ሰሕድ ቁ. 39

የሰፊው ሕዝብ ድምፅ

ቁጥር 39፣    ሚያዝያ 30፣ 1968

የፅሁፉ ፍሬ ሀሳብ

መኢሶን በዚህ የሰፊው ሕዝብ ድምፅ እትሙ፣ የመላ ኢትዮጵያ ሶሻሊስት ንቅናቄ የድርጅት ፕሮግራሙን በመጋቢት ወር 1968 ዓ.ም. በይፋ ለሕዝብ እንዳወጣና ይዘቱም የብሔራዊ ዲሞክራቲክ አብዮት ፕሮግራም እንደሆነ ይገልጻል። በዚህም መሠረት፣ ኢትዮጵያ ካለችበት የማህበራዊ እድገት ደረጃ አንጻር ተመጣጣኝ ፕሮግራም እንደሆነ በዝርዝር ያስረዳል። አያይዞም፣ ለሕዝቦቿ ጥቅም ሶስት ዋና ዋና ጠላቶች የሆኑትን ፊውዳሊዝም፣ ኢምፔሪያሊዝምና ቢሮክራቲክ ካፒታሊዝምን በማስወገድ ለወደፊት በረጅሙ መሠረታዊ ለውጥ ለማምጣት፣ መኢሶን የሚታገለው በዚህ መለስተኛ ፕሮግራሙ ትልም እንደሆነ ያረጋግጣል።

በዚህም መሠረት፣ በአንድ በኩል፣ መኢሶን አብዮታዊ የፖለቲካ መመሪያው ርዕዮተ አለሙ ማርክሲዝም ሌኒንዝም እንደሆነ ይገልጻል። በሌላ በኩል፣ትግሉ ግብ የሚመታው በሰፊው የኢትዮጵያ ሕዝብ ንቁና የተደራጀ ተሳትፎ ብቻ እንጂ፣ በጥቂት ግንባር ቀደም ነን በሚሉ ማንኛቸውም ኃይሎች ስብጥርጥር ጥረት እንዳልሆነ በአግባቡ ያረጋግጣል።

የሰፊው ሕዝብ ድምፅ

ለሰፊው ሕዝብ ሰራተኛ ገበሬ፣ ነጋዴ፣ ወታደር፣ ምሁር መብትና ጥቅም የሚታገል ጋዜጣ

የኢትዮጵያ ሰፊ ሕዝብ ይቅደም

ቁጥር 39                                                                     ቀን 30/8/68

 

መኢሶንና ኘሮግራሙ

መኢሶን፣ ምስጢራዊ መዋቅሩን ሳይገልጽ ሕልውናውንና ዝርዝር ኘሮግራሙን ባለፈው ወር በይፋ አስታውቋል። ይህ ኘሮግራም፣ መኢሶን ኢትዮጵያ በደረሰችበት የእድገት ደረጃ ለተነሱት ቅራኔዎች መፍትሄ ይሰጣል ብሎ የሚያምንበት የብሄራዊ ዲሞክራሲያዊ አብዮት ኘሮግራም ነው። የመኢሶን ኘሮግራም የኢትዮጵያ ሕዝቦች ሦስት ደመኛ ጠላቶቻቸውን ማለትም፣ ፊውዳሊዝምን፣ ኢምፔሪያሊዝምንና ቢሮክራሲያዊ ካፒታሊዝምን በመደምሰስ ለሶሻሊዝም ጽኑ መሰረት ሊገነቡ የሚያስችላቸው ኘሮግራም ነው። በተጨማሪም ይህ የመኢሶን ኘሮግራም፣ በፊውዳሊዝም፣ በኢምፔሪያሊዝምና በቢሮክራሲያዊ ካፒታሊዝም መደምሰስ ጥቅም የሚያገኙ የኢዮጵያ ጭቁን መደቦችና የሕብረተሰብ ክፍሎች ሁሉ (እነዚህም 90 በመቶውን የኢትዮጵያ ሕዝቦች ይጠቀልላሉ) ሊያቅፍ የሚችል ኘሮግራም ነው። ባጭሩ፣ የመኢሶን ኘሮግራም በማርክዚዝም ሌኒኒዝምና በታሪክ የተደገፈ አብዮታዊ ኘሮግራም ነው።

የዚህ የመኢሶን ኘሮግራም በዛሬው አብዮታዊ ወቅት በይፋ መውጣት ብዙ ታሪካዊ ትርጉሞች አሉት።

አብዮት የሰፊው ሕዝብ ሥራ ነው። የጥቂት ግንባር ቀደሞች የአብዮቱን ግብና ምንነት ማወቅ አንድን አብዮታዊ ትግል ከግብ አያደርስም። የአብዮቱ ባለቤት የሆነው ሰፊው ሕዝብ ይህ ለጉልበቱና ለሕይወቱ ሳይሳሳ የሚሳተፍበት አብዮት ምን እንደሚያመጣለት መረዳት አለበት። በሌላ አነጋገር፣ ሰፊው ሕዝብ ለዘመናት ያስመረረውን ሥርዓት በመታገል ላይ ሳለ፣ ይህን ሥርዓት ደምስሶ የትኛውን ሥርዓት ቢተካ ጊዜያዊ ሆኑ ዘላቂ ጥቅሞቹ እንደሚጠበቁ ማወቅ አለበት። በተለይ ከየካቲት ጀምሮ እስከ ዛሬ ካላከተመው የሁለት ዓመታት አብዮታዊ ትግል ድካሞች አንዱ፣ ይህ የዛሬው ትግል እንዴት ወደ ድል ሊያመራ እንደሚችል፣ሰፊው ሕዝብ አሮጌውን ሥርዓት ደምስሶ ምን ዓይነት ሥርዓት መገንባት እንዳለበት የሚያብራራና የሰፊውንም ሕዝብ ትግል ወደዚሁ አቅጣጫ የሚመራ ግንባር ቀደም ድርጅት አለመኖር ነው። ይህም  በመሆኑ እስከዛሬም ድረስ ስለአብዮታችንና ስለግባችን ምንነት በሰፊው ሕዝብ ውስጥ ሥር የሰደደ ቅስቀሳ አልተደረገም። ለተበታተነው የኢትዮጵያ ሕዝቦች ትግል አጠቃላይ መመሪያ የሚሰጥ ድርጅት ወይም ኘሮግራም አልነበረም። የመኢሶን ኘሮግራም አንዱ ዓላማ፣ ሰፊው ሕዝብ በብዙ ቆራጥነትና መስዋእትነት እዚህ ያደረሰውን አብዮታዊ ትግል ግቡንና ዓላማውን ጠንቅቆ በመረዳት ትግሉን በከፍተኛ ደረጃ ቀጥሎ ከፍጻሜ እንዲያደርስ የሚያስችለው አብዮታዊ መመሪያ ለመስጠት ነው።

