ሰሕድ ቁ. 22

የሰፊው ሕዝብ ድምፅ

ቁጥር 22፣    የካቲት 4፣ 1967 

የፅሁፉ ፍሬ ሀሳብ

መኢሶን በዚህ የሰፊው ሕዝብ ድምፅ እትሙ፣ የኤርትራና የኤርትራ ነጻ አውጭ ግንባሮችን ታሪክ ለመንደርደሪያ ካቀረበ በኋላ፣ ግንባሮቹ በገጠር ትግል ከጀመሩ 13 አመታት እንዳለፉ፣ በዚህም ጊዜ በጦርነቱ ምክንያት በሕይወትና በንብረት ላይ የሚደርሰው ጉዳት አሁንም እንዳልቆመ ይገልጻል። ምክንያቱም፣ የኤርትራ ችግር ከአጼ ኃያለ ሥላሴ መንግሥት ፍጻሜ በኋላ በሰላማዊ መንገድ ከመፍታት ይልቅ፤ ወታደራዊ መንግሥት በተራው እንደቀድሞው ችግሩን በጦር ኃይል ብቻ ደም እያፋሰሰ ጦርነቱን በመቀጠሉ ምክንያት እንደሆነ ይጠቁማል። በአንድ በኩል፣ ጊዜያዊ ወታደራዊ ደርግ ለኤርትራ ጥያቄ በጦር ኃይል ከማንበርከክ ባሻገር ፖለቲካዊ መፍትሄ ለመስጠት በጭራሽ ያልሞከረውን ያህል፤ የኤርትራ ነጻ አውጭ ግንባሮችም ለውይይት ፈቃደኛነታቸውን ለማሳየት ፈቃደኛነታቸውን ቢገልጹም፤ በቅድሚያ ግን የኤርትራን ነጻነት የኢትዮጵያ መንግሥት እንዲቀበል ቅድመ ሁኔታ ማስቀመጣቸውን ይጠቅሳ። ቢሆንም ግን ይህ ለድርድር እንቅፋት መሆን እንደማይገባውና፣ ሁለቱም ለችግሩ በውይይት ሰላማዊና ፖለቲካዊ መፍትሄ እንዲፈልጉና በሕዝቦች መካከል ደም መፋሰስ መቆም እንዳለበት አጥብቆ ያሳስባል።

የሰፊው ሕዝብ ድምፅ

ለሰፊው ሕዝብ ሰራተኛ ገበሬ፣ ነጋዴ፣ ወታደር፣ ምሁር መብትና ጥቅም የሚታገል ጋዜጣ

የኢትዮጵያ ሰፊ ሕዝብ ይቅደም

 
ቁጥር 22                                                                     ቀን 4/6/1967

 

የኤርትራን ችግር እንዴት በትክክል ለመፍታት ይቻላል?

“አንድ የተወሰነ ብሄር /ኔሽን/ ህይወቱን እንዴት እንደሚያደራጅና የወደፊት ተቋሙ ምን መልክ እንደሚይዝ የሚወስኑት የኢኮኖሚ የፖለቲካና የባህሉ ሁኔታዎች ናቸው። እያንዳንዱ ብሄር የራሱ የሆነ መፍትሄ ሊኖረው ይችላል። ዳያሌክቲካዊ አቀራረብ የሚያስፈልገው ነገር ቢኖር በቅድምያ የብሄሮች ጥያቄ ነው።”

“ለመድገም፣ ከተጨባጭ ታሪካዊ ሁኔታዎች መጀመር፣ ትክክለኛ ዳያሌክቲካዊ የሆነ አቀራረብ- የብሄሮችን ጥያቄ ለመፍታት ቁልፉ ይህ ነው።” ጄ.እስታሊን፣ ማርክሲዝም ኤንድ ዘ ናሽናል ኩዌስችን

“የብሄሮች ጉዳይ በከበርቴ ህብረተሰብ ውስጥ ታሪካዊ ቦታ አለው። ይህን በመመልከት የብሄራዊ ንቅናቄዎችን ታሪካዊ ስፍራ ማርክሲስት የሆነ ሁሉ ሙሉ በሙሉ ያውቅላቸዋል /ይደግፋቸዋል/። ለጠባብ ብሄረኛነት ምክንያት እንዳይሆንና የቡርዠዋ አይዲዮዩሎጂ ወዛደራዊ ንቃትን እንዳይጋርድ ግን ይህ ድጋፍ በንቅናቼዎቹ ውስጥ ላለው ተራማጅ ክፍል ብቻ መወሰን ይኖርበታል።” ሌኒን፣ ኮዎ. ቮ.2ዐ፣ ገጽ 34

የኤርትራ ሕዝቦች የኃይለሥላሴን ፋሽስታዊ አገዛዝ መቋቋም ከጀመሩ ይኸው አሥራ ሦስት ዓመታት አልፈዋል።

በነዚህ ዓመታት ውስጥ በነዚህ ሕዝቦች ላይ የደረሰው ግፍና በደል ተቆጥሮ የማያልቅ ነው። አሁን እነዚህ መስመሮች በሚፃፋበትም ወቅት በኤርትራ ውስጥ፣ በዋናው ከተማ፣ በነፃ አውጭ ግንባሮቹና በኢትዮጵያ ሰራዊት መካከል ውጊያ እየተካሄደ ነው። ይህም ሲሆን በብዙ ሰላማዊ ሕዝብ ላይ የሕይወትና የንብረት ጥፋት ይደርሳል፣ የስንቱ ንፁ ደም በከንቱ ይፈስሳል። የኃይለሥላሴ መንግሥት ከወደቀ ወዲህ በሰላም በቀላሉ ሊፈታ ይችል የነበረው የኤርትራ ጥያቄ ባሁኑ ጊዜ ወደከፍተኛ የወንድማማች ደም መፋሰስና እልቂት ደርሷል። ይህ ሁኔታ ከቀጠለ የኤርትራ ሕዝቦችና የኢትዮጵያ ሕዝቦች ፈጽመው አብረው ለመኖር ከማይችሉበት፣ ፍፁም መቆራረጥ ከማይቀርበት አስጊ ሁኔታ ላይ እንደሚደርስ ምንም ጥርጥር የለውም። ከዚህ ከሚያቆራርጥ ሁኔታ ላይ እንዳይደርስ ከተፈለገ በጣም አስቸኳይ በሆነ መንገድ ይህ የርስበርስ መፋጀት ቆሞ ሰላማዊ መፍትሄ መገኘት አለበት። በሁለቱም ወገኖች በኩል ለሰፊው ሕዝብ -ለኤርትራና ለኢትዮጵያ ሕዝቦች- ደህንነትና የወደፊት ግስጋሴ የሚያስቡ ካሉ ይህ ሰላማዊ መፍትሄ ሊገኝ ይችላል።

ይሁንናም ይህ መፍትሄ እንዴት ሊገኝ እንደሚችል ከማሰላሰላችን በፊት የኤርትራን ታሪክ ባጭሩ መመልከትና ሁኔታውም ከዚህ እንዴት እንደደረሰ ማጥናት አለብን። እንዲሁም ባሁኑ ጊዜ በቀይ ባህር አካባቢና ኢትዮጵያንም በሚመለከተው በኩል በዓለም አቀፍ ደረጃ ጊዚያዊው የኃይሎች አሰላለፍ እንዴት እንደሆነ ማጤን አለብን። እነዚህን ካላደረግን ትክክለኛውንና ተጨባጩን ሁኔታ ለማየትና ለማሳየት ካለመቻላችንም በላይ በዚህም ሆነ በዚያ በኩል የሚኖረን አቀራረብ ስህተተኛ ሊሆን ይቻላል።

1.የኤርትራ አጭር ታሪክና የራስን እድል በራስ ስለመወሰን ብት

የኤርትራን ትግል በሚመለከተው በኩል እስከዛሬ ድረስ የወጡት የግንባሮቹ ጽሁፎች ሊያሳምኑን የሚፈልጉት አንድ ነገር አለ። ይኸውም፣ ዛሬ ኤርትራ ተብሎ የሚጠራው አገር፣ ይህ የጣሊያን ቅኝ ገዥዎች ባለፈው ክፍለ ዘመን መጨረሻ ላይ ይህንን ስም ያወጡለት የሰሜን ምሥራቅ ክፍል በመቼውም ጊዜ ቢሆን የአበሻ መንግሥት ወይም የአገር ክፍል እንዳልነበረ ነው። እኤአ በ1967-68 ግድም ይወጡ የነበሩት አንዳንድ ጽሁፎችማ ከነጭራሹ የቋንቋም፣ የባህልም፣ የሀይማኖትም ግንኙነት በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል አልነበሩም እስከማለት የደረሱበት ወቅት ነበር። ከዚያ ወዲህ ታትሞ የተሰራጨ፣ ‘ኤርትራ፣ – ታሪክ፣ ጂኦግራፊ፣ ኤኮኖሚ’ የሚል፣ ቀን ያልተፃፈበት አንድ የግንባሩ ጽሁፍ ‘እንደእውነቱ ከሆነ መቼውንም ቢሆን ኤርትራ የኢትዮጵያ ክፍል ሆና አታውቅ’ ካለ በኋላ፣ በዘር፣ በቋንቋዎች፣ በሃይማኖቶች፣ በጂኦግራፊ ሁለቱ አገሮች ምን ያህል ልዩ እንደሆኑ ለማስረዳት ይሞክራል። እርግጥ ነው፣ ‘ኢትዮጵያ’ የሚለውን ቃል እንደምኒልክ የንጉሰ ነገሥት መንግሥት ግዛት ብቻ ከወሰድንና ከምኒልክ በፊትም ሆነ ከፌዴሬሽኑ ወዲህ ያለውን ሁኔታ ወደጐን ከተውን ይህ አባባል -ማለትም፣ የኢትዮጵያ ክፍል አልነበረችም የሚለው- ያስኬዳል። ይሁንናም፣ የተባለው ጽሁፍ እራሱ አልፎ አልፎ ለማመን እንደተገደደው ሁሉ ዛሬ ኤርትራ ከተባለችው አገር ዋናው ክፍል የጥንቱ የአበሻ መንግሥት አካል እንደ ነበር ምንም ጥርጥር የለውም። በተረፈ፣ የዘር፣ የቋንቋ፣ የሀይማኖት ‘አለመመሳሰል’ የሚለው በእውነቱ ምንም ክርክር የሚያስፈልገው ስላልሆነ ወደጐን እንተዋለን።

ኤርትራ የተባለው የዛሬይቱ ኢትዮጵያ ክፍለአገር ያሁኑን ስሙን ያገኘው በ1889 የጣሊያን ቅኝ ሆኖ በጣልያን መንግሥትና በምኒልክ መካከል የውጫሌ ውል በተፈረመበት ጊዜ ነበር። ከዚህ በላይ ያነሳነው የኤርትራ ግንባር ጽሁፍ የሚጠቃቅሰው የትሬቫስኪስ የኤርትራ ታሪክ መጽሃፍ ‘ከዚያ በፊት -ማለት ከ1889 በፊት-ኤርትራ ምንም አንድነት፣ አንዳችም የራስዋ መንግሥት የራስዋ ስም እንኳን አልነበራትም’ ይላል። በኤርትራነት ከታሰበ ይህም ትክክል ነው። ከውጫሌ ውል በፊት ኤርትራ የሚባል አገር አልነበረም። እንግዲህ የጥንቱስ?

