የሰፊው ሕዝብ ድምፅ
ቁጥር 61፣ ነሐሴ 16፣ 1969
የፅሁፉ ፍሬ ሀሳብ
“መኢሶን ከደርግ ጋር የነበረውን ትብብር ለምን አቆመ”፣”ከእንግዲህስ በኋላ የመኢሶን የትግል ስልት ምንድነው” የሚሉትንና የመሳሰሉትን ጥያቄዎች የሚመልሰው ይህ ጽሁፍ የወጣው መኢሶን በነሓሴ 1969 በህጋዊው የትግል መድረክ የተመደቡ ጓዶቹን በህቡዕ ትግል ለማሰማራት በወሰነበት ወቅት ነው። መኢሶን በዚህ ጽሁፍ የወቅቱን ሁኔታ ከገመገም በኋላ የትግል ስልት ለማድረግ የተገደደባቸውን ምክንያቶች በሰፊው ይዘረዝራል።
1. መግቢያ
ይህንን የሰፊው ሕዝብ ድምጽ ጋዜጣ ቁጥር አግኝተው የሚያነቡ፣ ወይም ደግሞ በወሬ ወሬ የሚሰሙ አንዳንድ ሰዎች፣ መኢሶን ዛሬ ይዞት የወጣውን የትግል ጥሪ ከቀድሞ የተለየ አድርገው ሊመለከቱት እንደሚችሉ እንገምታለን። ይህን እንጂ፣ እስከዛሬም ድረስ ሆን ብለው ውዥንብር ሲነዙ ከቆዩት የለየላቸው አድሃሪዎችና አወናባጆች በስተቀር፣ የፖለቲካ መስመር ትግልን ምንነት በትክክል ለመረዳት ካልቻሉት ሰዎች በስተቀር፣ የመኢሶንን የፖለቲካ መስመር በጥሞና የተከታተሉት ሁሉ፣ በዚህ ጽሁፍ አንዳችም “ከቀድሞ የተለየ አዲስ የፖለቲካ መስመርን” እንደማያነቡ እምነታችን ነው። የመኢሶንን ፕሮግራም የመጀመሪያ ገጾችን እንኳን ያነበበ ሰው፣ የድርጅቱን የፖለቲካ ትግል መስመር የሚረዳው ወዲያውኑ ነው። በመኢሶን ፕሮግራም መግቢያ ውስጥ እንደተገለጸው፡-
“መኢሶን ለኢትዮጵያ ጭቀኖች የተሟላ ነፃነትና ለሶሻሊዝም ቆሟል። ለዚህ አላማ ከሚታገሉ ኃይሎች ጋር ሁሉ፣ የትግል አንድነት ለመመስረት እጁን ይዘረጋል። ለቆመለት አላማ የላንዳች ማወላወል በምስጢር፣ በይፋ፣ በህጋዊ መንገድና በህገወጥነት፣ በሰላማዊ መንገድና በአመጽ፣ እንደ ጊዜው እና እንደ ሁኔታው በሚለዋወጥ ታክቲክ፣ ምንም ጊዜ ምንም ሁኔታ በማይለወጠው ቆራጥነትና ታታሪነት የሚታገሉ አብዮታዊያንን አስተባብሮ ለኢትዮጵያ ሰፊ ሕዝብ ነፃነትና እድገት ተሰልፏል። የኢትዮጵያ ጭቁኖች የሚያደርጉትን የተበታተነ ትግል ከዳር እስከዳር አስተባብሮ፣ የተጣራ አብታዊ አመራር ለመስጠት በጭቁን ሕዝቦችና ታሪክ ፊት የተቀበለውን አደራ እስከ መጨረሻው ይጠብቃል። ጭቁኖች በትግላቸው እንደሚገፉ፣ በትግል እሳት የተፈተኑ አባሎቹ አብዮታዊ ግዴታቸውን ከመፈጸም ወደ ኋላ እንደማይሉ የጠነከረ እምነት አለው። ስለሆነም፣ የወሰደውን ጊዜ ይወስዳል እንጂ፣ የኢትዮጵያ ጭቁኖች ወደ ነፃነትና ወደ ሶሻሊዝም ለሚያደርጉት ጉዞ የመጨረሻው ድል የእነርሱ እንደሆነ ቅንጣት አንጠራጠርም።”
እነዚህ ቃላት የተፃፉት በመጋቢት ወር 1968 ዓ.ም. መኢሶን ሚስጢራዊ መዋቅሩን ሳይገልጥ፣ ህልውናውን በፕሮግራሙ አማካይነት ባሳወቀበት ጊዜ ነበር። መኢሶን በዚያን ወቅት እና አሁንም፣ ጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ ብሄራዊ ዴሞክራሲያዊ አብዮቱን መርቶ ከግቡ ሊያደርሰው የማይችል ኃይል መሆኑን ቢያውቅም፣ ከታህሳስ 1968 ዓ.ም. ጀምሮ፣ አንዳንድ አባሎቹን በህጋዊ መስክ አሰማርቶ ሲታገል እንደቆየ የሚታወቅ ነው።
