የሰፊው ሕዝብ ድምፅ
ቁጥር 60፣ ሐምሌ 21፣ 1969
የፅሁፉ ፍሬ ሀሳብ
መኢሶን በዚህ ቁጥሩ፣ ከኢትዮጵያ ማርክሲስት ሌኒኒስት ድርጅቶች(ኢማሌድህ) ምስረታ በፊትና በኋላ ሲደረጉ የነበሩ ውይይቶችና ክርክሮች፣ እንዲሁም በአባል ድርጅቶቹ ስምምነት የተደረባቸውንና ገና እልባት ያላገኙ ጉዳዮችን ይዘረዝራል። ከእነዚህ የልዩነት ነጥቦች መሃል አንዱ የብሄረሰቦ ጥያቄ ሲሆን ሌላው ደግሞ በዴሞክራሲ መብቶች መታወጅ ላይ እንደነበረ በማስታወስ በነዚህ ጥያቄዎች ላይ መኢሶን ያለውን አቋም ያብርራል። ህብረቱና ህብረቱ የቆመለት ዓላማ ግቡን እንዲመታ፣ እያንዳንዱ አባል ድርጀት በሀቅና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ የድርጅቱ ውሳኔዎች፣ መርሃ ግብሩና የድርጊት ፕሮግራሙን በስራ ላይ ማዋል እንዳለባቸው ያስገነዝባል።
ከዚህ ጋር ተያይዞ ለሰፊው ሕዝብ ድምጽ አንባቢዎች የቀረበው “የኢትዮጵያ ማርክሲስት ሌኒኒስት ድርጅቶች ህብረት የድርጊት ፕሮግራም” በህብረት ኮሚቴው 30ኛ ስብሰባ ላይ፣ ሐምሌ 12 ቀን 1969 ተነቦና ታርሞ የፀደቀ ፕሮግራም ነው። እያንዳንዱ ድርጅት የራሱን መግቢያ ፅፎ ፕሮግራሙ በሰፊው እንዲሠራጭ የተወሰነው በዚሁ በ30ኛው ስብሰባ ላይ ነው። አንባቢ እንግዲህ ከሁኑ “የትኛው የህብረት ኮሚቴ፣ የምን 30ኛ ስብስብ?” ብሎ ጥያቄዎችን እንደሚያቀርብ ምንም ጥርጥር የለውም።
እንደሚታወቀው ባለፈው የካቲት ወር 1969፣ አምስት ሕቡዕ ድርጅቶች- ማለትም የመላ አትዮጵያ ሶሻሊስት ንቅናቄ (መኢሶን)፣ የኢትዮጵያ ጭቁኖች አብዮታዊ ትግል (ኢጭአት)፣ የወዛደር ሊግ (ሊግ)፣ አብዮታዊ ሰደድ (ሰደድ)፣ ማርክሳዊ ሌኒናዊ ሪቮሉሽናዊ ድርጅት (ማሌሪድ)፣አንድ የጋራ መግለጫና መርሀግብር አውጥተው አሰራጭተው ነበር። ከዚያን ጊዜ ወዲህ ሕቡዕ ድርጅቶችም በየልሳኖቻቸው፣ እንደዚሁም የተለያዩ አብዮታዊ ግለሰቦችና ቡድኖች በመንግሥት የዜና ማሰራጫ መሳሪያዎች፣ ደግመው ደጋግመው የተራማጆችን ህብረት መጠንከር ጠይቀዋል። በተለይም በአዲስ ዘመን ጋዜጣ አንዳንድ የጥናት ቡድኖች እና ግለሰብ ፀሐፊዎች በዛሬይቱ ኢትዮጵያ የጠላት ሰፈር እንዴት እንደተባበረ ከገለጹ በኋላ የወዳጅ ሰፈር፣ ይልቁንም ደግሞ የኢትዮጵያ ተራማጅና ማርክሲስት-ሌኒኒስት ቡድኖች ለምን በአፋጣኝ እንደማይተባበሩ፣ ለምን የየካቲት የጋራ መግለጫ እና መርሀግብር በተግባር ተተርጉሞ እንደማይታይ፣ ቅሬታ በተሞላበት አነጋገር ደጋግመው ጠይቀዋል። “የኢትዮጵያ ተራማጆች ተባብረዋል ይባላል፣ ምን ሠሩ?” የሚለው ጥያቄ በየዕለቱ ያጋጥማል። የዚህ አይነቱን ጥያቄ የሚያቀርቡና በሃቅ ለአብዮቱ ሰፈር መጠናከር የሚቆሙ፣ ስለ አብዮቱ የወደፊት እድል የሚጨነቁና የየበኩላቸውንም አስተዋጽኦ ለማድረግ የሚጓጉ ሁሉ፣ የህብረት ኮሚቴ የሚባል ነገር እንዳለ እና ይህም ኮሚቴ እስከ ዛሬ ድረስ 30 ጊዜ የተሰበሰበ መሆኑን ማወቃቸው እጅግ በጣም ያጠራጠራል። ለነዚህም ጓዶች ለመኢሶን አባላትና ደጋፊዎች፣ እንደዚሁም ባጠቃላይ ለሰፊው ሕዝብ፣ ህብረቱ ከየት ተነስቶ አሁን ከምን ላይ እንደደረሰ የሚገለጽበት ወቅት አሁን መጥቷል ብለን እንገምታለን። የዚህ አይነቱ ገለጻ ቢደረግ፣ አንዳንድ ሀቀኛ ጓዶች ከዜና ማጣት የተነሳ የሚያቀርቡት ሂስና የሚሰማቸውን ቅሬታ ምናልባት ይቀንስ ይሆናል።
የኢትዮጵያ ማርክሲስት-ሌኒኒስት ድርጅቶች ኅብረት የተቋቋመው ከረጅም ጊዜ ፖለቲካዊና ርእዮተአለማዊ ትግል በኋላ እንጂ ባለፈው የካቲት ወር የጋራ መግለጫው በወጣበት ጊዜ ድንገት የተፈጠረ አይደለም። በህብረቱ ትግል ድርጅቶች መካከል፣ ከዛሬ ዓመት ግድም ጀምሮ ረዘም ያሉ የሁለት ወገን /ባይላተራል/ ውይይቶች ተካሂደዋል። አንዳንዶች ድርጅቶች፣ ለምሳሌ መኢሶንና ሊግ፣ በጽሁፎችም ጭምር ሀሳቦች ተለዋውጠዋል፤ ክርክሮችም አካሄደዋል።
የዚህ ዓይነቱ የእርስ በርስ ውይይት ለስምንት ወራት ያህል ከተካሄደ በኋላ ባለፈው ጥር 24 ቀን 1969፣ ማለትም ከጥር 22ቱ የሰፊው ሕዝብ አብዮታዊ ቁጣ ሰልፍ በኋላና ለጊዜው ነግሰው የነበሩት እነአለማየሁ ሃይሌ ከመወገዳቸው 2 ቀን አስቀድሞ የአምስቱ ሰድርጅቶች ወኪሎች የተገኙበት የመጀመሪያው የህብረት ስብሰባ ተደረገ። ምንም እንኳ በትክክል ውይይት ተደርጎበት ስም ባይሰጠውም፣ “የህብረት ኮሚቴ” በመባል የታወቀው አካል በዚህ ዕለት፣ ከአንዱ ድርጅት በስተቀር የቀሩት ሁለት ሁለት ጓዶችን የወከሉበት የ9 አባላት ጉባኤ ነው። በግንቦት 20 ቀን 1969፣ በ18ኛው የኮሚቴው ስብሰባ ላይ፣ እያንዳንዱ ድርጅት ሶስት ሶስት ጓዶችን በመወከል፣ ኮሚቴው እንዲሰፋ ተደርጎ፣ አሁን አስራ አምስት አባላትን ይይዛል።
እንደተባለው የመጀመሪያው የኅብረት ስብሰባ የተካሄደው በጥር 24 ቀን ሲሆን፣ የኮሚቴው ሥራ በማያቋረጥ አኳኃን ቀጥሎ፣ በስምንተኛው ስብሰባ፣ የካቲት 18 ቀን 1969 የጋራ መግለጫውንና መርሀግብሩን ኮሚቴው አጸደቀ። እነዚህ ወዲያውኑ በየድርጅቱ ተባዝተው ተሰራጩ። ከጥር 24 እስከ የካቲት 18 ድረስ፣ በሦስት ሳምንታት ጊዜ ውስጥ በኛ አቆጣጠር ስምንት ስብሰባዎች ሲካሄዱ ከየካቲት 18 እስከ ሚያዚያ 18 ድረስ ማለትም በሁለት ወራት ጊዜ ውስጥ፣ የተካሄዱት ስብሰባዎች ሁለት ብቻ ናቸው። ከዚያም እንደገና ለሦስት ሳምንታት ያህል ምንም ስብሰባ ሳይኖር ቆይቶ፣ አስራ ሁለተኛው ስብሰባ ግንቦት 10 ቀን ይደረግና እስከ ወሩ መጨረሻ ድረስ አሥራ ሁለት ሌሎች ስብሰባዎች ይካሄዳሉ። በሰኔ ወር አንድም ስብሰባ ሳይኖር ይቆይና፣ አሁን ከሐምሌ አንድ ጀምሮ ደግሞ በተፋጠነ ሁኔታ ስብሰባው በመቀጠል ላይ ይገኛል።
የጋራ መግለጫውና መርሃ ግብሩ ከፀደቁ በኋላ፣ ወዲያውኑ የተጀመረው ሥራ የህብረቱን የመተዳደሪያ ደንብ ማርቀቅ ነበር። ይህ ደንብ ረቅቆ ለአንድ ወር ተኩል ያህል እንደዚሁ ከተቀመጠ በኋላ፣ የመጀመሪያው ውይይት የተከፈተበት ሚያዝያ 18 ቀን 1969 ነበር። በግንቦት ወር የተካሄዱት 13 ስብሰባዎች የዋሉት ይህን ያህልም በደንቡ ላይ ለመከራከር ሳይሆን፣ በየካቲት 18 መግለጫ ውስጥ በፀደቁት የውይይት እና የስምምነት ነጥቦች ላይ እንደገና በመከራከር ነበር!!
