ሰሕድ ቁ. 71

የሰፊው ሕዝብ ድምፅ

ቁጥር 71፣      ህዳር 30፣ 1972

የፅሁፉ ፍሬ ሀሳብ

ይህ እትም የሰፊው ሕዝብ ድምፅ ቁጥር 70 ተከታይ (ሁለተኛ ክፍል) ነው። በዚህኛው እትም መኢሶን የወዛደሩ ፓርቲ በግለሰቦች ውህደት ይፈጠራል በማለት ኢማሌድህ የሚያሰራጨውን የተሳሳተ አስተሳሰብ ይተቻል። እንዲሁም፣ በተለያዩ መድረኮች፣ በኢማሌድህ መመስረቻ ሰንዶች ላይ ሳይቀር የሰፈረው መርኅ እንደተጣሰ፣ ምሳሌዎች እየጠቀሰ  ያጋልጣል። በመቀጠልም የወዛደሩ ፓርቲ የሚመሰረተው ከወዛደሩ ጋር የተዋሃዱ ሃቀኛ ማርክሲስት ሌኒኒንት ቡድኖች በሚፈጥሩት የድርጅት ጥምረት እንደሆነ አስታውሶ፣ ይህንን ፓርቲ በአቋራጭ ለመፍጠር የሚደረገው  ግርግር ከወዛደሩ ቀድሞ የአድሃሪያንን ፓርቲ ለመፍጠር የሚደረግ ሩጫ እንደሆነ ያስገነዝባል።  

የሰፊው ሕዝብ ድምፅ

ለሰፊው ሕዝብ ሰራተኛ ገበሬ፣ ነጋዴ፣ ወታደር፣ ምሁር መብትና ጥቅም የሚታገል ጋዜጣ

የኢትዮጵያ ሰፊ ሕዝብ ይቅደም

ቁጥር 71                                                                     ቀን 30/3/72

 

ኢማሌድህ፣ ከአብዮታዊ መዓከል

ወደ ፀረ አብዮት መዓከል

ባለፈው ቁጥራችን ኢማሌድህ ከህብረት ወደ ክስረት ስላደረገው ጉዞ አትተናል። በዕትሙ ውስጥ ኢማሌድህ የተመሠረተበትን የኘሮግራምና የመርሃ ግብር መድረክ ከከዳ በኋላ፣ ድርጅታዊ ክስረት ደርሶበት ምንሽርሽሩ ቢወጣ ምንም አንደማያስደንቅ ገልፀን ነበር። አንደዚያ የከሰረው ኢማሌድህ፣ የወዝአደሩን ፓርቲ ለመመሥረት ብቃትና ጥራት ያለው አብዮታዊ መዓከል መሆኑ ያከተመው፣ ኢማሌድህ ከተመሠረተበት ፕሮግራምና መርሃግብር መንሽራተት በጀመረበት ጊዜ ነው። ታዲያ ከዚሁ ጊዜ ጀምሮ ደጋግመን እንዳልነው ደግሞ፣ ኢማሌድህ ይዞት በነበረው የክስረት ጐዳና ቀጥሎ፣ ወደ ውህደት ተሸጋገርኩኝ፣ “የሠራተኛ ፓርቲ” ተመሠረተ ቢል ኑሮ እንኳን፣ የኢትዮጵያ አብዮታዊያንና ግንባር ቀደም ወዝአደሮች አቋም ግልፅ ነበር። ከኪሳራ “ሕብረት” የሚፈልቀውን ኪሳራ “የሠራተኛ ፓርቲ” በምንም ዓይነት አንደማይቀበሉት ደጋግመው ያስታወቁት ጉዳይ ነበር።

ብቻ አንዱ አሳዛኝ ፈሊጥ ካለቀለት በኋላ፣ ሌላ የባሰ አሳዛኝና ምስኪን ፈሊጥ መስማት የተደጋገመው ልምዳችን የሆነው እና የኢትዮጵያ አብዮታዊያንና ግንባር ቀደም ወዝአደሮች፣ አሁን ደግሞ “አብዮታዊ መዕከል” ከአንግዲህ በግለሰብ “ኮሚኒስቶች” ውህደት “አንደሚለመልምና አንደሚያብብ” ሰማን። በዚህ ያገባኛል የሚለውም ሁሉ፣ ከአንድ “ኮሚሽን” ከተባለ ስመ ጥሩ የማጣሪያና የምልመላ ቢሮ አየሄደ አንዲጣራ ሰፊው ሕዝብም፣ “ኢማሌድህ ጥንስሱ ሳይፈላ ተደፋ” እያለ ገና በመተቸት ላይ ነበር። አሁን ግን፣ “አሱን ተወው፣ ሌላ ጥንስስ አየተቦካ ነው” ተብሎ ተነገሮታል።  ያባቶቸ ተረት ትዝ እያለው፣ “ግሩም ጥንስስ ሳይከካ ተቦካ” እያለ ነው።

እስቲ ደግሞ ይሄንን “አብዮታዊ” መዓከል እንመልከተው። ለዛሬው “በህብረት ደምጽ” መጽሔት ቁጥር አምስትና ስድስት ላይ ብቻ ተወስነን እንቀጥላለን። ይሁን እንጅ ወደሃተታው ከመግባታቸን በፊት ደግሞ፣ አንባቢው ከዚሁ መጽሔት ወስደንና በተራ ቁጥር እየለየን ከዚህ በታች የምንጠቅሳቸውን አቋሞች ልብ ብሎ ይመልከታቸውና የራሱን ፍርድ ይስጥ።

1/ ስለ “ህብረት”

ሀ. “የህብረቱ” አባሎች ሆነው የቀሩት ሦስቱ

“ማርክሲስት ሌኒኒስት ድርጅቶች/ ማሌሪድ፣ ሰደድና የወዝ ሊግ/ እስካሁን በርካታ የአብዮቱን ግንባር ቀደም ጥያቄዎች አበጥረውና አንጠርጥረው በመመርመር የሚያመረቁ የአንድነት አቋሞች ላይ ለመድረስ አስችሏቸዋል።” /ህብረት ድምፅ ቁ.4 ገፅ 32፣ ሚያዚያ 1970/።

“የዛሬው የህብረቱ የጋራ መግለጫ የህብረቱን እድገትና ጥንካሬ…. የህብረቱ አባሎች የሆኑትን የሦስቱን ማርክሲስት ሌኒኒስት ድርጅቶች /ማሌሪድ፣ ሰደድና ሊግ/ የርዕዮተዓለም አንድነት የሚያረጋግጥ ነው።” /የመሸጋገሪያ ወቅት የጋራ መግለጫና የድርጊት ፕሮግራም፣ ሰኔ 1970/

ለ. “ይህ በጎ አዝማሚያ ሲሆን፣ በዚያው ሰሞን ኢማሌድህ ውስጥ አንድ ያልተጠበቀ /?/ አዲስ ሁኔታ /?/ ተከሰተ። . . . አድሃሪያን በድርጅቶች ውስጥ በገፍ ተሰግስገው አብዮታዊያንን ለማመስ እድል በማግኘታቸው የውህደት ጉዳይ እየመነመነ መምጣቱ በተጨባጭ ታይቷል።” / “የህብረት ድምፅ” ቁ.5 ገፅ 13፣16፣ የካቲት 1971/

2/ ስለ መዓከል

ሀ. “የአብዮታችንን ሂደት ስንገመግመው፣ ትግላችን ዛሬም የሚጎድለው አብይና ወሳኝ ነገር አለ። ዛሬም በአንድ አስተማማኝ ዘላቂ መዓከል ለመመራት አልበቃም።” / “የህብረት ድምፅ” ቁ.5፣ ገፅ 4 የካቲት 1971/

ለ. “ለአብዮቱ አንድ መዓከል ማስገኘት አማራጭ የሌለው መሆኑን በመገንዘብ ኢማሊድህን መሥርተዋል።” / “የህብረት ድምፅ” ቁ.5፣ ገፅ 14፣ የካቲት 1971/

ሐ. “ወሳኝ በመሆኑ ጥያቄዎች ላይ ስምምነት ተደርሷል። እነዚህም. . . 2ኛ/ አብዮቱ ከተቀጣጠለበት ጊዜ ጀምሮ እስካሁንም መዓከል እንደነበረው፣ ይህም መዓከል ጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ እንደነበርና እሱም አብዮታዊ መሆኑን” / “የህብረት ድምፅ” ቁ.5፣ ገፅ 16፣ የካቲት 1971/

3/ ስለወዛደሩ ፓርቲ አፈጣጠር

ሀ. “ሰፊው ሕዝብ አስተማማኝ መሪ የወዝአደሩ ፓርቲ ይመሥረት ይላል። የዚህም ግንባር ቀደም መሪ ዕውን መሆኛ ብቸኛ ዘዴ በአገሪቱ ያሉት ማርክሲስት ሌኒኒስት ድርጅቶች ሕብረት መፈጠርና በትግል መዋሃድ መሆኑንም ጠንቅቆ በማወቁ ያለአንዳች መተካት “ኢማሌድህ ይጠንክር” እያለ ያስተጋባል። /“የህብረት ድምፅ” ቁ.4፣ ገጽ 31-32፣ ሚያዚያ 1970/

ለ. “የወዛደሩን ፓርቲ ለመፍጠር “ብቸኛው ዘዴ” በአገሪቱ ያሉትን ማርክሲስት ሌኒኒስት ድርጅቶች ህብረት መፍጠርና በትግል ማዋሃድ ሳይሆን፣ በማርክሲዝም ሌኒኒዝም ርዕዮተዓለም የታጠቁትን እውነተኛ ታጋዮች በማዋሃድ ነው” /“የህብረት ድምጽ” ቁ.5፣ ገጽ 16፣ የካቲት 1971/

እዚሁ ላይ እናቁመው። ከከሣራው ኢማሌድህ ጽሑፎች ውስጥ እንዲሁ እንደዚሁ እያልን መዓት እርስ በራሳቸው የሚቃረኑ አቋሞችን ልንጠቅስ እንችላለን። እነዚህኞቹማ ውልክፍክፋቸው የሚወጣው ከመስመር መስመር ነው። ለኛም መጥኔውን ይስጠን እንጂ፣ የፖለቲካ ክሥረት የተጠናወተው ድርጅት አንዲሁ “ኑሮ” ብሎ የያዘውን ቅዠት የሚገፋው አየተጠነጋገረ ነው። ይሁንና፣ ታዲያ ምን ፍርድ እንስጠው?

“አብዛኛውን ጊዜ ቀኞች የሚናገሩትና የሚሠሩት፣ የሚፅፉትና ወደ ተግባር የሚተረጉሙት ሁሉ ለየቅሉ ነው። በተለይም የወዝአደሩን ፓርቲ ጥያቄ በሚመለከተው ጉዳይ ላይ ደበስባሳና ሙልጭልጭ ያለ አቋም መውሰድና በተለያዩ ጊዜያት በልዩ ልዩ ጽሑፍቻቸው አንደ እስስት የሚቀያየሩ መንደርደሪያዎች አንደነበራቸው የቀኞችን ልሳን የተከታተለ ሃቀኛ ተራማጅ ሁሉ በትክክል ሊገነዘበው ይገባል።”

አንባቢው “መኢሶን ደግሞ ይሄንን የጻፈው መቼ ነው?” ብሎ ይጠይቅ ይሆናል። የለም ይህንን የጻፈው መኢሶን አይደለም። የነዚህ የብልህ አረፍተ ነገሮች ባለቤት አብዮታዊ ሰደድ ቁ.17 ነው። ታዲያ አብዮታዊ ሰደዱ ይህንን የፃፈው “ቀኝ መንገደኛውን” መኢሶንን ለማጋለጥ በማለት ነበር። ብቻ አኛም ብንሆን ምንም አንጨምርበትም። አንባቢው ከዚህ በላይ ከኢማሌድህ ጽሑፍች ውስጥ የጠቀስናቸውን አንደገና ተመልሶ አንዲመለከታቸውና አንዲያነፃፅራቸው በድጋሚ ጋብዘነው አናልፋለን። ብቻ፣ እዚሁ ላይ ደግሞ፣ ከኢትዮጵያ ማርክሲስት ሌኒኒስቶች የትግል ታሪክ ውስጥ አንድ የርዕዮተ ዓለም ግብ ግብ ምዕራፍ ትዝ አለንና፣ በማርክሲዝም ሌኒኒዝም የሚነግዱ አድርባይ ኃይሎች አንደምን እንደ ሁለት ጠብታ ውሃ አንደሚመሳሰሱ ስንመዘግብ እጅግ መደነቃችንም እንዳልቀረ አንባቢን ሳናስታውሰው አናልፍም።

በ1966 ዓ.ም. ነው። አንድ የኢህአፓ ግልገል ድርጅት ሆኖ በውጭ ሃገር የተቋቋመ “ፌደሬሽን” የሚባል ትርምስምስ ደርጅት ነበር። ይሄም ድርጅት “ቡሌቲን” የተባለ ጋዜጣ ያወጣ ነበር። ታዲያ፣ ስምንት የሚሆኑ “የቡሌቲን” ጋዜጣውን እትም ያወጣል። በዓመቱ መጨረሻ ላይ በአውሮፓ የኢትዮጵያ ተማሪዎች ማህበር ጉባኤ ተደረገና፣ የማህበሩ ሃቀኛ ታጋዮች “የቡሌቲንን” ጋዜጣ ቁጥር በቁጥር እየወሰዱ፦ “ቁጥር 1 እንደዚህ ብሎ ነበር፣ ቁጥር ሁለት ደግሞ እንደዚህ ይላል፣ ቁጥር ሦስት ደግሞ. . .” እያሉ በየእትሙ የተለያዩ አቋሞችን እንደወሰደ በማጋለጥ ግንጥልጥሉን ሲያወጡት፣ አንዱ ነገሩ የገባው ከመሃል ብድግ አለና፣ “ምን ቁጥር አንድ ቁጥር ሁለት አንላለን አቋም አንዱ አቋም ሁለት . . . እንበል እንጂ” በማለት ተችቶ፣ ሰዉን ሁሉ በሳቅ ጨረሰው። እኛም ዛሬ፣ “የህብረት ድምጽ” ቁጥሮች ስናገላብጥ፣ ምን “ቁጥር” አስጠቀሰን፣ አቋም አንድ አቋም ሁለት እንበል እንጅ ማለታችን አልቀረም። አዎን በማርክሲዝም የሚነግዱ አድርባዮች ምንጊዜም አንደዚሁ ናቸው።

ደግሞስ ካርል ማርክስ የቱን ያህል ዕውነት አለው? ካንድ ቦታ ላይ እንዲህ ይላል፦

“ታሪክ ራሱን ይደግማል ሲል ሄግል ዕውነት አለው። ይሁንና ሄጌል የረሳው ነገር ታሪክ ራሱን ሲደግም ለመጀመሪያው ጊዜ አንደአሳዛኝ ድራማ ነው። ለሁለተኛው ጊዜ ደግሞ አንደ አስቂኘና መሳለቂያ ትርዒት ነው።”

ይልቁና እኛ አሁን፣ ምንጊዜም ወዳልተድበሰበሰውና ወዳልተሙለጨለጨው አቋማችን እንመለስና ደጋግመን ያልነውና የፀና አቋማችንን አንደገና እንግለፀው። ስንት መዓት ጓዶቻችንን የሰዋንበትን አቋማችንን እንደገና እንግለፀው።

የወዝአደሩ ፓርቲ አንደዚሁ በአቦ ሰጡኝ የሚፈጠርና የሚሰየም ነገር አይደለም። የታወቁና አጠቃላይ የሆኑ ጠባዮች አሉት። አጠቃላይ የሆኑ የአመሠራረት ሂደቶች አሉት። ፓርቲው በፖለቲካ ብስለቱና ንቃቱ የመጠቀና የላቀ የወዝአደሩ ግንባር ቀደም መሪ ድርጅት ነው። የሚያስተሳስረውና የሚያቅፈው በትግል ልምዳቸውና በንቃታቸው፣ በአብዮታዊ ወኔያቸውና በተለይም የግል ጥቅማቸውን ክደው ለወዝአደሩና ለጠቅላላው ጭቁን ሕዝብ ቆመው በግንባር ቀደምትነት ለመታገል ባላቸው ዓላማ፣ ፍላጐትና ችሎታ የፀኑትን ማርክሲስት ሌኒኒስቶች ነው። አንደዚሁም በሚያሳዩት ዲሲፕሊን ሁሉ ልቀውና መጥቀው የሚገኙትን፣ በታጋይነታቸውና በታታሪነታቸው፣ በሃቀኝነታቸውና በአብዮታዊ ትህትናቸው ከሰፊው ሕዝብ ጋር የተዋሃዱትን፣ የሰፊውን ሕዝብ አክብሮት፣ ድጋፍና ተደማጭነት ያገኙትን አብዮታዊያን ነው። አዎን “የሚናገሩትና የሚሠሩት፣ የሚጽፉትና ወደ ተግባር የሚተረጉሙት ሁሉ ለየቅሉ” ሲሆን “በተለይም የወዝ አደሩን ፓርቲ ጥያቄ በሚመለከተው ጉዳይ ላይ ደበስባሳና ሙልጭልጭ ያለ አቋም” ሲወስዱ፣ “በተለያዩ ጊዜያት አንደ እስስት የሚቀያየሩ መንደርደሪያዎች” ሲኖራቸው፣ የዚህ ቢጤዎቹ “የሠርቶ አደሩን ፓርቲ” የሚያክል ነገር እንኳን ለመመሥረት “ለመጠንሰስም” አንደማይበቁ የዚያኑ ያህል ዕውነት ነው።

አንደዕውነቱም ከሆነ፣ በዚህ የወዝአደሩ ፓርቲ መሠረታዊ ጠባዮች ላይ በዙም መቆየት አያስፈልገንም። ይህ ጉዳይ ባለፉት ዓመታት ውስጥ በሰፊው ተብራርቷል፣ ተገልጿል። የኢትዮጵያ አብዮት በአፍላነት ይገሰገስ በነበረበት ወቅት፣ በሕጋዊ መድረኮች ላይ ይወጡ የነበሩትን “የአብዮታዊት ኢትዮጵያን” መጽሔት ቁጥሮች፣ የሕዝብ ደርጅት ጉዳይ ጊዜያዊ ጽ/ቤትና የፖለቲካ ት/ቤት ያቀርቧቸው የነበሩትን የጥናትና የምርምር ጽሑፎች፣ አዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ ይታተሙ የነበሩትን ክርክሮችና ውይይቶች፣ “በአዲስ ፋና” መጽሔት ላይ ይወጡ የነበሩት ጽሑፎች፣ “ዓለም አቀፍ አሳታሚዎች” ያሳተሟቸውን ጽሑፎች፣ አዎን ከነዚም ባሻገር ኢማሌድህ ራሱ የተመሠረተበትን የጋራ መገለጫና መርሃ ግብር ዘወር ብሎ ማየት ብቻ ይበቃል አንላለን። በነዚህ መድረኮች ላይ የተደረጉት ገለጣዎች ዛሬም ህያውና ትክክል ስለሆኑ፣ አንባቢን ወደነሱ ጽሑፎች ጋብዘነው ለማለፍ እንችላለን።

