ሰሕድ ቁ. 69

የሰፊው ሕዝብ ድምፅ

ቁጥር 69፣     ግንቦት 20፣ 1971  

የፅሁፉ ፍሬ ሀሳብ

በዚህ እትም መኢሶን፣ ባለፉት አመታት ሰፊው ሕዝብ በትግሉ በርካታ ድሎችን መጎናጸፍ ቢችልም ከ1969 ዓ.ም. ወዲህ የቀኝ ሃይሎች የበላይነትን እንዳገኙ በመተረክ ይጀምራል። ሰፊው ሕዝብ በመሸርሸር ላይ ያሉትን ድሎቹን አድኖ ወደ ፊት ለመጓዝ አሁንም በአንድነት መታገልና የጋራ ሕብረት መመስረት ወሳኝ ሚና እንዳላቸው አበክሮ ያስገነዝባል። ለእናት አገር ህልውናና ለብሄረሰቦች መብት መከበር የቆሙ ኃይሎች ሁሉ በመካከላቸው ያሉ ልዩነቶች ላይ በግልጽ ተወያይተው የተራማጆች ሕብረት መመሥረት እንዳለባቸውና መኢሶንም ለዚህ አላማ በግንባር ቀደምትነት ለመታገል ዝግጁ መሆኑን ቃል ይገባል።

የሰፊው ሕዝብ ድምፅ

ለሰፊው ሕዝብ ሰራተኛ ገበሬ፣ ነጋዴ፣ ወታደር፣ ምሁር መብትና ጥቅም የሚታገል ጋዜጣ

የኢትዮጵያ ሰፊ ሕዝብ ይቅደም

ቁጥር 69                                                                      ቀን 20/9/71
 

እንደገና ለኢትዮጵያ ተራማጆች አንድነት ጥሪ

የኢትዮጵያ ጭቁን ሕዝቦች ባለፉት አምስት ዓመታት ያካሄዷቸውን ትግሎች ታሪክ ወደፊት በሚመረምርበት ወቅት በአጠቃላይ ሁለት ታላላቅ ምዕራፎች ይኖራሉ። የመጀመሪያው ምዕራፍ ከየካቲት 1966 – የካቲት 1969 ዓ.ም ያለው የትግል ዘመን ነው። ይህ የሦስት ዓመት የትግል ዘመን ምንም እንኳን ብዙ መውደቅ፣ መነሳት፣ ማጥቃትና መከላከል የተፈራረቁበት ዘመን ቢሆን ቅሉ በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ጭቁን ሕዝቦች በቀንደኛ ጠላቶቻቸው ላይ የአጥቂነት ቦታን ይዘው ፍጹም ሕዝባዊነት ፍጹም ዴሞክራሲያዊት ወደ ሆነችው ኢትዮጵያ የሚገሰግሱበት ወቅት ነበር። ሁለተኛው የታሪክ ምዕራፍ ደግሞ ከየካቲት 1969 ዓ.ም አንስቶ ገና አሁንም የምንገኝበት የኢትዮጵያ ጭቁን ሕዝቦች ትግል ቀስ በቀስ ከአጥቂነቱ ደረጃ እየተፈናቀለ አብዮታችን አሁን የሚገኝበት የጣረሞት ደረጃ ላይ የደረሰበት አስከፊ ወቅት ሆኖ እናገኘዋለን።

የመጀመሪያውን የታሪክ ምዕራፍ በሚመለከተው በኩል የኢትዮጵያ ተራማጆች በሙሉ እጅ ለእጅ ተያይዘው በሚሊዮን የሚቆጠሩትን ጭቁኖች በግንባር ቀደምነት እያንቀሳቀሱ የተቀዳጇቸውን ድሎች በዚህ ላይ አንመለስባቸውም። ሰፊው የኢትዮጵያ ሕዝብና መላው ዓለም ያውቋቸዋል። በሁለተኛው ምዕራፍም ቢሆን አድሃሪ ኃይሎች በተለይ ንኡስ ከበርቴውን ደርግ ከተራማጆች ለመነጠል የጠነሰሱት ሴራ ከተሳካላቸው በኋላ ደርግ ከብሔራዊ ዴሞክራሲያዊ አብዮት ፕሮግራም ተንሸራቶ የወደቀበትን አሳፋሪ አዘቅት፣ ይኽንን መንሸራተት አሻፈረኝ ባሉ ኢትዮጵያዊያን ላይ የደረሰውን አሰቃቂ ግፍ ዛሬ ሰፊው የኢትዮጵያ ሕዝብና መላው ዓለምም ያውቁታል። ስለመሸራተቱ ጉዳይ አንባቢ በሚያዚያ ወር 1968 ዓ.ም የታወጀውን “የኢትዮጵያ ብሔራዊ ዲሞክራሲያዊ አብዮት ፕሮግራም” አንቀጽ በአንቀጽ እየተመለከተ ዛሬ ከሚያየውና ከሚሰማው ጋር ያነፃፅር እንላለን። በተራማጅ ኃይሎች ላይ ስለወረደው አመጽ ባለፈው ቁጥራችን እንዳሳየነው ዛሬ በኢትዮጵያ 20 ሺህ ተራማጅ፣ ዲሞክራትና አገር ወዳድ ኢትዮጵያዊያን “በአብዮታዊው ደርግ” እስር ቤቶች በመማቀቅ ላይ እንዳሉ፣ ይህ ቁጥር በኢትዮጵያችን ታሪክ ምንጊዜም ቢሆን ተደርሶበት የማያውቅ በመሆኑ፣ ይኽንን ያህል አብዮታዊያን በእስር ቤት ሲማቅቁ በአፍሪካ ምንም አይነት ተወዳዳሪ የሌለው ሁኔታ መሆኑንና በዓለም ምናልባት ቺሊና አርጀንቲና እንጂ ሌላ ተወዳዳሪ ሊኖር እንደማይችል…. ባለፈው ቁጥራችን ያቀረብነውን ግምገማ አንባቢ መለስ ብሎ እንዲመለከት እንጋብዘዋለን።

ዛሬ በኢትዮጵያ ምድር ከየካቲት 1969 ዓ.ም. ወዲህ በተጠነሰሰው አዲስ የቀኝ ኃይሎች ህብረት ምክንያት አብዮታችን ከተከላካይነትም ደረጃ ወርዶ በጣረሞት ደረጃ የሚገኝበት ሁኔታ አለ። እዚህ ሁኔታ ላይ እንዴት ደረስን? የሚለውን ጥያቄ ዛሬ በዚህ ጽሁፍ ለመተንተን አንቃጣም። የዚች ጽሁፍ ዋና አላማዋ ዛሬ የምንገኝበት ሁኔታ ምንድነው? ከዚህስ ሁኔታ ለመውጣት የኢትዮጵያ ተራማጆች ምን ማድረግ አለባቸው? የሚለውን ጥያቄ ለማንሳት እና በሌሎች ድርጅቶች ውስጥ ላሉም ሆነ ላልተደራጁ የኢትዮጵያ ማርክሲስት ሌኒኒስቶች፣ ለዲሞክራቶችና ለአገር ወዳጆች ሁሉ መልስ ሊሆኑ ይችላሉ የምንላቸው ነጥቦች ለውይይት ለማቅረብ ነው።

የዛሬው ሁኔታ ምንድነው? የመላው ኢትዮጵያ ሶሻሊስት ንቅናቄ ከተጠነሰሰበት ወቅት አንስቶ እጣው ከኢትዮጵያ ጭቁን ሕዝቦች ዕጣ ተለይቶ አያውቅም። ስለሆነም አዲሱ የቀኝ ኃይሎች ህብረት በኢትዮጵያ ገበሬዎች፣ ወዝአደሮች፣ መለዮ ለባሾች፣ ዲሞክራቶች፣ ወጣቶች፣ ምሁራን፣ ሴቶቸ፣ አገር ወዳድ የጦርና የፖሊስ መኮንኖች ላይ ሲዘምት የዚህን የፀረ ሕዝቦች ጥቃት እሱም አብሮ ቀምሶታል። ስፍር ቁጥር የሌላቸው አባላቱ ተረሽነዋል። በሺህ የሚቆጠሩ አባላቱና ደጋፊዎቹ ታስረዋል። ተሰደዋል። ተንገላተዋል። ነገር ግን በየድርጅቱ ላይ የተፈጠረው ከፍተኛ ፀረ ሕዝብ አመጽ፣ ለዚህ ፀረ ሕዝብ በአመፅ ጥቂት አድርባዮች ያሳዩት ተባባሪነት ጭፍን ያለ ትንተና ወይም በንኡስ ከበርቴ እልህ ላይ የተመረኮዘ አቋም እንዲይዝ አይገፋፋውም። የስንት ኢትዮጵያዊያን ደም የተገበረበት፣ የስንት ጓዶቻችን ሕይወት የተማገደበት፣ የስንት ጭቁኖች የኑሮ ተስፋ የተንጠለጠለበት፣ የእናት ሃገራችን ክብር ተስፋ የተጣለበት የአብዮት ጉዳይ ከማንኛውም ስሜትና ግለሰብኝነት በራቀ ጥሞና መታየትና መተንተን ያለበት ጉዳይ ነው ብሎ ያምናል። መኢሶን ዛሬ እንደገና ለተራማጆች ጥሪ ሲያደርግ የሚነሳበት መንፈስ ይኽ ነው።

ከዚህ ተነስቶ ዛሬ የኢትዮጵያን ሁኔታ ተረድቶ የወደፊቱን የግል ጎዳና ለመቀየስ የሚፈልግ ታጋይ ሁሉ እጅግ ግልጽ የሆኑ መሰረታዊ ነገሮች አሉ። ዛሬ የአገራችንን ሁኔታ መልክ ከሚሰጡት ነገሮች አንዱ በፖለቲካው መስክ ያለው ከፍተኛ ጥራት ነው እንላለን። ይህ ያለው የፖለቲካ ጥራት ለአብዮትና ለእናት ሀገር ብለው ለተነሱ ኢትዮጵያዊያን ሁሉ ለትግል ያመቸ ሁኔታ ይፈጥራል። ታድያ ወደፊት ለምን አንራመድም? ድልን ለመቀዳጀት ምን ይጐድለናል? የሚለው ጥያቄ ከዚህ ተከትሎ ይነሳል። መልሱም አጭር ነው። የቀኝ ኃይሎች ህብረት በአብዮቱ ላይ ባደረሰው ጥቃት የተነሣ የኢትዮጵያ ሕዝብ የትግል መሳሪያ የነበሩ ድርጅቶቹ ፈራርሰውበታል፣ ግንባር ቀደም የነበሩ እንቅስቃሴዎቹ በፀረ ሕዝብ አመጽና ባደርባዮች ሴራ ተኮላሽተውበታል፣ አንዳንዶቹም ተበታትነውበታል። ወደፊት ለመራመድ የግንባር ቀደም ድርጅቶች ጥንካሬ ሲያስፈልግ ፀረ ሕዝቦች እነሱን ለማፈራረስ ሌት ተቀን ይፍጨረጨራሉ። ወደፊት ለመራመድ የግንባር ቀደም ኃይሎች ህብረትና አንድነት ሲያስፈልግ ፀረ ሕዝቦች ተራማጆችን ለመለያየት ብቻ ሳይሆን በእነሱ ተጠቅመው ሌላውን ለመምታት ይሯሯጣሉ። ይህ ፀረ ሕዝብ ሴራቸው ደግሞ ለነሱ ጥሩ ውጤት አስገኝቶላቸዋል። በዚህ የተነሳ ዛሬ በሀገሪቱ ላለው የፖለቲካ ጥራትና በሚሊዮን የሚቆጠሩ ጭቆናዎች ለሚያሳዩት የትግል ስሜትና ፍላጎት ተመጣጣኝ የሆነ የተራማጅ ድርጅቶች ጥንካሬ እና ህብረት የለም። ከዚህ ተነስቶ በዛሬው ሁኔታ አንፃር የተራማጆች ትግል መያዝ ያለበት አቅጣጫ ምን እንደሆነ ለመገንዘብ ብዙም አያዳግትም።