በተለይ ከየካቲት 1966 ጀምሮ የሚካሄደው የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ትግል ጥልቀቱና ስፋቱ እየጨመረ፣ ታላላቅ ድሎችም እየተጐናፀፈ ይምጣም እንጂ አሁንም ቢሆን በተቀናበረ ሁኔታ አልተሰበሰበም። የአንድ ሕዝብ ትግል የፈለገውን ያህል ቆራጥነትና መስዋእትነት ቢኖረውም፣ በተበታተነ መልኩ ጠላቶቹን ድል ሊያደርግ አይችልም። በዛሬው የኢትዮጵያ ሁኔታ ከአገራችን የአብዮት ኃይሎች ይልቅ የኢትዮጵያ አብዮት ጠላቶች ይበልጥ ተደራጅተዋል፣ የሕዝቡን ትግል ለመቀልበስና የተገኙትንም ድሎች እንዳልነበሩ ለማድረግ በከፍተኛ ፍጥነት በመዘጋጀት ላይ ናቸው። ይህ ለአብዮታችን ትልቅ አደጋ እንደሆነ ለማንም ግልጽ ሊሆን ይገባል። በተበታተነ መልክ የሚታገለው ሰፊ ሕዝብ የጠላቶቹን የተደራጀ ኃይል ለዘለቄታው ሊቋቋም አይችልም። ስለዚህም የዛሬው አጣዳፊ ተግባር ይህን በብዙ ቆራጥነትና መስዋአትነት እዚህ የደረሰ የኢትዮጵያ ሕዝቦች የተበታተነ ትግል፣ የተደራጀ አብዮታዊ ኃይል እንዲሆን ማድረግ ነው። ይህም በመሆኑ፣ የመኢሶን ኘሮግራም አንደኛው ዓላማ፣ የኢትዮጵያ ሰፊ ሕዝብና እውነኛ ተራማጆች የዛሬውን አብዮታዊ ትግል በከፍተኛ ደረጃ ወደፊት መቀጠል ወይም መሸነፍ የሚወስን አጣዳፊ ጉዳይ መሆኑን ተረድተው በዚህ ኘሮግራም አካባቢ እንዲደራጁ ለማሳሰብ፣ ለመረዳትና ለመጋበዝ ነው። ሰፊው ሕዝብ በዚህ ኘሮግራም አካባቢ በፍጥነት ቢደራጅ፣ በጠላቶቹ ላይ ድልን በድል ላይ እየተጎናፀፈ ብሄራዊውን ዲሞክራሲያዊ አብዮት ከግብ ከማድረስ ወደ ሶሺያሊዝም ለመገስገስ ሙሉ ዋስትና እንደሚኖረው የመኢሶን እምነት ነው።

በአጠቃላይ አነጋገር፣ አሮጌውን ሥርዓት መጥላትና ግብን በደፈናው ማወቅ በራሱ ተወስዶ ለአንድ አብዮት መሳካት በቂ አይደለም። አብዮቱ በሚቆይባቸው ጊዜያቶች ውስጥ ለሚነሱ አዳዲስ ጥያቄዎች መልስ ለመስጠት መቻል ያስፈልጋል። አብዮቱ የሚያልፍባቸውን ደረጃዎች ጠንቅቆ በመረዳት አብዮታዊ ትግሉን ከአንደኛው ደረጃ ወደሌላኛው ሊያደርስ የሚችል ትክክለኛ ታክቲክ ለመንደፍ መቻል ያስፈልጋል። ወዘተ. ሰፊው ሕዝብ ለነዚህ ሁሉ ብቁ እንዲሆን ከራሱ ትግሎች ከሚያገኘው ንቃት አልፎ ሳይንስ ላይ በተመረኮዘ ሰፊ ቅስቀሳ ከፍተኛ ንቃት ማግኘት አለበት።

