ሰሕድ ቁ. 42

የሰፊው ሕዝብ ድምፅ

ቁጥር 42፣    ሰኔ 2፣ 1968

የፅሁፉ ፍሬ ሀሳብ

መኢሶን በዚህ የሰፊው ሕዝብ ድምፅ እትሙ፣ ኢሕአፓ የሚባል ድርጅት “በሶሻሊዝም” ስር በቅን ታጋዮችና በሕዝቡ መካከል ውዥንብር እየነዛና እያደናገረ አብዮቱን እያዘናጋ እንደሚገኝ ይገልጻል። ሆኖም፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን፣ የኢሕአፓ አወናባጅና ቀልባሽ ፖለቲካዊ አቋሞቹ በመኢሶን እየተጋለጠ፤ ከአድሃሪዎች ተራ እንደተሰለፈ በዝርዝር ያብራራል። በተጨማሪም፣ ኢሕአፓ “ፋሺስት” የሚለውን ደርግ እንዳመቸው “ከሕዝብ አብራክ የተገኙ” እያለና  እና ሙጥኝ ያለበትን “የጊዜያዊ ሕዝባዊ መንግሥትን” መፈክር ሲያወጣና ሲያወርድ  መሰነባበቱን ያስታውሳል። ከሰሞኑ ደግሞ  የፖለቲካ ሥልጣን በአቋራጭ መያዝ የሚቻል ስለመሰለው፣ የጊዜያዊ ወታደራዊ ደርግ በሚያዝያ 1968 ላወጣው የትግል አንድነት ጥሪ በቅርቡ መልስ እሰጣለሁ እያለ ዝግጅት ላይ እንዲሚገኝ ያትታል።        

የሰፊው ሕዝብ ድምፅ

ለሰፊው ሕዝብ ሰራተኛ ገበሬ፣ ነጋዴ፣ ወታደር፣ ምሁር መብትና ጥቅም የሚታገል ጋዜጣ

የኢትዮጵያ ሰፊ ሕዝብ ይቅደም

ቁጥር 42                                                                      ቀን 2/10/68

 

አብዮት ሲሉት ‘ወዴት’፣ ሥልጣን ሲሉት ‘አቤት’

ሰፊው ሕዝብ ድምጽ ጋዜጦችን ‘ኢህአፖ’ የተባለ አወናባጅ የንዑስ ከበርቴ ድርጅት ዲሞክራሲያ  በሚባል ልሳኑ የሚነዛውን የከሰረ ፖለቲካ፣ የሚያቀርበውን ፀረ ሳይንስ ትንተና የሚወረውራቸውን አድሃሪ መፈክሮች ማጋለጥ ከጀመረ ጊዜው ሩቅ አይደለም። በዚህ አጭር ጊዜ ውስጥ ብዙ የውይይት ጥያቄዎች ተነስተዋል፣ ብዙ የፖለቲካ ጥያቄዎች ቀርበው ሊብራሩ ችለዋል። በ‘ሶሺያሊዝም’ ስም እየተናገሩ ለአብዮታዊው ትግል መቀልበስ ነባራዊ ሁኔታውን በማመቻቸት ላይ ያሉ አወናባጆች መጋለጥ ጀምረዋል። የሆኖ ሆኖ፣ በዛሬው ተጨባጭ ሁኔታ የኢትዮጵያ ጭቁን ሕዝቦች ትግል በብሄራዊው ዲሞክራሲያዊ አብዮት ጐዳና ወደፊት እንዲገሰግስ ይህንን ቀልባሾችን ያግተለተለና ቅን ተራማጆችንም ያወናበደ ‘ኢህአፖ’ የሚባል ድርጅት በይበልጥ ገና በሰፊዉ ሕዝብ ፊት ማጋለጥና በትግሉ ሜዳ ድል መምታት ያስፈልጋል።

ዲሞክራሲያ፣ (ወይም ሽሙጥ እንዳቆላመጠቻት ‘ዲሞክራሲአይኤ) ውዥንብር ነዥነቷ፣ አቋም ቀያያሪነቷ፣ የቀልባሾች መሳሪያነቷ እየታወቀ ሄዷል። የዲሞክራሲያ መሪያዎች አቋማቸውን እንዳሰኛቸው እንደሚቀያይሩ ብዙ ምሳሌዎችን ማቅረብ ይቻላል። ቀደም ሲል፣ ወታደራዊውን መንግሥት ‘ፋሺስት’ ‘ፋሺስት’ ሲሉ ከረሙና መሃል ላይ ድንገት ‘ከሰፊው ሕዝብ አብራክ የወጡ’ ብለዋቸው ነበር። የዚያን ሰሞን የመሬቱ አዋጅ ወጥቶ ነበርና፣ ለደርጉ የመሬት አዋጅ ሰፊው ሕዝብ ድጋፉን ሰጥቶ ነበረና፣ ዲሞክራሲያ ‘ገበያው በደርግ ደጋፊነት ያዋጣል’ ብላ የያዘችው መስመር ነበር። እንደገና፣ መሬታቸውን የተነጠቁ፣ በስጋት ላይ የሚገኙ ባለንብረቶችና ተወናብደው አብዮቱን የከዱ ንዑስ ከበርቴዎች ባንድ ላይ የፀረ አብዮቱ ሰፈር እንዲያይል እየሞከሩ መሄዳቸው ‘ትኩስ’ ገበያ የከፈተ ስለመሰላት ዲሞክራሲያ ‘ፋሺስት፣ ፋሺስት’ ወደማለቷ ዞረች። የዲሞክራሲያ አቋም እንደገበያው መለዋወጥ ለችርቻሮ እንደሚቀርብ ለመረዳት ያ ጉደኛ የጊዚያዊ ሕዝባዊ መንግሥት ጥያቄ ስንት ጊዜ ወድቆ እንደተነሳ መመልከቱ ይበቃል። መቆየት ብዙ ያሳያልና፣ በቅርቡ ደግሞ ልዩ እትም ተብዬ የወጣ ዲሞክራሲያ ‘ምርጦች፣ ፋሺስት’ የሚሉት ቃላት የሌሉበት ሆኖ አገኘነውና ተገረምን።