ዛሬ የኢትዮጵያ ተራማጆች አንገብጋቢ ተግባሮች አንደኛ፣ ይህ የተገኘው የፖለቲካ ጥራት እንዳይደፈርስ አቅማቸው በሚፈቅድላቸው አጋጣሚ ሁሉ መታገል፣ ሁለተኛ፣ ለአብዮት፣ ለእናት አገር ሊንቀሳቀስ የሚችለውን ይህ ነው የማይባል ኃይል በግንባር ቀደምነት ለማንቀሳቀስ የሚያስችላቸውን የህቡዕ መዋቅር መዘርጋት፣ ሦስተኛ፣ ደግሞ ተራማጅ ኃይሎች በሙሉ ከማንኛውም የጠባብ ቡድን ስሜት፣ ከማንኛውም የንጉስ ከበርቴ እልህና ጨቅላነት ተጠብቀው አንድነታቸውን ማጠናከርና በህብረት መታገል አለባቸው እንላለን።

የዚህ ቁጥራችን ዋና ይዘት እንግዲህ ከሁለት ይከፈላል። በመጀመሪያው ክፍል የጊዜውን ሁኔታ ጥንድ መልኮች ለማሳየት እንሞክራለን። በሁለተኛ ክፍል ደግሞ ከዚህ ሁኔታ የሚፈልቁትን ተግባሮች በተለይ ደግሞ የተራማጅ ኃይሎችን ህብረት በሚመለከት በኩል አንዳንድ ሃሳቦችን ለኢትዮጵያ ተራማጆች እንሰነዝራለን።

 

ክፍል 1. የጊዜው ሁኔታ መልኮች

ከላይ እንዳልነው ዛሬ በኢትዮጵያ ምድር የፖለቲካ ጥራት ችግር የለም። ይህን ስንል ምን ማለታችን ነው? ይህ ማለት በታሪካችን ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ዛሬ የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚታገልለትን ዓላማ እጅግ ጥራት ባለው ሁኔታ ያውቀዋል። ወደዚህ አላማ የሚያደርሰውንም የትግል ፋና እንደዚሁ አጣርቶ ያውቀዋል። ከብዙ ዘመናት ትግል በኋላ ይፋ የወጣው የኢትዮጵያ ተራማጆች የትግል መድረክ ማለትም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ዲሞክራሲያዊ አብዮት ፕሮግራም፣ በሱ ዙሪያ ለሁለት ዓመታት ያህል የተደረገው ከፍተኛ ቅስቀሳ፣ ከሥራ ላይ እንዲውል ስፍር ቁጥር የሌላቸው ኢትዮጵያዊና ኢትዮጵያዊት ያፈሰሱት ደም የዚህ የፖለቲካ ጥራት መሰረት ሆኖ አናገኘዋለን። ይህ ፕሮግራም ሰፊው የኢትዮጵያ ሕዝብ ከዳር እስከዳር የተንቀሳቀሰበት መላው የኢትዮጵያ መደበኛና ሕዝባዊ ሰራዊት ቃል ኪዳን የገባለት ፕሮግራም ነው። ይህ ፕሮግራም በዚህ መልክ ባገኘው ተቀባይነት የተነሳ እስካሁን ድረስ በይፋ ሽሬዋለሁ ያለ ኃይል የለም። ከመታወጁ በፊት ተቃውመውት የነበሩ የደርግ አባላት እንኳን ከዚያ በኋላ አልተቃወሙትም። እነሲሳይ ሀብቴም ሆኑ እነዓለማየሁ ፕሮግራሙን ሽረው አብዮቱን ለመቀልበስ ቢነሱም ይሄንን አቋማቸውን በሆነ ባልሆነ ተልካሻ ቲዎሪ ለመሸፋፈን ሞከሩ እንጂ “ከዛሬ ወዲያ ብሔራዊ ዲሞክራሲያዊ አብዮት ተሽሯል”: ብለው ለመናገር አልደፈሩም። ግን ሌላም አለ በሕዝቡ ፊት ባገኘው ተቀባይነት የተነሳ በይፋ ሊሽሩት የማይችሉት ቀልባሾችና ተንሸራታቾች ይህ ፕሮግራም ባለው ጥራት የተነሳ ራሳቸውን ሳያጋልጡ በተዘዋዋሪም ቢሆን ሊሽሩት አይችሉም። በፕሮግራሙ ጥራት የተነሳ በድርጊት ፕሮግራሙን እየተቃወሙ በአፍ በፕሮግራሙ መድረክ ላይ ነን ለማለት ፈፅሞ አዳጋች ጉዳይ ነው። ሩቅ ሳይሄዱ መጋለጥና በሰፊው ሕዝብ መተፋትን ያስከትላል። ፕሮግራሙ “ዲሞክራሲ ባስቸኳይ” እያለ “ታግለህ ውሰድ” ማለት፣ ፕሮግራሙ “ሪጅናል ኦቶኖሚ” እያለ የመጀመሪያ ደረጃ የብሄረሰቦች እኩልነትን በትምክህተኛ እብሪት መርገጥ፣ ፕሮግራሙ “ቢሮክራሲ ይውደም” እያለ ከዚህ ከጠነባ ቢሮክራሲ ጋር ገጥሞ የአብዮቱን ሰፈር ማጥቃት፣ ፕሮግራሙ “የብሔራዊ ነፃነትና የገለልተኛ የውጭ ፖለቲካ” እያለ የአገሪቱን የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ፣ የባህል፣ የወታደር ተቋሞች እንደገና ለአዲስ ጌቶች አስረክቦ የእናት አገራችንን ክብር እንዳልነበረ ማውደም፣ ፕሮግራሙ “ሕዝባዊ ድርጅቶች ያብቡ” እያለ ያሉትን ማጠውለግና በፀረ ሕዝብ ሴራ ማፈራረስ፣ ፕሮግራሙ “የወዛደር ፓርቲ፣ ሌሎችም ዲሞክራሲያዊ ፓርቲዎች” እያለ የወዛደሩን ፓርቲ ጥንስሶች ማፈራረስ፣ ሌሎች ኢትዮጵያውያን ተራማጆች እንዳይደራጁ አፍኖ መያዝ…እነዚህ ድርጊቶችና አቋሞች ሁሉ ዛሬ የቀኝ ኃይሎች ህብረት ሙሉ በሙሉ ከፕሮግራሙ መንሸራተቱን የሚያሳዩና የሚያጋልጡ ናቸው። በዚህም የተነሳ ዛሬ የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚፈልገውን ያውቃል፣ ማን የሕዝቡን ፍላጎት እንደሚፃረር ያውቃል፣ ማን ከሕዝቡ ጎን እንደተሰለፈ ያውቃል።

ይህንን ጥራት ደግሞ በልፈፋና በአደናቋሪ ፕሮፓጋንዳ ማደፍረስ ዘበት ነው። ለምን? ምክንያቱም አንደኛ የዛሬ ተንሸራታቾች ራሳቸው ዛሬ የከዱትን ቃላቸውን በየአደባባዩ፣ በየሴሚናሩ በያለበት ግራ እጃቸው ከትከሻቸው ተነቅሎ እስኪሄድ ድረስ ከሕዝቡ ጋር ያስተጋቧቸው የነበሩ ስለ ነበሩ ዛሬ ቃል ማጠፋቸው የአተላነታቸውን አዘቅት ያሳያል እንጂ ሌላ የሚያሳየው ነገር የለም። ሁለተኛ ደግሞ ሰፊው የኢትዮጵያ ሕዝብ በልፈፋና በድርጊት መሃከል፣ በሃቀኛ ወዳጅ እና ባስመሳይ መካከል ለመለየት የሚያስችለው በቂ የፖለቲካ ንቃት ከአምስት ዓመት የአብዮታዊ ትግሉ ገብይቷል። ከሁሉ ይበልጥ የሚጮሁና የሚደነፉ በግድ ከሁሉ ይበልጥ የሕዝብ ወገኖች የሚመስሉበት ዘመን አክትሟል። “የተራማጅ ተራማጅ” መስሎ የተደባለቀውን የኢህአፓ ፀረ ሕዝብ መንጋ ከመሀሉ እየፈለፈለ ያወጣውና ወደ ተራ ነፍሰ ገዳይነት እንዲወርድ ያደረገው በዚህ በንቃቱ ነው። የቀድሞውን የዓለማየሁ ኃይሌ የቀኝ ኃይሎች ህብረት ተልካሻ የፖለቲካ መስመር ፊት ለፊት ገጥሞ አሻፈረኝ ያለው በዚህ በንቃቱ ነው። ዛሬ ደግሞ ያው የእነዓለማየሁ የፖለቲካ መስመር በአዲሱ የቀኝ ኃይሎች ህብረት አማካኝነት ሲከሰት አሻፈረኝ ብሎ “ከብሔራዊ ዲሞክራሲያዊ አብዮት ፕሮግራም ጋር ወደፊት” ብሎ ከፀረ ሕዝቦች ጋር እጅግ አስቸጋሪ የሆነ የትንቅንቅ ወቅት ውስጥ የገባው ከትግሉ ከእለት እለት እየተማረ፣ አስመሳይን ከሃቀኛው፣ ልፈፋውን ከድርጊት፣ ለመለየት የሚያስችለው የፖለቲካ ጥራት በማግኘቱ ነው።

