ሰሕድ ቁ. 73

የሰፊው ሕዝብ ድምፅ

ቁጥር 73፣      ሰኔ 5፣ 1972

የፅሁፉ ፍሬ ሀሳብ

በዚህ እትም፣ መኢሶን  የኢትዮጵያ ህዝቦች በኢጣልያን ፋሺሽት ወረራ ዘመን ለብሄራዊ ነፃነታቸውና ለክብራቸው ሲሉ ያደረጉትን ትግልና መስዋዕትነት በማስታወስ ጽሁፉን ይጀምራል። ከዚያም በመቀጠል፣ ፋሺሽት ኢጣልያን ከተባረረ በኋላ የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ መንግስትና ከዚያም በኋላ የመጣው የደርግ መንግሥት ኢትዮጵያን መጀመሪያ የአሜሪካን በኋላም የሶቪየት ሕብረት እጅ አዙር ቅኝ ግዛት እንዳደረጓት ያብራራል። ከተማሪው ንቅናቄ የወጡት ተራማጆች ከፊውዳሊዝምና ከኢምፔሪያሊዝም ጋር የሚደረገው ትግል ለኢትዮጵያ ፍቅርና ክብር መታገልንም እንደሚጨምር በሚገባ የተገነዘቡ እንደነበሩና መኢሶንም የብሄርዊ ነጻነትን ጥያቄ ከመሬት ላራሹ፣ ከዴሞክራሲና ሰብዓዊ መብቶች ትግል ሳይነጥል ለእናት አገሩ ክብር መታገሉን ያስታውሳል።

እንዲሁም፣የሶቪየት ሕብረት በመጀመሪያ የሶማሌን ጦር አስታጥቃ ኢትዮጵያን እንድትወር ስታዘጋጃት ከከረመች በኋላ አሁን ደግሞ በደርግና በዘመኑ አድርባዮች እየተረዳች አገራችንን ብሄራዊ ውርደት ውስጥ እንደከተተቻትና ብዙ ግፍ እየደፈጸመችባት እንደሆነ ይጠቁማል። አሁንም የኢትዮጵያ ሕዝቦች ለብሄራዊ ነጻነታቸው መታገል እንዳለበቻውና መኢሶንም የሶቬየት ሕብረት በኢትዮጵያ ላይ ያደረሰችውን ግፍ ለዓለም ሕዝብ የማጋለጥ ኃላፊነቱን እንደሚወጣ ያረጋግጣል።

የሰፊው ሕዝብ ድምፅ

ለሰፊው ሕዝብ ሰራተኛ ገበሬ፣ ነጋዴ፣ ወታደር፣ ምሁር መብትና ጥቅም የሚታገል ጋዜጣ

የኢትዮጵያ ሰፊ ሕዝብ ይቅደም

ቁጥር 73                                                                        ቀን 5/10/72

ብሄራዊ ነፃነትና መኢሶን

“ብሄራዊ ነፃነት ከማናቸውም ነገር በላይ የሚውል ነው”

/ሆቺሚን/

የኢትዮጵያ አርበኞችና አገር ወዳዶች አምስት ዓመት ሙሉ በዱር በገደል የተናነቁትን ፋሺስት ኢጣሊያን ድል አድርገው ከገቡ 39 ዓመት አለፈው።

መጋቢት 28 1933 ዓ.ም ፣ የብሄራዊ ነፃነትና የድል ዕለት ነበር። ያን የድል ዕለትም ከሃዲዎችና አገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን በአንድ መንፈስና በአንድ ዓላማ አያስቡትም። ከኃይለሥላሴ አንስቶ እስከ ዘመኑ ባንዳዎች ድረስ ያለው የፀረ ሕዝብ መንጋ ያን የድልና የነፃነት ዕለት ሲያስብ፣ “ተደፍራ የነበረችው ሃገራችን ዛሬ ነፃነቷን ተጎናፅፋለች” እያለ ለሚመፃደቀው፣ ዛሬ የኢትዮጵያ ሕዝብ ለብሄራዊ ክብሩና ነፃነቱ ማድረግ የሚገባውን ትግል ለማዘናጋት እንጂ ሌላ ፍላጐት ኖሮት አይደለም። የኢትዮጵያ አገር ወዳጆች ደግሞ ያን ዕለት የሚያስቡት “ሲያልፍ ዋዛ” እያሉ ለማዋዛት ሳይሆን፣ ዛሬም የአገራችን ብሄራዊ ነፃነት የተደፈረና የተረገጠ መሆኑን ተቀብለው፣ “ያልፋል፣ እኪያልፍ ያለፋል” እያሉ መራራውን የብሄራዊ ነፃነት ተጋድሎ ለመቀጠል፣ ቃል ኪዳናቸውን እያደሱ ነው። ምክንያቱም ቀላል ነው። ብሄራዊ ነፃነታችን በኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት በአሜሪካ ኢምፔሪያሊዝም የተረገጠውን ያህል፣ ዛሬም በአዲስ መጥ ተስፋፊዎች በመደፈሩ ነው። ኢትዮጵያ የብሄራዊ ከፍተኛ ውርደት አዘቅጥ ውስጥ ሰጥማለች። ዛሬ በዚህ ብሄራዊ ውርደት የማይቆጣና የማይበግን ሃቀኛ ኢትዮጵያዊ ዜጋ አይገኝም። መኢሶንም ከነዚህ ሃቀኛ ዜጎች የሚደመር፣ የሀገር ፍቅር ስሜት የሚያንገበግበው ግንባር ቀደም ድርጅት ነው። ብሄራዊ ነፃነትን የሚያክል የከበረ ውድ ነገር የለምና።