በዛሬው የኢትዮጵያ ሁኔታ ከአብዮታዊው ትግል ድካሞች ሌላኛው የሰፊው ሕዝብ አለመታጠቅ ነው። ጠላቶቻችን ድሮውንም ቢሆን የጭቆና ሥርዓታቸውን በቦታው ለማቆየት እስከ አፍንጫቸው ታጥቀዋል። ይህ አነሰ ተብሎ ዛሬም በኢምፔሪያሊስቶችና በአካባቢያችን አድሃሪዎች እርዳታ ትጥቃቸውን በማሳደግ ላይ ናቸው። ያልታጠቀ ሰፊ ሕዝብ የታጠቁ ጠላቶቹን ሊያሸንፍ አይችልም። ስለዚህም የኢትዮጵያ ሕዝቦች ትግል ከላይ የጠቀስነው ግብ ሊደርስ የሚችለው ሰፊው ሕዝብ በአስቸኳይ ለመታጠቅ የቻለ እንደሆነ ብቻ ነው። የመታጠቁ ጥያቄ፣ እንደ ንቃቱና እንደ ድርጅት ጥያቄ ሁሉ በቶሎ መመለስ ያለበት ጥያቄ ነው። የመኢሶን ኘሮግራም ሌላኛው ዓላማ፣ በኘሮግራሙ መግቢያ ላይ እንደተጠቀሰው ሁሉ፣ ሰፊው ሕዝብና እውነተኛ ተራማጆች እነዚህ ሦስት ሁኔታዎች ሳይሟሉ አብዮቱ ድልን ለመጎናፀፍ እንደማይችል እንዲረዱ ለማድረግና የዛሬው አብዮታዊ ትግል የነቃ፣ የተደራጀና የታጠቀ የትግል ጐዳና እንዲይዝ ለማገዝ ነው።

የየካቲት እንቅስቃሴ ገዥ መደቦች ባልጠበቁትና ባላሰቡት ጥልቀትና ስፋት ደርሶባቸው በከፊል ጠራርጓቸው ሲሄድ የብዝበዛ ሥርዓታቸውንም ከመሰረቱ አናግቷል። ግን ይህ አብዮታዊ እንቅስቃሴ እንደዱብ እዳ የደረሰው ገዥ መደቦች ላይ ብቻ አልነበረም። እውነተኛ ተራማጆችም እንደዚህ አይነቱን ስፋትና ጥልቀት ያለው አብዮታዊ እንቅስቃሴ በግንባር ቀደምነት ለመምራት ሳይዘጋጁና ሳይደራጁ የየካቲት እንቅስቃሴ መጥቶ ያገራችንን የመደብ ትግል ከከፍተኛ ደረጃ አደረሰው። ገና በጨቅላነት ላይ የነበረው የኢትዮጵያ ተራማጆች እንቅስቃሴ በሰፊው ሕዝብ ግብታዊ /ስፖንቴን የስ/ እንቅስቃሴ ተቀደመ። ይህም በመሆኑ እውነተኛ ተራማጆች የሰፊውን ሕዝብ አብዮታዊ ትግል ለመምራት ያለባቸውን የግንባር ቀደምነት ኃላፊነት ለመሸከም ሳይችሉ ቀሩ።

ባለፉት ሁለት ዓመታት በተካሄዱትም አብዮታዊ ትግሎች፣ እውነተኛ ተራማጆች ይህን የግንባር ቀደምነት ሚና ለመውሰድ ያልተቆጠበ ጥረት ቢያደርጉም፣ ዛሬም ቢሆን ለዚህ ታሪካዊ ሚና ብቁ አልሆኑም። ዛሬም የተራማጆች ትግል ከሰፊው ሕዝብ ግብታዊ ትግል ወደኋላ ቀርቷል። የሰፊውን ሕዝብ ትግል በግንባር ቀደምነት መምራት ያለባቸው ተራማጆች አብዮታዊውን ትግል በጭራነት ይከተላሉ። አሁንም ቢሆን የተራማጁ ሰፈር የተበታተነ ነው። የእውነተኛ ተራማጆች አንድነት ገና አልተመሰረተም። ይህም በመሆኑ የአወናባጆች እድሜ ተራዝሟል፣ የመከፋፈል ሙከራቸውም በመጠኑም ቢሆን ለእውነትኛ ተራማጆች እንደተለያዩ መቆየት ረድቷል። ይህ ሁኔታ በአስቸኳይ መቀየር አለበት። እውነተኛ ተራማጆች የሰፊውን ሕዝብ ትግል ከኋላ መከተላቸው አብቅቶ ለግንባር ቀደምነት በየሚናቸው በፍጥነት መደራጀትና መዘጋጀት አለባቸው። ለዚህም፣ ከሁሉ አስቀድሞ በሳይንሳዊ ርእዩተ ዓለምና በጠራ የፖለቲካ መስመር ላይ የተመሰረተ የእውነተኛ ተራማጆች የትግል አንድነት መገንባት አለበት። የመኢሶን ኘሮግራም ሌላኛው ዓላማ፣ በዚህ ኘሮግራም አካባቢ የእውነተኛ ተራማጆችን የትግል አንድነት ለመመስረትና ታሪካዊ ኃላፊነታቸውን ለመሸከም ብቁ እንዲሆኑ ለማገዝ ነው። መኢሶን እስካሁንም የእውነተኛ ተራማጆችን የትግል አንድነት ለመመስረት ያደረገው ጥረት ብዙ ቦታዎች ፍሬ እየሰጠ ነው። ወደፊት መኢሶን ይህን የእውነተኛ ተራማጆች የትግል አንድነት ለመመስረት በግንባር ቀደምነትና በቆራጥነት ይታገላል።

የመኢሶን ኘሮግራም አብይ ዓላማዎች ባጭሩ እነዚህ ናቸው። መኢሶን በኘሮግራሙ መግቢያ ላይ እንደገለፀውም፣ ለነዚህ አብይ ዓላማዎቹና በጠቅላላው ለኘሮግራሙ ሥራ ላይ መዋል

