ሰሕድ ቁ. 23

የሰፊው ሕዝብ ድምፅ

ቁጥር 23፣    መጋቢት 3፣ 1967 

የፅሁፉ ፍሬ ሀሳብ

መኢሶን በዚህ የሰፊው ሕዝብ ድምፅ እትሙ፣ የካቲት 25 ቀን በጊዜያዊ ወታደራዊ መንግሥት የታወጀውን ታሪካዊ የመሬት አዋጅ ጠቅሶ፣ መኢሶን አዋጁ        ሥራ ላይ እንዲውል ከሚደግፉት የፖለቲካ ኃይሎች ጋር እንደሚተባበር አረጋግጧል። ለመሬት አዋጁ በከተሞችና በገጠር በሕዝብ የተደረጉት የድጋፍ ሰልፎችን አስታውሶ፤ አዋጁን የማስፈጸሙ ትግል ግን ገና እንደሆነ ያሳስባል። የመሬት አዋጁ በመታወጁ ብቻ የአርሶ አደሩ መሠረታዊ ጥያቄ ተመልሷል ማለት እንዳልሆነ ያስገነዝባል። በዚህም መሠረት፣ አዋጁን የሚደግፉ የሕዝብ ወገኖችን እንዲደራጁና እንዲታገሉ፤ እንዲሁም መብታቸውና ነጻነታቸው መከበር እንዳለበት በአጽንኦት ይገልጻል።ስለሆነም፣ “መሬት ላራሹ” የሚለው ጥሪ “ነጻነት ላራሹ” ከሚለው ጋር የግድ ተያያዥ እንደሆነ በትኩረት ያመለክታል

የሰፊው ሕዝብ ድምፅ

ለሰፊው ሕዝብ ሰራተኛ ገበሬ፣ ነጋዴ፣ ወታደር፣ ምሁር መብትና ጥቅም የሚታገል ጋዜጣ

የኢትዮጵያ ሰፊ ሕዝብ ይቅደም

 
ቁጥር 23                                                                       ቀን 3/7/67

 

ስጋ ሰጥተው ቢላዎ አይነሱም

የገጠር መሬት የሕዝብ ለማድረግ ጊዜያዊው ወታደራዊ መንግሥት የካቲት 25 ቀን ታሪካዊ የሆነውን አዋጅ አውጇል። በዚሁ እለት ߵየሰፊው ሕዝብ ድምጽߴ ባወጣው ልዩ እትሙ ላይ ይህንን አዋጅ መደገፉንና ከሥራም ላይ ለማዋል ከሚታገሉት ኃይሎች ጋር እንደሚተባበር፣ ከነርሱም ጋር ሆኖ አድሃሪዎችን ለመቋቋም ያለውን ቁርጥ ሃሳብ አስታውቋል። ሰፊው ሕዝብ ለዚህ ታሪካዊ አዋጅ ያለውን የማያወላውል ድጋፍ በማያወላውል አኳኋን መግለጡን በአዲስ አበባም ሆነ በየክፍላሃገሩ የተደረጉት ሰላማዊ ሰልፎች ቋሚ ምስክሮች ናቸው። በዚህ አዋጅ አላማ ተነሳስተው ለብዙ ዘመናት የአድሃሪዎችን አመጽ የተቋቋሙት ተማሪዎች፡ ተራማጆችና በጠቅላላውም የሰፊው ሕዝብ ወገኖች ይህ አዋጅ ከሥራ ላይ በትክክል እንዲውል ገና ብዙ መስዋእትነትና ትግል እንደሚጠብቃቸው ያውቃሉ፣ ለዚህም ይዘጋጃሉ።

በአሁኑ ጊዜ ይህ አዋጅ በመታወጁ ብቻ የመሳፍንቱ ሥርዓት አለቀ ደቀቀ፣ በኢትዮጵያ በዝባዥ መደብ የሚሉ ነገር ጠፋ፣ እያሉ ሕዝቡን ለማዘናጋት የሚሞክሩ እንዳሉ የታወቀ ነው። እነዚህ ክፍሎች አውቀውም ሆነ ሳያውቁ የሬቮሉሽኑ እንቅፋት መሆናቸውን መገንዘብ አለባቸው። ትግሉ ገና ነው። ሰፊውን ሕዝብ ትግልህ ተፈፀመ፡ እፎይ በል ከማለት ፋንታ የመጭውን ትግል መራራነት እያፍረጠረጡ ቢነግሩት የተሻለ የድል ዋስትና ይኖረዋል።

እንደዚህም ስለሆነ ለመጭው ትግል ለመሰናዳት አንዳንድ ነገሮች ማጤን ይኖርብናል። የዚህ አዋጅ መሰረታዊ ይዘቶች ምንድን ናቸው? ማንን ይጎዳሉ? ማንንስ ይጠቅማሉ? የሬቮሉሽኑ ጠላት ማነው? ወዳጁስ? እነዚህ ጥያቄዎች በጥሞና ተጠንተው መታወቅ አለባቸው። ከታወቁም በኋላ ጠላቶችን መበተን፣ መከፋፈል፣ ማዳከምና መደምሰስ ያስፈልጋል። ወዳጆችን ደግሞ መሰብሰብ፣ ማደራጀትና ወደ ድል መምራት ያስፈልጋል። ይህ ማንኛውም ከግቡ የደረሰ ሬቮሉሽን የተከተለው ትክክለኛ የትግል ዘዴ ነው። ይህንንም ባለመከተላቸውና ወዳጅን ከጠላት በሚገባ ለይተው አስፈላጊዎቹን እርምጃዎች መውሰድ ተስኖአቸው ብዙ ሬቮሉሽኖች በእንጭጭ እንደተቀጩ ታሪክ ደጋግሞ የመዘገበው ነው።

