የሰፊው ሕዝብ ድምፅ
ቁጥር 45፣ ነሐሴ 10፣ 1968
የፅሁፉ ፍሬ ሀሳብ
መኢሶን በዚህ የሰፊው ሕዝብ ድምፅ እትሙ፣ ገና ግቡን ያልመታውና ከሁለት አመታት በላይ የተካሄደው እንቅስቃሴ በጸረ አብዮት ኃይሎች ጥቃት ሳይከሽፍ ለመጓዝ ከፍተኛ ትግል ላይ መሆኑን ይጠቁማል። ከዚህ ጊዜያዊ ውጥረት ለመውጣት እስካሁን የተገኙትን መጠነኛ ድሎች እየተጠቀሙ ለተጨማሪ ድሎች መታገል፣ እንዲሁም የአብዮቱን ቀልባሽ አድሃሪ ኃይሎች ሙከራዎች እያከሸፉ፤ የትግሉ ድሎች ዋስትና እንዲኖራቸው ማድረግ እጅግ አስፈላጊ እንደሆነ ያስገነዝባል።
በአገራችን፣ ከሁለት ዓመታት በላይ ያላቋረጠ፣ ብዙ ውጣ ውረዶችን የተጓዘ አብዮታዊ እንቅስቃሴ ዛሬም ይካሄዳል። ግቡን አልመታም፣ በፀረ አብዮት ኃይሎች አሸናፊነትም አልተገታም። እንደዚህም ሆኖ በነዚህ የትግል ጊዜያት ከፍተኛ ድሎች ተገኝተዋል። የሚቀሩን ድሎችም ብዙ ናቸው። እስካሁን የተገኙ ድሎች በበኩላቸው ለአብዮታዊው እንቅስቃሴ መቀጠል በጣም ምቹ ሁኔታ ፈጥረዋል። ነገር ግን፣ እስከዛሬም ድረስ በነዚህ ድሎች ተጠቅሞ ለድሎቹ ዋስትና ለመስጠትና የሚቀሩትን መሰረታዊ ድሎች ለመቀዳጀት ትግሉን ከከፍተኛ ደረጃ ለማድረስ አልተቻለም። የድሎቹ መጠበቅ ሆነ የትግሉ በከፍተኛ ደረጃ መቀጠል አሁንም አስተማማኝ ዋስትና የለውም። ጭቁኖችና ተራማጆች ትግላቸውን አፋፍመው አብዮቱን ከግቡ ለማድረስ የሚታገሉትን ያህል የሕዝብ ጠላቶችም ኃይላቸውን ሰብስበው አብዮቱን ለመቀልበስ በመታገል ላይ ናቸው። በሌላ አነጋገር፣ ዛሬ ጭቁኖችም ጨቋኞችም ለተቃራኒ ግቦች ተመሳሳይ ዝግጅት በማድረግ ላይ ናቸው። እንዲያውም ከጭቁኖች ይልቅ ጨቋኞች የተሟላ ዝግጅት ይዘው ለመቅረብ በመራወጥ ላይ ናቸው። የዛሬው አብዮታዊ ትግል ከነዚህ ሁለት ተፃራሪ ወገኖች በየትኛው አሸናፊነት ለጊዜው እንደሚዘጋ ለማረጋገጥ አስቸጋሪ የሆነበት ሁኔታ ውስጥ እንገኛለን። ከታሪክ አንፃር ሲታይ የሰፊው ሕዝብ ማሸነፍ የማይቀር ነገር ነው። ይህ ግን ፀረ ሕዝብ ኃይሎች አሸንፈው ለተወሰነ ጊዜ የሕዝቡን ትግል ሊቀለብሱ አይችሉም ማለትን አያመለክትም። የጭቁኖች የትግል ታሪክ የድል ብቻ ሳይሆን የመሸነፍም ገጾች አሉት። የኢትዮጵያ ሀቀኛ ተራማጆችና ጭቁኖች የምንገኝበት ሁኔታ ይኸ መሆኑን መረዳት አለብን።
በሰፊው ሕዝብ ድምፅ ቁጥር 40 ላይ፣ የደርጉ መለስተኛ ኘሮግራም መውጣት ለሰፊው ሕዝብ ትግል አመቺ ሁኔታ የመፍጠሩን ያህል ጠላቶቻችንም ከመቸውም የበለጠ ትግላቸውን እንዲያፋፍሙ ያስገድዳቸዋል ብለን ነበር። ከመለስተኛ ኘሮግራሙ ወዲህ ያለው የኢትዮጵያ ሁኔታ ይህንን ሀቅ በሚገባ ያረጋግጣል። የተለያዩ መልኮች ይዘው የሚቀርቡት የኢትዮጵያ አብዮት ጠላቶች በየፊናቸው ፀረ አብዮት ትግላቸውን አፋፍመዋል። ደርጉ ከሞላ ጐደል ወገን በመለየቱ፣ ኢምፔሪያሊስቶች የኢትዮጵያን ፀረ አብዮት ኃይሎች ለማስተባበርና ለመርዳት ከመቸውም ጊዜ የበለጠ ተነሳስተዋል። እንግዲህ፣ የፀረ አብዮት ኃይሎች ዝግጅትና ትግል በጣም ከፍ እያለና እየተጠናከረ መጥቷል ማለት ነው።
በአገር ውስጥ፣ ጥቅማቸው የተነካና በስጋት አብዮቱን የከዱ ነጋዴዎችና ከበርቴዎች የአገሪቷን የኑሮ ችግር ለማባባስና ኢኮኖሚውን የበለጠ ለማቃወስ ዛሬ በየቦታው በመጠኑ መጋለጥ የጀመሩትን አሻጥሮች በማካሄድ ላይ ናቸው። የሚሰሩት አሻጥር በመጠኑ ተጋለጠ እንጂ አሻጥረኞቹ አልተወገዱም። ዛሬም እነሱ በሚሰሩት አሻጥር የሚፈጠረው የኑሮ ችግር አልቀነሰም። የሚፈጥሩት የኢኰኖሚ ቀውስም አልተስተካከለም። የተባባሰ የኑሮ ችግር፣ የተተራመሰ ኢኰኖሚ ለአብዮት ቅልበሳ ጥሩ አካባቢ ስለሚፈጥር ወደፊትም ሙሉ በሙሉ እስካልተጋለጡና እንደ አንድ የአብዮቱ ጠንቅ እስካልተመቱ ድረስ ይህን ፀረ አብዮት ሴራ አያቆሙም። እንዲያውም ለነዚህ ፀረ ሕዝብ ክፍሎች የሚሰጠው ፀረ አብዮታዊ የትግል ድርሻ ዛሬ በተሰማሩበት የኢኰኖሚ አሻጥር በኩል ስለሆነ፣ ከሲአይኤ በሚጐርፍላቸው ገንዘብ አስፈላጊ ሸቀጦችን ገዝቶ መደበቅ፣ ሸማቹ የሚፈልገውን ሸቀጥ ማሳጣት፣ በዚህም የሰፊውን ሕዝብ ችግር ማባባስ ዓይነተኛ ተግባራቸው ይሆናል።
ለፊውዳሊዝምና ለኢምፔሪያሊዝም ጥቅም ማስጠበቂያ የቆመ ቢሮክራሲ በምንም ተዓምር የሰፊው ሕዝብ አብዮት ማራመጃ መሳሪያ ሊሆን አይችልም። የኢትዮጵያ ቢሮክራሲ ቁንጮው ላይ በመጠኑ ቢመታም እስካሁንም በበቂ ያልተነካ የአብዮት ጠላት ነው። ዛሬም ከአብዮቱ ትላልቅ እንቅፋቶች አንዱ ይኸው ከኃይለሥላሴ የተወረሰው ቢሮክራሲ ነው። ቢሮክራሲው በሺህ ድሮች ከአሮጌው ሥርዓት ጋር የተያያዘ በመሆኑ በአሰራሩ ሁሉ የዚህን አሮጌ ሥርዓት መደምሰስ ቀርቶ በቅጡ መሻሻል ለማስቀረት ይጥራል። በገጠር፣ ፀረ አርሶአደር እርምጃዎች በመውሰድ፣ በድብቅና በግልጽ ከአርሶአደሩ ጠላቶች ጋር በማበር የአብዮቱን ሂደት ለማደናቀፍ የተቻለውን ሁሉ በማድረግ ላይ ነው። ትላልቅና አድሃሪ ቢሮክራቶች፣ ፀረ አብዮት ኃይሎች በኢምፔሪያሊዝም አስተባባሪነት ደርጉን ገልብጠው ሊያስቀምጡ ለሚፈልጉት አሻንጉሊት ፀረ ሕዝብ መንግሥት፣ ለመሪነት የሚታጩ ናቸው። በኢምፔሪያሊዝም አስተባባሪነት የኢትዮጵያን አብዮት ጠላቶች የሚያግዝና የሚመራ ኃይል የሚፈልቀው ከቢሮ ከበርቴው ለመሆኑ ምንም ጥርጥር አይኖርም። ቢሮ ከበርቴው ከውስጥና ከውጭ አድሃሪዎች ጋር በገባው ፀረ አብዮት ቃል ኪዳን መሰረት፣ በሥልጣኑ ተጠቅሞ የአብዮቱን እድገት ሊገታ ይፍጨረጨራል። በስውርና በዘወርዋራ አሻጥር ትግሉን ሊያደናቅፍ ያሴራል። የኢትዮጵያ ሕዝቦች ትግል ወደፊት ይገፋ ዘንድ የቢሮክራሲውን አሻጥር እየሰባበረ መሄድ አለበት። ሰፊው ሕዝብ የድሉና የእድሉ ባለቤት መሆኑ የሚረጋገጠውም በነዚሁ ትግሎች ውስጥ አልፎ የዛሬውን ቢሮክራሲ ፈረካክሶ በመጣል በቦታው የራሱን ሕዝባዊ አስተዳደር ሲገነባ ብቻ ነው። የአብዮቱ ከግቡ መድረስ ዋስትና የሚኖረውም ያን ጊዜ ብቻ ነው። ይህ መታወቅ ያለበት የአብዮት ሀቅ ነው። ስለዚህም የዛሬውን የኢትዮጵያ ሕዝቦች ትግል ለመቀልበስ ከሚታገሉት ጠላቶች አንደኛው አሁንም ከሥልጣን ያልተወገደው ቢሮ ከበርቴ እንደሆነ መረዳት ያስፈልጋል።