ፀረ ሕዝቦችም ይህን በታጋይ ኢትዮጵያዊያን ደም የተገኘ ጥራት በአፈጻድቅ ፕሮፖጋንዳ ለማደፍረስ፣ እነሱ ከሃዲዎች ታጋዮች፣ ታጋይ የሕዝብ ልጆችን ከሃዴዎች አድርገው ለማቅረብ ያደረጉት ሙከራ በሕዝቡ ከፍተኛ የትግል ልምድና የንቃት ደረጃ የተነሳ ሙሉ በሙሉ መክሸፉን አላጡትም። ድሮውንም ቢሆን የቸገረው ዱቄት ከንፋስ ይጠጋል ነው እንጅ ፀረ ሕዝብ አቋም ይዞ፣ ዴሞክራሲ አያስፈልግም፣ የእናት ሀገር ብሔራዊ ክብር ገደል ይግባ፣ የጠነባው ቢሮክራሲ መልሶ ይፈንጭብህ…. እያሉ ወደ ነቃ ሕዝብ ለመጠጋትና ለዚህ ፖለቲካ የሱን ድጋፍ ለማግኘት መሞከር አንድም ተስፋ የሌለው ሞኝነት አሊያም ወደር የሌለው የሕዝብ ንቀት እንደሆነ ፀረ ሕዝቦች የተገነዘቡ አይመስልም። የሆነው ሆኖ ያለውን ጥራት በልፈፋ ማደፍረስ አልተቻለም። ስለሆነም ፀረ ሕዝቦች ልክ እንደ ኢህአፓው ዘመን፣ ልክ እንደ ቀድሞ የቀኝ ኃይሎች ህብረት ዘመን፣ በአብዮቱ ኃይሎች ላይ ተሰማሩ። ይህ በኢትዮጵያ ተራማጆች ሰፈር የተቃጣው ፀረ ሕዝብ አመፅ በትግሉ ላይ ያስከተለውን ጉዳት ዝቅ ብለን እንመጣብታለን። እዚህ ላይ ግን ለማለት የምንፈልገው አንዲት ነገር ብቻ ነው። ይህ አመጽ ምንም ጭፍን ቢሆን፣ ምንም አስከፊ ቢሆን በአብዮቱ ሰፈር ያለውን የፖለቲካ ጥራት እስከዚህም አላደፈረሰውም። አዲሱን የቀኝ ኃይሎች ህብረትም ይባሱን አጋለጠው፣ ይባሱን ፀረ ሕዝብነቱን፣ ይባሱን መክሰሩን አሳየበት እንጅ በሕዝቡ ዘንድ ተቀባይነትን አላስገኘለትም። በዚህም ሁሉ የተነሳ ዛሬ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሌላ ከፍተኛ የሆነ ድል ተቀዳጅቷል። የኢትዮጵያን አብዮትና የብሔራዊ ክብሯን የወደፊት እድል ከደርግ ለይቶ፣ ከደርግ ባሻገር መመልከት ጀምሯል። ከመጀመርያው አንስቶ የመላ ኢትዮጵያ ሶሻሊስት ንቅናቄ ወደ ሕዝባዊት ኢትዮጵያ የሚደርገው ትግል ንኡስ ከበርቴውን ደርግ አንድ የተወሰነ ደረጃ ላይ ጥሎ የሚያልፍ ትግል ነው ሲል ያስተጋባው የነበረው አቋም ዛሬ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን አእምሮ ውስጥ የታነጸ ሀቅ ሆኗል።

ይህ ዛሬ በሀገራችን የሚታየው የፖለቲካ ጥራት እንዲገኝ የመላ ኢትዮጵያ ሶሻሊስት ንቅናቄ እጅግ የሚኮራበት፣ ስፍር ቁጥር በሌላቸው አባላቱ ደም የከፈለው አስተዋጽኦ አድርጓል። በዚህ ሀቅ ላይ ትንሽ መለስ ማለት ያስፈልጋል።

እንደሚታወሰው የየካቲት አብዮት ከፈነዳ ከአንድ ዓመት በኋላ በጊዜው በነበሩት ተራማጅ ይባሉ በነበሩት ኃይሎች መካከል የሁለት መስመር ትግል ሲጀመር ተራማጁን ወገን በመወከል መኢሶን በግንባር ቀደምነት ሲሰለፍ የቀልባሹን መስመር በመወከል ደግሞ የኋላው ነፍሰ ገዳይ ቡድን ኢህአፓ ቆሞ ነበር። በዚህ ትግል የአድሃሪዎች ግንባር ቀደም የነበረው ኢህአፓ ድል ከተመታ በኋላ የፖለቲካ ክስረቱን ለመሸፈን ሲል በነፍሰ ገዳይነት ተሰማርቶ እጅግ ብዙ የመኢሶን አባላትንና ደጋፊዎችን ስፍር ቁጥር የሌላቸው ሌሎች አብዮታዊያንን እያደነ ገደለ። የመስመር ትግል ኢህአፓ ሲተፋ አላቆመም። ከዚህ ጋር በተያያዘ ሁኔታ የቀድሞ የነዓለማየሁ ኃይሌ የቀኝ ኃይሎች ህብረት በአንድ በኩል፣ በጊዜው የነበሩት የደርግ ተራማጆች መኢሶንና ሌሎች ተራማጅ ድርጅቶች በሌላ በኩል መሃከል እንደገና ሌላ ትግል ተጀመረ። በዚህም ትግል በግንባር ቀደምነት የተሰለፈው ንቅናቄያችን አሁንም እንደቀድሞ ውድ ጓዶቹን እየሰዋ በሀቀኛው መስመር ስር መታገሉን ቀጠለ። የእነዓለማየሁ ኃይሌ የቀኝ ኃይሎች ህብረት አናቱ ላይ ተመቶ ከተፍረከረከ በኋላ አብዮቱ ትንሽ ሳምንታት ወደፊት መገስገስ እንደጀመረ የነዓለማየሁ ኃይሌን ቀልባሽ የፖለቲካ መስመር ይዞ ሌላ አዲስ የቀኝ ኃይሎች ህብረት ተነሳ። የአንዳንድ የቀድሞ ተራማጆችና የአድርባይ የድርጅቶች ሰፈር መለወጥና በቀድሞ በነዓለማየሁ ፖለቲካ ስር መሰለፍ ለሰፊው የኢትዮጵያ ሕዝብ ፊት ውዥንብርን ሊፈጥርና እስካሁን የተገኘውን የፖለቲካ ጥራት ሊያደፈርስ የሚችል ሁኔታ ፈጠረ። እርግጥ ውሎ አድሮ ይህንን መንሸራተት ለመገንዘብ የሚያስችለው ንቃት ነበረው። ነገር ግን በዚህ ወቅት አዲሱን ዙር የመስመር ትግል በሕዝብ በኩል፣ በአብዮት በኩል ጸንቶ ለመምራት የሚችል ግንባር ቀደም ኃይል እጅግ አስፈላጊ ነበር። ስለሆነም መኢሶን ይህንን የግንባር ቀደምነት ኃላፊነት ያለ አንዳች ማመንታት ተቀብሎ፣ ከተንሸራታቾች ጋር መንሸራተትን አሻፈረኝ ብሎ በአብዮቱ ሰፈር በመጽናቱና እነዓለማየሁ ከተመቱ በኋላ በተከተሉት ወራት ከፍተኛ የሁለት መስመር ትግል ተካሂዶባቸዋል። በዚህ ትግል ውስጥ ሰፊው የኢትዮጵያ ሕዝብ ከዳር እስከዳር የነዓለማየሁን ቀልባሽ ፖለቲካ በተቃወመበት ወኔና ቆራጥነት የአዲሱን የቀኝ ኃይሎች ህብረት መስመር ተቃወመ። ሚያዚያ 23 ቀን 1969 ዓ.ም የወዛደር ቀንን ምክንያት በማድረግ ባሳየው ሰልፍ ይህ የሰፊው ሕዝብ አቋም፣ ይህ የሰፊው የኢትዮጵያ ሕዝብ በመኢሶን ግንባር ቀደምነት ለተወከለው አብዮታዊ መስመር ለመዋደቅ ዝግጁ መሆን ለወዳጅም ለጠላትም ይፋ ሆኖ ታየ። በዚህም የተነሳ በሰፊው ሕዝብ ሰፈር ያለውን የፖለቲካ ጥራት ለመቋቋም አዲሱ የቀኝ ኃሎች ህብረት የኪሳራው ምልክት በሆነው ፀረ ሕዝብ አመጽ ተሰማራ።

እንግዲህ ከዚህ ወቅት አንስቶ ለመኢሶን እና ለጠቅላላው የኢትዮጵያ አብዮታውያን ያለው ምርጫ ግልጽ ነበር። ወይ አሁንም ደርግ የያዘው መስመር ትክክል ነው፣ አድርባይ ድርጅቶች የሚያስተጋቡት ፖለቲካ አብዮታዊ ነው፣ ብሎ በመቀላመድ ከተንሸራታቾች ጋር “አብሮ መብላት” ፣ ከፀረ ሕዝቦች ጋር ተሻርኮ በአብዮቱ ጣረሞት ላይ ከሚደረገው “የስልጣን ድልድል” ድርሻውን ተቀብሎ የኢትዮጵያን ሕዝብ መክዳት፣ በታጋይ ጓዶች ንጹህ ደም ተገኝቶ የነበረውን የፖለቲካ ጥራት ገደል መጨመር፣ ወይ ደግሞ የተያዘውን ለአብዮታችንም ሆነ ለብሔራዊ ነፃነታችን እጅግ አደገኛ የሆነውን የፖለቲካ መስመር መታገሉንና ማጋለጡን ቀጥሎ ለማንኛውም መስዋዕትነት ራስን ማዘጋጀት። መኢሶን የትግል ስልት ለውጥ ከማድረጉ በፊት በነበሩት ሁለት ሦስት ወራት ለኢትዮጵያ ተራማጆች በሙሉ አይኑን አፍጥጦ ቀርቦ የነበረው ምርጫ ይህ ነበር። መኢሶን በታሪክ ፊት የተቀበለውን አደራ በማክበር የወሰደው ምርጫ ሁለተኛውን የትግል፣ የክብርና የመስዋዕትነት ጎዳና ነበር። በነሐሴ ወር 1969 ዓ.ም ይህንኑ የተሻለ ሁኔታ ለመቀጠል የትግል ስልት ለውጥ ያደረገውም ከዚህ ታሪካዊ ምርጫ ተነስቶ ነበር።

ይህ እርምጃ ለመኢሶን ብቻ ሳይሆን ለጠቅላላው የኢትዮጵያ ተራማጆች ታላቅ የፖለቲካ ድል ነው። ይህንን የምንልበት ብዙ ምክንያቶች አሉን። መኢሶን በዚያን ጊዜ ለቀረበለት ወሳኝ ምርጫ ፊት በፀረ አብዮትና በአብዮት ጎዳና መሃከል እያመነታ ቢቀጥል ኖሮ፣ “የደርግ ታሪካዊ ሚና እያከተመ ሲሄድ አብዮታዊያን ከሱ ጋር የሚያደርጉት ትብብር ያከተማል” ብሎ የገባውን ቃል ባያከብር ኖሮ፣ በደርግና ባድርባዮች በአንድ በኩል በመኢሶንና በሌሎች አብዮታዊያን በሌላ በኩል ያሉት ልዩነቶች እንደዚህ ግልጥልጥ ባለ ሁኔታ ተፍረጥርጠው ባይወጡ ኑሮ፣ ባጭሩ የአብዮቱን ሰፈር መፈክሮችና ስፍር ቁጥር የሌላቸው ሰማዕታት የተሰዉላቸውን ዓላማዎች አንስቶ መኢሶን ከቀኝ ኃሎች ህብረት ራሱን ነጥሎ ወደፊት ለመጓዝ አስፈላጊውን እርምጃ ባይወሰድ ኖሮ ዛሬ አብዮታችን ይገኝበት የነበረውን የፖለቲካ ውዥንብር ማን ሊገምተው ይችላል? መኢሶን አዲሱን የቀኝ ኃይሎች ህብረት በሰፊው ሕዝብ ፊት፣ ከሰፊው ሕዝብ ጋር ሆኖ መዋጋትን ትቶ እንደተቀሩት አድርባይ ድርጅቶች መሪዎች በፖለቲካ መስመር ጥያቄ ላይ ሳይሆን በቦታ ሽሚያ፣ በይገባኛል አይገባህም ውስጥ ውስጡን ሲራኮት ቢመታ ኖሮ ለኢትዮጵያ ተራማጆች ምን ያህል አሳፋሪ የሆነ የትግል ምዕራፍ በተጻፈ ነበር? በዚህ ሁኔታ መሠረታዊ የሆኑትን የሕዝብ ጥያቄዎች በአድርባይነት ሽሮ፣ ከአዲሱ ፀረ ሕዝብ ኃይል ጋር በጥቅም በተሳሰረ ኖሮ፣ ከሁለት ዓመት ወዲህ በአብዮቱ ስም የተደረጉትን ፀረ ሕዝብና ፀረ ኢትዮጵያ ክብር ድርጊቶች በአብዮትና በብሔራዊ ነጻነት ስም በግንባር ቀደምነት የሚቋቋም ኃይል ባይኖር ኖሮ፣ “የተሰውትን ጓዶች አርማ አንስተን እንዋጋለን” ያልንበትን ቃል ኪዳን ምንኛ በከዳን ነበር?