ዝርዝር ከመግባታችን በፊት አንድ አጠቃላይ ነገር ለመጥቀስ እንወዳለን። የዚህ ታሪካዊ አዋጅ መታወጅ የአድሃሪውን ወገን ብቻ ሳይሆን ከመሃል ሰፋሪውም መደብ ብዙዎቹን ወደ ፀረሬቮሉሽኑ ሰፈር ወርውሮአቸዋል። በተለይ ከንኡስ ከበርቴው መደብ አብዛኛው ክፍል ከመጠን በላይ ተደናግጧል። ለጥቅሙ ዋስትና ሊሰጠው የሚችል የተደራጀ ኃይል ስለሌለው መጭው ጊዜ አስጨንቆታል። ተወናብዶም ወደ ፀረሬቮሉሽኑ ሰፈር እየተደባለቀ ነው ማለት ይቻላል። በሌላ በኩል ደግሞ የሬቮሉሽኑ ኃይሎች ሊሰበሰቡ የሚችሉበት ግልጽ የሆነ የትግል አላማ በማግኘታቸው ከመቸውም ይበልጥ ሊጠናከሩ የሚችሉበት ብሩህ የሆነ ሁኔታ አጋጥሟቸዋል ማለት ነው። ባጭሩ በዚህ አዋጅ ምክንያት የኢትዮጵያ መደቦች በእርግጥ ወገን እየለዩና እየተሰባሰቡ ናቸው። ለወሳኙ፡ለሞት ወይም ለሽረት የሚደረገው ታላቅ የመደብ ጦርነት ግልጥ በሆነ ሰንደቅ አላማ ስር በመሰለፍ ላይ ናቸው።

እንግዲህ የሬቮሉሽኑን ወዳጆችና ጠላቶች ለማወቅ የዚህን አዋጅ ይዘት ማጤን ያስፈልጋል። በመሰረቱ ይህ አዋጅ ለአፈር ገፊው ጥቅም ሲባል የተደነገገ አዋጅ ነው። ቀጥታና ዋና ተጠቃሚው ለዘመናት እየተበዘበዘ በኑሮ ጠርዝ ላይ ተንጠልጥሎ የቁም ስቅሉን ሲያይ የቆየው አብዛኛው አርሶበሌ ሕዝብ ነው። ሰፊው አርሶበሌ ሕዝብ ለኑሮው ይበቃዋል የሚባለውን መሬት በይዞታው ያገኛል። ጥሮ ግሮ ከሚያፈራው ምርት ደግሞ በተቀምጦ በሌው ክፍል የሚዛቀው ፍሬ ሊቀርለት ነው። ነገር ግን በዚህ አዋጅ ተጠቃሚው አርሶበሌው ብቻ አይደለም። የመሳፍንቱና የሌሎች አድሃሪ ኃይሎች ኃይል ጨርሶ ተሰብሮ ይህ አዋጅ ከሥራ ላይ ሲውል ከመሬት የሚገኘው ምርት ይጨምራል። ለከተሜው ወዝአደር የእህል መርከስ፡ የሥራ መስፋፋት፡ ዋስትና ያለው የደመወዝ እድገት /ከባላገር እየፈለሰ ደመወዝን ወደታች የሚጫነው የሥራአጥ ሰራዊት ስለሚቀንስ/ ይከተላል። በጠቅላላው የገበሬው ኑሮ መሻሻል ለኢንዱስትሪ፣ ለንግድ፣ ለትምህርት፣ ለጤና፣ ለመገናኛዎች መስፋፊያ ወዘተ. ይህ ነው የማይባል ሰፊ ሜዳ ይከፈታል። እፍኝ ከማይሞሉት መሳፍንት፣ መኳንንት፣ አቀባባይ ከበርቴዎች፣ ኤምፔርያሊስቶች፣ አድሃሪ ከበርቴዎችና ንኡስ ከበርቴዎች… በስተቀር ይህ ለውጥ በሚያስከትለው እድገት ድርሻውን የማያገኝ ዜጋ የለም። ስለዚህም ከኢትዮጵያ ሕዝብ 90 በመቶ የሚሆነው ለዚህ ሬቮሉሽን ይሰለፋል። እንደዚህም እንደሆነ የሬቮሉሽኑ አላማ ለሰፊው ሕዝብ ወገኖች በፈርጅ በፈርጅ ሊገለጥላቸውና የአድሃሪ አወናባጆች ፀረሬቮሉሽን ኘሮፖጋንዳ በቅጡ መመታት ይገባዋል።

የኢትዮጵያ ሬቮሉሽን ደጋፊዎች እንደዚህ የበዙ ቢሆኑም እፍኝ የማይሞሉ ጠላቶቹ ደግሞ ያላቸውን ኃይል መናቅ ከጉዳት ላይ ይጥላል። የሕዝቡን ትግል ማዘናጋትና ትጥቁንም ማስፈታት ይሆናልና።