ይህ ልዩ እትም ‘ለታክቲክ ምክንያቶች’ ቀን አልተፃፈበትም። ቀደም ብሎ ሚያዝያ 27/68 የወጣው ዲሞክራሲያ ግን

“የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፖርቲ ወታደራዊው መንግሥት ሚያዝያ 12 ቀን 68 ዓ.ም በይፋ ባቀረበው ጥሪ ላይ ያለውን አቋም ባጭር ጊዜ ውስጥ በይፋ እንደሚያወጣ ያስታውቃል።”

ብሎ ማስታወቂያ ተናግሮ ነበር። ይህንን ማስታወቂያ አይተን የጠበቅነው የዲሞክራሲያ መሪዎች ወደዱም ጠሉ በኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ትግል ትልቅ ቦታ ስለሚይዘው የደርጉ የብሄራዊ ዲሞክራሲያዊ አብዮት መለስተኛ ኘሮግራም ላይ አቋም ሊወስዱ ነው ብለን ነበር። ተአምረኛዋ ልዩ እትም ወጣችና ስናያት በአብዩ ጉዳይ ላይ እስከነጭራሹ አቋም አትወስድም። ትልቅ ቦታ የተሰጠውና አቋም የተወሰደበት ሻለቃ መንግሥቱ መለስተኛ ኘሮግራሙን ሲያስተዋውቅ ወደ መጨረሻው ላይ ‘ቶሎ ብለን አብዮታዊ ግንባር ማቋቋም አለብን’ ያለው ነው። ለዚያውም የዚያ ንግግር መልእክት እንኳ ለዲሞክራሲያ መሪዎች በደንብ አልገባቸውም። ከዚህ ‘አቋም’ ግልጽ የሆነ ነገር ቢኖር፣ ድሮውንም የዲሞ መሪዎች ትግል፣ ዓይን፣ ዦሮ ያተኮረው ሥልጣን ላይ እንጂ አብዮት ላይ እንዳልሆነ ነው።

ይህችን ጉደኛ የዲሞክራሲያ ልዩ እትም በራሷ ቅደም ተከተል እየተራመድን እንያት። ያዘለችው ፍሬ ከርሲኪ ለአንባቢ ግልጽ እንዲሆንም በሰፊው እንጠቃቅሳታለን።

“አዲሱ ዲሞክራሲያዊ አብዮትን ለማካሄድም በላብ አደሩ መሪነት በአርሶአደሩ አጋርነት በሌሎች ጭቁን መደቦችና የሕብረተሰብ ክፍሎች ተባባሪነት የሚቋቋም የጋራ ግንባር የፖለቲካ ሥልጣን መጨበጥ እንደሚኖርበትም አማራጭ የሌለው ግዴታ ነው”( ገፅ 1 ስርዝ የተጨመረ)

በዚህ ዓረፍተ ነገር ምን ለማለት እንደተፈለገ በይበልጥ ግልጽ እንዲሆን ከዚሁ ልዩ እትም ሌላ አባባል እንጠቅሳለን።

“ኢትዮጵያን በአራቱም ማእዘናት ያጥለቀለቀው አብዮታዊ ማእበል በይዘቱ ፀረ ፊውዳልና ፀረ ኢምፔሪያሊስት ቢሆንም በአዲሱ ዲሞክራሲያዊ ጐዳና አቋርጦ/ /ወደሶሻሊዝም እንዳይገሰግስ ካገዱት ነገሮች መካከል ዋነኛው የፖለቲካ ሥልጣን ጥያቄ አለመፈታት ነው።” (ገጽ 1፣ ሰርዝና ቅንፍ የተጨመረ)

እዚህ ላይ የዲሞክራሲያ አድሃሪዎች የሚነዙትን ውዠንብር ልብ ብሎ ማስተዋል ያስፈልጋል። መጀመሪያ የጠቀሥነው ውስጥ ዲሞዎች ‘የሰሩት የቅደም ተከተል ስህተት ነው’ ብለን ባለፍንላቸው ነበር። ሆኖም ይህ ‘የቅደም ተከተል ስህተት’ ለምን እንደሚደረግ ቀጥሎ ያስቀመጥነው ጥቅስ በጉልህ ያሳያል። በወዛደሩ ፖርቲ የሚመራው ግንባር ተቋቁሞ ሥልጣን የሚጨብጠው በብዙ ትግልና መስዋአትነት አዲሱን ዲሞክራሲያዊ አብዮት ካካሄደ በኋላ እንጂ አዲሱን ዲሞክራሲያዊ አብዮት ለማካሄድ አይደለም። ይህ አብዮት ተካሄዶ ከግቡ ሳይደርስ እንዴት ሥልጣን ይያያዛል? አስቀድሞ ሥልጣን ይዞ ከዚያ አብዮት ማካሄድ የትም ታይቶ አይታወቅም። በቻይና እነማኦ፣ በቪየትናም እነሆቺሚን አብዮቱን ካካሄዱ በኋላ ሥልጣን ያዙ እንጂ አብዮቱን ለማካሄድ በመጀመሪያ ሥልጣን አልያዙም። ሥልጣን ከያዙ በኋላ ደግሞ ሶሻሊዝምን መገንባት ጀመሩ።

ከላይ እንዳልነው ዲሞክራሲያ ምን ለማለት እንደፈለገች የበለጠ ግልጽ የሚሆነው “የኢትዮጵያ ሕዝቦች ትግል በአዲሱ ዲሞክራሲያዊ ጐዳና አቋርጦ ወደ ሶሻሊዝም እንዳይገሰግስ ካገዱት ነገሮች መሃል ዋነኛው የፖለቲካ ሥልጣን ጥያቄ አለመፈታት ነው” ከሚለው ነው። ዲሞክራሲያ በዚህ ልዩ እትሟ የድሮ ቋንቋዋን ለመጠቀም ሀፍረት ሀፍረት ብሏት እንደሆነ እንጂ በዚህ ዓረፍተ ነገር ለማለት የፈለገችው ‘ጊዜያዊ ሕዘባዊ መንግሥት ባለማቋቋሙ’ ነው። ግን ዓይን አፋር የመሆን ጉዳይ ሳይሆን ይህ እንደበግ ላት አንጠልጥላው የነበረ መፈክር በአድሃሪነቱና በቀልባሾች ጥያቄነቱ እጅግ ስለተጋለጠባት ለይምሰል በፊት በር ያስወጣች መስላ አሁን ደግሞ በጓሮ በር መልሳ ማቅረቧ ነው።

