ሰሕድ ቁ. 52

የሰፊው ሕዝብ ድምፅ

ቁጥር 52፣    የካቲት 20፣ 1969 

የፅሁፉ ፍሬ ሀሳብ

መኢሶን በዚህ እትም፣ ጥር 1969 በአብዮት ቀልባሽ ኃይሎች ላይ የተወሰደው እርምጃ ለትግሉ ፋታ ቢያስገኝም አብዮቱን ለዘለቄታው ከቅልበሳ አድኖታል ማለት እንዳልሆነ በማብራራት ይጀምርና የወቅቱን ዋና ዋና ችግሮች ይተነትናል። በዚህ ትንተናው ዋናዎቹ ችግሮች፣ የኢኮኖሚው ሁኔታ፣ በአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም ድጋፍና መሪነት አብዮቱን ለመቀልበስ የሚሯሯጠው ቢሮክራሲ፣ የሶማሊያ ሠርጎ ገቦች እንቅስቃሴና የጂቡቲ ጉዳይ እንደሆነ ያብራራል። ለእነዚህ ችግሮች መፍትሄ የሚላቸውን ሃሳቦች ከሰነዘረ በኋላ አብዮቱን ማፋፋም እንደሚያስፈልግና ለዚህም የነቃ የተደራጀና የታጠቀ የሕዝብ ኃይል መገንባት ወሳኝነት ላይ ትኩረት ያደርጋል።

የሰፊው ሕዝብ ድምፅ

ለሰፊው ሕዝብ ሰራተኛ ገበሬ፣ ነጋዴ፣ ወታደር፣ ምሁር መብትና ጥቅም የሚታገል ጋዜጣ

የኢትዮጵያ ሰፊ ሕዝብ ይቅደም

ቁጥር 52                                                                    ቀን 20/06/69

 

አብዮቱን ማፋፋም፣ ለመጨረሻው ፍልሚያ መዘጋጀት።

ማንም ሰው በቀላሉ ሊገነዘበው እንደሚችል ሁሉ፣ በደርግ ውስጥ በነበሩት ቀንደኛ የቀልባሽ ኃይሎች ወኪሎች ላይ በጥር 26/1969 የተወሰደው ቆራጥ አብዮታዊ እርምጃ፣ የኢትዮጵያን አብዮት ለዘለቄታው ከቅልበሳ አደጋ አድኖታል ማለት አይደለም። ለአብዮቱ የጥቂት ጊዜ ፋታን ገዝቷል ማለት ግን ይቻላል። ከዚህ በፊት መኢሶን በየጋዜጣ ቁጥሩ ደጋግሞ እንደገለፀውና እስከመጨረሻውም ሳይሰለች እንደሚገልፀው ሁሉ፣ የኢትዮጵያውያን አብዮት ከቅልበሳ ለዘለቄታው ሊያድንና በአድሃሪ ኃይሎች ሁሉ ድልን አስገኝቶ አዲሲቷን ኢትዮጵያ ለመመስረት የሚችለው ኃይል የነቃ፣ የተደራጀና የታጠቀ ሕዝብ ኃይል ብቻ ነው። ስለሆነም፣ በጥር 26ቱ እርምጃ በተገኘው ውጤት አብዮታውያን ሁሉ ደስ ቢሰኙም፣ ወደፊት መሰራት ያለበት ፖለቲካዊ፣ ርእዮተ ዓለማዊና የድርጅት ሥራ ገና ብዙ መሆኑን፣ ስለዚህም አሁን በተገኘው ድል ፈጽሞ ለመዝናናት እንደማይቻል መታወቅ አለበት። ከፊታችን ተደቅኖ የሚገኘው ተግባር ብዙ ብቻ ሳይሆን ከባድና ውስብስብም ስለሆነ፣ አብዮታዊ አርቆ-ማየትን፣ ቆራጥነትንና ታታሪነትን በይበልጥ ከኛ የሚጠይቅ ነው።

በደርጉ ውስጥ ቁልፍ ቦታዎችን ይዘው የነበሩት ፀረአብዮት ግለሰቦች ቢወገዱምና አብዮቱም በዚህ ምክንያት ጥቂት ፋታን ቢያገኝም፣ ያገሪቷና የአብዮቱ ዋና ዋና ችግሮች አሁንም እንዳሉ ናቸው ለማለት ይቻላል። የኢኮኖሚው ችግር፣ የኢምፔሪያሊዝም ሴራ፣ የቢሮክራሲያዊ ካፒታሊዝም ፀረአብዮታዊ ድርጊቶችና ከነዚህም ጋር የተያያዙ ችግሮች ሁሉ አሁንም አሉ፣ ለወደፊትም ለተወሰነ የታሪክ ወቅት ከኛው ጋር ይቆያሉ።

እነዚህን ችግሮች የኢትዮጵያ አብዮት ሂደት በጥቂት ሳምንታት ወይንም ወራት ውስጥ ይፈታቸዋል ብሎ ማሰብ በከንቱ ምኞት መታለል እና በግለሰብኝነት /ሰብጀክቲቪዝም/ ውስጥ መውደቅ ነው። ችግሮችን እንደማይናዱ ተራሮች አድርጎ መውሰድና የሌላ ትውልድን ሥራ ይጠይቃሉ ብሎ ተስፋ መቁረጥም እንደዚሁ በግለሰበኝነት ውስጥ ይጥላል። ሁለቱም አስተያየቶች የንኡስ ከበርቴውን የደስታና የተስፋ መቁረጥ ተፈራራቂ ጠባዮችን የሚያንፀባርቁ ናቸው። ስለዚህ፣ አብዮታዊያን ራሳቸውም ከአጉል መዝናናትና ከተስፋ መቁረጥም ጠብቀው፣ የነባራዊውን ሁኔታ ጥቁር ነጭ ገጾች ሳያጋንኑ፣ ሳይንሳዊ ትንተናን አድርገው ለሁኔታው ተገቢ የሆኑትን ድርጊቶች መቀየስ ይኖርባቸዋል።

ከአብዮቱ ፊት የተደቀኑት ችግሮች የትኞቹ ናቸው?

