ሰሕድ ቁ. 9

የሰፊው ሕዝብ ድምፅ

ቁጥር 9፣    ጥቅምት 5፣ 1967 

የፅሁፉ ፍሬ ሀሳብ

መኢሶን በዚህ የሰፊው ሕዝብ ድምፅ እትሙ፣ለዲሞክራሲያዊ ሥርዓተ ማኅበር ለውጥ በታሪክ ለረጅም ጊዜ በተለያየ መልኩ በሕዝብ ሲካሄድ የቆየ ትግል እንደነበር ያስታውሳል። በ1967 ዓ.ም. መባቻ ላይ ኢትዮጵያ በታሪኳ ትልቅ የለውጥ ዋዜማ ላይ እንደምትገኝ ያረጋግጣል። ይህንንም ታሪካዊ ለውጥ ወታደራዊ ደርግ  ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ለሕዝብ ያበረከተው አድርጎ መለፈፉ አሳፋሪ የታሪክ ሽሚያ እንደሆነ ያጋልጣል። የለውጥ ትግሉ ወታደራዊ ደርግ ከመፈጠሩ በፊትና እንዲያውም ከየካቲት 1966 ዓ.ም. ሕዝባዊ ትግል ቀደም ባሉት ዓመታት የጀመረ መሆኑን በታሪክ ማስረጃ አጠቃሎ ያቀርባል። ቀደም ያሉት የሕዝብ ትግሎች በተለያየ ገጽታቸው፤  በ1953 ታህሳሳውያን፣ በራያና አዘቦ፣ በጎጃም፣ በባሌና በትግራይ ወዘተ. እንደተካሄዱ ይዘረዝራል። በእርግጥም፣ በየካቲቱም 1966 እንቅስቃሴ ቢሆን፤ ልዩ ልዩ ወታደራዊ ክፍሎች በደመወዝ ጭማሪ ጥያቄ ዙሪያ ተነስተው ብቅ ጥልቅ እያሉ በተቃውሞ የትግሉ ተሳታፊዎች እንደነበሩ ያረጋግጣል። እንዲያውም ሀቀኛ ወታደሮችና ዝቅተኛ የአየር ኃይል፣ የመሐንዲስ፣ የሕክምና፣ የሙዚቃ፣ የነገሌው አራተኛ ብርጌድ አባሎች፣ የኮንጎ ዘማቾች ለሕዝብ ጥይቄዎች መልስ እንዲሰጥ በመጎትጎታቸው፤ በወታደራዊው ደርግ ስደስት እንደተገደሉ፤ስደስት እንደቆሰሉ እና በርካቶች እንደታሰሩ ያትታል።የጊዜያዊ ሕዝባዊ መንግሥት ጥያቄ ጎልቶ በሕዝብ መቅረቡ ያሳሰባቸው የደርጉ የጦር መኮንኖች አፄ ኃይለ ሥላሴን አውርደው የመንግሥት ሥልጣን ለብቻቸው እንደጨበጡ ይገልጻል። አያይዞም፣ የሕዝብን ሰብአዊና ፖለቲካዊ መብቶች በተራቸው መግፈፍ እንደጀመሩ ያጋልጣል።    

የሰፊው ሕዝብ ድምፅ

ለሰፊው ሕዝብ ሰራተኛ ገበሬ፣ ነጋዴ፣ ወታደር፣ ምሁር መብትና ጥቅም የሚታገል ጋዜጣ

የኢትዮጵያ ሰፊ ሕዝብ ይቅደም

 
ቁጥር 9                                                                        ቀን 5/2/67

 

ሰፊው ሕዝብ ድሉን ተቀምቶ አይቀርም።

የኢትዮጵያ ሰፊ ሕዝብ ትግል የተጀመረው ትናንት ወይም ዛሬ አይደለም፤ ከአያሌ ምዕተ ዓመታት ጀምሮ በገዥና በተገዥ፡ በበዝባዥና በተበዝባዥ መካከል የመደብ ትግል ሲካሄድ ቆይቷል። የመሳፍንትና የመኳንንት አገዛዝም ራሱ በፈጠራቸው ቅራኔዎች ምክንያት ይወድማል፤ በሌላ በአዲስ በዲሞክራሲያዊ ሥርዓተ ማህበር ይተካል። ይህ ከቶ ሊታለፍ ወይም ሊዘለል የማይቻል ህገ ተፈጥሮ ነው። የሥርዓተ ማህበር ለውጥ ምንጊዜም ቢሆን የከፍተኛ ትግል ውጤት እንጂ ሰላማዊ ሽግግር አይደለም። የለውጥ ወቅት ትልቅ የትግል ወቅት ነው፤ እውነተኛ የሕዝብ ኃይል ጎልቶ የሚታይበት ጊዜ ነው።

ኢትዮጵያ ዛሬ ያለችው በትልቅ የለውጥ ዋዜማ ላይ ነው፤ የንጉሳውያን፣ የመሳፍንትና የመኳንንት ሥርዓት በሕዝብ ኃይል የሚደመሰስበት ጊዜ ነው። ንጉሡና መሳፍንቱ ሰፊው ሕዝብ እንዳይናገር አፉን በሳንሱር ለጉመው፡ እንዳያስብ በስመ እግዚአብሄር ጭንቅላቱን ተብትበው፡ መለኩታውያን ነን ብለው ይገዙት ነበር። አሻፈረኝ ሲልም በወታደር ኃይል ይደመስሱት ነበር። በዚህ በጨለማ ዘመን የሰፊው ሕዝብ ደም አንደውሃ ይፈስስ ነበር። መሳፍንትን፡ መኳንንትንና ከበርቴዎችን ለማክበርና ለማንደላቀቅ ገበሬውና ወዛደሩ መብቱን በሙሉ ተገፍፎ በችጋርና በበሽታ ይማቅቅና ያልቅ ነበር። እንዳያውቅ፡ ችግሩን እንዳያስብ እንዳያሰላስል፡ ለከፋ ኑሮውም የተሻለ መፍትሄ እንዳይፈልግለት መላው ሕዝብ በድንቁርና መስቀል ተባርኮ ነበር።

