ሰሕድ ቁ. 28

የሰፊው ሕዝብ ድምፅ

ቁጥር 28፣     ሰኔ 22፣ 1967 

የፅሁፉ ፍሬ ሀሳብ

መኢሶን በዚህ የሰፊው ሕዝብ ድምፅ እትሙ፣ የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮት ከተጀመረ አንድ ዓመት እድሜ የያዘ እንደሆነ አስታውሶ፤ በዚህ ጊዜው ውስጥ ሕዝቡ በርካታ ትምህርቶችን እንደቀሰመ ያስገነዝባል። በዚህም ምክንያት፣ትግሉ ይበልጥ ወደፊት እንዲገፋና ተጨማሪ ድሎች እንዲቀዳጅ ተስፋ የሚያስጨብጥ ሁኔታ ላይ አገሪቷ እንደምትገኝ ይገልጻል። ስለዚህም፣ የኢትዮጵያ ተራማጆች ሁሉ የአገሪቱን ተጨባጭ ሁኔታዎች አጥንተው፤ አጣዳፊ ተግባሮቻቸውን ለይተውና ተረድተው ትግሉ ወደፊት እንዲገፋ ትግላቸውን መቀጠል እንደሚገባቸው ጥሪ ያደርጋል።  

የሰፊው ሕዝብ ድምፅ

ለሰፊው ሕዝብ ሰራተኛ ገበሬ፣ ነጋዴ፣ ወታደር፣ ምሁር መብትና ጥቅም የሚታገል ጋዜጣ

የኢትዮጵያ ሰፊ ሕዝብ ይቅደም

 
ቁጥር 28                                                                     ቀን 22/10/67

 

አብዮቱ እንዲገፋ

አገራችን እጅግ ከፍተኛ የሆነ አብዮታዊ እንቅስቃሴ ውስጥ ከገባች እንሆ ዓመት ተኩል ሊሆናት ነው። በዚህ አጭር ጊዜ ውስጥ ሰፊው የኢትዮጵያ ሕዝብ ለዘመናት የማይገኙ ጠቃሚ ትምህርቶችን በትግሉ ውስጥ ቀስሟል። እጅግ መራራና ረዥም ትግል ገና ወደፊት ቢጠብቀንም ዛሬ የኢትዮጵያ አብዮት የወደፊት እድል ከፀሐይ ደርቶ የሚታይበት ወቅት ነው። ከዚህ ሁኔታ ተነስተን አብዮቱ ወደፊት የሚገፋበትን ዘዴ መመልከትና ማመልከት የተራማጆች ሁሉ ግዴታ ነው ብለን እናምናለን።

ዛሬ 1967 ዓ.ም የኢትዮጵያ ተራማጆች ምን ምን አጣዳፊ ተግባሮች እንዳሉብን ለማየት በቅድሚያ አገራችን በታሪክ እርምጃ ጎዳና ላይ የት እንደደረሰች ባጠቃላይ መጠቆም ተገቢ ነው። በዚህ ጎዳና ላይ የምንገኝበትን ምዕራፍ ለይተን ካላወቅን የመደቦችን አሰላለፍ መመልከትና ወዳጅን ከጠላት ለይቶ አቢዮቱን ወደፊት ማራመድ አይቻልም።

ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ከፊል ፊውዳላዊ ከፊል እጅ አዙር ቅኝ አገዛዝ የተጫናት፣ የሕዝቦችዋ ደህንነት፡ ነጻነት፡ እርምጃ …. በነዚህ ጥንድ ጠላቶች ታፍኖ የተያዘባት ሀገር ነች። በያዝነው ዘመን እንደ ኢትዮጵያ ባሉት ሀገሮች የሚደረገውና ሊደረግ የሚችለው አቢዮት በወዝአደሩ መደብ የሚመራው አዲሱ ዲሞክራቲክ አብዮት ነው። ይህ አብዮት ፊውዳሊዝምና ኢምፔሪያሊዝም ከምድረ ኢትዮጵያ ጠፍተው (ተደምሰው) አዲሱ ዲሞክራቲክ ስርዓት የሚመሰረትበት፡ ለሶሻሊስት ስርዓት መንገድ የሚጠረግበት፡ የዓለም ሶሻሊስት አብዮት የማይነጠል አካል የሆነ አብዮት ነው።

እንግዲህ ወደዚህ አብዮታዊ ግብ በመጓዝ ላይ እያለን ተጨባጩን የኢትዮጵያ ሁኔታ በምንመለከትበት ጊዜ ሁኔታው እጅግ የተወሳሰበ ሆኖ እናገኘዋለን። የአገሪቱን ሁኔታ ከመደቦች አሰላለፍ አንፃር ብናየው ይህ የተወሳሰበ መልክ ቁልጭ ብሎ ይታየናል። በአንድ በኩል የዚህ አብዮት ደጋፊዎች ሊሆኑ የሚችሉት ኃይሎች በሙሉ በትብብር ሊሰለፉ አልቻሉም። አጋዥ ሊሆኑ የሚችሉት አብዛኛው ንኡስ ከበርቴና ኢመንት ኃይል ብትኖረውም ከሕዝቡ ጎን መሰለፍ የሚችለው የብሔራዊ ከበርቴው ፀረፊውዳልና ፀረኢምፔሪያሊስት ክንፍ ጨርሰው ከአድሃሪዎቹ መደቦች ጋር ተደባልው ይገኛሉ። ይህም በተለይ ደግሞ ከከተሞች የአብዮቱን ኃይሎች አዳክሞ የፀረአብዮቱን ሰፈር አዳብሮታል። በሌላ በኩል ደግሞ ቁርጠኛ የሆኑት የአብዮቱ ደጋፊዎች (ወዛደሩና ሌሎችም አብዮታዊ የህብረተሰብ ክፍሎች…) ዲሞክራሲያዊ መብቶቻቸው ታፍነው መደራጀት ባለመቻላቸው አብዮቱ በተለይ በከተሞች ደረቱን ለጠላቶቹ አጋፍጦ የሰጠበት አስጊ ሁኔታ አለ። ከዚህም በተጨማሪ ከቀድሞ አገዛዝም ጋር ሆነ ዛሬ ከሚፍጨረጨሩት አድሃሪዎች ጋር በጥቅም በመያያዝ አብዮቱ ላይ ከማሴር በማይታክቱት አሜሪካኖች ላይ ቁርጥ ያለ ፀረኢምፔሪያሊስት አቋም በመንግሥቱ አልተወሰደም። እንዲያውም ሰፊው ሕዝብ ተገቢ የሆነ ፅረኢምፔሪያሊስት ትምህርት ቀስሞ ለብሄራዊ ነፃነቱ እንዳይታገል የአሜሪካን ኢምፔሪያሊስቶችን ስም በምንም ዓይነት በክፉ እንዳይነሳ ተከልክሏል።

