የሰፊው ሕዝብ ድምፅ
ቁጥር 27፣ ሰኔ 2፣ 1967
የፅሁፉ ፍሬ ሀሳብ
መኢሶን በዚህ የሰፊው ሕዝብ ድምፅ እትሙ፣ በምሥራቅ እስያ የቪየትናም ሕዝብ ነጻ አውጭ ታጋዮች በአደረጉት ረጅም ትግል ፤ ቪየትናም የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝምን ድል አድርጋ “ነጻ አገር ሆነች” በማለት ዜናውን ያበስራል። ከዚህም በመነሳት የቬትናምን ሕዝብ የሰላሳ አመት ጠንካራ ትግል ምን ይመስል እንደነበረና ቬትናም እንዴት ድል ልትቀናጅ እንደቻለች ዝርዝር ትንተና ያቀርባል። ጽሁፉ የቬትናምን ጸረ ፊውዳልና ጸረ ቅኝ አገዛዝ ታሪክ ከኢትዮጵያ ጸረ ፋሺስት ወረራ፣ ከመደቦች ትግልና ከአብዮቱ ሂደት ጋር በማነጻጸር የኢትዮጵያ ተራማጆች ምን ትምሀርት ሊቀስሙ እንደሚችሉ አንዳንድ ሃሳቦች ይሰነዝራል።
ቪየትናም ነፃ አገር ሆነች። ጨካኙና አመፀኛው የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም በጦር ተንበርክኮና ተዋርዶ አገር ለቅቆ ወጣ። እስስት አሜሪካ በቪየትናም ሕዝብ ላይ ይህ ነው የማይባል ጭካኔ የፈፀመችው የዓለምን ጭቁን ሕዝቦች በሙሉ ቪየትናትምን አይታችሁ ተቀጡ ብሎ ለማስፈራራትም ነበር። መላ የዓለም ተራማጆች ደግሞ በበኩላቸው ‘የቪየትናም ሕዝብ ያሸንፋል’ በሚል መፈክር ስር የተሰለፉትና ዛሬም ‘የቪየትናም ድል ድላችን ነው’ ያሉት ይህንኑ የትግሉን ዓለምአቀፍ መልክ በመገንዘብ ነበር።
የቪየትናም ሕዝብ ለሰላሳ አመት ወራሪዎች የጫኑበትን ጦርነት ተቋቁሞ ዛሬ ድልን ለመጐናፀፍ የበቃው ከሰማይ የወረደ ልዩ ተሰጥዎ ስላለው አይደለም፣ ባሳየው እጅግ ታላቅ የሆነ የሃገር ፍቅርና የጀግንነት ስሜት ላይ የተደራጀና ትክክለኛ የፖለቲካ አመራር ያለው ሕዝባዊ ጦርነት ለማካሄድ በመቻሉ ነው። የቪየትናም ሕዝብ ትግል የሚያረጋግጥልን የመላው ዓለም ሕዝቦች አምነውባቸው ከሥራ ላይ ለማዋል የሚታገሉላቸውን አንዳንድ መሰረታዊ ሃቆች ነው። እነዚህ መሰረታዊ ሃቆች ምንድን ናቸው?
ዛሬ ኢምፔሪያሊዝም በስብሶ ለመውደቅ የሚንገዳገድበት ጭቁን ሕዝቦች ደግሞ ለነፃነታቸው የሚያደርጉት ትግል እያየለና ድልን እየተጐናጸፈ የሚሄድበት የታሪክ ዘመን ነው። ይህን ትግል ከግቡ ለማድረስ ኢምፔሪያሊስቶችንና ቅምጦቻቸውን ነጥሎ ለመምታት የሰፊው ሕዝብና የወገኖቹ የተደራጀ ህብረትና ተጋድሎ ያስፈልጋል። በያዝነው ዘመን ይህንን ትግል በመደባዊ አቀማመጡ በበዝባዥና በተበዝባዥ መደቦች መካከል የሰፈረው የንኡስ ከበርቴ መደብ እስከመጨረሻው ሊመራው አይችልም። የሕዝቡ ፍራቻ ስላለበት መሃል ላይ ወገቤን ይላል። ከበዝባዦች ይዋዋላል። የድሉ ዋስትና ወዝአደሩ በመደባዊ ፓርቲው ተደራጅቶ ከአርሶአደር ወገኑ ጋር አንድነቱን አጠንክሮ ሲታገልና የተቀሩትንም ፀረፊውዳልና ፀረኢምፔሪያሊስት ሃይሎች በአንድ ዲሞክራሲያዊና ሕዝባዊ ግንባር ስር ስብስቦ ትግሉን መምራቱ ብቻ ነው። ይህ ትግል የተሰበጣጠሩ መልኮች ቢኖሩትም ኢምፔሪያሊስቶችና ቅምጦቻቸው በማያዳግም ሁኔታ የሚንበረከኩት በረጅም ጊዜ የጦር ትግል ብቻ ነው።
ይህ ሁሉ ከትልቁ የጥቅምት ሪቮሉሽን ወዲህ ከግባቸው የደረሱ አብዮቶች በሙሉ፡ የቻይናም ሆነ የኮርያ፣ የአልባንያም ሆነ የምሥራቅ አውሮፖ አገሮች ታሪክ ደጋግሞ ያሳየው ሃቅ ነው። የቪየትናምም ሕዝብ የረጅም ጊዜ ትግል አመፀኛውን የአሜሪካ ኢምፔሪያሊዝም አንበርክኮ የመጨረሻውን ድል ሲጐናፀፍ ያሳየው ሃቅ ይኸው ነው። የወዝአደር ፖርቲ፡ሕዝባዊ ግንባር፣ የረዥም ጊዜ ሕዝባዊ ጦርነት. . . እነዚህ ሲቀነባበሩ ሺህ ጊዜ ኃያል ቢመስል ኢምፔሪያሊዝም ይሸነፋል። ከነዚህ አንዱ ከተዛባ ወይንም ደግሞ እስካልተሟላ ድረስ ማንም ሕዝብ ቢሆን ድልን በምንም አይነት ሊጐናፀፍ አይችልም።
ለመሆኑ የቪየትናም ሕዝብ ትግል አነሳሱ እንደምን ነበር? ይህንንስ ከላይ የጠቀስነውን ሃቅ የቪየትናም አርበኞች እንዴት ከሥራ ላይ አውለው ነው አሜሪካንን ማንበርከክ የቻሉት?