ከላይ እንዳልነው፣ የፖለቲካ ሥልጣን ጥያቄ ‘የሚፈታው’ ከአብዮቱ መሳካት በኋላ እንጂ በፊት አይደለም። ይህ እንኳን ከ“ላብ አደር ፖርቲ” የሚሰወር ሃቅ ሊሆን ይቅርና የአብዮታዊ ቴዎሪ ሀ ሁ ነው።

ከቲዎሪ ተመልሰን ይህን የዲሞክራሲያ አባባል ከኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ አንፃር እንመርምር። የኢትዮጵያን ሕዝቦች የትግል “በአዲሱ ዲሞክራሲያዊ አብዮት አቋርጦ ወደሶሺያሊዝም መገስገስ ‘ካገዱት’ ነገሮች መሃል ዋነኛው  “ለዚህ አብዮት መገስገስ መሰረታዊ የሆኑት የንቃት፣ የድርጅትና የትጥቅ ዝግጅቶች አለመሟላት ነው።” የፖለቲካ ሥልጣን ጥያቄ ያልተፈታው” ብሄራዊው ዲሞክራሲያዊ አብዮት ከግቡ ስላልደረሰ ነው። “ብሄራዊው ዲሞክራሲያዊ አብዮት ከግቡ ያልደረሰው ደግሞ በመካሄድ ላይ ያለው አብዮታዊ ትግል ዛሬም የነቃ፣ የተደራጀና የታጠቀ ይዘት ስለሌለው ነው። ይህ እንዲሆን የወዛደሩን መደብ በራሱ ፖርቲ ስር ተደራጅቶ መቅረብንና ለነቃ፣ ለተደራጀና ለታጠቀ የሕዝብ ትግል አመራር መስጠትን ይጠይቃል። የዲሞክራሲያን አባባል ከዚህ አብዮታዊ ሀቅ አንፃር ስንመለከት፣ “የአብዮቱ ‘መታገድ’ ዋነኛ ምክንያት የፖለቲካ ሥልጣን ጥያቄ አለመፈታት ነው” ማለት፣ በቀጥተኛ አነጋገር፣ ‘አብዮቱ የታገደው ከግቡ ስላልደረሰ ነው’ እንደማለት ነው። ወይም ደግሞ ‘አብዮቱ ለምን ከግቡ አልደረሰም’ ተብሎ ሲጠየቅ፣ ‘አብዮቱ ከግቡ ስላልደረሰ ነዋ’ ብሎ እንደመመለስ ያህል የሚቆጠር እንቆቅልሽ ነው። ግን ሆን ተብሎ የሚቀርብ እንቆቅልሽ!

አብዮታዊ የሥልጣን አያያዝን መንገድ ሆነ የኢትዮጵን ተጨባጭ ሁኔታ የመረመረ ማንኛውም ተራማጅ እንደሚረዳው፣ የኢትዮጵያ ጭቁኖች ‘የፖለቲካ ሥልጣን ጥያቄ ለመፍታት’ ገና በበቂ አልተዘጋጁም። ሥልጣን ከመያዝ ደግሞ ሥልጣን ለመያዝ መዘጋጀቱ ይቀድማል። ሥልጣን ለመያዝ መዘጋጀት ማለትም መንቃት፣ መደራጀት፣ መታጠቅ ማለት ነው። የኢትዮጵያ ጭቁን ሕዝቦች የዛሬ ትግል ድካምም ይኸው ሥልጣን ለመንጠቅ አለመዘጋጀታቸው ማለትም በበቂ አለመንቃታቸው፣ አለመደራጀታቸውና አለመታጠቃቸው ነው። ያለፉት ሁለት ዓመታት ትግሎች ይህን የኢትዮጵያ ሰፊ ሕዝብ የትግል ድካም ለማስወገድ ምቹ ሁኔታ ፈጠሩ እንጂ ድካሙን ገና አላስወገዱም። አሁንም የኢትዮጵያ ጭቁኖች ተቀዳሚ ትግል ይህንኑ ድካም ለማስወገድ ነው። አስቸጋሪም ቢሆን ባለ ኃይል ሁሉ ይህንኑ ድካም ለማስወገድ መታገል ነው። በነቃ፣ በተደራጀና በታጠቀ ትግል እንጂ በሌላ ዓይነት ተዓምር የመንግሥት ይልጣን መያዝ አይቻላቸውምና።

