ሰሕድ ቁ. 63

የሰፊው ሕዝብ ድምፅ

ቁጥር 63፣    ጥቅምት 17፣ 1970 

የፅሁፉ ፍሬ ሀሳብ

መኢሶን በዚህ እትሙ ከዚህ በፊት በተደጋጋሚ ያነሳውን  የዴሞክራሲ መብቶችን አስፈላጊነት እንደገና ይመለስበታል። ጽሁፍ በተጨማሪ ዴሞክራሲን እንድ ቅንጦት በመቁጠር የዴሞክራሲ መብቶች እንዳይለቀቁ የሚሰጡ ምክንያቶችን (ለምሳሌ “ሕዝቡ የተሰጡትን መብቶች መች በደንብ ተጠቀመባቸው”፣ “እስካሁን የተሰጡት መብቶች በቂ ናቸው”፣ “አናርኪስቶች ወይንም አድሃሪዎች በመብቱ ሊጠቀሙበት ይችላሉ”፣ “በተራማጆች መሃል ንትርክ ይፈጥራል”፣ “አገራችን ህልውናዋ አደጋ ላይ ስለሆነ ዴሞክራሲ በኋላ ይደርሳል” … ወዘተ) አንድ በአንድ እያነሳ የተሰነዘሩት ሃሳቦች ከእውነት የራቁና የተሳሳቱ መሆናቸውን በሰፊው ያብራራል።

የሰፊው ሕዝብ ድምፅ

ለሰፊው ሕዝብ ሰራተኛ ገበሬ፣ ነጋዴ፣ ወታደር፣ ምሁር መብትና ጥቅም የሚታገል ጋዜጣ

የኢትዮጵያ ሰፊ ሕዝብ ይቅደም

ቁጥር 63                                                                       ቀን 17/2/70

 

ዲሞክራሲያዊ መብቶች ለጭቁኖች አለገደብ አሁኑኑ

ባለፈው የሰፊው ሕዝብ ድምጽ ቁጥር የዲሞክራሲያዊ መብቶች ያለገደብ የሚፃረሩ ድርጅቶችና ግለሰቦች የመከራከሪያ ነጥቦች ላይ እንመለስበታለን ያልነው ይታወሳል። የዲሞክራሲያዊ መብቶች ጥያቄ፣ እንኳን ዛሬ ዲሞክራሲያዊ አብዮት ፈንድቶና የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታቸውን ከተሳካ ፍጻሜ ለማድረስ ከመረረ ትግል ውስጥ ገብተው ቀርቶ፣ በጨለማው የኃይለሥላሴ አገዛዝ ዘመን እንኳ፣ “አንገብጋቢና መሰረታዊ” የነበረው ጥያቄ ነበር። ስለሆነም ነው፣ በየካቲት 1966 ዓ.ም፣ የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ እንቅስቃሴ በፈነዳበት ጊዜ፣ የአብዮቱ አንቀሳቃሽ የሆኑት ሁሉ /ተማሪ፣ ምሁራን፣ ወዛደሮችና፣ እርሶአደሮች፣ መለዩ ለባሾችና ሌሎችም/ በአንድ ድምጽና ከዳር እስከዳር ዴሞክራሲያዊ መብቶች እንዲታወቁ ይጠይቁና ይታገሉ የነበረው። ይህ እንግዲህ ምንም እንኳ እንደዚያ በግብታዊነት ቢፈነዳም ቅሉ ማለት ነው።

ምናልባት /እንድገመው ምናልባት/ የዛሬዎቹ የፖለቲካ ተዋናዮችና በየቦታው ተልፈስፍሰው የቀሩት “ተራማጆች” የተገዙት “ግራዎች” ይህንን “አሌ” የማይባለውን ሀቅ “ረስተውት” እንደው በወቅቱ በመለዮ ለባሾቹ ጭምር ይበተኑ የነበሩትን ወረቀቶችና መልዕክቶቻቸውን እንደገና ተመልሰው እንዲያነቧቸው ከማስታወስ በስተቀር ሌላ ልንጨምርላቸው የምንችለው ነገር የለም።

