የሰፊው ሕዝብ ድምፅ
ቁጥር 41፣ ሰኔ 2፣ 1968
የፅሁፉ ፍሬ ሀሳብ
መኢሶን በዚህ የሰፊው ሕዝብ ድምፅ እትሙ፣ የኢትዮጵያ ወዛደሮች ለኑሮአቸውና ለሥራ ሁኔታቸው መሻሻል ሲሉ መብታቸውን ለማስከበር በሙያ ማኅበር ለመደራጀት ያደረጉት ትግል ረዘም ያለ ቢሆንም፤ ብቃትና ትጋት ያላቸው አርቆ አስተዋይ መሪዎች በማግኘት ጉዳይ ግን እስከዛሬ “እንዳልታደሉ” ያትታል።በዚህም የረጅም ትግላቸው፣ የተጎናጸፉት ድል የኢትዮጵያ ሠራተኞች አንድነት ማኅበርን (ኢሠአማ) ማቋቋም እንደነበር ያስታውሳል። በዓጼ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት ቁጥጥር ተተብትቦ የነበረው ኢሠአማ ቀና ማለት የጀመረው፣ ከ1966 ዓ.ም. የኢሠአማ ሥራ ማቆም አድማ በኋላ እንደሆነ ይጠቁማል። ከዚያም በመቀጠል፣ ማኅበሩ በጊዜያዊ ወታደራዊ ደርግ ከተዘጋ በኋላ፣ የወዛደሩን ጥቅም እናስከብራለን በማለት በምስጢር “በኢላአማ” ሥር ተደራጅተናል የሚሉ ጥቂት የንዑስ ከበርቴ ደንፊዎች የማኀበሩን አመራር ለመጨበጥ እየተወራጩ እንደሆነ ጠቁማል። ከስሞኑም፣ “የኢትዮጵያ ሠራተኖች ህብረት መሪዎች ጉባኤ” በሚል የስብሰባ ጥሪ አድርገው ወዛደሮችን ለመከፋፈልና ለማደናገር ከንቱ ጥረት እያደረጉ እንደሚገኙ ያትታል።
ር ዕ ሰ አ ን ቀ ጽ
የሰሞኑ የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ሠራተኞች ማህበራት መሪዎች ‘ጉባዔ’
የኢትዮጵያ ወዛደር በሞያ ማህበር ለማደራጀት ያደረገው ተጋድሎ የረዥም ጊዜና ብዙ መስዋእትነት የጠየቀ ቢሆንም፣ በአመራር በኩል እስከዛሬም ‘ያልታደለ’ ሆኖ ቆይቷል። ወዛደሩ ከሥር በቆራጥነት ያካሄዳቸውን ትግሎች ከላይ የሚያደፈርሱበት፣ አቅጣጫ የሚያስቱበት ‘ጠላቶች’ በየጊዜው አጋጥመውታል። ወዛደሩ ከታች በወዛደራዊ ዓላማና መንፈስ የማይናቁ ድሎችን፣ ጥንካሬና ንቃት አግኝቷል። ከላይ በሚውጠነጠንበት ሴራ ግን በተከታታይ ‘ተሸንፏል’። በዚሁ ሴራ ምክንያትም፣ ‘ጠላቶቹ’ በወዛደሩ ትግል ተንተርሰው ከላዩ ጉብ እያሉበት ኢሰማአ እስከዛሬ ወዛደራዊ አመራር ሳያገኝ ቆይቷል።
የኢትዮጵያ ወዛደር፣ በመጀመሪያዎቹ፣ የሞያ ማህበር ለማቋቋም ባደረጋቸው ትግሎች ድልን ተቀዳጅቶ ለሞያ ማህበሩ መቋቋም በርግጥ የታገሉ የወዛደር መሪዎች የኢሰአማን አመራር ያዙ። ፋሺስታዊው የኃይለሥላሴ መንግሥት ይህን ከወዛደሩ ትግል በርግጥ የወጣ አመራር በመግደል፣ በማሰርና በማሰቃየት አስወገደ። በቦታውም ከኢምፔሪያሊስቶችና ከመንግሥቱ ጋር በጥቅምና በዓላማ የተሳሰረ አመራር ተካ። የኢትዮጵያ ወዛደር ከዚያን ጊዜ በኋላ ባንድ በኩል ከበዝባዦቻቸውና ከኃይለሥላሴ መንግሥት ጋር፣ በሌላ በኩል ከዚህ በጠላቶቻቸው ከተጫነባቸው አድሃሪ አመራር ጋር እየታገሉ እስከ የካቲት 1966ቱ አብዮታዊ እንቅስቃሴ ድረስ መጡ።
በዚህ እንቅስቃሴም፣ የራሳቸውን የኑሮና የሥራ ሁኔታ ለሚመለከቱ ጥያቄዎች፣ በአጠቃላይ በሰፊው ሕዝብ ወገኖች በኩል ለተነሱት ጥያቄዎች ተሰልፈው በመታገል ለተገኙት ድሎች ከፍተኛ ድርሻ አበረከቱ። በነበየነ ሰለሞን የሚመራው የነኃይለሥላሴ ‘ቅምጦች’ ከኢሰአማ አመራር ወጥተው ኢሰአማ ለወዛደሩ የቆመ ድርጅት እንዲሆንም ታገሉ። እንደገና፣ ቀደም ብሎ ከነበየነ ስለሞን ጋር ተሰልፎ ኢሰአማ ‘ጊዜያዊ ሕዝባዊ መንግሥት’ የምትለውን አድሃሪ መፈክሩን እንዲያሳልፍለት የጣረው የንዑስ ከበርቴ ደንፊና ቀልባሽ ቡድን፣ እነበየነ ሰለሞን ሲነሱለት፣ በዚሁ አጋጣሚ ተጠቅሞና አጋዦች ከአመራሩ ውስጥ ሰብስቦ ከወዛደሩ አናት ላይ ለመቀመጥ ሞከረ።
ከዚያም ወዲህ፣ ወዛደሩን ባልተዘጋጀበት ትግል በማጋፈጥ አስመትቷል። የወዛደሩ የሞያ ማህበር ተጠናክሮ ወዛደሩን የሚያገለግል ድርጅት እንዳይሆንና የዚህ ቡድን ተቀጥያ ሆኖ እንዲኖር ታግሏል። ወዛደሩ ለራሱ ጥቅም ለመቆም እንዳይበቃና እርሱ በወዛደሩ ስም የያዘውን ማወናበድ ለመቀጠል ከፍተኛ ጥረት አድርጓል። ሀቀኛ ወዛደሮች ይህ የንዑስ ከበርቴ ደንፊና ቀልባሽ ቡድን፣ በኢሰአማ አመራር ውስጥ ያሉትን ሰርጐገቦች ከመታገል ባይቆጠቡም፣ የዚህ ቡድን ምልምሎችና ሰርጐገቦች፣ በጠቅላላው የወዛደሩን እንቅስቃሴ እድገት እንደጐዱ፣ በተለይም የሞያ ማህበሩን መጠናከርና የወዛደሩ መገልገያ መሆን እንደገቱ ምንም ጥርጥር የለውም።