መኢሶን ከመጀመሪያው ይህንን የትግል መስክ የመረጠው፣ በነበረው አመቺ ሁኔታ የአቅሙን አበርክቶ አብዮቱን ትክክለኛ ፈር በማስያዝ፣ ሰፊው ሕዝብ ወዳጁንና ጠላቱን በትክክል እንዲለይ ለማገዝ እና በአጠቃላይም ንቃቱንና ድርጅቱን ለማዳበር በሚያስችለው ሁኔታ ሁሉ እንዲጠቀምበት ለመርዳት ነበር። በእርግጥም ደግሞ፣ በዚህ ትግሉ አማካይነት፣ ሰፊው ሕዝብ የብሄራዊ ዲሞክራሲያዊ አብዮቱን አላማዎችና ተግባሮች በመጠቀም እንዲረዳቸው፣ እርሱን መስለው በውስጡ የተሰገሰጉትን ቀልባሾችና ሌሎችንም አድሃሪዎች አጋልጦ እንዲመነጥራቸውና በዚህም ትግሉ ንቀተ ህሊናውንና የድርጅት ደረጃውን ከፍ እንዲያደርግ ለማገዝ ተችሏል። የኢትዮጵያ ሰፊ ሕዝብና የኢትዮጵያ ተራማጆች በመተባበር ባለፉት 2 ዓመታት ውስጥ ተደጋግሞ የተነሱትን የቅልሳ ሙከራዎች ለማክሸፍ በመቻላቸው አብዮታችን ወደፊት ተራምዷል።
2. የትግል ስልት ለውጥ
ከጥቂት ወራት ወዲህ በኢትዮጵያ አብዮትና በኢትዮጵያ አንድነት ላይ የተሰነዘሩት አደጋዎች እስካሁን ከታዩት ሁሉ በላይ ከባድና እስጊ ሆነዋል። በአሁኑ ጊዜ፣ ሀገራችንና አብዮቱ በትልቅ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የማህበራዊ ኑሮ ውጥረት ውስጥ እንደወደቀና ሁኔታውም በየእለቱ እየተባባሰ እንደሚሄድ በአይናችን የምናየው እውነት ነው።
በፖለቲካ በኩል፣ ሰፊው ሕዝብ ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶቹን ሊቀዳጅና በሙሉ ነጻነትና በሕዝባዊ ኃይሉ በአብዮቱ ሊሳተፍ አልቻለም። እንዲያውም በአንዳንድ ክፍላተ ሀገር- በሐረርጌ፣ በባሌ፣ በሲዳሞ፣ በከፋ፣ በጎንደር- ከፍተኛ እልቂት እየደረሰበት ነው። በተለይም በሐረርጌ ሰፊው አርሶአደር ሕዝብ በአንድ ወገን ውድ አገሩን በወረሩት የሶማሊያ ወታደሮች እየተጨፈጨፈ ነው። በሌላ ወገን ደግሞ፣ የብሄር ትምክህተኝነት ነግሶ የቀድሞዎቹ የመሬት ከበርቴዎች በገፍ እየረሸኑት ነው። በነዚህ ክፍላተሀገራት የሚገኙት ሕዝባዊ ድርጅቶች – የወዛደር፣ የገበሬ፣ የቀበሌ፣ የሴቶች፣ የወጣቶች ድርጅቶች- እየፈራረሱ ናቸው።…..
በኢኮኖሚ በኩል፣ የሸቀጣ ሸቀጥ መጥፋት፣ የእህል መወደድ፣ የዋጋ መናር እና የሥራአጥ መብዛት፣ ሰፊውን ሕዝብ፣ በተለይም ሰፊውን የከተማ ሕዝብ፣ በከባድ ችግር ውስጥ ጥለውታል። ….
በማህበራዊ ጉዳይ በኩል፣ በትምህርት፣ በጤናና በሌሎችም አገልግሎቶች በብሄራዊ ዲሞክራሲያዊ አብዮት ፕሮግራም ውስጥ የተጠቀሱት ተግባሮች ምንም ያህል ከሥራ ላይ አልዋሉም።….
