የሰፊው ሕዝብ ድምፅ
ቁጥር 70፣ መስከረም 20፣ 1972
የፅሁፉ ፍሬ ሀሳብ
መኢሶን በዚህ እትም፣ ኢማሊድህ የፖለቲካ ክስረት ውስጥ የገባውና የፈረሰው የህብረቱ አባል ድርጅቶች ያወጡትን የጋራ መግለጫ፣ መርሃ ግብርና የብሄራዊ ዴሞክራሲያዊ አብዮትን ፕሮግራም መሻር የጀመረ ጊዜ እንደሆን ያብራራል። ከዚህም አያይዞ፣ በተለይም የቀኝ አድርባዮች ለአብዮቱ ህልውና እጅግ አስፈላጊ የሆነውን የዴሞክራሲ መብቶችን ጉዳይ እያፈኑና ሕዝባዊ ድርጅቶችን እያፈራረሱ በሚገኙበት ወቅት የአገር ወዳዶች ተግባር ምን መሆን እንዳለበት ይዘረዝራል።
መግቢያ
“ኢማሌድህ ከህብረት ወደ ውህደት….ኢማሌድህ የወዛደሩ ፓርቲ ብቸኛ ጥንሰስ ነው….ኢማሌድህ በዚህ ይውረድ…. ኢማሌድህ በዚያ ይውጣ …..” ሲባልልን ተከረመና አሁን ደግሞ የተባለው፣ የተፃፈውን የተለፈፈውንና የተፈከረውን ሁሉ እንዳልነበረ ረስቶ ምድረ አደርባይና አድሃሪ ሁሉ “በውህደት ፓርቲ መመስረት እንደማይቻል ተደርሶበታል….ለወዛደሩ ፓርቲ ሌላ ጥንስስ መኖሩ ተረጋግጧል….ኢማሌድህ የአድሃሪያን መታጎሪያ ሆኖ ፈርሷል…..” “በኮሚኒስቶች፣ በኮሚኒስቶች አንድነት…. ማዕከል…..” እያለ ያዙኝ ልቀቁኝ በማለት ላይ ይገኛል።
ድሮስ ቢሆን? ባለፈው ቁጥራችን የፖለቲካ ክስረት ዞሮ ዞሮ ድርጅታዊ ክስረትን እንደሚያስከትል የፃፍነውን ልብ ያለ ሰው የከሰረው ኢማሌድህ በዚህ መልኩ ወደ ታሪክ ትቢያ መጣያ መውረድ ሊያስገርመው አይችልም። የቀኝ ኃይሎች ዛሬ የፀረ አብዮት የማየል ደረጃ አመቻችቷቸው “ኢማሌድህ ፈርሷል” ብለው አፍ አውጥተው ለማወጅ በቁ እንጂ ኢማሌድህ የሚባለው ነገር ካለቀለት፣ ውርደትም ተከናንቦ ወደ ታሪክ ትቢያ መጣያ ከወረደ ሰንበት ያለ ጉዳይ ነው። ኢማሌድህ ያለቀለት ዛሬ አይደለም። ኢማሌድህ ያበቃለት ራሱ የተመሰረተበትን የኢትዮጵያ ማርክሲስት ሌኒኒስት ድርጅቶች ህብረት የጋራ መግለጫንና መርሀግብር ረግጦ፣ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ዲሞክራሲያዊ አብዮት ፕሮግራም አንቀጽ በአንቀፅ ሽሮ የፀረ አብዮትንና የብሔራዊ ውርደትን ቁልቁለት ተያይዞ መንጎድ የጀመረ እለት ነው።
ኢማሌድህ ይዞት በነበረው የክስረት ጎዳና ቀጥሎ ወደ ውህደት ተሸጋገርኩ ብሎ የወዛደር ፓርቲ ተመሰረተ ቢባል ኖሮ እንኳን የኢትዮጵያ አብዮታውያን አቋም ግልጽ ነበር። ይህንን ከከሰረ “ህብረት” የፈለቀ ከሳራ “የወዛደር ፓርቲ” በምንም ዓይነት እንደማይቀበሉት ደጋግመው ያስታወቁት ጉዳይ ነበር። በዛው በከሳራና በፀረ ወዛደር መስመር ላይ ተመረኩዞ፣ በዛው በአቋራጭ የፓርቲ መመስረት ዘዴ የሚቋቋመውን የዚያድ ባሬው የወዛደር ፓርቲ የኢትዮጵያ አብዮታዊያን አይቀበሉትም።
የኢትዮጵያ ሰፊ ሕዝብ በጊዜው ደሙን እየገበረ የመሰረታቸውን የአብዮት አለኝታ የሆኑ ድርጅቶችን በጸረ ዲሞክራሲ ሰንሰለት እጅ ተወርች እያሰሩ፣ በተራ ሹምሽር ምንሸርሽራቸውን እያወጡ፣ ታጋይ ዲሞክራቶችንና ሃገር ወዳዶችን እየረሸኑ፣ እያስረሸኑና በየእስር ቤቱ እያጎሩ፣ በጠቅላላው በአብዮቱ ላይ እንደዛሬው በይፋ ከመነሳታቸው በፊት ብዙ ለማድበስበስ ሞክረዋል። የመላ ኢትዮጵያ ሶሻሊስት ንቅናቄ የዚህን ፀረ አብዮት ሂደት ጥንስስ ተመልክቶ ይህንን ለማጋለጥ ሲነሳና የቀኝ አደርባዮች ለአድሃሪው ቢሮክራሲ ፊታውራሪ በመሆን መኢሶንን ማጥቃት ሲጀምሩ ለመካድ የሞከሩት ይህንኑ ነበር። ለማሳመን የፈለጉት በተራማጆች ሰፈር ምንም ልዩነት እንደሌለና አንዳንድ ችግሮች ቢኖሩ መሰረታቸውን የሚያሳየው “የቡድን ስሜት” “የስልጣን ጥም” እንደሆነ ለማሳየት መውደቅ መነሳት ይዘው ነበር።
ነገር ግን መኢሶን ለዴሞክራሲ ሲቆምና ዲሞክራሲያዊ መብቶች ለአብዮታችን ሂደት እንደ ሕይወት እስትንፋስ ያስፈልገዋል ሲል፣ የቀኝ አድርባዮች ደግሞ በይፋ ሽንጣቸውን ገትረው ለፀረ ዲሞክራሲ ሲሟገቱ፣ መኢሶን ለብሄረሰቦች እኩልነትና አንድነት ሲዋደቅ፣ የቀኝ አድርባዮች ደግሞ ከትምክህተኞች ጋር ቆመው ሲያራግቡ፣ መኢሶን ሀገራችን የማንም ኃያል መንግሥት ተቀጥላ አንዳትሆን ሲታገልና ብሔራዊ ነፃነቷ መደፈሩን ሲቃወም፣ የቀኝ አድርባዮች ፊታውራሪዎች ደግሞ በሀገራችን የባዕድን ቅምጥ መንግሥት ለማቋቋም ሲያጎበድዱ፣ መኢሶን ለሃቀኛ የወዛደር ፓርቲና ለሀቀኛ ሕዝባዊ ዲሞክራሲያዊ መንግሥት ሲታገል፣ አድርባዮች በወዛደሩ ጀርባ ራሳቸውን “የወዛደር ፓርቲ” ብለው ሰይመው በአቋራጭ ለስልጣን ሲቋምጡ፣ መኢሶን ሕዝባዊ ድርጅቶች ያብቡ እያለ ከአድሃሪ ቢሮክራሲ ጋር ሲጋፈጥ፣ የቀኝ አድርባዮች በስንት ታጋይ ደም የተገነቡትን ሕዝባዊ ድርጅቶች በተራ ሹምሽር ምንሽርሽራቸውን ሲያወጧቸው፣ እጅ ተወርች እያሰሩ ለአድሃሪው ቢሮክራሲ ሲያስረክቧቸው፣ … በቀኝ አደርባዮችና በመኢሶን ግንባር ቀደምነት በሚንቀሳቀሰው የአብዮት ሰፈር መሃከል ያሉት ልዩነቶች በጸረ አብዮትና በአብዮት ማሀከል ያሉት ልዩነቶች መሆናቸው ይፋ እየሆነ ሄደ።
የቀኝ አድርባዮች የመኢሶንን “የቡድን ስሜት” ፌዝ ለመተውና ልዩነቶችን ለማመን ስለተገደዱ ብዙም ሳይቆዩ በድርጅታችን፣ በዲሞክራቶችና በሃገር ወዳድ ኢትዮጵያዊያን ላይ ለአድሃሪው ሰፈር ፊታውራሪ ሆነው በአመጽ ተሰማሩ። ምንም እንኳን መኢሶንንና ሌሎች ሀቀኛ አብዮታዊያን “ፈርጣጭ” “ተንሸራተች” እያሉ ለማወናበድ ቢሞክሩም ከአብዮቱ ሰፈር የፈረጠጠውና የተንሸራተተው ማን እንደሆነ ለመለየት ለሰፊው የኢትዮጵያ ሕዝብ ምንም ጊዜ አልወሰደበትም። ስለሆነም ከሚያየውና ከሚሰማው በየዕለትም ከሚኖረው ሀቅ ተነስቶ በቀኝ አድርባዮች ፊታውራሪነት የሚካሄደውን አመፅ ተቋቋመ።
ከዚህም ወቅት አንስቶ የኢትዮጵያ አብዮት ሂደት ፍጥነት አስመሳዩን እያንጓለለ እና እያጋለጠ እርቃኑን እያስቀረው በመምጣቱ ዛሬ ወለል ብሎ በመጣው የቀኝ አድርባዮች ክህደት ያልቆረጠለት ኢትዮጵያዊ አይገኝም ብንል ስህተት አይሆንም። በዚህ በኩል ባለፈው ቁጥራችን በኢትዮጵያ ምድር ስላለው ከፍተኛ የፖለቲካ ጥራት፣ የመኢሶንን የፖለቲካ መስመር ትክክለኛነት ከዕለት ዕለት እየተረጋገጠ ስለመሄዱ ፅፈን ነበር። ካለፈው ቁጥራችን ወዲህ ይህ ጥራት ሌላ ተጨማሪ “እምርታ” አግኝቷል። ይኸውም የወዛደሮች ጥንስስ እየተባለ ይለፈፍለትና ይደነፋለት የነበረው ከሳራው ኢማሌድህ በቀኝ ኃይሎች ትዕዛዝ፣ በቀኝ አድርባይ “ድርጅቶች” አጎብዳጅነት በይፋ እንዲፈርስ መደረጉ ነው። በዚህ “ሂደት” በውስጡ አሉ እየተባሉ ይወሸከትላቸው የነበሩት ከሳራ “ድርጅቶችም” ያው በመንግሥት ትዕዛዝ ፈርሰዋል!