ኢሰአማ ሲዘጋና በተለይም በኢሰአማ አመራር አካባቢ የተፈፀሙት ፀረ ወዛደር ድርጊቶቹ የአደባባይ ምስጢር እየሆኑ ሲሄዱ፣ ይህ የንዑስ ከበርቴ ደንፊና ቀልባሽ ቡድን በኢሰአማ አመራር አካባቢ ለሚፈጽማቸው ፀረ ወዛደር ድርጊቶች ማጠናከሪያ ‘ኢለአማ’ / የኢትዮጵያ ላብአደሮች አብዮታዊ ማህበር/ የሚባል ድርጅት አቋቁሜያለሁ እያለ በመለፈፍ ላይ ይገኛል። ኢለአማ የቆመለት ዓላማ ግልጽ ነው። የወዛደሩን መደብ ንቁ አባሎች ለመከፋፈል፣ የነዚህን ንቁ ወዛደሮችና የእውነተኛ አብዮታዊ ምሁራንን ውህደት ለማደናቀፍ ነው። ወዛደሩ መሀል ውዥንብር ነዝቶ ወዛደሩን የሚይዘው የሚጨብጠው ለማሳጣት ነው። በዚህም በደፈናው የወዛደሩን ትግል ብቻ ሳይሆን በተለይ የኢትዮጵያ አብዮት ዋስትና የሆነውን የእውነተኛ ወዛደር ፖርቲ መፈጠር ለማደናቀፍ ነው። ወዛደሩ ተጠናከሮ፣ ከአርሶአደሩና ከሌሎች ተራማጅ የሕብረተሰብ ክፍሎች ጋር አንድነት ፈጥሮ ሌት ተቀን የሚውጠነጠንበትን የፀረ አብዮት ሴራ ለመግታትና ለመምታት አስፈላጊውን ንቃትና ድርጅታዊ ጥንካሬ እንዳያገኝ ነው።
ይህ ለፀረ አብዮት ያደረ የንዑስ ከበርቴ ደንፊና ቀልባሽ ቡድን የተነሳው የወዛደሩን ትግል ከውስጥ ሆኖ ለማዳከም ብቻ ሳይሆን ከላይ ሆኖም ትግሉን አቅጣጫ ለማሳጣት ጭምር ነው። ለዚህም እስከዛሬ ያልቆመ ተከታታይ ሙከራዎች አድርጓል። በቅርቡ የኢትዮጵያን ኢንዱስትሪ ሠራተኞች አጠቃላይ ማህበር ለማቋቋም በተጠራው ጉባዔ አካባቢ የፈፀማቸው ሸፍጥ፣ ኢ- ዲሞክራሲያዊ እርምጃዎች የውንብድናና ፀረ ወዛደር ድርጊቶች ለዚሁ ማረጋገጫ ናቸው።
ድሮውንም ቢሆን፣ የዚህ ቀልባሽ ቡድን ፍላጐት ከወዛደሩ ፍላጐት ተፃራሪ ነው። ለዚህም ነው በቀጥተኛና በአብዮታዊ መንገድ ከወዛደሩ ጋር መደባለቅን ሳይሆን፣ ከወዛደሩ አናት ላይ በሴራና በውንብድና ፈጢጥ ብሎ መፈንጨትን የመረጠው። ደርጉ ያወጣው የሠራተኛው አዋጅ ፋሺስታዊ ነው፣ ፋሺዝምን ለማጠናከር ነው፣ አትደራጅ የሚለው ቅስቀሳው በወዛደሮች ቆራጥ ትግል ከሸፈበት። ቀልባሹ የአናርኪስት ቡድን የፈለገው ሳይሳካለት ቀረ። የኢትዮጵያ ወዛደሮች አዋጁ መሠረታዊ ጉድለቶች ቢኖሩትም፣ ይሁንና ሌላም ገና ብዙ የሚቀሯቸውን መሰናክሎች ለመወጣት ተደራጁ፡ ይህ ቡድን ግን ተስፋ አልቆረጠም። ተደራጅተው በስንት ትግል ሊያቋቁሙ ካቀዱት ማህበራቸው አናት ላይ ጉብ ለማለት ፀረ አብዮት ድርጊቶችን ማስፋፋት ጀመረ። በጉባዔው ለመካፈል ይቅርና ምንም ቦታ የማይሰሩ ምልምሎቹን አሰርጐ አስገባ። ብዙ ሺ ወዛደሮችን የሚወክሉ መሪዎች በሸፍጥና በማወናበድ እንዲወጡ አስደረገ። ጉባዔው ስለኢትዮጵያ ወዛደር አንገብጋቢ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ድርጅታዊ ጥያቄዎች መወያያ ሳይሆን፣ የዚህ ቡድን ፀረ አብዮት መስመር ማፀደቂያ፣ በጠቅላላው የፀረ አብዮት ሴረኞች ማገዣ እንዲሆን ጣረ።
ከዚህ ፀረ አብዮት ቡድን ድርጊቶችም ሌላ፣ በጉባዔው ዝግጅት በኩል በፍፁም የማይገቡ ጉድለቶች ነበሩ። በሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ውስጥ በሚከናወነው አሻጥር ምክንያት አንዳንድ የማህበር መሪያዎች ሆን ተብሎ የማህበር መሪነት መታወቂያቸው በወቅቱ አልተሰጣቸውም። ምንም ማህበር ለማይወክሉ አንዳንድ ግለሰቦች ግን የጉባዔ መግቢያ መታወቂያ ተሰጠ። ለአንዳንድ መህበራት ስለጉባዔው መደረግ የተነገረው ጉባዔው አንድ ቀን ሲቀረው ነበር። የጉባዔው ተሳታፊዎች ሊሆኑ የማይችሉ የአናርኪስቱ ቡድን ምልምሎች ከጉባዔው አዳራሽ ሊገቡና ሊበጠብጡ የበቁት በነዚህ ኃይሎች ሁሉ ትብብር መሆኑ ግልፅ ነው።
ወኪሎቻቸው የተባረሩባቸው ወዛደሮች ከሌሎች ንቁ ወዛደሮች ጋር ተባብረው ይህ የውንብድና ስብሰባ በሚካሄድበት ቦታና ጊዜ ተገኝተው ምሬታቸውን በታላቅ ሰላማዊ ሰልፍ ገልፀዋል። የተቀሩትም የኢትዮጵያ ወዛደሮች ወገን መስለው ሊበታትኗቸውና ትግላቸውን አቅጣጫ ሊያስቱባቸው የተነሱት ቀልባሽ አናርኪስቶች ከጀርባቸው ያውጠነጠኑባቸውን ሴራ ለማየት እድል አግኝተዋል። ለጊዜው ቀልባሽ አናርኪስቶቹ ያቀዱት ሴራ አልተሳካላቸውም። የኢትዮጵያ ወዛደሮችም ለጊዜው አጠቃላይ ማህበራቸውን ለማቋቋም አልቻሉም። በዚህ ሁኔታም፣ የኢትዮጵያ ወዛደሮች በሙሉ ከዚህ የቅርብ ጊዜ ድርጊትና፣ ካለፉት ከወዛደሩ ጀርባ እየተጠነሰሱ የወዛደሩን የሞያ ማህበር አመራር ወዛደራዊ መሆን ያላስቻሉ ሴራዎች ትምህርት ቀስመው፣ ለወደፊቱ ለራሳቸው ጥቅም የሚውል የሞያ ማህበር ለማቋቋም በከፍተኛ ጥንቃቄና ንቃት መታገል አለባቸው።
ለዚህም፣ በየፋብሪካው በሚቋቋሙ ማህበሮች፣ የአፍ ደላዩችን ሳይሆን በርግጥ ለወዛደሩ ጥቅም የሚቆሙ የማህበር መሪዎችን በዲሞክራሲያዊ መንገድ መመረጥ አለባቸው። ንቁ ወዛደሮች ይህን ምርጫ ከዳር ቆመው ማየት የለባቸውም። ለዲሞክራሲያዊ አመራረጥና ለሀቀኛ የወዛደር ወገኖች መመረጥ በግንባር ቀደምነት መታገል አለባቸው። እነዚህ በዲሞክራሲያዊ መንገድ የሚመረጡ የማህበር መሪዎች ለሚወስዱት እርምጃዎች ሁሉ ለመረጧቸው ወዛደሮች ተጠያቂ መሆን አለባቸው። ከወዛደሩ ፍላጐትና ጥቅም ተፃራሪ የሆኑ እርምጃዎችን ወስደው ሲገኙ በይፋ ተወግዘው ቦታቸውን መልቀቅ አለባቸው።