የሆነው ሆኖ፣ ጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ ሥልጣንን ከጨበጠበት መስከረም 1967 ዓ.ም ጀምሮ እንኳን በዲሞክራሲያዊ መብቶች ጥያቄ ላይ ብዙ፣ ብዙ ተፅፎና ተነግሮ እንደነበረም የማይዘነጋን ነው። እያንዳንዳቸው ነፃ የፖለቲካ ድርጅቶችና ቡድኖች በጋዜጦቻቸው ላይ አቋም ወስደዋል። ሕዝባዊ ድርጅቶቹም እንደዚሁ። እንደዚሁም የዲሞክራሲያዊ መብት ብልጭታ “ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ” “ከአብዮታዊ መድረክ” አምድ ላይ በታየበት “ዘመን” ብዙዎች ሰፋፊ ፅሁፎችን እያቀረቡ በጥያቄው ላይ ተከራክረውበታል። “ዲሞክራሲያዊ መብቶች ለማን፣ ለምን፣ በገደብ፣ ያለገደብ” የሚሉትንና ሌሎችንም ጥያቄዎች በዚያን “ዘመን” ሁሉም እንደ የሰፈሩ የተከራከረባቸው ጥያቄዎች እንደነበሩም አይዘነጋንም። ከዚያም፣ በሚያዚያ ወር 1968 ዓ.ም የወጣውን “የብሔራዊ ዲሞክራሲያዊ አብዮት ፕሮግራም” ያገላበጠ ሰው በጥቁርና በነጭ ተጽፎ እንደሚያነበው ሁሉ፣ ዲሞክራሲያዊ መብቶች ለጭቁኖች ያለገደብ “በአስቸኳይ” መለቀቃቸው ለአብዮቱ መግፋትና መሳካት “አንገብጋቢውና መሰረታዊ” ጥያቄ እንደነበረ ወዲያውኑ ይረዳል። በዚህም ሳይበቃን፣ የጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ ሊቀመንበር፣ ሌ/ኮ መንግሥቱ ኃይለማርያም ውስጥ የነበረውን ተራማጅ ክንፍ “እጅና እግሩን የፊትኝ አስረው” የነበሩት አድሃሪዎች ጥር 26 ቀን 1969 ከተወገዱ በኋላ በማግስቱ ያደረጉትን ንግግር ተመልሰን ብናነብ ስለ ዲሞክራሲያዊ መብቶች ለጭቁኖች ያለገደብ በአስቸኳይ መለቀቅ ጉዳይ ብዙ እንደተናገሩ እናያለን። ከዚህ ሁሉ በላይ ደግሞ የዲሞክራሲያዊ መብቶች ጥያቄ በቀድሞው የሕዝብ ድርጅት ጉዳይ ጊዜያዊ ጽ/ቤት አማካኝነት ረቅቆ ለደርግ ከቀረበ አንድ ዓመት ተኩል እንዳለፈውም የታወቀ ነገር ነው። የመጨረሻም የአምስት ተራማጅ ድርጅቶች “የሕብረት ኮሚቴ” የካቲት 18፣ 1969 ዓ.ም በወጣው “የጋራ መግለጫው” ውስጥ ከዚህ በታች በምንጠቅሰው ላይ ሙሉ በሙሉ ተስማምቶ እንደነበረ እናስታውሳለን።

“…በአሁኑ ወቅት” ይላል መግለጫው “አብዮቱን ለመቀልበስ ያሰፈሰፉትን አድሃሪያን በይበልጥ ለመቋቋም በስውር ታፍነው የሚሰሩ ድርጅቶች ትግላቸውን በይፋ ለማካሄድ እንዲችሉና በተለይም ደግሞ ሕዝባዊ አብዮታዊ ግንባር ለመመስረት የሚያስችሉትን ዲሞክራሲያዊ ፓርቲዎችና ሰፋፊ ድርጅቶች ለማቋቋም እንዲችሉ ባስቸኳይ ዲሞክራሲያዊ መብቶች ለጭቁኖች ያለ ገደብ መታወጅ አለባቸው”። በኋላ እንደታየው ግን መኢሶንና ኢ.ጭ.ሕ.አ.ት በዚህ አቋም ሲፀኑ አብዮታዊ ሰደድ፣ የወዝ አደር ሊግና ማሌሪድ አቋማቸውን ቀየሩ። በፕሮግራማቸው ውስጥ ሰፍሮ የሚገኘውን “መሰረታዊና አንገብጋቢ” ነጥብ መካድ ጀመሩ።