ባጭሩ፡ የአብዮቱ ደጋፊዎች በወጉ አልተሰበሰቡም፣ በወጉ አልተደራጁም። ወላዋይ መደቦችና የህብረተሰቡ ክፍሎች ጨረሰው ከጠላት ተደባልቀዋል። የአብዮቱ ጠላቶች መበተን መዳከም ሲገባቸው እየተደራጁና እየተጠናከሩ በመሄድ ላይ ናቸው። አጠቃላይ ስእሉ ይህ ቢሆንም ጠጋ ብሎ ለሚመለከተው ሰው በባላገርና በከተማ ፈጽሞ የተለያዩ ሁኔታዎች ይታያሉ። ባላገሩ እነዚህን እንቅፋቶች በኃይልና በትግል እየተወጣ ዛሬ ገጠሪቱ ኢትዮጵያ (በተለይ በደቡብና በምስራቅ) በአብዮታዊ ማእበል በመጥለቅለቅ ላይ ትገኛለች። በተሰበጣጠሩ ምክንያቶች፡ በተለይም በዲሞክራሲ መብቶች መታፈንና በመንግሥቱ አድሃሪ ተጽዕኖ የተነሳ በከተማ አብዮቱ እነዚህን እንቅፋቶች ለመወጣት የገጠሩን ያህል ፍጥነት አያሳይም። ይህ የተዛባ ሁኔታ በባላገር የተራወጡትን አድሃሪ ኃይሎች ከተሞች ፋታ አንዲሰጧቸውና የአድሃሪ ሴራቸው መጠንሰሻ መድረኮች እንዲሆኑ አድርጓቸዋል።

ይህ ከሆነ በአሁኑ ወቅት የተራማጆች ጥረት በሁለት አቅጣጫዎች መካሄድ አለበት። በባላገሩ ተራማጆች ኃይላቸውን አስተባብረው አብዮታዊው ማእበል በምንም አይነት ገብ እንዳይል፡ እንዲቀጥል፡ አቅጣጫ እያሳዩ መታገል አለባቸው። በከተሞች ደግሞ የአድሃዎች ሴራ የሚከሽፍበትን ሁኔታ እያጠኑ በዚሁ አቅጣጫ በህብረት መታገል አለባቸው።

I

በገጠር በኩል ኢትዮጵያ ዛሬ ለአብዮታዊ ትግል ያመቸች ምድር ሆናለች። ለብዙ ዘመናት ቦግ እልም እያለ  ሲካሄድ የነበረው የተበዝባዥ ገበሬዎች ትግል ዛሬ በአብዮታዊ ማእበል አገሪቱን በማጥለቅለቅ ላይ ይገኛል። በተለይ የገጠርን መሬት የሕዝብ ለማድረግ የወጣው አዋጅ በአገሪቱ ያለውን የመደቦች አሰላለፍ የጠራና ቁርጥ ያለ መልክ ሰጥቶታል። ይህ አዋጅ የመደቦችን ትግል ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ አክርሮትና አፋፍሞት እናያለን። ከዚህ አዋጅ በኋላ መሬት ከፍ ብትል ሰማይ ዝቅ ቢል ኢትዮጵያ የቀድሞይቱ ኢትዮጵያ አትሆንም። የየካቲት 25 አዋጅ ለኢትዮጵያ  አብዮት አዲስ የህይወት አስትንፋስና የተጣራ የትግል ዓላማ ሰጥቶታል። በኢትዮጵያ ገበሬዎች ልብ ግቡን ሳይመታ በምንም አይነት የማይጠፋ አብዮታዊ ቋያ ቀስቅሷል።

ይህንን አዋጅ ሙሉ በሙሉ ከስራ ላይ ለማዋል የሚደረገው ተጋድሎ ከኢትዮጵያ ምድር  ፊውዳሊዝምና ኢምፔሪያሊዝም ድምጥማጣቸው ሳይጠፋና ሕዝባዊ ዲሞክራሲያዊ አገዛዝ ሳይቋቋም በምንም ዓይነት ገብ አይልም። በኛ እምነት ይህንን አዋጅ ከስራ ላይ ለማዋል ዛሬ መሬት ላራሹ በሚለው መፈክር ስር የተሰለፈው በሚሊዮን የሚቆጠረው ገበሬ ቀስ በቀስ በትግሉ ውስጥና ለትግሉ መቀጠል ሲል ነጻነት ላራሹ በሚለው መፈክር ስር የግድ መሰለፍ ይኖርበታል። ይህ  ‘ነፃነት ላራሹ’ የሚለው መፈክር ደግሞ ሌላ ምንም ነገር ሳይሆን የኢትዮጵያ አርሶአደር ‘መሬት ላራሹን’ የሚፃረሩበትን የቀድሞ ስርዓት የመንግሥት አውታሮች ሰባብሮና ደምስሶ በትግል ውስጥ የራሱን ሕዝባዊ ዲሞክራሲያዊ አገዛዝ የሚመሰርትበት መሳሪያ ነው።

የኢትዮጵያ ተራማጆች ከዚህ በፊት ‘መሬት ላራሹ’ የሚለውን መፈክር በግንባር ቀደምነት አንስተው ለሰፊው ገበሬ የትግል አቅጣጫ አሳይተዋል። ከእንግዲህ ደግሞ መሬት ያለነፃነት እርም መሆኑን ለአራሹ ገበሬ በቅድሚያ ማመልከትና በዚህ ነፃነት ደግሞ የአድሃሪውን ስርዓት የመንግሥት አውታሮች ደምስሶ የራሱን አገዛዝ ለመመስረት መታገል እንዳለበት ከትግሉ ተዋህደው ሊያስተምሩት ይገባል።

ይህ እንዴት እንደሚሆን ለመረዳት ከአዋጁ በተጨማሪ ይህንን አብዮታዊ ማዕበል ለማስነሳት የረዱትን ነገሮች መመልከት ያስፈልጋል። በገጠር ዛሬ ይህንን አብዮታዊ ሁኔታ አዋጁ ብቻውን አልፈጠረውም። በቅድሚያ በባላገር የዘማቾች መገኘት የፈጠረው አብዮታዊ ‘ዳይናሚክስ’ መታየት አለበት። ከአስር ዓመታት በፊት ጀምሮ ‘መሬት ላራሹ’ በሚል መፈክር ሲሰዋ፡ ሲገረፍ፡ ሲታሰር፡ ሲሰቃይ የነበረው ወጣቱ የኢትዮጵያ ትውልድ ዛሬ በግንባር ቀደም ዘማቾች አማካኝነት ከደሀው ገበሬ ተዋህዷል። በአሁኑ ጊዜ የዘማቾች ከገበሬው ጎን መገኘት የፈጠረውን አብዮታዊ ማዕበል ስንመለከት ይህ አዋጅ የወጣት ተማሪዎች የቅስቀሳና የማደራጀት ተጋድሎ ባይጨመርበት ኑሮ አሁን ከምንገኝበት ከፍተኛ ደረጃ ምን ያህል ወደኋላ እንቀር እንደነበር ለመገመት አያዳግትም። ከእነዚህ አብዮታዊ ዘማቾች ጎንም ተራማጅ የመሬት ይዞታ ሰራተኞች፡ እንደዚሁም አንዳንድ የሕዝቡን ወገን ያቀፉ ተራማጅ አስተዳዳሪዎች መኖራቸው አብዮታዊውን ማዕበል ለመፍጠር የረዳ መሆኑን የሚጠራጠር የለም።

