ሰሕድ ቁ. 30

የሰፊው ሕዝብ ድምፅ

ቁጥር 30፣    ጳጉሜ 1፣ 1967 

መኢሶን በዚህ የሰፊው ሕዝብ ድምፅ እትሙ፣ የኢትዮጵያ ተማሪዎች ንቅናቄ ስመ ጥር መሆኑን አስገንዝቦ፤ የታገሉለት “የመሬት ላራሹ” ጥያቄ በታሪክ እውን እንደሆነ ያመለክታል። በዚህም ምክንያት የመሬት ላራሹ በተለይ በገጠሪቱ ኢትዮጵያ ውስጥ የትግሉ አንቀሳቃሽ ሞተር በመሆኑ፡ ተማሪዎች ከገበሬዎች ጎን በትጋት ተሰልፈው ትግላቸውን እንዲቀጥሉና የመሬት ላራሹን የድል ፍሬ እንዲያስከብሩ ያሳስባል። ምንም እንኳን ተማሪዎች በብዛት የሚሳተፉበት የእድገት በህብረት ዘመቻ ዝብርቅርቅ ያለና ችግሮች ቢኖሩበትም፤ በተወሰነም መልኩ ዘማች ተማሪዎች ገበሬዎችን የማስተማርና የማደራጀት ሥራቸውን መቀጠል እንደሚገባቸው ያሳስባል። አያይዞም፣ የመሬት ላራሹ ስኬትም ከገበሬዎች ማኅበራት በነጻ መደራጀትና ከገበሬዎች ትጥቅ መታጠቅ ጋር ሳይነጠል መታየት እንደሚገባው ይተነትናል። 

የሰፊው ሕዝብ ድምፅ

ለሰፊው ሕዝብ ሰራተኛ ገበሬ፣ ነጋዴ፣ ወታደር፣ ምሁር መብትና ጥቅም የሚታገል ጋዜጣ

የኢትዮጵያ ሰፊ ሕዝብ ይቅደም

ቁጥር 30                                                                     ቀን 1/13/67

 

ዘመቻውና አብዮቱ

ስመ ጥሩው የኢትዮጵያ ተማሪዎች ንቅናቄ ከአብዮታዊ የትግል ጥሪ ስር ተሰልፎ ከአስር አመታት በላይ በታላቅ ጀግነትና የወገን ፍቅር ስሜት ተዋግቷል። ተሰውቷል። በአለፉት የትግል አመታት ወጣቱ ትውልድ ከገበሬው ጎን በመሰለፍ ሲያስተጋባው የነበረው መሬት ላራሹ የሚለው አብዮታዊ መፈክር ዛሬ በመላው የኢትዮጵያ አርሶ አደር ዦሮ ገብቶ የትግሉ አንቀሳቃሽ ሞተር እስኪሆን ድረስ የኢትዮጵያ ተማሪዎች በብዙ መከራና ስቃይ የከፈሉት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳላቸው ታሪክ ሲያስታውሰው የሚኖር ነው።

በየካቲት 1966 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ሕዝብ ትግል እንደሰደድ እሳት አገሪቱን ማጥለቅለቅ ከዠመረበት ጊዜም አንስቶ የኢትዮጵያ ተማሪዎች ንቅናቄና ትግል ምስዋዕትነት እያደር ሲጨምር እንጂ የትምቦታ፣ ምን ጊዜም፣ ገብ ሲል አልታየም። በተለይም ደግሞ በእድገት በህብረት የእውቀትና የስራ ዘመቻ አማካይነት በገጠር ተሰማርተው እስካሁን የፈጸሙዋቸው የመማር፣ የማስተማርና የማደራጀት ተግባሮች በኢትዮጵያ ምድር ምንጊዜም የማይፋቅ መሠረቶች እንደጣሉ ግልጽ ነው።