ለስድስት ወይም ሰባት ክፍለዘመናት በዚህ በአፍሪካ ክፍል አሸብርቆ የነበረው የአክሱም ስልጣኔ ዛሬ ኤርትራ የተባለውንም አገር ያጠቃልል እንደነበር ብዙ የሚያከራክር አይደለም። የግንባሩ ፀሃፊዎች እራሳቸው ‘ኤርትራ የአክሱም ስልጣኔ እምብርት ነበረች’ ብለው የፃፉበት ወቅት ነበር። ደግሞም አክሱማውያን ከመውደቃቸው በፊት ቀይ ባህርንም ተሻግረው ደቡብ አረብን ለጥቂት ጊዜም ቢሆን አስገብረው እንደ ነበር የታወቀ ነው። የታሪክ ፀሃፊዎች እንደሚገምቱት ከሆነ፣ አሁን የኤርትራን ዋና ክፍልና ከመረብ አገር ያለውንም አገር የያዙት የትግራይ ነገዶች የተፈጠሩት፣ አገዎች የአክሱምን ስልጣኔ ደምስሰው አክሱማውያንን ከከላለሱ በኋላ፣ ከዘጠነኛው እስከ አሥራ ሁለተኛው ክፍለዘመን ግድም በነበረው ጊዜ ውስጥ ነበር። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ እስከጣልያን ቅን አገዛዝ መምጣት ድረስ፣ የኤርትራ ዋና ክፍሎች የሆኑት ሃማሴን፣ እከለጉዛይና ሥራዬ፣ አንዳንዴ ጥብቅ በሆነ አንዳንዴም በላላ መልክ፣ አክሱምን በተካው በአበሻ መንግሥት ስር እንደ ነበሩ ታሪክ ይመሰክራል። በዚሁ በአበሻ መንግሥት ስር የሆነው ገዥያቸውም ‘ባህረ ነጋሽ’ ይባል እንደ ነበር ተደጋግሞ ተገልጿል።

ይሁንናም፣ በ1557 ቱርኮች ምጽዋን ይዘው በዙሪያው ያለውን ቆላ አገር የሃርቂቆ ነይብ በሚባለው የቤጃ ባላባቶች ዘር ስር ያስተዳድሩት ነበር። ይህ ሁኔታ ለሦስት መቶ ዓመታት ቀጥሎ በ1872 ግብጾች ምፅዋን ያዙ። በሌላ በኩልም ግብጾች በ1875 ሀረርን ይዘው እንደነበር ይታወሳል። በዚሁ አመት የኤርትራን ደጋ አገር ከላይ የተጠቀሱትን ክፍሎች ለመያዝ ሲሞክሩ በጉንደት ላይ በአጼ ዮሃንስ ሰራዊት ተሸንፈው ወደ ምጽዋ ተወርውረዋል። በሚቀጥለው አመት፤ 1876 እንደገና ሙከራ ሲያደርጉ በጉራ ላይ ከበፊቱ በባሰ ሁኔታ ተሸንፈዋል።

አጼ ዮሃንስ ምጽዋንና ከበስተኋላው ያለውን፣ ያኔ በጐስ ተብሎ ይታወቅ የነበረውን፣ አገር በእንግሊዞች አማካይነት ወደራሱ ግዛት ለመመለስ ሞክሯል። በሰኔ 3 ቀን 1884 በእንግሊዝ፣ በግብጽና በአጼ ዮሃንስ መካከል በተፈረመው ውል መሰረት ግብጾች ሰራዊታቸውን ከዚያ ሰፈር ሲያስወጡ፣ የተባሉት ክፍሎች ወደ ኢትዩጵያ ይመለሰሉ ተብሎ ነበር። ነገር ግን የእንግሊዝ ኢምፔርያሊዝም ዮሃንስን በማታለል፣ በ1885 ጣሊያኖች ምጽዋን ይዘው በግብጾች ቦታ እንዲተኩ አደረጋቸው። የጣሊያን ቅኝ አገዛዝ ወዲያውኑ ደጋውን ኤርትራ ለመያዝ ሙከራ ማድረግ ጀመረ። ይሁንናም በ1886 እና 87 በተሰገነይቲ በዶጋሊ፣ በራስ አሉላ መሪነት የዮሃንስ ሰራዊት ጣሊያንንም አራውጦ እንደገና ወደባህሩ መልሶታል። በ1889 አገር ወዳዱና የዋሁ ዮሃንስ ከደርቡሾች ጋር ሲዋጋ በመተማ ሲሞት፣ ጊዜውን ሲጠብቅ የነበረው የሸዋው ንጉስ ምኒልክ ‘የኢትዮጵያ ንጉስ ነገስት’ ተብሎ ዘውድ ጫነ። ወዲያውኑም፣ ከጥንትም ጀምሮ ውስጥ ውስጡንም ሆነ በይፋ ይደግፉትና መሳሪያ ያቀበሉት ከነበሩት የጣሊያን ቅኝ ገዥዎች ጋር የውጫሌን ውል ተፈራረመ። ዮሃንስ  በስንት ጊዜ ለፍቶበት የነበረውንም ከመረብ ወዲያ ያለውን አገር ለጣሊያኖች ሸጠ።

ምንም እንኳን በ1896 የአድዋ ጦርነት ተደርጐ የጣሊያን ቅኝ አገዛዝ ቢደመሰስና የውጫሌም ውል ቢሰረዝ፣ ኤርትራን በማስለቀቅ ፈንታ ምኒልክ የጣሊያን ቅኝ አገዛዝ እንዳለ እንዲቆይ ሌላ ውል ተፈራርሟል።አንዳንድ ፀሃፊዎች እንደሚሉት፣ ምኒልክ ይህንን ያደረገበት ምክንያት፣ በዚያን ጊዜ በሰሜን ኢትዮጵያ የነበረው ታላቅ ረሃብ ጣሊያኖችን ወደባህሩ እንዳይወረውራቸው ስላገደው ነው። ሌሎችም ምክንያቶች ይሰጣሉ። ለማንኛውም የትግራይ ሕዝቦች አንድ ላይ እንዳይሆኑ፣ እንዲከፋፈሉ በመፈለጉ ነው ይላሉ። ወጣምወረደ፣ የዛሬይቱ ኤርትራ የተፈጠረችው በዚህ ሀኔታ ነበር።

ጣሊያኖች ለግማሽ ክፍለዘመን ኤርትራን ከበዘበዙና ሕዝቡን ከጨቆኑ በኋላ፣ እንደሚታወቀው፣ በ1941 ካገሪትዋ እንዲባረሩ ተደረገ። ኤርትራ በእንግሊዝ ተጠባባቂነት ስር ለአሥር ዓመታት አንድትቆይ ስትደረግ በነዚህ ዓመታት ውስጥ በመጠኑም ቢሆን ዲሞክራሲያዊ ኑሮን ለማየት በቅታለች። ነፃ ጋዜጦች፣ የወዝአደር ማህበራት፣ የፖለቲካ ፖርቲዎች ነበሯት።

በ1952 ከኢትዮጵያ ጋር በፌዴሬሽን መልክ ስትያያዝ፣ የኃይለሥላሴ መንግሥት ሳይውል ሳያድር የፌዴሬሽኑን

ህጐች መጣስ ጀመረ።አገሪትዋ በ1962 በጠቅላይ ግዛትነት በጉልበት እስከ ተያዘችበት ወቅት ድረስ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት የኤርትራን ነጻ ዲሞክራሲያዊ ድርጅቶች በተንኮልና በጉልበት ደምስሷዋል። ከኢትዮጵያ ጋር በፌዴሬሽን የመያያዝ ነገር መጀመሪያውንም የኤርትራ ሕዝብ ያልተጠየቀበትና ያልተስማማበት በተባበሩት መንግሥታት፣ በተለይም በዚያን ጊዜ በዚህ ድርጅት ውስጥ ፈላጭ ቆራጭ በነበረው የአሜሪካን መንግሥት ትእዛዝ ነበር። ከላይ የተገለፀው ጠቅላላ ሁኔታ ከአሥር ዓመታት በኋላ ወደ ነፃነት ግንባር መፈጠርና ከዚያም ወደ 13 ዓመታት የመሳሪያ ትግል መርቷል።

እንግዲህ ተጨባጩ የኤርትራ ታሪክ ይህ ሲሆን፣ የኤርትራ ነፃ አውጭ ግንባሮች ጽሁፎች በየጊዜው ይህንን ታሪክ በሌላ መልክ ለማቅረብ ሞክረዋል።ይሁን እንጂ፣ ይህንን እንዲያደርጉ የሚያስገድዳቸው አንዳችም ነገር አልነበረም፣ የለምም። ለአንድ ሕዝብ የራሱ ማንነት /አይደንቲቲ/ በግልጽ ከታየው በማንኛውም ጊዜ የራሱን እድል ከመወሰን ማንም ሊገታው አይችልም። ከሌሎች ሕዝቦች ወይም ብሄሮች ጋር በታሪክ መያያዙ፣ በመሰረቱ የራሱን እድል በራሱ የመወሰንና ከፈለገም የመገንጠል መብቱን አያስቀርበትም።