በዚህ ሁሉ ላይ ደግሞ፣ የአድሃሪዎች ከበባና ወረራ፣ እንደዚሁም የአብዮቱ ከውስጥ መቦርቦር በተፋጠነ እርምጃ በመካሄድ ላይ ይገኛሉ። በፊውዶ-ቡርዧው ቢሮክራሲ ውስጥ ቁልፍ ቦታዎችን የያዙ አድሃሪዎች የየራሳቸውን የቅጥረኛ ነፍሰ ገዳዮች ቡድኖች አቋቁመው፣ በደርጉም ውስጥ ሆነ ከዚያ ውጭ ያሉትን ተራማጆች ጨርሰው የመንግሥትን ስልጣን ለመያዝ አሰፍስፈዋል። ስለዚህም የጊዜው ሁኔታ ከመቼው ይበልጥ ለአብዮት ቀልበሳ እጅግ በጣም አመቺ ሆኗል።
በእንደዚህ አይነት የጠቅላላ ውጥረት ወቅት፣ የኢትዮጵያ ተራማጆችና አገር ወዳዶች ሁሉ እጅ ለእጅ ተያይዘው፣ ለሚወዷት እናት አገራቸውና ለአብዮታቸው በይፋ ለመዋደቅ መቻል ነበረባቸው። ግን በዛሬው ወቅት ህጋዊው የትግል መስክ እየመነመነና እየጠበበ በመሄዱ ይህንን የተቀደሰ ምኞት ከሥራ ላይ ማዋል ቀላል አልሆነም። ስለዚህም፣ መኢሶን አብዮቱን ትክክለኛውን ፈር ለማስያዝ፣ የአገሪቷን ብሔራዊ ነፃነት ለማስከበርና የሕዝቦችዋን አንድነት ለመጠበቅ በሚደረገው ጥረት፣ ምንም ተጽእኖ በማይኖረው መንገድ፣ የበኩሉን ለማበረከት በማለት በህጋዊ ሥራ ያሰማራቸውን አንዳንድ ጓዶች ወደ ህቡእ መስክ ለማዛወር ወስኗል። መኢሶን ይህንን እርምጃ እንዲወስድ ከተገደደበት ምክንያቶች አንዳንዶቹ የሚከተሉት ናቸው።
አንደኛ። በጥርና በየካቲት ወራት አብዮቱ ከተከላካይነት ወደ አጥቂነት በተሸጋገረበት ወቅት፣ ሰፊው ሕዝብ ነፃ አብዮታዊ እርምጃዎችን በመውሰዱ፣ በአንድ በኩል የውስጥ ፀረአብዮት ኃይሎች መፍጨርጨር ሲገታ፣ በሌላ በኩል ደግሞ፣ እነዚህ ነጻ አብዮታዊ እርምጃዎች ጊዜያዊ ወታደራዊ መንግሥትን አስደንግጠውት ነበር። ስለዚህም፣ ደርጉ የንኡሰ ከበርቴውን መደብ ወላዋይነት በማሳየት፣ የቀበሌዎችን ማስታጠቅ አቆመ፣ እንዲያውም በሚሰጠው ተስፋ አስቆራጭ ፕሮፖጋንዳ የቀበሌዎች ሞራል ሲሰበር፣ በወሰዳቸው አንዳንድ እርምጃዎች ደግሞ በቀበሌ መሪዎችና በወዛደሮች ላይ ጭቆናዎች ተፈጸሙ። ከመጋቢት ወር ጀምሮ በአዲስ አበባ እና በሌሎችም ከተሞች አብዮቱ እንደገና ወደ ተከላካይነት እንዲዘቅጥ ተደረገ። ከዚህም የተነሳ ሀገራችን በአጭር ጊዜ ውስጥ ልትተካቸው የማትችል በርከት ያሉ ቆራጥና ታታሪ አብዮታዊያንና አገርወዳጆች በአድሃርያን ጥይት ወድቀዋል፤ እየወደቁም ናቸው።
ሁለተኛ። አብዮቱ ከአጥቂነት ወደ ተከላካይነት ከተመለሰበት ምክንያቶች አንዱ፣ የጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ እምነቱን በሰፊው ሕዝብ እና በተራማጆች ላይ ሳይሆን፣ ይበልጡን በፊውዶ-ቡርዧው ቢሮክራሲ ላይ በመጣሉ ነው። በዚህም ሁኔታ በመጠቀም፣ አድሃሪዎች በተራማጆች መካከል አለመተማመን እንዲሠፍን አድርገው ተራማጆችን ከፋፍለዋል፤ መኢሶንን በጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ ለማስመታት ሞክረዋል፤ የዛሬውም ሥራቸው በዚሁ የማስመታትና የመምታት አላማ ዙሪያ እየተውጠነጠነ ነው። እንዲያውም በፊውዶ-ቡርዧው ቢሮክራሲ ውስጥ ያሉ፣ ከሁሉ አድሃሪ የሆኑ ቡድኖች፣ የታወቁና በህጋዊ ሥራ የተሰማሩ የመኢሶን ጓዶችን አንድ በአንድ እየገደሉ ለመጨረስ እንደወሰኑና ይህንንም ፋሽስታዊ አላማቸውን ከሥራ ላይ ማዋል እንደጀመሩ መኢሶን ደርሶበታል። በተጨማሪም፣ በሐረርጌ፣ በከፋ፣ በሸዋና በሌሎችም ቦታዎች ሀቀኛ ተራማጆች ይታሰራሉ፣ ይረሸናሉ። አድሃሪዎች ሃቀኛ ተራማጆችንና ሰፊውን ሕዝብ ለመነጣጠል የሚያደርጉትን መፍጨርጨር በከፍተኛ ደረጃ አፋፍመውታል።
ሶስተኛ። መኢሶን በአባልነት የሚገኝበትን “የኢትዮጵያ ማርክሲስት-ሌኒኒስት ድርጅቶች ህብረትን” የፈጥሩት አንዳንድ ድርጅቶችም በነዚህ የአድሃሪዎች ሴራዎች ላይ ነቅተው፣ ዋናና መለስተኛ ቅራኔዎችን ለይተው፣ ለሃቀኛ ህብረት በመሰለፍ ፈንታ በአድሃሪዎች ወጥመድ ውስጥ በመውደቅ፣ በድርጅታችን ላይ የስም ማጥፋትና የማጥላላት ዘመቻ አካሂደዋል፤ እያካሄዱም ናቸው። አንዳንዶቹም ራሳቸው ፈጥረው የሚነዙትን የስም ማጥፊያ ፕሮፓጋንዳ ራሳቸው ያመኑበት ይመስላል። ስለዚህም፣ ህብረቱ በዲሞክራሲያዊ አሰራርና በቁም ነገሮች ላይ የተመሰረተ መሆኑ ቀርቶ፣ አንድም እርምጃ ወደፊት ለመራመድ እንዳይችል ተሰናክሎ፣ “የማይተማመን ባልንጀራ በየወንዙ ይማማላል” እንደሚባለው ሁሉ በወረቀት ላይ የሚቀሩ ፕሮግራሞችን ብቻ ደጋግሞ በመንደፍ ተወስኗል።
አራተኛ። የአብዮታዊት ኢትዮጵያን ህልውና ለማስጠበቅና አብዮቱ ሥር እንዲሰድ ይጠቅማሉ በማለት፣ በህጋዊ ሥራ በተሰማሩት ጓዶች አማካይነት መኢሶን ለጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ እና ለተራማጆች ህብረት በየወቅቱ ያቀረባቸውን ሀሳቦች በቅን መንፈስና ከአብዮቱ አንጻር በመመለከት ፈንታ፣ ሀሳቦቹ ከመኢሶን በመንጨታቸው ብቻ ደርጉና አንዳንዶቹ ድርጅቶች በጥርጣሬ ዓይን እያዩዋቸው ከሥራ ላይ ሳይውሉ በመቅረታቸው ለውጥረቱ መፍትሄና ለአብዮቱ የተፈለገውንና የሚጠበቀውን ያህል አስተዋጽኦ ማድረግ ያልተቻለም።
ለምሳሌ ያህል፣ አሁን በየቦታው ደሙን በማፍሰስ እና አጥንቱን በመከስከስ ላይ የሚገኘውን “ሕዝባዊ ሠራዊት” በሚመለከተው በኩል፣ አብዮታዊ አመራር እንዲኖረው፣ ብቁ የሆኑ የፖለቲካ እንቂዎች ከላይ እስከታች በብዙ ሺህ እንዲሳተፉበት፣ በተለይም ደግሞ ወደየመጣበት ተመልሶ ፀረአብዮትን በሚያውቀው አካባቢ እንዲቋቋም የቀረበው ሐሳብ ምንም ተቀባይነት ሳያገኝ በመቅረቱ፣ ሰራዊቱ ዛሬ በብዙ ችግሮች ውስጥ ወድቋል። በተጨማሪም መንግሥት ሰፊው ሕዝብ በማመን በወቅቱ ስላላስታጠቀው ሀገሪቷ በምሥራቅ በኩል እስከ መወረር ደርሳለች። ቢሮክራሲን በሚመለከተው በኩል፣ በየሚኒስቴሩ፣ በየክፍለሃገሩና በጦር ኃይሎች ውስጥ ያሉትን አድሃሪዎች በወቅቱ በማስወገድ ፈንታ፣ ደርግ ስላቀፋቸው፣ በአሁኑ ወቅት አድሃሪው ቢሮክራሲ አንሰራርቶ ጠቅላላውን ሁኔታ ለቅልበሳ በማመቻት ላይ ይገኛል። ለኤርትራም ችግር፣ ፖለቲካዊ መፍትሄን በማስቀደም ፈንታ፣ “ተገንጣዮቹን አንበርክከን በኋላ የፖለቲካ ውይይት እናካሂዳለን” በሚል አስተሳሰብ በመመራቱ፣ ደርጉ አገሪቷንና አብዮቱን ወደማያዋጣ ጎዳና በመውሰድ ላይ ይገኛል።…
