ሰሕድ ቁ. 24

የሰፊው ሕዝብ ድምፅ

ቁጥር 24፣    መጋቢት 20፣ 1967 

የፅሁፉ ፍሬ ሀሳብ

መኢሶን በዚህ የሰፊው ሕዝብ ድምፅ እትሙ፣ በየዘመኑና በየአገሩ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ሥርዓት መለዋወጡ፤ በመደቦች መካከል በነበረው ትግሎችና በነዚህም ትግሎች አንቀሳቃሽነት የኅብረተሰብ ለውጥና እድገት እንደታየ ይገልጻል።ይሁንና፣ በመጋቢት 7፣ 1967 ዓ.ም. ጊዜያዊ ወታደራዊ ደርግ ‘አድሃሪውና ተራማጁ ማነው?’ በሚል ያቀረበው ትንታኔ ትምህርታዊ አይሉት ማብራሪያ ያልሆነ እጅግ ውሱን አቀራረብ እንደሆነ ያረጋግጣል። ሆኖም፣ በኢትዮጵያ በሚካሄደው አብዮታዊ ለውጥ ውስጥ ተራማጁን ወገንና አድሃሪውን በሚገባ ለይቶ፤ ሳያዘበራርቁ ግልጽ ትንታኔ ማድረግ የጊዜው የማይታለፍ ጉዳይ እንደሆነ ይገልጻል።

የሰፊው ሕዝብ ድምፅ

ለሰፊው ሕዝብ ሰራተኛ ገበሬ፣ ነጋዴ፣ ወታደር፣ ምሁር መብትና ጥቅም የሚታገል ጋዜጣ

የኢትዮጵያ ሰፊ ሕዝብ ይቅደም

 
ቁጥር 24                                                                      ቀን 20/7/67

 

አድሃሪ ማነው? ተራማጅስ?

ߵእስከዛሬ ድረስ ያለው ታሪክ የመደቦች ትግል ታሪክ ነውߴ ይላሉ የሶሻሊዝም አዛውንቶች ማርክስና ኤንግልስ። እውነትም ከዝቅተኛው የጋርዮሽ ዘመን ወዲህ የሰው ልጅ ታሪክ ብንመረምረው በየትም አገር በማንኛውም ጊዜ አራማጅ ሞተሩ በህብረተሰቡ ውስጥ በሚገኙት መደቦች መካከል የሚደረገው ትግል ነው። ባርያ ፈንጋይ መደብ ከባርያ መደብ፡ የባለርስት መደብ ከጢሰኛ፡ ከበርቴው ከወዝአደር፡ ባጭሩ በዝባዥ ከተበዝባዥ ጋር ሲታገሉ ታሪክን ወደፊት እየገፉ አሁን ካለንበት ወቅት አድርሰውታል። በዚህ በማያቋርጥ ትግል የታሪክን የወደፊት እርምጃ ለመግታት (ዞሮ ዞሮ ላይሳካላቸው) የሚፍጨረጨሩት አድሃሪ መደቦች ናቸው። ከታሪክ ጋር እየተጋገዙ ለእርምጃና ለሰው ልጅ ደህንነት የሚታገሉት ደግሞ ተራማጅ መደቦች ናቸው።

እርምጃን የሚፈልጉና ለዚህም የሚታገሉትን መደቦች ለመምራት በታሪክ ፊት ኃላፊነት የወሰዱ ግንባር ቀደሞች የሰፊውን ሕዝብ ትግል በዚሁ በመደቦች ትግል አንፃር መመልከት አለባቸው። ለዚህም በጠቅላላው የጊዜውን የዓለም ሁኔታና በተለይ ደግሞ በሚገኙበት ህብረተሰብ ውስጥ ያለውን የመደቦች አሰላለፍ በጥንቃቄ ማጥናት ተቀዳሚ ተግባራቸው ነው።ይህንንም የሚያደርጉበት ዋናው ምክንያት ማንኛውም መደብ የሬቮሉሽኑ ተፃራሪና አድሃሪ መደብ እንደሆነ፡ የትኛው መደብ ደግሞ የቮሉሽኑ  ደጋፊና ተራማጅ መደብ እነደሆነ ተገንዝበው ወዳጅን ከጠላት ለመለየት እንዲችሉ ነው። ባለፈው ߵየሰፊው ሕዝብ ድምጽߴ እትማችን እንዳመለከትነው በዚህ መልክ ወዳጅና ጠላትን የለየው ቮሉሽን ደጋፊዎቹን መሰብሰብ ማደራጀትና ለትግሉ ማጠናከር፡ ጠላቶቹን ደግሞ መከፋፈል መበተንና ማድከም ማንኛውም ከግቡ የደረሰ ቮሉሽን የተከተለው የትግል እቅድ ነው። የኛም ቮሉሽን ከዚህ የተለየ ጎዳና ሊከተል አይችልም።

በመጋቢት 7 ቀን 1967 ጊዜያዊው ወታደራዊ መንግሥት ߵአድሃሪ ማነው? ተራማጅስߴ በሚል አርእስት መግለጫ ማውጣቱ ይታወሳል። የኢትዮጵያ ሬቮሉሽን ወዳጅና ጠላት መደቦች በሚገባ ተለይተው ትግሉ ወደፊት ሊራመድ ነው ብለን ጓጉተን ነበር። ነገር ግን ተስፋችን ከንቱ ሆኖ ቀርቶአል። የቀረበው ትንተና ጊዜንና አካባቢን የሳተ ብቻ ሳይሆን የመደብ ትንተና ይዘትም ስለሌለው ለሰፊው ሕዝብ ምንም አይነት የረባ ትምህርት ሳይሰጥ ቀርቷል። የአንድን ቮሉሽን ወዳጅና ጠላት ለመለየት ተነስቶ አድሃሪ መደቦች እነማን እነደሆኑ፡ ተራማጅ መደቦችስ እነማ እንደሆኑ አላማውሳት ምን ይዞ ጉዞ ይሆናል። ይህም ትንተና ሳይንስን የተመረኮዘ ባለመሆኑ በሰው መንፈስ ውዥንብር ስለሚነዛ እንቅፋትነቱ ያመዝናል።

