ሰሕድ ቁ. 65

የሰፊው ሕዝብ ድምፅ

ቁጥር 65፣      ታህሣሥ 21፣ 1970

የፅሁፉ ፍሬ ሀሳብ

መኢሶን በዚህ እትም፣ “የወዛደር ፓርቲ በአስቸኳይ ይመስረት” የሚሉ አድርባዮች ወዛደሩ በገዛ ጥረቱ ከሚያቋቁመው ፓርቲ ቀድመው የራሳቸውን አላማ የሚንጸባርቅ ፓርቲ በአቋራጭ ለመመሥረት የሚያደርጉት ሙከራ መሆነን ይጠቁማል። በዚህ ትግል ውስጥ አብዮታዊያን ለሃቀኛ የወዛደር ፓርቲ መመስረት መታገል እንዳለባቸው ካስገነዘበ በኋላ፣ ለአብዮቱ ድል በወዛደሩ ፓርቲ የሚመራና ሌሎች የኅብረተሰቡ ክፍሎች የሚሳተፉበት ሰፊ ግንባር አስፈላጊና ወሳኝ መሆኑን ያስገነዝባል።

የሰፊው ሕዝብ ድምፅ

ለሰፊው ሕዝብ ሰራተኛ ገበሬ፣ ነጋዴ፣ ወታደር፣ ምሁር መብትና ጥቅም የሚታገል ጋዜጣ

የኢትዮጵያ ሰፊ ሕዝብ ይቅደም

ቁጥር 65                                                                       ቀን 21/5/70

 

የወዛደር ፓርቲ በአስቸኳይ ወይስ በአቋራጭ?

የመላ ኢትዮጵያ ሶሻሊስት ንቅናቄ በሀገራችን አብዮት አንገብጋቢ ጥያቄዎች ላይ ለትግሉ ይበጃል የሚላቸውን አቋሞች ከመሰንዘር ተቆጥቦ አያውቅም። በተራማጆች መካከል ልዩነቶች እንዳሉና እነዚህ ልዩነቶች በውይይት እንዲፈቱ ተደጋጋሚ ጥሪዎችን አድርጓል። ብዙን ጊዜ ግልጽ አቋም የሌላቸው ወይንም ደግሞ ያላቸውን አቋም በይፋ በሕዝብ ፊት ማብራራት የማይደፍሩ አድርባዮች ያሉትን መሰረታዊ ልዩነቶች በማቃለል የሰው አስተሳሰብ በተራ አሉባልታዎች ላይ እንዲያተኩር ይሞክራሉ። እንዲያውም መኢሶን “የቡድን ስሜት” ያጠቃዋል፣ መኢሶን “ሥልጣን የጠማው” ድርጅት ነው የሚሉት መሰረተ ቢስ አሉባልታዎች የመነጩት አድርባዮች ከሀቀኛ የመስመር ትግል ለመሸሽ ከሚያደርጉት ሙከራ ለመሆኑ ዛሬ ለማንም ግልጽ እየሆነ የሄደ ሀቅ ነው። የዚህ አሉባልታ ዓላማ “እስከዚህም የመስመር ልዩነት የለም፣ በተራማጆች መሃከል መከፋፈል ቢኖር መኢሶን አንድነትን ስለማይፈልግ፣ የቡድን ስሜት ስለሚያጠቃው፣ የሥልጣን ጥም ስላለበት ነው” በሚል ሽፋን ከክርክር በማምለጥ ነው።

እንደሚታወቀው መኢሶን የሥልጣን ጥም ያጠቃዋል መባል የጀመረው ዛሬ አይደለም ትላንት ንኡስ ከበርቴውና አድሃሪው ቢሮክራሲ ከዳር እስከ ዳር የተለቀቁበት ዜና ነበር። ነገር ግን መኢሶንና ሌሎች ሀቀኛ አብዮታዊያን ባካሄዱት መራራ ትግል ማን የሥልጣን ጥም እንዳሰከረው ማን በእርግጥ ለሰፊው ሕዝብ ሥልጣን እንደሚታገል ታየ። መኢሶን “በነቃ፣ በተደራጀና በታጠቀ ሕዝብ አመጽ” የሚያምን፣ በረጅም ጊዜ ትግል ለሕዝባዊ ሥልጣን የሚታገል፣ በአቋራጭ ሥልጣን ለመያዝ የሚፈልጉ አወናባጆችን ያለ አንዳች ርህራሄ የሚዋጋ ድርጅት መሆኑ ተረጋገጠለት። ታዲያ እንዲህ ሆኖ ሳለ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ቢሮክራሲ የተለቀቀበት “የመኢሶን የሥልጣን ጥም” ከየት መጣ?