በአዲሶቹ አምባገነኖች እንደሚሰበከው የኢትዮጵያ ሕዝቦች ወታደራዊውን ደርግ ‘እግዚአብሄር እስኪልክላቸው’ እጃቸውን አጣጥፈው የተቀመጡ አልነበሩም። ከየካቲት 1966 በፊት ብዙ ትግል ተደርጓል። ይህን እውነታ ከደርጉ ‘ምርጥ’ መኮንኖችና ከአንዳንድ አወናባጆቻቸው በስተቀር ለመካድ የሚቃጣ የለም። በሰፈው ሕዝብ አእምሮም በወንድሞቹና በእህቶቹ ደም ተጽፏል። በየገጠሩ የፈሰሰው የጭሰኛው እና የድሃ ገበሬ ደም፡በየከተማውና በፋብሪካዎችም የፈሰሰው የተማሪዎችና የወዛደሮች ደም፡ ከዚህም አልፎ ትልቅ ተጋድሎ አድርገው በአድሃሪ ጥይት የረገፉት የታህሳሳውያን ደም ላንዳፍታም ቢሆን ከህሊናችን የሚጠፋ አይደለም፣ በከንቱ የፈሰሰ ደም አይደለም፣ የኢትዮጵያን ሰፊ ሕዝብ ነፃ ለማውጣት የተሰውት ጀግኖች ክቡር ደም ነው። ይህ ሁሉ ትግሉ የረጅም ጊዜ ትግል፡ ጭቆናው የረጅም ጊዜ ጭቆና መሆኑን ያሳየናል። ለአስራ አምስትና ሃያ ዓመታት ታስረው አሁን የወጡት የነመቶ አለቃ በቀለ አናሲሞስ፡ የነአለቃ ፈጠነ የትግልና የእስራት ዘመን ኃይለሥላሴ የጭቆና አገዛዝ ዘመን ከፊሉ ነው። የኃይለ ስላሴን ዘመነ መንግሥት በሙሉ ከወሰድንማ ለአገሩ ነፃነት ለሕዝቡ ደህንነት ሲታገል ያለቀውን አገር ወዳድ ማን ቆጥሮት?

የገጠሩም ጭሮ አዳሪ ቢሆን ትዕግስቱን ባስጨረሱት ጊዜ በመሳፍንቱ፡ በመኳንንቱና በትላልቅ ባለመሬቶች ላይ ደጋግሞ ክንዱን ማንሳቱ የሚካድ አይደለም። በ1941 ገደማ የትግራይ ሕዝብ በኃይለሥላሴ ከሃዲ መንግሥት አንገዛም ብሎ ተቆጥቶ መታገሉን፡ በቦምብና በጥይት መደብደቡን ታሪክ ሲያስታውሰው ይኖራል። ከዚያም ወዲህ በራያና አዘቦ ሕዝቡ ለመብቱ፡ ለደህንነቱና ለነፃነቱ ተነስቶ በኃይለሥላሴ መንግሥት መደብደቡንና ማለቁን ማን ይክዳል? በ1955ስ በንጉሱ ልጅ በተናኘወርቅ፡ በባልዋ በራስ አንዳርጋቸውና እንዲሁም በሌሎች ነፍጠኞች መሬቱን የተቀማው የደራሳ ሕዝብ ለመሬቱ፡ ለመብቱና ለደህንነቱ ተነስቶ ብዙ ከታገለ በኋላ በኃይለሥላሴ መንግሥት ወታሮች መፈጀቱ በቀላል የሚዘነጋ አይደለም። የባሌና የኦጋዴን ሕዝብስ ቢሆን በርከት ላሉ ዓመታት የመንግስቱን ጦር ገትሮ እንደነበር ማን ይክዳል? ባንድ ፊት በውጭ እጅ የተገዛ ነው እየተባለ የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ ሲደረግበት፡ በሌላ በኩል ደግሞ የረከሰ የአሜሪካን መሳሪያ በታጠቁ የኃይለሥላሴ ወታደሮች በጥይት ሲቆላ፡ ከብቱ ቤቱና ንብረቱ ሲወድም፡ ሚስቱና ልጆቹ ሲታረዱ አልነበረምን? እንደነ ዋቆ ጉቱ ያሉት ባላባቶች ባይከዱና ባያዳክሙት ኖሮ እስካሁን የባሌው ትግል የት በደረሰ ነበር። ከጥቂት ዓመታት በፊትስ የጎጃም ጀግና ሕዝብ መሬቴን አላስነካም፡ የኃይለሥላሴን መንግሥት ባለሥልጣኖች ዘረፋ ዝም ብዬ አልቀበልም ብሎ በመነሳቱ፡ ሽንጡን ገትሮ በመዋጋቱ፡ ከዚያም ቀጥሎ የጎጃምን ሕዝብ በመታው ረሃብ ስንት ሰው አለቀ፡ ስንት ቤት ተፈታ?

ታዲያ፡ ይሄ ሁሉ ትግል ካልሆነ ሌላ ምን ሊባል፣ ምን ስም ሊሰጠው ይችላል? ላቡን ብቻ ሳይሆን ደሙንም ያፈሰሰውን ገጠሬ ትግል ዘንግቶ ተቃውሞውን ከየካቲት ወዲህ፡ በተለይም በወታደሩ፡ ምናልባትም በደርጉ ‘ምርጥ መኮንኖች’ አካባቢ ብቻ መወሰን እንዴት ይቻላል? ኤርትራውያን ወንድሞቻችንም ለብዙ ዘመናት ሲያደርጉ የቆዩት የነፃነት ትግል በቀላሉ የሚታለፍ አይደለም። በውድ ሳይሆን በግድ፡ በማጭበርበርና በማስፈራራት በኤርትራ ሕዝብ ላይ በአንድነት ስም የተጫነበት የመሳፍንት አገዛዝ ያስከተለው መዘዝ፡ ያፈሰሰው የድሃ ሕዝብ ደም እጅግ በጣም ብዙ ነው። ‘ምርጥ መኮንኖቹና’ አቸፍቻፊዎቻቸው ቢያቃልሉትም ለዚሁ ትግል በማወቅም ሆነ ባለማወቅ፡በመደገፍም ሆነ በመቃወም ደማቸውን ያፈሰሱ፣ ዘመዶቻቸውን ያጡ፣ ቤታቸው፣ ቀዬአቸው በሙሉ የወደመባቸው ምን ይሉ ይሆን? የኤርትራ ሕዝብ ከኃይለሥላሴ መንግሥት ጋር ያደረገው ተጋድሎ ቀላል ተጋደሎ አይደለም። እውነቱን ለመናገር ከፈለግን የኃይለሥላሴን መንግሥት ካጋለጡትና ካዳከሙት ምክንያቶች አንዱ የኤርትራውያን ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ትግል ነው።

