የሰፊው ሕዝብ ድምፅ
ቁጥር 51፣ የካቲት 5፣ 1969
የፅሁፉ ፍሬ ሀሳብ
ደርግ ውስጥ በተደረገው የስልጣን ሽኩቻ በአሸናፊነት የወጡት የኢህአፓ አባላትና ደጋፊዎች ዋና ጠላቶቻችን ኢድዩ፣ ሻዕቢያና የውጪ ኃይሎች ስለሆኑ ኢህአፓ እንዳይወገዝ ሲሉ ለመንግሥት የመገናኛ አካላት መመሪያ አስተላለፉ። በዚያኑ ሰሞን የኢህአፓ ግድያና የቢሮክራሲው ኃይልም በረታ። በዚህ ሁኔታ ደርግ ውስጥ በነበሩት በመቶ አለቃ አለማየሁና ሻምበል ሞገሰ የሚመራው የኢህአፓ በድን የሱዳንን ጣልቃ ገብነት ለማውገዝ በሚል ሽፋን፣ ኢህአፓን ስልጣን ለማስያዝ የሚደረገውን ሴራ ሊረዳ ይችላል በማለት የጥር 22ትን ሰልፍ ጠራ። በሰልፉ ላይም የአለማየሁ/ሞገስ ቡድን ያልጠበቁት ትልቅ ሕዝባዊ ተቃውሞ ታየ። ሰልፈኛው ኢሕአፓንና ኢድዩን ቢሮክራሲውን የሚያወግዙ መፈክሮች አሰማ። ከዚያም ብዙ ሳይቆይ ጥር 26፣ 1969 ዓ.ም. የኮሎኔል መንግስቱ ቡድን የኢህአፓ ደጋፊ የነበሩትን የሞገስ እና የአለማየሁን አንጃ ከስብሰባ ውስጥ ለቅሞ አውጥቶ ረሸናቸው። በማግስቱ ጥር 27 የተደረገው ሰልፍ በደርጉ ውስጥ የነበረው የኢህአፓ አንጃ ስለተሸነፈ የተደረገ የድጋፍ ሰልፍ ነበር።
መኢሶን በዚህ እትሙ ሁለቱ ሰልፎች የሕዝቡን ቁጣና ፍላጎት የሚያንጽባርቁ እንደነበሩ ያብራራል። በእነ አለማየሁ አንጃ መሸንፍ አብዮቱ ትንሽ ፋታ ማግኘት ቢችልም፣ ለወሳኙ ትግል የሚደረገው ዝግጀት ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ያስገነዝባል። አብዮቱ በድል ጎዳና እንዲጓዝ አመቺ ሁኔታ ይፈጥራሉ የሚላቸውንም አራት ነጥቦች ይሰነዝራል።
የሰፊው ሕዝብ ድምፅ
ለሰፊው ሕዝብ ሰራተኛ ገበሬ፣ ነጋዴ፣ ወታደር፣ ምሁር መብትና ጥቅም የሚታገል ጋዜጣ
የኢትዮጵያ ሰፊ ሕዝብ ይቅደም
ቁጥር 51 ቀን 5/6/69
| በአብዮታዊው መኮንን በኮሎኔል ዳንኤል አስፋውና በአብዮታዊው ምሁር በጓድ ሰናይ ልኬ ሞት የተሰማውን ሀዘን የሰፊው ሕዝብ ድምጽ ለነዚህ አብዮታዊያን ሰማዕታት ቤተሰቦች ይገልፃል። የነርሱ መውደቅ ሺህ በሺህ አብዮታዊያንን እስካፈራ ድረስ አብዮታውያን መስዋዕትነትን በደስታ ይቀበሉታል። |
የእሁድ 22 እና የአርብ 27 ሰላማዊ ሰልፎች