ከመንግሥት ሥልጣን ከሞላ ጐደል የተወገደው፣ የኢኰኖሚ ብዝበዛ መሰረቱን የተነጠቀው የፊውዳሉ መደብ እስከዛሬም ድረስ በተያያዘው አብዮታዊ እሳት ሙሉ በሙሉ አልተቃጠለም። ያመለጡ መሳፍንት ከውጭ አድሃሪዎች የመሳሪያ እርዳታ በመሰብሰብ ላይ ናቸው። በሲአይኤና በሌሎችም ኢምፔሪያሊስቶች እርዳታ ፋሺስታዊ ድርጅታቸውን በማጠናከር ላይ ናቸው። በውስጥ የሚገኙ ወኪሎቻቸውም በየቦታው ፀረ አብዮት አመፃቸውን በማቀጣጠል ላይ ናቸው። ዛሬም ቢሆን የብዙ ክፍላተ ሀገር አርሶ አደሮች ከመሬት ከበርቴዎች ጥይት እፎይ አላሉም። ከጥይቱም ሌላ አርሶአደሩን አወናብደው ከጐናቸው ለማሰለፍ የሚያደርጉት ጥረት በቀላሉ የሚታይ አይደለም። ፋታ አግኝተው ኃይላቸውን ባጠናከሩና የትጥቅ ትግላቸውን በየጊዜውና በየቦታው በለኮሱ ቁጥር በጭቁን ሕዝቦች ትግል ላይ የሚጥሉት አደጋ ቀላል አይደለም።
የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም የዓለም ኢምፔሪያሊስቶችን መሪነት ከያዘበት ጊዜ ጀምሮ፣ የጭቁን ሕዝቦችን ትግል ለመቅጨት፣ አድሃሪ ሥርዓቶችን ለመጠበቅ እጁን ያላስገባበት አገር በዓለም ላይ የለም። ከነዚህም በርከት ባሉ አገሮች /በኮርያ፣ በኮንጐ፣ በቪየትናም፣ በላኦስ፣ በካምቦዲያ. . ./ ቀጥተኛ ወራሪዎች በማድረግ ከፍተኛ የግድያና የማጥፋት ጦርነቶች አካሄዷል። ዞሮ ዞሮ በጭቁኖች አብዮታዊ አመጽ ተደቁሶ ሀፍረት ተከናንቦ ከነዚህ አገሮች ከመባረር ባይድንም በነዚህ ሕዝቦች ላይ ያደረሰው እልቂትና መከራ እጅግ ከባድ ነበር። በሌላ አንፃር፣ በአብዛኞቹ አገሮች የሕዝቦችን ትግል ለመደምሰስና ፀረ ሕዝብ አገዛዞችን ለመጠበቅ የተጠቀመበት ዘዴ ቀጥተኛ ወረራ ብቻ አልነበረም። ባንድ በኩል በየአገሩ ያሉ ቡችሎቹን እስከአፍንጫቸው በማስታጠቅ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ሲአይኤ በተባለው የስለላና የነፍስ ገዳይ ድርጅቱ አማካይነት ሕዝባዊ ትግል ገፍቶ አሻንጉሊት መንግሥቱን በሚያርበደብድበትና ተሳክቶም በሚጥልበት ጊዜ ፋሺስታዊ መፈንቅለ መንግሥት በማውጠንጠን የጭቁኖችን ትግልና እድገት የተገታበት ቦታ ጥቂት አይደለም። በኢራን፣ በኢንዶኒዚያ፣ በብራዚል፣ በቺሊ. . . ና በርከት ባሉ ሌሎች አገሮች የተቋቋሙት ፋሺስታዊ አገዛዞች በሙሉ የሲአይኤ ፍጡሮች ናቸው። እንደ ቪየትናም በቀጥታ ወረራ ባይሆንም፣ ሲአይኤ በመፈንቅለ መንግሥት ባመጣቸው አገዛዞች አማካይነት በነዚህ አገሮች ሕዝቦች ላይ ከፍተኛ ፍጅት ስቃይና በደል ተፈጽሟል፣ እየተፈጸመም ነው። በቀጥተኛ ወረራ የጭቁን ሕዝቦችን ትግል ለመደምሰስ ባደረጋቸው ተደጋጋሚ ሙከራዎች በደረሰበት ኪሳራና ውርደት፣ በተለይም የዓለም ተራማጅና ጭቁን ሕዝቦች ሁሉ ከፍተኛ ተቃውሞ ስላለበት፣ በዛሬዋ ዓለም የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም ያተኩረው በሲአይኤ አማካይነት አብዮት ለመቀልበስ በሚደረግ መፈንቅለ መንግሥት ላይ ነው። ወረራው ከጥያቄ ውጭ ሆኗል ለማለት ሳይሆን፣ በቅድሚያ የሚሞከረው የመፈንቅለ መንግሥቱ ሴራ እንደሆነ ለመጠቆም ያህል ነው። በየአቅጣጫው በጭቁኖች ትግል ተወጥሮ የሚያጣጥረው ኢምፔሪያሊዝም የጭቁኖችን ትግል ለመደምሰሰ ማንኛውንም ዘዴ ከመጠቀም አይመለስም።
እንግዲህ፣ ኢትዮጵያም ኢምፔሪያሊስቶች ከብዙ አመታት ጀምሮ በቁጥጥራቸው ስር አውለው ሲበዘብዟትና ሲጨቁኗት ያቆይዋት አገር በመሆኗ፣ በተለይም የአሜሪካ ኢምፔሪያሊዝም ነፃነቷን እንድትቀዳጅ፣ ከርሱ ተጽእኖ እንድትላቀቅ በፍፁም አይፈልግም።
ባለፉት ሁለት ዓመታት የተካሄደው እንቅስቃሴ በገቢር ፀረ ኢምፔሪያሊስት ይዘት ቢኖረውም፣ ኢምፔሪያሊዝምን በማያዳግም ሁኔታ ካገራችን ገጽ ሊያጠፋ የሚችለው የእንቅስቃሴ ደረጃ ገና ልንደርስበት የተቻኰልነው ነው። ወታደራዊው ደርግም በመሰረቱ አንዳንድ ፀረ ኢምፔሪያሊስት እርምጃዎች ቢወስድም፣ ከሞላ ጐደል ግልጽ ፀረ ኢምፔሪያሊስት አቋሞች ማሳየት ከጀመረ ጊዜው ሩቅ አይደለም። ስለዚህም፣ ባንድ በኩል የኢትዮጵያ ጭቁኖች ኢምፔሪያሊዝምን ካገራቸው ምድር ሳያባርሩ ነፃነታቸውን ለማግኘት እንደማይችሉ ተረድተው ለዚህ ትግል መዘጋጃቸው ጊዜ በመሆኑ የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም ትግላቸው በርግጥ እርሱን የመደምሰሻ ኃይል ሳያገኝ ባጭሩ ሊቀጨው በይበልጥ ተነሳስቷል። በሌላ በኩል ደግሞ፣ ደርጉ ከንግዲህ በመለስተኛ ኘሮግራሙ የወሰናቸውን ፀረ ኢምፔሪያሊስት አቋሞች በሥራ መተርጐም ከቀጠለ፣ ኢምፔሪያሊስቶች በተለይም የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም ከድሮው ይበልጥ ዛሬ “ይቺ ባቄላ ካደረች አትቆረጠምም” ማለቱ አልቀረም። እንዲያውም፣ ከዚህ በታች በምንመለስበት የመንግሥት ግልበጣ ሙከራ እንደምናየው፣ የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም እስካሁን እንዳደረገው በክሽ ክሽ የኩዴታ መከራ ሳይሆን፣ ወይንም ደርግንም አለሁልህ ጠላቶቹንም አለሁላችሁ እያለ ሳይሆን በተፋፋመና በተጠናከረ ዝግጅት ደርግን ለመገልበጥ ወስኗል። ሰሞኑን የኢምፔሪያሊስት ጋዜጦችና የዜና ማሰራጫዎች የኢትዮጵያን አብዮትና ባለንበት ተጨባጭ ሁኔታ ከሰፊው ሕዝብ ጐን የተሰለፈውን ደርግ በማጥላላት የሚያካሄዱት ዘመቻ በቺሊ አሌንዲን ለመገልበጥ የኘሮፖጋንዳ ዝግጅት ሲያደርጉ የነበረውን ሁኔታ ያስታውሰናል።
