሱን ከባድ የመጨቆኛ፣ የመበዝበዣ መሣሪያ ላይ ሌላ ተጨማሪ ከባድ ሸክም ሊሆን እንደሚችል ለመገመት አስቸጋሪ አይደለም። ቢሮክራሲ ስንል ምን ማለታችን ነው? ሲቪል ወታደር፣ በከተማ ያለ በገጠር ያለ፣ ትንሽ ትልቅ ሳይል የመንግሥትን ሥልጣን መከታ በማድረግ የራስን ጥቅም በመፈለግ ሌላውን /ሰፊውን ሕዝብ/ መጉዳት፣ እነዚህንና፤ የመሳሰሉትን በአጠቃላይ ቢሮክራሲ ለማለት ይቻላል። ቢሮክራቶች በቀጥታ በምርት ትግብርት ውስጥ አይገቡም፣ ቢሮው ውስጥ ሆነው አገልግሎት በመስጠት የህብረተሰቡን ምርት ዝቀው የሚወስዱ ከመሆናቸውም በላይ ተጨማሪ ጥቅም በማሳደድ የጠቅላላውን ህብረተሰብ የምርት ትግብርት ያሰናክላሉ፣ እንዲቆረቁዝ ያደርጋሉ። አጤ ኃይለሥላሴ አውርሰውን የሄዱት ቢሮክራሲ፡ ከሌሎች አገሮች ቢሮክራሲ የባሰ፣ የበሰበሰ የበሸቀጠ፣ ለራሱ ጥቅም በመስገብገብ ተወዳዳሪ የሌለው፣ የገዢው መደብ መሣሪያ በመሆን በሰፊው ለፍቶአደር ሕዝብ ላይ ከባድ ጉዳት ያደረሰ ለመሆኑ አንድና ሁለት የለውም። ትንሽም ብትሆን፣ አንዲት ጉዳይ ለመፈጸም፣ ሰው ለመቅጠር፣ ዕድገት ለማስገኘት፣ ከቦታ ቦታ ለማዘዋወር፣ ለሕዝብ አገልግሎት አንድ ነገር ለማድረግ፣ አንድ እርምጃ ለመውሰድ ወይም ላለመውሰድ፣ ከወንበሩ ላይ ለመንቀሳቀስ፣ ጥቅም ይፈልጋል፣ ዓይን ዓይን ያያል፣ ራሱ ባይጠቀም ዘመዱን ወዳጁን ለመጥቀም፤ የማይወደውን ጠላቱን በተሰጠው ሥልጣን ለመጉዳት አይመለስም። ከሕዝብ በአደራ የተሰጠውን ሥልጣን ለመጠቀሚያና ለመጉጃ ያውለዋል። ይህ አሁን ያለው ቢሮክራሲ ነው፣ በጣም ከባድ ሸክም መሆኑ ለማንም ግልጽ ነው። እንደሚታሰበው በመንግሥቱ ቁጥጥር ሥር አንድ ፓርቲ ሲቋቋም የግድ ሌላ ቢሮክራሲ ይፈጠራል። የፓርቲውን ሥራ የሚመሩ መሪዎች የግድ መኖር አለባቸው፡ ከእነዚህ ለጥቀው የሚመጡ የፓርቲውን መኪና የሚያንቀሳቅሱ፡ ከሰፊው ሕዝብ ጋር የሚያገናኙት፡ ካድሬዎች ይኖራሉ፣ ከዚህም ዝቅ ብለው የሚመጡ የፓርቲው ሠራተኞች አሉ። እነዚህ ሁሉ ቁጥራቸው ምን ያህል እንደሚሆን አሁን ለመተንበይ የሚቻል ባይሆንም፡ በሌሎች አገሮች ሲገመት በጣም ብዙ ሊሆኑ ይችላሉ። ከአስተዳደሩ ሊመጣጠኑ ይችላሉ። ስለሆነም ዋናው ጉዳይ የቢሮክራሲው መጠን መብዛት አይደለም፣ እርግጥ ይህም ቢሆን ለቆረቆዘውና ውልቅልቁ ለወጣው ኢኮኖሚያችን ቀላል ሸክም አይሆንበትም። ዋናው ችግር አንድ ፓርቲ ሲሆን፣ አንደኛ፡ የመንግሥቱ ቢሮክራሲና የፓርቲው ቢሮክራሲ ይመሳጠራሉ፣ ይደጋገፋሉ፣ ሁለተኛ፡ የሰፊው ሕዝብ ቁጥጥር ሊኖርባቸው ስለማይችል /የድርጅት የንግግርና የጽሑፍ የመሰብሰብ የሰላማዊ ሰልፍ መብቶቹን ስለሚገፈፉ/ ማናቸውንም ነገር በዘመድ በወዳጅ በአምቻ በጋብቻ በገንዘብ በጉቦ ወዘተ. ካልሆነ አይፈጸምም። የፓርቲው አባል፣ የፓርቲው ሠራተኛ፡ የሚታጠቀው የሥልጣን ሰይፍ በጣም ስለታም ስለሚሆን በዚህ የመጠቀሙና ሌላውንም የመቆራረጥ ኃይል ከአስተዳደሩ የበለጠ ሊሆን እንደሚችል አይጠረጠርም። ባሁኑ የኢትዮጵያ ሁኔታ ይህን የበለጠ የሚያባብሰው በሶሻሊዝም መንፈስ የታነፁ፣ ይህን ፍልስፍና አጣርተው የሚያውቁና ለሰፊው ሕዝብ ለማስተማር የሚችሉ፡ ካድሬዎች ወይም የፓርቲ ሠራተኞች አለመኖራቸው ነው። እነዚህ በጣም አስፈላጊ መሆናቸውንና ያለእነርሱም ምንም ለማድረግ እንደማይቻል ከሌሎች አገሮች የቅርብ ጊዜ ታሪክ ለመረዳት ይቻላል። እነዚህ ካድሬዎች የሶሻሊዝም ደቀመዛሙርት ወይም ሃዋርያ ስለሆኑ እነርሱ አስቀድመው ሳይፈጠሩ /ሳይዘጋጁ/ እንዴት አድርጎ አንድ ፓርቲ ለማቋቋም ይሞከራል? እነርሱንም ቶሎ አንፍጠር ቢባል ያለ ሰፊው ሕዝብ በትግሉ መሳተፍ እንዴት ሊፈጠሩ ይችላሉ? ደርጉ ወታደሮችንና ተማሪዎችን ካድሬዎች ለማድረግ ያሰበ መሆኑን በተግባር በመግለጥ ላይ ነው፣ የጥቂት ቀናት ሰሚናር በማድረግ ከሁለት መቶ በላይ የሆኑ ወታደሮች የለውጥ ሃዋሪያት፣ ተቆጣጣሪዎች ተብለው በየመንግሥቱ መ/ቤት በአዲስ አበባና በክፍለ ሀገሮች ተደልድለዋል። በመካሄድ ላይ ባለው የዘመቻ ዝግጅት ወደ ስድሳ ሺ የሚሆኑ ተማሪዎችና አስተማሪዎች በየገጠሩ እንዲሄዱና ስለለውጡ እንዲያስተምሩ ተወስኗል። ወታደሮች ሶሻሊዝምን የትና መቼ ተምረው ወይም አውቀው ነው ስለሌላው አስተማሪ ወይም ተቆጣጣሪ ሊሆኑ የሚችሉት? ሶሻሊዝም የሚለው ቃል ራሱ በስንቱ ዘንድ ይታወቅ ይሆን? ተማሪው እንኳን በመጠኑም ቢሆን ስለ ሶሻሊዝም ሰምቷል፣ ግማሹም ትንሽ አንቧል፣ ጥቂቶች በመጠኑም ቢሆን ሊረዱት ይችላሉ ብሎ ለመገመት ይችላል፣ ምክንያቱም ከባድ ትግል አድርገውለታልና ነው። እነዚህ ሁሉ እንደአሉ /ሰፋ ያለ ትምህርት ሳይሰጣቸው/ የፓርቲ ካድሬዎች ይሆናሉ ማለት ዘበት ይመስለናል። ግን የታሰበው እነዚህን በጥቂት ቀናት ሰሚናር ወደ ካድሬዎች ለመለወጥና በእነርሱ አማካይነት ለውጡንና ሶሻሊዝምን ለማስፋፋት የታሰበ ስለሆነ ከዚህ በላይ ከፍ ብለን ያመለከትነው የቢሮክራሲው ሁኔታ ከአር ወደ ቅዘን እየዘለሉ የማለፍ ነው። ወታደር፣ ተማሪ /ለዚያውም ደንበኛ የአይዲዮሎጂ ትምህርት ከተሰጣቸው በኃላ/ የካድሬዎች ረዳት በመሆን ለመስራት ይችላሉ እንጂ፡ ያለምንም ዝግጅት የፓርቲ ካድሬዎች የሆኑበት ስፍራ ወይም አገር አለ ብለን አንገምትም። ይህንን መርሳት የበሰበሰውንና የበሸቀጠውን የአጤን ቢሮክራሲ የበለጠ ማባባስ ይሆናል እንጂ ሶሻሊዝምን በኢትዮጵያ ሊያስፋፋ አይችልም። በሌሎች በመጠኑም ቢሆን፡ ደንበኛ ካድሬዎች በነበሩአቸው አገሮች እንኳን የቢሮክራሲን ነቀዝ ለመቋቋምና ጨርሶ ለማስወገድ ምን ያህል አስቸጋሪ እነደሆነ ሲታወቅ፡ ከዚህ ያለምንም ካድሬ ከዜሮ ተነስቶ እንዴት አሁኑኑ አንድ ፓርቲ እናቋቁም ለማለት ይቻላል? ይህንን ሁሉ ችግር እንዴት ልንዘለው እንችላለን? ይህ በቀላሉ የሚታለፍ ጉዳይ አይመስለንም፣ የሌሎች አገሮችን ታሪክ ደህና አድርገን እንመልከትና በዚህ ረገድ አስፈላጊውን ትምህርት ለመውሰድ በመሞከር ነገሩ የሚያዋጣ መሆኑን ልንገነዘበው እንችል ይሆናል።
  1. የንዑስ ከበርቴ ድርጅት፡-
ጫፉ ተከርክሞ ግንዱና ስሮቹ እንደነበሩ ያሉት ባላባታዊ ሥርዓት ዘርግቶት በነበረው ፍጹም የጭቆናና የብዝበዛ አገዛዝ ሰፊው ሕዝብ መሠረታዊ ሰብአዊ መብቶቹን በመገፈፉ የፖለቲካ ማህበሮች ለማቋቋም አልተቻለውም ነበረ። ከዚያም ወዲህ ምንም እንኳን የድሉ ባለቤት ቢሆን በተጣለበት ዕገዳ ምክንያት ትግሉን የሚያቀናብርና የሚመራ አጠቃላይና ጠንካራ የትግል ድርጅት ለመመሥረት ሁኔታው ሳይፈቅደለት እስካሁን በመታገል ላይ ነው። የወዝአደሩ መደብና የጢሰኛውና ደሃ ገበሬው ወገን የየራሳቸውን የፖለቲካ ድርጅቶች ሳይመሠርቱና ተገቢ ስፍራቸውን ሳይዙ አንድ የተራማጅ የፖለቲካ ድርጅት በርግጥ ሊቋቋምና የሚጠየቅበትን ተግባር ሊፈጽም ይችላልን? በሳይንሳዊ የህብረተሰብ ታሪክ ሕግጋት መሠረት አሁን የደረስንበት ደረጃ የሰፊውን ሕዝብ የትግል እንቅስቃሴና ከዚያ በሚቀጥለውም ወደ ሶሻሊዝም በሚደረገው ጉዞ መሪነቱን መያዝ ያለበት የወዝአደሩ ሬቮሉሽናዊ የትግል ድርጅት መሆን ነበረበት፣ ግን ወዝአደሩ በአጤ ዘመነ መንግሥትም ሆነ አሁን እንዳይደራጅ በመታገዱ የፖለቲካ ማህበር የለውም። በዚህ ጊዜ መሪነቱን ማን ይይዛል? እንዲቋቋም የታሰበው የተራማጃች የፖለቲካ ድርጅት የየትኛው መደብ ድርጅት ሊሆን ይችላል? ማነው መሪነቱን ሊይዝ የሚችለው? ወታደራዊውን ደርግ የሚመሩት መኮንኖች፡ በመንግሥቱ መኪና አካባቢ /ጫፍ የተቀነጣጠሰለት ቢሮክራሲ/ አለን አለን የሚሉት ሁሉ የንዑስ ከበርቴው መደብ ልዩ ልዩ ክፍሎች መሆናቸው ብዙ የሚያጠራጥር ወይም የሚያከራክር አይመስለንም። መምህራን፡ በዘመቻው ውስጥ ግንባር ቀደምነቱ፣ የያዙት ምሁራን፣ በከበርቴ ፍልስፍና የሚመሩ ደራሲዎች፡ ጋዜጠኞች ሰዓሊዎች መካከለኛ የቢሮና የንግድ ድርጅቶች ሠራተኞች፣ ሌሎች ባለሞያዎች፣ ተማሪዎች፣ ዝቅተኛና መካከለኛ ነጋዴዎች፣ እነዚህን የመሳሰሉት ነቅተናል ባዮች የንዑስ ከበርቴው ልዩ ልዩ ረድፎች ናቸው። በአዋጁ ውስጥ የተጠቀሰው አንድ ድርጅት ብቻ የተቋቋመ እንደሆን ያለምንም ጥርጥር ባሁኑ ሁኔታ ይህ የፖለቲካ ድርጅት የንዑስ ከበርቴው እንጂ የሌላው ሊሆን አይችልም። እርግጥ የንዑስ ከበርቴው መደብ በውስጡ ልዩ ልዩ ክፍሎችና ረድፎች ስለአሉት