መግለጫው አንድ አድሃሪ ግለሰብ ውይም አንድ ተራመጅ ግለሰብ ምን ምን አይነት ጠባዮችና ዝንባሌዎች ሊኖራቸው እንደሚችል ከማስገንዘብ አያልፍም። አድሃሪ ማለት ርኩስ፣ አወናባጅ፣ ተንኮለኛ፣ ደካማ ፍጡር፣ ድንጉጥ፣ የነጋበት ያፈና ጅብ … ማለት ነው ይላል። ተራማጅንም እንደዚሁ ግለሰባዊ ዝንባሌዎችን በሚመለከቱ ቅጽሎች ለመግለጽ ይሞክራል። እርግጥ ነው፡ አድሃሪ መደቦች ከህብረተሰቡ ጥቅም የራሳቸውን ጥቅም የሚያስቀድሙ ስለሆኑ የታሪክን እርምጃ ለመቋቋም በሚያደርጉት ትግል የተጠቀሱት ዝንባሌዎች ሊኖሯቸው ይችላሉ፣ አሏቸውም። ተራማጆችም የተጠቀሱት የሕዝብ ፍቅር፣ የመስዋእትነት፣ የጀግንነት ዝንባሌ አላቸው። ግን ይህ የግለሰቦች ዝንባሌ፡ ከሚገኙበት ሁኔታ ጋር ሲነፃፀር በሁለተኛ ደረጃ የሚታይ ነው። ይህ በግልጽ መታወቅ አለበት። ላይ ላዩን ሲመለከቷቸው ሰው አክባሪ፣ እግዚአብሄርን ፈሪ፣ ደግና ርህሩህ የሚመስሉት የመንደር አዛውንት በመደብ ትግል አንፃር ሲመጡባቸው እልም ያሉ አድሃሪዎች ሊሆኑ ይችላሉ። በመንደሩ በተመሰከረላቸው ግለሰባዊ ቁም ነገረኛነት የተጭበረበረ ተበዝባዥ፡ የመደብ ትግልን ተቀዳሚነት ያልተገነዘበ ተበዝባዥ፡ በእነኝህ አድሃሪ አዛውንት ሊወናበድ ይችላል ማለት ነው።

በኛ ግምት የኢትዮጵያን ቮሉሽን ወዳጅና ጠላት ለመለየት ከግለሰባዊ ዝንባሌዎች አልፈን አድሃሪ መደብ ማን እንደሆነ፡ ተራማጅስ መደብ ማን እንደሆነ ማየትነና ማሳየት ያስፈልጋል። ይህም ሆኖ በደፈናው አድሃሪ መደብ ወይም ተራማጅ መደብ ብሎ መናገር ችግር ነው። የመደቦች አሰላለፍ በሚጠናበት ጊዜ ህብረተሰቡንና ታሪካዊ ወቅቱን ለይቶ ማመልከት ፈጽሞ ሊዘለል የማይቻል ኃላፊነት  ነው። ስለዚህ ቮሉሽናችንን ለማራመድ መጠየቅና መመለስ ያለብን ዛሬ በ1967 ኢትዮጵያ አድሃሪ መደብ ማነው፡ ተራማጅ መደብስ ማነው የሚለውን ጥያቄ ነው።

በዛሬይቱ ኢትዮጵያ ይህንን ጥያቄ ለመመለስ ከሁሉ በፊት አገሪቱ የምትገኝበትን የእድገት ደረጃ ለይቶ ማወቅ ያስፈልጋል። ኢትዮጵያ ዛሬም ቢሆን ገና ከፊውዳሊዝምና ከኢምፔሪያሊዝም የጭቆናና የብዝበዛ ቀንብር ያልተላቀቀች አገር ነች። በዚች ምድር ላይ በአሁኑ ወቅት ሊደረግ የሚችለው ቮሉሽን ፀረ ፊውዳልና ፀረ ኢምፔሪያሊስት ስለሆነ ብሄራዊ ዲሞክራሲያዊ አብዮት ወይም ደግሞ አዲሱ ዲሞክራሲያዊ አቢዮት ነው። በዚህም አቢዮት የቮሉሽኑ አላማ ፊውዳሊዝምንና ኢምፔሪያሊዝምን ከኢትዮጵያ ገጽ አጥፍቶ በነርሱ መቃብር ላይ አዲሲቱዋን ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ በመመስረት ለሶሻሊዝም ጥርጊያ ጎዳናውን መክፈት ይሆናል።

እንግዲህ በዚህ ፊውዳሊዝምና ኢምፔሪያሊዝም ባንድ በኩል ሰፊው የኢትዮጵያ ሕዝብና አጋዦቹ በሌላ በኩል የተሰለፉበት ትግል በዝርዝር መልኩ መታየት አለበት። ባለፈው ቁጥራችን እንዳመለከትነው የገጠርን መሬት የሕዝብ ለማድረግ የወጣው አዋጅ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን የመደቦች አሰላለፍ የተጣራ መልክ ይሰጠዋል። በአድሃሪ መደቦች በኩል መሳፍንት፣ መኳንንት፣ ታላላቅ ጳጳሳት፣ ታላላቅ ነፍጠኞች፣ የሰሜንም ሆነ የደቡብ ክፍል ተወላጅ የሆኑ ታላላቅ ባላባቶች፣ ኢምፔሪያሊስቶችና ቡችሎቻቸው፣ አቀባባይ ከበርቴዎች፣ ከፍተኛ የቢሮ ከበርቴው፣ የፖለቲካ ኃይሉ ኢምንት ቢሆንም በቅርቡ የተወረሰው ብሄራዊ ከበርቴ፣ ገና ከአሁኑ ለውጡ ርቆ የሄደበት የንኡስ ከበርቴው ቀኝ ክንፍና በጠቅላላው የነዚህ አድሃሪ መደቦች አጫፋሪዎችና ርዝራዦች ናቸው። እነዚህ ዛሬ የቮሉሽኑ ጠላቶች ናቸው። በሌላ በኩል ደግሞ በተራማጅ መደቦች በኩል ወዝአደሩ፣ ከመሬታቸው ላይ የተነቀሉና የባለመሬት ጭቆና ያቆረቆዛቸው ጢሰኞች፣ መለስተኛ ደሃ ገበሬዎች፣ ምሁሩ፣ ተማሪው፣ የወታደሩ ተራማጅ ክፍል፣ ትናንሹ ነጋዴና ዝቅተኛው የመንግሥት ሠራተኛ፣ ከጢሰኛው ባልተሻለ ኑሮ የሚማቅቁት ዝቅተኛ ቀሳውስት….እነዚህ ሁሉ ባሁኑ ወቅት የቮሉሽኑ ደጋፊዎች ናቸው።

