የሰፊው ሕዝብ ድምፅ
ቁጥር 67፣ ነሐሴ 15፣1970
የፅሁፉ ፍሬ ሀሳብ
በዚህ እትም “መኢሶን ከኢማሌድህ ስለመባረሩ” በህብረቱ ጋዜጣ ላይ የተሰጡትን ምክንያቶች አንድ በአንድ እየመረመረና የመኢሶንን ምላሾች ከማስረጃ ጋር እያጣቀሰ ያቀርባል።ባለፉት ወራቶች መኢሶን ለተራማጆች ሕብረት ያደረጋቸውን ጥረቶችና ከሰደድ ጋር ተጀምሮ የነበረው ውይይት ምንም ውጤት እንዳላስገኘ ያስታውቃል። ከአንዳንድ የህብረቱ አባሎች ጋር በዴሞክራሲ መብቶች መለቀቅና በብሄረሰቦች መብት ጥያቄዎች ላይ ልዩነቶች እንደነበሩ ይጠቅስና አሁንም አንገብጋቢ ናቸው የሚላቸው ጉዳዮች ላይ ሰፋ ያለ ትንተና ያቀርባል።
ይገርማል! አንዳንድ ሰዎች ወሮች አልፈው ወሮች ሲተኩ ነገሮችን የመርሳት ዝንባሌ አላቸው። ነገር ግን ደግሞ፣ ከሁሉም ነገር ይልቅ በቅድሚያ ለመርሳት የሚፈልጉት ራሳቸው ተጠያቂ የሚሆኑባቸውን ጉዳዮች ነው። ከህሊናቸው ጋር ለማስታረቅ የሚያስቸግሯቸውን ጉዳዮች ነው። ስለዚህም፣ የማይፈልጉት ምክንያት፤ የማይፈጥሩት ሰበብ፤ ራሳቸውን ለማታለል የማያደርጉት ጥረት የለም። ጉድጓዶችን እየቆፈሩ ራሳቸውን ለመቅበር፣ ግድግዳዉን እየገነቡ ከበስተጀርባቸው ለመሸሸግ፣ በዚህም በዚያም ብለው ህሊናቸውን “ለማሳረፍ”…. አያሌ አስደናቂ ጥረቶችን ያሳያሉ። አስደናቂ የሆኑ የሎጂክ አክሮባቶችን እየሰራሉ።
ይሁንና እንደዚህ ያሉት ሰዎች ደግሞ፣ በአንድ ወገን ካለፈው ስህተታቸው ምንም አይማሩም። በሌላ ወገን ወደ ሚቀጥለው ከባድ ስህተት በቀላሉ ይገባሉ። የመጨረሻ መጨረሻም ወዳቂዎች ናቸው።
በፖለቲካ ድርጅቶችን በኩል እንደዚሁ ነው።
የፖለቲካ ድርጅቶች እውነተኛ ማርክሲስት ሌኒኒስት /ማሌ/ እስካልሆኑ ድረስ፣ “ኑሮውን” የሚገፉት እንደተባሉት ሰዎች ይሆናል። ስለዚህም ቅራኔዎችን ለይተው በመልክ በመልካቸው አይመለከቱም። የነገሮችን ምንነት ከሁሉም አንፃር አያጤኑም። በተቃራኒ፣ ለነርሱ ለጊዜው የሚጠቅሟቸውን ነገሮች በማውሳት ብቻ ይወሰናሉ። የሌላውን ወገን ክርክርና የአቋም ነጥቦች ወይም ፈጽሞ አያቀርቡም ወይ ደግሞ ቆነፃፅለውና አጣመው በማቅረብ መሰረት ሊያሳጧቸው ይጥላሉ። ነገሮችን ይሸፋፍናሉ። ራሳቸውን በጣም በቀላሉ ያመፃድቃሉ። ሌሎችንም በጣም በቀላሉ ይኮንናሉ። በነባራዊ ሁኔታዎች ላይ ተመርኩዘው ሃቀኛ ትንታኔዎችን ከማድረግ ይልቅ፣ ስሜቶችን በመቀስቀስና በመማፀን ላይ ያተኩራሉ። ስሜቶችን የሚማጸኑ ቃላቶችንና ሃረጎችን በመደርደር ከእውነት ለማምለጥ ይሞክራሉ። በተለይ የፕሮፓጋንዳ መሳሪያዎችንና መድረኮችን እስከያዙ ድረስ ደግሞ፣ ደጋግሞ በመለፍለፍ በዚህም በዚያም ማሳመኑ ቀላል ነው ብለው ያምናሉ። ይህንኑ አድራጎታቸውን ደግሞ ራሳቸው ተመልሰው እንደ አብዮታዊ ሥራ፣ እንደ አብዮታዊ ድል ይቆጥሩታል። ይኩራሩበታል። እስከሚቀጥለው ትርምስ ድረስ እንደዚሁ ይቀጥላል። ከዚያም እንደዚያው።
ኢማሌድህ፣ “መኢሶን ከኢማሌድህ አባልነት ተሰረዘ” በማለት “በህብረት ድምፅ” /ሕ.ድ ቁ.1 ቁ.4 ሚያዚያ 1970/ ልሳኑ ያወጣውን ፅሁፍና ውሳኔ ስንመለከት በመጀመሪያ የተገነዘብነው ከዚህ በላይ የተናገርነውን እውነት ነው። ስለዚህም ነገሮችንና ቅራኔዎችን ….ወዘተ ተመልሶ በትክክል የማስታወስ እና በትክክለኛ መልካቸው የማስቀመጡ ተግባር ዋናው ተግባር ሆኗል። ይህም ጽሑፍ የዚሁ ዝክር ነው።
ነገር ግን ከመቀጠላችን በፊት ደግሞ መኢሶን ዛሬም ቢሆን ሀቀኛ፣ ታጋይ፣ አብዮታዊና ዲሞክራሲያዊ የሆነ የተራማጆች ህብረት እንዲመሠረት የሚጠይቅና ለዚህ የተቀደሰ ተግባር ሳያቋርጥ የሚታገል መሆኑን ደግመን ልናሳውቅ እንወዳለን። በኛ ተራማጆች መካከል ያሉት ቅራኔዎች ዛሬም ቢሆን በውይይትና በዲሞክራሲያዊ ዘዴዎች ሊፈቱ እንደሚችሉ የመኢሶን ጽኑ እምነት መሆኑን በድጋሚ እናስታውቃለን።
መኢሶን በዚህ በኩል ከረጅም ጊዜ ጀምሮ የሚያደርገውን ጥረት በሀቅ እንደሚገፉበትም እንደዚሁ በድጋሚ እንገልፃለን። የተራማጆች በዚህም በዚያም እና ሆኖ ባልሆነው መካረር ለፀረ አብዮት እንጂ ለአብዮታችን መግፋት እንደማይጠቀም የመኢሶን እምነት ነው። መኢሶን ከተባለው ውሳኔም በኋላ ቢሆን ውይይትን በመጠየቅ ለኢማሌድህ ግልፅ ደብዳቤ እንደጻፈ በተጨማሪ እናስታውቃለን።
መኢሶን ከረጅም ጊዜ ጀምሮና ዛሬም የሚያቀርባቸው ጥያቄዎች ግልጽ ናቸው። እነርሱም የሚከተሉት ናቸው።
1/ ለውይይት አመቺ የሆኑ ሁኔታዎች ይፈጠሩ፣
2/ ለዚህም የታሰሩትን የመኢሶን አባሎች፣ ደጋፊዎችና ወዳጆች ይፈቱ
3/መኢሶን ላይ የሚደረገው የግድያ፣ የክትትልና የእስራት ዘመቻ ይቁም፣
4/ዲሞክራሲያዊ መብቶች ይታወቁ፣ ይከበሩ።
መኢሶን ስህተቶች ካሉ፣ በበኩሉ በመጀመሪያ በውስጥ ከዚያም በኋላ በይፋ ሂስና ግለ ሂስ ለማድረግ ዝግጁ ነው።ነገር ግን ለዚህም ቢሆን ያመቹ ሁኔታዎች መፈጠር ይቀድማል።
ከእንግዲህም ወደ “ሕብረት ድምፅ” ጋዜጣ እንመለስና ፅሁፉና ውሳኔውን አንድ በአንድ እንመልከት፣ አስተያየታችንን እንስጥ። አቋማችንን እንግለፅ። በዚህ ጽሁፍ ውስጥ በተለይ ካልተመለከቱ በስተቀር ስርዞችና ቅንፎች የኛ ናቸው። እንደዚሁም በተለይ ካልተመለከቱ በስተቀር በክንፎች ውስጥ የሚገኙት ቁጥሮች /የ“የሕብረት ድምፅ”/ ቁጥር 1 ቁጥር 4 መጽሄትን ገጾች የሚያመለከቱ ናቸው ።
ግንቦት 15 1970 ተጠናቅሮ ያለቀ
የኢማሌድህን ጽሁፍ የመጀመሪያው ገፆች ስናገላብጥ የምናገኘው የመጀመሪያወ ጉዳይ፣ ባለፉት ዘጠኝ ወሮች ውስጥ ኢማሌድህ በመኢሶን የትግል ስልት ለውጥ ላይ የወሰዳችውን ሁለት አቋሞች ነው። እነርሱም እንደሚከተለው ተገልጸዋል።
ኢማሌድህ በመጀመሪያ የወሰደው አቋም፣
“መኢሶን ከሌሎች የኢማሌድህ አባል ድርጅቶች ጋር ያሉት ልዩነቶች ሊፈቱ ይችላሉ” /12/ የሚል ነበር።
ኢማሌድህም ለዚህ፣
“ለቆይታው ፖሊሲ ምክንያት አለው። ኢማሌድህ መኢሶን የሰራውን ስህተት አርሞ፣ ካጋደለበት አደገኛ አዝማሚያ ተነስቶ ህብረቱን ለማጠናከር፣ አብዮቱን ለማራመድ እንደ ድሮ ትግሉን ይቀጥላል የሚል ግምት ስለነበረው ነው። በኋላ ግን” ይላል ጽሑፍ ቀጠል አድርጎ፣
“በኋላ ግን መኢሶን አንዳንዴ የተመልካችነት፣ አንዳንዴ ከአድሃርያን ጋር በተግባር በመተባበር ላይ በመሆኑ በፖለቲካ ወደ ኢህአፓ እየተጠጋ በመምጣቱ፣ ኢማሌድህ ዛሬ ነገ ሳይል ቁርጥ ያለ አቋም መውሰድን ውሳኔ መስጠት አስፈላጊና ወቅታዊ መሆኑን አምኖበታል” /12/
እንግዲህ መኢሶን በነሐሴ 1969 የትግል ስንት ለውጥ ካደረገበት ጊዜ ጀምሮ ዘጠኝ ወሮች አልፈዋል። በኢማሌድህ “የቆይታ ፖሊሲና ዛሬ ነገ የማያሰኘው ወቅታዊ ውሳኔም” መካከል እንደዚሁ ዘጠኝ ወሮች አልፈዋል። ይሁንና ከዚህ በላይ የጠቀስነውን ያነበበ ሰው “ለመሆኑ በመካከል ምን ተካሄደ” በማለት ራሱን መጠየቁ አይቀርም። ይህችን “በኋላ ግን….” የተባለችን ነገር ለማወቅ መጓጓቱም አይቀርም።
የኢማሌድህን ጽሁፍ ይህንኑ ጥያቄ በመመለስ ይመስላል “በኋላ ግን…..” በማለት ጀምሮ ነበር። ነገር ግን አንባቢው በጽሁፉ ውስጥ መኢሶን አንዳንዴ ተመልካች፣ አንዳንዴ አድሃርያን ጋር ተባባሪ፣ ደግሞ በፖለቲካ አቋሞች ወደ “ኢህአፓ የተጠጋ መሆኑን” የሚያስረዳ አንድም ነገር አያገኝም። አንባቢው ከመስመር መስመር ያነባል። እስከ መጨረሻው ድረስ ይወጣዋል። ተመልሶ እንደገና እስከመጨረሻው ድረስ በርጋታ ያነባል።…ወዘተ። ትርፉ ድካም ይሆናል። ብቻ በመጨረሻው ላይ የውሳኔውን ቁጥር 5 ሲያነብ የሚከተለውን “ነጥብ” ያገኛል፣
“ካደረገው አሳፋሪና ፀረ አብዮት ሽሽት እንደ ኢህአፓ ጭልጥ ብሎ ወደ ፀረ አብዮት ካምፕ በመንጎዱ” /27/
በዚህ “ሽሽት” በሚለው ጉዳይ ላይ ዝቅ ብለን እንመለስበታለን። ይሁንና ከመቀጠላችን በፊት ደግሞ፣ ኢማሌድህ “በኋላ ግን…” በማለት የጀመረውን ነገር በተጨባጭ ማሳየትና ማረጋገጥ ይኖርበታል እንላለን። በዚህ በኩል በኢትዮጵያ ሰፊ ሕዝብና በተራማጆች ሁሉ ዘንድ ተጠያቂ ነው። ነገር ግን፣ ዛሬም በሬዲዮና በገለፃዎች ላይ እንደሚደረገው አሉባልታዎች፣ የወሬ ወሬዎችና የፈጠራ መረጃዎች ተደርድረው ነገሮችን እንዳያተራሙስና እንዳይበክሉን ደግሞ ከአሁኑ አጥብቀን እንጠይቃለን። ይታሰብበት እንላለን። በኛ በኩል ግን ለኢማሌድህ ሂሳዊ ክስ የምንሰጠው ቀጥተኛ መልስ ከዛሬው ግልፅ መሆኑን ልናሳውቅ እንወዳለን።
መኢሶንን በሚመለከት ኢማሌድህ የሚገኝበት ግልጽ ችግር ቢኖር፣ ኢማሌድህ መኢሶንን በፖለቲካ መስመርና በርዕዮተ ዓለም ጥያቄዎች ላይ በሃቅና በዲሞክራሲያዊ መንገዶች ተከራክሮ ለመርታት አለመቻሉ ነው። የመኢሶንንም የፖለቲካ መስመር ከሰፊው ሕዝብ ውስጥ “ታግሎ” ለመውጣት አለመቻሉ ነው። ስለዚህም ኢማሌድህ መኢሶንን ለመምታት ያገኘው “ቀላል” መንገድ መኢሶንን “አዲሱ ኢህአፓ” ማድረግ ብቻ የሚለው ነው። ዘጠኝ ወሮች ሙሉ “ቀኝ መንገደኛ” ቢል “ፈርጣጭ” ቢል የሚሰማው፣ የሚያምነውና የሚያዳምጠው አጥቷል። መኢሶን በሥራ አንዲተረጎም የሚጠይቀውን የዲሞክራቲክ መብቶች ጥያቄ ከሰፊው ሕዝብ ውስጥ ሊያወጣው አልቻለም። ችግሩ ይህ ነው። ደግሞ ከሁሉም የሚያስገረመው ነገር፣ ይልቁኑ ኢማሌድህ “በፖለቲካ” ብቻ ሳይሆን በድርጅታዊ ሥራዎች ጭምር “ወደ ኢህአፓ እየተጠጋ በመምጣቱ” አያሌ መረጃዎች የተገኙ ናቸው። ለዚህም፣ በኢማሌድህ አባል ድርጅቶች ውስጥ ተሰግስገው የሚገኙትን /የቀድሞ/ የኢህአፓ አባሎች ልናስታውስ እንችላለን።በኢማሌድህ አባልነት ስምና መኢሶንን ለመቋቋም በሚደረገው ትግል /የቀድሞ/ የኢሀፓ አባሎች በሕዝባዊ ድርጅቶች ውስጥ በማንሰራራት ላይ መገኘታቸውን ልንገልጽ እንችላለን….ወዘተ
ለማንኛውም እኛ ደግሞ “ለመሆኑ በመካከል ምን ተካሄደ?” የሚለውን ጥያቄ ለመለስ እንሞክር። ኢማሌድህም ሆነ የሃቀኛ ተራማጆችን ህብረት በሚመለከት የመኢሶን አቋምና የወሰዳቸውን እርምጃዎች እናስታወቅ። የአንድ የፖለቲካ ድርጅት አቋም መቼም በልሳኑ አማካኝነት ነውና፣ እሱን በመጥቀስ እንጀምራለን። አንባቢዎች ቀኖችንና ወቅቶችን ልብ ብለው እንዲያገናዝቡ እናስታውሳለን።
ሰሕድ 61/ነሃሴ 1969
“መኢሶን አሁንም ቢሆን የተራማጆችን ህብረት በጥብቅ የፈልጋል። ነገር ግን ከብረት የተነቀረ ህብረት ሊፈጠር የሚችለው ከአድርባይነት፣ ለስልጣን፣ ለቦታና ለስም ከመስገብገብ ይልቁንም ደግሞ ሰፊውን ሕዝብ ከመፍራት ነፃ ሆነን፣ በሀቅና በዲሞክራሲያዊ ሥነሥርዓት በሰፊው ሕዝብ ፊት ስንናገር ነው።…. እውነተኛ ህብረት ለመፍጠር ከተፈለገ በልዩነት ነጥቦች ላይ ሁሉ፣ የየድርጅቶቹ አባሎች በሙሉ እና ሰፊው ሕዝብም ምንም ዓይነት ተፅዕኖ የሌለባቸው ዲሞክራሲያዊ ውይይቶችን ለማካሄድ መቻል አለባቸው።”
ሰሕድ ልዩ እትም/ 7.1.70
“የተራማጅን ህብረት በሚመለከተው በኩል፣ መኢሶን አሁንም ቢሆን የሃቀኛ ተራማጆችን ህብረት ይፈልጋል። ግን ከዚህ በፊት እንደነበረው፣ በወረቀት ላይ ህብረት፤ በተግባር ሽኩቻ ለኢትዮጵያ አብዮት አይጠቅምም። እነ እገሌ እንዲህ ናቸው፡ እንደዚያ ያደርጋሉ ማለትን ትተን በሚያስማሙንና በሚለያዩን መሰረታዊ ነጥቦች ላይ እንወያይ። ለእውነተኛ ውይይት ዲሞክራሲያዊ ውይይት ብቻ ሳይሆን፣ ሀቅም ያስፈልጋል።….ፀረ መኢሶን ዘመቻ የያዙ ድርጅቶችም የድብብቆሽ ጨዋታውን ወደ ጎን ይተውና በሃቅ እንወያይ።”
ሰሕድ 62/25.1.70
“የዲሞክራሲ መብቶች ለጭቁኖች ያለ ገደብ በአስቸኳይ መለቀቁ በአብዮቱ ሰፈር ለሚገኙት ብዙ ችግሮች መፍትሄ ይሰጣል።
“1 …በአብዮቱ ሰፈር የተሰለፉት ልዩ ልዩ ኃይሎች በመካከላቸው ያለውን ግንኙነት በየወቅቱ ለማስተካከልና ያሉትንና ሊነሱ የሚችሉትን ልዩነቶች ለማቻቻል ያበቃቸዋል። በትግልም ውስጥ የሚገጥሟቸውን የጋራ ችግሮች ለመፍታትና ለማስወገድ ለውይይት የሚያስችላቸውን ዲሞክራሲያዊ መድረክ ይከፍትላቸዋል።”
“2. የተራማጆችን ህብረት እውነት ያደርገዋል። በተግባር የሚተረጉምበትን ሁኔታ በጣም ያፋጥነዋል። የዲሞክራሲ መብቶች ለጭቆኖች ያለ ገደብ አለመለቀቅን ተገን አድርገው አሉባልታና ሃሜት የሚነዙትን ለማጋለጥ ያስችላል።”
ሰሕድ 63/17.2.70
“ነፃና ዲሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ ርዕዮተ አለማዊ ትግሎችን ማካሄድ አብዮታዊ ቴዎሪን ያስፋፋል ወይስ ያፍናል?
አብዮታውያን ያስፋፋል ይላሉ።
ነፃና ዲሞክራሲያዊ ውይይቶች ቢካሄዱ፣ አድሃሪዎች በሰፊው ሕዝብ የነቃ ትግል እየተጋለጡ ይተፋሉ ወይስ እንደ ዛሬው በየስርቻው መሽገው የተሳካን ፀረ አብዮት ያከናውናሉ?
አብዮታዊያን ተጋልጠው ይተፋሉ በማለት ይመልሳሉ።….ወዘተ”
ሰሕድ 64/7.3.70
ይህ “ለሃቀኛ ተራማጆች የትግል አንድነት ጥሪ” በሚል ርዕስ በ16 ገጾች የታተመው ሰሕድ፣ እንደለ ለውይይት፣ ለሀቀኛ የተራማጆች ህብረት፣ ለትግል አንድነት ጥሪ የሚያደርግ ነው። ለመጥቀስም ብንፈልግ ፅሁፉን በሙሉ መጥቀስ ይኖርብናል። አንዱን አንስቶ አንደኛውን ለመተው አይቻልም። አንባቢዎች ሰህድ 64ን እንደገና ተመልሰው እንዲያጠኑት ብቻ ጋብዘን እንመለሳለን።
ሰሕድ 65/ 21.5.70
“መኢሶን በአገራችን አብዮት አንገብጋቢ ጥያቄዎች ላይ ለትግሉ ይበጃሉ የሚላቸውን አቋሞች ከመሰንዘር ተቆጥቦ አያውቅም። በተራማጆች መካከል ልዩነቶች እንዳሉና እነዚህ ልዩነቶች በውይይት እንዲፈቱ ተደጋጋሚ ጥሪዎችን አድርጓል።ብዙን ጊዜ ግልጽ አቋም የሌላቸው ወይም ደግሞ ያላቸውን አቋም በይፋ በሕዝብ ፊት ማብራራት የማይደፍሩ አድርባዮች ያሉትን መሰረታዊ ልዩነቶች በማቃለል የሰው አስተሳሰብ በተራ አሉባልታዎች ላይ እንዲያተኮር ይሞክራሉ።… የመኢሶን ምኞት ሃቀኛ አብዮታዊ መስመር ላይ የተገነባ ከኢትዮጵያ ማርክሲስት ሌኒኒስቶች ድርጅቶች ውህደት የሚፈልቅ ከብረት የጠነከረ የወዛደር ፓርቲ ለመመስረት አስተዋጽኦ ለማድረግ ነው።”
ሌሎች ልንጠቅሳቸው የምንችላቸው አያሌ ጽሁፎች አሉ። ይሁንና በሰሕድ እትሞች ላይ ብቻ ተወስነን እዚሁ ላይ እናቆም። ጽሑፉ አለቅጥ እንዳይረዝም ብለን እናስባለን። በተረፈ ከዚህ በላይ ከጠቀስናቸው ጽሁፎች ብቻ እንኳ፣ የመኢሶን ያልተናወጸ አቋም እና መስመር ግልጽ ነው። ግን እንግዲህ፣ በእነዚህ ሁሉ ወራቶች ውስጥ ከባድ ጭቆናና አያሌ ግልጽ እና ስውር ጥቃቶች ቢደርሱበትም ማለትም ጭምር ነው።
ከእንግዲህም መኢሶን ወደ ወሰዳቸው ተጨባጭ እርምጃዎች እንሻገር እና ስለ እነርሱ ደግሞ እንናገር።
መኢሶን የትግል ስልት ለውጥ ካደረገም በኋላ ቢሆን፣ ከጊ.ወ.አ. ደርግ እና ከኢማሌድህ ጋር ለመገናኘትና ለመወያየት አያሌ ጥረቶችን አድርጓል። በዚህ ጽሁፍ ውስጥ ዝርዝር ነጥቦችን ለማንሳት ባንፈልግም፣ በመኢሶን ቀስቃሽነት በአዲስ አበባ ውስጥ ከሚገኙት አንዳንድ ወዳጅ ኤንባሲዎች ጀምሮ እስከ መንግሥትና የውጭ አገሮች ተራማጅ የፖለቲካ ድርጅቶች ድረስ ድምጻቸውን አሰምተዋል። በተጨማሪ ውይይቶች እንዲከፈቱ መኢሶን አያሌ ቀጥተኛ እርምጃዎችን ወስዷል። የዚህ “ታሪክ” እንደሚከተለው ነው። ይሁንና፣ ወደ “ታሪኩ” ከመግባታችን በፊት ደግሞ፣ በተባለው የመኢሶን ጓድ ላይ እርምጃ እንዳይወሰድበት እንጠይቃለን።
በጥር ወር ውስጥ መኢሶን አንድ አባሉ በመጀመሪያ በኢንፎርማል ደረጃ ውይይት ሊጀመር የሚችልበትን መንገዶች እንዲሻ ይመድበዋል። ጓዱም በዚህ ወር ውስጥ /በ24.5.70/ ከአንድ በአብዮታዊ ሰደድ ድርጅት ውስጥ አነስተኛ ቦታ አለው ከማይባል ጓድ ጋር ይገናኛል። በተራማጆች መሰብሰብና በውይይት ጉዳይ ላይ ሃሳብ ልውውጥ ያደርጋል። “መኢሶን አሁንም ቢሆን አብሮ የመስራት ፍላጎት እንዳለው” ያስረዳል። የአብዮታዊ ሰደድ ጓድም፣ የራሱን አንዳንድ አስተሳሰቦች ይሰነዝራል። መጨረሻም “የመወሰን መብት እንደሌለውና ጉዳዩን እንደሚያስተላልፍ” ገልጾለት ይለያያሉ።
በ29.5.70 እነዚሁ ሁለት ጓዶች እንደገና ይገናኛሉ። የአብዮታዊው ሰደድ ጓድ “ከሦስት ሰዎች ጋር መገናኘቱንና መወያየቱን” ይገልፃል። እነዚህ ሰዎች “በተራማጆች መሰብሰብ ላይ የሚስማሙ መሆናቸውንና መኢሶንም ወደ ሕብረቱ መግባት የሚፈልግ ከሆነ፣ ደስ የሚላቸው መሆኑን እንደገለጹ” ያሳውቃል። ይሁን እንጂ፣ “ከሦስቱ ሰዎች መካከል፣ ሁለቱ መኢሶን የተሳሳተ እርምጃ የወሰደ መሆኑን እንዲገልጽ እንደጠየቁና አንደኛው ግን ስህተቱን በአመራር ደረጃ ካመነበት ይበቃል የሚል አቋም እንደወሰደ” በተጨማሪ ይገልፃል።
በዚህ ጊዜ የመኢሶን ጓድ “እንደዚህ አይነቶቹን የቅድሚያ ግዴታዎች /ኮንዲሽንስ/ ከመጀመሪያው ማስቀመጥ ችግሮችን እንደሚፈጥር” ያስረዳል። “በቅድሚያ የተካረረው ቅራኔ እንዲለዝብ፤ ውይይቶች እንዲከፈቱ፤ የታሰሩት ጓዶች እንዲፈቱ፤ በመኢሶን ላይ የሚደረገው ክትትልና እስራት እንዲቆም፤ በአጠቃላይ ለውይይት አመቺ የሆኑ ሁኔታዎች እንዲፈጠሩ” ይጠይቃል። በተጨማሪ “ሂስን” በሚመለከተውን በኩል፣ “መኢሶን ስህተቶች ካሉ እንደማንኛውም ማሌ ድርጅት በመጀመሪያ በውስጥ ከዚያ በኋላ በይፋ ሂስና ግለ ሂስ እንደሚያደረግ” ያሳውቃል። ከዚህ በኋላ፣ የአብዮታዊ ሰደድ ጓድ “የታሰሩትን የመፍታት ጉዳይ የደርግ ጉዳይ መሆኑን” ይናገራል። ሁለተኛው ግንኙነት በዚህ ዓይነት ያከትማል።
ሦስተኛ ግንኙነት እጅግ ከፍተኛ በሆነ ደረጃ የተካሄደ ነበር። መኢሶን በወቅቱ በወሰደው ግምት፣ ይህ ሦስተኛው ግንኙነት ጉዳዩ ወደ ከፍተኛ ደረጃ እንደተሻገረ የሚያመለክት ነበር።
በ21.6.70 ከመኢሶን በኩል ለዚሁ ሥራ ለተመደበው ጓድ ከከፍተኛ ስፍራ ስልክ ይደወላል። ጓዱም ተጠርቶ ወደ ስፍራው ይሄዳል። በብዙ አርዕስቶች ላይ 45 ደቂቃ የፈጀ ውይይት ይካሄዳል። ውይይቱ በመጨረሻ ምንም እንኳ ለድጋሚ ግንኙነት ቢቀጠርም፣ አያሌ ፍንጮችን የሚሰጥ እና ለውይይት አመቺ ሁኔታዎች ሊፈጠሩ እንደሚችሉ የሚያመለክት ነበር። የመኢሶን ጓድ፣ “ድርጅቱ ስህተቶች ካሉ እርማቶችን ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን፤ ነገር ግን ባለው ተፅዕኖ ምክንያት ይህንን ለማድረግ እንኳ አመቺ ሁኔታ እንዳልተገኘ” ያስረዳል ከዚህም በማያያዝ “የታሰሩት ጓዶች እንዲፈቱ፤ በመኢሶን ላይ የሚደረገው ክትትልና እስራት እንዲቆም፤ ለውይይት አመቺ ሁኔታዎች እንዲፈጠሩ ጠይቆ” ቀጠሮውን በመጠበቅ ይሰናበታል።
ከዚህስ በኋላ?