በመጨረሻም፣ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ትግል በየካቲት/66 ሲቀጣጠል ባንድ ላይ የተነሳው ኃይል ሁሉ ዛሬ አብሮ የለም። የየካቲት እንቅስቃሴ ተጀምሮ የአክሊሉ ካቢኔ በሕዝቡ ትግል ሲወድቅ ከተከፋፈሉት የገዥ መደቦች ውስጥ የእንዳልካቸው ወገን ሳይቀር ደስ ብሎት ነበር። እነመንገሻ ሥዩምም አሁን ሲያወሩ የየካቲት እንቅስቃሴ እንደ ተጀመረ መደሰታቸውን ይገልፃሉ። በዘረፋ ላይ ከተጣሉዋቸው የመደብ አባሎቻቸው ከፊሉን አስወግዶ የሚገታ እንጂ እንደዚህ ገፍቶ መጥቶ ጉድ የሚሰራቸው እንቅስቃሴ አልመሰላቸውም ነበር። ከሰፊው ሕዝብ ጋር በኃይለሥላሴ የአመጽ አገዛዝ ላይ ክንዱን ያስተባበረ የንዑስ ከበርቴው የተወሰነ ክፍልም እንቅስቃሴውን ወደ መጀመሪያው ላይ በሙሉ ድጋፍ፣ ከዚያም በጥርጣሬ ሲከተል ቆይቶ በመደብ ጥቅም መነካት፣ በተስፋ ቆራጥነት ከአብዮቱ እየተራገፈ ቀርቷል። ከአብዮቱ ሰፈር ወጥቶ የአብዮት ጠላቶች ሰፈር ተደባልቋል። “ኢህአፓ” ብሎ እራሱን በሚጠራ የከሃዲ ምሁራን ጥርቃሞ የሚመራው ይህ ክፍል ዛሬ ከቀንደኛ ጠላቶቻችን ባላነሰ ትግል የኢትዮጵያን አብዮት ለመቀልበስ ሽር ጉድ በማለት ላይ ነው። የለየላቸው የሕዝብ ጠላቶች፣ ሰፊው ሕዝብ አንቅሮ የተፋቸው በመሆኑ በምንም ዓይነት ዘዴ ሰፊው ሕዝብ እንዲተባበራቸው ለማድረግ አልቻሉም። ስለዚህ፣ ሰፊው ሕዝብ ተወናብዶ በራሱ አብዮት ላይ እንዲያምጽ፣ ዛሬ በታሪክ አጋጣሚ በጊዚያዊ ድርጊቱ በጐኑ የቆመውን ደርግ የመጀመሪያው ጠላት ተደርጐ እንዲወሰድ ውዥንብር እንዲነዛ፣ በዚህም ድርጉቱ ሁኔታውን ለግልበጣ እንዲያመቻች የትግል ድርሻ የተሰጠው ለዚሁ ከሃዲ የንዑስ ከበርቴ ክፍል ነው።
የሕዝቦች ትግል ረዥምና መራራ የሚሆነው ከለየላቸው ጠላቶቻቸው ጋር መጋጠም ስላለባቸው ብቻ ሳይሆን፣ እነርሱን መስለው ተደባልቀው ትግሉን ከውስጥ ለማዳከም ከሚጥሩ አስመሳይ ተራማጆችም ጋር የሞትና የሽረት ትግል ማድረግ ስላለባቸው ነው። በመደብ ጦርነት፣ ፊት ለፊት ከሚጋጠም ጠላት ይልቅ አብሮ የተሰለፈ መስሎ ከጀርባ የሚወጋ የበለጠ አደገኛ የሚሆንበት ሁኔታ አለ። ዛሬ፣ ትግሉን ስንጀምር ፊት ለፊት ከገጠምነው ጠላት እንድንሸነፍ ከጀርባ የሚወጉንን ‘የውስጥ አርበኞች’ ሳናውቅና ስናጋልጥ አብዮታችን ያለበትን ችግርና ከግቡ የሚደርስበትን መንገድ ልንረዳ በፍፁም አንችልም።
ወታደራዊው ደርግ የቀድሞ ገዥ መደቦችን ሥልጣን አስለቅቆ ጊዚያዊ ወታደራዊ መንግሥት እንዲቋቋም ባገራችን የመደብ አሰላለፍ ለውጥ ተከተለ። የቀድሞው የትግል ስልት መቀየር ያለበት ሁኔታ ተፈጠረ። በኃይለሥላሴ ጊዜ መንግሥቱን ከተቃወመ ጋር ሁሉ መተባበር አብዮታዊ ግዴታ ነበር። በደርግ ዘመን መንግሥቱን ከተቃወመ ጋር ሁሉ መተባበር ግን ከቀድሞ ገዥ መደቦች ጋር መተባበርን ሊያስከትል የሚችል የትግል ስልት ሆነ። ምክንያቱም ደርጉን ለመተካት የሚፈልጉት ሁለት ተፃራሪ ኃይሎች – ሰፊው ሕዝብና ጠላቶቹ – ሆኑ። በተለይ ተከታታይ የደርጉ ተራማጅ እርምጃዎች ከመጡ በኋላ በሕዝብ ጠላቶች በኩል ደርጉን ለመተካት የሚፈልገው ወገን በረከተ። ደርጉን ለመተካት በሚፈልጉ ሁለት ተፃራሪ ወገኖች መሃል የነበረው /ያለው/ የኃይል ሚዛን ለጠላቶቹ ያመዝን ነበር። ደርጉ በፈለገው ምክንያት ፊትም ሆነ ዛሬ ቢወድቅ ሊተኩት የሚችሉ የሕዝብ ጠላቶች ነበሩ /ናቸው። የአብዮቱ ጠላቶች ከየካቲት እንቅስቃሴ ተምረው ስልጣን ያስለቀቃቸውን ድካም ለማስወገድ ከፍተኛ ዝግጅት አድርገዋል። ሰፊው ሕዝብ ግን በየካቲት እንቅስቃሴ ሥልጣን እጁ ለማስገባት ያላስቻለውን ድካም አላስወገደም።
የመንግሥት ሥልጣን ጉዳይ የጉልበት ጥያቄ ነው። የበለጠ የተዘጋጀና የተደራጀ ይወስዳታል እንጂ በአቦ ሰጡኝ ማንም እጅ አትገባም። ሃቀኛ ተራማጆች፣ ባንድ በኩል የሰፊውን ሕዝብ ድካም ተረድተው፣ በሌላ በኩል ሰፊው ሕዝብ ሥልጣን ካልያዘ መሰረታዊ ችግሮቹ ዋስትና ባለው መንገድ እንደማይፈቱ ተገንዝበው፣ ሰፊው ሕዝብ ለመንግሥት ሥልጣን የሚያበቁትንና ሊዘለሉ የማይችሉ ዝግጅቶችን እንዲያሟላ፣ ማለትም እንዲነቃ፣ እንዲደራጅና እንዲታጠቅ ቅስቀሳና ኘሮፖጋንዳቸውን አፋፋሙ። በዲሞክራሲያ ግንባር ቀደምነት የሚመራወ የከሃዲ ንዑስ ከበርቴ ክፍል ግን፣ መጀመሪያ ደርግን እንጣል፣ አስቀድመን ጊዚያዊ “ሕዝባዊ” መንግሥት እንመስርት፣ ንቃቱ፣ ድርጅቱ፣ ትጥቁ፣ ከዚያ በኋላ በየደቂቃው ይሟላል በሚል ፀረ አብዮት ቅስቀሳ ላይ ተሰማራ። እንግዲህ፣ ሰፊውን ሕዝብ ከጠላቶች አስተባብሮ ደርግን ለመጣል የተደረገው የከሃዲ ምሁራን ሙከራ “ጊዚያዊ ‘ሕዝባዊ’ መንግሥት” በሚለው መፈክር አካባቢ ነበር። ባንድ በኩል፣ ንቃቱ፣ ድርጅቱና ትጥቁ ከጊዜያዊ ሕዝባዊ መንግሥት በኋላ ይመጣል የሚለው ቅስቀሳ፣ ሰፊው ሕዝብ ሳይነቃ፣ሳይደራጅና ሳይታጠቅ “እየታገለ” በነቁ፣ በተደራጁና በታጠቁ ጠላቶቹ የሚያስመታው ቅስቀሳ ነው። በሌላ በኩል ደግሞ፣ ሰፊው ሕዝብ እነዚህን ሶስት መሠረታዊ ዝግጅቶች ሳያሟላ የፈለገውን ያህል “ቢታገል” የትግሉን ፍሬ ጠላቶቹ ይሰበስባሉ እንጂ እርሱ ሥልጣን ሊይዝ አይችልም። በዚህም ምክንያት ሰፊው ሕዝብ የመንግሥት ሥልጣን ለመያዝ ላይችል “ዝግጅቱን ትተህ ሥልጣን ለመያዝ ታገል” ማለት “ይበልጥ የተዘጋጁትን ጠላቶችህን ሥልጣን ለማስያዝ ታገል” ማለት እንጂ ሌላ ትርጉም የለውም። ለዚህ ነው “ጊዚያዊ ሕዝባዊ መንግሥት” የሚለው መፈክር ሰፊውን ሕዝብ ከጠላቶቹ ጐን እንዲሰለፍ ለማወናበድ የሚሰነዘር መፈክር ነው የምንለው። የሕዝብ ጠላቶችም ይህንኑ ጠንቅቀው በመረዳታቸው ይህን ቀልባሽ መፈክር አንግበው ተነስተዋል።