በመሠረቱ የማንኛውም የአብዮት ጥያቄ የሥልጣን ጥያቄ ነው። ስለሆነም “መኢሶን ለሥልጣን የሚታገል ድርጅት ነው” ማለት መኢሶን በአብዮቱ ትግል ውስጥ ይሳተፋል እንደማለት ያህል አስቂኝ “ክስ” ነው። ጥያቄው አንድ ታጋይ ድርጅት ለሥልጣን ይታገላል ወይስ አይታገልም ሳይሆን ያድርጅት ለየትኛው መደብ የበላይነት ይታገላል የሚል መሆን አለበት። በዚህ በኩል መኢሶን ከውሃ የጠራ የፖለቲካ አቋም አለው። መኢሶን ሰፊው የኢትዮጵያ ሕዝብ ነቅቶ፣ ተደራጅቶ፣ ታጥቆ የሥልጣን ባለቤት እንዲሆን፣ የገዛ እድሉ ወሳኝ እንዲሆን የታገለና የሚታገል ድርጅት ነው። በዚህም አቋሙ የተነሳ በሕዝብ ፊት ከሕዝብ በፊት ለመያዝ የሞከሩትን አቋራጮች ያለ ርህራሄ ተዋግቷል። “የሥልጣን ጥም” የሚባለው ክስ የሚወረወረው ብዙን ጊዜ ለሕዝብ ሥልጣን ሳይሆን “ለራሱ” ይቋምጣል ለማለት ነው። በዚህ አቅጣጫ ስንሄድ ግን ቁልጭ ብሎ የምናየው ሀቅ ምንድነው? ሃቁ መኢሶንን በሥልጣን ጥም የሚከሱት “የግራም” ሆኖ የቀኝ አድርባዮች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዎሪ የነቃ፣ የተደራጀ የታጠቀ ሕዝብን አመጽ ተቃውመው ባቋራጭ ለሥልጣን የሚቋምጡ፣ በሥልጣን ላይ ለመደላደል የሚሹ ኃይሎች መሆናቸውን ነው።

ግን ደግሞ ሰፊው ሕዝብ ለሥልጣን እንዲበቃ የወዝአደር ፖርቲ ያስፈልጋል። ይህም በመሆኑ ዛሬ “ሁሉም” የወዝአደር ፓርቲ በአስቸኳይ ይመስረት በሚለው አብዮታዊ መፈክር ስር ተሰልፏል። ነገር ግን አብዮታዊያና አድርባዮች ይህን መፈክር በየፊናቸው ሲያስተጋቡ ዓላማቸው የተለያየ መሆኑን ለማየት ብዙም አያስቸግር።

ሰፊው ሕዝብና አብዮታዊያን “የወዛደር ፓርቲ ባስቸኳይ ይመስረት” ሲሉና ለዚህም ሲታገሉ ቶሎ ቶሎ ተራምደን ጠንካራና ሀቀኛ የወዛደር ፓርቲ እንመስረት በዚህም የወዛደሩ አምባገነንነት ወደ ሚረጋገጥበት ሕዝባዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ እናምራ ነው። “ባስቸኳይ” ሲሉ ቶሎ ቶሎ እንራመድ ማለታቸው ስለሆነ በንቃት፣ በድርጅትና በትጥቅ ጎዳና ላይ ቶሎ ቶሎ ለመራመድ የሚያስችላቸውን ዲሞክራሲያዊ መብቶች ባጣዳፊ ይጠይቃሉ። የብሔራዊ ዲሞክራሲያ አብዮት ፕሮግራማችን ይከበር ይላሉ። እዚህ ላይ ግን ግልጽ መሆን ያለበት ነገር አለ። የሚፈለገው ዲሞክራሲ “ካልተሰጠን” በኢትዮጵያ ምድር የወዝአደር ፓርቲ አይቋቋምም ለማለት አይደለም። የፈጀውን ጊዜና የጠየቀውን መስዋዕትነት ከፍለው የኢትዮጵያ ወዛደሮች፣ ግንባር ቀደም አርሶአደሮች፣ መለዮ ለባሾችና ምሁራን በህቡዕም ሆነ በይፋ በህጋዊም ሆነ ከህግ ውጭ እየታገሉ የኢትዮጵያን ወዝአደሮች ፓርቲ ይመሠረታሉ። ጥያቄው ይህ አይደለም። ጥያቄው ሁለት ነገሮችን ለማጣራት ነው። አንደኛ የወዛደር ፓርቲ ባስቸኳይ ከተባለ ይህንን መፈክር የሚያስተጋባ ሁሉ ለዚህ አመቺ ሁኔታ ለሚፈጥሩት የዲሞክራሲ መብቶችን መታገል አለበት ለማለት ነው። ሁለተኛው ደግሞ ይህንን መፈክር ተቀብለው እያስተጋቡ ዛሬ ለዴሞክራሲ ከሚደረገው ትግል የለንበትም የሚሉ ኃይሎች ወይ የሚናገሩትን አያውቁም ወይ ደግሞ የወዛደር ፓርቲ ባስቸኳይ ይመስረት ሲሉ የወዛደር ፓርቲ ባቋራጭ ይመስረት የሚሉ መሆናቸውን ለመጠቆም ነው።