የወዝአደሩን ፓርቲ አፈጣጠር በሚመለከተውም በኩል፣ አንደዚሁ በተደጋጋሚ የተገለጹ መሠረታዊ ሃቆች አሉ። የወዝአደሩ ፓርቲ ከወዝአደሩ የሞያ ንቅናቄና በሳይንሳዊ ሶሻሊዝም ከታነጹ አብዮታዊያን ዉህደት የሚወጣ ግንባር ቀደም ድርጅት ነው። ጥቂት ማርክሲዝም ሌኒኒዝምን የተቀበሉ “አብዮታዊያን ነን” ባዮች ተጠራርተው “የሠራተኛ መደብ ፓርቲ” አይሆኑም። የወዝአደሩ የሞያ  ንቅናቄ ብቻውን የወዝአደር ፓርቲን አይወልድም። ደግሞም መቼም “ለቸርነቱ ምንም አይሰነውምና”፣ ይህች ታሪከኛ ምድራችን ያበቀለቻቸው “ኮሙኒስቶች”፣ “የወዝአደሩን ፓርቲ በማርክሲስት ሌኒኒስት ድርጅቶች ህብረትና ውህደት ለመመሥረት እንደማይቻል ተደርሶበታል። ሳይንሳዊው ጎዳና ‘ታጋዮችን’ ማዋሃድ ነው አያሉ “ሳይንሱን” ሲያዥጎደጉዱት ለመስማት በቃን እንጂ፣ የወዝአደሩ መደብ ፓርቲ በዚህ የግለሰብ “ታጋዮች” ውህደት ሲመሠረት ሰምተንም ዓይተንም አናውቅም ነበር ።

በየትኛውም አገር አንደታየው፣ በዚህ የወዝአደር ፓርቲ አፈጣጠር ሂደት ውስጥ፣ በመጀመሪያ ብቅ ብቅ የሚሉት ማርክሲዝም ሌኒኒዝምን የተቀበሉ ትናንሸ ቡድኖችና ድርጅቶች ናቸው። እነዚህ ቡድኖች በመጀመሪያው ላይ ርዕየተ ዓለሙን ለማስፋፋት በተለያየ መንገዶች ይታገላሉ። አንደዚሁም፣ ከነርሱ ቀጥጥር ውጭ በሚካሄደውና በሚያድገው የወዝአደር የሙያ እንቅስቃሴ ውስጥ እየገቡ በወዝአደሩ የኢኮኖሚና የነፃነት ትገል ይሰተፋሉ።

የወዝአደሩን መደብ በተግባር ይዋሃዱታል። ቡድኖቹ ለየቅል  የሚያደራጁት እነርሱ ፈለገውት ሳይሆን፣ ከነርሱ ቁጥጥር ውጭ የሆኑ ሌሎቸ ነባራዊ ሁኔታዎች በመኖራቸው ነው። ያም ሆኖ ይህ፣ እነዚህ ለየቅል በነፃ የተደራጁት ድርጅቶች በትግሉ ሜዳ መተዋወቃቸው አይቀርም። ነገሩ ተፈጥሮዋዊ ስለሆነ፣ በመሃከላቸውም ታክቲክና እስትራቴጂን፣ የፖለቲካና የአይዲዮሎጂ ጥያቄዎችን በሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ የመሥመር ትግል እያካሄዱ ይተባበራሉ /ህብረት/። ከዚያም ይዋሃዱና /ውሀደት/ የወዝአደሩን ፓርቲ ይመሠርታሉ።

ነገር ግን “ህብረታቸው” ህብረት የሚሆነው፣ “ከውህደታቸውም” የሠራተኛ ፓርቲ የሚመነጨው በመካከላቸው ያለው ግንኙነት ሁሉ በእኩልነትና በዲሞክራሲ መርሆዎች ላይ ፀንቶ ሲገነባ ነው። ማንኛውም ተባባሪ ድርጅት የበላይነትና ማንአህሎኝነት ሳይሰማው፣ ለመተባበር ፈቃደኛ የሆኑትን  “ማርክሲስት ሌኒኒስት” ድርጅቶች ነፃ  ህልውና ሲቀበልና ሲያከብር ነው። አንደዚሁም የትኛውም ድርጅት ቢሆን፣ መሠረታዊ ስምምነት የተደረሰባቸውን መሠረታዊ አቋሞች፣ ጀንበር በጠለቀበት ቁጥር እየለወጠ “ከመሙለጭለጭና” ዓይን ካወጣ ክህደት ሲገታ ነው።

በነዚህ ማርክሲስት ሌኒኒስት መርሆዎች ላይ የተባበሩት ማርክሲስት ሌኒኒስቶች፣ ወደ ውህደት ተሸጋግረው የወዝአደሩ ፓርቲ በቀላሉና በእውነተኛ የአብዮታዊ ጓድነት መንፈስ ይመሠርቱታል። ከውህደታቸው ጋር በተያያዘም ሁኔታ፣ ከወዝአደሩና ከተቀሩት ጭቁኖች ትግል በግንባር ቀደምትነት በመዋሃዱ ይህንኑ ግንባር ቀደምትነታቸውን በተግባርና በተጨባጭ ኑሮዋቸው ሁሉ እያስመሰከሩ ይጎለምሳሉ። ይዳብራሉ። ከዚህ ውጭ ሌላ የወዝአደር ፓርቲ፣ ከዚህ ውጭ ሌላ የአፈጣጠር ሂደት ፀረ አብዮት አቋራጭ ነው።

ብቻ እኮ “ቀኞች” የሚናገሩትና የሚሠሩት፣ የሚፅፉትና ወደ ተግባር የሚተረጉሙት ሁሉ ለየቅሉ ሆኖ ነው እንጅ፣ ከዚህ በላይ ያልነውንማ እነሱም በ“ህብረት ድምጽ” ቁጥር 5 ላይ ከገጽ 14-15 ድረስ ሌኒንና ሆ ቺሚንን እየጠቀሱ አንደሚከተለው “ተናገረውና ጽፈው” ነበር፦

“ይህን በውህደት ፓርቲ የማስገኘት ስልት፣ የሌሎች አገሮች አብዮታዊያንም በአግባቡ ተጠቅመውበት ተግባር ላይ ያዋሉት በመሆኑ ትክክለኛነቱ የሚያጠራጥር አይደለም። ለምሳሌ በሩሲያ በ1903 የጠራ የወዝአደር ፓርቲ ለመመሥረት በሁለተኛው ጉባዔ ላይ የተገኙት የ26 ድርጅቶቸ ተወካዬች ነበሩ። ምንም እንኳን የድርጅቶቹ አቋም የተለያየና ውጥንቅጡ የወጣ ቢሆን፣ በታላቁ ሌኒንና በቁርጠኛ አብዮታዊያን ተጋድሎ በመጨረሻ የተፈለገውን ዓይነት አብዮታዊ ፓርቲ ለመመሥረት ተቸሏል።”

“በቪየትናምም እንደዚሁ በ1929 ገደማ ሦስት ኮሙኒስት ድርጅቶች ነበሩ። ነገር ግን በወቅቱ ከፈረንሳይ ቅኝ አገዛዝ አርነት ለመውጣት ይታገሉ የነበሩት ወዝአደሮችና ሌሎች አብዮታዊያን ኃይሎች፣ የግድ የአንድ መአከል አመራር ይሹ ነበር። ስለሆነም ሆ ቺሚን በኮሚኒስት ኢንተርናሽናል ተጠሪነቱ፣ የኮሙኒስት ድርጅቶች ተወካዮች ሰብስቦ ለአንድነት ትግል ከተካሄደ በኋላ፣ እ.ኤ.አ. የካቲት 1930 የቪየትናም ሕዝብ አለኝታ የሆነውና “የቪየትናም ሠራተኞች ፓርቲ” በመባል የሚታወቀው ፓርቲ ሕልውና አገኘ።”

እዚህ ላይ ምን ይጨመርበታል። ምኑንስ “ለማድበስበስ” ይቻላል? ወዴትስ “ለመሙለጭለጭ” ይቻላል? ሌኒንም ሆቺሚኒም እንዳሉትና እንዳደረጉት የወዛደሩ ፓርቲ የሚፈጠረው “በውህደትና” ለአንድነት በሚካሄድ ቅን፣ ሃቀኛ፣ ዲሞክራሲያዊና የእኩልነት ትግል ነው። ሆኖም፣ የኛዎቹ ብልህና አስተዋይ “ሌኒኒስቶች” ይህንን ሁሉ ከፃፉ በኋላ የሚደርሱበት መደምደሚያ ደግሞ፣ የሚከተለው አይን ያወጣ ሸፍጥ ነው። እናንበው፣