ይህ እንዳይሆን መኢሶን እርምጃው የሚያስከትለውን መስዋዕትነትና ችግር አውቆ፣ ፈቅዶና መዝኖ በመቀበል የአብዮታችንና የኢትዮጵያ እናታችን ክብር የሚጠይቀውን እርምጃ ወሰደ። በአብዮቱ አንገብጋቢ ጥያቄዎች ሁሉ ደርግ በአብዮቱ ስም ከሚያመለክተው የቅልበሳ ጎዳና ሌላ አማራጭ፣ ሌላ የሀቀኛ አብዮት ፋና እንዳለ መኢሶን ማንኛውንም መስዋዕትነት እየተቀበለ ማስተጋባቱንና ማሳየቱን ቀጠለ። ደርግ እና አድርባይ ድርጅቶች አብዮቱንና የእናት ሀገራችንን ነፃነት ይዘው ወደመቀመቅ በማምራት ላይ መሆናቸውን፣ የአብዮትና የእናት ሀገር ክብር ጎዳና መኢሶን የሚያመለክተው መሆኑን ሕዝቡ የተቀበለው ሀቅ ከመሆኑም ሌላ ዛሬ በነዚህ ሁለት መስመሮች መሃከል ይካሄድ የነበረውን ትግል ዋና ዋና መልክ ስንመለከት መኢሶን ያመለከተው መስመር ምንኛ ትክክለኛ እንደነበር በማያደግም ሁኔታ ለመረዳት ይቻላል።

አዲሱ የቀኝ ኃይሎች ህብረት በአብዮቱ ስም የሰፊውን ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ መብቶች ሲረግጥ መኢሶን “ዴሞክራሲያዊ መብቶች ለጭቁኖች አሁኑኑ” ብሎ ከሰፊው ሕዝብ ጋር የትግል አርማውን አነሳ። የኢትዮጵያ አብዮት በደረሰበት ደረጃ ሰፊው ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ መብቶች ባስቸኳይ ካልታወቁ ከእንግዲህ ወደኋላ እንጅ ወደፊት እርምጃ እንደማይገኝ አስታወቀ። በሀገሪቱ የተፋጠጡት የሰፊው ሕዝብ የአዲሱ ሕዝባዊ ስልጣን ጥንስስ የሆኑት ሕዝባዊ ድርጅቶችና የበሰበሰው ቢሮክራሲ እንደዚያ በተፋጠጡበት ሁኔታ ትግሉ አንዱ አንዱን ሳያጠፋ ስለማይበርድ ሕዝባዊው ስልጣን ፀረ ሕዝቡን ቢሮክራሲ እንዲደመሰስ ዴሞክራሲ ያስፈልገዋል ሲል መኢሶን በቆራጥነት ታገለ። ይህ ካልሆነ ሕዝባዊ ድርጅቶች ቀስ በቀስ እንደሚጠወልጉና የአድሃሪው ቢሮክራሲ አሻንጉሊት እንደሚሆኑ መኢሶን ተናገረ። ዲሞክራሲያዊ መብቶች መታፈናቸውን ቀጠሉ። በዚያው ልክ ደግሞ አድሀሪ ቢሮክራሲ አይሎ ዛሬ ከነመኢሰማ አንስቶ ቀበሌዎች፣ የገበሬ ማህበራትና ሌሎች ሕዝባዊ ድርጅቶች “ሕዝባዊነታቸው” የወደመበት ደረጃ ደረሱ።

ዲሞክራሲ ከሌለ “የተራማጆች ህብረት” የሚባለው ቅጥፈት መሆኑን፣ ያለዲሞክራሲ ሀቀኛ ህብረት ለመመስረት አለመቻሉን መኢሶን ተናገረ። አዲሱ የቀኝ ኃይሎች ህብረት ዴሞክራሲን ማፈን ቀጠለ። ልዩነቶችን በዲሞክራሲያዊ ውይይት መፍታት ያልቻለው “ኢማሌድህ” ዝቅ ብለን እንደምናየው ከፍተኛ ኪሳራ ላይ ወድቆ ትንሽ ከተንገዳገደ በኋላ ዛሬ ጨርሶ መፍረሱ በይፋ ተነገረለት!

ዲሞክራሲ ከሌለ የብሄረሰቦች ችግር እየተባባሰ ይሄዳል እንጂ ለኢትዮጵያ አንድነት መፍትሄ የሚሆን ቁም ነገር ደርግ ከያዘው ትምክተኛ ፖለቲካ ሊመጣ አይችልም ያለው መኢሶን ለብሄረሰቦች የተሟላ አኩልነትና ለኢትዮጵያ ጭቁን ሕዝቦች አንድነት የሚደረገውን ትግል መለያየት እንደሌለበት አስገነዘበ። በጦር ኃይልና በትምክህተኝነት መሰረት ላይ የተገነባው የደርግ ፖለቲካ የኢትዮጵያን ሕዝቦች አንድነት አናግቶ በዚህ በኩል የኋሊት እንጂ ወደፊት እንዳላረመደን ዛሬ ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ግልጽ ነው።

አዲሱ የቀኝ ኃይሎች ህብረት የውጭን ጠላት ለመቋቋም ከአድሃሪ ኃይሎች ጋር እንታረቅ፣ ሁሉም ነገር ወደ ጦሩ ግንባር እያለ የቅልበሳ ፖለቲካውን ሲደረደር በመኢሶን ግንባር ቀደምነት የሚንቀሳቀሱ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ጭቁኖች “እርቅ አንፈልግም ትጥቅ!” “ቢሮክራሲው አያዝምት ይዘመትበት” “አብዮታዊት እናት ሀገር ወይም ሞት” ብለው ተሰለፉ። የቀኝ ኃይሎች ህብረት የያዘው ጎዳና ምናልባት የሀገሪቱን ድንበሮች ለማስከበር ቢችልም በምንም ዓይነት የኢትዮጵያን አብዮት ከቅልበሳ የሚያድን ጎዳና አልነበረም። ይህ ፖለቲካ በጦርነት ግርግር ፀረ ሕዝብ ኃይሎችን ቁልፍ ቦታ የሚያሲዝና የሚያጠናክር ፖለቲካ ነበር። መኢሶን ያራመደው የፖለቲካ መስመር ግን የሀገሪቱንም ህልውና፣ አብዮታችንንም የሚያድን ፖለቲካ ነበር። አዲሱ የቀኝ ኃይሎች ህብረት የተከተለው መስመር የሰጠው ውጤት መኢሶን “የተነበየው” ውጤት ነበር። “አያዝምት ይዘመትበት” በተባለው በአደሃሪው ቢሮክራሲ አማካኝነት በሚካሄድ ጦርነት ሌላው ጠርቶ ድንበርን እንኳን ለመከላከል አልተቻለም። አድሃሪው ቢሮክራሲ በግርግር በያዘው ቦታ በመጠቀም በሚሊተሪውም ሆነ በሚሊሻው ውስጥ ግንባር ቀደም ተራማጆችን እየለቀመ መምታት፣ በጠቅላላው በጦርነቱ ጥረት ላይ ይህ ነው የማይባል አሻጥር እየፈጸመ የሀገሪቱን ችግሮች ማባባስና ሁኔታውን ለቅልበሳ ማመቻቸቱን ትቶ በጦር ግንባር ድልን ይፈልጋል ማለት ዘበት ነበር! በመሆኑም ደርግ የአድሃሪውን የሚሊቴሪ ቢሮክራሲ አሻጥር ለመገንዘብ ብዙም ጊዜ አልወሰደበት። ግን ታዲያ ይህንን ተገንዝቦ ወደ ሕዝቡ ወደ ሃቀኛው መስመር ተመለሰ? የለም። ይህንን ከማድረግ ፈንታ፣ ለጦርነቱ አስፈላጊ የሆነውን አብዮታዊ አመራር በማስገኘት ፈንታ፣ “አብዮታዊት እናት ሀገር ወይም ሞት” እያሉ ለእናት አገራቸውና ለአብዮታቸው ለመሞት የተዘጋጁ በሺህ እና በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያን እያሉ ደርግ በአድሃሪ ቢሮክራሲ አሻጥር የተነሳ በየግንባሩ ለተፈጠረው ችግር ያገኘው መፍትሄ የውጭ ጦር ወደ አገሪቱ አስገብቶ ማዋጋትና የሃገራችንን ክብር ማስደፈር ነበር! አድሀሪው ቢሮክራሲ ሊያዘምት አልቻለም። ግን ደግሞ የሱን አሻጥር ተቋቁሞ በከፍተኛ መስእዋትነት ድልን በተቀዳጀው መደበኛና ሕዝባዊ ሠራዊት ላይ፣ የፈላጭ ቆራጭነት ቦታ ይዞ የወጣው ይኸው አድሀሪው ቢሮክራሲ እንደሆነ ግልጽ ነው። መኢሶን ቀደም ሲል ደርግ የተከተለው “ብሔራዊ እርቅ” ፖለቲካ ዞሮ ዞሮ አብዮት የሚያስቀለብስ አደገኛ ፖለቲካ ነው ያለው ለዚህ ነበር። ይህ ደግሞ ዛሬ ለማንም ግልጽ ሆኖ የሚታይ ሀቅ ነው።

አዲሱ የቀኝ ኃይሎች ህብረት የተከተለው በውጭ ኃይሎች ላይ የመተማመን ፖለቲካ አንደኛ ይህንን ህብረት አጠናክሮ በፀረ ዲሞክራቲክ ገጽታው እንዲገፋበት፣ “ከነቃ፣ ከተደራጀና፣ ከታጠቀ፣ ሕዝብ ትግል” ፈር የጀመረውን ማፈንገጥ እንዲቀጥል፣ ለሰፊው ሕዝብ ጥያቄዎች ጆሮ ዳባ ልበስ ማለት የጀመረውን ፈሊጥ ሥራዬ ብሎ እንዲይዘው የሚያግዝ፣ ሁለተኛው ደግሞ አገራችንን በሀያላን መንግሥታት በስትራቴጂያዊ ገበጣ ጨዋታ ወደ ተራ ጠጠርነት የሚያዋርድ፣ ብሔራዊ ነጻነታችንን አስደፍሮ በዓለም ሕዝቦች ፊትና በተለይ በአፍሪካ ሕዝቦች ፊት እንደገና “የአህጉር ሀፍረት” የሚያደርገን ሁኔታ የሚያመጣ አደገኛ ፖለቲካ መሆኑን መኢሶን ተናገረ። በሱ ፈንታ የአብዮቱን ችግሮች ለመወጣት እርግጥ የውጭ እርዳታ ያስፈልጋል ግን ከሁሉ በላይ የሕዝቡ መንቃት፣ መደራጀትና መታጠቅ ላይ መተማመን እንደሚያስፈልግ፣ እርዳታው ከዚህ የአብዮት ጎዳና የሚያርቅ እርዳታ እንዳይሆን፣ በእርዳታ ሰበብ ብሔራዊ ነፃነታችንም እንዳይደፈር፣ እርዳታ በአጋዥነት እንጂ በወሳኝነት ደረጃ መቀመጥ የለበትም ሲል ተከራከረ። የደርግ ፖለቲካ በሁለቱም በኩል ዛሬ የት ላይ እንደጣለን ግልጽ ነው።

