ሰሕድ ቁ. 26

የሰፊው ሕዝብ ድምፅ

ቁጥር 26፣    ግንቦት 24፣ 1967 

የፅሁፉ ፍሬ ሀሳብ

መኢሶን በዚህ የሰፊው ሕዝብ ድምፅ እትሙ፣ በወታደራዊው መንግሥትና በኢትዮጵያ ሕዝቦች መካክለ ያለው ቅራኔ በሁለተኛ ደረጃ የሚመደብ መሆኑን አስታውሶ፤ ደርጉ የመሬት አዋጁን በማወጁና አንዳንድ የግል ኢኮኖሚያዊ ተቋሞችን የሕዝብ በማድረጉ እንዲሁም በሕዝብ ጠላቶች በፊወዳሊዝምና በኢምፔሪያሊዝም ላይ በመዝመቱ፤ እነዚህ ልዩነቶች መጥበባቸውን ያሳያል። ሆኖም ግን፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ወታደራዊ መንግሥት በሕዝብና በተራማጆች ላይ የሚውስዳቸው የማሳደድና የእሥራት እርምጃዎች ቅራኔውን ወደ አንደኛ ደረጃ ከፍ የማለት አቅጣጫ እንደሚይዝ አስጊነቱን ይጠቁማል። የእዚህ ቅራኔ መባባስ ሕዝባዊ ትግሉን የሚያደናቅፍና የሚገታ መሆኑን በሰፊው ያትታል።

የሰፊው ሕዝብ ድምፅ

ለሰፊው ሕዝብ ሰራተኛ ገበሬ፣ ነጋዴ፣ ወታደር፣ ምሁር መብትና ጥቅም የሚታገል ጋዜጣ

የኢትዮጵያ ሰፊ ሕዝብ ይቅደም

 
ቁጥር 26                                                                      ቀን 24/9/67

 

የኢትዮጵያ ሰፊ ሕዝብ ያሸንፋል።

እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በወታደራዊው መንግሥትና በኢትዮጵያ ሕዝቦች መካከል የነበረው ቅራኔ የሁለተኛ ደረጃ ቅራኔ ነበር። ወታደራዊው መንግሥት ህብረተሰባዊነትን በማወጁ፣ የመሬትን ይዞታ በማስተካከሉ፣ አንዳንድ የኢኮኖሚ ድርጅቶችን የሕዝብ በማድተጉ፣ በፊውዳሊዝምና በኢምፔሪያሊዝም ላይ በመዝመቱ እነዚህ ደግሞ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ዋና ጠላቶች በመሆናቸው የመንግስቱና የሕዝቡ ትግል ከልዩነቱ ይልቅ አንድነቱ ያመዝን ነበር። ዛሬ ግን ባንድ በኩል በነዚህ ጥንድ ጠላቶች ላይ የሚደረገው ዘመቻ እየተበረዘ ሲሄድ በሌላ በኩል በሰፊው ሕዝብና ለርሱም በቆሙት ተራማጆች ላይ የሚደረገው ዘመቻ እያየለ ሄዶአል። ስለዚህም በሰፊው ሕዝብና በወታደራዊው መንግሥት መካከል የነበረው ልዩነት በፈጣን እርምጃ ወደ አንደኛ ደረጃ ቅራኔ በመለወጥ ላይ ነው።

በደርጉ ውስጥ ያሉ ተራማጆች ነቁበትም አልነቁበትም፡ ጠቅላላው የጊዜያዊው ወታደራዊ መንግሥት አሰራር ወደአድሃሪነት እያዘነበለ ለመሄዱ በፍፁም የማያጠራጥረ ምልክቶች አሉ።