ከአብዮቱ ፊት የተደቀነው የመጀመሪያው ችግር የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ሁኔታ፣ በተለይም ደግሞ የከተሞች የኢኮኖሚ ሁኔታ ነው። በተለይ አዲስ አበባ ያለው ከተማ በአሁኑ ወቅት የፀረ አብዮት ኃይሎች ምሽግ ከሆነበት ምክንያት አንዱ የኢኮኖሚ ችግር ነው። ይህንን ችግር ማንም ያውቀዋል፡- የሥራአጥ መብዛት፣ የኑሮ ውድነት፣ የጤፍ አለመገኘትና የዋጋው መናር፣ ወዘተ.። በአገራችን ሰፊውን ሕዝብ ከዳር እስከዳር የሚያንቀሳቀስና የሚመራው፣ በአገር-አቀፍ ደረጃ ስር የሰደደ የወዛደር ፓርቲ ቢኖር ኖሮ፣ ኢትዮጵያውያን እንደ ሩሲያ ሰርቶአደር ሕዝብ ሁሉ፣ አንዱን ዳቦ ለአራት ተካፍለው ለአብዮቱ እስከመጨረሻ እስትንፋሳቸው እንዲታገሉ ባደረገ ነበር። የኢትዮጵያ የታሪክ ደረጃ ጉዳይ ሆኖ፣ የዚህ ዓይነቱ ፓርቲ ገና በጥንስስ ላይ ባለበት ሁኔታ፣ ሰፊው ሕዝብ ለአብዮቱ ሕይወቱን እንዲሰጥ መጠየቁ ብቻ ብዙም አያራምድም። ስለሆነም፣ ይህ ሰፊ ሕዝብ፣ በተለይም በከተማው የሚኖረው ሰርቶአደር ሕዝብ፣ አሁን ያሉትን የኢኮኖሚ ችግሮች ከአብዮቱ ጋር ስለሚያያዝ፣ የግድ ካሁኑ ለችግሮቹ ጊዜያዊ መፍትሄ መገኘት ይኖርበታል። በእርግጥ የኢትዮጵያ ወዛደር “አብዮታችንን በ120 ብር አንሸጥም!” ብሏል። ቢሆንም፣ የሰፊው ሕዝብ ንቃተ ህሊና አሁንም ሰፊው ሕዝብ ለአብዮቱ እንዲሰዋ ዝግጁ ከሚሆንበት ሁኔታ ላይ ገና ስላልደረሰና በሌላ በኩል ደግሞ የፀረ አብዮት ኃይሎች ግፊት አሁንም አይሎ በሚታይበት ወቅት፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ በተለይ ለአዲስ አበባ ሥራአጥና ለጤፍ እጥረት መፍትሄ መገኘት ይኖርበታል። “ነፃና ራሱን የቻለ ኢኮኖሚ” የመገንባቱ ጉዳይ ካሁኑ መጀመር ቢኖርበትም በፊውዳሊዝም-ኢምፔሪያሊዝምና ቢሮክራሲያዊ ካፒታሊዝም ላይ ድል ከተገኘ በኋላ የሚሳካ ነገር እንጂ ዛሬውኑ ሊከናወን የሚችል ነገር ስላይደለ፣ በአሁኑ ሰዓት ሊወሰዱ የሚገቡ ኢኮኖሚያዊ እርምጃዎች ሁሉ ከሁሉም አስቀድሞ ፖለቲካዊ መሆን ይኖርባቸዋል። ማለትም ጥያቄው የአምስት ዓመት ወይንም የአስር ዓመት የኢኮኖሚ ፕላን የማውጣት ሳይሆን ለአብዮቱ የሰፊውን ሕዝብ ድጋፍ ዛሬውኑ ሊያስገኙ የሚችሉ ከአስፈለገ የዛሬ አምስት ዓመት ከጥቅም ውጪ የሚሆኑ የኢኮኖሚ እርምጃዎችን የመውሰድ ጥያቄ ነው። ስለሆነም፣ የኢትዮጵያ አብዮት የዓለም ተራማጅ ኃይሎችን ድጋፍ ባገኘበት በአሁኑ ወቅት ይህንን የጥያቄውን መልክ እነዚህ ተራማጅ እንዲረዱትና ድጋፋቸውን የቃል ብቻ ሳይሆን የግብርም እንዲሆን የማድረጉ ፋንታ የኢትዮጵያ መንግሥትና የኢትዮጵያ ተራማጅ ኃይሎች ነው።