በዚህ አይነት ብዙ መቀጠል ይቻላል። በአጭሩ ለማስቀመጥ ግን ዛሬ የኢትዮጵያ አብዮትና የሀገሪቱ ብሔራዊ ነፃነት የሚገኝበትን መቀመቅ የተመለከተ ሰው መኢሶን ያራምደው የነበረውና አሁንም የሚያራምደው ምን ያህል ትክክለኛ እንደነበር በቀላሉ ሊረዳው ይችላል። ይህንን የምናነሳው ከዛሬ ሁለት ዓመት ጀምረን ባነሳናቸው ከደርግና ካድርባይ ድርጅቶች መሪዎች ጋር በነበሩን ልዩነቶች የእኛ አቋም ትክክል ነበር ብለን “ታሪክን” ለመፃፍ አይደለም። መኢሶን አንስቷቸው የነበሩት ጥያቄዎች አሁንም የአብዮቱ አንገብጋቢ ጥያቄዎች ናቸው። አሁንም ሰፊው የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚዋደቅላቸው ናቸው። ዛሬ ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ የነዚህን ጥያቄዎች ትክክለኛነት፣ ሕዝቡ በመኢሶን ቅስቀሳ ብቻ ሳይሆን በተጨባጭ በሚሰማውና በሚያየው ተረድቷል። ስለሆነም ዛሬ ሰፊው ሕዝብ የሚፈልገውን ያውቃል። ማን በአብዮቱ ሰፈር እንደ ቀረ፣ ማን ከአብዮቱ ተንሸራቶ ወደ ታሪክ አተላነት በመንጎድ ላይ እንደሆነ ያውቃል።

ይህ የፖለቲካ ጥራት ደግሞ በቀላሉ የሚደፈርስ አይደለም። እንዲያውም በመጪው ጊዜ በዚህ በኩል ይበልጥ ጥራት እየተገኘ ይሄዳል። ለምን? ምክንያቱ አጭር ነው። አዲሱ የቀኝ ኃይሎች ህብረት በመደብ ይዘቱ የተነሳ የኢትዮጵያን አብዮትና የአገሪቱን ብሔራዊ ነፃነት ለሚመለከቱት ጥያቄዎች ለአንደኛቸውም ተገቢውን መልስ ለመስጠት ከዕለት ዕለት ይበልጥ እየተሳነው እንደሚሄድ ከአሁኑ “ለመተንበይ” ይቻላል። በዚህም የተነሳ ይህ ከዕለት ዕለት በአድሃሪ ቢሮክራሲና በውጭ ኃይሎች ቁጥጥር ስር እየገባ የሚሄደው “ህብረት ለጠቅላላው በብሔራዊ ዴሞክራሲያዊ አብዮት ፕሮግራም ላይ ፀንተው ከቆሙ ኃይሎች ጋር በሙሉ ከዕለት እለት የባሰውን እየተቆራረጠ፣ የባሰ ቅራኔ ውስጥ እየገባ ይሄዳል። በዚህም የተነሳ ከገባበት አዙሪት ውስጥ ለመውጣት የሚቀረው መንገድ የባሰውን ከቢሮክራሲና ከውጭ ኃይሎች ቁጥጥር ስር መውደቅ እንደሆነ ግልጽ ነው። ባለፉት ወራት ከመኢሶን አባላት ሌላ በተጨማሪ ከወዛደር ሊግ ከኢጭአት ከሰደድ ከራሱ አንዱ ክፍል ጋር እየተፋፋመ የሄደው ቅራኔ የኢትዮጵያን አብዮት አንገብጋቢ ጥያቄዎችን ለመመለስ ያልቻለው የቀኝ ኃይሎች ህብረት ይበልጥ በአድሃሪው ቢሮክራሲ ቁጥጥር ስር እየወደቀና በሀገሪቱ ካሉ ተራማጅ ኃይሎች ጋር እየተባባሰ የሚሄድ ቅራኔ ውስጥ እየወደቀ መሄዱን የሚያሳይ ሂደት ነው።

በሌላ በኩል ድግሞ መጪው ጊዜ በብሔራዊ ዲሞክራሲያዊ አብዮት ፕሮግራም ላይ የተሰለፉ ኃይሎች ለትግላቸው ይበልጥ ያመቸ እንደሚሆን የዛኑ ያህል ግልጽ ነው። መጪው ጊዜ ለዲሞክራሲ፣ ለብሔረሰቦች እኩልነት፣ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ክብርና ነጻነት፣ ለሃቀኛ የተራማጆች ህብረት፣… ለሚታገሉ ኃይሎች እንጂ ለፀረ ዲሞክራሲ፣ትምክህተኝነት፣ ለብሔራዊ ውርደት ለቆሙ ጥቂቶች እንዳይደለ ሳይታለም የተፈታ ጉዳይ ነው። ስለሆነም የኢትዮጵያ ተራማጆች በጠበቁትና ባልተገረሙበት የንዑስ ከበርቴ መደብ መንሸራተት በምንም ዓይነት ሳይሸበሩ፣ በአቋማቸው ትክክለኛነት ብቻ ሳይሆን በዚህ ትክክለኛነት ዘላቂነት ሙሉ በሙሉ በመተማመን፤ ጊዜ ለእነሱ እንጅ ለተንሸራታቾች እንዳልሆነ በማወቅ የታሪክ ሂደት ለእነርሱ እንጅ በቀልባሾቹ በኩል እንዳልቆመ በመረዳት ለመጪው የትግል ምዕራፍ በጥሞናና በዲስፕሊን፣ በቆራጥነትና ለመጪው ድል በማይጠራጠር መንፈስ ራሳቸውን ማዘጋጀት አለባቸው። ይብላን ለታሪክ አተላዎች እንጂ ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ እንደሆነች ሕዝባዊት ኢትዮጵያ እንደሆነች የተራማጆች ነፃ ኢትዮጵያ እንደሆነች፣ ከአብራኳ ከምታወጣቸው ታጋይ ልጆቿ ትግልና ደም በፊውዳሊዝም፣ በኢምፔሪያሊዝምና በቢሮክረሲያዊ ካፒታሊዝም መቃብር ላይ ትገነባለች።

ይህንን ስላልን መጪው ጊዜ አስቸጋሪ የትግል ጊዜ አይሆንም ለማለት አይደለም። የፖለቲካ ጥራት ብቻውን ፀረ ሕዝቦችን ተቋቁሞ ድል አያደርግም። ግን ይህ ራሱ በኢትዮጵያ ግንባር ቀደም ኃይሎች እጅ ያለ ከፍተኛ የትግል መሳሪያ ነው። በነሀሴ 1969 ዓ.ም የትግል ስልት ለውጥ ባደረግንበት ሰዓት በዚህ ጉዳይ ላይ እንደሚከተለው ብለን ነበር። “ኢትዮጵያ ሕዝቦች ለነፃነትና ለእኩልነት፣ ለሰላምና ለወደፊት እርምጃ የሚያደርጉት ተጋድሎ እንደ ዛሬ አመቺ ሁኔታን አግኝቶም አያውቅም። ችግሮቻችንና ድክመቶቻችን፣ የአብዮታችን መቦርቦርና የሃገራችን መወረር ጊዜያዊ ናቸው። ዘላቂነት የላቸውም። የፖለቲካ መስመር ትክክለኛነት ወሳኝ መሆኑን በመገንዘብ፣ ፖለቲካን አስቀድመን ችግርንና ሞትን ሳንፈራ በሰፊው ሕዝብ ተማምነን እስከመጨረሻው ለመታገል ቆርጠን ከተነሳን፣ አንድነታችንን አጠንክረን ወደፊት ከተራመድን የፈጀውን ጊዜ ቢፈጅም የፈለገውን መስዋዕትነት ቢጠየቅም በእርግጥ እናሸነፋለን”።

ይህ አነጋገር ሙሉ በሙሉ ትክክል ነበር። ግን አንድን አብዮት ለማራመድ ምንም ያህል ትክክለኛ አቋምን ቢይዙ አቅምም ያስፈልጋል። ዛሬ ባለው የሃገራችን ተጨባጭ ሁኔታ እንዲያውም አንገብጋቢ የሆነው ጥያቄ እስከዚህም ለሰፊው ሕዝብ የትግል አቅጣጫዎችንና አላማዎችን መጠቆም ሳይሆን በሕዝቡ ዘንድ ተቀባይነት ያገኘውን መስመር ከሥራ ላይ ለመዋል የሚያስፈልገውን ኃይል መሰብሰብና ማደራጃት ነው ብለን እንገምታለን። የቀኝ ኃይሎችም ይህንን ያውቁታል። የትግል መሣሪያ የሆኑትን ድርጅቶቹንም በሙሉ ያፈራረሱት፣ ግንባር ቀደም አንቂዎቹንና አደራጆቹን በሙሉ የረሸኑበትንና በየእስር ቤቱ ያጎሩበት፣ ተራማጅ የፖለቲካ ድርጅቶቹን ለማፈን የሞከሩበት ዋናው ምክንያትና ከዚያም “ታግለህ ውሰድ” ብለው ያሹፉበት ለዚህ ነው። የቀኝ ኃይሎች ይህንን የፖለቲካ ጥራት ማደፍረስ ስላቃታቸው፣ ይህ መስመር ከሥራ ላይ እንዳይውል በዚህ ቁልፍ በሆነው የመደራጀት ጥያቄ ላይ ተረባርበዋል። ተራማጆች ደግሞ በፖለቲካው መስመር ጉዳይ ባገኙት ይህ ነው የማይባል ድል ላይ ተመስርተው በዚህ ቁልፍ ጥያቄ ላይ መረባረብ አለባቸው። የጊዜው አንገባቢ ጥያቄ ይህ ነው።

አዎን! ዛሬ የሀገራችንን ሁኔታ ሌላ መልክ የሚሰጠው ባለው እጅግ አመቺ በሆነና ከእለት እለት ለአብዮታውያን ይበልጥ አመቺ እየሆነ በሚሄደው የፖለቲካ ጥራት አንጻር ሲታይ ይህንን ፖለቲካ ከሥራ ላይ ሊያውለው የሚችለው ኃይል ሁኔታው በሚጠይቀው ልክ አለመደራጀቱና ኃይሉን አለማስተባበሩ ነው። በዚህም የተነሳ የጊዜው ዋና አንገብጋቢ ጥያቄ የግንባር ቀደም ድርጅቶች ማጠናከርና ተራማጆች በቀኝ ኃይሎች ህብረት ሴራና ተንኮል የተበታተነውን ህብረታቸውን እንደገና መገንባት ነው እንላለን። ይህንን ተግባር በዚች ቁጥራችን ሁለተኛ ክፍል እስክንመለስበት ድረስ ዛሬ በድርጅት ጉዳይ ያለንበትን የመዳከም እና የመበታተን ሁኔታ መመልከቱ ይጠቅማል።