ሰፊው ሕዝብ ተወናብዶ ከጠላቶቹ ጐን እንዲሰለፍ ለማድረግ እነዲሞክራሲያ የተጠቀሙበት ሌላኛው ቅስቀሳ ባጠቃላይ በደርጉና በሰፊው ሕዝብ መሃል ያለውን ቅራኔ የሚመለከትና በተለይም ‘ደርጉ ፋሺስት ነው’ የሚለው ነው።
“ኢትዮጵያ ውስጥ ሰፈነ” ስለሚሉት “ፋሺዝም” በሰፊው ሕዝብ ድምጽ ቁጥር 43 ላይ በሰፊው የተቸንበት ስለሆነ ለጊዜው እዚህ ላይ በዝርዝር አንመለስበትም። ሆኖም ጥያቄውን ከሌላ አንፃር ባጭሩ እንመልከተው። በአንድ ጊዜ ሊኖር የሚችለው አንድ ዋና ቅራኔ ብቻ ነው። ይህ አንድ የማርክሲዝም ሕግ ነው። በኢትዮጵያ፣ ደርጉ ሥልጣን ከያዘ ጀምሮ በደርጉና በሰፊው ሕዝብ መሃል ያለው ቅራኔ ዋናው ቅራኔ ከሆነ፣ /ደርጉ ‘ፋሺስት’ ነው ከተባለ ደግሞ በደርጉና በሰፊው ሕዝብ መሃል ያለው ቅራኔ የግድ ዋነኛው መሆን አለበት።/ ሌሎች በኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ውስጥ ያሉት ቅራኔዎች በሙሉ የሁለተኛ ደረጃ ቅራኔዎች ናቸው ማለት ነው። በዚህ ዋና ቅራኔ መፈታት ጥቅም የሚያገኙ ኃይሎች ሁሉ ደግሞ የሁለተኛ ደረጃ ቅራኔዎቻቸውን አቻችለው ይህን ዋና ቅራኔ ለመፍታት በጋራ መታገል አለባቸው። ለምሳሌ፣ በብሄራዊ ዲሞክራሲያዊ አብዮት ጊዜ ዋናው ቅራኔ በፊውዳሊዝምና በኢምፔሪያሊዝም ባንድ በኩልና በሰፊው ሕዝብ በሌላ በኩል መሃል ያለው ቅራኔ ነው። በንዑስ ከበርቴውና በወዛደሩ መሃል ቅራኔ አለ። ነገር ግን በዚህ ዋና ቅራኔ መፈታት ሁለቱም ጥቅም ስለሚያገኙ በመሃላቸው ያለውን ቅራኔ ለጊዜው አቻችለው ዋናውን ቅራኔ ለመፍታት ይታገላሉ። እንግዲህ፣ በደርጉና በሰፊው ሕዝብ መሃል ያለው ቅራኔ ዋነኛው ከሆነ፣ ከደርጉ ጋር ቅራኔ ውስጥ የሚገኙ ኃይሎች ሁሉ መተባበር አለባቸው ማለት ነው። ከደርጉ ጋር በቅራኔ ውስጥ ከሚገኙት ኃይሎች ውስጥ ደግሞ የቀድሞ መሳፍንት እነመንገሻ ሥዩም/ነጋ ተገኝ. . . ይገኙበታል። ስለዚህም፣ ሰፊው ሕዝብ ከነዚህ መሳፍንት ጋር ተባብሮ ደርጉ ላይ መነሳት አለበት ማለት ነው። ከሃዲ ምሁራን ይህን በግልጽ ለመናገር እንደማይደፍሩና ለመካድም እንደሚሞክሩ የታወቀ ነገር ነው። ነገር ግን፣ በደርጉ ላይ ካላቸው አቋም የግድ ሊከተል የሚችለው መደምደሚያ ከላይ ያልነው ነው። አንደኛ፣ በደርጉና በሰፊው ሕዝብ መሃል ያለው ቅራኔ ዋነኛው ከሆነ የግድ በዚህ ቅራኔ መፈታት ጥቅም ያላቸው ሁሉ መተባበር አለባቸው። ሁለተኛም፣ ደርጉ “ፋሺስት” ከሆነ፣ ተደጋግሞ እንደተነገረው ከመሳፍንት ጋር ሳይቀር ተባብሮ ይህን “ዋና ጠላት” መታገል ያስፈልጋል። የቻይና ሕዝቦች ከፊውዳሊስቶች፣ የቪየትናም ሕዝብ ከኢምፔሪያሊስቶች ጋር ሆነው ፋሺስቶችን የታገሉት ፋሽዝም ስለነገሰ የቀድሞው ዋና ቅራኔ ወደ ሁለተኛ ደረጃ ቅራኔነት በመዞሩ ነው። ለምሳሌ፣ በቻይና በፊውዳሊዝምና በሰፊው ሕዝብ መሃል የነበረው ዋና ቅራኔ በፋሺዝም ምክንያት ወደ ሁለተኛ ደረጃ ቅራኔ በመለወጡ ነው። ደርጉ “ፋሺስት ነው” የሚለው የፈጠራ ቲዎሪ የተነሳውም ለዚሁ ግብ ነው። ማለትም፣ ሰፊውን ሕዝብና ደመኛ ጠላቶቹን “በፀረ ፋሺስት ግንባር” ለማስተባበር ነው። ሰፊውን ሕዝብ ከጠላቶቹ ጋር ለማስተባበር የነዙት ውዥንብር ለጊዜው ባይሳካም፣ የ‘ኢህአፓ’ ከሃዲዎች እራሳቸውን “ፀረ ፋሺስት” ብለው ከሚጠሩ ካገር የኰበለሉ ፋሽስቶች ጋር እንደሚተባበሩ በበኩላችን ምንም ጥርጥር የለንም። ዛሬማ ‘የኢህአፓ’ የውጭ ተጠሪ ነኝ የሚለው የፋሺስት ወጣቶች ድርጅት “በኢትዮጵያ ዲሞክራቲክ ሕብረት ውስጥ ያሉ አድሃሪዎች ይውደሙ” የሚል መፈክር አንግቦ ተነስቷል። “የኢትዮጵያ ዲሞክራቲክ ሕብረት” የነመንገሻ ሥዩም /አስፋወሰን ድርጅት መሆኑ እየታወቀ ይህን መፈክር ማንሳቱም እነ አስፋ ወሰን /መንገሻ ሥዩም መሀል “ሰርገው የገቡ” አድሃሪዎችን በማውገዝ “ተራማጆቹ” የዚህ ድርጅት አባሎች የትብብር እጁን መዘርጋቱ ነው። የኢዲህ ሰዎችም ከፀረ ፋሺስት ተራማጆች ጋር እንተባበራለን፣ ከነአስፋወሰን ጋር ግንኙነት የለንም ብለዋል። አድሃሪዎች በ‘ኢህአፓ’ የውጭ ተጠሪ ጥያቄ አማካይነት ከኢዲህ ውስጥ ‘ከተገለሉ፣ ደግሞ፣ የነመንገሻ ሥዩም ዓይነት “ተራማጆች” ና ‘ኢህአፓ’ “ፀረ ፋሺስት ግንባራቸውን” ለማቋቋም የሚያግዳቸው ነገር አይኖርም ማለት ነው።
ደርጉን “ፋሺስት” ነው በማለት እነ መንገሻ ሥዩምን ደጅ ለመጥናት ከተነደፈው ስያሜ ሌላ፣ የ‘ኢህአፓ’ አድሃሪዎች ሕዝቡና ጠላቶቹ እንዲተባበሩ የተጠቀሙበት ሌላ ዘዴ፣ ደርጉ በወሰዳቸው አድሃሪ እርምጃዎች ላይ በተናጠል ማተኰር ነው። ደርግ ሥልጣን ከያዘ ጀምሮ የነበረው አረማመድ ቅራኔ የተሞላው ነበር። ቅራኔያዊ በመሆኑም የደርጉን ሚና ለመረዳት ከአንድ አንፃር ብቻ ማየት አይቻልም። ለምሳሌ፣ የኢትዮጵያን አርሶአደር መሰረታዊ ጥያቄ የሆነውን መሬትን የሕዝብ ያደረገ አዋጁ አለ። በሌላም በኩል የአርሶአደሩን ትግል ያደናቀፈ የወላዋይነትና አድሃሪ እርምጃዎቹ አሉ። በተራማጅ አዋጁ ላይ ብቻ አተኩሮ እነዚህን ወላዋይና አድሃሪ እርምጃዎች መርሳት አድርባይነትና አርሶ አደሩ እነዚህን አድሃሪ እርምጃዎች ለመቋቋም ማድረግ ካለበት ትግል ማዘናጋት ነው። ተራማጅ አዋጁን ችላ ብሎ በወላዋይና በአድሃሪ እርምጃዎቹ ላይ ብቻ ማተኰር ደግሞ በነዚህ ወላዋይና አድሃሪ እርምጃዎች አሳቦ ተራማጅ አርምጃዎቹን መቃወም ነው። የዲሞክራሲያ ከሃዲዎች ባለፉት ሁለት ዓመታት ያካሄዱት ትግል እንደዚሁ በደርጉ የወላዋይነትና አድሃሪ እርምጃዎች እያሳበቡ የደርጉን ተራማጅ እርምጃዎች በመቃወም ላይ ያተኰረ ነበር። ይህም፣ በደርጉና በሕዝቡ መሃል ባለው ቅራኔ ላይ ብቻ በማተኰር በደርግና በሕዝብ ጠላቶች መሃል ያለውን ቅራኔ አዘናግቶ ሰፊው ሕዝብ ከፀረ ደርግ ጠላቶቹ ጋር እንዲዳበል ለማድረግ ነበር።