ዛሬ የዘመቻው ሥራ በልዩ ልዩ ምክንያቶች እየተሰናከለ እየተዘበራረቀ፣ እጅግ የተወሳሰቡ ችግሮች ውስጥ ገብቷል። እነኚህ ችግሮች በጣም የታወቁ ስለሆኑ አንዘረዝራቸውም። ዋና ዋናዎቹ ግን 1ኛ/ ብዙ አዝማቾችና የዕድገት በህብረት መምሪያ አብዛኞቹ ኃላፊዎች አድሃሪ መሆንና ተማሪዎቹን አድሃሪ የሆነ መመሪያ እየሰጡ ለማሳሳት መሞከር 2ኛ/ በገጠር የመሬትን አዋጅ መንፈስ በመጣስ አንዳንድ አስተዳዳሪዎችና የፖሊስ ሰራዊት አብዛኛዎቹ አባላት ለአድሃሪዎች ማንሰራራት መንገድ መስጠትና አድሃሪዎቹ ዘማቾችን በማጥቃት የገበሬዎችን ማህበሮች ለማፍረስ መጣር  3ኛ/ ይህ ሲሆን ደርጉ የወሰደው ምርጫ ከአድሃሪዎች ጋር በመሰለፍ የተራማጅ አስተዳዳሪዎችን የመሬት ይዞታ ወኪሎችንና የዘማቾችን ጥያቄ ሳይቀበል ከአድሃሪዎች ጋር በመሰለፉ ነው። ግንባር ቀደም ተራማጆች ሁሉ ደጋግመው ጠይቀውት እንደነበረው ሁሉ ዘመቻው በዲሞክራሲያዊና ብሄርአቀፍ በሆነ ዘዴ ተደራጅቶ እንዳይካሄድ ታግዶ ቆይቶ ነበር። ዘማቾች ለሚያገለግሉት ሕዝብ የተሻለ የሚሠሩበትን፣ ስራቸው የሚቀላጠፍበትን፣ የሚያጋጥሟውን ልዩ ልዩ ችግሮች በህብረትና በውይይት የሚፈቱበትን ብሄራዊ መድረክ ከመነፈጋቸው የተነሳ በአሁኑ ሰዓት ዘመቻው ባልተደራጀ መልክ የመበተንና በዚህም ለአድሃዎች ሴራና ተንኮል እጅግ ያመቸ አዝማሚያ በመፈጠር ላይ መሆኑን ማንም ሊታዘበው የሚችል ሃቅ ነው።

በእንደዚህ አይነቱ አስቸጋሪ ጊዜ ማንም ለኢትዮጵያ ሕዝብ አብዮት አስባለሁ የሚል ተራማጅ በህሊናውና በታሪክ ፊት ኃላፊነትን ተቀብሎ መፍትሄ ይሆናል የሚለውን ሀሳብ ለውይይት ማቅረብ አብዮታዊ ግዴታው ነው። በዚህ ሐሳብ በመገፋፋት አሁን የኢትዮጵያ ሕዝባዊ ንቅናቄ በደረሰበት ደረጃ ዘመቻው ምን ሚና ሊኖረው እንደሚችል ለማየት ይህችን አጭር ጽሁፍ እናቀርባለን።