ኤርትራ በርከት ያሉ ብሄሮችን /ናሽናሊቲስ/ የያዘች ቢሆንም የሃምሳ አመት ቅኝ አገዛዝና በተለይም የእስር አመቱ የፖለቲካ ኑሮ በመጠኑም ቢሆን ለኤርትራ ሕዝቦች አንዳች አይነት ማንነትን እንደሰጣቸው ለመገመት ይቻል ይሆናል። ኤርትራውያን ይህንን ማንነት በማወቅ አሥራ ሦስት ዓመታት ሙሉ የራሳቸውን እድል የመወሰን መብታቸው እንዲታወቅላቸው ሲታገሉ ቆይተዋል። የኃይለሥላሴ መንግሥትም ሆነ የጊዚያዊው የወታደር መንግሥት የኤርትራን የነፃነት ግንባሮች ‘ጥቂት ወንበዴዎ’፣ ‘ሽፍቶች’ ወዘተ. ማለታቸው ይህንን ሃቅ በምንም መንገድ አይለውጠውም። የኤርትራ የነፃነት ተዋጊዎች እንደዚያ እንደሚባሉት ቢሆን ኖሮ የኤርትራ ሰፊ ሕዝብ እነርሱን በማቀፍ ፈንታ አሳልፎ በሰጣቸው፣ እራሱ በያዛቸውና ባጠፋቸው ነበር። ስለኤርትራ የወደፊት እድል ከግንባሮቹ ጋር ለመነጋገር በመጀመሪያ ለግንባሮቹ የረጅም ጊዜ የነፃነት ትግልና ለተዋጊዎቹ ትክክለኛ የታሪክ ስፍራቸውን ለመስጠት ያስፈልጋል። ይህን መካዱ አይበጅምና። የኤርትራ ሕዝቦች ትግል የኃይለሥላሴን መንግሥት ካከሰሩትና ካጣሉት ዋና ነገሮች አንዱ መሆኑ እየታወቀ፣ በአሁኑ ጊዜ የነዚህን ሕዝቦች የራሳቸውን እድል የመወሰን መብት አለማወቅና አሁን ደርጉ እንደሚያደርገው የጉልበት መፍትሄ መፈለግ በኤርትራ ሕዝቦች ላይ ብቻ ሳይሆን በኢትዮጵያ ሕዝቦችም ላይ ታላቅ ጉዳትን ማድረስ ነው።ወታደራዊው መንግሥት በዚህ ጥያቄ ላይ ፈጽሞ የኃይለሥላሴን መንግሥት ጐዳና መከተል የለበትም።ጊዜው የሚጠይቀው አዲስና ዲሞክራሲያዊ ጐዳናን ነው። 

2. ከየካቲት እንቅስቃሴ ወዲህ የኤርትራ ጥያቄ አመጣጥ 

ከየካቲት እንቅስቃሴ ጀምሮ እስከ ሰኔ 22 ድረስ የኤርትራ ግንባሮች አቋም ‘ሁኔታው ወዴት እንደሚያመራ እናያለን’ የሚል ነበር።ምንም እንኳ አንዳንድ የጥቃት እርምጃዎች አልፎ አልፎ ቢወሰዱና አንዳንድ የኃይለሥላሴ መንግሥት ሹሞች በግንባሮቹ ተዋጊዎች ቢገድሉም፣ ጠቅላላው የግንባሮቹ አቀራረብ የዛሬውን አይመስልም ነበር። የአሁኑ የጦር ኃይሎች ደርግ በተፈጠረና አድሃሪዎቹን በያዘ ማግስት፣ ሰኔ 24 ቀን አንድ የግንባሩ ወኪል ኡኒታ ለተባለው የጣሊያን ጋዜጣ በሰጠው መግለጫ እንደሚከተለው ተናግሯል።

በኢትዮጵያ በመካሄድ ላይ የነበረውን ሕዝባዊ እንቅስቃሴ በሚመለከተው በኩል ለኤርትራ ሕዝብ ትርጉም የሚኖረው ነገር የኢትዮጵያ መንግሥት እስካሁን የነበረውን የመስፋፋት ፖሊሲ የለወጠ እንደሁ ነው። ቁም ነገረኛ ፖለቲካ ሊኖር የሚችለው የኤርትራ ትግል የታወቀ እንደሆነና ያለፉት 13 ዓመታት ትግል ለነፃነት መሆኑ የተረጋገጠ መሆኑን ነው፣ የዚህም መደምደምያ የሰላም ውይይት መሆን አለበት። አስከዚያ የኢትዮጵያን ሁኔታ በጥብቅ እንከታተላለን። ጊዚያዊው ሁኔታ ከቀጠለና የጥንቱ ፖለቲካም ከቀጠለ ኢትዮጵያ ማንም ሊቆጣጠረው ወደማይችል ኬኦስ /ምስቅልቅል/ መጓዝዋ ነው።

የኢትዮጵያ ወታደሮችና ሃቀኛ ብሄራዊ ኃይሎች መፍትሄ ማግኘት አለባቸው። ….ኢኤልፍና ፔኤልኤፍ /ሁለቱ ግንባሮች/ በሁሉም በኩል፣ በመሳሪያም ጭምር፣ ድርጊቶቻቸውን …እንዲያስፋፉ እናደርጋለን። በአውሮፖና በሌሎችም የዓለም ክፍሎች ያሉት መልእክተኞቻችን ኘሮፖጋንዳቸውን አጠንክረው የዓለምን ሕዝብ ድጋፍ ማስገኘት አለባቸው። በሴኘቴምበር /መስከረም/ ጉዳያችን ከተባበሩት መንግሥታት ፊት እንዲቀርብ ይደረጋል። /ሰርዝና ቅንፍ የተጨመረ/

ማንም ሊቆጣጠረው የማይችል ‘ኬኦስ’፣ ጠቅላላ ድብልቅልቅ፣ የሚለውን አስተሳሰብና የመሳሪያ ትግል ማስፋፋት የሚለውን በዚህ ሁኔታ ከማናቸውም ተራማጅ የማይጠበቀውን አባባል ወደጐን ብንተው፣ ከዚህ በላይ የጠቀስነው፣ ግንባሮቹ የሰላም ውይይት ይፈልጉ እንደ ነበር በግልጽ የሚያሳይ ይመስለናል። ነገር ግን፣ በዚያኑ ሰሞን ‘ኢትዮጵያ ትቅደም’ የሚለውን መመሪያ ማስፋፋት የጀመረው የጦር ኃይሎች ደርግ በዚህ ጥሪ በመጠቀም ውይይቱ እንዲጀመር ለማድረግ ምንም እርምጃ አልወሰደም። ይልቁንም ‘ኢትዮጵያ ትቅደም’ ከያዛቸው አላማዎች አንዱ ‘የኢትዮጵያ አንድነት ፍፁምነት’ መሆኑን በሰፊው በማብራራት ‘ብሄርተኛነቱን’ /ናሽናሊዝሙን/ ማጋነን ያዘ። በተረፈም፣ ለኃይለሥላሴ ካቀረባቸው የስልጣን መረከቢያ ድርድሮች አንዱ የፖለቲካ እስኞች መለቀቅ መሆኑ ሲታወቅ፣ በንጉሱ ‘ፈቃድ’ የተባሉት እስረኞች ሲፈቱ፣ የኤርትራ እስረኞች ግን እንዳይለቀቁ አደረገ።

በግንባሮቹም በኩል ሆነ በደርጉ በኩል ይህ ውዠንብር የሞላበት ሁኔታ ከወር በላይ ቆይቶ ነሀሴ 1ዐ ቀን ሃያ ሶስቱ የኤርትራ እንደራሴዎች የኃይለሥላሴን ፖርላማ ትተው ይወጣሉ። ለዚህ እርምጃቸው የሚሰጡአቸው ምክንያቶች የመንግሥቱን በኤርትራ ጉዳይ ቸልተኝነትና የአስመራ ኤኮኖሚ መሞት፣ የኦምሃጀር ፍጅት፣ የኤርትራን የፖለቲካ እስረኞች አለመለቀቅና በዚህም ልዩነት መደረጉን ነበር። ነሃሴ 14 ቀን ሚካኤል እምሩ ከፖርላማው ፊት ቀርቦ በፍፁም ግድየለሽነት ‘የኤርትራ ችግር ከሌሎቹ የኢትዮጵያ ችግሮች የተለየ አይደለም’ ሲል፣ በበኩሉ የአሜሪካኖች ሰው የሆነው በላቸው ጀማነህ የፖለቲካ እስረኞች መለቀቅ የተባለው ‘በመሳሪያ ኃይል የንጉሰ ነገሥቱን መንግሥት የሚዋጉትን አይመለከትም’፣ ስለዚህ የኤርትራ የፖለቲካ እስረኞች አይለቀቁም አለ።

ምንም እንኳን በደርጉ በኩል ፍፁም ይቅርታ የማይደረግለት ቸልተኝነት ቢታይም፣ ሚካኤል በተናገረ ማግስት፣ በካይሮ የሚገኘው የግንባሩ /የኢኤልኤፍ/ ወኪል ውይይት ይከፈት የሚል መግለጫ ያወጣል። በዚህ መግለጫ ውስጥ ግንባሩ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ለኤርትራ ‘ሙሉ ብሄራዊ ነፃነት’ ውይይት ለመክፈት ዝግጁ መሆኑን ያመለክታል።ውይይቱ የሚከፈትበትን አገር ሁለቱ ወገኖች /የኤርትራ ግንባርና የኢትዮጵያ መንግሥት/ ይመርጣሉ። ይሁንናም ለውይይቱ መከፈት ግንባሩ የሚያቀርበው ድርድር የኤርትራ ግንባር የኤርትራ ሕዝብ ህጋዊና ለብቻው ወኪል መሆኑን የኢትዮጵያ መንግሥት እንዲያውቅለት የሚል ነበር። በተጨማሪም የተባበሩት መንግሥታት በፍጥነት አንድ መርማሪ ኮሚስዩን ወደኤርትራ ልከው ይህ ኮሚስዩን የሕዝቡን የራሱን እድል የመወሰን መብት እንዲጠበቅለትና በተባበሩት መንግሥታት፣ በአፍሪካ አንድነት ድርጅትና በአረብ ሊግ ቁጥጥር ስር በኤርትራ ሬፈሬንደም /የሕዝብ ፈቃድ ጥያቄ/ እንዲደረግ ይጠይቃል።

ከአምስት ቀናት በኋላ፣ ማህሙድ ሰይድ ኢድሪስ የተባለው የግንባሩ ወኪል ይህንኑ የመሰለ መግለጫ በቤይሩት ይሰጣል። የሚያቀርበው ድርድር ያው ግንባሩ የሕዝብ ወኪል መሆኑ እንዲታወቅለት ነው። ምርጫው የሚደረገው ያው ከዚህ በላይ በተጠቀሱት ድርጅቶች ስር ይሆናል ይላል። ይኸኛውን መግለጫ ይበልጥም የውይይት ግብዣ የሚያደርገው የሚከተለው አረፍተ ነገር ይገኝበታል። ‘ለኤርትራ ድራማ፣ ለብዙ መቶ መንደሮች መደምሰስና ለሰባ ሺህ ኤርትራውያን መበታተን ዋናው ሃላፊ ኃይለሥላሴ ነው።’