የኢማሌድህ ልሳን “የህብረት ድምፅ” ቁጥር 5 በየካቲት ወር 1971 ዓ.ም በወጣው ቁጥሩ በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ የውህደት ቲዎሪ እንደማይሰራ አረጋግጦ፣ ኢማሌድህ መፍረሱን ካረጋገጠ በኋላ ከእንግዲህ የወዛደሩ ፓርቲ ጥንስስ ይህ ኢማሌድህ የተባለ ነገር ቀርቶ አንድ “በአብዮታዊው” ደርግ የበላይነት የሚቋቋም የምልመላ ቢሮ እንደሆነ ገልጿል። የኢማሌድህ ልሳን ነኝ የሚለው “ህብረት ድምፅ” ቁጥር 6ትም ይህንኑ በማጠናከር ስለዚህ የምልመላ ቢሮ “ማእከል” አትቶልናል። በዚህ መሠረት የኢትዮጵያ ወዛደሮች ፓርቲ (ዛሬ ደግሞ፣ ሰርቶ አደር እንዲባል ተወስኗል!!?) ከላይ በአዋጅ ለማቋቋም በተደረገው “ታሪካዊ ውሳኔ” መሠረት “ያገባኛል የምትል ሁሉ” ማመልከቻህን “እያስገባህ ተመልመል” ተብሏል። ወደዚህ በአዋጅ ይቋቋማል ወደ ተባለው የዚያድ ባሬ አይነት ፓርቲ ለመግባት የመራኮትንና የመስገብገቡን “ክብር” ለአተላ አድርባዮችና ለለየላቸው አድሃሪዎች ትተን እኛ የኢትዮጵያ አብዮታዊያን ስለዚህ አዲሱ ሁኔታና ስለሚወድቅብን ታሪካዊ ኃላፊነት በጥሞና መወያየት ይኖርብናል።
በዚህ አዲስ ሁኔታ አንፃር የኢትዮጵያ ማርክሲስቶች፣ ዲሞክራቶችና አገር ወዳድ ኃይሎች ተግባር ምንድነው? ይህንን በአጭሩ ከመመልከታችን በፊት ኢማሌድህ ከህብረት ወደ ክስረት ተዋርዶ ዛሬ ታሪክ ትቢያ የወረደበትን ሂደት ብንመለከት መልካም ነው።
ክፍል አንድ፡ ኢማሌድህ የክስረት ጉዞ
ለመሆኑ ኢማሌድህ ማን ነበር? ኢማሌድህን በመፍረሻው ዋዜማ ላይ ለተመለከተው ሰው ይህ ህብረት በምን ላይ “ማርክሲስት ሌኒኒስት” የት ላይ “የድርጅቶች ህብረት” እንደሆነ የሚያጠያይቅበት የሙሉ ክስረት ደረጃ ላይ ደርሶ እንደነበር ይታወሳል። በመፍረሻው ዋዜማ ኢማሌድህ “አብዮታዊ ሰደድ” ይባል የነበረው ድርጅት መጠሪያ ብቻ አልነበረም። በመፍረሻው ዋዜማ ኢማሌድህ አብዮታዊ ሰደድ ውስጥ ነግሶ የነበረው የነለገሠ አስፋው እልም ያለ የፀረ ዲሞክራሲና የስልጣን ጥሙን ለማርካት የሚያስፈልገው ድጋፍ ሲል የሀገራችንን ክብር ለባዕዳን ያስረከበውን ፀረ ኢትዮጵያ ፖለቲካ በፊትኣውራሪነት የመራው ክሊክ መጫወቻ ድርጅት ሆኖ ነበር። ዛሬ ኢማሌድህ ሲፈርስ ከአብዮቱ ሰፈር አንድም የተቃውሞ ቃል አለመሰማቱ በዚህ “ህብረት” ጠቅላላ ክስረትና ከውስጡ ያሉትን አብዮታዊያን ሁሉ “አጥርቶ” የዚህ ክሊክ ሌላ መጠሪያ ስም ሆኖ በመቅረቡ እንደሆነ ግልጽ ነው። ነገር ግን ኢማሌድህ በተመሠረተበት ወቅት ሊፈርስ ዋዜማ ላይ የነበረው ከሣራ ድርጅት አልነበረም። እንዲያውም በየካቲት 1969 ዓ.ም ላይ ከዚያም በኋላ ለተወሰነ ጊዜ ሰፊው የኢትዮጵያ ሕዝብ እንደወዛደር ፓርቲ ጥንሰስ ቆጥሮት ሲደግፈው ቆይቷል። ይህ ህብረት ተጠናክሮ ወደ ውህደት እንዲሸጋገርና የኢትዮጵያ ወዛደሮች ፓርቲ እንዲመሠረት ሰፊው ሕዝብ አብዮታዊ ትግል አካሂዷል። ነገር ግን የኢትዮጵያ አብዮታዊያን “ከህብረት ወደ ውህደት” ብለው የታገሉት፣ ኢማሌድህ በተመሠረተበት አቋምና የጋራ መርሃግብር ላይ ፀንቶ እስከ ቆመ ድረስ ብቻ ነበር። ከዚያም መድረክ ሲንሸራተትና የፀረሕዝቦች መጫወቻ አሻንጉሊት ሲሆን ይህንን ከሣራ ህብረት የኢትዮጵያ አብዮታዊያንና ጭቁኖች በሙሉ አክ እንትፍ ብለው ተፍተውት ነበር።
ኢማሌድህ የመመስረቻ መድረክ ምን ነበር? ከዚህ መስመርስ ለምንና እንዴት ተንሸራቶ በሰፊው ሕዝብ ለመተፋት በቃ? እነዚህን ጥያቄዎች በአጭሩ ለመመለስ እንሞክራለን።
ሀ/ የኢማሌድህ አመሰራረት
ተደጋግሞ እንደተነገረው የማንኛውም አብዮት መሰረታዊ ጥያቄ የመንግሥት ስልጣን ጥያቄ ነው። የኢትዮጵያ አብዮት ከፈነዳበት ወቅት አንሰቶ በዚህ ወሳኝ ጥያቄ ላይ ከፍተኛ ትግል ተካሂዷል። በዚህ ትግል ውስጥ በአጠቃላይ ሁለት ሰፈሮች ተፋጠው በፖለቲካ፣ በርዕዮተዓለም፣ በድርጅት፣ ከዚያም አልፎ በትጥቅ ደረጃ ተፋልመዋል። አሁንም እየታገሉ ናቸው። በዚህ በስልጣን ጥያቄ ዙርያ የተደረጉት ትግሎች በአንድ በኩል በሕዝብ ስም ከሕዝብ ፊት በአቋራጭ ስልጣን ለመያዝ በሚቋምጠው በቀኝ ንዑስ ከበርቴ ፊታውራሪነት የሚንቀሳቀሰው የአድሃሪ ቢሮክራሲና የጠቅላላው የቀኝ ኃይሎች ህብረት ሲሆን፣ በሌላ በኩል ደግሞ በማርክሲስቶች፣ በዲሞክራቶችና አገር ወደድ ኢትዮጵያውያን ግንባር ቀደምነት የሚዋደቀው የሰፊው ሕዝብ ሰፈር ነው።
ከዚህ አንጻር ሲታይ ቀደም ሲል “በግራ” አድርባዮች በኢህአፓ ፊት አውራሪነት አድሃሪው ቢሮክራሲና ጠቅላላው ፀረ ሕዝብ ክፍል ያነሳው የጊዜያዊ ሕዝባዊ መንግሥት ጥያቄ የዚህ ፀረ ሕዝብ ሴራ የማይነጠል አካል እንደሆነ ዛሬ
ማንም የማይክደው ሀቅ ነው። በመኢሶን ግንባር ቀደምነት ዲሞክራቶችና አገር ወዳድ ኢትዮጵያዊያን ባካሄዱት ተጋድሎ ይህ አቋራጭ ሙሉ በሙሉ ተጋልጦ ኢህአፓ ወደ ታሪክ ትቢያነት ወረደ። ከዚህ ድል በመነሳት በሚያዚያ ወር 1968 ዓ.ም የኢትዮጵያ ብሄራዊ ዲሞክራሲያዊ አብዮት ፕሮግራም ይፋ ወጥቶ ለስልጣን ጥያቄ ሊሰጠው የሚገባውን መልስ አበሰረ። ይህ ፕሮግራም የኢትዮጵያ ሕዝብ ለዴሞክራሲያዊ ስልጣን የሚበቃበትን ትልም አሳየ። የኢትዮጵያ ሕዝብ ለስልጣን የሚበቃው የቀኝ ኃሎች በሚታገሉለት ጊዜያዊ ሕዝባዊ መንግሥት ሳይሆን፣ ንኡስ ከበርቴው ከላይ በሚያውጀው ፓርቲ አማካኝነት ሳይሆን በነቃ በተደራጀና በታጠቀ የረዥም ጊዜ ትግል፣ በሃቀኛ የወዛደር ፓርቲና በሌሎች ዴሞክራሲያዊ ፓርቲዎችና ድርጅቶች ትብብር በሚቋቋም ሕዝባዊ አብዮታዊ ግንባርና ሕዝባዊ አብዮታዊ ሠራዊት እንደሆነ ተረጋገጠ። ይህን ዓላማና ህልምም ሰፊ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሙሉ በሙሉ ተቀብሎ ከዳር እስከዳር ተዋደቀለት። ከዚህም ወቅት አንስቶ በቀኝ ኃይሎችና በአብዮታውያን ማሀከል የተካሄደው ትግል የዚህን ፕሮግራም ከስራ ላይ መዋል በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በሚቃወሙ ኃይሎችና በዚህ ፕሮግራም አርማ ስር ተሰልፈው በመጓዝ በሚዋደቁ ታጋይ የኢትዮጵያ ልጆች መካከል ነበር።