ዛሬ አገራችን በአዲሱ ዲሞክራሲያዊ አብዮት ጎዳና በመጓዝ ላይ ትገኛለች። ስለዚህም የኢትዮጵያ ሕዝብ የጊዜው ዋና ጠላቶች ፊውዳሊዝምና ኢምፔሪያሊዝም በተለይም የአሜሪካ ኢምፔሪያሊዝም ናቸው። በዚህ አንፃር አብዮታዊው የመሬት አዋጅ የአንዳንድ የማምረቻና የማከፋፈያ ድርጅቶች መወረስ፣ የከተማ ቦታና ትርፍ ቤቶች የመንግሥት መሆን….በአብዮታዊ ጎዳና ባይፈጸምም የማይናቁ ድሎች ናቸው። ነገር ግን እነዚህ ሁሉ በአዋጅ በመነገራቸው ብቻ አብዮት ተደረገ ብለው የሚያምኑ በአዋጅ እንጂ በሰፊው ሕዝብ ትግል እምነት የሌላቸው ብቻ ናቸው። ሌላ ቀርቶ በአዋጅ ደረጃ እንኳን ገና የአዲሱ ዲሞክራሲያዊ አብዮት አካል የሆኑት ለምሳሌ በኢምፔሪያሊዝም ላይ ቁርጥ ያለ አቋም መውሰድ፣ የብሔሮችን እኩልነት ማረጋገጥ፣ የሰፊው ሕዝብ ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች መታወቅ…. ገና ያልታዩ ነገሮች ናቸው። እዚህ ላይ ግን መርሳት የማይገባን አንድ ቁምነገር ነገር አለ። የታወጀውን ከስራ ላይ ለመዋል ሆነ የጎደለውን ለማሟላት፣ የነቃ፣ የተደራጀና የታጠቀ የሕዝብ ትግል አስፈላጊ መሆኑን ነው። እነዚህን አሟልቶና ቋሚ የሆነ ዋስትና ሰጥቶ ትግሉን ወደፊት ሊገፋ የሚችለው ሰፊው ሕዝብ ጠላቶቹን እየደመሰሰ የራሱን ዲክታተርሺፕ የሚያረጋግጥበት ሕዝባዊ መንግሥት ሲያቋቋም ብቻ ነው።

ይህ እስኪሆን ድረስ የአድሃሪዎችን ርዕዮተአለም የነቃው ሰፊ ሕዝብ ርዮተአለም እየተካው፣ የአድሃዎችን ሴራ የሰፊው ሕዝብ ድርጅቶች እየተቋቋሙትና የአንድነት ግንባር እያሸነፉት፣ የአድሃዎችን ውንብድና የታጠቀው ሕዝባዊ አመጽ እየደመሰሰው ለምንገነባው አዲስ ሕዝባዊ ሥርዓት በየጊዜው ከትግሉ ደረጃ የሚጣጣም ታክቲክ እየቀየስን መጓዝ ይኖርብናል።

ዛሬ የደረስንበትን ደረጃ ለመመልከት የአብዮቱ ወሳኝ ከሆነው ከመሬት ጉዳይ ልንነሳ እንችላለን። በአሁኑ ጊዜ የየካቲቱ የመሬት አዋጅ መላውን ገጠር በተለይ ደግሞ የደቡቡን ኢትዮጵያ ክፍል ከፍተኛ የሆነ የትግል ማዕበል ውስጥ ጨምሮታል የመደቦች ትንንቅ ታይቶ በማይታወቅ መልክ አፋፍሞታል።

መሬት እንደ ውሃ የጠማው ገበሬ በመጀመሪያ ከተንቀሳቀሰበት መሬት ላራሹ ከሚለው መፈክር አከታትሎ ዛሬ ከትግሉ በቀሰመው ትምህርት ምክንያት ነፃነት ላራሹ በሚለው መፈክር ስር እየተሰለፈ ሲሄድ እናየዋለን። ይህ የሚሆንበት ዋናው ምክንያት (ይህ ደግሞ የማንም አብዮት ታሪክ አበጥሮ ደጋግሞ ያሳየው ሃቅ ነው) ሰፊው ገበሬ ነጻነቱን ካላገኘ – የመደራጀት፣ ራሱን በራሱ የማስተዳደር፣ መሪዎቹን የመምረጥ፣ የመቆጣጠርና የመሻር መብቱን የማስከበር፣ መሬት ላራሹን የሚቃወሙትን ከጥንትም የታጠቁትን አድሃሪዎች ለመቋቋም የመታጠቅ መብቱን የማረጋገጥ…. እነዚህንና እነዚህን የመሳሰሉትን መብቶቹን ካላገኘ- መሬት እርም መሆንዋን በትግሉ ውስጥ እየተገነዘበ ስለሚሄድ ነው።