አሁን በሥልጣን አካባቢ ላቅ ብለው የሚታዩና ሶሻሊዝም! ሶሻሊዝም! እያሉ የሚያስተጋቡት፡ በአስተሳሰባቸው በስተግራ በኩል የሚገኙት ሊሆኑ ይችላሉ፣ የግራ ክንፍም ሆኑ፣ ማዕከላውያን፣ ሁሉም ንዑሳን ናቸው፣ የፍልስፍናውም መሠረት ወዝአደርነት /ፕሮሌታሪያኒዝም/ ይባል እንጂ አንድም ወዝአደር አለበት ለማለት ከቶ አይቻልም። ድርጅቱ በሚቋቋምበት ጊዜ የሠራተኞች ማህበራት፡ ለምሳሌ እነ ኢሠአማ በውስጡ እንዲገቡ ቢታወጅና አንዳንድ ሠራተኞችም ከፍ ያለ ሥልጣን ቢሰጣቸው ይህ ሁሉ ማህበሩ የንውስ ከበርቴ መሆኑን ይለውጠዋል ብለን አናምንም። የንዑስ ከበርቴ መደብ በውስጡ ብዙ ረድፍና ክፍሎች አሉት ብለናል፣ በወዝአደሩ አይዲዮሎጂ ስር የሚሰለፉና ራሳቸውንም ወደዚያው የለውጡና የሚለወጡም አሉ። ሌሎችም ደግሞ ወላዋዮች፣ ከበርቴው ሲጫናቸው አይናቸውን ወደወዛደሩ የሚመልሱና የሚጠጉ፣ የከበርቴው መደብ ተጫን ሲቀላቸው ደግሞ ፊታቸውን በወዝአደሩ የሚመልሱነ የሚርቁት፣ በከበርቴው ስፍራ ተተክተው ሊጨቁኑትና ሊበዘብዙት የሚመኙና የሚመክሩ አሉ። ከዚያም አልፎ ዘወትር ከከበርቴው ስር ጭራቸውን እየቆሉ መኖር እንጂ ወዝአደሩን የሚጠሉና የሚፈሩ መኖራቸው በታሪክ የታወቀ ነው። ዛሬ በአገራችን እነዚህ ሁሉ በሥልጣን አካባቢ ቸፍ ቸፍ በማለት ላይ መሆናቸው የሚያጠራጥር አይመስለንም። ብዙዎቹ አጭበርባሪዎች በመሆናቸው የሶሻሊዝምን ካባ ደርበው በጩኸታቸው ሰውን እስከማደንቆር ይድረሱ እንጂ፡ የመጀመሪያ ዕድል ሲያገኙ ወደ ከበርቴ ከመመለስ አይቆጠቡም፣ እነዚህ የቀበሮ ባህታውያን በመፈንቀል መንግሥት ሆነ በሌላ መንገድ ሶሻሊዝምን ከመጥፋት የማይመለሱ፣ ዋና ጠላት መሆናቸውን ደህና አድርገን መገንዘብ ያሻል። እንግዲህ ሀሳባችንን ለማጠቃለል፣ ይህ የታሰበው ዓይነት ድርጅት፣ አንደኛ፡ ባሁኑ ሁኔታ የንዑሳን እንጂ ሌላ ሊሆን እንደማይችል፣ ሁለተኛ፡ የሰፊውን ሕዝብ የበለጠ የሚጨቁንና የሚበዘብዝ አቆርቋዥ ተደራቢ ቢሮክራሲን መሆኑን ለማስረዳት የሞከርን ይመስለናል። የጊዜያችንን የፖለቲካ ንቅናቄዎችና ፓርቲዎች ታሪክ በተለይም የአህጉራችንን፡ አንዳንድ ሶሻሊዝምን ዋና መመሪያቸው አድረገው የተነሱትን አገሮች የቅርብ ጊዜ ታሪክ ጠልቆና ቀረብ ብለን ብንመለከት ከትልቅ ስህተት ልንድን እንችል ይሆናል። ነገሩን በቀላሉ መመልከትና ከዚህ በፊት እንደተደረገው እኛ ካልን ወይም ከፈለግን ማን ሊከለክለን፡ ማን ሊያግደን ይችላል? ሁሉም በእኛ እጅ ነው፣ ከአይናችን ሥር የሚወጣ የለም፣ በማለት ከባሰ ውድቀት ውስጥ እንድንገባ፡ በጉዳዩ ላይ አጥብቆ ማሰብና የተሻለ መፍትሔ መፈለጉ፡ ከብልህነት የሚቆጠር ነው ብለን እንገምታለን
ለ/ መፍትሔው ምን መሆን አለበት?