“…ያለአንዳች ማወላወል፣ በምስጢርና በይፋ፣ በሕጋዊ መንገድና በሕገወጥነት፣ በሰላማዊ መንገድና በአመጽ፣ እንደ ጊዜውና እንደሁኔታው በሚለዋወጥ ታክቲክ፣ ምንም ጊዜና ምንም ሁኔታ በማይለውጠው ቆራጥነትና ታታሪነት የሚታገሉ አብዮታውያንን አስተባብሮ ለኢትዮጵያ ሰፊ ሕዝብ ነፃነትና እድገት አሰልፏል። የኢትዮጵያ ጭቁኖች የሚያደርጉትን ትግል ከዳር እስከ ዳር አስተባብሮ፣ የተጣራ አብዮታዊ አመራር ለመስጠት በጭቁን ሕዝቦችና በታሪክ ፊት የተቀበለውን አደራ እስከመጨረሻው ይጠብቃል። ጭቁኖች በትግላቸው እንዲገፉ፣ በትግል እሳት የተፈተኑ አባሎቹ አብዮታዊ ግዴታቸውን ከመፈጸም ወደኋላ እንደማይሉ ሙሉ እምነት አለው።”

የመኢሶንን አብይ ዓላማዎችና ታሪካዊ ትርጉማቸውን ከላይ ባጭሩ ገልፀናል። በሚቀጥሉ የጋዜጣችን እትሞች የኘሮግራማችንን ይዘቶችና ታሪካዊ ቦታቸውን በማሳየት በየጊዜው ማብራሪያዎች እንሰጣለን። ለዛሬው ግን በኘሮግራሙ ሁለት ነጥቦች ላይ እንወስናለን።

 

ስለመኢሶን አርማ

የንቅናቄያችን አርማ ዙሪያውን በስንዴ የተከበበ ሆኖ በመሃሉ መዶሻና ማጭድ እንዲሁም አሥራ ሁለት /12/ ትናንሽ ከዋክብትና አንድ ትልቅ ኮከብ ይገኙበታል። በክቡ ዙሪያ ያለው ስንዴ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ሦሶት ደመኛ ጠላቶቻቸውን አሸንፈው በሚመሰርቷት ኢትዮጵያ የሚኖረውን እድገትና ልምላሜ ለመግለጽ ነው። መዶሻውና ማጭዱ የኢትዮጵያ አብዮት መሪ የሆነውን ወዛደርና የኢትዮጵያ አብዮት ምሶሶ የሆነውን አርሶአደር የትግል ሕብረት የሚያመለክት ነው። 

12ቱ ከዋክብት የቆሙት በአገራችን በፊውዳሊዝም፣ በኢምፔሪያሊዝምና በቢሮክራሲያዋ ካፒታሊዝም የሚጨቆኑና የሚበዘበዙ፣ በእኩልነት ላይ በተመሰረተ ሕብረት ለነጻነት፣ ለእድገና ለሶሺያሊዝም የሚታገሉ የኢትዮጵያ ብሄረሰቦችን ሰፊ ሕዝብ ለማመልከት ነው። የነዚህ ከዋክብት 12 መሆን በአገራችን ያሉ ብሄረሰቦች 12 ብቻ ናቸው ማለት አይደለም። ማንም እንደሚያውቀው በአገራችን ያሉ ጭቁን ብሄረሰቦች በጣም ብዙ ናቸው። ብዙ ከመሆናቸውም የተነሳ በአንድ አርማ ላይ እያንዳንዱ ብሄረሰብ በአንድ ኰከብ እንዲወከል ለማድረግ አይቻልም። ስለዚህ፣ በአርማችን ላይ ያሉ 12 ከዋክብት የቆሙት ለ12 ብሄረሰቦች አይደለም። በጠቅላላው ኢትዮጵያ በአራቱም ማዕዘን ላሉት ብሄረሰቦች ሁሉ የቆሙ 12 ከዋክብት ናቸው። 

መሃል ላይ ያለ ትልቅ ኰከብ፣ በአርማችን ላይ በ12 ትናንሽ ከዋክብት የተመለከቱት መላ የኢትዮጵያ ብሄረሰቦች፣ በእኩልነት ላይ በተመሰረተ ሕብረት፣ ፊውዳሊዝምን፣ ኢምፔሪያሊዝምን፣ ቢሮክራሲያዊ ካፒታሊዝምን በመደምሰስ ብሄራዊውን ዲሞክራሲያዊ አብዮት ካካሄዱ በኋላ ሶሻሊዝም ከሥር ከሥሩ በመገንባት የሚፈጥሯትን ሶሺያሊስት እናት አገር ኢትዮጵያን የሚያመለክት ነው። 

ስለብሄረሰቦች ጥያቄ

በመኢሶን ኘሮግራም በአገራችን ካሉት ዋና ዋና የፖለቲካ ጥያቄዎች አንዱ ስለሆነው የብሄረሰቦች ጥያቄ የሚከተለውን ይዟል። 

1.ብሄረሰቦች፣(የናሺናሊቲስ) የራሳቸውን እድል በራሳቸው ለመወሰን እስከመገንጠል ድረስ ያላቸው መብት የታወቀ ይሆናል። የኢትዮጵያ ብሄረሰቦች አንድነት፣ ብሄረሰቦች በአንድነት ለመኖር ባላቸው ፈቃደኝነት ላይና በእኩልነት፣ እርስ በርስ በመረዳዳት በሚያገኙት ጥቅም፣ በመፈቃቀር፣ በወንድማማችነት፣ በመከባበርና በመተባበር ላይ የተመሰረተና የተገነባ ይሆናል። 
2. እያንዳንዱ ብሄረሰብ የራሱን ታሪክ፣ ባህልና ልማድ ለማስፋፋት፣ በራሱ ቋንቋ ለመጠቀም ሙሉ ነፃነት ይኖረዋል። /የመኢሶን ኘሮግራም ገጽ 13 እና 14/ 