እንደእውነቱ ከሆነ በነበረው ሁኔታ ከዚህ የበለጠ የሰላም እጅ ለመዘርጋት እንደማይቻል ግልጽ ነው። መቼም አሥራ ሦስት ዓመታት ሙሉ ለብሄራዊነት ሲታገል የቆየ እንደ ኤርትራ ግንባር ያለ ድርጅት ውይይትን ለመክፈት ከ ‘ሙሉ ነፃነት’ ያነሰ ነገር ለውይይት መንደርደሪያ ማቅረብ አይችልም። በዚህ አይነቱ ሁኔታ እንደምንም ተከራክሮ ዋናው ነገር – የውይይት መከፈት- እንዲገኝ ለማድረግ ሲቻል፣ ደርጉ ግን አማን አንዶምን ወደ ኤርትራ ልኮ እርሱ ሕዝቡን እንዲደልል መረጠ።

በእርግጥ፣ የውጭ አገር ጋዜጦች እንዳመለከቱት ሁሉ፣ ያሜሪካኖች ሰው ነበረ የሚባለው አማን አንዶም ለጥቂት ጊዜም ቢሆን የኤርትራን ሕዝብ ለማወናበድ ችሎ እንደነበር የተደረገለት የጋለ አቀባበል አሳይቷል። ከአሥራ ሁለት ቀናት ጉብኝት በኋላ ጳጉሜ 1 ቀን ወደ አዲስ አበባ ሲመለስ ለኤርትራ ሕዝብ የሚከተሉትን ነገሮች ለማስፈጸም ቃል ገብቷል።ከአምስት አመት በፊት በኤርትራ ላይ የተጫነው የልዩ ጊዜ አዋጅ እንደሚነሳ፣ የኤርትራ ኤኮኖሚ እንዲንቀሳቀስ እንደሚያደርግ፣ በኦምሃጀር የፍጅት ወንጀል የፈፀሙት ፖሊሶችና ወታደሮች ለፍርድ እንደሚቀርቡ፣ ከአራት መቶ በላይ የሆኑት ኤርትራውያን የፖለቲካ እስከረኞች እንደሚፈቱ፣ ኤርትራውያን ወደውጭ አገር ለመሄድ ሲፈልጉ ችግር እንደማይደርስባቸው፣ የተዘጉት የኤርትራ እንዱስትሪዎች እንደሚከፈቱ ወዘተ. ቃል ገብቶ ነበር። ይሁንናም አማን አንዶም ኤርትራ በቆየበት ጊዜ በተለይ የጐበኘው የመንግሥቱን ሰራዊትና የፖሊስ ክፍሎች ከመሆኑም በላይ፣ ደጋግሞ ‘የኢትዮጵያና የኤርትራ አንድነት ፍፁም ነው። ኤርትራ የኢትዮጵያ አንድ ክፍል ናት’ በማለት በይፋ ተናግሯል። በተረፈም፣ ከላይ ከተጠቀሱት ተስፋዎች አንዱም እንኳን ከሥራ ላይ ለማዋል እርምጃ አልተወሰደም።

በደርጉ በኩል፣ ባንድ ወገን የበጎ ፈቃደኛነት ጉድለትና ቸልተኝነት፣ በሌላ ወገን ደግሞ የኃይለሥላሴና ግብረአበሮቹን ከስልጣን የማስወገዱ ተግባር መንዛዛት ጉዳዩን ሲያዘገየው፣ በኤርትራ ግንባሮች በኩል ደግሞ የአማን ጉብኝት ግራ አጋብቶአቸው ለጥቂት ጊዜ ፀጥ ያሉ ይመስሉ ነበር። መስከረም 2 ቀን ንጉሱ ከስልጣን ተወገደ። የኤርትራ ግንባሮች ስላገራቸው ከእንግዲህ አንዳች የተጨበጠ ውሳኔ ይደረጋል ብለው ከጠበቁ በኋላ፣ መስከረም 15 ቀን ኦስማን ሳላህ ሳቤ /የፒኤልኤፍ አፈጉባኤ/ በቤይሩት የጋዜጠኞች ጉባኤ አድርጐ የውይይቱን አሳብ ከማስጠንቀቂያ ጋር አቀረበ። ይህ መግለጫ ከዚህ በላይ ካየናቸው ይበልጥ ጠንከር ያለ ቢመስልም፣ ከነዚያኞቹ ይበልጥ ሰላምን ፈላጊ እንደ ነበር ግልጽ ነው። የኦስማን መግለጫ ዋና ይዘቶች እንደሚከተሉት ናቸው።

አንደኛ፣ የግንባሩና የኢትዮጵያ መንግሥት ወኪሎች በተባበሩት መንግሥታት ተጠበባቂነት ስር ውይይት ይክፈቱ ይላል። የኃይለሥላሴ መውደቅ ለዚህ ውይይት መከፈት ጥሩ ሁኔታን እንደፈጠረ ያመለክታል።ሁለተኛ፣ ‘የኤርትራ ግንባር ከብሄራዊ ነፃነት ሌላ ማንኛውንም መፍትሄ በጥብቅ መቃወሙን ይገልፃል፣ ’ ሆኖም ‘የኢትዮጵያን የንግድና የባህር ጥቅሞችና እንደዚሁም የሁለቱን ወገኖች መከላከያና ፀጥታ በሚመለከተው በኩል አንዳንድ ነገሮችን ለመቀበል /ኮንሴሺኖች ለማድረግ/ ዝግጁ ነን’ ይላል።ሶስተኛ፣ የኤርትራ ሪቮሉሽን ግቡ የሆነውን ብሄራዊ ነፃነትን እስካላገኘ ድረስ ትጥቁን እንደማይፈታ ኦስማን አመልክቶ፣ ኢትዮጵያ ካንገራገረች ግን ‘ኢትዩጵያን ከቀይ ባህር ፈጽሞ ለማራቅ ትግላችንን እንደምናፋፍመው’ እንድታውቁት በማለት ይደመድማል።

በዚህ መግለጫ ውስጥ በቁጥር 2 የቀረበው የኦስማን አሳብ ምንም ትችት የማያስፈልገው ግልጽ ነገር ይመስለናል። በዚህ መግለጫ ምክንያት እንደሆነ አይታወቅም፣ በማግስቱ መስከረም 16 ቀን፣ በሁለቱ የኤርትራ ግንባሮች መካከል፣ በከረን አጠገብ ሃይለኛ ግጭት ተደረገ። ኢሳያስ የተባለው መሪ ተገደለ የሚባል ወሬም ተሰራጨ። በዚህ ሁኔታ፣ ኤርትራውያን ተዋጊዎች እርስበርስ ሲገዳደሉ፣ የሰሜኑ ክፍለ ጦር በግንባሮቹ ላይ ሃይለኛ ማስጠንቀቂያ አወጣ። በመካከሉ፣ በኢትዮጵያ መንግሥት በኩል በኦስማን መግለጫ ላይ ምንም እርምጃ ሳይወሰድ ሲቀር፣ መስከረም 25 ቀን ሁለቱ ግንባሮች በአስመራ አጠገብ ስብሰባ አደረጉ።ይህ ሁለት ቀን የቆየና ብዙ ሺህ ሰው የተገኘበት ስብሰባ ሁለቱን ግንባሮች ያስታረቀ ይመስላል።

ከዚህን ቀን ጀምሮ በኤርትራ ያለው ሁኔታ የተባባሰ ይመስላል። መስከረም 26 ቀን ግንባሮቹ የስብሰባ ጉዳይ እንዳለቀ፣ አማን አንዶም እንደገና ወደአስመራ ሄዶ በሬዲዩ የተነበበ ጥብቅ ማስፈራሪያ ሰጠ።በመግለጫው ውስጥ አማን ‘የጦር ኃይሎች ደርግ ደም እንዲፈስስ አይፈለግም። ነገር ግን ሁኔታው ካስገደደው ማንኛውም እርምጃ ከመውሰድ አይቆጠብም።…..ለኢትዮጵያ ደህንነት ሰራዊቱ አስፈላጊውን እርምጃ ሁሉ በመውሰድ ኢትዮጵያ ትቅደም የሚለውን መመሪያ ከሥራ ላይ እንዲውል ያደርጋል።’ ከዚህ በኋላ ሃይለኛ ማስጠንቀቂያ በመስጠት አማን እንዲህ ብሏል፣ – ‘ይህንን የተሰጣችሁን እድል ካልተጠቀማችሁበት በኋላ ይቆጫችኋል፣ ሰራዊቱ ጥብቅ እርምጃ መውሰዱ የማይቀር ነውና።ሰላምን በኤርትራ ለማስፈንና በኤርትራና በኢትዮጵያ መካከል የኖረውን አንድነት ለመጠበቅ እድል ተሰጥቶአችኃል።…’

እንግዲህ ሁለቱ በኩል በዚህ ሁኔታ ዛቻና ማስጠንቀቂያ ከተወረወረ በኋላ፣ የኤርትራ ግንባሮችም አንዳች የርስበርስ ግንኙነት ካደረጉ በኋላ፣ በዚያም በዚህም በጥቅምት ወር ምንም ነገር ሳይነሳና ሳይሰማ ጊዜው አለፈ።ግንባሮቹ በበኩላቸው የአረብ አገሮችን እርዳታ ለማግኘት በይበልጥ ሲፍጨረጨሩ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ደግሞ የበጐ ፈቃድ ጓዶችን በየቦታው እየላከ የእነዚሁ የነፃነት ግንባሮች ደጋፊ አገሮች እርዳታቸውን እንዲያቆሙ ለማድረግ ሞከረ።በዚህ ሁኔታ ለአንድ ወር ያህል በሁለቱም በኩል ውስጥ ውስጡን የዲኘሎማቲክ ትግል እንደቀጠለ የህዳር 13 ቀን የአማንና የ59ኙ ሰዎች መረሸን ድርጊት ተፈፀመ።ኢምፔሪያሊስቶችና በርካታው የሶስተኛው ዓለም መሪዎች በደርጉ ላይ ትልቅ የማውገዝና የመኮነን ዘመቻ ሲጀምሩ ግንባሮቹም ይህንኑ ማስተጋባት ቀጠሉ።