አንድ የፖለቲካ ማህበር ብቻ ይቋቋም ማለት፤ ሰፊው ሕዝብ ይበልጡኑ በቢሮክራሲ ይቆርቁዝ፣ ወዝአደሩና ደሃው ገበሬ አይዘጋጅ፣ እንዲያው መብታቸውንና ነፃነታቸውን ተገፈው በጭቆና ቀንበር ስር ይማቅቁ /ንዑስ ከበርቴው ብቻ ይደራጅ፡ በጋራ የተገኘውን የዕድል ፍሬ ንዑሳን ብቻ ይጠቅልሉት፣ ወዘት. ማለት እንደሆነ ከዚህ በላይ ለማመልከት ከሞካከርን፡ አሁን ደግሞ ወደ ሁለተኛው ክፍል በመግባት በእኛ ግምት መደረግ ይገባል የምንለውን እናመለክታለን።

  1. ልዩ ልዩ የፖለቲካ ማህበሮች፡ አንድ ግንባር፡-

ካለፈው የካቲት ጀምሮ በይፋ የተካሄደው ትግል በሰፊው ሕዝብ ልዩ ልዩ መደቦች የተመራ መሆኑን ባለፈው ቁጥርና ከዚህ በላይ ማመልከታችን ይታወሳል። ድሉን ያስገኘው የእነዚህ የሶስቱ መደቦች የጋራ ትግል እንደመሆኑ መጠን በፍሬውም አብረው መሳተፍ የኖረባቸዋል እንጂ አንዱ ብቻ ሊቀማቸው አይገባም። በፍሬው ለመሳተፍ በሚችሉት መሠረታዊና ሰብአዊ መብታቸው ተጠብቆ ለመደራጀት ሲችሉ ብቻ ነው ብለን እንገምታለን።ብዙ ጊዜ ወዝአደሩና ጢሰኛው ገበሬ የፖለቲካ ንቃት የላችውም ገና ዓይናቸውን አልከፈቱም፤ መብታቸውን እንዲጠቀሙበት ብንተዋቸው የተሸነፉት መደቦች በውስጣቸው ሰርገው በመግባት እንደገና የጭቆናና የብዝበዛ ሥርዓታቸውን መልሰው ይተክላሉ። በምንም ዓይነት የፖለቲካቸውን ድርጅት እንዲያቋቁሙ አንፈቅድም፣ ወዘተ. ስለዚህ መብታቸውን ሊጠቀሙበት ስለማይችሉ አይሰጣቸውም። በንዑሣን ሞግዚትነት ሥር ሆነው መቆየት አለባቸው፣ የሚለው ወደ ቀኝ በኩል ያሉ ንዑሣን ውስጡ ተንኮል አስተሳሰብ መሆኑን ከዚህ በላይ በመጠኑ ለማመልከት ሞክረናልና እዚህ ለማስታወስ እንጂ አንመለስበትም። መሠረተቢስ አስተሳሰብ መሆኑ ግን በግልጽ መታወቅ አለበት።