ለዲሞክራሲያ ግን ሁሉ ነገር የሚታያት ተገላቢጦሽ ነው። የትግሉ ግስጋሴ የታገደው ሥልጣን ስላልተያዘ ነው ትላለች። የኢትዮጵያ ሕዝቦች ደግሞ ሥልጣን ለመያዝ እንዳልተዘጋጁ ግልጽ ነው። የዲሞክራሲያም መፍትሄ ‘ሥልጣን ለመያዝ ያላስቻላቸውን ድካም ለማስወገድ መታገላቸውን ትተው ሥልጣን መያዝ አለባቸው’ የሚል ነው። ሰፊው ሕዝብ ሥልጣን ለመያዝ መዘጋጀቱን ትቶ፣ ማለትም የዛሬ ደካሙን ለማስወገድ መታገሉን ትቶ፣ ማለትም የዛሬ ትግሉን የነቃ፣ የተደራጀና የታጠቀ ጐዳና ለማስያዝ መታገሉን ትቶ፣ “ሥልጣን ለመያዝ” ቢታገል ደግሞ፣ የፈለገውን ያህል ይታገላታል እንጂ በፍጹም ሥልጣን አይይዝም። ስለዚህ፣ ይህን ዝግጅት አስትቶ፣ ይህ ዝግጅት ሳይደረግ የመንግሥት ሥልጣን ለመያዝ አትችልም የሚል ቅስቀሳ ትቶ ‘ሥልጣን ለመያዝ ታገለ’ ማለት ደግሞ የረቀቀ ማወናበድ ብቻ አይደለም። ዘወር ተደረገ እንጂ፣ በማር አነጋገር ተለወሰ እንጂ፣“ያንተን ዝግጅት ትተህ እኛ ሥልጣን እንድንይዝልህ ታገል” ማለት ነው። የቅድመ ዲሞክራሲያ ‘የቅደም ተከተል ስህተት’ ወደዚሁ ለማምራት እንዲረዳ ነው። ከላይ ከዲሞክራሲያ ልዩ እትም የጠቀሥነውን እንደገና ብንመለከት የቅድሙ እንቆቅልሽ አሁን ይፈታልናል። የኢትዮጵያ ሕዝቦች ትግል “በአዲሱ ዲሞክራሲያዊ ጐዳና አቋርጦ ወደ ሶሺያሊዝም እንዳይገሰግስ ካገዱት ነገሮች መካከል ዋነኛው የኢህአፖና የመሰሎቹ ሥልጣን አለመያዝ ነው።” እንግዲህ፣ የኢትዮጵያ ሰፊ ሕዝብ ዛሬ ሥልጣን ለመያዝ መዘጋጀቱን ትቶ፣ በቅድሚያ እነኢህአፖን ሥልጣን ለማስያዝ መታገል አለበት። ለዚህም ውለታ ‘ሥልጣን ለመያዝ ሙሉ ዝግጅት ሊያደርግ የሚያስችሉት መብቶች’ እንደ “ወሮታ” ይሰጡታል። የኢትዮጵያ ጭቁኖች እራሳቸው ሥልጣን ለመያዝ መዘጋጀቱን ይተው እንጂ እንዲህ ዓይነት “ወሮታ” እከፍላለሁ የማይል ጠላት የላቸውም። ሰሞኑን ለአንድ የምዕራብ ጋዜጣ በሰጠው ቃለ መጠይቅ ‘ከአልጋ ወራሹ ጋር ምንም ግንኙነት የለንም፣ የኛ ትግል ከፀረ ፋሺስት ተራማጆች ጋር ለመተባበር ነው’ ያለው የነመንገሻ ሥዩም/ ነጋ ተገኝ “የኢትዮጵያ ዲሞክራቲክ ሕብረት”ም ይህን ዓይነት ወሮታ ለመክፈል ቃል ገብቷል። አዎ! የኢትዮጵያ ጭቁኖች እራሳቸው ሥልጣን ለመያዝ ሳይዘጋጁ ቀድመዋቸው ከላያቸው ጉብ ለማለት ብዙ ጠላቶች ተዘጋጅተዋል።

ወደ ዲሞክራሲያ ልዩ እትም እንመለስ። ከላይ፡-

      “የፖለቲካ ጥያቄ አለመፈታት…ከመጀመሪያውም አብዮቱን ልጓም ያሥነከሰ ቢሆንም ሁኔታው ከእለት ወደ እለት እየተለዋወጠ ሲሄድ ልጓሙም እየጠበቀ፣ አብዮቱም አቅጣጫውን ይዟል ማለቱ ይበልጥ እያዳገተ ሄዷል።”

የሚል ‘ክፉ ወሬ’ በገጽ 1 ላይ ተነግሮን፣ ከዚሁ ገጽ ላይ ትንሽ ዝቅ ስንል ደግሞ፣

“ፀረ ፊውዳልና ፀረ ኢምፔሪያሊስቱ ትግል ከቀድሞው ብዙ እጅ ልቆ ይበልጥ የሕብረተሰብ ክፍሎች በውስጡ አክሎ፣ወደፊት እየገሰገሰ ነው። የንቃት መጠን እየመጠቀ፣ የድርጅት ገመድ እየጠበቀ ትግሉ ከእለት ወደእለት እየከረረና እየተጠናከረ በመሄድ ላይ ይገኛል።”

የሚል ‘ቸር ወሬ’ ተበሰረልን።

በመጀመሪያ የዚህ ጉደኛ “ላባደር ፖርቲ” ስለዚህም “የኢትዮጵያ ሕዝቦች ግንባር ቀደም” አብዮቱ ምን ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ አለማወቅ ገረመን። መቼም አንድ አብዮት ባንድ ጊዜ ሁለት ቦታ ላይ ሊገኝ አይችልም። ማለትም አንዴ አቅጣጫ መያዙ እያጠራጠረ፣ አንዴ ደግሞ እየመጠቀ፣ እየጠበቀ፣እየከረረ. . .  ወደፊት መገስገስ አይችልም። ከሁለት አንዱ ነው። “ግንባር ቀደምን” ያህል ነገር ግን አብዮቱ ወይ አቅጣጫ ይሳት ወይ እየመጠቀ .  .  . ይሂድ በውል ገብቶት ሊነገረን አልቻለም።

ሁለተኛ ሃሳብ ላይ የዲሞክራሲያን ‘ደጋፊዎች’ አሰብን። ዲያቢሎስ የገሃነመ እሳት ደንበኞቹን አንዴ ሙቅ ውሃ ውስጥ አንዴ ቀዝቃዛ ውሃ ውስጥ እየጨመረ ያሰቃያል የሚባለው ‘ታሪክ’ ትዝ አለን። ዲሞክራሲያም ደጋፊዎቹን አንዴ ‘አብዮቱ አቅጣጫ ይዟል ለማለት አዳግቷል’ የሚል መርዶ ነገሮ ሲያስለቅስ፣አንዴ ብዙም ሳይቆይ፣ ‘አብዮቱ እየመጠቀ፣ እየጠበቀ፣ እየጠበቀ፣እየከረረ፣ እየተስፋፋ ወደፊት በመገስገስ ላይ ነው’ የሚል የምስራች ነገሮ ሲያስደስት ግራ መጋባታቸው ታየንና አዘንንላቸው።

በሶስተኛው ይህ ተቃራኒ ግምት የዲሞክራሲያን አድሃሪ የትግል ዘዴ ቁልጭ አድርጐ አሳየን። ‘አብዮቱ አቅጣጫ ስቷል’ የሚለው “እኛ ሥልጣን ካልያዝን ወዩላችሁ” በሚል ማስፈራሪያ ለኢህአፖና ለኢዲዩ ‘ጊዜያዊ ሕዝባዊ መንግሥት’ አዳኝነት የሚቀርበው የጨረታ ማስታወቂያ ነው።  ‘አብዮቱ ከረረ፣ መጠቀ፣ ጠበቀ. . . የሚለው ደግሞ የኢትዩጵያን ሕዝቦች ዛሬ ሥልጣን ለመያዝ አለመቻል ሸፍኖ ‘ሥልጣን ለመያዝ በቅታችኋል፣ የኛ ሥልጣን መያዝ እኮ የናንተም ሥልጣን መያዝ ነው’ ለማለት የቀረበው የድለላ ማስታወቂያ ነው።