ሁለተኛው ከአብዮቱ ፊት የተደቀነው መሰናክል የአሜሪካ ኢምፒሪያሊዝም ነው። የየካቲት እንቅስቃሴ ከጀመረበት እና በተለይም አብዮታዊ አቅጣጫ ከያዘበት ወቅት ጀምሮ እስካሁን የያንኪ ኢምፒሪያሊዝም ሁለት ጨዋታዎችን በአንድነት ሲጫወት ቆይቷል። ባንድ በኩል በደርጉ ውስጥም ሆነ በቢሮክራሲ ውስጥ ያሉትን ኤጀንቶቹን በማሰለፍ ወይ በደርጉ እንዲገለበጥ ወይም ሙሉ በሙሉ በቁጥጥር ስር እንዲሆን ሲያሴር ቆይቷል። መጀመሪያ በእንዳልካቸው መኮንን፣ ከዚያም በአማን አንዶም፣ ቀጥሎ በእነሲሳይ ሀብቴ አሁን በቅርቡም በእነ ተፈሪ በንቲ አማካኝነት ያካሄዳቸው የቁጥጥር ወይንም የቅልበሳ ሙከራዎች ያረጋግጣሉ። በሌላ በኩል  ግን፣በሶቭየት ህብረት ተጽዕኖ ስር ባለችው ሶማሌያና በርሱ ቁጥጥር ስር በነበረችው ኢትዮጵያ መካከል ባሉት ቅራኔዎች በመጠቀም፣ እንደዚሁም በቀይ ባህር አካባቢ ያለውን ይዞታ ላለማጣት፣ ከዚህ መንግሥት ጋር ግንኙነቱን ለመቁረጥ ስላልፈለገ፣ ምንም እንኳን ጊዜን በመጎተት አሻጥሮችን ቢፈጽምም፣ ለኢትዮጵያ መንግሥት የጦር መሳሪያዎችን መሸጡን አላቆመም።

ጊዜያዊ ወታደራዊ መንግሥትም በበኩሉ የያንኪዎችን አይነት ሁለት ጨዋታ ሲጫወት ቆይቷል ለማለት ይቻላል። በአንድ በኩል፣ መጀመሪያ ላይ፣ ኢምፔሪያሊዝምን በጠቅላላ፣ ስም ሳይጠራ፣ አሁን ደግሞ የአሜሪካ ኢምፔሪያሊዝም፣ “ሲ.አይ.ኤ” እያለ የቃላት ጦርነትን ከፍቶበታል። በሌላ በኩል ደግሞ መሳሪያውን የሚገዛው ከእርሱ ነበር፣ የኢኮኖሚ “እርዳታ”፣ የድርቅ “እርዳታ” ተብሎም ምጽዋት ከእርሱ ተወርውሮለታል። በተለይም ግን የኃይለሥላሴ መንግሥት ከያንኪ ኢምፔሪያሊዝም ጋር የተፈራረማቸውን የኢትዮጵያን የባርነት ውሎች አሁንም አክብሮ ይዟቸዋል። እዚህ ላይ አስተሳሰቡ ተጠናክረን፣ ቀስ በቀስ፣ አዘናግተን፣ ከኢምፔሪያሊዝም ቁጥጥር ስር ነፃ እንወጣለን የሚል ይመስላል።

የያንኪ ኢምፔሪያሊዝምና ጊዜያዊ ወታደራዊ መንግሥት እስከ ዛሬ የያዙትን ጨዋታ፣ ባለፈው ዓመት በአንድ የሰህድ ቁጥር ተገልጾ እንደነበረ ሁሉ፣ የድመትና የአይጥ ጨዋታ ነው። ወይ ድመቷ አይጧን ትበላለች፣ ወይንም አይጧ ታመልጣለች። በአሁኑ ወቅት ይህ ኢምፔሪያሊዝም በአገራችን ውስጥ የሚያካሂዳቸውን ነገሮች ስንመለከት፣ አካባቢው፣ አዝማሚያው፣ ይበልጥ የሚያመቸው ለድመቷ ነው።

ያሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም ከያዛቸውና እላይ ከጠቀስናቸው ሁለት ታክቲኮች የመጀመሪያውን፣ ማለትም ደርግንና አብዮቱን የመገልበጥን ታክቲክ አጥብቆ ይዞታል። ከአደሃሪ የአረብ አገሮች በስተጀርባ ያለው እርሱ ነው። ከነኢ.ዲ.ዩ.-ኢ.ህ.አ.ፓ-ኢ.አል.ኤፍ በስተጀርባ ያለውም እርሱው ነው። ከቢሮክራሲውም በስተጀርባ ያለው እርሱው ነው። ያለኢምፔሪያሊዝም እነዚህ ሁሉ የፀረአብዮት ኃይሎች አሁን የሚፈነጩትን ያህል ባለፍነውና በሰፊው ሕዝብ ወገኖች ላይ አሁን የሚያደርሱትን ጥቃት ባላደረሱ ነበር። የዛሬይቱ ኢትዮጵያና የአብዮቱ ዋና ጠላት ኢምፔሪያሊዝም፣ በተለይም የአሜሪካ ኢምፔሪያሊዝም ነው።

ይሁንናም፣ ይህም እየታወቀ፣ ኢምፔሪያሊዝም በ“አብዮታዊት ኢትዮጵያ” የፈለገውን ነገር፣ በፈለገበት ቦታና ሁኔታ እንደልቡ ይሰራል። ሰፈው ሕዝብና ወገኖቹ ገና ለነፃ ድርጊት በሚታገሉበት ወቅት፣ እርሱ ግን በዚህ ባገራችን የነፃ ድርጊቶች ባለቤት ነበር፣ ነውም።. . .

