ሰሕድ ቁ. 46

የሰፊው ሕዝብ ድምፅ

ቁጥር 46፣    ጳጉሜ 5፣ 1968

የፅሁፉ ፍሬ ሀሳብ

መኢሶን በዚህ የሰፊው ሕዝብ ድምፅ እትሙ፣ በየካቲት 1966 የተካሄደውን ሕዝባዊ የለውጥ ንቅናቄ ተከትሎ የዓጼ ኃይለ ሥላሴ መንግሥትና የፊውዳሉ ሥርዓት ለአንዴም ለመጨረሻም ጊዜ መወገዱን አስታውሶ፣ በኢትዮጵያ የሚካሄደው ሕዝባዊ እንቅስቃሴ አመርቂ ድሎችን እንዲጎናጸፍና ድሎቹም ዘለቄታ እንዲኖራቸው፣ አስተማማኝ አመራር፣ ሕዝባዊ ንቃት፣ ድርጅታዊ ጥንካሬና ትጥቅ ወሳኝ እንደሆኑ ይገልጻል። የቀድሞ መሳፍንታዊ ኃይሎችና ቢሮክራቶች፣ የሚካሄደውን አብዮታዊ ትግልና የተገኙትን ድሎች ለመቀልበሰ ያልተቋረጠ ጥረት እያደረጉ እንደሆነ ይጠቁማል። ስለሆነም፣ የአብዮቱ መቀጠልና ሕዝባዊ የትግል ድሎችን በአስተማማኝ ለመጨበጥ የነቃ፣ የተደራጀና የታጠቀ ትግል የጊዜው አጣዳፊ የተግባር መመሪያ እንደሆነ ያረጋግጣል።

የሰፊው ሕዝብ ድምፅ

ለሰፊው ሕዝብ ሰራተኛ ገበሬ፣ ነጋዴ፣ ወታደር፣ ምሁር መብትና ጥቅም የሚታገል ጋዜጣ

የኢትዮጵያ ሰፊ ሕዝብ ይቅደም

ቁጥር 46                                                                      ቀን 5/13/68

 

“Workers, you have performed miracles of proletarian heroism, the heroism of the people, in the civil war against tsarism. You must perform miracles of organization, organization of the proletariat and of the whole people, to prepare the way for your victory in the second stage of the revolution” (Lenin 1(20) March 1917)

ለነቃ፣ ለተደራጀና ለታጠቀ የሕዝብ ትግል

ጭቆና ባለበት ሕብረተሰብ ውስጥ የጭቁኖች ተጋድሎ የማይቀይር የታሪክ ሕግ ነው። የጭቁኖች ምሬት ተባብሶ፣ የዘመናት ተጋድሏቸው ተጠራቅሞ በአንድ በተወሰነ ወቅት በአሮጌው ሥርዓት ላይ  ተባብረው ወደሚነሱበት ሕዝባዊ እንቅስቃሴ ያደርሳቸዋል። ይህም ሕዝባዊ እንቅስቃሴ ትክክለኛ አመራር፣ ድርጅታዊ ጥንካሬና ትጥቃዊ ኃይል ካገኘ አሮጌውን ሥርዓት ገርስሶ ይጥላል። እነዚህ ካልተሟሉለት ደግሞ የእንቅስቃሴው እሳት ጠላቶቹን ለብልቦ ያኮማትራቸዋል እንጂ ሙሉ በሙሉ አቃጥሎ አይደመስሳቸውም።

በየካቲት 1966 በአገራችን የተጀመረው የጭቁኖች እንቅስቃሴ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ከደመኛ ጠላቶቻቸው ጋር ለረዥም ጊዜ ያካሄዱት ተጋድሎ ተጠራቅሞ በአገራችን ታሪክ ወደር ወደማይገኝለት ሕዝባዊ አብዮታዊ እንቅስቃሴ የተለወጠበት ወቅት ነበር። የሕዝብ ጠላቶቹ ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ከሕዝብ ተነጥለው ለብቻቸው የቀሩበት፣ ሕዝብ ወገኖች ደግሞ ለመቸውም ጊዜ ይበልጥ ጎን ለጎን ቆመው የተጋደሉበት [የአዘጋጆች እርማት] ወቅት ነበር። ኢትዮጵያ ጭቆኖች በድሮው ሥርዓትና በድሮው ሁኔታ ውስጥ መኖር የማይችሉበት ደረጃ መድረሳቸውን የገለፁበት እንቅስቃሴ ነበር።