በዚህ ሁኔታ የተመረጡ የልዩ ልዩ ወዛደር ማህበራት መሪዎች አጠቃላይ ጉባዔ ከማድረጋቸው በፊት የጉባዔው አጀንዳ ለየቅርንጫፍ ማህበራቱ በነዚህም በኩል ለወዛደሮች ሁሉ መቅረብ አለበት። እያንዳንዱ የወዛደር ማህበር በአጀንዳው ላይ መነጋገር፣ ሃሳቡን መግለጽ አለበት። የአንድ ቅ/ማህበር መሪ ወደ አጠቃላዩ ጉባዔ ሲመጣ፣ የመረጡት አባሎች በዲሞክራሲያዊ መንገድ ተወያይተውበት የደረሱበትን ውሳኔ ይዞ መምጣትና በጉባዔው ላይ ሲካፈልም ይህንኑ ውሳኔ ማንፀባረቅ አለበት። በዚህ ጉባዔ ላይ የሚካፈል የወዛደር መሪ ተጠያቂነቱ ለመረጡት ወዛደሮች ነው።
ጉባዔውም፣ እያንዳንዱ ቅ/ማህበር ተወያይቶበት ባፀደቀው አጀንዳና ወኪሎች ከማህበራቸው ባመጡት ውሳኔ ላይ በመመርኮዝ መሥራት አለበት። የዚህ ጉባዔም ውሳኔ ቢቻል አጠቃላይ ስምምነት የሚገኝበት፣ ካለዚያ ከአባል ማህበራት አብዛኞቹ የሚደግፉት መሆን ይገባዋል። በዚህ ጉባዔ ላይ የሚመረጠው የአጠቃላይ ማህበሩ አመራር እንደገና በዴሞክራሲያዊ መንገድ መመረጥ ይኖርበታል። ተመርጦም የየትኛውም ቡድን ተቀጥያ ሳይሆን የጠቅላላ ጉባዔውን ውሳኔ በሥራ ላይ የሚያውልና የጠቅላላውን ወዛደር ጥቅምና መብት የሚያስከብር መሆን አለበት። ከላይ የዘረዘርነውን ዲሞክራሲያዊ መንገድ ካልተከተለ፣ የወዛደሩ መደብ የሞያ ማህበር የዚህ መደብ መገልገያ ሊሆን አይችልም። ከፀረ ወዛደር ቡድኖች መጠቀሚያነት ሊያልፍ አይችልም። የኢትዮጵያ ወዛደሮች ባጠቃላይ ንቁ ወዛደሮች በተለይ ይህንን ሀቅ ተረድተው በርግጥ ሊያገለግላቸው የማይችል አጠቃላይ የሞያ ድርጅት ለማቋቋም ከፍተኛ ትግል አለባቸው።
የኢትዮጵያ ተራማጆችም የወዛደሩ መደብ የሞያ ድርጅት እንዲቋቋም በሚደረገው ትግል ገለልተኛ ሊሆኑ አይችሉም። እንኳን ከጭቆና ባልተላቀቀበት ሁኔታ፣ ከሶሻሊስት አብዮት በኋላም የወዛደሩ መደብ የሞያ ድርጅት ከፍተኛ ግልጋሎትና ቦታ አለው። ከሞላ ጐደል ጅምላ መደቡን ሊይዝ የሚችለው የወዛደሩ የሞያ ማህበር ብቻ ነው። ከኢኮኖሚያዊ ትግል ወደፖለቲካ ትግል፣ ከስፖንቴንየስ ትግል ወደነቃና በራሱ ርእዩተ ዓለም የታጠቀ ትግል ወዛደሩን የሚያሸጋግረው ድልድይ ይህ የሞያ ማህበር ነው። የወዛደሩ ርእዩተ ዓለም መቅሰሚያ ሜዳ፣ የትግል መለማመጃ ት/ቤት የሞያ ማህበሩ ነው። ታሪካዊ ግቡ ደርሶ ሥልጣን እስኪጨብጥ ድረስ የዘላቄታ ዓላማውን ሳይዘነጋ ለእለታዊና ጊዜያዊ ጥቅሞች መታገያ ድርጅቱ ይኸው የሞያ ማህበር ነው።
በኢትዮጵያ፣ የወዛደሩ የሞያ ማህበር ከነዚህም አልፎ የተለየ ቦታ አለው። የወዛደሩ ፓርቲ እስካሁንም ስላልተፈጠረ፣ የሞያ ማህበሩ የዚህን ፖርቲ ቦታ ሊይዝ እንደማይችል ቢታወቅም፣ ይህ ፖርቲ እስኪፈጠር ድረስ ወዛደሩ በዚህ አብዮታዊ ትግል ሊያሳትፍ የሚችለው የሞያ ማህበሩ ነው። በዛሬው የኢትዮጵያ ሁኔታ፣ ፀረ አብዮት ሴራን ለመግታት ሆነ የተገኙትን ድሎች ለማስጠበቅ የወዛደሩ ተሳትፎ እጅግ አስፈላጊ ነው። ለዚህ ተሳትፎ ደግሞ እውነተኛ ወካዩን፣ የወዛደር ፖርቲውን እስኪያገኝ ድረስ ከዳር ቆሞ ለማየት አይችልም። ዛሬ ባለው ድርጅት አማካይነት መታገል አለበት።
ስለዚህም፣ የኢትዮጵያ ሃቀኛ አብዮታውያን የወዛደሩን ትግል በሚመለከተው በኩል ሁለት የሚደጋገፉ ቀዳሚና አጣዳፊ ተግባሮች አሉባቸው። ከቀን ወዛደሮች ጋር ተባብረው የወዛደሩን ፖርቲ ለመመስረት ከፍተኛ ትግል ማካሄድ አንደኛው ነው። ሁለተኛው፣ ወዛደሩ የራሱ አገልጋይ የሆነ አጠቃላይ የሞያ ማህበር ለማቋቋም በሚያደርገው ትግል ከጐኑ መሰለፍ፣ ንቃቱን እንዲያሳድግ እያገዙ ድሎችን ሊቀሙት የሚያሰፈስፉትን ቀልባሽ አናርኪስቶች ማጋለጥ ነው።
ለነዚህ ሁሉ ከግብ መድረስ ከወዛደሩ መደብ ጋር መዋሃድ ዓይነተኛውና መሰረታዊው መንገድ ነው። የወዛደሩን ንቅናቄና ሳይንሳዊ ሶሻያሊዝምን ለማዋሃድ እስካሁን ከተደረገው ከፍተኛ ጥረት ይበልጥ ማድረግ አጣዳፊ ነው። የኢትዮጵያ ወዛደር በሰርጎ ገቦች እየተወናበደ፣ በፀረ አብዮት ቅስቀሳቸው ሕብረቱ እየላላ ከሄደ የኢትዮጵያ አብዮት ምንም ዋስትና አይኖረውም። እውነተኛ አብዮታውያንና ንቁ ወዛደሮች ከበረቱ ግን፣ ትግላቸውን ካጣመሩ ግን፣ የኢትዮጵያ ወዛደር ቀልባሽ አናርኪስቶች የሚቀራመቱት ሳይሆን የኢትዮጵያ ሕዝቦች ትግል አብዮታዊ ኃይል ይሆናል።
የወዛደሩ ንቅናቄ ከፀረ ወዛደር ሰርጐገቦች እናጽዳ
የወዛደሩን ንቅናቄና ሳይንሳዊ ርእዩተዓለሙን እናዋህድ
ከወዛደሩ ጋር እንዋሃድ፣የወዛደሩን ፖርቲ እንመስርት
አብዮትና የኢኮኖሚ ችግር