ቪየትናም ከዛሬ መቶ ዓመታት በፊት የፈረንሳይ ቅኝ ገዥዎች ከያዝዋት ጀምሮ የነፃነት ተጋድሎዋን ያቋረጠችበት ወቅት የለም። ያለማቋረጥ የተካሄደው የሰላሳ አመት ጦርነት በወዝአደሩ ፖርቲ መሪነት የተጀመረው በሁለተኛው የኢምፔሪያሊስቶች ጦርነት መጀመሪያ ላይ ፈረንሳይ ድል ሆኖ ፋሽስት ጃፖን ቪየትናም ውስጥ እገሯን ለማስገባት ስትሞክር ነው። የቪየትናም አርበኞች አሥር ዓመታት ያህል ቀደም ብሎ በ1923[1] በተቋቋመው የወዝአደር ፖርቲና ቪየትሚን በሚባለው የአርበኞች ጦር ስር ባደረጉት ተጋድሎ የተነሳ ጃፖን ስር መስደድ አልቻለችም። ይህ ትግል በመካሄድ ላይ እንዳለ ጃፖን ተሸንፋ በነሃሴ ወር 1938 እጇን ሰጠች። የአርበኞቹ መሪ ሆቺሚን በዚሁ ወር ሃኖይ ከተማ ላይ የቪየትናምን ነፃነት አወጁ። ወር ሳይሞላው በጃፖኖች ተባርረው የነበሩት የፈረንሳይ ኢምፔሪያሊስቶች ተመልሰው ‘ቀኝ ግዛታቸውን’ ለመያዝ በሳይጎን በኩል ገቡ። ባኦ ዳይ የተባለውን ሰው ‘የቪየትናም ንጉስ’ ብለው አስቀመጡት። ሳይጐንም መናገሻ ከተማ ተባለች። የነፃዋን ቪየትናምም መንግሥት ለመደምሰሰና የእጅ አዙር ቅኝ ግዛታቸውን ለማጠንከር ጦር አነሱ። በዚህ የተነሳ በአርበኞቹና በወራሪዎቹ መካከል 9 አመት የፈጀው ጦርነት ተጀመረ። በመጨረሻው በታላቁ ሆቺሚንና በጄኔራል ጂያኘ የሚመራው የቪየትሚን ጦር ሚያዝያ 29 ቀን 1946 የፈረንሳዩንና ቅምጡን መንግሥት ጦር ዲየን ቢያንፉ በተባለው ጦር ሜዳ በማያዳግም ሁኔታ ድል አደረጉ።
ፈረንሳይም የማትችለው ማጥ ውስጥ መግባትዋን አምና በዚሁ አመት ጄኔቫ ላይ የሰላም ውል ፈርማ ሃገሩን ለቅቃ ወጣች። ይህ ውል የቪየትናምን አንድነትና ነፃነት በማያወላውል ሁኔታ አረጋገጠ። በሁለት አመትም ውስጥ ጠቅላላ ምርጫ ተደርጐ የቪየትናም ሕዝብ የሚስማማውን መንግሥት እንዲያቋቁም ተወሰነ። እስከዚያው ግን ቪየትናም በሁለት ቀጠና /ዞን/ ተከፍላ የአርበኞቹ ጦር በስተሰሜን በኩል እንዲሰባሰብ ስምምነት ተደረገ።
ቀደም ብላ ለፈረንሳዩች ስንቅና መሳሪያ ስታቀብል የነበረችው አሜሪካ በቪየትናም ላይ ብቻ ሳይሆን በጠቅላላው በኢንዶቻይና መርዘኛ አይኗን ተክላ ኖሮ ይህንን ውል ሌሎች ኃያላን መንግሥታት ሲፈረሙ እሷ አልፈርምም አለች። የእጅ አዙር ቅኝ ግዛት አላማዋንም ከሥራ ላይ ለማዋል የፈረንሳዩችን ቅምጥ ንጉስ አስገልብጣ ‘ሬፑብሊክ’ ነው ብላ ዲየም የተባለውን ቅምጥ ኘሬዝደንት በስልጣን ላይ ጐለተች። በነሃሴ ወር ላይ አይዘንሃወር ‘የዚህ ውል አንቀጾች በአሜሪካን ላይ አይፀኑም’ ብሎ ለዓለም ሲገልጽ ቅምጡ ዲያም አከታትሎ ይህ ውል እንደማያስነውርና ጠቅላላ ምርጫ የተባለውንም ለማድረግ ምንም የሚያስገድደው ነገር እንደሌለ በይፋ ገለጠ።
ከዚህ ጊዜ ጀምሮ የአሜሪካኖችና የቅምጦቻቸው አላማ ቪየትናምን ከፋፍለው ለመግዛት፣ የደቡቡን ‘መንግሥት’ ማጠንከርና ሰሜን ቪየትናምን በልዩ ልዩ ሳቦታዥ አዳክሞ ሰበብ ፈልጐ መውረር እንደሆነ ግልጽ እየሆነ ሄደ። ግን የትግሉ መሪ የሆነው የቪየትናም ወዝአደሮች ፖርቲም ሆነ በጠቅላላዉ አርበኞችና ሰፊው ሕዝብ በእንደዚህ አይነቱ ተንኮል የሚፈታ አልነበረም። አሜሪካኖችና ቅምጦቻቸው ይህንን ኘላን ሲያወጡ የቪየትናም ሰፊ ሕዝብ ለአንድነቱ፣ ለነፃነቱና ለእርምጃው ያለዉን የጋለ ስሜት ከቁጥር ሳያስገቡ ነበር። ትልቁ ስህተታቸው እዚህ ላይ ነው።
በተለይ በዚህ ወቅት የቪየትናም ሕዝብ እርም ብሎ ለአሥር ዓመታት ያህል ባደረገው ተጋድሎ ባላገሩ ከሞላ ጐደል ነፃ ወጥቷል፣ በነፃ ክፍለሃገሮች ውስጥ መሬት ለአራሹ ተከፋፍሏል፣ የሴቶች እኩልነት መብት ተረጋግጧል፣ ድንቁርናም በመጥፋት ላይ ነው። ገበሬው በያለበት ተደራጅቶ በየመንደሩ በመረጣቸው ወገኖቹ ራሱን ያስተዳድራል። የተለያዩ ብሄሮች በእኩልነትና በወንድማማችነት መንፈስ እጅ ለእጅ ተያይዘው እየተደጋገፉ መራመድ ጀምረዋል። ባጭሩ በሚልዩን የሚቆጠር የቪየትናም ሰፊ ሕዝብ በነፃነትና በአንድነት ተሳስሮ አዲስ ኑሮ መገንባት ጀምሯል። በተለይም ደግሞ በሰሜን በኩል ባለው ቀጠና እንዲያውም ሶሻሊዝም ታውጆ ታላቅ አርአያነት ያለው እርምጃ መታየት ጀምሯል።
እንግዲህ የቪየትናም ሕዝብ ሁኔታ ይህ ሲሆን አሜሪካኖችና ቅምጦቻቸው የጠነባ ሥርዓታቸውን በዚህ ንቁ ሕዝብ ላይ ለመጫን ከፈለጉ፣ የሕዝብን ሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች ለመንፈግ ከተነሱ የግድ ጭፍን በሆነ አመጽ ሕዝቡን ማስፈራራት እንዳለባቸው ተረዱ። ስለዚህም መሬታችንን መልሰን አንሰጥም ‘ብንሞትም ብንኖርም መሬታችን ላይ’ በሚል መፈክር የተነሱትን የቀድሞ ጭሰኞች ‘ኮሚኒስት’ እያሉ ይፈጇቸው ጀመር። የቀድሞ አርበኞችን እያሳደዱ ማደን፣ የጃኔቫን ውል ከሥራ ላይ ማዋል የሚጠይቅን አርበኛ ሁሉ፡ ዲሞክራሲና ሕዝባዊ ምርጫ የሚል አገርወዳድን ሁሉ እያደኑ መፍጀት ሥራዬ ብለው የያዙት ፈሊጥ ሆነ። በአሜሪካኖች መሳሪያና ምክር የተነሳ በአንዳንድ ቀበሌዎች የቀድሞ የጭሰጭነት ሥርዓት እንኳን መልሶ ማንሰራራት ጀመረ።