ይህ የቀኖችና የስብሰባዎች ቁጥር ድርደራ አንባቢን እንደሚያሰለች ብናውቅም፣ እነዚህ የጠቀስናቸው ከእነርሱ ብቻ አንኳን በመነሳት፣ አንባቢ ሁለት ቁም ነገሮችን ለመገንዘብ እንደሚችል በማመን ነው። እነዚህም፣ አንደኛው፣ በህብረቱ አባል ድርጅቶች መካከል በተካሄዱት ውይይቶች ውስጥ፣ በሥራ ብዛት የመገናኛ ጊዜ መጥፋቱ ብቻ ሳይሆን የፖለቲካዊ ችግሮች እንደነበሩና፣ ሁለተኛ፣ እንደዚያም ሆኖ ግን፣ ለሰፊው ሕዝብ በዝርዝር ያልተገለፁና በፖለቲካዊ ይዞታቸው በጣም የዳበሩ ውይይቶች እንደተካሄዱ ነው። ጊዜው እና ሁኔታው ፈቅደው በዚህ በኩል ያለው ሥነጽሁፍ በይፋ በሚወጣበት ወቅት ሰፊው ሕዝብ በተጨባጭ መንገድ ዲያሌቲክንና የመደብ ትግልን ያጠናበታል ብለን እናምናለን። በሌላ በኩል ደግሞ፣ በሀቅና በአብዮታዊ መንፈስ ተገፋፍተው፣ በአዲስ ዘመን ላይ በየጊዜው ስለተራማጆች ህብረት፣ ስለውህደት፣ ስለ ወዛደሩ ፓርቲ፣ ስለ ሕዝባዊ አብዮታዊ ግንባር …… አስፈላጊነት በመቆርቆርና አንዳንዴም በምሬት የሚጽፉት ጓዶችና የጥናት ቡድኖች ይህንን ሥነጽሑፍ ቢያገኙት ኑሮ ስላሉት ችግሮች ምንኛ በተገነዘቡና የየበኩላቸውም አስተዋጽኦ ምንኛ ባበረከቱ ነበር!!
ከጥር 24 ጀምሮ እስከዛሬ፣ ማለትም ከዚህ ጋር የተያያዘው የህብረቱ የድርጊት ፕሮግራም እስከ ፀደቀበት 30ኛው ስብሰባ ድረስ፣ ፈረንጆች እንደሚሉት ሁሉ፣ በድልድዩ ስር ብዙ ውሃ አልፏል። ብዙ ነገሮች ተለዋውጠዋል። ከጥር 24 በኋላ፣ በጥር 26 የእነዓለማየሁ ኃይሌ መወገድ ከዚያም የአብዮቱ ከተከላካይነት ወደ አጥቂነት መሸጋገር፣ እንደገናም በአብዮት ሰፈር ውስጥ የውዥንብር መስፈንና የጸረአብዮቱ ሰፈር መጠናከር ተፈራርቀው መጥተዋል። የኢትዮጵያን ማርክሲስት ሌኒኒስት ድርጅቶች፣ የህብረቱን ድርጅቶች በሚመለከተውም በኩል፣ የጠበቀ መቀራረብና ደግሞም መራራቅ፣ ጓዳዊ ትብብርና ደግሞም የእርስ በርስ ሽኩቻ፣ አብዮታዊ አንድነት መንፈስና ደግሞም ክፉኛ እርስ በርስ የመጠራጠርና፣ በህብረቱም ውስጥ በልዩ ልዩ ነጥቦች ላይ የድርጅቱ የአሰላለፍ ለውጦች ታይታዋል። እንግዲህ አሁን ያለንበት ደረጃ የመቀራረብ እና አገሪቷንና አብዮቱን እየከበቡና አየቦረበሩ ሁኔታውን ለቅልበሳ በሚያመቻቹት ኃይሎች ላይ በጋራ የመሰለፊያ ደረጃ ነው። የህብረቱ የድርጊት ፕሮግራም ይህንን ተግባር ለማከናወን እንዲያስችለን እየታቀደ ሲሆን ወደ ፕሮግራሙ ይዘት ከማለፋችን በፊት አንዳንድ መሰረታዊ ጉዳዮችን በቅድሚያ ማንሳት ያስፈልጋል ብለን እናምናለን።
1. የቆዩ የውይይት ነጥቦች
ከህብረቱ የመጀመሪያ ስብሰባ፣ ማለትም ከጥር 24 በፊትም ቢሆን፣ መኢሶን ከሕብረቱ አባል ድርጅቶች ጋር ለስምንት ወራት ያህል ውስጥ ያካሄዳቸው የሚመለከታቸው ነጥቦች በየካቲት የጋራ መግለጫ ውስጥ ከወጡት ነጥቦች የተለዩ አይደሉም። እነዚህም የኢትዮጵያ አብዮት መሠረታዊ ጥያቄዎች የሆኑት፣ የጊዜው ሁኔታ ትንተና፣ የስልጣን አያያዝ ጥያቄ፣ የዲሞክራሲያዊ መብቶች ጥያቄ፣ የብሄረሰቦች ጥያቄ፣ ስለ ኢትዮጵያ መለዩ ለባሽና ሕዝባዊ ጦር ስለሚመሠረትበት ሁኔታ፣ ስለ ወዛደሩ ፓርቲ አመሰራረት ናቸው። በዚህ ነጥቦች ላይ በህብረት ኮሚቴው ውስጥም ሆነ ከዚያ በፊት ተደጋግሞ ውይይት የተደረገው፣ የህብረቱ አባል ድርጅቶች የመኢሶንን አቋም ቀደም ብለው ስላላወቁት ሳይሆን፣ ወይንም አባል ድርጅቶቹ የመኢሶንን ፕሮግራም ስለላዩትና የሰፊው ሕዝብ ድምጽን ይዘቶች ስላልተከታተሉት ሳይሆን፣ በአንድ በኩል በእነዚህ ነጥቦች ላይ ሙሉ መግባባት እንዲኖርና በሌላ በኩል ደግሞ ልዩነቶችም ካሉ እነርሱን የምናስወግድበትን መንገድ በጋራ ለመቀየስ እንድንችል ነበር።
በነዚህ መሰረታዊ የኢትዮጲያ አብዮት ጥያቄዎች ላይ፣ በየካቲት ወር በወጣው የጋራ መግለጫ ውስጥ የየድርጅቱ አቋም፣ በአንድ ነጥብ፣ ማለትም በብሄረሰቦች ጥያቄ ላይ እንጂ በሌላው ሁሉ ላይ አንድ እንደሆነ ተገልጿል። የኢትዮጵያን ህብረተሰብ ዋና ዋና ቅራኔዎችና የጊዜውን ሁኔታ በሚመለከተው በኩል አንድ አይነት አስተያየት ነበረን። የወዛደሩን ፓርቲ አመሰራረት በሚመለከተው በኩል፣ “በኢትዮጵያ ሁኔታ አሁን በህቡዕ የሚታገሉት ማርክሳዊ ሌኒናዊ ቡድኖችና ሌሎችም በትግሉ ውስጥ የሚፈጠሩ ቡድኖች ተዋህደው እንጂ አንድ ድርጅት ብቻውን ተስፋፍቶና አድጎ ወይንም ደግሞ ከውስጡ ፀረወዛደር የሆኑ ኃይሎችን አፅድቶ ብቻውን ወደ ወዛደር ፓርቲነት የሚለውጥበት ሁኔታ የለም” በሚለው ላይ ተስማምተው ነበር። ምንም እንኳ መኢሶን ስለ ወዛደር ፓርቲ አፈጣጠር የተባለውን “የውህደት ቴኦሪ” ያቀረበው ከማንኛውም ድርጅት በፊት በየካቲት 1967 መሆኑን በፕሮግራሙም ውስጥ ይኸው ነገር በግልጽ እንደሰፈረ፣ እንደዚሁም ድርጅታችን ለተራማጆች ህብረት ጥሪ እንዳደረገ ቢታወቅም፣ በዚያን ጊዜ የዚህ አረፍተ ነገር ሁለተኛ ክፍል የተጨመረው፣ በአንዳንድ የሕብረቱ ድርጅቶች በኩል መኢሶን ብቻውን ወደ ወዛደር ፓርቲ ለመለወጥ ይፈልጋል የሚል ጥርጣሬ ስለነበረ ነው። ይሁንናም፣ ከጋራ መግለጫውም ወዲህ ከነበሩት ሁኔታዎችና ከተካሄዱት ውይይቶች እንደሚታየው ሁሉ፣ መኢሶን ቢምልና ቢገዘትም፣ ስለዚሁ ጉዳይ ደጋግሞ ቢጽፍም፣ በተግባርም ለህብረትና ለውህደት የሚታገል መሆኑን ቢያሳይም፣ ጥርጣሬው ፈጽሞ ሊወገድ ባለመቻሉ፣ ባንዳንድ አካባቢዎች በሰበብ በአስባቡ በዚሁ ጥያቄ ላይ ዘመቻዎች ተካሄደውብናል።
የዲሞክራሲያዊ መብቶችን ጥያቄ በሚመለከተው በኩል፣ የድርጅታችን አቋም ብቻ ሳይሆን የሌሎቹም ድርጅቶች አቋሞች በየፅሁፎቻቸው ተደጋግሞ ተገልጸዋል። ሁሉም “ዲሞክራሲያዊ መብቶች ለጭቁኖች ያለገደብ” የሚለውን መፈክር፣ በሞላ ጉደል ከተፈጠሩበት ቀን ጀምሮ ለማለት ይቻላል፣ ሲያስተጋቡ ቆይተዋል። በጋራ መግለጫውም ውስጥ የሚከተለው ሰፍኖ ይገኛል፣-