ሦስተኛው የኢትዮጵያን አብዮት ከውጥረት ውስጥ ያስገባው የሶማሊያ ሰርጎ-ገቦችና የጅቡቲ ጉዳይ ነው። እንደሚታወቀው፣ የሶማሊያ መንግሥት ከስምጥ ሸለቆ በስተምስራቅ ያለውን አገር፣ ማለትም ባሌን፣ ሀረርጌንና የወሎን ምስራቃዊ ክፍል ይዞ እስከ አሰብ ድረስ ያለውን መሬት በሙሉ የሱማሊያ ክፍል ነው ይላል። በመሰረቱም በውጋዴን፣ በባሌ፣ በሲዳሞ፣ የሚገቡት ሰርጎ-ገቦች “የምእራብ ሶማሊያ ነፃ አውጪ ግንባር” ወታደሮች ናቸው ይባላሉ። ግን ደግሞ ኢ.ዲ.ዩም፣ “የኦሮሞ ነጻ አውጭ ግንባርም” የሚባሉበት ጊዜ አለ። ዋናው ቁም ነገር እንግዲህ እነዚህን ሰርጎ-ገቦች የምታስታጥቅና የምታሰማራው ሶማሊያ መሆኗ ነው።

ጅቡቲን በሚመለከተው በኩል ግዛቲቱ ከሁለት ወራት ከኋላ ለሪፍረንደም (ጠቅላላ ድምጽ መስጠት) ትጠራለች፣ የምትመርጠውም ነፃነትን እንደሚሆን ይታወቃል። ከዚህ በኋላ ህግ-አውጪ ሸንጎ ተቋቁሞ፣ አዲስ ምርጫ ይደረግና አገሪቷ ነፃ ወጥታ አዲስ መንግሥት ታቆማለች ተብሎ ይገመታል። ይህም የሚሆነው በሚመጣው ዓመት መጀመሪያ ላይ ነው። ኢትዮጵያን በሚመለከተው በኩል ያለው ችግር፣ የኢትዮጵያ መንግሥት የዚችን የፈረንሳይ ቅኝ ግዛት ነጻ መውጣት ሲያውቅና ምንም አለኝታ በርሷ ላይ እንደሌለው ሲገልፅ፣ ሶማሊያ ግን በህገ መንግሥቷ ጭምር ግዛቲቷ የእርሷ መሆኗን ማስታወቋና እንደ ኢትዮጵያ ምንም አለኝታ የለኝም ለማለት ዝግጁ አለመሆንዋ ነው። ሁኔታው ኢትዮጵያን የሚያሰጋት ሶማሊያ በ“ህጋዊ” መንገድም ሆነ በኃይል ጅቡቲን ይዛ የኢትዮጵያን ጥቅም ከመጻረሯም በላይ ለቀሩት የመሬት ጥያቄዎቿ መንደርደሪያ የጦር ሰፈር ታደርጋለች የሚል ሲሆን፣ የዚህ ዓይነቱ ሁኔታ ከተፈጠረ፣ ኢትዮጵያ ባሏት ችግሮቿ ላይ በተጨማሪ ወደ ጦርነት ተጎትታ ትገባለች የሚል ነው።

እንግዲህ የኢትዮጵያን አብዮት በአሁኑ ወቅት ወጥረው የያዙትን ነገሮች በአጠቃላይ ስንመለከት፣ እነዚህ ከዚህ በላይ የተጠቀሱት ሦስት ነገሮች ሆነው እናገኛቸዋለን- ማለትም የኢኮኖሚ ሁኔታ፣ ኢምፔሪሊዝምና የሶማሊያ መንግሥት የመስፋፋት ምኞት። ኢምፔሪሊዝም በኢኮኖሚ ችግራችንና ከሶማሊያ ጋር ባለን ቅራኔ የሚጠቀም ከመሆኑም በላይ፣ እነ ኢ.ዲ.ዩ-ኢ.ህ.አ.ፓ-ኢ.አል.ኤፍንና ፊውዶ-ቡርዧ ቢሮክራሲውን በቀጥታም ሆነ በእጅ አዙር በአብዮቱ ላይ አሰልፏቸዋል። ስለሆነም፣ እላይ እንዳልነው ሁሉ፣ ዋናው ጠላት እርሱው ነው። ኢ.ዲ.ዩ. በበጌምድር ውጊያን የጀመረው የኢትዮጵያን ክፍለተአገር አንድ በአንድ ከሰሜን ወደ ደቡብ እይዛለሁ ብሎ አይደለም። ኢ.ህ.አ.ፓም ተራማጆችን እያደነ የሚገድለው በእርግጥ በዚህ መንገድ የመንግሥትን ስልጣን ለመያዝ እችላለሁ ብሎ አይደለም፤ አይችልም። የኤርትራ ግንባሮች ጥቃታቸውን የሚያፋፍሙት በእርግጥ ለዘለቄታው ኤርትራን ገንጥለን እንቆያለን ብለው ስለሚያስቡ አይመስለንም። ሶማሊያም የሰርጎ-ገቦች ድርጊቶችን የምታስፋፋው እና በጅቡቲም ላይ አጠራጣሪ ሁኔታን የምትፈጥረው በእርግጥ ከአዋሽ በታች ያሉትን አገር ገንጥላ ለመውሰድና ለማቆየት እንደምትችል ስለምታምን አይደለም። የነዚህ ፀረአብዮት ኃይሎች ሁሉ አላማ በአዲስ አበባ የመንግሥት ለውጥን በማምጣት፣ አብዮቱን በአጭሩ ለመቅጨትና ኢትዮጵያ ወደ ቀድሞ የጨለማ ሥርዓት ተመልሳ፣ ደካማ፣ የተከፋፈለችና ወደኋላ የቀረች አገር ሆና እንድትቆይ ለማድረግ ነው።