ሰላማዊ ሰልፎች ሰፊው ሕዝብ ስሜቱንና ምኞቱን የሚገልጽባቸው ስብሰባዎች ሳይሆኑ፣ ሕዝቡ ኃይሉን በማሳየት፣ በእርግጥም የታሪክ ሰሪ እራሱ መሆኑን ለራሱም ለተመልካቹም የሚያረጋግጥባቸው ሸንጎዎች ናቸው። እንደ ሁኔታው፣ ሰፊው ሕዝብ ደስታውንና ስምምነቱን፣ ወይንም ተቃውሞውንና ቁጣውን በሰላማዊ ሰልፎች ይገልጻል። ሰላማዊ ሰልፎች ከተቃውሞና ከቁጣ አልፈው ወደ ሕዝብ አመፅ የተሸጋግሩባቸው ሁኔታዎች በሀገራችንም ሆነ በሌሎች አገሮች ተደጋግመው ታይተዋል። በነዚህ ዓይነት ሁኔታዎች ወይ ሰፊው ሕዝብ በጭቆና በዝባዥ መደቦች ላይ ትላልቅ ድሎችን በማግኘት አንድ እርምጃ ይሄዳል፣ ወይንም ደግሞ ለጊዜው ተሸንፎ፣ ከስህተቶቹ ተምሮ ለሌሎች ከፍተኛ ግጥሚያዎች ይዘጋጃል።
በዓለም ታሪክ ውስጥ ከፍተኛ ቦታን ከያዙት ትላልቅ ሰልፎች ውስጥ፣ በመጀመሪያው የሩሲያ አብዮት፣ እኤአ በጥር 1905 በፐርቶግራድ /ሌኒንግራድ/ ከተማ የተደረገው የሩሲያ ወዛደር ሰልፍ አንዱ ነበር። በዚህ ሰልፍ ላይ በሺህ የሚቆጠሩ ወዛደሮች ተገደሉ፣ በብዙ ሺህ ቆሰሉ። እንደዚሁም በሌሎች የሩሲያ ከተሞች በተከተሉት ሁለት ዓመታት ውስጥ በተደረጉት ሰልፎች የወዛደሩ ደም እንደ ጎርፍ ፈስሶ አብዮቱም ከሸፈ። ነገር ግን እነዚያን በውድቀት ያከተሙትን የሕዝብ ትግሎች ሌኒን መለማመጃዎች ናቸው ብሏል። በርግጥም የሩሲያ ወዛደር ከውድቀቶቹ ተምሮ፣ ኃይሉንና አንድነቱን አጠንክሮ፣ በኦክቶበር 1917 አድሃሪ መደቦችን ደምስሶ የመጀመሪያዋን ሶሻሊስት አገር መሰረተ።
የኢትዮጵያ ሰርቶአደር ሕዝብ በጥር 22 እና 27 ቀኖች ያደረጋቸው ሰላማዊ ሰልፎች ከቀድሞዎቹ ሰልፎች ሁሉ በቅርጽም በይዘትም ፈጽሞ የተለዩ ነበሩ ለማለት ይቻላል። መጀመሪያ ነገር፣ እነአለማየሁ ኃይሌ በደርግ ውስጥ ከያዙት ቁልፍ ቦታ የተነሳ፣ የአብዮታዊው እንቅስቃሴ መቀዝቀዝና ወደ ቅልበሳ ማምራት ለሰፊው ሕዝብ ተሰምቶት፣ ይህ ሕዝብ አንድ አይነት እርምጃን የሚወስድበትን መንገድ ሲፈልግ ነበር። የሬዲዮ የትዝታ ዘፈኖች፣ የቢሮክራሲ በየቦታው እንደገና ቀና ቀና ማለት፣ የኢ.ዲ.ዩ መጠናከርና የኢ.ህ.አ.ፓ የነፍሰ ገዳይነት ድርጊቶቹን ማፋፋም፣ እነዚህ ሁኔታዎች ባንድነት ተደማምረው ለሰፊው ሕዝብ በቂ የቅበልሳ ምልክቶችን ሰጥተውት ነበር። ስለዚህም፣ አንድ ነገርን የማድረጊያ፣ አንድ ነፃ እርምጃን የመውሰጃው ወቅት እንደተቃረበ ተሰምቶት ስለነበር፣ የእሁዱ ሰልፍ ጊዜውን ጠብቆ የመጣለት ሰልፍ ነበር።