ከላይ የጠቀስነው የትግል ዘዴ ሌላ ዘርፍ፣ በቢሮክራሲውና በአንዳንድ የደርግ አድሃሪ አባሎች የሚወሰዱ አድሃሪ ድርጊቶችን በማእከላዊው ደርግ የተወሰዱ በማስመሰል የሚያደርጉት ቅስቀሳ ነው። እርግጥ ደርጉ ቢሮክራሲው ሆነ አድሃሪ አባሎቹ በሚወስዱት አድሃሪ እርምጃ ላይ ተገቢና ቆራጥ እርምጃ በማይወሰድበት ወቅት ለድርጊቱ ተጠያቂ ነው። ቢሮክራሲው የሚፈጽማቸው ሁሉ የደርግ እርምጃዎች ተብለው ከተወሰዱ ደግሞ በደርጉና በቢሮክራሲው መሃል ቅራኔ እንዳለ መካድ ነው። በደርግና በቢሮክራሲው መሃል ያለውን ቅራኔ መካድ፣ ደርጉ በቢሮክራሲው ላይ እርምጃ ለመውሰድ ያለውን ቸልተኝነት መታገል አይደለም። ቢሮክራሲው በሚያካሄደው ፀረ ደርግና ፀረ አብዮት ሴራ ተባባሪነትን የሚያስከትል ነው። ቢሮክራሲው የሚፈልገውም የኢትዮጵያ ሰፊ ሕዝብ ልክ እዚህ ወጥመድ ውስጥ እንዲገባለት ነው። በቢሮክራሲው አሻጥር የሚፈፀሙ ድርጊቶች ሁሉ የደርጉ እንዲመስሉ፣ ከደርጉ “አስተዳደር አለመቻል” የመጡ እንዲመስሉ ነው። ሰፊው ሕዝብ የትግሉ እንቅፋት ቢሮክራሲው መሆኑን ተረድቶ እንዳይታገለው፣ ዓይኑን ከቢሮክራሲው ወደ ደርጉ እንዲያዞርለት እርሱም ፋታ አግኝቶ የሚተበትበውን ፀረ ደርግና ፀረ አብዮት ሴራ ይበልጥ እንዲያፋፍም ነው። “ተፈሪ ማረኝ የደርጉስ ነገር ምንም አላማረኝ” እንዲባልለት ነው። ደርጉን ለመተካት በኢምፔሪያሊስቶች ሆነ በፊውዳሎች የታጨው የቢሮ ከበርቴው ስለሆነ፣ በደርጉና በቢሮክራሲው መሃል ያለውን ቅራኔ ሳይረዳ ሰፊው ሕዝብ ቢሮ ከበርቴውን ትቶ ደርጉ ላይ ሲነሳ፣ ጠላቶቹ ደርጉን ለመጣል የሚያደርጉትን ትግል አገዘላቸው ማለት ነው። እነ ‘ኢህአፓ’ም፣ የቢሮክራሲውን አሻጥሮችና አድሃሪ እርምጃዎች በደርጉ የተወሰዱ አስመስለው ሲያቀርቡ ይህንኑ ግብ ለመምታት ነው።
እንግዲህ፣ የኢትዮጵያ ሰፊ ሕዝብ ጠላቶች “ተራማጅ ኮከብ” የሆነው ‘ኢህአፓ’ ባለፉት ሁለት ዓመታት ከላይ ባጭሩ ለማስቀመጥ እንደሞከር ነው ሕዝቡን መስሎ በሰፊው ሕዝብ ትግል ውስጥ በመግባት ባንድ በኩል የሕዝቡን ትግል ከውስጥ ሆኖ ለማዳከም፣ በሌላ በኩል የሕዝቡ ትግል ከጠላቶቹ ጋር የሚያሰልፈው አቅጣጫ እንዲይዝ ከፍተኛ ትግሎች አካሄዷል። በዚህም ፀረ አብዮት ትግሉ ለኢትዮጵያ ጭቁን ሕዝብ ጠላቶች ከፍተኛ አገልግሎት አበርክቷል። ሌላ ሌላውን የተከፈለውን ወሮታ በርግጥ ባናውቅ እንኳ በፊውዳሎች በነ መንገሻ ሥዩም “እውነተኛ የኢትዮጵያ ልጆች” እንደአፍሪካ እዚ ባሉ የሲአይኤ ጋዜጦች “የኢትዮጵያን ከወደቀችበት የፋሺስት ሥርዓት ለማውጣት የሚታገል ግንባር ቀደም ድርጅት”. እየተባለ ይሞካሻል።
‘ኢህአፓ’ በሕዝብ ጠላቶች ዘንድ ተወዳጅነት እያተረፈ ይሂድ እንጂ፣ በአንፃሩ ደግሞ እንኳን ድሮውንም አጠገባቸው ባላደረሱት ጭቁኖች ዘንድ፣ ወዳጅ መስሎ ያወናበዳቸው ሃቀኛ ዜጐች ሳይቀሩ እየነቁበትና እያጋለጡት መጥተዋል። የኢትዮጵያን ጭቁኖች ከጠላቶቻቸው ጋር ለማስተባበር ያደረገው ትግል እስካሁን የአብየታዊውን ትግል ከከፍተኛ ደረጃ መድረስ ካደናቀፉት ምክንያቶች አንዱ ቢሆንም፣ ከእንግዲህ በሰፊው ሕዝብ መሃል ‘በውስጥ አርበኝነት’ ለአብዮት ጠላቶች የሚያገለግል ድርጅት መሆኑ እየታወቀበት መጥቷል።
‘ኢህአፓ’ን ያከሰሩት፣ በፀረ ሕዝብነቱ እርቃነ ስጋውን ያስቀሩት ምክንያቶች ሃቀኛ ተራማጆች ከዚህ ቡድን ጋር ያካሄዱት ጽኑ የርእዩተ ዓለምና የፖለቲካ ትግል ብቻ አይደሉም። ባንድ ፊት የኢትዮጵያ ሕዝቦች ትግል መስመር እየያዘና የመደብ አሰላለፉም እየጠራ መምጣት፣ በሌላ በኩል ደግሞ የደርጉ የራሱ ወገን መለየትና ከሞላ ጐደል ሳይንሳዊ ፈለግ የተከተለ የፓለቲካ መስመር መያዝ ነው።
በተለይ ከጥቂት ወራት ወዲህ ለአብዮቱና ለሃቀኛ ተራማጆች ምቹ እየሆነ የሚሄድ አካባቢ እየተፈጠረ ነው። በተከታታይ፣ በደርጉና በሕዝብ መሃል ያለውን ጥራኔ የሚያለዝቡ፣ በደርጉና በሕዝብ ጠላቶች መሃል ያለውን ቅራኔ የሚያከሩ እርምጃዎች ተወስደዋል። የመለስተኛ ኘሮግራሙ መታወጅ፣ የዲሞክራሲ ጮራ መፈንጠቅ፣ የኤርትራን ችግር በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የፖሊሲው ውሳኔ መውጣት. . . እነዚህና የመሳሰሉት ከላይ ያልነውን ሀቅ የሚያረጋግጡ ናቸው። ለዚህም ነው ሃቀኛ ተራማጆች፣ አንዳንድ የደርጉን አድሃሪ እርምጃዎችና ወላዋይነት ከማጋለጥ ሳይቆጠቡ፣ እነዚህን ተራማጅ እርምጃዎች በመደገፍ ሊጠቀሙባቸው የሚታገሉት። ሰፊው ሕዝብም እነዚህን ተራማጅ እርምጃዎች በልዩ ልዩ መንገዶች ደግፏል፣ እየተጠቀመባቸውም ነው። የነዚህ እርምጃዎች ተቃዎሚ ሆነው የቀረቡት የለየላቸው የሕዝብ ጠላቶች ብቻ ናቸው። የዲሞክራሲያ ከሃዲ ቡድንም ከሕዝብ ጠላቶች ጋር እነዚህን ተራማጅ እርምጃዎች ተቃውሟል፣ ከአድሃሪዎች ጋር ተዳብሎም እንዲቀለበሱ እየታገለ ነው።
ለምሳሌ፣ ከላይ እንዳልነው፣ ለሃቀኛ ተራማጆችና ለአብዮቱ ይበልጥ ምቹ ሁኔታ እየተፈጠረ ነው። ለከሃዲዎቹ ግን “ከመለስተኛ ኘሮግራሙ /እነርሱ ከጥሪው ወዲህ ነው የሚሉት/ ወዲህ ያለው ፋሺዝም ይውደም” ያሰኛቸው ሁኔታ መጥቶባቸዋል። የኢትዮጵያ ጭቁኖች በጠላቶቻቸው ላይ ለከፈቱት ጦርነት የበለጠ እንዲዘጋጁ የሚያመቿቸው እርምጃዎች በተወሰዱ ቁጥር፣ የደርጉን ከሞላ ጐደል ባሁኑ ወቅት ከሰፊው ሕዝብ ጐን መሰለፍ የሚያሳዩ እርምጃዎች በተወሰዱ ቁጥር በዲሞክራሲያ ግንባር ቀደምነት ለሚመራው የከሃዲ ንዑስ ከበርቴዎች ጥርቃሞ “ፋሺዝም” የመፋፋሙ ምልክት ነው ማለት ነው። ከመለስተኛ ኘሮግራሙ መውጣት ወዲህ ስለተፈጸሙ “ፋሺስታዊ” ድርጊቶች አንዱን ሲጠቅስ ዲሞክራሲያ በኪነት ሠራተኞች ላይ ያደረሰውን ያመለክትልናል።