አድርባዮች ንዑስ ከበርቴው መደብና አድሃሪው ቢሮክራሲ ይህንን መፈክር ሲያስተጋቡ ወደ ሀቀኛ የወዛደር ፓርቲ ቶሎ ቶሎ እንራመድ ለማለት ሳይሆን የኛን ህብረት የሚያንፀባረቅ “የወዛደር ፓርቲ” ባቋራጭ ከወዛደሩ ቀድመን እንመስርት ማለታቸው ነው። ባስቸኳይ ሲሉ ባቋራጭ ማለታቸው በመሆኑ ለንቃት ለድርጅት እና ለትጥቅ አመቺ ሁኔታ የሚፈጥሩትን ሀቀኛ የሆነ የወዛደር ፓርቲ ባስቸኳይ ለመመስረት የሚረዱትን ዲሞክራሲያዊ መብቶች አሁኑኑ መለቀቅ ይቃወማሉ። ዛሬ ወደዱም ጠሉም የኢትዮጵያ ማርክሲስት ሌኒኒስት ድርጅቶች ያለ ዲሞክራሲ በምን ተዓምር የወዛደር ፓርቲ በአስቸኳይ እንደሚመሠረት እስካላሳዩን ድረስ ይህን መፈክር እያስተጋቡ በዚያው ታታሪነት የዲሞክራሲ መብቶች ለጭቁኖች ያለአንዳች ገደብ እንዲለቀቁ ካልታገሉ ፀረ ሕዝብ ንዑስ ከበርቴና አድሃሪው ቢሮክራሲ ወጥመድ ውስጥ በመውደቅ ላይ መሆናቸውን መገንዘብ አለባቸው።

ያለ ዴሞክራሲ “የወዛደር ፓርቲ ባስቸኳይ ይመስረት” ማለት ሌላ አይነት የሥልጣን በአቋራጭ ቲዎሪ ነው። የኢትዮጵያ ማርክሲስት ሌኒኒስት ድርጅቶች ይህ አለመሆኑን እንዲያስረዱን ወይም ደግሞ አደጋውን ተገንዝበው ከሌሎች አብዮታዊያን ጎን ለዲሞክራሲ ትግል እንዲሰለፉ ጥሪ የምናስተላለፈው ከፍ ብለን ከጠቀስነው መሰረታዊ ሀቅ ተነስተን ነው።

ግን እዚህም ላይ አንድ ነገር ግልጽ መሆን አለበት። አደጋውን እየጠቆምን የትግል አንድነት ጥሪያችንን የምናስተላልፈው ለሀቀኛ ማርክሲስት- ሌኒኒስቶች ለግንባር ቀደም ወዛደሮች፣ አርሶአደሮች፣ መለዮለባሾች፣ ወጣቶች፣ ሴቶችና ምሁራን ብቻ ነው። የቀኝ አድርባዮቹማ፣ በየድርጅቶቹ እየሰረገ የገባው ፀረ ሕዝብ ንዑስ ከበርቴ እና አድሃሪ ቢሮክራሲማ የሚሰራውን ያውቃል!! ለመደባዊ ጥቅሙ ይታገላል። በወዝአደሩ ስም፣ በወዝአደሩና በሰፊ ሕዝብ ላይ ፀረ ሕዝብ ጥቅሙን ለማንገስ ይፍጨረጨራል። ለዚህ ፀረ ሕዝብ ክፍል የወዛደር ፓርቲ በአቋራጭ መመስረት በምንም አይነት አደጋ ሊባል ይችልም። የፀረ ሕዝብ ትግሉ አይነተኛ መሣሪያ ነው።