በነዚህ ወዳጅና ጠላት መደቦችና የህብረተሰብ ክፍሎች መካከል የሚወላውሉና አንዴ ወደአንዱ አንዴ ደግሞ ወደሌላው እያዘነበሉ አንጨበጥ የሚሉ ኃይሎች አሉ። እነዚህ በመሰረቱ እድገታቸው በመሳፍንቱ ሥርዓትና በኢምፔሪያሊዝም ታፍኖ የቆረቆዘባቸው፡ እስካሁንም የተደረገው ለውጥ በቀጥታ ያልመታቸው የብሄራዊ ከበርቴውና የንኡስ ከበርቴው ታዳጊ ክንፎች ናቸው። እድገታቸውን ስለሚያደናቅፏቸው ፀረ ፊውዳልና ፀረ ኢምፔሪያሊስት ትግል ውስጥ ለመሳተፍ ይፈልጋሉ። ግን ደግሞ በህብረተሰቡ ውስጥ መደባዊ አቀማመጣቸው በመጠኑም ቢሆን ከበዝባዥ ወገን ስለሚያሰልፋቸው የሰፊውን ሕዝብ ንቅናቄ በሙሉ ልብ ለመደገፍ ይፈራሉ። በማንኛውም ቮሉሽናዊ ትግል እንደታየው ቁርጠኛ የሆኑት የቮሉሽኑ ጠላቶችና ደጋፊዎች የሚያደርጉት ትንንቅ ጣምራ መልክ አለው። ከጎኑ ባንድ በኩል ራሳቸውን ለማደራጀትና ለወሳኙ ትግል ኃይላቸውን ለማጠናከር አጥብቀው ይሰራሉ። በተጨማሪ ደግሞ እነዚህን መሃል ሰፋሪ የሆኑ ኃይሎች በማረጋጋትና በማግባባት ለመሳብና በአጋዥነት ለማሰለፍ ይጥራሉ።

በበኩላችን የሬቮሉሽኑን ቁርጠኛ ደጋፊዎች የማደራጀቱም ጉዳይና ለዚህም ዛሬ የኢትዮጵያ ሰፊ ሕዝብ ዲሞክራሲያዊ መብቶቹ እንደሕይወት እስትፋስ የሚያስፈልጉት መሆኑን ባለፈው እትማችን አስገንዝበናል። አሁንም ቢሆን ለመደራጀት በሚደረገው ጥረት የሰፊው ሕዝብ ጠላቶች እንዳይቀድሙን በጣም መትጋት ያስፈልጋል።

እዚህ ላይ ለማተኮር የምንፈልገው ጉዳይ በሁለተኛ ደረጃ የሚታይ ቢሆንም መሃል ሰፋሪዎቹን ወደሬቮሉሽናችን የመሳቡን ጉዳይ ነው። ነገሩ ግልጽ ነው። አሁን እነደሚታየው ከሆነ የደርጉ ያልተጣራ ፖለቲካ የብሄራዊ ከበርቴውን ተራማጅ ክንፍና ንኡስ ከበርቴውን ወደ ፀረቮሉሽኑ ሰፈር ወርውሯቸዋል። በዚህ በኩል በሚደረገው ትግል አድሃሪ ኃይሎች ከመጠን በላይ በመፍጨርጨር ላይ ናቸው። ቮሉሽኑን በተቻለ መጠን ለማስጠላትና ተራማጆችን ለመነጠል፡ በዚህ መሃል ሰፋሪውን ሁሉ ወደነርሱው አደባልቀው ኃይላቸውን ለማዳበር ይጥራሉ። ለዚህ ምሳሌ የሚሆን በመላ ዓለም የሲአይኤ ቡችሎች የሰለጠኑበት በወሬና በፕሮፖጋንዳ ሰውን የማስከር ዘዴ አለ። በቅርቡ ‘የኢትዮጵያ ድል በኮሙኒስት ትግል’ የሚል በነዚህ ቡችሎች የተበተነው ፀረ ኮሚኒስትና ፀረተራማጅ ጽሁፍ አድሃሪዎቹ ይህንን በመላ ዓለም እጅ እጅ ብሎ የተጣለውን ጥንብ የትግል ዘዴ ወደ ሃገራችን ማስገባታቸውን ያሳያል። የኢትዮጵያ ሰፊው ሕዝብ በስንት መከራና ስቃይ ከዚህ ደረጃ ያደረሰውን የነፃነት ትግሉን በዚህ ርካሽ ፕሮፖጋንዳ ይፈታዋል ብሎ ማለም የአድሃሪዎችን ደደብነት የሚጠይቅ ቅዠት ነው። ጽሁፉ የሚመክረው ምንድነው? በአሁኑ ወቅት ከመሃል ሆነው የሚወላውሉትን ኃይሎች አስፈራርቶና አወናብዶ ወደአድሃሪው ሰፈር ለማፈናቀል ነው። እነደዚህም ስለሆነ ይህ ߵኮሚውኒስት ነኝߴ የሚለውን ፀረኮሙኒስትና የሲአይኤ ቡችሎች ጽሁፍ ߵጠላት ናቸው እናጥፋቸውߴ የሚላቸው ኃይሎች ቄሱን፣ ሼሁን፡ ከሁለት መቶ ብር በላይ ገቢ ያለውን ማናቸውንም ኢትዮጵያዊ፣ ከሩብ ጋሻ በላይ ያለውን ባለርስት፣ ምሁራኑን፣….. እየጠቀሰ ነው። እኛ ቁርጠኛ የቮሉሽናችን ጠላቶች የምንላቸውን መደቦች ፈጽሞ አያነሳቸውም።

የሆነ ሆኖ ደርጉ የቮሉሽናችንን ዋና ጠላቶች ለይቶ ለማሳየትና እነርሱንም ነጥሎ ለመምታት እንዲችል ጊዜያዊም ቢሆን ሊገኙ የሚችሉትን ደጋፊዎች ለመሰብሰብ የሚያደርገው ጥረት ፈጽሞ ጥራት የለውም። ስለዚህ አድሃሪዎችና ቡችሎቻቸው እነዚህን ኃይሎች በፀረ ቮሉሽናዊ ፕሮፖጋንዳቸው አስክረው እንዲስቧቸው ሰፊ የማወናበጃ መድረክ ሰጥቷቸዋል። ከላይ እንዳልነው የኢትዮጵያ ሕዝብ ትግል በዚህ ርካሽ ማወናበጃ ይፈታል የሚል እምነት የለንም። ነገር ግን በዚህ አቅጣጫ ግልጽ የሆነ ፖለቲካ ሲጠፋ ትግሉ ለጊዜውም ቢሆን ሊደናቀፍ ይቻላል።