ከዚህ በኋላ መኢሶን በተባለው ቀጠሮ መሰረት የግንኙነቱን መቀጠል ይጠብቃል። ነገር ግን ቀጠሮው ተራዝሞ ይቆያል። ሆኖም፣ መኢሶን እስከዚሁ ጊዜ ድረስ በተደረጉት ኢንፎርማል ውይይቶች ላይ በመመርኮዝ፣ ውይይቱን ወደ ፎርማል ደረጃ ለማሳደግ ጥረቶችን ያደርጋል።
ይህንንም ሀሳቡን በ21.7.70 በተፃፈ በአንድ ደብዳቤ አማካኝነት በቀጥታ ያሳውቃል። በተጨማሪ በዚሁ ወር ውስጥ በአብዮታዊ ሰደድ በኩል ለጊ.ወ.አ ደርግ በተላለፈ ደብዳቤ አንደኛ ከሦስት—አምስት ተወካዮች የሚገኙበት አንድ የውይይት ኮሚቴ እንዲቋቋም ይጠይቃል። ሁለተኛ የመኢሶንን ጥያቄዎች ዘርዝሮ ያስታውቃል። ሦስተኛ መኢሶን ከመጀመሪያው የሚቀበላቸውን ነጥቦች ይገልፃል። በመጨረሻም ውይይቱ ወደ ፎርማል ደረጃ እንዲሻገር ሀሳብ ያቀርባል። በዚሁም አቅጣጫ አንዳንድ እርምጃዎችን የወሰደ መሆኑን ያስታወቃል።… ወዘተ።
እንግዲህ አያሌ ዝርዝር ነገሮችን ወደ ጎን ትተን፣ መኢሶን በነሐሴ 1969 እና በሚያዚያ 1970 ዓ.ም. መካከል የወሰዳቸው አቋሞችና እርምጃዎች ከዚህ በላይ የተመለከቱት ነበሩ። አሁን በሚያዚያ ወር፣ መኢሶን ለውይይት እንዲያመች በማለት “በጊዜው የኢትዮጵያ ሁኔታ ላይ ያሉትን አስተያየቶችና አቋሞች” በዝርዝር ጽፎ/ ጽሁፉ በሰሕድ 66 ታትሞ ወቷል/ ለመላክ በመዘጋጀት ላይ እንዳለ፣ ከሌላው መስመር “ዛሬ ነገ ሳይል ቁርጥ ያለ አቋም መውሰድና ውሳኔ መስጠት አስፈላጊና ወቅታዊ መሆኑን አምኖበታል” የሚል “ውሳኔ” ደረሰው። መኢሶን በዚህ ሰዓት “ዛሬ ነገ የሚያሰኝ” ምን ጉድ ተፈጠረ! “ወቅታዊውን” ወቅትስ ምን ዓይነት ተአምር ወቅታዊ አደረገው? በማለት ከመጠየቅ በስተቀር የሚጨምርለትን ነገር አጥቷል!!! የፖለቲካ ድርጅቶች ዛሬም ቢሆን በመኢሶን ላይ ለመወሰንና ለመረባረብ የሚያደርጉትን ጥረት በመገረም ጭምር!!! እየተመለከተው ነው።
ውሳኔውስ ይሁን፤ ይወሰን። ነገር ግን ኢማሌድህ ስለ “ቆይታው ፖሊሲ” ከተናገረ አይቀር፣ ከዚህ በላይ ያነሳናቸውን ጉዳዮች ሁሉ የሸፈናቸው ለምንድነው? ይህንን ጉዳይ በሚመለከት፣ 9 ወሮች ሙሉ ምን ሲያደርግ ነበር “የቆየው”? ኢማሌድህ የመኢሶንን ተደጋጋሚ ጥያቄዎች እንዴት “ሊረሳቸው” ቻለ? “በኋላ ግን….” የሚለውን የሚያረጋግጠው በምንድን ነው? ወይንስ “መቆየት” የእኛ ፋንታ፤ ውይይትና መሻት የነእርሱ በሚል “ዛሬ ነገ ሳይባል” ከመጀመሪያው ተወስኖ ነበር? ይህ ከሆነ “ያሉት ልዩነቶች ሊፈቱ ይችላሉ”፣ ስለዚህም “የቆይታን ፖሊሲ” ተከተልን በማለት የተፃፈው ከማን በፊት ለመመጻደቅ ነው? ከማን በፊት ለመመጻደቅ ነበር? ኢማሌድህ መኢሶንን አስመልክቶ እንደጠየቀው ለመጠየቅ ያህል፣ “ለመሆኑ ኢማሌድህ ማንን ነው የሚሸነግለው? የሚያታልለው? ራሱንና አባላቱን? ኢማሌድህን? ወይንስ ሰፊውን ሕዝብ? “/21/
እርግጥ ነው። እነዚህን የሃቅ ጥያቄዎች በማቅረባችን የበለጠ የጭቆና አመጽ እንዳይወርድብን ደግሞ እናስባለን። ይሁንና፣ መኢሶን አሁንም ቢሆን በአቋሙ የጸና መሆኑን ደግሞ እዚሁ ላይ በድጋሚ እናሳውቃለን። ሃቀኛ ተራማጆች ችግሮቻቸውንና ቅራኔዎቻቸውን በውይይትና በዲሞክራሲያዊ ዘዴዎች ሊፈቷቸው ይችላሉ። የጊዜው የተራማጆች ዋነኛ የትግል መስመር ሃቀኛ፣ ታጋይ፣ አብዮታዊና ዴሞክራሲያዊ የሆነ የተራማጆች ህብረት እንዲመሰረት መታገል ነው። መኢሶን ያሻው ነገር ቢደርስ ከዚህ ዋነኛ መስመሩ ዝንፍ አይልም። ትክክለኛው መስመር ይህ ብቻ ነው በሚለው መስመሩ የጸና ነው።
ሆኖም፣ አመቺ ሁኔታዎችን ለመፍጠር የሚችለው ደግሞ ጊ.ወ.አ ደርግ ነው። የታሰሩት የመኢሶን አባሎች ይፈቱ፣ ወዳጆችና ደጋፊዎች ይፈቱ። በመኢሶን ላይ የሚደረገው የክትትልና የእስራት ዘመቻ ይቁም። መኢሶን ለውይይት፣ ለሂስና ለግለ ሂስ፣ለሃቀኛ የተራማጆች ህብረት አመቺ ሁኔታዎች እንዲፈጠሩ ይጠይቃል፣ ለዚህም ይታገላል። ትግሉ ይቀጥላል።
የኢማሌድህ ጽሁፍ እንደሚያስረዳው ከሆነ፣ መኢሶን የትግል ስልት ለውጥ ከማድረጉ በፊት የነበሩት የልዩነት ጥያቄዎች ሁለት ናቸው። እነዚሁም የብሔረሰቦችን ጥያቄና የዲሞክራሲ መብቶችን ጥያቄ የሚመለከቱ ነበሩ።
እስከዚህ ድረስ እኛም እንስማማለን። ይሁንና፣ ወደ ኋላ በአያሌ ጥያቄዎች ላይ ልዩነቶች ተፈጥረው እንደነበረም የሚታወቅ ነው ብቻ በነዚህኞቹ ላይ ዝቅ ብለን የምንመለስባቸው ስለሆነ እነሱን ለጊዜው ትተን ወደ ኢማሌድህ ጽሁፍ እንመለስ።
ኢማሌድህ ባነሳቸው የልዩነት ነጥቦች ላይ የጻፋቸውን ሐተታዎች በአንክሮ የተመለከተ ሰው፣ ከመጀመሪያው የሚያነሳው ጥያቄ “ታድያ እነዚህ ልዩነቶች ናቸው ወይ?” የሚለውን ጥያቄ ነው። በእውነትም ደግሞ የልዩነቶች አቀራረብ ጨርሶ ልዩነቶችን የሚያሳይ አይደለም። እንዲያውም በኢማሌድህ በራሱ አባባል “ሰበቦች” ብቻ እንጂ ልዩነቶች የሉም የሚል ነው። ስለዚህም የኢማሌድህን ጽሑፍ ከተወጣነው በኋላ፣ እኛም ሆንን አንባቢው፣ መኢሶን የትግል ስልት ለውጥ እንዲያደርግ የተገደደባቸውን ምክንያት፣ በመኢሶን ላይ ያንን የሚያህል ውሳኔ ለምን እንደተላለፈ ሳንረዳ እንቀራለን። በአጭሩ ሁለቱም ነገሮች የታሪክ እንቅፋቶች መስለው ቁጭ ይላሉ።
ብቻ ነገሮችን ለመሸፋፈን ካልሆነ በስተቀር፣ ለመገላለጥ ከሆነ እንደዚህ በቀላሉ ለመዝለል የሚቻል አይመስለንም። እኛው ብንቀጥል የተሻለ ነው።
ጽሑፉን ያነበቡት ሰዎች እንደሚረዱት፣ ኢማሌድህ ባነሳቸው ሁለት ጥያቄዎች ላይ ያሉትን ልዩነቶች “ለማሳየት” የሚፈልገው ድርጅቶቹ የፕሮግራም ነጥቦች ላይ ብቻ በመወሰን ነው። ስለዚህም ነው ኢማሌድህ ስለልዩነቶቹ “ሲናገር” አንዳችም ልዩነቶች አጥቶ ቁጭ የሚለው። እንዲያውም “ሰበቦች” ብቻ እንጂ፣ ልዩነቶች የማይታዩት። ይሁንና ከመጀመሪያው እንኳ ደግሞ ኢማሌድህ ይህንን ዓይነቱን አቀራረብ መርጦ መነሳቱ በራሱ የሚያስገረም ነገር ነው።
በብሔረሰብ ጥያቄ ላይ ለማተት ሲጀምር፣ በቅድሚያ አምስቱ ድርጅቶች ውስጥ በፕሮግራማቸው ውስጥ ስለዚህ ጉዳይ ያሰፈሩትን ነጥብ ይጠቅሳል። ምንም ዓይነት “የመርሆ ልዩነት” ያጣበታል። ስለዚህም በመጨረሻው ላይ፣ “ይህን ደግሞ” ይልና፣
“ይህን ደግሞ እንደ ፕሮግራማቸው ከሆነ ሁሉም ውጠውታል። እውነቱ ይህ ሆኖ ሳለ፣ መኢሶን ልዩነቱ በመርህ ደረጃም እንደሆነ አድርጎ ያቀርበዋል። ይህ መቼም አልኩባይነት ነው። የኢማሌድህ ድርጅቶች የሚያምኑበትን፣ የሚሉትን፣ እንደማያምኑበት፣ እንደማይሉት አድርጎ የሕዝቡን አስተያየት ለመወናበድ ነው” /16/ በማለት ይደመድማል።
ኢማሌድህ ስለ ሊሞክራሲ መብቶችም ሲናገር የሚከተለው ይህንኑ መስመር ነው። በዚህም በኩል፣
“የያንዳንዱ ድርጅት አቋም /በዲሞክራሲያዊ መብቶች ጥያቄዎች ላይ-ቅንፍ የሰ.ሕ.ድ./ ባጭሩ ከፕሮግራማቸው ላይ በመጥቀስ ማሳየቱ ለአመለካከታችንና ለምንወስደው አጠቃላይ አቋም ይጠቅማል” /18/
በማለት ይጀምርና ይቀጥላል። በመጨረሻም ሁሉም ፕሮግራም፣
“መሰረታዊ የሕዝብ መብቶች በሚቋቋመው “ሕዝባዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ” ውስጥ እንደሚረጋገጡ ይገልፃሉ /ሁሉም ድርጅቶች/…በሕዝባዊ ሥርዓት ውስጥ መሆኑን በፕሮግራማቸው አማካኝነት ያረጋግጣሉ” /19/
በማለት ደግሞ “ልዩነት” ያጣበታል።
በእውነቱ ከዚህ በላይ እንዳልነው፣ ይህ ከሆነ መኢሶን ለምን የትግል ስልት ለውጥ እንዳደረገ አንገነዘብም። በመኢሶን ላይ ያንን የሚያክል “ውሳኔ” ለምን እንደተላለፈም አንረዳም።
ነገር ግን ጽሁፉ ደግሞ ይቀጥላል። እንደውነቱ ከሆነ የሚደመደመው፣
“መኢሶንና ኢጭአት ይህንን ሁሉ ይስቱና “የዲሞክራሲ መብቶች ለጭቁኖች አሁኑኑ በአስቸኳይ ይታወጁ” እያሉ ከሰፊው ሕዝብ ዘንድ አደገኛ ውዥንብር መንዛት ጀምረው ነበር። /ሆኖም ይህ/ መሰሪና ትጥቅ አስፈቺ መፈክር በርዮተዓለማዊ ትግል ተሸንፏል። ተጋልጧል። ሰፊው ሕዝብ አልተቀበለውም።” /19-20/ በሚል ፍርድ ነው።
መቼም በዚህ በኩል ጠበቃውም ዳኛውም አንድ አካል እስከሆኑ ድረስ፤ “ይግባኙን” በአብዮታዊ ትግል አማካኝነት እናመለክታለን ከማለት በስተቀር ሌላ አማራጭ የለንም። ብቻ በዚሁ ከመቀጠላችን በፊት ደግሞ፣ የመጀመሪያው ሥራችን ስለ ፕሮግራምና የፖለቲካ አቋም ጥያቄ መናገር ሳይሆን አይቀርምና በእርሱ እንጀምር። “በርዕዮተዓለም ትግል ተሸንፏል። ተገልጧል። ሰፊው ሕዝብ አልተቀበለውም” የሚለውን ለራስ የተሰጠ የስልጣን ፍርድ እስኪ ሰፊው ሕዝብ በዲሞክራሲያዊ መንገድ አቋሙን እንዲገልጽ ዴሞክራሲያዊ መብቶች አሁኑኑ ይሰጡትና ይታይ ብለን እናልፈዋለን።
መቼም ለአንድ የፖለቲካ ድርጅት፣ ፕሮግራምን የማርቀቅ ያህል ከሰማያት በታች የቀለለ ነገር የለም። ይሁንና አንድን የፖለቲካ ድርጅት ደግሞ ለፕሮግራሙ የመታገልን ያህል ከባድ ትግል፣ ከባድ ፈተና አይገጥመውም። በተጨማሪ፣ የአንድ ድርጅት ማንነት በፕሮግራሙ ነጥቦች ብቻ የሚገለጽ ቢሆን ኖሮ የፖለቲካ መስመር ትግል…. ጨርሶ አስፈላጊ ባልሆነ ነበር፣ አንደዚሁም ድርጅቶች በፕሮግራማቸው ላይ አንድ ዓይነት ወይም ተመሳሳይ ነጥቦችን በማስፈራቸው ብቻ የሚተባበሩ ቢሆኑ ኖሮ፣ እንደ ሕብረትም የቀለለ ነገር ባልኖረ ነበር። በመጨረሻም፣ ፕሮግራም የሚባለው ነገር ብቻ በቂ ቢሆን ኖሮ፣ ድርጅቶች ልሳኖችን፣ መጽሔቶችን፣ መግለጫዎችን….ወዘተ ለማውጣትና በየጊዜው አቋማቸውን ለመግለጽ ባልተገደዱ ነበር። ለኛም ቢሆን ይህ አድካሚ ፅሁፍ ወድያ በቀርልን ነበር።
ነገር ግን የአንድ የፖለቲካ ድርጅት ፕሮግራም የድርጅቱን ርዕዮተ ዓለማዊ እምነትና የመደብ አቋም የሚያሳይ፣ ድርጅቱ የቆመላቸውን መርሆች በአጭር ባጭሩ የሚገልጽ፣ የድርጅቱን የቅርብና የሩቅ ጊዜ አላማና ግብ የሚዘረዝር አጭር መግለጫ ነው። የአንድ ድርጅት የድርጊት አጠቃላይ መመሪያ ነው። ከዚህ ውጪ ሌላ ትርጉም ምንም አይኖረውም።
ይሁንና የአንድ ድርጅት ማንነት ደግሞ በፕሮግራም መግለጫዎች ብቻ አይታወቅም። አይገለጸም። የአንድ ድርጅት ማንነት ይልቁኑ የሚታወቀው፣
አንደኛ፣ ድርጅቱ ለፕሮግራሙ ባለው ታማኝነት። ሁለተኛ፣ ፕሮግራሙን ለማሟላት የሚያካሂደው ጽኑና ቆራጥ ትግል። ሦስተኛ፣ ከፕሮግራሙ ጋር አገናዝቦ በየግዜው በሚነሱት የፖለቲካ ጥያቄዎች ላይ ሁሉ በሚወስደው የፖለቲካ አቋሙ። አራተኛ፣ የድርጅቱን የውስጥ የፖለቲካ መስመርና የርእዮተዓለም ጥራት ለመጠበቅ በሚያካሄደው ትግል። አምስተኛ፣ በመደብ ደረጃ ከሚቃረኑትና ከሌሎችም አድርባይ እና በራዥ ክፍሎች ጋር በሚያካሄደው የፖለቲካ መስመር፣ የርዕዮተአለም እና ሌሎችም ትግሎች። ስድስተኛ፣ የድርጅቱን የመደብ መሠረት አጥርቶ ለመጠበቅ በሚያካሄደው ትግል። ሰባተኛ፣ በጠቅላላ የትግል ዘዴውና ታክቲኩ…..ወዘተ ነው።
ፕሮግራም አጠቃላይ መግለጫ፣ አጠቃላይ መመሪያ ነው። ለረጅም ጊዜ የሚቆይ ነው። የፖለቲካ ሁኔታዎች ግን በየጊዜው ይቀያየራሉ። የፖለቲካ ጥያቄዎች በየጊዜው ይፈልቃሉ። አንዳንዴም በየዕለቱና በየሰዓቱ ሊሆን ይችላል። በዚያው ልክ ደግሞ፣ ለአንድ የፖለቲካ ድርጅት በየጊዜው ጥያቄዎች ላይ አቋሙን መግለጽ ግዴታ ነው። የአንድ የፖለቲካ ድርጅት ማንነትና ምንነት የሚታወቀውም ይልቁንም በየጊዜው ጥያቄዎች ላይ በሚወስዳቸው አቋሞች ነው።
እነዚህ ሁሉ የፖለቲካ እውቀት ሀሁ ናቸው። የኢማሌድህ አባል ድርጅቶች እነዚህን ሁሉ የመጀመሪያ ደረጃ ዝርዝሮች ያጧቸዋል ብለን አንገምትም። እኛም የዘረዘር ናቸው “ለአልኩባይነት” አይደለም። ይሁንና፣ እንደምን እንደረሷቸውም ሳይደንቀን አልቀረም። ወይንስ ነጥቦቹን ሁሉ አንስቶ ልዩነቶችን ማሳየት “ለምንወስደው አጠቃላይ አቋም የሚጠቅም” /18/ ሳይሆን ቀርቶ ይሆን?
ጥያቄውን መመለስ የኢማሌድህ ጉዳይ ነው። እኛ ግን፣ ልዩነቶች ግልጽ ሆነው የሚታዩት በፕሮግራም ነጥቦች ሳይሆን፣ በየጊዜው የሚነሱት የፖለቲካ ጥያቄዎች ላይ በሚወሰዱት ወይንም በማይወሰዱት የፖለቲካና የርዮተዓለም አቋሞች ነው እንላለን። እንደውም ዋነኛው መመዘኛ ይህኛው ነው እንላለን። ነገር ግን ደግሞ አንዲት የመጨረሻ ነጥብ፡-
አንድ የፖለቲካ ፕሮግራም እንዳልነው፣ የአንድ የፖለቲካ ድርጅት የቅርብና የሩቅ ጊዜ አላማና ግብ ያሳያል። በመሆኑም፣ በኢማሌድህ በትክክል እንደተጠቀሰው ለምሳሌ መኢሶን በእውነትም ፕሮግራሙ ውስጥ፡-
“ሕዝባዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ኢትዮጵያ ስትመሰረት የሰፊው ሕዝብ የንግግር፣ የጽሁፍ፣ የጋዜጣ፣ የመሰብሰብ፣ በፖለቲካም ሆነ በሞያ የመደራጀት ነፃነቶች፣ ሰላማዊ ሰልፍና የሥራ ማቆም መብቶች ያለአንዳች ገደብ ተከብረው በስራ ላይ እንዲውሉ ይደረጋል” ይላል።
ታዲያ እኮ ኢማሌድህ ለማሳመን እንደሚፈልገው፣ይህ “ዲሞክራሲያዊ መብቶች አሁኑኑ” እንዲገኙ ከመጠየቅና ከመታገል አያግድም። የፕሮግራም ነጥብም ንግርት አይደለም። በቀላሉ እናስረዳ።
የኢትዮጵያ ተማሪዎች በኃይለሥላሴ ዘመን “መሬት ላራሹ” የሚለውን ፕሮግራም በድርጅቶቻቸው ፕሮግራምና አርማ ላይ ጽፈውት ነበር። በዚያን ጊዜ የነበረው የመኢሶን ፕሮግራምም እንደዚሁ “ሕ.ዲ.ሬ.ኢ ስትመሠረት መሬት ላራሹ እንዲሆን ይደረጋል” ይላል።
ታዲያ ይህ በመሆኑም፣ የኢትዮጵያ ተራማጆች በኃይለሥላሴ ዘመን “ለመሬት ላራሹ” ሳይታገሉ ቀሩ ወይ? “መሰረታዊ የሕዝብ መብቶች የሚረጋገጡት ሕዝባዊ ሥርዓት ሲመሰረት ብቻ መሆኑን በፕሮግራማቸው አማካኝነት አረጋግጠው” /19/ በቀጠሮ አሳደሩት ወይ? በመጨረሻስ “በትግላችን” የምትለው ተቀፅላ ኖረች አልኖረች፣ ትግሉ ሊቀር ነው ወይ? የመደብን ትግል ተቀብሎ “በትግላችን” ብሎ መፈክር እኮ፣ ራስን እንደ መደቦች ትግል ፈጣሪ አድርጎ እንደ ማቅረብ የሚያስቆጥር ነው። የመደብ ትግል እንዲሁ፣ ብንወድም ብንጠላውም አለ። አለ።
ይልቁኑ የጦፈውን የመደቦች ትግል ተራማጆች እንዴት ተባብረው ይምሩት? አንገብጋቢው ጥያቄ ይህኛው ነው።
ወደ ልዩነቶች ጥያቄ እንመለስ።
እንደተመለከትነው፣ ኢማሌድህ በብሔረሰቦች ጥያቄ ላይ “በመርህ ደረጃ” ልዩነት የለም ይላል። እኛ ደግሞ፣ በብሔረሰቦች ጥያቄ ላይ ያለው ልዩነት አሁንም ቢሆን “በመርህ ደረጃ” ጭምር ነው እንላለን። ይህ ልዩነት ደግሞ፣ በተለየም ከወዝ ሊግ ጋር ከፕሮግራም ነጥብ አንስቶ ይጀምራል። እንደሚከተለው ነው።
በእውነትም፣ የኢማሌድሕ ጽሑፍ በትክክል እንደጠቀሰው፣ ወዝ ሊግ በፕሮግራሙ ውስጥ፣
“ የራስን እድል በራስ መወሰን እስከ መገንጠል ድረስ የሚለው ሌኒኒስት ስታሊንስት መርህ ሳይንሳዊነት ትክክለኛ መርህ መሆኑን ይቀበላል” /14/
ይሁንና፣ ወዝ ሊግ በፕሮግራሙ ውስጥ ቀጥሎ ደግሞ፣
“ይሁንና፣….በአሁኑ የኢትዮጵያና የዓለም ሁኔታ…. ይህ የሌኒኒስት መርህ ሁለት ገጾች /የመገንጠል ገፅና የአንድነት ገፅ- ቅንፍ ሕ.ድ/ በአንደኛው ላይ፣ በአንደቱ ገፅ ላይ እናተኮራለን። ይህ አንድነት የሪጅናል እና ኦቶኖሚ/ የራስን በራስ አገዛዝ -ቅንፍ ሰ.ሕ.ድ./ ቅርጽ መያዝ አለበት ብለን እናምናለን” /14-15/ ይላል።
እንግዲህ፣ ክቡራን የኢማሌድህ ጓዶች! እዚህ ላይ “ከማርክስስት ሌኒኒስቶች” መካከል “በመርህ ደረጃ” ጭምር ልዩነት አይነሳም ወይንም የለም ለማለት ማርክሲዝምን ሌኒኒዝምን ማሰናበት ያስፈልጋል። ምክንያቱም በዚህ ረገድ፣ “ሌኒኒስት መርህ” በምንም ዓይነት ቢሆን “ሁለት ገጾች”‘ የሉትም። እንደዚህ ቢሆን ኖሮ ሌኒን፣ “ብሔረሰቦች የራሳቸውን እድል በራሳቸው ለመወሰን ያላቸውን መብት መገንጠልን ጨምሮና እስከ መገንጠል ድረስ ነው” በማለት ደጋግሞ ባልተናገረ ነበር። ታድያ ከዚህ “ሌኒኒስት መርህ” ውስጥ፣ በምን ዓይነት ተአምር “ሁለት ገጾች” ሊወጡ ይችላሉ? ልዩነቱስ “በመርህ ደረጃ” ካልሆነ፣ በምን “ደረጃ” ላይ ያለ ልዩነት ሊሆን ነው? ሌኒን አዘውትሮ ይጠቀምበት የነበረውን ምሳሌ እንውሰድና “ትዳር መፋታትንም ጨምሮ እስከ መፋታት ድረስ ነው” ወይንስ “ሁለት ገጾች” አሉት? በእውነቱ ሌኒን ስለዚህ “ሁለት ገጾች” ቢሰማ ኖሮ፣ ሌኒን እራሱ “እኔ ሌኒኒስት አይደለሁም” ይል ነበር።
ሁለተኛው ልዩነት ብሄር ወይስ ብሄረሰቦች በሚለው ጥያቄ ላይ የሚነሳው ነው። እንደሚታወቀው በዚህ ጥያቄ ላይ አንዳንዶቹ በኢትዮጵያ ውስጥ ከብሔር /ኔሽን/ ደረጃ የደረሱ ክፍሎች እንዳሉ ሲናገሩ፣ ሌሎቹ የኢትዮጵያ ሕዝቦች በብሔረሰብ /ናሽናሊቲስ/ ደረጃ የሚገኙ ናቸው ይላሉ። ይህንን ጥያቄ በሚመለከተው በኩል፣ መኢሶን እስካሁን የወሰደው አቋም፣ አብዛኞቹ የኢትዮጵያ ሕዝቦች በብሔረሰብ ደረጃ እንደሚገኙ ነው። ይሁንና፣ በተጨማሪ ደግሞ የበለጠ ጥናት መደረግ እንዳለበት ያምናል። በኢትዮጵያ ውስጥ ስለ ብሄረሰቦች ያለን እውቀት እጅግ ዝቅተኛ እንደሆነ እውቅ ነው።
ያም ሆነ ይህ፣ የልዩነቱ መሰረታዊ ጥያቄ ይህ አይደለም። ልዩነቱ የሚነሳው፣ በተለይ ወዝ ሊግና አብዮታዊ ሰደድ፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ማሌሪድም ተጨምራ፣ “በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉት ብሔረሰቦች ብቻ ስለሆኑ፣ እስከመገንጠል ድረስ የሚለው ሌኒኒስት ስታሊኒስት ሳይንሳዊና ትክክለኛ መርህ ለእነርሱ አይውልም። ይህ መርህ የሚውለው ለብሔሮች ብቻ ነው” ሲሉ ነው።
መኢሶን ደግሞ /እኛ እስከምናውቀው ድረስ ኢጭአትም ጭምር/ የሌኒን መርህ ለብሔርም ለብሔረሰቦችም የሚውል ነው ይላል። ለብሔረሰቦች ቁራሽ ዳቦ፣ ለብሔሮች “ሙሉ” ዳቦ የሚል ሌኒኒስት ስታሊኒስት መርህ የለም ይላል። በዚህ መርህ መፋለስ ምክንያት በብሔረሰቦች ላይ የሚጣለውንም ፀረ ዲሞክራሲያዊ ገደብ ይቃወማል።
እንግዲህ ኢማሌድህን እንጠይቀውና፣ ለመሆኑ በዚህ ጥያቄ ላይ ያለው ልዩነት “በመርህ ደረጃ” ጭመር ካልሆነ በምን ደረጃ ላይ ያለ ልዩነት ነው? ወይንስ ኢማሌድህ የብሔረሰቦችና የብሔሮችን መብት “የሚያውቀው” ለአልኩ ባይነት ነው?
ሦስተኛው፣ የልዩነት ነጥብ፣ “ሪጅናል ኦቶኖሚ አማራጭ የሌለው ተግባራዊ መፍትሄ ነው” ከሚባለው አቋም የሚመነጭ ነው። ይህንን አቋም ወዝ ሊግና አብዮታዊ ሰደድ አጠንክረው ሲይዙት፣ ማሌሪድ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ተጨምራበታለች። እነዚህ ድርጅቶች ዛሬ በይፋ ቅስቀሳ እያካሄዱበት ናቸው።
መኢሶን ግን /እኛ እስክምናውቀው ድረስ ኢጭአትም/፣ አንድ “አማራጭ የሌለው ተግባራዊ መፍትሄ” ብቻ አለ ብሎ አያምንም። በዚህ በኩል መኢሶን የወሰደው አቋም፣ “ተግባራዊው መፍትሄ እንደሁኔታውና እንደየጊዜው” መታየት አለበት የሚል ነው። ይህም እንደ ሁኔታውና እንደጊዜው ቢሻው በጠበቀ ወይንም በላላ ኮንፌዴሬሽን፣ ቢሻው በጠበቀ ወይንም በላላ ፌዴሬሽን፣ ቢሻው በሪጅናል ኦቶኖሚ፣ ቢሻው አውቶኖመስ ሪጅን፣ ቢሻው በውህደታዊ ….ወዘተ ሊፈታ ይችላል ማለት ነው። በአንድ አስቀድሞ በግትሩ በተወሰነ “አማራጭ በሌለው መፍትሄ” መመራት ግን አያሌ ችግሮችንና አደጋዎችን ይፈጥራል ማለት ነው።
ሆኖም፣ ይላል የኢማሌድህ ጽሑፍ ግን፡-
“ተግባራዊውን መፍትሄ በሚመለከተው በኩል ያለውን ልዩነት ውይይት እንዲፈታው አባል ድርጅቶች ስለ ተስማሙ ጉዳዩ በጣም አሳሳቢ ሊሆን ባልተገባው ነበር”/16/ እርግጥ ነው። በየካቲት 1969 ከእንደዚህ ዐይነቱ ስምምነት ተደርሶ ነበር። ይሁንናም፣ በአንድ በኩል በአንዳንዶቹ አባል ድርጅቶችና በመንግሥት ደረጃ ጭምር “አማራጭ ስለሌለው ተግባራዊ መፍትሄ” በይፋ ቅስቀሳው ሲጦፍና፣ በሌላው በኩል በሀገሪቱ በመላ የብሄረሰቦች ጥያቄ ገፍቶ ሲመጣ በተለይ ማሌ ድርጅቶች አቋማቸውን ከማሳወቅ ይልቅ ሲያደፍጡ ደግሞ፣ ይህንኑ እንደ አቋም አለመቁጠር የዋህነት ይሆናል። የሰጎንን ፖለቲካ መጫወት ይሆናል።
በዚህ በኩል ለምሳሌም ያህል፣ የአፋር ብሔረሰብ ጠይቆት የነበረውንና እስከ ዛሬም የሚታገልለትን የሪጅናል አውቶኖሚ መብት ጥያቄ ልንጠቀስ እንችላለን። በሀረርጌ ውስጥ የሲቪል/ሚሊቴሪው ቢሮክራሲ የቀድሞ ፊውዳሎችን አስታጥቆ በኦሮሞዎችና በሌሎች ብሔረሰቦች ላይ የፈጸመውን ጭፍጨፋ ልናስታውስ እንችላለን። በባሌ/ሲዳሞ በአርሲና በጉጂ ብሄረሰቦች ላይ የደረሱትንም ጭፍጨፋዎች ልናወሳ እንችላለን። እንደዚሁም፣ ካለፈው አመት ጀምሮ በተለይ በደቡብ ክፍላተ ሀገር እየገፋ የመጣውን የብሄረሰብ ጥያቄና የሚሰጡትን ቀላል መልሶች /“ጠባብ ብሄረተኛ”…../ ልናመለክት እንችላለን። በዚህም፣ ብሄረሰቦች መብታቸውን ለማስከበር የሚያደርጓቸው ዲሞክራሲያዊ እንቅስቃሴዎች እየተገደቡ ናቸው። እየታፈኑ ናቸው። ይህ በራሱ ትምክህተኝነትን የሚያጠናክሩ ሁኔታዎች ፈጥሯል። በዚህ በያዝነው ዓ.ም እንኳን በከምባታ /ሃዲያ/ ብሔረሰቦች ላይ ከፍተኛ ጭፍጨፋ ተፈጽሟል። በየስፍራው “ጠባብ ብሄረተኞች” እየተባሉ አያሌ የጭቁን ብሄረሰብ ታጋዮች እስር ቤቶች ውስጥ ተወርውረዋል። ወይንም በጭፍን ተረሽነዋል።
በሌለው በኩል ጉዳዩን “ለማጥናት” አያሌ ኮሚቴዎች እየተቋቋሙ ተመልሰው ፈርሰዋል እንጂ፣ የተወሰደ ተጨባጭ እርምጃ የለም።አሁን ደግሞ፣ “ከተጨባጭ እርምጃዎች በፊት የብሄረሰቦች ኢንስቲትዩት” የሚል መፈክር እየተስተጋባ ነው። ይሁንና፣ በመካከል ደግሞ የብሄረሰብ እንቅስቃሴዎች ስፋት እያገኙ፣ እየተሰበሰቡና እየተደራጁ በመምጣት ላይ ናቸው።
እንግዲህ አቋማችን ምንድነው?