ከዚህ በላይ ያሰፈርነው አንዳንድ ዋና ዋና ምዕራፎችን ያመለክት እንደሁ ነው እንጂ፣ በዲሞክራሲያዊ መብቶች ጥያቄ ላይ፣ በተፃፉት፣ በተነገሩትና በተደረጉት ላይ ብናትት አንድ ወፍራም መጽሐፍ እንደማይበቃን ግልጽ ነው። እንዲያም ሆኖ ዲሞክራሲያዊ መብቶች ጥያቄ ሲነሳ በአደባባዮች፣ በሴሚናሮች በውይይት ክበቦችና በልዩ ልዩ ስብሰባዎች ላይ ያኔ “በደህናው ቀን” የተገኘ ሁሉ ግራ ክንዱ ከብብቱ እስኪነቀል ድረስ ወደ ሰማይ እየሰቀለ “ዲሞክራሲያዊ መብቶች ለጭቁኖች ያለገደብ ባስቸኳ” እያለ ያሳይ የነበረውን ትርዒት ለቲያትር ደረሲዎች መተው እንደሚኖርብን አንጠራጠርም። እንቀጥልና፣

ዛሬስ በዚህ “አንገብጋቢና መሰረታዊ” ጥያቄ ላይ ከየት ደርሰናል? ሁለቱ መስመሮች የትኞቹ ናቸው? ለአብዮቱ መግፋትና መሳካት “አማራጭ የሌለው” የትግል መስመር የትኛው ነው?

የመጀመሪያው መስመር ምን ይላል?

የመጀመሪያው መስመር ተከታዮች ስለ ዲሞክራሲያዊ መብቶች ጥያቄ እንዲነሳ አይፈልጉም። ቢነሳም በጣም ተድበስበሶ እንዲያልፍ ይፈልጋሉ። የመከራከሪያ ነጥቦቻቸውም፣ ከዚህ በታች የምናሰፍራቸው አራት ነጥቦች ናቸው። እንዘርዝራቸው እነሱ እንደሚሉት፣

አንደኛ የዲሞክራሲያዊ መብቶች ለጭቁኖች ባይሟሉም የተወሰኑ ዲሞክራሲያዊ መብቶች ተሰጥተዋል። ለምሳሌ የገበሬ ማህበራት፣ የሠራተኛ ማህበራት፣ የከተማ የቀበሌ ማህበራት… አንዳንዶቹ ናቸው። በነዚህ ለመጠቀም ሳይችሉ ተጨማሪ መብቶችን መጠየቅ የአድሃሪዎች መሳሪያ መሆን ነው።”

ሁለተኛሞክራሲያዊ መብቶች ከመንግሥት ስልጣን ጥያቄ ተገንጥለው የማይታዩ/ ስለሆነም፣ ዛሬ ዲሞክራሲያዊ መብቶች ለጭቁኖች ያለ ገደብ ባስቸኳይ” ወይንም ደግሞ “አሁኑኑ ማለት የመንግሥትን ስልጣን መጠየቅ ነው።” በነሱ አባባልማ ይህ ደግሞ “የጊዜያዊ ሕዝባዊ መንግሥት” ወይንም ደግሞ የአናርኪቲስት ኢ.ሕ.አ.ፓ ወይንም ደግሞ የአደሃሪዎች ጥያቄ ነው።”

ሦስተኛ “በተራማጆች መካከል ንትርክ መፍጠርና ለአድሃሪዎች በር በመክፈት ነው

አራተኛ “አብዮት የምትኖረው አገር ስትኖር ነውና፣ የዲሞክራሲያዊ መብቶችን ጥያቄ በአሁኑ ጊዜ ማንሳት ግራ ቀደምነት ነው።”

የመጀመሪያው መስመር ተከታዮች የዲሞክራሲያዊ መብቶች ለጭቁኖች ያለ ገደብ መለቀቅን በመፃረር የሚያቀርቧቸው ዋና ዋና የመከራከሪያ ነጥቦቻቸው ከዚህ በላይ እንደተዘረዘረው ነው። “ስለሆነም ይላሉ መጨረሻው ላይ” የጊዜው ትክክለኛና አብዮታዊ መፈክር “ዲሞክራሲያዊ መብቶች ለጭቁኖች ያለገደብ ባስቸካይ ወይንም አሁኑኑ” ሳይሆን “ዲሞክራሲያዊ መብቶች ለጭቁኖች በትግል” የሚለው ነው ይላሉ።