የነዚህ ልዩ ልዩ ሁኔታዎች ህብረት የፈጠረው አብዮታዊ ማዕበል ተጠራቅሞና ተቀነባብሮ መልክ የሚያገኘው በገበሬዎች ማህበር አማካኝነት ነው። የገበሬዎች ማህበራትን ጉዳይ በሁለት አንጻር መመልከት ያስፈልጋል። ማህበሮቹ የተቋቋሙት አዋጁን በስራ ላይ ለመዋል ሲሆን መደባዊ ይዘታቸውና (የቀድሞ ከፍተኛ ባለርስልቶች አይገቡባቸውም) ዓላማቸው የፊውዳል ኢትዮጵያ መደምሰሻ መሳርያ ያደርጋቸዋል። እነዚህ ማህበራት እንደተራ ‘የሙያ ማህበራት’ መታየት የለባቸውም። ባለው ስርዓት ውስጥ የጢሰኛውን የኑሮ ሁኔታ ለማሻሻል ሳይሆን ጢሰኝነትን ጨርሶ ለማጥፋት የሚታገሉ አብዮታዊ አካላት ናቸው። እነዚህን ማህበራት የፊውዳሊዝም መደምሰሻ መሳሪያዎች ብቻ አድርጎ መመልከት አይቻልም። አገራችን ከዚህ ረዥም የትግል ድብልቅልቅና ውሽንፍር ፊውዳሊዝምንና ኢምፔሪያሊዝምን በሕዝባዊ ኃይል ደምስሳ ብቅ ስትል ለሚጸድቀው ሕዝባዊ ዲሞክራሲያዊ አገዛዝ ጽኑ መሠረትና ተሸካሚ አውታሮች ሆነው ከትግሉ ውስጥ ብቅ የሚሉት እነዚህ አብዮታዊ ማህበራት ናቸው። ባጭሩ ዛሬ የኢትዮጵያን ገጠር በማጥለቅለቅ ላይ ያሉት የገበሬዎች ማህበራት የአድሃሪው ስርዓት ቀባሪዎች ብቻ አይደሉም፤ የአዲሲቱ ኢትዮጵያችን ጥንስስ ኃይሎችም ናቸው እንጂ።

ይህንን ለመገንዘብ ብዙም የሚያዳግት አይመስለንም። በመጀመሪያ ደረጃ ልክ በአዋጁ መሰረት መደባዊ ጥራታቸውን ይዘውና ዓላማቸውን ተከትለው ቢሠሩ እንኳን እነዚህ ማህበራት መሬትን ከባለርስት ነጥቀው ለአራሹ በይዞታ ለመስጠት ሆን ብለው የተደራጁ በመሆናቸው የኢትዮጵያን ፊውዳል ስርአት ጨርሰው ሳይደምስሱ እንደማይገቱ ግልጽ ነው።

ልብ ላላለው ሰው የማይታየው እነዚህ ማህበራት ለተጠቀሰው ዓላማ ሲታገሉ ትግሉ ራሱ የሚፈጥራቸውን ሌሎች ትግሎችና አቅጣጫዎች እንደሚወለዱ ነው። በአዋጁ መሰረት ተደራጅተው ሲታገሉ እነዚህ ማህበራት የግድ የአዋጁን ወሰን በጣጥሰው፣ አዋጁ ከሚሰጣቸው መብት አልፈው የአብዮታዊ ሕዝባዊ ስልጣን አውታሮች ለመሆን ይገደዳሉ። ይገደዳሉ የምንለው አውቀን ነው። የኢትዮጵያ ገበሬዎች ‘መሬት ላራሹ’ በሚለው መፈክር ተሰልፈው ሲታገሉ መሬት ለማግኘት ስልጣንን ከአድሃሪዉ ስርዓት መንጠቅ እንዳለባቸው ይረዱታል። ገበሬዎች በየአካባቢያቸው የሚገኙትን የቀድሞውን ስርአት የመንግሥት ስልጣን አውታሮች ሰባብሮ ስልጣን እጃቸው ካላስገቡ ትግሉ ወደፊት ሊገፋ እንደማይችል ይረዱታል። ለአድሃዎች የሚታዘዘው የመንግሥት ስልጣን መኪና ለአዋጁ እንቅፋት ከመሆን አልፎ እነሱ ካላጠፉት እሱ ሊያጠፋቸው እንደሚሞክር፣ እነሱ ካልተኩት እሱ ሊተካቸው እንደሚሞክር በትግል ውስጥ ይማሩታል።

የሌሎችን አብዮቶች ታሪክ ብናይ ሰፊው ገበሬ ለመሬቱ የሚያደርገው ተጋድሎ ዞሮ ዞሮ ለነፃነትና ለዴሞክራሲ ከሚያደርገው ተጋድሎ ያልገጠመበት አብዮት የለም። ‘መሬት ላራሹ’ የሚለው መፈክር በርግጥ በስራ ላይ ባዋለበት ስፍራ ሁሉ የሕዝቡ ትግል ‘ነፃነት ላራሹ’ በሚለው መፈክር ስርም ተሰልፎ ታይቷል። እርግጥ መጀመሪያ ላይ ራሱ ኑሩው፡ ብዝበዛው፡ ጭቆናው ወጥሮ ይዞታልና፣ የመሬት ጥማት አቃጥሎታልና ሰፊውን ገበሬ ሊያንቀሳቅሰው የሚችለው መሬት ላራሹ የሚለው መፈክር ብቻውን ሊሆን ይችላል። ነገር ግን መሬቱን ከአድሃሪ ኃይሎች ነጥቆ ለመውሰድ የሚደረገው ትግል እያየለ ሲሄድ ሰፊው አርሶ በሌ መሬት የጠማውን ያህል ነፃነትና ዲሞክራሲ ለትግሉ እንደ ህይወት እስትንፋስ አስፈላጊ መሆናቸውን ይገነዘባል።

ይህ ‘ነጻነት ላራሹ’ የሚባለው መፈክር ምን ይዘት አለው? ሰፊው ገበሬስ በትግሉ አፍላ ውስጥ የዚህን ነጻነት ጠቃሚነት ተገንዝቦ በዚህ መፈክር ስር ይሰለፋል የሚባለውስ እንዴት ነው?

ታላቁ ሌኒን በመሬት ጉዳይ ሰፊው ገበሬ ያስፈልጉታል ብሎ የገመታቸውን ነጻነቶች በሦስት ከፍሎ የዘረዘራቸው ሲሆን ዋና ዋና ሃሳቦቹ ሲጠቃለሉ እንደሚከተለው ሊታዩ ይችላሉ፡-

    1. ሰፊው ሕዝብ ለጋራ ጉዳይ አስፈላጊ የሆኑትን አስተዳዳሪዎችና የመንግሥት ባለስልጣኖች በሙሉ ከሕዝባዊ ምርጫ የማፍለቅ ሙሉ መብት ሊኖረው ይገባል።
    2. በሕዝብ ፊት ኃላፊነት የሌለው፣ በሕዝብ ያልተመረጠ፣ ለሕዝብ ተጠያቂ ያልሆነና አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ በሕዝቡ ሊሻር የማይችል መንግሥታዊ አስተዳደር ሙሉ በሙሉ መደምስስ አለበት።
    3. አስተዳዳሪዎች በሕዝብ የሚታዘዙ መሆን አለባቸው እንጂ ሕዝቡ ያስተዳዳሪዎች ታዛዥና መሳሪያ መሆን የለበትም።