አድሃሪው መንግሥት የተወጠረው በገጠሩ ሕዝብ ብቻ ሳይሆን በወዛደሩም ጭምር ነው። እንደገጠሬው መሳሪያ ይዞ የመንግሥቱን ወታደሮች ፊት ለፊት ባይገጥማቸውም ከአቅሙ ጋር የተመጣጠነ ብዙ ትግል አድርጓል፤ ብዙ መስዋእትነት ተቀብሏል። መብታቸውንና የጉልበታቸውን ዋጋ ስለጠየቁ ብቻ ብዙ ወዛደሮች ከስራቸው ተፈናቅለዋል፣ ብዙ ቤት በችግር ተፈትቷል፣ ብዙ ታጋይ ወዛደሮች በአድሃሪው መንግሥት ወታደሮች በሳንጃ ተተልትለው፡ በጥይት ተቆልተው ቀርተዋል። አቃቂ፣ ወንጂ፤መልካሴዴ ወዘተ. የወዛደሩ ንፁህ ደም ፈሶባቸዋል። ወዛደሩ ባዶ እጁንም አድሃሪውን መንግሥትና አሰሪዎቹን መቋቋሙ አልቀረም። አንዳንድ አድርባዮች በወዛደሩ አናት ላይ ተቀምጠው ማህበራትን ባያዳክሙ ኖሮማ ትግሉ የት በደረሰ ነበር።

የተማሪዎችስ ትግል ቢሆን ባለፉት 15 ዓመታት እንደታየው በቀላሉ የሚገመት አይደለም። በርከት ላሉ ዓመታት በተከታታይ ተማሪዎች የኃይለሥላሴን አምባገነን መንግሥት ባያጋልጡ፡ የሰፊውን ሕዝብ ችግርና ብሶት ባያጋልጡ ኖሮ አሁን ካለንበት የፖለቲካ ንቃት ደረጃ መድረሳችን ያጠራጥራል። ይህን ሁኔታ ለመፍጠር ብዙ ተማሪዎች ከትምህርታቸው ተፈናቅለዋል፣ ብዙዎች በየእስር ቤቱ ተሰቃይተዋል፣ አካለ ስንኩላን ሆነዋል፣ ብዙዎችም የጥይት ቀለብ ሆነው ቀርተዋል። የታህሳስ 19ና 20 ቀን አልቂት ብቻ አንድ ራሱን የቻለ የትግል መሰረት አይደለምን? አሁንስ በቅርቡ የየካቲቱ ትግል የተፋፋመው በተማሪ ድንጋይ መሆኑን ማን ይክዳል።

ከዚህ በላይ ለማሳየት እንደሞከርነው የሰፊው ሕዝብ ትግል ሲፋፋምና ሲጋጋል ለብዙ ዘመናት የቆየ አንጂ በየካቲት 1966 ሀ..ሁ..ብሎ የተጀመረ አይደለም። ይህን የሚክዱ ካሉ በጣም የዋሆች ወይም አጭበርባሪዎች ናቸው። እርግጥ ከየካቲት ወር ጀምሮ ትልቅ እንቅስቃሴ ታይቷል። ይህም የሚያመለክተው ለብዙ ዓመታት ሲቀጣጠል የቆየው ትግል በጊዜው አመች ሁኔታ ምክንያት በአንድነት ለመያያዝ መሞከሩን ይበልጥ መጋጋሉ፣ መፈንዳቱን ነው።

በየካቲት ወር የተማሪዎች፣ የአስተማሪዎችና የታክሲ ነጂዎች ትግል በልዩ ልዩ ወታደራዊ ክፍሎችም መደገፉ በአገሪቱ ውስጥ ፍፁም አዲስ የሆነ ሁኔታ ተፈጥሮ ነበር። ለዚህም አድሃሪው መንግሥት የሰጠው መልስ ለወታደሩ ከአንዴም ሁለት ጊዜ ደሞዝ መጨመር ነበር። ወታደሩ በዚያን ጊዜ የደሞዝ ጭማሪውን ይዞ ወደ ሰፈሩ ተመልሷል። የቀረው ታጋይ ሕዝብ ግን ያቀረባቸው ዲሞክራሲያዊ ጥያቄዎች ካልተፈፀሙ፡ እነአክሊሉም ከስልጣን ወርደው ካልታሰሩ በስተቀር ፍንክች አንደማይል በማስታወቅ ትግሉን ቀጠለ። የአክሊሉም ካቢኔ ፈረሰ፤ ሚኒስትሮቹም ታሰሩ። ሰፊው ሕዝብ ወታደሩን ግብ በማድረግና ፖሊሱን በድንጋይ በመቋቋም የኃይለሥላሴን መንግሥት እውነተኛ ድካም አሳየ። ሰፊው ሕዝብ የራሱ ጠንካራና አጠቃላይ የትግል ድርጅት ቢኖረው ኖሮ ኃይለሥላሴንና ቡችሎቹን ገፍተር አድርጎ ለትግሉ ደህና መልክ ይሰጠው ነበር። ከኃይለሥላሴ እጅ ያፈተለከች ስልጣን በአየር ላይ ትንሳፈፍ ነበር። በዚህ ጊዜ በተፈጠረው የተምታታ ሁኔታ በመጠቀም እንዳልካቸው መኰንን አንዳንድ ወታደሮችን ደልሎ በሰሜኑ ጦር ድጋፍ የጠቅላይ ሚኒስትርነቱን ስልጣን ያዘ። እንዳልካቸው እግዚአብሄር ነው ያስመረጠኝ እያለ መስበኩን ሲጀምርም ሕዝቡ የእንዳልካቸውን ጠ/ሚኒስትርነት አልተቀበለውም፤ ስለዚህም ‘እንዳልካቸው ይውረድ፣ ከጓደኞቹ ጋር ይታሰር፣ ይሰቀል..’ የሕዝቡ ጥያቄ ሆነ። የኢትዮጵያ ሠራተኞች አንድነት ማህበርም በኢትዮጵያ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የአራት ቀናት የሥራ ማቆም እርምጃ ወስዶ የእንዳልካቸው መንግሥት አናጋው።