“…. በአሁኑ ወቅት አብዮቱን ለመቀልበስ ያሰፈሰፉትን በይበልጥ ለመቋቋም በስውር ታፍነው የሚሰሩ ተራማጅ ድርጅቶች ትግላቸውን በይፋ ለማካሄድ እንዲችሉና በተለይ ደግሞ ሕዝባዊ የአብዮታዊ ግንባር ለመመስረት የሚያስችሉትን ዲሞክራሲያዊ ፓርቲዎችና ሰፋፊ ድርጅቶች ለማቋቋም እንዲችሉ ባስቸኳይ የዲሞክራሲያዊ መብቶች ለጨቁኖች ያለገደብ መታወጅ አለባቸው። ለዚህም የኢትዮጵያ ማርክሲስት ሌኒኒስቶች የጋራ ትግል ያደርጋሉ።”
ይህ አቋም ፍጹም አብዮታዊ እንደሆነና የኢትዮጵያን ሕዝቦች የጊዜውን አጠዳፊ ጥያቄ እንደሚያስተጋባ ግልፅ ስለሆነ፣ መኢሶን በዚህ የጋራ አቋም ላይ ሲፀና አንዳንድ የሕብረቱ ድርጅቶች ግን ማፈግፈግ የጀመሩ ይመስላል። ይህንን ከታች እንመለስበታለን።
የመንግሥትን ስልጣን በሚመለከተው በኩል፣ የየካቲቱ የጋራ መግለጫ ፍጹም ማርክሳዊ ሌኒናዊ የሆነ አቋምን ያዘለ ስለሆነ፣ መኢሶን ቀድሞም ዛሬም በዚያን አቋም ላይ ፀንቷል። የመንግሥትን ስልጣን መያዝ ያለበትና የሚችልም አንድ ድርጅት ወይም ቡድን ሳይሆን የነቃ፣ የተደራጀና የታጠቀ ሰፊ ሕዝብ ነው። የነቃ፣ የተደራጀ፣ ሰፊ ሕዝብ ማለት ደግሞ ማርክሲዝም ሌኒኒዝም የሚመራ የደርግ ፓርቲና በዚህ ፓርቲ አመራር ስር የቆሙ ሕዝባዊ አብዮታዊ ግንባርና ሕዝባዊ አብዮታዊ ጦር ያሉት ሕዝብ ማለት ነው። እነዚህ ሦስት መሳሪያዎች እስከሌሉት ድረስ የኢትዮጵያ ሰፊ ሕዝብ ፊውዳሊዝምን፣ ኢምፔሪያሊዝምንና ቢሮክራሲያዊ ካፒታሊዝምን ሊደመስስ አይችልም። እነዚህን ሦስት ጠላቶች ካልደመሰሰ ደግሞ የመንግሥትን ስልጣን ለመያዝ፣ ለመደላደልና አዲስ ህብረተሰብን ለመገንባት ፈጽሞ አይችልም። ድርጅታችን ለዚህ አይነቱ የሕዝብ ስልጣን እንደሚታገልና ይህም ትግል ደግሞ የረጅም ጊዜ መራራ ትግል እንደሚሆን ዛሬ ሳይሆን ግን በጨለማው የኃይለሥላሴ ዘመን አምኖበት ሰፊውን ሕዝብ ሲቀሰቅስበት የኖረ የፖለቲካ መስመር ነው። ይሁንናም፣ የቀኝም ሆነ የግራ የመኢሶን ተቃዋሚዎች ይህንን የድርጅታችንን አቋም እያጣመሙ፣ ነጩን ጥቁር፣ ጥቁሩን ነጭ እያሉ፣ ለማንም ሀቀኛ ተመልካች ግልጽ የሆነውን ነገር በአሉባልታ ጉም እየሸፋፈኑ፣ መኢሶን በአቋራጭ ስልጣን ለመያዝ ይፈልጋል በማለት በኛና በሌሎች ተራማጅ ድርጅቶች መካከል ጥርጣሬን ለመፍጠር ሲፍጨረጨሩ ቆይተዋል፤ እየተፍጨረጨሩም ናቸው።
የኢትዮጵያን መለዮለባሽና የወደፊቱን ሕዝባዊ አብዮታዊ ጦር አመሰራረት በሚመለከተው በኩል በጋራ መግለጫ
ውስጥ በሰፈረው ነጥብ ሙሉ በሙሉ እናምንበታለን። “…. ይህንን ሕዝባዊ አብዮታዊ ጦር ከወዛደሩ፣ አርሶ አደሩ፣ ከሌሎች ተራማጅ ኃይሎችና አሁን ካለው መለዮ ለባሽ ለአብዮቱ ከቆመው ወገን ማቋቋም የሚቻልበት ሁኔታ አለ።” ይላል መግለጫው። ከዚህ ጋር ተያይዞ የቀረበው የድርጊት ፕሮግራምም በመሠረቱ ይህንን አስተሳሰብ የሚያስተጋባ ሲሆን፣ ከየካቲት ወዲህ ሕዝባዊ ሠራዊት፣ ማለትም ከአርሶአደሩ የመነጨ ሠራዊት ስለተገነባ፣ የወደፊቷ ሕዝባዊ አብዮታዊ ጦር ከዚህኛው ኃይል እንደሚያገኝ ይታመናል። ሕዝባዊ አብዮታዊ ጦር እንዲመሠረት ለማድረግ እጅግ አስፈላጊ ከሆኑት ነገሮች አንዱ የሶሻሊዝምን ርዕዮተዓለም በመደበኛው መለዮለባሽና በሕዝባዊ ሠራዊቱ ውስጥ በሰፊው ማስገባት ነው። ስለሆነም፣ እንደ ሌሎች ማርክሲስት ሌኒኒስት ድርጅቶች ሁሉ፣ መኢሶንም ለዚሁ መታገል ይቀጥላል።
በህብረቱ አባል ድርጅቶች መካከል ሙሉ ስምምነት ያልተደረገበት አንድ ነጥብ ቢኖር፣ የብሔረተሰብ ጥያቄ ነው። በጋራ መግለጫ ውስጥ እንደተጠቀሰው ሁሉ፣ “በዚህ ጥያቄ ላይ ለወደፊቱ ሰፊ የሆነ ውይይት እና ክርክር ለማድረግና ወደጋራ አቋም ለመድረስ ቡድኖቹ ተስማምተዋል።” ይሁንናም፣ ውይይቱ ገና በሚገባ ተጀምሯል ለማለት በማይቻልበት ሁኔታ፣ ይህ ጥያቄ በመኢሶን ላይ ዘመቻ ከሚካሄድባቸው ነጥቦች አንዱ ሆኖ ቆይቷል። እንመለስበታለን።
የወዛደር ፓርቲ አመሰራረት፣ ዲሞክራሲያዊ መብቶች ጥያቄ፣ የመንግሥት ስልጣን ጉዳይ፣ …. ወዘተ. እነዚህ ከላይ የተጠቀስናቸው ነጥቦች በሙሉ፣ የቆዩ የውይይት ነጥቦች ናቸው። ባለፈው ዓመት የኢትዮጵያ ብሄራዊ ዲሞክራሲያዊ አብዮት ፕሮግራም ሊታወጅ ሰሞኑን ሲታይ በነበረው የዲሞክራሲ ሽውታ፣ እነ አዲስ ዘመን በ25 ሳንቲምና ለዚያውም በስንት ሽሚያ ይሸጡ በነበረበት ወቅት፣ እንኳንስ ሕቡዕ ድርጅቶች ቀርተው ያልተደራጀውም ሰፊ ሕዝብ ቢሆን፣ ከነዚህ የውይይት ነጥቦች በትላልቆቹ ላይ ሰፊ ክርክር አካሂዷል።
ይሁንናም፣ እነዚህን የቆዩ የውይይት ነጥቦች የጋራ መግለጫው ለመጨረሻ ጊዜ አከራካሪ ያደረጋቸውና ከዚያም ሁሉም ድርጅት ይበልጥ እርስ በርስ ከሚተማመንበት ደረጃ ላይ ይደርሳል ተብሎ ሲጠበቅ፣ ከላይ እንደተጠቀሰው ሁሉ፣ መግለጫ ወጥቶ በሦስተኛው ወሩ ነጥቦቹ እንደገና ለውይይት እስከ መቅረብ ደርሰዋል። ይህም የሆነበት ዋናው ምክንያት በእነዚህ ነጥቦች ላይ የእያንዳንዱ ድርጅት አቋም ግልጽ ሳይሆን መቅረቱ ሳይሆን፣ በድርጅቶቹ መካከል የመጠራጠር መንፈስ ሊጠፋ ባለመቻሉ ነው። መኢሶን በልዩ ልዩ እትሞቹ ደጋግሞ እንደገለፀው ሁሉ፣ ይህ ጥርጣሬ ሊጠፋ ያልቻለው ህብረተሰባችን ገና ከፊውዳላዊ ሥርዓት የአስተሳሰብ ዘዴዎች ባለመላቀቁና ዴሞክራሲያዊ መብቶቹም ሆኑ ዲሞክራሲያዊ ያስተሳሰብና የአሰራር ዘዴዎች በፍጹም ያልተለመዱ በመሆናቸው ነው። በዚህ አይነቱ ህብረተሰብ ውስጥ ሰዎች ያንድን ድርጅት አላማ “የሚገምቱት” በተጨባጭ መንገድ ድርጅቱ በወሰደው ግልጽ አቋምና በተጨባጭም መንገድ በሚሰራው፣ ማንም በቀላሉ ሊያየው በሚችለው እንደ ፀሐይ በጠራ ድርጊቱ ሳይሆን፣ ሰዎች በሚያወሩት አሉባልታ፣ በሃሜት፣ በተንኮለኞች የነገር ሽረባ ላይ ተመስርተው ነው። እነዚህ “የመገመቻ” ዘዴዎች ደግሞ ከሳይንሳዊ የአመለካከትና የአሠራር ዘዴዎች፣ ከዳይሌክቲካዊና ማቴርያሊስት አቀራረብ እጅግ በጣም የራቀ እና የሚቃረኑትም ዘዴዎች ናቸው። የነገሩ እምብርት እንግዲህ ይህ ሆኖ ሳለ የኢትዮጵያ አብዮት በተቀየሰለት ፕሮግራም መሰረት ግቡን እንዲመታ ከተፈለገ፣ ፊውዳላዊ ያስተሳሰብና የአሠራር ዘዴዎችን ለማሸነፍ መቻል ይኖርብናል። ለዚህም ፍቱን የሚሆነው መድኃኒት የዲሞክራሲያዊ መብቶች ለሰፊው ሕዝብ መታወቅ ነው። ያለነዚህ መብቶች፣ ያለ ሰፊው ሕዝብ በሙሉ ተሳትፎ፣ በኢትዮጵያ ማርክሲስት ሌኒኒስት ድርጅቶች መካከል ያሉትንና ወደፊትም እስከ ውህደታችን ድረስ ሊፈጠሩ የሚችሉትን ልዩነቶች ለመፍታት የማይቻል ነው ባይባልም እጅግ በጣም ብዙ ችግሮች ይኖራሉ፤ ረጅም ጊዜንም ይፈጃል።