የየካቲቱ እንቅስቃሴ እንደ ተጀመረ፣ የፈላጭ ቆራጩ መንግሥት እንቅስቃሴውን ለመደምሰስ ኃይል አልነበረውም። የሕዝቡም እንቅስቃሴ የነጋሲውን መንግሥት ለመጣል ኃይል አላገኘም። “ቀን ያመጣቸው” የቢሮ ከበርቴው መደብ መሪዎች በመጀመሪያው የሕዝብ ትግል ወላፈን ተገርፈው ከሥልጣን ሲወርዱ ሰፊው ሕዝብ በትግሉ ላይ ይበልጥ እምነት አደረበት። ካልታገለ ከ“ርሁሩሁ ንጉሥ” ምንም እንደማያገኝ፣ ከታገለ ደሙን ሲመጡ በኖሩት መዥገሮች ላይ ድልን እንደሚቀዳጅ ይበልጥ እየተረዳ ሄደ። ከሕዝብ ጠላቶችም በኩል በዚህ የህዝብ ድል የተደሰቱ ነበሩ። በእንዳልካቸው -አስራት ካሳ- አብይ አበበ የሚመራ የነቃ መሳፍንት ቡድን በገዥ መደቦች መሃል በነበረው ትግል ተቀናቃኙ የነበረው የቢሮ ከበርቴ ከመሪነት ተወግዶ እርሱ ሙሉ ሥልጣን የሚይዝበት ቀን የመጣለት መስሎት ነበር። ይህም የነቁ መሳፍንት ቡድን በመጀመሪያ በሽንገላ፣ ከዚያም በኃይል ጭምር እንቅስቃሴውን ለመግታት ሞከረ። ሰፊው ሕዝብ ግን “ነጭ ወረቀት” ሲባል፣ “ሕገ መንግስት ይሻሻላል” ቢባል፣ አደርባይ ጋዜጠኞች “ለአዲሱ ካቢኔ ጊዜ እንስጥ” ብለው ቢወተውቱት እሺ አላለም። እንዳልካቸውን ከመሰለ ቀንደኛ የመሳፍንት መሪና የኢምፔሪያሊዝም ቀኝ እጅ ምንም ነገር እንደማይጠበቅ በቀጠለው ትግል አረጋገጠ። በአብይ አበበ መሪነት የተቋቋመው የመሳፍንቱ “የፀጥታ ኮሚሽን” በጉልበት ሕዝቡን ፀጥ ለማሰኘትና በወታደሩ ውስጥ ይካሄድ የነበረውን ዲሞክራሲያዊ እንቅስቃሴ ለመግታት ተፍጨረጨረ። የሕዝብ ትግል ግን የበለጠ ተቀጣጠለ እንጂ አልተዳፈነም።

በትረ መንግስቱን ጨብጦ ለረጅም ጊዜ ሥርዓቱን አስጠብቃለሁ ብሎ ያመነው እንዳልካቸው ውጥኑ የህልም እንጀራ ሆነበት። የሕዝቡን ትግል አፍንበታለሁ ብሎ እንዳልካቸው በአብይ አበበ መሪነት ያቋቋመው የፀጥታ ኮሚሽን የሰፊውን ሕዝብም ሆነ የጭቁን ወታደሮችን ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ ሊያቆመው አልቻለም። ወታደሩ ራሱ  በእንዳልካቸው ላይ ዞረበት።