እንዳልካቸው ራሱን በሥልጣን ላይ ካመቻቸ በኋላ የፀጥታ ኮሚሽን የሚባል በገንዘብ የተገዛ ጦር አቋቋመ፣ የቴሌኮሙኒኬሽንን የአውራ ጎዳናንና ሌሎችንም ሠራተኞች አስደበደበ፣ አሳብን የመግለጥን ነፃነት ከለከለ፣ ሰብአዊ ብሄራዊ መብቶችን በሙሉ ከሕዝቡ ገፈፈ። በፀጥታ ኮሚሽኑ ክንድ ብዙ ሕዝብ /በተለይ ሠራተኛው/ ተጎሸመ። ብዙ ወዛደሮችም ከሥራ ገበታቸው ተባረሩ፤ 1400 የሚሆኑ የብላቴ የእርሻ ጣቢያ ሠራተኞች ከነቤተሰቦቻቸው በወታደር መኪና ተጭነው በአዋሳ ከተማ እንዲፈስሱ የተገደዱት በዚህ ጊዜ ነው።

እንዳልካቸው የዚህ ክፍል ሕዝብ የዚያ ክፍል ሕዝብ ደገፈኝ እያለ በሃሰት ሲደነፋ ተማሪው፡ አስተማሪው፡ ሠራተኛውና ሥራ አጡ በየፊናው ተቃውሞውን ይገልጥ ነበር። የገጠሩም ሕዝብ ወኪሎቹን እየላከ ብሶቱን ያሰማ ነበር። በየከተማውም ሕዝቡ ምሬቱን በሰላማዊ ሰልፍ ይገለጥ ነበር። በአዲስ አበባ ከሁለት መቶ ሺ የማያንስ ሕዝብ የተሳተፈበትና በሌሎቹም ትናንሽ ከተሞች ከአሥርና ከአስራአምስት ሺ የማያንስ ሕዝብ የተሳተፈበት የሃይማኖት እኩልነት ሰልፍ የተደረገው በዚህ ጊዜ ነበር። በሰልፉም ላይ ‘..ሃይማኖቶች እኩል ይከበሩ፤ መንግሥቱ ከሃይማኖት ውጭ ይሁን፤ እንዳልካቸው ይውረድ፣ የሕዝብ መብቶች ይከበሩ፣ በይጠናል አናምንም…’ የሚሉ ሕዝባዊ ጥያቄዎች ቁጣ በተቀላቀለበት ስሜት ተገልጠዋል። አንዳንድ ለመጣው ሁሉ የሚያጨበጭብ እጅና ቀባጣሪ ምላስ ያላቸው ፀረ ሕዝብ እስስቶች ‘.. ጊዜ እንስጠው..’ እያሉ ቢወተውቱም የእንዳልካቸው መውደቅ በግልጽ ይታይ ነበር።

በዚያን ጊዜ በእንዳልካቸው ላይ ብቻ ሳይሆን በወታደሩም ላይ ሕዝቡ ጥላቻውን መግለጥ ጀምሮ ነበር። የሠራተኛውና የገበሬው ጥያቄ አንዱም ሳይመለስ ወታደሩ ብሩን ጨብጦ ወደሰፈሩ በመመለሱ፡ ከዚያም በመሳፍንት፡ በመኳንንት፡ በባለትልልቅ መሬቶችና በውጭ አገር ከበርቴዎች ጎን ተሰልፎ ወዛደሩንና አርሶአደሩን መጨፍጨፉ ወታደሩን በሕዝብ ዘንድ አስጠላው። ሌላው ሥራ ሁሉ ቀርቶ ወታደሩ በየመንገዱ ቀሚስ ቀዳጅና ጠጉር ሸላች፡ ባህል ጠባቂ መሆንን መረጠ፤ ራሱን ከታጋዩ ሕዝብ ለየ።

በዚህ ጊዜ የኮንጎ ዘማቾችም አበል ጉዳይ በጦሩ ውስጥ ትልቅ ያለመረጋጋት ስሜት ስለፈጠረና የሰፊው ሕዝብ ወገኖች ንጉሱ ለፍርድ እንዲቀርብ፡ ንጉሳዊ አስተዳደር ቀርቶ የሕዝብ መንግሥት እንዲቋቋም መወትወታቸውን ስለቀጠሉ ሶስተኛው ዙር የወታደሮች እንቅስቃሴ በመጠኑም ቢሆን ተራማጅ ጥያቄዎችን ይዞ በደርግ መልክ ብቅ አለ፤ በርከት ያሉ መሳፍንት መኳንንትና ባለስልጣኖችን አሰረ። ከእንዳልካቸው መንግሥት ጎን የደርግ መንግሥት አቋቋመ፤ የስራም ትርምስ ተፈጠረ። የእንዳልካቸውን መንግሥት ማስወገድ እንደሚያስፈልግ በሰፊው ሕዝብ ወገኖች የሚደረገው ትግል ወላዋዩን ደርግ ፋታ አልሰጠውም። ትግሉ ከየከተማው አልፎ በገጠሩም ተስፋፋ።