መለስተኛ ኘሮግራሙ በቀረበ ማግስት መሆኑ የአጋጣሚ ነው? ተብሎ ቢያስጠይቅም፣ የኪነት ሠራተኞች ተገቢ ጥያቄ ይዘው ሰላማዊ ሰልፍ ማድረጋቸው ይታወሳል። ሰፊውን ሕዝብ ተታኰ የራሱን ቀልባሽ ጥያቄዎች ማስተጋባት ዋና ሥራው የሆነው ‘ኢህአፓ’ ጥቂት የተወናበዱና ከሃዲ ወጣቶችና ቦዘኔዎች ተጠቅሞ ሰልፉ ውስጥ ማደባለቁም አይዘነጋም። በዚህም፣ የኪነት ሠራተኞችን ሰልፍ ለራሱ ቀልባሽ ዓላማ ለማዋል ባደረገው ሙከራ በነርሱ ላይ ለተወሰደው እርምጃ የበኩሉን አስተልጽኦ አድርጓል። የትግል ዘዴውም ሠራተኛውን አስገድሎ “ይኸውላችሁ ፋሺዝም” ለማለት ስለሆነ፣ በመጠኑ ተሳካለት። ሰላማዊ ሰልፉ ላይ ከወታደሩ በተተኰሰ ጥይት ሰርጎ ገቡ ‘ኢህአፓ’ ከሃዲ ሠራዊት ሳይሆን አንድ ንፁህ ሠራተኛ ወደቀ። የ‘ኢህአፓ’ ዓላማ ለሠራተኛው ለመሞት ሳይሆን አስገድሎ ለመሸሽ፣ በዚህም የ“ፋሺዝምን” መኖር ለማሳየት ስለሆነ የሞተው ንፁህ ሠራተኛ እንጂ የ‘ኢህአፓ’ ደጋፊ አለመሆኑ የሚያስገርም አይደለም። ለማንኛውም ተገቢ ጥያቄ ባቀረቡ ሰላማዊ ሰልፈኞች ላይ ጥይት መተኰስን ማንኛውም ተራማጅ ያወግዘዋል፣ እጃቸው ያለበት ሁሉ በሕግ ሊጠየቁበት ይገባል። ‘ኢህአፓ’ ግን አንድ ሰው ብቻ በመገደሉ የከነከነው ይመስላል። የፈለገው የሻርቪልን አይነት ጭፍጨፋ ነበር። በጋዜጣውም በሃቁ የነበረውን ሳይሆን በምኞቱ የነበረውን ሲገልጽ “የሻርኘቪል ዓይነት ግድያ” ይለዋል። የሻርኘቪል ጭፍጨፋ፣ መቶ ግድም የአዛንያ አፍሪካውያን በፋሽስቱ መንግሥት ወታደር የተገደሉበት ጭፍጨፋ ነበር። ታዲያ በኪነት ሠራተኞች ላይ የተወሰደው እርምጃ በፈለገው ማይክሮስኰኘ ጐልቶ ቢቀርብ ሻርኘቪልን ሊሆን አይችልም። ‘ኢህአፓ’ የፈለገው የቫርኘቪሉን ዓይነት ጭፍጨፋ እንደነበረ ነው የሚገልጸው። ለወደፊቱም፣ የ‘ኢህአፓ’ ደጋፊዎች እየተነኰሱ ሠርቶአደሩን ማጋፈጥ ዓይነተኛ የትግል ዘዴያቸው ይሆናል። የኢትዮጵያ ወዛደሮችና ሠርቶ አደሮች ሁሉ በሰርጐ ገቦች ተገፋፍተው ባልተዘጋጁበት ትግል እየተጋፈጡ የአናርኪስቶች መጠቀሚያ እንዳይሆኑ ነቅቶ መጠበቅ ኃላፊነታቸው ነው።
ሌላ ምሳሌ ለመጨመር ያህል፣ ደርጉ ስለኤርትራ ጉዳይ ያሳለፈውን የግንቦት 8 የፖሊሲ ውሳኔ እንመልከት። የዚህን ውሳኔ መውጣት፣ ለኤርትራ ችግር ዛሬውኑ መፍትሄ በማስገኘቱ ሳይሆን፣ የኤርትራን ችግር ለመፍታት ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር በመሆኑ፣ ማንኛውም ሃቀኛ ተራማጅ እንደሚደግፈው በዚሁ ጉዳይ ላይ ባወጣነው የሰፊው ሕዝብ ድምፅ ልዩ እትም ላይ ገልፀናል። ውሳኔው ለኤርትራ ችግር መፈታት ጥርጊያ መንገድ የሚከፍት በመሆኑም የኤርትራና የኢትዮጵያ ጭቁኖች ድጋፋቸውን ገልጸዋል። ከኢትዮጵያ አብዮት ጠላቶችና ከኤርትራ አድሃሪዎች ጐን በመሰለፍ የ ‘ኢህአፓ’ ከሃዲዎች ይህን ውሳኔ ተቃውመው “ተራ ማጭበርበሪያ”፣ “አንካሳ መፍትሄ”፣ “ቅንነት የለሽ መፍትሄ” ይሉታል። /ዲሞክራሲያ፣ ቅጽ 3 ቁጥር 5፣ ገጽ 4 /የኤርትራ ችግር በሰላማዊ መንገድ መፈታት የኢትዮጵያንና የኤርትራን ጭቁኖች አንድነት መፍጠርና በሕብረት በደመኛ ጠላቶቻቸው ላይ መዝመትን ያስከትላል። የደርጉ የፖሊሲ ውሳኔ ለዚሁ ግብ ትልቅ ጥርጊያ መንገድ የሚከፍት ነው። የኢትዮጵያ አብዮት ጠላቶችና የኤርትራ አድሃሪዎች የሚፈልጉት ደግሞ ጦርነቱ እንዲቀጥል፣ የጭቁኖች አንድነት እንዳይፈጠርና በነርሱ ላይ እንዳይዞር ነው። የበኩር ልጃቸው ‘ኢህአፓ’ በዚህ ጥያቄ የፖሊሲ ውሳኔውን ተቃውሞ ከነርሱ ጐን በግልጽ ቆሟል።
ያም ሆነ ይህ፣ ‘ኢህአፓ’ ሰፊውን ሕዝብ ከጠላቶቹ ጐን ለማሳለፍ ያደረጋቸው ሙከራ እየከሸፈ መጥቷል። ከንግዲህ የሕዝብ ወገን መስላ ማወናበዷ አክትሟል። ትግሉ እየከረረና እየጠራ ሲመጣ፣ ኢህአፓ በሕዝብ ፊት ለሚደርስባት መጋለጥ በአብዮት ጠላቶች ታዝላ እሽሩሩ ስትባል፣ አንዳንዴም ከእቅፍ ወርዳ ለፋሺስታዊ ቅልበሳ በገቢር የሚጠቅሙ ቅስቀሳዎች ስታካሄድ ነው የምታጋጥመን።
እንግዲህ፣ የኢትዮጵያ አብዮት የጠላቶች በራሳቸው የትጥቅ ትግል እየከሰሩ ሲመጡ፣ ሕዝቡን ለማወናበድ ያካሄዱት ፕሮፖጋንዳ ዋጋ ቢስ እየሆነ ሲሄድ፣ ሕዝቡ ውስጥ አስርገው ያስገቡት ‘የውስጥ አርበኞች’ እየተነቃበት ሲሄድ፣ ስልጣን ላይ ለመመለስ ያላቸው አማራጭ በፋሽስታዊ የመፈንቅለ መንግሥት አማካኝነት ይሆናል። ባለፈው የከሸፈው ፋሺስታዊ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ የሚያርቀው ይህንኑ ነው። ሙከራው በአሁኑ ጊዜ የተደረገው፣ በአንድ በኩል የኢትዮጵያ ሕዝቦች ትግል አይሎ ጠላቶቹም ከመቼውም ይበልጥ ያስደነገጠበት ደረጃ መደረሱ፣ በሌላ በኩል ደግሞ የፊቱ ማወናጃ ፕሮፖጋንዳ ሁሉ ተቀባይነት ማጣቱና ጠላቶቻችን ስልጣን ላይ ለመመለስ የሞትና የሽረት ትግል ማካሄድ ያለባቸው ዛሬ መሆኑ ግልጽ ስለሆነ ነው።