ከዚህም በማያያዝ ይህንን ነፃነት ሕዝቡ በገዢዎች ወይም ደግሞ በአንዳንድ ግለሰቦች መልካም ፍቃድ የማያገኘው መሆኑ የታወቀ ስለሆነ ‘ነጻነት ላራሹ’ የሚለው መፈክር ከስራ ላይ የሚውለው በሕዝባዊ ጦር ተመርኩዞ እንደሆነ ሌኒን ያስተምረናል። ይህንን ሁሉ ተራማጆች በሙሉ ያቁታል። ሰፊው ገበሬ ግን እነዚህን ሃቆች የሚገነዘባቸው ተራማጆች በሚያደርጉት ቅስቀሳ ብቻ ሳይሆን ከአድሃዎች ጋር በሚያደርገው ተጋድሎ ከሚያገኘው ትምህርትም ነው።

ዛሬ በአገራችን በአይናችን ስር የምናየው ይህንኑ ሃቅ ነው። ሰፊው ገበሬ መሬት ላራሹ በሚለው መፈክር ተሰልፎ ሲታገል ከአድሃዎቹ ጋር ብቻ ሳይሆን ከእነርሱም ጋር በሺህ የጥቅም ክሮች ተተብትቦ ከተያያዘው የመንግሥት መኪና (ስቴት ማሺነሪ) ጋር ይጋጫል። ይህ ግጭት ትግሉ በተፋፋመባቸው ቦታዎች ሁሉ የሚታይ ሲሆን አንዳንድ የጋራ የሆኑ ተጨባጭ መልኮች አሉት።

ግጭቱ በመሠረቱ የሚነሳው የቀድሞው ባለርስት በአዋጁ ላይ በማመፁ ነው። አመፀኛው ባለርስት አዋጁን በማደናቀፍ፣ ወይ መሬቴን አታርስም፡ በሬዬን  አልሰጥም ብሎ ያስቸግራል፣ አለበለዚያም ምርቱን እንደድሮ እወስዳለሁ ይላል፤ በአጭሩ እንደ ቀድሞ እቀጥላለሁ ብሎ ይነሳል። ተራማጁ ወገን ይህንን አመጸኛ፡ ይህንን ህገወጥ ለመንግሥቱ ፖሊስ ይጠቁማል፣ ይያዝልን ይላል። ፖሊስ ‘የቀን አበል ይከፈልኝ’: ‘ብዙ መሳሪያ ይሰጠኝ’… እያለ ሰበብ ያበዛል፣ እንዲያውም አሁን በብዙ ቦታዎች እንደሚታየው እነዚህን ፀረሕዝብ ዘራፊዎች ያስተናግዳል። አስተዳዳሪው ‘ ገንዘብ የለም… በቂ መሳሪያ የለም’ ብሎ ነገሩን ይዘጋዋል። ሕዝቡ በራሱ ብቻ መተማመን እንዳለበት ተገንዝቦ አመጸኛውን በመከራ ከቦ ይይዝና ለፖሊስ ያስረክባል። ፖሊስ ጉቦ በልቶ ‘በዋስ መብት’ ይለቀዋል። ሕዝቡ ጠላቱን እንደገና ይዞ ራሱ ‘ወደ ዳኛ’ ይወስደዋል። የመንግሥቱ ዳኛም ራሱ ከፍተኛ ባለርስትና በጥቅም የተገዛ  መሳሪያ በመሆኑ ‘የመሬት ጉዳይ ነውና የማየት መብት የለኝም’ ብሎ ይዘጋል። የገበሬዎች ሸንጎ በአመጸኛው ላይ ይፈርዳል። ግን ሕዝቡ ያሰረውን ፖሊስ መልሶ የፈታዋል። ሕዝቡ ጠቅላላውን ከቢሮክራሲውና ከፖሊሱ ኃይለኛ ግጭት ይጀምራል። በዚህ ግጭት መሳሪያ የያዘው አድሃሪው ወገን ስለሆነ ሕዝቡ ይጠቃል፣ በዚህ ሁሉ ማን ወዴት እንደማያደላ ይገነዘባል። አድሃሪውን ፖሊስ በራሱ ፖሊስ ካልተካ፣ ዳኛውን በዳኛ፡ ቢሮክራቱን በሕዝባዊ አስተዳዳሪ፡ ጦሩን በሕዝባዊ ጦር ካልተካ ሕዝቡ ምንም ዓይነት መውጫ እንደማይኖረው ይማራል። ከዚህም አልፎ የመንግሥቱ ፈጥኖ ደራሽ እንደደረሰ ሲደበድበው በመሃከላዊ መንግሥት ደረጃም ቢሆን እሱው የመረጠውና በእርሱ ድጋፍና ቁጥጥር ስር ብቻ የሚሰራ ‘ሕዝባዊ መንግሥት’ እንደሚያስፈልገው በሚሊዮን የሚቆጠረው ገበሬ እንደዚህ በትግል ይገነዘባል።

የሕዝቡን ነፃነት ረግጦ ይዞ መሬትን ለአራሹ ‘አደላድላለሁ’ የሚለው ደርግ የገባበት ማጥና ሊወጣው የማይችለው ቅራኔ እንግዲህ የሚፈልቀው ከዚህ መሰረታዊ ግጭት ነው። የኢትዮጵያ አብዮት ከንኡስ ከበርቴው ቁጥጥር ስር እንዳይመጣ ስለሚፈልግ ደርጉ ይህንን አብዮታዊ አዋጅ ከስራ ላይ ለመዋል የሚሞክረው በቀድሞ ስርዓት አድሃሪ ቢሮክራሲ ተመርኩዞ ነው። በያለበት እንደሚታየው (ይህ ደግሞ ሊያስደንቀን አይገባም!) የጥንቱ ቢሮክራሲ ይህንን አዋጅ ሙሉ በሙሉ ይቃወማል። ሰፊው ገበሬ ግን ከላይ እንዳየነው ይህንን ሀቅ በእለታዊ ትግሉ የተማረው በመሆኑ ትግሉን በራሱ ቁጥጥር ስር ማካሄድ እንዳለበት ይገነዘባል።

እንግዲህ ይህ መሰረታዊ ግጭት የደርጉ ሚና ካሁን ወዲያ በኢትዮጵያ አብዮት ውስጥ እየቀነሰ እንደሚሄድና እየቀነሰ መሄድ እንዳለበትም ያበስርልናል። ለደርጉ የሚቀረው ምርጫ ትግሉ ከቁጥጥሩ ወጥቶ ከሕዝብ እጅ እንዳይገባ ሲፍጨረጨር አዋጁን ማደናቀፍና ከአድሃሪዎቹ ካምፕ ጠቅልሎ መግባትና የእነርሱ መሳሪያ መሆን አለበለዚያ ደግሞ ቢሮክራሲያዊው መፍትሄ ጨርሶ እንደማያዋጣ ተገንዝቦ ለዲሞክራሲ የሚደረገውን ትግል አለማደናቀፍና ከሕዝቡ መዋሃድ ብቻ ነው። ሌላ አማራጭ ጎዳና የለውም።

በተራማጆች በኩል ይህ ጉዳይ የደርጉ ውሳኔ የሚጠበቅበት ጉዳይ አይደለም። በያለበት ለመሬትና ለነፃነት የሚደረገው ትግል በምንም አይነት ሊነጣጠል ስለማይችል አዋጁን ከስራ ላይ ለመዋል የሚታገሉት ማህበራት የዚህን የዲሞክራሲ ጉዳይ ዋናነት እንዲገነዘቡት ማገዝ ያስፈልጋል። ስለዚህ በኛ ግምት በአሁኑ ወቅት የተራማጆች ጥረት ራሳቸውን በአገር አቀፍ ደረጃ ማስተሳሰርና ገጠሩን በሚመለከተው በኩል የሚከተሉትን እርምጃዎች መውሰድ ነው።