በህዳር ወር ከሁለቱ ወገኖች በኩል የጦርነት ዝግጅት ሲደረግ ቆየ። የኤርትራ ግንባሮች በይፋ እንደተናገሩት ሁሉ በርከት ካሉ የአረብ አገሮች በብዙ ሚሊዩን ብር የሚቆጠር የመሳሪያ እርዳታ ሲያገኙ ደርጉ ደግሞ በበኩሉ በኤርትራ የሚገኘውን ጦር በብዙ ሺህ ወታደር በማጠንከር ዝግጅቱን ቀጠለ። ቀድሞ የኤርትራን ግንባር ከመደገፍ ይቆጠቡ የነበሩት እንደነ ሳውዲ አረቢያና ኩዌይት ያሉ አድሃሪ መንግሥታት ግንባሮቹን እንደሚደግፉ በግልጽ አስታወቁ። በታህሳስ 12 ‘የኢትዮጵያ ሶሻሊዝም’ ከታወጀ ወዲህ ኤምፔሪያሊስት አገሮች በኘሮፖጋንዳ በኩል የግንባሮቹን ትግል በመደገፍ የኤርትራን ጉዳይ ከባንግላዴሽና ከፍልፋጥኤም ጉዳይ ጋር አመሳሰለው ያቀርቡ ጀመር።

በታህሳስ አጋማሽ ላይ በኤርትራ፣ ከኢትዮጵያ መንግስትና ከግንባሮቹ አሥራ አምስት ሺህ ተዋጊዎች፣ በጠቅላላው ሰላሳ ሺህ ተዋጊዎች ፊት ለፊት ተሰልፈው ነበር። በዚህ ሁኔታ ታህሳስ 16 ቀን ያንዱ ግንባር ዋና ፀሃፊ የሆነው ኦስማን ሳላህ ሳቤ እንደገና በቤይሩት የጋዜጠኞች ጉባኤ ያደርጋል። በዚህ የጋዜጠኞች ጉባኤ ላይ ኦስማን የሚያቀርባቸው ዋና ዋና ነጥቦች እንደሚከተሉት ናቸው። የኤርትራ ግንባር ከደፈጣ /ጎሪላ/ ጦርነት ወደፊት ለፊት ጦርነት መሸጋገሩ ነው። የኤርትራን ገጠር በሙሉ ከቁጥጥሩ ስር ያደረገው የኤርትራ ሪቮሉሽን ከእንግዲህ ድርጊቶቹን ከገጠር ወደከተማ በመዛወር ከተሞችን ለመያዝ ይዘጋጃል። የጦር ኃይሎች ደርግ እንደ ኃይለሥላሴ መንግሥት ሁሉ ኤርትራን በጉልበት ለመያዝ ሲል ከሃያ ሺህ በላይ የሚሆን ወታደር በኤርትራ አስፍሯል። ይሁንናም የኤርትራ ግንባሮች በቅርቡ ፀረታንክ መሳሪያዎች፣ መድፎችን፣ ያውሮኘላን መከላከያዎችን በብዛት በማግኘታቸው ሃይላቸው ከኢትዮጵያ ሰራዊት ያነሰ አይደለም። የኢትዮጵያ መንግሥት በአስመራ ከአራት መቶ ሰዎች በላይ ይዞ ማሰሩንና ብዙዎችንም መግደሉን፣ እንደዚሁም በኢትዮጵያ ሰራዊት ውስጥ ያሉት ኤርትራውያን ከድተው ለግንባሮቹ መግባታቸውን ከተመለከተ በኋላ ኦስማን በሚከተሉት የምስጋና ቃላት ጉባዔውን ፈጽሟል፣ – ‘የኤርትራ ግንባር እንደነ ሊቢያ፣ ዲሞክራሲያዊ የመን፣ ኢራቅ፣ ሶርያና ሌሎችም የአረብ አገሮች ያሉትን፣ ግንባሩን የደገፉትንና እንደወዳጅ የሚቀርቡትን ሁሉ  ያመሰግናል።’ ይህ የኦስማን የጋዜጠኞች ጉባኤ የጦርነት አዋጅ እንደ ነበር ግልጽ ነው።

በዚህ ሁኔታ፣ የጦር ኃይሎች ደርግ ታህሳስ 19 ቀን በሚካኤል እምሩ የሚመራ ቡድን ወደ አስመራ ልኮ ወደ አራት መቶ ከሚጠጉ ያገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት መሪዎች ጋር ውይይት በማስደረግ እርቅ እንደሚፈልግ ለማድረግ ሞከረ። ከነዚህ የኤርትራ ሽማግሌዎች ውስጥ 38 ተመርጠው ከግንባሮቹ ጋር ግንኙነት በማድረግ ሰላማዊ መፍትሄ የሚገኝበትን መንገድ እንዲፈልጉ ተደረገ። ይሁን እንጂ፣ ምንም እንኳን ቀደም ብሎ መደረግ የነበረበት ቢሆንም ሙከራው ተገቢ ነበር። ደርጉ በሽማግሌዎቹ አሳሳቢነት አንዳንድ የበጐ ፈቃድ እርምጃዎችን ቢወስድም አሁን በአስመራ ከተማና አካባቢ በመካሄድ ላይ ያለው ጦርነት እንደሚያሳየው ሁኔታው ከመባባስ አላቆመም።

እንግዲህ ካለፉት ጥቂት ወራት ጀምሮ የኤርትራ ሁኔታ አመጣጥ ይህ ሲሆንና በሁለቱም ወገኖች በኩል ጥፋቶች መኖራቸው በማያጠራጥር አኳኋን ሲታይ፣ በደርጉ በኩል የተደረጉት ዋናዎቹ መሆናቸው ለማንም ግልጽ ይመስላል። በነሃሴና በመስከረም፣ በተለይ ኃይለሥላሴ ከወደቀ ወዲያ፣ ከኤርትራ ግንባሮች የቀረበውን የውይይት ሃሳብ ደርጉ በቶሎ መቀበል ነበረበት።

የግንባሩ ‘ሙሉ ነፃነትን” መጠየቅ በኛ አስተያየት ምንም ያህል እንቅፋት መሆን አልነበረበትም። አሥራ ሦስት አመት ሙሉ የታገለ ግንባር ለመነሻ ያህል ከዚህ ያነሰ ነገርን በመጠየቅ ውይይት ለመክፈት የማይመቸው እንደ ነበር ሲታወቅ፣ ደርጉ በዚህ ነገር ቸልተኝነትንና ‘ፍፁም አንድነት’ በማለት አድሃሪ የጉልበት መፍትሄ አሳቡን ከሥራ ላይ ለማዋል መሞከር አይገባውም ነበር። በሌላ በኩል ደግሞ የኤርትራ ግንባሮች ከቅርብ ጊዜ ጀምሮ ኤምፔሪያሊስቶች በደርጉ ላይ የሚያደርጉትን ከባድ ተጽእኖና ኘሮፖጋንዳ በመመልከት፣ ከእነዚህና ከሌሎች አድሃሪ ኃይሎች ጋር በመተባበር፣ ምንም እንኳን ለጊዜው በፀረዲሞክራሲያዊነቱ የማያጠራጥር ቢሆንም፣ ወታደራዊውን ደርግ እንደዋና ጠላት መቁጠርና ለማጥፋት መሞከር ትክክል አይመስለንም። የሁለቱ ወገኖች የፖለቲካ ጥፋቶች በሰላማዊው ሕዝብ ላይ ያደረሱአቸው ጉዳቶች የኤርትራንና የኢትዮጵያን ሕዝቦች ከመቆራረጥ ላይ እንዳያደርሱ ከሚያሰጋበት ሁኔታ ላይ የመጣነው በዚህ አይነት ነው።

3. ከኢትዮጵያ ህብረተሰባዊነት መታወጅ ወዲህ ኃይሎች አሰላለፍ

መላው ዓለም፣ ኤምፔሪያሊስት አገሮችም ጭምር፣ ምናልባት ፍፁም አድሃሪ ከሆኑት አንዳንድ አገሮች በስተቀር፣ የየካቲትን የኢትዮጵያ ሕዝቦች ሪቮሉሽናዊ እንቅስቃሴ ወደመጀመሪያው ገደማ በበጐ አይን ይመለከቱት እንደነበር የታወቀ ነገር ነው። ኃይለሥላሴ ከስልጣን ሲገለል አድሃሪ ኃይሎች የእንቅስቃሴውን አዝማሚያ መጥላትና አልፎ አልፎም ማንቋሸሽ ጀመሩ። የቀድሞዎቹ አድሃሪ ባለስልጣኖች መረሸንና የኢምፔሪያሊስቶች በደርጉ ውስጥ ያሏቸው ኃይሎች ለጊዜው መዳከም የብዙውን የዓለም ፀረ-ሪቮሉሽናውያን የስድብና የቁጣ መአት ሲያስከትል፣  የታህሳስ 12ቱ  ‘የኢትዩጵያ ህብረተሰባዊነት’ አዋጅ ፈጽሞ እብድ ውሻ አድርጓቸዋል።መላው ኢምፔሪያሊስት ዓለም ከማንቋሸሽና ከተግሳጽ ወደ ቀጥታ የኘሮፖጋንዳ ዘመቻ ተዛወረ። ተራማጁ ዓለም ግን በበኩሉ ከተቆጠበ አቋም ወደ ቀጥታም ሆነ ዘወርዋራ ድጋፍ አልፏል።

የኢትዮጵያ ሕዝቦች አንደኛ ዋና ጠላት የሆነው የአሜሪካ ኢምፔሪያሊዝም መጀመሪያ በእንዳልካቸው አማካይነት፣ ከዚያም በደርጉ ውስጥና አካባቢ በአማን አንዶም በኩል ያደረጋቸው ፀረሕዝብ ሴራዎች ለጊዜው ስለከሸፉበት ‘የእርዳታውን’ አቅጣጫ በመለወጥ የኃይለሥላሴ ሞግዚት በነበረበት ጊዜ የፈጠራቸውን ቡችሎቹንና አድሃርያንን በድብቅ ማዘጋጀትና ማጠናከር ጀምሯል። በአሁኑ ጊዜ የአሜራካን ኤምፔሪያሊዝም በአንድ በኩል በቢሮክራሲው ውስጥ ባሉት ሰዎቹ- እንደነ በላቸዉ ጀማነህና ተካልኝ ገዳሙ ባሉት- በሌላ በኩል እንደነሳውዲ አረቢያ ባሉት አድሃሪ መንግሥታት አማካይነት እነመንገሻ ስዩምን፣ ነጋ ተገኝን፣ አሊ ሚራህን፣ በውጭ ያሉትን መሳፍንትና የቀድሞ ባለስልጣኖች በማደራጀትና በማስታጠቅ የየካቲትን እንቅስቃሴ ውጤቶች ለመደምሰስና አድሃሪ ኃይሎችን መልሶ ከስልጣን ላይ ለማስፈር በብዙ መንገዶች በመጣር ላይ ነው። በወታደራዊው መንግሥት ላይ ልዩ ልዩ የኤኮኖሚ ተጽእኖ ለማድረግም እየሞከረ ነው። ለምሳሌ የንግስት ዘውዲቱን ሆስፒታል እስካሁን ሲያካሂዱት የነበሩ የአሜሪካ ሚሲዩኖች በቅርቡ በሙሉ ለቅቀው እንደሚወጡ ለጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አስታውቀዋል። ከልዑል መኮንንም ሆስፒታል ስዊሶች እርዳታቸውን እንደሚያቋርጡ ሰሞኑን አስታውቀዋል ይባላል። ያንኪ አሜሪካኖችም የዘንድሮን ቡና እንደማይገዙ ‘በአማካሪዎቻቸዉ’ በኩል በሰፊው አስወርተዋል።[1]