“የኢትዮጵያን አብዮት ልዩ ባሕሪ የተገነዘቡና ከአብዮቱ ወገን ቆመው የሚታገሉ የኢማሌድህ አባል ድርጅቶች /ሰደድ፣ ሊግ፣ ማሌሪድ/ የወዛደሩን ፓርቲ ለማስገኘት ድርጅትን ከድርጅት ጋር በጅምላ በማዋሃድ ሳይሆን፣ በማርክሲዝም ሌኒኒዝም ርዕዮተዓለም የታጠቁትን እውነተኛ ታጋዮች በማዋሃድ መሆኑን” አምነዋል። /“የህብረት ድምጽ” ቁ.5 ገፅ 16/

በዚህ “በጅምላ ማዋሃድ” በሚለው ጥያቄ ላይ ወደኋላ እንመለስበታለን። ከዚህ በላይ ለጠቀስነው አንቀጽ ግን የሚከተለውን ተናገረን ብቻ እንለፍ። በዕውነቱ፣ በኢማሌድህ አባል ድርጅትነት የቀሩት “ሦስቱ” ድርጅቶቸ ይህንን ድፍረት የተመላበትና ዓይን ያወጣ ሸፍጥ ሲፅፉ፣ ያለጥርጥር “ማንም የለብንም” በማለት ከፍተኛ የእብሪትና የንቀት መንፈስ አድሮባቸዋል። ያለጥርጥር ደግሞ፣ የኢትዮጵያን ዕውነተኛ ማርክሲስት ሌኒኒስቶች ገድለንና አስረን ጨርሰናል ብለው ተማምነዋል። ይህ ሁሉ ካልሆነ ደግሞ፣ ለሥልጣን፣ ለክብርና ሞገስ የተያያዙትን እሽቅድምድም የዕውር የድንብራቸውን ሊገፉበት ቆርጠዋል ማለት ነው። ሌላ ምንም ፍቺ ሊኖረው አይችልም። እኛም፣ አዲዮስ “መንገዱን ጨርቅ” አይሆንም ብለን እንተቻቸውና እንቀጥል።

ለመሆኑ ይሄ “የኢትዮጵያ አብዮት ልዩ ባህሪይ” እየተባለ የሚነገርለት ጉዳይ ምንድን ነው? በኢትዮጵያ የወዛደሩ ፓርቲ አፈጣጠር ሂደት እንዴት ነው?

የኢትዮጵያ የመጀመሪያ ማርክሲስት ሌኒኒስት ትውልድ የዛሬ አስራ አንድ ዓመት ወደ ሃቀኛ የወዝአደር ፓርቲ መመሥረት፣ ወደ እርግጠኛው የኢትዮጵያ ጭቁኖች ነፃ መውጣት የሚወስደውን የመጀመሪያውን የማርክሲስት ሌኒኒስት ድርጅት መሠረት ጥሎ፣ የመላ ኢትዮጵያ ሶሻሊስት ንቅናቄን አቋቋመ። ዛሬ በትግሉ መስክ ላይ በተሰውት በነጓድ ዶክተር ከበደ መንገሻ፣ በነጓድ ዳንኤል ታደሰ፣ በነጓድ ዶክተር ከድር መሃመድና በነጓድ መስፍን ካሡና በእሥር ተይዘው በመሳቀቅ ላይ በሚገኙት በነጓድ ኃይሌ ፊዳ አርቆ አስተዋይ አመራር ሥር፣ የኢትዮጵያን ወዝአደሮች ፓርቲ ለመመሥረት የሚያስፈለገው ሂደት በመኢሶን ኘሮግራም ላይ በትክክል ተተለመ። ሲፈጠር ጀምሮ ከአቅም በላይ መተንፈስ የማያውቀው ድርጅታችን፣ በዚያን ሰዓት ጊዜያዊ ድክመቶችን ለራሱም ሆነ ለማንም አልሸሸገም። ከሃቀኛ ወዝአደር ፓርቲ አፈጣጠር ሂደት አንፃር፣ ገና ብዙ የሚጐድሉት ነገሮች እንዳሉ ያውቅ ነበር። የመኢሶን ታጋዮች፣ በሃቀኝነታቸውና በቆራጥነታቸው እስከመጨረሻው ለመጓዝ ባላቸው ፍላጎት ፅናታቸውን ምን ጊዜም ቢሆን ተጠራጥረውት ባያውቁም፣ ከታሪክ ሂደትና ከሰፊው ታጋይ ሕዝብ ተሽቀዳድመው ራሳቸውን የወዝአደሩ ፓርቲ ብለው አልሰየሙም።

ምንም እንኳን መኢሶን ባንድ በኩል በጊዜው አሉ የሚባሉትን ማርክሲስት ሌኒኒስቶችና ማርክሳዊ የጥናት ቡድኖች ከሞላ ጐደለ ያቀፈ ድርጅት ቢሆንም፣ ከማርክሲዝም መስፋፋት ጋር ሌሎች ቡድኖቸ ሊመሠረቱ አንደሚችሉ ተገንዝቦና አውቆ ነበር። ሌላው ቀርቶ፣ በዚያን ወቅትም ቢሆን አንኳን፣ ሌሎች የህቡዕ ድርጅቶች ሊኖሩ አንደሚችሉ ገምቶ ነበር። ስለሆነም፣ በጊዜው ሊኖሩ ከሚችሉት የህቡዕ ቡድኖችም ሆነ፣ ገና የታሪክ ሂደት ሊፈጥራቸው ከሚችላቸው ሌሎች ማርክሲዝም ሌኒኒዝምን ከተቀበሉ ቡድኖች ጋር ሃቀኛ የሆነ የርዕየተ ዓለም ትግል አካሂዶ ከነርሱ ጋር በመዋሃድ የሠራተኛውን ፓርቲ ለመፍጠር ራሱን ንቅናቄ ብሎ ሰየመ።

ይህም ብቻ አይደለም። መኢሶን በየካቲቱ ሕዝባዊ አብዮታዊ እንቅስቃሴ ወቅት በስውር የነበሩትን ተራማጅ ድርጅቶችንና ቡድኖችን ሁሉ ለማስተባበር እንዲቻል፣ ከነስሙ “የተራማጅ ህብረት” የተሰኘን ጋዜጣ እያወጣ በመቀስቀስና በማወያየት ታግሏል። ከዚህ በኃላ፣ መኢሶን ኢማሌድህ አንዲመሠረት ያደረገው ተጋድሎና ከትግል ስልት ለውጥ በኋላ ለተራማጆች ህብረት ያደረገው ቅስቀሳ የታወቁ ናቸው። አሁን በነርሱ ላይ አንመለስም። አንባቢን ወደ ሰህድ 67 ጠቁመነው እናልፋለን ።

በሌላ በኩል ግን የወዝአደሩን ፓርቲ ለመፍጠር አብዮታዊ ምሁራን ከወዝአደሩ የሙያ ንቅናቄ ጋር መዋሃድ እንዳለባቸው የታወቀ ነገር ነው። ይሁንና በጊዜው በወዝአደሩ ውስጥ የመግባቱ ነገር ገና የመጀመሪያ ደረጃዎች ላይ ነበር። ስለሆነም የኢትዮጵያ ጭቁኖች በየመሥመሩና በየረድፉ ከሚያካሂዱት ዕለታዊ ትግል በሺህ በሚቆጠሩ ክሮች ሳይተሳሰር በፊት መኢሶን ራሱን “የሠራተኞች ፓርቲ” ብሎ ለመሰየም አልፈለገም። ይህ አጉል መመፃደቅና በሠርቶአደሩ ህዝብ ሥም ለመነገድ ሆን ብሎ መነሳሳት በሆነ ነበር ። ባጭሩ መኢሶን ሲፈጠር ጀምሮ፣ ራሱን ለኢትዮጵያ ወዝአደሮች ፓርቲ እንደ አንድ እጡብ ከመቁጠር አልፎ፣ ጣራም ግድግዳም ነኝ ብሎ አልቆጠረም። ዕውነተኛ የወዝአደሮች ፓርቲ እንዲፈጠር፣ የምንግዜም ጥሪው የኢትዮጵያ ማርክሲስት ሌኒኒስት ድርጅቶች ሁሉ በእኩልነት መድረክ ላይ ነፃና ዲሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ እንተባበር፣ ከዚህ መድረክ ላይ ተነስተን ሃቀኛውን የወዝአደር ፓርቲ እንፍጠር የሚለው ነው። መኢሶን ሺህ ቢነገርበት፣ ሺህ ግፍ ቢፈፀምበት፣ በዚህ መላው ሃቀኛ ማርክሲስት፣ መላው ግንባር ቀደም ወዛደር፣ መላው አብዮታዊና አገር ወዳድ ምሁር፣ መለዮ ለባሽ፣ የጭቁን ብሄረሰብ ታጋይ፣ ዲሞክራትና ታጋይ ወጣትና ሴት በሚደግፉት አቋም ላይ አንደፀና ይቆያል።