እንደማንኛውም መስክ በቀኝ ኃይሎች ህብረት ሴራ የተነሳ በዚህ በድርጅትም መስክ የተገኙት ድሎች ሁሉ ተበትነዋል። የኃሊት ጉዞ ተደርጓል። ይህ በድርጅት ጎዳና ላይ ያደረጋቸው የኃሊት ጉዞ ከብዙ አንፃር ሊታይ ይችላል። በመጀመሪያዎቹ አብዮት ሰፈር ተደራጅቶ ይገኝ ከነበረው ኃይል ዛሬ ወይ በአመራር የፖለቲካ ክስረት የተነሳ ተስፋ እየቆረጠም ሆነ በቀኞች እየተመታ በመበታተን ላይ ይገኛል፣ ወይ ደግሞ በጠራና ግልጽ በሆነ አብዮታዊ መስመር ተሰልፎ በከፍተኛ ፀረ ሕዝብ አመጽ የተነሣ ድርጅቶቹ ተዳክመዋል። ከዚህም ከአመራሮች የፖለቲካ ክስረት ከተከተለው መበታተንና በፀረ ሕዝብ አመፅ የተነሳ ከተከተለው ድርጅታዊ መዳከም ጋር ተያይዞ ዛሬ የኢትዮጵያ ተራማጆች በየካቲት ወር 1969 ዓ.ም ደርሰውበት የነበረው የህብረት ደረጃም ተቀልብሶ እናገኘዋለን። በዚህ የተነሳ ዝቅ ብለን እንደምናየው “ኢማሌድህ” ይባል የነበረው የህብረት መዋቅር ጨርሶ ከመደምሰሱ በፊት የቱ ላይ “ማርክሲስት ሌኒኒስት” የትኛው ላይ “የድርጅቶች ህብረት” ሊባል እንደሚችል የማይታወቅበት ጥንድ የሆነ የክስረት ደረጃ ላይ ወድቆ እንደነበር እናያለን።

የተለያዩ በአብዮቱ ሰፈር የነበሩትንም ሆነ ያሉትን ድርጅቶች ሁኔታ እንመልከት። እዚህ ላይ በአንድ በኩል የ“ግራ” አድርባዩና የቀኝ አድርባይ ድርጅቶች ሁኔታ አለ። የነዚህ ድርጅቶች አመራሮች ተራ በተራ የተከተሏቸው የከሰሩ የፖለቲካ መስመሮች ነበሩ። በዚህም የተነሳ ውሎ ይደር እንጂ ሁሉም ከፖለቲካ ክስረታቸው ጋር የተያያዘ ድርጅታዊ ክስረትና መበታተን መፍረክረክ ደርሶባቸዋል። በሌላ በኩል ደግሞ ዛሬም ቢሆን በሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን አንግበው የሚታገሉለትን የፖለቲካ መስመር በግንባር ቀደምት አንስቶ የሚዋጋው መኢሶን አለ። መኢሶን የተከተለውንና አሁንም የሚከተለው ፖለቲካ የሕዝብ መስመር ነው። የፖለቲካ ኪሳራ የለበትም። ስለሆነም በፀረ ሕዝብ ኃይሎች የተሰነዘረበት አመፅ ድርጅታዊ መዳከምን እንጂ ኪሳራን ሊያመጣበት አይችልም። አላመጣበትምም። ፖለቲካውና መስመሩ ትክክለኛ ስለሆነ፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ማርክሲስቶች፣ ዲሞክራቶችና አገር ወዳዶችም አንደሱ ዲሞክራሲ፣ ብሔራዊ ነፃነት፣ የብሄረሰቦች እኩልነት፣ ሀቀኛ የተራማጆች ህብረት ስለሚሉ ለጊዜው ሁኔታ መዋቅሩን አስተካክሎ ወደፊት ይጓዛል እንጂ ምንም አይነት አመጽ ሊደመስሰው አይችልም።

በመጀመሪያ ከፖለቲካ ኪሳራ ጋር ድርጅታዊ ኪሳራ የደረሰባቸውን እንመልከት። ብዙ ጊዜ ተደጋግሞ እንደተወሳው የኢህአፓ ጀብደኞች ትግል በኢትዮጵያ ተራማጆች በተለይም በወጣቱ አካባቢ ያስከተለው እጅግ አስከፊ የሆነ ውጤት አለ። ኢህአፓ የኢትዮጵን አብዮት የበደለው በብዙ መቶ የሚቆጠሩ ተራማጅ ኢትዮጵያዊያንን መጨረሱ፣ በሃቅና በጥሞና የሚካሄድ ትምህርታዊ ውይይት እንዳይካሄድ አፍኖ አንድን ታጋይ ትውልድን አደንቁሮ በቀልባሽ ፖለቲካው ለማሰለፍ መፍጨርጨሩ ብቻ አይደለም። ዛሬ እንደምናየው መስሏቸው የተከተሉት ሀቀኛ ተራማጅ ኢትዮጵያዊያን፣ በከንቱ ተጨፍጭፈው ያለቁትም፣ የኢህአፓ ክስረት በምንም አይነት በማያወላውል ሁኔታ ይፋ ሲወጣ የወደቀበት ውዥንብርና ተስፋ መቁረጥ፣ ምን ሀቀኛ መስመር ቢኖር ከሱ ስር ለመሰለፍ የሚያሳዩት ከፍተኛ ጥርጣሬና ማመንታት ለጠቅላላው በፖለቲካ ትግል የሚያሳዩት ገለልተኝነት. . . የኢህአፓ መሪዎች በኢትዮጵያ ታጋይ ትውልድ ላይ የፈፀሙት ታሪክ ምን ጊዜም ይቅር የማይላቸው ወንጀል እንደሆነ ለማየት አያስቸግርም።

የኢህአፓ ቀልባሽ የፖለቲካ መስመርና ጀብደኛ የትግል ዘዴ ካስከተለው መበታተን ሌላ ከአንድ ዓመት ወዲህ ደግሞ የቀኝ አድርባይ ድርጅቶች መሪዎች አመራሮች የተከተሉት ፖለቲካ ያመጣው ውዥንብርና ድርጅታዊ ክስረት አለ። የቀኝ አድርባይ ድርጅቶች መሪዎች የከሰረና የኢትዮጵያን ጭቁኖች አንገብጋቢ ጥያቄዎች የሚፃረር የፖለቲካ መስመር ተከተሉ። ይህንን መስመራቸውን የተቃወሙትን ሀቀኛ አብዮታዊ ቢሮክራሲ ጋር አብረው አሳደዱ። እየጠቆሙ አስያዙ፣ አስገረፉ፣ አስረሸኑ። ፀረ ሕዝብ ፖለቲካቸውን በውሳኔ መልክ “ሕዝቡ አሳለፈው፣ ሕዝቡ ይደግፈናል” እያሉ በራዲዮና በጋዜጣ አስለፈፉ። ነገር ግን በዚህ ፖለቲካቸው ኪሳራ የተነሳ ሕዝብ እንደተፋቸው፣ ሕዝብ ከተፋቸው በኋላ ደግሞ ባሸዋ ላይ የገነቡት “ድርጅታዊ ቤታቸው” ፀረ ሕዝቡ ቢሮክራሲ “እፍ” ሲለው እንደሚፈርስ አልተገነዘቡም ነበር። ነገር ግን ተጠቅሞባቸው ከጨረሰ በኋላ አድሃሪ ቢሮክራሲ እንደደረቀ ሎሚ ጣላቸው። አምኖ ይከተላቸው የነበረው ዲሞክራትና አገር ወዳድ፣ አድርባይ መሪዎቹ በምን ላይ ከፀረሕዝቡ ቢሮክራሲ እንደ ተለዩ ሳይገባው እየታደነ ይመታ ጀመር። መኢሶን በፀረ ሕዝቦች ቢመታ “ዲሞክራሲ” ብሎ ነው። መኢሶን የትምክተኞች አመጽ ቢወርድበት “የብሄረሰቦች እኩልነት” ብሎ ነው።. . . ባጭሩ ፀረ ሕዝቦችና ፀረ ኢትዮጵያ ኃይሎች ቢያጠቁት በግልጽ እና በይፋ ከሕዝቡ ወገን መሆኑን አረጋግጦ ነው። በአድርባይ ድርጅቶች ስር ተደራጅቶ የነበረው ሀቀኛ ታጋይ በእንዲህ ዓይነቱ ሁኔታ ከላይ መሪዎቹ በሚያካሂዱት የስልጣን ሽኩቻ ምክንያት እሱም እየተመታ ሲሄድ ሙሉ በሙሉ ግራ መጋባቱ ምንም የሚያስገርም አይደለም። ግራ መጋባት ብቻ ሳይሆን ለዚህ ክፍል ትግልም ሊቀጥል ሲል አስቸጋሪ ሁኔታ ላይ ነው። የአድርባዮቹ ድርጅቶች አመራሮች ያስጨበጡትን የከሰረ የፖለቲካ መስመር ይዞ ወደ ሕዝብ ሊሄድና ሊያደራጅ አይችልም። ያለው አማራጭ ሀቀኛውን መስመር አንስቶ የሕዝቡን አንገብጋቢ ጥያቄዎች ከሌሎች አብዮታዊያን ጋር በአንድነት መቆም ብቻ ቢሆንም ይህ በአድርባይ ድርጅቶች ውስጥ የነበረው የሃቀኛ ታጋዮች ክፍል ከፀረ ሕዝቦች ኃይሎች በኩል በወረደበት ዱብ እዳ ገና ግራ ከመጋባት ደረጃ አልፎ፣ በውዥንብር ውስጥ ከመዋዥቅ አልፎ አልሄደም። በዚህም የተነሳ ዛሬ በተለይ “በወዛደር ሊግ” ውስጥ ተሰልፈው የነበሩት ታጋዮች ብቻ ሳይሆኑ በአብዮታዊ ሰደድ በራሱ ውስጥ የሚገኙት ሃቀኛ ማርክሲስት ሌኒኒስቶች በአመራር ስህተትና አድርባይነት ካጋጠማቸው የፖለቲካ ክስረት ጋር ከፍተኛ ድርጅታዊ ክስረት ውስጥ ወድቀው ይገኛሉ።