በአገራችን በመፋፋም ላይ የሚገኘው አብዮታዊ እንቅስቃሴ ከተቀጣጠለ ይኸው ሁለት ዓመት ተኩል ያህል ሆኖታል። በዚህ አጭር ጊዜ ውስጥ በኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ትግል ያደረገው ፈጣን እርምጃ በቀላሉ የሚገመት አይደለም። አብዮታዊው ትግል እንዲህ የተበታተነ መልኩን ይዞ በሚገባ ሳይቀነባበርና በድርጅት ሳይመራ፣ በሕዝብ ትጥቅ ሳይደገፍ ያስገኛቸው ድሎች ብዙ ናቸው። እነዚህን የሕዝብ ድሎች ባለፉት የሰፊው ሕዝብ ድምጽ እትሞቻችን ሳናነሳቸው ያለፍንበት ጊዜ የለም።
ዛሬ በምንገኝበት ወቅት፣ የአብዮታችንን የወደፊት ግስጋሴ ሊወስን የሚችል አሳሳቢ ሁኔታ በተጨባጭ መልኩ ከፊታችን ተደቅኖ እናያለን። ይኸውም ሰፊው ሰርቶ አደር ሕዝብ የተዘፈቀበት ታላቅ የኢኮኖሚ ችግር ነው። ምንም እንኳ የአብዮት ጊዜ ቢሆን አገራችን የምትገኝበት የኢኮኖሚ ሁኔታ እጅግ አስከፊ መሆኑ ለአብዮት ወዳጆች በሙሉ ግልጽ ሊሆን ይገባል። የአስፈላጊ ዕቃዎች ዋጋ ከመጠን በላይ እየጨመረ በመሄድ ላይ ነው። አንዳንድ አስፈላጊ ሸቀጦችማ እስከነጭራሹ ከገበያ ለማግኘት አስቸጋሪ ሆኗል። የስኳር፣ የዘይት፣ የእንጨትና በተለይም የጤፍና የበርበሬ ዋጋ ወዘተ. በበዙ እጅ ወደ ሰማይ መጥቋል። የሠርቶ አደሩ ሕዝብ ደመወዝ ግን ካለበት አልተነቃነቀም። ይህ ጠቅላላ የኢኮኖሚ ችግር በጣም ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን ወዛደሩንና ሌሎች ሠርቶአደሮችን ይቅርና መሃከለኛ ገቢ ያላቸውንም እንኳ ከትልቅ ችግር ጥሏቸዋል። በሜይ አንድ የወዛደሮች ቀን ተይዞ የነበረው “የጤፍ ዋጋ ስልሳ፣ የወዛደሩ ደመወዝ ሠላሳ” የሚለው ሰሌዳ የወዛደሩን እሮሮ የሚያንፀባርቅ ነው።
በእርግጥ በአንድ አገር ውስጥ አብዮት በሚደረግበት ወቅት የኢኮኖሚ ችግር አለ። ወደኋላ መለስ ብለን ብንመለከት ለየካቲቱ 1966 አብዮታዊ ሁኔታ መፈጠር ምክንያት ከሆኑት አንዱ ይኸው የኢኮኖሚ ችግር ነው። የየካቲት እንቅስቃሴ እንደዚያ ሕብረተሰባዊ መደቦችንና ክፍሎችን አስተባብሮ እንዲነሱ ካደረገበት ምክንያቶች የኑሮ ዋጋ መወደድና በአጠቃላይ የኢኮኖሚ ችግር መባባስ እንደ ነበር የሚታወስ ነው።
ባለንበት በዛሬው ወቅት አገሪቷን የገጠማት የኢኮኖሚ ችግር ለየካቲት እንቅስቃሴ መነሾ ከሆኑት ችግሮች የተወረሰ ቢሆንም፣ የዛሬው የኢኮኖሚ ችግር ግን ከየካቲት 1966ቱ ጋር በእኩል ዓይን የሚታይ አይደለም። የማምረቻና የማከፋፈያ ድርጅቶች በመንግሥት እጅ በመግባታቸው የጥቅም ምንጫቸው የቀረባቸው አቀባባይና ቢሮክራት ከበርቴዎች ምርት እንዲቆረቁዝ ያደርጋሉ። ሸቀጣ ሸቀጦች በተስተካከለ ዘዴ ለገበያ እንዳይቀርብ ታላቅ ቀውስ ይፈጥራሉ። የከተማ ትርፍ ቤትና ቦታ የተወረሰባቸው፣ ሌሎችም ገና ለገና ይወረስብናል ብለው የሚሰጉ እንደ የትራንስፖርት ንብረት ባለቤቶች ያላቸውን ተቀማጭ ገንዘብ ከባንክና ከመሳሰሉት በከፍተኛ እጅ እያወጡ ያባክናሉ። ይህ ራሱ በሸቀጣ ሸቀጡ ላይ ከፍተኛ ጥያቄ /የመግዛት ፍላጐት/ ስለሚያስከትል ለዋጋ መናርና ለሸቀጥ እጥረት ምክንያት ሆኗል። ከዚሁ ጋር ጠቀስ ለማድረግ የሚቻለው፣ የገጠሩ መሬት ለአራሹ ገበሬ ከተመለሰ ወዲህ ገበሬው ምርቱን ሽጦ በሚያገኘው ገንዘብ ለኑሮው አስፈላጊ የሆኑ ሸቀጦችን ከድሮው በበለጠ መጠን ለመግዛት ስለሚሻ ለእቃ እጥረት ተጨማሪ ምክንያት እንደሆነ ነው። ከዚሁ ጋር የብሄራዊ ኃብት ልማትና የንግድ ሚኒስቴር የመሳሰሉት የቢሮክራሲው አካሎች ችግሮቹ እንዲባባሱ የሚሸርቡት ራሱን የቻለ አሻጥር አለ።
በአብዮት ወቅት የሚገጥመውን የኢኮኖሚ ቀውስ ደግሞ ሙሉ በሙሉ ለማስተካከል የረጋ ሁኔታን፣ የአብዮታዊውን ትግል ከግብ መድረስ ይጠይቃል። አብዮቱ ከግቡ ሳይደርስ አብዮታዊው ትግል ፋታ ሰጥቶ የኢኮኖሚውን ችግር በማስቀደም ችግሩን ለመቋቋም ባለ ኃይል ሁሉ መሰለፍ አይቻልም። እንኳን አብዮቱ ግቡን ባልመታበትና ሰፊው ሕዝብ ስልጣን ባልጨበጠበት የአገራችን ሁኔታ ይቅርና፣ በሩሲያ ውስጥ በነሌኒን ተመርቶ ወዛደሩ ሥልጣን ከጨበጠ በኋላ የሰፊው ሕዝብ የኑሮ ችግር ተባብሶ ነበር።
ይህ ስለተባለ ግን፣ አብዮታዊ ሁኔታ ስላለ የኢኮኖሚ ችግር ይኖራል፣ ስለዚህ አዲስ ነገር አይደለም፣ አስቸኳይ መፍትሄ መሻት አያስፈልግም ማለት አይደለም። የዚህ ኢኮኖሚያዊ ችግር መኖር በአብዮታዊው ትግል ላይ የሚያስከትለው ጉዳት በቀላሉ የሚገመት አይደለም። ይህንኑ በመገንዘብ የኢኮኖሚውን ችግር ለማባባስ አድሃሪ ኃይሎች የማይገለብጡት ድንጋይ አይገኝም። ስለዚህም፣ በዚሁ አብዮታዊ ትግል ውስጥ እያለንም የኤኮኖሚው ችግር ሙሉ በሙሉ ባይወገድ እንኳ ገብ የሚልበትን መንገድ፣ የአድሃሪዎች አሻጥር የሚከሽፍበትን ብልሃት መመርመርና ማግኘት ያስፈልጋል።