ለብዙ ዓመታት በፊውዳሉ መደብ ለመሪነት የታጨው እንዳልካቸው በጥቂት ወራት ውስጥ ከታሪክ መድረክ ተሰናበተ። በቦታውም ሚካኤል እምሩ ተተካ። እርሱም ለስሙ ጠቅላይ ሚኒስቴር ተባለ እንጂ የእንዳልካቸውን ፕላን ሥራ ላይ ለማዋል፣ የፊውዳሉን መደብ ጥቅም ለማስጠበቅ አልተቻለውም። ሥልጣን ቀስ በቀስ ከመሳፍንቱ እጅ መውጣት ጀምራ ነበርና። የሆነ ሆኖ፣ አንዳልካቸው በሚካኤል እምሩ ሲተካ ሰፊው ሕዝብ “ጉልቻ ቢቀያየር ወጥ አያጣፍጥም” ብሎ ትግሉን ገፋበት። እንዳልካቸውን ከሥልጣን አውርዶ፣ ቀንደኛ ፊውዳሎችን አስሮ የፊውዳሉን ሥርዓት ቁንጮ የፈራው ወታደር፣ “የመሳፍንቱ ደን እየተመነጠረ” ቢመጣ የገዥው መደቦችና ኃይለሥላሴም ካለወታደሩ የመጨቆኛ በትር እንደሌላቸው እየተረዳ መጣ። “ለንጉሠ ነገሥቱ ታማኝ ነን” ሲል የነበረው የጦር ኃይሎችና የፖሊስ ሠራዊት አስተባባሪ ደርግ ይህን ጥሎ ለኢትዮጵያ ሕዝቦች መከራና ስቃይ የንጉሱን የመጀመሪያ ደረጃ ተጠያቂነት ወደ ማስተጋባቱ ዞረ። የሰፊው ሕዝብ ትግል ግፊት፣ የወታደሩ ገዥ መደቦችን ክዶ ከሕዝብ ጎን በመሰለፍ በሕዝብ ጠላቶች ላይ መዞር ተጣምሮ መስከረም 2 1967 በፋሽስታዊ አመጽ ሰፊውን ሕዝብ በጭቆናና በድንቁርና ሰንሰለት ተብትቦ ሲገዛ የኖረውን አረመኔ ንጉሥ የሀፍረት ማቅ አልብሶ ከሁሉም በላይ ከሚወዳት ሥልጣኑ አስወገደ።

እርግጥ፣ በመስከረም 2/67 ፊውዳሊዝምና ኢምፔሪያሊዝም ከኃይለሥላሴ ጋር አብረው አልተገረሰሱም። የሰፊውን ሕዝብ ዲሞክራሲያዊ መብቶቸ የሚነጥቅ አዋጅም በዚሁ ቀን ወጥቷል። ነገር ግን፣ የአረመኔው ንጉስ ከሥልጣን መወገድ ከየካቲት እስከመስከረም የተካሄደው የኢትዮጵያ ሕዝቦች ትግል ያስገኘው ከፍተኛው የድል ምእራፍ ነው። በዚህ ቀን ሰፊው ሕዝብ ያስተጋባው እልልታና ሆታ የፊውዳሊዝም ሥርዓት ግባዐተ መሬት መጀመሩን የሚያበስር ነበር። የቀድሞ ገዥ መደቦችና የጨቋኙ ንጉሥ ከመንግስት ሥልጣን መወገድ በቀጠሉት ወራት የተካሄዱት ትግሎች ላስገኟቸው ድሎች በር የከፈተ ሕዝባዊ ድል ነው። ፊውዳሊዝምንና ኢምፕሪያሊዝምን ከአገራችን ምድር ለማጥፋት፣ ለነቃ፣ ለተደራጀና ለታጠቀ የሕዝብ ትግል ኖሮ የማያውቅን ምቹ ሁኔታ የከፈተ አብዮታዊ ድል ነው። ስለዚህም፣ የመስከረም ሁለትን የድል ቀንነት የሚክዱ ሁሉ፣ የኃይለሥላሴ ከሥልጣን መወገድ ተቆርቋሪዎች ወይንም ይህ ቀን ለተከተሉት ጥቅማቸውን ለነኩ ድሎች በር ከፋች በመሆኑ የተማረሩ ከሃዲዎች ብቻ ነው። ሰፊው ሕዝብ ግን፣ በዚሁ ግን የተነጠቀውን ዲሞክራሲያዊ መብት ለማስመለስ እየታገለ፣ ለሚቀሩት ድሎቹ ይበልጥ ለመዘጋጀት እየታገለ፣ የመጀመሪያውን ከፍተኛ የድል ምእራፍ የጻፈበትን ይህን ቀን በጋለ አብዮታዊ ስሜት ያከብረዋል። መስከረም 2/ አድሃሪዎችና ከሃዲዎች የፈለጉትን ያህል ቢፍጨረጨሩ ሊፍቁት የማይችሉት፣ በኢትዮጵያ ጭቁኖች የነፃነት ተጋድሎ ታሪክ ውስጥ ከፍተኛ ቦታ የሚይዝ ቀን ነው። ይህን ቀን እናክብር ወይስ አናክብር የሚለው አቋም፣ በዛሬው የኢትዮጵያ ሕዝቦች ትግል ውስጥ በአብዮቱና በፀረ አብዮት ኃይሎች መሃል ያለውን ተፃራሪ አቋም ያንፀባርቃል።