በኢትዮጵያ “ማርክሲስት ሌኒኒስት ነን” ይሉ የነበሩት አምስት ድርጅቶች ከዚህ ሀቅ በመነሳት በአብዮቱ ሂደት ውስጥ ቁልፍ ሚና የሚጫወተውን የወዛደር ፓርቲ ለመመስረት ከዚያም አልፎ ለሕዝባዊ ግንባሩ አስፈላጊ የሆኑትን ዲሞክራሲያዊ ፓርቲዎችና ሕዝባዊ ድርጅቶች እንዲፈጠሩና እንዲፋፋ ለማገዝ ከፍተኛ ተጋድሎ ሲያካሄዱ ቆይተው ነበር። በዚህም ትግላቸው በተለይ ለኢትዮጵያ ማርክሲስቶች ሌኒኒስቶች አንድነት ያደረጉት ትግል ፍሬ ሰጥቶ በየካቲት ወር 1969 ዓ.ም የኢትዮጵያ ወዛደር ፓርቲ ጥንስስ ይሆናል ተብሎ ተስፋ የተጣለበትን የኢትዮጵያ ማርክሲስት ሌኒኒስቶች ህብረት “ኢማሌድህን” መሰረቱ። ይህ ለጠቅላላው በኢትዮጵያ ተራማጆች በተለይ ደግሞ ለኢትዮጵያ ወዛደሮች አንድ ትልቅ የድል ምዕራፍ ነበር። ታላቅነቱም ህብረቱ መመስረቱ ብቻ ሳይሆን ስለወደፊቱ ሂደት፣ ስለወዛደሩ ፓርቲ አመሰራረት ሁኔታ፣ ስለ ማርክሲስት ሌኒኒስቶች አጣዳፊ ተግባሮች ለአስመሳይና ለከሃዲ ንዑስ ከበርቴዎች በምንም አይነት በማያወላዳ ሁኔታ ግልጽ የሆነ አቋም መያዙ ነበር።
የኢትዮጵያን አብዮትና ብሔራዊ ክብር ለስልጣን ጥማቸው ማርኪያ ለፍርፋሪ በመሸጥ ከሁለት ዓመት ወዲህ ሊያድበሰበሱት እና ሊያወድሙት ሞከሩ እንጂ ኢማሌድህ ገና ሲመሰረት ስለወዛደሩ ፓርቲ አመሰራረት ጉዳይ ቁልጭ ያለ ትክክለኛ አቋም ነበረው። በጊዜው የወጣውን መግለጫ የፈረሙት ድርጅቶች በዚህ ጉዳይ ላይ እንደሚከተለው ብለው ነበር።
“… ከነዚህ የተለያዩ ቡድኖች በምን ዘዴ የወዛደሩ ፓርቲ ሊመሰረት ይችላል ለሚለው ጥያቄ የብዙ አገሮች አብዮታዊ ትግል ታሪክና የኢትዮጵያን ተጨባጭ ሁኔታ በመመርመር ከተለያዩ የወዛደር ፓርቲ አመሰራረት ዘዴዎች ፍቱንና ሳይንሳዊ የሆነው ዘዴ ልዩ ልዩ ማርክሳዊ ቡድኖች ኃይላቸውን አስተባብረው የትግል አንድነት መስርተው በመካከላቸው በታክቲክ እና በስትራቴጂ ጥያቄዎች ላይ ሀቀኛ የሆነ የርዕዮተ ዓለም ትግል አካሄደው የሚዋሃዱበት ዘዴ መሆኑን አምነውበታል።”
ካሉ በኋላ ለዚህ ሃቀኛ የርዕዮተ ዓለም ትግል አመቺ ሁኔታ ለመፍጠር በስውር ታፍነው የሚሰሩት ተራማጅ ድርጅቶች ትግላቸውን በይፋ ለማካሄድ እንዲችሉ “በአስቸኳይ ዲሞክራሲያዊ መብቶች ለጭቁኖች አለገደብ እንዲታወጁ” የጋራ ትግል ለማድረግ ወስነው ነበር። ይህ ሂደት በእርግጥ ሃቀኛ የሆነ የኢትዮጵያ ወዛደሮች ፓርቲ ለመመስረትና ወደ ሕዝባዊ ስልጣን ለመጓዝ ቁልፍ ከሆኑት ጥያቄዎች አንዱ የሆነውና ወዛደር ፓርቲ ጥያቄን በአብዮታዊ መንገድ የሚመልስ ሂደት ነበር።
ነገር ግን በዚው በትክክል እንደተቀመጠው እና በጋራ መግለጫው ላይ እንደተጠቀሰው የኢትዮጵያ ማርክሲስት ሌኒኒስቶች ትግላቸው ለወዛደር ፓርቲ ብቻ አልነበረም። በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ አንድ ፓርቲ ብቻውን ስልጣን የሚይዝበት ሂደት ፀረ አብዮትን እንጂ አብዮትን አያመጣም። በኢትዮጵያ ሁኔታ የኢትዮጵያ ሰፊ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ስልጣን ሊረጋገጥ የሚችለው ከወዛደሩ ሌላ በሀገሪቱ ያሉ ዲሞክራሲያዊና ሀገር ወዳድ ኃይሎች በመሰላቸው ተደራጅተው ግንባር ሲፈጥሩ ብቻ በመሆኑ በመግለጫው ላይ ይህ ነጥብ በግልጽ እንዲገባ መኢሶን ባካሄደው ከፍተኛ ትግል እየተነሳ
“… ሕዝባዊ አብዮታዊ ግንባር ለመመስረት የሚያስችሉትን ዲሞክራሲያዊ ፓርቲዎችና ሰፋፊ ድርጅቶች ለማቋቋም እንዲችሉ ባስቸኳይ ዲሞክራሲያዊ መብቶች ለጭቁኖች ያለገደብ መታወጅ አለባቸው።”
ለዚህም የኢትዮጵያ ማርክሲስት ሌኒኒስት ድርጅቶች ይህንን ተግባር ከሥራ ለማዋልና ሕያው የሆነ ሕዝባዊ አብዮታዊ ግንባር ለማቋቋም እንዲችሉ በዚህ መግለጫ ውስጥ በወዛደሩ፣ በአርሶአደሩ፣ በወጣቶች፣ በሴቶች፣ በቀበሌዎች አካባቢ ጠንካራና ሕዝባዊ ድርጅቶች እንዲያብቡ፣ ለዚህ እንቅፋት የሆነውን አድሃሪ ቢሮክራሲ እንዲጋለጥና እንዲደመሰስ ለመታገል ቃል ገቡ።
በብሔራዊ ዴሞክራሲያዊ አብዮት ፕሮግራም በተተለመው መሰረት አብዮቱን ከግቡ ለማድረስ አስፈላጊ ከሆኑት መሣሪያዎች አንዱ ሕዝባዊ አብዮታዊ ጦር መሆኑን በመገንዘብ “ይህንን ሕዝባዊ አብዮታዊ ጦር ከወዛደሩ፣ ከአርሶአደሩ፣ ከሌሎች ተራማጅ ኃይሎችና አሁን ካለው መለዮ ለባሽ ለአብዮቱ ከቆመው ወገን ማቋቋም የሚቻልበት ሁኔታ አለ። አሁን ያለው የኢትዮጵያ መለዮ ለባሽ በመደብ ምንጩ ከደሃው ገበሬ እንደመሆኑ መጠን ከውስጡ የሚገኙትን ፀረ አብዮት ኃይሎች ለማጽዳት ከሰራዊቱ ይበልጡን ወደ ሕዝቡ ለመሳብ የማርክሲስት ሌኒኒስቶች ተግባር መሆን አለበት። የቀድሞ ፊውዶ ቡርዧዋው ቢሮክራሲ እንዳለ ለአብዮቱ መቆም አንደማይችል ተገንዝበው ይህ ቢሮክራሲ እንዲሰበር መታገል ይኖርባቸዋል።” በማለት ለኢማሌድህ አባል ድርጅቶች ግልፅ የሆነ የትግል መድረክ ተከፍቶላቸው ነበር።
እንግዲህ ኢማሌድህ ሲመሠረት የተቆረቆረበት የጠራ መስመር ይህ ነበር። የቀኝ አድርባዮች የዚህን መድረክ አንቀጾች አንድ በአንድ እየሻሩ ወደ ፀረ አብዮት በመንሸራተታቸው ኢማሌድሃቸውም ከስሮ ከሰፊው ሕዝብ ተተፍቶ ለዛሬው ታሪካዊ ውርደት በቃ።
ለ/ የኢማሌድህ የክስረት ሂደት
ኢማሌድህ ከፖለቲካ ክስረቱ ጋር ድርጅታዊ ክስረት ተደርቦበት ዛሬ በአድሃሪዎች ግፊት በቀላሉ ሊፈርስ የቻለው በዚህ ክስረቱ የተነሳ አብዮታዊያንና ሰፊው የኢትዮጵያ ሕዝብ አክ እንትፍ ብለው ስለተፉት እንደሆነ ግልጽ ነው። ዛሬ የኢማሌድህ መፍረስ ሁለት ችግሮችን ያሳያል። በመጀመርያ የቀኝ አድርባዮቹ በፊታውራሪነት ወግተው በአደከሙት የአብዮቱ ሰፈር ላይ የቀኝ ኃይሎች ህብረት በጠቅላላው መጠናከራቸውን ያሳያል።ሁለተኛ ደግሞ በዚህ በቀኝ ኃይሎች ህብረት ውስጥ የነለገሠ አስፋው ክሊክን በተለያዩ ምክንያቶች እና በተለያዩ አቅጣጫዎች የሚቃወሙት ኃይሎች ማየላቸውን ያሳያል።