በአሁኑ ጊዜ የኢትዮጵያ ቮሉሽን ወደፊት ሊራመድ የሚችለው ዋና ጠላቶቹን ነጥሎ በመምታት ደጋፊ ሊሆኑ የሚችሉትን ፀረ ፊውዳልና ፀረ ኢምፔሪያሊስት ኃይሎች በሙሉ ሰብስቦና አደራጅቶ ለትግል ያሰለፈ እንደሆነ ብቻ ነው። ከዚህ አልፎ ተርፎ የትግሉ መሪ የሆነው ወዝአደርና የትግሉ ምሰሶ ገበሬ ገና በሚገባ ባልተደራጁት ወቅት ከፊውዳሊዝምና ከኢምፔሪያሊዝም ሌላ ተጨማሪ ጠላት ማፍራት ቮሉሽናችንን አደጋ ላይ ይጥለዋል።

የቸገረው ዱቄት ከንፋስ ይጠጋል ይባላል። ወዳጅና ጠላትን በተጣራ ሁኔታ አልለየንም። በተወናበደ ፖለቲካ ወደአድሃሪው ሰፈር በመደባለቅ ላይ ያለውን ንኡስ ከበርቴና እንዲሁም ፀረ ፊውዳልና ፀረ ኢምፔሪያሊስት ትግል ውስጥ ሊሳተፍ የሚችለውን የብሄራዊ ከበርቴ ተራማጅ ክንፍ አርቀን እንደገና የቮሉሽናችን ደመኛ ከሆነው ከአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም ጋር የመታረቅ ፖለቲካ እንዳይሰፍን ያሰጋል። ወዳጅና ጠላት በጊዜ ካልተለየ ቮሉሽናችን ከትልቅ አደጋ ላይ ይወድቃል፣ ፀረ ኢምፔሪያሊስት መልኩን ይስታል። እንዲህ ከሆነ ደግሞ ለጊዜውም ቢሆን የአድሃሪዎችን እንደገና ማንሰራራት እንደሚያስከትል ማንም አይስተውም።

ዛሬ እነዚህን ወላዋይ ኃይሎች ማረጋጋት አለመሞከርና ዝም ብሎ በነሲአይኤ አስካሪ ፕሮፖጋንዳ እንዲወናበዱ መልቀቅ ሁለት የተያያዙ አደጋዎችን ያመጣል። የኢኮኖሚና የፖለቲካ ችግሮቻችን ከመጠን በላይ ሊባባሱ ይችላሉ።

በኢኮኖሚው በኩል የሄድን እነደሆነ ተራማጁ የብሄራዊ ከበርቴ ክንፍና ንኡስ ከበርቴው የኢትዮጵያ ሰፊ ሕዝብ እያፈራረሰ በመጣል ላይ ካለው ከፊውዳሉ ሥርዓት ጋር ሲነፃፀሩ ተራማጅ አምራቾች ናቸው። አገራቸውን ሸጠው ከኢምፔሪያሊስቶች ጋር ከተቆራኙት አቀባባይ ከበርቴዎች ጋር ሲነፃፀሩ እንደነሱ የሃገሪቱን ኃብት በትርፍ ስም እየዛቁ ወደውጭ በማጋዝ ኢኮኖሚውን የሚያቆረቁዙ ኃይሎች አይደሉም። ባጭሩ በአሁኑ ጊዜ ከደመኛ ጠላቶቻችን ከፊውዳሊዝምና ከኢምፔሪያሊዝም ጋር ሲተያዩ እነዚህ ኃይሎች አነሰም በዛም ለጊዜው ከተራማጁ ኃይሎች ጋር ሊደመሩ ይችላሉ። እንደዚህም ስለሆነ ቅደም ተከተልን በሳተ ፖለቲካ፡ ለምሳሌ ፈጽሞ አድሃሪ የሆኑትን የኢምፔሪያሊስት ወኪሎችና የኢኮኖሚያችንን አቆርቋዦች በጠቅላላው በቁጥጥር ስር ሳያደርጉ፡ ለጊዜውም ቢሆን ተራማጅ የሆኑትን ኃይሎች ለመምታት መሞከር የኢኮኖሚያችንን ከመጠን በላይ መዝረክረክ ያስከትላል። ይህ ደግሞ ሬቮሉሽናችንን ለጊዜው ከአቅሙ በላይ ከሆነ የፖለቲካ ችግር ውስጥ ይከተዋል።

የፖለቲካው ችግር የጠላቶች ከመጠን በላይ መብዛት የሚያመጣው ችግር ነው። ሰፊው የኢትዮጵያ ሕዝብ ገና በዲሞክራሲ መንገድ የመደራጀት፣ የመናገር፣ የመሰብሰብ መብቴ ይመለስልኝ፣ በገዛ ሃገሬ አንገብጋቢ ችግሮች ላይ ሳልፈራ ሳልገላመጥ ሃሳቤን የመስጠት ሰብአዊና ብሄራዊ መብቴ ይከበርልኝ እያለ እሪታውን በማሰማት ላይ ነው። ይህ ጥሪ ሳይመለስ የምታልፈው እያንዳንዷ ቀን ለአድሃሪዎቹ የወራት ፋታ ትሰጣቸዋለች። በእንዲህ አይነቱ አስጊ ሁኔታ ላይ እያለን ዛሬ ለኢትዮጵያ ሬቮሉሽን ሳይንሳዊ ትንተናና ወቅቱ ከሚፈቅድለት ጠላቶች በላይ፡ ከዋና ጠላቶቹ ከፊውዳሊዝምና ከኢምፔሪያሊዝም ሌላ ተጫማሪ ጠላቶች ማጋፈጥ የመጨረሻ ድላችንን ቀን ማራዘም ነው። ከላይ እንዳልነው በዚህ የፖለቲካ ውዥንብር ውስጥ ወዳጅ ከጠላት ተደበላልቆ ለኢምፔሪያሊስቶች በመዘጋት ላይ ያለው በር ተበርግዶ እንዳይከፈት ያሰጋል። ይህ ከሆነ፡ የኢትዮጵያ አብዮት ምን አይነት ውጥንቅጥ ውስጥ ሊገባ እንደሚችል በኢንዶኒዢያና በቺሊ የተፈፀመውን የኢምፔሪያሊስቶች ግፍ፡ እንዲሁም ሌሎች የኢምፔሪያሊስቶች ሴራ ለጊዜው ያከሸፋቸው ሕዝባዊ ትግሎች የወደቁበትን መከራ መመልከት ብቻ ይበቃል። ስለዚህ በታሪክ ፊት ኃላፊነታችንን ወስደን ካሁኑ ቁርጠኛ የሆኑት ወዳጆችና ጠላቶች እንደለዩ፣ መሃል ሰፋሪና ወላዋይ መደቦች ወደሬቮሉሽኑ ተደባልቀው እንዲረጋጉ፣ ለማንኛውም ደግሞ የነፃነቱ ትግል ባለቤትና ወሳኝ ኃይል የሆነው ሰፊው የኢትዮጵያ ሕዝብ ባስቸኳይ እንዲደራጅና እንዲታጠቅ ሳንሰለች እንወተውታለን። የኢትዮጵያ ተራማጆች በሙሉ አንድነታቸውን ከብረት አጠንክረው በተጣራ መስመር ወደፊት እንዲራመዱ ጥሪያችንን እናቀርባለን።