እዚህ ላይ ወደ ታች እንደምናመለክተው ይህ መፈክራቸው የፖለቲካ ፌዝ እንደሆነ ግልጽ ነው። ከዚያም በላይ ለመጨመር ያህል መጪዎቹ ዲሞክራቲክና ተራማጅ ደራሲያን የትርዒቱን ገቢር ሁለት ሊጀምሩ እንደሚችሉ አንጠራጠርም።

እስቲ ተመልከቱት፦

የጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ ስልጣን ለሰፊው ሕዝብ ለማስረከብ ቃል ኪዳን በገባበት የብሄራዊ ዲሞክራሲያዊ አብዮት ፕሮግራም ላይ ዲሞክራሲያዊ መብቶች ያለ ገደብ በአስቸኳይ እንደሚለቀቁ አስታውቆ ሌሎችም ይህንን የሚያረጋግጡ መግለጫዎች እንዲተላለፉ ከዚህ በላይ ተገልጿል። ግን እንደገና ከጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ አባሎች ጭምር “ዲሞክራሲያዊ መብቶች ለጭቁኖች በትግላችን” የሚለውን “አዲስ” መፈክር ሲያስተጋቡ ማየት እጅግ በጣም ግራ የሚያጋባ ነገር አይደለም ወይ? በዛሬይቱ ኢትዮጵያ የፖለቲካ ስልጣንን የያዘው ጊዜያዊ ወታደራዊ መንግሥት ነው። ይህ መንግሥት ደግሞ እንደሚያውቀው ዲሞክራሲያዊ መብቶች ለጭቁኖች ያለገደብ እንዲለቀቁ ለማድረግ ቃል ገብቷል። ሰፊው የኢትዮጵያ ሕዝብ በዚህ ረገድ ዛሬ የሚያደርገው ትግል ጊዜያዊ ወታደራዊ መንግሥት ይህንን በፅሁፍ፣ በአደባባይ የገባውን ቃል እንዲያከብር ነው። የጊዜያዊ ወታደራዊ መንግሥት አባሎች እንኳን ሳይቀሩ “ዲሞክራሲያዊ መብቶች ለጭቁኖች” ያለገደብ/ “ያለ ገደብ የሚለው ቃል ብዙ ጊዜ አይታይም/ በትግላችን” በሚለው መፈክር ሕዝብን ለማሰለፍ ሲሞክሩ ማየት ሚስጥሩ ምንድነው። ትግሉ ከማን ጋር ነው? ሰፊው ሕዝብ ከሆነ ግን የሚታገለው ጊዜያዊ ወታደራዊ መንግሥት ቃሉን እንዲያከብር ነው። ጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ ከሆነ ግን ከማን ጋር ነው የሚታገለው? ከራሱ ጋር? ሁሉንም ነገር የያዘው እሱ ነው። ወደ ርእሳችን እንመለስና የመጀመሪያውን መስመር የክርክር ነጥቦችን እንመልከት።

“ዲሞክራሲያዊ መብቶች ባይሟሉም” ይላሉ። እኛም አልተሟሉም እንላለን። “የተወሰኑ ዴሞክራሲያዊ መብቶች ተሰጥተዋል” ይላሉ። እኛም እንላለን። ግን እዚህ ላይ ጥንቃቄ አድርጎ ጭራቅን እየሳሉ ጭራቅ መሆን የሚባለውን አስታውሱ።

ለመሆኑ የኢትዮጵያ ጭቁን ሕዝቦች “ባልተሟሉት” ዲሞክራሲያዊ መብቶችን እንኳን ለመጠቀም ያልቻሉት ለምንድነው?