2. እውነተኛ የልዩነት ነጥቦች
ባለፈው የካቲት ወር የጋራ መግለጫው ከመውጣቱ በኋላም ሆነ ከዚያ በፊት፣ በመኢሶንና ባንዳንድ የህብረቱ አባል ድርጅቶች መካከል እውነተኛ የልዩነት ነጥብ ሆኖ የቀየረው የብሄረሰቦች ጥያቄ ነው። ከነዚህ ድርጅቶች ጋር በፕሮግራሞቻችን ደረጃ ልዩነቶች አሉ። ግን ይህ ብቻ ሳይሆን፣ በቲኦሪው ደረጃና እንደዚሁም በዛሬይቱ ኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ጥያቄውን እንዴት መመልከት አለብን በሚለው ላይ ልዩነቶች አሉ። ይሁንናም፣ እስከዛሬ ድረስ፣ ድርጅታችን ከማንኛውም ሌላ የህብረቱ አባል ድርጅት ጋር የይፋ ክርክር በጽሁፍ አልጀመረም። ለምን?
ድርጅታችን በብሄረሰብ ጥያቄ ላይ በተለይና በሌሎችም አንዳንድ ጥያቄዎች ላይ ባጠቃላይ የይፋ ክርክርን ያልጀመረው፣ የኢትዮጵያ አብዮት አሁን በደረሰበት ደረጃ፣ ለአብዮቱ ወደፊት መግፋት እና ለተራማጆች የተፋጠነ ህብረት ሲባል፣ ከልዩነት ነጥቦች ይልቅ በስምምነት ነጥቦች ላይ ማተኮሩ ይበልጥ ስለሚጠቅምና እንደዚሁም አብዮቱ እየገፋ ሲሄድ የልዩነት ነጥቦቹ እየጠሩ ሊሄዱ ይችላሉ በሚል ነበር። ይሆነናም የእርስ በርስ ውይይቶቹም ሆኑ የህብረት ውይይቶች በተካሄዱበት ወቅት ሁሉ፣ ያለንን አስተያየት ለሌሎች ድርጅቶች ጓዶቻችን ከመሰንዘር ፈጽሞ አልተቆጠብንም። በፅሁፍ ክርክር ለመክፈት የመቆጠብ አቋማችንን ግን ሌሎቹ ከኛ ጋር ያስተሳሰብ ልዩነት የላቸው ጓዶች የተረዱልን አይመስለንም። ስለሆነም፣ በኛ ግምት ስተተኛ ናቸው የምንላቸው ነጥቦች በሰፊው መሰራጨታቸው ብቻ ሳይሆን፣ አንዳንዶቹን እንዲያውም ወደመንግሥት አቋም እስከመለወጥ ድረስ ደርሰዋል።
የብሄረሰቦች ጥያቄና ለርሱ የተሰጠው የሪጅናል ኦቶኖሚ መልስ ከነዚህ አይነት ነጥቦች ውስጥ አንዱ ነው። በብሔረሰብ ጥያቄ ላይ የመኢሶን ፕሮግራም ይዘት በእኛ አስተያየት ፍጹም ማርክሳዊ ሌኒናዊ ስለሆነ፣ የዚህን አስተያየት ተቀራኒ የሚያሳምነን ሰው ወይንም ድርጅት እስኪመጣ ድረስ በእርሱ አንፀናለን። ሪጅናል ኦቶኖሚን በመፈክርና በመፍትሄ ደረጃ የሚያቀርቡት ድርጅቶች አንዳንዴ የሚሉን፣ “የፕሮግራም አቋማችሁ ልክ ነው፤ ግን አሁኑኑ ‘ተግባራዊ መፍትሄን’ ማቅረብ አለባችሁ” ነው ከዚያም የራሳቸውን አቋም ትክክለኛነት ለማሳመን ሲፈልጉ ስታሊን ሪጅናል ኦቶኖሚን መርጧል፣ ሪጅናል ኦቶኖሚ አማራጭ የሌለው መፍትሄ ነው….. ወዘተ ይላሉ።
በመሠረቱ ግን እንድንከራከርበት ያስፈልጋል ከተባለ፣ ለአንድ ማርክሲስት ሌኒኒስት ድርጅት፣ የብሄረሰቦችን መብት በገደብ የማወቅ ጉዳይ በፍጹም አብዮታዊ አይደለም። ብሄረሰቦች የራሳቸውን እድል የሚወሰን መብት አላቸው ማለት፣ ብሄረሰቦቹ ከፈለጉ ከአንድ ከተወሰነ ግዛት ተገንጥለው የራሳቸው መንግሥት እስከማቋቋም ድረስ መብት አላቸው ማለት እንደሆነ ሌኒንና ስታሊን ደግመው ደጋግመው አስተምረዋል። በዚያውም ግን ይህንን መብት ማወቅ ማለት ደግሞ ብሔሮች ወይንም ብሄረሰቦች ሁሉ ይገንጠሉ ማለት እንዳይደለም ያስተምሩናል። እንዲያውም ይህንን መብት፣ ይህንን ምንም ገደብ ሊደረግበት የማይገባ መብትን በቅድሚያ ማወቁ በብሔሮች ወይንም በብሄረሰቦች መካከል ፍጹም እኩልነትና እንዳለና ለዚህም እኩልነት እንደሚታመን ስለሚያረጋግጥ፣ በአንድ በኩል ብሄረሰቦች ይበልጡን አንድነትን እንዲሹ ያደርጋቸዋል፤ በሌላ በኩል ደግሞ የብሄረሰብን እንቅስቃሴዎች ከመሬት ከበርቴዎችና ከሌሎቹም አድሃሪ መደቦች ቁጥጥር ስር ያወጣቸዋል። ስታሊን “ዳይሌክቲካዊ የምርምር አቀራረብ የሚያስፈልገው አንድ ነገር ቢኖር፣ እርሱም የብሔሮች ጥያቄ ነው” የሚለው እነዚህን መሰረታዊ የመነሻ ነጥቦች በማስታወስ ነው።
በዚህ በብሔረሰቦች ጥያቄ ላይ በሌላ ጊዜና ቦታ በሰፊው እንመለስበታለን እዚህ ላይ ግን ስላለን ልዩነቶች አንዳንድ ነጥቦችን ብቻ አንስተን እንለፍ።
አንደኛ፣ የብሄረሰቦች ጥያቄ፣ እንደ ሌሎች የዲሞክራሲያዊ መብቶች ጥያቄዎች ሁሉ፣ እውነተኛና ዘላቂ መፍትሄውን ሊያገኝ የሚችለው የመንግሥት ስልጣን በሰፊው ሕዝብ እጅ ሲገባ ብቻ ነው።
ሁለተኛ፣ ስታሊን ሪጅናል ኦቶኖሚን የሚመርጠው በአንድ ግዛት ውስጥ ለመቆየት በቅድሚያ ምርጫ ለሚያደርጉት ብሄሮች ወይንም ብሔረሰቦች ነው። ማለትም መጀመርያ የብሔሮች የመገንጠል መብት ይታወቅና ነው ወደ መፍትሄ ሽግግር የሚደረገው። ደግሞም መፍትሔው አንድ ብቻ፣ ለምሳሌ ሪጅናል ኦቶኖሚ ብቻ፣ ሳይሆን ሌሎችም አሉ። ዋናው ቁም ነገር ግን የያንዳንዱ ብሄር ወይንም ብሄረሰብ የፈለገውን አይነት መፍትሄ ለመምረጥ የመቻል መብቱ መታወቅ ነው።