በዚህ አብዮታዊ እርምጃ ለመደራጀትና ለነፃነት የሚደረገው ትግል ለማስፈጸም ተብለው የተቋቋሙት የገበሬ ማህበራት ምን አይነት አብዮታዊ ሚና እንዳላቸው ባለፈው ቁጥራችን /የሰፊው ሕዝብ ድምፅ ቁ. 28/ በሰፊው አትተናል። ባጭሩ ለመድገም ያህል እነዚህ ማህበራት በዓላማቸው ሆነ በመደባዊ ይዞታቸው አብዮታዊ ናቸው። ሲወለድ አብሯቸው የሚወለደው ፀረፊውዳል ጠባያቸውና አብዮታዊውን አዋጅ ከስራ ላይ ለመዋል የሚያደርጉት ትግላቸው የግድ ወዲያውኑ ከአድሃሪውና አዋጅን ከሚቃወመው፣ የቀድሞ ሥሪት ጋር ያጋጫቸዋል። ትግሉ እየገፋ ሲሄድ በሁለቱ መሃከል ያለው ቅራኔ በእርግጥ ተፃራሪ መሆኑን አንዱ አንዱን ካልደመሰሰ ምንም አይነት እርቅ ሊኖር እንደማይችል ለአድሃሪም ለተራማጅም ግልጽ ይሆናል። በአስተዳደር፣ በፀጥታው፣ በዳኝነቱ ተግባር…. በአጭሩ በመንግሥት ስልጣን ጉዳይ የማይቀረው ትንንቅ ይጀምራል። ለዚህ የሞት ወይም የሽረት ትግል አድሃሪዎች ቀደም ሲልም ታጥቀዋልና በቅድሚያ መሳሪያ ያነሳሉ። በእንደዚህ አይነቱ ጊዜ ለተራማጅ ወገን ከፀሐይ በርቶ የሚታየው ሀቅ መሬትን እጅ ለማስገባት የፈለገ አድሃሪዎችን ለመቋቋም መታጠቅ እንዳለበት ነው። ትግሉ እዚህ ደረጃ ከደረሰ በኋላ፣ ሰፊው የኢትዮጵያ ሕዝብ በገዛ አገሩ ላቡን አንጠጥፎ በሰላም እየሰራ ለመኖር ያለውን መብት ለማሰናከል አድሃሪዎች የእርስ በርስ ጦርነት ካወጁበት በኋላ፣ በሕዝቡ አብዮታዊ ትግል ተደናግጠው እንዳበደች ውሻ መናከስ ከጀመሩ የሕዝቡን መታጠቅ ጉዳይ እንደቀላል ነገር መውሰድ ወንጀል ነው። አብዮቱ ሊቀጥል የሚችለው ትግሉን እዚህ ከፍተኛ ደረጃ ያደረሱት የገበሬ ማህበራት ታጥቀው ሲገፉ ነው። በዚህ አንጻር እነዚህ ማህበራት ዛሬ የትግል ሞተር ከመሆን አልፈው አድሃሪው ስርአትና አድሃሪው የመንግሥት መኪና ተሰባብሮ በሚወድቅበት ጊዜ የአዲሱ ሕዝባዊ ሥርዓት ጽኑ መሠረቶች ሆነው ብቅ እንደሚሉ በሰፊው አትተናል።

እውነቱ እንደዚህ ከሆነ የነዚህ የገበሬ ማህበራት መቋቋም ትግሉ ከፍተኛ ደረጃ መድረሱን የሚያሳዩ ምልክቶች ብቻ አድርጎ መቁጠር የነገሩን አንድ ጎን ብቻ መመልከት ይሆናል። የዋህነት ነው። በዚያው ልክ በነዚህ ገበሬ ማህበራት አማካኝነት፣ በነሱ የተነሣ አድሃሪውም ተራማጅም የትጥቅን ጉዳይ ከአጀንዳቸው አስገብተውታልና፣ አንዱ አንዱን ለመደምሰስ ግልጽ የሆነ ዝግጅት በማድረግ ላይ ናቸውና የኢትዮጵያ አብዮት አንድ አዋሳኝ መድረክ ላይ በመንገዳገድ ላይ እንዳለ መገንዘብ ያስፈልጋል። ከዚህ አዋሳኝ መድረክ ብዙ መቆየት አይችልም። ወይ የተቀጣጠለ እዚህ የደረሰው አብዮት ለጊዜው ክፉኛ የመቀልበስ አደጋ ላይ ይወድቃል። ወይም ደግሞ አብዮቱ አዲስ እስትንፋስ አግኝቶ ግስጋሴውን ይቀጥላል።