እንቀጥል። ለሥልጣኑ አያያዝ በአብዮትም በአብዮታዊ ሳይንስም ታይቶ የማይታወቅ ‘የቴዎሪ ዝግጅት’ ከተደረገ በኋላ ዲሞክራሲያ ትቀጥልና፡

“አብዮቱን ወደፊት ማራመድ የሚችል፣ ለአብዮቱ እድገት የጋት ታህል እንኳ መንገድ የሚከፍት ሁኔታ ከተፈጠረ ያንን ሁኔታ መርምረን መሰረታዊ እምነታችንን ሳንለቅ በዚህ ሁኔታ ለመጠቀም መሞከር አብዮቱ ውስጥ የምንጫወተው ሚና የጣለብን ግዴታ ነው። ወታደራዊው መንግሥት ሚያዝያ 12 ቀን 1968 ለአብዮታዊ ግንባር መቋቋም ያቀረበውን ጥሪ በመሰረተ ሃሳቡ የምንቀበለው ለዚህ ነው”/ገጽ 2/

በዚህ ጥቅስ መገረም የምንጀምረው፣ ‘ለአብዮቱ የጋት ያህል እንኳ መንገድ የሚከፍት ሁኔታ ከተፈጠረ በዚህ ሁኔታ ለመጠቀም መሞከሩ . . . የተጣለብን ግዴታ ነው’ ከሚለው ዓረፍተ ነገር አንስተን ነው። ደርጉ እስከዛሬ ድረስ ብዙ ተራማጅ እርምጃዎች ወስዷል። እነዚህም እርምጃዎች ለአብዮቱ እድገት ‘የጋት ያህል’ ሳይሆን ትላልቅ ‘መንገዶች’ የከፈቱ ናቸው። ታዲያ የኢህአፖ ሰዎች እነዚህን ተራማጅ እርምጃዎች ‘ፋሺዝምን ለማጠናከር የወጡ ናቸው’ እያላችሁ እንዲቀለበሱ ስትታገሉ እንጂ አብዮቱን ለማራመድ ስትጠቀሙባቸው ታይታችሁ አታውቁም። እንዲያውም እነዚህን ተራማጅ እርምጃዎች ለመቀልበስ በምታደርጉት ‘ፀረ ፋሺስት’ ትግል አንካፈልም ብለው ተራማጅ እርምጃዎቹን በመጠቀም አብዮቱን ለማራመድ የሚታገሉ ተራማጆችን ‘ባንዳ’ የሚል ስያሜ ሰጥታችሁ ዋና ጠላት አድርጋችኋቸዋል። ታዲያ እስካሁን የነበሩትን የደርግ ተራማጅ እርምጃዎች ተጠቅማችሁ አብዮቱን ወደፊት ለመራመድ ሳትሞክሩ ምነው የዛሬው አቋማችሁ አዲስና የተለየ ሆነ! ምክንያቱ ግልፅ ነው።

ካሁን በፊት የተወሰዱት ተራማጅ እርምጃዎች ለትግል፣ በርግጥም አብዮቱን ለማራመድ የሚበጁ ስለነበሩ ተቃወማችሁ። ያሁኑ ግን ሥልጣን ያዙ /ተካፈሉ/ የሚል ስለመሰላችሁ ‘በዚህ ሁኔታ መጠቀም ግዴታችን ነው’ አላችሁ። ሥልጣን ሲሉት ‘አቤት’ አብዮት ሲሉት ‘ወዴት’ የሚል “የላብአደር ፖርቲ” እናንተን አየን።

ከዚህ ጥቅስ ሁለተኛው አስገራሚ ነገር፣ ‘ወታደራዊ መንግሥት ለአብዮታዊ ግንባር መቋቋም ያቀረበውን ጥሪ በመሰረተ ሃሳቡ እንቀበላለን’ የሚለው ነው። ማን ጠራችሁ ማን ጋበዛችሁ ‘ጥሪ’ ከተባለ ጥሪው የቀረበው ለሰፊው የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው። እናንተ ግን ሥልጣን ለመያዝ ያላችሁ ጉጉት ጆሮዎችሁን ደፍኖ አይናችሁን አሳውሮ የተደረገው ‘ጥሪ’ እንኳ አልገባችሁ አለ። ‘ፋሺስት’ የምትሉት /ትሉት የነበረው/ ደርግ በአዋጅ እንኳን ደረጃ ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንፈስ ‘የሰፊው ሕዝብ ትግል ተደራጅቶና ገፍቶ አብዮታዊ ግንባር እንደተቋቋመ . . .’ እያለ ሰፊው ሕዝብ ሲደራጅ ‘ሥልጣን እንደሚያስረክብም’  ተናገረ። እናንተ፣ ይህን ሰፊው ሕዝብ ተደራጅቶ፣ አብዮታዊ ግንባር መስርቶ ሥልጣን ይያዝ የሚለው ጥሪ ሳትሰሙት ቀርታችሁ ሳይሆን አስደነገጣችሁ። ሰፊው ሕዝብ ይህን ‘ጥሪ’ ተቀብሎ ከተነሳና ከተደራጀ ከሕዝቡ ጀርባ ሥልጣን ለመያዝ የምታደርጉት ሴራ እንደሚቀጭባችሁና የናንተ ሥልጣን መያዝ ህልም ሆኖ እንደሚቀር ገባችሁ። ስለዚህ፣ ደርጉ ይህን ‘ስህተት’ ሳይሰራ፣ ማለት ሰፊው ሕዝብ ደርጉን የሚተካበትን ሁኔታ የበለጠ የሚያመቻች እርምጃ ሳይወስድ፣ ከርሱ ጋር ‘በመግባባት’ ሥልጣን ለመያዝ የምትችሉ መሰላችሁና ተቻኩላችሁ ላልተጠራችሁበት ግብዣ ‘እሺ እንመጣለን’ አላችሁ። ደርጉ ይህን ሕዝቡ ተደራጅቶ ሥልጣን ለመያዝ እንዲበቃ ያደረገውን ‘ጥሪ’ ትቶ፣ ከናንተ ጋር ግንባር ፈጥሮ ሥልጣን እንድትጋሩ ማመልከቻ አቀረባችሁ።