በቀድሞ ገዥ መደቦችና በመሪያቸው በኃይልሥላሴ ከሥልጣን መወገድ የተከፈተው የኢትዮጵያ ጭቁኖች የድል ጎዞ ውስጥም ሌሎች ከፍተኛ ድሎች ተገኝተዋል። የማምረቻና የማከፋፈያ ድርጅቶች መወረስ፣ መሬት ላራሹን ያፀደቀው አዋጅ መውጣት፣ የትርፍ ቤቶችና የከተማ ቦታ በመንግስት ቁጥጥር ሥር መሆን፣ የብሄራዊ ዲሞክራሲያዊ አብዮት ፕሮግራም እንደ መንግሥቱና እንደ ሕዝቡ የትግል መመሪያ መውጣት፣ የኤርትራን ችግር በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የሰላምና የትግል አንድነት ጥሪ መደረግ፣ እነዚህ ሁሉ የመስከረም ሁለቱ ታሪካዊ ድል በከፈተው በር በሰፊው ሕዝብ እጅ የገቡ፣ በመራራ ትግልና በከፍተኛ መስዋእትነት የተቀዳጀናቸው ድሎች ናቸው። እነዚህም ድሎች መዘጋጃና መንደርደሪያ ጎዳና ለመሆን ችለዋል።

የሰፊውን ሕዝብ ንቃት፣ ድርጅትና ትጥቅ በሚመለከተውም በኩል እንደዚሁ የማይናቁ የወደፊት እርምጃዎች ተደርገዋል። “በአብዮት ወቅት ብዙ ሚሊዮን ሕዝቦች በ‘ሰላም ጊዜ’ በዓመት ውስጥ ከሚማሩት የበለጠ በሳምንት ውስጥ ይማራሉ” የሚለው ሌኒናዊ ሀቅ በአገራችንም አውነተኛነቱን አስመክሯል።

በአደናቋሪው የኃይለሥላሴ መንግሥት ፕሮፖጋንዳ ታፍኖ የኖረው የሰፊ ሕዝብ ንቃተህሊና ከመቸውም የበለጠ እየጎለመሰ ነው። ከአድሃሪው ሥርዓት ጋር የተጣበቀው አድሃሪ ፐሮፖጋንዳ በመገርሰሱ ዛሬ የሳይንሳዊ ሶሻሊዝም ሥር በሰፊው ሕዝብ ውስጥ እየተተከለ ነው። የኢትዮጵያ ተራማጆች በረጅም ጊዜ መራራ ትግላቸው ባገኙት ድል ተጠቅመው መትከል የጀመሩትን የሳይንሳዊ ሶሻሊዝም አትክልት ፍሬ ለመሰብሰብ የሚችሉበትም ቀን እየተቃረበ ነው።

በድርጅትም በኩል፣ የወዛደሩ መደብ በኃይለሥላሴ መንግሥት የተጫነበትን የሞያ አመራር አሽቀንጥሮ ጥሏል። ይህን ድል ተጠቅሞ እንደገና ከአመራሩ ላይ ቂብ ያለበትን የአናርኪስቶች ጥርቃሞ በሁለተኛ ዙር ትግሉ አድቅቆታል። ብዙ የሞያ ማህበራት፣ ሰርገው ገብተው የወዛደሩን ንቅናቄ ለመበታተን የተነሱባቸውን አናርኪስቶች በማጋለጥና መንጥቆ በማውጣት ጠንካራ የሞያ ማህበር ለመመስረት ባደረጉት ትግል ከፍተኛ ድሎች ተጎናጽፈዋል። ከቅጥር አድሃሪዎችና ከሰርጎ ገብ አናርኪስቶች አጽድቶ እውነተኛና ጠንካራ አጠቃላይ የወዛደር የሞያ ማህበር ለማቋቋም የሚያደርገው ትግል ከከፍተኛ ደረጃ ደርሷል።

የወዛደሩ መደብ ታሪካዊ መሪ፣ የጭቁኖች ቡድን አስተባባሪ የሆነውን ወዛደሩን የፖለቲካ ፓርቲ ለመመስረት የተደረገውም ትግል እንደዚሁ ከፍተኛ የወደፊት እርምጃ አድርጓል። የኢትዮጵያን ሃቀኛ ተራማጆች አስተባብሮ፣ ከንቁ ወዛደሮች ጋር ተዋህዶ በፅኑ መሰረት ላይ የወዛደሩን ፓርቲ ለመመስረት የሚታገለው የመላ ኢትዮጵያ ሶሻሊስት ንቅናቄ /መኢሶን/ ከመቸውም ይበልጥ ተጠናክሮ ሕልውናውን በይፋ አስታውቋል። ሌሎች ተመሳሳይ አላማ ያላቸው ቡድኖችና ድርጅቶችም ተጠናክረው የሃቀኛ ተራማጁን አንድነት ለመገንባት፣ የወዛደሩን ፓርቲ ለመመስረት በከባድ ትግል ውስጥ ይገኛሉ።