ይህንን የተንኮል አስተሳሰብ ወደዚያ በመጣል ወዝአደሩና ጢሰኛው ገበሬ እንዲደራጅ መደረግ አለበት፣ መከልከል የለባቸውም። ሙሉ ሳባዊና ብሔራዊ መብቶችና ነፃነቶች፡ የመናገር ሃሣብን በጽሑፍ የመግለጽ የመሰብሰብና የመደራጀትን የመሳሰሉት ሁሉ አሁኑኑ ሥራ ላይ እንዲውሉ ተደርጎ የመደራጀቱ ሥራ እንዲጀምር መሆን አለበት።

በቅድሚያ የፖለቲካ ማኅበሮቹ እንዲደራጁ መንገድ መክፈት ይኖርበታል፣ ወዝአደሩ ለብቻው /የሱን አይዲዮሎጂ የተቀበሉና ከእርሱ ጋር የተዋሃዱትም አብረውት ሊደለደሉ መቻል ይኖርባቸዋል/ ለመደራጀት እንዲችል መሆን አለበት፣ ጢሰኛው ገበሬ በላብአደሩና በተራማጆች ርዳታ በመደራጀት መብቱ መጠበቅ አለበት። እነዚህ ሁለቱ በቅርብ አብረው ለመሥራትና ትግላቸውን ለመቀጠል በሚችሉበት ሁኔታ ለመገኘት እንዳይከለከሉ ያስፈልጋል።

እንግዲህ የሰፊው ሕዝብ መደቦች በየመደባቸው ከተደራጁ፣ ከንዑስ ከበርቴው ጋር ሆነው ባንድ የግንባር ድርጅት ውስጥ ገብተው ለመሥራት የማይችሉበት ምክንያት ያለ አይመስለንም። ሲሆን በወዝአደሩ መሪነት ካልሆነም በእኩልነት ሶስቱ ድርጅቶች በአንድነት ሆነው በግንባር ድርጅት ውስጥ ተጠቃልለው የድላቸውን ውጤት ለማጠናከርና ወደፊት ለመግፋት ይችላሉ።

እዚህ ላይ ሁለት ልናተኩርባቸው የሚገቡ ዓብይ ነገሮች አሉ፣ በመጀመሪያ የተባሉት የፖለቲካ ማኅበሮችና አጠቃላዩም ግንባር በሶሻሊዝም አይዲዮሎጂ የሚመሩ፣ ዓላማቸው ሶሻሊዝም መሆን አለበት። ይኸም ሲባል ሶሻሊዝምን እንደ ግብ አድረገው ወደዚሁ ለመገስገስ የቆረጡ መሆናቸውን በዓላማቸው ውስጥ መግለጥና በግብርም ቢሆን ይህን የሚፃረር ድርጊት መፈጸም የለባቸውም እንጂ፣ አሁኑኑ ሶሻሊስት ይሁኑ ማለት እንዳልሆነ በግልጽ መታወቅ አለበት። ሁለተኛው አብይ ጉዳይ ደግሞ፤ የመደብ ጠላቶች ድል የሆኑት እንዳይገቡ በጥንቃቄ መደረግ አለበት። ከዚህ በላይ ከፍ ብሎ እንደተመለከተው ያለፉት ጨቋኝ መደቦች ከወደጫፋቸው ጥቂት ተመለመሉ እንጂ እስካሁን ድረስ እንዳሉ ስለሆኑ ሊያመጡ የሚችሉት አደጋ በቀላሉ መታየት የለበትም። የንዑሳን ቀኝ ክንፍም በሥልጣን አካባቢ የሶሻሊዝምን ካባ ለብሰው በማጋራት ላይ ስለሆኑ አደገኝነታቸው እጅግ በጣም ከባድ ነው።