ይሁንና፣ መኢሶን በተለመው አብዮታዊ ጐዳና ለመግፋት ተነሳስቶ እንዳለ፣ ከወዝአደሩና ከሰፊው ታጋይ ሕዝብ ቀድመው ፀረ ሕዝብ ዓላማቸውን ለማረጋገጥ የሚፈልጉ ንዑስ ከበርቴዎች ከውስጡ ተነሱበት። እነዚህ ፀረ ሕዝቦች “የሠራተኛ ፓርቲ” የሚለውን መጠሪያ የፈለጉት ለስሙ ብቻ ስለሆነ፣ ከሌሎች ማርክሲስቶች ጋር ሃቀኛ የመስመርና የርዕዩተ ዓለም ትግል አካሂዶ መዋሃድንም ሆነ፣ ከራሱ ከአብዮቱ ባለቤት ከሆነው ወዝአደርና ሰፊ ሕዝብ መዋሃድን እንደጦር ፈሩት። ስለሆነም፣ ስምን ብቻ በመንጠቅ በወዝአደሩ ለመነገድና በኢትዮጵያ ጭቁን ሕዝቦች ትግል ለማላገጥ ወሰኑ። ነገር ግን ንቅናቄያቸንን የመከፋፈልና በእንጭጩ የመቅጨት ሴራዎች ስለከሸፈ፣ ከመኢሶን ተገንጥለው ራሳቸውን “የኢትዮጵያ ሕዝብ አብዮታዊ ፓርቲ” ብለው ሰይመው ተቋቋሙ። እንደሚታወቀው፣ ይህ ድርጅታቸው በኢትዮጵያ የፖለቲካ መድረክ ላይ ቦግ ብሎ ጠፍቷል። የኢትዮጵያ ታጋይ ትውልድ ምንጊዜም የማይረሳው ቁስል ትቶ አልፏል። መኢሶን ግን እንኳን የዚያን ጊዜ ቀርቶ፣ አብዮቱ ተቀጣጥሎ ይህ ነው የማይባል ድል አየተቀዳጀ ወደፊት በሚገሰግስበት ወቅት ህልውናውን ከስምንት ዓመቶች የስውር ትግል በኋላ በመጋቢት 28 ቀን 1968 ዓ.ም. ይፋ ቢያስታውቅም፣ በአቋሙ ፀንቶና የትግል መሥመሩን በገልፅ ቋንቋዎች አስፍሮ ነው። የመኢሶንን ፕሮግራም አንጥቀሰው፦

“መኢሶን በተቋቋመበት ወቅት፣ በብዛት በአባልነት የያዛቸው አብዮታዊ ምሁራን እንጅ፣ በላብአደሩም ውስጥ ሆነ፣ በጠቅላላው በሰፊው ሕዝብ መሃል ገብቶ፣ ሰፊ ቅስቀሳና የማደራጀት ጥረት አድርጐ ለመላ ኢትዮጵያ ጭቁኖች ትግል ተገቢውን አመራር የሚሰጥ ድርጅት አልነበረም። ይህንንም በመገንዘብ ከፓርቲ ይልቅ ራሱን ንቅናቄ ብሎ ሰየመ። አሁንም ቢሆን ምንም እንኳን ተጠናክሮና ከላብ አደሩና ከሰፊው ሕዝብ ተዋህዶ ለትግሉ የተጣራ አመራር ለመስጠት ያደረገው ቆራጥ ተጋድሎ ብዙ ከፍተኛ ፍሬዎችን ቢያስገኘም፤ አንደኛ ፣ በላብ አደሩ ውስጥ የመዋሃዱ ዘመቻ ገና ብዙ ተጋድሎ አንደሚቀረው በመመልከት፤ ሁለተኛ፣ ከማርክሲዝም ሌኒኒዝም ተከታይ ቡድኖች ጋር ሃቀኛ የርዕዮተዓለም ትግል አድርጎ፣ ከነርሱ ጋር ተዋህዶ በተጣራ የፖለቲካ መሥመር የሚመራና በላብ አደሩ መደብ ላይ የተመሠረተ ፓርቲ ለመገንባት ያለውን ፍላጐት ለማመልከት ‘ንቅናቄ’ የሚለውን መጠሪያ ይዞ እንዲቆይ ተደርጓል። /የመኢሶን ፕሮግራም፣ መጋቢት 28 1968 ዓ.ም./

እንወያይ፣ እንከራከር፣ እንተባበር፣ እንዋሃድ፣ ለሚለው የመኢሶን ጥሪ የከሣራው ኢህአፓ መልስ በመኢሶን ታጋዮች፣ በግንባር ቀደም ወዝአደሮችና አርሶአደሮች፣ መለዩ ለባሾች፣ ምሁሮች፣ በታጋይ ወጣቶቸና ሴቶች ላይ የጥይት ዝናብ ማውረድ ሆነ። ለወዝአደሩ ፓርቲ መፈጠር በይበልጥ ወደ ወዝአደሩ እንግባ ብሎ መኢሶን ለሃቀኛና ዲሞክራሲያዊ የሠራተኞች የሙያ ማህበሮች መመሥረት ፈንታ፣ የኢህአፓ ቅጥረኞች መልስ ሲቻል ፀረ-ዲሞክራሲያዊ በሆነ ዘዴ በነዚህ ድርጅቶች አመራር ላይ ፊጥ ማለት፣ ካልተቻለም ደግሞ እነዚህን ድርጅቶች በነጭ ሽብር ለመበተን መፍጨርጨር ሆነ። ነገር ግን ደግሞ በዚያው ልክ ከኢትዮጵያ ጭቁን ሕዝቦችና በተለይ በወዝአደሩ መደብ እያደረ መንቃት የተነሳ፣ “ኢህአፓ” እየተተፋ ወደማይቀረው የታሪክ ትቢያ ወርዶ ተከሰከሰ።

የዛሬ ሦስት ዓመት በኢህአፓ ላይ የተገኘው ድል በየአቅጣጫው የሆነውን ያህል፣ በዚህ በወዛደር ፓርቲ አፈጣጠር ጉዳይም ላይ ፀረ ሕዝቡ ቡድን ይነዛ የነበረው ውዥንብርም እየጠራ መጣ። በሁለቱም አንጻር የኢትዮጵያ ማርክሲስት ሌኒኒስቶች መኢሶን ሲጠነሰስ ጀምሮ ይታገልለት በነበረው መስመር ላይ ተስማምተው አቋማቸውን በይፋ ገለፁ።

የኢትዮጵያን ወዝአደሮች ፓርቲ ለመመሥረት ማርክሲስት ሌኒኒስት ቡድኖች በሃቀኛ የርዕዮተ ዓለም ትግልና በዲሞክራሲያዊ የትግል ዘዴ ማስተባበርና ከዚያም ማዋሃድ አማራጭ የሌለው ዘዴ እንደሆነ በይፋ ተነገረ። በየካቲት 1969 ዓ.ም. መኢሶን በጊዜው “ማርክሲስት ሌኒኒስት” ነን ይሉ ከነበሩት ድርጅቶች ጋር ባወጣው የጋራ መግለጫ ላይ በትክክል እንደሚከተለው ሠፈረ፦

“ከተለያዩ ቡድኖች በምን ዘዴ የወዝአደር ፓርቲ ለመመሥረት ይቻላል ለሚለው ጥያቄ፣ የብዙ አገሮችን የአብዮታዊ ትግል ታሪክና የኢትዮጵያን ተጨባጭ ሁኔታ ከመረመረና ካጠና በኃላ፣ የወዝአደሩን ፓርቲ ለመፍጠር ከተለያዩት የወዝአደር ፓርቲ አመሰራረት ዘዴዎች ፍቱንና ሳይንሳዊ የሆነው ልዩ ልዩ ማርክሲስት ሌኒኒስት ቡድኖች ኃይላቸውን አስተባብረውና የትግል አንድነት መሥርተው በመሃከላቸው በታክቲክና በስትራቴጂ ጥያቄያቸው  ላይ ሃቀኛ የሆነ የርዕዮተ ዓለም ትግል  አካሂደው የሚዋሃዱበት ዘዴ መሆኑን አምነውበታል።”

በሌላ በኩል ደግሞ፣ ለዚህ ፓርቲ መፈጠር አስፈላጊ የሆነውን ከወዛደር መደብ የመዋሃድ ጉዳይ ተገቢ ቦታውን ሰጥተውት ስለ ነበረ፣ በዚሁ መግለጫቸው ላይ፦

“በየፋብሪካውና፣ በየማከፋፈያ ድርጅቶች በተካሄደው የከረረ ትግል በአያሌ ፋብሪካዎች ሃቀኛ የሆነ የማህበር አመራር ያለውና በቅርቡ የተቋቋመ ‘የመላ ኢትዮጵያ ሠራተኞች ማህበር’ በተጠናከረ አመራር ተመስርቷል። ድርጅቱ የሙያ ማህበር ጠባይ ያለው ቢሆንም፣ ለወዝአደሩ የፖለተካ ትግል ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማድረግ ስለሚችል፣ በየደረጃው የተመሠረቱትን የወዝአደር ማህበሮች ለማጠናከር ሰፋ ያለ የፖለቲካ ቅስቀሳ ለማካሄድና የውይይት ክበቦች የአብዮታዊ ንቃት መድረኮች እንዲሆኑ ለመታገል . . .”