የመጀመሪያውን ነጥብ እንውሰድ። እንደሚታወቀው የኢትዮጵያን አብዮት ሂደት ለመግታት ብሎም ለመቀልበስ የቀኝ አድርባዮች፣ የጊዜያዊ ወታደራዊ መንግሥትና አድሃሪው ቢሮክራሲ የጠነሰሱት የቀኝ ኃይሎች ህብረት አብዮቱን ማጥቃት የጀመረው ከዛሬ 2 አመት ቀደም ሲል ነው። የሰፊው ሕዝብ ድምጽ ቁጥር 68 ላይ ስለዚህ አዲስ የቀኝ ኃይሎች ሕብረት መጠንሰስ እና አስተዳደግ ባጭሩ ተንትነናል። እዚህ አንመለስበትም። የዚህን ሕብረት እየተጠናከረ መምጣትን ጉዳይ ስንተነትን ጊዜ እስካላመቸው ድረስ አብዮቱን በአብዮት ስም ለመውጋት ይገደዳል እንጂ የጸረ አብዮቱ ዕድገት ደረጃ እንደፈቀደለት ክህደቱን ሁሉ ከዕለት ዕለት ይፋ እያወጣው ይሄዳል ብለን ነበር። ከዚያን ጊዜ ወዲህ የኢትዮጵያ የፖለቲካ መድረክ ጉድ ያሳየን ጀምሯል! የቀኝ ኃይሎች ህብረት ክህደት በድፍረት ይፋ የወጣ ነው።
አድሃሪ ኃይሎች በተለይም ግንባር ቀደማቸው የሆነው አድሃሪው ቢሮክራሲ የቀኝ አድርባይ ድርጅቶች “በትግላችን” እያሉ “ገና ጊዜው አልደረሰም” እያሉ ሲያሾፉበት የነበረውን የዲሞክራሲ ጥያቄ ዛሬ “ዲሞክራሲ ጊዜው ያለፈበት ጥያቄ ነው” ማለት አምጥተዋል። ያ ሁሉ ደም ተገብሮበት በኢትዮጵያ ስር የሰደደውን የአብዮታችን መመሪያ የሆነውን ብሔራዊ ዲሞክራሲያዊ አብዮት ፕሮግራም ሽረን ከሱ የበላይነት ያለው “የአዲስ አበባ ማኒፌስቶ እናውጣ” እያለ ሽር ጉድ በማለት ላይ ነው። የቀኝ አድርባይ ድርጅቶችም በትእዛዝ መፍረሳቸውን ባስታወቁበት የህብረት ድምፅ ቁጥር 5 ላይ ስለዚህ መመሪያነት ሳንቲም ሳያነሱ እንዲያውም የአብዮቱን መመሪያ በታህሳስ “በአብዮታዊው” ጊዜያዊ ወታደራዊ መንግሥት የታወጀው የኢትዮጵያ ሶሻሊዝም መሆኑን “አብስረውልናል”። በአጠቃላይ “አዲሱ ዲሞክራሲያዊ አብዮት” ብለው ከሶሻሊዝም በፊት በዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ማለፍ የሚሉት ነገር “የንዑስ ከበርቴ ሶሻሊዝም ነው እየተባለ መለፈፍ ተጀምሯል።
ሕዝባዊ ድርጅቶችን በሚመለከት በኩል የቀኝ አድርባዮች በኢትዮጵያ አብዮት አንገት ላይ የጠመጠሙት የቢሮክራሲ ማነቆ ድርጅቶችን ሁሉ ምንሽርሽራቸውን ካወጣ በኋላ አሁን ደግሞ እነዚህ ድርጅቶች የተቋቋሙባቸው አዋጆች እንደገና መታየትና መሻሻል ያለባቸው እያለ ሊሽራቸው በመሰናዳት ላይ ነው። በመጋቢት ወር ላይ የኮሎኔል መንግሥቱን የደቡብ ክፍለ ሃገራት ጉብኝት በማስመልከት የተካሄደው የኢኮኖሚና የባህል ዘመቻ መመሪያ ጉባዔ ላይ አድሃሪው ቢሮክራሲ በይፋ ከጠየቀው ከአዋጆች ሁሉ በላይ የሆነ “የአዲስ አበባ ማኒፌስቶ” ጋር ጨምሮ የ1969 ዓ.ም እነ ኢህአፓ “የባርነት አዋጅ” ብለው የታገሉትን የሠራተኞች ጉዳይ አዋጅ “እንዲሻሻል” የሠራተኛው ተወካዮች የሌሉበት ኮሚቴ መቋቋሙ… ወዘተ ለዚህ “የድፍረት ሂደት” ተጨማሪ ማስረጃ ነው። ገና ደግሞ ብዙ እናያለን። በዚህ ሂደት ላይ ብሔራዊ ዲሞክራሲያዊ አብዮት ፕሮግራም የቀኝ መንገደኞች ፕሮግራም ተብሎ በይፋ የሚሻርበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም።
ለማንኛውም ዛሬ ኢማሌድህ እንደዚያ እንዳልተፈከረለት፣ እንደዚያ የአድሃሪው ቢሮክራሲ መንጋ ከሰፊው ሕዝብ ተደባልቆ ከአንገት በላይ “ይደግ ይመንደግ” አያለ እንዳላስተጋባ ሁሉ ዛሬ እንዲፈርስ መደረጉ የዚህ ፀረ አብዮት ሂደት የማይነጠል አካል ነው ለማለት ይቻላል።
የትኛው ሕዝባዊ ድርጅት፣ የትኛው የአብዮቱ ተቋም እየፋፋ እንደሄደ ኢማሌድህ ይፋፋል? ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ የትኛው የአብዮቱ መፈክር፣ የትኛው የአብዮቱ ሰነድ ተከበረና የኢማሌድህ መርሐ ግብርና መድረክ ይከበራል? የትኛውም ሊከበር አይችልም። ባለፉት ሁለት አመታት ውስጥ በቀኝ ኃይሎች ህብረት እያየለ መምጣት የተነሳ በታጋይ ኢትዮጵያውያን/ት ደም ተገንብተው ማበብ የጀመሩት ሕዝባዊ ድርጅቶች በሙሉ ፈራርሰዋል፣ እንደ ሕዝብ ድርጅት ጉዳይ ጊዜያዊ ጽ/ቤት አይነቶቹ ተቋሞችም እንደዚሁ ፈራርሰዋል። የዛሬው “ባለ ሳምንት” ደግሞ ኢማሌድህ ሆኗል። ዛሬ የኢማሌድህ በይፋ መፍረስ በጠቅላላው የቀኝ ኃይሎችን ህብረት መጠናከርና በተለይ ደግሞ በዚህ ህብረት ውስጥ የቀኝ አድርባዮችን መዳከም ያሳያል ስንል ምን ማለታችን ነው? በቀኝ ኃይሎች ህብረት ውስጥ በፊታውራሪነት የተሰለፉት የቀኝ አድርባይ ድርጅቶችና እርሱ በስተጀርባ ያለው የህብረቱ አንቀሳቃሽ የሆነው አድሃሪ ኃይል ለጊዜው “ታክቲካዊ” ህብረት ፈጠሩ እንጂ የዓላማቸው ርቀት የተለያየ ነበር። የፊታውራሪዎቹ ከበርቴዎች “ሕልም” የአብዮቱን ሂደት ባለበት ገትተው ስልጣናቸውን ለማደላደል እንጂ ሂደቱን ጨርሰው ለመቀልበስ አልነበረም። ከፊታውራሪዎቹ በስተጀርባ በቀኝ አድርባዮች በስተቀኝ ያለው ፀረ አብዮት ግን ምስኪኖቹን አድርባዮች ለጊዜው የአብዮቱን ሂደት ለማቀዝቀዝ እና በቁጥጥር ስር ለመዋል በመሳሪያነት ይጠቀሙባቸዋለን እንጂ የሱ ዓላማ አብዮቱን ከመግታትም አልፎ መቀልበስ እንደሆነ ግልጽ ነበር።አሁንም ነው።
የአብዮቱን ሰፈር ድርጅቶችና ተቋሞች (የሕዝብ ድርጅት ጉዳይ ጽ/ቤት፣ ኢማሌድህ . . .ወዘተ) በሚመለከት በኩል የአደርባዮች ዓላማ እነዚህን ድርጅቶች ከሃቀኛ አብዮታዊያን “አጽድተው” በቁጥጥራቸው ሥር ማዋልና በአብዮቱ ስም ፀረ ሕዝብ ሥልጣናቸውን ማጠናከር ነበር። አድሃሪዎቹ ደግሞ እነዚህን ድርጅቶችና ተቋሞች ከቆሙበት መድረክ አፈራርሰው ለማውደም ይታገላሉ። እዚህ ላይ ግን ሁለት ኃይሎች የሚሄዱበት ርቀት የተለያየ ቢሆንም በዚህ ሂደት ላይ ባሉት የመጀመሪያዎቹ እርምጃዎች ይስማማሉ። ሁለተኛ እነዚህ ድርጅቶችና ተቋሞች እንዳይፋፉ ዲሞክራሲን ያፍናሉ። ያሻጥራሉ፣ ሁለቱም እነዚህ ድርጅቶችና ተቋሞች ከመኢሶንና ከሌሎች ዲሞክራቶችና አገር ወዳዶች በ“ማጽዳቱ” ላይ ይስማማሉ።
በዚህ ሁኔታ ምስኪኖቹ የቀኝ አደርባዮች ከሁሉ “ተወርዋሪ” በመምሰልና የመደባቸው ዘላለማዊ ምልክት በሆነው ድንፋታ እየተውጠረጠሩ ሕዝባዊ ድርጅቶችን ከአብዮታውያን “ለማጽዳት” በፊታውራሪነት ታገሉ። በዚህ ትግል ከቁጥጥራቸው ሥር ሲያውላቸው ያዳከማቸውን፣ ከሰፊው ሕዝብ ያቆራረጧቸውን ሕዝባዊ የነበሩ ድርጅቶች አድሃሪው ቢሮክራሲ በቀላሉ አፈራረሳቸው። ዛሬ እነዚህ ድርጅቶች በአሻጥር ጠውልገው፣ በፀረ ዲሞክራሲ ታፍነው፣ በአደርባዮች ቁጥጥር ሥር በመሆናቸው በሰፊው ሕዝብ ተተፍተው ስለሚገኙ አሉ ወይስ የሉም እያሉ የሚያወራርዱበት የጣረሞት ደረጃ ላይ ደርሰዋል።