የኢማሌድህ ጽሁፍ በትክክል እንደጠቀሰው፣ መኢሶን በአሁኑ ወቅት /እንደገና! በአሁኑ ወቅት/፣ “በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉት ብሄረሰቦች” /በኤርትራ የሚገኙትም ብሄረሰቦች ጨምሮ ቅንፍ ሰ.ሕ.ድ./ መገንጠል አይበጃቸውም፣ አንደግፍም ብሏል” /17/
ይህኛው ዛሬም ቢሆን የመኢሶን አቋም ነው። በተጨማሪ፣ ወዝ ሊግ እንደሚለው “የብሔረሰቦች ኢንስቲትዩት” ቢቋቋም መኢሶን ይደግፋል። እንደዚሁም፣ መኢሶን እንደሚለው “የብሄረሰቦች ሸንጎ ቢቋቋም፣ ለብሔረሰቦች አብሮ መኖርና ለአብዮታችን መግፋት የሚጠቅም ይሆናል…ወዘተ።
ነገር ግን መፈክሮች ብቻ ዋጋ የላቸውም። የብሄረሰቦችን ዲሞክራሲያዊ እንቅስቃሴዎች “ጠባብ ብሄረተኛ” በሚል ብቻ ወደ ጎን መገፍተሩም አያዋጣም። “የብሄረሰቦች ኢንስቲትዩትና የብሄረሰቦች ሸንጎ” አንድ እርምጃ ወደፊት የሆኑትን ያህል፣ መሰረታዊ መፍትሄ አይሰጡም።
የመኢሶን ጥያቄ፣ ተግባራዊ እርምጃዎች አሁኑኑ ይወሰዱ የሚል ነው። በዲሞክራሲያዊ ጥያቄዎች አካባቢ የብሄረሰብ እንቅስቃሴዎች አይታፈኑ። እንደውም ይታውቁ። ከነርሱ ጋር ውይይት ይደረግ። እንደሁኔታው መንግሥታዊ ድጋፍ ጭምር ይሰጣቸው የሚል ነው። መንግሥትና ተራማጅ የፖለቲካ ድርጅቶችን እንኳን በእንደዚህ የተደራጁትን ቀርቶ ያልተደራጁትን ለማደራጀት እና ለመደገፍ አሁኑኑ መጣር አለባቸው የሚል ነው።
እርግጥ የባህል ትርዒቶች ጥሩ ናቸው። ሆኖም፣ በፖለቲካዊ ትርጉም መሰረታዊ አይደሉም። የብሄረሰቦች ጥያቄ ከቲያትር ቤትና ከቴሌቪዥን መድረኮች አልፎ እንደሚሄድ ሁላችንም እናውቃለን። የጊዜው ጥያቄ በእርግጥ ድፍረት የሚጠይቀውን ተጨባጭ ተግባራዊ እርምጃዎች የመውሰድ አለመውሰድ ጥያቄ ነው። ይሄኛው የራስን ፊደሎች ከማውጣት መብት አንስቶ እንደሚጀምር ሁላችንም መቀበል ይኖርብናል። ነገር ግን ምን ዓይነት አስተሳሰብ አለ?
በዛሬው ወቅት አንዳንድ ክፍሎች ብሔረሰቦችን በአባታዊነት /ፓቴርናሊዝም/ ሊያዩ ይጥራሉ በሌላው በኩል ትምክተኝነት እየተስፋፋ ነው። የጭቁን ብሄረሰቦች ዴሞክራሲያዊ ትግሎች በሌሊን ስም እየታፈኑና እየተወገዙ ናቸው።
የኤርትራን ጥያቄ በሚመለከተው በኩል፣ ወታደራዊ ኃይላችን በምስራቅ ላይ ቆሞ ወደ ሰሜን መጠናከሩ ትክክለኛ ነው። ይሁንና፣ የኤርትራ ጥያቄ ወታደራዊ የሆነውን ያህል ፖለቲካዊ ፖለቲካዊ የሆነውን ያህል ወታደራዊ ነው። ስለዚህም በሁለቱ ጉዳዮች መካከል ያለው ዲያሌክቲካዊ ግንኙነት በጥንቃቄ መጠበቅና መታየት አለበት። ለኤርትራ ጥያቄ በአሁኑ ወቅት ከመገንጠል በስተቀር፣ ኢትዮጵያ የግዛት አንድነት ውስጥ ማንኛውም የፖለቲካ መፍትሄ የሚያዋጣ ነው። ወታደራዊ መፍትሄ ብቻ ግን፣ ገና ለረጅም ጊዜ አያሌ ችግሮችን ያስከትላል። ስለሁሉም ጉዳይ ከዛሬው ለመናገር የሚቻል አይሆንም።
እንግዲህ ይህኛውን ክፍል በዚህ እንጨርሰው። ይሁንና የመጨረሻው መጨረሻ ደግሞ፣ ይህንን ሁሉ የተናገርነው “ለአልኩ ባይነት” እንዳልሆነ አሳውቀን ወደሚቀጥለው ክፍል እንለፍ። የኢማሌድህ አባል ድርጅቶች እንደእኛ “ካሉ” ደስታችን ነው። እንደኛም “የማይሉ” ከሆነ፣ ለመወያየት ዝግጁ ነን። በተረፈ፣የብሄረሰቦችን ጥያቄ ለመፍታት በሚወሰዱ ዲሞክራሲያዊ እርምጃዎች ሁሉ ባለን አቅም መጠን ከመሳተፍ ወደኋላ እንደማንል እንገልጻለን። ለተቃራኒው አስተላለፋችን ምን ጊዜም ቢሆን የትምክህት ጭቆናና አመጽ ከሚወርድባቸው ጭቁን ብሔረሰቦች ጋር ይሆናል። ነገር ግን እዚሁ ላይ ደግሞ፣ በጥያቄው ላይ ማርክሳዊ ፖሌሚክስን ለማካሄድ፣ አስቀድሞ ማርክሲስት መሆን እንደሚያስፈልግ ለኢማሌድህ ሳናሳስበው አናልፍም። በተረፈ፣ “አዝምሪ! ወፌ አዝምሪ”።
የኢማሌድህ ጽሁፍ በዲሞክራሲ መብቶች ጥያቄም ላይ ያሉትን ልዩነቶች እንዴት እንዳቀረባቸው ከዚህ በላይ አመልክተናል። ይሁንና ኢማሌድህ በጽሁፍ ውስጥ የየካቲት 1969 ዓ.ምን “የጋራ መግለጫ” እንደዚያ ደጋግሞ ሲጠቀስ፣ ስለነበሩ ስምምነቶች እንደዚያ ደጋግሞ ሲያስታውስ፣ በዲሞክራሲ መብቶች ጥያቄ ላይ የተደረሰበትን የጋራ አቋም ግን አንድም ጊዜ እንኳን አለማውሳቱ እጅግ አስገርሞናል። ለምን ይሆን?
ለማንኛውም፣ ኢማሌድህ ከረሳው አይቀር፣ እኛ እናስታውስና እንጥቀሰው። በዚህ ጥያቄ ላይ በየካቲት 1969 የተደረገው ስምምነት የሚከተለው ነበር።
“…… በአሁኑ ወቅት አብዮቱን ለመቀልበስ ያሰፈሰፉትን አድሃሪያን በይበልጥ ለመቋቋም በስውር ታፍነው የሚሰሩ ተራማጅ ድርጅቶች ትግላቸውን በይፋ ለማካሄድ እንዲችሉና በተለይም ደግሞ፣ ሕዝባዊ አብዮታዊ ግንባር መመስረት የሚያስችሉትን ዲሞክራሲያዊ ፓርቲዎችና ሰፋፊ ድርጅቶችን ለማቋቋም እንዲችሉ፣ ባስቸኳይ ዲሞክራሲያዊ መብቶች ለጭቁኖች ያለ ገደብ መታወጅ አለባቸው።”
ስምምነቱ ይህ ከሆነ፣ እንግዲህ በየካቲት እና በነሐሴ 1969 መካከል ድርጅቶቹ ምን ነካቸው? ስምምነቱንስ ያፈረሰው ማን ነው? በተጨማሪ በብሔራዊ ዲሞክራሲያዊ አብዮት ፕሮግራም ውስጥ ስለዚህ ጉዳይ የተጻፈውን ልናስታውስ እንችላለን። በርሱ ውስጥ፣ የፕሮግራሙን ዓላማዎች ከሥራ ላይ ለማዋል ….. ጊዜያዊና አጣዳፊ ተግባሮች” በሚለው ክፍል የሚከተለው ሠፍሯል:-
“1.ሕዝቡ በአብዮቱ መግፋት የሚችለው ነቅቶ፣ ተደራጅቶ፣ ታጥቆ ለትግሉ የተሟላ ዝግጅት ሲኖረው ብቻ በመሆኑና ይህ ዝግጅት ውጤት ሊሰጥ የሚችለው የሰፊው ሕዝብ ወገኖች በሙሉ ለመማር፣ ለማስተማር፣ ለመደራጀትና ለማደራጀት አስፈላጊ የሆኑትን ዲሞክራሲያዊ መብቶች ያለአንዳች ገደብ ከሥራ ላይ ሲያውሉ ብቻ ስለሆነ፣ ለጸረ ፊውዳል፣ ፀረ ቢሮክራሲያዊ ቡርዧ ፀረ ኢምፔሪያሊስት ኃይሎች በሙሉ የመናገር፣ የመፃፍ፣ የመሰብሰብ፣ ስላማዊ ሰልፍ የማድረግ፣ የመደራጀትና የመሳሰሉት ሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች በአስቸኳይ ከሥራ ላይ ማዋል” /25/
የጠቀስናቸው እነዚህ ስምምነቶች እና የጋራ አቋሞች እንደ ኩል ውኃ ጥርት ያሉ ናቸው። ተወዳዳሪ የማይገኝለት የህግ ሊቅ እንኳ፣ ሲፈልግ ቢውል አንድም የሚያሻማ ነገር አያወጣላቸውም። ደግሞ “በሰው ነገር ገባችሁ” እንዳንባል እንጂ፣ የኢማሌድህ ጽሑፍ እንደጠቀሰው በፕሮግራሙ ላይማ ማሌሪድም እንደዚህ ሲል በግልጽ ጽፎ ነበር፡-
“በተለይም የሰፊውን ሕዝብ መደራጀት ለማፋጠን ለጭቁኖች ብቻ የሚሆን የዲሞክራሲ መብታቸውን የመንጠቁ ጉዳይ የጊዜው ዋና ጥያቄ ነው።…. የሰፊው ሕዝብ የመታጠቅ ጉዳይ ከዴሞክራሲያዊ ጥያቄ ጋር እንደ አውራ ሆኖ ቀርቧል።… ይህ ድርጅት፣ /ማሌሪድ/ በቅድሚያ የሚታገልለት ይህ የሰፊው ሕዝብ የዲሞክራሲና የትጥቅ ጥያቄ በሪቮሉሽናዊ መንገድ ግቡን እንዲመታ ነው” /19/
ማሌሪድ ይህንን በግልጽ ቃላት የፃፈውን ፕሮግራሙን፣ እንደገና ተመልሶ ሲያነበው፣ “ታዲያስ በትግላችን ብለን እየታገለን አይደለም ወይ?” ይል ይሆናል። የኛም መልስ አጠር መጠን ያለ ነው።
የመደቦችን ትግል ተቀብሎ “በትግላችን” ማለት፣ ምግብን የምበላው እያኘኩ ነው የማለት ያህል ነው።የመጀመሪያው ሰዎች ቢወዱትም ባይወዱትም፣ ቢጠሉትም ቢፈልጉትም ያለና ነባራዊ የሆነ የህብረተሰብ ሕግ የሆነውን ያህል፣ የኋለኛው ደግሞ ነባራዊ የተፈጥሮ ሕግ ነው። ስለዚህም “በትግላችን” የሚለው በዚህ ነባራዊ ህግ ምክንያት “ሳይንሳዊ” የሚሆነውን ያህል፣ “አሁኑኑ” ደግሞ በዚህ ምክንያት “ኢ-ሳይንሳዊ” አይሆንም። እንደውም “አሁኑኑ” የሚለው ወዲያ ወዲህ ሳይል እንደሚባለው “የምስማሩን ጭንቅላት ይመታል”። “በትግላችን” የሚለውን “ሳይንሳዊ” ማለት፣ ሳይንስን አስማት ለማድረግ እንደሁ እንጅ፣ ለሌላ ለምንም አይጠቅምም። እውነትም አንዳንዴ ስንመለከተው፣ ሰዎች “ሳይንሳዊ” ባሉ ቁጥር አስማት የሚሰሩ ሳይመስላቸው አልቀረም።
መኢሶን “አሁኑኑ” በማለት ያነሳው የዲሞክራሲ መብቶች ጥያቄ ብዙ መጎሳቆል እንደደረሰበት የማይካድ ነው። ይህም የሆነው በመኢሶን ላይ የዞሩ ክፍሎችን ዓይን ያወጡ አድርባዮች በሰጡት የትርጉም ትርጉምና ካካሄዷቸው አጉል ቅስቀሳዎች የተነሳ ነው። ይሁንና፣ መኢሶን የቆመለት መፈክር ወደ ተግባራዊ ነጥቦች ሲተረጎም ሌላ ምንም ፍቺ የለውም። ከዚህ በታች እንደገና የምንዘረዝራቸው አብዮታዊ እርምጃዎች “አሁኑኑ” ይወሰዱ ማለት ነበር። ነውም። አንባቢዎች ጥያቄዎቹን በጊዜው ከነበሩትና ዛሬም ካሉት የፀረ አብዮት ሁኔታዎች ጋር ጭምር አገናዘበው እንዲመለከቷቸው በቅድሚያ በማስታወስ እንቀጥል። “አሁኑኑ” ማለት፡-
- የፊውዶ ቡርዧው ሥርዓት ቢሮክራሲ አሁኑኑ ይመታ ማለት ነበር፤ ነውም።
- የሰፊውን ሕዝብ በበለጠ መደራጀት፣ መንቃትና መታጠቅ አሁኑኑ በበለጠ እናጣድፍ፣ ማለት ነበር፤ ነውም።
- የሕዝባዊ ድርጅቶች ዲሞክራሲያዊና ነፃ ህልውና አሁኑኑ ይታወቅ፤ ይከበር ማለት ነበር፤ ነውም።
- የሰፊው ሕዝብ ነፃ እርምጃዎች አሁኑኑ ይቀጥሉ፣ ይፋፋሙ ማለት ነበር፤ ነውም።
- በሰፊው ሕዝብ ድርጅት ውስጥ የሚያቆጠቁጡትን መሥፍንነትና አምባገነንነት አሁኑኑ እንቅጭ፣ እንቆጣጠር ማለት ነበር፤ ነውም።
- በታሰሩት የኢህአፓ ቅጥር ነፍሰ ገዳዮች ላይ አሁኑኑ እርምጃ ይወሰድ ማለት ነበር፤ ነውም።
- የታሰሩት ሀቀኛ ታጋዮችና የሕዝብ ወገኖች አሁኑኑ ይፈቱ ማለት ነበር፤ ነውም።
- በተራማጆች መካከል ያሉት ልዩነቶች አሁኑኑ በዲሞክራሲያዊ ዘዴ ይፈቱ ማለት ነበር፤ ነውም።
- የተራማጅ የፖለቲካ ድርጅቶች ዴሞክራሲያዊና ነፃ ሕልውና አሁኑኑ ይታወቅ ማለት ነበር፤ ነውም።
- በሲቪል /ሚሊቴሪው አሻጥረኛ ቢሮክራቶች ላይ አሁኑኑ እርምጃ ይወሰድ ማለት ነበር፤ ነውም።
- ከዚህ ሁሉ በላይ ረቅቆ የተቀመጠው የዲሞክራሲ መብቶች አዋጅ፣ አሁኑኑ በሥራ ላይ ይዋል ማለት ነበር፤ ነውም።…….ወዘተ
እንግዲህ እነዚህ ሁሉ ዲሞክራሲያዊ ጥያቄዎች በዚያን ጊዜ ሆነ አሁን ለአብዮታችን መግፋት ወሳኝ አልነበሩም ወይ? አይደሉም ወይ? ለመሆኑ ጥያቄዎቹ በተግባር ሲተረጎሙ ከዲሞክራሲያዊ መብቶች ሌላ ምንድን ናቸው? በዚያን ጊዜ የነበረው የፀረ አብዮቱ ውጥረት ለመከላከል የዘረዘርናቸው ዓይነት አብዮታዊ እርምጃዎች ወዲያውኑ /“አሁኑኑ”/ መውሰድ አያስፈልግም ነበር ወይ? አይቻልም ነበር ወይ? አብዮትና ፀረ አብዮት ዛሬስ እንደምን ተሰልፈዋል?
ኢማሌድህ በዲሞክራሲ መብቶች አስቸኳይነት ጥያቄ ላይ ለመተንፈስ እንኳ አይፈልግም።
አስቸኳይነታቸውን ለመግለጽ የሚፈራውን ያህል፣ “በትግላችን” እያለ ይጮኻል። ነገር ግን ወደመቻል አለመቻል ስንመጣ፣ ኢማሌድህ፡-
“በሰፊው ሕዝብ ‘ነፃ እርምጃ፣ የውስጥ ፀረ አብዮት ኃይሎችን መፍጨርጨር በመግታትና’ በጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ ‘መደናገጥ’ /መካከል/ ያለውን ግንኙነት የደርግ የመደብ ጠባይ መሆኑ ግልጽ ነው።” /25/
በማለት “እቅጩን” ይመልስና ያልፈዋል።
እንደእውነቱ ከሆነ፣ ኢማሌድህ ይህንን ከተናገረ አይቀር፣ በዚያን ጊዜ በደርጉ ውስጥ የነበረውን አሰላለፍ የኃይል ሚዛንን ቢያብራርልን ኖሮ ብዙ ነገሮችን ልንረዳ በቻልን ነበር። ሆኖም፣ ከኢማሌድህ ጽሁፍ ውስጥ ስለዚህ ጉዳይ የምናነበው አንድም ነገር የለም። እኛንም ለብዙ ጊዜ አስቸግሮን የቆየው የአብዮታችን ጥያቄ፣ በአብዮታዊ ሰደድና “በደርግ” መካከል ያለው ልዩነት ነው። በጊዜው “የተለያዩ መሆናቸውን አሳያለሁ” እያለ ሲፎከር የነበረው ወዝ ሊግ እስከ ዛሬ ድረስ አድፍጧል። አስገራሚ ደፈጣ!!!
በእውነትም እርምጃዎቹ በዚያን ጊዜ ያልተወሰዱት “የደርግ የመደብ ጠባይ” አግዶ አይደለም። በደርጉ ውስጥ የነበረው አሰላለፍና የኃይል ሚዛን አግዶ አይደለም። የዘረዘርናቸው ዓይነት እርምጃዎች በዚያን ጊዜ ያልተወሰዱት፣ አንደኛ፣ ባጠቃላይ በተራማጆች መካከል በተፈጠረው አለመተማመን። ሁለተኛ፣ አንዳንድ ድርጅቶች በአድርባይነት ከአቋማቸው በመንሽራተታቸው። ሦስተኛ፣ በተለይ በመኢሶን ላይ በነበሩት ጥርጣሬዎችና እንደዚሁም ጥያቄዎቹ መኢሶን “ሊስፋፋ፣ ሊያብጥ፣ ሊፈነዳ፣ ሌሎችንም ድርጅቶች ሊውጥ…. ወዘተ” ያቀረባቸው ጥያቄዎች ናቸው በሚል ስለተገመቱ ነው። መኢሶን በዚያን ጊዜ ይህንኑ በማመልከት እንደሚከተለው የፃፈውም ስለዚህ ነው። እንጥቀስው፡-
“….ሕብረቱ በዲሞክራሲያዊ አሠራር በቁም ነገሮች ላይ የተመሠረተ መሆኑ ቀርቶ፣ አንድም እርምጃ ወደፊት ለመራመድ እንዳይችል ተሰንኩሎ የማይተማመን ባልንጀራ በየወንዙ ይማማላል እንደሚባለው ሁሉ፣ በወረቀት ላይ የሚቀሩ ፕሮግራሞችን ብቻ ደጋግሞ በመንደፍ ተወስኗል። የአብዮታዊት ኢትዮጵያ ሕልውና ለማስጠበቅና አብዮቱ ስር እንዲሰድ ይጠቅማል በማለት፣ በህጋዊ ሥራ በተሰማሩት ጓዶች አማካይነት፣ መኢሶን ለጊ.ወ.አ ደርግና ለተራማጆች ህብረት በየወቅቱ ያቀረባቸውን አሳቦች በቅን መንፈስና ከአብዮቱ አንጻር በመመልከት ፈንታ፣ አሳቦቹ ከመኢሶን በመንጨታቸው ብቻ ደርግና እንዳንዶቹ ድርጅቶች በጥርጣሬ አይን እያዩዋቸው ከሥራ ላይ ሳይውሉ በመቅረታቸው ለውጥረቱ መፍትሔ፣ ለአብዮቱ የተፈለገውንና የሚጠብቀውን ያህል አስተዋጾ ለማድረግ አልተቻለም” ሰሕድ 61-ነሐሴ 1969/
ነገር ግን መኢሶን ይህንን ሲናገር፣ ኢማሌድህ እንደሚባለው “ወደ ደመናዎቹ ግርማዊ የሆነ ማሸግሸግ” ያደርግና፡-
“መኢሶን በአሉባልታ ብዙ ያምናል። በአሉባልታ ይደናገጣል። አድሀርያን ባወሩና ጡሩምባቸዉን በነፉ ቁጥር የንዑስ ከበርቴ ወኔው ይክደዋል። ስሜን አጠፉት፣ አጥላሉኝ፣ ሊያስመቱኝ ነው በማለት ሮሮውን ያሰማል እንጅ፣ ችግሮቹን አብዮታዊ በሆነ መንገድ ለመፍታት ሙከራ አላደረገም” /26/
በማለት ከባድ “ሂስ” ይሰነዝራል። እንግዲህ በኛም በኩል፣ ወደነበሩት ሁኔታዎች ተመልሰን አንዳንድ ነገሮችን ማስታወስ የግዴታ ሊሆን ነው። ሆኖም፣ እዚህ ላይ ልብ እንበልና፣ ዋናው “ሂስ” “መኢሶንን…..ሮሮውን ያሰማል እንጅ፣ ችግሮችን አብዮታዊ በሆነ መንገድ ለመፍታት ሙከራ አላደረገም” የሚለው እንደሆነ ሁልጊዜም እንድናስታውስ እንጠይቅ። “ሙከራው” ተደርጓል አልተደረገም?— የሚከተሉት ክፍሎች የዚህ ጥያቄ መልሶችም ናቸው።
የኢማሌድህን “የሕብረት ድምጽ” ጋዜጣ በደንብ ያነበቡ ሰዎች እንደተገነዘቡት ሁሉ፣ ኢማሌድህ “ድምፁን” የማያሰማበት ጉዳይ ቢኖር፣ ከጥር 69 እስከ ነሐሴ 69 በነበሩት የህብረቱ ችግሮች እና ጥያቄዎች ላይ ነው። በተጨማሪ፣ አንባቢው፣ በኢማሌድህ ጽሁፍ ውስጥ የሰሕድ እትሞች ቢጠቅሱ ቁጥር 60ና 61 ብቻ እንጂ፣ ከዚያ በፊትም ሆነ በኋላ የወጡት ቁጥሮች አንድም ቦታ ላይ ቢሆን እንዳልተወሱ እንኳ ይገነዘባል። ደግሞ፣ ከሁሉም በላይ የሚያስገርመው ነገር፣ አንደኛ፣ የተጠቀሱት እትሞች በደንብ አልተጠቀሱም። ሁለተኛ፣ የተጠቀሱትም “ጥቅሶች” ቢሆኑ ፈጽሞ አልተተነተኑም። ብቻ መኢሶንን በራሱ ጽሁፍ መልሰው የገረፉት ለማስመሰል፣ “ከጥቅሶቹ” በፊት ወይንም በኋላ “መኢሶን እንዲህ ሲል ገልፆ ነበር” ፣ “ቃል ሲገባ እንዲህ ብሎ ነበር” ፣ “በውሸት ሲመልና ሲገዘት”፣ “ማስመሰልና የአዞ እንባ ማንባት”…. የሚሉት አያያዥ ሐረጎች ተደርድረዋል። “ትንትናውም” በዚህ ያበቃና ስሜትን ብቻ ለመማፀን ሌሎች ሐረጎች ይፈልጋሉ።
መቼም፣ አሁንም እነርሱ ከተውት፣ እኛ ደግሞ እንመለስበትና የነገሮችን ዕድገት ከወቅት ወቅት በአጭሩ እናስታውስ። አንባቢዎች በአንዳንድ ጥቅሶቻችን ርዝማኔ ምክንያት እንዳይሰለቹ ካሁኑ ትዕግስታቸውን እንጠይቃለን። በተጨማሪ የህብረቱን ታሪክ ትንሽ ቀደም ብለን እንጀምራለን። በተረፈ ስህድ ቁ.60 በዚያ መልክ ለምን እንደወጣ ወደፊት ጊዜ ሲመጣና ሁኔታዎች ሲመቻቹ እንደሚገለጽ እናሳውቃለን።
ሰህድ ቁ. 60 /21.11.69/ በትክክል እንዳመለከተው፡-
“የኢትዮጵያ ማርክሲስት ሌኒኒስት ድርጅቶች ህብረት የተቋቋመው፣ ከረጅም ጊዜ ፖለቲካዊና ርዕዮተዓለማዊ ትግል በኋላ እንጂ፣ ባለፈው የካቲት /1969/ ወር የጋራ መግለጫው በወጣበት ጊዜ በድንገት የተፈጠረ አይደለም። በህብረቱ ድርጅቶች መካከል፣ ከዛሬ አመት ገደማ ጀምሮ፣ ረዘም ያሉ የሁለት ወገን /ባይላትራል/ ውይይቶች ተካሂደዋል። አንዳንዶቹ ድርጅቶች፣ ለምሳሌ መኢሶንና ሊግ፣ በፅሁፎቻቸውም ጭምር አሳቦች ተለዋውጠዋል ክርክሮችንም አካሄደዋል።”
ይህንን ጥቅስ የኢማሌድህ ጽሑፍ ጠቅሶታል። ነገር ግን እንደዚህ መሆኑ “ሀቅ ነው” ከማለት በስተቀር፣ ሌላ ተጨማሪ ነገር አይነግረንም። እኛ እናስታውስና ገና ጊ.ወ.አ. ደርግ ከመመስረቱ በፊት፣ መኢሶን ከ1966 ዓ.ም ጀምሮ “የተራማጆች ህብረት” በተሰኘው ጋዜጣው አማካኝነት በዚያን ጊዜ ከነበሩ ከሌሎች ቡድኖች ጋር /ከኢህአፓ ጋር ጭምር/ የጹሁፍ ልውውጥ ሲያደርግ ነበር። ኢህአፓን በሚመለከተው በ1966/67 በቃል ጭምር ብዙ ውይይቶች ተካሄደው ነበር። ሊግን በሚመለከተው በ1968 ዓ.ም መጀመሪያ ላይ “የአዲስ ፋናን” መጽሄት በጋራ በማውጣት በተግባር እንዲተባበሩ ጭምር መኢሶን ሀሳብ አቅርቦ ነበር። ሁለቱ ድርጅቶች አንድ ለዚህ መጽሄት የተመሰረተ የጋራ ኮሚቴ አቋቁመው ለጥቂት ጊዜ ሰርተው ነበር። ይሁንና፣ ወዝ ሊግ በመካከል በአንድ የውስጥ ጹሁፉ ባሰራጨው ፀረ ህብረት ጽሁፍ ምክንያት 1968 ዓ.ም መጀመርያ ላይ ተጀምሮ የነበረው ተግባራዊ ህብረት ተቋረጠ።
ሆኖም፣ ሕዝብ ድርጅት ጽ/ቤት እንደተቋቋመ መኢሶን፣ ሊግ እና ኢጭአት በዚያው ሕዝብ ድርጅት ጽ/ቤት ውስጥ አንድ “ኮከስ”/ የሥራ ቡድን/ የጋራ ቡድን አቋቁመው በህብረት ለመስራት ጀመሩ። የሕዝብ ድርጅት ጽ/ቤትና የፖለቲካ ት/ቤትን በመምራትና ….ወዘተ አያሌ ሥራዎችን ይሰሩ የነበሩትም በዚህ የጋራ የሥራ ቡድን /“ኮከስ”/ በተሰኘው የጋራ መድረክ አማካይነት ነበር። ማሌሪድና አብዮታዊ ሰደድ በዚያ ሰዓት አልተመሠረቱም ነበር።
ይሁንና፣ ማሌሪድ ከተቋቋመ ከጥቂት ወራት በኋላ፣ የማሌሪድ አባሎች በሕዝብ ድርጅት ጽ/ቤትና በፖለቲካ ት/ቤት እንዲሳተፉ ሆነ። በቢሮክራሲውም ውስጥ እንደዚሁ። ከዚያም በኋላ፣ በመኢሶንና በማሌሪድ መካከል “ህብረት” ተፈጠረ። እነርሱም “እውነት” የተሰኘውን ጋዜጣ በጋራ ማውጣት ጀምረው ነበር። አልፈውም፣ በአስቸኳይ ወደ ውህደት ለመሻገር አንዳንድ የጋራ ተግባራዊ ኮሚቴዎችን እስከማቋቋም ደርሰውም ነበር። ሆኖም፣ ይሄኛው ክፍል ገና ከመጀመሩ፣ በተፈጠሩት መሰረታዊ የአቋም እና የአሠራር ልዩነቶች የመኢሶን- የማሌሪድ “ህብረት” በጥቂት ወራት ውስጥ አከተመ።
በዚህ ጊዜ ውስጥ ሀምሌ/ነሐሴ 1968 ዓ.ም ጀምሮ መኢሶን ሰፊ ህብረትን ለመመስረት በአንድ በኩል ከወዝ ሊግ፣ በሌላ በኩል ከኢጭአት ጋር አያሌ የሁለት ወገን /ባይላተራል/ ውይይቶችን ያካሄድ ነበር። በወቅቱ የማሌሪድ አቋም “እናንተ /መኢሶን/ ተወያዩና በተስማማችሁበት እንስማማለን” የሚል ነበር። አብዮታዊ ሰደድን በሚመለከተው፣ ይህ ድርጅት ምንም እንኳን ከሐምሌ/ ነሃሴ 1968 ዓ. ም ጀምሮ መቋቋም ቢጀምርም፣ ከርሱ ጋር የነበረው ግንኙነት በደርግ ደረጃ እንጂ፣ በነፃ የፖለቲካ ድርጅት ደረጃ አልነበረም። ከአብዮታዊ ሰደድ ጋር እንደዚህ ዓይነቱ ግንኙነት የተጀመረው በጥር 1969 ነው። ይህም ቢሆን፣ በየጊዜው በአብዮታዊ ሰደድና በደርግ መካከል ያለውን