የኤርትራ ጥያቄ በኢትዮጵያ ውስጥ በመካሄድ ላይ ካለው ሪቮሉሽናዊ እንቅስቃሴ ተነጥሎ ሊታይ አይችልም። የኃይለሥላሴ መገልበጥ፣ የጥቂት መሳፍንትና መኳንንት መረሸንና ‘የኢትዮጵያ ሶሻሊዝም’ መታወጅ፣  ኤምፔሪያሊዝምና የመላው ዓለም አድሃሪዎች ባንድ በኩል፣ ደርጉና የኢትዮጵያ ሰፊ ሕዝብ በሌላው በኩል እንዲሰለፉ በማድረግ ላይ ነው። ኢምፔሪያሊዝምና በተለይም በቀይ ባህር አካባቢ የሚገኙት አድሃሪ ኃይሎች በኤርትራ ጥያቄ በመጠቀም ባሁኑ ጊዜ የየካቲትን ሕዝባዊ እንቅስቃሴ ውጤት ለማጨናገፍ በኢትዮጵያ ሕዝቦች ላይ ለመዝመት በመዘጋጀት ላይ ናቸው። የኤርትራ የነፃነት ግንባሮች ይህንን ሁኔታ አጤነው በመመልከት፣  እርግጥ በአሁኑ ጊዜ ፀረኢምፔርያሊስት ትግልም እናደርጋለን የሚሉ ከሆነ፣  በሰፊው የኤርትራ ሕዝብ ጥቅም ላይ በመመስረት ሰላማዊ መፍትሄውን መፈለግ እንጂ ወደዱም ጠሉም ከኢትዮጵያና ከኤርትራ ሕዝቦች እውነተኛ ጠላቶች ጋር የሚያሰልፋቸውን እርምጃ መውሰድ አይገባቸውም።

በአሁኑ ጊዜ የቀይ ባህር አከባቢና የኢትዮጵያዊ ውስጣዊ ሁኔታ እንደእውነቱ ከሆነ በጣም የተወሳሰበ ነው። በኤርትራ ጥያቄ አማካይነት ኢምፔሪያሊዝም፣  በተለይም ዋናው ጠላታችን የአሜሪካ ኢምፔሪያሊዝም፣  የኢትዮጵያን ሪቮሉሽናዊ እንቅስቃሴ ለማጨናገፈ ይጣጣራል። በፕሮፓጋንዳ ደረጃ የኤርትራን ግንባሮች እንደሚደግፍ የጋዜጠኞችና የሬዲዮኖቹ ኦፊሲዮል ያልሆኑ ዘመቻዎች ያሳያሉ። ዛሬ በዚህ ደረጃ ከደገፈ ነገ ደግሞ በግልጽ በመሳሪያም ጭምር ለመደገፍ የማይነሳበት ምክንያት ያለ አይመስለንም። እንዳጋጣሚ ሆኖ የያንኪ ኢምፔሪያሊዝም በዓለምአቀፍ ደረጃና በውስጥም በብዙ ችግሮች ተወጥሮ ባይያዝ ኖሮ የሳንቶዶሚንጎን የመሰለ እርምጃ እስካሁን በኢትዮጵያ ላይ ሳይወሰድ አይቀርም ነበር ብሎ ለመገመት ይቻላል። ከዚህ ሌላ ግን ባሁኑ ወቅት ኢምፔሪያሊዝም ከውጭ ካሉት መሳፍንትና መኳኳንት ጋር ሆኖ የመንገሻ ስዩምን፣ የነአሊሚራህን፣ የብሩን ልጆች ፀረሕዝብ ሴራዎችና ድርጊቶች እንደሚያደራጅ ምንም ጥርጥር የለውም።

በአሜሪካ ኢምፔሪያሊዝምና በቀይ ባህር አካባቢ ባሉት አድሃሪ ኃይሎች፣ በነሳውዲ አረቢያ፣ በነኩዌይት ትብብር ለጊዜው በኤርትራ ጥያቄ አማካይነት ፀረኢትዮጵያ የሆነ ግንባር ተቋቁሟል ለማለት እንችላለን። በሌላ በኩል ግን፣ በገሃድ እንደገለፀው ሁሉ፣ የአሜሪካ ኢምፔሪያሊዝም እነዚህን አገሮች -ነዳጅ ዘይት የሞላባቸውን የአረብ አገሮች – ለመውረር ዝግጅት በማድረግ ላይ እንደሆነ ከኪሲንጀርና ከፎርድ መግለጫና ማረጋገጫ ወዲህ ያደባባይ ምስጢር ነው። በዚህ አይነት፣ መንገድ ከተከፈተለትና የብዙ ሚሊዮን ብር ወጭም አድርጎ ከቀናው፣ የአሜሪካ ኢምፔሪያሊዝም ኤርትራን ለአረብ አገሮችም ሆነ ለኤርትራ ጥቃት የጦር ሰፈር ሊያደርጋት ይችላል ማለት ነው። ይህ አደጋ ስላለ የኤርትራ ሰፊ ሕዝብ በጥብቅ እንዲያስብበት ያስፈልጋል። 

ለማጠቃለል ያህል፣ ያሁኑ የውስጥና የውጭ ሁኔታችን እነደዚህ ነው፤ በኤርትራ ጥያቄ በማሳበብ ኢምፔሪያሊዝምና አድሃሪዎቹ የቀይ ባህር አካባቢ ኃይሎች በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ላይ ለመዝመት አይመለሱም። በኢትዮጵያ ላይ ሲባልም በአሁኑ ጊዜ አገሪትዋን በሚያስተዳድረው ደርግና በሰፊው ሕዝብ ላይ ማለት ነው። እነዚህ ፀረሕዝብ ኃይሎች የኤርትራን ሕዝቦች ከመቼውም ይበልጥ በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ በመቀስቀስ፣ ከውስጥ የተነሱትን ባላባታዊ ኃይሎች በገሃድም ሆነ በስውር በመደገፍ በማደራጀትና በማበረታታት፣ ሌሎችንም በየቦታው ለመቀስቀስ በመሞከር፣ በመንግሥቱ ቢሮክራሲ ውስጥ ባሉት ሰዎቻቸውና ምናልባትም በደርጉ በራሱ ውስጥ ባሉት የቀኝ ሰዎች አማካይነት በልዩ ልዩ ደረጃ ብዙ ሳቦታጅ በማከናወን አሁን በደርጉ ውስጥ ያሉትን ተራማጆች ለማዳከምና ለመገልበጥ ይፈልጋሉ። በርሱ ቦታ ባላባቶች ርዝራዦችና በቢሮ ከበርቴው የሚመራ፣ የኢምፔሪያሊያሊስቶች ቡችላ የሆነ መንግሥት ፈጥረው የጭቆናና የብዝበዛ ቀንበራቸውን መልሰው በኢትዮጵያ ሕዝቦች ላይ ለመጫን ይጣጣራሉ።/ይሁንናም ኢምፔሪያሊዝምና ባላባታዊ ሥርዓት ገና ስላልተደመሰሱ ሰፊው ሕዝብ አሁንም ምንም አለማግኘቱን አንዘነጋም።/ እንግዲህ በአሁኑ ሰአት፣ ወደዱም ጠሉም፣ የኤርትራ ግንባሮች የተሰለፉትና እርዳታም የሚቀበሉት ከእነዚህ አድሃሪ ኃይሎች ነው።[2]

[1] አሁን ሰሞኑን የአሜሪካ ኢምፔሪያሊዝም ለኢትዮጵያ መንግሥት /ለደርጉ/ መሳሪያ ለመስጠት እንደሚፈልግ ጠቁሟል።ይህ አዲስ የመግቢያ ታክቲክ ሊሆን ስለሚችል በደርጉ ውስጥም ሆነ ውጭ ያሉ ተራማጆች አጥብቀው እንዲያስቡበት ያስፈልጋል።

[2] ኦሳማን ሳሌህ ሳቤ ካሳኡዲ አረቢያ መንግሥት ብዙ የገንዘብ እርዳታ እንደሚያገኝ ማስታወቁን የጀርመን ድምጽ ሬዲዮ በየካቲት    3 ቀን 1967 ገለፀ።

4. የኤርትራ ጥያቄ ዘላቂ መፍትሄና የተራማጆች ጊዜያዊ ተግባር

የኤርትራ ጥያቄ ዘላቂ መፍትሄና የተራማጆች ጊዜያዊ ተግባር

  • ጋራተኞች [ኮሚኒስቶች ለማለት ነው – በአዘጋጆች የተጨመረ] ከሠራተኛው መደብ ማህበሮች የተለየ ማህበር የላቸውም።
  • በአጠቃላይ ከወዝአደሩ የተለየ ጥቅም የላቸውም።
  • የወዝአደሩን ንቅናቄ ለራሳቸው የተለየ አላማ ሲሉ አያጎብጡትም።
  • ጋራተኞች ከቀሩት የሠራተኛ መደብ ማህበሮች የሚለዩት በሚከተለው ብቻ ነው።-
    1. የልዩ ልዩ አገሮች ወዝአደሮች በሚያካሄዳቸው የትግል እንቅስቃሴዎች፣ የብሄር ልዩነት ሳያደርጉ የጠቅላላውን ወዝአደር ጥቅም ይዘው በግንባር ቀደምነት ይሰለፋሉ።
    2. የሠራተኛው መደብ ከከበርቴው ጋር በሚያደርገው ትግል በልዩ ልዩ ደረጃ ላይ፣ በማናቸውም ጊዜና ስፍራ፣ የጠቅላላውን ንቅናቄ ጥቅም ይጠብቃሉ።
  • እንግዲህ ጋራተኞች፣ ባንድ በኩል፣ በማናቸውም አገር ህብረተሰቡን ወደ ፊት የሚያንቀሳቅሰው፣ የሠራተኛው መደብ ብሄራዊ ማህበራት ግንባር ቀደም ቆራጥ ታጋዮች ናቸው። በሌላ በኩል ደግሞ፣ ከሰፊው ወዝአደር ይልቅ እነርሱ የጠቅላላውን ወዝአደር ንቅናቄ የጉዞ መስመር፣ የሚያልፍባቸውን ልዩ ልዩ ሁኔታዎችና የመጨረሻ ግብ ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ አጣርተው የመረዳትና የማወቅ ችሎታ አላቸው።