ከዚህ ሌላ እንግዲህ የማንክደው ድርጅታዊ መድከም አለ። በሺህ የሚቆጠሩ አባላቱ ታስረውበት፣ በመቶ የሚቆጠሩ አባላቱ በያለበት ወድቀውበት እንኳን እንደኛ አይነቱ ለጋ ድርጅት ይቅርና ማንም ድርጅት ቢሆን መዳከሙ አይቀርም። ነገር ግን ሁለት ነገሮች አሉ። መኢሶን የሚከተለው መስመር ሕዝባዊ ስለሆነ ምን ጊዜም ቢሆን ድርጅታዊ ኪሳራና መበተን ሊደርስበት አይችልም። ይህንን ደግሞ ባለፈው አንድ ዓመት ተኩል የአብዮታችን ሂደት በሚገባ አሳይቶታል። አዲሱ የቀኝ ኃይሎች ህብረት በአድርባይ ድርጅቶች “ግንባር ቀደምነት” በመጀመሪያ መኢሶንን ከሕዝቡ ለመነጠል ሞከረ። የመስመር ትግል ብሎ የጀመረው የራሱን ኪሳራ ማጋለጫ ሆነ ከሕዝብ የመነጠሉ ፖለቲካ አልሰራም። ድርጅቱን ለመከፋፈል ሞከረ። ልክ አሁን “በወዛደር ሊግ” ድርጅት ላይም ሲሞክር እንደሚታየው በሰደድም ውስጥ “ግራ ክንፍና” ቀኝ ክንፍ እያለ እንደጀመረው አድሃሪው ቢሮክራሲ በመኢሶንም ውስጥ “ግራ ክንፍ” አገኘሁ ብሎ ቀላምዶ ነበር። “ግራ ክንፍ” የተባለችው ነገር እንኳን ክንፍ ልትሞላ ቀርቶ በስተቀኝ በኩል የረገፈች የታሪክ አተላ ላባ ሆና ትገኛለች። ይቺ “ግራ ክንፍ” ቢላት ቢላት ከአስር ሰው አልበለጠችም። ማንንም አላታለለችም እንግዲሀ ይህ አልሰራ ሲል በድርጅቴ ላይ በለየለት ፀረ ሕዝብ አመጽ ተሰማራ። ከላይ እንዳልነው በዚህ አመፅ ንቅናቄያችን ተዳከመ ግን አልተደመሰሰም። በፖለቲካው አንጻር በሃቅ ለአብዮት፣ ለሕዝብ፣ ለእናት ሃገር ባደረገው ምርጫ እስከ መጨረሻ የሚሰዋ ድርጅት መሆኑን በሰፊው ሕዝብ ፊት አስመሰከረ። በንጹሕ ጓዶች ደምና መከራ መኢሶን የሚጽፈው የትግል ታሪክ በሕዝብ ዘንድ ተቀባይነቱን ጨመረለት። በድርጅታዊ ጥንካሬ በኩል ደግሞ ለዘላቂው ትግሉ በውድ ጓዶቹ ደምና መከራ እየከፈለ የቀሰማቸውን ትምህርቶች በሚገባ አዋህዶ በአብዮቱ ሰፈር መታገሉን ቀጠለ።

ነገር ግን የኢትዮጵያ አብዮት በመኢሶን ግንባር ቀደም ታጋዮች ትከሻ ላይ የወደቀ ኃላፊነት ብቻ አይደለም። ዋናው ኃይል በሚሊዮን የሚቆጠረው የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው። ይህንን ኃይል ለማንቀሳቀስ የኛ ብቻ ሳይሆን በግንባር ቀደምነት የተሰለፉ የኢትዮጵያ ማርክሲስት ሌኒኒስቶች፣ ዲሞክራቶችና አገር ወዳዶች ተግባር መሆኑን እያንዳንዱ ሀቀኛ ኢትዮጵያዊ፣ እያንዳንዷ ሀቀኛ ኢትዮጵያዊት አምነው መቀበል አለባቸው። ለዲሞክራሲ፣ ለእኩልነት፣ ለብሔራዊ ነፃነት የቆሙ ኃይሎች ሁሉ ዛሬ ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ የወደቀበትን ውዥንብር ተወጥተው፣ የፀረ ሕዝቦች አመጽም ሆነ የተለያዩ አድርባይ አመራሮች የከሰረ የፖለቲካ ምስመር ያመጣባቸውን መበታተን አሸንፈው በሀቀኛ መስመር ላይ ለእናት ሃገርና ለአብዮት በህብረት መዋደቅ አለባቸው።

የዛሬው፣ የመኢሶን የህብረት ጥሪ ይህ ነው። ውዥንብር ይብቃ፣ መበታተን ይብቃ፣ ከሁሉ በፊት ለአብዮታችን፣ ከሁሉ በፊት ለእናት አገራችን የምንል ኢትዮጵያውያን ሁሉ እጅ ለእጅ ተያይዘን ወደፊት እንራመድ ይላል። አንባቢ ይህንን ሌላ የተራማጆች ጥሪ ስናስተጋባ “ኢማሌድህስ” ብሎ ይጠይቀን ይሆናል። በይፋ ከመፍረሱ በፊት ቢሆን “የወዝአደሩ ፓርቲ ጥንሰስ” እየተባለ ይተረትለት የነበረው “ኢማሌድህ” የካቲት 1969 ዓ.ም “ኢማሌድህ” አልነበረም። ከዚያኛው ጋር ሲነፃፀር ከላይ እንደጠቆምነው “ኢማሌድህ” ይባል የነበረው ህብረት ጥንድ ኪሳራዎች ደርሶበታል።

የመጀመሪያው “የኢማሌድህ” የፖለቲካ ክስረት ነው። አንድ ድርጅት መቼም ራሱ ማርክሲስት ሌኒኒስት ነኝ ስላለ ብቻ “ማርክሲስት ሌኒኒስት” ነው ማለት አይቻልም። በኢማሌድህ የፖለቲካ ክስረት ከውስጡ ቀሩ ከተባሉት ድርጅቶች የፖለቲካ ክስረት ጋር የተያያዘ ነው። ይህንን ክስረታቸውን ለማሳየት ሌላ ዝብዝብ ውስጥ ከመግባት እነዚህ “ማርክሲስቶች” “ይህ ዝቅተኛው ነው ከዚህ አልፈን እንሄዳለን” ይሉት የነበረውን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ዲሞክራሲያዊ የአብዮት ፕሮግራም እንዴት አድርገው ምንሽርሽሩን እንዳወጡት መጠቆም፣ ከዚያስ ወዲህ የየካቲት 1969 ዓ.ም የኢትዮጵያ ማርክሲስት ሌኒኒስቶች ድርጅቶች ህብረት የጋራ መግለጫና መርሀ ግብር ላይ ከማሉበትና ከተገዘቱበት አቋማቸው የትኛውን እንዳከበሩ ራስን መጠየቅ ብቻ ይበቃል።

ሌላው ደግሞ ኢማሌድህ ላይ የደረሰው ድርጅታዊ ክስረት ነው። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ኢማሌድህ የሚባለው ነገር የቱ ላይ “የድርጅቶች ህብረት” እንደሚባል ግራ የሚያጋባ ነበር። መኢሶን እንደሆነ “ተባሯል” ኢጭአት እንደሆነ “ለጊዜው”፣ ተወግዷል፣ “የወዝአደር ሊግ” እንደሆነ የአድሃሪው ቢሮክራሲ ሹማምንት “ግራ ክንፍ” ተብለው አመራሩን ከያዙ በኋላና አባሉ ሁሉ እየታፈሱ በየእስር ቤቱ ከታጎሩ በኋላ ምኑ ቀርቶ የዚህ “ህብረት” አባል እንደሚሆን አይታወቅም። አዲሱ የቀኝ ኃይሎች ህብረት በየካቲት 1969 ዓ.ም የኢትዮጵያ አብዮታዊያን ለትግላቸው መሳሪያ እንዲሆናቸው በደማቸው ከፍለው ያቋቋሙትን “ኢማሌድህን” ማራቆቱን ከዚህ ላይ አላቆመም። አድሃሪው ቢሮክራሲ ሰደድን ራሱንም ቢሆን የሚፈልገው በአብዮቱ ስም እየማለ ለሚያደርገው ጭፍጨፋ “ሽፋን” እስከሰጠው ነው እንጂ ተራማጁን “ከጨረሰ” በኃላ ምን ሊያደርግለት “እሹሩሩ” ይለዋል? በዚህም የተነሳ አድሃሪው ቢሮክራሲ “ዘመቻውን” ቀጥሎ አሁን ደግሞ “ሰደድም በአድሃሪዎች የተጥለቀለቀ ድርጅት ነው” በማለት በዚያ ውስጥ ያሉ ሃቀኞችን እየመታ ያፈራርሰው ይዟል። እሱም የነወዝ ሊግ ድርጅታዊ ኪሳራ እየወደቀበት ነው።

በኪሳራ ድርጅቶች “አባላት” የተመሰረተ “ህብረት” ድምሩ ያው ኪሳራ በመሆኑ ይኸው በየካቲት ወር 1971 ዓ.ም የወጣው “የህብረት ድምፅ” ህብረቱ መፍረሱን፣ “ኢማሌድህ” የነበረው ነገር እራሱ “በአድሃሪያን ስለተጥለቀለቀ” ከእንግዲህ እሱን “አዋህዶ” ፓርቲ ማቋቋም የማይቻል መሆኑን አብስሮልናል። ለአድሃሪዎች “የኢማሌድህ ታሪካዊ ሚና” አለቀ ማለት ነው። ከእንግዲህ ብሔራዊ ዲሞክራሲያዊ አብዮትን በይፋ ክደው፣ ቢያንስ በዚህ ፕሮግራም ላይ ቆመው የሚታገሉ ድርጅቶችንም ሆነ ግለሰቦችን በይፋ ተቋቁመው የሚታገሉበት በፀረ ሕዝብ ገጽታቸው ደፍረው የሚወጡበት ደረጃ እየደረሱ ነው ማለት ነው። የየካቲት 1971 የህብረት ድምፅ ይህንን በፀረ አብዮት ጎዳና ላይ የተደረገ አንድ “የወደፊት እርምጃ” አዲስ ምዕራፍ ብሎ ሰይሞታል።

ይህ “አዲስና ወሳኝ ምዕራፍ” የኢትዮጵያ ወዝአደሮች ፓርቲ “ከድርጅቶች ውህደት” ሳይሆን “ከግለሰብ ኮምኒስቶች ውህደት” ይመሠረታል ብሎ የኢማሌድህንም ሆነ እውስጡ ቀርተናል ይሉ የነበሩትን ድርጅቶች መፍረስ አብስሯል። በዚህ “ሂደት” ታሪክ ላይ ወደፊት በሰፊው እንመለሳለን። ይህ “አዲሱ ምዕራፍ” በከሠረ ፖለቲካ ላይ መጓዝ ጀምሮ የነበረው “ኢማሌድህ” “ራሱም ወደ ወዛደር ፓርቲነት” በመለወጥ ሳይሆን እንዲሁ በመበተን ወደ ታሪክ ትቢያ መጣያ የወረደበት ምዕራፍ መሆኑን ብቻ ጠቁመን ለጊዜው እናልፈዋለን።

እንግዲህ የቀድሞ ኢማሌድህ ከስሯል። ፈርሷልም። ነገር ግን ይህ ብቻ አይደለም። ይህ ክስረት ባይኖር እንኳ ኖሮ ኢማሌድህ “የማርክሲስት ሌኒኒስቶች” ብቻ ስለነበር ዲሞክራቶችንና አገር ወዳዶችን የሚጨምር ህብረት አልነበረም። ዛሬ ከመቼውም ጊዜ የኢትዮጵያ አብዮት በቀኝ ኃይሎች ህብረት ሤራ የተነሳ ከገባበት መቀመቅ ወጥቶ ወደ ፊት እንዲጓዝ የማርክሲስት ሌኒኒስቶች ብቻ ሳይሆን የጠቅላላው ተራማጅ ኃይሎች ህብረት ያስፈልጋል። ዛሬ መኢሶን ከላይ ባቀረባቸው የጊዜው ሁኔታዎች ትንተናዎች ላይ ተመርኩዞ ለዚህ ህብረት ጥሪ ያደርጋል።

ክፍል 2  የመላው ኢትዮጵያ ሶሻሊስት ንቅናቄ ለመላ ማርክሲስት ሌኒኒስቶች፣ ዴሞክራቶች፣ አገር ወዳዶች ሁሉ የትግል አንድነት ጥሪ

ጓዶች፣ ጓዲቶች፣ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን!