ሰፊው ሕዝብ ገዢዎቹን ለማዳከም ቢችልም ወደ ስልጣን የሚመራው ጠንካራ ድርጅት አለመኖሩን፡ የእንዳልካቸውም ስልጣን ኃይልን ያልተመረኮዘ፡ ምንም ድጋፍ የሌለው የውሸት ስልጣን መሆኑን ከዳር ቁጭ ብለው ይመለከቱ የነበሩት እነአማን አንዶም በሲአይኤ ድጋፍና አበረታችነት ውስጥ ውስጡን ሲዶልቱ ቆይተው ለማወናበድ ያህል ሚካኤል እምሩን በጠ/ሚኒስትርነት ሾሙ፤ እውነተኛ ስልጣንን ግን አማን አንዶም ከጥቂት ሴረኞቹ ጋር ጨበጠ።

አማንና ሴረኞቹ ወደስልጣን የተሸጋገሩት በኮንጎ ዘማቾች ጉዳይ ነው። የአማን የሴራ ጓደኞች ለኮንጎ ዘማቾች ጉዳይ የተቋቋመውን ኮሚቴ በመጠጋትና ሰርገው በመግባት ቁልፍ ቁልፍ ቦታዎችን ያዙ፤ የደርጉን ሥራ ከኮንጎ ጉዳይ ወደ ጠቅላላ ስልጣን ጉዳይ አዞሩት። እነዚሁ የአማን ሴረኞች በደርጉ ውስጥ በፈጠሩት ኃይለኛ ተጽእኖ አማካይነት አማንን ስልጣን ላይ አወጡት። አማን ከመሰሎቹ ጋር ለረጅም ጊዜ ሲያሴርና ሲዶልት ከቆየ በኋላ በቡችሎቹ በነሻለቃ መንግስቱ ኃይለማርያም አማካይነት አቢይ አበበን አስነስቶ ወታደራዊ ሥልጣንን አጠቃሎ ያዘ፤ ለሴራ ጓደኞቹም ቁልፍ ቁልፍ ቦታ ሰጣቸው። ደርጉም በጠቅላላው ወታደር ዘንድ ያለውን አነስተኛ ተቀባይነት በመገንዘብ አማን በየቦታው እየተዘዋወረ የጠቅላላውን ጦር ድጋፍ ለማግኘትና የትእዛዝ ሰነሰለቱን መልሶ በወታደሩ ላይ ለመጫን አራምባና ቆቦ ዘለለ። የኤርትራን ሕዝብም ትግል አቆማለሁ በሚል የተወናበደ ተስፋ የኤርትራን ሕዝብ ለማታለል ሞከረ፤ በኋላም ማስፈራራቱን ጀመረ።

ከወታደራዊው ደርግ ውስጥ ራሳቸውን አጠንክረው በመውጣት ከሲአይኤ ጋር ቀጥታ ግንኙነት የጀመሩት ጥቂት መኮንኖች የአድሃሪውን መንግሥት የጭቆና መሳሪያዎች በሞላ ጎደል እንዳሉ ትተው በኃይለሥላሴ መንግሥት የአገር ወዳዶችን ሕይወት ማጥፊያ ድርጅት መሪ የነበረውን ኰሎኔል በላቸው ጀማነህን የአገር ግዛት ሚኒስትር ብለው ሾሙ። አማን አንዶምንም ያለወታደሩ ምርጫና ፈቃድ የደርጉ ሊቀመንበር አደረጉት።

በኢትዮጵያ ሕዝቦች ላይ ለደረሰው ግፍና መአት ንጉሱ ዋና ተጠያቂ በመሆኑ ንጉሱ ከስልጣን ወርዶ ለፍርድ ይቅረብ፣ ቅጣቱንም ይቀበል፣ ደንበኛ ዲሞክራሲያዊ ሕገመንግሥት እሰኪወጣና ትክክለኛ በሆነ የሕዝብ ምርጫ ሕዝባዊ መንግሥት እስኪቋቋም ድረስ ከወታደሩም ከሲቪሉም በምርጫ የተውጣጣ ጊዜያዊ ሕዝባዊ መንግሥት ይቋቋም የሚለውን የሕዝብ ጥያቄ መፋፋም በማየት በመስከረም 2 ቀን 1967 ንጉሱን ከዙፋኑ አወረዱ፤ አማንን የካቢኔውም ሰብሳቢ /ሊቀመንበር/ አድርገው በመሾም ‘ጊዜያዊ’ የሚል የማታለያ ቅጥያ ከሕዘቡ ፍላጎትና ጥያቄ ውጭ የሆነውን እርምጃ ወሰዱ፤ ወታደራዊ አስተዳደር መሰረቱ፤ ብሄራዊ ሰብአዊ መብቶችን እንደገና ከሕዝቡ ላይ ሙልጭ አድርገው ገፋፉ።

መጀመሪያ ነገር ሰፊውን ሕዝብ ሲጨፈጭፍ የኖረ ወታደር መንግስታዊ ስልጣንን ሊቀዳጅ የቻለው ሕዝቡ የራሱን የትግል ድርጅት አቋቁሞ ስልጣንን በእጁ ለማግባት ባለመቻሉ ነው፣ ስፊው ሕዝብ መብቱን ተገፍፎ ታፍኖ በመቆየቱ ነው። አሁንም ቢሆን የሕዝቡ ዋና ጥያቄ ችግሮቹን ሊፈታ መብቶቹን ሊያስከብር የሚችልበት ዲሞክራሲያዊ አስተዳደር ነው። ሕዝቡ አጥብቆ የጠየቀው ዲሞክራሲን ነው። ኃይለሥላሴ ሃምሳ አመት ሙሉ ጨቁኖ ሲገዛን የኖረው ለዲሞክራሲ አልደረሳችሁም በሚል ሸንካፋ ምክንያት ነው። እንዳልካቸው እንኳን በገዛበት በነዚያ ጥቂት ወራት ውስጥ ‘..ጊዜያዊ ነኝ…ከዚያ በኋላ በሕዝቡ ምርጫ ዲሞክራሲያዊ መንግሥት ይቋቋማል…’ ይበል እንጂ ሰብአዊ መብቶቻችንን ገፍፎ እንዳንደራጅ አድርጎን ነበር። አሁንም እነዚህ ጥቂት መኮንኖች የሕዝቡን መብት ጨርሰው ገፍፈው፡ አፋችንን ለጉመው ‘..ቆዩ ጠብቁ᎓ ሕዝባዊ መንግሥት ማቋቋም እምትችሉበት ሁኔታ ላይ እስክትደርሱ ድረስ የወታደር አገዛዝ ያስፈልጋል…’ ይሉናል፤ ከመሄዳችን በፊት የመሳፍንትን ርዝራዦች ጨርሰን ማጥፋት᎓ ፊውዳሊዝምን ከስሩ መንቀል᎓ መሬትን ላራሹ መስጠት አለብን ይሉናል። አሁን ግን ሕዝቡ እንዳይደራጅ አጥብቀው ይከለክላሉ። ኧረ ለመሆኑ ሕዝቡን እንዳይደራጅ እየከለከሉ፡ ያለሕዝቡ ድጋፍ ወታደር እንዴት አድርጎ ነው ፊውዳሊዝምን የሚያጠፋው፣ እንዴትስ ነው ወታደር መሬትን ላራሹ የሚሰጠው፣ በየት አገር ነው እንዲህ ያለ ነገር ተሰርቶ የሚያውቀው?