ካርል ማርክስና ፍሬደሪክ ኤንግልስ፣ ዘ ከሙኒስት ማኒፌስቶ።

  • ለብሄሮች ጥያቄ መፍትሄ የአገሪትዋ ሙሉ በሙሉ ዲሞክራሲያዊ መሆን መሰረትና አስፈላጊ ነው።

 ጂ. ስታሊን፣ ማርክሲዝም ኤንድ ዘ ናሽናል ኩዌስችን፣ ገጽ 74

የኢትዮጵያ ተራማጆች ደጋግመው እነደገለፁት ሁሉ የኤርትራን ሕዝቦች የራሳቸውን እድል የመወሰን መብት ያውቅላቸዋል። የኤርትራም ሆነ የሌሎቹ ብሄሮች ጥያቄዎች በትክክል ሊፈቱ የሚችሉት ይህ ዲሞክራሲያዊ መብት ሲታወቅና ከሥራ ላይ ሲውል ነው። ብሄሮች የራሳቸውን የወደፊት እድል የመወሰን መብት አላቸው ማለት ማንም በግድ ቋንቋቸውን እንዲደመስስ፣ ባህላቸውን እንዲያንቋሽሽ፣ ማንነታቸውን እንዲያጠፋባቸው መብት የለውም ማለት ነው፣ አንድ ብሄር በፈለገው መንገድ፣ በፌደሬሽን ሆነ በኦቶኖሚ ወይንም በሙሉ አንድነት ከሌላ ብሄር ጋር ሊያያዝ መብት አለው ማለት ነው፣  የለም አልፈልግም ካለም የመገንጠልና የራሱን መንግሥት የመመስረት መብቱ የተጠበቀ ነው ማለት ነው።

የኢትዮጵያ ሰፊ ሕዝብም ሆነ የኤርትራ ሰፊ ሕዝብ የሰፊ ግዛትን፣ በወንድማማችነትና በፍፁም እኩልነት በመፈቃቀድ አብሮ የመኖርን ጥቅም ያውቃል። ድር ቢያብር አንበሳ ያስር እንደሚባለው ህብረት፣ ሰብሰብ ብሎ በአንደነት እየሰሩ መኖር ለጠላት አይመችም፣ አያስጠቃም። ሰፊ አገር ለንግድ ለኢንዱስትሪና ለጠቅላላ ብልጽግና ያመቻል። ይህንን ሃቅ የተጨቆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች ሁሉ ያውቃሉ። ስለዚህ በአሁኑ ጊዜ ምናልባት፣ ምናልባት የኤርትራ ሕዝቦች በታላቅ ጭቆናና ግፍ፣ በነዚህ አሥራ ሦስት ዓመታት በደረሰባቸው ጭፍጨፋ ተማርረው ለመገንጠል ይፈልጉ እንደሁ አናውቅም። መገንጠሉና የራሱን መንግሥት ማቆሙ መሰረታዊ መብታቸው ቢሆንም ባሁኑ ጊዜ ይህን እርምጃ መውሰድ ለሰፊው የኤርትራ ሕዝብ ይጠቅማልና ይገንጠሉ አንልም።

ይሁንናም የብሄሮች ሁሉ፣ ትልቅ ሆነ ትንሽ፣ የራሳቸውን የወደፊት እድል የመወሰን መብት መታወቅና በትክክል ከሥራ ላይ መዋል አለበት። ብሄሮች ቋንቋቸውንና ጠቃሚ የሆኑትን ባህሎቻቸውን በነፃ እንዲያዳብሩ መደረግ አለበት። ማንም ሰው በውስጥ አስተዳደራቸው ላይ ጨቋኝ ተጽእኖ እንዳያደርግ መከልከል አለበት። ኢትዮጵያን ከብሄሮች እስር ቤትነት ወደ ብሄሮች ማበብያ ስፍራ እንድትለወጥ ማድረግ ያስፈልጋል፣ ይቻላልም። ይህም የሚሆነው የሁሉም እኩልነት ከላይ በተጠቀሰው አይነት ከሥራ ላይ ሲውል ሲሆን፣ እውነተኛ የሕዝቦች አንድነት በሳንጃና በመድፍ ያልተቋቋመ አንደነት፣ በማግባባትና በመፈቃቀር ላይ የተመሰረተ አንድነት ለመሰረትና እነደአለት ፀንቶ ለመኖር የሚችለው በዚህ መንገድ ብቻ ነው።

እውነተኛ ሶሻሊስቶች በብሄሮች ጉዳይ ላይ የሚወስዱት አቋም ሁለት አንፃሮች አሉት። በአንድ በኩል ብሄሮች የራሳቸውን እድል በራሳቸው ለመወሰን ያላቸው መብት ያለአንዳች ማወላወል ይደግፋሉ። ይህም ማለት በመሰረቱ ማንኛውም ብሄር በመሰረቱ ከመረጠ፣ ያለምንም ተጽእኖ ከሌሎች ብሄሮች ጋር በፌዴሬሽን ወይም በኦቶኖሚ ወይንም በአንድነት መልክ መንግሥት አቋቁሞ ሊተዳደር እንደሚችልና ካልፈለገም የራሱን ነፃ መንግሥት ለማቋቋም ሙሉ መብት እንዳለው ያምናሉ ማለት ነው። በሌላ በኩል ደግሞ እውነተኛ ሶሻሊስቶች የብሄሮችን ጉዳይ ከጠቅላላው የአካባቢው ጊዜያዊ ሁኔታ ጋር ጥብቅ የሆነ ዲያሌክቲካዊ ግንኙነት እንዳለው ያምናሉ ማለት ነው። ይህም ማለት አንድ ብሄር ከሌሎች ተነጥሎ የራሱን ነፃ መንግሥት ለማቋቋም በሚጠይቅበት ጊዜ ይህንን ጥያቄ ይደግፉ ወይንም ይቃወሙ እደሆን ለመወሰን አስቀድመው ጠቅላላውን ጊዜያዊ የኅብረተሰብ ሁኔታ ያጠናሉ። የብሄሩ መገንጠል የተገንጣዩን ብሄርና የቀሩትንም ብሄሮች ሰፊ ሕዝብ ፈላጎት ያሟላ እንደሆነ፣ በሁለቱም በኩል ያሉትን ሰፊ ሕዝቦች ለዲሞክራሲና ለደህንነት የሚያደርጉትን ትግል ያራምድ እንደሆነ መገንጠሉን ያላማወላወል ይደግፉታል። ነገር ግን የብሄሩ መገንጠል ከጊዜያዊው ኅብረተሰባዊ ሁኔታ ጋር ሲመሳከር ከሰፊው ሕዝብ ጥቅምና ፍላጎት ጋር የሚፃረር፣ ሰፊው ሕዝብ ለዲሞክራሲና ለደህንነት የሚያደርገውን ትግል የሚያዳክም ሆኖ ካገኙት መገንጠሉን ያቃወማሉ። ያም ሆነ ይህ በመሰረቱ እውነተኛ ሶሻሊስቶች በመሰረቱ የብሄሮች ጉዳይ በሰላማዊና በዲሞክራሲያዊ መንገድ፣ የሰፊው ሕዝብ ፈቃድ በግልጽ ታውቆ መወሰን እንዳለበት ያምናሉ።

በማንኛውም ብሄር የመገንጠል ጥያቄ ላይ አቋም ሲወሰድ ከነዚህ መሰረተሃሳቦች ዝንፍ ከተባለ ውጤቱ ወይ የኔ ብሄር ከሁሉ ብሄሮች በላይ ነው የሚሉትን ትምክህተኛ ብሄረኞችን (ሾቨኒስቶችን) አለበለዚያም፣ የኔ ብሄር ከሁሉም ብሄር ልዩነቱን በግድም ሆነ በውድ ጠብቆ መኖር አለበት በማለት የልዩ ልዩ ብሄሮችን ሰፊ ሕዝቦች መቀራረብ የሚቃወሙ ጠባብ ብሄረኞችን የሚደግፍ ይሆናል። ከዚህ በላይ በተዘረዘሩት መሰረተሃሳቦች ላይ በመመርኮዝ የኤርትራን ፕሮብሌም ለመፍታት የሚቀጥሉትን ሃሳቦች እንሰነዝራለን፣ – 

ከሁሉ አስቀድሞ ይህ የሰፊው ሕዝብ ደም መፍሰሻ የሆነው የወንድማማች ጦርነት በፍጥነት እንዲቆምና የሰፊው ሕዝብ መጉላላት እንዲቀር፣ ሁለቱም ወገኖች – ግንባሮችና የኢትዮጵያ መንግሥት – ሌላውን ወገን በቅድሚያ ምንም አይነት ግዴታ እንዲገባ ሳይጠይቁ፣ ሳይውሉ ሳያድሩ ለሰላም ውይይት ተቀምጠው በአንድአንድ የመነሻ ስምምነቶች ላይ ለመድረስ ግዴታ እንዳለባቸው አውቀው መቀበል ይኖርባቸዋል።

ሁለተኛ፣ የኤርትራ ተገንጥላ መውጣት ወይንም ከኢትዮጵያ ጋር በአንድ አይነት የፖለቲካ ግንኙነት ተዋህዳ የመኖሩዋ ጉዳይ ከመወሰኑ በፊት የኤርትራ ሰፊ ሕዝብ ስለወደፊት እድሉ አሰላስሎና ተወያይቶ በዲሞክራሲያዊ መንገድ ያለምንም ተጽእኖ ለመወሰን የሚችልበት ሰላማዊ ሁኔታ ተፈጥሮ ለተወሰነ ጊዜ እንዲቆይ ያስፈልጋል። የጊዜው እርዝመት በሁለቱ ወገኖች መካከል በስምምነት መወሰን አለበት። እዚህ ላይ መታወስ የሚገባው ግን ሰፊው የኤርትራ ሕዝብ ድርድሩን ከመጀመሩ በፊት ጉዳዩን ለማብላላትና በትክክል ለማየት በቂ ጊዜ እንደሚያስፈልገው ነው። በዚህ በሰላም ጊዜ ውስጥ በኤርትራም በኢትዮጵያም ሙሉ ዲሞክራሲያዊ መብቶች ተረጋግጠው፣ ሰፊው ሕዝብ በሁለቱም በኩል ሰፋ ያለ ውይይት ሊያደርግበት ይገባል።