1ኛ በአዋጁ መሰረት እንደተጀመረው አገሪቱን በገበሬ ማህበራት ማጥለቅለቅ። በአሁኑ ጊዜ ከነቤተሰቦቻቸው ወደ 10 ሚሊዮን የሚጠጉ ገበሬዎች የተደራጁባቸው 12 ሺህ የገበሬ ማህበራት እንዳሉ ይገመታል። ይህ ገበሬዎችን የማደራጀት ጥረት ከግቡ ደረሰ ማለት የሚቻለው 25 ሚሊዮን ገደማ የሚሆኑ ኢትዮጵያዊያን በግምት 25 ሺህ ማህበራት ውስጥ ሲደራጁ በመሆኑ በዚህ በኩል የቀረው ተግባር በቀላሉ የሚገመት አይደለም። በተለይ ደግሞ በደቡብና በሰሜን ክፍለ ሃገራት መካካል ያለው መዛባት በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል እስካሁን ድረስ የተቋቋሙት ማህበራት ከቁጥር የሚገቡ እንኳን ሆነው እንዳይገኙ አድርጓቸዋል። ይህ መዛባት ለአብዮቱ የሚያመጣውን ጠንቅ በመረዳት በሰሜን በኩል ያሉትን መሰናክሎች ለመወጣትና በብዛት እነዚህን ማህበራት በማቋቋም ላይ ከፍተኛ ጥረት መደረግ ይኖርበታል።

እርግጥ ነው፣ እነዚህ ማህበራት እንዳይቋቋሙ አድሃሪዎች የማይጠነስሱት ሴራ የላቸውም። ዘማቾችንና ተራማጅ አስተዳዳሪዎችን ከሕዝቡ ለመነጠል የፈጠራ ወሬ ይነዛሉ፣ ተራማጅ ዘማቾችን ያስራሉ፡ ያባርራሉ፡ ይገድላሉ፣ አንዳንድ ዘመቻ ጣቢያዎችን ከነጭራሹ ይዘጋሉ፣ ተራማጅ አስተዳዳሪዎችን ያስፈራራሉ፡ ያነሳሉ፣ የገበሬ ማህበር መሪዎችን አለምክንያት በየፖሊስ ጣቢያው ያስራሉ። ይህ ሁሉ አልሳካ ብሎ ማህበራት ቢቋቋሙ ስልጣናቸውን ለመቀነስ ከአድሃሪው ቢሮክራሲ ጋር ተጣብቀው ያሴራሉ።

ለጊዜው የገበሬዎች ማህበራት ውሱንነት (ከአውራጃ ደረጃ አያልፉም፣ የሚታዘዛቸው ፖሊስና ጦር ሰራዊት የላቸውም፣ የወሰኑትንና የፈረዱትን ማስፈፀሚያ ስልጣን የላቸውም…) አንዳንዶችን ተስፋ ሊያስቆረጥ ይችላል። ግን ይህ በፍፁም የገበሬ ማህበራትን አብዮታዊ ሚና ሊያስተን ይገባም። እንደዚህ የተወሰነውም ቢሆን የገበሬዎች ማህበራት በአገራችን ያብቡ። ይህ የዛሬው ውሱንነታቸው ራሱ ገና ከመጠንሰሳቸው ከአድሃሪው ስርዓት የስልጣን አውታሮች ጋር ስለሚያጋጫቸው የወደፊቱን የትግል አቅጣጫ የሚያመለክት ቀስት ነው።

2ኛ ዛሬ (ገና ደግሞ ለጥቂት ጊዜ) ይህን አዋጅ ስላወጀ ብቻ ደርጉ ከስራ ላይ ያውለዋል የሚል የተሳሳተ እምነት በሰፊው ሕዝብ ዘንድ ይታያል። የዚህ እምነት ፉርሽነት በተግባር ይገለጣል። በሚሊዮን የሚቆጠሩ ገበሬዎች በየእለቱና በየመንደሩ፡ በየጥቃቅኑ አጋጣሚ ከአድሃሪዎቹ እንቅፋትነትና ከደርጉ ተባባሪነት ወይም ወላዋይነት በሚያገኙት ትምህርት መተማመን የሚቻለው በሕዝቡ ትግልና በሕዝቡ ስልጠና ላይ ብቻ መሆኑን ይረዱታል። ተራማጆች ካሁኑ የሚጠብቀን የግንባር ቅደም ተግባራችን ከተጨበጡ እለታዊና ጥቃቅን ግጭቶች እየተነሳን የቅስቀሳው ተግባር በዚህ እየተፋፈመ በሚሄደው የመንግሥት ስልጣን ጉዳይ ላይ እንዲያተኩር ማድረግ ነው።

3ኛ በቀበሌ ደረጃ ሕዝቡ በትግል ስልጣኑን ከእጁ ማስገባት ቢችል እንኳን መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጠላቶቹን ደምስሶ የራሱን ሕዝባዊ ዲሞክራሲያዊ አገዛዝ (ዲክቴተርሺፕ) በአገር አቀፍ ደረጃ እስኪመሰረት ድረስ የተበታተነ ድል ምንም አይነት ቋሚ ዋስትና እንደሌለው መረዳት ይገባል። ስለዚህም እስከአገርአቀፍ ደረጃ የተሳሰሩትን አድሪዎች በመቋቋም ሰፊው አርሶበሌ በዚሁ አኳያ የግድ መደራጀት እንዳለበት አንረሳም። በተጨማሪም ይህ አገርአቀፍ ትግል ከሌሎች አብዩታዊ ሃይሎች (በተለይ ደግሞ ከወዝአደሩ) ጋር ትብብርና አንድነትን የሚጠይቅ መሆኑን ተገንዝቦ የባላገሩ ትግል በከተማ ከሚደረገው ትግል ጋር የሚቀነባበረበትን ዘዴ መሻትና በሱው አቅጣጫ፡ በሱ መንፈስ ገበሬዎችን ማስተማር ያስፈልገዋል።

II

ዛሬ የኢትዮጵያ አብዮት በማጥለቅለቅ ላይ ያለው ገጠሩን እንደሆነና የመሬት አዋጅ የኢትዮጵያን ገጠር (በተለይ ደግሞ የደቡብንና የምስራቅን ክፍለአገራት) ታላቅ አብዮታዊ ማእበል ውስጥ እንደጨመረው ግልጽ ነው። ከተሞች በዚህ ትግል ውስጥ የራሳቸውን የሆነ የትግል ሞተር እንዳላቸው ግልጽ ቢሆንም እነርሱ በገጠሩ፡ ገጠሩ ደግሞ መልሶ በእነርሱ ላይ ታላቅ ተጽዕኖ እንዳለው አይካድም።