እነዚህን ጠላቶች በሁለት ግርድፍ ክፍሎች ልንከፍላቸው እንችላለን። በአንድ በኩል ሬቮሉሽኑን ለማጥፋት እስከመጨረሻው የማይሰለቹና የማይተኙ አድሃሪ ኃይሎች አሉ። በሌላ በኩል ደግሞ በመደባዊ ጠባያቸው ወላዋይነት የሚያጠቃቸውና እነርሱንም በሚመለከተው በኩል ትክክለኛ ዋስትና የማይሰጠው የደርጉ ፖለቲካ አደናግሮአቸው ወደፀረሬቮሉሽኑ ሰፈር በመወርወር ያሉ ኃይሎች አሉ። እነዚህ ገና ሳይነኩ ߵነግ በኔߴ በማለት ብቻ የፈረጠጡ በተለይ የንኡስ ከበርቴው ወገኖች በአሁኑ የሬቮሉሽን ደረጃ በአጋዥነት ሊሰለፉ ስለሚችሉ በጥንቃቄ ሊያዙና ሊመለሱ ይገባል።

በምንም አይነት ሬቮሉሽኑን ለመደምሰስ የማይመለሱት ኃይሎች – መሳፍንቱ፣ መኳንንቱ፣ ጳጳሳትና ከፍተኛ የቤተክህነት አለቆችና ርዝራዦቻቸው፣ ኢምፔሪያሊስቶች፣ በደቡብ ኢትዮጵያ የሚገኙ ነፍጠኞች፣ በሰሜንም ሆነ በደቡብ ተወላጅ የሆኑት ከፍተኛ ባላባቶች፣ አቀባባይ ከበርቴዎች፣ በቅርቡ የተወረሰው ብሄራዊ ከበርቴና የመደብ ወንድሙ፣ የንኡስ ከበርቴው የቀኝ ክንፍ፣ ወዘተ. – ባአሁኑ ጊዜ እነዚህ ሁሉ ሬቮሉሽኑን ለማጥፋት ከምንም የሚመለሱ አይደሉም። በዚህ ሁሉ ላይ እነዚህን አድሃሪ ኃይሎች ሊያስተባብርና ሊያግዝ የሚችል የቀድሞ ሥርዓት የመንግሥት መኪና ገና በቅጡ አልተነካም።

እነዚህ አድሃሪዎች ለጊዜው የተደናገጡ ቢመስልም ነፍስ እንደዘራባቸው ተመልሰው ለማንሰራራት መሞከራቸው ሳይታለም የተፈታ ነው። ከሰፊው ሕዝብ የተሻለ የድርጅት ልምድ አላቸው፣ በውጭ ሀገርና በሃገር ውስጥ ያካበቱት ሀብት አላቸው። ተንሰራፍቶ የሚገኘው መሪ ርእዩተዓለም /አይዲዩሎጂ/ የነርሱ ነው። ኢምፔሪያሊስቶችም ትግላቸውን ለማገዝና ለማስተባበር ይሞክራሉ። ካሁኑ ኩታ መግጠም የጀመሩት እነመንገሻ ስዩም፣ እነ ነጋ ተገኝ፣ እነ ብርሃነመስቀል ደስታ፣ እነ መርእድ ብሩ፣ እነ ከበደ ብዙነሽ…. እንደሸረሪት በሀገሪቱ ላይ አድሃሪ ትብብራቸውን ማድራት ጀምረዋል። ከውጭ አልጋወራሹና የቀድሞው ቢሮክራሲ ርዝራዦች /አምባሳደሮች፡ ሚኒስትሮች ወዘተ./ በእንግሊዝ፣ በጀርመንና በተለይም ደግሞ በአሜሪካ ኢምፔሪያሊስቶች እየተረዱ ፀረሕዝብ አላማቸውን ለማስተባባር በመሞከር ላይ ናቸው። ገና ብዙዎች ከመንግሥቱ ቢሮክራሲና ምናልባትም ከደርጉ ጭምር ወጥተው ከነዚህ ጋር ይሰለፋሉ። በመጨረሻም የውጪዎቹንና የውስጦቹን አድሃሪዎች ኢምፔሪያሊዝም ያገናኛቸዋል፣ ያስተባብራቸዋል።