1ኛ/ ባሁኑ ጊዜ የኢትዮጵያ ሪቮሉሽን፡ የሰፊው ሕዝብና የደርጉም ተራማጅ ክንፍ ዋና ጠላቶች የአሜሪካ ኢምፔሪያሊዝምና በርሱም አማካኝነት የሚቀነባበሩት የውስጥና የውጭ አድሃሪዎች መሆናቸው ለማንም ሰው ግልጽ በሆነበት ወቅት፡ በነዚህ ፀረሕዝብ ኃይሎች ላይ የማያወላውልና ቆራጥ እርምጃ በመውሰድ ፈንታ ወታደራዊው መንግሥት ተራማጆችን ማሳደድ ይዟል። ከንግድ ምክር ቤት ወረቀት አባዛችሁ ተብለው ከተያዙት ወደሃያ ከሚጠጉት ሰዎች ውስጥ ሶስቱ አሁንም በእስርቤት በመማቀቅ ላይ ናቸው። ከጭላሎ የእርሻ ልማት ድርጅት በርከት ያሉ ተራማጆች ተይዘው መታሰራቸው ይታወቃል። በተረፈም ለሕዝቡ ጥቅም መቆማቸው ፈጽሞ የማያጠራጥር አንዳንድ ዘማቾች፣ የወረዳ አስተዳዳሪዎች፣ የመሬት ይዞታ ወኪሎች ካሉበት ሥራ ተባርረዋል፣ ብዙም ታስረዋል። ወታደራዊው መንግሥት ከዚህ በፊት ያለአንዳች ምክንያት ያሰራቸውን ተራማጆች አልፈታም። እነዚህ ድርጊቶች ሁሉ መንግስቱ መላውን የኢትዮጵያን ተራማጆች አሳድዶ ለመያዝና ለማሰር መነሳቱን የሚያመለክቱ ናቸው ብለን እንገምታለን ።

2ኛ/ በጠቅላላው ዘማች ሲባል ቀድሞ በትምህርት ቤትም ሆነ ዛሬ በየገጠሩ ለሰፊው ሕዝብ የቆመ፣ ማንኛውንም መስዋእትነት ከመቀበል ያልተቆጠበና የማይቆጠብ፣ በሙሉ ልቡ ከጭቁኑ ሕዝብ ጐን እየተሰለፈ መሆኑ እየታወቀ፣ በዘማችና በባለርስቶች፣ እንዲሁም የባለርስትን ጥቅም ለመጠበቅ በቆሙ ፖሊሲዎችና አስተዳዳሪዎች መካከል ግጭት በተነሳ ቁጥር መንግስቱ የአድሃሪዎቹን ወገን ሲመርጥ ይታያል። ሰፊው ገበሬና ዘማቹ፣ እንደዚሁም አንዳንድ ተራማጅ አዝማቾችና ያገር አስተዳዳሪዎች ተባብረው የባለርስቱን መሳሪያ ሲቀሙትና በሕዝብ ላይ ፋሽስታዊ አመጽ እንዳይፈጽም ለፖሊስ ሲያስረክቡት ፖሊስ የባለርስቱን መሳሪያ እየመለሰ ይፈታዋል። ባንዳንድ ቦታዎችም ፖሊስና ባለባቶች ባንድ ወገን ሁነው ሰፊውን ገበሬ ፈጅተዋል። በዚህ አይነት ሁኔታ ወታደራዊው መንግሥት ከጨቋኙ ወገን ጋር ደጋግሞ ተሰልፏል። ባለርስቱ መሳሪያውን መቀማትና መታሰር ሲገባው ዘማቾች እንዲታሰሩ፣ ወይንም ከየጣቢያቸው እንዲባረሩ ተደርጓል። በርከት ያሉ ጣቢያዎች ተዘግተዋል።