የአብዮት ተሸካሚ የሆነው የአርሶአደር፣ በተለይ የገጠርን መሬት የሕዝብ ያደረገው አዋጅ ከወጣ ወዲህ፣ በታላቅ ቆራጥነት ትግሉን ቀጥሏል። በተራማጅ ዘማቾች አብዮታዊ አስተዋፅኦና በጭቁኑ አርሶአደር መራራ ትግል በኢትዮጵያ ገጠሮች ዛሬ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ የገበሬ ማህበራት ተደራጅተዋል። በአድሃሪው ቢሮክራሲ አሻጥር፣ በመሬት ከበርቴው አመጽ ሳይበታተኑ ለዘመናት ትግል የተቀዳጁትን ድል በመጠባበቅ ላይ ናቸው።

በትጥቅም በኩል፣ ቀደም ብሎ ከነበረው ሁኔታ ጋር ሲነፃፀር የማይናቅ የወደፊት እርምጃ ተደርጓል። መጠነኛም ቢሆኑ፣ በገበሬ ማህበራት ሥር የተቋቋሙት የአርሶአደሩ ደህንነት ጥበቃ ጓዶች የወደፊት ሕዝባዊ ሠራዊት ጥንስሶች ናቸው። በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ፣ እነዚህ የጥበቃ ጓዶችና ጭቁኑ ወታደር በመተባበር የአድሃሪያንን ምሽግ ለማፈራረስ የሚያደርጉት ትግል “አድሃሪ አለቀለት” ባያሰኘንም ለአብዮቱ መቀጠል መጠነኛ ዋስትና እንደሚሆን አይጠረጠርም።

እንግዲህ፣ እነዚህ ሁሉ ከላይ የዘረዘርናቸው ድሎች የሕዝብ ትግል ውጤቶችና የእድገትም ምልክቶች ናቸው። በጠላቶቻችንስ ሰፈር ያለው ሁኔታ እንዴት ነው? በመጀመሪያ ደረጃ አብዮታዊው ትግል እስከዛሬም ድረስ መቀጠልና ድልን በድል ላይ እየተጎናፀፈ መምጣት ራሱ ጠላቶቻችን በነዚህ ሁለት ዓመታት ውስጥ አብዮታችንን ለመቀልበስ፣ ያገኘናቸውን ድሎች መልሰው ለመንጠቅ አለመቻላቸውን ያረጋግጣል። ይህም በነዚህ ሁለት ዓመታት ፀረ አብዮት ትግላቸውን የቅልበሳ መከራቸውን አላፋፋሙትም ነበር ማለት አይደለም። በሰፊው ሕዝብና በጭቁኑ ወታደር የተባበረ ክንድ እየተኮረኮሙ አልሳካ አላቸው እንጂ አብዮታችንን ለመቀልበስ የሞትና የሽረት ትግል ሲያካሂዱ ቆይተዋል። አሁንም፣ የቀድሞ መሳፍንትና የቢሮውና አቀባባይ ከበርቴዎች፣ እንዲሁም ከሃዲው ቀኝ ንዑስ ከበርቴ መሪ የሆኑት አናርኪስቶች በአሜሪካ ኢምፔሪያሊዝም አስተባባሪነት የኢትዮጵያን ጭቁኖች አብዮታዊ ትግልና ድሎች ለመቀልበስ ከፍተኛ ድርጅታዊና ትጥቃዊ ዝግጅቶች በማድረግ ላይ ናቸው። በኢትዮጵያ ገጠሮች አሁንም ያልተዳፈነው የአድሃሪዎች ፀረ ሕዝብ አመጽ፣ በሲአይኤ መሪነት የሚዘጋጁት ፋሽስታዊ የመፈንቅለ መንግስት ሙከራዎች፣ በቢሮክራሲውና በአድሃሪ ነጋዴዎች የሚሸርቡት ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ አሻጥሮች፣ በአናርኪስቶች ቡድን የሚካሄደው ሽር ፈጠራና ለቅልበሳ አመቻች ቅስቀሳ፣ እነዚህ ሁሉ የአብዮታችን ጠላቶች የኢትዮጵያ ጭቁኖች የከፈቱባቸውን የመደብ ጦርነት ለማዳፈን የሚያደርጉት ዝግጅት ነፀብራቅ ነው። ስለዚህም፣ በሰፊው ሕዝብ የነቃ፣ የተደራጀና የታጠቀ ኃይል የአድሃሪ ኃይሎች ሁሉ የመጨረሻ ምሽግ እስኪፈራርስ ድረስ ፀረ ሕዝብ አመፃቸው፣ የቅልበሳ ሙከራቸው በፍፁም ሊገታ አይችልም።