ሌሎችንም ምሳሌዎች ለመጥቀስ በተቻለ ነበር። ነገር ግን ደርግና በፍፁም አድርባይነት የታወሩት አንዳንድ የህብረቱ ድርጅቶች መሪዎች፣ ከጥቂት ወራት ወዲህ ተጨባጭ ሁኔታና የሰፊውን ሕዝብ ጥያቄዎች ለመከታተልና ለመረዳት በመሞከር ፈንታ፣ ድርጅታችንን ያጠቁና ያደከሙ እየመሰላቸው፣ መኢሶን የሚያቀርባቸውን ሀሳቦችና መፈክሮች በመቃወም ላይ ብቻ ስላተኮሩ፣ ኃይላቸውን ሁሉ ሰብስበው አብዮቱን ለማራመድና የአገሪቱን ክብርና አንድነት ለመጠበቅ በሚደረገው ጥረት ላይ ለማዋል አልቻሉም።
እላይ ከተጠቀሱት ምክንያቶች የተነሳ፣ መኢሶን የቀየሰውንና እስካሁንም ሲሰራበት የቆየውን “አብዮታዊ ሂስ” መመርያውን ያላንዳች ተፅዕኖ ከሥራ ላይ ሊያወል የማይችልበት ሁኔታ ተፈጥሯል። ስለዚህም፣ መኢሶን አሁንም የሚያምነበትን “የአብዮታዊ ሂስ” መመርያውን ያላንዳች ተጽዕኖ በሥራ ለመተርጎም ይቻለው ዘንድና፣ ስለ ኢትዮጵያ አብዮትና ስላገሪቷ አንድነት፣ ስለ ብሔራዊ ነፃነትና ስለ ወደፊቱ ትግል ያለውን አስተሳሰብ ለሰፊው ሕዝብ ለማስተጋባት ያመቸው ዘንድ፣ እስከዛሬ በህጋዊ የትግል መስክ ያሰማራቸውን አንዳንድ ጓዶቹን በህቡዕ አሰማርቶ ለመታገል መርጧል።
3. አብዮቱንና አገሪቷን ለማዳን
ከዚህ በላይ እንደተመለከተው፣ አብዮታችንና የሀገራችን አንድነት በአሁኑ ወቅት በከባድ ፈተና ላይ ይገኛሉ። የእለቱ ጥያቄ አብዮቱን ከቅልበሳ ለማዳንና የአገሪቷን አንድነት ለመጠበቅ ምን መደረግ አለበት የሚለው ነው። ዝርዝር መግለጫን እስኪያወጣ ድረስ፣ መኢሶን ለጊዜው የሚከተሉትን ዋና ዋና ነጥቦች በአጭሩ ይጠቁማል፡-
አንደኛ። ካሁኑ ከባድ ውጥረት ለመውጣት የሚቻለው፣ ሰፊው የኢትዮጵያ ሕዝብ ከዳር እስከዳር ሲንቀሳቀስ፣ አንደ አንድ ሰው ሆኖ ሲነሳና የራሱን ታሪካዊ ድርጊቶች ለማከናወን ሲችል ብቻ ነው። ይህ እንዲሆን ደግሞ፣ ሰፊው ሕዝብ አብዮቱንና አገሪቷን በሚመለከቱት ጉዳዮች ላይ ሁሉ ሙሉ ተሳትፎ እንዲኖረውና ውሳኔዎቹን ሁሉ በሙሉ እምነት እንዲቀበል ያሻል። ለዚህ ደግሞ ቢያንስ ቢያንስ ሰፊውን ሕዝብ ለመንቀሳቀስ እና ለመነሳት የሚያስችሉት የዲሞክራሲ መብቶች መለቀቅ አለባቸው። ደርጉን ተቃውመው፣ ወይንም በመንግሥት ላይ ሂስ አቀረቡ በመባል ሀቀኛ የሰፊው ሕዝብ ወገኖች መያዛቸው፣ መታሰራቸውና በዚህም የነጻ አስተሳሰብ መታፈን መቆም አለበት። ሰፊው ሕዝብ ያገኛቸውን ድሎች ሙሉ በሙሉ የመጠቀምና በሥራ የመተርጎም እድል የሚያገኘው መብቶቹ ሲታወቁለት ነው።
ሰፊው ሕዝብ በእነዚህ መብቶች በመጠቀም፣ አድሃሪ ቢሮክራቶችን ከላዩ ላይ አሽቀንጥሮ ጥሎ አዲስ የአስተዳደርና የአሰራር ዘዴዎችን ይፈጥራል። የሰፊው ሕዝብ ንቃተ ሕሊና በአጭር ጊዜ ውስጥ ይዳብራል። የመፍጠር ችሎታው ነፃ ስለሚወጣ፣ ሰፊው ሕዝብ ችግሮቹን በራሱ ጥረት እና ትግል ያሸንፋል። የመደቦች ሰልፍ ግልጽ ስለሚሆንና ትግሉም ፈር ይዞ ስለሚፋፋም፣ ሰፊው ሕዝብ የገዛ እድሉን በገዛ እጆቹ ለመጨበጥ የሚችልበት ወቅት ይቃረባል። የጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ ሰፊውን ሕዝብ በመፍራት ወይም በመናቅ ሁሉንም የሕዝቡን እንቅስቃሴ በፊውዶ- ቡርዧው የሲቪልና የሚሊተሪ ቢሮክራሲ አማካይነት ለመቆጣጠር መሞከሩን ከቀጠለ ግን፣ ይበልጡን ወደ ፀረአብዮት ሰፈር እየዘፈቀ ይሄዳል። የመጨረሻ መጨረሻም ከሕዝቡ ጋር ይቃቃራል፤ ይቆራረጣል።