አንድነትና ልዩነት ለይቶ ማስቀመጡ አስቸጋሪ እንደሆነ ነበር። ስለዚህም፣ በህብረቱ ጥያቄ ላይ ለከፍተኛ ችግሮች ተደንቅረው እንደቆዩ ለመረዳት አስቸጋሪ አይመስለንም። መኢሶንም አንድነታቸውንና ልዩነታቸው እንዲገለጽለት በተደጋጋሚ ላቀረባቸው ጥያቄዎች መልስ ሳያገኝ ቀርቷል። ከደርግ ጋር “ሂሳዊ ድጋፍ”፣ ከአብዮታዊ ሰደድ /ደርግ/ ጋር “ህብረት” የቱን ያህል አስቸጋሪ እንደሆነ መረዳቱ ቀላል ይመስለናል።
እንደሚታወሰው ጥር 1969 በደርጉ ውስጥ በነበሩት የኢህአፓ የውስጥ አርበኞች ጭምር አብዮታችን ተወጥሮ የተያዘበት ጊዜ ነበር። ይህንን ሁኔታ ተራማጆችም በትክክል ተገንዝበውት ነበርና፣ በዚህ ጊዜ ውስጥ በጋራ ተሰልፎ ከመዋደቅ በስተቀር ሌላ አማራጭ እንደሌላቸው በመረዳት የተራማጆችን ህብረት ወደ መመስረት አመሩ። ስለዚህም ከእያንዳንዱ ድርጅት ሁለት ሁለት አባሎች የተወከሉበት የህብረት ስብሰባ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥር 24/1969 ዓ.ም በብሔራዊ ሸንጎ ውስጥ ይደረጋል።
ይህ በራሱ አንድ ትልቅ እርምጃ ወደፊት ነበር። ወቅቱን በትክክል ብናስተውል፣ በጥር 22 በአብዮት አደባባይ ቁጣ የተመላበት የሰፊው ሕዝብ አብዮታዊ ሰልፍ ከተደረገ ሁለት ቀኖች በኋላና፣ እነዓለማየሁ/ ሞገስ ከመወገዳቸው ሁለት ቀናት በፊት ነው። ጥር 26 1969 በነዓለማየሁ/ ሞገስ ፈጣንና አብዮታዊ እርምጃ ሲወሰድ፣ አብዮታችን ባጠቃላይ “ከተከላካይነት ወደ አጥቂነት” ተሸጋገረ። በእውነትም፣ ተራማጆችን ከረጅም ጊዜ ሰንክሎ ያሰራቸው የውስጥ አርበኞች ሴራ ተበጣጠሰ። ከዚህ ጊዜ በኋላም፣ የህብረቱ መመስረት በሙሉ ኃይሉና ችሎታው ይጣደፋል።
ነገር ግን ህብረቱ፣ እውነተኛ ህብረት ሊሆን የሚችለው በተለይ አብዮታዊ ሰደድ /“ደርግ”/ ዲሞክራሲያዊ ሲሆንና የዲሞክራሲ መብቶችን ሲያውቅና ሲያከብር ብቻ እንደሆነ እጅግ ግልጽ ነበር። ምክንያቱም፣ ህብረቱ በአንድ በኩል በፖለቲካ ስፍራና በማቴሪያላዊ ኃይል ተመጣጣኝነቱ በሌላቸው የፖለቲካ ድርጅቶች መካከል የተመሰረተ ነበር። በሌላ በኩል፣ እኩልነታቸው ሊረጋገጥ የሚችለው በዲሞክራሲ ብቻ ነበር። በየካቲቱ የጋራ መግለጫ ላይ፡- “ባስቸኳይ ዲሞክራሲያዊ መብቶች ለጭቁኖች ያለ ገደብ መታወጅ አለባቸው” በማለት “በስውር ታፍነው ስለሚሰሩት ተራማጅ ድርጅቶች” ጭምር የተገለጸው ስለዚህም ነበር። መኢሶንም፣ በተደጋጋሚ “የዲሞክራሲ መብቶች ለጭቁኖች ያለ ገደብ አሁኑኑ ይታወቁ” እያለ የጨቀጨቀው አንድም በዚህ ምክንያት የተነሳ ነው። የድርጅቶቹ እኩልነት ሊጠበቅ እና ሊከበር የሚችለው፣ በሆነ የፖለቲካ ስፍራና ኃይል፣ ወይ ደግሞ በዲሞክራሲ እንደሆነ መረዳቱ ቀላል ይመስለናል።
ወደ ርእሳችን እንመለስና፡-
የመጀመሪያው ወቅት አይነተኛ የሚሆነው ባንድ ወገን ህብረቱን ለመመስረት በሚደረገው ጥድፊያና፣ በሌላው ወገን የአብዮቱን ወደ አጥቂነት መሸጋገር እውነት ለማድረግ ወዝአደሮች፣ በቀበሌ ተመራጮችና በአብዮታዊ ወጣቶች ይወሰዱ የነበሩት ነጻ ሕዝባዊ እርምጃዎች ነበር። ይህ ወቅት በተጨማሪ አብዮታችን ከብቸኝነት መውጣት የጀመረበትና የአንዳንድ የውጭ አገሮች ድጋፍ ማግኘት የጀመረበት ወቅት በመሆኑም አይነተኛ ይሆናል።
የመጨረሻዎቹን ሁለቱን በሚመለከተው፣ በአንድ ወገን በየፋብሪካው፣ በየትምህርት ቤቶችና ቀበሌዎች የሚካሄዱት ሕዝባዊ ነጻ ርምጃዎች አንስቶ እስከ መጋቢት 1969 “የመንጠር ዘመቻ” ድረስ የነበሩት እንቅስቃሴዎች የሚታወሱ ናቸው። በሌላ በኩል ከፊደል ካስትሮ/ ላምበርትስና ሌሎችም መሪዎች አንስቶ ይጎርፉ የነበሩት የውጭ ሀገር መልእክተኞችና የባህል ተጫዋቾች ሁሉ ይታወሳሉ። ይህ የመጨረሻው በራሱ ራሱን የቻለ ታሪክ ነው።…
ህብረቱን በሚመለከተው በኩል፣ ከጥር 24 እስከ የካቲት 18/69 ድረስ በተደረጉት ስምንት ስብሰባዎች ብቻ የህብረቱ “የጋራ መግለጫና መርሀግብር” ፀድቀው ይወጣሉ የህብረቱ ኮሚቴ በስንት የኃላፊነት ሥራዎች መካከል በ24 ቀኖች ውስጥ ብቻ ይገባደደው ሥራ እጅግ የሚያኩራና የሚያስደስት ነበር። በየካቲት ወር የህብረቱ “የጋራ መግለጫ እና መርሃ ግብር” ሲወጡ እነዚሁኑ እንደ ታላቅ ድል ያልቆጠራቸው አንድም ሀቀኛ ተራማጅ አንድም የአብዮቱ ወገን አልነበረም። በዚያን ጊዜ በሕብረቱ አባሎች መካከል “እውነተኛ ልዩነት” ቢኖር በብሄረሰቦች ጥያቄ ላይ ነበር። በገሃድም የተነገረው በዚህ ጥያቄ ላይ ስላሉት ልዩነት ብቻ ነበር። መኢሶን በሚመለከተው በኩል፣ በነዚያ ውይይቶች ላይ በተለይ በዲሞክራሲ መብቶች ጥያቄ ላይ ቀደም ስንል ከጠቀስነው ስምምነት ላይ በመድረሱ ከፍተኛ መርካት ሰፍኖ ነበር። ይሁንና፣ በደርግ እና በአብዮታዊ ሰደድ /“ደርግ”/ መካከል ያለው ልዩ ሁኔታ አሁንም አሳሳቢ ሆኖ ቀርቶ ነበር። ወደኋላም እንደታየው፣ ለምሳሌ አንድ ነገር ደርሶ ወደ ደርግ ሲኬድ ይህ የአብዮታዊ ሰደድና የህብረቱ ጉዳይ ነው” ይባል ነበር። ወደ እነርሱ ስኬድ ደግሞ “ይህ የደርጉ ጉዳይ ነው” ይባል ነበር።
የመጀመሪያው ወቅት፣ አያሌ የህብረት ግንኙነቶችና ሥራዎች የተከናወኑበት ወቅት ነበር። ለዚህ ምንም ጥርጥር የለውም። ነገር ግን በዚህ ወቅት ውስጥ ህብረት የነበረውን ያህል፣ ጸረ ህብረት ሥራዎችም እያቆጠቆጡ መታየት ጀመረው ነበር። አንዳንድ ምልክቶች መታየት እንደጀመሩም፣ መኢሶን ለመጀመሪያው ትዕግስትና ትህትና በተመላባቸው አቋሞች ድምጹን ያሰማል። በጥር እና የካቲት ወሮች በልሳኖቹ ላይ የሚከተለውን ጽፎ ነበር፡-
ሰህድ 50/ ጥር 30.1969
ይህ እትም፣ የመኢሶንን ታሪክ በአጭሩ ለማሳወቅ የተደረሰ ነበር። ጽሁፉ በወቅቱ እንዳመለከተው፣ “የዚህ ዓይነት ትንተና አሁን ባለንበት ወቅት /ጥር 69/ አስፈላጊ የሆነበት አንደኛው ምክንያት” እንደሚከተለው ተገልጾ ነበር።
“ከማርክሲስት ሌኒኒስት ድርጅቶች ጋር በመጀመሪያ ደረጃ ህብረትን፣ ከዚያም ውህደትን በመፍጠር፣ የወዛደሩን ፓርቲ ለመመስረትና ለመገንባት ጽኑ ፍላጎት አለን። እነዚህ የህብረት ጓዶቻችንን የመኢሶንን አጭር ታሪክ ቢያውቁ፣ የበለጠ መግባባትን እና መቀራረብን እንደሚፈጥሩ እናምናለን የዚህ ዓይነቱ እውቀት አጉል ጥርጣሬንና አለመተማመንን ሊያስወግድ ይችላል” /2/
ሰሕድ 52 /የካቲት 20. 1969
“የተራማጆችን ህብረት መፍጠር ሁሉ ሰው በቃል ቢደግፈውም፣ በገቢር ግን ባሁኑም ወቅት እንኳ፣ ብዙ ፀረ ህብረት ሥራዎች ይካሄዳሉ። የኢትዮጵያ አብዮት አሁን ባለበት ሁኔታ፣ መኢሶን የሚያቀርበው ሃሳብ ዲሞክራሲያዊና ሃቀኛ ውይይት፣ ሽኩቻን፣ አሉባልታንና የስም ማጥፋት ዘመቻን እንዲተኩ ነው። የእነዚህኞቹ መቀጠልና የህብረትን የመቀራረብ አዝማሚያዎች ማደናቀፍ፣ ፍጹም አብዮታዊ ኃላፊነትን መዘንጋት ይሆናል።”
እነዚህ ቃላቶች በወቅቱ ያለ ምክንያት የተጻፉ አልነበሩም። በዚያ ሰዓት በመኢሶን ላይ የሆኑ ያልሆኑ የማጥላላት ዘመቻዎች ተጀምረው ነበር። የሆኑ ያልሆኑ ቅጽሎች /“ጠባብ ቡድን”፣ “ጠባብ ብሄረተኛ”/ ይለጠፉበት ነበር። አያሌ የፈጠራ ክሶች አናት ባናት ይተረተሩ ነበር።…..ወዘተ።
ደግሞ፣ የነዚህ ሁሉ ፀረ ህብረት ፈጣሪዎች ሌሎች ሳይሆኑ፣ አንዳንድ የህብረቱ አባል ድርጅቶችና ግለሰቦች ጭምር ነበሩ። ዛሬ እነዚህ ክፍሎች “መኢሶን በአሉባልታ ይደናገጣል። አድሃሪዎች ባወሩና ጥሩንባቸውን በነፉ ቁጥር የንዑስ ከበርቴው ወኔ የክዳዋል” …ወዘተ በማለት እንደተመለሱብን ስንሰማቸው፣ “ጅራፍ ራሱ ገርፎ ራሱ ይጮሃል” ከማለት በስተቀር የምንመልሰላቸው ተጨማሪ ነገር አይኖረንም።
የሆነው ሆኖ፣ ሽኩቻውና አሉባልታው፣ የፈጠራ ክሶችና የስም ማጥፋት ዘመቻ በመጋቢት ወር እየባሰ ይመጣል። ከእነዚህ ፀረ ህብረት ዘመቻዎች መብዛትና መባዛት የተነሳ፣ ሊቀመንበር መንግሥቱ ኃይለማርያም በመጋቢት ወር ላይ አራት የመኢሶን አባሎች ቢሮአቸው ድርስ ጠርተው ለሁለት ሰዓት ያህል ያነጋግሯቸዋል። የታሪክ ምፀት መስሎ ቢታይም፣ በዚያን ጊዜ በቤተመንግሥት ውስጥ “በአሉባልታዎችና በፈጠራ ክሶች ላይ” ውይይት ሲካሄድ፣ በዚያኑ ሰዓትና ደቂቃ ደግሞ በአዲስ አበባ በከተማ ውስጥ “የመንጥር ዘመቻ” እየተካሄደ ነበር። በሁለቱ ሁኔታዎች /“ህብረትና” ፀረ ህብረት/ መካከል የነበረው ቅራኔ እስከዚህ ድረስ አፍጥጦና አግጥጦ ነበር ለማለት እንችላለን።
ለማንኛውም በውይይቱ ወቅት መኢሶን ለሚነዙበት አሉባልታ የፈጠራ ክሶች አንድ በአንድ ማብራሪያዎችና መልሶችን ይሰጣል። “ገለልተኛ ዳኛን” ይጠይቃል። በተጨማሪ፣ እንደዚህ ዓይነት ውይይት ከሌሎችም ድርጅቶች ጋር ተራ በተራ እንዲደረግ ሃሳብ ያቀርባል። ዲሞክራሲያዊና ሀቀኛ የሆነን የተራማጆች ህብረት በጋራ ለመመስረት ጽኑ ፍላጎት እንዳለው ደጋግሞ ያሳውቃል።…
የተባለው ዓይነት ውይይት ከሌሎች የህብረቱ አባል ድርጅቶች ጋር ተረ በተራ ተካሂዶ እንደሁ፣ መኢሶን የሚያውቀው ነገር የለም። መኢሶን የሚያውቀው ነገር ቢኖር፣ በተፈጠሩት ጥርጣሬዎችንና እንቅፋቶች ምክንያት ብቻ፣ የህብረቱ ስብሰባዎች ሙሉ በሙሉ መቀዝቀዛቸውንና መቋረጣቸውን ነው።
ከየካቲት 18 እስከ ግንቦት 10/1969 የተደረጉ የህብረቱ ስብሰባዎች ሁለት ብቻ መሆናቸውን ነው። ሁኔታዎችን ለማመዛዘን እንዲረዳን፣ በመጀመሪያው ላይ በአማካይ ቁጥር በየሦስት ቀን አንድ ስብሰባ ሲደረግ ሁለተኛው ስብሰባ የተካሄደው በ35 ቀኖች ውስጥ አንድ ጊዜ ብቻ ነበር ማለት ነው። በዚህ ጊዜ ውስጥ ገና ከህብረቱ የመጀመሪያ ቀኖች ተረቅቆ የነበረው የህብረቱ የመተዳደሪያ ደንብ የቀኖችን ብርሃን ለማየት እድል ሳያገኝ ቀርቶ፣ የጠረጴዛ መሳቢያዎችን ሲያሞቅ ከርሟል። በምትኩ ተፋፍሞ የነበረው በመኢሶን ላይ ይደረግ የነበረው ዘመቻ ነበር። ስለሆነም፣ በመጋቢት ወር እትሙ፣ መኢሶን የሚከተለውን እንዲፅፍ ተገደደ።
ሰሕድ 53- መጋቢት 15/69
“….. እነዓለማየሁ ኃይሌ ከሰኔ 68 ጀምሮ ጽ/ቤቱ ላይና በተለየም ደግሞ በድርጅታችን ላይ ሀይለኛ ዘመቻን በይፋ ሲያካሂዱ እንደቆዩ፣ ጽ/ቤቱ የመኢሶን ጽ/ቤት ነው በማለት እንዲፈርስ መጠየቃቸው እና በመጨረሻ ይህንኑ የማፍረስ ዓላማቸውን በጉልበት ከሥራ ላይ ለመዋል እንደሞከሩ ይታወቃል።
“አሁን በጥር 26 በደርጉ ውስጥ የነበሩት የኢሕአፓና የኢምፔሪያሊዝም ወኪሎች ከተደመሰሱ በኋላ፣ በጽ/ቤቱና በእርሱም ሳቢያ በመኢሶን ላይ የሚደረገው ዘመቻ በተፋፋመ ሁኔታ ቀጥሏል። የዚህ ዘመቻ ዋነኛ ኃላፊዎች በየቦታው የተቀመጡት አድሃሪ ቢሮክራቶች ናቸው። በሲዳሞ፣ በከፋ፣ በሌሎችም ክፍላተ ሀገር ቢሮክራሲ ጽ/ቤቱን በሚመለከተው በኩል ‘ከተከላካይነት ወደ አጥቂነት ተሸጋገሮ’ ካድሬዎችን እስከ ማስገደልና እስከማሰር ደርሷል።”
እንደዚህ ያለው ዘመቻ በመኢሶን ላይ በሚያዚያ፣ ግንቦት፣ ሰኔ፣ ሐምሌና ነሐሴ ወሮች ውስጥ ተስፋፍቶ እንደቀጠለ ነበር። በእነዚህ ወሮች ውስጥ መኢሶን ያሰማቸው ጥያቄዎች ጫጫታ ብቻ እንጂ፣ አንዲትም ፍሬ ሊሰጡ ሳይችሉ ቀርተዋል። በዚህ ጊዜ ውስጥ ባንድ በኩል እንደዚህ ያለው ዘመቻ እየተካሄደ፣ በሌላው በኩል ደግሞ፣ አንዳንድ የህብረቱ አባል ድርጅቶችና ግለሰቦች ጭምር በመኢሶን ላይ ግልጽ እና ኃይለኛ ዘመቻ ይከፍታሉ። በተለይ ከሚያዚያ ወር የሜይ ዴይ በዓል በኋላ፣ ጸረ መኢሶን ዘመቻ ተፋፍሞ ይቀጥላል።
በሚያዚያ ወር በተደረገ አንድ የህብረት ስብሰባ ላይ፣ “በሜይዴይ ዕለት፣ እያንዳንዱ ድርጅት የራሱን አርማ፣ የህብረቱን ድርጅቶች አርማዎችና መፈክሮች ይዞ እንዲወጣ” ከስምምነት ላይ ይደረሳል። መኢሶን ስምምነቱን አክብሮ ይሰራል። በዚሁ መሰረት በአዲስ አበባና በክፍላተ ሃገር ከፍተኛ ዝግጅቶችን ያደርጋል።….ወዘተ
ይሁንና፣ ዕለቱ ከመድረሱ ሁለት ቀኖች በፊት “ተስማምተናል፤ አልተስማማንም” የሚል “የእምነት ክህደት” ክርክሮች ይነሳሉ። በመጨረሻም፣ በዓሉ እንደ ነገ ሊሆን እንደ ዛሬ መኢሶን ዝግጅቱን እንዲያቆም ትዕዛዝ ይደርሰዋል። መኢሶነም በዚህ ጊዜ፣ ትእዛዙ እጅግ ዘግይቶ እንደመጣ በማስታወቅ፣ ምንም ለማድረግ እንደማይችል ያስታውቃል። ትእዛዙን በሥራ ለመተርጎም በቂ ጊዜ እንደሌለው ያስረዳል። ሜይ ዴይ 1969 በተከበረበት መልክ ተከብሮ ይውላል።
ነገር ግን ያ ዕለት ደማቅ የነበረውን ያህል፣ ብዙ ድክመቶችም ነበሩበት። መኢሶንም በወቅቱ አድርጎት በነበረው ግምገማ፣ ከዚህ በታች የምንጠቅሰውን ጽፎ ነበር። ይሁንና፣ ከዚያ በፊት ደግሞ፣ በጊዜው ባንዳንድ አካባቢ የነበረው ስሜታዊነት፣ ከዚህ በታች የምንጠቅሰውን አጠቃላይ ግምገማ በጥሞና ከመመልከትም አግዶ እንደነበረም ሳናስታውስ አናልፍም። እስቲ የመኢሶንን ግምገማና አቋም እንደገና አስታውሰን እንመለከተው፡-
ሰሕድ 54- ሚያዚያ 30/69
“የዘንድሮውን /1969/ ሰልፍ ብንመለከት፣ ከተያዙት መፈክሮች ምናልባት እስከ 80 በመቶው የፖለቲካ መፈክሮች ነበሩ። ‘አብዮታዊት እናት አገር ወይም ሞት!’ ‘የተራማጆች ህብረት ይለምልም’፣ ‘ሃቀኛ የወዛደር ፓርቲ እንመሥረት’፣ ‘ዲሞክራሲያዊ መብቶች ለጭቁኖች ያለገደብ’፣ ‘ዲሞክራሲያዊ መብቶች አሁኑኑ’፣ ‘የመንጥር ዘመቻ ይቀጥል’፣ ‘ለአብዮታዊው የዘመቻ ጥሪ ተዘጋጅተናል’….. የሚሉት በብዛት የወጡ መፈክሮች ነበሩ። ሁሉም የኢትዮጵያን አብዮት አንገብጋቢ ጥያቄዎች የሚያነሱ ናቸው።
መፈክሮችን በሚመለከተው በኩል የሚያበረታታና ተስፋ የሚሰጡ ሁኔታ ሲታይ፣ የሰልፉን ዝግጅት በሚመለከተው በኩል ደግሞ በርከት ያሉ ድክመቶች ታይተዋል። ባጠቃላይ፣ ሰልፉ የዲስፕሊን ጉድለትን አሳይቷል። ለምሳሌ ብዙ ድርጅቶች የራሳቸውን የሥነ ሥርዓት ጠባቂ አላሰለፉም ነበር። በርከት ያሉ ቦዘኔዎች በየድርጅቱ መካከል ከመግባታቸውም በላይ፣ቅጥየለሽ አሰላለፍ፣ ብዙ ድንፋታና ሁካታን አልፎ አልፎ አሳይተዋል።
እነዚህ የዝግጅትና የዲሲፕሊን ጉድለቶች ሲሆኑ፣ በተለይም መኢሶንን በሚመለከተው በኩል፣ አንዳንድ የድርጅታችን ደጋፊዎች የፖለቲካ ስህተቶችን ፈጽመዋል።
‘መኢሶን ፓርቲያችን ነው’ ‘መኢሶን አስታጥቆናል’ የሚሉ የቃል መፈክሮች ተደጋግመው ተሰምተዋል። እነዚህም መፈክሮች ያሰሙ የነበሩት ግለሰቦች የመኢሶን ደጋፊ ሆነው የተሳሳቱና የድርጅታችን የፖለቲካ መስመር በቅጡ ያልተገነዘቡ ጓዶች ናቸው። አለበለዚያም፣ በአሉባልታ አካባቢ በሚደረገው ትግል ላይ ብቻ ስላተኮሩ፣ ለጊዜው በስሜት ብቻ በመገፋፋት የተሳሳቱ ጓዶች ናቸው። መኢሶን ፓርቲም አይደለም። ይህንን በፕሮግራሙ ውስጥ ጭምር ገልጾ፣ በተደጋጋሚም በጽሁፎቹ ውስጥ ከሌሎች ሃቀኛ ተራማጆች ጋር ህብረትንና ከዚያም ውህደትን አድርጎ የወዛደሩን ፓርቲ አብሮ ለመፍጠር እንደሚታገል ገልጿል። ትጥቅን በሚመለከተው በኩል፣ መኢሶን ከሌሎች ሀቀኛ ተራማጆች ጎን በመሰለፍ ፣ሰፊው ሕዝብ እንዲነቃ፣ እንዲደራጅ እንዲታጠቅ ታግሏል። ሰፊውን ሕዝብ ያስታጠቀውና በማስታጠቅ ላይም የሚገኘው ግን ጊ.ወ.አ ደርግ መሆኑ የታወቀ ነው።
የእሁዱን ሰልፍ ዓይነተኛ ከሚያደርጉት ነገሮች አንዱ፣ የተራማጆች ህብረት አባል ድርጅቶች፣ ማለትም የመኢሶን፣ የማሌሪድ፣ የኢጭአት፣ የወዛደር ሊግና የአብዮታዊ ሰደድ አርማዎች በይፋ መውጣታቸውና ወዛደሩም ለህብረት የቁመ መሆኑን ማሳየቱ ነው። እንደዚሁም፣ ካምናው ይልቅ ዘንድሮ፣ የመኢሶን-የማሌርድ አርማዎችና መፈክሮች በርከት ብለው በመታየታቸው ባንዳንድ የህብረት ጓዶቻችን ዘንድ ቅሬታ እንደተፈጠረ ሲሰማ፣ በሌላ በኩል ደግሞ በአንዳንድ የመኢሶንና የማሌሪድ ጓዶች ዘንድ፣ በወዛደር ውስጥ የሰፈነውን ድርጅታዊ ሥራ የማጋነን አዝማሚያ ይታያል።
ለጓዶቻችን ሁሉ የምንነግረው ነገር ቢኖር፣ የሰልፉ አንድ ጎን ብቻ ከማየት፣ ጠቅላላውን እንዲመለከቱት ነው። ከተሰለፉት 150 ወይም 200 ሺህ ወዛደሮች ውስጥ፣ የማንንም ይሁን የማንን ዓርማ ይዘው የወጡት ምናልባት 15 ወይም 20 በመቶ ያህሉ ብቻ ናቸው!! ይህም እንግዲህ ሀቀኛ ተራማጆች ገና ከወዛደሩ ጋር በሚገባ አለመዋሃዳቸውን ስለሚያሳይ፣ ለወደፊቱ፣ የኢትዮጵያ አብዮታዊያን የሚጠብቃቸው ተግባር በጣም ከፍተኛ ነው ማለት ነው። ነገሮችን ከሁሉም ማዕዘን ሳይሆን ከአንድ ጎን ብቻ፣ የወደፊት እድገታቸውን ሳንጨምር የዛሬውን ብቻ ከተመለከትን እንሳሳታለን።
ድርጅታችንን በሚመለከተው በኩል፣ መኢሶን ለተራማጆች ህብረት መጠንከር፣ የዲሞክራሲያዊ መብቶች፣ ለወዛደሩ ፓርቲና ለአብዮታዊ ግንባር መፈጠር እስከመጨረሻው ድረስ ይታገላል።”
መኢሶን ይህን ሁሉ ቢናገርም፣ አቋሙን በግልጽ ቢያሳውቅም፣ ስህተቶችን ለማስረዳት ቢጥርም፣… ወዘተ፣ እንዳልነው በጊዜው የነበረው ስሜታዊነት ነገሮችን በአንክሮ ከመመልከት አገደ። ይልቁኑ በመኢሶን ላይ የሚደረጉት ዘመቻዎች ተፋፈመው ነጎዱ። አንዳንዶቹ “ለመኢሶን ጠባብ ቡድንነት” ከዚህም የበለጠ ማስረጃ እንደሌለ ያሳወቁ ጀመር። ሌሎቹ መኢሶንን “አዲሱ ኢህአፓ” አድርገው ሳሉት። ሌሎችም “የመኢሶንን የስልጣን ጥም” አነበቡ። ስምምነቱ ተረሣ። በጭፍን ተካደ። በምትኩ፣ ጥርጣሬዎች አለመተማመን ሰፈሮችን ሁሉ አዳረሱ። በተጨማሪ፣ በተለይም በመጀመሪያው ላይ፣ በክፍላተ ሀገር ውስጥ ካድሬዎችንና ደጋፊዎችን ማሳደድና ማሰር ተፋፍሞ ቀጠለ። በሕዝብ ድርጅት ፅ/ቤት ሳቢያ በመኢሶን ላይ የሚደረገው ዘመቻ በራፖር ክሶች የደርግ ጽ/ትን ቢሮ አጥለቀለቀው። በወዛደሩ አካባቢ /በአቃቂና በወንጂ…/ ከፍተኛ ሽኩቻ ተቀሰቀሰ። መኢሶንን ለመክሰስ “መረጃዎች ይቃረሙ ጀመር። ስለላው ጦፈ።….ወዘተ።
በግንቦት ወር የህብረቱ ስብሰባ እንደገና ሲቀጥል፣ ሁኔታዎች ከዚህ በላይ እንደገለጽነው በአያሌ ፀረ ሕብረት ሥራዎች ተጨመላልቀው ነበር።
የህብረቱን ጉዳይ በሚመለከተው በኩል፣ የግንቦት ወር በአንድ ወገን በጥቂት ቀኖች ውስጥ እንደገና አያሌ የህብረት ሰብሰባዎችን ያየ ሲሆን፤ በሌላው ወገን በአያሌ የፖለቲካ ጥያቄዎች ላይ ከፍተኛ የአቋም ልዩነቶች ገሃድ የወጡበት ጊዜም ነበር። ቀደም ሲል በአሉባልታዎችና በፈጠራ ክሶች የተፈጠሩት አለመተማመንና እርስ በርስ መጠራጠር ከከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሱበት ወቅት ነበር።
ከግንቦት 10 እስከ 30 ባሉት ጊዜዎች ውስጥ ብቻ 13 ሰብሰባዎች ይካሄዳሉ። ይህኛው በአማካይ ቁጥር በአንድ ቀን ተኩል አንድ ስብሰባ ማለት ነበር። ስብሰባው በተጨማሪ ወኪሎች /ከእያንዳንዱ ድርጅት አሁንም ሁለት ሁለት ተጨማሪ ወኪሎች ታክለው/ የተካሄደ ነበር። ከእንግዲህም ቃለ ጉባኤዎችን በደንብ መያዝ ተጀምሮ ነበር።….