እዚህ ፍጥጫ ላይ የሚገኙት በተለይ በደቡብ ያሉት ትግሉ የተፋፋመባቸው ማህበራት ብቻ በመሆናቸው የነዚህ ጥቂት ማሕበራት እድል የአብዮቱን እድል ይወስናል ማለት የማግነን እንዳይመስልብን።ይህ አነጋገር የተጋነነ የሚመስለው ሰው፣ በድፍን ኢትዮጵያ የገበሬ ማህበራት ተቋቁመው ግንባር ቀደሞቹ የደረሱበት ደረጃ ደርሰው እስኪፋጠጡ ድረስ የጊዜው ዋና ተግባር እነዚህን ማህበራት ቁጥር ማብዛት ብቻ አድርጎ ይወስደዋል። እኛ ግን ከላይ ባልነው ሃቅ በመጀመር አሁን ባለንበት ሰዓት የአቢዮቱ እድል የሚወሰነው በግንባር ቀደምነት በሚገኙት ማህበራት መታጠቅ ወይም አለመታጠቅ ነው እንላለን። በነዚህ ቦታዎች የሕዝቡ መታጠቅ ችላ ተብሎ አድሃሪዎች እንደጀመሩት ማንሰራራታቸውን ከቀጠሉ ተከታዩ የማስተማርና የማደራጀት ትግል ፈጽሞ አብዮታዊ ትርጉሙን ይስታል። በነዚህ ቦታዎች ሕዝቡ ከታጠቀና አድሃሪዎች ከተመቱ ለመጪው ትግል ታላቅ በር ተከፈተ ማለት ነው። የሰፊው ሕዝብ መታጠቅ ወይም አለመታጠቅ፣ የአድሃሪያንን ትጥቅ ማስፈታት ወይም አለማስፈታት፣ የጊዜው ጥያቄ ይህ ነው።

እንግዲህ በኢትዮጵያ አብዮት ውስጥ የዘማቾችን ከማስተማርና ከማደራጀት የማያልፍ ሚና መመልከት የምንችለው ከዚህ ሃቅና ከዚህ የጊዜው አንገብጋቢ ጥያቄ ተነስተን ብቻ ነው።

የዘመቻው ጊዜ ተራዘመ ተባለ። ለሰፊው የኢትዮጵያ ሕዝብ ነፃነት ያላቸውን የጋለ ስሜት እስካሁን በደማቸውና በመከራ ሲከፍሉ እዚህ የደረሱና ትግሉን እዚህ ያደረሱ ወጣት ተራማጆች የዘመቻውን መቀጠል ለአብዮቱ አስፈላጊ እስከሆነ ድረስ በዚህ አያማርሩም። ግን በመሠረቱ የኢትዮጵያ ሕዝብ አብዮት የመግፋት ወይም የመቀልበስ እድል በዘመቻው መቀጠል ወይም አለመቀጠል ላይ የተንጠለጠ አድርጎ ማቅረብና ከዚህም ይባስ ብሎ ደርጉ እንደሚያቀርበው የዘመቻው መቋረጥ ነገ በታሪክ ፊት የሚያስጠይቅ ወንጀል አድርጎ ለማቅረብ መሞከር አጉል ማወናበድ ነው። የራስን ወንጀልና የራስን በታሪክ ፊት ተጠያቂነት አድበስብሶ ለማለፍ መሞከር ነው። በገዛ አይን ውስጥ ያለውን ስንጥር አልፎ በሰው ዓይን ውስጥ ያለውን ጉድፍ ማየት ነው። ስለዚህ ነው ስለዘመቻው ያለንን ሃሳብ ከማቅረብ በፊት ሁለት ነገሮችን ማብራራት አስፈላጊ የሚሆነው።