የኑሮ ውድነት፣ የሥራአጥ መብዛት፣ ወዘተ… በአጠቃላይ የሰፊው ሕዝብ ምሬት መብዛት ለፀረ አብዮት ቅልበሳ የተመቻቸ ሁኔታን ይፈጥራል። ፀረ ሕዝብ ኃይሎች አብዮቱን የሚቃወሙት በደፈናው የአብዮቱን ግቦች አንቀበልም በማለት አይደለም። እነዚህን የሰፊው ሕዝብ ምሬቶች በመጠቀም አብዮቱን ያጥላላሉ። በኢትዮጵያ ሁኔታም፣ ‘ለውጥ ለውጥ ብላችሁ ታግላችሁ ከኃይለሥላሴ ጊዜ የባሰ ሊመጣባችሁ ነው’ በሚለው ቅስቀሳ ላይ ይሰማራሉ። ሶሺያሊዝም በቃል ብቻ የተዋበ ስርዓት ነው ብሎ መለፈፍ ይቀናቸዋል። ሰፊው ሕዝብ አብዮታዊ ትግሉ በዚህ አጭር ጊዜ ውስጥ እለታዊ ችግሮችን ሲያስወግድለት ስለማያይም፣ እነዚህ አድሃሪዎች በዚሁ ተጠቅመው በአብዮታዊ ትግሉ ላይ እምነት እንዲያጣ ከፍተኛ ጥረት ያደርጋሉ። እንደዚህ ዓይነቱም ሰበካ፣ ለፀረ አብዮት ቅልበሳቸው ፖለቲካዊ ዝግጅት መሆኑ ነው። የቀናቸውለት ‘ከውድቀት ልናድንህ መጣን’ ለማለት ያመቻቸዋልና።
አብዮቱን በትክክለኛ አቅጣጫ ወደፊት ማራመድ የማይሳካላቸው፣ በርግጥም ለሰፊው ሕዝብ እለታዊ ችግሮች መፍትሄ ለማምጣት የሚያስችል መንገድ ለመጠቆም የሚያቅታቸው አናርኪስቶችና አብዮቱን የከዱ ቀልባሾች የሚጠቁሙት በዚሁ በሰፊው ሕዝብ ችግር፣ በቁስሉ እንጨት በመስደድ ነው። በቅርቡ በቢሾፍቱ፣ በአዳማና በሻሸመኔ ቀልባሽ አናርኪስቱ ቡድንና ሌሎችም አድሃሪዎች ሥራ አጡን በብዛት አነሳስተው በማሰለፍ ‘በሶሻሊዝም ሥርዓት ውስጥ የግል ሃብት አይኖርም’ በሚል የተወናበደ መፈክር ሰበብ ጥቃቅን ሀብቶችን፣ ጋሪና የፀጉር ማስተካከያዎች ሳይቀሩ፣ የ‘መውረስ’ እርምጃዎች አስወስደው ነበር። ይህን ዓይነቶቹ እርምጃዎች፣ በስቃይ ላይ የሚገኘውን ሥራአጥና ሌሎችንም ከማወናበድ በስተቀር ለችግሮቹ ምንም መፍትሄ የማያመጡ ናቸው። አብዮቱን በዛሬው ደረጃ የማይፃረሩ ኃይሎችን ወደ ፀረ አብዮት ድንኳን በመወርወር የጠላቱን ሰፈር ማጠናከርም ነው። በጠቅላላው ሁኔታውን አተራምሶ፣ ለአብዮቱ የሚታገሉ ኃይሎችን አቅጣጫ አስቶና ነጣጥሎ፣ ከጀርባችን ፀረ አብዮት አመጽ ለሚያዘጋጁ ጠላቶቻችን ዕድልና ፋታ መስጠትና በግርግሩ ከላያችን ጉብ እንዲሉ ለመርዳት ነው።
እንደገናም፣ በገቢር የሚሰቃየው ሠርቶ አደር፣ የነዚህን ችግሮች ምንነት፣ የሚወገዱበትን ዘዴ ጠንቅቆ ለመረዳት ከፍተኛ የፖለቲካ ንቃት ያስፈልገዋል። በዛሬ ችግሩ ምክንያት ትጥቁን እንዳይፈታ፣ አብዮታዊው ትግሉ ቀጥሎ በዚሁ አማካይነት ለችግሮቹ መፍትሄ እያበጀና እየታገለ እንዲሄድ እንደዚሁ ከፍተኛ የፖለቲካ ንቃት ያስፈልገዋል። የኢኮኖሚው ችግር ከቀን ወደ ቀን እየተባባሰ መሄድ ደግሞ ለወዛደሩና ለሠርቶ አደሩ የፖለቲካ ንቃት እድገት እንቅፋት ነው። ባገራችን ሳይንሳዊ ርእዩተ ዓለም ላይ የተመረኰዘ ቅስቀሳ በሰፊው ሕዝብ መሃል መካሄድ ከጀመረ ጊዜው በጣም ቅርብ ነው። በመሰረቱ ይኸ ርእዩተ ዓለም ዛሬም በሰፊው ሕዝብ መሃል ገና ሥር አልሰደደም። በዕለት ኑሮው የሚሰቃየውን ሠርቶ አደር ደግሞ ጊዚያዊ ችግሩ ጋብ የሚልበትን ዘዴና ብልሃት ሳይፈጥሩለት ርእዩተ ዓለሙን እንዲቀስም ብቻ ለማድረግ ስልሳ ጊዜ ቢሞከር ውጤቱ የሚፈልገውን ያህል ሊሆን አይችልም። በቅርቡ በተጀመሩት የውይይት ክበቦች፣ በብዙ ቦታ ከርእዩተ ዓለም ትምህርት ይልቅ በዕለታዊ ችግሮች ላይ ለመወያየት መሞከሩ አንድ መሰረታዊ መደገፊያ እንደሌለው ለመቁጠር አይቻልም። ይኸውም ባለንበት ሰዓት የሠርቶ አደሩ ዕለታዊ ችግር ፋታ የማይሰጥ መሆኑን ነው። በዚህ ላይ ደግሞ የቀልባሽ አናርኪስቶችና የአድሃሪዎች የውንብድናና የማጥላላት ዘመቻ አለ። ከሰለጠኑ አድሃሪዎች እንኳን አንዳንዶቹ ሳይንሳዊ ርእዩተ ዓለምን ፊት ለፊት በማጥላላት አይሰለፉም። ይህ ሳይንስ በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ይቅርና በአገራችንም ኃያልነቱን እያስመሰከረ መጥቷልና። በዚሁም ምክንያት አድሃሪዎቹም ሁኑ ቀልባሽ አናርኪስቶች ‘የለት ዳቦን ሳታገኝ ዳቦ በሬድዩ/በሬዲዮ የሚተላለፉትን አብዮታዊ ትምህርቶች ለማለት ነው።/ በልተህ ልትኖር ነው?’ ማለት ጀምረዋል። ወዛደሩና ሠርቶ አደሩ ከእለታዊ ችግሮቹ አልፎ ለዘላቂ ጥቅሙ ሊያሰልፈው የሚያስችለውን ንቃት እንዳያገኝ ይጣደፋሉ። ይህንን ንቃት ካገኘ በነርሱ ፀረ አብዮት ቅስቀሳ ሊፈታ እንደማይችል ጠንቅቀው ያውቃሉና።