አሁን በደረስንበት የትግል ደረጃ፣ በጋዜጣችን ላይ ደጋግመን እንዳነሳነው ሁሉ፣ ፀረ ሕዝብ ኃይሎችም ጭቁኖችም ለወሳኙ ግጥሚያ በመዘጋጀት ላይ ናቸው። እስካሁን የተካሄደው ትግልና ያስገኛቸው ድሎች የኢትዮጵያን ሕዝቦች ትግል ወደዚሁ ወሳኝ ግጥሚያ አሸጋገረው እንጂ የጭቁኖችን ትግል ከግብ መድረስ አላበሰረም። የኢትዮጵያ ጭቁኖች ከዚህ ወሳኝ ግጥሚያ በድል አድራጊነት የሚወጡት በነቃ፣ በተደራጀና በታጠቀ አመፃቸው ብቻ ነው።

በአሁኑ ጊዜ የኢትዮጵያ ጭቁን ሕዝቦች ትግል ጥንካሬ እያገኘ ቢሄድም፣ ብሄራዊውን ዲሞክራሲያዊ አብዮት ከግቡ ለማድረስ የሚያበቃ የነቃ፣ የተደራጀና የታጠቀ ኃይል ገና አልሆነም። ነገር ግን፣ በሕዝቡ ትግል ጥንካሬ የተነሳ፣ እስካሁን በተገኙት አብዮታዊ ድሎች ምክንያት እነዚህን ንቃታዊ፣ ድርጅታዊና ትጥቃዊ ዝግጅቶች ለማሟላት በጣም አመቺ ሁኔታ አለ። ኃላፊነታቸውን የተገነዘቡ ሃቀኛ ተራማጆች ሁሉ፣ የሁኔታውን አመቺነት በመረዳት እነዚህን ዝግጅቶች ለማሟላት መጣደፍ የኢትዮጵያ ጭቁኖች ትግል የጣለባቸው ከፍተኛ አደራ ነው። መኢሶንና ሃቀና ተራማጆች ሁሉ ለረዥም ጊዜ ያለማቋረጥ “ለነቃ፣ ለተደራጀና ለታጠቀ የሕዝብ ትግል” የሚለው መፈክር የሚያስተጋቡትና በተግባር ለመተርጎም የሚታገሉት ለዚህ ነው።

በነቃ፣ በተደራጀና በታጠቀ ኃይል ካልሆነ በስተቀር የኢትዮጵያ ጭቁኖች ከመደብ ጠላቶቻቸው ጋር በሚያደርጉት ወሳኝ ግጥሚያ አሸናፊትነት አያገኙም ብለናል። የዛሬው አጣዳፊ ተግባር እነዚህን ዝግጅቶች ለማሟላት በቆራጥነት ሌት ተቀን መታገል መሆኑን ገልፀናል። እነዚህን ዝግጅቶች ለማሟላት ሃቀኛ ተራማጆች የግንባር ቀደምነት ግዴታ እንዳለባቸውም ደጋግመን አንስተናል። መከተል ያለበት ጉዳይ እነዚህ ዝግጅቶች እንዴት ነው የሚሟሉት የሚለው ነው።

ንቃት፣ ድርጅትና ትጥቅ፣ እነዚህን ለማሟላት የሚደረጉት ዝግጅቶች ዲያሌክቲካዊ በሆነ መንገድ የተያያዙና ተደጋጋፊ ናቸው። የተወሰነ የንቃት ደረጃ በተወሰነ የድርጅት ኃይል ይገለፃል። የተወሰነ ድርጅት ጥንካሬ የተወሰነ ትጥቃዊ ኃይል ይኖረዋል። ሦስቱም ተያይዘው የሚመጡ የትግል እድገት ውጤቶች ናቸው።