ደርጉ ዘመቻው የተራዘመበትን ሁኔታ ሲገልጽ ዋና ብሎ ከሚያቀርባቸው ምክንያቶች ሁለቱን መጥቀስ ይቻላል። በመጀመሪያው ዘመቻው እንዲቀጥል የተደረገው የዘመቻው ተካፋዮች ከጎናቸው እንዳይለዩና ርዳታቸው እንዳይቋረጥባቸው የዘመቻው ተጠቃሚ የሆኑት በየጊዜው አጥብቀው የሚጠይቁ ስለሆነ ነው ይላል።

ይህ መቸስ ጨርሶ አለማፈር ነው። እርግጥ የኢትዮጵያ ሕዝብ ዘማቾች እንዳይለዩት ይጠይቃል። ግን በአሁኑ ጊዜ ዘማቾች የሚፈለግባቸውንና የሚጠበቅባቸውን የማስተማርና የማደራጀት ተግባር በሚገባ ባከናወኑበት ቦታ ሁሉ ሰፊው ሕዝብና ዘማቹ ከታጠቁ አድሃሪዎች ጋር ባዶ እጃቸውን ተጋፍጠው አድሃሪዎች በዘማቾች በገበሬዎች፣ በተራማጅ አዝማቾችና አስተዳዳሪዎች ላይ ይህ ነው የማይባል የማስፈራራት፣ የማንገላታት፣ የውንብድና ተግባር በመፈፀም ላይ ናቸው። ስለዚህ በአሁኑ ጊዜ አጥብቆ የሚጠየቀው ደርጉና አድሃሪዎች ደግሞ አጥብቀው የሚቃወሙት ሰፊው ሕዝብ አድሃሪዎችን አበጥሮ የሚለይበትን የዲሞክራሲ መብቶችና ራሱን ለመጠበቅ እንኳን የሚሆነው መሣሪያ ማግኘቱን ነው። ይህ ሆኖ ሳለ የሕዝቡ ዋና ጥያቄ ዘማች አይለየኝ የሚል ነው ብሎ የሚያቀረብ ሰው ለኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ አይኑን የጨፈነ ለሰፊው ሕዝብ ሮሮ ጆሮውን የደፈነ ብቻ ነው።

በሁለተኛ ደረጃ ደርጉ የሚሰጠው ምክንያት የዘመቻው መቋረጥ የሰፊው ሕዝብ አብዮት በመራመድ ላይ ባለበት በዚህ አፍላ ጊዜ ዘመቻው እንዲያበቃ ወይም ገብ እንዲል ማድረጉ አብዮቱ መድረስ ካለበት አድማስ ወደኋላ ሊያስቀረው ከመቻሉም በላይ ለጭቁኑ ሰፊ ሕዝብ እስከአሁን የተደከምለትን እንዳልነበረ ሊያደርገው ስለሚችል የሚል ነው።

ይኽም ጨርሶ አይን የማውጣት ነው ከላይ እንደተነተነው አሁን በደረስንበት ሁኔታ አብዮቱ መድረስ ካለበት አድማስ ወደ ኋላ እንዳይቀር አብዮቱ በጦር ኃይልና በልዩ ልዩ ተንኮል መዳከምና መበተን እንዳይደርስበት ከልብ ከተፈለገ ዋናው የጊዜው ተግባር የአድሃሪዎችን ቅስም መስበር ብቻ ነው። ይህ ካልሆነና ይህ እስካልሆነ ድረስ የዘማቾች ከገበሬው ጎን አለመለየት ለአድሃሪዎች አመጽ በታሪክ ፊት ምስክርነት ለመቆም እንደሆነ እንጂ ሌላ የሚረዳው ነገር የለም። ዘማቾች ሺህ ጊዜ ቆራጥ ቢሆኑ፣ ሺህ ጊዜ ለመስዋአትነት ዝግጁ ቢሆኑ ከእግር እስከ ራሳቸው ታጥቀው እንዳበደች ውሻ መናከስ የጀመሩትን አድሃሪዎች ተቋቁመው አብዮቱን አድማስ ማድረስ አይችሉም።