የቬይትናም አርበኞችና ሰፊው ሕዝብ መልሶ ጦሩን ከማንሳትና ለረጅም ጊዜ ጦርነት ከመታጠቅ ሌላ ምንም ምርጫ እንዳልተተወላቸው ተረዱ። ሰላምን፣ አንድነትን፣ ነፃነትን በታላቅ ጉጉት የሚጠብቀው የቪየትናም ሕዝብ ሰላም ስለተነፈገ፣ አንድነቱ ስለፈረሰ፣ ነፃነቱ ስለተደፈረና እርምጃው ስለተገታ እንደገና ወደትግል እንዲገባ ተገደደ። ይህ እንግዲህ በአሜሪካ ወራሪዎች በሰላማዊው የቪየትናም ሕዝብ ላይ የተጫነው ጦርነት ‘ሁለተኛው የአርበኝነት ዘመን’ ተብሎ የታወቀውና በ1952 የተጀመረው ተጋድሎ መሆኑ ነው።
ይህ ትግል ፍሬ ይሰጥ ዘንድ መሰብሰብና መቀነባበር እንዳለበት ስለታመነ የቪየትናም ሕዝባዊ አብዮታዊ ፖርቲ (ወዝአደሮች ፖርቲ መሆኑ ነው) ግንባር ቀደምነት በታህሳስ ወር 1952 ‘የቪየትናም ነፃ አውጭ ግንባር’ የተባለ ድርጅት ተቋቋመ። አሜሪካኖችም በበኩላቸው ትግሉን በእንጭጩ ለመቅጨትና ለአካባቢውም ሆነ ለዓለም ጭቁን ሕዝቦች የማያዳግም ትምህርት ለመስጠት ተሰናዱ። ማክስዌል ቴለር የተባለው የኬኔዲ አማካሪ ለኘሬዚዳንቱ ‘ልዩ ጦርነት’ (ስፔሻል ዋር) የተባለውን ስልት አውጥቶ ፀደቀለት። ይህ የማክስዌል ቴለር ወገኛ ፕላን በሦስት ምእራፎች የተከፈለ ሲሆን አላማው፡-
1ኛ/ አርበኞችን በ18 ወር ውስጥ ጨርሶ ለመደምሰስ
2ኛ/ ቅምጡን መንግሥት በመሳሪያና በገንዘብ ኃይል ማጠንከርና በሌላ በኩል ደግሞ የሰሜን ቪየትናምን ኢኮኖሚ በልዩ ልዩ የሳቦታዡ ድርጊቶች ማዳከምና ማዝረክረክ
3ኛ/ የቬየትናም አርበኞች ጨርሰው እንደተደመሰሱና ቅምጡ መንግሥት እንደተጠናከረ፡የሰሜን ቪየትናም በሳቦታዥ መዳከም እንደተረጋገጠ ሰበብ ፈልጐ መውረር የሚል ነበር።
አስራ ስምንት ወር ይቅርና ይኸው የማክስዌል ቴለር ወገኛ ኘላን 15ኛ አመቱን አከበረ። የሆነውን ሁላችንም እናውቀዋለን። አርበኞቹ እንኳን ሊደመሰሱ ይቅርና ድልን ተጐናፀፉ። ቅምጡ መንግሥት እንኳን ሊጠናከር ይቅርና እንደእንቧይ ካብ ፈራረሰ። ሰሜን ቪየትናምም እንኳን ልትዳከም ይቅርና ድልን ተጐናፀፈች። አሜሪካኖች ግን አልተሳካላቸውም እንጂ ይህንን እርኩስ ኘላናቸውን ከሥራ ላይ ለማዋል ያልሞከሩት ዘዴ፣ ያልተጠቀሙበት መሳሪያ፣ ያልፈፀሙት ጭካኔ የለም።
ኘላኑ እንደወጣ ወዲያውኑ ቅምጡ መንግሥት 5ዐዐ ሺ ወታደር ተቀጠረለት። ይህ ሁሉ ሰራዊት በአሜሪካ ዘመናዊ መሳሪያ ከእግር እስከራሱ ታጠቀ። ‘ማግ’ (የጦር እርዳታ አማካሪ ቡድን) በተባለው የአሜሪካኖች የጦር ድርጅት አማካይነት 12ሺ የአሜሪካ ወታደሮች ‘አማካሪዎች’ እየተባሉ በጦሩ ውስጥ በያለበት ተሰካኩ። (በነገራችን ላይ ይህ ስመጥፉ ማግ የተባለ የጦር ድርጅት አሜሪካኖች የቅኝ ግዛታቸውን ለማስፋፋት በፊታውራሪነት የሚልኩት ጦር ሲሆን በኢትዮጵያም ውስጥ አለ።)
ይህም ሆኖ ታዲያ በ18 ወር ይፈፀማል የተባለው ‘ልዩ ጦርነት’ ቢሉት ቢሉት የሚገፋ አልሆነም። መድፍ፣ መትረየስ፡ቦምብ፣ የጥይት ዝናብ፣ የመርዝ ጢስ፣ ፀረ-አዝርእት ኬሚካሎች፣ ሳይንስ የፈለሰፋቸው ዘመናዊ የማጥፊያ ሃይሎች በቪየትናም ምድርና በቪየትናም ሕዝብ ላይ ለፍተሻ እየቀረቡ ይፈራረቁበት ጀመር። ግን አመት፣ ሁለት አመት፣ ሦስት አመት፣ አራት አመት ታየ፡ አርበኞቹ አልተደመሰሱም። በቅምጦቹና በጌቶቹ መሃል መነታረክና መወነጃጀል ተፈጠረ። ‘ጥፋት ከኛ አይደለም፡ከቅምጦቹ ነው’ ብለው የደመደሙት ወራሪዎች ዲያም የተባለውን ቅምጥ ኘሬዜዳንታቸውን በህዳር ወር 1952 ዓ.ም አስገልብጠው አሳረዱት። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ለአራት ዓመታት ያህል የቅምጦች መፈራረቅ ብቻ ሆነ። የተመቸው ስድስትም ወር እየተቀመጠ ያልቀናው ደግሞ በግማሽ ቀንም እየተባረረ ወደ ሃያ የሚጠጉ ኩዴታዎች (መፈንቅለ መንግሥቶች) ተደረጉ። በዚህ ሁሉ እንግዲህ ፀረሕዝብ ወገኖች የባሰውን በፖለቲካም በሞራልም እየደቀቁ ሄዱ።
አሜሪካኖች ‘ልዩ ጦርነት’ የሚሉት ኘላን ሲከሽፍ ተሰማቸው። ዞሮ ዞሮ የነሱው የወረራ ጦርነት ነውና በእጅ አዙር እየተዋጉ ‘ነገር ከማንዛዛት’ አንዴ እንደመብረቅ ቪየትናምን በቀጥታ ወርሮ ‘ነፃ መውጣት’ ይሻላል የሚል ኘላን ተነደፈ።
ደግሞ ስምንት አመት ሙሉ ዋትተው ‘ታክቲክ’ እስኪለውጡ ድረስ ይህን ኘላን ‘የተወሰነ ጦርነት’ (ሊሚትድ ዋር) በሚል ስም አጠመቁት። ይህም ከዚያኛው የባሰ ወገኛ ኘላን ነበር። ግን ከ36ዐ ሺህ በላይ የአሜሪካ ወታደር ሞቶና ቆስሎ፣ በሚልዩን የሚጠጋ ሰላማዊ የቪየትናም ሕዝብም አልቆ፣ አገሪትዋ ተቃጥላ የቪየትናም ሕዝብ ትጥቁን እንዳልፈታ እስከተገነዘቡ ድረስ የዚህ ኘላናቸዉ ፉርሽነት አልታያቸውም ነበር። ይህ ‘የተወሰነ ጦርነት’ ይዘቱ ምንድነው?