በየአቅጣጫው ዛሬ የተጣራ ፖለቲካ ይጠየቃል። በዛሬ ወቅት የሰፊው የኢትዮጵያ ሕዝብ ዋናና ደመኛ ጠላቶች ፊውዳሊዝምና ኢምፔሪያሊዝም በተለይም የአሜሪካ ኢምፔሪያሊዝም ናቸው።

የፊውዳሉን ሥርዓት በሚመለከተው በኩል ߵመሬት ላራሹߴ መታወጁ፣ የኢትዮጵያ አርሶአደር ሕዝብ በመደቡ ተሰልፎ እንዲያደራጅ መታገዙ ለሬቮሉሽናችን አንድ የድል ዋስትና ነው፣ የተጣራ ፖለቲካ ነው። ነገር ግን ይበልጥ መጣራት አለበት። አወናባጁ የሲአይኤ ቡችሎች ጽሁፍ እንደሚለው ߵመሬት ላራሹߴ ሲባል፡ የመሬት ይዘት ከሩብ ጋሻ አይበልጥ ሲባል፡ ከሩብ ጋሻ በላይ ያለው ሁሉ፣ ግማሽም ጋሻ፣ እንድም ጋሻ፣ ሁለትም ጋሻ የሚያርሰው ባለርስት ሁሉ የሬቮሉሽኑ ደመኛ ጠላት አይደለም። እንዲያውም ይህ ባለርስት በተወሰነለት ይዞታ ላይ እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ ቢያርስ አዲሱ ሬቮሉሽናዊ ፖለቲካ ለሰፊው የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚያተርፈው ፀጋ እሱንም ከቆረቆዘ ኑሮው ሊያላቅቀው እንደሚችል ማስረዳት ያስፈለጋል። በሃገራችን መንደሮች ትምህርት ቤቶች ቢከፈቱ፡በጨለማ ለኖረው ለርሱም ልጅ የእውቀት በር እንደሚከፈትለት መነገር አለበት። የጤና ጣቢያዎች ቢከፈቱ ለዘመናት ከተቆራኙት በሽታዎች እርሱም ሆነ ቤተሰቡ እንደሚፈውሱ እንዲያውቀው ማድረግ ያስፈልጋል። ባጭሩ ንግድ፣ ትምህርት፣ ጤና፣ ማመላለሻ፣… ቢስፋፋ ከዚህ ሁሉ ብልጽግና ይህም ጎስቋላ ባለርስት ሰርቶ ተገቢ ድርሻውን ሊያገኝ እንደሚችል ተገልጦለት ሬቮሉሽኑ ደጋፊ እንዲሆን ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል።

ፀረ ኢምፔሪያሊስት ትግላችንን በሚመለከተው በኩል የተጣራ ፖለቲካ ሲባል በቅድሚያ በማያወላውልና ምንም አይነት ወለም ዘለም በሌለበት ሁኔታ የሃገራችንን ኢኮኖሚ ከባእድ ቁጥጥር ስር ጨርሶ ማላቀቅ ያስፈልጋል። ባንኮችና ኢንሹራንስ ኩባንያዎች ብቻ ሳይሆኑ በባእዳን ቁጥጥር ስር ሆነው በትርፍ ስም የሚዝቁትን ኃብት ወደባህር ማዶ የሚያሻግሩትና የሃገሪቱን ኢኮኖሚ የሚያቆረቁዙት የኢምፔሪያሊስቶች የንግድ እርሻዎች፣ ፋብሪካዎችና ኢንዱስትሪዎች በሙሉ መወረስ አለባቸው። በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ የሃገሪቱ ኢኮኖሚ ለኢምፔሪያሊስቶችና ለነርሱ ገበያ ታዛዥ እንዳይሆን የውጭ ንግድ፣ የአስመጭና ላኪ ተግባር የመንግሥት ሞኖፖል መሆን ይገባዋል።

ፀረ ፊውዳልና ፀረ ኢምፔሪያሊስት የሆነው ትግላችን ተቀነባብሮ ለሃገሪቱ ጠቅላላ እድገት እንዲያተርፍ ኤኮኖሚያችን በአንድ ማአከላዊና አጠቃላይ ኘላን መመራት ይኖርበታል።

የፊውዳሊዝምንና የኢምፔሪያሊዝምን ጠንቅ ከሃገራችን መንግሎ ለመጣል እነዚህ እርምጃዎች መወሰድ አለባቸው። ይህ ስለሆነም በተለይ አሁን እንደሚደረገው በኢምፔሪያሊስቶች ላይ ወለም ዘለም የሚል ፖለቲካ መከተል ትግላችንን ፀረ ኢምፔሪያሊስትና የብሄራዊ ዲሞክራቲክ ሬቮሉሽን መልኩን ያስተዋል። ይህንንም አጥብቀው ሳይይዙ ወደሶሻሊዝም መንጠራራት የቆጡን አወርድ ብላ የብብቷን ጣለች እንደሚባለው ይሆናል።