ይህ እንደዚህ ሆኖ ሳለ የኢትዮጵያ ገበሬ አስታጥቁኝ፣ ወይም የአድሃሪውን ትጥቅ ላስፈታ አያለ እሮሮውን ሲያሰማ ከቀን ቀን የልብ ልብ እየተሰማው፣ የታጠቀና እያየለ ለሚሄደው ጠላቱም እጅና እግሩን አስሮ በማስረከብ ላይ የሚገኘው ደርግ ዘመቻው ቢቋረጥ ሰፊውን ገበሬ ለጠላት አጋፍጦ እንደመስጠት ይቆጠራል ሲል ይህ አነጋገር ምን ያህል ግብዝነት የተሞላው እንደሆነ አንባቢ ይገንዘበው ብለን ብቻ እናልፋለን።

ዘማቾች እስካሁን በታላቅ ቆራጥነትና መስዋዕትነት ሕዝቡን አስተምረውና አደራጅተው እዚህ ከፍተኛ ደረጃ አድርሰውታል። ፈረስ ያደርሰል እንጂ አይዋጋም ከአሁን ወዲያ የአብዮቱ መግፋት ወይም ለጊዜው መገታት እድል ያለው በመሠረቱ በሕዝቡ መታጠቅ ወይም አለመታጠቅና በዲሞክራሲ መብቶች መፈቀድ ላይ ነው ነገር ግን የዘመቻው ጉዳይ በሁለተኛ ደረጃ የሚታይ ጉዳይ ነው ለማለት እንጂ የወጣቱ ምሁር ከሰፊው ሕዝብ መዋሀድ እንኳን ዛሬ ይቅርና ምንጊዜም ቢሆን አስፈላጊ እንደሆነ ግልጽ ነው።

አብዛኛው ዘማች ሊያከናውነው የሚችለው የማስተማርና የማደራጀት ጉዳይ ቢያንስ የገበሬ ማህበራት በመላ ሃገሪቱን እስኪያለብሷት ድረስ መቀጠል ያለበት አብዮታዊ ተግባር ነው። ነገር ግን ከላይ እንዳሳየነው በዚህ በአሁኑ ሰዓት ይህ ተግባር ባይናቅም ዋናው ጥያቄ የገበሬ ማህበራት ቁጥር ብቻ ማበርከት ብቻ አይደለም። የአድሃሪውም ሆነ የተራማጅ አይን ያተኮረው ነቀተውና ተደራጅተው በከፍተኛ ደረጃ ከአድሃሪ ኃይሎች ጋር የተፋጠጡት ግንባር ቀደም የገበሬ ማሀበራት ላይ ነው። በተለይ በደቡብ ኢትዮጵያ እነዚህ ማህበራት በአድሃሪዎች ተንኮልና አመጽ ለጊዜውም ቢሆን ታፍነው መራመድ ካቃታቸውና አሁን አዝማሚያው እንደሚያመለከተው መበተን ከጀመሩ ጠቅላላውን አድሃሪዎች የልብ ልብ የሚያገኙበት በመላ ኢትዮጵያ የማስተማሩና የማደራጀቱ ተግባር ቅስም የሚሰበረበት ሁኔታ ይፈጠራል። ትግልን ትግል እየወለደና እየተቀጣጠለ ከዚህ ከፍተኛ ደረጃ የደረሰው አብዮት ለጊዜው ተገታ ማለት ነው። አብዛኛው ዘማች በግንባር ቀደምትነት ሊያበረክት የሚችለው የማስተማርና የማደራጀት ተግባር የዚያኑ ያህል ትርጉምና አብዮታዊ ዓላማ ያጣል ማለት ነው። የዘማቾች ከገበሬው ጎን አለመለየትና ተግባራቸውን መቀጠል ትርጉም የሚኖረው አብዮቱ ሊቀጥል የሚችልበት ሁኔታ ሲፈጠር ብቻ ነው።