ስለሆነም የወዛደር ፓርቲ ባስቸኳይ ይመስረት ከሚለው አብዮታዊ መፈክር ተነስተን እኛ ቶሎ ቶሎ እንራመድ ስንል እነሱ ደግሞ ባቋራጭ እንራመድ ሲሉ በመሃከላችን ያለው ትግል የለየለት የመደቦች ትግል ነው። ጥያቄው የወዛደር ፓርቲ እንዴት ይመስረት የሚል ጥያቄ አይደለም የወዛደር ፓርቲ ይመስረት ወይስ አይመስረት የሚለው እጅግ ቁም ነገር ያለው ጥያቄ ነው። ትግሉ በማርክሲዝም ሌኒኒዝምና በንዑስ ከበርቴ ሶሻሊዝም መሀከል የሚካሄድ የመደቦች ትግል ነው። “አቋራጭን” የሚቃወሙ አብዮታውያን ለሃቀኛ የወዛደር ፓርቲ የሚታገሉ የኢትዮጵያ ማርክሲስት ሌኒኒስቶች ለጥቂት ጊዜም ቢሆን የወዛደሩ ፓርቲ እንዳይመሰረት የሚጥሩ ፀረ ሕዝቦች ተብለው ይከሰሱ ይሆናል። አብዮታዊያን ይህንን አቋራጭ ለማጋለጥ የሚፈልጉትን ክርክር በጸረ ዲሞክራሲ፣ በስም ማጥፋት ዘመቻና በመንደር አሉባልታ ብርታት ለመሸሽ ይሞከር ይሆናል። አድሃሪዎች ይህ ወጥመዳቸው ጨርሶ ሲጋለጥ እና ከማርክሲዝም ሌኒኒዝም አንፃር መከራከሪያው ሲቸግርና ማጣፊያው ሲያጥር በኢትዮጵያ ማርክሲስቶች ላይ በአመጽ ይነሱባቸው ይሆናል። ግን ትግሉ ሺህ ጊዜ መራራ ቢሆን፣ ሺህ አሉባልታ ቢነዛ የወሰደውን ጊዜ ቢወስድ በስመ ወዛደር ፓርቲ የኢትዮጵያ አብዮት እንዳይቀለበስ በቆራጥነት መዋጋት ሃቀኛ የኢትዮጵያ ወዛደሮች ፓርቲ እንዲመሠረት እስከመጨረሻው መሟሟት የእያንዳንዱ ግንባር ቀደም ወዛደር፣ አርሶአደር፣ መለዮለባሽና አብዮታዊ ምሁር ግዴታና ተግባር ነው እንላለን።

እንደዚህ አይነቱ ትግል ደግሞ በኛ አልተጀመረም። የትም ቢሆን በነፃነት ትግል ከወዛደሩ ቀደም ብሎ ነቅቶ ለተወሰነ ጊዜ ንጉስ ከበርቴው መደብ የግንባር ቀድምነት ሚና ይጫወታል። ከዚህም ሚናው በመነሳት ንኡስ ከበርቴው መደብ ራሱን የጠቅላላው ተራማጅ ክፍል ወኪል አድርጎ ከመውሰዱ ሌላ በተለይ በዚህ አመራር ሚናው ተቀናቃኝ የሆነውን የወዛደር መደብ እና አጋሮቹን እጅግ አድርጎ ይፈራል። ስለሆነም ወዛደሩ በገዛ ጥረቱ ተደራጅቶ የግንባር ቀደም ሚናውን እንዳይዝ ለማፈን ንኡስ ከበርቴው መደብ “ሁሉንም የሚወክል አንድ ፓርቲ በሚል ሰበብ የሌሎችንም በተለይም የወዛደሩን መደብ የመደራጀት መብት ያፈናል። ሌላው ቀርቶ “ሶሻሊስት ነኝ” “የወዛደር ፓርቲ ነኝ” ብሎ እስከመጻደቅ ይደርሳል። ከቦልሼቪኮች ታሪክ አንስቶ “እስከ አፍሪካ ሶሻሊዝም” ድረስ በልዩ ልዩ የሶሻሊዝም “አዝማሚያዎች” መሃከል የተደረገው ትግል አንድ መልኩ ንዑስ ከበርቴው መደብ ከሃቀኛ ማርክሲስትቶች ሌኒኒስቶች ይልቅ ወዛደሩን እኔ እወክላለሁ የሚልበትን አቋሙን ለማጋለጥም የተደረገ ትግል የሚሆነው ለዚህ ነው። ሃቀኛ የወዛደር ፓርቲ በወዛደሩ ስም የሚመፃደቁ ንዑስ ከበርቲዎችን ሳያሸንፍ የተመሠረተበት ቦታ በታሪክ አይገኝም።