ጥያቄው እንግዲህ የእነዚህ ፀረ አብዮት ኃይሎች ምኞት ከግቡ እንዳይደርስ ምን መደረግ አለበት ነው? አሁን በደረስንበት ሁኔታ፣ የኢትዮጵያ አብዮት ከፀረ አብዮት ኃይሎች ለመከላከልና ወደፊት ለመግፋት ምን እርምጃዎችን መውሰድ ይኖርበታል?

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ዲሞክራሲያዊ የአብዮት ፕሮግራም ፊውዳሊዝም፣ ኢምፔሪያሊዝምና ቢሮክራሲያዊ ካፒታሊዝም መደምሰስ እንዳለባቸውና በነርሱም መቃብር ላይ አዲሲቷ ኢትዮጵያ እንደምትገነባ ይገልፃል። ይህንን አብዮታዊ ግዴታ የሚያከናውነው የነቃ፣ የተደራጀና የታጠቀ ሕዝባዊ ኃይል፣ ማለትም የሰፊው ሕዝብ ግንባርና ይህንንም ግንባር የሚመራ የወዛደር ፓርቲ ናቸው። በሌላ በኩል ደግሞ፣ በዛሬይቱ ኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ሦስቱን ፀረ ሕዝብ ኃይሎች መደምሰስ ማለት ኢ.ዲ.ዩን፣ኢ.ህ.አ.ፓን፣ኢ.ኤል.ኤፍን እና ቢሮክራሲውን መደምሰስ ማለት እንጂ ሌላ ምንም ትርጉም የለውም። እነዚህን ደግሞ ለመደምሰስ መሳሪያው- ማለትም የነቃ፣ የተደራጀና የታጠቀ የሕዝብ ኃይል፣ ማለትም ሕዝባዊ አብዮታዊ ግንባርና ይህንንም ግንባርንማ ይህንንም የሚመራው ፓርቲ- በአሁኑ ወቅት እንደሌለ ግልጽ ነው ስለሆነም፣ በደርግ ውስጥ የነበሩት ፀረአብዮት ኃይሎች ስለተደመሰሱ አብዮታችን ከተከላካይነት ወደ አጥቂነት የተሸጋግሯል ተባለ እንጂ፣ የተባለውን የነቃ፣ የተደራጀና የታጠቀ የሕዝብ ኃይል አሁንም ገና አላገኘንም። ስለዚህም ነው የወቅቱ ታክቲካዊ መመሪያ “አብዮቱ ማፋፋም፣ ለመጨሻው ፍልሚያ መዘጋጀት” መሆን ያለበት። ምን መደረግ አለበት ለተባለው ጥያቄ መልሱም ይህ ነው፤- አብቱን መፋፋም ለመጨረሻው ፍልሚያ መዘጋጀት።

አብዮቱን ማፋፋም ማለት ምን ማለት ነው?

አብዮቱን ማፋፋም ማለት ባጭሩ የምንፈልገውን የነቃ፣ የተደራጀና የታጠቀ የሕዝብ ኃይል ለመገንባት የሚያስችሉንን እርምጃዎች ሁሉ መውሰድ ማለት ነው። ይህንን ኃይል እንዳናዘጋጅ መሰናክል የሆኑትን ነገሮች ካሁኑ ማስወገድ ማለት ነው። በተጨባጭ መንገድ የሚከተሉት እርምጃዎች አብዮቱን ያፋፍሙታል፡-

1ኛ/ ለጊዜው የኢኮኖሚ ችግሮች በተቻለ ፍጥነት ጊዜያዊ መፍትሄዎችን ማግኘት። ከዚህ በላይ እንደተገለፀው ሁሉ፣ ጥያቄው አሁኑኑ የአምስት ወይም የሰባት ወይንም የአሥር ዓመታትን ፕላን ማውጣትና ያንን ከሥራ ላይ ለማዋል መታገል ሳይሆን፣ የኢኮኖሚ እርምጃዎቹ ለፖለቲካ ግቦች ለአጭር ጊዜም ቢሆን እንዲያገለግሉ የማድረግ ነው። ፊውዳሊዝም-ኢምፔሪያሊዝምና ቢሮክራሲያዊ ካፒታሊዝም ፈጽሞ ሳይደመሰሱ የመጀመሪያውን ዓይነት ፕላን ከሥራ ላይ ለመዋል ይቻላል ብሎ ማሰብ ከንቱ ነው። ሰለረጅም ጊዜው የኢኮኖሚ እድገት አሁን ማሰብ እና አንዳንድ ዝግጅቶችን መጀመር አያስፈልግም ለማለት ሳይሆን፣ አሁን አጣዳፊው ጥያቄ የሥራ አጡን ቁጥር መቀነስ፣ የእህል እጥረትን ለማስወገድ መጣር፣ የዋጋ መናርን መቆጣጠር፣ የመሳሰሉትን እርምጃዎች የመውሰድ ጉዳይ ነው።