3ኛ/ በየገጠሩ፡ በተለይም በሰሜን ኢትዮጵያ ያለውና በክፍለአገር አስተዳዳሪዎች ስብሰባ ላይ ጉዳዩ የተነሳው ‘ነጭ ለባሽ’ የተባለው ድርጅት የፊውዳሉ ሥርዓት የስልጣን ሰንሰለት መሆኑ እየታወቀ፡ ወታደራዊው መንግሥት ባንድ በኩል ገበሬው ለነዚህ ነጭ ለባሾች እንዲያርስ ለማድረግና በሌላ በኩል ደግሞ እነዚህ ነጭለባሾች በሌሉባቸው የደቡብ ክፍለሃገሮች እንዲያቋቁሙ ለማድረግ ሞክሯል። ይህም አዲስ አይነት ባለርስቶችን ለመፍጠር የታቀደ መሆኑ አይካድም። ከደረጉ በመጋቢት 8 ቀን በታዘዘው መሰረት በአድሃሪው በመሃረነ ምንዳ የአስተዳደር ሚኒስቴር ቋሚ ተጠሪ በመጋቢት 15 ለየወረዳዎች የተጻፈ አንድ ደብዳቤ(ዟሪ)  እንደሚያስረዳው የየካቲቱን የመሬት ይዞታ አዋጅ ለማክሸፍ ኮሚቴ እየተባለ የገበሬዎች ማህበሮችን ሥልጣን የሚቀማ አድሃሪ ድርጅት እንዲቋቋም ከመንግሥት ሥራ በጡረታ የወጡ ከበርቴዎችና ነጭለባሾች አሁንም ባለርስት ሁነው እንዲቀሩ ለማድረግ በደርጉና በቢሮክራሲው ውስጥ ተንሰራርተው የተቀመጡ አድሃሪዎች ትልቅ ጥረት እንደሚያደርጉ ያስረዳል። ይህ ዟሪ በቀጥታ የመሬት ይዞታ አዋጅን የሚያፈልስ ስለሆነ በየቦታው የሚገኙ ተራማጅ የመሬት ይዞታ ወኪሎችና አስተዳዳሪዎች ከስራ ላይ እንዳይውል አድርገውታል። ይሁንናም የተባለው ዟሪ በወጣ ሰሞን መላውን ገጠር ያዳረሰ ሲሆን እርሱን በመሰረዝ የወጣው ትእዛዝ ግን እስከዛሬ በብዙ ቦታዎች አልደረሰም። ይህም አድሃሪዎች ከላይ እስከታች በሚገባ በቢሮክራሲ ውስጥ የተደራጁና የኢትዮጵያን አብዮታዊ እንቅስቃሴ ለመደምሰስ በይፋ የሚፍጨረጨሩ መሆናቸውን ያሳያል። ባሁኑ ወቅት ከመሸፈትም ይልቅ ይህኛው መንገድ የሚያመቻቸው መሆኑን አውቀዋል። መንግሥት በነዚህ ላይ አንዳችም እርምጃ አልወሰደም።

4ኛ/ ባለፉት ሁለት ሶስት ወራት በየቦታው፡ በየመስሪያ ቤቱ በዲሞክራሲያዊ መንገድ ሳይሆን በፊውዳል ሥርዓት መሰረት፣ በትውውቅ፣ በምል፣፡ በሴራ ወዘተ. የተሾሙት ግለሰቦች ሕዝብ ያወገዛቸው አድሃሪዎች መሆናቸው እየታወቀ፡ ባሉበትም ቦታ ሳቦታዥ ለማድረግና እንቅስቃሴውን ለመቀልበስ ምንም ከማድረግ እንደማይቆጠቡ በተግባር እያሳዩ፡ እነዚህ ግለሰቦች በቦታቸው እንዲቆዩ ተደርጓል። ከነዚህ ሰዎች ጥቂቶቹን ለመጥቀስ ያህል፡- ያገር አስተዳደሩ መሀረነ ምንዳ፣ የእርሻ ሚኒስትሩ፣ የህዝባዊ ኑሮ እድገት ተፈራ ኃይለሥላሴ፣ የጐጃሙ አስተዳዳሪ፣ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር የአክሊሉ ቀኝ እጅ የነበረው አክሊሉ ሀብቴ የታወቁ አድሃሪዎች ናቸው።