ይህንን የአድሃሪዎቹን ሽርጉድ እንደ ቀላል ነገር ማየት ወይም ደግሞ አድበስብሶ ለማለፍ መሞከር የሰጎንዋን ፍልስፍና ይሆናል። ከኛ በፊት የቀደሙንን ሬቮሉሽኖች ታሪክ መመርመርና ከነርሱም ትምህርት መቅሰም ያስፈልጋል። የፈረንሳይ ሬቮሉሽን ታሪክ ተሰድደው የወጡት መሳፍንት ተመልሰው ሬቮሉሽኑን እርምጃ ለመግታት እንደቻሉ ያሳያል። የሩሲያ ሬቮሉሽን ታሪክ ከስልጣን የወረዱት አድሃሪዎች በኢምፔሪያሊስቶች እየተረዱ ተመልሰው ሦስት ዓመት ሙሉ ሰፊውን ሕዝብ አሰቃቂ የርስበርስ ጦርነት ውስጥ እንደጨመሩት ያሳያል። በቪየትናም የሄድን እንደሆነ ከ1954 የዲየንባየንፉ ድል በኋላ በአሜሪካን ኢምፔሪያሊስቶች በቪየትናም ሕዝብ ላይ የተጫነው የዲየም መንግሥት ሬቮሉሽኑ ለአርሶበሌው ያከፋፈለውን መሬት እንደገና ቀምቶ በመውሰድ ሃገሪቱን እስከዛሬ ድረስ ከባድ ጦርነትና ፈተና ላይ እንደጣላት እናያለን። ቺሊን ያየን እንደሆነ በሕዝብ ምርጫ ስልጣን የጨበጠው የአሌንዴ መንግሥት ሕዝቡን አስታጥቅ ሲሉት አሻፈረኝ በማለቱ ዛሬ በቺሊ ሕዝብ ላይ የወረደውን የፋሽስት አገዛዛ ፈተና ሁሉም የሚያውቀው ነው። በኛም አገር ቢሆን ካሁኑ በርግጥ ልናያቸው የምንችላቸው አንዳንድ ነገሮች አሉ። አንደኛ አድሃሪዎቹ በኢምፔሪያሊስቶች የበላይ ጠባቂነት እንደሚሰበሰቡና ብሄርና ሃይማኖት ሳይሉ ፀረሕዝብ አንድነት እንደሚመሰርቱ የታወቀ ነገር ነው። ሁለተኛ ደግሞ የሞት ወይም የሽረታቸው ትግል መሆኑን ስለሚያውቁት እስከመጨረሻው ድረስ እንደሚፍጨረጨሩ ሳይታለም የተፈታ ነው። ጠቅላላው ሠራዊት ዛሬ ከሕዝቡ ጐን የተሰለፈ ቢሆንም አድሃሪዎችና ኢምፔሪያሊስቶች በአጭር ጊዜ ውስጥ የራሳቸውን የፀረሬቮሉሽን ሠራዊት ሊፈጥሩ እንደሚችሉ አይጠረጠርም።

የሬቮሉሽናችን ድል ዋስትና የሚያገኘው፣ የዚህ የመራራ ትግል ውጤት የሚሰምረው በአንድ ዘዴ ብቻ ነው። የሕዝቡ ወገን ከአድሃሪዎቹ ወገን ይበልጥ ስልትና ቆራጥነት ባለው ዘዴ ከነርሱ በልጦ ሲደራጅና ሲታጠቅ ብቻ ነው። ሌላ ምንም መፍትሄ የለም። ለዚህ ደግሞ ሰፊው ሕዝብ የገዛ ነፃነት ትግሉን በሚመለከቱት ጊዜያዊና አንገብጋቢ ጥያቄዎች ላይ መወያየት፣ ሃሳቡን መግለጽ፣ መመካከር ስለሚያስፈልገው ዲሞክራሲያዊ መብቶቹ ያለአንዳች ገደብ ከሥራ ላይ መዋል አለባቸው።

መሬት ለአራሹ የሚለውን መሰረታዊ ዲሞክራሲያዊ አዋጅ አውጆ የመናገርን፣ የመፃፍን፣ የመሰብሰብን፣ የመደራጀትንና የመታጠቅን ዲሞክራሲያዊና ሰብአዊ መብቶች አፍኖ ለያዘ መንግሥት ߵስጋ ሰጥተው ቢላዎ አይነሱምߴ እንለዋለን።

ባጭሩ ደግመን ደጋግመን እንዳልነው በርግጥ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ትግል ወደፊት እንዲራመድ የሚፈልጉ ኃይሎች ተቀዳሚ ተግባራቸው የመደራጀትና የማደራጀት ሥራቸውን ማጣደፍ ነው እንላለን። ጠላቶቻችንም ኃይለኞች ስለሆኑ በዛሬው ወቅት ይህ አዋጅ በሥራ ላይ እንዲውል የሚታገሉትን ፀረፊውዳልና ፀረኢምፔሪያሊስት ክፍሎች በሙሉ ማደራጀትና ማስተጋገዝ ያስፈልጋል። እነዚህም ኃይሎች ጢሰኛው፡ አነስተኛውና ድሃው ገበሬ፣ ከመሬቱ የተነቀለውና ሥራአጥነት ያጠወለገው ባላገር፣ ወዝአደሩ፣ አሽከሩ፣ ገረዲቱ፣ ሴተኛ አዳሪዋ፣ ተራማጁ ምሁርና ወታደር፣ ተራማጁ ተማሪና አስተማሪ፣ ኢትዮጵያዊው ጭቁን ነጋዴ፣ በጠቅላላው የንኡስ በከበርቴው ተራማጅ ክንፍና የጭቁን ብሄሮች ተራማጅ ኃይሎች…ናቸው። የደርጉን ፈቃድ ሳይጠብቁ ተራማጆች ተደራጅተው እነዚህን መደቦችና የሕዝብ ክፍሎች ማደራጀት አለባቸው።