2ኛ/ አድሃሪዎችን በተለይም በአዲስ አበባ የመሸጉትን አድሃሪዎች ትጥቅ ማስፈታትና የሰፊውን ሕዝብ መታጠቅ ማፋጠን ያስፈልጋል። በተለይ በአዲስ አበባ ከተማ የተባሉትን የአብዮት ጥበቃ ኮሚቴዎችን ማቋቋም ማፋጠን ያስፈልጋል። በጉያችን ስር የመሸጉትን አድሃሪዎች በቁጥጥር ስር ለመዋል እስካልቻልን ድረስ የውጭ ጠላቶችን ለመቋቋም እንደማንችል በጥር 22ቱ ሰላማዊ ሰልፍ ላይ በግልጽ ተነግሯል። የአብዮት ጥበቃ ኮሚቴዎችን መቋቋምና የሰፊውን ሕዝብ መታጠቅ ከሚያዘገዩት ነገሮች አንዱ በሰፊው ሕዝብ ላይ መንግሥት ያለው እምነት አነስተኛነት ከሆነ፣ ይህንን ባፋጣኝ ለማስቀረት መቻልና በሰፊ ሕዝብ ላይ ሙሉ እምነትን ለመመስረት መቻል አለበት።

3ኛ/ በብሔራዊ ዴሞክራሲያዊ አብዮት ፕሮግራሙ እንደተነገረው ሁሉ ፊውዳሊዝምን፣ ኢምፔሪያሊዝምንና ቢሮክራሲ ካፒታሊዝምን ለመደምስስና አብዮቱን ከግቡ ለማድረስ የሚቻለው የወዛደሩ ፓርቲ አመራር የተገኘ እንደሆነ ነው ተብሏል። የፖለቲካ አመራር ጥያቄ የአብዮቱ ወሳኝ ጥያቄ ነው። ስለሆነም፣የወዛደሩን ፓርቲ በአንድ ጊዜ በተአምር ለመፍጠር ስለማይቻል መጀመሪያ በኢትዮጵያ ያሉት ማርክሲስት-ሌኒኒስት ድርጅቶች ህብረትን ፈጥረው፣ ከዚያም እየተቀራረቡና እና ይበልጥ እየተባበሩ ሄደው ውህደትን ማስከተል ይኖርባቸዋል። የዚህ አይነቱ ህብረት ለአብዮታዊ ግንባርም መፈጠር መንገድ ይከፍታል። የተራማጆችን ህብረት መፍጠር ሁሉም ሰው በቃል ቢደግፈውም በገቢር ግን በአሁኑም ወቅት እንኳን ብዙ ፀረ ህብረት ሥራዎች ይካሄዳሉ። የኢትዮጵያ አብዮት አሁን ባለበት ሁኔታ፣ መኢሶን የሚያቀርበው አሳብ ዲሞክራሲያዊና ሃቀኛ ውይይት ሽኩቻን፣ አሉባልታንና የስም መጥፋት ዘመቻን እንዲተኩ ነው። እነዚህኞቹን መቀጠልና የህብረትና የመቀራረብ አዝማሚያዎችን ማደናቀፍ ፍፁም አብዮታዊ ኃላፊነትን መዘንጋት ይሆናል።

4ኛ/ ሰፊውን ሕዝብ ባጭር ጊዜ ውስጥ ከዳር እስከዳር ለማንቀሳቀስም ሆነ የተባለውን የተራማጆች ሕብረትን ለማቃናትና ለማፋጠን የዲሞክራሲያዊ መብቶች ለሰፊው ሕዝብ ወገኖች መለቀቅ እጅግ በጣም አስፈላጊ እንደሆነ በጋዜጣችን ተደጋግሞ ተነግሯዋል። እነዚህ መብቶች ካልተለቀቁ አብዮቱ ይህን ያህልም የመፋፋም ፍጥነትን አያገኘም። በፕሮግራሙ ውስጥ ጊዜያዊ ወታደራዊ መንግሥት የነዚህን መብቶች መሰጠት “አጣዳፊ” ከተባሉት እርምጃዎች ውስጥ ከመመደቡም በላይ፣ ፀረ ሶስት ለሆኑ ድርጅቶች ሁሉ ማቴሪያላዊና የሞራል ድጋፍ እንደሚሰጥ ገልጿል። ከአብዮታውያን ጋር ተሰልፎ የነዚህን መብቶች በትክክል ከሥራ ላይ ማዋል የሚቃረኑትን ኃይሎች ለመደምሰስ ቃል ገብቷል፤ በግብርም ይህንኑ እንዳሳየ ነው። ስለዚህም፣ የዲሞክራሲያዊ መብቶች ለሰፊው ሕዝብ ወገኖች መለቀቅ አብዮቱን ከሚያፋፍሙት ዋና ዋና ነገሮች አንዱና ዋናው መሆኑ ታውቆ በዚህ በኩል ፈጣን እርምጃ እንዲወሰድ ያስፈልጋል።