አሜሪካ ባላት ይህ ነው በማይባል የሰውና የጦር ኃይል አንድ ጊዜ ‘እንደመብረቅ’ በቪየትናም ሕዝብ ላይ ታወርዳለች። አርበኞችዋን እንዳልነበር አድርጋ ትደመስሳለች። ሰሜን ቪየትናምን አንድ የአሜሪካ ጄኔራል እንዳለው በልዩ ልዩ ቦምብ ዝናብ ወደ ‘ድንጋይ ዘመን’ ተመልሳ ትንበረከካለች።[የአዘጋጆች እርማት ተደርጓል] እንግዲህ በዚህ መልክ አርበኞች ልጆችዋ ተደምስሰው፣ ምድርዋ ተቃጥሎ፣ የተረፈው ሕዝብዋ በማይደፈረው የአሜሪካ ክንድ ተቀጥቶ ሰጥለጥ ብሎ የተረጋጋችውንና በአሜሪካን ወረራዎች ብርታት ‘ነፃ የወጣችውን’ ቪየትናምን መልሰው ለቅምጡ መንግሥት ያስረክባሉ። ‘ሰላመ አሜሪካ’ በምድረ ቪየትናም ይወርዳል። ደቡብ ምሥራቅ እስያ አርፋ ትገዛለች። የዓለም ጭቁን ሕዝቦች ለማይደፈረው የአሜሪካ ክንድ ሰጥ ለጥ ብለው ይገዛሉ። ይህ ‘የተወሰነ ጦርነት’ የተባለው ኘላን እንዲህ እንዲህ ያሉ ቅዥቶች ነበሩበት።
ተወጥኖም አልቀረ። በዚሁ ኘላን መሰረት ‘መብረቁ’ የአሜሪካ ጦር በሚያዝያ ወር 1957 የመጀመሪያዎቹን 3500 ወታደሮች ይዞ ደረሰ። ትንሽ ሳይቆይ የቀደመውን ጦር ለመርዳት እየተባለ እንዲሁ አንዱ ባንዱ ላይ እየተደራረበ በ1960 ላይ የአሜሪካ ጦር ብቻውን ‘አገር አስለቀቀ’፣ ብዛቱ ከግማሽ ሚልዩን በላይ ሆነ። ወራሪውን ጦርም ለማገዝ በአካባቢው ካሉት ቅምጥና አድሃሪ መንግሥታት የተውጣጣ ጦርም በቪየትናም ላይ እንዲዘምት ተደረገ። ባጭሩ በ1960 የቅምጡ መንግሥትና የወራሪዎቹም ጦር ተደምሮ አንድ ሚልዩን ሁለት ወቶ ሺህ ሰው ሆነ። ለ15 ቪየትናማውያን አንድ ከእግር እስከራሱ የታጠቀ ወታደር ተደረገበት ማለት ነው። በዚህ ላይ የመሳሪያው ብዛቱ፣ አይነቱ፣ ረቂቅነቱ።
ነገር ግን በዚህ ሁሉ ድርጊታቸው ቀደም ሲል በእጅ አዙር ይሰሩ የነበሩት አሜሪካኖች በእርግጠኛው በወራሪ መልካቸው ተጋለጡ። በእጅ አዙሩ ጊዜ ተወናብዶ ከነበረው አብዛኛው የአርበኞቹን ወገን እየመረጠ ስለሄደ ወራሪዎቹና ቅምጦቻቸው በብቸኝነት ይታጠሩ ጀመር። በዓለም አቀፍ ደረጃም መላው የዓለም ሕዝብ /የአሜሪካ ሕዝብ ሳይቀር/ ይህንን ወረራ በጥብቅ ያወግዝ ጀመር። የተወረረችው ቪየትናም ጠላቷን እንድትቋቋም የሶሻሊስት አገሮች በተለይም ሕዝባዊት ቻይናና የሶቪየት ህብረት የጦር፣ የፖለቲካና የኢኮኖሚ እርዳታቸውን ለገሱ። በፖለቲካም ሆነ በጦር በኩል የአርበኞቹ ወገን ከመቼውም ይበልጥ ዳበረ። ይህንንም ለማረጋገጥ ወራሪቹ የሰውም ሆነ የመሳሪያ ኃይል እጅግ ከፍተኛ ደረጃ ደርሷል ተብሎ በሚገመትበት ጊዜ በጥር ወር 1960 ‘ቴት ኦፊንሲቭ’ የተባለውን የማጥቃት ኘላን አውጥተው የቪየትናም አርበኞች 34 ታላላቅ ከተማዎችንና ዋና ከተማዋን ሳይጐንን በተቀነባበረ ዘዴ በአንድ ጊዜ አጥፍተው ብዙዎቹን ነፃ አወጡ። ወራሪዎቹ ከተማ ከተማውን በታላቅ ጭንቅና በተለይ ደግሞ ሕዝብና ንብረትን በጭካኔ በቦምብ በመደብደብ ቢያስለቅቁም ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ቅስማቸው ጨርሶ ተሰበረ ለማለት ይቻላል።
በዚሁ አመት ወራሪዎቹ መሽገው ከተቀመጡባቸዉ ከተማዎች በስተቀር ሃገሪቱን በሙሉ ከቁጥጥሩ ስር ያደረገው ‘ብሄራዊ ነፃ አውጭ ግንባር’ በፖለቲካውም በኩል ድልን በመጎናፀፍ ‘ጊዚያዊ አብዩታዊ መንግሥት’ ተቋቋመ። በሌላ በኩል ደግሞ ጆንሰን የጦሩ ነገር እንዳላዋጣ ስለተገነዘበው ለብዙ ጊዜ አሻፈረኝ ያለውን የእርቅ ንግግር እንዲጀምር በመገደዱ በግንቦት ወር በፖሪስ ከተማ ንግግር ተጀመረ።
ነገር ግን የአሜሪካ ኢምፔሪያሊዝም ሰላም የሚፈልግ መስሎ በእርቅ ንግግሩ ውስጥ ቢሳተፍም ቅሉ የወረራ አላማውን አልለቀቀም ነበር። ስለዚህ የቪየትናምን ሕዝብ ትግል አዘንግቶ ለመደምሰስ ሰላም የሚፈልግ መስሎ አዲስ የጦር ኘላን አወጣ። ይህ ደግሞ ‘ቪየትናማይዜሽን’ ወይም ቪየትናማውያንን በቪየትናማውያን መውጋት የሚል ርኩስ ኘላን ነበር።
በዚህ ጦር ኘላን መሰረት አሜሪካ በምድር ለሚዋጋው የቅምጡ መንግሥት ጦር መሳሪያ፣ የመገናኛ፣ የስንቅ፣ የአማካሪ እርዳታ እየሰጠች ወንድማማቹን ሕዝብ እርስ በርስ ለማጫረስ ወሰነች። በተጨማሪም ደግሞ ሰሜንንም ሆነ ደቡብ ቪየትናምን የአሜሪካ ፓይለቶች በአውሮኘላን ያለማቋረጥ እንዲደበድቡ አደረገች፣ የአርበኞቹን ጦር በዚህ ዘዴ ለመደምሰሰና የሕዝቦንም ሞራል ለመምታት ፈለገች። በዚህ ወቅት ወራዳው ኒክሰን በተለይ ከ1960 ጀምሮ የሃገሪቱን ከተሞች፣ ሆስፒታሎች፣ ት/ቤቶች፣ ድልድዩች፣ ፋብሪካዎች . . . በጭካኔ በቦምብ በማስደብደብ እነሂትለር እንኳን ያለፈፀሙትን ወንጀል ፈጽሟል። ለምሳሌ ያህል በ1965 በታህሳስ ወር መጨረሻ ላይ በሃኖይና በአካባቢዋ በ4 ቀናት ውስጥ ወንጀለኞቹ በሰላማዊው ሕዝብና በንብረት ላይ ያዘነቡት ቦምብ ሂትለር በሁለተኛው የዓለም ጦርነት በእንግሊዝ አገር ላይ ካዘነበው ቦምብ እንደሚበልጥ ይታወቃል። ይህ የወራሪዎችን ወሰን የሌለው ጭካኔ ለማሳየት ይበቃል ብለን እንገምታለን።
ግን የቪየትናም ሕዝብ ትጥቁን አልፈታም። ይህም የወራሪዎቹ ሶስተኛ ኘላን በመክሸፉ የተነሳ አሜሪካ ፋታ ለማግኘት በጥር ወር 1965 ወታደሮችዋን ፈጽማ ከቪየትናም ምድር ለማውጣት፣ የጊዜያዊ ሪቮሎሽናዊ መንግሥትን ለማወቅ፣ የቪየትናም ሕዝብ ያለአንዳች ተጽእኖ የራሱን እድል በራሱ ለመወሰን ያለውን መብት ለማወቅ የተገደደችበትን የፖሪሱን ስምምነት ፈረመች። ከዚያም ጊዜ ወዲህ ቢሆን ይህንን ውል ለመጣስና በልዩ ልዩ ስውር ተንኮል ለማደናቀፍ በመሞከር ጦርነቱ ይኸው እስከዛሬ ድረስ አላቋረጠም ነበር። አሁን ግን ሚያዝያ 22 ቀን 1967 ዓ.ም. ለ3ዐ ዓመታት ሙሉ ትጥቁን ያልፈታው ጀግናው የቪየትናም ሕዝብ አሜሪካኖች ቅምጣቸውን አግተልትለው በታላቅ ሽብርና ሽሽት ሳይጐንን እንዲለቅቁ አድርጓቸዋል። የቪየትናም ሕዝብ ሙሉ በሙሉ ድልን ተቀዳጀ።
ቪየትናም ትንሽ አገር ናት። በጦርም ሆነ በኢኮኖሚ የኢምፔሪያሊስቶች ቀንደኛ ኃይል የሆነውን የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም እንደዚህ ማንበርከክ የቻለው እንዴት ነው? የቪየትናም ሕዝብ ትግል ድልን የተጐናፀፊው ከትልቁ የጥቅምት ሪቮሉሽን ወዲህ ድልን የተጐናፀፉ አብዮቶች የተከተሉትን ሳይንሳዊ ጐዳና በመከተሉ ነው። የቪየትናም ሕዝብ ድልን የተቀዳጀው፡ 1/ በሳይንሳዊ ሶሻሊዝም የታነፀ የወዝአደር ፖርቲ፣ 2/ በዚህ ፖርቲ ግንባር ቀደምነት ሌሎቹም የተደራጁ ፖርቲዎችና ሕዝባዊ ድርጅቶች ትግላቸውን የሚያስተባብሩበት ግንባርና 3/ በዚሁ ግንባር የሚመራ የተደራጀ ሕዝባዊ ጦር ስለነበረው ነው። የቪየትናም አርበኞች እነዚህን ሦስት ነጥቦች ከሃገራቸው ታሪክና ተጨባጭ ጊዚያዊ ሁኔታ ጋር አዛምደው ከሥራ ላይ በማዋላቸው ድልን ለመቀዳጀት በቁ።
ለመሆኑ በጠቀስነው መልክ ተደራጅተው የታገሉት መደቦችና የህብረተሰብ ክፍሎች እነማን ናቸው?