ሶስተኛ፣ ስታሊን ደጋግሞ እንደሚያስተምረን ሁሉ፣ የብሄሮችን ጥያቄ በሚመለከተው በኩል ጊዜ ከተጨባጩ የታሪኩ ሁኔታ መነሳት አለብን እንጂ እንደዚሁ “ተግባራዊ መፍትሄን ማቅረብ አለብን” በሚል፣ በራስ ላይ ሰው ሰራሽ በሆነ መንገድ በተጫነ ግዴታ ይህንን ወይንም ያንን “መፍትሄ” ለማቅረብ መጣደፍ የለብንም። የኢትዮጵያን ታሪክና ህብረተሰቦቿ ያሉበትን ደረጃ በትክክል ብናጤን፣ ይህቺ አገር ከዛሪስት ሩሲያ ቢበልጥ እንጂ በላነሰ መንገድ “የብሄረሰቦች እስር ቤት” ሆና እንደኖረች እንረዳለን። በኢትዮጵያ ጭቁን ብሔረሰቦች ላይ በፊውዳላዊው ሥርዓት የተፈጸሙት እጅግ በጣም አሰቃቂ ስለነበሩ፣ ዛሬም ቢሆን በጨቋኝና በተጨቋኝ ብሄረሰቦች መካከል ብዙ ቂም፣ ጥርጣሬ እና ጥላቻ አለ። በዚህ አይነቱ ሁኔታ ማርክሲስት ሌኒኒስቶች ቅስቀሳቸውን ማተኮር ያለባቸው በብሄረሰቦች ሙሉ የእኩልነት መብቶች ላይ ነው። ስለዚህም ነው መኢሶን “ተግባራዊ መፍትሄ” የሚባለውን ነገር እንደ ሁኔታውና፣ እንደጊዜው፣ እንደመፍትሄ ጠያቂው ብሔረሰብ አይቶ መወሰንን የሚመርጠውና በአሁኑ ወቅት ይበልጡን በእኩልነትና በአንድነት ላይ ቅስቀሳውን የሚያተኮረው።
የኤርትራን ጥያቄ በሚመለከተው በኩል፣ መኢሶን የክፍለ ሃገሩን ከኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት መገንጠል እንደሚቃወም ደጋግሞ በየፅሁፉ አቋም ቢወስድም፣ ደግሞም በተለይ የግንቦት ስምንቱን የጊዜያዊ ወታደራዊ መንግሥት የፖሊሲ ውሳኔ በሙሉ ልብ ደግፎ መግለጫ ቢያወጣም፣ አንዳንድ ድርጅቶችና ግለሰቦች፣ መኢሶን የኤርትራን መገንጠል ይደግፋል በማለት በየአካባቢው የሐሰት ዘመቻን አካሂደውብናል። በኤርትራ ጥያቄ ላይ አሁንም ቢሆን መኢሶን የግንቦት 8ን የጊዜያዊ ወታደራዊ መንግሥትን የፖሊሲ ውሳኔ በመደገፍ፣ ችግሩ ሰላማዊ መፍትሄን እንዲያገኝ ጠይቋል። በእርግጥ በአሁኑ ወቅት የኤርትራ ተገንጣይ ድርጅቶች በተለያዩ ደረጃዎች የኢምፔሪያሊዝምና የአረብ አድሃሪ መንግሥታት መሳሪያዎች ሆነው አብዮቱን ለመቀልበስ ከሚፈልጉ አድሃሪዎች ጋር ተሰልፈዋል። ይሁንና ሰፊው የኤርትራ ሕዝብ መገንጠልን አይፈልግም። ስለዚህም፣ በአሁኑ ወቅት በመካሄድ ላይ ባለው ትግል ውስጥ፣ የኤርትራን ሰፊ ሕዝብ ድጋፍ ለማግኘት መታገል፣ በተቻለ መጠን ይህ ሕዝብ እስከ ዛሬ በተቀበለው ስቃይ ላይ አሁንም እንደገና እንዳይመታ መጠንቀቅ፣ የተገንጣይ ድርጅቶቹ መካከል ያሉትን ቅራኔዎች በመጠቀም እነርሱን ብቸኛ ማድረግ፣ እነዚህ ድርጅቶች ውስጥ ካሉት ተራማጆች ጋር ውይይትን ለመክፈት መጣጣርና አድሃሪዎችን ደግሞ በኃይል መምታት ያስፈልጋል።
ባለፈው የካቲት ወር የኢትዮጵያ ማርክሲስት ሌኒኒስት ድርጅቶች የጋራ መግለጫ በወጣበት ወቅት፣ በኛና ባንዳንድ የህብረቱ አባል ድርጅቶች መካከል የነበረ እውነተኛ የልዩነት ነጥብ የብሄረሰብ ጥያቄ ብቻ ነበር ለማለት ይቻላል። የኢትዮጵያ አብዮት በጣም ፈጣን ነው ተብሏልና፣ ካለፈው ግንቦት ወዲህ ደግሞ ሌሎች የልዩነት ነጥቦች ብቅ ብቅ ማለት የጀመሩ ይመስለናል። “ቢሮክራሲ ይውደም”፣ “የነቃ የተደራጀ፣ የታጠቀ የሰፊው ሕዝብ አመጽ ያሸንፋል” ብለን ከአመት በላይ ሁላችንም አንግበናቸው የቆየን መፈክሮች ወደ ልዩነት ነጥብነት እየተለወጡ የሄዱ ይመስላል። ይሁንናም፣ እነዚህ ገና በጥቁርና ነጭ የመጨረሻ መልካቸውን ይዘው አልመጡምና እነርሱን ለጊዜው ወደ ጎን ትተን፣ በዲሞክራሲያዊ መብቶች ላይ በመካሄድ ላይ የሚገኙትን ክርክሮች መመልከቱ ይጠቅማል። እዚህ ላይ፣ ከጋራ መግለጫው ከዚህ በላይ የተጠቀሰውን አንቀጽ እንደገና ተመልሶ አንባቢ እንዲያጤነው እንጋብዛለን።
መግለጫው “ባስቸኳይ ዲሞክራሲያዊ መብቶች ለጭቁኖች ያለገደብ መታወጅ አለባቸው” ይላል የእነዚህ መብቶች መታወጅ ለምን እንደሚያስፈልግ ምክንያቶች ሲሰጥም 1. “በስውር ታፈነው የሚሰሩ ተራማጅ ድርጅቶች “አብዮቱን ለመቀልበስ ያሰፈሰፉትን አድሃሪያን በይበልጥ ለመቋቋም እንዲችሉ፣ 2. ትግላቸውን በይፋ ለማካሄድ እንዲችሉ 3. ዴሞክራሲያዊ ፓርቲዎችንና ሰፋፊ ድርጅቶችን ለማቋቋም እንዲችሉ ነው ይላል። ከመርሃ ግብሩ 13 ነጥቦችም ሁለተኛው “ይህንን የሰፊውን ሕዝብ መንቃትና በየፈርጁና በየደረጃው መደራጀት ለማገዝ አስፈላጊ የሆኑት ዲሞክራሲያዊ መብቶች በአስቸኳይ እንዲለቀቁ በህብረት መታገል።” ብሏል።
“ዲሞክራሲያዊ መብቶች ለጭቁኖች ያለገደብ” የሚለውን መፈክር ቢያንስ ቢያንስ ለአንድ አመት ሁሉም ድርጅት ሲያስተጋባው ቆይቷል። ዛሬ ግን አንዳንዶቹን ድርጅቶች ይህ መፈክር በልዩ ልዩ ምክንያቶች ይህ መፈክር ይቀፋቸው ጀምሯል። ለምሳሌ የወዛደር ሊግ ልሳን ወዝ ሰኔ 17 ቀን በወጣው 32ኛው ቁጥሩ፣ “ያለገደብ የሚለው ሀረግ አሁንም ቢሆን አሻሚና የዲሞክራሲ ትርጉም ጽንሰ ሀሳብን ያዝላል” እና መፈክሩ “የዲሞክራሲ መብቶች ለጭቁኖች” በሚለው ይተካ የሚል ሀሳብ አቅርቧል። በገደብ ያለ ገደብ፣ ለምን ለማን፣ የሚለው ክርክር ባለፈው ዓመት በጥቂት ወራት ዲሞክራሲ ሰፍኖ በነበረበት ወቅት በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ብዙ ተተችቶበት ያለቀለት ነገር መሆኑን ስናስታውስ፣ ሊግ አሁንም ይህንን ጥያቄ ማንሳቱ በአጠቃላይ ሰለዲሞክራሲያዊ መብቶች ጉዳይ የመንፈስ ጭንቀት መኖሩን ከማሳየቱ በስተቀር. በእውነቱ በክርክር ላይ የሚጨምረው ምንም አይነት አዲስ ነገር የለም። ይህ ያለቀለት ክርክር ከአመት በኋላ ዛሬ እንዴት ተነሳ?
ግን ከዚህም ይበልጥ የሚያሳስበው ስለመብቶች መለቀቅ ጉዳይ ይህ የወዝ ቁጥር የሚሰነዝረው አስተየየት ነው። በሰፊው እንጠቅሳለን።
“የዲሞክራሲ መብቶች ጭቁኖችን ለወሳኝ ፍልሚያ በከፍተኛ ደረጃ እንዲዘጋጁ በር ከፋች ናቸው። ይሁን እንጂ ጭቁኖች ዲሞክራሲያዊ መብቶች በብቸኝነት ለደህንነታቸው ሊጠቀሙበት የሚችሉት አንድ ማእከል ሲኖራቸው ነው። ቀደም ብለን እንደጠቀስነው ይህ የግራው ክፍል ማዕከል የሚገኘው የተራማጆች ህብረት በውይይትና በትግል ተፈጥሮ በመጠናከር ወደ ውህደት ሲያመራ ብቻ ነው።…..”