ማመልከቻችሁ ማመልከቻ እንዳይመስልባችሁ ‘የጥሪ መልስ’ ብላችሁ ሰየማችሁት። ለዚህ ግብዣ ገና ሳትጠሩ መኳኳል ስትጀምሩም ለወትሮ ባንድ ገጽ ጽሁፋችሁ 10 ጊዜ እየተጫሩ የሚያሰለቹት ‘ፋሺስት’ ‘ምርጥ መኮንኖች’ የሚሉት ቃላት በዚህ አራት ገጽ አትማችሁ አንዴም ብቅ ሳይል ቀረ።

እንግዲህ፣ ደርጉን ለምን ‘ፋሺስት’ ትሉት እንደነበር እስካሁን ላልገባው ሁሉ አሁን ግልጽ ይሆናል። በኢትዮጵያ ሕዝቦች ትግል ውስጥ በተጫወተው ሚና ሳይሆን እናንተን ስልጣን ስላላጋራ ነበር ‘ፋሺስት’ የሆነው። አሁን ስልጣን የሚያጋራችሁ ስለመሰላችሁ ‘ፋሺስትነቱ’ ቀረ። ‘ፋሺስቱ’ ደርግ እራሱ ስልጣን ለቆ ሰፊው ሕዝብ ሥልጣን ሊይዝ የሚችልበትን ዲሞክራሲያዊ መንገድ ገና በመግለጫ መልክ ስታዩ ጊዜ፣ ሰፊው ሕዝብ ከደርጉ ሥልጣን ከሚወስድ ‘ፋሺስት’ የምትሉት ደርግ ከናንተ ጋር ተጋርቶ ሥልጣን ላይ እንዲቆይ ትማጠኑት ጀመር።

የዲሞክራሲያዊ አብዮትን አካሄድ ያወቀ ይቅርና የደርጉ መለስተኛ ኘሮግራም ብቻ በጥሞና ያነበበ እንኳ፣ ከሰፊው ሕዝብ መሃል የወዛደሩ ፖርቲና ሌሎች ተራማጅ የፖለቲካ ድርጅቶች ተቋቁመው ከዚያም በወዛደሩ ፖርቲ መሪነት በትግል አብዮታዊ ግንባር ፈጥረው ለሥልጣን ንጥቅያው እንደሚዘጋጅ ይረዳል። በነዴሞክራሲያ ‘ፋሺስት’ ሲባል የከረመው ደርግ፣ ይህን የብሄራዊ ዲሞክራሲያዊ አብዮት አካሄድ በመቀበል፣ ተራማጆች በፍጥነት የሕዝቡን ትግል አደራጅተው ይህን አብዮታዊ ግንባር እንዲያቋቁሙ የሚጠራና ለዚህም ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር ኘሮግራም አወጣ። ኢህአፖ በዚህ ደነገጠና ከሰፊው ሕዝብ ተሽቀዳድሞ ከሰፊው ሕዝብ ጀርባ ሥልጣን ለመያዝ ደጅ ጥናት ያዘ። ለራሱ በሰፊው ሕዝብ ስም ሥልጣን መያዝ የሚታገል እንጂ ለሰፊው ሕዝብ ሥልጣን መያዝ እንደማይታገልና እንዲያውም ይህን ለማገድ እንደሚያሴር እስካሁን ላላወቁት አሳወቀ።

ለዚህ ዲሞክራሲያ ሳትጋበዝ ለመሄድ ለምትዘጋጅበት ግብዣ ‘ለግብዣው አብረውሽ የሚመጡትን አንቺው ምረጪ’ የተባለች ይመስል፣ ወይም ደግሞ ለጥሪው የምደርሰው እኔ ብቻ አይደለሁም ለማለት፣ ለሚቋቋመው ‘አብዮታዊ ግንባር’ አምስት አይነት ድርጅቶች ጠቃቅሳለች። ለግንባሩ መሪነት ቦታው ለኢህአፖ እንዲለቀቅ ተጠይቋል። በድርጅቱ ዝርዝር ላይም ኢህአፖ የመጀመሪያውን ቦታ ይዟል። ከተቀሩትም፣ አንዳንዶቹ እስከነመኖራቸው የተገለጠው በዚችው የዲሞክራሲያ ‘ማመልከቻ’ ላይ ነው። /ለምሳሌ የኢትዮጵያ ዘማቾች ማህበር፣ የኢትዮጵያ ጦር ኃይሎች ንቅናቄ የተባሉት።/ አንዳንዶቹ፣ መኖራቸው እንዲሁ በወሬ ተሰምቶ ይሆናል እንጂ እነሱ ስለመኖራቸው በሰፊው ሕዝብ ውስጥ ያደረጉት ቅስቀሳ ታይቶ የማይታወቅ ናቸው። /ለምሳሌ የኦሮሞ አርነት ግንባር።/ ኢሠአማ አሁን የሌለና ሠራተኛውን የማይወክል ማህበር ቢሆንም ተጠቅሷል። ወዛደሩ ‘ኢሠአማ አሁን የለ እኛ ማን እንዲወከል’ እንዳይልም ‘ኢለአማ’ የሚባለው ‘ሌላ ድርጅት ተጠቅሷል። ወዛደሩ የበለጠ ደስ እንዲለው ነው መሠል ኢህአፖ ኢሠአማ፣ ኢለአማ ሁሉም የወዛደሩ ወኪሎች የኢትዮጵያ ሴቶች አስተባባሪ ኮሚቴ /የኢት.ሴቶች አባራሪ ኮሚቴ/ ተጠቅሷል። እነርሱ ፈርሰናል ቢሉም የለም ሥልጣን ለመያዝ እድል ተገኝቷልና 13 ሚሊዩን ሴቶች እንወክላለን ብላችሁ ለግንባር ተዘጋጁ ሊባሉ ነው። በተረፈ የመንግሥት ሥልጣን ለመያዝ ያልቆሙ ሌሎች ብዙዎችም ተጠቅሰዋል። /ለምሳሌ የኢትዮጵያ ተማሪዎች ንቅናቄ፣ የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር።/ ከዚያም ለቁጥር ማበራከቻ የገበሬ ማህበራት፣ የከተማ የሕብረት ሥራ ማህበራትም ተጠቅሰዋል። ዝርዝሩን ያየ ማንም ሰው እንደሚረዳው ወዛደሩና አርሶአደሩ የቀረቡት ለይስሙላ፣ ለቁጥር ማበራከቻ፣ ‘ሕዝባዊ’ የሚል ቅጽል ስያሜ ለማንጠልጠል ነው። ወዛደሩ ያለ ፖርቲው፣ አርሶአደሩ ያለወዛደር አርሶአደር ሕብረት፣ ግንባር ሊፈጥሩና የመንግሥት ሥልጣን ሊቀናቀኑ እንደማይችሉ በጣም ግልጽ ነው። ከተጠቀሱት ‘ድርጅቶች’ ከመሪው እስከ ተከታዩች ዋነኞቹ፣ በፖለቲካ መስመር ቀርቶ በ‘ያቸንፋል’ እንኳን ከኢህአፖ የማይለዩ ናቸው። እንኳን ልዩ ሊሆኑ የኢህአፖ የፈጠራና የይምሰል ድርጅቶች መሆናቸው የማያጠራጥር ነው። ከዚህም በፊት ‘ጊዚያዊ ሕዝባዊ መንግሥት’ ለማቆም የተዘረዘሩት እነዚሁ ‘ድርጅቶች’ ነበሩ። ባጭሩ ኢህአፖ ፊትም በጊዚያዊ ሕዝባዊ መንግሥት አሁንም በግንባር ሥም ‘በብዙሀን’ መስሎ እራሱን ለመንግሥት ሥልጣን ‘እጩነት’ ሊያቀርብ ነው።