በደቡብ ቪየትናም ያለውን የመደቦች አሰላለፍ ብናይ ሕዝቡ 8ዐ ከመቶ በግብርና የሚተዳደር ሲሆን ከነዚህ ውስጥ ከግማሽ በላይ መሬት የሌላቸው ጢሰኞች ነበሩ። ከነዚህ ገበሬዎች ባለርስቶች ይህ ነው የማይባል ግፍና በደል ሲፈጽሙባቸው ኖረዋል። በአንዳንድ ቦታ ልክ አንደኛው አገር ከምርታቸው እስከሦስት ሩብ ድረስም ለማስረከብ የሚገደዱበት አካባቢ ይገኝ ነበር። ባጭሩ አብዛኛው የቪየትናም ሕዝብ ከባድ የፊውዳል ጭቆና የተጫነውና መሬት እንደውሃ የጠማው ሕዝብ ነበር ማለት ነው። የቪየትናም ሪቮሉሽናውያን ይህንን ሃቅ ተረድተው ነበር። ገበሬውን ያልያዘ፣ ገበሬው ያላቀፈው ምንም አይነት ሪቮሉሽን ሊደረግ አለመቻሉን ስለተረዱ ከመጀመሪያው ይዘው የተነሱት መፈክር መሬት ላራሹ የሚለው ቢሆን አያስገርምም።
በቅኝ ገዥዎች ከመቶ አመት ወዲህ የሚስፋፋው የካፒታሊስት ሥርዓት ምንም እንኳን ያገሬውን ከበርቴ እንዳያድግ አፍኖ ቢይዘውም ቅሉ በህብረተሰቡ ውስጥ የወዝአደሩ መደብ ስር እንዲሰደድ አድርጐአል። ይህ መደብ በቁጥር እጅግ አነስተኛ ቢሆንም ከፍተኛ ብዝበዛና ጭቆና ስለነበረበት የትግል መንፈሱ በጣም ከፍተኛ ነበር። ስለዚህም ከጽንሱ ጀምሮ፡ በተለይም የኢንዶቻይና የሠራተኞች ፓርቲ ከተቋቋመበት ከ1923 ዓ.ም ጀምሮ ታላቁ ተጋድሎ ያደረገና በፖርቲው አማካይነት የትግሉን አመራር የጨበጠ መደብ ነው።
የነፃነቱ ተጋድሎ ዋና ምሰሶዎች እነዚህ መደቦች- ወዝለአደሩና አርሶአደሩ – ናቸው። የሰፊውም ሕዝብ አንድነት የተመሰረተው በወዝአደሩና በአርሶአደሩ ህብረት አካባቢ ነበር። ፊውዳሊዝምንና ኢምፔሪያሊዝምን ለመደምሰስ በተደረገው ትግል ውስጥ ሌሎችም መደቦችና የህብረተሰብ ክፍሎች ታላቅ አስተዋጽኦ አድርገዋል። እነዚህም ነጋዴዎች፡ ምሁራን፡ ዝቅተኛ የመንግሥት ሰራተኞ፡ በተለይም ደግሞ አስተማሪዎችና ተማሪዎች ናቸው። የቪየትናም ሠራተኞች ፖርቲ ዋና ጠላቶቹን ነጥሎ ለመምታት ስልት ባለው አመራር እነዚህ ሃይሎች ሁሉ እንዲደራጁ ማገዝና ለትግሉ ማሰለፍ እንዳለበት ፈጽሞ አልሳተውም ነበር፣ ከልባቸው የትግሉ ደጋፊ እንደሆኑና በዲሞክራሲ ላይ የተመሰረተ የየራሳቸው ድርጅት እንደሚያስፈልጋቸው ያውቅ ነበር። ስለዚህም ትግሉ ሊቀነባበር የሚችለው እነዚህ ፖርቲዎችና ድርጅቶች የሚሰበሰቡበት ሕዝባዊ ግንባር ሲቋቋም መሆኑን በማመን ይህ ግንባር እንዲቋቋም ፖርቲው በትጋት ታገለ። ወራሪዎቹን ጨርሶ ለመደምሰስ የሚቻለውም በረዥም ጊዜ በሚካሄድ ሕዝባዊ ጦርነት ብቻ መሆኑን በማመን በየደረጃው የነቃና የታጠቀ ጦር አደራጀ።
የሃገሪቱን ፀረፊውዳልና ፀረኢምፔሪያሊስት ኃይሎች ለመሰብሰብ ሲል ሕዝባዊ ግንባሩ እንዲቋቋም ፖርቲው ታላቅ ተጋድሎ በማድረጉ ከላይ እንደጠቀስነው በ1952 ዓ.ም. ‘የቪየትናም ነጻ አውጭ ግንባር’ የተባለው ተቋቋመ። ኢምፔሪያሊስቶችና ቅምጦቻቸው የዚህን ግንባር ተወካይነት ለማጥበብና ‘ኮሚኒስቶች ብቻ ናቸው’ ብሎ ለማውራት ይህንን ድርጅት ‘ቪየትኮንግ’ ወይም የቪየትናም ኮሚኒስት የሚል ቅጽል አወጡለት። ግንባሩ የኮሚኒስት ፖርቲው ብቻ ሳይሆን ሃገር-ወዳድና የሰፊው ሕዝብ ወገኖች ሁሉ ተደራጅተው የሚሳተፉበት ግንባር ነበር። ለዚህ ማስረጃ ‘የቪየትናም ነፃ አውጭ ግንባር’ ውስጥ ካሉት ድርጅቶች ዋና ዋናዎቹን መጥቀስ ብቻ ይበቃል።
ይህ ግንባር ሦስት የፖለቲካ ፖርቲዎች የያዘ ግንባር ነው። ከነርሱም አንደኛው፡ ከሁሉ ቆራጥ የሆነውና በገበሬው ትብብር የአመራሩን ቦታ የያዘው የቪየትናም ሠራተኞች ና ሪቮሉሽናዊ ምሁራን ‘ሕዝባዊ አብዩታዊ ፖርቲ’ የተባለው ነው። ከዚህ ሌላ ‘ራዲካል ሶሻሊስት ፖርቲ’ የተባለው አገር ወዳድና ተራማጅ ምሁራን የተሰለፉበት ፖርቲ አለ። ሶስተኛ ደግሞ የሃገሩ ከበርቴዎች የተሰበሰቡበት ‘ዲሞክራሲያዊ ፖርቲ’ የተባለው ድርጅት አለ። በተጨማሪ በግንባሩ ውስጥ የሚወከሉ የሰፊው ሕዝብ ልዩ ልዩ ድርጅቶች መአት ናቸው። ከነዚህም ውስጥ በብሄርአቀፍ ደረጃ ‘የገበሬዎች ህብረት’ ለነፃነት፣ ‘የሠራተኞች ህብረት ለነፃነት’፣ ‘የወጣቶች ፌዴሬሽን ለነፃነት’፣ ‘የሴቶች ህብረት ለነፃነት’፣ ‘የደራሲያንና የአርቲስቶች ህብረት ለነፃነት’፣ ‘የቡድሃ ምእመናን የሃገር ፍቅር ማህበር’፣ ‘ለእናትና ሃገርና ለእግዚአብሄር ታማኝ ካቶሊኮች ማህበር’፣ ‘አገርወዳድ ጋዜጠኞች ማህበር’፣ ‘አገር ወዳድ አስተማሪዎች ማህበር’፣ ‘የቀድሞ አርበኞች ማህበር’ ወዘተ. ይገኙበታል።