ኢትዮጵያ አገራችን፣ ምንም እንኳ ትላንት የአሜሪካ ኢምፔሪያሊዝም፣ ዛሬ ደግሞ የሶቭየት ህብረትና የቡችሎቿ ቡችላ ሆና በዓለም ሕዝቦች ፊት መሳለቂያ ብትሆንም፣ ስሟና ታሪኳ ከሀገር ፍቅርና ከብሄራዊ ነፃነት ተጋድሎ ጋር አንድ ሆኖ ሲወሳ የቆየላት ኩሩና ታሪካዊት ሀገር ናት። የኢትዮጵያ ሕዝብ በታሪኩ ውስጥ ያጋጠሙትን ወራሪዎች ሁሉ፣ አስፈላጊውን መስዋዕትነት እየከፈለ በመመለስ ለነፃነትና ለክብሩ ቀናተኛና ተጋዳይ ሕዝብ መሆኑን ደጋግሞ ያስመሰከረ ሕዝብ ነው። በሌላ በኩል ደግሞ፣ ለዚህ ክብሩ ከፍተኛ መስዋዕታትን የከፈለው ይህ ታጋይ ሕዝብ ለብዙ ዘመናት በፊውዳሊዝም ጨለማ ታፍኖ እየተበዘበዘ፣ በማሀይምነት፣ በረሃብና በበሽታ ሲቀጣ የቆየ ሕዝብ መሆኑን የማይታበል ሀቅ ነው። የኢትዮጽያ ሕዝብ በእርግጥ ደግሞ እንደጊዜውና እንደሁኔታው ግፍንና ጭቆናን ለመቋቋም እየተነሳ ከግፈኛው ሥርዓት ጋር ተናንቋል። ሆኖም፣ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ያለውን የኢትዮጵያ ሕዝብ የትግል ታሪክ የተመለከተ ሰው፣ የሚረዳው አንድ ሃቅ አለ። ከውጭ ወራሪዎች ጋር ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ክብርና ነፃነት የተደረገው ተጋድሎ ለሕዝቧ እርምጃና ለፍትህ ከውስጥ ጨቋኞች ጋር ከሚደረገው ትግል ጋር እንደሚገባው ተያይዞ አልቀረበም ነበር።

በተለይ ኢምፔሪያሊዝም በዓለም ተንሰራፍቶ የኢትዮጵያ ቀንደኛ ፊውዳሎች ከነዚህ ቀንደኛ የሕዝብ ጠላቶች ጋር በጥቅም ከተላላሱበት ወቅት አንስቶ፣ እንዲህ አይነቱ መዛባት ለሀገሪቱ ክብርና ለሕዝቦቿ ደህንነት ለሚደረገው ትግል ከፍተኛ እንቅፋት ሆኖ ቆይቷል። እንደዚህ በተጣመሩና በሚደጋገፉ ጥንድ ጠላቶች አንፃር አንደኛውን ትቶ ሌላውን “ለመታገል” መሞከር በአንድ እጅ እንደማጨብጨብ ነበር፣ ነውም። ምንም እንኳን ከየካቲት 1966 ዓ.ም ወዲህ ይህ የውስጥና የውጭ ጠላቶች መያያዝ ለመላው ኢትዮጵያ ሕዝብ ግልጽ ቢሆንና፣ ከዳር እስከ ዳር “አብዮታዊት እናት ሃገር ወይም ሞት” የሚለውን መፈክር አንግቦ ቢዋደቅም፣ እንዲህ አይነቱ ጥረት በትግሉ ታሪክ ውስጥ አዲስ ነው።

ፋሺስት ጣሊያን ኢትዮጵያን ስትወር፣ ቀደም ሲል ከሞሶሎኒ ጋር “የወዳጅነት ስምምነት” ተፈራርሞ መንገዱን የጠረገለት ንጉስ ኃይለሥላሴ ነበር። አገሪቱን እጅ እግሯን አስሮና አዳክሞ ለወረራ ያመቻቻት የፊውዳሉ ሥርዓት ነው። ወረራው ሲጀመር፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ በአንድነት ሆኖ እንዳይመክት የከፋፈለውንና ትግሉን ያዝረከረከበት ከኃይለሥላሴ አንስተው የነበሩት ቀንደኛ ፊውዳሊስቶችና ሌሎች በከሃዲ ኢትዮጵያውያን ከወራሪው ጦር ጋር ተዳብለው እናት ሀገራቸውን መውጋታቸው ነበር። ይህም ሆኖ፣ ከሀገሪቱ ዲሞክራሲያዊና ሀገር ወዳድ ኃይሎች ዝቅተኛ የእድገት ደረጃ የተነሳ፣ ፋሺስት ኢጣሊያንን ከኢትዮጵያ ለማባረር የተደረገው ትግል፣ ከፀረ ፊውዳሉ ትግል ጋር በቅጡ አልተያያዘም ነበር።