ይሁንና ደግሞ፣ እነዚህ ስብሰባዎች የዋሉት አስከዚህም ድረስ ለአዲስ ነገር ሳይሆን፣ በሰሕድ ቁ.60 እንደተገለጸው፣ “በየካቲቱ የጋራ መግለጫ ውስጥ በጸደቁ የውይይት እና የስምምነት ነጥቦች ላይ እንደገና “ለመከራከር” ነበር።
ነገር ግን ስብሰባዎቹ እርስ በርስ ባለመተማመን አየር የታመቁ ነበሩ። በመኢሶን ላይ የሚደረጉት ዘመቻዎች ሁሉ እንደ እውነት ተወስደው ለፍርድ የቀረቡባቸው ስብሰባዎች ነበሩ። መኢሶን፣ እንደሚባለው “በመሃላና ግዝት” ጭምር፣ አቋሙን ደጋግሞ ቢገልጽም፣ ጥርጣሬዎች ለመወገድ ያልቻሉበት ስብሰባዎች ነበሩ።
የዚያኑ ያህል ደግሞ፣ የግንቦት ወር ስብሰባዎች፣ የድርጅቶች አሰላለፍና የፖለቲካ አቋም ለውጦች በገሃድ የተከሰቱባቸው ስብሰባዎች ነበሩ። በዚህም አንጻርም፣ ወዘ ሊግ፣ ማሌሪድና አብዮታዊ ሰደድ በአንድ ወገን ተሰልፈው ነበር። ኢጭአትና መኢሶን ደግሞ በሌላው ወገን ሆነው ነበር። ደግሞ ከሁሉም ድርጅቶች ይልቅ፣ ማሌሪድ አስደናቂ የሆኑ የአቋም ለውጦች ያሳየባቸው ስብሰባዎች ነበሩ። እንደእውነቱ ከሆነ፣ በነዚያ ስብሰባዎች ላይ የማሌሪድ አቋም ለውጦች ለሁሉም ድርጅቶች እጅግ ፈጣን ከመሆናቸው የተነሳ፣ ሁሉም ቢሆኑ ለማመንም፣ ለመከተልም ተቸግረው ነበር ብንል ፈፅሞ ስህተት አይሆንም። የማሌሪድ መሪዎች ከኢሕአፓ ዘመናቸው አንስቶ ያደረጉት ጉዞ በራሱ እንደዚሁ አስደናቂ ነው። የነዚያ ስብሰባዎች ቃለገባኤ በሁሉም ድርጅቶች ዘንድ ለታሪክ ተቀምጧል። ሁኔታዎች ሲጠይቁ የቀኖችን ብርሃን ማየቱ አይቀርም።
ለማንኛውም፣ ሰህድ ቁጥር 60 እንዳለው “በየካቲት የጋራ መግለጫ ውስጥ የፀደቁት የውይይት እና የስምምነት ነጥቦች እንደገና ለውይይት እስከመቅረብ የደረሱት”
“በነዚህ ነጥቦች ላይ እያንዳንዱ ድርጅት አቋም ግልፅ ሳይሆን በመቅረቱ ቀርቶ ሳይሆን፣ በድርጅቶች መካከል የመጠራጠር መንፈስ ሊጠፋ ባለመቻሉ ነው። መአሶን በልዩ ልዩ እትሞቹ ደጋግሞ እንደገለፀው ሁሉ፣ ይህ ጥርጣሬ ሊጠፋ ያልቻለው፣ ህብረተሰባችን ገና ከፊውዳላዊው ሥርዓት ያስተሳሰብ ዘዴዎች ባለመላቀቁና ዲሞክራሲያዊ መብቶቹም ሆኑ ዲሞክራሲያዊ ያስተሳሰብና የአሰራር ዘዴዎች በፍፁም ያልተለመዱ በመሆናቸው ነው።”
እርግጥ፣ ዛሬ ደግሞ በተጨማሪ ደርግ/=አብዮታዊ ሰደድ/ የመኢሶን “የስልጣን ጥም” የሚለውን የአድሀሪዎች ቅስቀሳ እንደ እውነት በመውሰዱም ጭምር ነው ልንል እንችላለን።
በመሆኑም፣ መኢሶን የሚገልጻቸው የፖለቲካ አቋሞች ላይ ሁሉ ከፍተኛ ጥርጣሬዎች አደሩ። አሉባልታዎችና የፈጠራ ክሶች ሁሉ እንደ እውነት ተወሰዱ። በነገሮች ውስጥ ሁሉ “የመኢሶን የስልጣን ጥም” የሚባለው ነገር ለማንበብ ተሞከረ። መኢሶን የሚያቀርባቸው ጥያቄዎች ሁሉ “መኢሶን ለመስፋፋት፣ ለማበጥ፣ ለመፈንዳት፣ ሌሎቹን ለማዋጥ…” የሚያቀርባቸው ጥያቄዎችና ሀሳቦች ናቸው በሚል ተገመቱ። መተማመን ጠፋ። ውይይቶቹ አስቸጋሪ ሆነው ነበር።
የዚህ ሁሉ መሠረት ግን፣ መሰረታዊ በሆኑት የፖለቲካ ጥያቄዎች ላይ አቆጥቁጠው የመጡት የመስመር ልዩነቶች ነበሩ። ልዩነቶቹ በየካቲት ወር በብሄረሰቦች ጥያቄ ላይ “ብቻ” የነበሩትን ያህል፣ አሁን ደግሞ በዲሞክራሲ መብቶች፣ በቢሮክራሲው፣ በትጥቅ፣ በአብዮታዊ አመራር፣ በሕዝባዊ ነጻ እርምጃ፣ በራስን መቻል ጥያቄዎች ላይ ሁሉ አያሌ ልዩነቶች መታየት ጀመሩ። እንደሚታወሰው እነዚህ ሁሉ የአብዮቱ ጥያቄዎች፣ የአዲስ ዘመን ጋዜጣ አንድ ሰሞን /ህዳር 1970/ ለውይይት ጋብዞ በነበረበት ጊዜ፣ የውይይት አርዕስት እንዲሆኑ የተገለፁ ነበሩ።
ነገር ግን በጥያቄዎቹ ላይ ተጀምሮ የነበረው ውይይት ወዲያውኑ ታፈነ። ውይይት ተጀምሮበት የነበረው የዲሞክራሲ መብቶች ጥያቄ ላይ እንኳ፣ ወዲያውኑ ፀረ ዲሞክራሲያዊ ዕገዳ ተደረገበት። ቀደም ስንል ጠቅሰን እንዳመለከትነው፣ በተለይ በዚህ የዲሞክራሲ መብቶች ጥያቄ ላይ “መኢሶን በርዕዮተ ዓለም ትግል ተሸንፏል። ተጋልጧል። ሰፊው ሕዝብ አልተቀበለውም” በሚል የተበየነው ፍርድ ለመስማት የበቃ ነው ገና አሁን ነው።
ይሁንና፣ በተነሱት የአብዮቱ ጥያቄዎች ላይ ሁሉ አሁንም ቢሆን በሃቅ የሚያከራከሩ አያሌ ጉዳዮች ተሸፍነው እንዳሉ ናቸው። ስለዚህም፣ “አለባብሰው ቢያርሱ በአረም ይመለሱ” ነውና፣ የኢትዮጵያ ሕዝቦች በእነዚህ እና በሌሎችም ጥያቄዎች ላይ እንደ ሁኔታውና እንደ ጊዜው እየደጋገሙ መመለሳቸው አይቀርም። አብዮታዊ ትግል በሁለት መስመር ትግል እንደሚቀጥልም ፍጹም የሚያጠራጥር ጉዳይ አይደለም።
ወደ ርእሳችን እንመለስና፤ ግንቦት 69 የብዙ ስብሰባዎችን አያሌ ያቋም ለውጦች የታየበት ወቅት የሆነውን ያህል፣ መኢሶን ላይ የተፋመው ዘመቻ እጅግ የሞቀበት ወቅትም ነበር። ባንድ ቃል፣ “ህብረትና” ፀረ ህብረት አንድ አምሳል፣ አንድ አካል ሆነው የታዩበት ወቅት ነበር። ስለዚህም ነበር፣ መኢሶን በነበሩት ፀረ ህብረት እድገቶች ላይ በየእትሞቹ ላይ ደግሞ ደጋግሞ እንዲመለስባቸው የተገደደው። ይህንኑ ሀቅ፣ የልሳኑን ቁጥሮች አልፎ አልፎ በመጥቀስ ለማሳየት ይቻላል። እንመልከተው፡-
ሰሕድ 55 -ግንቦት 7/69
“የተራማጆችን ህብረት ለማጠናከርና አብዮታዊያን በይበልጥ ከሰፊው ሕዝብ ጋር እንዲዋሃዱ ለማድረግ፣ የወዛደሩን ፓርቲና ሕዝባዊ አብዮታዊ ግንባሩን በመፍጠር የኢትዮጵያን ሰፊ ሕዝብ ከዳር እስከ ዳር ለማንቀሳቀስ፣ ዲሞክራሲያዊ መብቶች እጅግ አስፈላጊ ስለሆኑ፤ እነዚህ መብቶች በፍጥነት ለሰፊው ሕዝብ መለቀቅ እንዳለባቸው መኢሶን ያምናል። በአሁኑ ወቅት በተራማጅ ድርጅቶች መካከል ኃይለኛ ሽኩቻና አለመግባባት የሚፈጠረው፣ ዲሞክራሲያዊ መብቶች ስለሌሉና እውነተኛ ልዩነት ነጥቦች እንዳሉ እነርሱን በይፋ አውጥቶ በሰፊው ሕዝብ ፊት ለክርክር ለማቅረብ ስላልተቻለ ነው። እነዚህ መብቶች በሌሉበት ሁኔታ፣ በድርጅቶች መካከል የሚካሄደው “ትግል”፣ በአሉባልታ፣ በሃሜት፣ በጥርጣሬና በስም ማጥፋት ዘመቻዎች ላይ የሚያተኩር ከመሆኑም በላይ፣ የዚያ ዓይነቱ “ትግል” ሰፊውን ሕዝብ በማስተማር ፈንታ ያወናብዳል፣ በመሰብሰብ ፈንታ ይከፋፍላል…..
“መኢሶን የሚፈልገው ሃቀኛ የተራማጆች ህብረትና ከዚያም እውነተኛ የወዛደሩ ፓርቲ እንዲፈጠር፣ ሕዝባዊ አብዮታዊ ግንባር ተመስርቶ ሰፊ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከዳር እስከዳር እንዲያንቀሳቀስና፣ ይህ ሕዝብ እንደአንድ ሰው ሆኖ ሦስቱ ጠላቶቹ ላይ እንዲነሳ ለማድረግ ነው።”
ሰሕድ 57- ሰኔ 7/69
“ድርጅታችን ከፕሮግራሙ ማውጣት በፊትም ሆነ በኋላ፣ በርከት ባሉ ጽሁፎች፣ ምናልባት ከማንኛውም ማሌ ድርጅት ይበልጥ፣ ደጋግሞ ስለወዛደሩ ፓርቲ አመሰራረት ጽፏል። ችግሩ በፊውዳላዊት ኢትዮጵያ፣ የክርክር መብትም ሆነ ልምድ ስላልነበረና ዛሬም ዲሞክራሲያዊ መብቶች ለሰፊው ሕዝብ ገና ስላልተለቀቁ፣ የሚደረግብን ዘመቻ በሃቅ እና ተጨባጭ ነገሮችን እያዩ በማመዛዘን፣ ለእውነት በመቆም ሳይሆን፣ ቀድሞ በነበረው የመደብ ትግል ስልት፣ በወሬ፣ በአሉባልታ፣ ከንቱ ጥርጣሬን በመንዛት ላይ የተመረኮዘ ሆኖብን ነው።
የኢትዮጵያ አብዮታዊያንና ሰፊውን ሕዝብ የምንለው፣ የእኛን ብቻ ሳይሆን የሁሉንም ድርጅቶች ጽሁፎች በሚገባ አንብቡ፣ የሁሉንም ድርጅቶች የቅስቀሳ ይዘት አጥኑ፣ በጽሁፍና በተግባር መካከል ያሉትንም ግንኙነቶች በሚገባ አስተውሉ ነው…..”
የሰሕድ እትሞችን ሁሉ እያገለበጥን ጥቅሶችን በማቅረብ መቀጠል እንችላለን። ይሁንና፣ ጽሁፉ አለቅጥ ይረዝምብናል። ስለዚህም፣ አንባቢዎችን በተለይም ወደ ሰሕድ 59 /4.11.69/ እና ሰህድ 60 /21.11.69/ ጋብዘናቸው ብቻ እዚህ ላይ እናቁም። ከዚህ በላይ ተጠቅሰው በተመለከቱት አንቀጾች ብቻ እንኳ፣ የመኢሶን ያልተቋረጠና ያልተናወፀ አቋም ግልፅ ሆነዋል ብለን እንገምታለን። ወደሚቀጥለው ክፍል እንሻገር።
እንደማንኛውም ድርጅት ሁሉ፣ የህብረቱም ድርጅት እንደተመሠረተ የመተዳደሪያ ደንብ እንደሚያስፈልገው የታወቀ ነው። ስለዚህም በየካቲት 69 የህብረቱ የጋራ መግለጫና መርሃግብር ከወጡ በኋላ፣ ወዲያውኑ የሚከተለው ተግባር፣ በተመሠረተው የህብረት ድርጅት መተዳደሪያ ደንብ ላይ ተወያይቶና ተስማምቶ መልክና ሥርዓት ማስያዝ ነበር። እንደ እውነቱም ከሆነ፣ ይህ ግልፅ የሆነ ተግባር ወዲያውኑ ተጀምሮም ነበር። በዚህ ወር ውስጥም፣ የህብረቱ የመተዳደሪያ ደንብ ረቂቅ ለውይይት ቀርቦ ነበር።
ሆኖም በመኢሶን ላይ በነበሩት ጥርጣሬዎች ምክንያት፣ ውይይቱ ለረዥም ጊዜ ታግዶ ቆየ። መኢሶን በመተዳደሪያው ደንብ ላይ፣ በአስቸኳይ ውይይት እንዲደረግ ደጋግሞ ቢወተውትም፣“አዎን ብቻ!!” በሚሉ መልሶች ነገሮች ሁሉ እንዲራዘሙ ተደረገ። እኛ እንደምናስታውሰው፣ የመተዳደሪያ ደንቡ ለውይይት ሊቀርብ የቻለው፣ የጋራ መግለጫው ከወጣ ከአምስት ወሮች በኋላ፣ በሐምሌ 1969 ነበር። በመጨረሻም፣ በዚህ ወር ውስጥ ይጸድቅና የቀኖችን ብርሃን ለማየት ይበቃል። ይሁንና፣ በዚህ ወቅት ደግሞ፣ ለወራት እየተጠራቀሙ በመጡት መራራቆች ምክንያት አዲስ ሁኔታ ተፈጥሮ ነበር። በዚህ ጥያቄ ላይ፣ “የትግል ስልት ለውጥ ለምን?” በሚለው የዚህ ጽሁፍ አምስተኛ ክፍል ውስጥ እንመለስበታለን። አሁን ለማመልከት የምንፈልገው ሦስት ፍሬ ነገሮችን ብቻ ነው።
አንደኛ፣ ቀደም ስንል እንዳልነው “ህብረቱ” እውነተኛ ህብረት ሊሆን የሚችለው፣ወይ ተባባሪዎቹ ድርጅቶች ተመጣጠኝ የሆነ የፖለቲካ ስፍራና ማቴሪያላዊ ኃይል ሲኖራቸው፣ ያለዚያም በተለይ የአብዮታዊ ሰደድ /=‘ደርግ’/ ፍጹም ዲሞክራሲያዊ ሲሆን ብቻ ነበር። እንደሚታወቀው፣ የመጀመሪያው ያልነበረውን ያህል፣ አብዮታዊ ሰደድም /=‘ደርግ’/ ዲሞክራሲያዊ መብቶችን ለማወቅ፣ ለመጠበቅ እና ለማክበር ዝግጁ አልሆነም። ይባስኑ ከህብረቱ አባል ድርጅቶች መካከል ማሌሪድ እና ወዝሊግ አቋማቸውን በ180 ዲግሪ ለወጡት፣ በየካቲት 69 የጋራ መግለጫ ላይ ስምምነት የተደረሰበት የዲሞክራሲ መብቶች ጥያቄም ተፋቀ።
ሁለተኛ፣ ከሐምሌ በፊት ለስድስት ወሮች የተካሄዱት ፀረ ህብረት ሥራዎች፣ መርሆዋዊ ህብረት እንደማይኖር የሚያረጋግጡ ነበሩ። ይህ ደግሞ፣ ወረቀት ላይ በሰፈረ የመተዳደሪያ ደንብ ብቻ መልክና ሥርዓት ሊኖረው እንደማይችል ግልጽ ሆኖ ነበር። በዚህ ወቅት መኢሶን ሰሕድ 60ን አውጥቶ ብዙ ቢጽፍም፣ ምክንያቶች ነበሩት።
ሦስተኛ፣ በስድስቱ ወሮቹ ውስጥ በተፈጠሩት አሰላለፎች እንደታየው፣ የ3 ለ 2 አሰላለፍ እንደዚሁ ለረጅም ጊዜ የማይፋቅ መሆኑም የዚያኑ ያህል ግልጽ ሆኖ ነበር። በደንቡም መሠረት ቢሆን፣ የአንድ አባል ድርጅት ዲሞክራሲያዊና ነጻ ህልውና የማይጠብቁና የማያከብሩ እንደሚሆን ቀደም ሲል የተከናወኑት አያሌ ድርጊቶች ሁሉ ግልጽ አድርገውት ነበር።
እነዚህ በወቅቱ መኢሶን በትክክል የተረዳቸው መሰረታዊ ጉዳዮች የቱን ያህል ትክክለኛ ግምገማዎች እንደሆኑ ለመረዳት ሩቅ መሄድ ያስፈልግም። እነሆ ዛሬ በገቢር ተረጋግጠው እናያቸዋለን። የኢጭአት ከህብረቱ መታገድ ጉልህ የሆነው የታሪክ ምስክር ነው። ስለ ዲሞክራሲያዊ መብቶች ጥያቄ ሰፊው ሕዝብ ብዙ ብዙ ለመናገር ይቻላል።
ስለዚህም ነው፤ መኢሶን በሐምሌ 69 እንዳለው ዛሬም ቢሆን ለሀቀኛ አብዮታዊያን ሁሉ እንደሚከተለው የሚለው፦ “ደንቡን በሚገባ እንዲያጠኑትና በትክክል እሥራ ላይ ማዋል አለመዋሉን እንዲከታተሉት” /ሰሕድ 60/
ከዚህ የተለየ ጥሪ የለንም። የዲሞክራሲያዊ ትግላችን ጥሪ፣ አንዱም ይህንን መሠረታዊ ጉዳይ የሚመለከት ነው። የድርጅቶች ዲሞክራሲያዊና ነፃ ህልውና እስካልተጠበቁ ድረስ፣ ስለዚህም በፖለቲካ ጥያቄዎች ላይ ዲሞክራሲያዊ፣ ነፃና ሀቀኛ ውይይቶችን ለማድረግ እስካልተቻለ ድረስ፣ የህብረቱ ድርጅት ጥንካሬና ጥራት ቢያንስ አከራካሪ ሆነው ይቆያሉ። ውህደትና የወዛደሩም ፓርቲ ጥያቄ የቶሎ ቶሎና ያቋራጭ መንገዶችን መስመር ይይዛሉ….ወዘተ።
ብቻ ይህኛውን ታሪክ ደግሞ፣ ለሚቀጥሉት ጽሁፎቻችን ማቆየት ሳይኖርብን አይቀርም።
የተራማጆች ህብረት መመስረት አንድ አብዮታዊ እርምጃ ወደፊት እንደነበር፣ አንድም ሀቀኛ ተራማጅ፣ አንድም የአብዮቱ ወገን የሆነ ሰው የማይክደው ጉዳይ ነው። ነገር ግን ለስድስት ወሮች ሙሉ የተራማጆችን ህብረት ሰንክለው የያዙት ጉዳዮች ደግሞ፣ በአያሌ አሉባልታዎችና የፈጠራ ክሶች የተፈጠሩት አለመተማመንና አጉል ጥርጣሬዎች እንደነበሩም የዚያኑ ያህል እውነት ነው። ሆኖም፣ ከሁሉም በላይ እንቅፋቶች የሆኑት ደግሞ፣ በአንድ ወገን እነዚህ ጎጅ ነገሮች በኣንዳንድ የህብረቱ አባል ድርጅቶችና ግለሰቦች ጭምር መስፋፋታቸውና እንደ እውነት መወሰዳቸው ነው። በሌላው ወገን፣ ዲሞክራሲያዊና ሀቀኛ ውይይቶች ለማካሄድ ባለመቻላቸው ነው። እንደዚሁም፣ የፖለቲካ አቋሞች በአጭር ጊዜ ውስጥ መለዋወጣቸውና ፍፁም መቀየራቸው ሌላው ተጨማሪ ምክንያት ሆኗል። በመጨረሻም፣ ዛሬ በገሃድ ልንናገረው የማንችለው በብሄራዊ ፖለቲካችን ውስጥ የገባ ወሳኝ ምክንያት አለ። ለእርሱ ጊዜው ይመጣል። ይሁንና፣ ዞሮ ዞሮ ግን፣ መሰረታዊና ዋናው ምክንያት ዴሞክራሲያዊ መብቶች በተለይ በአብዮታዊ ሰደድ/=“ደርግ”/ አለመታወቃቸው ነው።
በክፍል አራት ውስጥ የመኢሶንን ልሳን በሰፊው እየጠቀሰን እንዳሳየነው፣ መኢሶን “ዲሞክራሲያዊና ሀቀኛ ውይይት ሽኩቻን፣ አሉባልታንና የስም ማጥፋት ዘመቻን እንዲተኩ” ያልወተወተበት አንድም ጊዜ አልነበረም።
እንደዚሁም “የመኢሶን እምነትና ምኞች፣ ሃቀኛ የተራማጆች ሕብረት እንዲመሰረት፣ ከዚያም እውነተኛ የወዛደሩ ፓርቲ እንዲፈጠርና ሕዝባዊ አብዮታዊ ግንባር እንዲቋቋም መሆኑን” ያላሳወቀበት አንድም ጊዜ አልነበረም።
ይሁንና፣ የመኢሶን ስድስት ወሮች ሙሉ “መማልና መገዘት” የተፈጠሩትን ጥርጣሬዎች ሊያስወግድ አልቻለም። አለመተማመንን በመተማመን ሊተካ አልቻለም። በተቃራኒ፣ ጸረ መኢሶን ዘመቻን በሚመለከተው በኩል፣ አሉባልታዎችና የፈጠራ ክሶች በስድስት ወሮች ውስጥ፡- “መኢሶን የነፍጠኞችና የትምክህተኞች ድርጅት ነው፤ መኢሶን የጠባብ ብሄረተኛ ድርጅት ነው፤ መኢሶን የኤርትራን መገንጠል ይደግፋል፣ መኢሶን የሕዝብ ድርጅት ጉዳይ ጊዜያዊ ጽ/ቤትና የፖለቲካ ት/ቤትን በሞኖፖል ይዟል፤ መኢሶን የቢሮክራት ማርኪሲስቶች ድርጅት ነው፤ መኢሶን የጠባብ ቡድን ድርጅት ነው፤ መኢሶን ስልጣን የጠማው ድርጅት ነው፤ መኢሶን አዲሱ ኢህአፖ ነው፤ መኢሶን ህብረትን አይፈልግም፤ መኢሶን፤ መኢሶን…” ከሚሉት አልፈው፣ በሰኔና በሃምሌ ወሮች ውስጥ፡- “መኢሶን ት/ቤቶችን ለማስቆም አድማ እየቀሰቀሰ ነው፤ መኢሶን በፋብሪካዎች ውስጥ የሥራ አድማ ሊጠራ ነው፤ መኢሶን በሊቀ መንበሩና በደርግ ላይ ሰላማዊ ሰልፍ ሊያስደረግ ነው፤ መኢሶን ዘመቻውን አይደግፍም፤ መኢሶን ከውጭ የምናገኘውን ድጋፍ ይቃወማል፤ መኢሶን፣ መኢሶን…..” ወደሚሉ ተሻገረ።
መንግሥትም በደረሱት “መረጃዎች” መሰረት አንዳንድ እርምጃዎች መውሰድ ጀመረ። ሰላዮቹን አሰማራ። ዟሪ ደብዳቤዎችን በተነ። እንቅስቃሴዎችን መቆጣጠር ጀመረ። አንዳንድ አባሎች ከሕዝብ ድርጅት ጽ/ቤት ታገዱ። አንዳንድ ካድሬዎችም ይታሰሩ ጀመር። አንዳንዶቹም ተረሸኑ። በመኢሶን ላይ የሚደረገው ቅስቀሳ፣ ከነጭራሹ “የፀደይ መጽሔት፣ የጋዜጦችንና የቴሌቪዥን ቴያትር መድረኮችን እስከ መያዝ በቃ። እያለም፣ ወደ ሴሚናር አዳራሾች ዘለቀ። በአደባባዮች ተስተጋባ። “ታጠቅ” ጦር ሠፈር ገባ። መኢሶን “የሚመታው” ብቻ ሳይሆን፣ እየተመታ ያለው ድርጅት ሆነ።
ሆኖም፣ የኢማሌድህ ጽሁፍ እነዚህን ሁሉ ጉዳዩች፡-
“መኢሶን በአሉባልታ ያምናል። በአሉባልታ ይደናገጣል። ስሜን አጠፉኝ፣ አጥላሉኝ፣ ሊያስመቱኝ ነው በማለት ሮሮውን ያሰማል እንጂ፣ ችግሮችን አብዮታዊ በሆነ መንገድ ለመፍታት ሙከራ አላደረገም” /26/
በማለት ያልፋቸዋል። እኛም እንግዲህ አንባቢ ያገናዝብ ብለን ከመጠየቅ በስተቀር ሌላ አማራጭ አይኖረንም።
አንደኛ፣ መኢሶን “ችግሮቹን አብዮታዊ በሆነ መንገድ ለመፍታት” የወሰዳቸው አቋሞችና ያቀረባቸው ጥያቄዎቹች ሁሉ፣ በሰሕድ ቁጥሮች ውስጥ በገሀድ ተጽፈው ይገኛሉ። እንደዚሁም፣ የአብዮት ፋናን፣ የአዲስ ፋናንና የታጋይ ኢትዮጵያዊትን እትሞች መመልከት ይቻላል። በዚህም ጽሁፍ ውስጥ አልፈን አልፈን እየጠቀስን ለማመልከት ሞክረናል። በተጨማሪ የዚህን ጽሑፍ ክፍል ስድስት ለማገናዘብ ይቻላል።
ሁለተኛ፣ ሌሎቹ ድርጅቶች “ችግሮቹን አብዮታዊ በሆነ መንገድ ለመፍታት” በዚያ ወቅት ውስጥ የወሰዱትን ወይንም ያልወሰዱትን አቋም ከልሳናቸው ላይ አንብቦ ለመገንዘብ ይቻላል። እንደ ወዝ ሊግ ማድፈጥም አቋም እንደሆነ ማመልከቱ ትርፍ ይመስለናል።
ሶስተኛው፣ በጊዜው በመኢሶን ላይ የተወሰዱት የጭቆና እርምጃዎች የታወቁ ናቸው።
በመጨረሻም፣ በአሉባልታዎችና በፈጠራ ክሶች ላይ፣ በዚያን ጊዜም ሆነ አሁን ያለው ግልጽ አቋም፣ የድርጅቱን ልሳን በማንበብ ለመረዳት የሚቻል ነገር ነው። እንደሚከተለው ነው፡-
ሰሕድ 59 -ሐምሌ 4/69
“ዛሬ አገራችን በስንት ችግሮች ተውጣ እያየናት፣ ከዚህ ላይ /አሉባልታዎችን/ ማንሳታችን ለነሱ ዋጋ ለመስጠት አይደለም። አሉባልታ፣ ሃሜት በተገለጹ አቋም ላይ ሳይሆን፤ ባልተባለ፣ ባልተፃፈና ባልተነገረ ጉዳይ ላይ አንድን ንቅናቄ መተቸት የሚያሳየው ምንድነው? ቢያንስ ሁለት ችግሮችን ያሳየናል። አንደኛ አድሃሪዎችና አድርባዮች በአንድ ንቅናቄ ላይ አሉባልታ ሲያበዙ፣ ያ ንቅናቄ በያዘው አብዮታዊ አቋም የተነሳ፣ ለጠላቶቹ ከአሉባልታና ከፊውዳል ሃሜት ሌላ መፈናፈኛ ነስቷቸዋል ማለት ነው። ሁለተኛ፣ ደግሞ፣ ሌኒን እንዳለው በአሉባልታ መጠቀም የፖለቲካ ክስረት አስተማማኝ ምልክት ነው።