በወታደሩ ውስጥ አገር ወዳድነት ያላቸው የሕዝብ ወገኖች እየታደኑ በመታሰርና በመገደል ላይ ናቸው። ከሲቪሉም ቢሆን ተራማጆች ከመሳፍንትና ከመኳንንት እኩል እንደ ሕዝብ ጠላት ተቆጥረው በመታደን፡ በመታሰር ላይ ናቸው። በየገጠሩም መሬት ፈላጊው አርሶአደር በወታደሮች በባለመሬቶች ጥይት እየተቆላ በማለቅ ላይ ነው። ተማሪውንም ለመከፋፈል የሚደረገው ዘመቻ ቀላል አይደለም። ታዲያ ይህ ወታደራዊ አገዛዝ ለሕዝብ አንዳንድ ማታለያዎችን አልፎ አልፎ ከመወርወር በስተቀር ሊሰራ የሚችለው ምን ነገር አለ? ምንም አይታየንም። የኃይለሥላሴን የጭቆና አገዛዝም ቢሆን ያወደመው ሕዝቡ በመላ እንጂ ወታደሩ ብቻውን አይደለም። ታዲያ ሰፊው ሕዝብ በላቡና በደሙ ያፈራውን ድል ወስዶ መመፃደቅ ሃቁ ምኑ ላይ ነው? ሃቀኝነት ከሌለ ደግሞ የሚረባ ሥራ መስራት አይቻልም፤ ተጋልጦ መውደቅም አለ።

ሶስተኛው ዙር የወታደሮች እንቅስቃሴ በመሰረቱ በተራ ወታደሮች የተጀመረ ተራማጅ እንቅስቃሴ ነበር። በጠቅላላው የደርጉን ሥራ ስንመለከት በመጀመሪያ ብዙ የማወላወልና የማመንታት ዝንባሌ ቢያሳይም በቅንነት ላይ የተመሰረተ ይመስል ነበር። ነገር ግን ቀስ በቀስ በሲአይኤ የተገዙ ‘ምርጥ መኮንኖች’ አመራሩን ከያዙ በኋላ የደርጉ ሥራ በሙሉ የነዚህን ጥቂት ሰዎች ጠማማ ፍላጎት የተከተለ፡ በማወናበድ የተሞላና ፋሽስታዊ መልክ ጎልቶ የሚታይበት መሆኑ ግልጽ ነው። ሰው የሚማረው ከተግባር ነውና እስካሁን ባየነው መጠቆም የምንችላው ይህ ወታደራዊ አገዛዝ አወናባጅና ፀረ ሕዝብ ከመሆኑ የተነሳ ዘላቂነት እንደሌለው ነው። እነርሱ መሳሪያ ይዘው ሲንደፋደፉ የአገሪቱ ኢኮኖሚ እያቆለቆለ በመውረድ ላይ ነው። ስለዚህ የሕዝቡ ኑሮ በዚሀ በወታደራው አገዛዝ ውስጥ የባሰውን ይበላሻል እንጅ አይሻሻልም። ለዚህ ማስረጃ ፍለጋ ብዙ መሄድ አያሻም፤ ከሥራ የሚባረሩትን፡ ሥራ አጥተው በከፍተኛ ችግር ላይ የሚገኙትን ሰዎች ብዛትና የጠቅላላውን ንግድ መዳከም መመልከቱ ይበቃል።

በመካከላቸው ያለውም ንትርክ እየበዛ እንጂ እያነሰ አይሄድም። እነዚህ ጥቂት መኮንኖች ከተሳካላቸው ሁሉንም አፍነው ደርጉንም ራሱን በመበተን አማን አንዶምና በላቸው ጀማነህ ከጥቂት ‘ምርጥ’ መኮንኖች ጋር በመሆን ‘እግዚአብሄር’ የመረጠው ዘለአለማዊ መንግሥት ያቋቁማሉ።

ፍላጎታቸው ይህ ሆነም አልሆነ ዋጋ የለውም፤ አይሰምርላቸውም። ያለቀው ቢያልቅ የሰፊው ሕዝብ ትግል ከንግዲህ እያደገና እየጎለመሰ እንጂ እየቆረቆዘ አይሄድም። ሁለተኛ ባርነትን አንሻም፤ ባለን ኃይልና ዘዴ እሰከመጨረሻው የደማችን ጠብታ እንታገላለን። ሕዝባዊ መንግሥትም ይቋቋማል። ያለሕዝባዊ መንግሥት ኢትዮጵያ ልታድግ የሕዝቦችም ኑሮ ሊሻሻል አይችልም። መንገዱ በወታደርና ሲቪሉ ወንድሞቻችን ደም ታጥቧል። ፋናቸውን እንከተላለን፤ እስከመጨረሻው ድል እንታገላለን።

 

 