ወዝ ቁጥር 32ን ጓዶች ሁሉ ፈልገው ማንበብ አለባቸው፤ ማጥናት አለባቸው። ስለ ዲሞክራሲ ብቻ ሳይሆን ስለሌሎችም ነጥቦች በጣም ጠቃሚ የሆኑ፣ ግን ደግሞ ይህን ያህልም ግልጽ ባልሆነ ቋንቋ ያልተሰነዘሩ አስተያየቶች አሉበት። ስለሆነም፣ ይህኛው ቁጥር ከሌሎች የወዝ ቁጥሮች ለየት ያለ ሆኖ አግኝተነዋልና ይጠና። ዲሞክራሲን በሚመለከተው በኩል ከዚህ በላይ የቀረበው ጥቅስ፣ እንደገባን ከሆነ፣ የሊግ አስተሳሰብ፣ በቀላል አማርኛ፣ የወዛደሩ ፓርቲ ካልተፈጠረ፣ ዴሞክራሲያዊ መብቶች ሊለቀቁ አይገባም ነው። ምክንያቱም “አንድ ማእከል” መኖር ስላለበትና ይህም “የሚገኘው የተራማጆች ህብረት በውይይትና በትግል ተፈጥሮ በመጠናከር ወደ ውህደት ሲያመራ ብቻ” ነውና! ውህደት ማለት የወዛደር ፓርቲ መፈጠር ማለት ነው። የለም የወዛደር ፓርቲ ካልተፈጠረ ማለታችን ሳይሆን፣ ወደ ውህደት “ስናመራ” ማለታችን ነው እንዳይባል፣ ዛሬም፣ በሐምሌ ወር 1969፣ ወደዚያው “በማምራት” ላይ እንደሆንን ነው የሚገባን። በዚህ ሁኔታ እንግዲህ መቼ ነው የተራማጆች ህብረት ተጠናክሮ “ወደ ውህደት አመራ” የሚባለው? ማን ይወስንልናል?
ግን ደግሞ ሌላ የጥቅሱ ነጥብ አለ። ይኽውም የተራማጆች ህብረት “በውይይትና በትግል መጠናከር” ነው። ዲሞክራሲያዊ መብቶች በሌሉበት ሁኔታ ምን አይነት ውይይትና ትግል ነው ሊኖር የሚችለው? ወይንስ ውይይቱና ትግሉ በአሁኑ ወቅት በኅብረት ኮሚቴው፣ ማለትም በ15 ሰዎች መካከል፣ ባንድ ጠረጴዛ ዙሪያ የሚካሄደውን ማለት ነው? መኢሶን በተለያዩ የልሳኑ ቁጥሮች ደጋግሞ እንደገለፀው ሁሉ፣ የተራማጆችን ህብረት ለማጠናከር፣ የወዛደሩን ፓርቲ ለመገንባት፣ ሕዝባዊ አብዮታዊ ግንባሩን ለመመስረትና በጠቅላላውም አብዮቱ ወደፊት ገፍቶ ግቡን እንዲመታ ለማድረግ፣ እነዚህ መብቶች የግድ ባስቸኳይ ያስፈልጋሉ። ስለሆነም፣ የሊግ ጓዶችና የእኛ አቀራረብ ፍጹም ተቃራኒዎች ሆነው እናገኛቸዋለን። እነርሱ የሚሉት የወዛደሩን ፓርቲ ፈጥረን ዲሞክራሲያዊ መብቶቹ ይምጡ ሲሆን፣ እኛ ደግሞ የወዛደሩን ፓርቲ ለመፍጠር ዲሞክራሲያዊ መብቶች ያስፈልጋሉ ነው። እንደሚባለው የመኢሶን “ፍልስፍና” የሚመሠረተው አብዮትን የሚሰራው በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠረው ሰፊው ሕዝብ እንጂ ጥቂት ግለሰቦች ወይንም ቡድኖች አይደሉም በሚለው ላይ ነው።
በዚህ በወዝ 32 ጥቅስ ላይ ሌሎችንም ትችቶች ለማቅረብ ይቻል ነበር። እነርሱን ለአንባቢ እንተውና ወደ መግለጫው ጥቅስ እንመለስ።
መግለጫው ለዴሞክራሲያዊ መብቶች ባስቸኳይ መታወጅ አስፈላጊነት የሚሰጠው የመጀመሪያው ምክንያት፣ “በአሁኑ ወቅት አብዮቱን ለመቀልበስ ያሰፈሰፉትን አድሃርያን በይበልጥ ለመቋቋም” እንዲቻል ነው ይላል። ማንም ተመልካች በግልጽ እንደሚያየው ሁሉ፣ ከየካቲት ወር ወዲህ፣ የተባሉት አድሃሪያን ይበልጥ፣ አስር እጅ ይበልጥ፣ “አሰፈሰፉ” እንጂ በምንም መንገድ ፀረ አብዮት ትግላቸውን አልቀነሱትም። በመግለጫው ትክክለኛ አስተያየት ተመርኩዞ ከተሄደ፣ ዲሞክራሲያዊ መብቶች ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ዛሬ አስፈላጊ ናቸው ተብሎ ታምኖበት እርምጃም ሊወሰድ ሲገባው፣ በአንዳንድ አካባቢዎች ለዴሞክራሲያዊ መብቶች በአሁኑ ወቅት አለማስፈለግ እንዲያውም የአድሃሪች መጠናከርና “ማሰፍሰፍ” እንደ ምክንያት ሆኖ ይቀርብ ጀምሯል። የተጨባጭ ነገሮች ሂደት በግልጽ የሚታይና የዛሬ 6 ወር የተባለውን በተጨባጭ መንገድ እንደሚረጋገጥ ባይኖቻችን እያየን፣ ያን ጊዜ ለአንድ አላማ የተሰጡት ምክንያቶች ዛሬ ለምን ለተቃራኒው አላማ እንደሚቀርቡ ግራ የሚያጋባ ነው! በኛ በኩል አሁንም የምንለው፣ ሰፊው ሕዝብ ጠላቶቹን ይበልጥ ለመቋቋም እንዲችል ይበልጥ መንቃት፣ ይበልጥ መደራጀት፣ ይበልጥ መታጠቅ፣ አለበት ነው። ለዚህም ደግሞ የዲሞክራሲያዊ መብቶች መለቀቅ ሊታለፍ የማይችል አስፈላጊ ነገር ነው።
በመግለጫው ውስጥ “በስውር ታፍነው የሚሠሩ ተራማጅ ድርጅቶች” ስለተባለው፣ አንዳንድ የህብረት ኮሚቴው አባላት፣ “ዲሞክራሲያዊ መብቶች ቢፈቀዱም እንኳን፣ እነዚህ ሕቡዕ ድርጅቶች በይፋ መውጣት የለባቸውም!” የሚል አሰቂኝ ምክንያት እየተሰጠ ነው። እዚህ ላይ ማስታወስ የሚያስፈልገን ቁም ነገር አለ። ይኽውም መኢሶን ዴሞክራሲያዊ መብቶችን የሚጠይቀው ይህን ያህልም ለራሱና ለህቡዕ ድርጅቶች ሳይሆን፣ ለሰፊው ጭቁን ሕዝብ ነው። ይሕ ሕዝብ የንግግርን፣ የጽሑፍን፣ የመስብሰብን፣ የመደራጀትን መብቶች እስካላገኘ ድረስ በፍጥነት ሊነቃና ሊደራጅ አይችልም። በእርግጥ ለሰፊው ሕዝብ አሁንም ቢሆን መብቶች አሉ ይባላል። የአርሶአደር፣ የወዛደርና የሌሎችም ሰርቶ አደሮች ማህበራት አሉ፤ በፈለጋቸው ጊዜ ይሰበሰባሉ፤ የፈለጋቸውን ይናገራሉ፣ ….. ወዘተ ይባላል። ግን አሁን ያለውን ተጨባጭ ሁኔታ አጋኖ ባሸበረቁ ቀለማት ሽፋፍኖ ማቅረብ ነው። ሰፊው ሕዝብ አሁንም ቢሆን፣ በከተማም ሆነ በገጠር፣ በፊውዶ ቡርዧው የመንግሥት አውታሮች ተወጥሮ ተይዟል፤ ከቢሮክራሲውም ጋር ኃይለኛ ትግልን እያካሄደ ነው። ሰፊው ሕዝብ የገዛ እድሉን በገዛ እጆቹ ጨብጧል ከሚባልበት ደረጃ አሁንም ገና በጣም ርቆ ይገኛል። ስለሆነም፣ ጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ የሰፊው ሕዝብ አጋር እስከሆነ ድረስ ሰፊው ሕዝብ ወደዚያ ደረጃ የሚያቀርቡትን እርምጃዎች ሁሉ በወቅቱ የመውሰድ ኃላፊነት ስላለበት፣ ይህ መንግሥት በሰፊው ሕዝብ እምነት እስከኖረው ድረስ፣ በኛ አስተያየት ዴሞክራሲያዊ መብቶች ለጭቆች ያለ ገደብ እንዲለቀቁ የማድረግ አብዮታዊ ግዴታ አለበት እንላለን።