በሚለው ከስምምነት ላይ ተደርሶ እንደነበረ ይታወቃል።

እንግዲህ በአብዮቱ የዲሞክራሲ ዘመን ታላቁ የኢትዮጵያ አብዮት ከፊት የሚጋፈጡትን ፀረ አብዮት ኃይሎች ሁሉ በማንኛውም የትግል መስክ እያጋለጠና እየመከተ ለዘላለሙ ወደፊት የሚገሠግሥ ይመስል በነበረበት ወቅት፣ ምድረ የቀኝ አደርባዮች ሁሉ ያስተጋቡት የነበረው አቋም ይህ ነበር። ብሩሁም የወዝአደር ፓርቲ አፈጣጠር መንገድ ይሄው ነበር። ትክክለኛውም የአብዮቱ ፋና ይህ ነበር።

ዛሬ ግን የአብዮታዊው መዓከል ጥንስስ “ኢማሌድህ፣ ሳይፈላ ተደፍቶ” ፣ ሳይከካ የተቦካ ሌላ የፀረ አብዮት መዓከል ተተክቷል። ይህ “አዲሱ ጥንስስ” ወይንም “መዓከል” ወይንም “ኮሚሽን” ወይንም “የማጣሪያ ቢሮ”   . . . ወዘተ የተፈጠረው፣ ከዛሬ ሁለት ዓመት ተኩል በፊት የኢትዮጵያ ማርክሲስት ሌኒኒስቶቸ በይፋ የተለሙትን፣ ከዚያም የቀኝ አድርባይ ድርጅቶቸ ሁሉ ተራ በተራ እየተንጠባጠቡ የከዱትን የወዝአደር ፓርቲ አፈጣጠር ዘዴ ተከትሎ ሳይሆን እሱን ተፃርሮ ነው። ይህ ፀረ ወዝአደር፣ ፀረ ሕዝብና ፀረ አብዮት ጎዳና ደግሞ፣ በጠቅላላው በሃገራችን የፀረ አብዮት ኃይሎችን ማየልና የውጭ ኃይሎችን ባገራቸን ላይ መንገሥ ተከትሎ በፀረ አብዮት ፋና እየተጋገዘ የመጣና እዚህ የደረሰ ሂደት ነው። በታጋዮች ደም ተራ በተራ የተገኙት የአብዮታቸንን ድሎች ከሰፊው ሕዝብ እጅ አየፈለቀቀና እንዳልነበሩ አድርጐ ማውደም የያዘው የቀኝ ኃይሎች ህብረት፣ ዛሬ ሥልጣኑን ወደ ማደላደል እያመራ ይህንን “ኮሚሽኑ” የተባለ ስመ ጥሩ “መዓከል” ሲያውጁ፣ በዚያው በፀረ ወዝአደሩና ፀረ ሕዝብ ጐዳናው ወደ ፊት መራመዱን እንጅ፣ ከፀረ አብዮት አፋፍ ተመልሶ ወደ አብዮቱና ወዳጆቹ ሠፈር መዋሃዱ አይደለም።

ነገር ግን ይህንን ክፍል ከመዝጋታቸን በፊት ደግሞ፣ ስለ “ኮሚሸኑ” ወይንም ስለ “ማዕከሉ” ወይንም ስለ “ማጣሪያው ቢሮ” መፈጠር በሚነገረው ዓይን ያወጣ ሸፍጥ ላይ መመለስ አስፈላጊ ነው። በዕውነቱ ይህንን ፀረ ወዛደር፣ ፀረ ሕዝብና  ፀረ አብዮት “የሠርቶ አደር ፓርቲ” ለመመሥረት ያሰፈሰፉት ኃይሎች በገሃድ ያለውን  ነገር ለመሸፈጥ ዓይናቸውን አንኳን አያሹም። እስቲ እንመልከተው፦

እነሱ አሁን ደግሞ አንደሚሉት ከሆነ፦

“በየትኛውም የኮሙኒስቶች ንቅናቄ ታሪክ፣ ከራሺያ አስከ ቪየትናም አብዮት፣ የፓርቲ አመሠራረት በጅምላ /?/ የድርጅቶች ወይም የግለሰቦቸ መገጣጠም ወይም መቀላቀል ሳይሆን በመሠረቱ የታጋይ ኮሙኒስቶች አንድነት ነው። የኢማሌድህን የህብረት ሂደት ስንመለከተው ግን፣ መሠረታዊ ሃሳቡ የኮሙኒስቶችን አንድነት ዕውን ለማድረግ ሳይሆን፣ መካኒካል በሆነ መንገድ /?/ ድርጅቶችን በጅምላ /?/ በመገጣጠም ‘ፓርቲ’ ለመመሥረት ነበር። ስለዚህም፣ ኢማሌድህ ውስጥ የነበሩ የእነመኢሶንና ኢጭአት መንሸራተት፣ መፈርጠጥ ወይንም መፍረክረክ መሆን ነበረበት / … /” /ህብረት ደምጽ ቁ.6፣ ገጽ 4-5 ግንቦት 1971/

“ከራሺያ አስከ ቪየትናም”፣ “በመሰረቱ” “ሜካኒካል በሆነ መንገድ” …ወዘተ። በዕውነቱ ትላልቅና የብልሆች ቃላት ናቸው። ሲባል ተሰምቷል። የሚያሳዝነው ግን ባዶ ገላጣዎች መሆናቸው ነው።

አንደዕውነቱም ከሆነ ይሄንን ዝባዝንኬ እኛም መተቸት አያስፈልገንም። አንባቢው በዛው በህብረት ድምጽ መጽሔት ቁጥር 5 ላይ የተፃፈውን አግኝቶ በዚህ ጽሁፍ ውስጥ ከዚህ በላይ የጠቀስነውን አንቀጽና አሁን ደግሞ ከዚያው ከህብረት ድምጽ ቁ.6 የጠቀስነውን አንቀጽ አስተያይቶ ፍርዱን ይስጥ ብለን ልናልፈው እንችላለን። ብቻ እንዳው “የኮሚሽኑና የመዓከል” ደብሮች ሆነው የተነሱትን ኃይሎች ለነገሩ ያህል እንጠይቃቸውና፣ ለመሆኑ የሠርቶ አደሩን ፓርቲ የሚያክል ነገር “ድርጅቶችን ወይንም ግለሰቦችን በጅምላ፣ ሜካኒካል በሆነ መንገድ በመገጣጠም ወይንም በመቀላቀል” ለመፍጠር ይቻላል የሚለው “መሠረታዊ ሃሳብ” የቀረበው የትና መቼ ነው? በየትኛው ጽሑፍና በየትኛው የቅስቀሳ መድረክ ነው?

ክቡራን “ጓደች”! የታወቀውን መድገም አይሁንብንና የሠራተኛው ፓርቲ “መሠረታዊ” ድርጅታዊ መርሆ ዲሞክራሲያዊ መአከላዊነት ነው። የዚህን ሀ ሁ የቆጠረ ማንም ሰው ቢሆን፣ “ድርጅቶችን ወይንም ግለሰቦችን በጅምላና መካኒካል በሆነ መንገድ በማገጣጠም ወይንም በመቀላቀል” የሠራተኛውን ፓርቲ የሚያክል ነገር ሊፈጥር ይችላል ብሎ አይናገርም። በዚህ ማንንም ለማታለል አይቻልም። “ተንሸራተቱ”፣ “ፈረጠጡ”፣ “ተፍረከረኩ” የሚባልልን ድርጅቶችም፣ እንኳን ዛሬ ቀርቶ፣ ከዛሬ አስራ አንድ ዓመት በፊት ከተናገርነውና ከፃፍነው የቅንጣት ያህል ዝንፍ አላልንም። የወዝአደሩ ፓርቲ አንዳች ዓይነት ኮን-ፌደሬሸን አንዳልሆነ የምናውቀው ዛሬ አይደለም። ዛሬም የምንለው እውነተኛ ፓርቲ የሚፈጠረው፣ በማርክሲስት ሌኒኒስት ድርጅቶች መካከል በእኩልነት መድረክ ላይ ነፃና ዲሞክራሲያዊ የሆኑ የርዕዮተዓለም፣ የፖለቲካ መሥመር፣ የፖለቲካና የእስትራቴጂ ውይይቶች ሲካሄዱ ነው። አያንዳንዱ ድርጅት የሌላውን ድርጅት ነፃ ህልውና ተቀብሎ አክብሮ ቅንና የእኩልነት ህብረት ሲመሠረት ነው። ደግሞም፣ ጀንበር በጠለቀች ቁጥር አቋሙን መለዋወጥ ሲያበቃ ነው። እንደዚህ በዲሞክራሲ፣ በእኩልነት፣ በመከባበርና በፅናት ላይ የተመሠረተ ህብረት፣ ህያው በሆነ የጋራ ትግል፣ ህያው በሆነ መፈቃቀር ይተሳሰራል። እያንዳንዱም የራሱን ድርጅት ህልውና ፈልጎና ፈቅዶ እንዲያከትም ለማድረግ ዝግጁ ይሆናል። አዎን ይዋሃዳል። የወዝ አደሩን ፓርቴ በዲሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት መርሆዎች ይመሠረታል።

እንግዲህ እስቲ “ተንሸራተቱ”፣ “ፈረጠጡ”፣ “ተፍረከረኩ” የሚሏቸውን መኢሶንና ኢጭአትን ለጊዜው ወደ ጐን እንተዋቸውና፣ ኧረ ለመሆኑ “ኢማሌድህ መድረክ ላይ ጸንተው ቆዩ” የሚባልላቸውን “ማሌሪድ፣ ሰደድና ሊግ” የበላቸው ምንድን ነው? ወዝ ሊግ አንደሚለው፣ ፈልገውና ፈቅደው “እድሜያቸውን አሳጠሩ”! በበኩላችን መልሱን በቁጥር 70 ላይ ሰጥተናል። አንመለስበትም።