አምባገነን ወታደራዊ አገዛዝ ይውደም
ጊዜያዊ ሕዝባዊ መንግሥት ይቋቋም።

የደም ድምጽ

በመስከረም 27/67 ለሕዝባዊ መንግሥት ሲሉ ደማቸውን ያፈሰሱት የምድር ጦር መሃንዲስ አባሎች የሰባት ቀን ቁርባን ያለፈው ሰኞ ነበር። የሰፊው ሕዝብ የትግል እንቅስቃሴ በየካቲት ፈንድቶ መቀጣጠል ከጀመረ ወዲህ አየር ኃይል፡ የቦረና ነገሌው 4ኛ ብርጌድ᎓ የምድር ጦር መሃንዲስ᎓ የምድር ጦር የአየር ክፍል /አርሚ አቪየሽን/፡ የህክምና መምሪያ፡ 17ኛ ሻለቃ፡ የሙዚቃ ክፍል፡ የኮንጎ ዘማቾች፡ የክብር ዘበኛ ጦር፡ ቁራጩና ፍላጩ ከሆነው ከሰፊው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጎን በመሰለፍ የሕዝብ መንግሥት ይቋቋም በማለት ድምፃቸውን አሰምተዋል፤ አብዛኞቹ አሁንም በማሰማት ላይ ናቸው።

     ቆራጦቹ የምድር ጦር መሃንዲስ አባሎቸ ግንባር ቀደሞቹን የሕዝብ ወገኖች ከመካከላቸው አሳልፈን አንሰጥም በማለት ለአዲሱ ዘመን የመጀመሪያዎቹን የኢትዮጵያ ሰማእታት አበርክተዋል። በዚህ አንጻር በቀደምለት የክብር ዘበኛ ጦር ግንባር ቀደም መሪ የነበረውን ሻምበል ደምሴ ተፈራን ለ‘ምርጦቹ’ አሳልፎ መስጠቱ በጣም የሚገርም ነው። የምድር ጦር መሐንዲሶች ጓደኞቻቸውን አሳልፈን አንሰጥም በማለት መሳሪያ ሳይይዙ ከሀረር በመጣ ጦር በከባድ መትረየስ ቢደበደቡ፡ የአርሚ አቪየሽን /አየር ክፍል/ እንደዚሁ መሪያዎቻቸውን አሳልፈን አንሰጥም፤ ሁላችንንም ያዙን ብለው ሳይነጣጠሉ ታፍሰው ታሰሩ። ክብር ዘበኞች ግን እንዴት ጓደኞቻቸውን /ከሻምበሉ ጋር ወደ ስምንት ሳይደርሱ አይቀርም/ ያለምንም መቋቋም አሳልፈው ሰጡ::

የአዲሱ ዓመት ሰማእታት /የሞቱ/፡

  1. የሃምሳ አለቃ መንግሥትአብ ኃይሌ
  2. ም/ የአሥር አለቃ መኮንን ካሳ
  3. ም/አሥር አለቃ ጣሰው ኃ/ሚካኤል
  4. ም/ አሥር አለቃ ብርሃኑ መሃሪ
  5. ም/ አሥር አለቃ ወ/ሚካኤል ከበደ

የቆሰሉ/ ከመካከላቸው ቆይተው የሞቱም አሉ፤ እነማን እንደሆኑ ለመለየት አልቻልንም/።

  1. ሻለቃ በሻ ኢተና በርኬሳ
  2. የሃምሳ አለቃ በቀለ ተክሉ
  3. ም/ የአሥር አለቃ በቃና ሙታር
  4. ም/ የአሥር አለቃ ወ/ጊዮርጊስ ታቱ
  5. ም/ የአሥር አለቃ ስንታየሁ አደገ
  6. ወታደር እንዳልካቸው አስፋው

እነዚህን ግንባር ቀደም ሰማእታት ኢትዮጵያ ሕዝብ ሲያስታውሳቸው ይኖራል፤ የደማቸው ባለእዳ ነው። የእነዚህ የሕዝባዊ   መንግሥት ሰማእታት ደም፡ እንደጎርፍ የፈሰሰው ንፁህ ደም ለምልሞ የሚያሳድጋቸው ንፁህ አትዮጵያውያን ሰማእታቱ የተሰውለትን የትግል አርማ ይዘው ትግሉን ይቀጥላሉ። ሕይወታችሁን የሰዋችሁለት ደማችሁን ያፈሰሳችሁለት አላማ እስኪሟላ ድረስ ግንባር ቀደም ተራማጆች ከቶ እረፍት አይኖራቸውም።

 የሰማእታቱ ደም በከንቱ አይቀርም
 ዲሞክራሲ ድል ያደርጋል
      ፋሽዝም ይወድማል።

አጫጭር የትግል ዜናዎች

  1. የሠራተኞች ችግር፡-

ኢኮኖሚው አቆልቆሎ በመንኮታኮት ላይ ነው። ነጋዴዎች ወደውጭ የመላኩንና ከውጪ የማስመጣቱን፡ አገርም ውስጥ የመግዛቱንና የመሸጡን ነገር ችላ እያሉት ሄደዋል። ብዙ የንግድ ድርጅቶች ተዘግተዋል አሁንም በመዘጋት ላይ ያሉ ብዙ ናቸው። የአገር ውስጥ ፋብሪካዎች በኃይል እየተዳከሙ በመሄድ ላይ ናቸው። የውጭ አገር ከበርቴዎች ገንዘባቸውን ይዘው እግሬ አውጭኝ ሲሉ ብሔራዊ ከበርቴዎች ደግሞ ገንዘባቸውን በየስርቻው በማሸሽና በመቅበር ላይ ናቸው።

ይህ ሁሉ ላብአደሩን ጦሙን ሊያሳድረው ነው። አሰሪው ከስሬአለሁ በማለት እንኳን አዲስ ሠራተኛ ሊቀጥር ቀርቶ በሥራ ላይ ያለውንም ዝም ብሎ በማባረር ላይ ነው፤ ደርጉ ለአሠሪዎች የሰጠው የአንገት በላይ ማስጠንቀቂያ ምንም ለውጥ አላመጣም። ሰኞ ጥቅምት አራት ቀን ቁጥራቸው በርካታ የሆነ ስራጦች ‘ሥራ ሥራ ሥራ ይሰጠን፡ ሰርተን እንድንበላ ሥራ ይሰጠን፡ በችጋር አለቅን’ ወዘተ በማለት በባቡር ጣቢያ አካባቢ ሰላማዊ ሰልፍ አድርገው ወደ አራተኛ ክፍለ ጦር አምርተዋል።