እንግዲህ፣ እነዚህ ሁሉ አንድ ላይ ሲያያዙ፣ የኤኮኖሚ ችግር መኖር ለአብዮቱ በትክክለኛ አቅጣጫ ወደፊት መቀጠል እንቅፋት እንደሚሆን እናያለን። አድሃሪ ኃይሎች ያለውን ችግር ለማባባስ በየፈርጁ ጉድጓድ ሲቆፍሩ እንመለከታለን። የኤኮኖሚ ችግር አብዮቱን ለመቀጠል የሚኖረው እንቅፋትነት ብቻም ሳይሆን አድሃሪ ኃይሎች ይህን የሰፊው ሕዝብ ምሬት እያባባሱ በመጠቀም የሚያካሄዱት ቅስቀሳ ለፀረ አብዮት ሁኔታውን የሚያመቻች ነው። ሂትለር ሥልጣን ላይ ለመውጣት ካደረጋቸው ዋነኛ ትግሎች አንዱ፣ በሕዝብ ሥቃይ ላይ እየተመረኰዘ ያደረገው ‘ልብ ነኪ’ ቅስቀሳ ነው። ከአሌንዴ መውደቅ ቀደም ብሎ ለፋሺስቶች ሥልጣን ላይ መውጣት መንገድ የጠረገው ቅስቀሳ በዚሁ የሰፊው ሕዝብ ዕለታዊ ችግሮች አካባቢ የተደረገ ነው። ስለዚህም የዛሬው የአገራችን የኤኮኖሚ ችግር በቀላሉ የሚታለፍ ሳይሆን፣ የአብዮቱን እድል ከሚወስኑት ከፍተኛ ጉዳዩች እንደ አንዱ መታየት አለበት።
በበኩላችን አስቸኳይ መፍትሄዎች ናቸው ወደምንላቸው ሳንሄድ ግን፣ ይህ የኤኮኖሚ ችግር እንዲባባስ የሚያደርጉትን ኃይሎችና ዘዴዎቻቸውን መመርመር አለብን።
ለኑሮ አስፈላጊ የሆኑትን ዕቃዎች ከአምራቹ ወደ ሸማቹ የሚያስተላልፉት ነጋዴዎች ናቸው። የአገራችን ነጋዴዎች፣ በተለይ ከፍተኛዎቹ፣ በየካቲት እንቅስቃሴ ጥቅማቸው ተነክቷል። አብዮቱን ከሚፃረሩ ኃይሎች ጋር ተሰልፈዋል። ጥቅማቸው እስከዚህም ያልተነካ አንዳንድ ነጋዴዎችም አብዮቱ ከቀጠለ እኛንም ያሰጋናል በሚል ፍርሃት በርግገው ከፀረ አብዮት ተደባልቀዋል። ስለዚህ አብዮቱን ለመቀልበስ የሚያመቹ አሻጥሮችን ከመሥራት ወደኋላ አይሉም። በዝቅተኛ ዋጋ ከአምራቹ የገዙትን በከፍተኛ ዋጋ ለሸማቹ ይሸጣሉ። በሌላ በኩል፣ “ከኃይለ ሥላሴ ዘመን የባሰ መጣ” እንዲባልላቸው ከአምራቹ የገዙትን ዕቃ በመጋዘናቸው ይዘጉበታል፣ ከገበያ እንዲጠፋ ያደርጋሉ። /የአንዳንድ አስፈላጊ ሸቆጦችን ዋጋ መጨመር መጥቀስ ቢያስፈልግ፣ ለምሳሌ በያዝነው 1968፣ ከየካቲት እስከ መጋቢት ባለዉ የአንድ ወር ጊዜ ብቻ፣ የምግብ ዋጋ 6.9 በመቶ ከፍ ብሏል። እህል 2.0 በመቶ፣ ሥጋ 23.5 በመቶ፣ አሳ 3.6 በመቶ፣ ከቀንድ ከብቶች የሚገኙ እንደ ወተትና ቅቤ የመሳሰሉት 11 በመቶ፣ ቅመማ ቅመም 14.9 በመቶ ዋጋቸው ከፍ ብሏል።
በዚህም ላይ፣ የማከፋፈያ ድርጅቶች /በተለይም ከውጭ ለሚመጡ ዕቃዎች/ አሁንም አብዮቱን በሚፃረሩ ኃይሎች እጅ ናቸው። የነዚህም አሻጥር ሁለት ፈርጅ አለው። ባንድ በኩል በተጭበረበረ ፋክቱር የሃገሪቷን ሃብት ወደውጭ ያሸሻሉ። የውጭ አገር ደንበኞቻቸው፣ ኢትዮጵያ በምትገኝበት አብዮታዊ እንቅስቃሴ፣ እንኳን ፋክቱር በማጭበርበር ይቅርና በሌላም ብዙ ብዙ ነገሮች እንደሚረዷቸው ግልጽ ነበር። በሌላ በኩል፣ የገባው ዕቃ በትክክል እንዳይከፋፈል አሻጥር ይሰራሉ። እቃው የሚፈለግበት ቦታ እንዳደርስ፣ ዋጋው ከሚገባው በላይ እንዲወደድ ያደርጋሉ።
የኢትዮጵያ አብዮት ጠላቶች መሃል ከፍተኛ የሥራ ክፍፍልና ሕብረት አለ። ይህም አብዮቱ ውሉ ሲያድር የሚጨምር ነገር ነው። ፊውዳሎች በጫካና በውጭም እየተደራጁ በግልጽ አብዮቱን ይፃረራሉ። ነጋዴው በመስኩ በልዩ ልዩ አሻጥሮች ለፀረ ሕዝብ ኃይሎች አመጽ ሁኔታውን የሚያመቻች ሚና ወስዷል። ከኃይለሥላሴ የተወረሰው ቢሮክራሲ በበኩሉ በሥልጣኑ እየተጠቀመ፣ እራሱም አሻጥር እየሰራ፣ የሌሎችንም አሻጥር እንዳላየ እያየና ቦታም እየሰጠ የራሱን ፀረ አብዮት ድርሻ ያበረክታል።
እንደ ብሄራዊ ኃብት ልማት የመሳሰሉት በአገሪቱ ብሄራዊ ኤኮኖሚ ላይ የሚፈጽሙት ወንጀል ዛሬ ለብዙሃኑ ተራማጆች ስውር አይደለም። በቁጥጥራቸው ሥር እንዲውሉ በተደረጉት የማምረቻና የማከፋፈያ ድርጅቶች የተጠበቀባቸውን የምርት ውጤት ለማስገኘት ሳይችሉ ቀርተው አብዛኞቹ በኪሳራ ላይ ይገኛሉ። ብሄራዊ ኃብት ልማት ከመንግሥት እርሻዎች በጊዜው ምርት እንዲሰበሰብ ሳያደርግ በመቅረቱ እህሉ እዚያው ታጭዶ በተከመረበት ቦታ እስከመበስበስ የደረሰበት አንድ ሁለት የሚባል አይደለም። በወሊሶ አካባቢ ብቻ እስከ ሃያ ሺህ ኩንታል በቆሎ ከአገልግሎት ውጭ ሆኗል። በአሩሲና በሸለቆው አካባቢም የእህል መበስበስ ደርሷል። በአዋሽ ሸለቆም እንዲሁ በብዙ መቶ ኩንታል የሚቆጠር ጥጥ የተከመረበት ቦታ እስከመቅለም ደርሷል። በብሄራዊ ኃብት ልማት እጅ በሚገኙት የከብት እርባታ ጣቢያዎች የሚገኙት የቀንድ ከብቶች አስፈላጊው እንክብካቤ ሳይደረግላቸው ቀርቶ የሞቱት ቁጥራቸው በቀላሉ የሚገመት አይደለም። በፋብሪካና በኢንዱስትሪ አካባቢም የምርቱ ውጤት እንዲያቆረቁዝ፣ በነዚህ ውስጥና በእርሻ ሥራ በተሰማሩት ወዛደሮችና ሠርቶ አደሮች የሚፈፀመው ግፍ ሁኔታውን ለመቀልበስ ሆን ተብሎ የሚደረግ አሻጥር መሆኑን ማንም ሊረዳው ይችላል። ሠርቶ አደሩ በተደጋገመ ጊዜ በብሄራዊ ኃብት ልማት ላይ እሮሮውንና አቤቱታውን ማሰማቱ የታወቀ ቢሆንም፣ በአድሃሪዎች ባለሥልጣኖችና የኰርፖሬቲቭ [ኮኦፖሬቲቭ] ኃላፊዎች ላይ በመንግሥቱ በኩል እስካሁን የተወሰደ እርምጃ የለም።
የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴርም እንዲሁ ብዙ የኢኮኖሚ አሻጥር የሚፈፀምበት፣ የተበሻቀጠና ጠቅላላ ኰራኘሽን የነገሰበት የቢሮክራሲው አንድ ክፍል ነው። ዛሬ፣ እንኳንስ ለወዛደሩና ለአርሶአደሩ ይቅርና በመሃከለኛ ገቢ አግኚው ከተሜ እንኳን የሸቀጣ ሸቀጥ ዋጋ እንዲህ በመናር ላይ እያለ፣ የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የዋጋ ቁጥጥር ለማድረግ ዳር ዳር ሲል እንኳ አይታይም። ባለው የኤኮኖሚ ችግር የተነሳ፣ ለኑሮ አስፈላጊ የሆኑትን ለምግብ የሚያገለግሉና ሌሎችም ሸቀጦች ለነጋዴውም ሆነ ለሸማቾች በክፍፍል /ራሺን/ መልክ እንዲዳረስ የማድረጉ ሙከራ የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴርን ጭራሽ የሚያሳስበው አይደለም። ከዚህም አልፎ፣ ከትላልቅ ነጋዴዎች ጋር /ከውጭዎቹም ጭምር/ በጥቅምና በጉቦ እንደሸረሪት ድር የተሳሰሩ አድሃሪና የተግማሙ ቢሮክራቶች ስላሉ ሠርቶ አደሩ ሕዝብ በዕለት ችግሮቹ ተወጥሮ እንዲያዝና ለቀልባሾች መሳሪያ እንዲሆን ትልቅ አሻጥር ይፈትላሉ።
ስለብሄራዊ ኃብት ልማት አንድ ሌላ ጉዳይ መጥቀስ ቢያስፈልግ፣ በአሁኑ ጊዜ በከተማው የወተተ እጥረት ሲኖር ይህም ድሮ ከሚገኘው በአንድ አራተኛ ዝቅ ብሏል። የሚገርመው ግን፣ ከዓለም ባንክ በተገኘው ብድር ለወተት ኢንዱስትሪ ማስፋፊያ ተብሎ ወደ 2 ሚሊዩን ብር የሚያወጣ ገንዘብ የተገዛ መሳሪያ አገልግሎት ላይ እንዳይውል ብሄራዊ ኃብት ልማት ካሸገው ሁለት ዓመት ሆኖታል። የብሄራዊ ኃብት ልማት የዕቃ ግምጃ ክፍል ከእነ ሚቼል ኮትስና ከመሳሰሉት የውጭ አገር ካፒታሊስቶች ድርጅቶች ጋር በመመሳጠር ሌሎች አሻጥሮችን እንደሚሰራም የታወቀ ነው።
ከነጋዴዎች፣ ከአድሃሪ ቢሮክራቶች ሌላም፣ የንዑስ ከበርቴው ቀልባሽ አናርኪስት ቡድን በዚሁ የኤኮኖሚ ችግር እንዳቅሚቲ የፀረ አብዮት ድርሻ ተሰጥቶታል። ለምሳሌ በወሊሶ አካባቢ አርሶ አደሮች እህላቸውን ከተማ እንዳይሸጡ ሰፊ ቅስቀሳ አካሄደ። ተመልሶ ለከተሜው ገበሬው እህል አልሸጥ አለ ምን ይዋጣችሁ? ወዘተ… የሚል ቅስቀሳ ያዘ። ይህ ድርጊት ባንድ በኩል በአርሶ አደሩና በከተማው ሠርቶ አደር መሃል መቃቃር እንዲፈጠር ለማድረግ ነው። በሌላ በኩል የከተማውን ሠርቶ አደር ችግር በማባባስ፣ በፀረ አብዮት ቅስቀሳ እንዲፈታ ለማመቻቸት ነው።
በሌላ ቦታም፣ /በሐረር ክፍለ ሃገር/ እንደዚሁ አርሶ አደሩን በበሬ አትረስ፣ መንግሥት የወረሳቸው ትራክተሮች ሊያርሱልህ ይገባል በሚል ቅስቀሳ አርሶአደሩን አሳምነው በሬውን አሸጡ። የእርሻው ወቅት ሲዳረስ የአካባቢው ትራክተር ነጂዎች ሥራ እንዲያቆሙ መቀስቀስ ያዙ። ትራክተር ያርስልኛል ብሎ በሬዎቹን የሸጠው አርሶአደር በምኑ ይረስ? ካላረሰ ምን ይብላ? ካልበላ እንዴት አብዮቱን ከግቡ ያድርስ? ቀልባሽና አናርኪስቶቹ የፈለጉትም የዚህ ዓይነቱን ሁኔታ መፈጠር ነው። ይህም ብቻ ሳይሆን አርሶአደሩ የሚጋጨው ከነርሱ ጋር ሳይሆን ከትራክተር ነጋዴዎቹ ጋር በመሆኑ፣ እንደገና ለኢትዮጵያ አብዮት ዋስትና ስለሆነው ወዛደር አርሶአደር ሕብረት መሰናክል መሥራታቸው ነው።
እንግዲህ፣ የአገራችን የኤኮኖሚ ችግር መፍትሄ እንዳያገኝ ብቻ ሳይሆን እንዲባባስ የሚጥሩት የኢትዮጵያ አብዮት ጠላቶች በሞላ ናቸው። ይህም የዚህ ኢኮኖሚያዊ ችግር መባባስ ለነርሱ ፀረ አብዮት አመጽ ትልቅ አመቺ ሁኔታ እንደሚፈጥር እንደገባቸው ያሳየናል። በአንፃሩ፣ የሰፊውን ሕዝብ ወገንነት የመረጡ ተራማጆች ደግሞ ይህ የኢኮኖሚ ችግር ለፀረ አብዮት ቅልበሳ እንዳይመች ብቻ ሳይሆን የሰፊው ሕዝብ እለታዊ ችግሮች መፍትሄ እያገኙ እንዲሄዱም መታገል ይኖርባቸዋል።
የሥራ አጡንና የቦዘኔዎችን ችግር በሚመለከተው በኩል፣ አገራችን ዛሬም ወደኋላ የቀረች አገር መሆንዋን መረዳት ያስፈልጋል። ኢንዱስትሪ በቅርብ ጊዜ ውስጥ ተስፋፍቶ ሥራ አጡንና ቦዘኔውን በኢንዱስትሪ ሥራ ላይ ማሰማራት አይቻልም። ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉት እንደልብስ ሰሪዎችና የመሳሰሉት የእደጥበብ ሥራዎች በሕብረት እንዲደራጁና ወደ መለስተኛ ኢንዱስትሪዎች እንዲያድጉ ማድረግ ያስፈልጋል። እነዚህን የእደጥበብ ሥራዎችና የኢትዮጵያን ሥራ አጥና ቦዘኔዎች ቁጥር ስናነፃፅር በዚህ በኩል ሊሰማሩ የሚችሉት በጣም አነስተኛው ክፍል ብቻ ነው። በሌላ በኩል፣ በአዲስ አበባ ዙሪያ ብቻ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ሥራአጦችንና ቦዘኔዎችን በአትክልት፣ ፍራፍሬና ችግኞችን በመትከል ሥራ ማሰማራት ይቻላል። ይህ ዓይነቱ የ“አረንጓዴ መቀነት እቅድ” በመባል የሚታወቀው የማሰማራት ዘዴ ባንድ በኩል ባጭር ጊዜ ውስጥ ከሥራ አጡና ከቦዘኔዎች የተወሰነውን ክፍል ሥራ ለማስያዝ ሲጠቅም፣ በሌላ በኩል እንደዚህ ዓይነቶቹን የእርሻ ምርቶች ከፍ ለማድረግ ያስችላል። ሥራ አጡና ቦዘኔውም ከለመደው የከተማ ኑሮ ብዙ ሳይርቅ ቀስ በቀስ በእርሻ መተዳደርን እንዲላመድ ያደርጋል። በእንደዚህ ዓይነቱ ብዙ ወጭ የማይጠይቅ ዕቅድ የሥራአጥ ችግራቸውን ማስታገስ ከቻሉ ሶሻሊስት አገሮች ኩባን እንደምሳሌ መጥቀስ ይቻላል።