ሁለተኛ። ከነዚህም መብቶች ጋር ተያይዞ፣ የብሄረሰቦች የእኩልነት መብት በቃልና በፕሮግራሞች ብቻ ሳይሆን፣ በግብር መታወቅ አለበት። የያንዳንዱም ብሄረሰብ ቋንቋ፣ ባህል፣ ሃይማኖትና ሌሎችም መለያዎች፣ በእኩልነት መታወቅና መከበር አለባቸው። እያንዳንዱ ብሄረሰብ የራሱን አስተዳደር በየደረጃው ለመምረጥ የሚችልበት መንገድ ካሁኑ መቀየር አለበት። በኤርትራ ክፍለሀገር በመካሄድ ላይ ያለውን ከንቱ የወንድማማቾች ደም መፍሰስን ለማቆም እንዲቻል፣ ጊዜያዊ ወታደራዊ መንግሥት ሰፊውን የኤርትራ ሕዝብ ማመን፣ ለሁለቱ ዋና ተገንጣይ ድርጅቶች በይፋ የውይይት ጥሪን ማድረግ አለበት።
ሶስተኛ። አብዮቱ የፈጠራቸው ሕዝባዊ ድርጅቶች፣ ማለትም የቀበሌ፣ የወዛደር፣ የገበሬና ሌሎችም ማህበራት የበለጠ ስልጣን አግኝተው አደሃሪውን ቢሮክራሲ በቁጥጥራቸው ስር እንዲያውሉት ማድረግ ያስፈልጋል። ሰፊው ሕዝብ በነጻ ድርጊቶቹ ለርሱ አመቺ የሆኑትን ያስተዳደር ያሰራር ዘዴዎችን እንዲፈጥር መንገድ መክፈትና እስከዚያውም ግን የታወቁ የሲቪል የሆኑ የሚሊተሪ ቢሮክራቶችን ከስልጣን ቦታቸው አስወግዶ በተራማጆችና በሃገር ወዳድ ግለሰቦች መተካት ያስፈልጋል።
አራተኛ። በኢትዮጵያ ውስጥ የደርግ አባሎች በአጠቃላይ ያደረጉት አስተዋጽኦ ከፍተኛ ቢሆንም፣ ከደርግ አባሎች አመዛኙ ክፍል አሁንም ቢሆን ለአብዮቱና ለሰፊው ሕዝብ የቆመ መሆኑ ቢታወቅም፣ በአሁኑ ወቅት በርከት ያሉ በክፍላተ ሀገር የተሰማሩ የደርግ አባሎች ከአድሀሪዎች ጋር ደጋግመው ይሰለፋሉ። በደርግና በሕዝብ መካከል መራራቅን ይፈጥራሉ። የሕዝቡን ንቃት፣ ድርጅት፣ ትጥቅና ነፃ አብዮታዊ ድርጊቶችን በማበረታታት ፈንታ ያፍናሉ። አንዳንዶቹን ጭፍን ፋሽስታዊ ጭፍጨፋን በማካሄድ ላይ እንዳሉ አገር ያወቀው ነገር ነው። ስለዚህም፣ በክፍላተ ሀገር የተሰማሩትና በድርጊታቸው ከአድሃሪዎች ጋር መሰለፋቸውን ያረጋገጡ የደርግ አባሎች እንዲነሱ ማድረግ ያሻል።
አምስተኛ። በምሥራቅ እና በደቡብ ምሥራቅ ክፍላተሀገር ለሰርጎገቦች መስፋፋትና ለአገሪቷ በቀላሉ መወረር ኃላፊው ቢሮክራሲው ነው። እንደዚሁም፣ ሰፊውን ሕዝብ በማመንና ፓለቲካን በማስቀደም ፈንታ፣ በወታደራዊ አስተሳሰብ በመመራት መንግሥት በመሳሪያ ብዛትና በውጭ ኃይሎች ላይ መተማመንን ይዟል። የሶማሊያ ወረራ በተስፋፋባቸው ክፍላተሀገር ውስጥም አርሶአደሩን በጥርጣሬ ዓይን በመመልከትና በብሄር ትምከህተኞችም በማስጨፍጨፍ ለአብዮትና ለሚወዳት አገሩ ሊቀሰቅስና ሊሰለፍ ይችል የነበረው ሰፊ ሕዝብ ጠቅላላውን አብዮቱን መልሶ እራሱ በጥርጣሬ ዓይን እንዲመለከተው ተደርጓል። ከዚህም የተነሳ፣ ወይ ሰርጎገቦች ጋር የተሰለፉት፣ ያለዚያም ደግሞ ከዚያም ከዚህም ሳይሆኑ ቤትና ንብረታቸውን በትነው ጫካ ውስጥ የሰፈሩ በርካታ የአርሶደር ቤተሰቦች እንዳሉ የታወቀ ነው። ስለሆነም፣ ከነዚህ ሁሉ በሽታዎች ተላቆና ሰፊውን ሕዝብ አምኖና አስታጥቆ በየአካባቢው የሰረጉትን ወረራዎች በራሱ ኃይል እንዲቋቋም ማድረግ ያስፈልጋል።