በሻለቃ ሲሳይና በጀኔራል ጌታቸው መሪነት የተሞከረው የፋሽታዊ የመንግሥት ግልበጣ፣ በጥቂቶች የተወጠነ ተራ የኩዴታ ሙከራ አልነበረም። ከኢትዮጵያ የቀድሞ መሳፍንትና ከበርቴዎች፣ እንዲሁም ከሌሎች ጋር ሁሉም በመተባበር የተዘጋጀ ውጥን ነበር። ሙከራው የከሸፈው በአጋጣሚ እንጂ በሞካሪዎቹ በኩል የተደረገው ዝግጅት ቀላል ሆኖ አልነበረም። ወታደሩን ለመከፋፈል ከፍተኛ ሴራዎች ተካሄደዋል። ሁኔታውን ለኩዴታ ለማመቻቸት ትላልቅ የኢኮኖሚ ኣሸጥሮች እንዲፋፋሙ ተደርገዋል። የሚገዙ ኃይሎችን ለመግዛት ብዙ ሚሊዮን ዶላር ተመድቧል። በሞምባሳ ወደብ እና በቀይ ባህር አካባቢ በዛን ሰሞን አውሮፕላን ተሸካሚ የጦር መርከቦች የተሰማሩት አሳ ለማጥመድ አልነበረም። በፕሮፖጋንዳ ደረጃም፣ ስለደርጉ ‘የምርጥ መኮንኖች መንግሥት መሆን’፣ የኢትዮጵያ ጭቁን ወታደሮች ተባብረው ይህን ‘የምርጥ መኮንኖች መንግሥት’ መጣል እንዳለባቸው፣ በጠቅላላው አላማቸው ‘ኢትዮጵያን ከውድቀት ለማዳን’ ባለመሆኑ፣ ወረቀት በመበተንና በማስወራት ትልቅ ፖለቲካዊ ዝግጅት አድርገዋል። በገቢር ለፋሽስታዊ የመንግሥት ግልበጣዎች ሁኔታውን ለማመቻቸት የሚታገለው ‘ኢህአፓ’ም የበኩሉን ሰርቷል። በአንድ በኩል ወዛደሩ ሠራተኛው በተናጠል የሥራ ማቆም እርምጃዎች እንዲወስድ፣ አርሶ አደሩ እንዳያርስ፣ ያመረተውን እንዳይሸጥ ለማድረግ ጥረቱን አፋፍሞ ነበር። በሌላ በኩል፣ የደርጉ መለስተኛ ፕሮግራም የጠቀሰው የኢትዮጵያ ሕዝቦች ራሳቸው ተደራጅተው በወዛደሩ ፓርቲ መሪነት የሚያቋቁሙትን አብዮታዊ ግንባር ሆኖ ሳለ፣ ይህንን ያልተረዳ በመምሰል፣ እነዚህ ፋሽስታዊ የመንግሥት ግልበጣ ጠንሳሾች ሊጠቀሙበት ላቃዱት ‘ግንባር’ ቅስቀሳ ሲያካሄዱ ነበር።
ባጭሩ፣ የነሲሳይ የመንግሥት ግልበጣ ሙከራ የኢትዮጵያ አብዮት ጠላቶች በሙሉ በቀጥታና በተዘዋዋሪ መንገድ የተካፈሉበት፣ ከፍተኛ ዝግጅት የተደረገበት ሙከራ ነው። እንድገመውና፣ የከሸፈው በአጋጣሚ እንጂ በዝግጅቱ አነስተኝነት አልነበረም። የእነ ሲሳይ ሙከራ መክሸፍ ግን በአገራችን ፋሺታዊ የመንግሥት ግልበጣ ሙከራዎች ከእንግዲህ አይኖርም ማለትን አያበስርም። የመንግሥት ግልበጣ ሙከራ ከእንግዲህ ከነጭራሹ ሊጠፉ ይቅርና ይህኛው የነሲሳይ ሙከራ እንኳን ከላይ ተቀጨ እንጂ እስከታች ድረስ ሙሉ በሙሉ አልተመታም። ለብዙ ዓመታትና በብዙ አገሮች የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራዎችን የመራው ሲአይኤ በአንድ ሙከራ መክሸፍ ተስፋ የሚቆርጥ አይደለም። በአንድ ጊዜ እንኳን የሚዘጋጀው በርከት ያሉ አማራጭ ሴራዎችን ነው። አንዱ ሲከሽፍ ሌላውን ለመሞከር። ስለዚህ፣ ፋሺስታዊ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራዎች አደጋ ዛሬም አልተወገደም። ወደፊት ሊመጡ የሚችሉት የግልበጣ ሙከራዎች እንደነ ሲሳይ ሙከራ ሁሉ ይከሽፋሉ ወይንም ሥራ ላይ ሳይውሉ ይነቃባቸዋል ማለት ደግሞ እጅን አስሮ እራስን ለጠላት ማስረከብ ነው። ከነሲሳይ ቀጥሎ ሊመጣ የሚችለው የቅልበሳ ሙከራ ከዚህኛው የበለጠ ዝግጅትና ጥንቃቄ እንደሚኖረው ሳይታለም የተፈታ ነው። በአንጻሩም፣ በጭቁኖች ወገንም የቅልበሳ ሙከራዎችን ለማክሸፍና አብዮቱ ከግብ ለማድረስ ከመቼውም የበለጠ ዝግጅት መደረግ ይኖርበታል።
በአሁኑ የኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ የተደረገ ወይንም የሚደረጉ የቅልበሳ ሙከራዎች ሁሉ የቅርብ ጊዜ አላማቸው ደርግን ለመጣል ቢሆንም መሰረታዊ ግባቸው የኢትዮጵያን ሕዝቦች ትግል በአጭሩ ለማስቀረት ነው። የቅልበሳ ሴራዎቹ ፀረደርግ ብቻ ሳይሆን ፀረ አብዮት ጭምር ናቸው። አብዮቱን ከቅልበሳ መጠበቅ የደርግ ተግባር ብቻ ስላልሆነ፣ ወታደራዊዉ ደርግ እነዚህን የቅልበሳ ሙከራዎች ለማክሸፍ ሰፊው ሕዝብ ተሳታፊነት እንዲኖረው ተጨባጭ እርምጃዎችን መውሰድ አለበት። ባለፈው የመንግሥት ግልበጣ ሙከራ ተካፋይ ሆነው ያመለጡ ግለሰቦችን እንዲከታተል ሰፊው ሕዝብ መጋበዙ ለዚህ ተሳታፊነቱ በቂ አይደለም። ደርጉ፣ እንኳን ሕዝቡ የቅልበሳ ሙከራዎችን ለመመከት በሚያደርገው ትግል የሚሳተፍበትን እርምጃ ሊወስድ፣ ስላለፈው ፋሽስታዊ የመንግስት ግልበጣ ሙከራ ለሰፊው ሕዝብ በቂ ገለጣ አላደረገም። ሌላው ቀርቶ፣ የሲአይኤ እጅ እንደነበረበት በተዘዋዋሪ መንገድ እንኳን አልተገለጠም። ለጥቂት ስለከሸፈው ሴራ በቂ ገለፃ ስላልተደረገለት፣ ሰፊው ሕዝብ አብዮቱን ለመቀልበስ የታቀደውን የእነሲሳይ ሙከራ የወሰደው በቀላል ግምት ነው። በራሱ አብዮት ላይ የተጠነሰሰውን ከባድ ፀረ ሕዝብ ሴራ በቀላሉ መገመቱ ደሞ ሌሎች ሴራዎችን ለመመከት ማድረግ ካለበት ከፍተኛ ዝግጅት የሚያዘናጋው ነው።
ወታደራዊው ደርግ፣ የቅልበሳ ሙከራዎችን ማክሸፍን የራሱ ተግባር ብቻ አድርጎ እስከወሰደ ድረስ፣ የሴራውን ምንነት በራሱ በጸጥታ ክፍሉ መሐል ብቻ እስካስቀረ ድረስ፣ እንኳን የቅልበሳ አደጋን ሊደመስስ፣ የቅልበሳ ሙከራዎችን በበለጠ ይጋብዛል። ሰፊው ሕዝብ ቅልበሳ ሙከራዎችን ለማክሸፍ በሚያደርገው ትግል ሙሉ በሙሉ እስካልተሳተፈ ድረስ፣ ወታደራዊው ደርግ ከሰፊው ሕዝብ ተገንጥሎ “እኔው እቋቋመዋለሁ” እስካለ ድረስ፣ ቀልባሾች አንድ ሙከራቸው ቢከሽፍ ከተከታታይ ሙከራዎቻቸው በአንደኛው እንደሚያሸንፉ ያውቃሉ። የፀጥታ ድርጅቶች ክትትል የአጋጣሚ እንጂ ዋስትና ያለው የፀረአብዮት ሴረኞች መደምሰሻ አይደለም። ዋስትና ያለው የቀልባሾችን ሴራ መደምሰሻ የሰፊው ሕዝብ የነቃ፣ የተደራጀና የታጠቀ ኃይል ብቻ ነው።
ስለዚህም፣ በአገራችን አብዮት ቀልበሳን ለመቋቋምና በመጨረሻም ላለማስቻል የሰፊ ሕዝብ መንቃት፣ መደራጀት እና መታጠብ እጅግ አጣዳፊ ጉዳይ ነው።
በማንቃቱ ተግባር፣ ሳይንሳዊ ሶሻሊዝምን ማስተማሩ ብቻ በፍጹም በቂ አይደለም። የኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ በሚገባ መታወቅ አለበት። በዚህ ተጨባጭ ሁኔታ የመደቦች አሰላለፍ በሚገባ መታወቅና ሕዝቡ ወዳጅና ጠላቱን ጠንቅቆ እንዲረዳ ማድረግ ይገባል። የኢትዮጵያ አብዮት የውስጥና የውጭ ጠላቶች የሚተበትቡትን ሴራ በተጨባጭ መንገድ በሚገባ ማብራራትና ሰፊው ሕዝብ የሚዘጋጅበትን ፀረአብዮት አመፅ ጠንቅቆ በማወቅ አፀፋውን ለመመለስ እንዲዘጋጅ ማገዝ እጅግ አስፈላጊ ተግባር ነው። የነሲሳይን የቅልበሳ ሙከራ በተመረኮዘ [የሚደረገው] ቅስቀሳ ፀረአብዮት ኃይሎች ለፋሽታዊ የመንግሥት ግልበጣ ትልቅ ዝግጅት በማድረግ ላይ መሆናቸው በሰፊው መገለጽ አለበት።