እንግዲህ እነዚህ ሁሉ በመሰረቱ ዛሬ ፀረፊውዳልና ፀረኢምፔሪያሊስት አላማ ላይ ሊተባበሩ ይችላሉ። ከዚህ አልፎ በሚመጣው አላማ ግን ሁሉም በአንድነት ሊሰለፉ እንደማይችሉ ግልጽ ነው። ስለዚህ ዛሬ ከፊታቸው በተደቀነው የጋራ ጠላት ላይ፡ ሁሉም በሚስማሙበት ፀረፊውዳልና ፀረኢምፔሪያሊስት ትግል ላይ ለመተባበር እንዲችሉ ሁሉም በመሰላቸውና በሚያመቻቸው በዲሞክራሲያዊ ዘዴ ተደራጅተው በአንድ የጋራ ሬቮሉሽናዊ ግንባር መተሳሰር አለባቸው።

እንደዚህ ከየመደቡ ለተውጣጡና በዘላቂ አላማቸው ለተለያዩ ውስብስብ ኃይሎች ሁሉ ከላይ ሆኜ አንድ ߵተራማጅ ድርጅትߴ እወረውራለሁ የሚለውን የደርጉን ቢሮክራሲያዊ መፍትሄ ሰፊው ሕዝብ የሚቃወመው እዚህ ላይ ነው። ነገር ግን እንደዚህ አይነቱ፡ ማን የት ድረስ እንደሚራመድ ሳይጣራ ሁሉንም በስመ ተራማጅ አንድ ላይ አምቄና አስተፋፍጌ እታገላለሁ የሚል አቋም ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል።

ደርጉ፡ ሰፊው ሕዝብ በመሰለው እንዳይደራጅ ዲሞክራሲያዊ መብቶቹን አፍኖ ይዞ አንድ ‘ተራማጅ ድርጅትߴ አቆማለሁ ሲል በእውነቱ ምን ለማለት እንደታሰበ ለማወቅ ያስቸግራል። ነገር ግን በየትም ብንሄድ ይህ ድርጅት የግድ ከሁለቱ ነገሮች አንድ መሆን አለበት ወይ ሕዝባዊ ሬቮሉሽናዊ ግንባር ነው። ወይም ደግሞ የአንድ የተወሰነ መደብ ፓርቲ ነው።

በሰፊው ሕዝብ ክልል የሚጠቃለሉትን ተራማጅ መደቦችና የህብረተሰብ ክፍሎች ጥቅም ለመጠበቅ የቆመ ሕዝባዊ ሬቮሉሽናዊ ግንባር ነው እንበል። ግንባር ሲባል መቸም የድርጅቶች ድርጅት ማለት ነው። ፀረፊውዳልና ፀረኢምፔሪያሊስት በሆነው በዚህ ሬቮሉሽናችን በሠራተኛው መደብ ፓርቲ የሚመራ ሕዝባዊ ግንባር እንደሚያስፈልገን ተደጋግሞ የተጠቀሰ ጉዳይ ነው፣ አንመለስበትም። አንድ ግንባር እንግዲህ ሊጠነክር የሚችለው ከውስጡ ያሉት አባል ፓርቲዎችና ሌሎች የሰፊው ሕዝብ ድርጅቶች ጠንክረው ሲገኙ መሆኑን ለመረዳት ጠንቋይ መቀለብ የሚያስፈልግ አይመስለንም። እንግዲህ ይህ የተራማጅ ድርጅት ግንባር ነው ከተባልን መሪው የሠራተኛው መደብ ፓርቲ የታለ? በውስጡስ የሚሳተፉት የድሉ ዋስትና የሚሆኑን የጠነከሩ ተራማጅ ፓርቲዎችና ሕዝባዊ ድርጅቶች የት አሉ? ብለን እንጠይቃለን። አሁንም ቢሆን ዲሞክራሲያዊና ሰብአዊ መብቶቹ ተረግጠው የተያዙበት ሰፊው የኢትዮጵያ ሕዝብ ገና እነዚህን የሕዝባዊ ግንባር አውታሮች አልመሰረተም። የመደራጀት መብቱ ያለአንዳች ገደብ ታውቆለት ሳይደራጅም ስለግንባር ማውራት ከብት ባልዋለበት ኩበት ለቀማ ይሆናል።

የሰፊው ሕዝብ ሰብአዊ መብቶች ሳይረጋገጡና ዲሞክራሲ ከሥራ ላይ ሳይውል ይህ የታሰበው የደርጉ ቢሮክራሲያዊ ድርጅት ፓርቲ ነው ቢባልም ፈጽሞ የሚያወጣ አይመስለንም። ፓርቲ ሲባል በየትም አገር፡ በማንኛውም ጊዜ ቢሆን ለአንድ መደብ ዘላቂ ጥቅም የመንግሥት ስልጣን ለመያዝ የሚታገል የዚያ መደብ ግንባር ቀደም ድርጅት ነው። ስለሆነም የራሱ መደብ ርእዩተዓለም፡ የራሱ የትግል ስልት፡ የራሱ የቅርብ ጊዜና የሩቅ ጊዜ አላማ፡ የራሱ የመደብ ግብ አሉት። እርግጥ አልፎ አልፎ፡ በተወሰኑና ዘላቂ ግቡን በማያፋልሱ አላማዎች ላይ ከሌሎች መደቦች ፓርቲዎችና ድርጅቶች ጋር አብሮ መሰለፍ ይቻላል። ነገር ግን በምንም አይነት ይህ ትብብር የመደብ ጠባዩንም ሆነ መደባዊ ግቡን አያስተውም።