ሙሉ ዲሞክራሲያዊ መብቶች ስላልታወቁና ስላልተለቀቁ ነው። መቶ አብዮታዊ አዋጆች ቢወጡ፣ በሺህ ድር በተሳሰረው ቢሮክራሲ ሙሉ በሙሉ “እንዳይሟሉና” ወደ ሥራ እንዳይተረጎሙ ስለሚደረግ ነው። የኢትዮጵያ ጭቁን ሕዝቦች “ባልተሟሉት” ዲሞክራሲያዊ መብቶች ለመጠቀም ቢታገሉ እንኳ፣ አድሃሪ የደርግ አባሎችና አሮጌው የኃይለሥላሴ ቢሮክራሲ ስለሚያፍኗቸው ነው። የኢትዮጵያ ሕዝቦች “ያልተሟሉትን” ለማሟላት አንድ እርምጃው ወደፊት ባሉ ቁጥር አድሃሪዎችና ቢሮክራሲው ሁለት ሦስት እርምጃዎች ወደ ኋላ ስለሚገፈትሯቸው ነው።

ታዲያ ዲሞክራሲያዊ መብቶች ሙሉ በሙሉ ባለመለቀቃቸው የአድሃሪዎች መሳሪያ የሆነው ማነው? እነሱ ወይንስ ሰፊው ሕዝብ? እነሱ ወይንስ ሃቀኛ ተራማጆች?

ዲሞክራሲያዊ መብቶች ቢለቀቁስ?

የዲሞክራሲያዊ መብቶች ያለገደብ ለጭቁኖች ያለገደብ ቢለቀቁ ማለት ከአድሃሪው የፊውዶ-ቡርዧ ሥርዓት የተወረሰውን ቢሮክራሲና የመጨቆኛ መሳሪያዎች መደምሰስ ማለት ነው።

ለሰፊው ሕዝብ ሙሉ የመናገር፣ የመፃፍ፣ የመሰብሰብ፣ በነፃ የመደራጀት መብቶችን ማወቅና መልቀቅ ማለት ነው። የሰፊውን ሕዝብ ነጻ እርምጃዎች በክፉ አይን እየተመለከቱ መዓትን ከማውራት ይልቅ፣ ሕዝባዊና አብዮታዊ ዕርምጃዎች መሆናቸውን አውቆ መቀበል ማለት ነው። ስህተቶችና እላፊዎች ቢኖሩ አንኳ፣ ለጉልበት መፍትሄዎች ከመሽቀዳደም ይልቅ፣ በአብዮታዊ መንገዶች ማረም ማለት ነው። እንደዚሁም ሰፊውን ሕዝብ ሳይፈሩ ስለ አብዮቱና ስለ ውድ ሀገሩ እውነቱን መናገር ማለት ነው። ሰፊውን ሕዝብ ማመንና ማስታጠቅም ማለት ነው። በመጨረሻም በተለይ በዚች አገር ውስጥ የሚገኙትን ጭቁን ብሔረሰቦች የራሳቸውን እድል በራሳቸው ለመወሰን የሚያደርጉትን ተጋድሎና ያላቸውንም ሙሉ ዲሞክራሲያዊ መብቶች ማወቅ ማለት ነው። በአጭሩ ሰፊው የአብዮትና የዲሞክራሲ ፍላጎት፣ አብዮታዊነትና የመፍጠር ችሎታዎች ላይ መተማመን ማለት ነው።

ታዲያ እነዚህን አብዮታዊ እርምጃዎች የሚፈሩት እነማን ናቸው? ሰፊው ሕዝብ ወይንስ አድሃሪዎች? ሙሉ ዲሞክራሲን የሚፈሩት የኢትዮጵያ ሕዝቦች ሳይሆኑ፣ አድሃሪዎች ብቻ ናቸው። ስለዚህም “የአድሃሪዎች መሳሪያ የሆነው” በጭቁኖች ላይ የተገደበ ዲሞክራሲ ለመጫን የሚፈልገው ብቻ ነው።

ሰፊው ሕዝብ ሙሉ ዲሞክራሲያዊ መብቶችን ቢቀዳጅ በደመኛ ሦስቱ ጠላቶቹ መቃብር ላይ ይቆማል፣ ሌኒን እንደሚለው

“ወዝአደሩ ተተብትቦ ከታሰረበት ሰንሰለት በስተቀር የሚያጣው አንድም ነገር የለም። ሆኖም፣ በዲሞክራሲ በታገዘው ትግሉ ግን፣ አለማትን በሙሉ የራሱ ለማድረግ ይችላል።”