ዲሞክራሲያ ሳትጠራ ልትሄድ በምትዘጋጅበት ግብዣ ላይ የምታስከትላቸውን ‘ድርጅቶች’ ዝርዝር ካቀረበች በኋላ፣ ‘በግብዣው ላይ መቅረብ ስላለባቸው ኘሮግራም አይነቶች’ ወደማተቱ ገባች።

“ይህን ጥሪ በመሠረቱ ብንቀበለውም የወጣውን ኘሮግራም እንደህብረት ግንባር ኘሮግራም አንቀበለውም።” /ገጽ 3/ ስትል፣ የደርጉ ኘሮግራም ምን ወጣውና አንቀበለውም አለች ብለን እየተገረምን ዝቅ ስንል፣ “ቢሆንም የህብረት ግንባር ለማቋቋም የተደረገውን ጥሪ በመሠረተ ሃሳቡ በመቀበላችን ኢህአፖ የሕብረት ግንባሩ ኘሮግራም የሚከተሉትን ነጥቦች መያዝ አለበት በማለት የበኩሉን ያቀርባል።” ሀ. በነሃሴ 1967 ዓ.ም የወጣው የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፖርቲ ኘሮግራም ያዘላቸው ዘጠኝ መሠረታዊ ነጥቦች . . .

ተብለው ዘጠኝ ነጥቦች ተደርድረዋል። ዘጠኙንም አየናቸው። እናንተ ከኛ በኋላ ስላወጣችሁ የኛ ይቀድማልና የኛን ውሰዱ በማለት ካልሆነ በቀር እነዚህ ዘጠኝ ነጥቦች በደርጉ መለስተኛ ኘሮግራም ላይ ያመጡት አዲስ ነጥብ የለም። እንዲያውም የደርጉ መለስተኛ ኘሮግራም የበለጠ ንፁህ፣ የተብራራና ተራማጅ ነው። ይህ የሆነውም እነዚህ ዲሞክራሲያ የጠቀሳቸው ዘጠኝ ነጥቦች ‘የመሬት ይዞታ ሦስት አይነት ይሆናል’ ‘የተወረሱ ቤቶች ቀስ በቀስ ወደ ግል ንብረትነት ይቀየራሉ’ የሚለውና የመሳሰሉት የኢህአፖ ኘሮግራም ቀልባሽ ይዘቶች ስላልተጨመሩ ነው።

ተጨማሪ ተብለው ሌሎች ስድስት ነጥቦች ተዘርዝረዋል። ጊዚያዊ ሕዝባዊ መንግሥት የሚለው ነጥብ ካልሆነ፣ እነዚህ ተጨማሪ ነጥቦችም በመሠረቱ በደርጉ መለስተኛ ኘሮግራም ላይ የሚጨምሩት አዲስ ነገር የለም አንድ ቁልጭ ያለ አድርባይነት ግን በዚህ ተጨማሪ በተባለው ክፍል ውስጥ ስለ ብሄረሰቦች ጥያቄ የተጠቀሰው ነው። ኢህአፖ ፕሮግራም ውስጥ “ብሄሮች የራሳቸውን እድል በራሳቸው ለመወሰን ያላቸውን ያልተገደበ መብት ያውጃል፣ ከሥራም ላይ ያውላል።” ብሎ ነበር። ያውም ያውጃል ነው። ያውም ሥራ ላይ የሚውለው የኢህአፖ ጊዚያዊ ‘ሕዝባዊ’ መንግሥት እንጂ ጭቁን ብሄሮች እራሳቸው አይደሉም። በዚህ ኘሮግራሙ ላይ የብሄረሰቦችን የመገንጠል መብት በማድበስበስ፣ ጨቋኝ ብሄረሰብንም ተጨቋኝ ብሄረሰቦችንም ላለማስከፋት ‘በዲኘሎማሲ’ ቋንቋ ተጠቀመ። በኋላ ሲታይ፣ ደርጉ በመለስተኛ ኘሮግራሙ ‘ብሄረሰቦች የራሳቸውን ዕድል በራሳቸው የመወሰን መብት’ የሚለውን አወጀ።

በዚያን ጊዜ ከደርጉ ለመለየትና ይበልጥ ዲሞክራቲክ ለመምሰል፣ የ‘የላባደር ፖርቲ’ ነው በተባለው ድርጅታቸው ኘሮግራም ላይ የሌለው የመገንጠል መብት መታወቅ እንዳለበት ተጠቀሰ። የ‘ላባደር ፖርቲ ኘሮግራም ያልያዘውን ‘የሕብረት ግንባር’ እንዲቀበል ተጠየቀ።