ባጭሩ ይህ ግንባር የሪቮሉሽኑ አጋዥ ሊሆኑ ይችላሉ ተብለው የሚታሰቡትን መደቦችና የህብረተሰብ ክፍሎች ጾታ፣ ብሄር፣ ሃይማኖት . . . ሳይለዩ በየድርጅቶቻቸው አማካይነት የሚሳተፉበት ሰፊ ግንባር ነው። እንደዚህም ስለሆነ ይህ ግንባር በቪየትናም ምድር ላይ ከወራሪዎቹና ከቅምጦቻቸው በስተቀር ሰፊውን ሕዝብ አቅፎ የያዘ ግንባር ነበር። እነዚህ ሃይሎች በግንባሩ ከፍተኛ አካላት ውስጥ ተገቢ የሆነ ተወካይነት ስላላቸው ግንባሩ የሚከተለውን የፖለቲካ መስመር ለመቀየስ ዲሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ ሙሉ በሙሉ ይሳተፋሉ።
በፖለቲካ እንደዚህ የተደራጀው የቪየትናም ሕዝብ ትግል ወራሪያቹን ለመቋቋምና ለመደምሰስ አስፈላጊ የሆነው የሕዝባዊ ጦር ድርጅት ነበረው። ሰፊው ሕዝብ በወኪሎቹ አማካይነት የሚቀይሰውን ፖለቲካ ከሥራ ላይ ለማዋል እንደዚሁ በየደረጃው ሕዝቡ ራሱ የሚሳተፍበት ሙሉ የሆነ የጦር ድርጅት አለው።
የጦሩ ድርጅት ሦስት የተለያዩ በጣም የሚተጋገዙ ደረጃዎች አሉት። በመጀመሪያው ደረጃ ያለው ‘አገር ጠባቂ’ የሚባለው ከየቀበሌው ገበሬዎች የተውጣጣ ሕዝባዊ ጦር ነው። በዚያው በመንደሩና በአካባቢው እርሻውን እያረሰ ጠላትን ይከላከላል። ከዚያም በሁለተኛ ደረጃ በክፍለሃገር ተወስኖ የሚሰራ ጦር አለ። በከፍተኛ ደረጃ ደግሞ ዘመናዊ ትጥቅና ትምህርት ያለው ቋሚ የሆነ ሕዝባዊ ጦር ሰራዊት አለ።
ከቪየትናም ሕዝብ ትግል የሚረጋገጠው አንድ ሃቅ ይህ በፖለቲካና በጦሩ መካከል ያለው ግንኙነት ነው። እርግጥ ጦሩ የፖለቲካው ታዛዥ ነበር። ግን ደግሞ እንደከበርቴዎች አስተሳሰብ የፖለቲካው ድርጅት ‘አንጐል’ የጦሩ ድርጅት ደግሞ ‘ክንድ’ እንዳይሆኑ ጥብቅ ጥንቃቄ ይደረግ ነበር። ጦሩ እውር ዲሲኘሊን የሚከተል ጦር አልነበረም። ተዋጊዎቹ የማያቋርጥና የተጣራ የፖለቲካ ትምህርት ይሰጣቸዋል። በየክፍሉ ለዚህ ተመድበው የሚሰሩ የፖለቲካ ክበቦች አሉ። የውስጣዊ አሰራሩን ብንመለከት የጦሩ መመሪያ ‘ዲሞክራቲክ ሴንትራሊዝም’ የተባለው መርህ ነው።አንድ ጠላትን የማጥቃት ተግባር ከመወሰዱ በፊት ጐልቶ በሚመለከተው የጦር ቡድን ውስጥ ሰፊ የሆነ ውይይት ይደረግበታል። ስለዚህ በፖለቲካ የነቃ፡ በዲሞክራሲ የሚመራ ጦር በመሆኑ በሞራልም ሆነ በጀግንነት በገንዘብ ብቻ ከተገዛውና በትእዛዝ ብቻ ከሚሰራው የቅምጦች ሰራዊት ጋር ትልቅ የአላማና የሞራል ልዩነት አለ ማለት ነው። ይህንን ልዩነት፡ ይህንን የሕዝቡን ጦር የበላይነት ሚልዮን አይነት መሳሪያ ቢፈስ ሊለውጠው አይችልም። ወራሪዎቹና ቅምጦቻቸው አልገባ ያላቸው አንድ ሃቅ ይህ ነበር።
እንግዲህ የቪየትናም ሕዝብ ትግል ድልን የተጐናፀፈው ባለንበት ዘመን አንድን ሕዝባዊ ትግል ከግቡ ለማድረስ የሚያስፈልጉትን ሦስት የተያያዙ ነገሮች ከሃገሪቱ ተጨባጭ ሁኔታ ጋር አዛምዶ ከሥራ ላይ ማዋል በመቻሉ ነው። ሌላ ተአምር የለውም።
የኛም ሪቮሉሽን ፊውዳሊዝምንና ኢምፔሪያሊዝምን ደምስሶ ነፃ ኢትዮጵያ ለማቋቋም ይህንን ፍቱን የሆነ ዘዴ ከሃገራችን ታሪካዊና ጊዚያዊ ሁኔታ ጋር አዛምዶ ሥራ ላይ ከማዋል ሌላ መንገድ ሊከተል አይችልም። የኢትዮጵያ ሰፊ ሕዝብ ከጀግናዋ ቪየትናም ትግል የሚያገኛቸው ትምህርቶች በሁለት ዋና ዋና ክፍሎች ሊመደቡ ይችላሉ። አንደኛው አረመኔውን የአሜሪካ ኢምፔሪያሊዝም የሚመለከት ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ትግሉ እንዲቀጥል መወሰድ ያለባቸውን እርምጃ የሚመለከት ነው።
የአሜሪካ ኢምፔሪያሊዝምን በሚመለከተው በኩል የሚገኙትን ትምህርቶች በሶሶት ዋና ሃቆች ልናጠቃልለው እንችላለን።
አንደኛ፡ የአሜሪካ ኢምፔሪያሊዝም ዛሬም ሆነ በመላ ዓለም ታሪክ ምንም አይነት ተወዳዳሪነት የሌለው ጨካኝና አረመኔ አውሬ ነው። ጅብ የማያውቁት አገር ሄዶ ቁርበት አንጥፉልኝ ይላል። ቪየትናምን ያየ ከዚህ አውሬ ጋር አይዋዛም። ሙሶሎኒ በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ አምስት አመት ሙሉ የፊፀመውን በደል የአሜሪካ ኢምፔሪያሊዝም በቪየትናም ሕዝብ ላይ ሃያ አመት ሙሉ እጥፍ ድርብ አድርጐ ፈጽሞታል። ፋሽስት ጣሊያን በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ እንደፈፀመችው ሁሉ አሜሪካኖችም ቤት እየዘጉ፣ ቤንዚን እያርከፈከፉ ሰላማዊ ሕዝብ በእሳት ጨርሰዋል፣ እርጉዞችን በሳንጃ እየወጉ ገድለዋል፣ አርበኞችን ከተራቡ ነብሮች ጉድጓድ ጨምረዋል፣ በአንዳንድ መንደሮች (ለምሳሌ በማይ ላይ/ በመንደሩ ያለውን ሰው በሙሉ አሰልፈው ለዘር እንኳን እንዳይቀር እያደረጉ ረሽነዋል፤ የአርበኞች፣ የሴቶች፣ የህፃናት አንገት እየቆረጡ ፎቶግራፉን ጣልያኖች እዚህ ያደርጉ እንደ ነበረው፣ ‘ለመታሰቢያ እያሉ’ ለወዳጆቻቸው ወደ አገራቸው ልከዋል፤ አይን የሚያጠፋ፣ ሰውነት የሚጠብስና የሚያቃጥል ጋዝ በቪየትናም ሕዝብ ላይ አፍስሰውበታል፤ በወደቀበት አካባቢ ያለውን አየር በሙሉ በመምጠጥ ሰውን ሁሉ ትንፋሽ አሳጥቶ አፍኖ በሚገድል ቦምብ ተጠቅመዋል። በታህሳስ 1965 ዓ.