በዚህ ትግል ደግሞ ወዝአደሩ ሲሸነፍ የሚከተለው ፀረ አብዮት ውሎ ይደር እንጂ ይፋ መውጣቱ የማይቀር ነው። ሩቅ ሳንሄድ የሱማሌ ወዛደርና ሰፊ ሕዝብ የደረሰበትን ውድቀት እንመልከት። በሶማሊያ እንደምንም ተውተፍትፎ “የወዛደር ፓርቲ በአስቸኳይ ተመሰረተ”። መሀመድ ዚያድ ባሬ የሰፊውን ሕዝብ ወገኖች የመደራጀት መብትና ዲሞክራሲን አፍኖ ይዞ በጨለማና በግርግር “የወዛደር ፓርቲ” አቋቋመ። ከአክስቶቹና ከአጎቶቹ ልጆች፣ በአምቻና ጋብቻ፣ ከአበልጅና አብሮ አደግ፣ ከአድሃሪው የሚሊተሪና የሲቪል ቢሮክራሲ፣ ወዛደሩን እንወክላን ከሚሉ “የወዛደር መሳፍንት” ካለኛ ማርክሲስት ሌኒኒስት ላሳር ከሚሉ የቀኝ አድርባዮች ምሁራን “አውጣጥቶ” ንዑስ ከበርቲንና የአድሃሪ ቢሮክራሲ ህብረት የሚያንፀባርቅ “የወዝአደር ፓርቲ” ፈጠረ። በዚህ መልክ ተውተፍትፎ የተቋቋመ ፓርቲ ውሎ ሲያደር ምን አይነት ፋሽስታዊና እብሪተኛ መልክ እንደሚይዝ የዚህን እብሪት ገፈት በመቅመስ ላይ ያለው የሱማሊያ ወዛደርና ሰፊው ሕዝብ ብቻ ሳይሆን ለአብዮታዊት እናት አገራችን ክብርና ህልውና በመዋደቅ ላይ ያለው መደበኛና ሕዝባዊ ሠራዊት የተገነዘበው ሀቅ ነው። እኛ የኢትዮጵያ አብዮታውያን እንዲህ አይነቱ ኪሳራ ላይ ወድቀን የአፍሪካ ሀፍረትና የዓለም መሳለቂያ ከመሆናችን በፊት ለሃቀኛ የወዛደር ፓርቲ እንታገል የምንለው እንደ ሱማሊያ አብዮት በአፍጢማቸው ተደፍተው ከተከሰከሱ “አብዮቶችም” ትምህርት በመቅሰም ነው።

ሰፊው ሕዝብ ለሥልጣን እንዲበቃ የወዛደር ፓርቲ ብቻ ሳይሆን በሱ የሚመራው እንደዚሁ የይስሙላ ሳይሆን ሀቀኛ የሆነ ሕዝባዊ አብዮታዊ ግንባር ያስፈልገዋል። ይህንንም ሀቅ ዛሬ “ሁሉም” አምንበታለሁ ይላል። ነገር ግን እዚህም ላይ ንዑስ ከበርቴውና አድሃሪው ቢሮክራሲ በአንድ በኩል፣ ሀቀኛ ማርክሲስት ሌኒኒስቶች በሌላ በኩል ሆነው እንደ አብዮትና ፀረ አብዮት የተለያየ አቋም አላቸው።