5ኛ/ ወታደራዊው መንግሥት ተራማጆችን እየለቀመ ይሰር እንጂ እነደጃዝማች ብርሃነ መስቀል፣ መርእድና መስፍን ብሩ፣አሊ ሚራ፣ ስሜነህ ደስታ፣ በሀገረማርያምና በሻሸመኔ አካባቢ በሸፈቱት፣ በሸንኮራና በምንጃር አካባቢም ሸፍተው ባሉትና በገጠሩ በመጠናከር ላይ ባሉት የባላባቱ መደብ ርዝራዦች ላይ አንዳችም እርምጃ አልወሰደም። እነዚህንና ወደውጭ የወጡትን አድሃሪዎች ፀረሪቮሉሽናዊ እንቅስቃሴ በሚያስተባብረውና በደርጉም በራሱ ውስጥ ሰርጐ በገባው በአሜሪካ ኢምፔሪያሊዝም ላይ አንዳችም እርምጃ አልተወሰደም። የአሜሪካ ኢምፔሪያሊዝም ሃያ አመት ሙሉ ከስድስት ቢሊዩን ዶላር በላይ አውጥቶና ወደ ስድሳ አምስት ሺ የሚጠጉ የያንኪ ወታደሮች አስፈጅቶ በታላቅ ውርደት ከኢንዶቻይና በሕዝብ ትግል ተባርሮ ሲወጣ፡ የኢንዶቻይና ሕዝቦች ድል የአለም ጭቁን ሕዝቦች ሁሉ- የኢትዮጵያ ሕዝብም ጭምር- ድል መሆኑ እየታወቁ፡ ወታደራዊው መንግሥት ገና መንግስታቸውን አላወቀም። የኢትዮጵያ ሕዝብም የዚህን ድል ትልቅነትና ምሳሌነት እንዳያውቀው ተደርጓል። ይህ ሁሉ ወታደራዊው መንግሥት ባድሃሪ ኃይሎች ቁጥጥር ስር እየወደቀ በመሄድ ላይ መሆኑን ያሳያል።

6ኛ/ ወታደራዊው መንግሥት በያዘው አድሃሪ ጉዳና በመገፋት አሁን በመጨረሻ የኢትዮጵያን ሠራተኞች አንድነት ማህበር ዋና መስሪያ ቤት ዘግቷል። የመንግስቱ መግለጫ እንደሚለው ሁሉ በርግጥ ይህ ድርጅት መጀመሪያ ሲቋቋም ለፊውዳሉ ሥርዓትና ለኢምፔሪያሊዝም አገልግሎት ነበር። ነገር ግን ለፊውዳሉ ሥርዓትና ለኢምፔሪያሊዝም አገልግሎት ያልተቋቋመ የመንግሥት ድርጅት የትኛው ነው። እንዲያውስ የኢትዮጵያ አብዮት አንድ ዋና ጠላት ጠቅላላው ቢሮክራሲ አይደለም ወይ?

በኢሰአማ ውስጥ ከረጅም ጊዜ ጀምሮ የቆየው ትግል በነአለም አብዲ አድሃሪ ክንፍና በተራማጁ ክንፍ መካከል የነበረው ነው። ተራማጁ ክንፍ የጠየቀው ይህ ትግል በዲሞክራሲያዊ መንገድ እንዲፈታ ጠቅላላ ጉባኤ እንዲደረግ ነው። ወታደራዊው መንግሥት ግን የዚህን ክንፍ ትክክለኛ ጥያቄ ችላ በማለት እነአለም አብዲን ከስልጣን ላይ ካቆየ በኋላ አሁን ሁለቱንም ወገኖች ያለአግባብ በአንድ አይነት በማየት መስሪያ ቤቱን እስከመዝጋት ደረሰ። በዲሞክራሲያዊ መፍትሄ ፈንታ የጉልበትን መፍትሄ መርጧል ማለት ነው። ይህም የሚወገዝ እርምጃ ነው። በኢሰአማ ውስጥ ያለው ቅራኔ በውስጡ ባሉት ኃይሎች ትግልና በዲሞክራሲ እንጂ በጉልበት የሚፈታ አልነበረም። አይደለም።