ም. በአራት ቀናት ውስጥ ብቻ በሃኖይና በአካባቢዋ የተጣለው ቦምብ ፋሽስት ጀርመን በሁለተኛው ዓለም ጦርነት በእንግሊዝ አገር ላይ የጣለችውን የሚስተካከል መሆኑ ተገምቷል። በነዚህና እነዚህን በመሳሰሉ ድርጊቶች የተነሳ ከመላው ዓለም የተውጣጡ ሽማግሌዎች በስዊድን አገር ለዚሁ ጉዳይ ባቋቋሙት ‘የበርትራንድ ራስል የፍርድ ሸንጐ’ ይህ ሁሉ ‘በመላ የሰው ዘር ላይ የተፈፀመ ወንጀል’ ነው በማለት በተጨባጭ መረጃዎች ላይ ተመርኩዘው ፍርዳቸውን ሰጥተዋል።
ሁለተኛ፡ የአሜሪካ ኢምፔሪያሊዝም የተኩላ ባህታዊ ነው። ትናንትና ሙሶሎኒ ሲገባ እወራለሁ ብሎ አይደለም፣ አገር አሰለጥናለሁ ብሎ ነበር። ዛሬ የአሜሪካ ኢምፔሪያሊዝም እኛ አገር እንደገባው ትናንትናም ቪየትናም ሲገባ አሰለጥናለሁ ብሎ ነበር። በሜይ ዴይ በዓል ላይ ተይዘው ከነበሩት ሰሌዳዎች አንዱ የመላ ኢትዮጵያን ሕዝብ ድምጽ የሚያስተጋባ ነው፣ ‘የአሜሪካ ወዳጅነትና እርዳታ በአፍንጫችን ይውጣ’ የሚል ነው። እስኪነቃበትና እስኪጋለጥ ድረስ የአሜሪካ ኢምፔሪያሊዝም የስውር ወረራውን የሚያካሄድባቸው፣ እኛ አገር ጨርሶ ገና ያልተጋለጡ፣ በቪየትናም ግን ተጋልጠው ያበቃላቸው መሰርሰሪያ ዘዴዎቹ ከአሸዋ የበዙ ናቸው። ስመ ጥፉው ማግ የሚሉት የጦር ድርጅት፣ የጦር አማካሪዎች፣ በየባላገሩ የሚላኩ ሚስዩናውያን፣ ወደሕዝቡ የሚሰረስሩ የበጐ አድራጐት ወኪሎች፣ ‘ለምርምር፣ ለጥናት፣ እንዲሁም ለማስተማር’ እያሉ በየዩኒቨርሲቲውና በየመፃህፍት ቤቱ የሚሰሩ ሰላይ ምሁራን፣ የካርታ ማንሻ ድርጅቶች፣ በየመስሪያ ቤቱ በአማካሪነት የተቀመጡ ‘አዋቂዎች’ እነዚህ ሁሉ እስኪጋለጡ ድረስ ሰላማዊ መሰርሰሪያዎች፡ ሲጋለጡ ደግሞ እንደአበደ ውሻ የሚክለፈለፉ ተናካሽ አውሬዎች መሆናቸውን ያለፉት 2ዐ ዓመታት የቪየትናም ሕዝብ ፈተና አበጥሮ ያሳያል።
ሶስተኛው ትምህርት ደግሞ የአሜሪካ ኢምፔሪያሊዝም ይሸነፋል የሚል ነው። የኢምፔሪያሊዝምን ጠባይ ጠንቅቀው ለተረዱ የበሰበሰና ለመሞት የሚያጣጥር ካፒታሊዝም መሆኑን ለሚያውቁ ሁሉ ይህ አዲስ ነገር አይሆንባቸውም። የአሜሪካ ኢምፔሪያሊዝም በቪየትናም ላይ ይህንን ሁሉ በደል የፈፀመው የዚህን ሕዝብ ትግል ደምስሶ የማይደፈር ለመምሰል፣ ቪየትናምን ለዓለም ሕዝብ መቀጣጫ ለማድረግ ነበር። የተቀጣው እርሱ ሆነ። ይህንን ሁሉ ውርደት ተከናንቦ ሲወጣ መሰረታዊ ደካማነቱ ታየበት። የቪየትናም ሕዝብ እንዳሸነፈው ሌሎችም የዓለም ጭቁን ሕዝቦች ያሸንፉታል። በተለይ ደግሞ በታሪኩ የወራሪዎችን ሙከራ ደጋግሞ እያከሸፈ በመላ ዓለም ፊት አድናቆት ያተረፈው ጀግናው የኢትዮጵያ ሕዝብ የአሜሪካ ኢምፔሪያሊዝም ከሃገሩ ጠራርጐ እንደሚያወጣው ፈጽሞ አንጠራጠርም። እንዴት ለሚለው ጠያቂም የቪየትናም ሕዝብ ትግል ያረጋገጠልንን ትክክለኛ መንገድ መከተል ብቻ ነው እንላለን።
በያዝነው ክፍለ ዘመን የታዩት አብዮቶች ያረጋገጡት ሃቅ ዛሬ በአይናችን ስር በመታየት ላይ ነው። በአሁኑ ወቅት ፊውዳሊዝምንና ኢምፔሪያሊዝምን ደምስሶ ትግሉን ከዳር ሊያደርሰው የሚችል አመራር የሠራተኛው አመራር ብቻ ነው። በተሰበጣጠሩ ታሪካዊ ምክንያቶች በትግሉ መጀመሪያ ላይ በግንባር ቀደምነት ሊመራ የሚችለው የንኡስ ከበርቴ መደብ በበዝባዥና በተበዝባዥ መደቦች መካከል የሚፋፋመው ትግል ሲያሸብረው ይዋልላል፣ ትግሉ ከደረሰበት ቦታ ወደፊት እንዳይራመድ መፍጨርጨር ይጀምራል፣ ከያለበት ተቀስቅሶ በየአቅጣጫው እየቀደመው የሚሄደውን ትግል ለመግታት መልሶ ከአድሃሪ ሃይሎች ጋር፡ በተለይም ከሕዝቡ ደመኛ ጠላቶች ከኢምፔሪያሊስቶች ጋር መዋዛትና መታረቅ ይሞክራል።
ለተወሰነ ጊዜ ከሕዝቡ ጐን ተሰልፎ ይራመድ የነበረው ደርግ ዛሬ ታሪክ እየቀደመው ስለሄደ ከትግሉ ኋላ ቱስ ቱስ በማለት ላይ ነው። መምራት ተስኖት ለመግታት የሚፈልገውን የኢትዮጵያን ሰፊ ሕዝብ የነፃነት ትግል ወደፊት እንዳይቀጥል ፍቱን የሆኑትን የትግል ዘዴዎች አፍኖ ይዞ ይታያል።