እነዚህ እርምጃዎች በፍጥነት ከተወሰዱ፣ የተራማጆችን ህብረት ለማጠናከርና ብሎም የኢትዮጵያን የወዛደር ፓርቲ፣ ሕዝባዊ አብዮታዊ ግንባርንና ሕዝባዊ አብዮታዊ ጦሩን ለመመስረት እጅግ አመቺ ሁኔታ ይፈጠራል። አብዮቱ ስር የሰደደባቸውን የአገሪቱዋን ክፍሎች በመገንባት፣ የውስጥና የውጭ አድሃሪዎችን ደምስሶ አብዮቱ ግቡን እንዲመታና የአገሪቷም አንድነት እንዲጠበቅ ለማድረግ ይቻላል። የኢትዮጵያ ጭቁን ሕዝቦች አብዮትን ይፈልጋሉ። የአብዮታዊት እናት ሀገርን ክብርና አንድነት ይሻሉ። ለብሔራዊ ነፃነታቸውና ሕዝቦችዋን በኩልነት ላቀፈች ኢትዮጵያ እስከመጨረሻው ይዋጋሉ። ሰፊው ሕዝብ ከዳር እስከዳር ተንቀሳቅሶ ኃይሉን ለዚህ የተቀደሰ ፍላጎቱ የሚያውልበት ሁኔታ ከተፈጠረ ኢትዮጵያን በአፍሪካ ምድር እውነተኛ የአብዮት ምሸግ ልናደርጋት እንችላለን።
4. መኢሶን የሚያቀርባቸው ጥሪዎች
አንደኛ። ለጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ፣ በተለይም በዚያ ውስጥ ላሉት ተራማጆች የምናቀርበው ጥሪ፣ በስሜትና በቸኩልነት እንዳይመሩ ነው። ጥቂት የመኢሶን ጓዶች ትግላቸውን በጥብቅ ህቡእ እንዲቀጥሉ ድርጅቱ ስለወሰነ፣ መኢሶን አቋራጭ የመንግሥት ስልጣን ለመያዝ ይፈልጋል በሚል ስህተተኛ አስተሳሰብ በመመራት፣ የመኢሶን አባሎች ወይንም ደጋፊዎች ናቸው ተብለው በሚጠረጠሩ አብዮታዊያንና አገርወዳዶች ላይ መንግሥት ምንም አይነት የጭቆና እርምጃን መውሰድ የለበትም። መኢሶን ይህንን ውሳኔ ያደረገው የወደፊት እርምጃ የበለጠ አስተዋጽኦን ለማበረከት እንዲያመቸው ብቻ እንጂ፣ ስልጣንን በአቋራጭ ለመያዝ አይደለም። መኢሶን ለሰፊው ሕዝብ ስልጣን እንጂ፣ አንዳንድ አወናባጆች እንደሚሉት፣ ራሱን በስልጣን ላይ ለማስቀመጥ አይታገልም። ነገር ግን መንግሥት ይህንን ሀቅ ስቶ በተራማጆችና በአገርወዳድ ሰዎች ላይ በግልፅ ይሁን በስውር የጭቆና እርምጃዎችን መውሰድ ከጀመረ፣ ያሉትን የአብዮትና የአገሪቷን ችግሮች ያባብሳቸዋል። በኢትዮጵያ ምድር ላይ የሱዳን እና የቺሊ ሁኔታዎች እንዳይፈጠሩም ያሰጋል። ስለዚህም፣ አብዮቱንና አገሪቷን ከውድቀት ለማዳን ከመቼውም ጊዜ ይልቅ ትእግስትና አርቆ- አስተዋይነትን ይጠይቃል። የጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ ከመቼውም ጊዜ ይልቅ ትልቅ ጥንቃቄን ማድረግ ይኖርበታል።
ሁለተኛ። ለኢትዮጵያ ሀቀኛ ተራማጆች የምንለው፣ መኢሶን አሁንም የሃቀኛ ተራማጆችን ህብረት እንደሚፈልግ ነው። እስካሁን የተፈጠረው ህብረት የይስሙላ እንጂ፣ እውነተኛ ህብረት አልነበረም። በህብረቱ ውስጥ እኩልነት የለም። ህብረቱ በዲሞክራሲና በቁም ነገሮች የሚመራ አይደለም። በህብረቱ ውስጥ ቅጥ ያለው የአሰራር ዘዴ የለም። እንዲያውም አሁን የተያዘው ግልጽ አዝማሚያ ህብረቱን የቢሮክራሲ ተቀጥላ ድርጅት ለማድረግ ነው።