“ነገር ግን ይህንን ስላልን፣ አሉባልታዎች አደጋ የላቸውም ማለት አይደለም። ዝም ብለው ከተጠራቀሙም አድሃሪዎችና አድርባዮች የአብዮቱን ሰፈር ለመከፋፈል፣ ለማጋጨትና ለማዳከም ሊጠቅሟቸው ይችላሉ። እንዲያውም ዛሬ አገራችን በብዙ ችግሮች ተወጥራ፣ በነዚህ ጉዳዮች ለመጻፍ መነሳታችን፣ ዛሬም በመኢሶን ላይ የተጠራቀሙት አሉባልታዎች ከመግነናቸው የተነሳ፣ ተራማጆችን ሊያጋጩና የአብዮቱን ሰፈር ሊከፋፍሉ የሚችሉበት አደገኛ ደረጃ ላይ ደርሰዋል ብለን በማመናችን ነው። ስለሆነም፣ የዚህ ጽሁፋችን ዓላማ፣ በአድሃሪዎች የመከፋፈል ሴራ በተራማጆችና በሰፊው ሕዝብ ሰፈር የተነሳው አደገኛ ውዥንብር እንዲጠራና የአብዮቱ ሰፈር በዚያው ልክ ጥራትና ጥንካሬ አግኝቶ ትግልን ለማድረግ ነው።”
መቼም፣ በአሉባልታና በፈጠራ ክሶች ላይ ከዚህ የበለጠ ግልፅ ለመሆን አስቸጋሪ ነው። ደግሞ መፍትሄያቸው ዛሬም ቢሆን ዲሞክራሲና ሀቀኛ ውይይት ብቻ ነው።
ስለዚህ ነው፣ መኢሶን ዛሬም ቢሆን ዲሞክራሲያዊና ሃቀኛ ውይይቶችን ያለማቋረጥ የሚጠይቀውና ለዚሁ የሚታገለው። ጥራትና ጥንካሬ ያለው ሀቀኛ፣ ታጋይ፣ አብዮታዊና ዲሞክራሲያዊ የሆነ የተራማጆች ህብረት ሊመሠረትና እንደ ብረት ጠንክሮ ሊገነባ የሚችለው፡- በዚህ ዓይነቱ የአንድነትና የትግል ማስመር ብቻ ነው የሚለው። ጊ.ወ.አ. ደርግ እና ኢማሌድህ፣ አሁንም ቢሆን ለዚህ ለመኢሶን ተደጋጋሚ ጥያቄ ጆሮአቸውን እንዲሰጡ፣ ለውይይት አመቺ የሆኑ ዲሞክራሲያዊ ሁኔታዎችን እንዲፈጥሩ አጥብቆ የሚጠይቀው።
ይሁንና፣ እዚህ ላይ ደግሞ፣ መኢሶን ውይይትና ሀቀኛ ህብረት ባለ መጠን፣ የመንግሥት ጭቆና በመኢሶን ላይ እየከፋና እየተባባሰ እንደመጣ ሳይገልጽ ለማለፍ አንችልም። በዚህም፣ መኢሶን ሳይሆን ጊ.ወ.አ. ደርግና ኢማሌድህ፣ በኢትዮጵያ ሕዝቦችና በዓለም ተራማጆች ፊት እየተጋለጡበት ናቸው።
የትግል ስንት ለውጥ ለምንና መቼ? የሚሉትን ጥያቄዎች፣ የኢማሌድህ ጽሁፍ ከፊል እውነት በመናገር መልሷቸዋል። ነገር ግን፣ ልብ ብሎ ያነበበው ሰው ደግሞ፣ የኢማሌድህ መልስ በብረዛ የተበከለና ትጥቅ አስፈቺ እንደሆነ ወዲያውኑ ይረዳል። እነርሱኑ እንጠቅሳለን።
“ማርክሳዊ ሌኒናውዊያን ከሰፊው ሕዝብ ጋር ተዋህዶ ለመታገል የፕሮፓጋንዳና የቅስቀሳ ተግባር በሚገባ ለማካሄድ፣ ያለበትን ታሪካዊ ወቅት፣ የህብረተሰብ፣ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮችን እንዲሁም አለማቀፋዊ ሁኔታዎችን በማጥናት፣ በመተንተንና ትክክለኛ ግምገማ በማድረግ፣ የአብዮቱን ሰፈር ስትራቴጂያዊ አላማ እግቡ ለማድረስ የሚያስችሉ ሕጋዊ እና ስውር የትግል ስልቶችን በማቀናበር መታገል አለባቸው።” /22/
የኢማሌድህ መልስ እስከዚህ ነጥብ ድረስ እጅግም የሚያከራከር አይደለም። መኢሶንም ከግንቦት 67 እስከ ነሐሴ 69 የታገለው “ህጋዊ እና ስውር የትግል ስልቶችን በማቀናበር” ነበር። ይህንንም ያደረገው “የአብዮቱን ሰፈር ስትራቴጅያዊ አላማ እገቡ ለማድረስ” ለማገዝ ነበር።
ይሁንና፣ ኢማሌድህ ከዚህ ቀጥሎ ደግሞ፣
“አብዮታዊያን ሕጋዊ ትግል ለማካሄድ በፍጹም የማይችሉበት ደረጃ ከደረሱ ግን፣ ያላቸው ብቸኛ አማራጭ መንገድ በስውር የሚደረገውን ትግል ማስፋፋትና ማጠናከር ነው። ከትግል ስልታቸው አንዱ ስለሆነ፣ ይህን ማሌዎች ሁሉ ይደግፉታል።” /22/
ሲል ግን ብርሃንና የጨለማን ያህል እንለያያለን።
አንባቢዎች የኢማሌድህ “ማርክሲስት ሌኒኒስት” አባል ድርጅቶችና የዘቀጡበትን በራዥነት ልብ ብላችሁ ተመልከቱት።
የመጀመሪያ አቋም “ህጋዊና ስውር የትግል ስልቶችን ለማቀነባበር መታገል” ነበር። ነገር ግን አለፍ ሳይሉ ደግሞ፣ “በስውር የሚደረገውን ትግል ማስፋፋትና ማጠናከር” የሚገባው “ሕጋዊ ትግል በፍጹም ለማካሄድ ካልተቻለ ነው” ይላሉ። ደግሞ፣ ይህንኑም፣ ማሌያዊ አቋም ብለውት፣ “ይህን ማሌዎች ይደግፉታል” ይላሉ።
ይህ ምን ማለት ነው? ይህ በአጭሩ፣
አንደኛ፣ “ስትራቴጂያዊ አላማ” በሕጋዊ ትግል እግቡ ይደርሳል። ምክንያቱም በኢትዮጵያችን ላይ ፍጹም ዲሞክራሲ ሰፍኗል ማለት ነው። መንግሥት ከመደቦች ውጪ ነው ማለት ነው።
ሁለተኛ፣ “ሕጋዊ ትግልን” በፍጹም ለማካሄድ እስካልተቻለ ድረስ፣ የህቡዕ ትግልን ለማስፋፋትና ለማጠናከር የሚታገሉትን የፖለቲካ ድርጅቶች እናወግዛለን ማለት ነው። ብቻ እዚህም ላይ፣ የኢማሌድህ ጽሁፍ ደራሲዎች “በፍጹም” መች “ፍጹም” እንደምትሆን ቢገልፁልን በተገባ ነበር።
ሦስተኛ በመጨረሻም፣ ጭቁኑ የኢትዮጵያ ሰፊ ሕዝብ፣ ሕዝባዊ መንግሥትን ከምርጫ ሳጥን በሚመነጭ ኃይል ላይ መስርቶ፣ የፖለቲካ ስልጣንን ሊጨብጥ ይችላል ማለት ነው። ከዚህም ከተነሳን፣ “ለነቃ፣ ለተደራጀና ለታጠቀ ሕዝባዊ አመጽ” ጥሪ የሚያደርጉትንና ለዚህም አቋም የሚታገሉት ተራማጆች ክፍሎች እንደ “ቀኝ መንገደኛ”፣ “ጀብደኛ”፣ “ብርዝ”…. ወዘተ ከሚታዩበት አስተያየት ላይ እንደርሳለን። ነገ ጠዋት፣ “በሕጋዊ ትግልና” በሆነው ዓይነት “የወዝአደሩ ፓርቲ” ከተመሠረተልን በኋላም፣ “ኢትዮጵያ ተአምር አሳየች”፣ “ማርክሲዝም ሌኒኒዝም ቢያንስ በዚህ በፖለቲካ ስልጣን ጥያቄ ላይ መታረም አለበት” ልንባል ነው። “ነገሩ በግብጽ፣ በቺሊ፣ በሱማሊያ፣ በሱዳን፣ በአንጎላ…. ባይሰራም፣ በኢትዮጵያ ምድር ላይ ለምልሞ፣ ፈንድቶ፣ አብቦ ታየ” ልንባል ነው።
እንግዲህ የኢትዮጵያ ሕዝቦችና ተራማጆች ምን ትፈልጋላችሁ?!! የኢትዮጵያ ሰማያት ቀልተዋል!!! ምድሩም ገነት ሆኗል!!! ሌላው ቀርቶ የኢትዮጵያ ዶሮዎችና አእዋፋት እንኳ ሶሻሊስት የሆኑትን ቀያይ እንቁላሎች እየጣሉ ናቸው!!!….ወዘተ። አላስ፣ “ያለምንም ደም፣ ኢትዮጵያ ትቅደም”።
ለማንኛውም፣ በነሐሴ 1969 መኢሶን የትግል ስልት ለውጥ እንዳደረገ የተወቀ ነው። መኢሶንም፣ የትግል ስልት ለውጥ ያደረገው በነሲብ ሳይሆን “ታሪካዊውን ወቅት፣ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ ጉዳዮችንና ዓለም አቀፋዊ ሁኔታዎችን አጥንቶ፣ ተንትኖና ገምግሞ፣ የአብዮቱን ሰፈር ስትራቴጅያዊ አላማ ከግቡ ለማድረስ” በማለት ነው። ይሁንና፣ እዚሁ ላይ ስንደርስ ደግሞ፣ “ሁኔታዎችን በትክክል አጥንቷል፣ ተንትኗል፣ ገምግሟል” ወይ? የሚለው ጥያቄ መነሳቱ አይቀርም። አንዳንዶቹ “አማራጭ መንገድ” አልነበረም እያሉ ራሳቸውን ይጠይቁ ይሆናል። ኢማሌድህ ደግሞ፣ “ሕጋዊ ትግልን ለማካሄድ በፍፁም ከማይቻልበት ደረጃ” “ፍፁም” መች ደረስንና ይላሉ።
ኢማሌድህ ለነዚህ ጥያቄዎች የሚሰጠው መልስ ፍጹም አጭር ነው። እርሱን በመጥቀስ እንጀምር፡-
“መኢሶን ዝባዝንኬውን፣ ዝክንትሉን፣ እንደምክንያት ከደረደረ በኃላ ፈረጠጠ” /26/ የሚል ነው። የኢማሌድህ መልስ እቺው ብቻ ናት። እኛም እንግዲህ አሁንም “ዝባዝንኬውንና ዝክንትሉን እንደመደርደር” አይቆጠርብንና፣ የአንባቢዎችን ትዕግስት ጠይቀን እነርሱን ወደ መደርደር እናምራ። ወደ ነበሩት ሁኔታዎች ተመልሰን በእውነት ስለ እውነት እናስተውል።
-መኢሶን የትግል ስልት ለውጥ ያደረገው:-
አንደኛና ከሁሉም በፊት፣ ባለው አቋሙና ችሎታው ሁሉ “ለዘላቂው ትግል” /የሰህድ 61 ርእስ/ አመቺ የሆኑ ሁኔታዎችን ለመፍጠር ነው። ስለዚህም ጉዳይ፣ የትግል ስልት ለውጥ ማድረጉን ባስታወቀበት የልሳኑ እትም ቁ. 61 ውስጥ እንደሚከተለው ተናግሯል።
“መኢሶን የትግል ስልት ለውጥ ያደረገው አብዮቱን ትክክለኛውን ፈር ለማስያዝ፣ የአገሪቷን ብሔራዊ ነፃነት
ለማስከበርና ምንም ተጽዕኖ በማይኖረው መንገድ የበኩሉን አስተዋጽኦ ለማድረግ ነው።”
ሁለተኛ፣
“ለጊ.ወ.አ. ደርግ እና ለተራማጆች ህብረት በየወቅቱ ያቀረባቸውን ሐሳቦች በቅን መንፈስና ከአብዮቱ አንጻር በመመልከት ፈንታ፣ ሀሳቦቹ ከመኢሶን በመንጨታቸው ብቻ ደርግ እና አንዳንዶቹ ድርጅቶች በጥርጣሬ አይን እያዩአቸው ከሥራ ላይ ሳይወሉ በመቅረታቸው ነው። ስለዚህም፣ ለአብዮቱ የሚፈለገውንና የሚጠበቀውን ያህል አስተዋጽኦ ለማድረግ ባለመቻሉ ነው።” /ሰህድ 61/ ነሐሴ 1969/
በዚህም አንጻር በየክፍሉ የሚከተሉትን ሀሳቦችና ጥያቄዎች ቀርበው ነበር።
ሀ/ ዘመቻውና አብዮታዊ አመራርን በሚመለከተው በኩል
- የሐረርጌ፣ ባሌ ሲዳሞ አርሶ አደሮች ባስቸኳይ እንዲታጠቁ፣
- ከህብረቱ አባል ድርጅቶች የተወጣጡ ካድሬዎች ባስቸኳይ ወደዚህ ስፍራዎች በብዛት እንዲላኩ፣
- በታጠቅ ጦር ሰፈር ውስጥ የህብረቱ አባል ድርጅቶች ካድሬዎች እንዲመደቡ፣
- በዕርዮተ ዓለም አስተሳሰብ፣ በአሰራር ዘዴና በአብዮታዊ ዲሲፕሊን የተሳሰሩ የፖለቲካ አንቂዎች ከሰራዊቱ ጋር እንዲዋሃዱ እና ከተራው ተዋጊ ጋር በጥብቅ እንዲተሳሰሩ፣
- የተራማጆች ህብረትን ለማጠናከር ጥድፊያ እንዲደረግ፣
- የጠላትን ሰፈር ቅራኔዎች በብልሃት እና በአስተዋይነት እንድንጠቀም፣
- የታወቁ አድሃሪዎችን በቁጥጥር ስር ለማዋል፣
- ዲሞክራሲያዊ መብቶች በሥራ ላይ እንዲወሉ፣
- የሕዝባዊ ድርጅቶች መንቃት፣ መደራጀትና መታጠቅ ተጠናክሮ እንዲፋፋም፣
- የታሰሩት ተራማጆችና አገር ወዳዶች እንዲፈቱ፣
- የብሄረሰቦችን መብት ደረጃ በደረጃ ከሥራ ላይ ማዋል፣
- በመሐል አገር አብዮቱን ማስፋፋም።
ነገር ግን፣ የኢማሌድህ ጽሑፍ እነዚህን ሁሉ ጉዳዮችና “ዝባዝንኬና ዝክንትል” ብሎ በመተቸት ያልፋቸዋል። ምክንያቱም ግልጽ ነው። ምክንያቱም ለእያንዳንዱ ነጥብ መልስ ለመስጠት አይቻልምና።
ስለዚህም፣ ኢማሌድህ መኢሶንን ለማቅረብ የሚፈልገው፣ ይልቁኑ “ፈርቶ እንደፈረጠጠ”፣ “ፈርቶ እንደሸሸ” ድርጅት ነው። “ማርክሲዝም” ሲቸግረው፣ ወደ ፊውዳል አስተሳሰብ ይዞርና፣ ነገሮችን ሁሉ “የወንድነት” ጥያቄ አድርጓቸው ቁጭ ይላል። “ፈረጠጠ” ፣ “ሸሸ”…ወዘተ ይላል። ከፍ ሲልም ከዚህ በታች የምንጠቅሰውን ጽፎ ነበር።
“መኢሶን ራሱን ካልወደደና ያለሁት አብዮተኛ ድርጅት፣ ታጋይ ድርጅት እኔ ብቻ ነኝ” ካላለ በስተቀር፣ እሱን ብቻ አድሃሪያን ሊፈልጡትና ሊቆርጡት የሚችሉበት ምክንያት የለም። ዕርግጥ፣ የሕዝብ ድርጅት ጉዳይ ጊዜያዊ ጽ/ቤት ሰፊውን ሕዝብ በማስተማር፣ በማንቃትና በማደራጀት በኩል ከፍተኛ ሚና መጫወቱን የተረዱ አድሃሪያን/ ከደርግ አካባቢ ጭምር-ቅንፍ የሰህድ/ ሊያፈርሱትና ካድሬዎችን ለማሳደድ ከፍተኛ ዘመቻ ያደርጉ ነበር። ሕዝብን በማንቃት፣ በማደራጀት ተግባር የተሰማሩት ለአብዮቱ የቆሙት የመኢሶን ደጋፊዎችና አባሎች ብቻ አልነበሩም” /26/
ይህ የኢማሌድህ ጽሁፍ ውስጥ የጠቀስነው አነጋገር እንደሚታየው በእውነቱ ልብን የሚበላ ነው። ይሁንና ከነባራዊ ሁኔታዎች ጋር ሲገናዘብ ደግሞ፣ ስሜትን ለመማፀን የተጫረን እንጂ፣ ሌላ ትርጉም የለውም። ከመጀመሪያው መኢሶን “ያለሁት አብዮተኛ ድርጅት፣ ታጋይ ድርጅት እኔ ብቻ ነኝ” ብሎ አያውቅም። ይህ እንዲያው በባዶ ሜዳ ነገር ማሳመር እና አንገብጋቢ ጥያቄዎችን ለመሸወድ መንሸዋረር ነው።
ሁለተኛ፣ መኢሶን “ለአብዮቱ የቆሙት የመኢሶን አባሎችና ደጋፊዎች ብቻ ናቸው” ብሎም አያምንም። መኢሶን የሚያምነው፣ ለብሔራዊ ዴሞክራሲያዊ አብዮት የቆሙት ከ90 በመቶ በላይ የሚሆኑት የኢትዮጵያ ሕዝቦች ናቸው ብሎ ነው። ነገር ግን ኢማሌድህም ለአብዮቱ ከቆመ ደግሞ፣ እንደዚህ ካሉት ርካሽና የቦዘኔ ክርክሮች ዘዴዎች መላቀቅ አለበት።
ሶስተኛ፣ ስለዚህም፣ እነዚህም ላይ ቢሆን እውነቱን መናገር ያስፈልጋል። በወቅቱ በነበረው ሁኔታ በህጋዊ መስክ ላይ ይገኙ የነበሩት አብዛኛዎቹ ጓዶች የመኢሶን አባሎችና ደጋፊዎች ነበሩ። አብዛኞቹ በቅጥር ነፍሰ ገዳዮች እየተረሸኑ የወደቁት ጓዶችም የመኢሶን አባሎችና ደጋፊዎች ነበሩ። ይህንን እውነት የሕዝብ ድርጅት ጽ/ቤት፣ የፖለቲካ ትምህርት ቤት፣ የቀበሌ ማህበራት የወዛደር ቤቶች ወዘተ ስታትስቲክሶች በቀላሉ ያረጋገጡታል። ኢማሌድህ፣ ይህንን እውነት ለመናገር የሚፈራበት ወይንም የሚያፍርበት ምክንያት ሊኖረው ባልተገባ ነበር።
አራተኛና በመጨረሻም፣ “እርግጥ …. አድሀሪያን ጽ/ቤቱን ሊያፈርሱትና ካድሬዎችን ለማሳደድ ዘመቻ ያደርጉ ነበር” ካለ አይቀር፣ በጽ/ቤቱ ስም የሚደረገው ዘመቻ በተለይ ሰው ላይ እንደነበረ መግለጽ ነበረበት። ይህ ጉዳይ ከነ-አለማየሁ— ሞገሰ ጀምሮ የታወቀ መሆኑን ማሳወቅ ነበረበት። ከነርሱሰ በኋላ ለምን ቀጠለ?
“እርግጥ” እንበል፣ እኛ ደሞ፣ “እርግጥ” ይህንን ማለት፣ “አድሃሪያን ሊፈልጡና ሊቆርጡ” የተነሱት መኢሶንን ብቻ ነው ማለት አይደለም። በአንጻሩ፣ አድሃሪያን በኢትዮጵያውያን ሀቀኛ ተራማጆች፣ አገር ወዳዶች፣ ዲሞክራቶች፣ የሕዝብ ተመራጮች…..ወዘተ. የሚቃጡት ሴራ ሁሉ ደግሞ፣ የመኢሶን ጉዳይ ብቻ ነው ማለት አይደለም። የአብዮታችንና የአብዮታዊ ኃይሎች ሁሉ ጥያቄ ነው።
ይልቁኑ፣ እንደዚያ ባለው ሰዓት ሀቀኛ ተራማጆችና አብዮታዊያን በጋራ ምን ዓይነት አቋም ይወስዳሉ? በዚያ ሰዓትስ፣ ለምን ከአንዳች ዓይነት የጋራ አቋም ላይ ለመድረስ ሳይችሉ ቀሩ?
የኢማሌደህ ጽሁፍ መመለስ የነበረበት እነዚህን ጥያቄዎች ነበር። እኛ በዚህ ጽሁፋችን ውስጥ በሙሉ በመሠረቱ የመለስነው እነዚህን ጥያቄዎች ነው።
የኢማሌድህ ጽሁፍ ደራሲዎች እነዚህ ላይ እንደገና ጣሪያዎችን ከማተሩ በኋላ፣
“እኮ! ተራማጆች ታግለው ደርግን እንደገና ከአብዮቱ ሰፈር አቁመውታል” ቢሉን፣ ወንድሞች! የብሔራዊ ዲሞክራሲያዊ አብዮትንና ማርክሲዝም ሌኒኒዝም በጭንቅላታቸው ተተክለዋል ብለን እንመልስላቸዋለን። የኢትዮጵያችን ሁኔታ ይናገር።
የብሄራዊ ዲሞክራሲያችን አብዮታችን ፕሮግራም ለዘላለም ይኑር!
ማርክሲዝም ሌኒኒዝም ለዘላለም ይኑር!
እንግዲህ ወደ መጨረሻው ጥያቄ እንመለስ።
እኛ እንደተረዳነው፣ በመኢሶን ላይ የሚቀርበው “ሂስ” እስከዚህም መኢሶን የትግል ስልት ለውጥ በማድረጉ ምክንያት ሊሆን አልቻለም። ይልቁኑ “በዚያ ሰዓት” የትግል ስልት ለውጥ በማድረጉ ነው። እስኪ ይህንን ደግሞ እንመለከተው።
እርግጥ፣ ይህ ጥያቄ ከዘጠኝ ወሮች በኋላ ሲቀርብ አደናጋሪ ሊሆን አይችልም። በሌላ በኩል ደግሞ፣ ስሜትን ለመቀስቀስ፣ ለዲማጎዢ… ወዘተ አመቺም ነው። ይኸው በየአደባባዩ እንደሚሰማው፣ አንደኛው መኢሶንን ከንጉሥ ኃይለሥላሴ ጋር ለማነጻጸር ይሞክራል። ሌላው፣ የመደብ መንሸራተት ነው ይላል። ሌሎቹም እንደ “ክህደት” ሊቆጥሩት ይቃጣቸዋል። ሁሉም ስሜትን ለመቀስቀስ፣ ዲማጎዢን ለመንዛት የታቀዱ ናቸው።
ይሁንና፣ በነዚህ ምክንያቶች ደግሞ፣ በዚያ ሰዓት የነበሩት ነባራዊ ነገሮችና ሁኔታዎች፣ ከምድረ ኢትዮጵያና ከኢትዮጵያ ሕዝቦች የትግል ታሪክ ውስጥ በቀላሉ የሚፋቁ አይሆኑም። ስለዚህም፣ በዚያን ጊዜ በነበሩት ሁኔታዎች ምክንያት ዛሬ ያሉትን ገና ለረጅም ጊዜ አንደ ነቀርሳ ተተክለው የሚቆዩት ሁኔታዎች ከምድረ ኢትዮጵያ አይጠፉም። ዕውነተኛ ማርክሲስቶች፣ “አብዮትና ፀረ አብዮት በኢትዮጵያ” በሚል ርዕሰ ለሚጽፉት ድርሰት፣ ከዕንቁ የሚከብርን መረጃዎች እየሰበሰቡ ናቸው። የኛም ገለጻ ትንቢት አይደለም። የምንናገረው ስላሉ ነገሮች ነው።
ለማንኛውም፣ ማርክሳዊ ታሪክ ነገሮችን የሚመረምረውና የሚገመግመው፣ ነገሮቹ በተከናወኑበት ነባራዊ ሁኔታ ውስጥ…….. አድርጎ ነው። ከስሜትና ከቂም አርቆ ነው። የኢማሌድህ ጽሁፍ ራሱ ከአንድ ቦታ ላይ እንዳለው፡-
“የነገሮችንና የክስተቶችን አስተዳደግ በማጤንና ሁኔታዎችን በተጨባጭ በመገምገም፤አዝማሚያዎችን በመገንዘብ፤ ቅራኔዎችን በየደረጃቸው በመመድብ”/31/ ነው።
በእውነቱ፣ ኢማሌድህም በመኢሶን የትግል ስልት ለውጥ ጥያቄም ላይ ማርክሳዊ ለመሆን ቢሞክር በተሻለ ነበር። ከዚህም አልፎ በፍጹም እውነት ያልሆኑ ነገሮችን እስከመጻፍና እስከ መናገር ደርሷል። ለምሳሌ፣“ለሰፊው ሕዝብ ሸቀጣ ሸቀጥ ያመጡ ይመስል ወደ አውሮፓ ተሰደዱ” /23-24/ ሲል፣ እነማንን ማለት እንደሆነ ግራ የሚያጋባ ነው። ሰፊው ሕዝብ “ሸቀጣ ሸቀጥ” እንደቸገረው ለመናገር ፈልጎ እንደሆነ፣ ሌላ መድረክ ቢመርጥ በተሻለ ነበር።
ለማንኛውም እውነቱ እንደሚከተለው ነው። በመኢሶን በኩል በድርጅቱ የውጭ ሥራ ተመድቦ ወደ ውጭ የተላከው አንድ ሰው ብቻ ነው። ይህ ደግም፣ ኢማሌድህ ቢወድም ቢጠላም የድርጅቱ መብት ነው። ሌሎች የመኢሶን አባሎች፣ ደጋፊዎችና ወዳጆች ግን ታስረውም ይሆን ተገድለው እዚህ በኢትዮጵያ ምድር የሚገኙ ናቸው። ሌሎቹም እንደሁኔታውና እንደ ጊዜው እየታገሉ ናቸው።
በእውነቱ ኢማሌድህ እንደዚህ ዓይነቱን ርካሽና የቦዘኔ የክርክር ዘዴዎች መጠቀሙ እጅግ የሚያስገርም ነው።
ይልቁኑ፣ የኢማሌድህን ጽሁፍ ደራሲዎች፣ ደጋግሞ የጠቀሱትን ሰህድ 61ን በደንብ ቢያነቡት ኑሮ፣ ከእንደዚህ ዓይነቱ አሳፋሪ እና የሚያስገምት ስህተት ውስጥ ባልወደቁ ነበር። መኢሶን በትግል ስልት ለውጡ ሌላ ምንም አላደረገም “በህጋዊ የትግል መስክ ያሰማራቸውን አንዳንድ አባሎቹን ወደ ህቡእ የትግል መስክ አዛውረ እንጂ”። “ለዘላቂው ትግል” ብሎ ቆራጥ እርምጃው ወሰደ እንጂ። ለአብዮታዊ አመራር፣ የዲሞክራሲና ለብሔራዊ ነፃነት የሚደረገውን መራራ ትግል ለማገዝ ወሳኝ የሆነን ለውጥ አደረገ እንጂ….ወዘተ።
እንግዲህ እስቲ ኢማሌድህን እንጠይቀው፡-
ለመሆኑ አንድ የፖለቲካ ድርጅት እንደዚህ ዓይነቱን እርምጃ የመውሰድ መብት አለው ወይንስ የለውም?
ለመሆኑ አንድ የፖለቲካ ድርጅት፣ በአንድ በኩል ፀረ አብዮት እንደዚያ እያስገመገመ በመጣበት ወቅት፤ በሌላው በኩል፣ ህጋዊው የትግል መድረክ እንደዚያ እየጠበበ በሄደበት ወቅት፤ እንደዚሁም የተራማጆች ህብረት በአያሌ ፀረ ህብረት አድራጎቶች ተሰንክሎ በቆመበት ወቅት፣ የዲሞክራሲ መብቶች እንደሚታፈኑ ግልጽ በሆነበት ወቅት፤ ብሔራዊ ነፃነታችን ከከፍተኛና አሳሳቢ ከሆነ ሁኔታ ውስጥ በወደቀበት ወቅት፤ የወዛደሩም ፓርቲ በዚያም በዚህ ለመጠፍጥፍ በሚሞከርበት ወቅት፤ በመጨረሻም፣ አባሎቹ፣ ደጋፊዎች፣ ወዳጆችና በጠቅላላው የአብዮቱ ወገኖች መከላከያ አጥተው እንደ ቅጠል በሚረግፉበት ወቅት…. ወዘተ፤ እንደዚህ ዓይነቱ እርምጃ የመውሰድ ግዴታ አለበት ወይንስ የለበትም?