እንግዲህ ለማጠቃለል ያህል፣ በዚህ ነጥብ ላይ ብዙ ሀተታዎችን ሳንጨምር፣ በአሁኑ ጊዜ በመኢሶንና በሌሎች የህብረት አባል ድርጅቶች መካከል አንድ የቆየ ልዩነትና አሁን ደግሞ አንድ ሌላ እየጎላ የሚሄድ ልዩነት እንዳለ አንገንዘባለን። በጋራ መግለጫው ውስጥም ሆነ በየድርጅቱ ልሳን ውስጥ፣ ህብረቱን ለማጠናከር ዲሞክራሲያዊ የሆነ የፖለቲካና የርዕዮተዓለም ትግልን ማካሄድ እንዳለብን ተደጋግሞ ተገልጿል። ስለዚህም፣ ከአሁን ጀምሮ እነዚህን የልዩነት ነጥቦች ለውይይት ማቅረቡ ይጠቅማል ብለን እንገምታለን። ደግሞም በህብረት ኮሚቴው የጸደቀው የህብረቱ መተዳደሪያ ደንብ ለዚህ አመቺ ሁኔታን ይፈጥራል።
3. ስለ ህብረቱ የድርጊት ፕሮግራም
የብሄረሰቦች ጥያቄ፣ የዲሞክራሲ ጥያቄ፣ የማርክሲስት ሌኒኒስት ድርጅቶች መቀራረብ፣ መተባበርና ተዋህዶ ፓርቲን መፍጠር፣ እነዚህ ሁሉ ጥያቄዎች የተያያዙ ብቻ ሳይሆን እንዲያውም በአንድ መሰረት ላይ የቆሙ ነገሮች ናቸው። ብሔረሰቦች ከብረት የጠነከረ የጭቁን መደቦች አንድነት እንዲመሠረቱና በመካከላቸው ለብዙ ዘመናት የኖረውን ጥላቻና የእርስ በርስ ጥርጣሬ እንዲወገድ የብሄረሰቦችን የእኩልነት መብት ማወቅ ያስፈልጋል። ተራማጆች በሃቅ እንዲተባበሩ፣ በመካከላቸው ያሉት አለመተማመንና ሽኩቻዎች ጠፍተው ያስተሳሰብ እና የድርጊት አንድነትን ገንብተው እውነተኛ የወዛደሩን ፓርቲ እንዲፈጥሩ ከተፈለገ፣ ዲሞክራሲያዊና በእኩልነት ላይ የተመሰረተ ግንኙነት በመካከላቸው መፈጠር ይኖርበታል። ዲሞክራሲያዊ መብቶች በሌሉበትና የየካቲቱ መግለጫ እንዳለው ሁሉ ድርጅቶቹ “ታፍነው” በሚሰሩበት በአሁኑ ሁኔታ ግን ይህ እኩልነት አለ ለማለት ፈጽሞ አያስደፍርም። እኩልነት የለም ብንልም አንዱ ድርጅት በአባል ብዛት ወይም በስፋት ከሌላው ይበልጣል ለማለት ሳይሆን፣ አንዱ ወይም ሌላው ድርጅት እንደ ሁኔታው በጊዜያዊ ወታደራዊ መንግሥት በኩል ከሌሎቹ የበለጠ ተደማጭነትን ለማግኘት የሚችልበት ሁኔታ አለ ለማለት ያህል ነው። ስለዚህም ነው ሃቀኛና ዲሞክራሲያዊ አሰራር ይኑር የምንለው።
እስከዚያው ድረስ ግን፣ አብዮታዊያን በአንድ በኩል በአንድ በተወሰነ ወቀት የኃይሎችን አሰላለፍ አጢኖና በዚያም ላይ የራስን ድርጊት የመቀየስ ግዴታ ስላለባቸው፣ በሌላ በኩል ደግሞ እያንዳንዱ ሁኔታ በሚያበረክተው እድል ትንሽም ብትሆን መጠቀምም ስላለባቸው፣ በአሁኑ የኢትዮጵያ ሁኔታ እጅግ አስፈላጊ የሆነውን የተራማጆችን ህብረት ለማጠናከርና አብዮቱ ወደፊት እንዲራመድ ለማድረግ እንታገላለን። ከዚህ ጋር የተያያዘውን የድርጊት ፕሮግራም የምንቀበለውና የመኢሶን ጓዶችና ደጋፊዎች ሁሉ እንዲታገሉለት ጥሪ የምናቀርብላቸውም በዚሁ ምክንያት ነው። እንደዚሁም ጓዶች ሁሉ በየካቲት ወር የወጣውን የጋራ መግለጫ እና መርሃ ግብር እንደገና እንዲያጠኑትና ከሥራ ላይ እንዲያወሉት እንጠይቃለን። እንደዚሁም የኢትዮጵያን ብሄራዊ ዲሞክራሲያዊ የአብዮት ፕሮግራም!! እንደዚሁም የመኢሶንን ፕሮግራም!!
አንባቢ ይህንን ድርደራ ተመልክቶ “የኢትዮጵያ አብዮት በዕውነቱ በፕሮግራም እጦት አልተቸገረም!” ሳይል አይቀርም። በኛ አስተያየትን ኅብረትም ቢሆን በፕሮግራም እጦት አልተቸገረም፤ ለመሥራት ከተፈለገ፣ በእርግጥና በሃቅ ሁሉም ድርጅት ለህብረት፣ ከዚያም ለውህደትና ለወዛደሩ ፓርቲ መፈጠር የሚታገል ቢሆንማ ኖሮ የየካቲቱ መርሃ ግብር እራሱ በበቃ ነበር። የድርጊት ፕሮግራምን ማውጣት በራሱ ለመስራት ያለንን ፍላጎትና ችሎታ አይጨምርልንም። ይሁንናም፣ መኢሶን ይህንን የድርጊት ፕሮግራም ሀላፊነት በተሞላበት መንፈስ ይቀበላል፤ አባሎችና ደጋፊዎቹም ሁሉ እንዲያጤኑትና ይዘቱንም ከሥራ ላይ እንዲያውሉት ይጠይቃል።
ማንም በቀላሉና በአንድ ጊዜ ለማየት እንደሚችል ሁሉ፣ ከዚህ የድርጊት ፕሮግራም ውስጥ ባለመኖሩ ብቻ እንኳን የተለየ አትኩሮትን የሚጠይቀው የዲሞክራሲ መብቶች ጉዳይ ነው። በርሱ ፈንታ፣ ፕሮግራሙ
“ለትግሉና ለሽግግሩ ይበልጥ አመቺ ሁኔታን ለመፍጠር የብሔራዊ ዲሞክራሲያዊ አብዮት ፕሮግራምን መሰረት በማድረግ ጊዜያዊ ወታደራዊ መንግሥት ለህብረቱ፣ ላሉትና ወደፊትም ለሚፈጠሩት ማርክሲስት ሌኒኒስት ድርጅቶች፣ ለተራማጅ ድርጅቶችና ለፀረፊውዳል፣ ፀረኢምፔሪያሊስት፣ ፀረቢሮክራሲያዊ ካፒታሊስት ኃይሎች የማቴሪያርና የሞራል ድጋፍ እንዲሰጥ መታገል” ይላል።
መኢሶን በበኩሉ በውይይቱ ላይ የጠየቀው ሌላው ቢቀር ዲሞክራሲያዊ መብቶች ለጭቁኖች እንዲታወቁ መታገል የሚለው መርሀግብሩ ነጥብ ቢያንስ በዚህ ፕሮግራም ውስጥ እንዲገባ ነበር።ይህ የተቀባይነት ሊያገኝ አልቻለም።
ይሁን እንጂ፣ በሌላ በኩል ደግሞ፣ ይኸው የድርጊት ፕሮግራም በአምስተኛ፣ በስድስተኛና በሰባተኛ ነጥቦች የሚያቀርባቸው ተግባሮች በእርግጥ ከሥራ ላይ እንዲውሉ፣ አብዮቱም ባጠቃላይ ወደፊት እንዲጓዝ ለማድረግ ከተፈለገ፣ የሰፊው ሕዝብ ሙሉ ተሳትፎ፣ ማለትም መብቶች ያስፈልጋሉ።…. ሁሉም ዞሮ ዞሮ ከዚሁ ጋር የተያያዘ ነው።
መኢሶን ይህንን የድርጊት ፕሮግራም ስለሚያምንበት ብቻ ሳይሆን፣ በህብረቱ ደንብም መሠረት፣ በነጥቦቹ ላይ ልዩነቶች ቢኖሩትም፣ ፕሮግራሙን ከሥራ ላይ የማዋል ግዴታ አለበት። የኅብረቱ ደንብ በህብረት ኮሚቴው 29ኛ ስብሰባ ላይ ሐምሌ 11 ቀን ፣1969 ፀድቋል።
በኛ አስተያየት፣ እንደ የጋራ መግለጫ ሁሉ፣ ይህም ደንብ በኢትዮጵያ አብዮት ታሪክ ውስጥ ከፍተኛ ቦታን ይይዛል። ደንቡ ዴሞክራሲያዊ ነው። አብዮታዊ ነው። ለአባል ድርጅቶቹ የሚሰጠው መብትና ግዴታ ትክክለኛና ከጊዜ ሁኔታ ጋር የሚሄዱ ናቸው። የእያንዳንዱ ድርጅት ነፃነት እንደተጠበቀ ሆኖ፣ በዚያውም ግን በዛሬይቱ ኢትዮጵያ ሁኔታ ብዙ ተግባሮችን በህብረት ለማከናወን እንደሚችል የሚያበስር ደንብ ነው። ይሁንናም፣ ከዚህ በላይ በተጠቀሱት የህብረቱ ችግሮች ሁሉ ምክንያት፣ ይህ ደንብ እንደ ኃይለሥላሴ ህገ መንግሥት ሁሉ፣ የወረቀት ጉዳይ ሆኖ እንዳይቀር እያንዳንዱ ድርጅት መቻኮል አለበት። መኢሶን ለደጋፊዎችና በጠቅላላውም ለሰፊው ሕዝብ የሚያደርገው ጥሪ፣ ደንቡም በሚገባ እንዲያጠኑትና በትክክል ከሥራ ላይ ማዋል አለመዋሉንም እንዲከታተሉ ነው። በድርጅታችን በኩል ይህ ደንብ በትክክል ከሥራ ላይ እንዲውል እስከመጨረሻው ለመታገል ቃል እንገባለን።