ሁለተኛ ነገር፣ ሁለቱም ሰልፎች የኢትዮጵያ ተራማጆች በሰፊው ሕዝብ ውስጥ በመጠኑም ቢሆን መተከላቸውንና ሊያንቀሳቅሱትም መቻላቸውን ለተራማጆቹ ለራሳቸው ያረጋግጡላቸው ሰልፎች ነበሩ። የንዑስ ከበርቴው ደንፊ ቡድንና ሌሎችም አድሃሪዎች የሚያምኑት በሰፊ ሕዝባዊ እንቅስቃሴ ሳይሆን በጥቂት “ጀግና” ግለሰቦች ድርጊት ስለሆነ ፓፕሊስት ናቸው። ሃቀኛ ተራማጆች ግን ታሪክን የሚሰራው፣ አብዮትን የሚያካሄደውና የሚፈጸመው ሰፊው ሕዝብ እራሱ መሆኑን ስለሚያምኑበት፣ ይህንን ትዕግስትና ረዘም ያለ የትግል ጊዜን የሚጠይቀውን የማንቃትና የማደራጀት ተግባር ይጋተሩታል። የእሁድና የዓርብ ሰላማዊ ሰልፎች የኢትዮጵያ ተራማጆች ትግል ውጤት ማሳየት መጀመሩን አረጋግጠውላቸዋል።
ሶስተኛ ነገር፣ የመፈክሮቹ ይዘትና በሕዝቡ ዘንድ ያገኙት ተቀባይነት፣ በተራማጆችና በሰፊው ሕዝብ መካከል የነበረው የልብ ለልብ ግንኙነት፣ የቋንቋ አንድነትና የጋራ የልብ ትርታ ከዚህ በፊት ታይቶ የማይታወቅ አይነት ነበር። ይህ ሁኔታ የኢትዮጵያ ሀቀኛ ተራማጆች በእርግጥም ከሰፊው ሕዝብ ጋር መዋሃድ መጀመራቸውን፣ ስለዚህም ስሜቱንና ፍላጎቱን ለማወቅና ለመከተል መቻላቸውን በሚገባ አሳይቷል።
አራተኛ ነገር፣ ሁለቱም ሰልፎች፣ በተለይም የዓርቡ ሰልፍ በጣም አጭር በሆነ ጊዜ ውስጥ የተዘጋጁ ሲሆኑ፣ የሰልፈኛው ያደረጃጀት ስልትና ዲሲፕሊኑ በጣም አስደናቂዎች ነበሩ። ይህም እንግዲህ የኢትዮጵያ ሰፊ ሕዝብ፣ የኢትዮጵያ ወዛደር መደብ ለነጻ ታሪካዊ ድርጊቶች ራሱን በራሱ [ሊያሰልፍ] እንደሚችል አረጋግጧል።
በመጨረሻም፣ ሁለቱ ሰልፎች ለወዳጅም ሆነ ለጠላት በማያዳግም አኳዃን ያረጋገጡት አንድ ታሪካዊ ሀቅ አለ፣ ይኸውም፣ ኮሎኔል መንግስቱ በሁለተኛው ሰልፍ ሲናገሩ እንደጠቀሱት ሁሉ፣ የኢትዮጵያ አብዮት የወደፊት እድል ከእንግዲህ በጥቂት ሰዎች ብቻ፣ በቤተመንግሥት ፖለቲካ የማይወሰን መሆኑን፣የአብዮቱ ባለቤት የሆነው ሰፊው ሕዝብ የአብዮቱ ዋና ተከላካይና ጠባቂ ለመሆን መብቃቱ ነው። ስለሆነም፣ የኢትዮጵያ ሰፊ ሕዝብ የገዛ እድሉን በገዛ እጆቹ የሚጨብጥበት ወቅት እየተቃረበ መሄዱን እነዚህ ሁለት ሰልፎች በሚገባ አሳይተዋል።