በአብዮቱ ተቋሞችም በኩል ይኸው ነው። የሕዝብ ድርጅት ጉዳይ ጊዜያዊ ጽ/ቤትን አደርባይ ድርጅቶች በተለይ ደግሞ የአብዮታዊ ሰደድ ክሊክ በራሱ ቁጥጥር ሥር ለማድረግ አስቦ ከአብዮታውያን ለ“ማጽዳት” ሞከረ። አድሃሪያን ግን ይህ ተቋም ከተመሠረተበት ወቅት አንስቶ ያልሙና ይታገሉ የነበረው ይኸንን ተቋም ጨርሶ ለማፍረስ ነበር። ዛሬ ይኸንን ተቋም ከመኢሶን ለማጽዳት የተከፈተው ዘመቻ ሁለት ዓመት ሲሆን በዚህ በኩል የምናየው ምንድን ነው? የሕዝብ ድርጅት ጉዳይ ጊዜያዊ ጽ/ቤት “የኢትዮጵያ አብዮት አለኝታ ነው” እያለ ሰፊው ሕዝብ ያልተዋደቀለትን ያህል፣ ያ ሁሉ ታጋይ ደሙን እየገበረ ትግሉን ያላፋፋመውን ያህል በሰፊው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጨርሶ ተተፍቶ፣ ከታጋዮች ፀድቶ አድሃሪዎች እንዳልነበር አድርገው አውድመውታል። የኢማሌድህም ክሥረት የተከተለው ጎዳና ይኸው ነው።
የቀኝ አደርባይ ንዑስ ከበርቴዎች “ህልም” ኢማሌድህን ከአብዮታውያን “አፅድተው”፣ ሥፍር ቁጥር የሌለው ታጋይ ወዝአደር ረሽነውና አስረሽነው፣ በሺህ የሚቆጠር ታጋይ በየእሥር ቤቱ ወርውረው፣ የአንድ ትውልድ ትግል ያፈራቸውን ማሌዎች ለማስጨፍጨፍ መሣሪያ ሆነው በቁጥጥራቸው ሥር ካደረጉት በኋላ ማርክሲስት ሌኒኒስቶች ለመድሃኒት የማይገኙበት “የማርክሲስት ሌኒኒስቶች ፓርቲ” ያለወዝአደሮች የወዝአደር ፓርቲ ለመመሥረትና ከዚህ ከኢማሌድሃቸው ወደ ውህደት በተሸጋገረ ፓርቲያቸው አማካኝነት ስልጣን ለመጨበጥ ነበር! ነገር ግን ይኽንን አላማ ሲከተሉ ባዳከሙት አብዮት አንፃር እየተጠናከረ የመጣው የቀኝ ሰፈር አማሌድሃቸውን አፈራርሶ የነለገሠ አስፋው ክሊክ ብቻውን ሥልጣን ለመጠቅለል የቋመጠበት ሂደት ውሃ ገባ! ይኸ የጠቅላላው የአድሃሪው ሰፈር መጠናከር ደግሞ አንዱ ትርጉም በቀኝ ኃይሎች ህብረት ውስጥ የለየላቸው ቀልባሽ ኃይሎች በቀኝ አድርባዮች ላይ የበላይነትን ተቀዳጁ ማለት ነው። ይኸንን የኃይል ሚዛን ለውጥ በይበልጥ ጠጋ ብሎ መመልከት ያስፈልጋል።
ከላይ እንዳልነው የኢማሌድህ መፍረስ በቀኝ ኃይሎች ህብረት ውስጥ በልዩ ልዩ ምክንያቶች ከልዩ ልዩ አቅጣጫዎች በአብዮታዊ ሰደድ ውስጥ የበላይነት ይዞ የነበረውን የነለገሠ አስፋው ክሊክ የሚቃወሙ ኃይሎች ግፊት እንደሆነና የዚህን ክሊክ መዳከም የሚያሳይ ነገር ነው ብለናል። ዞሮ ዞሮ ከሣራው ኢማሌድህ የወዝአደር ፓርቲ ጥንስስ ከመሆን አክትሞ ነበር። ይህንን አብዮታውያንም ፀረ ሕዝቦችም ያውቁት ነበር። ኢማሌድህ ይፍርስ በተባለበት ጊዜ ይህ በትር የተሰነዘረው በተለይ በነለገሠ አስፋው ክሊክ ላይ ነው የምንለው ኢማሌድህ ከሁለት ዓመታት ወዲህ “እየፀዳ እየፀዳ መጥቶ” የዚህ ክሊክ ሌላ መጠሪያ ስም ስለነበረ ነው። የቀኝ አድርባዮች በአብዮታውያን ላይ ዘምተው ከዚያ በኋላ ደግሞ እርስ በእርስ በገጠሙት ግብግብ ተዳክመው የኢትዮጵያን አብዮት ገደል ይዘው ከመግባታቸው በፊት ስልጣንን ጠቅልለው ለመያዝ የቀየሱት ታክቲክ ነበራቸው። ይህ ታክቲክ ምንድን ነበር? ዛሬ የዚህ ታክቲክ መክሸፍ ምን አዲስ ሁኔታ ፈጠረ?
ከኢማሌድህ መፈጠር በኋላ በአብዮታዊ ሰደድ እና ዛሬ በአዋጅ በፈረሱት በሌሎች ማርክሲስት ሌኒኒስት ነን ይሉ የነበሩ ድርጅቶች አድርባይ መሪዎች የተጠነሰሰው የሥልጣን ባቋራጭ ሴራ ሁለት ምዕራፎች ነበሩት። የመጀመሪያው ምዕራፍ ኢማሌድህን ከሃቀኛ ማርክሲስት ሌኒኒስቶች አጽድቶ በአብዮታዊ ሰደድ ቁጥጥር ሥር ማዋልና ይህንን ከማርክሲስት ሌኒኒስት ጠርቶ “ማርክሲስት ሌኒኒስት” የሚባል፣ ከድርጅቶች ጠርቶ “የድርጅቶች ሕብረት” የሚባል ቆፎ ነገር “አዋህዶ” ወደ ወዝአደር ፓርቲነት መለወጥ ነበር። ሁለተኛውና ከዚህ የሚከተለው ምዕራፍ ደግሞ በዚህ “የወዛደር ፓርቲ” አማካኝነት “ንዑስ ከበርቴ” “ወላዋይ” ይባል የነበረውን ደርግ አፍርሶ ስልጣንን በአብዮታዊ ሰደድ ክሊክ እጅ መጠቅለል ነበር።
ይህንን ታክቲኩን የተገነዘበ ሰው ባለፉት ሁለት ዓመታት የአብዮታዊ ሰደድ ክሊክ ለምን ኢማሌድህን ሊጠቀምበት እንጂ ሊያፈርሰው እንዳልፈለገ ይገነዘባል። ይህንን ታክቲኩን የተገነዘበ ሰው አብዮታዊ ሰደድና ሌሎች የቀኝ አደርባዮች የሚከተሉት ፀረ ወዝአደርና ፀረ ሕዝብ ፖለቲካ ይፋ እየወጣ ሲሄድ ስለወዛደሩ ፓርቲ አጣዳፊነት፣ ስለኢማሌድህ ከህብረት ወደ ውህደት መሸጋገር የአብዮታችን የሞት የሽረት ጥያቄ መሆን ወዘተ. የሚደረገው ቅስቀሳ ለምን እየጨመረ እንደሄደ ይረዳል። ይህ ሁሉ ድንፋታ ኢማሌድህን ወደ ወዛደር ፓርቲ ለውጦ ስልጣን ለመጠቅለል የቀኝ አድርባዮች መቋመጥ እንደነበር ግልጽ ነው። የአብዮታዊ ሰደድ ክሊክ እና ሌሎች የቀኝ አደርባይ ድርጅቶች መሪዎች ይህንን “ኢማሌድህን ከቁጥጥር ሥር ማዋል” የሚል ፖለቲካ ሲያብራሩ ለአንድ ዓመት ተኩል ያህል በአብዮቱ ሰፈር ፀረ ሕዝብ አመጽ አወረዱ። ከኢማሌድህ ውስጥ መኢሶንና ኢጭአትን አባረሩ። ይህ ጉዳይ “ተጠናቀቆ” የነሰደድ ወደወዛደር ፓርቲነት መለወጥ እየተቃረበ ሲሄድ አምና በሚያዚያ ወር “በህብረት ድምጽ” ጋዜጦች ላይ
“ሰፊው ሕዝብ . . . አስተማማኙ የወዝአደር ፓርቲ ይመሥረት ይላል . . . ያለአንዳች መታከት ኢማሌድህ ይጠናከር እያለ ያስተጋባል። በአጠቃላይ ሰፊው ሕዝብ ተጨባጩ ሁኔታ በሚጠይቀው መሠረት በወዝአደሩ ፓርቲ ለመመራት ያለው ፍላጎትና የጋለ ስሜት ከፍተኛ ደረጃ ላይ ድርሷል።” ብለው ነበር።
የአብዮታዊ ሰደድ ወደ ውህደት የመሸጋገር መቋመጥ ከዚህ ላይ አልቆመም። ትንሽ ቆይተው ዲሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ ተመርጠው ሕዝባዊ ድርጅቶችን በግንባር ቀደምነት እየመሩ የታመቁትን ኃይሎች ሁሉ እየለቀሙ የመረሸኑንና በየእሥር ቤት የማጎሩን ተግባር እንዳጠናቀቁ፣ በዚህ ሕዝባዊ ድርጅቶችን በቁጥጥራቸው ሥር ያደረጉ እንደመሰላቸው በሰኔ ወር 1970 “የሰፊው ሕዝብ የሥልጣን መሠረት የሆኑት ድርጅቶች ራሳቸውን ለኢማሌድህ አመራር አዘጋጅተው ኢማሌድህ አመራር ይሰጠን. . .” እያሉ በማመን ላይ መሆናቸውን በአብዮታዊ ሰደድ ቁጥር 21 ላይ አብስሮልን ነበር!