የተጣራ ፖለቲካ የምንለው ቁርጠኛ ጠላቶችን ግልጥልጥ አድርጐ ለይቶ ለነርሱ መጥፊያ እርምጃዎች ከመውሰድ አይመለስም። ሬቮሎሽኑ ደጋፊ ሊሆኑ የሚችሉትን ኃይሎች በጥንቃቄ መያዝና ወደሬቮሉሽኑ መሳብ ይገባዋል። ታላቁ ሌኒን በዚህ በኩል የሚሰጠን ትምህርት በማያዳግም ሁኔታ ግልጥ ነው። በሱ ግምት ተራማጆች አጋዥን ለመሰብሰብ የአጋጣሚ ፍንጭ እንኳን መዝለል የለባቸውም። ይህንንም አጋዥ ጊዚያዊ ነው ብሎ መተው፣ወላዋይና ቁንጥንጥ ነው ብሎ መናቅ፣ አያስተማምንም ብሎ ችላ ማለት ሬቮሉሽናዊ የትግል ስልት አይደለም። በዋናው ጠላትና በሬቮሉሽኑ መካከል የሚወላውል ኃይል ሲሆን ጥቅሙን አሳይቶ ማረጋጋት የግንባር ቀደሙ ተግባር ነው። የማያስተማምን ከሆነ ራሱ በሬቮሉሽኑ እምነት ማጣቱ ነውና በተጣራ ፖለቲካ እምነት እንዲያድርበት ማድረግ የትግሉ አመራር ኃላፊነት ነው።

በኛ ግምት በነዚህ መሃል ሰፋሪና ወላዋይ ኃይሎች ላይ የሬቮሉሽኑ ፖለቲካ በሁለት አቅጣጫ ሊታይ ይችላል። በመጀመሪያ ደረጃ መቼስ እነዚህ ኃይሎች ከሕዝቡ ጐን ተሰልፈው ፊውዳሊዝምንና ኢምፔሪያሊዝምን ለመውጋት ፈቃደኞች እስከሆኑ ድረስ የሬቮሉሽኑ ወዳጆች መሆናቸው መታወቅ፣መታወጅ፣መለፈፍ አለበት። ሁለተኛ ደግሞ በአሁኑ ጊዜ በልዩ ልዩ የንግድ ሥራዎች፣ትናንሽ ኢንዱስትሪዎችና ፋብሪካዎች፣ በትራንስፖርት፣ በሆቴል…. የተሰማሩት የብሄራዊ ከበርቴው ተራማጅ ክፍሎችና ንኡስ ከበርቴዎች ሰርተው ተገቢ ጥቅማቸውን ሊያገኙ የሚችሉባቸው መስኮች ተጣርተው ሊብራሩ ይገባል። እንደዚህም ከተለየላቸው በኋላ ለነሲአይኤ የሽብር ዘመቻ እንዳይመቹ በየሙያቸው ተደራጅተው ዋስትና ያለው ኑሮ ሊኖሩ ይገባል። ይህም ሆኖ በነዚህ በሚሰማሩባቸው መስኮች የህብረተሰቡንም ጠቅላላ ጥቅም እንዳያዛንፉ መንግሥት ቁጥጥር ሊያደርግባቸው ይገባል።

በመጨረሻም ልንጠቅሰው የምንወደው ነገር አለ። የኢትዮጵያን ሬቮሉሽን እድል የሚወስነው ኃይል ሰፊው የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው። ይህም ማለት ከሁሉ አስቀድሞ ወዝአደሩና አርሶአደሩ ማለት ነው። እንደዚህም ስለሆነ የብሄራዊ ከበርቴው ተራማጅ ክንፍና ንኡስ ከበርቴው ባላቸው ኃይል ወደ ጠላቶቻችን ከሚደረቡ ይልቅ ወደሬቮሉሽኑ ይደባለቁ ብንልም እነዚህ ኃይሎች በምንም አይነት ከአጋዥነት ደረጃ ሊያልፉ አይችሉም፣ አይገባቸውምም። የኢትዮጵያ ሬቮሉሽን ዋናው አመራሩ በቁርጠኞቹ ሬቮሉሽናዊ መደቦች በተለይም በወዝአደሩ መያዝ ይኖርበታል። ለዚህም የኢትዮጵያ ወዝአደር መደብ ከሌሎች ሁሉ ይበልጥ ተደራጅቶና በትግሉም ውስጥ ግንባር ቀደምነቱን አስመስክሮ የአመራሩን ችቦ መያዝ ይኖርበታል።

ኢምፔሪያሊስቶችን በመሰለ የዓለም ሕዝቦች ቋሚና ዋና ጠላት ላይ የተድበሰበሰ አቋም ሲወስድ እየተመለከቱ፣ ትግላችን ብሄራዊ ዲሞክራሲያዊ መልኩን ስቶ ባልተጣራ ፖለቲካ ወዳጅ ከጠላት ሲደበላለቅ እያዩ፣ የኢትዮጵያ ተራማጆች በምንም አይነት ዝም አይሉም። ቋሚ ጠላት ተነጥሎ እንዲጠቃ፣ ጊዚያዊ ወዳጅ ከሬቮሉሽኑ እንዲደባለቅ፣ የሬቮሉሽኑ ባለቤት የሆነው ሰፊው ሕዝብ ተደራጅቶ በትግሉ ውስጥ ተገቢ ድርሻውን እንዲጨብጥ በሚደረገው ትግል ምንም አይነት አደርባይነት ሳያወናብዳቸው ወደፊት መራመድ አለባቸው።

የሲ.አይ. ኤ ሴራ

‘ጨለማ የለበሱ ሃሳዊ መሲሆች’ በሚል አርእስት ስር መጋቢት 15 ቀን ከጊዜያዊው ወታደራዊ መንግሥት አንድ ሰፊ መግለጫ ወጥቶ እንደነበር ይታወሳል። ይህ መግለጫ የሚመለከተው ‘የኢትዮጵያ ድል በኮሙኒስት ትግል’ በሚል ርእስ ስር ተጽፎ የተበተነውን አንድ ተንኮለኛ ጽሁፍ ነው። አንድ ሰው ሙሉ ጽሁፉን ሳያነብም እንኳን፡ የወታደራዊው መንግሥት መግለጫ ከሚጠቅሳቸው ጥቂት አረፍተነገሮች ብቻ ለመረዳት የምንችለው አንድ ነገር አለ። ይኸውም፡ የተባለው ጽሁፍ በፍፁም የእውነተኛ ኮሚኒስቶች ሥራ ሊሆን የማይችል መሆኑን ነው። ማንኛውም የኢትዮጵያ ኮሙኒስት፡ማንኛውም ተራማጅ፡ማንኛውም ቅን አሳቢ ሰዉ የዚህን አይነት ጽሁፍ አዘጋጅቶ እንደማይበትን ሳይታለም የተፈታ ነው። ሥራው በማያጠራጥር አኳኋን የአሜሪካኑ የስለላ ድርጅት የሲአይኤ ሥራ ነው።