ስለሆነም፣ ጣሊያን ስለተባረረች የኢትዮጵያ ሕዝብ ሙሉ ነፃነቱን አልተጎናፀፈም። በሚገባ ያልተጋለጠውና ያልተዳከመው ፊውዳል ሥርዓት ከእንግሊዝ “ነፃ አውጪዎች”፣ ከዚያም ከአሜሪካ ኢምፔሪያሊዝም ጋር ተሻርኮ የአንድ ድፍን ትውልድ ዲሞክራቶችንና አገር ወዳዶችን በማውደሙ፣ ግፈኛው ሥርዓት እንደገና ሊያንሰራራ ቻለ። ከ1950 ወዲህ እንደገና ነፍስ የዘራበት ትውልድ ደግሞ፣ የራሱ የሆነ መዛባት ነበረበት። የነግርማሜ /መንግሥቱ ነዋይን አገር ወዳድነት መጠራጠር ባይቻልም፣ ለኢትዮጵያችን ደህንነት፣ ነቀርሳ አድርገው የቆጠሩት ግፈኛውን የፊውዳል ሥርዓትና የሱ ቁንጮ የሆነውን ኃይለ ሥላሴን እንጂ፣ እሱን “በወዳጅነትና በጋራ መከላከያ ስምምነት” አቅፎና ደግፎ የያዘውን የአሜሪካ ኢምፔሪያሊዝምን እስከዚህም ልብ ያሉት ጠላት አልነበረም። እንዲያውም፣በሙከራቸው ወቅት ከፈፀሟቸው አንዳንድ ድርጊቶች ለመረዳት እንደሚቻል በዚህ ትግላቸው የአሜሪካ ኢምፔሪያሊዝምን ቢያንስ ገለልተኛ እናደርገዋለን የሚል የዋህ አስተሳሰብ እንደነበራቸው ግልፅ ነው። በዚህም ወቅት ፀረ ፊውዳሉ ትግል፣ ከፀረ ኢምፔሪያሊስቱ ተጋድሎ ጋር በማይነጠል መልኩ ገና መታየት አልጀመረም ነበር ማለት ነው። ነገር ግን የታህሳሳውያን እንቅስቃሴ በሌሎች ነገሮች ትምህርት ሰጥቶ ያለፈውን ያህል፣ በተለይ የአሜሪካ ኢምፔሪያሊዝም ይህን ሙከራ በመደምሰስ የተጫወተው ሚና፣ ለብዙ ኢትዮጵያውያን ከፍተኛ ትምህርት ሰጥቷል።

የታህሳሱን ትምህርት አጣጥሞና ከርሱ ተከትሎ ያደገው ስመ ጥሩ የኢትዮጵያ ተማሪዎች ንቅናቄ በዚህ አንፃር ሲታይ፣ አንድ ታላቅ የንቃትና የትግል ምዕራፍ  ነበር ለማለት ይቻላል። ከዚህ የተማሪ ንቅናቄ ማደግ ጋር በኢትዮጵያ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ፊውዳሊዝምና ኢምፔሪያሊዝም የኢትዮጵያ ሕዝብ ጥንድ ጠላቶች መሆናቸውን ያመነና ለኢትዮጵያ ዕድገትና ብልጽግና ሲባል ለሚደረገው ትግል፣ እነዚህን ጥንድ ጠላቶች በአንድነት መደምሰስ አስፈላጊ መሆኑን የተገንዘበ ታዳጊ ኃይል ከታሪክ መድረክ ላይ ወጣ። ከዚህ ወቅት አንስቶ፣ ፊውዳሊዝምና ኢምፔሪያሊዝም በኢትዮጵያ ጭቁኖቹ የትግል ውሳኔ ላይ እንደ አንድ ጠላቶች ሰፈሩ።

ከዚህ ከታዳጊው የተማሪ ንቅናቄ ውስጥ መጀመሪያውኑ የሀገር ፍቅራቸውንና የነጻነት ፍላጎታቸው ወደ ማርክሲዝምና ወደ አብዮታዊ ትግል ያመጣቸው ግንባር ቀደም ወጣቶች፣ በነሃሴ ወር 1960 ዓ.ም የመላ ኢትዮጵያን ሶሻሊስት ንቅናቄ ሲመሰርቱ፣ በታሪክ ፊት የተቀበሉት ተግባርና ኃላፊነት ግልጽ ነበር። ትግሉ ከፊውዳሊዝምና ከኢምፔሪያሊዝም ጋር በአንድነት የሚካሄድ የአብዮትና የሀገር ፍቅር ትግል ነበር። መኢሶን በዚያን ጊዜ በፕሮግራሙ ላይ እንዳስቀመጠው፣ ፀረ ኢምፔሪያሊስቱ ትግል በወቅቱ ያተኮረው አገራችንን በተለያዩ ወታደራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና የባህል  “የተራድኦ” ውሎች አውተብትቦ ይዞ በነበረው የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም ላይ ነበር። ነገር ግን ትግሉ ፀረ አሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም ብቻ አልነበረም። ለኢትዮጵያ ክብርና ነፃነትም ነበር። ይህም መሠረታዊ ጉዳይ የምናነሳው ያለምክንያት አይደለም። በተለይ ዛሬ የአሜሪካ ኢምፔሪያሊዝምን “ማባረር” ማለት፣ ለሶቭየት ተስፋፊዎችና ቡችሎቻቸው ማጎብደድ ማለት የሚመስላቸው ከሃድያን የመንግሥት ሥልጣን ይዘው በሚገኙበት ወቅት፣ የሀገር ፍቅር ማለት ለኢትዮጵያ ክብርና ብሄራዊ ነፃነት ቀናተኛ መሆን እንደሆነ በግልፅ መናገር ያስፈልጋል። ይህ ያልገባው ሰው፣ የኢትዮጵያ ሀቀኛ ተራማጆች፣ አገር ወዳዶችና ዲሞክራቶች የዛሬው ትግል ይዘትና ትርጉም ሊገባው አይችልም።