ታዲያ እንደዚህ መጣ፣ ደረሰ እየተባለ ሲሄድና አድርባዮቹ “የወዝአድር ፓርቲ” ብለው የዝያድ ባሬን ዓይነት ፓርቲ ለማወጅ ሲሰናዱ በአካባቢያቸው ሌላ የሥልጣን ግብግብ ምዕራፍ ተከፈተ። “በዚያው ሰሞን” ይለናል የሕብረት ድምጽ ቁጥር 5 “በዚያው ሰሞን በኢማሌድህ ውስጥ አንድ ያልተጠበቀ /?/ ሁኔታ ተከሰተ። ይኸውም በአብዮታዊ ሰደድና በወዝአደር ሊግ መካከል የታየው ውስብስብ ቅራኔ ነው።”
ማንም እንደሚያውቀው ይኸ ቅራኔ በነለገሠ አስፋው ክሊክ በአንድ በኩል በራሱ በሰደድ ውስጥ ይገኙ በነበሩ ዛሬ በታሰሩና በተረሸኑ አባላትና በወዝ ሊግ በሌላ በኩል የፈነዳ ቅራኔ ነበር። ጥሉ በዋና መልኩ የሥልጣን ግብግብ ነበር። የፖለቲካ መስመር ልዩነት ቢኖር ለሰፊው ሕዝብ የተነገረው በይፋ ውይይት የተካሄደበት ነገር የለም። አልነበረምም። በጊዜው በይፋ የተገለፀውና በአብዮታዊ ሰደድም ሆነ በአዲሱ “ተራማጅ” በተባለው የወዝአደር ሊግ አመራር እንደተገለፀው ከሆነ ጉዳዩ “የቁልፍ ቦታዎች” ንትርክ ነበር። የአብዮታዊ ሰድድ ክስም የሚለው ይኸንኑ ነበር። በዚህ ህብረት ድምፅ ቁጥር 5 ላይ “የወዝአደር ሊግ አድሃሪ አመራር አንዳንድ አባላቱን በአብዮታዊ ሰደድ ውስጥ አስርጎ በማስገባት ሁለቱን ድርጅቶች በአንድ ማዕከል ሲቆጣጠር መቆየቱ ነው።” ተብሏል። እንግዲህ በሰደድ ውስጥ የነለገሠ አስፋው ክሊክ በሥልጣን የተጋፋ ሁሉ ለአድሃሪነቱ የማያወላዳ ማስረጃ ተገኘበት ካልተባለ በስተቀር ጭቅጭቅ የተነሳበት የፖለቲካ ልዩነት እስከዚህም ግልፅ አይደለም። የሆኖ ሆኖ በዚህ ህብረት ድምፅ ውስጥ እንደተባለው ኢማሌድህ “ቀደም ሲል ያጋጠሙትን ችግሮች እንደተወጣ ሁሉ በመጨረሻም የተከሰተውን አሳሳቢ ቅራኔም ተወጥቷል።” ማለትም ኢማሌድህ በርግጥ በአብዮታዊ ሰደድ ውስጥ የነገሰው የነለገሠ አስፋው ክሊክ ሌላ መሳሪያ ሥም ሆነ። በርግጥም እንግዲህ እንደዚሁ ክሊክ ቢሆን ኖሮ ኢማሌድህ ከህብረት ወደ ውህደት ለመሸጋገር ምንም እንቅፋት አልነበረበትም!
የአብዮታዊ ሰደድ ክሊክ ወደ ሥልጣን ጥቅለላ በተለመው ጉዞ የመጀመሪያውን ምዕራፍ ለማከናወን ከአድሃሪዎች ፊታውራሪ በመሆን በአብዮታችንና በብሄራዊ ክብራችን ላይ ከፍተኛ ወንጀል ፈፀመ። ይህ “የሥልጣን ባቋራጭ” ዓላማው የጠየቀውን የማርክሲስት ሌኒኒስቶች፣ የዲሞክራቶችና የአገር ወዳዶች ደም አፈሰሰ። ከ20 ሺህ በላይ የሚቆጠሩ ተራማጅ ኢትዮጵያውያንን በየእሥር ቤቱ ወረወረ። የውስጥ ፀረ አብዮት ኃይሎች ቡራኬ ለማግኘት የትውልዱን ግንባር ቀደም ኃይል ጨፈጨፈ፣ ሕዝባዊ ድርጅቶችን ምንሽርሸራቸውን አውጥቶ የተቋጠረውን ሁሉ በታተነ፣ የውጭ ኃይሎችን ድጋፍ ለመቃረም የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካ፣ የወታደራዊ፣ የባህልና፣ የትምህርት ተቋሞች የባዕዳን ተቀጥላ እንዲሆኑ፣ በኢትዮጵያ የኢትዮጵያ ሕዝብ አለኝታ ሳይሆን የውጭ ባለሥልጣኖች ቅምጥ መንግሥት ለማቋቋም ሽንጡን ይዞ ተሟገተ። ይኸንን የተቃወመ ኃይል ሁሉ በተለይ በጦር ኃይላችን ውስጥ የሚንቀሳቀሱትን ተራማጅና አገር ወዳድ መለዩ ለባሾች “በወዛደራዊ አለም አቀፋዊነት” ስም ጨፈጨፈ። የትምክህተኞችን ቡራኬ ለማግኘት በኢትዯጵያ ብሄረሰቦች መሃከል እንደገና የከፋፍለህ ግዛ ፖለቲካን አስፋፋ። ይኸንን ሁሉ አድርጎ በኢትዮጵያ አብዮትና ብሄራዊ ክብር ጣረሞት ላይ ተጠናክሮ የመጣ ሲመስለው “የወዝአደር ፓርቲ” የሚለውን የመንግሥት መሥሪያ ቤት አቋቁሞ ሥልጣን ለመጠቅለል ቋመጠ። ይኸ ታክቲኩ ስለከሸፈበት ሁኔታ ከመዘርዘራችን በፊት የዚህ ሥልጣን ጥቅለላ ጉዞ ሁለተኛ ምዕራፍ ምን እንደነበር እንመልከት።
የዚህ “የሥልጣን ባቋራጭ” ታክቲክ ሁለተኛ ምዕራፍ ባቋራጭና በወዝአደሩ በስተጀርባ በተቋቋመው የወዝአደር ፓርቲ አማካኝነት “ንዑስ ከበርቴ ወላዋይ” ይባልለት የነበረውን ደርግ አፍርሶ ሥልጣንን መጠቅለል ነበር። በዚህም ጥያቄ ላይ አብዮታዊ ሰደድ ቀደም ሲል ከተራማጆች ጋር ተደባልቆ ትክክለኛውን አቋም ይዞ ሲያስተጋባ መቆየቱ ይታወሳል። ዛሬ በዚህ ጥያቄ ላይ አቋሙን መቶ ሰማንያ ዲግሪ ለመለወጥ ተገዶ ምንም ዓይነት ሃፍረት ሳይሰማው ተቃራኒውን ይዞ እስከሚሟገት ድረስ ከአብዮታውያን እኩል የጠራ አቋም ነበረው። የንዑስ ከበርቴ መደብ የማይነጠል አካል እንደሆነና የኢትዮጵያን አብዮት በምንም ዓይነት ከግቡ ሊያደርስ የሚችል ኃይል አለመሆኑን አብዮታዊ ሰደድ ሙሉ በሙሉ ይቀበል ነበር።
“የወዝአደሩ ፓርቲ ተፈጥሮ አመራር የመጨበጡን ጥያቄ አንገብጋቢ ከሚያደርጉት መሠረታዊ የአብዮቱ ጥያቄዎች መሃል መነሳት ያለበት ዓብይ ጉዳይ የሰፊው ሕዝብ ሥልጣን የጨበጠው ጊ.ወ.አ. ደርግ ታሪካዊ ሚና ጉዳይ ነው። ደርግ በደርግነቱና በሚወክለውም መደብ አንፃርና በአብዮታዊ ሂደት ትይዩ ታሪካዊ ሚናው የሚመዘነው ከሥር በንቃት፣ በድርጅትና በትጥቅ እየዳበረ በተራማጆች ህብረት (ማለትም ሰደድ!-ሰሕድ-) እየተመራ ከሚመጣው ሕዝባዊ ኃይል አንፃር ነው። የኢትዮጵያ አብዮት ከውስጥ ሆነ ከውጭ የወጠሩት ጠላቶች እያበጡ ሲመጡ ደርግ አመራር መስጠት በሚሳነው ወቅት ሰፊውን ሕዝብ አንቀሳቅሶ ለወሳኝ ፍልሚያው ለሚያደርገው ትግል ውጤት ኢማሌድህ ተጠያቂ ይሆናል። ይህንን ሃሳብ ለመጠቆም የተገደድንበት ዋናው ምክንያት ደርግ ባለው የመደብ ፀባይና ይዘት የፈለገውን ያህል ተራማጅ ቢሆን ለሰፊው ሕዝብ ንቃት፣ ድርጅት፣ ትጥቅ፣ አመቺ ሁኔታን ከመፍጠር ለሃቀኛ ተራማጆች ትግል በሕዝባዊ ጎኑ አማካኝነት ድጋፍ ከመስጠት ሌላ እንዲሁም በጊዜያዊ መንግሥትነት የመንግሥት ሃላፊነቱን ከመወጣት ሌላ ስለወዝአደሩ ፓርቲ መፈጠር የሚኖረው ሚና የተለየ ሊሆን አይችልም” አ.ሰ. ቁ.19 ታህሣሥ 1970።