የፅሁፉ ዋና አላማ የመንግሥቱ መግለጫ እንደሚለው ‘ወታደሩን ከወታደሩ፣ ሕዝቡን ከሕዝብ፡ እርስበርስ ለማጋጨት’ አይደለም። የጽሁፉ ዋናና የመጀመሪያ አላማ ኮሙኒዝምን እንደጭራቅ ማስፈራሪያ አድርጐ ለማቅረብና ደርጉን እራሱን ደግሞ በዚያው ኮሙኒስት ለማሰኘት ነው። ወታደራዊው መንግሥት ህብረተሰባዊነትን ካወጀ ወዲህ፡ በኢምፔሪያሊስት ጋዜጦች ኮሙኒስት ነው’ ተብሎ ሲወራበት ቆይቷል። አንዳንድ የምእራብ ጋዜጦችማ የደረጉን አባሎች ስም ጭምር እየጠቀሱ እገሌ ማኦይስት ነው ብለው ደጋግመው ጽፈዋል። አሁን ወታደራዊው የመንግሥት መግለጫ ያወጣበት ጽሁፍ በኛ ግምት የተሰነዘረው ኮሙኒዝምንና ደርጉን አንድ አድርጎ ሁለቱንም በማስጠላት የዚህኛውን የመገልበጫ ሁኔታ ለማዘጋጀት ነው። ይህም በብዙ አገሮች ተደጋግሞ የተሰራበት የታወቀ የሲአይኤ ዘዴ ነው።

በዚህ ሁኔታ፡ መንግሥቱ ያወጣው መግለጫ ፈጽሞ አላማውን ስቷል ማለት ነው። ነገሩ ከሁለት አንድ ነው። ወይ ወታደራዊው መንግሥት ይህ ጽሁፍ የያንኪዎች ሥራ መሆኑን ተገንዝቦታል፣ ግን ልጁን በስሙ አልጠራውም። ወይንም ደግሞ ነገሩ የመጣው በርግጥ ከኢትዮጵያ ኮሙኒስቶች ነው ብሎ አስቧል። ይህም ከሆነ መንግሥቱ በኢምፔሪያሊስቶች ሥራ ላይ የመንቃት ችሎታ የለውም ማለት ነው። ጊዚያዊው ወታደራዊ መንግሥት የተባለው ወረቀት የተንኮለኞችና የአድሃሪዎች፡ የሰላዩች ሴራ መሆኑን ካወቀ ለምን ልጁን በስሙ ጠርቶ በተጣራና በማያሻማ ቋንቋ እነዚህን አላጋለጣቸውም? ወደ ፊት መንግሥቱ በሌሎች ወረቀት በሚበትኑ ተራማጆች ላይ ለመውሰድ የሚያስበው እርምጃ ኑሮት ያንን ለመሸፈኛ ይህ ጥሩ አጋጣሚ መስሎት ይሆን? ማንም እንደሚያውቀው በአሁኑ ጊዜ ይህ ጋዜጣችንና ሌሎችም እንደዲሞክራሲያ፡ እንደአብዩት ያሉት ነፃና ተራማጅ ጋዜጦች የሚሰራጩት በሽሽግ ነው። እንዲህ ‘ጨለማ የለበሱ’ የሚለው እኛንም የሚያጠቃልል ከሆነ -መንግሥቱ ይህንን በመግለጫው አልለየምና- መግለጫው የታቀደው ወደፊት ሊፈፀሙ የሚችሉትን ፀረዲሞክራሲያዊ ድርጊቶች ለመሸፈን ነው ማለት ነው።

በሌላ በኩል፡ መንግሥቱ እውነተኛ ተራማጆች የዚህ አይነነቱን አድሃሪ ጽሁፍ ይበትናሉ ብሎ ከገመተ፣ አሁንም ለነዚህ ነፃ ጋጤጦቻችን አደጋ አለ ማለት ነው። ይህ ነው እንዳይባል ደግሞ በዚሁ መግለጫ ውስጥ መንግሥቱ ‘በመላው የኢትዮጵያ ተራማጆች የተደገፈው የመለዩ ለባሾች አላማ…ወዘተ.’ እያለ ጽፏል። ይሁን እንጂ የዚህ አይነት አድሃሪ ሴራ ከኢትዮጵያ ኮሙኒስቶችና ተራማጆች ብእር ጨርሶ ሊመጣ እንደማይችል እምነቱ መሆኑን በግልጽ ማስፈር ነበረበት።

የዚህ አይነቱ መግለጫ በሚወጣበት ጊዜ በፍፁም አሻሚ መሆን የለበትም። በአሁኑ ሰአት ለደርጉም፣ ለተራማጁም፣ ለሰፊው የኢትዮጵያ ሕዝብም ያለው ትልቅ አደጋ የኢምፔሪያሊዝም፣ የውስጥና የውጭ አድሃሪዎች ተንኮል ነው እንጂ አንዳች ከግራ በኩል የሚሰነዘር ‘የስልጣን ሽሚያ’ ወይንም ያንዳች ‘ቡድን እምነቱን በሕዝቡ ላይ’ የመጫን አደጋ አይደለም።

ወታደራዊው መንግሥት በተባለው የተንኮል ወረቀት ሳቢያ ከሰጠው መግለጫ ውስጥ አንድ ጥሩ ነጥብ ቢኖር የሚከተለው ነው፡-

‘የተማረውና የተደራጀው ወገን ለመሪነት በሰፊው ሕዝብ ይታጭ ዘንድ፣ አስቀድሞ ሰፊውን ሕዝብ ማስተማር ይኖርበታል። ሕዝብን ማስተማር ከሕዝብ መማርንም ይጠይቃል። … ወደሕዝቡ እንሂድ፣ እናስተምር፣ ከሕዝቡም እንማር።…..’