በመኢሶን እምነት፣ ስለብሄረሰቦች መብትና ነፃነት በኘሮግራሙ የሰፈረው ይህ አቋም፣ በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ዋና ዋና ከሆኑት የፖለቲካ ጉዳዩች አንዱ ለሆነው የጭቁን ብሄረሰቦች ጥያቄ ትክክለኛ መፍትሄ የሚሰጥ ነው። የኢትዮጵያን ጭቁን ሕዝቦች እውነተኛና በኩልነትና በመፈቃቀድ ላይ የተመሰረተ አንድነት ለመመስረት የሚያስችል ጐዳና የሚከፍት ነው። 

ኢትዮጵያ የብዙ ብሄረሰቦች አገር ናት። እነዚህ ብሄረሰቦች በሙሉ በፊውዳሊዝም፣ በኢምፔሪያሊዝምና በቢሮክራሲያዊ ካፒታሊዝም ሲጨቆኑና ሲበዘበዙ ኖረዋል።  ከዚህ በሁሉም ላይ ከደረሰውና ከሚደርሰው ብዝበዛና ጭቆና አልፎ ተርፎ፣ አብዛኞቹ የኢትዮጵያ ብሄረሰቦች እንደብሄረሰብ ሲጨቆኑ፣ ሲናቁ፣ ሲደፈሩና እንደሁለተኛ ደረጃ ዜጋ ሲቆጠሩ ቆይተዋል። ቋንቋቸውን እንዲያሳድጉ ሊታገዙ ይቅርና ቋንቋቸው እንዲጠፋና እንዳይበለጽግ ይጣር ነበር። ከዘመኑ ሥልጣኔ ትምህርት ለመካፈል የሌላ ብሄረሰብ ቋንቋ እንዲማሩ ይገደዱ ነበር። ባህላቸው እንዲያድግና እንዲዳብር ሊደረግ ይቅርና እንዲደመሰስና እራሳቸው እንኳ እንዲያፍሩበት ለማድረግ ይጣር ነበር። ታሪካቸው በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ታሪክ ተገቢ ቦታ ሊሰጠው ይቅርና ፍጹም ታሪክ እንደሌላቸው አድርጐ ለማቅረብ ይጣር ነበር። እነዚህ ጭቁን ብሄረሰቦች የነበረባቸውን የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካና የብሄር ጭቆና በመቃወም ለመብታቸው ያካሄዷቸውን ትግሎች ለመደምሰስ የቦንብ የጥይትና የመርዝ ጭስ ናዳ ይወርድባቸው ነበር። እስካሁን የነበረው የኢትዮጵያ ሕዝቦች “አንድነት” ይኸው በጭቆናና በጉልበት ላይ የተመሰረተ አንድነት ነው። ኢትዮጵያ የብዙ ጭቁን ብሄረሰቦች እስር ቤት እንጂ በእኩልነት፣ በመፈቃቀድና በመፈላለግ ላይ የተመሰረተ የጭቁን ሕዝቦች አንድነት የተመሰረተባት አገር አይደለችም። 

ይህቺን በእኩልነትና በመፈቃቀድ በመፈላለግ ላይ የተመሰረተ የጭቁን ሕዝቦች አንድነት የሰፈነባት ኢትዮጵያ ለመገንባት ከላይ ከጠቀስነው ሀቅ መነሳት ያስፈልጋል። ይህም ማለት የዛሬው የኢትዮጵያ “አንድነት” በአያሌ ብሄረሰቦች ጭቆና ላይ የተመሰረተ አንድነት መሆኑን ከመረዳት መነሳት ያስፈልጋል። 

የኢትዮጵያ ሕዝቦች በእኩልነት በመፈቃቀድና በመፈላለግ ላይ የተመሰረተ አንድነታቸውን ለመገንባት፣ ሁሉንም ብሄረሰቦች የሚበዘብዘውንና የሚጨቁነውን ሥርዓት መደምሰሰ አለባቸው። ፊውዳሊዝምን፣ ኢምፔሪያሊዝምንና ቢሮክራሲያዊ ካፒታሊዝምን በመደምሰስ ብሄራዊውን ዲሞክራሲያዊ አብዮት ከግቡ ማድረስ አለባቸው። ከነዚህ ሦስት ዋነኛ ጠላቶች የተላቀቀች ኢትዮጵያ አንዱ ብሄር ሌሎችን የሚጨቁንባት ኢትዮጵያ ልትሆን አትችልም። ማንኛቸውም ዓይነት የአንድን ብሄረሰብን የበላይነት የሚያፀድቁ ሕጐች፣ ወጐችና ልማዶች የሚደመሰሱባት፣ ብሄረሰቦች ሁሉ በእኩልነት በመፈቃቀርና በመፈላለግ በአንድነት የሚኖሩባት ኢትዮጵያ ብቻ ነው ልትሆን የምትችለው። 

እዚህኛው ግብ ለመድረስ፣ የዛሬው የብሄር ጭቆና የሚያስነሳቸውን ጥያቄዎች ለመመለስና እንደአንድ የጭቆና ዘርፍ የሚጠፋበትን መንገድ ለማመልከት መቻል አለብን። 

የጭቁን ብሄረሰቦችና የጨቋኝ ብሄረሰብ ሰፊ ሕዝቦች በመሰረቱ የተለያየ ግብ፣ የተለያዩ ጠላቶች የሏቸውም። በጨቋኝ ብሄረሰብ ስም የጭቁን ብሄረሰቦችን ሰፊ ሕዝብ የሚጨቁኑትና የሚበዘብዙት የዚሁ ጨቋኝ ብሄረሰብ ገዥ መደቦች ናቸው። ይህም ሀቅ ለትግላቸው [የማይታይ መስመር – አዘጋጆች]   