ይኸው ፅሁፍ ዝቅ ብሎ “ከዛሬው ደርግ ባሻገር” ትግሉን ለመቀጠል የሚያስችል የወዝአደር ፓርቲ ለኢትዮጵያ አብዮት ሂደት እጅግ አስፈላጊ የሆነ ነገር እንደሆነ ያሳያል። ይኸንን ፅሁፍ በረጅሙ የጠቀስነው ሆነ ብለን ነው። በዚህ ጥቅስ ውስጥ “የደጉ ጊዜ” አብዮታዊ ሰደድ ብቻ ሳይሆን የጠቅላላው የተራማጆችም አቋም በመሆኑ ነው። ከዚህ ጥቅስ እንደሚታየው አንደኛ ደርግ በሚወክለው መደብ የተነሳ በኢትዮጵያ አብዮት ሂደት ውስጥ በአመራር ሚናው የሚልፈሰፈስበት ታሪካዊ ወቅት ይመጣል። ይህ በሚመጣበት ሰዓት ተራማጆች ትግሉን “ከከዛሬው ደርግ ባሻገር” አካሂደው አብዮቱን ከግብ ለማድረስ እንዲችሉ የወዝአደር ፓርቲ መሥርተው ለመራመድ መዘጋጀት አለባቸው። ሁለተኛ፤ እንደዚህ አይነቱ የታሪካዊ መልፈስፈስ ወቅት ሲመጣ ለአብዮቱ አመራር የወዝአደሩ ፓርቲ ብቸኛ ጥንስስ የተባለው ኢማሌድህ ተጠያቂ ይሆናል። ሶስተኛ፤ ደርግ የፈልገውን ያህል ተራማጅ ቢሆን ንዑስ ከበርቴ በመሆኑ የወዝአደሩን ፓርቲ ለመፍጠር አይችልምና በዚህ በኩል ገብቼ እፈተፍታለሁ ቢል ተቀባይነት አይኖረውም የሚል ሃሣቦች ይገኛሉ።
ይኸ ሁሉ የአብዮታዊ ሰደድ አቋም ምንኛ አብዮታዊ ነበር! ታዲያ ምን ይሆናል! ይኸን ሁሉ የአብዮት ሂደት ተቀብሎ የነበረው ለሱ የሥልጣን ባቋራጭ መቋመጥ ያመቸው መስሎት ነበር። ይኸንን ዓላማ ሲያሳድድ የወዝአደር ፓርቲ ብሎ የሚሰይመውን የፀረ ሕዝብ ጉሮኖ ሲገነባ እንኳን “የውጭ” ተራማጆችን ቀርቶ በራሱ በሰደድ ውስጥ የነበሩት ዲሞክራቶችና አገር ወዳዶችን አሠረ፣ ረሸነ። ጠቅላላውን ተራማጅ ሰፈር በፊታውራሪነት አዳከመ። ሰደድ ራሱ ከላይ የጠቀስነው የነለገሠ አስፋው ክሊክ መጫወቻ ሆኖ ፈራረሰ። ደርግን አፍርሶ ሥልጣን የሚይዘው በነለገሠ አስፋው ጥንስስነት የሚቋቋመው “የወዝአደር ፓርቲ” ሳይሆን በራሱ “በአብዮታዊው ደርግ” በሚቋቋመው አድሃሪው ቢሮክራሲው ሞግዚትነት በሚንቀሳቀሰው ሌላ “ማዕከል” ነው ተባለ። በአብዮታችንና በእናት አገራችን ብሄራዊ ክብር ጣረሞት ላይ በቀኝ ኃይሎች ህብረት ውስጥ የሚካሄደው የሥልጣን ግብግብና መራኮት አንዱ ዙር በነለገሠ አስፋው መዳከም አከተመ። ገና ብዙ እናያለን። ዝቅ ብለን እንደምናሳየው ይኸንን ክሊክ የተዋጉት የለየላቸው አድሃሪዎች ብቻ አይደሉም። ከደርግ ከራሱ ውስጥ አንስቶ ይኸ ክሊክ ፀረ ዲሞክራሲን ለማንገሥ ባሳየው ፊታውራሪነትና ብሄራዊ ክብራችንን ለመሸጥ ባሳየው ደላላነትና ገሀድ እየሆነ በመጣው ትምክህተኝነቱ የተነሣ የተቆጡ ዲሞክራቶችና አገር ወዳዶችም በዚህ ትግል ተሳትፈዋል። በተጨማሪ ደግሞ የክሊኩ ሥልጣን ታጋፊነትና ተቀናቃኝነት ያሳሰባቸው ክፍሎችም በዚህ ዘመቻ ተሳትፈዋል። ስለሆነም በነዚህ በተሰበጣጠሩ ኃይሎች መሃከል ከለገሠ አስፋው ክሊክ ባሻገር ሌላ ትግል ዙር በቅርቡ እንደሚጠብቀን ለመተንበይ አያስቸግርም። የተራማጆች ተግባር የሚታለመው ከዚህ አዲስና የተወሳሰበ ሁኔታ በመነሳት ነው።
ክፍል ሁለት፡ አዲሱ ሁኔታና የተራማጆች ተግባር
የዛሬውን አያደርገውና አብዮታዊ ሰደድ እነመኢሶንን ውሃ በልቷቸዋል፣ የቀረነው እኛ ብቻ ነን እያለ የደነፋበት ወቅት በዚህ በወዝአደሩ ፓርቲ አመሰራረት ጉዳይ እኛ “ቀኞቹ” ስለምናስተጋባው አቋም እንደሚከተለው ጽፎ ነበር።
“አብዛኛውን ጊዜ ቀኞቹ የሚናገሩት እና የሚሰሩት፣ የሚጽፉትና ወደ ተግባር የሚተረጉሙት ሁሉ ለየቅሉ ነው። በተለይም የወዛደሩን ፓርቲ ጥያቄ በሚመለከተው ጉዳይ ደበስባሳና ሙልጨልጭ ያለ አቋም መውሰድ እና በተለያዩ ጊዜያት በልዩ ልዩ ፅሁፎቻቸው እንደእስስት የሚቀያየሩ መንደርደሪያዎች እንደ ነበራቸው የቀኞቹን ልሳን የተከታተለ ሀቀኛ ተራማጅ ሁሉ በትክክል ሊገነዘበው ይገባል።” አ.ሰ. ቁ. 17 ታህሳስ 1971።
የኛ “ግራዎችስ”! ሁለት አመት ሙሉ “በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ የወዛደር ፓርቲ በድርጅቶች ውህደት ይፈጠራል።” እያሉ እንዳላስተጋቡ ሁሉ ዛሬ ደግሞ በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ይኸው የውህደት ቲዎሪ እንደማይሰራ ሲያበስሩልን በህብረት ድምፃቸው ቁጥር 5 ላይ “… በውህደት ስም ድርጅቶችን እንዳሉ በማገጣጠምና በውክልና /ኮታ/ የወዛደሩን ፓርቲ ለመፍጠር የማይቻል መሆኑን” አመልክቶ “በማርክሲዝም ሌኒኒዝም ርዕዮተዓለም የታጠቁትን እውነተኛ ታጋዮች ማዋሃድ” አስፈላጊ መሆኑን በዚያው ባስለመዱን ድንፋታ አስታወቁን።
ሁለት አመት “ኢማሌድህ አማራጭ የሌለው ብቸኛ የወዛደሩ ፓርቲ ጥንስስ ነው” ሲባልና ሲደነፋ ተከረመና ዛሬ ደግሞ ይህ ጥንስስ ፈረሶ ሌላ መቋቋሙን “የህብረት ድምጽ” “ፓርቲውን ለመፍጠር በቅድሚያ በአብዮታዊ ችሎታቸውና አስተዋጽዋቸው፣/ሜሪት/፣ ከኢማሌድህ አባል ድርጅቶችና መመዘኛውን የሚያሟሉ ከተገኙ ከአባል ድርጅቶች ውጭ የሚገቡበት ማዕከል መመስረት” አስፈላጊ እንደሆነ በመግለጽ አብስሮልናል። (የህብረት ድምጽ ቁጥር 6 ስለዚሁ ጉዳይ የተረከልንን ሌላ ጊዜ እንመጣበታለን።)
በመሀል ደግሞ የወዛደሩ ፓርቲ መፈጠር ጉዳይ ሲነሳ “አመቺ ሁኔታን ከመፍጠር አልፎ ሌላ ጉዳይ ውስጥ መፈትፈት የለበትም” ይባል የነበረው ንዑስ ከበርቴ ከየት መጣ ሳይባል “አብዮቱ ከተቀጣጠለበት ጊዜ ጀምሮ እስካሁንም ቢሆን ማዕከል እንደነበረው፣ ይህም ማዕከል ጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ እንደሆነና እሱም አብዮታዊ መሆኑን….” ስምምነት የተደረሰ መሆኑ ተነገረ!