እንግዲህ ይህ የደርጉ ቢሮክራሲያዊ ድርጅት ፓርቲ ነው ከተባለ የማን መደብ ፓርቲ ነው የሚለው ጥያቄ መመለስ ይኖርበታል። ይህንንም ጥያቄ ለመመለስ ߵየወረት ውሻ ስሟ ወለተጴጥሮስߴ እንዲሉ በመጠሪያ ስሙ በምንም አይነት ማወናበድ አያስፈልግም።(በነገራችን ላይ፡ ደርጉ ለፓርቲው የመረጠውን ስም ቢለውጠው ይሻላል? በዓለም ታሪክ ውስጥ አስፈሪና አሰቃቂ የሆኑትን ድርጊቶች የሚያስታውስ ስም ነውና።) ከዚህ አልፎ አንደኛ ይህ ፓርቲ ጠቅላላውን ተራማጅ መደቦችንና ህብረተሰባዊ ክፍሎችን ሊወክል እንደማይችል፣ ሁለተኛ ደግሞ፡ በርግጥ የየትኛው መደብ ወኪል እንደሆነ ማየትና ማሳየት ያስፈልጋል።

በመጀመሪያ ደረጃ ሁሉን ተራማጅ መደቦች አቀፍ የሆነ ፓርቲ እናቋቁማለን ማለት ራሱ ፀረሳይንስ የሆነ፡ የትግሉን ጥራት የሚያደፈርስ፡ በመደቦች መካከል የተጣራና ወግ የያዘ ትግልን የሚያፍን ፀረ ሬቮልሽናዊ አቋም ስለሆነ እውነተኛ ተራማጆች አይደግፉትም። እንደዚህም ስለሆነ አንድ ድርጅት ቁርጥ አድርጎ የአንድ ሬቮልሽናዊ መደብ ፓርቲ ነኝ ማለትን ትቶ ߵሁሉንም እወክላለሁߴ ማለት ሲቃጣው ያን ጊዜ ፀረ ሪቮልሽናዊ ሚናው ይጀምራል። በታሪክ ውሰጥ ተደጋግሞ የታየው እውነት ይህ ነው። ለመደባዊ ጥቅሜ፡ በመደባዊ ርእዩተአለሜ ተመርኩዤ ለመደባዊ አላማዬ እታገላለሁ ብሎ በማስታወቅ ግልጥልጥ አድርጎ ለመጀመሪያም ለመጨረሻም ጊዜ በታሪክ አምድ ላይ የታየውና በመታየት ላይ ያለው የሠራተኛው መደብ ፓርቲ ብቻ ነው። ሌላው ሁሉ አወናባጅ ነው። ከንኡስ ከበርቴው አንስተን  ወደቀኝ እስከከበርቴውና መሳፍንት ስንሄድ በዚህ ጉዳይ ላይ አንድ የሚያደርጋቸው ነገር ቢኖር ሲደራጁና ሲገዙ የመደብ ይዞታቸውን በመሸሸግ የኛ ድርጅት፡ የኛ ፓርቲ፡ የኛ መንግሥት ለመላው ሕዝብ የቆመ ነው እያሉ መለፈፋቸውና ማወናበድ መቻላቸው ነው።

ስለዚህ ይህ ቢሮክራሲያዊ ድርጅት ፓርቲ ነው ቢባልም የመላ ተራማጆች ፓርቲ ነኝ ቢል የሚሸሽገውን የመደብ ይዘት ፈልቅቆ ማውጣትና ማሳየት ያስፈልጋል። በዚህ መልክ ደግሞ ሰፊው ሕዝብ ዲሞክራሲያዊ መብቶቹን ገና ሳይጎናፀፍ የወዝአደሩ ፓርቲ ነኝ ቢልም ተቀባይነት አይኖረውም።ለምን?

እርግጥ ነው፣ ደርጉ ሲሻሊዝምን ለመገንባት እታገላለሁ ብሏል። በዚህ አቅጣጫ እስካሁን እንዳንድ ቁም ነገር ያዘሉ እርምጃዎች ተወስደዋል። ነገር ግን ደርጉ የሚያቋቁመው ድርጅት የሠራተኛ መደብ ፓርቲ ነው ከማለት በፊት ሁለት ነገሮችን ማጤን ያስፈልጋል።

አንደኛ፡ በሃገሪቱ የሚገኙ በሳይንሳዊ ሶሻሊዝም የሚያምኑ ኃይሎች ከአጠቃላይ ቴዎሪ አልፈው በጊዜው የሃገራችን አንገብጋቢ ጥያቄዎች ላይ እንዲወያዩ የተራ ዲሞክራሲ መብቶች እንኳን ተነፍገው እናያለን። ታዲያ በምን አይነት ዘዴ ነው የሲሻሊዝምን መሰረተሃሳቦች ተመርኩዘው፣ የሃገራችንን ተጨባጭ ሁኔታ መርምረው ታክቲካቸውን፡ ጊዜያዊ አጣዳፊ ተግባራቸውን፡ ዋና ጠላታቸውን፡ ጊዜያዊ ወዳጃቸውን ሳይለዩና ከሠራተኛው ሳይዋሃዱ በምን ፕሮግራም ላይ ነው ይህን ፓርቲ ሊያቋቁሙ የሚችሉት? ነው ወይስ ከላይ ታክቲኩ፡ ስትራተጅው፡ አላማው፡ ይህ ነው፡ በዚህ ስር ተሰለፉ ተብለው ሊታመቁ ነው?