በንቃትና በድርጅት መሃል ያለውን ግንኙነትና ዘምድና ባጭሩ እንመልከት። የወዛደሩ መደብ እንደተፈጠረ፣ ወዛደሮች የሚጫንባቸውን የጭቆና ቀንበር እኩል መሸከማቸው፣ ኑሯቸውና እድላቸው ተመሳሳይ መሆኑን ይረዱና እንደ ወንድምና እህት መተያየት ይጀምራሉ። የመተሳሰርና የመተባበር ፍላጎት ያድርባቸዋል። በዚህም ለጋ የንቃት ደረጃ በእድርና በመሳሰሉት ድርጅቶች መደራጀት ይጀምራሉ። በዚህ ደረጃ ላይ የትግል ዘዴያቸውም እንደ ንቃትና እንደ ድርጅቱ ሁሉ ወደኋላ የቀረ ነው። የአሰሪ መደብደብና ፋብሪካ መሰባበር…. ነበር ትግላቸው። በዚህ የመጀመሪያ ደረጃ ትብበርና በየቀኑ ፋብሪካ ውስጥ ከሚቀስሙት ትምህርት በጋራ በሚበዛብዛቸው የጋራ ጠላት እንዳለ፣ በዚህ የጋራ ጠላት ጋር በሚያደርጉት ትግል በህብረት ቢሰለፉ የበለጠ ውጤት እንዲያገኙ ይረዳሉ። ከዚህም የንቃት ደረጃ በሙያ ማህበራት ስር መደራጀት ይጀምራሉ። ንቃታቸውና ድርጅታቸው እዚህ ደረጃ ሲደርስ በስራ ማቆምና በመሳሰሉ በሞላ ጎደል የተደራጁ የትግል ዘዴዎች ለደሞዝ እና ለሥራ ሁኔታ መሻሻል ይታገላሉ። በሙያ ማህበራቸው አማካይነት ወዛደሮች ከመደብ ጠላቶቻቸው ጋር በሚያደርጉት ትግል ውስጥ የወዛደሩን ርዕዮተ ዓለም የተቀበሉ አብዮታዊ ምሁራን ሳይንሳዊ ሶሻሊዝምን ለማስፋፋት፣ የሙያ ማህበር ንቅናቄና ሳይንሳዊውን ርዕዮተ ዓለም ለማዋሃድ የሚያደርጉት የትግል ፍሬ ሲሰጥ፣ በራሳቸው ርዕዮተዓለም የታነፁ ወዛደሮች ይፈልቃሉ። በዚህኛው የንቃተ ህሊና ደረጃም የወዛደሩ መደብ የፖለቲካ ፓርቲ ይፈጥራል። በዚህም የንቃትና የድርጅት ደረጃ ወዛደሩ ከኢኮኖሚያዊ ትግል አልፎ የመንግሥት ስልጣን ለመጨበጥ፣ ራሱን እና ጭቁኖቹን ሁሉ ነጻ ለማውጣት ይታገላል።

አርሶአደሩንም ብንወስድ፣ በአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ እንደታየው፣ በተራማጅ ዘማቾች አብዮታዊ አስተዋጽኦና የመሬቱ አዋጅ በፈጠረው ምቹ ሁኔታ የመሬት ከበርቴዎችን አመጽ በተናጠልና ለየብቻ መቋቋም እንደማይችል በመረዳት በቀበሌ የገበሬ ማህበራት ተደራጅቷል፣ እየተደራጀም ነው። ነገር ግን ገና በዛሬው ቢሮክራሲ ሥር መሬትን የሕዝብ ያደረገው አዋጅ ሙሉ በሙሉ ሥራ ላይ እንደማይውል፣ ዋስትና ባለው መንገድ ሥራ ላይ ይውል ዘንድ ቢሮክራሲው ተንኮታኩቶ አርሶአደሩ ራሱ በወዛደሩ መሪነት ሥልጣን መከፋፈል እንዳለበት በበቂ መረዳት ይገባዋል። የአርሶአደሩ ንቃተህሊና እዚህ ደረጃ ሲደርስ በወዛደር አርሶአደር ሕብረት ድርጅታዊ መዋቅር ያገኛል።