በአጭሩ ምን ለማለት ነው የሚፈልገው? በኢማሌድህ ውስጥ አብዮታዊ ሰደድ፣ በአብዮታዊ ሰደድ ውስጥ የነለገሰ አስፋው ክሊክ አይሎ ራሱን ወዛደር ፓርቲ ሊለውጥና የደርግን ስልጣን አፍርሶ ስልጣን ለመያዝ ሲቋምጥ ፓርቲም ብቻህን አትሆንም፣ ደርግንም ብቻህን አፍርሰህ አትተካም ተባለ ለማለት ነው። በሁለቱም አንጻር የሰደድ የሥልጣን ሞኖፖል ህልም ቢያንስ ለጊዜው ውሃ ገባ ማለት ነው።
አብዮታዊ ሰደድ ስለ ወዛደር ፓርቲ መመስረት ጉዳይ እንግዲህ እንዲህ አይነት “እንደ እስስት የሚቀያየር” “ሙልጭልጭ” ያለ አቋም ለመውሰድ ያስገደደው ምንድን ነው? ራሱን ለማፍረስ “የተስማማው” ለምንድን ነው? ወዶ አይደለም ተገዶ ነው።
ከሁሉ በፊት በአብዮታዊ ሰደድ ውስጥ እያየለ የመጣው የነለገሠ አስፋው ክሊክ ዛሬ በጠቅላላው በኢትዮጵያ ሕዝብ በተለይ ደግሞ በማርክሲስቶች፣ በዲሞክራትና አገር ወዳድ ኃይሎች ጨርሶ የተተፋ ክሊክ ነው። ዋና ድካሙ ይህ መተፋቱ ነው። በፊታውራሪነት ያካሄደው ፀረ ሕዝብ ትግል ለአብዮቱ ሰፈር መዳከም ለፀረ አብዮት ማየል ያደረገውን እርኩስ አስተዋጽኦ ዛሬ በመክፈል ላይ ነው።
ነገር ግን ዛሬ አብዮታዊ ሰደድን ያፈረሱት ኃይሎች የተሰበጣጠሩ ኃይሎች እንደሆኑ መገንዘብ ያስፈልጋል። የኢትዮጵያ ማርክሲስቶች፣ ዲሞክራቶችና አገር ወዳዶች በዚህ ክሊክ ላይ ባላቸው ጥላቻ ታውረው አዲሱን የኃይል አሰላለፍ ከመመዘንና አደጋዎቹን ከማጤን መቆጠብ የለባቸውም።
ዛሬ ይህንን በሕዝብ የተተፋ ክሊክ ተረባርበው ያፈራረሱት ኃይሎች ውስጥ ከሁሉ በፊት እልም ያሉ ፀረ አብዮት ኃይሎች አሉ። እነዚህ ኃይሎች በተለይ ደግሞ አድሃሪው ቢሮክራሲ የአብዮታዊ ሰደድ ክሊክንም ሆነ ሌሎችን ዛሬ በአዋጅ የፈረሱትን አድርባይ ድርጅቶች በፊታውራሪነትና በመሳርያነት ከተጠቀመባቸው በኋላ ተመጦ እንዳለቀ ሎሚ እንደሚጥላቸው ደጋግመን “የተነበይ ነው” ነገር ነው። ለአድሃሪው ቢሮክራሲ ዛሬ እነዚህ ንዑስ ከበርቴዎች ታሪካዊ ሚና አክትሟል። ስለሆነም ጠራርጎ ሊጥላቸው ይፈልጋል። ዛሬ አድርባይ ድርጅቶች ሁሉ በተለይ ደግሞ የነለገሠ አስፋው ክሊክ እንዲፈርስ ያዘዘው ዋና ኃይል ይህ አድሃሪ ቢሮክራሲ ነው።
አድሃሪው ቢሮክራሲ የነለገሠ አስፋውን ክሊክ ለመደመሰስ እና በሱ በራሱ ቁጥጥር ስር ፓርቲውን ለመመስረት ሲነሳ እነሱን አፍርሶ ይበልጥ አገር ወዳድ ይሆናል፣ እነሱን አፍርሶ ያነሰ ትምክሕተኛ ይሆናል ማለት የለየለት የዋህነት ነው። አድሃሪው ቢሮክራሲ በነለገሠ አስፋው ክሊክ ላይ የተነሳው ይህ ክሊክ ፀረ ዴሞክራሲ ስለሆነ ሳይሆን ስልጣንን ለመጠቅለል ስለፈለገ ነው። አድሃሪው ቢሮክራሲ የነለገሠን “የቅምጥ መንግሥት” ፖለቲካ ቢቃወምና በውጭ ፖለቲካው በአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም እግር የገባውን ሌላ ኃያል መንግሥት ቢፃረር፣ ሀገራችንን የሃቀኛ ገለልተኛ ፖለቲካ እና የብሄራዊ ነፃነት መስመር ለማስያዝ አይደለም። እሱ ደግሞ የእናት ሀገራችንን ክብር ለአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም ለመሸጥ ነው። በአጭሩ በዚህ በኩል የአድሃሪው ቢሮክራሲ ማየል በምንም ዓይነት የኢትዮጵያን ዲሞክራቶችና አገርወዳዶች የሚያዝናና ሁኔታ አያመጣም።
ነገር ግን የነለገሠ አስፋውን ክሊክ ያፈረሰው ኃይል ውስጡ ሌሎችም ኃይሎች አሉ። በሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን/ት ለቆሙለት የዲሞክራሲ፣ የብሔራዊ ነፃነትና የብሄረሰቦች እኩልነት ቆመው፤ ይህ ክሊክ የተከተለውን የጭፍጨፋ ፣የፀረ ዲሞክራሲ፣ የፀረ ኢትዮጵያ ክብር፣ የፀረ ወዛደር፣ ፀረ ወጣት፣ የፀረ ምሁር፣ የፀረ ጭቁን ብሔረሰቦች ፖለቲካ በመቃወም የታገሉ ዲሞክራቶችና ሀገር ወዳዶች አሉ። እነዚህ ኃይሎች ከደርግ ከራሱ ውስጥ አንስቶ በሌሎችም የስልጣን አውታሮች፣ በተረፉት ሕዝባዊ ድርጅቶች ወዘተ. ቢገኙም እጅግ እየተዳከሙ ስለመጡ የረባ ቅንብር የሌላቸው ኃይሎች ናቸው። ምንም እንኳን ዛሬ በሀገሪቱ በሰፈነው ፀረ ዴሞክራሲ ጨለማ ያልተቆጣ፣ በሀገራችን ክብር መደፈር ያልበገነ፣ በነዚያ ሁሉ ታጋይ ደም አብቦ የነበረው አብዮታችን መቀልበስ ያላረረ ሀቀኛ ኢትዮጵያዊ ባይኖርም እነዚህ ዲሞክራቶችና አገር ወዳዶች አሁን ባሉበት ሁኔታ ይህንን ሁሉ ኃይል አስተባብሮ ፀረ አብዮትን ለመቋቋም ገና እጅግ እንደሚያስቸግራቸው ግልጽ ነው።
ከዚህ የተወሳሰበ ሁኔታ በመነሳት መኢሶን ለኢትዮጵያ ተራማጆች የሚጠቁመው ነገር ምንድነው?
1ኛ/ ይህ የተፈጠረው አዲሱ ሁኔታ ባለፈው የሰሕድ ቁጥር ያደረግነውን “የትግል አንድነት ጥሪ” ይበልጥ አጣዳፊ አደረገው እንጂ በምንም ዓይነት አይለውጠውም። ስለሆነም መኢሶን በሰፊው ሕዝብ ድምጽ ቁጥር 69 ላይ ለኢትዮጵያ ማርክሲስት ሌኒኒስቶች፣ ዲሞክራቶችና አገር ወዳዶች ያደረገላቸው ጥሪ ያድስላቸዋል።
2ኛ/ የኢትዮጵያ ማርክሲስት ሌኒኒስቶችን ከከሳሪው ኢማሌድህ ይፈልቃል ተብሎ የነበረውን የዘይድ ባሬን አይነቱን ፀረ ወዛደር ፓርቲ እንደማይቀበሉት አስታውቀው ነበር። በዚያው በከሳራ ፖለቲካ ላይ፣ በአድሃሪው ቢሮክራሲ ቁጥጥር ስር በአዋጅ ይፈጠራል የተባለውና ከአዲሱ መአከል ይፈልቃል የተባለውን “የወዛደር ፓርቲ” አይቀበሉትም። ሌላ “የክርስትና ስም” ሰጡት አልሰጡት መሰረታዊውን ነገርም አይለወጠውም። ከዚህም በመነሳት ለሀቀኛ የወዛደሮች ፓርቲ ከዚህ መንግሥት የምልመላ ቢሮ ውጪ የሚካሄዱትን ትግል ያለአንዳች ማወላወል ይቀጥላሉ።
3ኛ/ በአድሃሪው ቢሮክራሲ ትእዛዝ፣ ታሪክ በተፋቸው የአድርባይ ድርጅቶች መሪዎች አጎብዳጅነት እንዲፈርሱ በተበየነባቸው በአብዮታዊ ሰደድ፣ በወዝ ሊግ፣ በማሌሪድ ውስጥ የሚገኙ ሀቀኛ አብዮታዊያን ይህንን ትዕዛዝ እንዳይቀበሉ፣ በአዋጅ እንዳልተቋቋሙ ሁሉ በአዋጅ የማይፈርሱ መሆናቸውን አብስረው፣ ካለፈው ኪሳራ አስፈላጊውን ትምህርት ቀስመው ለኢትዮጵያ ወዛደሮች ፓርቲ መፈጠር የሚያካሄዱትን ትግል ከሃቀኛ ማርክሲስት ሌኒኒስቶች ጋር ለማስተባበር እንዲገፉበት መኢሶን ጥሪ ያደረግላቸዋል።
4ኛ/ በዚህ በተወሳሰበ ሁኔታ ውስጥ የነለገሠ አስፋው ክሊክ ለአድሃሪያን ፊታውራሪ ሆኖ በተጫወተው አሳፋሪ
ሚና በመታወር ተራማጆች አዲሱ ሁኔታ የሚፈጥረውን አደጋ ከማጤን እንዳይቆጠቡ፣ በያለበት የህቡዕ አሰራር ስልታቸውን እንዲያቀናብሩ እና የህቡዕ መዋቅሮችን አጠናክረው እንዲራመዱ ጥሪ ያደርግላቸዋል።
5ኛ/ በከሣራው ኢማሌድህ መፍረስ ውስጥ የነለገሠ አስፋው ክሊክ ፀረ ዴሞክራሲና ፀረ አብዮታዊያን ፖለቲካ በመቃወም ተነሳስተው ሚና የተጫወቱ ማርክሲስቶች፣ ዲሞክራቶች አገር ወዳዶች ሁሉ በነሱና በለየላቸው አድሃሪዎች መካከል ያሉት ልዩነቶች እየተጧጧፈ እንደሚመጡ በመገንዘብ ብሔራዊ ዲሞክራሲያዊ አብዮት መድረክ ላይ ከሌሎች ተራማጆችና ከሰፊው ሕዝብ ጋር የትግል አንድነታቸውን እንዲያጠናክሩ መኢሶን ጥሪ ያደርግላቸዋል።
===========================================
-ይቀጥላል-