  1. የማህበሮቹና የግንባሩ አሠራር፡-

የግንባሩም የማህበሮቹም ግንኙነትና አሠራር በዲሞክራሲ ላይ የተመሠረተ መሆን ይኖርበታል፣ ከሁሉ አስቀድሞ ዲሞክራሲ የሰብአዊና ብሔራዊ መብቶች ነፃነቶች መከበርና በሥራ ላይ መዋል ማለት ነው፣ ከዚያም አልፎ እኩልነት ማለት ነው። እያንዳንዱ ማህበር የሶሻሊስትን ርዕዮተ ዓለም በመቀበል አመሠራረቱ አደረጃጀቱና አሠራሩ ዲሞክራሲያዊ ይሆናል፣ የዚህ በትክክል ሥራ ላይ መዋልና መከበር መረጋገጥ ይኖርበታል።

እንደዚህም ሆኖ ግንባሩ በንዑስ ከበርቴው ተፅእኖ ስር ሊወድቅ አይችልም ማለት አይደለም፣ ይህ ሊሆን እንደሚችል አስቀድሞ በመገንዘብ ነቅቶ መከላከል ያስፈልጋል። የንግግርና የጽሑፍ ነፃነት፣ የድርጅቶች በመጀመሪያ ደረጃ ላይ በየመደባቸው መደራጀት ይህንን ስጋት ሊቀንሰው ይችላል፣ ቀደም ብለን ያመለከትነውንም አቆርቋዥ ቢሮክራሲ ለመቋቋም የሚቻለው በዚሁ ዓይነት መንገድ ነው ብለን እንገምታለን።

ከላይ ከፍ ብለን ያመለከትነውን ዓይነት ጨቋኝና አቆርቋዥ ቢሮክራሲ ለማቋቋም የንግግርና የጋዜጣ ነፃነት ብቻ አይበቃም፣ የግድ የተባሉት ዓይነት ድርጅቶች መኖር አለባቸው። ለምን የሚለው ጥያቄ መልሱ በመጀመሪያ ላይ የንግግርና የጋዜጣ ነፃነት ቢፈቅድም ቢሮክራሲው በዚህ በዚያ እያሳበበ ቀስበቀስ ያፍነዋል፣ ከነጭራሹ ያወድመዋል። ጋዜጣው በመጠኑ ቢሆን ቁጥጥር /ለጠላት መሳቢያ እንዳይሆን/ ይደረግበታል፣ ይህ ተቆጣጣሪ የቢሮክራሲው አካል ነው። የቢሮክራቶች ጥፋት በጋዜጣ እንዲገለጥ ጽሑፍ ተዛጋጅቶ ሲመጣ፣ ጠብቀኝ እጠብቅሀለሁ፣ አውለኝ አውልሃለሁ፣ በሚለው የተለመደ ዘዴ ተቆጣጣሪ አጣሞ በመተርጎም ወይም ልዩ ልዩ ምክንያት በመፍጠር አፍኖ ያስቀረዋል። የንግግርም ጉዳይ ያው ተመሳሳይ ነው፣ እንዲህ ያለው በጠላት ተገዝቶ ነው፣ ወዘተ. በማለት ከባሰ ጭቆና ውስጥ ይገባል። የፖለቲካ ድርጅቶች ያሉ እንደሆን በጋዜጣቸው ጉዳዩን ያወጡታል፣ በድርጅታቸውም ውሰጥ ተነጋግረውበት ርምጃ ለመውሰድ የሚከለክላቸው አይኖርም፣ ከዚያም አልፎ በግንባሩ ድርጅት ውስጥ ጉዳዩ ሲነሳና በከፍተኛ ደረጃ ውሳኔ ሊወሰድበት የሚደረግ ሊሆን ይችላል።