አብዮታዊያን ሕዝባዊ አብዮታዊ ግንባር ሲሉ በፀረ ፊውዳል፣ ፀረ ኢምፔሪያሊስትና፣ ፀረ ቢሮክራሲያዊ ካፒታሊስት ትግሉ አንፃር ተራማጅ ተብለው የሚታወቁ ኃይሎች በሙሉ በየፈርጃቸውና በየደረጃቸው ተደራጅተው የሚተባበሩበት የድርጅቶች ድርጅት ነው። ግንባር ቀደም የሆነው ለዴሞክራሲ በሚደረገው ትግል እስከመጨረሻው የሚገፋው የወዛደሩ መደብ እንኳን የነዚህን ኃይሎች መደራጀት ሊፈራና ሊያደናቅፍ ቀርቶ መደራጀት ሲሳናቸው እንኳን በዚህ ጥረታቸው በማገዝ ግንባር ቀደምነቱን ማሳየት ያስፈልጋል። ሌኒን እንዳለው “ግንባር ቀደም ነን ብሎ ማወጁ ብቻ አይበቃም። ሌሎች መደቦች በሙሉ በስተግንባር መራመዳችንን እንዲያዩና አመራራችንን አምኖ እንዲቀበል ማድረግ ያስፈልጋል።” ለዚህም ደግሞ አሁንም ሌኒን እንዳለው ማርክሲስቶች “እንደቀስቃሽ፣ እንደ አስተማሪና እንደ አደራጅ ሆነው በሕዝቡ ልዩ ልዩ ክፍሎች በሙሉ መሠራጨት አለባቸው” ባጭሩ ማርክሲስቶች የሌሎችን ተራማጅ ኃይሎችን መደራጀት አይፈሩም። በኢትዮጵያም ሰፊውን የኢትዮጵያ ሕዝብ ከዳር እስከዳር የሚያንቀሳቀስ፣ የሰፊው ሕዝብ ወገኖች በሙሉ የሚያምኑትና አለኝታችን ብለው የሚቆጥሩት፣ ህያው የሆነ፣ የትግላቸው መሳሪያ የሆነ፣ ግንባር እንዲመሠረት ይጥራሉ።

ይህ ግንባር በእርግጥ ሕዝባዊና አብዮታዊ እንዲሆን ከተፈለገ ከመጀመሪያው በውስጡ ያሉት ድርጅቶች በአመሰራረታቸውና በአሰራራቸው ዲሞክራሲያዊ መሆን አለባቸው። ለምሳሌ የወጣቶችን ድርጅት ብንወስድ የኢትዮጵያ ወጣቶች ይህ ግንባር የነሱም እንደሆነ የሚረዱትና ግንባሩን የሚከተሉት ዴሞክራሲያዊ በሆነ ዘዴ ያቋቋሙትና የሚቆጣጠሩት፣ ድርጅታቸው በግንባሩ ውስጥ ዲሞክራሲያዊ የሆነ ተሳትፎ ሲኖረው ብቻ ነው። የግንባሩ ጥንካሬም ሆነ ዲሞክራሲያዊነት የሚለካው በውስጡ ያሉት ድርጅቶች ባላቸው ጥንካሬና ዲሞክራሲያዊነት ነው ማለት ነው። ስለሆነም አብዮታዊያን ጠንካራ ሕዝባዊ አብዮታዊ ግንባር ለመመስረት በጠቅላላው በሀገሪቱ ያሉትን ፀረ 3 ኃይሎች ለማንቀሳቀስ የሰፊው ሕዝብ ወገኖች የሆኑ ሁሉ በፈርጃቸውና በየደረጃው ዲሞክራሲያዊ በሆነ ዘዴ እንዲደራጁና፣ ዲሞክራሲያዊ በሆነ ዘዴ እንዲሠሩ ይታገላሉ።

ንዑስ ከበርቴው መደብና አድሃሪው ቢሮክራሲ ይህንን በአፍ ቢቀበሉም ከነሱ ቁጥጥር ውጪ የሚመሠረቱና የሚሰሩ ድርጅቶችን ይፈራሉ። ከተቻለ ገና ከመመስረታቸው ለመቆጣጠርና የድርጅቶች አመሰራረት ቢሮክራሲያዊ በሆነ ዘዴ እንዲካሄድ ይሞክራሉ። ይህ ካልተሳካ ግን ዲሞክራሲን በተቻለ በማፈን የሚቋቋሙት ድርጅቶች በቢሮክራሲ አሻጥር እንዲጠወልጉና በጸረ ሕዝቦች ቁጥጥር ስር እንዲወድቁ ያደርጋሉ። ዲሞክራሲ በሌለበት አካባቢ ሊመሠረት የሚፈልጉ ሕዝባዊ ድርጅቶች ከውሃ ውስጥ ወጥቶ ለመኖር እንደሚፈልግ ዓሳ ናቸው። ይጠወልጋሉ። ይሞታሉ። በዚህ መልክ ዲሞክራሲ በመታፈኑ የተነሳ አመራሩ ከአባላት ይቆራረጣል። እንደዚህ የተቆራረጡ “መሪዎች” ደግሞ በአድርባይነትም ሆነ በተፅዕኖ ቀስ በቀስ የቢሮክራሲው ተቀፅላ ሆነው መቅረታቸው ፈጽሞ የማይቀር የታሪክ ሃቅ ነው። ንዑስ ከበርቴውና አድሃሪው ቢሮክራሲ ዲሞክራሲን የሚቃወሙት እንደዚህ አይነቶቹ ከአባላት ከተቆራረጡ ቁንጮች “አውጣጥተው ሕዝባዊ አብዮታዊ ግንባር ይህውላችሁ” ለማለት እንደሆነ ግልጽ ነው።