ሆኖም፣ እነዚህ ከላይ የጠቀስናቸው ሁሉ ግፋ ቢል ከፊል መፍትሄ ቢሆኑ ነው። የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ዋና መሰረት እርሻ ነው። ስለዚህ ሥራአጡንና ቦዘኔውን በአስቸኳይና ዋስትና ባለው መንገድ ሥራ ለማስያዝ ከተፈለገ ዋናው እነኚህን በእርሻ ሥራ ላይ ማሰማራት ነው። ይህ ሲሞከር ባንድ በኩል ከተማ መኖር የለመዱ ሥራአጦችና ቦዘኔዎች /በተለይም ቦዘኔዎች/ ከገጠር ኑሮ ጋር እንደገና ለመላመድ ያስቸግራቸዋል። በሌላ በኩልም፣ የተገኘችዋንም ገቢ በቀን በቀኑ ማግኘት የለመዱ ሥራአጦችና ቦዘኔዎች /በተለይም ቦዘኔዎች/ ገቢያቸውን ዓመት ጠብቆ ማግኘትን እንደችግር መመልከታቸው አለ። በዚህም ላይ ከሥራ አጥነት ጋር ተያይዘው የሚመጡ፣ በተለይም በቦዘኔው ላይ ጎልተው የሚታዩ ለዲሲኘሊንና ትዕግስት ለሚጠይቁ ሥራዎች ጠንቅ የሆኑ ጠባዩች አሉ። እነዚህ ሁሉ ችግሮች የሚወገዱት በእርሻ ሥራ ላይ ለሚሰማሩ ሥራ አጦችና ቦዘኔዎች በቂ ፖለቲካዊ ትምህርት መስጠት ንቃታቸውን እንዲያዳብሩ በማድረግ ነው። ንቃታቸውን በማሳደግና የመቋቋሚያ እርዳታ በመስጠት ሥራ አጦችንና ቦዘኔዎችን በእርሻ ሥራ ማሰማራት የአገሪቷን ሥራአጥ ችግር ማስወገዱ ብቻ ሳይሆን ለኢኮኖሚያዊ እድገትም ትልቅ አስተዋጽኦ አለው።
የኑሮ ውድነትንና የእቃዎችን ከገበያ መጥፋት በሚመለከተው በኩል፣ ትላልቅ የማከፋፈያ ድርጅቶች /በተለይ ከውጭ ለሚመጡ እቃዎች/ ተወርሰው በመንግሥት ቁጥጥር ሥር መዋል አለባቸው። በዚህም፣ በተጭበረበረ ፋክቱርና በሌላም ዘዴ በነዚህ አስመጪና ላኪዎች ወደውጭ የሚሰረቀው የአገሪቷ ገንዘብ አገር ውስጥ ቀርቶ በሥራ ላይ ይውላል። በተጨማሪም፣ በነዚህ ማከፋፈያ ድርጅቶች የሚሰራው አሻጥር ገደብ ያገኝና ከውጭ የሚመጡ ዕቃዎች የተመረጡ፣ ለሰፊው ሕዝብ ጥቅምና አገልግሎት ተፈላጊ የሆኑ ብቻ ይሆናሉ። እነዚህም እንደ አስፈላጊነታቸው ይከፋፈላሉ፣ ዋጋቸውም ከሕዝቡ የኑሮ ደረጃ ጋር ተመጣጣኝ እንዲሆን ይደረጋል።
ከዚህም በላይ፣ በሸማቾችና በአምራቾች መሃል ሆነው የሚያሻጥሩ ነጋዴዎችን ለመቋቋም፣ መንግሥት የራሱን የማከፋፈያ ጣቢያዎች መክፈት አለበት። በተጨማሪም የከተማው ሰርቶአደር የሕብረት ሥራ ሱቆች እንዲጠናከሩ መረዳት አለባቸው። የገበሬ ማህበራትም በማህበራቸው ስር የሕብረት ንግድ እንዲያቋቁሙ መታገዝ አለባቸው። እነዚህ ሲፈጸሙ፣ ነጋዴዎች የግድ ከነዚህ ከሕዝቡ የኑሮ ደረጃ ጋር ተመጣጣኝ በሆነ ዋጋ ከሚሸጡ መንግሥታዊና ሕዝባዊ ማከፋፈያዎች ጋር መወዳደር ስለሚገደዱ ዛሬ እንደሚያደርጉት ዋጋቸውን እንደፈለጉት የመስቀል እድል አይኖራቸውም።
ከነዚህ በተረፈ፣ የቢሮክራሲውን አሻጥርና አሻጥረኞችን መደገፍ መቋቋም የሚቻለው በቅርብ ጊዜ ሲታይ ቢሮክራሲውን በጥብቅ በመቆጣጠርና በማፅዳት ነው። መሰረታዊ መፍትሄው ግን ለሰፊው ሕዝብ ዲሞክራሲያዊ መብቶችን በማክበር ነው። ቢሮክራሲው በሥልጣኑ ተጠቅሞ የሚሰራውን አሻጥር ባጠቃላይና ተጠያቂ የሆኑ ግለሰቦችን ለማጋለጥ የሚቻለው ዲሞክራሲያዊ መብቶች ሲከበሩ ነው። በሥልጣን ሌላ ነገር ሠርቶ በአፍ የሕዝብ ወገን እየመሰሉ ማወናበድ የሚቀረው፣ ሁሉም በሥራው የሚፈተንበት ሁኔታ የሚፈጠረውም ዲሞክራሲያዊ መብቶች ለሰፊው ሕዝብ ሲከበሩ ነው። ሰፊው ሕዝብ የእለት ችግሮቹን ተጨባጭ ምክንያቶች ጠንቅቆ የሚረዳውና ለመፍትሄዎቹ መታገል የሚችለው ሌሎች እናስብልሃለን በሚሉት ሳይሆን ዲሞክራሲያዊ መብቶቹን በጁ ጨብጦ ሲታገል ነው።
እንድገመውና፣ የዛሬው የኢኮኖሚ ችግር የኢትዮጵያን አብዮት ዕድል ከሚወስኑት ከፍተኛ ጉዳዩች አንደኛው ነው። የሰፊው ሕዝብ እለታዊ ችግሮች እንዲወገዱ፣ ለዘላቂ መፍትሄውና ለዘላቂ ድሉ በሙሉ ኃይሉ እንዲሰለፍ መታገል አጣዳፊ ሃላፊነት ነው። በዚህም አንፃር፣ ሰፊው ሕዝብ፣ በእለታዊ ችግሩ እየተጠቀሙ የአዞ እንባ በሚያነቡ ጠላቶቹ ቅስቀሳ ትጥቁን እንዳይፈታ፣ በነዚህ እለታዊ ችግሮቹ ላይ ተራምዶ ለዘላቂ መፍትሄዎቹና ግቡ እንዲሰለፍ ንቃቱ ማደግ፣ ድርጅቱ መጠናከር አለበት። እውነተኛ ተራማጆችም የሰፊውን ሕዝብ እለታዊ ችግሮች ችላ ብለው ለዘላቂ ግቡ ሊያሰልፉት እንደማይችሉ ተረድተው፣ እነዚህን እለታዊ ችግሮች ለማሰወገድ በሚደረገው ትግል በግንባር ቀደምነት መሰለፍ አለባቸው።