የእሁዱ ሰልፍ ዋና መልእክት የመደብ ትግሉን እናፋፍም፣ በአድሃሪዎች ላይ እንነሳ የሚል ነበር። ኢ.ህ.አ.ፖ፣ ኢ.ዲ.ዮ.፣ ኢ.ኤል.ኤፍ. መደምሰስ አለባቸው የሚል ጥሪ ነበር። የውስጥ ጠላቶችን በማንበርከክ ወደ ውጭ ጠላቶች፣ ወደ ኢትዮጵያ ድንበሮች ማንጋጠጥ ለአብዮቱ ጉድጓድ እንደመቆፈር ነው የሚል ማስጠንቀቂያ ነበረበት። እነአለማየሁ ኃይሌና ሌሎችም በደርጉ ውስጥ ቁልፍ ቦታዎችን ይዘው የነበሩት አድሃሪዎች ግን ይህ አብዮታዊ መልዕክት እንዳይተላለፍ፣ የሰፊው ሕዝብ ድምጽ እንዲታፈን፣ ሰፊው ሕዝብ ከደመኛ ጠላቶቹ ጋር እንዲታረቅና የአገሪቷን ድንበሮች አፍጦ ሲመለከት ከበስተጀርባ ተወግቶ እንዲወድቅ ነበር የፈለጉት። ሰፊው ሕዝብ ለመዋጋትና ለመሞት የፈለገው ለአብዮታዊት ኢትዮጵያ ነው። እነርሱ ሊያዋጉት የፈለጉት ለፊውዳላዊት ኢትዮጵያ ነበር። የሰፊው ሕዝብ ጥሪ መደብን የለየ ሀገር ወዳድነትን የሚያንጸባርቅ ጥሪ ነበር። የነርሱ ግን በዝባዥና ተበዝባዥን፣ ጨቋኝና ተጨቋኝን በአንድነት ለማሰለፍ የሚሻ፣ እውር፣ ጊዜው ያለፈበት አድሃሪ የብሄርተኞች ጥሪ ነበር። ስለዚህ ነበር፣ በእሁዱ ሰልፍ በነተፈሪ በንቲና በሰፊው ሕዝብ መካከል የነበረው ርቀት የሰማይንና የምድርን የሚያክል የነበረው። ስለዚህም ነበር፣ ጀነራሉ ንግግራቸውን ሲጀምሩ ሰፊው ሕዝብ በበኩሉ አደባባዩን ጥሎ መውጣት የጀመረው።
በእሁዱ ሰልፍ ሰፊው ሕዝብ ይጠብቅ የነበረው የርሱን ቋንቋ የሚናገሩለትን፣ የጥያቄዎቹን ትክክለኝነት የሚገነዘቡለትን፣ በነኢ.ህ.አ.ፓ- ኢ.ዲ.ዩ. ኢምፔሪያሊዝም ወንጀሎቹ አንጀቱ ማረሩን የሚያውቁለትን መሪዎች ነበር። ዋናው ሊቀመንበር ለራሳቸው አንድ እሁድ የከብት እርባታውን የሚጎበኙ ከበርቴ መስለው ከመምጣታቸው በላይ፣ በርሳቸው ዙሪያ የነበሩትና አሁን የተወገዱት አድሃሪዎች ለሰፊው ሕዝብ ያሳዩ የነበረው ንቀት ይህ ነው አይባልም። እንደነርሱማ ፍላጎት ሰፊውን ሕዝብ ወክለው ለመናገር የቀረቡት የመ.ኢ.ሠ.ማ.፣ የቀበሌ ማህበራት፣ የገበሬ ማህበራትና የሕዝብ ድርጅቶች ጉዳይ ጽ/ቤት አባሎች የእነርሱን የበላይነት ሰጥ-ለጥ ብለው በመቀበል ንግግሮቻቸውን ለእነርሱ፣ ለሳንሱር ማቅረብ ነበረባቸው። በዚያም እሁድ እነዚህ ወኪሎች ያደረጉት ትግል ለሰፊው ሕዝብ ያላቸውን ፍጹም ታማኝነት ስለሚያረጋግጥ አብዮታዊን ሁሉ ያኮራል።