ይህ እንኳ እግረ መንገዳችንን የታዘብነውን አደርባይነት ለመጠቆም ያህል ነው። እንቀጥል።

ከዚህ ‘የኘሮግራም ዓይነቶች’ ዝርዝር በኋላ ዲሞክራሲያ ትቀጥልና፣ “ውይይቱ እንዲጀመር መሟላት ያለባቸው” ብላ ደርጉ ለዚህ ‘ግብዣ’ እንዴት መልበስ /መቅረብ/  እንዳለበት የሚነግሩት አምስት ነጥቦች ታቀርባለች። /እራሷ ቀደም ብላ ለዚህ ‘ግብዣ’  ‘ስትለባብስ’  ‘ፋሽስት፣ ምርጥ መኮንኖች’ የሚሉትን ልብሶቿን አውልቃለች። /ከነዚህ አምስት ነጥቦች የመጀመሪያው ስለዲሞክራሲያዊ መብቶች ነው። ቀደም ሲል በዚህ ጥያቄ ላይ በተደረጉት ክርክሮች ከዲሞክራሲያ ክርክሮች ከዲሞክራሲያ አካባቢ ‘ዲሞክራሲያዊ መብቶች ለሁሉም’ የሚል አቋም እንደነበረ የሚታወስ ነው። በዚህ ጉደኛ ዲሞክራሲያ ላይ ግን ይህ ተቀይሯል፣ እንዲያውም ከደርጉ መለስተኛ ኘሮግራም ላይ ተገልብጧል። የመጨረሻው ነጥብም “መንግሥቱ በነዚህ (አራት) ነጥቦች ላይ መስማማቱንና በሥራ ላይ ማዋሉን በሬዲዩ በጋዜጦችና በሌሎች የመገናኛ ዘዴዎች በይፋ እንዲገለጽ” የሚለው ነው። ይህም በቀጥተኛ ቋንቋ ደርጉ ከዲሞክራሲያ ጋር ለመወያየት መዘጋጀቱን በይፋ ይንገርልን ነው።

ከዚህ ቀጥላ፣ ዲሞክራሲያ ያልተጠራችበት ግብዣ የሚከተለውን ሥነ ሥርዓት እንዲኖረው ትጠይቃለች።

“ውይይቱ ከተጀመረ በሰፊው ሕዝብ ፊት መላው የደርግ አባሎች እያወቁና እየፈቀዱ እንጂ ከሁለትና ከሦስት የደርግ አባሎች ጋር በድብቅ የሚደረግ ስምምነት መሆን የለበትም”

የዲሞክራሲያ ትራጄዲና ኮሜዲ ወደማለቂያው የሚጠጋው እርሷ ሥልጣን ለመጋራት ሥነ ሥርዓቱ ደመቅ እንዲልም ከሙሉ የደርግ አባሎች ጋር ‘ስትወያይ’፣ ሰፊው ሕዝብ ይህን ‘ታሪካዊ’ ሥነ ሥርአዓት በአንክሮ እየተመለከተ ነው። ይኸውም ኢህአፖ ለሰፊው ሕዝብ ያስገኘው ‘ታላቅ’ ድል ነው። ኢህአፖ በሰፊው ሕዝብ ስም ስልጣን ለመጋራት ስትወያይ ሰፊው ሕዝብ የተመልካችነት መብት ማግኘቱ ራሱ ‘ታላቅ ድል’ ነው። መች አነሰውና።

የትርዒቱ መጋረጃ የሚዘጋው ዲሞክራሲያ “ላልተጠራሁበት ግብዣ ደጅ ጥናቴ ባይሳካም ብቻዬን ብቀርስ በሚል ጥርጣሬ ተውጣ ወደ ዉጭ ግን ‘ጀግና’ መስላ ያልጋበዛትን ግብዣ ስታስጠነቅቅ ነው።

“መንግሥቱ ከላይ የተዘረዘሩት ተቀዳሚ ግዴታዎች ባለመስማማት ውይይት የማይጀመር ከሆነ መንግሥት የማይገኝበት የህብረት ግንባር ማቋቋም የመላ አብዮታዊያንና ዲሞክራሲያዊ ኃይሎች ታሪካዊ ግዴታ ነው።”/ ገፅ 4 / ሰርዝ የተጨመረ

እስካሁን ካተትነው ሆነ ከዲሞክራሲያ ‘የግንባር ጥሪ መልስ’ ግልጽ የሚሆንልን፣ ኢህአፖ ሰፊው ሕዝብ ራሱ አይሁን እንጂ፣ ከማንም ጋር ተባብሮ ሥልጣን ላይ ለመንጠልጠል የቆመና የሚታገል ድርጅት መሆኑ ነው። ደርግ እንኳን ሰፊውን ሕዝብ አደራጅታችሁ ከዚሁ መሀል አብዮታዊ ግንባር ፈጥራችሁ ‘ሥልጣን ተረከቡኝ’ ሲል፣ ኢህአፖ የለም ‘ሰፊውን ሕዝብ ተውና እኔና አንተ ግንባር ሰርተን ስልጣን እንካፈል ማለቷ ይህንኑ ሥልጣን ላይ ከሕዝቡ ጀርባ  ለመንጠልጠል ያላትን ጉጉት በሚገባ ያሳያል።

እውነተኛ ተራማጆች ሰፊው ሕዝብ ስልጣን በጁ ለማስገባት የሚያስችሉትን ንቃታዊ ድርጅታዊና ትጥቃዊ ዝግጅቶች እንዲያሟላ ማገዝ ተቀዳሚ ትግላችን ነው። እነዚህም ዛሬውኑ አይሟሉም፣ ነገር ግን የፈጀውን ያህል ጊዜ ይፈጃል እንጂ፣ የጠየቀውን ያህል መስዋዕትነት ይጠይቃል እንጂ የሰፊው ሕዝብ አማራጭ የለሽ የትግልና የሥልጣን አያያዝ ጐዳና ይህ ብቻ ነው።  ስለዚህም ከመቼውም ጊዜ በላይ ዛሬ፣ የሰፊው ሕዝብ ትግል የነቃ፣ የተደራጀና የታጠቀ ጐዳና አስይዞ ሥልጣን ለመጨበጥ ማብቃት የግንባር ቀደምትነትና የተራማጅነት ግዴታችን ነው።

ከሰፊው ሕዝብ ጀርባ ሥልጣን ላይ ለመንጠልጠል የሚያሴሩ አወናባጆች ይወድማሉ!
የነቃ፣ የተደራጀና የታጠቀ ሰፊ ሕዝብ ያሸንፋል።
Scroll to Top