የሰፊው ሕዝብ የትግል ማእበል እያስበረገጋቸው የሚሸፍቱት፡ ገጠሩን እየለቀቁ በከተሞች የሚከማቹትና የሚደራጁት አድሃሪዎች ስፍር ቁጥር የላቸውም። በዚህና በሌሎችም ምክንያቶች በአሁኑ ጊዜ ገጠሩ ለአብዮት እጅግ ያመቸውን ያህል በከተሞች ደግሞ አብዮቱ ለአድሃዎች ደረቱን ገልጦ የሰጠ ነው ለማለት ይቻላል።

በከተማ ያለውም ትግል ቢሆን የባላገሩን ያህል ቁርጥ ያለና የተጠራ መልክ አይኑረው እንጂ አሁንም በመፋፋም ላይ መሆኑ ግልጽ ነው። በወዝአደሩ በኩል ኢሰአማ በደርጉ የተሰነዘረበትን ጣልቃገብነት ሙሉ በሙሉ አክሽፎ ድርጅቱን መልሶ አቋቁሟል። የተወረሱት ፋብሪካዎችና ልዩ ልዩ ድርጅቶች ‘የሕዝብ’ ተባሉ እንጂ እስካሁን ድረስ የሃብቱ ፈጣሪ የሆነው ወዝአደር ከዚህ ወረሳ ያገኘው ትርፍ እያቆለቆለ የሚሄድ የኑሮ ደረጃ ብቻ ነው። በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የኑሮ ዋጋ ወደ ሰማይ እየመጠቀ ሲሄድ አንድም የደሞዝ ጭማሪ በመነፈጉ ወዝአደሩ መኖር ከማይችልበት ሁኔታ ላይ ወድቆ ይገኛል። የአስተማሪዎችም ጥያቄ የረባ መልስ ሳያገኝ በ‘ይታይላችኋል’ ብቻ ዓመት ከመንፈቅ ሙሉ ቁጭ ብለዋል። የደርጉ ፈጽሞ ያልተጣራ የተወናበደ ፖለቲካ ትንሽ ነጋዴዎችን ምንም አይነት የህልውና ዋስትና ስለነሳቸው የንግድ እንቅስቃሴ በጣም ተዳክሟል። በየቦታው የሚሰማው እሮሮ ብቻ ነው።ያአገሪቱ ኢኮኖሚ እያዘቀጠ በመሄድ ላይ ይገኛል። በዚህ ላይ የኢምፔሪያሊስቶች፡ የአቀባባይ ከበርቲዎች፡ የቢሮ ከበርቴዎች ወዘተ. ሳቦታጅ ከቀን ቀን እየተቀነባበረ በሚሄዱ አገሪቱ ወደ ትልቅ የኢኮኖሚ ክሪስ በማምራት ላይ ትገኛለች።

ይህንን ሁሉ የሚያባብስ ደግሞ የተወዛገበ የፖለቲካ ሁኔታ አለ። የአብዮቱ ወዳጅና ጠላቶች በቅጡ አልተለዩም። ወላወይና መሃል ሰፋሪ የሆኑት ሃይሎች ወደአድሃሪው ወገን እየተደበለቁ ናቸው። ቁርጠኛ የሆኑት ጠላቶች እየተደራጁና ትግላቸውን እያስተባበሩ ናቸው። ወዝአደሩ ተደራጅቶና አርሶ አደሩን አስከትሎ አመራሩን ባልጨበጠበትና ተራማጁን ወገን እንደዚህ ተራቁቶና ተበታትኖ በሚገኝበት በአሁኑ ሰዓት አብዮቱ በተለይ በከተሞች ከፍተኛ አደጋ ላይ እንደሆነ ግልጽ ነው።

ይህንን አደጋ ጠንቅቀው በመመልከት የኢትዮጵያ ተራማጆች በሙሉ፡ የአድሃሪዎችን ሴራ ለማክሸፍና አብዮቱን ወደፊት ለመግፋት የኢትዮጵያ ሰፊ ሕዝብ በአዋጅ የተነጠቃቸውን ሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶቹን እንዲጎናፀፍ ከጎኑ ተሰልፈው ጠንክረው መዋጋት አለባቸው። በአሁኑ ጊዜ ከስልጣን ኮርቻ ላይ ቁብ ካለውና በመደባዊ ጥቅሙ ታውሮ እውነቱን አላይ ካለው የንኡስ ከበርቴ ፀረዲሞክራቲክ ክንፍ በስተቀር ዲሞክራሲ ለሕዝቡ ትግል የህይወት እስትንፋስ መሆኑን ያልተገነዘበ ተራማጅ የህብረተሰብ ክፍል የለም። እንደዚህ ስለሆነ የመጣ ‘መከራከሪያ’ ቢመጣ ይህንን ሃቅ ሊሸፍንብን ስለማይችል፡ በዚህ በኩል የሚደረገው ትግል ዞሮ ዞሮ በተራማጆችና በአድሃሪዎች መካከል የሚደረግ ትግል ሆኖ መታየት አለበት።

ፀረ ዲሞክራሲያዊው ደርግ መላው ተራማጅ በዚህ ጥያቄ ላይ ተነሳስቶ ወጥሮ ስለያዘው ‘ዲሞክራሲን የከለከሉኩት ቢታወጅ ከሕዝቡ ይልቅ ለአዳሪዎች ይረዳል ብዬ በመፍራት ነው’ የሚል ተልካሻ ሰበብ ይሰጣል። የኢትዮጵያ ተራማጆ ደግሞ በአንድ ድምጽ በፊትም አሁንም የአድሃሪዎችን ቅስም ለመስበር፣ ሴራቸውን ለማክሸፍ፣አወናባጅ ‘ተራማጆችን’ ለማጋለጥ፣ የቀበሮ ባህታውያንን ከሕዝቡ ለመነጠል፣ የትግሉ ባለቤት የሆነውን ሰፊውን ሕዝብ ለማደራጀት የግድ እነዚህ ዲሞክራሲያዊ መብቶች ያስፈልጉናል ይላሉ።

መቼስ ይህ ዲሞክራሲ ከስራ ላይ ቢውል አድሃሪዎችን ያግዝብናል የሚለው ሰበብ በሕዝብ ንቀት የተበከለ፡ ራሱ አደሃሪ የሆነ አስተሳሰብ ብቻ ሳይሆን የማንኛውም አብዮት ሆነ የጊዜው የኢትዮጵያ ሁኔታ የሚያስተባብለው ከንቱ ማወናበጃ ነው። አድሃሪዎች አንድን ሕዝብ ረግጠው ለመግዛት የትና መች ነው ዲሞክራሲያዊ መብቶች አስፈልገዋቸው የሚያቁት? አሁንስ ቢሆን እፍኝ የማይሞሉ አመፀኛ ባለርስቶች በያለበት ዘማችና ተራማጅ አስተዳዳሪዎችን፡ ድሃ ገበሬዎችን የሚያስሩትና የሚረሽኑት በሚሊዮን የሚቆጠረው ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ መብቱን ተነፍጎ ለነሱ ስለተመቻቸው አይደለም ወይ?

የመደራጀት መብት ከተፈቀደ አድሃሪዎች ይደራጃሉ የሚል ሌላ ማወናበጃ አለ። እዚህስ ላይ አድሃሪዎች ለመደራጀትና ጥቅማቸውን ለማስተሳሰር መቼ ነው ዲሞክራሲ አስፈልጎአቸው የሚያውቁት? እስከዛሬስ ተደራጅተው ሲረግጡን ለዘመናት የቆዩት በየትኛው ዲሞክራሲ ተጠቅመው ነው? ትላንት ሙሉ በሙሉ በመንግሥት ደረጃ ተደራጅተው አልነበረም? ዛሬስ አድሃሪው የመንግሥት ቢሮክራሲ መች ተነካ? ተበታትነዋል ቢባልስ ዲሞክራሲ ተፍኖ እስከተያዘ ድረስ ከሕዝቡ ቀድመው እንደሚደራጁ ለማየት እንዴት አዳጋች ይሆናል?