ይህንን የጭቁን ብሄረሰቦችና የጨቋኝ ብሄረሰብ ሰፊ ሕዝቦች የትግል አንድነት ለመመስረት የገዥ መደቦች የዘመናት የጥላቻና የከፋፍለህ ግዛ ፖሊሲ ያስከተለው መቃቃር መወገድ አለበት። ይህም ማለት፣ የጨቋኝ ብሄር ትምክህተኝነት መወገድ አለበት። በጨቋኝ ብሄረሰብ ሰፊ ሕዝብና በጭቁን ብሄረሰቦች መሃል አስፈላጊውን የትግል ትብብር ለመመስረት በመጀመሪያ ደረጃ እንቅፋት የሚሆነው ይኸው የጨቋኝ ብሄረሰብ ሰፊ ሕዝብ የጭቁን ብሄረሰቦችን እኩልነት በመቀበል፣ የራሱ ገዥዎች በጭቁን ብሄረሰቦች ሲፈጽሙ የኖሩትን ግፍና በደል ለማውገዝ፣ ከጭቁን ብሄረሰቦች ጋር ጐን ለጐን ተሰልፎ በጋራ ጠላታቸው ላይ መዝመት አለባቸው። ስለዚህም፣ የጭቁኑን ሰፊ ሕዝብ የትግል ትብብር ለመመስረት አስቀድሞ የጨቋኝ ብሄርን ትምክህተኛነት መታገል ያስፈልጋል። 

በሁለተኛ ደረጃ፣የጨቋኝ ብሄረሰብን ሰፊ ሕዝብና የጭቁን ብሄሰቦችን ሰፊ ሕዝቦች የትግል ትብብር ለመመስረት እንቅፋት የሚሆነው የጭቁን ብሄረሰቦች ጠባብ ብሄረኛነት ነው። የጭቁን ብሄረሰቦችን ጠባብ ብሄረኛነት የሚወልደው የጨቋኝ ብሄረሰብ ትምክህተኛነት ነው። ይህንን መረዳት ያስፈልጋል። ቢሆንም፣ በዚህ የጭቁን ብሄረሰቦች ጠባብ ብሄረኛነት የሚጠቀሙና ይህ ተራዝሞ እውነተኛ የጭቁኖች በእኩልነተ ላይ ተመሰረተ የትግል አንድነት እንዳይመሰረት የሚጥሩ የጭቁን ብሄረሰቦች አድሃሪ ክፍሎች ናቸው። ስለዚህም፣ይህን በጭቁን ብሄረሰቦች አድሃሪ ክፍሎች የሚታገዘውንና የሚለፈፈውን ጭቁን ብሄረሰበች ጠባብ ብሄርተኛነት በሁለተኛ ደረጃ መታገልና ለእውተኛ የጭቁን ሰፊ ሕዝቦች አንድነት መቆም ያስፈልጋል። 

በጨቋኝ ብሄረሰብና በጭቁን ብሄረሰቦች ሰፊ ሕዝቦች መሃል በጠንካራ መሰረት ላይ፣ በመተማመንና በመፈላለግ ላይ የተመሰረተ አንድነት ሊኖር የሚችለው የጭቁን ብሄረሰቦች የራስን እድል በራስ የመወሰን መብት በማያሻማ ሁኔታ ሲታወቅና ሲገለጽ ብቻ ነዉ። ይህም የመገንጠልን መብት ይጨምራል። 

ከላይ እንዳልነው፣ የኢትዮጵያ ሕዝቦች እስካሁን አንድ ላይ የኖሩት በጉልበትና በጭቆና እንጂ ወደውና አንድ ላይ መኖርን መርጠው አይደለም። ሆኖም ይህ ወደፊት በፈቃደኝነትና በእኩልነት መሰረት አንድ ላይ ለመኖር አይመርጡም ወይም አይችሉም ማለትን አያመለክትም። ነገር ግን ጭቁን ብሄረሰቦች በዚህ በእኩልነት ላይ ለሚመሰረት አንድነት ሊሰለፉ የሚችሉት እስካሁን የተነፈጉትን የእኩልነት መብታቸውን ሲያገኙ ብቻ ነው። በግድ አብረው እንዲኖሩ የተደረጉ ጭቁን ብሄረሰቦች በውድ አንድ ላይ ለመኖር የሚፈቅዱት ይህ የእኩልነት መብታቸው በማያሻማ ሁኔታ ሲታወቅና ሲገለጽ ብቻ ነው። 

ይህ የብሄረሰቦችን የራስ እድል በራስ የመወሰን መብት ብዙ የብሄር ጭቆና መፍትሄዎችን ያጠቃልላል። ዋና ትርጉሙ በብሄረሰቦች መሃል የማያወላውለውን ገደብ የለሹን እኩልነት ሲሆን ከዚሁ ጋር የሚጣመረው ደግሞ፣ ማንም ሰው በአንድ ብሄረሰብ ጉዳይ ውስጥ በጉልበት ጣልቃ የመግባት መብት እንደሌለው የሚያሳዩ፣ ብሄረሰቡ የራሱን ኑሮ፣ ሕይወትና ሕልውና ለመወሰን ከራሱ በስተቀር ሌላ ኃይል እንደማይገባበት የሚገልጽ ነው። 