5ኛ/ ኢምፔሪያሊዝምና ቢሮክራሲያዊ ካፒታሊዝምን ዛሬውኑ ለመደምሰስ ባይቻልም፣ እነዚህን ፀረአብዮት ኃይሎች በተቻለ ፍጥነት ከቁጥጥር ስር ማዋል ያስፈልጋል። ማለትም፣ ኢምፔሪያሊዝምን በሚመለከተው በኩል የኃይለሥላሴ ፊውዶ-ፋሽስት መንግሥት የተፈራረማቸውን ፀረሕዝብና ፀረ ነፃነት “የጋራ መከላከያ” ውሎችን በመሠረዝ፣ ያንኪዎች አሁን የሚያካሄዱትን በነፃና ሳይመረመሩ የፈለጉትን ነገር– መሳሪያ፣ ሃሺሽ፣ ብር አስገብተው ለነኢህአፓ የሚያከፋፍሉትን እንዲያቆሙ ማድረግ፣ ሚሲዮኖችን በቁጥጥር ስር ማዋል፣ የኢምፔሪያሊስት አገሮችን ቱሪስቶች ከነ ዶላራቸው እንዲቀሩብን ማድረግ፣ የኤምባሲዎችን ባገር ውስጥ የመዘዋወር ችሎታ መወሰንና መቆጣጠር፣ የኢትዮጵያን ግለሰቦችንና የውጭ ኤምባሲ ሠራተኞችን ግንኙነቶች መቆጣጠር፣ ወዘተ ማለት ነው። ቢሮክራሲያዊ ካፒታሊዝምን በሚመለከተው በኩል፣ የታወቁ አድሃሪ የኢ.ዲ.ዩ አባላትና የኢምፔሪያሊዝም ቅጥረኞች የሆኑትን ቢሮክራቶች ከስልጣን ማባረር፣ ተራማጆችን ለማስገደልና ልዩ ልዩ አሻጥሮችን በመፈፀም ላይ ለሚገኙት አብዮታዊ ቅጣት መስጠትን የመሳሰሉ እርምጃዎችን መውሰድ ያስፈልጋል። ባንዳንድ ቦታ ላይ የተቀመጡት ቢሮክራቶች ፀረአብዮተኞች መሆናቸው እየታወቀ፣ “ጠንካራ ሠራተኞች ናቸው” ወይም “የሥራ ችሎታ አላቸው እየተባለ፣ እዚያው ባሉበት እንዲፀኑ ተደርጓል። ጥያቄው ዛሬ የሥራ ችሎታ ሳይሆን የሚሰራው ለአብዮት ነው ወይንስ ለፀረአብዮት የሚለው ስለሆነ፣ በመንግሥት በዚህ በኩል ለአብዮቱ በቆሙ ግን ይህን ያህልም ልምድ በሌላቸው ግለሰቦች ላይ የበለጠ እምነትን ማኖር ይገባዋል።

እነዚህ ከዚህ በላይ የተጠቀሱት እርምጃዎች በርግጥ አብዮቱን ያፋፍሙታል። ግን ደግሞ በዚያውም ለመጨረሻው ፍልሚያ የሚያዘጋጁ ጠንካራ የጥገና /ሪፎርም/ እርምጃዎች መሆናቸውን በቀላሉ ለመገንዘብ ይቻላል። ይሁንናም፣ ለተባለው የመጨረሻ ፍልሚያ የሚያዘጋጁንን የፀረአብዮት ኃይሎችን መመከቻ እርምጃዎችን እንደሚከተለው ለመጠቆም ይቻላል።

ሀ/ ከዚህ በላይ ተደጋግሞ እንደተጠቀሰው፣ የኤርትራ ግንባሮችና ኢ.ዲ.ዩ. በሰሜን ኢትዮጵያ የሚካሄዱት ፀረሕዝብና ፀረአብዮት ጦርነት የመጨረሻውን መፍትሄውን የሚያገኘው አብዮቱ ተፋፍሞ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ እንዳንድ ሰው ሆኖ ሊነሳባቸው ሲችል ነው። በነዚህ ፀረአብዮት ኃይሎች ላይ ድልን መቀዳጀት ኢምፔሪያሊዝምን መደምሰስ ነው ተብሏል። እንግዲህ፣ እስከዚያ ድረስ እነዚህ ኃይሎች ለመመከት የሚቻለው በተለይ የኤርትራን ክፍለሃገር በሚመለከተው በኩል፣ እስከተቻለ ድረስ እዚያ የተሰማራውን ጦር በሰውም በትጥቅም በማጠናከር፣ በጦሩ ውስጥ ያሉትን አድሃሪ መኮንኖች በመመንጠርና ለሰራዊቱ አብዮታዊ ትምህርትን በመስጠት፣ ባስተዳደሩ፣ በፀጥታውና በሌሎችም የመንግሥት መስሪያ ቤቶች የተሰገሰጉትን ጉቦኛ ቢሮክራቶች በማስወገድ፣ የኮሚሽኑን ሥራ በማፋጠንና በእርሱም አማካይነት የክፍለአገሩን ሰፊ የሕዝብ ድጋፍና እምነት እያጠናከሩ በመሄድ ነው። በተጨማሪም፣ የአፋር ብሔረሰብ ጉዳይ እና የኤርትራ ጉዳይ የተያዘ ስለሆነ፣ ይህ ብሄረሰብ በአሁኑ ጊዜ በጥብቅ የሚጠይቀውን ያስተዳደር አንድነቱን ከሥራ ላይ በማዋል፣ የተገንጣይ ድርጅቶቹን ጥቃት ለመከላከል ይቻላል።