የዲሞክራሲ መጥፋት አድሃሪዎችን በምንም አይነት ከመደራጀት አያግዳቸውም። መጀመሪያ ነገር በሚሊዮን ከሚቆጠረው ሰፊ ሕዝብ ጋር ሲወዳደሩ እጀግ በጣም ጥቂት ከመሆናቸው ሌላ በተለይ ቀንደኞቹ ከድሮም የሚተዋወቁና በጥቅም የተሳሰሩ ናቸው። በተጨማሪ ደግሞ አብዮት በሚፋፋምበት ጊዜ ‘አግኝተው ያጡና’ ጥቅማቸውን ጠንቅቀው የሚያውቁ በመሆናቸው በእንደዚህ አይነቱ ጊዜ አብዮቱን ለመቋቋም በፖለቲካና በድርጅት በኩል የሚያሳዩትን ጥረት እጥፍ ድርብ ያደርጉታል። በዚህ ላይ የገንዘብ ኃይል አላቸው። በህብረተሰቡ ውስጥ ያንሰራራውና ገና በቅጡ ያልተመታው (ዲሞክራሲ ባለመኖሩ) የእነርሱ ርእዮተዓለም ነው። ገና ያልተሰበረው (አሁን ዲሞክራሲ ባለመኖሩ!) የነርሱው ታዛዥ ቢሮክራሲ ነው። ይህንን ሁሉ ስናይ የዲሞክራሲ መጥፋት አድሃሪዎችን የሚያግዝ መሆኑን እንገነዘባለን ማለት ነው።

ደርጉ ይህ እንደማያዋጣው ተገንዝቦ ሌላ ያገኘው የንዑስ ከበርቴ ሴራ ከዚህ በፊት እንዳልነው አንድ ‘ተራማጅ ድርጅት’ አቋቁሞ የሕዝቡን ትግል ለመግራት የሚያደርገው ሙከራ ነው። ከዚህ በፊት በሰጠነው ትንተና (ሰ.ሕ.ድ ቁጥር 24) ይህ ‘ተራማጅ ድርጅት’ የሆነውን ቢሆን ዲሞክራሲ በስራ ላይ ሳይውል ከላይ ቢወረወርልን የኢትዮጵያ ተራማጆዎች በሙሉ ያው እንደ አገር አስተዳደር፡ እንደፍርድ፡ እንደገንዘብ ሚኒስቴር…  የመንግሥት ተቀጥላ የሆነ መስሪያ ቤት እንጂ ሌላ ነገር አድርገን አንወስደውም። በእንደዚህ አይነቱ ‘ተራማጅ’ ድርጅት መታወጅ፡ በኢትዮጵያ ዲሞክራሲ ሰፈነ ብሎ የሚያጨበጭብ አይገኝም። እንዲያውም እንዲህ አይነቱ ድርጅት ሕዝቡ ለዲሞክራሲያዊ መብቶቹ የሚያደርገውን ትግል የሚያወናብድ የንጉስ ከበርቴዎች ሴራ በመሆኑ መላው ኢትዮጵያ ተራማጆች አጥብቀው ይዋጉታል።

በዚህ ጉዳይ ሁለት ነገሮችን መጨመር እንወዳለን። ተራማጆች አንድ ፓርቲ የሚለውን የንዑስ ከበርቴዎች ፈሊጥ አይቀበሉትም። ፓርቲ ማለት የአንድ መደብ ንቁና ግንባር ቀደም ግለሰቦች በመደባዊ ዓላማ ተደራጅተው የዚያን መደብ ጥቅም ለማስከበር የሚቆሙበት መደባዊ ቡድን ማለት ነው። ግንባር ማለት የተለያዩ መደቦችና የህብረተሰብ ክፍሎች ለአንድ ለተወሰነ የጋራ አላማ ድርጅታዊ ነፃነታቸውን እንደጠበቁ ሆነው በጋራ ጠላት ላይ ትግላቸውን የሚያስተባብሩበት የድርጅቶች ድርጅት ማለት ነው።

እንግዲህ እንዲህ ከሆነ አንዳንድ ሃቆች ግልጽ ሆነው ይታያሉ። በአገራችን የሚካሄደው ትግል ፀረፊውዳልና ፀረኢምፔሪያሊስት ሲሆን ትግሉ ከግቡ እንዲደርስ ከተፈለገ የተለያዩ መደቦችና የህብረተሰብ ክፍሎች (90 በመቶ የኢትዮጵያን ሕዝብ ያቀፉ) በቅድሚያ ራሳቸውን በፓርቲ መልክ አደራጅተው በግንባር መልክ ትግላቸውን ማስተባበር አለባቸው። ስለዚህ ሕዝቡ በልዩ ልዩ ድርጅቶች ዲሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ ተደራጅቶ በሙሉ ልቡ የማይሳተፍበትና የማያስተሳስርበት ድርጅት ትግሉን ከግቡ ሊያደርሰው አይችልም።ደርጉ እንግዲህ አቋቁማለሁ የሚለውን ‘ተራማጅ’ ድርጅት የሰጠውን ስም ቢሰጠው የሕዝቡን ትግል ለማፈን የሚሞክሩ የንኡስ ከበርቴ ግለሰቦች ጥርቅም እንጂ ከዚህ አልፎ የሚሄድ አይደለም።

ይህ ‘ተራማጅ’ ድርጅት ፓርቲ ነኝ ብሎ ቢቀርብ ከብረተሰቡ መደቦች ሊወከል የሚችለው የንጉስ ከበርቴውን መደብ ፀረዲሞክራሲያዊ ክንፍ ብቻ ነው። ግንባር ነኝ ብሎ ቢቀርብ፡ አስቀድመው በዲሞክራሲ ተደራጅተው ፕሮግራማቸውን የጋራ ከሆነው ሕዝባዊ ፕሮግራም አስተያይተው፡ ተወያይተውና ፈቅደው በሙሉ ልብ የገቡበት ፓርቲዎችና ሌሎችም ድርጅቶች ስለሌሉበት ቀፎ ‘ግንባር’ ነው ማለት ነው። እንደዚህም ስለሆነ አሁንም ቢሆን ይህ ‘ግንባር’ በኢትዮጵያ አብዮት ላይ ከሚያሴሩ ፀረ ዲሞክራቲክ ንኡስ ከበርቴ ግለሰቦች አልፎ አይሄድም።