ዛሬ ለዲሞክራሲ የሚደረገው ትግል በንዑስ ከበርቴውና በአድሃሪው ቢሮክራሲ በአንድ በኩል በሰፊው ሕዝብና አብዮታዊያን በሌላ በኩል የሆነበት ዋናው ምክንያት በዚህ አንገብጋቢ በሆነው የመደራጀት ጥያቄ ላይ የዲሞክራሲ መኖርና አለመኖር ወሳኝ የሆነ ሚና ስለሚጫወት ነው።

እርግጥ ዲሞክራሲ በሚታወጅበት ጊዜ መጀመሪያ ላይ ሊመጣ የሚችለው ውዥንብር ሊያስፈራ እንደሚችል ለመረዳት ይቻላል። ዲሞክራሲን ሲቃወሙ ፀረ ሕዝቦች ከመደብ ጥቅማቸው አንጻር ሲሆን አንዳንድ ሀቀኛ ማርክሲስት ሌኒኒስቶች ደግሞ ከዚህ ጭንቀት ተነስተው እንደሆነ ይገባናል። በአንዳንድ ሀቀኛ ማርክሲስት ሌኒኒስቶች ዘንድ “ከዲሞክራሲ በኋላስ” የሚለው ጭንቀት እንዳለ ለማየት አያዳግትም። አንዳንድ ድርጅቶች “አብጠው” ራሳቸውን የወዛደር ፓርቲ ቢሉ ውዥንብር አይመጣም ወይ? የሚል ስጋትም አለ።

ዲሞክራሲ በሚታወጅበት ጊዜ ለአብዮቱ ይበልጥ ጥራትና ምጥቀትን እንዲሰጥ ከፍተኛ የግንባር ቀድምነት ሚናና ሃላፊነት በማርክሲስት ሌኒኒስት ድርጅቶች ትከሻ ላይ እንደሚወድቅ ግልጽ ነው። በተለይ ማርክሲስት ሌኒኒስቶች የዲሞክራሲ መታወጅ በሚያመጣው አመቺ ሁኔታ በመጠቀም ቶሎ ቶሎ መራመድና ወደ ውህደት ተጉዘው የወዛደሩን ፓርቲ መፍጠር ታሪክ የጣለባቸው ኃላፊነትና ግዴታ ነው።

ምንም እንኳን የወዛደሩን ፓርቲን ለመመስረት የሚችለው ማርክሲስት ሌኒኒስት ቡድኖች ጋር በመዋሃድ መሆኑን ሌላው ቀርቶ በፕሮግራሙ ላይ ቢገልጽም ቅሉ መኢሶን ለብቻው ፓርቲ ለመሆን ይፈልጋል የሚል አሉባልታ አሁንም እንደሚሰነዘር የታወቀ ነው። የመኢሶን ምኞት በሃቀኛ አብዮታዊ በሆነ መስመር ላይ የተገነባ ከኢትዮጵያ ማርክሲስት ሌኒኒስት ድርጅቶች ውህደት የሚፈልቅ ከብረት የጠነከረ የወዛደር ፓርቲ ለመመስረት አስተዋጽኦ ለማድረግ ነው።

የኢትዮጵያ አብዮታዊያን!

በአገራችን ውስጥ ትልቅ፣ ትልቅ ትርምስና የተተራመሰ ሁኔታ ሰፍኗል። ነባራዊ ሁኔታው ለአብዮታዊ ትግላችን መግፋት እጅግ አመቺ ነው። የኢትዮጵያ ጭቁን ሕዝቦች በአብዮታቸው ለመግፋትና ብሔራዊ ነጻነታቸውን ለማስከበር ይፈልጋሉ። ሆኖም በዚህ ትግላቸው ገፍተው በአሸናፊነት ለመውጣት የሚችሉት ዛሬ የተያያዙትን የሁለት ግንባር ትግል በተደራጀ አብዮታዊ አመራር ስር በአገር አቀፍ ደረጃ ሊገፉበት ሲችሉ ብቻ ነው።