ይሁንና፣ የወዛደሩ ፓርቲ የሚመሠረተው “ድርጅቶችን ወይንም ግለሰቦችን በጅምላና ሜካኒካል በሆነ መንገድ በማገጣጠም ወይንም በማቀላቀል አይደለም” ከተባለልን አይቀር፣ ይሄንን “ከህብረት ድምጽ” መጽሔት የምንጠቅሰውን ጉደኛ “ስምምነት” ምን አመጣው? በእውነቱ እንደሚባለው ማርክስና ሌኒኒን በመቃበራቸው ውስጥ እየተገላበጡ ናቸው። አንባቢም እንደኛው አንብቦ “ጉድ” ይበል። ይሄውና፦ /ይሄ ጉደኛ “ስምምነት” ራሳቸውን ቀስቅሶ አላሳርፍ ብሏቸዋል።/

“1. የወዝአደሩን ፓርቲ ለማስገኘት /የሚቻለው/. . . በማርክሲዝም ሌኒኒዝም ርዕዮተ ዓለም የታጠቁትን ዕውነተኛ ታጋዮች /ግለሰቦች “የኛ”/ በማዋሃድ ነው።”

“3. ፓርቲውን ለመፍጠር በቅድሚያ በአብዮታዊ ችሎታቸውና አስተዋፅኦዋቸው /ሜሪት/ ከኢማሌድህ አባል ድርጅቶችና መመዘኛውን /የግለሰብ “የኛ”/ የሚያሟላ ከተገኙ ከአባል ድርጅቶችም ውጭ የሚገቡበት መዓከል መመሥረት አስፈላጊ ነው።”

“ 4. ይህ . . . መዓከል በአብዮታዊው መመዘኛ መሠረት ለኢማሌድህ አባል ድርጅቶች አባላት ቅድሚያ በመስጠት የፓርቲ አባላትን /ግለሰቦችን “የኛ”/ ይመለምላል። /“የህብረት ድምፅ” ቁ.5፣ ገጽ 16-17 የካቲት 1971/

ከዚህስ በኋላ?

“ስምምነቱ” በጥሩና በከባዱ ቋንቋ እንደሚለው ከሆነ፣ ከዚህ በኋላ “ማዕከሉ ፓርቲውን ያዋቅራል”። ይሁንና፣ እኛ ደግሞ በቀላሉ እንናገረውና፣ “የመለመላቸውን” ግለሰቦች “እያገጠጠመ ያቀላቅላል” እንበል። ሌላ መንገድ የለውም።” . . . ሳታመሃኝ ብላኝ” ነው?

አይ “አብዮታዊ ሰደድ” “ቀኞች የሚናገሩትና የሚሠሩት፣ የሚጽፉትና ወደተግባር የሚተረጉሙት ሁሉ ለየቅሉ ነው” ይበል? በተለይም የወዝአደሩ ፓርቲ በሚመለከተው ጉዳይ ላይ ደበስባሳና ሙልጭልጭ አቋም ይወስዳሉ” ይበል? “በልዩ ልዩ ፅሑፎቻቸው እንደ እስስት የሚቀያይሩ መንደርደሪያዎች ይኖራቸዋል” ይበል? እኛን “ቀኝ መንገደኞች” መንካቱ እኮ ነው። ጉድ ነው!!

ብቻ ደግሞ ከመጨረሳችን በፊት፣ ዛሬ ለመጨረሻው ጊዜም ባይሆን፣ ከዚህ የወዝአደር ፓርቲ ጥያቄ ላይ ያለፉት ሁለት ዓመታት ያዩትን የፀረ እውነተኛ ወዝአደር ፓርቲ ዘመቻ ባጭሩ እንመለስበትና አንባቢን አንዳንድ ቁም ነገሮችን እናስታውሰው።

የቀኝ ኃይሎች ህብረት ይህንን ፀረ ወዝአደር ሂደት ሲጀምር በመጀመሪያ በስንት መከራ የተገኘውን የተራማጆች ህብረት ማፍረስ ጀመረ። የኢትዮጵያ ማርክሲስት ሌኒኒስቶች ድርጅቶች ሃቀኛ የሆነ የርዕየተዓለምና የፖለቲካ መሥመር ትግል በመካከላቸው አካሂደው ወደ ውህደት እንዳይሸጋገሩ ዲሞክራሲያዊ ውይይቶችን አፈነ። ለዚህ ውይይት አመች ሁኔታ ሊፈጥሩ የሚችሉት ዲሞክራሲያዊ መብቶች እንዲዳብሩ ከማድረግ ፈንታ፣ ይባሱኑ ደብዛቸውን አጠፋቸው።ምንም አንኳን ለአብዮታቸን ወደፊት መራመድ የሚቆረቆሩ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ጭቁኖች ከዳር አስከ ዳር ያስተጋቡት የነበረውን “የወዝአደር ፓርቲ ባስቸኳይ ይመሥረት”፣ “የተራማጆች ህብረት ይጠንክር”፣ “ኢማሌድህ ከህብረት ወደ ውህደት ይሸጋገር” የሚሉትን መፈክሮች ቀልብሶ ቢያስተጋባም፣ በይፋ ድርጊቱ የሚፈጸመው የዚህን ተቃራኒ ነበር። ስለሆነም፣ እነዚህን መፈክሮች ከሰፊው ሕዝብ ተደባልቀው እያስተጋቡ የዲሞክራሲ መብቶችን መለቀቅ መቃወም፣ “የሠራተኛውን ፓርቲ” ባቋራጭ ለመመሥረትና በኢትዮጵያ ጭቁኖች ትከሻ ላይ ለመፈናጠጥ የታሰበ የከሃዲ ንዑስ ከበርቴዎቸና የአድሃሪው ቢሮክራሲ ሴራ መሆኑን መኢሶን አስገነዘበ። በሰህድ ቁ.65 በጥር ወር 1970 ዓ.ም. እንዳስቀመጠው፦

“አድርባዮች፣ ንዑስ ከበርቴው መደብና አድሃሪው ቢሮክራሲ ይህንን መፈክር ሲያስተጋቡ ወደ ሃቀኛ የወዝአደር ፓርቲ ቶሎ ቶሎ እንራመድ ሳይሆን፣ የኛን ህብረት የሚያንጸባርቅ “የወዝአደር ፓርቲ” ባቋራጭ ከወዝአደሩ ቀድመን እንመሥርት ማለታቸው ነው። “ባስቸኳይ” ሲሉ “ባቋራጭ” ማለታቸው ስለሆነ፣ ለንቃት፣ ለድርጅትና ለትጥቅ አመቺ ሁኔታ የሚፈጥሩትን፣ ሃቀኛ የወዝአደር ፓርቲ ባስቸኳይ ለመመሥረት የሚረዱትን ዲሞክራሲያዊ መብቶች አሁኑኑ መለቀቅ ይቃወማሉ። ስለሆነም፣ የወዝአደር ፓርቲ ባስቸኳይ ይመሥረት ከሚለው መፈክር ተነስተን፣ እኛ ቶሎ ቶሎ እንራመድ ስንል፣ እነሱ ደግሞ “ባቋራጭ”  እንራምድ ሲሉ፣ በመሃከላችን ያለው ትግል የለየለት የመደቦች ትግል ነው። ጥያቄው የወዝአደር ፓርቲ እንዴት ይመሥረት የሚል ጥያቄ አይደለም።”

ከዚህ በኋላ የሆነውን ሁሉ ሁላችንም እናውቀዋለን። “ከህብረት ወደ ውህደት ይሸጋገር” ይባልለት የነበረው ኢማሌድህ፣ ለኢትዮጵያ ማርክሲስት ሌኒኒስቶቸ የጋራ ትግል፣ የሃቀኛ የርዕዩተዓለም ትግልና ወደ ውህደት መሸጋገሪያ መድረክ መሆኑ ቀርቶ፣ ከአባል ድርጅቶቹ እየተራቆተ፣ በፖለቲካ መሥመሩ ከኪሣራ ወደ ኪሣራ እየተደፋ ወደ ታሪክ አተላነት ዘቀጠ። በቀኝ ኃይሎች ህብረት ውስጥ እያየለ የመጣው አድሃሪ የሲቪልና የሚሊቴሪ ቢሮክራሲ፣ በቀኝ አድርባይ ድርጅቶች ፊታውራሪነትና በነለገሠ አስፋው ሸረኛ ክሊክ አስፈፃሚነት የአብዮቱን ሠፈር ካጠቃና ከዳከመ በኋላ፣ ኢማሌድህን በአዋጅ አፈረሰው። አንድ ትውልድ ያፈራቸውን ማርክሲስት ሌኒኒስቶችና ግንባር ቀደም ወዝአደሮች በየሥፍራው ረሽኖና በየእሥር ቤቱ  አጉሮ “ያጠናቀቀ” ሲመስለው፣ ከኢትዮጵያ ግንባር ቀደም ወዝአደሮች፣ አብዮታዊ ምሁራንና መለዮ ለባሾች ውጭ፣ ራሱን “የሠርቶአደር ፓርቲ” ብሎ ለመሰየም እስክስታ እየወረደ መጣ።