ለ/ ኢ.ዲ.ዩ የተተከለበትን የቤጌምድር ክፍለአገር በሚመለከተው በኩል የክፍለአገሩን ሕዝብ በሰፊው በማንቀሳቀስና ሕዝባዊ ጦሩን በማጠናከር፣ የመለዮለባሽና የሲቪል ካድሬዎች በብዛት እንዲሰማሩ በማድረግ ኢ.ዲ.ዩን ለመቋቋም ይቻላል። በተጨማሪም ለክፍለአገሩ አዋሳኝ የሆኑትን ጎጃምን፣ ወሎንና ትግራይን በማጠናከር– ማለትም የገበሬ ማህበራትና ሕዝባዊ ጦሮችን በፖለቲካና በጥቅም በመንከባከብ– የኢ.ዲ.ዩ.ን መስፋፋት ለመግታትና ምናልባትም ኢ.ዲ.ዩን ለማባረር ይቻላል።

ሐ/ የሱማሊያን ሰርጎ-ገቦች፣ የጅቡቲን ጉዳይና ሌሎችንም ያገሪቷን የውጭ ችግሮች በሚመለከተው በኩል፣ በዲፕሎማሲው መስክ ኢትዮጵያ ብዙ ድሎችን ልታገኝ ትችላለች። በአሁኑ ሰዓት የዓለም ተራማጆች ሁሉ የኢትዮጵያን አብዮት ለመደገፍና በማቴሪያልም ለመርዳት ዝግጁ እንደሆኑ ይታወቃል። በአብዮቱ ፕሮግራም በተጠቀሰው መሰረት ኢትዮጵያ ብሔራዊ ክብሯንና ነፃነቷን በምንም መንገድ ሳታስነካ፣ በእኩልነትና በመከባበር ላይ የተመሰረቱ ግንኙነቶችን ከውጪው አለም ጋር መፍጠር ይኖርባታል። አብየቱ ስለተከበበና በብዙ ችግሮች ውስጥ ስለገባን የአገራችንን ክብርና ነፃነት ለምንም አይነት ጊዜያዊ ጥቅም መሸጥ የለብንም።

እንግዲህ ለማጠቃለል ያህል፣ ከኢትዮጵያ ብሄራዊ ዲሞክራሲያዊ አብዮት አንፃር ሲታይ፣ አሁን አብዮቱ በደረሰበት ደረጃ፣ መመሪያ ሊሆነን የሚገባው “አብዮቱን ማፋፋም፣ ለመጨረሻው ፍልሚያ መዘጋጀት” የሚለው ነው። አብዮቱን ለማፋፋም ለኢኮኖሚ ችግሮቻችን ጊዜያዊ መፍትሄዎችን በጥድፊያ ማግኘት፣ አድሃሪዎችን ትጥቅ ማስፈታትና ሰፊውን ሕዝብ ማስታጠቅ፣ የተራማጆችን ህብረት በፅኑ መሠረት ላይ መገንባት፣ ዴሞክራሲያዊ መብቶችን ለሰፊው ሕዝብ ወገኖች ማስገኘትና ኢምፔሪያሊዝምንና ቢሮክራሲያዊ ካፒታሊዝምን በቁጥጥር ስር ለመዋል መቻል ያስፈልጋል። እነዚህ እርምጃዎችም አብዮቱን ከማፋፋማቸውም በላይ ለመጨረሻው ፍልሚያ ያዘጋጃሉ። ይሁንናም፣ በተጨማሪ፣ ለመጨረሻ ፍልሚያ ለመዘጋጀት በእነዚህ ላይ ብቻ ማተኮር ስለማይበቃ፣ የኤርትራን ተገንጣዮችና ኢ.ዲ.ዩ.ን አሁን ባለው ኃይልና ለመሰብሰብም፣ ባጭር ጊዜ ውስጥ ለማሰማራትም የሚቻሉ ኃይሎች ማቋቋም አለብን። እንደዚሁም የኢትዮጵያ አብዮት አለማቀፋዊ ድጋፍ እንዲያገኝ በዲፕሎማሲና በውጭ ፕሮፓጋንዳ በኩል መጠናከር ያስፈልጋል።

የአብዮቱን ችግሮች በጥቂት ሳምንታት ውስጥ ለመፍታት ይቻላል በሚል እምነት መቸኮል፣ ወይንም ደግሞ ችግሮቹን የማይናዱ ተራሮች አድርጎ በመውሰድ የተስፋ መቁረጥ በንኡስ ከበርቴው ግለሰበኝነት ውስጥ መውደቅ ነው። መኢሶን በበኩሉ አብዮቱን ለማፋፋምና ለመጨረሻው ፍልሚያ ለመዘጋጀት መወሰድ ያለባቸው እርምጃዎች ለሰፊው ሕዝብ ከማስታወቅና እራሱም ተገቢዎቹን ትግሎች ሁሉ ከማድረግ አይቆጠብም።

አብዮቱን እናፋፍም፣ ለመጨረሻው ፍልሚያ እናዘጋጅ!
ዲሞክራሲያዊ መብቶች ለሰፊው ሕዝብ!
ሃቀኛ የተራማጆች ህብረትን እንፍጠር!
ሰፊው ሕዝብ ያሸንፋል!
Scroll to Top