መኢሶን ከተጠነሰሰበት ወቅት አንስቶ፣ ለኢትዮጵያ አብዮት ግብ መምታት የሚደረገውን ትግል ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ነፃነት ከሚደረገው የሀገር ፍቅር ተጋድሎ ነጥሎ የተመለከተበት ወቅት የለም። በአንፃሩም ደግሞ በዚህ ትግል ውስጥ እየተፈራረቁ የተነሱበት ፀረ አብዮት ሀይሎች ሁሉ፣ ከግራ አድርባዩ ከኢህአፓ አንስቶ እስከ “አብዮታዊ” ሰደድና ሌሎች ፀረ ሕዝቦች ድረስ ያለው የከሃዲያን መንጋ፣ በሕዝቡ ላይ ለመጫን የፈለጉትን ቀንበር ለማደላደል ሲሉ በተለያዩ የውጭ ተስፋፊ ኃይሎች ጋር ከመመሳጠር፣ ቃል ኪዳን ከመግባትና እናት ሀገራችንን ከማስማማት የተቆጠቡበት ጊዜ አይገኝም። ስለሆነም፣ የፋሺስት ኢጣሊያን “የስልጣኔ ተልዕኮ”፣ የእንግሊዝን “ነፃ አውጪነት”፣ የአሜሪካ ኢምፔሪያሊዝምን “ልማትና ተራድኦ” ብቻ ሳይሆን፣ ዛሬም የሶቭየት ተስፋፊዎችን “ዓለም አቀፋዊነት” ለመከላከል የተደረገው ትግል ከባእድ ተስፋፊዎች ብቻ ጋር ሳይሆን በባንዳነት ካደሩላቸው ከሀዲ ኢትዮጵያውያን ጋር ጭምር የተደረገና የሚደረግ ትግል መሆኑ ግልፅ ነው። የውስጥ አድሃሪዎችና የውጪ ጠላቶች እንደዚህ የተያያዙም በመሆናቸው፣ የመኢሶን ታጋዮች አብዮታዊ ጥራታቸውን በሀገር ፍቅር ወኔ እያገዙ ለኢትዮጵያ አብዮት ብለው ያፈሰሱት ደማቸው በሀገር ፍቅር ስሜት የነደደ ደም ነው ማለት ይቻላል።

መኢሶን ሲፈጠር አንስቶ ይህንን ጥራት ያለው የአብዮትና የአገር ፍቅር አቋም ሲይዝ፣ እስከ ዛሬም ድረስ ቢሆን አሻፈረኝ ብሎ የቆየው የማንም የውጭ ሀይል ተጠሪ መሆንንና በሚናገረውና በሚሰራው ሁሉ ያስመሰከረው ከኢትዮጵያ ጥቅምና ክብር ሌላ ምንም ነገር ያለማስቀደም አላማ ነው። በውጭ ኃይሎች ድጋፍ ከመኢሶን ተገንጥሎ ራሱን “ኢህአፓ” በማለት በጠራው ስመ ጥፉ ድርጅትና በመኢሶን መካከል ካሉት ልዩነቶች አንዱ፣ እንዲያውም ይህ የአመለካከትና አቋም ልዩነት ነበር። መኢሶን እድሉንና ዕጣውን፣ ህልሙንና ጉጉቱን ከማንም ቅን ኢትዮጵያዊ ሳይለይ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ ወደ ፊት ሲራመድ፣ አብሮ በግንባር ቀደምነት ወደ ፊት የተራመደ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ ወደ በፀረ- አብዮትና በፀረ-ኢትዮጵያ ኃይሎች ጥቃት ሲደርስበት ደግሞ፣ የዚህን ጥቃት ግፊት በግንባር ቀደምነት የተጋፈጠ አብዮታዊ ድርጅት ነው።

የየካቲት አብዮት ከፈነዳ ወዲህ፣ መኢሶን በፕሮግራሙ ላይ የታለመውን የብሄራዊ ነጻነት ጥያቄ፣ ከመሬት ላራሹ፣ ከዲሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብቶች፣ ከብሄረሰቦች እኩልነት…ጥያቄዎች ለአንዲት አፍታ እንኳን ሳይነጥል፣ ለአብዮትና ለእናት ሀገሩ ክብር ትግሉን ቀጠለ። እንደዛሬው የአምባ ገነኖች መፈንጫ ሳይሆን፣ ከጊ.ወ.አ.ደ ጋር በሰራበት ወቅትም፣ ይህንን በኘሮግራሙ ላይ የታለመውን ዓላማ ከሥራ ላይ ለማዋል የአዲሲቷ ኢትዮጵያ የውጭ ፖለቲካ ብሄራዊ ዲሞክራሲያዊ አብዮት ኘሮግራም ላይ እንዲሰፍር አደረገ። በዚህ ኘሮግራም ላይ የተነደፈው መመሪያ፤ አንደኛ፣ በቆየው የኢትዮጵያ ሕዝብ ለነጻነት ቀናተኛና ለብሄራዊ ክብር ታጋይነት መንፈስ፣ የእናት ሀገራችንን ነጻነት ለማስከበር መታገል። ሁለተኛ፣ በአለም ከሚገኙ ተራማጅና ፀረ ኢምፔሪያሊስት ኃይሎች፣ በተለይም በአፍሪካ፣ ከላቲን አሜሪካና ከእስያ ተራማጆች ጋር የትግል አንድነት መመስረት። ሦስተኛ፣ ከሁለቱ ሀያላን መንግሥታት ነፃ የሆነ የገለልተኛ ፖለቲካ ማካሄድ የሚል ነበር። መኢሶንና የኢትዮጵያ ሕዝብ ይሄንን ግልጽ መመሪያ አንግበው ለአብዮትና ለእናት ሀገር ክብር ያካሄዱት ትግል በሁለት ምዕራፎች አልፏል።

የመጀመሪያው የትግል ምዕራፍ ከውስጥ አድሀሪዎችና ከምዕራብ ኢምፔሪያሊዝም ጋር ነበር። በመጋቢት 1969 የጀመረው አዲስ የትግል ምዕራፍ ደግሞ፣ በኢትዮጵያ ሕዝብ በአንድ በኩልና በውስጥ ቀልባሾችና የሶቪየት ተስፋፊዎች በሌላ በኩል ሆኗል።