ከፍተኛ የፖለቲካ ንቃት በከፍተኛ ፖለቲካ ድርጅት እንደሚገለጽ ሁሉ፣ የትጥቅም ኃይል በከፍተኛ የፖለቲካ ድርጅት ላይ ተመርኩዞ የሚገኝ ነው። ሌኒን የትጥቅ ዝግጅትን በሚመለከተው በኩል የትጥቅን  ጉዳይ ከድርጅት ጉዳይ ተነጥሎ እንደማይታይ ያስረዳል። መደራጀት ራሱ ለትጥቅ ትግል መዘጋጀት እንደሆነ ፣ድርጅታዊ ዝግጅቱ ከተሟላ የትጥቅ ዝግጅቱ እንደሚመጣ አስተምሯል። (ቭላዲሚር [የአዘጋጆች እርማት] ሌኒን፣ ምን መደረግ አለበት፣ ፔኪንግ 1975፣ በገጽ 218 እስከ 220)

ንቃት ድርጅትና ትጥቅ የሚለው ቅደም ተከተል አንዱ ሲያልቅ ወደ ሌላ መዞርን የሚያመለክት አይደለም። ተያይዘው የሚመጡ የዝቡ ትክክል ውጤቶች ናቸው። ከላይ እያርሶ አደሩ የጥበቃ ጓዶች፣ የአርሶአደሩ በመጠኑም መታጠቅ ለወደፊቱ ህዝባዊ ጦር ጥንሰሶች ናቸው ብለን ነበር። እንደዚሁም፣ አርሳደሩ ባለፉት ሁለት አመታት ባካሄዳቸው ትግሉ ያገኘው የንቃትና የድርጅት ዕድገት ውጤቶች ናቸው። ይህ መጠነኛ ትጥቅ ወደ ሙሉ ትጥቅ የሚቀይረው ንቃቱና ድርጅቱ በተፈጠነ  መጠን ነው።

እናጠቃል። ያለፉት ሁለት አመታት የኢትዮጵያ ጭቁኖች ትግል በንቃት፣ በድርጅትና በትጥቅ የማይናቁ የወደፊት እርምጃ አድርጓል። ጭቁኖች ትግሉን በከፍተኛ ደረጃ ወደፊት ለመቀጠል፣ ለወሰኙ ግጥሚያ በይበልጥ ለመዘጋጀት ካሁኑ በበለጠ መንቃት፣ መደራጀትና መታጠቅ አለባቸው። የኢትዮጵያ የዛሬ ተጨባጭ ሁኔታ የሕዝቡን ትግል የነቃ፣ የተደራጀና የታጠቀ ጎዳና ለማስያዝ በጣም አመቺ ነው። የኢትዮጵያ ሀቀኛ ተራማጮች በዚህ ዓመቱ አመቺ ሁኔታ ባስቸኳይ መጠቀም ከቻሉ፣ የግንባር ቀደምነት ኃላፊነታቸውን ለማሟላት ሌት ተቀን ከታገሉ፣ የኢትዮጵያን ሕዝቦች ትግል በትክክለኛ ታክቲክና በትራቴጂ ስር መርተው ፣የነቃ እየተደራጀና የታጠቀ የትግል ጎዳና እንዲይዝ ረድተው ያሁኑን አብዮታዊ እንቅስቃሴ ከግቡ እንዲደርስ ከማድረግ የሚያግዳቸው ኃይል አይኖርም።

ሰፊውን ሕዝብ ለማንቃት፣ የነቃውን ክፍል ለማደራጀት፣ የተደራጀውን ለማስታጠቅ መታገል ፋታ የማይሰጥ የጊዜው አጣዳፊ ተግባር ነው። ይህ ተግባር ሲከናወን አብዮታችን ካለበት አደጋ ወጥቶ በድሉ ጎዳና ላይ እየተጓዘ ከግቡ ይደርሳል። ለዚህም ለኢትዮጵያ ጭቁኖች ነፃነት እስከመጨረሻው ለመቆም የቆረጡ ሃቀኛ ተራማጆች እነዚህን የተያያዙ ተግባሮች በሥራ ላይ ለመዋል አንድነታቸውን  ማጥበቅ አለባቸው። የተጣመረ ኃይላቸውን በሰፊው ሕዝብ ትግል ውስጥ አሰማርተው የአብዮት እሳት የበለጠ እንዲቀጣጠል መታገል አለባቸው።

የሀቀኛ ተራማጆች አንድነት ይጠንከር
የአናርኪስቶች የአድሃሪዎች ፀረሕዝብ አንድነት ይውድም
የነቃ፣ የተደራጀና የታጠቀ የሕዝብ ትግል ያሸንፋል።
Scroll to Top