የተፈጠረውን ህብረት በሚመለከተው በኩል፣ መኢሶን በተቻለው መንገድ ሁሉ በህብረቱ በሃቅና በዲሞክራሲያዊ መንገድ እንዲሰራና እንዲጠነክር ጥረት ያደርጋል። ምንም እንኳን በድርጅታችን ላይ
“መኢሶን አብጦ እራሱ ፓርቲ ለመሆን ይፈልጋል፤ መኢሶን በህብረት አያምንም፣ መኢሶን የጠባብ ቡድን ስሜት ያጠቃዋል … ወዘተ” የሚሉ ዘመቻዎች ተደጋግመው ቢካሄዱበትም፣ መኢሶን ህብረትን ይፈልጋል። የዛሬ ሰባት ወር በሰፊው ሕዝብ ድምጽ፣ ቁጥር 48፣ ሌኒንን በመጥቀስ እንደገለጽነው ሁሉ፣ እንኳንስ ለአብዮት እስከ አሁን ይሄን ያህል አስተዋጽኦ ካደረጉ ድርጅቶች ጋር ይቅርና፣ “ከማይታመኑ ሰዎች ጋርም እንኳን ቢሆን ጊዜያዊ ህብረትን መፍጠር የሚፈሩ በራሳቸው የማይተማመኑ ብቻ ናቸው። የዚህ አይነቶቹን ህብረቶችን ሳይፈጠር ሊኖር የሚችል አንድም የፖለቲካ ፓርቲ የለም።”
ለመቀራረብ፣ ለመተማመን፣ አብሮ ለመታገልና በዚህም ሂደት ያስተሳሰብ እና የድርጊት አንድነትን ፈጥሮ የኢትዮጵያን የወዛደር ፓርቲ ለማቋቋም የዚህ ዓይነቱ ህብረት እጅግ በጣም አስፈላጊ መሆኑን መኢሶን ያምናል። እያንዳንዱ የህብረት አባል ድርጅት ወይም የየድርጅቱ ግለሰብ አባሎች ህብረቱን ለልዩ ልዩ የቅርብ ጊዜ እና የረዥም ጊዜ አላማዎች ሊፈልጉት ይችላሉ፤ መኢሶን ግን ህብረቱን የሚፈልገው የኢትዮጵያ አብዮታዊያን እንዲዋሃዱና የወዛደርን ፖርቲ ፈጥረው፣ በዚህም ፓርቲ አማካይነት ሰፊውን ሕዝብ ከዳር እስከዳር አንቀሳቅሰው አብዮቱን ከግቡ ለማድረስ እንዲታገሉ ለማድረግ ብቻ እንደሆነ እንዲታወቅልን እንወዳለን።
ህብረቱ በራሱ ግን የሚፈልገው ለዚህ ለርምጃም ጊዜ አላማ ብቻ ሳይሆን፣ ኢትዮጵያ ዛሬ ለገባችበትም ውጥረት ሊያስወጣት የሚችል መሳሪያ ስለሆነ ነው። በእርግጥም ደግሞ ይህ ውጥረት ሊወገድ የሚችለው የሰፊው ሕዝብ ሙሉ ተሳትፎ ሲገኝ ነው ከተባለ፣ ይህንን ሰፊ ሕዝብ ለመቀስቀስና በአብዮቱ ጠላቶችና ችግሮች ላይ እንዲሰለፉ ለማድረግ፣ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ታጋዮች ያስፈልጋሉ። ይህንን ሁሉ ታጋይ ደግሞ እንኳንስ አንድ ህቡዕ ድርጅት ለብቻው ሊያሰልፍ ቀርቶ፣ ያሉት ድርጅቶች ሁሉ ተባብረውም እንኳን በአጭር ጊዜ ውስጥ ሊያሰልፉ እንደማይችሉ ለማንም ግልጽ ይመስለናል።
ስለዚህም፣ የኢትዮጵያ አብዮት በአሁኑ ወቅት ከኢትዮጵያ ማርክሲስት ሌኒኒስት ድርጅቶች ህብረት ከፍተኛ ኃላፊነትን ይጠይቃል። ይህንን ኃላፊነት በሚገባ ለመወጣት የሚቻለው፣ በሀቅና ዲሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ፣ እያንዳንዱ አባል ድርጅትም ሆነ ህብረቱ የህብረቱን ደንብ፣ የጋራ መግለጫውንና መርሐ ግብሩን፣ እንደዚሁም ከዚህ ጋር የተያያዘውን የድርጊት ፕሮግራም በትክክልና በሃቅ ከሥራ ላይ ለማዋል ሲታገሉ ብቻ ነው። ያለበለዚያ ግን፣ በልዩ ልዩ ምክንያቶች፣ አንድ ድርጅት ወይም ሌላው የተወሰነውን ነገር ከሥራ ላይ የማያውለው ከሆነ፣ ወይንም የህብረቱን ውሳኔዎች ወደጎን ትቶ በበኩሉ የሚታየውን የሚያደርግ ከሆነ፣ ወይንም ደግሞ ከመጀመሪያውም ውሳኔዎቹ ዲሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ የተደረሰባቸዉ እንዳይሆኑ ከተደረገ፣ ህብረቱም የወረቀት ህብረት ብቻ ይሆናል።
ከዚህ በፊት በየፅሁፎቻችን ደጋግመን እንደገለጽነው ሁሉ፣ መኢሶን ገና ለጋ ድርጅት ነው። አንዳንዶች እንደሚሉት እራሱ “አብጦ” ወይንም ሌሎችንም “ውጦ” ወደ ወዛደር ፓርቲነት ለመለወጥ ምንም ምኞት እንደሌለው እንደገና በዚህ አጋጣሚ ለማረጋገጥ እንወዳለን። ድርጅታችን እንደ ሌሎቹ ድርጅቶች ሁሉ ገና የሚያድግና የሚበስል ድርጅት እንጂ የረጅም ዘመናት ታሪክና የትግል ልምድ ያለው ድርጅት አይደለም። መኢሶን የሳይንሳዊ አመለካከትና የአሰራር ዘዴ ሞኖፖል የለውም። እንደማንኛውም ድርጅት ከትግሉና ከሌሎችም የአገርና ዓለምአቀፍ የወዛደር ድርጅቶች ለመማር ዝግጁ የሆነ ድርጅት ነው። እንደማንኛውም ድርጅት ደግሞ ለራሱ በቀየሰው የፖለቲካ መስመር ያምንበታል፤ ለመስመሩ ይታገላል። የሚያደርጋቸው ስህተቶች ሲኖሩም ወይም የያዘውን መስመር ልክ አይደለም ከተባለ፣ እነዚህ ዲሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ፣ በሃቅና በጓዳዊ መንፈስ ተገልጸውለት እንዲያምንባቸው ሲደረግ እንደሚታረም የድርጅቱ የራሱ የውስጥ ትግሎች ያረጋግጣሉ።
ከመስከረም 69 ወዲህ በተካሄደው ኃይለኛ የመደብ ትግል ውስጥ፣ የመኢሶንን መስመር በመደገፍና ለአብዮቱ በመከላከል፣ በሕዝብ ድርጅት ጉዳይ ጽ/ቤት ሥራ፣ በቀበሌ ማህበራት፣ በገጠር ከኢዲዩና ከሶማሊያ ሰርጎገቦች ጋር በመዋጋት፣ በርከት ያሉ ጓዶቻችን ህይወታቸውን ከፍተኛ መስዋዕትነት አድርገዋል። የነዚህን ፍጹም አብዮታዊ ጓዶቻችንን አርማ ይዘን ለሰፊው ሕዝብ የነቃ፣ የተደራጀና የታጠቀ ትግል እስከመጨረሻው ድረስ እንታገላለን። የጠየቀውን መስዋዕት ቢጠይቅም የፈለገው የአብዮታዊ ጓደኞቻችን ቁጥር በጠላት ጥይት ቢወድቅም ችግርንና ሞትን ሳንፈራ ወደፊት እንራመዳለን። ምኞታችን ለሰፊው ሕዝብ ትግል፣ ለአብዮቱ፣ ለነፃና ኩሩ ኢትዮጵያ ታግለን መሰዋት ብቻ ነው። እንግዲህ መስመራችን ይህ እስከሆነ ድረስ ከኢትዮጵያ ሀቀኛ ተራማዶች ሁሉ ጋር የማንገባበትና የማንዋሃድበት ምክንያት ስለሌለ፣ ህብረቱን እናጠንከር እንላቸዋለን።
ዲሞክራሲያዊ መብቶች ለጭቁኖች ያለ ገደብ ባስቸኳይ!!
የማርክሲስት ሌኒኒስት ድርጅቶች ሕብረት ይጠንክር!!
የነቃ፣ የተደራጀና የታጠቀ የሰፊው ሕዝብ አመጽ ያሸንፋል!!
ማስታወሻ፡-
ይህ ጽሑፍ ተዘጋጅቶ እንዳለቀ፣ የሶማሊያ ጦር ኦጋዴንን መውረሩ ተነገረ። በፅሁፉ ላይ ለመጨመር የሚቻለው የተጠቀሱትን ተግባሮች በጥድፊያ ከሥራ ላይ እናውል የሚል ማሳሰቢያ ብቻ ነው።