/ሌኒን “ሁለት ታክቲኮች… የሕዝባዊ ቻይና እትም፣ 1970 ዓ.ም፣ ገጽ 46/

ወደ ሁለተኛው ነጥባቸው እንሻገር፦

በዚህኛው የክርክር ነጥባቸው ለእኛ የሚያሳዩት የፖለቲካ “የዋሆች” መሆናቸውን ነው። የፖለቲካ “የዋሆች” ያልንበት ምክንያት፣ ከመንግሥት ስልጣን ጥያቄ ጋር ያልተያያዘ እንዳችም የፖለቲካ ጥያቄ ስለሌለ ነው። እንኳን የዲሞክራሲ መብቶችን የሚያከለው “አንገብጋቢና መሰረታዊ” ጥያቄ ጠርቶ፣ በያንዳንዱ የማምረቻ ድርጅት ውስጥ የምትነሳው የኢኮኖሚ ጥያቄ እንኳ፣ የፖለቲካ ብሎም የመንግሥት ስልጣን ጥያቄ ነች።

በተጨማሪ እስቲ የሚከተሉትን ሁለት ነጥቦች እናመልክት፦

አንደኛ የዛሬውን መንግሥት ምንነትም ሆነ ከዚያም ተያይዞ “የመንግሥትን ስልጣን ጥያቄ” በነፃ ለመወያያ በዚህም ላይ አቋም ለመውሰድ እንኳ ሙሉ ዲሞክራሲያዊ መብቶች ያስፈልጋሉ። ያድሃሪው ቢሮክራሲ የመጨቆኛ እና የስለላ መሳሪያዎች ካራቸውን በሰፊው አንገት ላይ አሳረፈው ግን ምንም ለመተንፈስ አይቻልም።

ሁለተኛ ጊዜያዊ አብዮታዊ መንግሥት ምንነት፣ በአገራችን ውስጥ የተካሄዱት ክርክሮች እንኳን ቢረሱ፣ ከዚህ ቀደም ስንል ከጠቀስነው መጽሐፍ በገጽ ላይ የሰፈረውን እና የሚከተለውን እንጥቀስ፣

“ጊዜያዊ አብዮታዊ መንግሥት በአቢዮታዊ ወቅት ለሚቋቋም መንግሥት የተሰጠ ስም ነው። ይህ መንግሥት የወደቀውን መንግሥት በቀጥታ የሚተካና በሕዝባዊ አመጽ ላይ የተመረኮዘ እንጅ፣ በአንድ በሆነ የውክልና አይነት የሚመሰረት አይደለም። ጊዜያዊ አብዮታዊ መንግሥት አብዮቱ በፍጥነት ድልን እንዲቀዳጅ የሚያገለግል የትግል መሳሪያ ነው። ማናቸውንም አይነት ፀረ-አብዮታዊ ሙከራ ሁሉ፣ ወዲያውኑ ለመደምሰስ የሚውል የትግል መሳሪያ ነው።”

እንግዲህ ፊታችሁን በመስታወቱ ውስጥ ተመልከቱት

ወደ ሦስተኛው ነጥብ እንለፍ።

ይህኛው ነጥባቸው “በተራማጆች መካከል ንትርክ ይፈጥራል፣ ለአድሃሪዎች በር መክፈት ይሆናል” የሚለው አባባል ርእዮተዓለማዊ ትግልን የሚያውሸለሽል ነጥብና ሰፊውን ሕዝብ ከመፍራት የሚመነጭ አቋም ነው።

አረ ለመሆኑ በፖለቲካ መስመሮች ላይ ነፃና ዲሞክራሲያዊ ክርክሮችን ማካሄድ የሰፊውን ሕዝብ የፖለቲካ ንቃትና ድርጅት ያጠናክራል ወይስ ያዳክማል።

አብዮታዊያን ያጠናክራል ብለው ይመልሳሉ።

ነጻና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ ርዕዮተዓለማዊ ትግሎችን ማካሄድ አብዮታዊ ቲዎሪን ያስፋፋል ወይንስ ያፍናል?