የኢትዮጵያ አብዮታዊያን ለሃቀኛ የወዛደር መደብ ፓርቲ መመስረት እየታገልንና ሌሎችንም ተቀዳሚ ተግባሮች እያከናወንን፣ ጊዜያዊ ጥቃቶች ከዚያም አልፎ መሸነፍ እንኳን ቢደርስብን፣ በኢትዮጵያ ሕዝብ እና በታሪክ ፊት ተጠያቂ አንሆንም። ይህ ከደረሰ፣ በአጭሩ ነባራዊ ሁኔታዎች /የትግል ልምዳችንንም ጨምሮ/ ከኛ አቅም በላይ ክብደት ኖሯቸዋል ማለት ነው። መጭው አብዮታዊ ትውልድም ከኛ ድክመቶችና ጉድለቶች ተምሮ በበለጠ ብልህነትና ጥንካሬ የድሉ ባለቤት ለመሆን ይበቃል። በተቃራኒ ግን ተግባራችንንና ያለብንን ኃላፊነት እያወቅን በቸልተኝነት፣ በለዘብተኝነት በአድርባይነት አስፈላጊ ያልሆኑ ጥቃቶችም ከዚህ አልፎ ጊዜያዊ መሸነፍ እንኳን ቢደርስብን በኢትዮጵያ ሕዝቦች በታሪክ ፊት ተጠያቂ ከመሆን አንድንም።

የዲሞክራሲ መብቶች ለጭቁኖች ያለ ገደብ አሁኑኑ!
የወዛደሩን ፓርቲ በአስቸኳይ እንመስርት!
የታሰሩ የሕዝብ ወገኖች በአስቸኳይ ይፈቱ!
ተራማጆችን ማሳደድ ይቁም!
የነቃ፣ የተደራጀ፣ የታጠቀ የሕዝብ አመፅ ያሸንፋል!
 
ዜናዎች
ዶ/ር ተረፈ ወ/ጻድቅ በአሰቃቂ ሁኔታ ተገድሏል

በነሐሴ ወር 1969 መኢሶን የትግል ስልት ለውጥ ማድረጉን እንዳስታወቀ ይታወሳል። በዚህም አማካኝነት አንዳንድ አባሎቹን ወደ ህቡዕ ትግል መስክ አዛውሮ ነበር።

ዶ/ር ተረፈ ወ/ጻድቅና ከዚህ በታች ስማቸው የተዘረዘረው በሁለት ከሃዲዎችና አንድ ተባባሪ አማካኝነት የነበሩበት ቦታ ከተጠቆመ በኋላ በታህሳስ 30 1970 የመንግሥት ወታደሮች በቦታው ደርሰው እጃቸውን እንዲሰጡ ካደረጉ በኋላ በቦታው ተረሽነዋል።

የተገደሉት

  1. ዶክተር ተረፈ ወ/ጻድቅ የትምህርት ሚኒስትር
  2. ባለቤቱ አጥናፍ
  3. ከበደ ድሪባ የሸዋ ክፍለ ሀገር የሕዝብ ድርጅት ጉዳይ ጊ/ጽ/ ቤት ኃላፊ
  4. ኢዮብ ታደሰ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባልደረባ የነበረ
  5. መርእድ ከበደ የአዲስ አበባና የአካባቢው የሕዝብ ድርጅት ጊ.ጽ/ ቤት ባልደረባ የነበረ
  6. ለማ ፊዳ ካድሬ ሸዋ ሕ.ድ.ጉዳይ ጊ/ጽ/ቤት
  7. ሽመልስ ኦላና ከፋ ክፍለ ሀገር የሕዝብ ድርጅት ጉዳይ ጊ.ጽ.ቤት ም/ ሀላፊ
  8. ታደሰ የሸዋ ሕዝብ ድርጅት ጉዳይ ጊ/ጽ/ቤት ሾፈር
  9. አልፋ ነምራ
  10. ሁለት በጅባትና ሜጫ አውራጃ የነበሩ ካድሬዎች

ስለ እነዚህ ታጋዮችና ሌሎችም ባለፉት ወራት ስለወደቁት የመኢሶን አባሎችና ደጋፊዎች ዝርዝር ሐተታ ወደፊት እናወጣለን።

በተረፈ ግን በየቦታው የ“ፈርጣጩ” መኢሶን አባሎችና ደጋፊዎች ናቸው ተብለው በሚጠሩት ታጋዮች ላይ ክትትልና ማሳደድ አሁንም እንደቀጠለ ነው። የስውርና የግልፅ የጭቆና እርምጃዎች መጠን እየጨመረ በመሄድ ላይ ይገኛል።

Scroll to Top