የአሁዱ ሰልፍ በደርጉ ውስጥ ቁልፍ ቦታዎችን ይዘው ሁኔታውን ለቅልበሳ ሲያመቻቹ የነበሩት የኢ.ህ.አ.ፓ-የኢ.ድ.ዮ.- የኢምፔሪያሊዝም ሰርጎገቦችና ቡችሎች ፍጹም ተስፋ አስቆረጣቸው፣ አቅበዘበዛቸው፣ የሚይዙት የሚለቁትን አሳጣቸው። ረቡዕ ከሰዓት በኋላ በዩኒቨርስቲ የተደረገው የተማሪዎች ስብሰባ፣ እንደ ልማዳቸው የኢ.ህ.አ.ፓ ነፍሰገዳዮች አብዮታዊ ተማሪዎችን ገድለው “ድል ይቀዳጃሉ” የሚል ምኞት በነአለማየሁና ኩባንያ ዘንድ ነበር። ግን እዚያም አብዮታዊዎቹ ተማሪዎች ሁኔታውን ስለለወጡት፣ ቅጥርነፍስ ገዳዮቹ “ባንዳዎችን እንጨርሳለን” ከማለት “ባንዳዎቹ ሊጨርሱን ነው!”… ወደ ማለት ተሸጋግረው ስለፈረጠጡ እነአለማየሁ እብድ ሆነው ነበር። የኢ.ህ.አ.ፓ ግልገል ፋሽስቶች የመጨረሻው ምሽግ መውደቁ ስለተሰማቸው የነበራቸው ምርጫ የደርጉን አብዮታዊ አባሎችና የጽ/ቤቱን አባሎች ለማፈንና ለመግደል የመንግሥትን ግልበጣ ለማድረግ መሞከር ነበር። ይህ ተንኮል በአብዮታዊ የደርግ አባሎች ንቃትና ቆራጥ እርምጃ ለመደምስስ መቻሉ ለኢትዮጵያ ሕዝቦች ትግል አንድ ትልቅ አስተዋጾ ነበር። አብዮት ልጆቿን ትበላለችና የአብዮታዊው መኮንን የኮሎኔል ዳንኤል አስፋውና የአብዮታዊ ምሁር የጓድ ሰናይ ልኬ፣ እንደዚሁም የሌሎች የጭቁኖች መውደቅ የኢትዮጵያን ተራማጆች ይበልጥ ቆራጥ፣ ይበልጥ ለመስዋዕት ዝግጁ ያደርጋቸዋል። የነዚህ ጓዶች ደም የኢትዮጵያ ሰፊ ሕዝብ ይበቀልላቸዋል።
በእሁዱ ሰልፍ ሰፊው ሕዝብ አንድ አይነት እርምጃን፣ አንድ አይነት ውሳኔን ጠበቆ ነበር ተብሏል። የአርቡ ሰልፍ ምንም እንኳን በስድስት ሰዓቶች ውስጥ ብቻ የተዘጋጀ ቢሆንም፣ በስፋቱ እንዲያውም ከእሁዱ በልጦ ተገኝቷል። በሐምሌ ወር 1968 እነሲሳይ ሀብቴ አዘጋጅተውት የነበረው የቅልበሳ ሙከራ አሁን በጥር ወር እነአለማየሁ ካዘጋጁት ሙከራ በምንም ያህል አያንስም ነበር። የተወሰደባቸውም እርምጃ እንደዚሁ የማያዳግም ሆኖ ሳለ፣ ያን ጊዜ ወዲያውኑ ሰልፍ ሊደረግ የቻለው በወለጋ ክፍለ አገር ብቻ እንደነበረና አዲስ አበባ ምንም እንዳልተንቀሳቀሰ ይታወሳል።