በመጀመሪያው ወቅት የምዕራብ ኢምፔሪያሊስቶችና ቡችሎቻቸው ለውስጥ አዳሃሪዎች የማቴሪያል እና የፖለቲካ ድጋፍ በመስጠት በሀገሪቱ ላይ ያደረሱትን ጥፋት የኢትዮጵያ ሕዝብ በሚገባ ያውቀዋል። አዎን፣ በአብዮታችን የዲሞክራሲና ሕዝባዊነት ዘመን፣ ኢምፔሪያሊስቶች አብዮታችንን ከዓለም ተራማጆች ለመነጠል የተሳካ ሙከራ አድርገዋል። ችለውም ነበር። የኢትዮጵያ ሕዝቦች በአብዮታቸው የዴሞክራቲክ ዘመን /1966 – 1969/ እነዚያን ሁሉ ያሸበረቁ ድሎች በቀንደኛ ጠላቶቻቸው ላይ ለመጎናጸፍ ቢችሉም፣ በራሳቸው ባደረጓቸው መራራ ትግሎች እንጂ፣ ዛሬ በ“ዓለም አቀፋዊነት” ስም በአገራችን ምድር ላይ የሚጨፍሩት ሶቭየቶችና ቡችሎቻቸው በሰጧቸው የማቴሪያልም ሆነ የፖለቲካ ድጋፍ አልነበረም። በተቃራኒው ይልቁኑ፣ የታሪክ ምፀትዋ ሆኖ እንበለውና፣ የኢትዮጵያ ሕዝቦች በራሳቸው ትግል ያገኙዋቸውን አኩሪ ድሎች መነጠቅ የጀመሩት፣ በሀገራችን ምድር ላይ የሕዝባዊ ዲሞክራሲያዊ ጭላንጭል እየጠፋ የሄደው፣ በጭቁን ብሄረሰቦች ላይ ታሪካችን አይቶት የማያውቀው ግፍ የወረደው፣ የሃገራችን ብሄራዊ ነፃነት እንዳልነበረ ሆኖ የተረገጠውና የተዋረደው፣ አዎ! ሕዝባችን ጥቂት የሥልጣን ጥም ላሰከራቸው ግለሰቦችና ዘመናዊ የሃገር ደላሎች “አሜን” ባይና ተሽቆጥቋጭ እንዲሆን የተደረገው፣ እነዚህ ሶቪየቶችና ተቀጥላዎቻቸው “በአለም አቀፋዊነት” ስም አገራችንን ስርገው ከገቡ በኃላ ነው።

እዚሁ ላይ እንቆይና፤ ታዲያ ለመሆኑ በነዚያ የህዛባዊ አመታት እነሶቪየት ህብረት የት ነበሩ? የውስጥና አለም አቀፍ አድሃሪዎች በአብዮታችን ላይ እንደዚያ እየተረባረቡበት፣ ቢያንስ ቢያንስ “እስከነመፈጠሩ” እንኳን እንዲታወቅ የኢትዮጵያ ታጋዮች አስቸጋሪ የሆነ የፕሮፓጋንዳ ትግል ስናካሂድ፣ እነሱ ይሄንን አብዮታችንን ከብቸኝነት ለማውጣት ምን ሰርተው ነበር? አለም አቀፍ አድሃሪዎች ፀረአብዮት ኃይሎችን እስከ ፀጉራቸው ድረስ እያስታጠቁ በገጠርና በከተማ ይህ ነው የማይባል ጥፋት ሲደርስና የኢትዮጵያ ጭቁን ሕዝቦች  ባንድነት በራሳቸው መሳሪያዎች/ አንዳንዴም በጦርና በዱላ ጭምር/ ከጠላቶቻቸው ጋር እየተጋፈጡ ሲሟሟቱ፣ እነዚህ የዛሬዎቹ “የዓለም አቀፍ ሰራዊቶች” ምን ድጋፍ ለገሱት?

መልሱ ምንም ነው። ነገር ግን ደግሞ የባሰም ሰርተዋል። በአብዮታችን የዴሞክራሲያዊነት ዘመን፣ በአብዮታችን ሕዝባዊነት ዘመን፣ አብዮታችን እውነተኛ ብሄራዊና የኛው የሕዝቦቿና እውነተኛ ታጋይ ልጆቿ ሥራ በነበረበት ዘመን፣ ሶቪየት ህብረትና ቡችሎቿ የፖለቲካና የማቴሪያል ድጋፋቸውን የሚለግሱት ይልቁኑ ለኢህአፓ ከሀዲዎችና ነፍሰ ገዳዮች ነበር። ሶቪየቶች በዚያን ጊዜም ሆነ አሁን የኢትዮጵያ ሃቀኛ ታጋዮችና መኢሶን በግንባር ቀደምትነት ተሰልፈው የሚዋደቁለት አብዮትና ሀገሪቱን ከምዕራብ ኢምፔሪያሊዝም አላቀው ለአዲስ ተስፋፊዎች እንደማያስረክቡ ጠንቅቀው ያውቁታል። አዎን! ከዚህ በላይ እንዳልነው፣ መኢሶን ከእነርሱ ቁጥጥርና እርዳታ ውጪ የተፈጠረ ኢትዮጵያዊ ድርጅት መሆኑንም አጥብቀው ያውቁታል።