ነገር ግን ይህ “የሠርቶአደር ፓርቲ” የሚታወጅበት ቀን እንደተነገረን ከሆነ “ሩቅም” ባይሆን ገና ነው። ዛሬ “ሠርገኛ ደረሰ በርበሬ ቀንጥሱ” እየተባለ ነው። ለዚህም ምክኒያቱ የስልጣን ሽኩቻውና እሽቅድምድም ገና ያልተረጋጋ በመሆኑ ነው። በዚህ ሽኩቻ ውስጥ፣ ባንድ በኩል ፍፁም ከሃዲውና የስልጣን ጥም ያናወዘው የነለገሠ ክሊክ አለ። በሌላው በኩል፣ ይህንን ክሊክ ለማዳከም ሲል በተሰበጣጠሩ ምክኒያቶች ለጊዜው የተቆላለፈው የከፍተኛ መኮንኖችና ሲቪል ቢሮክራቶች ክንፍ አለ። በነዚህ ሁለት ክንፎች መሃከል የሰነበተው ግብግብ፣ ሽኩቻና ኢንትሪግ በኮሚሽኑ መቋቋሚያ ዋዜማ የታየውን ያህል ከዚያም ወዲህ፣ “የሠርቶ አደር” ፓርቲያቸውንም ሲወልዱ እስኪለይለት መቆየቱ የማይቀር ነው። የመጀመሪያው በተለይ፣ በኢማሌድህ ምርኩዝ ያደረገው ጉዞ ቢቀጭበትም ሌሎች የውጭ ኃይሎች ጣልቃ ገብነትን ጨምሮ፣ ያጠመዳቸው ተንኮሎችና መንገዶች እንዳሉ ብዙ ምልክቶች እየታዩ ናቸው። ወደፊት ገሃድ ይታያሉ። ያለፈው ሰሞን የነታምራት/ እንዳለ ትርዒትም የዚሁ ነፀብራቅ መሆኑ እንጅ፣ ሌላ ትርጉም የለውም። እዚሁ ላይ መነገር ያለበት ሌላው መሠረታዊ ጉዳይ ግን፣ በዚህ በኋለኛው ክፍል ውስጥ ዛሬም ቢሆን አገር ወዳድና ዲሞክራት የሆኑ ግለሰቦች እንዳሉና አንዳንዶቹም በሁኔታዎች ተገደው የተቀላቀሉት እንደሆነ ነው። መኢሶን፣ ዛሬ ይህንን ስመ ጥሩ “ኮሚሽን” እየተቃወመ አቋሙን የሚገልጸው ፍፁም ዕውር በመሆን ሁኔታዎችን በስሜተኝነት በመመልከት አይደለም። ይልቁኑ የያንዳንዱን ጉዳይ ነባራዊ ህልውና ከስሜትና ከቂም በቀል ውጭ እየመረመረና እያጠና ነው። እንደዕውነቱ ከሆነ፣ መኢሶን ማለትም ይህ ነው።

ስለሆነም፣ መኢሶን ዛሬም አንደገና እውነተኛ የወዝአደር ፓርቲ እንዲፈጠር፣ ሃቀኛ ማርክሲስት ሌኒኒስቶች ሁሉ በዲሞክራሲያዊ የትግልና የአንድነት መድረክ ላይ እንተባበር፣ ተባብረንም ፈልገንና ፈቅደን የየራሳችን ድርጅቶች ህልውና እንዲያከትም በማድረግ እንዋሃድና እውነተኛውን የወዝአደሩን ፓርቲ እንመሥርት እያለ ድምፁን ከፍ አድርጐ ያሰማል።

በየትኛውም የህብረተሰቡ ክፍየሥራ ስክ ያላችሁ የኢትዮጵያ አገር ወዳድና ዲሞክራቶች ሆይ!

እኛ የመኢሶን ታጋዮች ፀንተን የቆምነው በኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ አብዮት ፕሮግራም ላይ ነው። ይህ መድረክ የአገር ወዳዶችንና የዲሞክራቶችን በነፃ የመደራጀት መብት ይፈቅዳል። እስካሁን “ማርክሲስት” ብትሆኑም ባትሆኑም “ማርክሲዝም፣ ሶሻሊዝም” እያላችሁ ብዙ ስትናገሩ፣ ብዙ ስትሠሩ አይተናል። ይልቁኑ ማንነታችሁን በሃቅ ጠብቃችሁ፣ በአገር ወዳድና በዲሞክራትነታቸሁ ተደራጁ። በተለይ ዛሬ የአብዮታችን የዲሞክራሲ ዘመን አክትሞ፣ ፀረ ዲሞክራሲ በነገሠበት ዘመን፣ የውድ አገራችን ብሄራዊ ክብር ተገርስሶ፣ ብሄራዊ ውርደትን በተከናነብንበት ወቅት የናንተ መደራጀት እንደ ሕይወት እስትንፋስ ያስፈልጋል። የትግላችን መድረክ ሰፊ ነው። ይህች ውድ ሃገራችን  የጀግና አገር ወዳዶችና ዲሞክራቶች አገር ናት። የዛሬው አገር ወዳድና ዲሞክራት ትውልድ ይህንን የምንኮራበትን ታሪክ ዓይኑን ጨፍኖ ለመርሳት የተዘጋጀና የዳሸቀ ትውልድ መሆን የለበትም። እንዲያውም ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ከፍተኛ የታሪክ ግዴታና ሃላፊነት ያለበት ትውልድ ነው።

በየትም ስፍራ ለምትዋደቁ የኢትዮጵያ ጭቁን ብሄረሰቦች ታጋዮች ሆይ!

በብሄረሰቦች እኩልነት ያሸበረቀች አዲሲቱ ኢትዮጵያ የምትመሠረተው ብሄረሰቦች የራሳቸውን ዕድል በራሳቸው ለመወሰን ያላቸው ሙሉ መብት የታወቀ፣ የተረጋገጠና የተከበረ ሲሆን ነው። የብሄረሰቦቿ አንድነት በእኩልነትና በመከባበር መርሆች መሠረት ሲመሠረትና ሲደረጅ ነው። ነገር ግን ለዚህ ቅዱስ ግብ፣ ከየትኛውም ብሄረሰብ ይሁን ከየትኛው፣ ይህች አገር ያበቀለቻቸው የጨቋኝና የተጭቋኝ ብሄረሰቦች ታጋዮች ሁሉ መተባበር አለባቸው። እጅ ለእጅ ተያይዘው ወደ ነፃነትና ዲሞክራሲ፣ ወደ እኩልነትና መከባበር መጓዝ አለባቸው። ስለሆነም፣ መኢሶን ዛሬም መልሶ ባንድ በኩል ትምክህተኝነትን፣ በሌላው በኩል ጠባብ ብሄረተኝነትን በጋራ እየተዋጋን በነፃነትና በዲሞክራሲ የትግል ጐዳና ላይ እንግፋ እያለ ከየትኛውም ብሄረሰብ ለሚመጡ ታጋዬች ሁሉ ድምፁን ከፍ አደርጐ ያሰማል። መኢሶን ዛሬ ትምክህተኝነት ነግሶ ታሪካችን አይቶት በማያውቀው መጠንና ስፋት በሲዳሞ፣ በባሌ፣ በወለጋ፣ በሐረርጌ፣ በአርሲ፣ በትግራይ፣ በኤርትራና በሌሎችም ጭቁን ብሄረሰቦች ላይ የሚወርደውን ጭፍጨፋና ግፍ የተመላበት አመጽ እያወገዘ፣ ለእውነተኛ እኩልነት ከቆሙ ዲሞክራሲያዊ ኃይሎች ጋር ሁሉ ለመተባበር ያለውን ፍላጐትና ጥሪም በዚሁ አጋጣሚ ለጭቁን ብሄረሰቦች አብዮታዊ ታጋዩች ሁሉ ያድስላቸዋል።

እንግዲህ ትግል ያሻውን ጊዜ ይወስዳል እንጅ፣ ያሻውን መስዋዕትነት ይጠይቃል እንጅ፣ ያሻውን ያህል መራራ ይሆናል እንጅ፣ ያሻውን ያህል ውስብስብና ከባድ ይሆናል እንጅ፣ ያሻውን ያህል ትዕግስት ይጠይቃል እንጅ፣ ኢትዮጵያችንን በሚወዷት ቀናተኛ በሆኑት ልጆቿ የተባበረ ትግል፦ በሕዝባዊነቷ ደምቃ፣ በዲሞክራሲያዊነቷ ፈክታ፣ በብሄረሰቦቿ እኩልነት አሸብርቃ፣ በብሄራዊ ነፃነቷ ኮርታ፣ በሕዝቦቿ ታታሪነት በልፅጋና አብባ እንደምናያት ከቶም አንጠራጠርም። ድሉ የሰፊው ሕዝብ ነው። ትግሉ ይቀጥላል።

ሃቀኛ ማርክሲስቶች፣ ዲሞክራቶች፣ ሃገር ወዳዶች፣ የጭቁኝ ብሄረሰቦች
አብዮታዊ ታጋዮች ትግላችሁን አስተባብሩ!
ለዲሞክራሲና ለብሄራዊ ነፃነት ትግሉ ይቀጥላል!
የነቃ፣ የተደራጀና የታጠቀ የሕዝብ ትግል ያሸንፋል።
Scroll to Top