ኢምፔሪያሊስቶችና በያለበት የሰካኳቸው ወኪሎቻቸው የኢትዮጵያን ሕዝብ ትግል ለመቀልበስ ሴራ እየደጋገሙ በመምታት ላይ መሆናቸውን እናውቃለን። ከእለት እለት በአድሃሪ ሃይሎች እየተመሰጠ የሚሄደው ደርግ በነዚህ ፀረሕዝቦች ላይ ጥብቅ እርምጃ በመውሰድ ፈንታ እንዲያውም የአሜሪካ ኢምፔሪያሊስቶች ስም በክፉ እንዳይነሳ ከልክሏል። ሕዝቡን የማስተማርና የማንቃት፡ ጠላቶቹን እየጠቆሙ የማሳየት ኃላፊነት ያላቸው ጋዜጦችና ሬዲዩ በዚህ በማጋለጥ ተግባር እንዳይሳተፉ ተከልክለዋል።
የዛሬ አራት አምስት ወር እንኳን ይደረግ የነበረውን ያህል ፀረኢምፔሪያሊስት ኘሮፖጋንዳ ዛሬ ማድረግ አይቻልም። አድሃሪዎችና የኢምፔሪያሊስቶቹ ወኪሎች ቦታ ቦታ ለመያዝ ባደረጉት ትግል ጊዚያዊ ድል ስላገኙ ቡችሎቻቸው እነበአሉ ግርማ ‘የዜና አገልግሎት’ የመሳሰለውን ቁልፍ ቦታ እንዲይዙ አድርገዋል።
የሰፊውን ሕዝብ ትግል በማደራጀትም በኩል ደርጉ ከንኡስ ከበርቴው መደባዊ ጥቅም ሌላ ምንም አይነት ምክንያት የማይገኝለት ፖለቲካ እኝኝ ብሎ ይዟል። የንኡስ ከበርቴው ጥቅም ምንድነው? የሱ ጥቅም ትግሉ አሁን ካለበት ደረጃ ባያልፍ ነው። በአሁኑ ደረጃ ደግሞ የሰፊው ሕዝብ ጥቅም በምንም አይነት ቋሚ ዋስትና የለውም። ይህ ከተፈለገ ሕዝቡ ራሱ ተደራጅቶ ትግሉን ከግቡ ማድረስ አለበት። ከተደራጀ ግን ትግሉ ወደ ድል ያመራል ማለት ነው። ወደ ድል ካመራ ደግሞ የፊውዳሊዝምና የኢምፔሪያሊዝም ጭቆና በሌላ አይነት ጭቆና አይተካም። ንኡስ ከበርቴውም ሊዘረጋ የሚፈልገው ሥርዓት በትግሉ ማእበል ተጠራርጐ ይደመሰሳል ማለት ነው። የደርጉ ንኡስ ከበርቴዎች ይህንን ፍራቻ ለመሸፈን፡ ትግሉ ይቀጥል የሚላቸዉን ሁሉ ደስ ሲላቸው ‘አለቅጥ ተራማጅ’ ይሉታል፣ ሲያሰኛቸው ደግሞ እስከናካቴው ‘አድሃሪ’ እያሉ ያወግዙታል።
በሌላ በኩል ደግሞ ትግሉ እንዲቀጥል የግድ አስፈላጊ የሆኑት እርምጃዎች እንዳይወሰዱ አፍነው ይዘዋል። የሠራተኛ መደብ ፖርቲ ለትግሉ መቀጠል እንደሕይወት እስትንፋስ ያስፈልገዋል። ንኡስ ከበርቴው ወዝአደሩን እንኳን በከፍተኛ በፖርቲ ደረጃ ሲደራጅ ዝም ሊለው ይቅርና ‘የሞያ ማህበርም እንኳን በዝቶብሃል’ ብሎ በአዋጅ ማህበሩን ያፈርሳል። ዛሬ የሪቮሉሽኑ ደጋፊዎች ተብለው የሚገመቱት ሃይሎች ሁሉ በየፖርቲዎቻቸውና በየድርጅቶቻቸው አማካይነት ከትግሉ በሙሉ ልብ መሳተፍ ሲገባቸው እንዳይደራጁ፣ እንዳይናገሩ፣ እንዳይጽፉ፣ እንዳይሰበሰቡ ተከልክለው ትግሉ እጅግ የተበታተነ መልክ እንደያዘ ይገኛል። ይህም በበኩላቸው ባስደናቂ ፍጥነት በመሰብሰብና በመደራጀት ላይ ላሉት አድሃሪ ሃይሎች እጅግ አመቺ የሆነ ሁኔታ መፍጠሩን እናያለን።
ይህንን ሁሉ እየተመለከተ ደርጉ አስፈላጊዎቹን እርምጃዎች ባይወስድ መደባዊ ጥቅሙ አሸንፎ አብዩቱ እንዳይቀጥል ፍላጐት ስላደረበት ነው። ስለዚህም ዛሬ የድላችን ፍቱን ዘዴዎች ማለትም የሠራተኛው ፖርቲ እንዳይቋቋም፣ ሌሎች ፀረፊውዳልና ፀረኢምፔሪያሊስት ሃይሎች በአንድ ሕዝባዊ ግንባር ስር እንዳይተባበሩ፣ አድሃሪዎች እንዳይደመሰሱ አስፈላጊው ሕዝባዊ ጦር እንዳይቆም ጥረት የሚያደርጉ ሁሉ ትግሉን ለመቅጨት የሚፈልጉ፡ ታሪክ አልፏቸው የሄደ ኃይሎች ብቻ ናቸው።
ይህንንም ብንል የአንድ መደብ ታሪካዊ የአመራር ሚና ስላከተመ ብቻ የኢትዮጵያ ሕዝብ አብዮት አብሮ አከተመ ማለት አይደለም፣ ይህን የሚያደርግበት ምክንያት የለም። አብዮታውያን ይህንን ሃቅ ተገንዝበው በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በማፋፋም ላይ ያሉትን ለዲሞክራሲያዊ መብቶች የሚያደርገውን ተጋድሎ በቆራጥነት መቀጠል አለባቸው።የሠራተኛው ፖርቲ መደራጀት አለበት። ሌሎችም ተራማጅ መደቦችና የህብረተሰቡ ክፍሎች በመሰላቸው መደራጀት አለባቸው። በተጨማሪ ደግሞ የማንም አብዮት ታሪክ ደጋጋሞ ያሳየን ሃቅ አለ። አድሃሪዎች በአዋጅ ‘በቃችሁ’ ስለተባሉ ብቻ እጅ ነስተው ከታሪክ መድረክ የወረዱበት ጊዜ የለም። ሪቮሉሽኑን (ይኸው ባገራችን እንደምናየው) በሴራና በመሳሪያ ኃይል ለማጥፋት ይሞክራሉ። እንደዚህ ሲሆን ደግሞ ለአድሃሪዎች ፀረ ሕዝብ አመጽ ያለው አንድ መፍትሄ የነቃና የተደራጀ ሕዝባዊ ጦር ብቻ ነው። ይህንን ችላ ማለት ለአድሃሪዎች ፊት መስጠትና ትግሉን ማደናቀፍ ነው። የቪየትናም ሕዝብ ድል የሚያስተምረን ይህንንም ሃቅ ጭምር ነው።
[1] የቀኑ አቆጣጠር እንደ ኢትዮጵያ አቆጣጠር ነው።