ሁለተኛ ነገር ደግሞ አለ። ይህ የወዝአደሩ ፓርቲ በተአምር ተቋቋመም ብንል በየትኛው አገር ሪቮልሽን ነው ወዝአደሩ ለዲሞክራሲ ሳይታገል፡ በርሱ ፓርቲ ብቻ፡ በርሱ ድርጅት ብቻ፡ በሌሎች ሬቮሉሽናዊ ክፍሎች የተደራጀ ኃይል ሳይታገዝ ሪቮልሽኑን ከግቡ ያደረሰው? በየት አገር፡ በምንስ ጊዜ ነው የሠራተኛው መደብ ራሱ በመሰለው እንዳይደራጅ ታፍኖ፡ በሶሻሊዝም ስም ተራማጆች እንዳይደራጁ ታግደው ከላይ በተወረወረ ድርጅት ብቻ ድልን የተጎናፀፈው? አላየንም፣ አልሰማንም።

ባጭሩ ለማለት የምንፈልገው፡ የደርጉ ቢሮክራሲያዊ መፍትሄ የወዝአደሩም የሬቮልሽኑም መፍትሄ አይደለም። እንዲያውም ሬቮልሽኑን ሊያዳክምና ሊያሰናክል ይችላል። የሰፊው ሕዝብ ወገኖች በሙሉ ዲሞክራሲያዊ መብቶቻቸው ታውቀውላቸው በመሰላቸው መደራጀት አለባቸው። እነዚህም የጋራ የሆነውን ፀረፊውዳልና ፀረኢምፔሪያሊስት ትግላቸውን በአንድ በወዝአደሩ በሚመራ ሕዝባዊ ግንባር ስር ማስተባበር አለባቸው። በዚህ መልክ የጊዜውን ወዳጆች ሁሉ በመሰብሰብና የጊዜውን ዋና ጠላቶች በመነጠል፡ በተደራጀ ኃይል መምታትና መደምሰስ ያስፈልጋል።

ጥያቄአችንን ደግመን ደጋግመን እናሰማለን። የድላችን ዋስትና ይኸው ብቻ ነውና። ለሰፊው የኢትዮጵያ ሕዝብ የመሰብሰብ ነፃነቱ ይታወቅለት። የጋዜጦች ነፃነት ይታወጅ። የመደራጀት መብቱ ተረግጦ አይያዝ። መሰረታዊና ሰብአዊ መብቶች አይታፈኑ። እነዚህን ዲሞክራሲያዊ የሕዝብ መብቶች ረግጦ ይዞ ደርጉ ለኢትዮጵያ ሰፊ ሕዝብ         ߵሶሻሊዝምߴ ይኸውልህ ቢለው መልሱ በጣም አጭር ነው። ጽድቁ ቀርቶብኝ በወጉ በኮነነኝ ይለዋል።

በዛሬው ወቅት ከዚህ ከመደራጀት ጥያቄ ጋር እጅግ የተያያዘ አንገብጋቢ ጥያቄ የሰፊው ሕዝብ የመታጠቅና ለማይቀረው የርስበርስ ጦርነት ተዘጋጅቶ የመገኘቱ ጉዳይ ነው። ይህ ዛሬ ߵመሬት ላራሹߴ ከሚለው መሪ ቃል እኩል የሰፊው የኢትዮጵያ ሕዝብ አጣዳፊ ጥያቄ ሆኗል። የሳምንቱ ሰልፈኛ ጉሮሮው እስኪነቃ የጮኸው ይህንኑ ነው። ߵአስታጥቀው መሳሪያውን፡ ገበሬውን!’  ߵአስታጥቀው መሳሪያውን፡ ወዝአደሩን!ߴ ብሎ ከዳር እስከዳር አስተጋብቷል።

ሰፊው ሕዝብ እንዲህ ስለጠየቀ አንዳንድ አወናባጆች ሰው ልታጫርሱ ነው እያሉ ማስተጋባት ጀምረዋል። ግን ዛሬ አድሃሪው ወገን ከእግር እስከራሱ የታጠቀና በመታጠቅ ላይ ያለ መሆኑን እናውቃለን። ማስታጠቅ ማለት ሕዝብ ማጫረስ ነው የሚሉት አወናባጆች አለማስታጠቅ ደግሞ ሕዝቡን ማስጨረስ መሆኑን መገንዘብ አለባቸው። ሰፊው ሕዝብ ታጥቆና ተደራጅቶ በሙሉ ንቃት ራሱን መጠበቅና መብቱን ማስከበር ካልቻለ የአድሃርያን መጫወቻ እነደሚሆን ጥርጥር የለውም።