ደርጉ አሁንም እውነተኛውን ዲሞክራሲ ለማድበስበስ ይህ የሚያቋቁመው ድርጅት የተለያዩ የሞያና የሰፊ ሕዝብ ድርጅቶችን የያዘ ‘ግንባር’ ይሆናል ይላል። በዚህም የሚወናበድ ተራማጅ አይገኝም። እርግጥ የተባሉት የሙያና የሰፊው ሕዝብ ድርጅቶች ከዚህ ‘ግንባር’ ውስጥ ሊገቡ ይችላሉ። ነገር ግን የሙያ ድርጅቶች አባሎችና አመራሩንም የሚይዙት ግለሰቦች የሚመረጡት እሰከዚህም በፖለቲካ አቋማቸው ሳይሆን ለሞያቸው ወይም ላሉበት ሌላ ድርጅት እድገት በሚያሳዩት ትግልና ታታሪነት ነው። አንድ የሞያ ማህበር ውስጥ (ለምሳሌ ኢትዮጵያ ሀኪሞች ማህበር) አድሃሪም ተራማጅም ወላዋይም አባል ሊሆኑ ይችላሉ። ስለዚህ ሃኪሞች ሞያቸውን በሚመለከተው በኩል እሰከተወሰነ ደረጃ ድረስ በአንድ የሞያ ድርጅት ውስጥ መታገል ቢችሉም ቀጥታ ፖለቲካን በሚመለከተው በኩል የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች አባል ይሆናሉ። ስለዚህ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሳይኖሩበት በሞያና የሰፊ ሕዝብ ድርጅቶች ብቻ የተቋቋመ ግንባር የራሱ የሆነ የተጣራ የፖለቲካ አቋም ስለማይኖረው በዚህ በኩል በቀጥታ በመንግሥቱ (ማለት በንኡስ ከበርቴው) የፖለቲካ አመራር ስር ይወድቃል ማለት ነው።

ይህንን እንኳን ይሁን ብለን ይህ ‘ግንባር’ በነዚህ ድርጅቶች ብቻ ተቋቋመ ቢባልም በዚህ ደረጃ እንኳን ደርጉ  የዲሞክራሲን ጥያቄ ሊያመልጠው አይችልም። ምክንያቱም ሁለተኛው ቁምነገር ይህ ‘ግንባር’ በውስጡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ያስፈልጉታል ብቻ ሳይሆን ያቀፋቸው ድርጅቶች በሙሉ አሰራራቸው በዲሞክራሲ ካልሆነ ሰፊውን ሕዝብ ያቀፈና ሰፊው ሕዝብ መልሶ ያቀፈው ‘ግንባር’ ሊሆን አይችልም። ‘ግንባር’ ያስፈልጋል የሚባለው የሰፊውን ሕዝብ የተለያዩ ክፍሎች በአንድ የጋራ ዓላማ ላይ አንቀሳቅሶ ለመታገል ነው። ይህን የጋራ ዓላማ ሕዝቡ እንዲቀሰቀስበትና ስራ ላይ ለማዋልም አስፈላጊውን መስዋእትነት ለመቀበል ዝግጁ እንዲሆን ከተፈለገ ከሰፊው ሕዝብ ፍላጎት የመነጨ አላማ መሆን ይገባዋል። ስለዚህ እነዚህ ድርጅቶች የግንባሩ አባል ከመሆናቸው በፊት እንወክላለን የሚሉትን ክፍል ፍላጎትና አላማ የሚያንፀባረቁ ዲሞክራሲያዊ ድርጅቶች መሆን አለባቸው ማለት ነው። ለዚህ ደግሞ የግድ በዲሞክራሲ መወያየት፡ መወሰን፡ መሪዎችን መምረጥ፡ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ደግሞ መሻር የሚቻልበት አካባቢ መፈጠር አለበት ማለት ነው።

ይህ ካልሆነ እነዚህ ድርጅቶች ሕዝቡን በምንም አይነት አይወክሉም ማለት ነው። ሕዝቡን ለትግሉ ማንቀሳቀስም አይችሉም ማለት ነው። እንደዚህ ከሆነ ደግሞ ይህ ‘ግንባር’ ድርጅቶችን አቅፌያለሁ ብሎ ለማወናበድ ቢሞክር በአባልነት የሚይዛቸው ሰዎች ከራሳቸው በስተቀር ማንንም የማይወክሉ ግለሰቦች ብቻ መሆናቸው ግልጽ ነው።

የኢትዮጵያን አብዮት ሰፊው ሕዝብ እንጂ ፀረዲሞክራቲክ ግለሰቦች ከስራ ላይ እንደማያውሉት ግልጽ ነው።  በዲሞክራሲያዊ አሰራር ተመርኩዞ፡ በወዝአደሩ አመራር ስር ተሰልፎ፡ በአንድ አብዮታዊ ሕዝባዊ ግንባር እስካልተሰለፈ ድረስ የኢትዮጵያ አብዮት ከግቡ አይደርስም። ይህንን በመረዳት በዴሞክራሲያዊ ግንባር ትግላቸውን ማፋፋም የያዙት ተራማጆች በሙሉ በኛ ግምት የሚከተሉትን ርምጃዎች መውሰድ ይኖርባቸዋል፡-

  1. ለዲሞክሪሲ መብቶች ሲታገሉ የቆዩ የሞያ መህበሮች፡ የሰፊው ሕዝብ ድርጅቶችና ተራማጅ የህብረተሰብ ክፍሎች በሙሉ ለዲሞክራሲ በሚያደርጉት ትግል ከውሳኔ አልፈው በተግባር በአንድነት የሚሰለፉበትን ዘዴ ተገናኝተው ማጥናት አለባቸው።
  2. በዚህ በዲሞክራሲ ጥያቄ ላይ ምንም አይነት ማወናበድ እንዳይኖር፣ የሚቀርቡት ጥያቄዎች የመደራጀት፡ የመፃፍ፡ የመሰብሰብ…. የመሳሰሉትን ሰብአዊ መብቶች ያለአንዳች ገደብ እንዲታወጁ ለማድረግ መታገል ያስፈልጋል።

ትግላችን በገጠርም ሆነ በከተማ በዚህ አቅጣጫ ከተቀናበረ የኢትዮጵያ አብዮት ከመታፈን አልፎ አዲስ እስትንፋስ፡ አዲስ ጉልበት እንደሚያገኝ አንጠራጠርም። ባላገሩ በአብዮቱ መጥለቅለቁን ይቀጥላል። የአድሃሪዎች ምሽግና የሴራ መጠንሰሻ ዋሻ መሆን በጀመሩት ከተማዎች ትግሉ እንዳይታፈንና አድሃሪዎን መድረሻ ለማሳጣት በዲሞክራሲ ግንባር የሚካሄደው ትግል መግፋት አለበት። ከእንግዲህ ሰማይ ዝቅ ምድር ከፍ ቢል በምንም ኃይል ሊገታ የማይችለውን የኢትዮጵያን አብዮት ባለበት ገርቼ እይዛለሁ የሚለው የንኡስ ከበርቴው ደርግ አቋም በመሰረቱ ለአብዮቱ ሳይሆን ለአድሃሪ ሃይሎች የሴራ መጠንሰሻ ፋታ የሚሰጥ አቋም መሆኑ ግልጽ መሆን አለበት። እንደዚህም ስለሆነ ራሱ አድሃሪ አቋም በመሆኑ የኢትዮጵያ ተራማጆች በሙሉ ሃይላቸውን አስተባብረው ይዋጉታል።

አብዮታዊ የገበሬ ማህበራት ያብቡ!
የሰፊው ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ መብቶች ትግል ይግፋ!
ፊውዳሊዝምና ኢምፔሪያሊዝም ይወድማሉ።
የኢትዮጵያ ሕዝብ ያሸንፋል።
Scroll to Top