7ኛ/ ከሦስት ሳምንት በፊት የመንግሥት ግልበጣ ሙከራ ተደርጐ እንደነበረ ማንም የሚያውቀው ያደባባይ ምስጢር ነው። ወታደራዊው መንግሥት ስለዚህ ጉዳይ አንዳችም መግለጫ ለሕዝብ አላቀረበም። የመንግሥት ግልበጣው ሙከራ የተደረገው በደርጉ ውስጥ ባሉ አድሃሪ ኃይሎች መሆኑ እየታወቀ፡ መንግስቱ መግለጫና ማብራሪያ ለማውጣት አለሞመከሩ በደርጉ ውስጥ የአድሃሪዎችን መጠንከር ያሳያል።

ከዚህ በላይ በተጠቀሱት ነጥቦች ላይ ሌሎችንም ብዙ ምሳሌዎች ለመጨመር ይቻላል። የኤርትራ ጥያቄ፡ የቢሮክራው ጠቅላላ ሳቦታጅ፡ የምስጢር ፖሊሱና የሳንሱሩ ሁኔታ ሁሉ በዝርዝር መጠቀስ በተገባቸው ነበር። ነገር ግን ባሁኑ ጊዜ ወታደራዊው መንግሥት ባድሃሪ ኃይሎች ሥር ለመውደቁና አድሃሪዎች እየተጠናከሩ፡ የደርጉም ተራማጅ ክንፍ እየተዳከመ፡ ለብቻው እየተነጠለ ለመሄዱ ምንም ጥርጥር የለውም። ጠቅላላው የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ እንቅስቃሴ የመቀልበስን ጐዳና ይዟል። ይሁንናም ይህ መቀልበስ ቢደረግም፡ ተራማጆች ሁሉ ቢታሰሩና ቢገደሉም፡ የአሜሪካ ኢምፔሪያሊዝምና አድሃሪዎች የቀኑን ድል ቢያገኙም ሰፊው የኢትዮጵያ ሕዝብ የመጨረሻውን ድል ይቀዳጃል።

ለዚህም የወዝአደሩ ተራማጆች፣ የኢትዮጵያ ማህበር ጠቅላላ ጉባኤ፣ በልዩ ልዩ የመንግሥት መ/ቤቶች (ለምሳሌ በንግድ ሚኒስቴር፣ በፍርድ ሚኒስቴር፣ በኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ በመሬት ይዞታ ሚኒስቴር . . . ) የሚገኘው ተራማጅ ሠራተኛ፣ ተማሪዎችና የዩኒቨርሲቲ አስተማሪዎች፣ ባጭሩ ጠቅላላው ተራማጅ ምሁራን ደጋግመው እንደጠየቁት ዲሞክራሲ መብቶች ሳይውሉ ሳያድሩ ከስራ ላይ መዋል አለባቸው። ከላይ የተጠቀሱት ተራማጆችና በጠቅላላው የሰፊው ሕዝብ ወገኖች በዚህ በዲሞክራሲ ግንባር የሚያካሂዱትን ትግል ዛሬ ከመቸውም ጊዜ በበለጠ እንደሚገፉበት ጥርጥር የለንም። የጊዜው ዋና ጥያቄ ይህ የዲሞክራሲ መብቶች ጥያቄ ነው።

​​​​የታሰሩት ተማሪዎችና ተራማጆች በሙሉ ይፈቱ
​​​​​ዲሞክራሲ መብቶች ለሰፊው ሕዝብ
​​​​​አድሃሪዎችና ኢምፔሪያሊዝም ይውደሙ
​​​​​የኢትዮጵያ ሕዝብ ያሸንፋል
Scroll to Top