አባባሉ በጣም ጥሩ ነው። ግን ዲሞክራሲያዊ መብቶች በሌሉበት ሁኔታ፣ ጋዜጦቻችንን እንኳን ሳንገላመጥ ለማሰራጨት በማንችልበት ሁኔታ፡ እንዴት ሕዝቡን ለማስተማር ይቻላል? ሕዝቡስ በምን መንገድ ስሜቱንና ምኞቱን በመግለጽ ሊያስተምረን ይችላል? ማንም እንደሚያውቀው ፣ትምህርት የሚገኘው በነፃ ለመወያየትና ለመከራከር ሲቻል አይደለምን?

ዲሞክራሲያዊ መብቶች ከተፈቀዱ አድሃሪዎችም ይደራጃሉ፣ ያወናብዳሉ ይባላል። ታዲያ ጊዜያዊው ወታደራዊ መንግሥት ‘በቂ ኃይልና ድርጅት’ አለኝ ካለ፣ ዲሞክራቲክ የፖርቱጋል ወታደሮች ንቅናቄ እንደሚያደርገው ለምን በፀረ ሕዝብ መደቦችና ክፍሎች ላይ ተገቢ ቁጥጥር እያደረገ የሰፊው ሕዝብ ወገኖች በነፃ እንዲደራጁ አስፈላጊውን አካባቢ አይፈጥርም? እንደገና ለማስገንዘብ የምንፈልገው ኢምፔሪያሊዝምና ቡችሎች እስካሉ ድረስ የኢትዮጵያን ተራማጆች ለማስጨፍጨፍ፣ በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካና ባስገባቸው ቀዳዳ ሁሉ እየገቡ ሳቦታዥ ለማድረግና በመጨረሻም አሁን በስልጣን ላይ ያለውን ደርግ ገልብጠው በቦታው አንዳች አድሃሪ ደርግን ወይም ሌላ የራሳቸውን ምልምል መንግሥት ለማቆም፣ አለዚያም ይህንኑ ደርግ ራሱን ቀስ በቀስ እያሻሹ የጥቅማቸው ጠባቂና ታዛዥ አሽከር ለማድረግ መፍጨርጨራቸው ፈጽሞ የማይቀየር መሆኑን ነው። የወታደራዊው ደርግ ግራ ክንፍ በዚህ ነገር ላይ ካልነቃበት፣ እውነተኛ ጠላትንና እውነተኛ ወዳጅን ካልለየ፣ በነርሱ ወጥመድ ውስጥ ወድቆ የኢትዮጵያን ሕዝቦች ሬቮሉሽናዊ ትግል ወደመቀልበስ ሊጓዝ ይችላል። ዛሬ ተራማጆቻችን የሚጠብቃቸው አንደኛው ከፍተኛ አደጋ ይህ ነው።

የነመለስ ተክ መገደል

አድሃሪዎች በተረሸኑ ቁጥር ወታደራዊው መንግሥት አንዳንድ ተራማጆችንም አብሮ የመረሸንን ፖለቲካ እንደልማድ የወሰደው ይመስላል። እነዚያ የታወቁ አድሃሪዎች የዛሬ አራት ወር በተረሸኑበት ወቅት ተራማጆችም አብረው ተገድለው እንደ ነበር ይታወሳል። አሁንም ከኃይሉ ረጋሳና እነጓድ ጥላሁን ግዛውን አስገድሏል ከሚለው ከአሉላ በቀለ ጋር ሶስት ወጣት ተራማጆች አብረው ተረሽነዋል። እነዚህ ሦስት ወጣቶች እንደተነገረው በሞት የሚያስቀጣ ወንጀል ፈጽመው እንደሆን የመንግሥቱ መግለጫ አያሳይም። እነዚያን ቦምቦች ለማፈንዳታቸው ምንም የቀረበ ማስረጃ የለም። እንዲያውም ሁለቱ በዚያን ጊዜ አዲስ አበባ እንዳልነበሩ ይነገራል። ታዲያ የእነዚህ ወጣት ተራማጆች ንፁህ ደም የፈሰሰው ለምንድነው? ለፍርድ ሳይቀርቡ እንደቀረቡ አስመስሎ መነገሩስ ምን ጥቅም ሊያስገኝ ነው? ማንን ለማሞኘት ነው? መለስ ተክሌ፣ ግደይ ገብረዋህድና ረዘነ ኪዳኔ በተማሪው አካባቢ የታወቁ ተራማጆች ነበሩ። የእነዚህ ተራማጆች መገደል በቀላሉ የሚታለፍ ነገር አይደለም። የአንድ ንፁህ ተራማጅ መሞት የአድሃሪዎችን እጅ ያጠነክራል፣ የሰፊውን ሕዝብ ትግል በመጠኑም ቢሆን ወደኋላ ይጐትታል። ስለዚህ ፋሺስታዊ ድርጊት ነው።

የነርሱ መገደል አሁንም ቢሆን መንግሥቱ እውነተኛ ወዳጅንና ጠላትን እንዳለየ ያሳያል። ይህም መንግሥትን እራሱን፡ በተለይም የደርጉን የግራ ክንፍ ለብቻው የሚነጥለውና መጥፊያውንም የሚያስከትል ድርጊት ነው። በርግጥ እነዚህ ወጣቶች ጥፋተኛ ናቸው ከተባለ ደግሞ ዝርዝር ሁኔታቸውን ግልጥልጥ አድርጐ ለሰፊው ሕዝብ ማቅረብ ያስፈልጋል። ያለበለዚያ፣ መንግሥቱ ሺህ ጊዜ ደጋግሞ የሰፊው ሕዝብ ወገን ነኝ ቢልና ከሕዝብ የሚደበቅ ነገር የለኝም እያለ ቢለፍፍም ሰፊው ሕዝብም ሆነ ተራማጁ ክፍል ምንም አይነት እምነት ሊኖረው አይችልም። ውሎ አድሮም ከሰፊው ሕዝብና ከተራማጁ ወገን ይቆራረጣል፣ታሪክም ይፋረደዋል።

ወዳጆችና እውነተኛ ጠላቶች ይለዩ!
ዲሞክራሲያዊ መብቶች ለሰፊው ሕዝብ ወገኖች!
ሰፊው ሕዝብ ያለራሱ ድርጅት ምንም አያገኝም!
ፊውዳሊዝምና ኢምፔሪያሊዝም ይውደሙ!
ሰፊው ሕዝብ ያሸንፋል!
Scroll to Top