ስለዚህ ጉዳይ ሲነሳ፣ የኢማሌድህ ጽሁፍ የሚጀምረው እንደተለመደው መኢሶንን በመኢሶን ጽሑፍ የገረፈው ለማስመሰል፣ ሰህድን በመጥቅስ ነው። ስለዚህም፣ “የት ላይ ይሆን?” ይላል፣ የኢማሌድህ ጽሁፍ ገና ከመጀመሪያው።
“መኢሶን ‘የትግል ስልት ለውጥ’ ካደረገ 9ኛ ወሩን ይዟል። ግን የት ላይ ይሆን፣ መኢሶን ‘አብዮቱን ትክክለኛውን ፈር ለማስያዝ፤ የአገሪቷን ብሔራዊ ነፃነት ለማስከበርና የሕዝቦቿን አንድነት ለመጠበቅ በሚደረገው ጥረት…’ የበኩሉን ያበረከተው?” /22/
በእውነቱ አስገራሚ ጥያቄ ነው። ወይ ኢማሌድህ አብዮታችን ዛሬ ስለያዘው “ፈር” ጨርሶ አላስበበትም ወይንም አልተረዳውም። እንደዚሁም፣ ስለብሔራዊ ነጻነታችን ምንም አልታየውም።… ወዘተ። በተጨማሪ፣
አንደኛ ነገር፣ ቀደም ስንል እንዳልነው፣ የኢማሌድህ ፅሁፍ ደራሲዎች፣ መኢሶን ከትግል ስልቱ ለውጥ በፊትና በኋላ ያወጣቸውን ጽሁፎች ወይ አላነበቡዋቸውም ወይንም አልተረዷቸውም አለዚያም ሊረዷቸው አልፈለጉም።
ሁለተኛ ነገር፣ ህብረቱን በሚመለከተው በኩል፣ በዚህ ጽሁፉ ክፍል 2 ውስጥ ያመለከትናቸውን ጉዳዮች ሁሉ ወይ ጨርሰው “አያውቋቸውም” ፣ ወይንም ደግሞ እ ያወቋቸውም ቢሆን፣ ሆን ብለው ለመርሳትና ለማስረሳት ቆርጠው ተነስተዋል።
ሦስተኛ ነገር፣ ሌላው ቀርቶ “በዲሞክራሲ መብቶች ጥያቄ” ላይ እንኳ በገሃድ የተደረጉት “ውይይቶችና” ዛሬም እንደ ሁኔታ የሚደረጉትን ትግሎች ወይ ዘንግተዋቸዋል፣ ወይንም ጉዳዩን ከበፊቱም “በውሳኔ” ዘግተውት ነበር።
አራተኛ ነገር፣ ይህንንም ጽሁፍ ጨምሮ የሚቀርቡት ጽሁፎች፣ “አብዮቱን ምንም ተጽዕኖ በሌለው መንገድ ትክክለኛውን ፈር ለማስያዝ” በማለት እንደሆነ ወይ ሊረዱት አልቻሉም፣ ወይንም ተረድተውትም እንደሁ ሊቀበሉት አልፈለጉም።
አምስተኛ ነገር፣ በዚህ ትግል ላይ እንዳሉ፣ አያሌ ጓዶችና ታጋዮች እንደተሰዉ፣ ኢማሉድህ ወይ ፈፅሞ “አያውቅም” ወይ አብዮትን እና ፀረ አብዮትን እንደአንድ ነገር አድርጎ ወስዷቸዋል።
ስድስተኛ ነገር፣ በዚህ ትግል ላይ እንዳሉ፣ አያሌ ጓዶችና ሀቀኛ ታጋዮች እንደታሰሩና እንደታፈኑ ….ወዘተ.፣ኢማሌድህ ወይ ፈጽሞ “አያውቅም”፣ ወይንም አሁንም አብዮትና ፀረ አብዮት ተማተውበታል። ዛሬም አያሌ ጓዶችና ሀቀኛ ታጋዮች እየተገደሉ፣ እየታሰሩ፣ እየታፈኑ ናቸው….ወዘተ።
በመጨረሻም፣ “የት ላይ ይሆን?” የሚለው ጥያቄ፣ አድራሻዎችን የሚጠይቅ እንደሁ፣ በብዕራችን እንደ ማንጠቁም ግልጽ ይመስለናል። ነገር ግን፣ መኢሶን ከትግል ስልት ለውጡም በኋላ፣ አብዮቱን ለማራመድ በሚጠቅሙ አብዮታዊና ዲሞክራሲያዊ እርምጃዎች ውስጥ ሁሉ፣ እንደ ሁኔታው በአያሌ ቀጥተኛና ተዘዋዋሪ መንገዶች እንደተሳተፉ ልንገልጽ እንወዳለን። ለወደፊቱም በዚሁ ይቀጥላል። ሆኖም፣ በዚህ ቦታ፣ በዚህ ጊዜ፣ በእንደዚህ፣ በነገሌ፣ በእነገሊት…ወዘተ ማለቱ የኛ ጉዳይ አይደለም።
በተረፈ ግን፣ ትግሉ ገና ረጅም እና መራራ ነው። ለዴሞክራሲያዊ፣ ለአብዮታዊ አመራር፣ ለብሔራዊ ነፃነትና ለኢትዮጵያ ሕዝቦች አንድነት፣ በአጭሩ ለብሔራዊ ዲሞክራሲያዊ አብዮት መታገል እንደሚባለው “የእራት ግብዣ አይደለም”። የጉራና የድንፋታም ነገር አይደለም። ዲማጉዢና የስልጣን ትምክህትም የአብዮት አዋላጆች አይሆኑም…. ወዘተ.። ተፀንሶና ተርግዞ ከ“ዘጠኝ ወሮች” በኋላ የሚወለደው፣ ሰው ብቻ እንደሆነ እናውቃለን።
ሆኖም፣ ባለፉት ዘጠኝ ወሮች ውስጥ ከፍተኛ ግልፅና ስውር ጭቆና በመኢሶን ላይ የተፈጽሟል። አያሌ አባሎቹ፣ ደጋፊዎቹና ወዳጆቹ በግልጽ እና በስውር ታስረዋል፣ ተገርፈዋል፣ ታፍነዋል፣ ተረሽነዋል፣ ተሰቃይተዋል። ዛሬም ቢሆን በመኢሶን ላይ ከፍተኛ የክትትል፣ የእስራትና የቅስቀሳ ዘመቻ እየተካሄደ ነው።
ይሁንና፣ በነዚህም ምክንያቶች ደግሞ፣ መኢሶን ከአቋሙና ከመስመሩ የቅንጣት ያህል እንኳ ዝንፍ አላለም። ለወደፊቱም ዝንፍ አይልም። ሀቀኛ ተራማጆችና የአብዮቱ ወገን የሆኑት ታጋዮች ሁሉ ይህንን ሀቅ በውል ያውቁታል።
ከእንግዲህም፣ አንባቢዎች የኢማሌድህን ፅሁፍና ይህንን የኛን ጽሑፍ ከስሜቶች ርቀው በአንክሮና በጥሞና እንዲያነቧቸው፣ እንዲያጠኗቸውና በሳይንሱ እንዲመዝኗቸው ጠይቀን ብቻ ወደ ሚቀጥለው ክፍል እንሻገር። በሚቀጥለው ክፍል ወስጥ፣ የኢማሌደህ ጽሁፍ እዚህም እዚያም ላስቀመጣቸው አንዳንድ ጥያቄዎች ትናንሽ ማስታወሻዎችን ልናስቀመጥ እንሞክራለን።
የኢማሌድህ ጽሑፍ በትክክል እንደጠቀሰው፣ በሰህድ ቁጥር 60 ውስጥ፡-
“የብሔሮች ጥያቄ እንደሌሎቹ ዲሞክራሲያዊ መብቶች የሚሟላው የመንግሥት ስልጣን በሰፊው ሕዝብ እጅ ውስጥ ሲገባ ብቻ ነው”
የሚለው የመኢሶን አቋም ተጽፏል። ኢማሌድህም ይህንን ከጠቀሰ በኋላ፣ ይህ “አቋም ትክክለኛ ሲሆን የዲሞክራሲ መብቶች ለጭቁኖች ያለ ገደብ አሁኑኑ ነው የሚለውን መፈክር በቀጥታ ይቃረናል” /20/ ሲል ተችቷል።
በኛ አስተሳሰብ፣ ነገሩ እንኳን እስከዚህ ድረስ የሚያከራከር አይደለም። ይልቁኑ የሚያስገርመው ነገር፣ ኢማሌድህ የጠቀሳቸውን ጉዳዮች እንደ “ተቃራኒ” ወይም “በቀጥታ ተቃራኒ” አድርጎ ማቅረቡ ነው። ይህንን ስንመለከት፣ በእውነቱ ኢማሌድህ በመኢሶን ጹሁፍ ውስጥ “ተቃራኒ” ነገሮችን ፈልጎ ፈልጎ አይቷል ብለን አሰብን። ኢማሌድህ “ተቃራኒ” ነገሮችን ለማጋለጥ ሲል የገባበትን ቅራኔ ስናስበውም፣ ልባችን በሳቅ ፈረሰ።
ምክንያቱም የጠቀሳቸውን ጥቅሶች ተመልሶ ቢመለከታቸው ኑሮ፣ አንዳችም “ቅራኔ” ባላገኘባቸው ነበር።
በአጭሩ አንድ የፖለቲካ ግብ፣ በዚህ ጊዜ “ይሟላል” ስለተባለ፣ ለእርሱ “መሟላት” አሁኑኑ እና ዛሬ “ዲሞክራሲያዊ መብቶች” አያስፈልጉም ማለት አይደለም። መኢሶን፣ በብሔረሰቦች ጥያቄ ላይ አሁኑኑ እንዲወሰዱ የሚያቀርባቸው ሐሳቦችም “ስልጣን በሰፊው ሕዝብ እጅ ውስጥ መግባቱን” የሚያግዙ እንጂ “የሚቃረኑ” አይደለሁም። አለበለዚያ ከዚህ በላይ እንዳልነው ፕሮግራምን እንደ ንግርት መውሰድ ያስፈልጋል። መኢሶን በንግርት አያምንም።
ወይንስ ኢማሌድህ ዴሞክራሲያዊ መብቶች አሁኑኑ መለቀቃቸውን የሚቃወመው፣ ስልጣን ወደ ሰፊው ሕዝብ እጅ መግባቱን በመፍራት ይሆን?
ይህ ካልሆነ፣ ኢማሌድህ የጠቀሳቸውን ጉዳዮች “በቀጥታ ተቃራኒ” አድርጎ የሚያቀርባቸው ለምንድነው? ጉዳዩን አጥቶት ይሆን? ወይንስ “ከብት ካልዋለበት ኩበት ለቀማ” ሄዷል?
ስለዚህ ጥያቄ በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ ጭምር “ውይይት” ተካሂዶበት እንደነበረ የሚታወስ ነው። “ውይይቱም” እንዴት እንደተመራና በኋላም እንዴት ታፍኖ እንደተቋረጠ በሁሉም ዘንድ ይታወቃል። እንደዚሁም፣ በዚያን ጊዜ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ የታላኩለት አያሌ ጽሁፎች እስከ ዛሬም ቢሆን የጠረጴዛዎች መሳቢያዎች እንዳሞቁ ናቸው።
የኢማሌድህም ጽሑፍ ይህንኑ በማስታወስ ይመስላል፣ በጽሁፉ ውስጥ “ማርክሲስት ሌኒኒስቶች መቼም” ይላል፡-
“ማርክሲስት ሌኒኒስቶች መቼም በመካከላቸው ያሉትን ልዩነቶች በቅድሚያ የሚፈቱት ወይንም የሚያስወግዱት በውይይት ነው። ስለዚህም ውይይቶችንና ክርክሮችን፣ በየልሳኖቻቸው አማካኝነት በሕጋዊ መድረክም ለማካሄድ ሙከራ አድርገዋል” /19-20/።
እርግጥ ነው። የድርጅቶቹ ልሳኖች፣ የየድርጅቶቹ ነፃ ጋዜጦች በመሆናቸው በእነርሱ ላይ እንደ ሁኔታውና ጊዜው ውይይቱ ዲሞክራሲያዊ በሆኑ መንገዶች ተካሂዷል። በመኢሶንም በኩል ገና የሚቀጥል ምዕራፍ ነው። ይሁንና፣ “በሕጋዊ መድረክ” የሚባለው ግን፣ አነሰ ቢባል ገሃድ ሸፍጥ በማለት እንድንተቸው እንገደዳለን። “የውይይቱ” አመራር፣ በኋላም መታፈንና መቋረጥ፣ በምንም ዓይነት ማስክ ቢሆን ሊሸፈኑ እንደማይችሉ መግለፁ ትርፍ ነገር ይመስለናል። የአደባባይ ሚስጥር፣ አገር ያወቃቸው ጉዳዮች ናቸው።
ብቻ እዚህም ላይ ተመልሰን እንጠይቅና፣ ኢማሌድህ “ልዩነቶች በቅድሚያ የሚፈቱት ወይንም የሚወገዱት በውይይት ነው” ካለ አይቀር፣ በዚህ ፅሁፍ ክፍል ሁለት ውስጥ ያነሳናቸውን ጉዳዮች ሁሉ የደበቀው ለምንድነው? ወይንስ ኢማሌድህ አሁንም አጉል እየተመፃደቀ ራሱን፣ አባሎቹን ሰፊውን ሕዝብ በገሀድ እየደለለና እያታለለ ነው?
ነገር ግን የኢማሌድህ ጽሁፍ በዚህም ብቻ አያበቃም። ቀደም ስንል እንደጠቀስነው፣ እርሱ ራሱ ዳኛ እና ጠበቃ ሆኖ የሚከተለውን ፍርድ ተንብይዋል።
“የዲሞክራሲ መብቶች ለጭቁኖች ያለ ገደብ፣ አሁኑኑ፣ ባስቸኳይ፣ በአፋጣኝ የሚለውን መሠሪና ትጥቅ አስፈቺ መፈክር በርዕዮዓለም ትግል ተሸንፏል። ተጋልጧል። ሰፊው ሕዝብ አልተቀበለውም።” /20/….
ኢማሌድህ በእውነቱ እዚህ ላይ ሲደርስ ጣፊያ ጣፊያውን እየቆጠረ ነው። ኢማሌድህ አተኩሮ ቢመለከት፣ ይልቁኑ ዛሬ በገሃድ የሚታየው ነገር፣ ሰፊው ሕዝብ ስለዚህም ለመናገር ሳይችል ቀርቶ እንደታፈነ መሆኑን በቀላሉ በተረዳው ነበር። የነበሩትም የዲሞክራሲያዊ መብቶች እጅግ አንደጠበቡና በኃይል እንደተገደቡ በተረዳው ነበር። ሕዝባዊና ዲሞክራሲያዊ ድርጅቶች የሕዝባዊነትና የዲሞክራሲያዊነት ባህሪያቸውን እያጡ፣ ወደ መንግሥታዊ ድርጅትነት እየተለወጡ መሄዳቸውን በተገነዘበ ነበር። የመንግሥት የመጨቆኛና የስለላ ድርጅቶች እየሰፉና እየደለቡ መሄዳቸውን በተመለከተ ነበር። ስለዚህም፣ ፍርሃት፣ እርስ በርስ መጠራጠር፣ ራስን ማዳን፣ “እሺ ጌታዬ”፣ ጭፍን ያለው አድርባይነት መረን ለቀው መስፋፋታቸውን በተረዳ ነበር። እንደዚሁም፣ እንደሚባለው “ቤቱን ዘግቶ ደርግን የማያማ” እንደሌለ ባወቀ ነበር። ስለዚህም ደግሞ፣ ወዝአደሩ፣ ወጣቱ፣ መለዮ ለባሹ፣ ሃገር ወዳዱ፣ አርሶ አደሩ፣ ጭቁን ብሔረሰቦች፣ ወዘተ፣ …የዲሞክራሲ መብቶችን አስፈላጊነት ከምንጊዜውም ይልቅ የተረዱት መሄዳቸውን በተገነዘበው ነበር። ……ወዘተ። በመጨረሻም፣ ሰፊው ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ መብቶች የሚያደርገውን ትግል ከሁኔታዎች ጋር አገናዝቦ እንደተያያዘው በተረዳው ነበር።- ትግሉ ይቀጥላል።
8.3 ይህች “ዲሞክራሲ አንድ የመንግሥት ገጽታ ነው” የሚሏት ነገር!
ይህችን የሌኒን ጥቅስ፣ መቼም እንደማሌሪድ የሚወዳት ፍጡር የለም። ይሁንና፣ ይህቺኑ ጥቅስ እንደ ማሌሪድ ያልተረዳት፣ ወይንም ሆን ብሎና አዘውትሮ ዉዥንብር ለመንዛት የሚጠቀምባት ሌላ ፍጡር ደግሞ ተፈልጎም አይገኝም። ለመሆኑ ምን ማለት ናት? ችግሩ ከምን ላይ ነው?
አንደኛው የአብዮታችን ችግር፣ በሀገራችን ውስጥ ማርክሲዝም ሌኒኒዝም ገና በመሰራጨት ላይ መሆኑም ነው። ይህ ሳይንስ ገና መሰረት አለ መርገጡም ነው። ስለዚህም፣ ሰዎች ነገሮችን ሁሉ “ጥንት ጥንት በጋርዮሽ ሥርዓት ዘመን” ከማለት ተነስተው ለመግለጽ ይሞክራሉ። ከዚህም የተነሳ በጣም ቀላል የሆኑና ሼማቲክ አቀራረቦች እጅግ የተለመዱ ሆነዋል። አለበለዚያም አጠቃላይ እውነቶችን በመደርደር /ብዛት፣ ጥራት፣ እመርታ….. / ሊያሰፏቸው ይሞክራሉ። በዚህም ደረጃ፣ የማቴሪያሊዝም ዲያሌክቲክስን ቃላቶችና ፅንሰ ሀሳቦች በመወርወር ብቻ አስማት ለመስራት ይሞክራሉ። ወይንም ጥቅሶችን ቦጭቆ በመውጣትና “እንዳለው…” በማለት፣ ተራሮችን ለመናድ ይሞክራሉ።
ሳይንሱን መሳሪያ አድርጎ ነባራዊ እና ጊዜያዊ ሁኔታዎችን ለመተንተን ግን እስከዚህም ሙከራ፣ እስከዚህም ጥረት አይደረግም። አንድ አጠቃላይ እውነት፣ አንድ የሚስብ ጥቅስ፣ አንድ የሚስብ አባባል፣ ወይንም አንድ የታሪክ “ተመሳሳይነት”…..ወዘተ ከአንድ መጽሐፍ፣ ከአንድ ጋዜጣ፣ከአንዲት ብጫቂ ወረቀት ውስጥ ተፈልጎም ሆነ ባጋጣሚ ከተገኙ፣ እነርሱ ለአዳማጭ አስኪሰለቹ ድረስ ይደጋገማሉ። በእንደዚህ ዓይነትም፣ በአንድ በኩል በ“ጥቅስ” ስም ከአንገብጋቢ ጥያቄዎች ለመሸሽ ሞክራል። ከ“ጥቅሶቹ” በስተጀርባ ይመሸጋል። በሌላው በኩል፣ እንደሚባለው “በጥቅስ ጅራፍ” አከራካሪ ጥያቄዎች ይቀጫሉ። ይዳፈናሉ……
ነገር ግን በዚህ ዓይነት ከቀጠለ ደግሞ፣ ሳይንሳዊ ትንተናን “የጥቅሶች አምልኮ” ይተካዋል። አደገኛ የሆነ ቀኖናዊነት ይስፋፋል። ማርክሲዝም የትግል መሣሪያ መሆኑ ቀርቶ ዶግማ ይሆናል። የሳይንሳዊ ትንተና መሳሪያ መሆኑ ቀርቶ የጥቅሶች መጋዘን ይሆናል። እንደ ሕይወት ዛፍ ለምልም መሆኑ ቀርቶ፣ በእሳት ተለብልቦ እንደተገተረ ግንድ ደረቅ ይሆናል። የቀኝ አድርባዎችና የከላሾች መሳሪያ ይሆናል።…..
እንግዲህ ሌኒን፣ “ዲሞክራሲ አንዱ የመንግሥት ገጽታ ነው” ሲል ምን ማለቱ ነው?
ማሌሪድ ይህችን ጥቅስ የሚወስደው “መንግሥትና አብዮት” ከሚለው የሌኒን መጽሐፍ ውስጥ ነው። እርሱኑ በመጥቀስ እንጀምር። ማሌሪድ “ገጽታ” በማለት የሚተረጉመው ሌኒን “ፎርም” ሲል የገለፀውን ነው።
“ዲሞክራሲ የመንግሥት ፎርም ነው። አንደኛው የመንግሥት ዓይነት ነው። ስለዚህም እሱ /ዲሞክራሲ/፣ እንደማንኛውም መንግሥት ሁሉ፣ ባንድ ወገን፣ የተደራጀውን፣ በሰዎች ላይ የሚፈጸመውን የተቀናበረ ጭቆና ይወክላል። በሌላ በኩል ደግሞ፣ የዜጎች እኩልነት ፎርማሊ መታወቁንና ሁሉም የመንግሥቱን መዋቅርና አስተዳደር በሚመለከተው በኩል ያላቸው የመወሰን መብት መጠበቁን ያመለክታል። በዚህም ዲሞክራሲ እየዳበረ ሄዶ ከአንድ የተወሰነ ደረጃ ላይ ሲደርስ፣ ከካፒታሊዝም ጋር በአብዮታዊ ትግል የተናነቀውን የወዝአደሩን መደብ በከፍተኛ ደረጃ ያስተባብረዋል። ያስተሳስረዋል። የወዝአደሩ መደብ ቡርዥዋዜውን እንዲደመስስ፣ ወደ አቶሞች እንዲፈልጠው የቡርዧዜውን ሬፕብሊክ መንግሥት ማሽን /ቋሚ ሠራዊቱን፣ ፖሊሱን፣ ቢሮክራሲውን/ ከምድር ገጽ እንዲጠፋ ያስችለዋል። እነዚህን፣ የቡርዧዚውን የመንግሥት ማሽን የበለጠ ዴሞክራሲያዊ በሆነ የመንግሥት ማሽን እንዲተካ ያስችለዋል። ይህኛው የመንግሥት ማሽን ግን፣ የታጠቁት ወዛደሮች የሚንከባከቡበት እነርሱም ወደሚሊሺያ የሚደራጁበት፣ ሕዝቡ በሙሉ የሚሳተፍበት ይሆናል።”
“Democracy is a form of the State, one of it’s varieties. Consequently, it, like every state, represents on the one hand the organized, systemic use of violence against persons; but on the other hand, it signifies the formal recognition of equality of citizens, the equal right of all to determine the structure of and to administer the state. This in turn results in the fact that, at the certain stage in the development of democracy, it first welds together the class that wages a revolutionary struggle against capitalism- the proletariat, and enables it to crush, smash to atoms wipe of the face of the earth the bourgeoisie, even the republican bourgeoisie state machine, standing army, the police and the bureaucracy, to substitute for them a more democratic state machine, but a state machine nevertheless in the shape of the armed masses of workers who develop into militia in which the entire population takes part.”
እንደሚታየው የማሌድን “ገጽታ” ሌኒን እንደዚህ ግልጽ በሆኑ ቃላቶች ነው የሚገልጻቸው። ተጨማሪ የማብራሪያ ትችት እንኳ የሚጠይቁ አይደሉም። ይሁንና፣ ማሌሪድ ይህንን የሌኒንን ጥቅስ ያልተረዳውን ያህል፣ ወይንም ባወቅኩኝ ባይነት ሆን ብሎ ውዥንብር የሚነዛውን ያህል፣ ሌኒን ደግሞ ከጠቀስነው ጥቅስ ጥቂት መስመሮች ከፍ ብሎ እንዲህ ይላል።
“ የወዝአደሩ መደብ ከካፒታሊስቶች ጋር ለነፃነቱ በሚያደርገው ትግል፣ ዲሞክራሲ እንደ ሕይወት እስትንፋሱ የሚያስፈልገው መሳሪያ ነው። ነገር ግን ዲሞክራሲ የማይሻገሩት የመጨረሻው ድንበር አይደለም። ከፊውዳሊዝም ወደ ካፒታሊዝም፣ ከካፒታሊዝም ወደ ኮሙኒዝም ካሉት የሽግግር ደረጃዎች ውስጥ አንደኛው ደረጃ ነው”
“Democracy is of enormous importance to the working class and it’s struggle against the capitalist for its emancipation. But democracy is by no means a boundary not to be over-stepped it is only one of the states on the road from feudalism to capitalism and from capitalism to communism”
/ሁለቱም ጥቅሶች የተወሰዱ፣ ሌኒን “መንግሥትና አብዮት”፣ የቻይና እትም፣ 1973 ገጽ 118-119/
ይህኛው የሌኒን ገለፃም እንደዚሁ በጣም ግልጽ ነው። ታዲያ የኛዎቹ “ሌኒኒስቶች” ሌኒንን በ“ሌኒን” ለመዋጋት ቆርጠው የተነሱት ለምን ይሆን? ጠፍቷቸው? ወይንስ የወዛደሩ መደብ የትግል መሳሪያ የሆነውን የዲሞክራሲ መብቶች፣ የወዝአደሩን ፓርቲ ሊነፍጉት ስለፈለጉ?
እኛ፣ በዲሞክራሲ የደረጀውን ወዛደር ስለሚፈሩ ነው እንላለን።
በተጨማሪ ደግሞ፣ የፈለገውን ዓይነት መንግሥት ለመውሳድ እንችላለን። መንግሥቶች ባጠቃላይ መልካቸው እንጅ፣ መንግሥት በመሆናቸው ብቻ፣ “ያው መንግሥት መንግሥት ነው” ብሎ ለማለት አይቻልም። ሁለተኛ በታሪክ የሚታወቁትን የመንግሥት ዓይነቶች /ስቴት ፎርሜሽንስ/ አንድ ዓይነት አይደሉም። የባሪያ አሳዳሪና የባርያ አሳዳሪ፣ የፊውዳልና የፊውዳል፣ የቡርዧና የቡርዧ ….ወዘተ መንግሥት አሉ። “ሶሻሊስት ነን” የሚሉና ሶሻሊስት መንግሥታትም አሉ። ለምሳሌም፣ የዲሞክራሲን ጥያቄ እንውሰድ።
በዲሞክራሲያዊነት ሚዛን፣ ለምሳሌ ሁሉም የቡርዧ ሪፐብሊኮች አንድ ዓይነት “ገጽታ” የላቸውም። እንዲያው ባጭሩ ከሌሴ ፌር /laisser faire/ የቡርዧ ዲሞክራሲ አንስቶ ፋሽስት መንግሥትና አገዛዝ ድረስ ይደርሳሉ። በዚህም፣ የቡርዟ ሪፐብሊኮችን “ዲሞክራሲያዊነት” ከ- እስከ ልንረዳ እንችላለን። ስለዚህም፣ በፋሽስት የቡርዣ መንግሥት ስር የወዝአደሩ የመደራጀት መብት የታፈነውን ያህል፣ በሌሎችም የቡርዟ ሪፐብሊኮች ውስጥ ወዛደሩ የተሻለ የመደራጀት ዕድል አለው። ይህንን እውነት “ገጽታ” በማለት አሌ ለማለት አይቻልም። እንደዚሁም በተጨማሪ፣ በምሳሌ ሌኒን በጊዜው ከነበሩት የቡርዟ ዲሞክራቲክ ሪፑብሊኮች ሁሉ፣ በተለይ የስዊዝን ቡርዟ ዲሞክራሲ ያደንቅ እንደ ነበር የታወቀ ነገር ነው። ምክንያቱም ሌኒን እራሱ ይል እንደነበረው፣ “የቡርዧ ዴሞክራሲና የቡርዧ ዴሞክራሲ አሉና”
“የቡርዧን ዲሞክራሲ በመናፈቅ ነው” የሚል አጉል ዘመቻ እንዲከፈትብን ጥሪ ማድረግ አይሁንብና፣ እኛም የምንለው እንደ ሌኒን ነው። አዎን! የሀገራችን ንዑስ ከበርቴና ወዛደሩ በታሪኩ ውስጥ የቡርዧ ዴሞክራሲን እንኳ ቢቀምስ ኖሮ፣ አብዮታችን የበለጠ መልክ፣ ሥርዓትና ሕይወት ይኖረው ነበር። ይህንን የማይረዱት ቀኖናውያን ብቻ ናቸው።
ሦስተኛ፣ ሌኒን “ዲሞክራሲ አንድ የመንግሥት አንዱ ገጽታ ነው” ሲል፣ በተጨማሪ፣ የአንድን መንግሥት “ገፅታ”፣ ያ የተባለው መንግሥት በሚፈቅደው ዲሞክራሲ መጠን/ በአዋጅ፣ በሕግ፣ በደንብ፣ በተግባር…../ዲሞክራሲያዊነቱን ወይንም ጸረ ዲሞክራሲያዊነቱን ልናነብ እንችላለን ማለት ነው። ወደ ምሳሌያችን እንመለስና፣ ይህ ባይሆን ኖሮ፣ ለምሳሌ የቡርዟው ዲሞክራሲ ዓለም ውስጥ ወግ አጥባቂ፣ ሊብራል /ለዘብተኛ/፣ ሶሻል ዲሞክራሲ….ወዘተ የሚሉትን ልዩነቶች ባልተመለከትን ነበር። አለበለዚያ፣ እንደው በደፈናው “የቡርዧ መንግሥት የቡርዧ፣ የሕዝብ መንግሥት የሕዝባዊ……” እንደሚለው አጠቃላይ ድፍን አነጋገር እንሄዳለን። ይህ ደግሞ “እንቁላል እንቁላል ነው” ከማለት በምንም አይለይም። እዚሁ ላይ፣ እኛም እንደሌኒን “ወዳጄ ቲዎሪ ደረቅ ነው፤ የሕይወት ዛፍ ግን ለምለም ነው” እንላቸዋለን።
እንግዲ ሌኒን ስለ ዲሞክራሲ ጉዳይ የተናገረው ከዚህ በላይ የተመለከትነውን ነው። ይሁንና፣ ማሌሪድ በዚህች የሌኒን ጥቅስ ለማወናበድ የቀኝ አድርባይነቱን ለመሸፈን የሚጥረውን ያህል፣ ተወጥሮ ሲያዝ ደግሞ፣ ተራማጆችን ሁሉ “በግራ” በኩል ይቀድማቸውና፣ የሚከተለውን ይላል:- ደርግ እኮ “ከበርቴ ነው። ወላዋይ ነው። ድንጉጥ ነው። በደርግ ስር ዲሞክራሲ መብቶችን ያለገደብ ለማግኘት አይቻልም። በትግላችን” ይላል። “የለም ዛሬም ቢሆን አያሌ ዲሞክራሲያዊ መብቶችን በሰላም /አዎን! በአዋጅ/ ከጊዜያዊ ወታደራዊ መንግሥት ለማግኘት ይቻላል” የሚሉትን ደግሞ፣ “አድርባይ፣ መሰሪ፣ ትጥቅ አስፈቺ…” እያለ ይከሳቸዋል። ከተራማጆች ሁሉ ተራማጅ ሆኖ ቁጭ ይላል፣ የኢትዮጵያን ሕዝቦች “ባለውም አላወቃችሁበት፣ በትግላችን” ይላቸዋል።
ሀቀኛ ተራማጆች፣ “ዲሞክራሲያዊ መብቶች ከደርግ /= አብዮታዊ ሰደድ/ ለማግኘት ካልተቻለ ቁርጥ ያለ አቋም እንውሰድ” ሲሉ ደግሞ፣ የቀኝ አድርባዮቹ ድርጅቶች ሁሉ በአንድነት ይሆኑና “አብዮታዊያን ሕጋዊ ትግል ለማካሄድ በፍጹም የማይችሉበት ደረጃ ላይ መች ፍጹም ደረስንና ይላሉ። እነዚህ አድርባዮች ግን፣ አድርባዮች ስለሆኑ፣ ሕጋዊ ትግል የሚቻለው አብዮታዊ ሰደድ /=“ደርግ”/ ዲሞክራሲያዊ የሆነውንና ዲሞክራሲያዊ መብቶችን ያወቀውን፣ የጠበቀውን፣ ያከበረውን ያህል እንደሆነ ፍጹም ሊረዱት አልቻሉም። ወይም አልፈለጉም። የደርግን ወላዋይነትና ድንጉጥነት . ..ወዘተ ደግሞ ማሳወቁ ብቻ አንዲት እርምጃ ወደፊት አይወስደንም። ይህ ብዙ ስበላ ቁንጣን ይወጥረኛል። ምንም ሳልበላ ረሃብ ይይዘኛል የሚለውን ተፈጥሮኣዊ እውነት ደጋግሞ የማሳወቅ ያህል ነው።ደርግ የንዑስ ከበርቴው መደብ ክፍል መሆኑን ደጋግሞ መግለፁ ብቻ ዋጋ የለውም። የንዑስ ከበርቴ መደብና የንዑስ ከበርቴ መደብ አሉ። የግራ ንዑስ ከበርቴና የግራ ንዑስ ከበርቴም አሉ።
ይልቁኑ፣ የንዑስ ከበርቴው የደርግ መንግሥት “ግራነት” እስከምን ድረስ ነው?