በዚህ አንጻር፣ እኛን የመኢሶን ታጋዮች ከሰማዕቶቻችን ባሻገር ሲያኮራን የሚኖረው አንድ ቁም ነገርም፣ ይኸው “እምቢ ለሀገራችን” ባይነታችንና የማንም ተቀጥላ አለመሆናችን ነው። ያሻውን ያህል ታጋዮች በፀረ ሕዝቦች ጥይት እየወደቀ ቢሆንም፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ አኩሪ ድሎችን ሁሉ ያላንዳች የውጭ እርዳታ ለመጎናፀፍ ችሎ እንደነበር አይተናል። ይህንንም መላው ሕዝብ መስክሮታል። ይህ ሀቅ ግን ለታሪክ የሚታይ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን፣ ዛሬም ቢሆን “ሶቭየቶችና ቡችሎቻቸው ያስፈልጉናል” ዘመናዊ የሃገር ደላሎች ለሚነዙት ወኔ ቢስ “ክርክር” የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚመለስባቸው ተጨባጭ የታሪክና የኃይሉ ማስረጃ ነው። እኛ፣ ይህ በራሱ እየተነሳና እየተሟገተ ለነፃነቱና ለክብሩ መዋደቅ ልማዱ የሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ፣ ለወደፊቱም ቢሆን ዳግማዊ የካቲትን ለመስራት በየረድፉ እንደሚንቀሳቀስ ከቶ አንጠራጠርም።

የኢትዮጵያ ሕዝብ በራሱ እየተነሳና እየተሟገተ ዲሞክራሲያዊና ብሄራዊ አብዮቱን ገፋበት። ይህ ሁኔታና የወቅቱ የውስጥ አድሃሪዎችም መዳከም ግን ሶቭየቶችን “ፈረስ እንዲለውጡ” አደረጋቸው። አዲሱ ፈረሳቸው ለመሆን የተመረጠው “አብዮታዊ” ሰደድ ነበር። ከዚያም፣ የኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊና ብሄራዊ አብዮትን የከዳው የ“አብዮታዊ ” ሰደድ አመራር በከፈተላቸው በር ገብተው ሀገሪቱን በቁጥጥራቸው ስር የማዋል ፖለቲካቸውን በአዲስ፣ በተጠናከረ እና በተስፋፋ መንገድ ተያያዙት። ይህ የሶቭየቶች ሀገራችንን በቁጥጥር ሥር የማድረግ ሂደት ራሱን የቻለ አርዕስት ስለሆነ፣ ሌላ ጊዜ በሰፊው የምንመጣበት ጉዳይ ነው። ለማናቸውም በዚህ ሁኔታ በየካቲት ወር 1969 ዓ.ም ፊደል ካስትሮ ወደ ኢትዮጵያ መጣ።

ፊደል ካስትሮ በዚያ ወቅት ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ፣ ለዚህ አብዮት “ድጋፍ” ለመስጠት ቃል ሲገባ፣ የኢትዮጵያ ሀቀኛና ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን ግልፅ የሆነ አቋም መያዝና ማስተጋባት ነበረባቸው። በጊዜው የቀረቡትም መሰረታዊ ጥያቄዎች፣ ሀገሪቷ የአዲስ ተስፋፊዎች ተቀጢላና ቡችላ ሳትሆን፣ በአለም አቀፍ ደረጃ የምትገኝበትን ብቸኝነት በምን ዘዴ ትስበር? የውስጥና የውጭ አድሃዎችን ሴራና ጥቃት በምን ዘዴ ተቋቁማ በድል አድራጊነት ትወጣ? በአንድ በኩል አብዮቷን፣ በሌላ በኩል ብሄራዊ ነፃነቷን እንደምን ትጠብቅ? የሚሉት ነበሩ። በዚህ አዲስ ሁኔታ እንደሚታወቀው መኢሶን ትክክለኛና ተስማሚ ነው ብሎ ያመነበትን አቋም ፊደል ካስትሮ አዲስ አበባን ጎብኝቶ በተመለሰ በሳምንቱ በሰፊው ሕዝብን ድምፅ ቁጥር 53 ላይ ግልፅ አድርጎ ለኢትዮጵያ ሕዝብ አቀረበ። አሰማ።

መኢሶን ድጋፉን፣ ሦስት ዓመት ሙሉ በብቸኝነት ለተጓዘውና በወቅቱ ይህ ነው በማይባል አለማቀፍ አድሃሪዎች ሴራ ተወጥሮ ለተያዘው አብዮት እንደ አንድ ድል የሚቆጠር፣ የአብዮቱን ብቸኝነት የሚሰብር አንድ እርምጃ መሆኑን አምኖ ተቀበለ። ነገር ግን ደግሞ፣ የዚህን ድጋፍ ወሰንና መዘዝም በማያሻማ ሁኔታ ለኢትዮጵያ ሕዝብ አያይዞ አሳወቀ። በዚያን ጊዜ የሀገራችንንና የአብዮታችን እድልን በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ሳይሆን፣ በውጭ “ድጋፍና እርዳታ” ላይ ጥለው አብዮታችንን ወደ ቅልበሳ፣ እናት ሀገራችንን ወደ ብሄራዊ ውርደት ይዘው ለመንጎድ ዳር ዳር የሚሉ ሀይሎች እንዳሰፈሰፉ በግልፅ ጠቆመ። እንጥቀሰው፡-