በሌላ አንፃር፣ ኢትዮጵያ ጭቁን ወታደሮችና ተራማጅ መኮንኖች ከጭቁኖች ጎን ተሰልፈው ለጀመሩት እንቅስቃሴ እስካሁን ታማኝ ሆነው ቆይተዋል። በነሲሳይ የመከፋፈል ሙከራ ያለመፈታታቸው ብቻ ሳይሆን የነሲሳይን ግብረአበሮች በመደምሰስ የወሰዱት ቁርጠኛ እርምጃ ለዚህ ምስክር ነው። የሆነ ሆኖ፣ እነሲሳይ እንዳደረጉት ሁሉ፣ የሚቀጥሉት የቀልበሳ ሙከራዎች የሚያተኩሩት ወታደሩን በመከፋፈል ላይ ነው። ስለዚህ፣ አድሃሪዎች ወታደሩን ለመከፋፈል የሚያደርጉት ሙከራ እንዲከሽፍ፣ በማንኛውም ሁኔታ ጭቆን ወታደሮችና ተራማጅ መኮንኖች ከጭቁኖች ጎን በመሰለፍ ፀንተው እንዲቆዩ የአድሃሪዎችን ሴራ ለእነርሱም ማሳወቅና የፖለቲካ ንቃታቸውን ከፍ ማድረግ ከጊዜው አጣዳፊ ተግባሮች አንዱ ነው።
ድርጅታዊ ዝግጅትን በሚመለከተ በኩል፣ አሁንም የወዛደሩ ፓርቲ መፈጠር የኢትዮጵያ አብዮት አንገብጋቢ ጥያቄ ነው። ሰርጎ ገቦችንና በወዛደሩ የሞያ ማህበር አመራር ላይ የተሰገሰጉትን ቀልባሽ አናርኪስቶች በማጋለጥ የተደረገው ትግል ብዙ ድሎችን በማቀዳጀቱ በወዛደሩ እንቅስቃሴ ውስጥ ሳይንሳዊ ሶሻሊዝምን ለማስፋፋት፣ ከነቁ ወዛደሮች ጋ የትግል ሕብረት ለመፍጠር እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ያልነበረ ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል። በሌላ አነጋገር የወዛደሩን ፓርቲ ለመፍጠር ለሚደረገው ትግል የቀና መሰረት ተጥሏል። እንግዲህ የወዛደሩን ፓርቲ መመስረትን እንዳላማቸው አድርገው የወሰዱ ሀቀኛ ማርክሲስቶች ከመቼውም ጊዜ የበለጠ አንድነታቸውን ገንብተውና ኃይላቸውን አስተባብረው መታገል አለባቸው። የኢትዮጵያ አብዮት የሩቅ ጊዜ ግብ ሆነ የቅርብ ጊዜ እድል የተያዘው ከወዛደሩ ፓርቲ መፈጠር ጋር ነው። ስለዚህም፣ የወዛደሩ ፓርቲ መፈጠርና አለመፈጠር ወሳኝ ጉዳይ መሆኑን በመረዳት የኢትዮጵያ ሀቀኛ ተራማጆች በዚህ ጉዳይ ያለባቸውን ከባድ ኃላፊነት ተረድተው ፓርቲ መፈጠር ሌት ተቀን መታገል አለባቸው።
የአርሶአደሩ ማህበራት፣ የዛሬውን አብዮት ትግል ለማራመድ ከፍተኛ ሚና ይጫወታሉ። በአንድ በኩል የተራማጅ ዘማቾች መመለስ፣ በሌላ በኩል የአድሃሪ ቢሮክራቶች ተጽዕኖ እነዚህን ማህበራት እንዳያዳክም፣ የአርሶአደሩን ትግል ለማገዝ የተሰለፉ ተራማጅ የመሬት ይዞታ ሠራተኞችና አስተዳዳሪዎች ከመቼውም የበለጠ ከአርሶአደሩ ጎን መቆም አለባቸው። ደርጉም ቀን በቀን ከአርሶአደሩ ጋር የሚፋጠጡ አድሃሪ አስተዳዳሪዎችንና ቢሮክራቶችን በማንሳት በተራማጅ አስተዳዳሪዎች መተካት አለበት። የገበሬ ማህበራት መጠናከር ቀርቶ መዳከም፣ በየቦታው የተፋፋመው የመሬት ከበርቴዎችን ፀረአብዮታዊ አመፅ የበለጠ የሚያበረታታ መሆኑ ግልጽ ነው። በዚያው መጠን ደግሞ፣ በመንግሥቱ የመገናኛ ዘዴዎች ጭምር እየተጠቀሙ በልዩ ልዩ ብሄረሰቦች ቋንቋ ቅስቀሳ በማድረግ ያርሶአደሩን ንቃት ማሳደግ የተራማጅ ሁሉ ግዴታ ነው።
የትጥቁን ጥያቄ በሚመለከት በኩል፣ የቅልበሳ ሙከራዎችና ባጠቃላይ የፀረ አብዮት ኃይሎች ትግል መፋፋም የሰፊውን ሕዝብ መታጠቅ ጉዳይ እጅግ አጣዳፊ አድርጎታል። ከላይ እንዳልነው ሁሉ፣ ደርግ የቀልበሳና የመንግሥት ግልበጣ ሙከራዎችን ለማክሸፍ “እኔ እበቃለሁ” እስካለ ድረስ በገቢር የቅልበሳና የግልበጣ ሙከራዎችን መጋበዙ ነው። እንዲሁም፣ ያልታጠቀን ሕዝብ በታጠቀ ኃይላቸው ማሸነፍ እንደማያቅታቸው ጠንቅቀው ያውቃሉ። ስለዚህ በሰበብ ባስባቡ የሰፊው ሕዝብ መታጠቅ እስከ ዘገየ ድረስ የቅልበሳና የመንግሥት ግልበጣ ሙከራዎች በሙሉ ድፍረት ይዘጋጃሉ። ይህም በተዘዋዋሪ መንገድ የቅልበሳና የግልበጣ ሙከራን መጋበዝ ነው። አሊንዴ፣ ሰፊው ሕዝብ ለማስታጠቅ በመወላሉ የከፈለው ቅጣት ለደርግና ለኢትዮጵያ ጭቁኖች ትምህርት ሊሆን ይገባል።
ለማጠቃለል ያህል፣ የኢትዮጵያ ጭቁኖች ትግል ማየል የጠላቶቻችንን የቅልበሳ ዝግጅት አፋፍሞታል። በነሲሳይ የተሞከረው የመንግሥት ግልበጣና የአብዮት ቅልበሳ ሴራ ቢከሽፍም፣ የቅልበሳ ሴራ ለዘላለሙ ጠፋ ማለት አይደለም። እንዲያውም የላቁ ሙከራዎች ወደ ፊት ይመጣሉ። ወታደራዊው ደርግ በአጋጣሚ ካልሆነ እነዚህን ሙከራዎች እስከመጨረሻው ሊመክት አይችልም። አብዮት ደግሞ በመደቦች ትግል ሕግ የሚመራ እንጂ በአጋጣሚ ላይ ተማምኖ የሚራመድ ነገር አይደለም። ስለዚህ፣ አብዮታችንን ከቅልበሳ ሊያድንና ከግብ ሊያደርስ የሚችል የሰፊው ሕዝብ የነቃ፣ የተደራጀና የታጠቀ ኃይል ብቻ ነው።
የሩስያ ጭቁን ሕዝቦች ከ1905 እስከ 1907 ያደረጉት አብዮታዊ ትግል የኢትዮጵያ ሕዝቦች ባለፉት ሁለት ዓመታት ካደረጉት ትግል ቢበልጥ እንጂ የሚያንስ አልነበረም። ሆኖም የሩስያ ጭቁኖች በዚያን ጊዜ ያካሄዱት የሁለት ዓመት ትግል በበቂ የነቃ፣ የተደራጀና የታጠቀ የሕዝብ ትግል ሊሆን ስላልቻለ በአድሃሪዎች አሸናፊነት አክትሞ እንደገና የ10 ዓመት ፋሽስታዊ አገዛዝ በሩሲያ ሕዝቦች ላይ ሰፈረ። ተስፋ ለማስቆረጥ ሳይሆን፣ ያለብንን ከባድ ሃላፊነት ለመሸከም እንድንችል የኢትዮጵያ ጭቁኖችም ትግል ከተመመሳሳይ ፈተና ላይ መሆኑን መረዳት አለብን። አብዮታችን የነቃ፣ የተደራጀና የታጠቀ ጎዳና እስካልያዘ ድረስ የቅልበሳ አደጋ እየጨመረ የሚሄድ ነው። ስለዚህ፣ የሰፊውን ሕዝብ ንቃታዊ፣ ድርጅታዊና ትጥቃዊ ዝግጅቶች በፍጥነት አሟልተን ጠላቶቻችንን ለአንዴና ለሁልግዜ ለመደምሰስ ከመቸውም የበለጠ እንነሳ!!