ስለዚህም ዘመቻው አሁን በያዘው መልክ ፈጽሞ መቀጠል አይችልም። እስካሁን በተገኘው የስራ ልምድ፣ ባጋጠሙት ችግሮች፣ በሚቀርቡት መፍትሄዎች በእነዚህና በሌሎች ዘመቻውን በሚመለከቱ መአት ችግሮች ሰፊና ዴሞክራሲያዊ የሆነ ውይይት መደረግ አለበት። ከዚህ ሰፊ ውይይት የዘማቾች ጥረት መልካም ፍሬ ሊሰጥ የሚችልበትን የተደራጀ መልክ ይዞ እንዲወጣ ያስፈልጋል። በዚህ ጉዳይ አጠቃላይ ሀሳቦችን ከመሰንዘር አልፈን ዝርዝር ለመግባት አንችልም። ይህንን ሊያደርጉ የሚችሉት በያለበት በቅርቡ ከሕዝቡ ጎን ተሰልፈው በመታገልና በመሰዋት ችግሩን ሁሉ የቀመሱት ግንባር ቀደም ዝማቾች ናቸው። በበኩላችን ግን ለመደምደሚያ ያህል ሦስት አጠቃላይ ሃሳቦችን እንሰጣለን።

1ኛ/ በመጀመሪያ ደረጃ እንኳን የዘመቻውን ይቅርና የጠቅላላውን የኢትዮጵያ አብዮት የቅርብ ጊዜ እድል የሚወስነው የዲሞክራሲ መብቶችና የሰፊው ሕዝብ መታጠቅ ጉዳይ ሳይፈጸሙ ከአድሃሪዎችም ሆነ ከደርጉ በዘማቾች ላይ የሚደረገው የማሰር፣ የማጉላት፣ የማስፈራራት፣ የመረሸን ወንጀል ሳይቆም በዚህ ሁሉ መሃል የዘመቻው መቀጠል ምንም ትርጉም የለውም።

2ኛ/ ለአብዮቱ ተገቢ አስተዋጽኦ ሊያደርግ የሚችለው ከአሁን ወዲያ ዘመቻው በውስጡ ላሉት መአት ችግሮች መፍትሄ ከሰጠ በኋላ ስለሆነ፣ ለነዚህም ችግሮች መፍትሄ ለመሻት ከራሳቸው ከዘማቾች ተቀነባብሮ የቀረበ ሐሳብ ስለሌለ በጠቅላላው ከአመቱ ትግል የተገኘው ትምህርት ላይ ተመርኩዞና እቅድና ፕላን የሚያወጣ አንድ ብሄር አቀፍ የዘማች ወኪሎች ጉባዔ ባስቸኳይ መጠራት አለበት።

3ኛ/ ከውይይቱ በኋላ አንድ የዘማች ኮሚቴ በቋሚነት ተመስርቶ በመምሪያው ዕቅድና የሥራ አፈጻጸም ተካፋይና በተለይም ዘማቾችን በሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ ድምፅ እንዲኖረው ማድረግ አስፈላጊ ነው።

4ኛ/ ይህ እስካልተደረገ ድረስ ዘመቻው አሁን ባለበት የተዘበራረቀ መልክ ቢቀጥልም ወይም ደግሞ አሁን እንደተያዘው በተዘበራረቀ መልክ ቢበተን ሁለቱም ለአድሃሪዎች ሴራ የተመቸ ስለሆነ በዚህ በኩል በአብዮቱ ላይ ለሚደርሰው መሰናክልና ሃገራችን ለምትገባበት ውጥንቅጡ የወጣ ሁኔታ በታሪክ ፊት ተጠያቂ ከፀረ-ዲሞክራሲያዊ ደርግ ሌላ ማንም አይኖርም።

ዲሞክራሲያዊ መብቶች ይፈቀዱ
ሰፊ ሕዝብ ይታጠቅ
ብሄርአቀፍ የዘማች ወኪሎች ጉባኤ በአስቸኳይ
ቋሚ የዘማች ብሄርአቀፍ ኮሚቴ ይቋቋም
የኢትዮጵያ ሰፊ ሕዝብ ያሸንፋል።
Scroll to Top