       “በማንኛውም ጊዜና  ሁኔታ ቢሆን፣ ምንም ያህል ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና የማሕበራዊ ችግሮች ቢኖሩ፣ የፈለገውን ያህል አብዮታውያን በአድሃሪያን ጥይት ቢወድቁም፣ ባጭሩ ማንኛውንም መስዋዕትነት ቢጠይቅምና የፈለገውን ጊዜ ቢፈጅም፣ አብዮታውያን ከሁሉም በላይ መተማመን ያለባቸው በሀያ ስምንቱ ሚሊዮን የኢትዮጵያ ሕዝብና በኢትዮጵያ ምድር ሀብት ላይ ነው። ከዚህ አይነቱ እምነት መዛነፍ የመጣ ዕለትና ተስፋችንን በውጭ ኃይሎች ላይ መጫን ያመጣን እለት የተኮላሸ “በነፃነቷ ለዘላለም ትኑር” የተባለችው ሀገራችን ተመልሳ ከባርነት ሥር የምትወድቅበት ቀን እንዲመጣ ማገዛችን እንደሆነ መታወቅ አለበት” /ስህድ ቁጥር 53፣ መጋቢት 1969/

ይህ ግልጽ የሆነው የመኢሶን አቋም በዚያን ጊዜም ሆነ አሁን፣ በመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ የተደገፈ ነው። ይሁን እንጂ፣ ይህ አቋም ደግሞ፣ በዚያን ጊዜም ሆነ አሁን ብሄራዊ ነፃነትን በብሄራዊ ውርደት፣ በራስ መተማመንን በውጭ ኃይሎች ላይ በመመካት ሊለውጡ ላሰፈሰፉት የውጭ ሃይሎች እና የውስጥ የአገር ደላሎች በጉሮሮ ላይ እንደተሰካ አጥንት ሆነ። ስለሆነም፣ የውስጥ ቀኞች ባንድ በኩል “ሀገሪቱን ወዳጅ ለማሳጣት የሚያሴሩ ድርጅት” ብለው በመኢሶንና በወዳጆቹ ላይ ተነሱ። በሌላ በኩል አዲስ መጪዎቹ ተስፋፊዎች ደግሞ ብሄራዊ ነፃነትና በራስ መተማመን የሚሉት አቋሞች “የከበርቴ ብሄርተኛ አቋም ናቸው” በማለት ዘመቻቸውን ከፈቱ። መኢሶንም፣ ሶቪየት ህብረት የዓለም አብዮቶች መሪ መሆኗን እንዲያምን ከፍተኛ ተፅዕኖ ይደረግበት ጀመር። ይሁንና፣ መኢሶን ባመነበት ዓላማና መስመር ላይ ፀንቶ ቅስቀሳውን አፋፋመ። አስፈላጊውንም መስዋዕትነት ለመክፈል ተዘጋጅቶ በትግሉ ቀጠለ። ሃቀኛ የኢትዮጵያ ተራማጆችና ሰፊው የኢትዮጵያ ሕዝብም፣ ይህንኑ የመኢሶንን አቋም አንግበው “አብዮታዊት እናት አገር ወይም ሞት” በሚለው መፈክር ስር ተሰለፉ።

ይሁንና፣ ሰፊው የኢትዮጵያ ሕዝብ “አብዮታዊት እናት አገር ወይም ሞት” እያለ ለአብዮቱና ለብሄራዊ ነፃነቱ እየተዋደቀ ሳለ፣ የዘመኑ ባንዳዎች የእናት አገራችንን ብሄራዊ ነፃነት በሚያሳፍር ሁኔታ አስደፈሩ። ሶቭየቶች ራሳቸው አስታጥቀውና አሰልጥነው ከለቀቁብን የሶማሌ ወረራ አንስቶ ዘመናዊ ባንዳዎቹ በህዳር ወር 1971 ዓ.ም እስከ ተፈራረሙበት የዘመኑ የውጫሌ ውል ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥ እናት አገራችንን በብሄራዊ ውርደት አዘቅት ውስጥ በመወርወር ዓላማቸውን አገባደዱ። በዚህ ጊዜ ውስጥና እስከ ዛሬ እለት ድረስ በካሀዲዎችና በተስፋፊዎች ይህ ነው የማይባል ግፍና ስቃይ በኢትዮጵያ ሰፊ ሕዝብ ላይ ወረደበት። ይህን ወደፊት በሰፊው እንመለከተዋለን።

ባጭሩ ግን የአሜሪካው ኢምፔሪያሊዝም የእጅ አዙር ቀኝ አገዛዝ በልዩ ልዩ ገፅታዎቹ፣ ዛሬ በሶቭየት ተስፋፊዎችና ተቀጢላዎቻቸው በአገራችን እየተደገመ ነው። የኢትዮጵያ ሕዝብና ግንባር ቀደም ልጆቹ ደግሞ የአሜሪካንን ኢምፔሪያሊዝም የተዋጉት ብሔራዊ ክብራቸውንና ነፃነታቸው እንደዚህ ለሶቭየት ህብረት ለማስከበር እንዳልነበር ግንጽ ነው። መኢሶን ይህንኑ አቋም ለማብራራት እንዳለው፡-

“በመኢሶን በኩል፣ ጠላቶቹን የፈለጉትን ቢያወሩም፣/ አንዳንዶቹ “የሶቭየት ደጋፊ ድርጅት ነበር”፣ ይላሉ፣ ሌሎቹ ደግሞ “የኦሮሞ ድርጅት ነው” ይላሉ፣ ሌሎች ደግሞ “ፈርጣጭ” ይላሉ፣…. የማይሉት ነገር  የለም/ መኢሶን ከሰፊው የኢትዮጵያ ሕዝብ ተለይቶ የሚመኘውና የሚፈልገው ምንም ነገር እንደሌለ እናረጋግጣለን . . . መኢሶን የሚፈልገው ሰፊው ሕዝብ በአብዮታዊ አመፅ ጠላቶቹን ሁሉ ደምስሶ፣ እኩልነትና ነፃነት የሰፈነባት፣ የሕዝቦቿ አንድነት ከብረት የጠነከረበትና ብሄረሰቦቿ ሁሉ ያበቡበት፣ የማንም ተመፅዋች ያልሆነ፣ በራሱ የሚተማመን፣ በማንም ፊት የበታችነት ስሜት ሊኖረው የማይችል፣ በትግልና በመስዋዕትነት ውጤቶቹ የሚኮራ፣ በአለም ሕዝቦች ሸንጐ ተገቢ ቦታውን የያዘ ሕዝብ የሚኖርባት አዲስ ሕዝባዊት ኢትዮጵያ እንድትመሰረት ነው” /ስህድ ቁጥር 55፣ ግንቦት 7 1969 ዓ.ም፣ ቅንፍ የአሁን/