የንጉስ ከበርቴው የደርግ መንግሥት ዴሞክራሲያዊ “ገጽታ” እስከምን ድረስ ነው?
እነዚህ ጥያቄዎች ሲነሱ፣ ማሌሪድና ሌሎቹ የቀኝ አድርባይ ድርጅቶች “ዕርግጥ ነው” ይላሉ፡-
“ዕርግጥ ነው። በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው አስተዳደር ለሕዝብ ጥያቄዎች የዝሆንን ጆሮ አልሰጠም። እስካሁን ከሕዝብ ጎን ቆሟል። የሪቮሉሽኑን ሂደት አግዟል። ግን፣ በመጨረሻ ትንተና ላይ፣ የሕዝብ አስተዳደር ስላልሆነ፣ አሮጌውም የመንግሥት አውታር ገና ስላልተደመሰሰ፣ በዚህ ሁኔታ የዲሞክራሲ መብቶች ለጭቁኖች ያለገደብ ሊገኙ አይችሉም። በዚህ ሁኔታ የዲሞክራሲ መብቶች ለጭቁኖች ያለገደብ ሊገኙ ቢችሉ ኖሮ፣ ‘ዲሞክራሲ የመንግሥት ገጽታ ነው’ የሚለው የሌኒን አባባል ትክክል ባልሆነም ነበር። ሕዝባዊ መንግሥት ማቋቋም አስፈላጊነቱ አይኖርም ነበር።” /ሬቮ. ቁ.21/
እንግዲህ ተመልከቱት።
ማሌሪድ ይህንን ሁሉ ከተናገረ በኋላ፣ ታዲያ ምን ይሻላል? ሲባል፣ መልሱ “በትግላችን” የሚለው ነው። ለኛም፣ “በመጨረሻ ትንተና” ማን ከማን ጋር እንደሚታገል በመታገል ላይ እንዳለ ግልጽ ሳይሆንልን ይቀራል!! ይህ “እስካሁን ድረስ ከሕዝብ ጎን የቆመው መንግሥት” ምን ዓይነት “ዲሞክራሲያዊ ገጽታ” እንዳለው ለማወቅም ተቸግረናል!!
ነገር ግን ጉዳዩ እስከዚህም አስቸጋሪ አይደለም።
በመጀመሪያ አስተባባሪ ኮሚቴ ነበር። ከዚያም ደርግ ነበር። ከዚያም በኋላ “ደርግ” /=አብዮታዊ ሰደድ/ ሆነ።
በያንዳንዱ ደረጃ ራሱን የቻለ ባህርይ እንደ ነበሩት መግለጹ ትርፍ ነገር ነው። በያንዳንዱ ደረጃ ሀቀኛ ተራማጆችና ሰፊው ሕዝብም የተለያዩ አቋሞችን እንደወሰዱ ማብራራቱ፣ የታወቀውን መድገም ይሆናል። በሀገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ አሰላለፎች ተለውጠዋል። በተለይ በመጨረሻው ደረጃ ላይ፣ በብሔራዊ ፖለቲካ ውስጥ ወሳኝ የሆኑ የውጭ ኃይሎች እንደተቀላቀሉበት የታወቀ ነው።…..ወዘተ.
እንግዲህ፣ የማሌሪድ “የመጨረሻ ትንተና”፣ “መጨረሻው” የሚደርሰው መች ይሆን? አስተባበሪ ኮሚቴ፣ ደርግና “ደርግ” አንድ ናቸው ወይ?
“የሕዝብ አስተዳደር ከሌለ፣ አሮጌው የመንግሥት አውታር ገና ካልተደመሰሰ” ይልቁኑ “በዚህ ሁኔታ የዲሞክራሲ መብቶች ለጭቆች ያለ ገደብ” አሁኑኑ አያስፈልጉም ወይ?
እኛ፣ “ለጭቁኖች ያለ ገደብ አሁኑኑ” በማለት፣ ከዚህ “በመጨረሻ ትንተና የሕዝብ አስተዳደር ካልሆነው” አስተዳደር እንጠይቃለን እንላለን።
ማሌሪድ፣ “ከቶም ሊገኙ አይችሉም” ይላል።
እኛ፣ ይህ እውነት ነው። ይሁንና “የደርግ” መንግሥት እሰከ መደብና እስከ ዲሞክራሲያዊነቱ ገደብ ድረስ ቢያውጀው አዋጁን በደስታ እንቀበለዋለን። በሥራ ላይ እንዲውልም እንታገላለን። “የደርግን” መንግሥት ዲሞክራሲያዊ “ገፅታ” ከማድነቅ ወደ ኋላ አንልም እንላለን።
ማሌሪድ፣ ይህማ ከሆነ፣ “ዲሞክራሲ የመንግሥት ገጽታ ነው የሚለው” የሌኒን አባባል ትክክል ባልሆነ ነበር” ይላል።
እኛ፣ ስለዚህም “ዲሞክራሲያዊ መብቶች ለጭቁኖች ያለገደብ አሁኑኑ” እንዲታወቅ የምናደርገውን ትግል እንቀጥላለን። “በደርግ” መንግሥት በዲሞክራሲያዊ “ገጽታ” ብቻ አንወስንም እንላለን።
ማሌሪድ፣ ይህማ ከሆነ፣ “ሕዝባዊ መንግሥት ማቋቋም አስፈላጊ ባልሆነ ነበር” ይላል።
እኛ፣ “ደርግ” በዲሞክራሲያዊ “ገጽታው” ልክ ገድቦ የሰጠው ዴሞክራሲያዊ መብት፣ የሰፊውን ሕዝብ ትግል ለማስተባበር እና ለማስተሳሰር ይጠቅማል እንላለን። ሕዝባዊ መንግሥት የበለጠውን የተቃረበ ይሆናል እንላለን።
ማሌሪድ፣ “በመጨረሻ ትንተና” ይላል።
እኛ፣ ታዲያስ ምን ይሻላል? እንላለን።
ማሌሪድ፣ “በትግላችን” ይላል።
እኛ፣ ማን ከማን ጋር ነው የሚታገለው? እንላለን።
ማሌሪድ፣ ጣሪያዎችን ካማተረ በኋላ፣ አሁንም መልሶ “በትግላችን” ይላል
እኛ፣ ጥያቄ አቅርበን ነበር እንላለን።
ማሌሪድ፣ “በትግላችን” ብለናል፣ “በትግላችን” ነው ይላል።
እኛ፣ ይህማ የማይቀረው ጉዳይ ነው፤ እንላለን። የመደብ ትግልን ተቀብሎ፣ እንደ ፖለቲካ ድርጅት ተመሥርቶ፣ ካልታገሉማ፣ ወደ ደብረ ጽጌ መውረዱ የተሻለ ነው እንላለን።
ማሌሪድ፣ “አሁኑኑ” የሚለውን ትጥቅ አስፈቺ ነው ይላል።
እኛ፣ “በመጨረሻ ትንተና” የማሌሪድ አቋም፣ የማሌሪድ ዲሞክራሲያዊ “ገጽታ” ነው እንላለን።
ስለ ዲሞክራሲ መብቶች ሲነገር፣ ከማሌድህ አባል ድርጅቶች፣ በተለይ ከማሌሪድ፣ ተደጋግሞ የሚሰማው አንድ ነገር፣ ዲሞክራሲ ከመንግሥት ስልጣን ተነጥሎ አይታይም የሚለው “ቲኦሪ” ነው። “ስለዚህም” ይላሉ እነዚህ ክፍሎች፣መኢሶን “ዴሞክራሲያዊ መብቶች አሁኑኑ” ሲል፣ “የመንግሥትን ስልጣን በአቋራጭ
መጨበቅ ፈልጎ ነው። መኢሶን የስልጣን ጥም አለበት…..”።
ይህ አባባል፣ አነሰ ብንል የዋህ ነው። በዕውነቱ ከሆነም፣ የቀኝ አድርባዮቹ በመኢሶን ላይ የሚሰነዝሩት ይህ ክስ ከተናጋሪዎቹ አፍንጫ እርቆ የሚሄድ አይደለም። ምክንያቱም የሚከተሉት ናቸው።
አንደኛ፣ እንኳን የዲሞክራሲያዊ መብቶችን የሚያክል ጥያቄ ይቅርና፣ ትንሿ የፖለቲካ ጥያቄ እንኳ ከመንግሥት ስልጣን ጥያቄ ጋር የተያያዘች ናት። ስለዚህም፣ ይህንን መደጋገሙ ለጉዳዩ አንዳችም አዲስ ነገር አይጨምርለትም።
ሁለተኛ፣ የፖለቲካ ድርጅት ነኝ ብሎ ተደራጅቶና የፖለቲካ ትግል እያካሄዱ እያሉ፣ የፖለቲካ ስልጣንን አልፈልግም ማለት አጉል መመጻደቅ ነው። ማንኛውም የፖለቲካ ድርጅት የሚቋቋመውና የሚታገለው የፖለቲካ ስልጣንን ለመጨበጥ ነው። አንድ የፖለቲካ ድርጅት ይህ ዓላማ እስከሌለው ድረስ፣ ወደ ዕድር፣ ወይንም ወደ ሰንበቴ፣ ያለዚያ የአቦ ገብርኤል ጠበል ፃድቅ ወደሚቀምስበት ማሕበር ቢለወጥ ይሻለዋል።
ሦስተኛ፣ የፖለቲካ ስልጣን ይዞ፣ የመንግሥትን ስልጣን አልፈልግም ማለትም፣ አነሰ ቢባል፣ መንግሥትን ከመደቦች ትግል ውጭ እንዳለ ድርጅት አድርጐ መቁጠር ነው። ተዋዋዮቹንም፣ ወደ ፃድቃንና ቅዱሳን ዓለም ማሻገር ነው። በዚህ ዓይነት፣ ሕዝቦችም “የተባረኩ አማኞች” ሊሆኑ ነው። ነገር ግን ለክፋቱ የመደቦች ትግል የሚሉት አለ። መንግሥትም ከመደቦች ትግል ውጭ አይደለም። እንደውም፣ የማርክሲዝም ሀ ሁ መድገም አይሁንብንና፣ በከፍተኛ ደረጃ የተደራጀውና የገዢ መደብ ወይንም ክፍል ጠንካራ መሳርያ ነው። ተዋናዮቹም ቢሆኑ፣ ከመደቦች ትግል ውጭ “አይፀድቁም”።
አራተኛ፣ መኢሶን “ዴሞክራሲያዊ መብቶች ለጭቁኖች ያለ ገደብ አሁኑኑ” የሚለውን መፈክር ከነባራዊ ሁኔታዎች ጋር አገናዝቦና አያይዞ እንጂ፣ እንዲሁ በሜዳ ላይ አይደለም። “አሁኑኑ ማለት ምን ማለት እንደሆነም፣ ከትግል ስልት ለውጥ በፊትና በኋላ / ከዚህም ጽሁፍ ውስጥ ጭምር/ ተገልጿል። ከእነዚህ ውጭ የትርጉም ትርጉሞችን መስጠት ግን “ከብት ካልዋለበት ኩበት ለቀማ መሄድ” ይሆናል። ነው።
አምስተኛ፣ ከየካቲት 1966 ዓ.ም. አንስቶ፣ በኢትዮጵያ አብዮት ውስጥ የመንግሥት ስልጣን ጥያቄ በከፍተኛ ደረጃ ሲያከራክር የቆየ ነው። እንደሚታወሰው 1966 ዓ.ም የእንዳልካቸው መኮንን መንግሥት ነበር። በዚህ ዓ.ም “አስተባባሪ ኮሚቴ” ነበር። በ1967/68 ዓ.ም ባንድ በኩል ደርግ ነበር። በሌላው በኩል የኢህአፓ “ጊዜያዊ ሕዝባዊ መንግሥት” ጥያቄ ነበር። ከሁሉም በተለየ ደግሞ ሀቀኛ ተራማጆች የቆሙለት “የነቃ፣ የተራጀና የታጠቀ የሕዝብ ትግል” የሚለው መስመር ነበር። አለ። ከ1969 አጋማሽ አንስቶ ደግሞ፣ የ“ደርግ”/=አብዮታዊ ሰደድ/ መንግስት አለ። እንደዚሁም፣ ደርግ የገባው “ቃል ኪዳንና” የብሔራዊ ዲሞክራሲያዊ አብዮት ፕሮግራም አሉ።
ስድስተኛና በመጨረሻም፣ መኢሶን ለምን የፖለቲካ ስልጣን እንደሚታገል፣ ከፕሮግራሙ በይፋ መውጣት በፊት ሆነ፣ በፕሮግራሙ ውስጥ ወይንም ከዚያ በኋላ ባወጣቸው ጽሁፎች ደጋግሞ ግልጽ አድርጓል። የኢማሌድህ ፅሁፍ ደራሲዎች፣ በጽሁፋቸው ውስጥ ደጋግመው የጠቀሱትን ስህድ 60 ጠንቅቀው ቢያነቡት ኑሮ እንኳ፣ በዚያው ቁጥር ውስጥ ከዚህ በታች የምንጠቅሰውን ባጤኑት ነበር።
ስህድ 60/ ሐምሌ 1969
“የመንግሥትን ስልጣን በሚመለከተው በኩል፣ መኢሶን ቀድሞም ዛሬም በዚያው አቋሙ ፀንቷል። የመንግሥትን ስልጣን መያዝ ያለበትና የሚችል አንድ ድርጅት ወይም ቡድን ሳይሆን፣ የነቃ፣ የተደራጀና የታጠቀ ሰፊ ሕዝብ ነው። የነቃ፣ የተደራጀ የታጠቀ ሰፊ ሕዝብ ማለት ደግሞ በማርክሲዝም ሌኒኒዝም የሚመራ /እውነተኛ/ የወዛደር ፓርቲና በዚህ ፓርቲ አመራር ስር የቆሙ ሕዝባዊ አብዮታዊ ግንባርና ሕዝባዊ አብዮታዊ ጦር ያሉት ማለት ነው። እነዚህ ሦስት መሳሪያዎች እስከሌሉት ድረስ የኢትዮጵያ ሕዝብ ፊውዳሊዝምን፣ ኢምፔሪያሊዝምንና ቢሮክራሲያዊ ካፒታሊዝምን ሊደመሰስ አይችልም። እነዚህን ሦስት ጠላቶች ካልደመሰሰ ደግሞ የመንግሥትን ስልጣን ለመያዝ፣ መደላደልና አዲስ ህብረተሰብን ለመገንባት ፈጽሞ አይችልም። ድርጅታችን ለዚህ ዓይነቱ የሕዝብ ስልጣን እንደሚታገልና፣ ይህም ትግል ደግሞ የረጅም ጊዜ መራራ ትግል እንደሚሆን ዛሬ ሳይሆን፣ ገና በጨለማው ኃይለሥላሴ ዘመን አምኖበት ሰፊውን ሕዝብ ሲቀሰቅስ የኖረበት የፖለቲካ መስመር ነው። ይሁንና የቀኝም ሆኑ “የግራ” ተቃዋሚዎች ይህንን የድርጅታችንን አቋም እያጣመሙ፣ ነጩን ጥቁር፣ ጥቁሩን ነጭ እያሉ፣ ለማንም ሃቀኛ ገልጽ የሆነውን ነገር በአሉባልታ እየሸፋፈኑ ‘መኢሶን ባቋራጭ ስልጣን ሊይዝ ይፈልጋል’። በማለት በኛና በሌሎች ተራማጅ ድርጅቶች መካከል ጥርጣሬን ለመፍጠር ሲፍጨረጨሩ ቆይተዋል። እየተጨረጨሩም ናቸው።”
እነዚህ ቃላቶች የተጻፉት ገና ከትግል ስልት ለውጥ በፊት ነው። ዛሬም ቢሆን በዚህ ላይ የምንጨምርበት ሌላ ምንም ነገር የለንም። በተጨማሪ፣ የኢማሌድህ አባል ድርጅቶች፣ በእጃቸው ውስጥ የሚገኘውን የህብረት ስብሰባዎች ቃለ ጉባዔ ሊመለከቱት ይችላሉ። በዚህ ለታሪክ የቀረው ቃለ ጉባኤ ውስጥ፣ “መሃላውና ግዝቱ” ሰፍሮ ይገኛል። እኛም በቅጅ ይዘነዋል። ከዚህ በተረፈ መኢሶን የፖለቲካ አላማና ግብ ያለው የፖለቲካ ድርጅት ነው። እንደ ፖለቲካ ድርጅት ተመሰረተው “እድሜያችን እንዲያጥር እንፈልጋለን” /ወዝ ሊግ/ የሚሉትን ክፍሎችንም እንደጻድቃን አንቆጥራቸውም።
የኢማሌድህ ጽሑፍ፣ የመጨረሻ መጨረሻ እንደማፌዝም እንደማንጓጠጥም ብሎ፣ የሚያቀርበው “ትችት” የመኢሶንን “አብዮታዊ ሂስ” መስመር የሚመለከት ነው ስለዚህም ሲጽፍ እንደዚህ ይላል።
“ወገኛውን መኢሶን! አጉል ሲውጠረጠርና ሲደነፋ በጣም ያስቃል። ህቡዕ ገብቶ አብዮታዊ ሂስ እንዴት ይሰራል? አብዮታዊ እንቅስቃሴን ለሚገታ ኃይል፣ ቢሮክራዊው ላይ እምነት ላለው ደርግ፣ ምን አብዮታዊ ሂስ ያስፈልገዋል? ዶሮን ሲያታልሏት…..ይባል የለ!!” /26-27/
በእውነቱ ይህንን “ትችት” ዝም ብሎ ማለፍ የተሻለ በሆነ ነበር። ርካሽ ነው። ስሜትን ለመቀስቀስ፣ ሸውዶ ለማምለጥ፣ ባዶ አነጋገሮችን አስጨብጦ ለማለፍ የተፃፈ “ዝባዝንኬ” እንጅ ምንም የሚናገረው ነገር የለውም። ይሁንና፣ ጥያቄዎች ተወርውረዋልና በአጭሩ እንድንመለስባቸው እንገደዳለን።
ለመጀመሪያው፣ የመደብ ትግል ቁማር አይደለም። “አሌሆይ፤ አላሌሆይ” እንደሚባለውም ጨዋታ አይደለም። የትኛውም መደብ ቢሆን፣ ሌላውን መደብ ሊያታልለው አይችልም። እንደዚሁም፣ አንድን የመደብ ድርጅት /መንግሥትንም ጭምር ማለት ነው/ ለማታለል አይቻልም። መኢሶንም “ዶሮውን” የደርግ መንግሥት “ለማታለል” መጫኛ የሚጎትትበት ምክንያት የለውም። ደርግ “ዶሮ” አይደለም። መኢሶንም “መጫኛ ነካሽ” አይደለም። “ደርግ” መንግሥት ነው። መኢሶንም የፖለቲካ ድርጅት ነው።
ሁለተኛ፣ ስለ “አብዮታዊ ሂስ” ምንነት መናገር ከፈለጉ፣ ስለ እርሱ መናገር እንጂ፣ እብሪትና ትምክህት የተመላባቸው አነጋገሮች ለመለደፍ ለመማርም ሆነ ለማስተማር የሚጠቅም አይደለም አብዮታዊም አያሰኝም። ኢማሌድህ ይህንን መረዳትና ከርካሽ አባባሎች በላይ ለመሆን መጣር ነበረበት።
ሦስተኛ፣ ኢማሌድህ፣ መኢሶን ከትግል ስልት ለውጥ በኋላ የወስዳቸውን የፖለቲካ አቋሞች፣ ያቀረባቸውን ሐሳቦች፣ ጥሪዎችና ጥያቄዎች ሁሉ በአንክሮ ቢመለከታቸው ኑሮ፣ “አብዮታዊ ሂስ” ሁነው ያገኛቸው ነበር። የአብዮታዊ ሂስን ትርጉም ጨርሶ አልተረዳም።
አራተኛ፣ ተጨማሪ ምሳሌ ከፈለገ፣ ይህ ጽሁፍ በራሱ እንኳ “አብዮታዊ ሂስ” ነው።
አምስተኛ፣ “አብዮታዊ ሂስ” እንደሚታወቀው፣ አብዮታዊና ዲሞክራሲያዊ እርምጃዎችን ሁሉ መደገፍ፤ ፀረ አብዮታዊና ፀረ ሕዝብ፣ ፀረ ዴሞክራሲያዊ እርምጃዎችን ሁሉ፣ ከሁኔታዎች ጋር አገናዝቦና አመዛዝኖ ይቅርታ በሌለው ሂስ መቋቋም ማለት ነው። ስለዚህም ነው፣ መኢሶን ከትግል ስልት ለውጡ በኋላም ቢሆን አብዮታዊና ዲሞክራሲያዊ እርምጃዎችን ሁሉ ባለው አቅምና ባሉት መንገዶች ሁሉ የደገፈው። ባንፃሩ፣ ፀረ አብዮታዊና ፀረ ሕዝብ፣ ፀረ ዲሞክራሲያዊ እርምጃዎችን ሁሉ ባለው አቅሙና ባሉት መንገዶች ሁሉ በመታገል ላይ ያለው።
ስድስተኛ፣ ይሁንና፣ በተጨማሪ ደግሞ፣ ዛሬ መዓት ሂስና ተቃውሞ የሚቀርብባቸው አያሌ አሳሳቢ ጉዳዮች እያሉ፣ መኢሶን በእነርሱ ላይ አስተያየቱን በይፋ ከመስጠት ተቆጥቧልም። ይህንንም መስመር የተከተለው ዛሬም “የአብዮታዊ ሂስ” አቋም ስላለው እንጅ፣ በሌላ በምንም ምክንያት አይደለም። መኢሶን ነገሮችን ሳያመዛዝን ላንቃውን እንደማይሰነጥቅ የታወቀ ጉዳይ ነው።
በመጨረሻም፣ የኤማሌድህ አባል ድርጅቶች አልተረዱትም እንጂ፣ የአብዮታዊ ሂስ ከ-እስከ የሚስተያየው ከደርግ ጋር ሳይሆን፣ ከኢትዮጵያ ሕዝቦች ንቃት፣ ድርጅትና ትጥቅ ጋር ነው። ማለትም፣ ከኢትዮጵያ ሕዝቦች ህሊናዊ ሁኔታና ሀገሪቱ ከምትገኝበት ነባራዊ ሁኔታ ጋር ነው። በዚህ ውስጥ፣ ደርግ ምንም እንኳ የማይታለፈው አንደኛው ክፍል ቢሆንም፣ ለአብዮታዊ ሂስ አቋም ወሳኙ ክፍል አይደለም። ይህንንም ታሪክ ገና ያሳየናል።
እንግዲህ በእውነቱ፣ መኢሶን ለምን ኩዴታ ሲጠነሰስ አልተገኘም? የሚል ቅሬታ ከሌለ በስተቀር፣ የመኢሶን መስመር ዛሬም ቢሆን “አብዮታዊ ሂስ” ነው። ምክንያቱም፣ መኢሶን የኢትዮጵያ ሕዝቦች የሚገኙበትን ነባራዊ እና ህሊናዊ /በተለይም ህሊናዊ/ ሁኔታ በቅጡ ያውቀዋል። እዚህ ውስጥ፣ “የዶሮና የመጫኛ” ጨዋታ የለበትም። የመደቦች አሠላለፍ፣ የኃይለ ሚዛን፣ የአብዮታችን መግፋት አለመግፋት፣ የአመቺ ሕሊናዊ ሁኔታዎች መኖር አለመኖር ጥያቄ ነው ያለው።
እንግዲህ ከዚህ ሁሉ በኋላ፣ የኢማሌድህ አባል ድርጅቶችና በውስጡ የሚገኙት አንዳንድ ግለሰቦች፣ አሁንም የነገሮችን ምንነት ሳይረዱ በመቅረታቸው፣ “ታዲያ ይህ ከሆነ፣ የትግል ስልት ለውጥ ለምን አስፈለገ? “የሚል ጥያቄ ያነሱ ይሆናል።
እኛም ጥሩ ጥያቄ ነው። እንደዚህም ከሆነ፣ ይህ ጽሁፋቻችን በ“ህብረት ደምፅ” ጋዜጣ ላይ ታትሞ እንዲወጣ፣ እንዲሠራጭ እና ሰፊው ሕዝብ አገናዝቦ በዲሞክራሲያዊ መንገዶች እንዲወያይበት ይደረግ እንላለን።
የኢማሌድህ ውሳኔ የደረሰን፣ ቀደም ሲል እንዳመለከትነው፣ ለውይይት እንዲያመች በማለት የሰህድ 66 እትም በሚዘጋጅበት ወቅት ነበር። በኛ ግምት፣ ይህ ቀደም ሲል የተጻፈው ጽሁፍ የዚህኛው ጽሑፍ መጠቃለያ ሆኖ ለመቅረብ ይችላል። ስለዚሀም፣ በቅድሚያ የተነበበውን ያህል የዚህ ፅሁፍ ማጠቃለያ ሆኖ ሊወሰድ ይችላል። ቀደም ተከተሉ በዚህ ምክንያት አይዛባም።
አንባቢዎችን ልናስታውስ የምንፈልገው ነገር ቢኖር፣ ሰህድ 66 ለውይይት መነሻ እንዲሆን ለኢማሌድህ የተጻፈ ወረቀት እንደነበር ነው። የኢማሌድህ መልስ በገቢር የምናየው እንደሆነ፣ በተጨማሪ ማውሳቱ የአደባባዩን ሚስጥር መድገም ብቻ ይሆናል። በኢትዮጵያ ሕዝቦችና በታሪክ ፊት ተጠያቂ የሆኑትን ክፍሎች ታሪክ እየመሰከረች ናት።
በዚህ ጽሁፍ ውስጥ፣ “የመኢሶንን ከኢማሌድህ አባልነት መሰረዝ” ምክንያት በማድረግ፣ “የህብረት ድምጽ” የተሰኘው ጋዜጣ የደረሰውን ጹሁፍ በሃቅና በግልጽ ለመተቸት ሞክረናል። አስተሳሰቦችና አቋሞች በመልክ በመልካቸው ለማቅረብ ጥረት አድርገናል። በአንጻሩ የኢማሌድህ ጽሁፍ ባነሳቸው ፍሬ ነገሮች ላይ ሁሉ፣ ሁኔታዎችን ለማስታወስ እና ለመግለጽ ሞክረናል።
እንደ እውነቱ ከሆነ፣ ይህንን ጽሑፋችንን እዚህ ላይ መደምደሙ በቂ ነው ብለን እናምናለን። አያሌ ሊነገሩ የሚገባቸውን ጉዳዮች እንዳልተናገርን ይታወቀናል። አንዳንዶቹን የተውነው በአሁኑ ወቅት ልናነሳቸው ስላልፈለግን ነው። ከጥቅማቸው ይልቅ ጉዳታቸው ያመዘናል ብለን ስለገመትን ነው። ሌሎቹን ደግሞ ጽሁፉን ያለቅጥ ያራዝሙታል በማለት ትተናቸዋል። እንደዚሁም፣ ስለ መኢሶን በተናገሩት አንዳንድ ትርፍ አባባሎች ላይ ልንተች አልፈልግንም። በአደባባይ የሚነገሩት የውሸትና የዲማጎዢ ገለፃዎችም ላይ ልንመለስባቸው አልፈለግንም። እነዚህን የተውነው፣ ከፍሬ ነገሮች ይርቃሉ ብለን በማሰብ ነው።
ይሁንና የማይሳቱ እውነት ነገሮች ደግሞ አሉ።
ኢማሌድህ መኢሶንን የሚከራከረው የመኢሶንን አቋም በመተቸት አይደለም። ኢማሌድህ መኢሶንን የሚከራከረው የኢድህና የኢህአፓን /በተለይም የኢህአፓን/ አቋሞች በመኢሶን ላይ በመለጠፍ ነው። ይህም፣ የኢማሌድህን ክስረት የሚያሳየን ጉዳይ ነው።
ሁለተኛ፣ ኢማሌድል መኢሶንን “ፈርጣጭ”፣ “ቀኝ መንገደኛ” ፣“በራዥ” ….ወዘተ. እያለ “ለማጋለጥ” ከፍተኛ ጥረቶችን አድርጓል። ይሁንና፣ በአንደኛውም ጥያቄ ላይ ቢሆን፣ ይህ ነው የሚባል የክርክር ነጥብ እንኳ ሊያቀርብ አልቻለም። ይህም እንደዚሁ፣ የኢማሌድህን ክስረት የሚያሳየን ጉዳይ ነው።
ሦስተኛ፣ የዲሞክራሲ መብቶች “በደርግ” /= አብዮታዊ ሰደድ/ ዘመን ከምንጊዜውም ይበልጥ በአሁኑ ወቅት ታፍነዋል። የቀኝ አድርባይነት ከምንጊዜውም ይበልጥ ተስፋፍቷል። በኢትዮጵያችን ውስጥ፣ በአብዮታችንና በሶሻሊዝም ስም አስጊና አደገኛ ሁኔታ እየተፈጠረ ነው። የኢትዮጵያ ሕዝቦች አንድነትና ብሄራዊ ነፃነታችን አሳሳቢ ከሆነ አደገኛ ሁኔታ ውስጥ ወድቋል።
በዚህ እና በሌሎችም ፅሁፎች ውስጥ ደጋግመን እንደገለጽነው፣ የመኢሶን ምኞት፡-
- አብዮታዊና ዴሞክራሲያዊ የሆነ ሀቀኛ የተራማጆች ህብረት እንዲመሠረት ነው።
- በእንደዚህ ዓይነቱ የጠነከረ ህብረት ላይ እውነተኛ የወዛደሩ ፓርቲ እንዲራጅና እንዲመሠረት ነው።
- በእንደዚህ ዓይነቱ ፓርቲ አመራር ስር፣ ሕዝባዊ አብዮታዊ ግንባርና ሕዝባዊ አብዮታዊ ጦር እንዲመሠረቱ ነው።
- መንግስታዊ ስልጣን ወደ ሰፊው ሕዝብ እጅ እንዲገባ ነው።
- አብዮታዊና ዲሞክራሲያዊ የሆነች፤ ኩሩና ነፃነቷን የተከበረን፤ እኩልነት፣ ዴሞክራሲ፣ ሰላም፣ ፍትህና ብልጽግና የሰፈነባትን፤ የሕዝቦቿ አንድነትና እኩልነት የተጠበቀባትን ሕዝባዊና ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ ለማየት ነው።