የቴሌኮሙኒኬሽን ‘የቀን ሠራተኞች’ የቀን ሠራተኛ ተብለን ሃያ ዓመት ያህል ስንሰራ ቆየን፡ እንዴት ቋሚ ሠራተኛ አንሆንም በማለት ከየካቲት ጀምሮ ከአሰሪው ጋር ትግል ሲያደርጉ ነገሩ ከዛሬ ነገ እየተጎተተ እስከዛሬ ቆዩ። ነገሩ ስለተንዛዛ ‘የቀን ሠራተኞቹ’ ቆራጥ እርምጃ በመውሰድ መስከረም 25/67 የክፍሉን አለቃና ሥራ አስኪያጁን ቢሮ ውስጥ አስረው በመጨረሻ አንዳንድ መተማመኛ በማግኘት ለቀቋቸው።

የአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት የመንገድ ጽዳት ሠራተኞች ከመስከረም 27/67 ጀመረው ሥራ በማቆም ጉዳያቸውን አስፈጽመዋል።

መስከረም 25/67 ያለአግባብ ከሥራ ተባርረው ደጅጥናቱ ያጎበጣቸው፡ መጉላላቱ እጅ እጅ ያላቸው፡ ችግር የበዛባቸው በመቶ የሚቆጠሩ ሠራተኞች በሕዝባዊ ኑሮ እድገት ያሰሪና ሠራተኛ ጉዳይ ክፍል ሹማምንትን ከቢሯው ውስጥ አናስወጣም በማለት ለጉዳያቸው ተጨባጭ መልስ ለማግኘት ችለዋል።

በሃረርጌ ክፍለአገር በአለምማያ ኮሌጅ ሠራተኞቹ አማረ የተባለውን የኮሌጁን አስተዳዳሪ ከቦታው እንዲነሳ ደጋግመው ጠይቀው ሳይሆን ስለቀረ በመጨረሻ እዚያው አስረውታል።

 

 

 

 

  1. የተራማጆች መታፈንና መታሰር፦

በጥቂት እርስ በርሳቸው በተመራረጡ መኮንኖች የበላይ መሪነት የሚካሄደው የወታደር መንግሥት የኃይለሥላሴን መንግሥት በቆራጥነት በመቋቋም ለብዙ ዓመታት በአለም በቃኝ የማቀቁትን እነኮሎኔል እምሩ ወንዴን፡ እነአቶ ዘውዴ በዳዳን᎓ የሕዝብ መንግሥት ይቋቋም፡ የወታደር መንግሥት ለኢትዮጵያ አያስፈልጋትም ብለዋል ተብለው ከቀድሞዎቹ ጨቋኞች ጋር 4ኛ ክፍለ ጦር ውስጥ ተይዘው ታስረዋል።

ከትምህርት ቤት ጀምሮ በተራማጅነቱና በታጋይነቱ የታወቀው ዶክተር እሸቱ ጮሌም በዚሁ ምክንያት ከተጠቀሰው ስፍራ ከቀድሞ የኃይለሥላሴ የግፍ ግብረአበሮች ጋር ተይዞ እንደታሰረ ባለፈው ቁጥር ተገልጧል። ‘የምርጦቹ’ መንግሥት ግን እስካሁንም ምንም አይነት መግለጫ አልሰጠም።

ከአለማያ ኮሌጅ ቁጥራቸው ከ50 በላይ የሚገመት ተማሪዎች፡ አስተማሪዎችና ሠራተኞች ታፍነው ወደ ኦጋዴን በረሃ መወሰዳቸው ይወራል። ምክንያቱ ያው ሕዝባዊ መንግሥት ነው።

በአዲስ አበባም ብዙ ተማሪዎች የወታደር መንግሥት የኢትዮጵያን ችግር ሊፈታ አይችልም፡ ሕዝባዊ መንግሥት ይቋቋም በማለት ሰሞኑን በማከታተል ሰልፍ አድርገዋል። ብዙዎች ተደብድበዋል፣ ቆስለዋል፣ ታስረዋል የታሰሩት ቁጥራቸው ምን ያህል እንደሆነ በእርግጥ አልታወቀም። ትግሉ ግን በየቦታው እየቀጠለ ነው።

ከሻምበል ደምሴ ተፈራ ጋር በርከት ያሉ የክብር ዘበኛ አባሎች /ምናልባትም የንዑስ ደርጉ አባሎች በሙሉ/ መያዛቸውና መታሰራቸው ይወራል። ደርጉ ሻምበሉን አወናባጅ ቢለውም እርሱም ሆነ ጓደኞቹ የወታደርን መንግሥት የሚቃወሙና የሕዝብ መንግሥት እንዲቋቋም ደጋግመው እንደጠየቁ የአደባባይ ምስጢር ነው፤ ከአወናባጅነት በጣም የራቀ ነው።

የምድር ጦር መሐንዲስና የአርሚ አቪየሽን አባሎች ከስድስት መቶ በላይ የሚሆኑ በጅምላ መታሰራቸው ቀደም ብሎ ታውቋል። አንዳንድ ግንባር ቀደሞቹ በጨለማ ቤት ውስጥ ተይዘው በመሰቃየት ላይ ሲሆኑ አብዛኞቹን ግን ወደ ሆለታ ወስደው አስረዋቸዋል። ይህ ሁሉ የወታደር መንግሥትን በመቃወም ሕዝባዊ መንግሥት እንዲቋቋም ፊት ለፊት በመጋፈጣቸው ነው፤ የትግሉ ግንባር ቀደም በመሆናቸው ነው።

በየክፍለ ሃገሩና በየአውራጃውም የወታደሩን መንግሥት በመቃወም፡ የሕዝብ መንግሥት ይቋቋም በማለት ድምፃቸውን ያሰሙ የነቁ ተራማጆች እየታፈኑ ናቸው። በሲዳሞ፣ በሃረርጌና በሌሎችም ክፍለ ሃገሮች በርከት ያሉ ሰዎች ታስረዋል፤ ቁጥራቸውና ሁኔታቸው ገና በደንብ አልታወቀም።

Scroll to Top