በሌላ በኩል አሁንም በመጠኑ እንደአሉት ዓይነት ብዙ የሕዝብ ድርጅቶች ይኖራሉ፣ እርግጥ እነዚህ በወደቀው ባላባታዊ አገዛዝም ውስጥ ነበሩ፣ አንድ ፓርቲም ቢቋቋም ይኖራሉ፣ ግን የበለጠ ፍሬ ሊሰጡ የሚችሉት እነዚህ በየሞያቸው፣ አካባቢያቸው፣ ፍላጎታቸውና ወዘተ. የተደራጀ የሰፊው ሕዝብ ድርጅቶች፣ በየመደባቸው አኳያ የተሰለፉና በዚያ በኩል የሰሩ እነደሆነ ብቻ ነው። መብታቸውንና ጥቅማቸውን ለማስከበር የመናገር የጋዜጣ የመሰብሰብ የመደራጀት ነፃነቶች ያስፈልጋቸዋልና ነው። ይህንን ደግሞ በእርግጥ ለማግኘት የሚችሉት በየመደባቸው በኩል በመደራጀት ነው። በመጨረሻም አስፈሪውን ቢሮክራሲ ለመቋቋም፣ ለማጋለጥ ሕዝብን እንዲያገለግል እንጂ በሕዝብ እንዳይገለገል ለማድረግ የሚቻለው በዚህ በኩል ነው።

የዚህ ዓይነት አደረጃጀት /ሦስት የፖለቲካ ማኅበሮችና አጠቃላይ ግንባር/ ወደ ሶሻሊዝም የሚያደርገውንም ጉዞ ሊያፈጥነው ይችላል፣ አፈርገፊው ገበሬ የፖለቲካ ንቃቱ እየዳበረ ሲሄድ ሶሻሊዝምን በደንብ በመረዳት ከወዝአደሩ ጋር ይዋሃዳል፣ መጀመሪያ ላይም ቢሆን በድርጅትና በሌላውም በኩል የሚረዳውና የፖለቲካ አስተሳሰብ ከፍ ከፍ እንዲል የሚያስተምረው የወዝአደሩ ግንባር ቀደም ድርጅት ነው። ንዑስ ከበርቴው ቀስ በቀስ ከወላዋይነቱና ከመደብ ጭቅቅቱ በመንፃት ወደ ወዝአደሩ በመምጣት ሶሻሊዝምን በአዋጁ ብቻ ሳይሆን በእውነትና በተግባር እንዲቀበለው ይሆናል። በዚህን ጊዜ የአሁኑ ግንባር ሙሉ በሙሉ መሪነቱን ይዞ የምርት ኃይሎችን በተፋጠነ መንገድ በማሳደግ ሶሻሊዝምን ይገነባል። በሌላ መንገድ ሶሻሊዝምን እንገነባለን ማለት ዘላቂነት አለው ብለን አንገምትም። ውሎ ሳያድር ወደ ነበርንበት ወይም የባሰ አዘቅት ውስጥ መውደቅ እንጂ ሌላ ምርጫ አይኖረንም።

ለማጠቃለል፣ ባለፈው ቁጥር ያመለከትናቸው ነገሮች በፍጥነት ሥራ ላይ ካልዋሉ፣ ምንም እንኳን በቀደም ዕለት እንደተደረገው፣ የባንኮችና የኢንሹራንሶች የመንግሥት ንብረት መሆን ዓይነት እርምጃዎች ቢወሰዱም ሰፊው ሕዝብ በታወጀው ሶሻሊዝም እምነት እንዲኖረው በቂ አይሆንም። የታሰሩት ተራማጆች መፈታት፣ የተውጣጣ ጊዜያዊ መንግሥት መቋቋም፣ የመሰረታዊ መብቶችና ነፃነቶች መከበርና ሥራ ላይ መዋል ወዘተ. ውሎ ማደር የሌለባቸው አጣዳፊ ጉዳዮች መሆናቸው መረሳት የለበትም። መንዛዛት ማመንታት፣ መጎተት በእንደዚህ ያለ ሁኔታ በስተቀር ጥቅም እንደሌለው ካለፈው መማር ይገባል።

ወደ እውነተኛው ሶሻሊዝም ለመገስገስ ትክክለኛውን መንገድ እንከተል፣
ድሉ የሰፊው ሕዝብ ነው።
Scroll to Top