አንዳንድ የህብረቱ አባል ድርጅቶች አባሎች፣ ሀቀኛ የፖለቲካና የርዕየተአለም ትግልን በማካሄድ ፈንታ፣ በመኢሶን ላይ ጆሮ ጠቢና የሰብቅ ሴራዎችን ሲያካሂዱ ቆይተዋል። ሕዝቡን እንዴት እናንቃው፣ እንዴት እናደራጀው እያሉ በመጨነቅ ፈንታ፣ መኢሶን ምንድነው የሚሠራው፣ ማን ነው የሚያደራጀው፣ ከማን ጋር ግንኙነት አለው? ….. ወዘተ የሚሉትን የሰላይ ጥያቄዎችን መከታተልና ከዚያም በቀጥታና በተዘዋዋሪ መንገድ ማሳበቅን ሥራቸው ብለው ከያዙት ውለው አድረዋል።
መኢሶን አሁንም ቢሆን የተራማጆችን ህብረት በጥብቅ ይፈልጋል። ነገር ግን ከብረት የተነከረ ህብረት ሊፈጠር የሚችለው ከአድርባይነት፣ ለስልጣን፣ ለቦታና ለስም ከመስገብገብ ይልቁንም ደግሞ ሰፊውን ሕዝብ ከመፍራት ነፃ ሆነን በዲሞክራሲያዊ በሀቅና በዲሞክራሲያዊ ስነስርዓት በሰፊው ሕዝብ በፊት ስንናገር ነው። ያለበለዚያ በጥቂት ግለሰቦች መካከልና ከሰፊው ሕዝብ በስተጀርባ፣ ለሰፊው ሕዝብ ሳይገልጹ፣ የሚካሄዱ የህብረት ውይይቶችና ስምምነቶች የቤተመንግሥት ዱለታዎችን እንጂ አብዮታዊ ሥራዎች አይሆኑም። እውነተኛ ህብረትን ለመፍጠር ከተፈለገ፣ በልዩነት ነጥቦች ላይ ሁሉ፣ የየድርጅቶቹ አባሎች በሙሉ እና ሰፊው ሕዝብም ምንም አይነት ተጽዕኖ የሌለባቸው ዲሞክራሲያዊ ክርክሮችን ለማካሄድ መቻል አለባቸው።
ሶስተኛ። የኢትዮጵያ ወዛደሮች፣ አርሶ አደሮች፣ መለዩ ለባሾች፣ የጭቁን ብሄረሰቦች ታጋዮች፣ ጭቁን ሴቶች፣ ታጋይ ወጣቶች፣ ዲሞክራቲክና አገር ወደድ ግለሰቦች ሁሉ፣ ከላይ ለተጠቀሱት ለአብዮቱና ለአገሪቷ ማዳኛ እርምጃዎች በቆራጥነት እንዲታገሉ መኢሶን ጥሪ ያደርግላቸዋል።
አብዮቱንና አገሪቱዋን ከውድቀት ሊያድን የሚችለው ሀይል የእናንተ ትግል ብቻ ነው። ዛሬ ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ንቃታችንን፣ ድርጅታችንን፣ ትጥቃችንንና አንድነታችንን ማጠናከር አለብን። ባሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ሰማይ ላይ ጥቁር የፀረአብዮት ደመና ቢያንዣብብም፣ በሶማሊያ ወረራ በምሥራቅ እና በደቡብ ምሥራቅ ኢትዮጵያ አንዳንድ ቦታዎች ቢያዙም፣ አገራችንን ብሩህ የእኩልነት፣ የሰላም፣ የብልፅግናና የስልጣኔ ዘመናት ይጠብቋታል። የኢትዮጵያ ሕዝቦች ለነፃነትና ለእኩልነት፣ ለሰላምና ለወደፊት እርምጃ የሚያደርጉት ተጋድሎ እንደዛሬ አመቺ ሁኔታን አግኝቶም አያውቅም። ችግሮቻችንንና ድክመቶቻችንን፣ የአብዮታችን መቦርቦርና የአገራችን መወረር ጊዜያዊ ናቸው። ዘላቂነት የላቸውም። የፖለቲካ መስመር ትክክለኛነት ወሳኝ መሆኑን በመገንዘብ፣ ፖለቲካን አስቀድመን፣ ችግርንና ሞትን ሳንፈራ፣ በሰፊው ሕዝብ ተማምነን እስከመጨረሻው ለመታገል ቆርጠን ከተነሳን፣ አንድነታችንን አጠንክረን ወደፊት ከተራመድን፣ የፈጀውን ጊዜ ቢፈጅና የፈለገውን መሰዋዕትነት ቢጠይቅም በእርግጥ እናሸንፋለን።