ከሐምሌ ወር ጀምሮ አብዮታችን በውጥረት ውስጥ መግባቱ ቢታወቅም፣ በዚያው መጠን ደግሞ የሰፊው ሕዝብ ንቃተ ህሊና መምጠቁን የአርቡ ሰልፍ በሚገባ አሳይቷል። ሰፊው ሕዝብ በደርጉ ውስጥ የነበረውን ሁኔታ ለመከታተል ብቻ ሳይሆን፣ ስለ ተወሰደውም እርምጃ ፈጣን በሆነ መንገድ አስተያየቱን ለመግለጽ የሚችል መሆኑን በአርቡ ሰልፍ አረጋግጧል።
የአርቡ ሰልፍ ዋና መልዕክት እርምጃውን ስንጠብቀው ነበር፣ አሁንም እንደግፈዋለን ነው። ወዳጅና ጠላትን በሚገባ ለይተናል፣ አስታጥቁንና ለአብዮቱ እንሰዋለን ነው። በተጨማሪም፣ እንደ እሁዱ ሰልፉ ሁሉ፣ የአርቡ ሰልፍ አንድ ትልቅ መልዕክት ምሩን እንከተላለንም ነበር።
በደርጉ ውስጥ የተሰገሰጉት የኢ.ህ.አ.ፓ-ኢ.ዲ.ዩ.-ኢምፔሪያሊዝም ቢችሎች በሕዝቡም ውስጥ ሆነ በሠራዊቱ ውስጥ ምንም ድጋፍ ሳይኖራቸው፣ ከቁጥር የሚገባ ምንም መመርኮዣ እንደሌላቸው እያወቁ፣ በቅጥረኛ ነብሰ ገዳዮች ድርጊት ብቻ በመተማመን፣ በተለመደው የንዑስ ከበርቴው የቀኝ ክንፍ ድንፋታ ተነፋፍተው ለጥቂት ወራት የአብዮቱን ሂደት ክፉኛ አደናቅፈዋል። አሁንም ቢሆን በጥቂት አብዮታዊያን ላይ ነፍሰገዳዮቻቸው አደጋን ሊያደርሱ ይችላሉ። ግን ከንግዲህ የኢትዮጵያ አብዮት የወደፊት ግስጋሴ የሰፊው ሕዝብ ጉዳይ ስለሆነ፣ ቅጥር ነፍሰገዳዮቹ የፈለጉትን ያህል ቢራወጡ እነርሱ ብቻቸውን አብዮቱን ሊቀለብሱት አይችሉም።
ይህንን ማለት ግን ከፀረ አብዮት ኃይሎች ጋር የሚደረገው ትንንቅ አልቋል፣ አክትሟል ማለት እንዳይደለ ግልጽ ነው። ፊውዳሊዝም፣ ኢምፔሪያሊዝምና ቢሮክራሲያዊ ካፒታሊዝም ፈጽሞ እስኪደመሰሱ ድረስ የአብዮት ቅልበሳ አደጋ ሙሉ በሙሉ እንደማይወገድ ተደጋግሞ የተነገረ ስለሆነ፣ አሁን አብዮቱ በአድሃሪዎች የውስጥ አርበኞች ሊቀለበስ አይችልም ማለት፣ እንደገና የጥቂት ወራትን ፋታ ሊያገኝ ይችላል ማለት ብቻ ነው። እንግዲህ ይህንን ፋታ ለማራዘም፣ ለወሳኙ ትግል ዝግጅት ለማድረግና የየእለቱንም ትግል በተቀናበረ መንገድ ወደፊት ለመግፋት አሁን ምን መደረግ አለበት የሚለው ጥያቄ አንገብጋቢ ነው። በኛ አስተያየት የሚከተሉት አራት ነጥቦች ከሥራ ላይ ቢውሉ ለኢትዮጵያ አብዮት ይበልጥ አመቺ የሆነ ሁኔታ ይፈጠራል፡-