አዎን! መኢሶን አሁንም ትግል እስከመጨረሻው ድል ብሎ በተነሳበት ቆራጥነት፣ አሁንም ይህንን ሁሉ መስዋትነት እየከፈለ የሚታገለው ለእንደዚች አይነቷ ኢትዮጵያ ነው። ይህ ትግል መራራና ረጅምም እንደሚሆን ያውቃል። ይህ ትግል ከሶቪየት ተስፋፊዎች ጋር ብቻም አይሆንም። ከላይ እንዳልነው ምንጊዜም ቢሆን፣ በሀገራችን ብሄራዊ ክብርና ነፃነት መደፈር ጥቅማቸውን አይተውበት ክብራችንንና ሀገራችንን ሸጠው፣ ኢትዮጵያን የሚወጉ “ኢትዮጵያውያን” አሉ። እነዚህ ከተስፋፊዎቹ ተነጥለው አይታዩም። በአንፃሩ ደግሞ፣ እንደ ኢትዮጵያ ባለች የሀገር ወዳዶች ሀገር፣ ከእነዚህ እፍኝ ከማይሞሉ ከሃዲ “ኢትዮጵያውያን” በስተቀር፣ በዚህ ሁኔታ የማያፍርና የማይቆጣ፣ ለትግልም ወኔው የማይቀሰቀስበት ዜጋ አለ ብለን አናምንም። የማይቀረው ድላችን ተስፋና ዋስትና ይህ ነው።

ይህ ለማይቀረው ድላችን ተስፋና ዋስትና የሆነው የሀገር ፍቅር ስሜታችን ደግሞ የሚፈላና የሚገነፍል ነው። ዛሬ ገንፍሏል።

መኢሶን፣ አብዮታችን እንዳይቀለበስና ብሄራዊ ነፃነታችንም እንዳይደፈር፣ በአርቆ አስተዋይነት የተሞሉ ልዩ ልዩ ትግሎችን በልዩ ልዩ ዘዴዎች ሲያካሂድ ቆይቷል። በተለይ ከመጋቢት 1969 አንስቶ እስከ ዛሬ ድረስ መኢሶን ከተስፋፊዎቹና ከቡችሎቻቸው ጋር ባደረገው ፖለቲካዊ ርዕዮተ ዓለማዊና እንዲሁም ዲፕሎማሲያዊ ትግል ውስጥ ብዙ መስዋዕትነት እንደከፈለም የታወቀ ነው። መኢሶን እስከዛሬ ለአብዮቱና ለብሄራዊ ነፃነት ያደረገው ያለፈው ትግሉን መቀጠልና ዛሬ አዲስና ከፍተኛ ምዕራፍ ይከፍታል። ይህ አዲስና ከፍተኛ ምዕራፍ በአንድ በኩል፣ ለብሄራዊ ነጻነትና ለአብዮት፤ በሌላ በኩል ደግሞ ለፀረ ብሄራዊ ነፃነት፣ ተስፋፊ ኃይሎችና ቡችሎቻቸው መካከል የሚካሄድ ግልፅ አብዮታዊ ትግል ነው።

ተስፋፊዎች በሀገራችን ውስጥ ጣልቃ ከገቡ ወዲህ፣ በሀገራችንና በሕዝባችን ላይ ያወረዱት በደልና ግፍ ብዙ ነው። ተስፋፊዎቹ ሶቪየት ህብረት እና ቡችሎቹ፣ ብሄራዊ ነፃነታችንን ረግጠው፣ ዛሬ በኢትዮጵያ ሕዝቦች ላይ የሚወርደውን ግፍና ስቃይ ለማድረስ የተሳካላቸው ቀድሞም ቢሆን የረዥም ጊዜ ዕቅድ አውጥተው ነው። አብዮታችን ከፈነዳ በኃላ ደግሞ እስከ 1969 አጋማሽ ድረስም ብዙ ደባ በኢትዮጵያ አብዮት ላይ ተከትበው ነው። ተስፋፊዎችና የዘመኑ ባንዳዎች በተራቸው የታሪክ ትብያ ሆነው እስከሚወርዱበት ድረስ፣ ይህንንና እስካሁን በኢትዮጵያ ላይ ያደረሱትን ሁሉ፣ መኢሶን ለኢትዮጵያና ለዓለም ሕዝቦች ከእንግዲህ በግልጽ የማጋለጥና የመታገል የሀገር ፍቅርና የብሄራዊ ስሜት ግዴታ አለበት።

ብሄራዊ ነፃነታችን ተረግጧል። ለእኛ ደግሞ፣ ከብሄራዊ ነፃነት የከበረ ውድ ነገር የለም። “ብሄራዊ ነፃነት ከማናቸውም ነገር በላይ የሚውል ነው”።

ሞት ለተስፋፊዎችና ለዘመኑ ባንዳዎች!
ኢትዮጵያ በነፃነቷ ተከብራ ለዘለዓለም ትኑር!
ሰፊው የኢትዮጵያ ሕዝብ ያሸንፋል!
Scroll to Top