የአንድን ብሄረሰብ የራስን እድል በራስ የመወሰን እስከመገንጠል ድረስ ያለው መብት ማወቅ በርከት ያሉ የብሄር ጭቆና መፍትሄዎችን ያጠቃልላል። በአቋም ደረጃ፣ በአጠቃላይ ኘሪንሲኘል ደረጃ ከነዚህ የመፍትሄ መንገዶች አንዱን መቀነስ ወይም አንዱን ብቻ መጥቀስ ገና ከመጀመሪያው በብሄረሰቦች የራሳቸውን እድል በራሳቸው የመወሰን መብት ላይ ገደብ ማበጀት ነው። “አንቺው ታመጪው አንቺው ታሮጪው” እንደሚባለው ይህም የብሄረሰቦች የራስን እድል በራስ የመወሰን መታወቅ የታቀደለትን ግብ እንዳይመታ መሰናክል ማበጀት ነው። ይህም ማለት የብሄረሰቦችን ያልተገደበ መብት በማወቅ በመተማመንና በመፈቃቀድ ላይ የተመሰረተ አንድነት እንዳይመጣ ለሚሹ አድሃሪያን መግቢያ ቀዳዳ መተው ማለት ነው። 

ለምሳሌ፣ ከመርህ /ከኘሪንሲኘል/ አንፃር የመገንጠል መብት የብሄረሰቦች የራስን እድል በራስ የመወሰን መብት አንድ አካል ነው። የመገንጠል መብትን ማወቅና በመፈቃቀድ ላይ ለተመሰረተ አንድነት መታገል የማቃረኑ ማርክሲስት ሌኒኒስት አቋሞች ናቸው። የመገንጠል መብት ከብሄረሰቦች የራስን እድል በራስ የመወሰን መብት አንድ አካል መሆኑን በይፋ መግለጽ፣ብሄረሰቦች እንዲገነጣጠሉ መጋበዝ፣ መደገፍ፣ ወይም መገፋፋት አይደለም። ሆኖም፣ የመብቱ መታወቅና የመብቱ አጠቃቀም ጉዳይ ተለይቶ መታየት ያለበት ጉዳይ ነው። የአንድን ብሄረሰብ የመገንጠል ፍላጎት የሚያመጣው በመጀመሪያ ደረጃ የብሄረሰብ ጭቆና መኖር ነው። እንዲሁም በተለያዩ አብረው እንዲኖሩ በተገደዱ ብሄረሰቦች መሃል መቃቃርና ጥላቻ ሲሰፍን ነው። የአንድን ብሄረሰብ የመገንጠል ፍላጎት የሚያግዙ ወይም የሚገፋፉ ሁኔታዎች እነዚህና የመሳሰሉት እንጂ የራስን እድል በራስ የመወሰን መብት መገንጠልን ጨምሮ መታወቁ አይደለም። 

እዚህ ላይ ሌኒን የተጠቀመበትን ምሳሌ መጥቀሱ ይበጃል። ለምሳሌ፣ ወደኋላ በቀሩ የጭቆና ሥርዓቶች ባል ሚስቱን እንደፈለገው የማስተዳደር መብት ሲኖረው ሚስትየዋ የመፍታት መብት የላትም ነበር። ሚስት የመፍታት መብት እንዲኖራት ብዙ ትግሎች ተደርገዋል። ይህም ባልና ሚስት አብረው እንዳይኖሩ ለማድረግ አልነበረም፣ የተከተለውም ውጤት ተቃራኒው ነበር። ሚስት የመፍታት መብቷ ቢታወቅላት ከባሏ ጋር የምትኖረው ተገድዳ መፍታት ስለማትችል ሳይሆን በፈቃዷ፣ አብሮ መኖር ለራሷና ለባሏም ደህንነት እንደሚጠቅም በመረዳት እንዲሆን ነበር። በዚሁ ምሳሌ መሰረት የብሄረሰቦችም መብት መገንጠልን ጨምሮ ሲታወቅ፣ መድረሻ ግቡ አንድ ብሄረሰብ ከሌሎች ጋር የሚኖረው ተገዶና የመገንጠል መብት ስለሌለው ሳይሆን፣ አብሮ መኖሩ ለራሱ ብሄረሰብና ለሌሎችም ጭቁኖች እንደሚጠቅም በመረዳት እንዲሆን ነው። ይህን መረዳቱ ደግሞ አብሮ ወደመኖር በይበልጥ እንደሚገፋፋ አይጠረጠርም። 

ቀደም ብለን በአንድ ቦታ የጭቁን ብሄረሰቦችንና የጨቋኝ ብሄረሰብን ሰፊ ሕዝብ የትግል አንድነት መመስረት ከሚያደናቅፉት አንዱ የጭቁን ብሄረሰቦች ጠባብ ብሄርተኝነትና በዚህም ሊጠቀሙና ይህንኑ ለማስፋፋት የሚጥሩ አድሃሪዎች መኖር መሆኑን ጠቅሰን ነበር። እነዚህ አድሃሪ ኃይሎች ይህንን የብሄረሰቦች የመገንጠል መብት ለራሳቸው ጥቅም ለማዋል እንደሚታገሉ ግልጽ ነው። እነዚህን አድሃሪዎች መታገያ መሳሪያ ለማሳጣት የብሄር ጭቆና ያሳደረውን መቃቃርና ጥላቻ አሸንፎ በተለይም የጨቋኝ ብሄረሰብ ሰፊ ሕዝብና ተራማጆች በገዥ መደቦቻቸው በደል ከደረሰባቸው ጭቁን ብሄረሰቦች ጥርጣሬ እንዳይደርስባቸው የጭቁን ብሄረሰቦች የራስን እድል በራስ ለመወሰን እስከመገንጠል ድረስ ያላቸውን መብት ማወቅ አለባቸው። ይህ ሲደረግ እነዚህ የጨቋኝ ብሄረሰብ ሰፊ ሕዝብና ተራማጆች የብሄር ጭቆናን ለማጥፋት ያላቸውን ፍላጎት ለጭቁን ብሄረሰቦች በገቢር ሊያሳዩ ይችላሉ። 