1ኛ/ አሁን በተፈጠረው አዲሱ ሁኔታ በመጠቀም በተቻለ ፍጥነት ቢሮክራሲውን ማጽዳት ያስፈልጋል። የነኢ.ህ.አ.ፓ-ኢ.ዲ.ዩ.-ኢምፔሪያሊዝም ደጋፊዎች እና ቡችሎች በመሆን የታወቁትን ቢሮክራቶች ከስልጣን ማስወገድ ብቻ ሳይሆን መቅጣትም ያስፈልጋል። እንደዚሁም፣ በሰፊው ሕዝብና በተራማጆች ላይ የግድያ ሙከራ የፈጸሙትን ቅጥረኛ ነፍሰገዳዮች ያለምህረት መቅጣት የግድ አስፈላጊ ነው። እነኢ.ህ.አ.ፓ- ኢ.ዲ.ዩ.- የኢምፔሪያሊዝም መሳሪያዎች እንደመሆናቸው መጠን፣ የእነርሱን ደጋፊዎችና ቡችሎች በመቅጣት ብቻ ሳይወሰኑ፣ የኢምፔሪያሊዝምን ልዩ ልዩና ቀጥተኛ ኤጀንቶችንም በሚገባ ከቁጥጥር ሥር ማዋል የግድ ያስፈልጋል። ያለበለዚያ አለባብሰው ቢያርሱ በአረም ይመለሱ ይሆናል። ለአብዮቱ ፋታን ለማግኘት አድሃሪዎችን ፋታ ማሳጣት አስፈላጊ ነው።
2ኛ/ አድሃሪዎችን ትጥቅ ማስፈታትና ሰፊውን ሕዝብ፣ በተለይም በቅድሚያ ያዲስ አበባን ሰፊ ሕዝብ ማስታጠቅ ያስፈልጋል። ይህንንም መንግሥት አምኖበት በአርቡ ሰልፍ ላይ ቃል እንደገባበት ይታወሳል።
3ኛ/ ተራማጆች የጠበቀ ህብረትን መፍጠር አለባቸው። ባሁኑ ሰዓት በየድርጅቶቻችን መካከል ባሉት የሁለተኛ ደረጃ ልዩነቶች ላይ ማተኮርና ህብረቱን አለማፋጠን የኢትዮጵያ አብዮት ሂደት እንደማሰናክል ሊቆጠር ይችላል።
4ኛ/ የኢትዮጵያን የወዛደር ፓርቲና የሰፊውን ሕዝብ አብዮታዊ ግንባር በፍጥነት ለመመስረት ከሚያስችሉ ነገሮች አንዱ የዲሞክራሲያዊ መብቶች ለሰፊው ሕዝብ ወገኖች መለቀቅ ነው። እነዚህ መብቶች በፍጥነት መምጣት አለባቸው።
መኢሶን ከመቸውም ጊዜ ይበልጥ በነዚህ እርምጃዎች ከሥራ ላይ መዋል አጥብቆ ይታገላል። የኢትዮጵያ ሕዝቦችን አብዮታዊ እንቅስቃሴ መልካም ቀኖች ይጠብቁታል።ይሁንናም ጎዳናው አሁንም ጠመዝማዛና በብዙ መሰናክሎች የተጋረጠ ይሆናል። እንደእሁድ 22 እና አርብ 27 ያሉትን ውጤቶች ለማግኘት ይበልጥ መድከም፣ ይበልጥ መታገል፣ በቆራጥነት ግን ደግሞ በትዕግሥት ወደፊት መግፋት አለብን ።