በየትም አገር ታሪክ ቢሆን ገዢ መደቦች በገዛ ፈቃዳቸው፡ ሳይዋጉ፡ ከሞቀ ስፍራቸው ወርደው አያውቁም። የርስበርሱ ጦርነት ተወግዶ ለውጡ በሰላም ቢከናወን ሰፊው ሕዝብ የሚጠላ አይደለም፡ ነገር ግን በዚህ ተአምር ተማምኖ በአሁኑ ጊዜ የመደራጀቱንና የመታጠቁን ተግባር ችላ ሊለው አይችልም። ሰላምን ከፈለግህ ለጦርነት ተዘጋጅ ይላል አስተዋዩ አነጋገር። ስለዚህ አድሃሪዎችን ገና በቅጡ ነፍስ ሳይዘራባቸውና ሳይተባበሩ ሰፊው ሕዝብ በተሻለ ተደራጅቶና ታጥቆ ከጠበቃቸው ሰላምንና ነፃነትን መጎናፀፍ ይቻላል። አለበለዚያ ይህ አዋጅ ከታወጀ በኋላ በልዩ ልዩ ፀረዲሞክራሲያዊ ዘዴዎች ሰፊው ሕዝብ እንዳይደራጅና እንዳይታጠቅ ከታገደ በታሪክ ፊት አስጠያቂ ወንጀል ተፈፀመ ማለት ነው።

እስካሁን ሰፊው ሕዝብ ዲሞክራሲያዊና ሰብአዊ መብቶቹን ተነፍጎ በመቆየቱ ብዙ ወርቃማ ጊዜ አልፏል። አሁንም በየሰአቱና በየደቂቃው አድሃሪዎቹ ነፍስ ሲዘራባቸው እየታየ የሰፊው ሕዝብ መብቶች ጉዳይ እንደቀላል ነገር ተወሰዶ ወርቃማው ጊዜ በመባከን ላይ ነው። በመደራጀትና በትጥቅ ጉዳይ ላይ ሰፊው ሕዝብና አድሃሪዎቹ እሽቅድድም ይዘዋል። ስለዚህም ዲሞክራሲያዊ መብቶችን ባስቸኳይ አለማወጅ አድሃሪዎችን የሚያስቀድም /ለአድሃሪዎች የሚመች/ አደገኛ አዝማሚያ መሆኑ መታወቅ አለበት።

የሆነ ሆኖ በዚህ አጣዳፊና ታሪካዊ ጊዜ ለኢትዮጵያ ሰፊ ሕዝብ እንደሕይወት እስትንፋሱ የሚያስፈልገው የዲሞክራሲ መብቶችና የመደራጀት ጉዳይ እንደቀላል ነገር የሚታይ አይደለም። እድሉንም በግድ በደርጉ ውስጥ ተራማጅና አድሃሪው ወገን ከሚያደርጉት ትግል ጋር ማያያዝ የለበትም። እርግጥ በደርጉ ውስጥ የሰፊው ሕዝብና የተራማጅ ወታደር ወገን ነን የሚሉት ኃይሎች ቢያይሉና እነዚህ ሕዝባዊ መብቶች ቶሎ ቢታወጁ የሰፊው ሕዝብ ትግል በጣም ሊፋጠንና ሊገሰግስ ይችላል። ነገር ግን ይህ የሞት ወይም የሽረት ትግል ነውና የኢትዮጵያ ተራማጆች የተቸገሩትን ተቸግረው ራሳቸውን ማደራጀት ይገባቸዋል። ይህን ተግባር ከመቸውም ይበልጥ ሊገፉበት ይገባል። ለዚህ ለታጠቁበት አላማ ከዚህም በፊት የማንንም ፈቃድ ጠይቀው አያውቁምና አሁንም ߵፈቃድ እስኪሰጣቸውߴ ቁጭ ብለው መጠበቅ የለባቸውም። አይጠብቁምም።

ከእንግዲህ እንደሆነ ሰፊው የኢትዮጵያ ሕዝብ ወደነፃነቱ የሚያደርገውን ጉዞ ከፀሃይ በታች ሊቋቋመው የሚችል ምንም አይነት ኃይል የለም። እስከዛሬ በሕዝቡ ጎን ተሰልፈው ለመማርና ለማስተማር፣ ለማደራጀትና ለትግሉ አቅጣጫ ለመስጠት በታላቅ መስዋአትነት ሲታገሉ የቆዩት ተራማጆች ዛሬ ከመቸውም ጊዜ ይበልጥ ለአንድነታቸው መጣር ይኖርባቸዋል። ይህ የመሬት አዋጅ ሰፊውን ሕዝብ ለማደርጀት ይህ ነው የማይባል አዲስና ታሪካዊ አጋጣሚ ከፍቶላቸዋል። በዚህም አጋጣሚ ታሪክ በትከሻቸው ላይ የሚጥለውን አደራ አንድነታቸውን አጠንክረው ሊቀበሉት ይገባል። ስለዚህ በአሁኑ ወቅት የሰራዊቱ ተራማጅ ክንፍና በጠቅላላው የኢትዮጵያ ተራማጆች አንድነታቸውን ከብረት አጠንክረው፡ ለሰፊው ሕዝብ እንደሕይወት እስትፋስ የሚያስፈልጉት ዲሞክራሲያዊ መብቶች እንዲረጋገጡ በግንባር ቀደምነት መታገል አለባቸው።

ዲሞክራሲያዊ መብቶች ለሰፊው ሕዝብ!
 እንዘጋጅ!! እናደራጅ!
ለማይቀረው የርስበርስ ጦርነት!
Scroll to Top