የተጨቋኝ ብሄረሰቦች አድሃሪዎች የብሄረሰቦችን የመገንጠል መብት ለራሳቸው ጥቅም ለማዋል የሚያደርጉትን ትግል ለማክሸፍና ሌላኛው ሃላፊነት የሚወድቀው በጭቁን ብሄረሰቦች ተራማጆች ትከሻ ላይ ነው። እነዚህ የጭቁን ብሄረሰቦች ተራማጆች፣ የብሄረሰባቸውን አድሃሪዎች ለማጋለጥ የሰፊውን ጭቁን ብሄር ድጋፍ ሊያሰጣቸው ይገባል። ለጭቁን ብሄረሰቦች ትግል ትክክለኛ አመራር በመስጠት የጭቁን ብሄረሰቦች ትግል ለሰፊው ሕዝብ ጥቅም የሚውልበትን ጐዳና ማስያዝ አለባቸው። በተጨማሪም፣የጭቁን ብሄረሰቦችንና የጨቋኝ ብሄረሰብ ሰፊ ሕዝቦች አንድነት ጠቃሚነት በመረዳትና በማስረዳት ጠባብ ብሄርተኝነትን በመቃወም ለእውነተኛ የጭቁኖች አንድነት መታገል አለባቸው። 

የጨቋኝ ብሄረሰብ ተራማጆች ለመገንጠል መብት መታወቅ፣ የጭቁን ብሄረሰቦች ተራማጆች ለአንድነትና ለመዋሃድ በቆራጥነት ሲታገሉ የጨቋኝ ብሄረሰብን ትምክህተኝነትና የጭቁን ብሄረሰብን ጠባብ ብሄርተኝነት በማክሸፍ እውነተኛ የጭቁኖች አንድነት ይገነባሉ። 

በሌላ አንፃር የራስን እድል በራስ የመወሰን አንድ አካል የሆነው የመገንጠል መብት ከአቋምና ከኘሪንሲኘል ጥያቄነት አልፎ የገቢር ጥያቄ ሲሆን ከቀረበበት ተጨባጭ ሁኔታ አንፃር መመርመር ይኖርበታል። የመገንጠሉ ጥያቄ በገቢር በተነሳበት ተጨባጭ ሁኔታ የአንድ ብሄረሰብ መገንጠል ለዚህ ብሄረሰብ ጨቋኞች እንጂ ለዚህ ብሄረሰብ ሰፊ ሕዝብ የሚያመጣው ጥቅም ከሌላ፣ መገንጠሉ የብሄርን ጭቆና በኢምፔሪያሊስት ጭቆና የሚተካ ከሆነ፣ ለተገንጣዩ ሰፊ ሕዝብ ነፃነት ከማምጣት ይልቅ፣ ወይም የጊዜውን ዋና ጠላቶች ፊውዳሊዝም፣ ኢምፔሪያሊዝምንና ቢሮክራሲያዊ ካፒታሊዝምን ከማዳከም ይልቅ የአካባቢውን አብዮታዊ ሁኔታ ለመቀልበስ የሚያሰጋ ከሆነ፣ የዚህ ብሄረሰብ መገንጠል በገቢር የሚደገፍበት ምክንያት የለም። በዚህ መብት ካልተጠቀምን ብለው የተነሱ ኃይሎች ሁሉ ደግሞ በታሪክ ተደግፈውም አያውቁም። ዛሬም የጭቁን ብሄረሰቦች ሰፊ ሕዝብን ዘላቂ ጥቅምና ደህንነት ተፃራሪ፣ ጭቁን ብሄረሰቦች ለአርነታቸው የሚያደርጉትን ተጋድሎ የሚያጨናግፉ ኃይሎች የመገንጠሉን መብት ሥራ ላይ ለማዋል ሲነሱ ከተራማጁ ዓለም /ከራሳቸውም ተራማጆች ጭምር/ የመረረ ተቃውሞ ይደርስባቸዋል። 
ዛሬ፣ ከጨቋኝና ከተጨቋኝ ብሄረሰቦች የተውጣጡ አድሃሪዎች በመሃላቸው ያለውን የብሄር ልዩነት ወደጐን ጥለው፣ የመደብ ጥቅማቸውን አስቀድመው በሕብረት ለፀረአብዮት ተዘጋጅተዋል። ይህ የአድሃሪዎች ሕብረት በኢትዮጵያ ጭቁን ሕዝቦች የትግል አንድነት መመታት አለባቸው። ለዚህም የኢትዮጵያ ሕዝቦች የመደብ ጥቅማቸውን አስቀድመው፣ በብሄር መከፋፈላቸውን ትተው በጋራ ይሰለፉ ማለቱ ብቻ አይበቃም። የመኢሶን ኘሮግራም እንዳደረገው ሁሉ የኢትዮጵያ ብሄረሰቦች የራሳቸውን እድል በራስ ለመወሰን ያላቸውን ያልተገደበ መብት በማወቅ በእኩልነትና በመፈቃቀር ላይ ለሚገነባ የጭቁን ሕዝቦች አንድነት መታገል ግዴታ ነው። 

የኢትዮጵያ ሕዝቦች የትግል አንድነት ይጠንክር
ፊውዳሊዝም፣ ኢምፔሪያሊዝምና ቢሮክራሲያዊ ካፒታሊዝም፣ ይውደሙ
የነቃ፣ የተደራጀና የታጠቀ ሰፊ ሕዝብ ያሸንፋል
Scroll to Top