አብዮታዊያን ያስፋፋል ይላሉ።

ነፃና ዲሞክራሲያዊ ውይይቶች ቢካሄዱ፣ አድሃሪዎች በሰፊው ሕዝብ የነቃ ትግል እየተጋለጡ ይተፋሉ ወይንስ እንደዛሬው በየስርቻው መሽገው የተሳካን ፀረ-አብዮት ያከናውናሉ።

አብዮታዊያን ተጋልጠው ይተፋሉ በማለት ይመልሳሉ…. ወዘተ እንግዲህ የመጨረሻውን ነጥባቸውን እናንሳ።

እንደሚታወሰው የክርክር ነጥባቸው “አብዮት የሚኖረው አገር ሲኖር ነው፤ በአሁኑ ጊዜ የዲሞክራሲ መብቶችን ጥያቄ ማንሳት “ግራ ቀደምነት ነው” የሚለው ነው።

ማርክሲስቶች ማርክሲዝምን ቁልቁል ዘቅዝቀው እንደዚህ ባናቱ ያቆሙበት የታሪክ ጊዜ ቢኖር በአንደኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ነው። በዚያን ጊዜ የጀርመኑ ካውትስኪ፣ የሩሲያው ፕሊካኖቭና ሌሎችም እንደዚሁ “እናት አገር” በሚል ስም በየሀገራቸው ወዛደርና ሰፊ ሕዝብ ውስጥ ይህ ነው የማይባል ትምክህተኝነትን አስፋፍተው ነበር። በሃቅ ለመናገር ከተፈለገ ምንም እንኳ አብዛኞቹ የኢትዮጵያ ተራማጆች በነካውትስኪና ፕሊካኖቭ ሬት “አቡጊዳ ቆጣሪዎች” ቢሆኑም በማርክሲዝም ስም ተነስተው “ አብዮት የምትኖረው አገር ስትኖር ነው” ሲሉ በተጨባጭ የሚፈጸሙት ተፋጥጠው ባሉት መደቦች መካከል ሰላም እንዲሰፍንና የመደቦች እርቅ እንዲወርድ ነው።

በኢትዮጵያ ውስጥ ስለ ጦርነት እንነጋገር ከተባለ በአሁኑ ወቅት በብዙ ቦታዎች ጦርነቶች የተባባሱት አብዮቱ “በተሟላ” ዲሞክራሲያዊ ይዘቱ ወደፊት እንዳይራመድ “እጅና እግሩን ተጠፍሮ ስለታሰረ” ነው። በሌላ አነጋገር ሙሉ ዲሞክራሲያዊ መብቶች ስላልታወቁ፣ ስላልተጠበቁና በሥራ ላይ ስላልዋሉ ነው። የኢትዮጵያን ሕዝቦች አንድነት እኩልነት፣ ወንድማማችነትና በመፈቃቀድ ላይ ከመገንባት ይልቅ፣በጠመንጃ አፈሙዝና በትምክህተኝነት “ለመጠበቅ” ስለሚደረግ ነው።

በመጨረሻም አንዲት ማስታወሻ

ዛሬ ለዴሞክራሲያዊ መብቶች “የሚታገሉት ጭቁኖች” ወዝአደሮች፣ አርሶአደሮች፣ መለዮ ለባሾች፣ ምሁራንና ወጣቶች፣ ዲሞክራሲያዊ ግለሰቦችና አገር ወዳዶች፣ እውነተኛ ተራማጅ የፖለቲካ ድርጅቶችና ዲሞክራሲያዊ የጭቁን ብሄረሰቦችን እንቅስቃሴዎች አባሎች እየታደኑ እየተገደሉ ነው።

የታሰሩ ተራማጆች በፍጥነት ይፈቱ!
መኢሶንን ማሳደድ ይቁም!
ዲሞክራሲያዊ መብቶች ለጭቁኖች ያለገደብ አሁኑኑ!
ዲሞክራሲያዊ መብቶች ለጭቁኖች ያለገደብ በአስቸኳይ!
የብሄር ትምክተኝነት ይውደም፣ የብሄረሰቦች እኩልነት ይኑር!
የሀቀኛ ተራማጆች ህብረት ይመስረት!
የፊውዶ ቡርዧው ቢሮክራሲ ይውደም!
የነቃ፣ የተደራጀ፣ የታጠቀ የሕዝብ አመጽ ያሸንፋል!
Scroll to Top