ሶስተኛ፣ ይህ በእርቅ በስምምነት የሚወሰነው የሰላምና የውይይት ጊዜ እንዳለቀ የኤርትራ ሰፊ ሕዝብ ያለምንም ተጽእኖ በዲሞክራሲያዊ መንገድ ድምጽ በመስጠት የወደፊት እድሉን በምን አኳን ለመወሰን እንዳሰበ ፍላጎቱን ገልጾ፣ ይህም ፍላጎት ያለአንዳች ማወላወል በሥራ ላይ እንዲውል መድረግ አለበት። 

ነገር ግን ይህ በሚሆንበት ጊዜ መታየት ያለባቸው፣ –

  1. ወታደራዊው መንግሥት ፀረኢምፔሪያሊስትና ፀረፊውዳል መሆኑን በተግባር ጭምር ቢገልጥም የሰፊውን ሕዝብ ዲሞክራሲያዊ መብቶችና ነፃነቶች እንደከለከለ ነው። በኢኮኖሚ በኩል የወሰዳቸው እርምጃዎች – ዋና ዋናዎቹን የማምረቻና የማከፋፈያ ድርጅቶች፣ መሰረታዊ የሃብት ምንጮች የሕዝብና በመንግሥት ቁጥጥር ስር ማድረግ የሶሻሊዝምን ፈለግ የተከተለ በመሆኑ የሰፊውን ሕዝብ ጥቅም የሚያረካ ቢሆንም፣ ሰፊውን ሕዝብ በመንግሥቱ ስልጣን ውስጥ እንዳይካፈል አግልሎታል። ደርጉ ሶሻሊዝምን ያውጅ እንጂ አሁንም ብዙ ፀረ-ሶሻሊስት የሆኑ ድርጊቶች ይፈጽማል። እነዚህን ሙሉ በሙሉ እስካላስወገደ ድረስ አቋሙ ሙሉ በሙሉ ሊደገፍ አይችልም።
  2. የኤርትራ ነፃ አውጭ ግንባሮች ለኤርትራ ሰፊ ሕዝብ ምንድነው የሚያቀርቡለት እንደሚታወቀው የኤርትራ ልዩ ልዩ ግንባሮች የተለያዩ ኘሮግራሞች አሉአቸው። ለማቋቋም የሚፈልጉት መንግሥት የትኛውን ኘሮግራም ይከተላል፣ የማንንስ ጥቅም ይጠብቃል የሰፊው ሕዝብ መንግሥት ከሆነ የግድ ፀረ-ኢምፔሪያሊስትና ፀረ-ፊውዳል መሆን ይኖርበታል፣ ይህ እርግጥ ነው በመሰረቱ ኤርትራ ራስዋ የብዙ ብሄሮች አገር ናት። የኤርትራ ልዩ ልዩ ብሄሮች እድላቸውን ለመወሰን ያላቸውን መብት ግንባሮቹ ያውቁላቸዋልን በነዚህና በሌሎችም ተመሳሳይ ጉዳዩች ላይ ያላቸውን አቋም አጣርተው ለሰፊው ሕዝብ መግለጽ ይኖርባቸዋል።

በኤርትራ ጥያቄ ላይ ያለን አቋም ይህ ሲሆን አሁን ደግሞ የተራማጆችን ጊዜያዊ ተግባር በማውሳት እንደምድም።

ከዚህ በላይ ያቀረብነው ትንተና እንደሚያሳየው ሁሉ፣ የኢትዮጵያ ሪቮሉሽን በአሁኑ ጊዜ ከትልቅ አደጋ ላይ አለ ብለን እንገምታለን። የመንግሥትን ስልጣን የያዘው የጦር ኃይሎች ደርግ ፀረ-ኢምፔሪያሊስትና ፀረ-ፊውዳል እርምጃዎችን – ከፀረዲሞክራሲያዊ እርምጃዎች ጋር ቢቀላቀልም – አልፎ አልፎ ስለወሰደ በአሁኑ ጊዜ ከሰፊው ሕዝብ ጐን ተሰልፎ ይገኛል። በዚህም ምክንያት በርሱና ከኢትዮጵያ ሕዝቦች ጥንድ ጠላቶች፣ በኤምፔሪያሊዝምና በፊውዳሊዝም፣ መካከል ቅራኔ አለ። ስለዚህም በአሁኑ ሰአት፣ ከዚህ በላይ እንደተባለው፣ እነርሱ በደርጉ ውስጥና በውጭም ያሉትን ተራማጆች ለማስገልበጥና የሰፊውን ሕዝብ እንቅስቃሴ ለማጨናገፍ በመዝመት ላይ ይገኛሉ።በማንኛውም መንገድ የኢትዮጵያ ተራማጆች ከነዚህ የኢትዮጵያ ሕዝብ ጠላቶች ጋር እንዳይሰለፉ ትልቅ ጥንቃቄ መደረግ አለበት እንላለን።በአሁኑ ሰአት ደርጉ በፀረዲሞክራሲያዊነቱ ከሰፊው ሕዝብ ጋር ቅራኔ ቢኖረውም በደርጉ ተራማጆችና በኢምፔሪያሊዝም- ፊውዳሊዝም መካከል ያለው ቅራኔ እጅግ በጣም የላቀ መሆኑ የማያጠራጥር ነው።

ከዚህ በላይ እንዳመለከትነውና ገሃዱ ያገሪትዋ ሁኔታ እንደሚያሳየው ከእንግዲህ በኢትዮጵያ ሲቪል ጦርነት ተጀምሯል ብለን እንገምታለን። ባንድ በኩል የተሰለፉት ኢምፔሪያሊዝምና የባላባታዊው ሥርዓት የቀድሞ ቀንዳሞች እነመንገሻ ስዩም፣ እነመስፍንና መርእድ ብሩ፣ እነነጋ ተገኝ፣ አሊሚራህ ወዘተ. ያሉት አድሃሪዎች ናቸው። በተጨማሪም የኤምፔሪያሊዝም ቡችሎች በደርጉና በመንግሥቱ ቢሮክራሲ ውስጥ ተገጥግጠው ሲመቻቸው የተቻላቸውን ሁሉ ሳቦታጅ በማድረግ ከነዚያ ጋር ይሰለፋሉ።ወደፊት ወታደራዊው መንግሥት ያውጃል የተባለው የመሬት ይዞታ አዋጅ ሲታወጅ ደግሞ የገጠሩ ባላባትና ነፍጠኛ ሁሉ ገበሬውን እራሱን አወናብዶ ለማስነሳት መሞከሩ የማይቀር ነው። በሌላ በኩል ግን የተሰለፉት ለጊዜው በደርጉ ውስጥና ውጭ ያሉት ተራማጆችና ሰፊው ሕዝብ ናቸው ለማለት የሚቻል ይመስለናል። በደርጉ ውስጥ ያሉ ተራማጆች ሁኔታውን ደህና አድርገው ባለመረዳታቸው ተራማጁ ወገን በሚገባ ተደራጅቶ አፈርገፊውን ገበሬና ወዝአደሩን እንዲያደራጅ አልተደረገም። እንግዲህ በእኛ ግምት የተጀመረው ወይንም በመጀመር ላይ ያለው የሲቪል ጦርነት ለሰፊው ሕዝብ በሚያመች ሁኔታ ነው ለማለት ያዳግታል።

በዚህ ሁኔታ የእኛ የተራማጆች ተግባር በተቻለ ፍጥነት መደራጀትና ማደራጀት ለመሆኑ ምንም ጥርጥር የለውም። ከኢምፔሪያሊዝምና ከአድሃሪ ኃይሎች ጋር በሚደረገው ትግል ከደርጉ ተራማጆች ጋር ብንተባበርም ለዲሞክራሲ የምናደርገውን ትግል መቀጠል አለብን፣ ዲሞክራሲያዊ መብቶችና ነፃነቶች ሥራ ላይ እንዲውሉ፣  ሰፊው ሕዝብ የራሱ በሆነው የመንግሥት ስልጣን ውስጥ እንዲሳተፍ፣ የብሄሮች ጥያቄና በተለይም የኤርትራ ችግር ሊፈታ የሚችለው፣ የታወጀው ሶሻሊዝም ራሱ ስር ለመያዝና ለመለምለም የተሻለ እድል ሊኖረው የሚችለው በዲሞክራሲ ውስጥ መሆኑን በማብራራትና በማስረዳት ትግሉን መቀጠል ያስፈልጋል።

በኛ ግምት የኢትዮጵያ ሪቮሉሽናዊ ጐዳና ጠመዝማዛና ወጣገባ የሞላበት ይሆናል። አንዳንዴ መንገዱ የሚጠመዘዝበት ማእዘን ላይታይ ይችላል። አንዳንዴም በቀላሉ ልንወናብዳቸው የምንችልባቸው ሁኔታዎች ሊፈጠሩ ይችላሉ። ይሁንናም የኢትዮጵያ ተራማጆች ከዶግማቲዝም ከተጠበቁና መንገዳቸውን ሁሉ በሳይንሳዊ መንገድ በየደረጃው ከቀየሱ የሚጠበቅባቸውን አስተዋጽኦ ሊያበረክቱ ይችላሉ ብለን እንገምታለን።

ይሁንናም፣ ስለደርጉ ፀረዲሞክራሲያዊ ድርጊቶችስ ምን እናድርግ? የደርጉ ፀረዲሞክራሲያዊ አዋጆች፣ የደርጉ ተራማጆችን በእስር ቤት ከአድሃሪዎች እኩል ማጉርስ የመደራጀትና የማደራጀት ሥራችንን አያደናቅፍም ወይ? በርግጥ የደርጉ ፀረዲሞክራሲያዊ አስተሳሰቦችና ድርጊቶች የሕዝቡን ትግል ወደኋላ ይጎትቱታል። ደርጉ ምንም እንኳን አገርወዳድ ቢሆንም እስካሁን በወሰዳቸው አንዳንድ ስህተተኛ እርምጃዎች የሕዝቡን ትግል ወደኋላ እንደጎተተ ምንም አይጠረጠርም ። እነዚህንና የመሳሰሉትን የደርጉን ፀረዲሞክራሲያዊ ውሳኔዎችና እርምጃዎች ማጋለጥ አለብን። ከደርጉ ጋር በዚህ ደረጃ የፖለቲካ ትግል ማድረግ ይኖርብናል ማለት ነው።

እንደራጅ፣ እናደራጅ።
Scroll to Top