የመላ ኢትዮጵያ ሶሻሊት ንቅናቄ የሰፊውን ሕዝብ ወገን መርጦ ለአብዮታችንና ለእናት አገራችን ክብርና ነጻነት በግንባር ቀደምነት ሲዋደቅ የቆየ እና አሁንም በመዋደቅ፣ በመሰዋትና ወደፊት በመራመድ ላይ መሆኑን ወዳጅ በደስታ ጠላት በመርበትበት የሚመለከተው ሀቅ ነው። ቀደም ሲል በጨለማው በኃይለሥላሴ አብዮታዊ አገዛዝ፣ ከዚያም በየካቲት የዲሞክራሲያዊ አብዮት ፍንዳታ ወቅት የሰፊውን የኢትዮጵያ ሕዝብ ትግል ፈር ለማስያዝ ከሌሎች ታጋይ ኢትዮጵውያን ጎን ተሰልፎ አብዮቱና የእናት አገር ፍቅር የጠየቀውን ማንኛውንም መስዋዕትነት እየከፈለ በግንባር ቀደምነት ተሰልፎ ቆይቷል፣ አሁንም እንደተሰለፈ ይገኛል። በዚህ ትግሉ በኢትዮጵያ አብዮት ላይ ተራ በተራ የተነሱ ኃይሎች ሁሉ ከተራ ፊውዳል አሉባልታና ሃሜት አንስቶ እስከ ለየለት ፀረ ሕዝብ አመጽ ድረስ በማፈራረቅ መኢሶንም ላይ ተነስተው ሊያጠፉት ሞክረዋል። ደግመን እንዳልነው የመአሶን የፖለቲካ አቋሞች የመላው ኢትዮጵያን ሕዝብ ፍላጎቶችና ምኞቶች የሚያንፀባርቁ፣ የሀገራችንን ክብር ነፃቷንና አንድነትዋንና ብልጽግናዋን የሚያረጋግጡ አቋሞች ስለሆኑ ማንኛውም ፀረ ሕዝብ ኃይል መኢሶንን በሰፊው የኢትዮጵያ ሕዝብ ፊት፣ በግንባር ቀደም ኢትዮጵያዊያን ፊት በፖለቲካ መስመሩ ሊያጋልጠውና ሊያዳክመው አልቻለም። ስለሆነም የኢትዮጵን አብዮት በመቃወም የተነሱ ኃይሎች በሃቀኛ ተራማጆች ላይ በፀረ ሕዝብ አመጽ ከመሰማራት በስተቀር ያገኙትን ሂደት መቋቋሚያ ዘዴ የለም።

ፀረ ሕዘብ ኃይሎች በተለይ ከሁለት ዓመት ወዲህ በአብዮቱ ላይ ያካሄዱት የጥቃት ዘመቻ በመጠኑም ቢሆን ለጊዜውም ቢሆን የአብዮቱን ሰፈር ማዳከም የቻለው ተራማጆች መከፋፈል በመቻላቸው ብቻ ሳይሆን በኢትዮጵያ ግራ ኃይል ጨቅላነት ተጠቅመው አንዱን በአንዱ ለመምታት ያደረጉት ጥረት ስለተሳካላቸው ነው። ሰፈራችንን ያስጠቃው ለከፋፋዮች ሴራ ድርጅታችንን ሰጥተን በመገኘታችን ነው። ከዚህ ሁኔታ ሊያወጣን የሚችለው በመሀከላችን መከፋፈልን አጥፍተን ለፀረ ሕዝቦች መግቢያ ቀዳዳ ስንነሳ ብቻ ነው።

“መከፋፈል ይብቃ” ስንል ካሁን ወዲያ ሁሉ እንደ መኢሶን ያስብ፣ ሁሉ የኛን መስመር ሙሉ በሙሉ ይከተል ማለታችን አይደለም። ለኢትዮጵያ አብዮትና ብሔራዊ ነፃነት በቆሙ የተሰበጣጠሩ ኃይሎች መካከል ብዙ ልዩነቶች አሉ። ወደፊትም ይኖራሉ። ነገር ግን ከእነዚህ ልዩነቶች ባሻገር የአብዮቱን ሰፈር የሚያያይዙ እጅግ መሰረታዊ የሆኑ ነገሮች አሉ። መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ዴሞክራሲን ይፈልጋል። በመላ ኢትዮጵያ የብሔረሰቦች እኩልነት ይጠይቃል። የሀገራችን ብሔራዊ ነፃነትና ክብር አይደፈር ይላል… በአጭሩ በብሔራዊ ዲሞክራሲያዊ አብዮት ፕሮግራም ላይ የተጠቀሱት አላማዎች ሙሉ በሙሉ ከሥራ ላይ እንዲውሉ ይጠይቃል። በነዚህ አላማዎች የምንስማማ ሃይሎች ሁሉ መሰረታዊ አንድነቶች አሉን። እነሱ ላይ ተመርኩዘን፣ እነሱን ከሥራ ላይ ለማዋል በአንድነት ወደፊት መጓዝ አለብን። ይህ ፕሮግራም ከሥራ ላይ ስለሚውልበት ዘዴ በመሃከላችን ልዩነቶች ሊኖሩ ይችላሉ። ግን እነዚህ በአብዮቱ ወዳጆች መሀከል ያሉ ልዩነቶች ናቸው። እኩልነት፣ አንድነት፣ ብልጽግና፣ ብሔራዊ ክብር እስካልን ድረስ፣ ለእነዚህ አላማዎች በሃቅ እስከቆምን ድረስ የኢትዮጵያ አብዮትና ብሔራዊ ነፃነት ጠላቶች በኛም መሃከል ምንም ልዩነት አያዩም፡ ለፀረ ሕዝብ አላማዎች እንዲያመች ብቻ ቀደም ተከተል ይሰጡታል እንጂ ዞሮ ዞሮ ለማውደም የሚፈልጉት አብዮትና እናት አገር የሚለውን እና ለፀረ ሕዝብ ፖለቲካቸው አላጎበድድም የሚለውን ግንባር ቀደም ኃይል ሁሉ ነው።

መኢሶን ለመላ ኢትዮጵያ ተራማጆች ዛሬ የሚያደርገው ጥሪ ከሁሉ አስቀድመን ይህንን ሀቅ ተገንዝበን ፀረ ሕዝቦች  አንዱን ከሌላው እያጋጩ፣ አንዱን ለመምታት በሌላው እየተጠቀሙ ሁላችንንም ተራ በተራ ለማውደም ለሰነዘሩት ሴራ መሣሪያ ከመሆን እንዲቆጠቡ ነው። ሁለተኛ ደግሞ መኢሶን ለመላው ኢትዮጵያ ተራማጆች የሚያደርገው ጥሪ በመካከላችን ስላሉት መለስተኛ ልዩነቶች እንደሁኔታው አመችነት በይፋ ወይንም በህቡዕ ሃቀኛ ውይይቶችን እንድንጀመርና የትግል አንድነታችንን በተወሰኑ ተጨባጭ የትግል መስኮች ላይ እንደገና መገንባት እንድንጀምር ነው።

1. ከሁሉ መጀመሪያ መኢሶን የሚያቀርበው ጥሪ ለፀረ ሕዝቦች መሳሪያነት ይብቃ! የሚል ጥሪ ነው። ዛሬ የኢትዮጵያ ተራማጆች ይህንን ያህል በገፍ ቢታሰሩ፣ ቢሰቃዩና ቢረሸኑ ለዚህ ሁኔታ ተጠያቂው ደርግ ብቻውን እንዳይደለ ግልጽ ነው። የአድርባይ ድርጅቶች የኢትዮጵያን አብዮት ለፍርፋሪ በመሸጥ፣ ከአባሎቻቸው አንዳንዶቹ ደግሞ በዚህ በተሳሳተ አሳፋሪ አመራር በመወናበድ ብዙ የመኢሶን ጓዶችን ብቻ ሳይሆን ዲሞክራቶችንና አገር ወዳዶችን ለጠላት እያሳለፉ ሰጥተዋል። ይህ እነዚህን ኃይሎች በታሪክ ፊት ሲያስጠይቃቸው የሚኖር አሳፋሪ ተግባር ከጨቅላነት፣ ከጭፍን ጥላቻና ከስግብግብ አድርባይነት ሌላ ምንም ምክንያት የለውም። የመኢሶን አባላት “ማርክሲስት ሌኒኒስት አይደላችሁም” ቢባሉ እንኳን ቢያንስ ቢያንስ በብሔራዊ ዴሞክራሲያዊ አብዮት መድረክ ላይ ፀረ ፊውዳል ፀረ ኢምፔሪያሊስት እና ፀረ ቢሮክራሲያዊ ካፒታሊስት ኃይሎች ናቸው። ስለሆነም የአድርባይ ድርጅቶች መሪዎች ከመኢሶን ጋር ያለው ልዩነት በሁለተኛ ደረጃ የሚታይ በአብዮት ሰፈር ያለ ልዩነት መሆኑን እያወቁ ይህ ቅራኔ በውይይት ሳይሆን በእሥራትና በርሸና እንዲፈታ መወትወታቸው ምን ያህል እንደታወሩና ምን ያህል ለፀረ አብዮት እንዳጎበደዱ የሚያሳይ ተግባር ነው። ውጤቱም የአብዮቱን ሰፈር እያደከመ የፀረ አብዮቱን ሰፈር የሚያጠናክር መሆኑና እነዚህ ድርጅቶች በራሳቸው ውስጥ ለሚገኙ ሀቀኛ ታጋዮችም መቃብር መቆፈር እንደሆነ ዛሬ በአዋጅ በፈረሱት ድርጅቶች ውስጥ ተሰለፈው ይታገሉ የነበሩት ተራማጆች የወደቀባቸው እድል የማያጠራጥር ማስረጃ ነው። አንዳንዱ ተራማጅ አውቆም ሆነ ሳያውቅ የብሔራዊ ዴሞክራሲያዊ አብዮት ፕሮግራም ጠላት አድርጐ ካልወሰዳቸው ኃይሎች አንድ ግለሰብ እንኳን ለፀረ ሕዝቦች ቢጠቁምና አሳልፎ ሲሰጥ ለኢትዮጵያ ተራማጆች ሰፈር መዳከም አሳፋሪ አስተዋጽኦ ማድረጉ፣ ህብረታቸው እንዳይመሰረት ተጨማሪ የጥላቻና የጥርጣሬ ግንብ ለመገንባት ማገዙና ዞሮ ዞሮ ደግሞ ፀረ ሕዝቦችን ለማጠናከር የራሱን መቃብር መቆፈሩ እንደሆነ መገንዘብ ይኖርበታል። በተቃራኒው ደግሞ አንዳንዱ ተራማጅ ሌላ ተራማጅ ላይ ፀረ ሕዝቦች ሊሰነዝሩ ለሚችሉት አመፅ ከመተባበር ሆነ ብሎ ሲቆጠብ የአብዮቱ ሰፈር እንዳይዳከም የሚፈልግበትን አስተዋፅኦ ከማድረጉ በላይ በፀረ ሕዝቦች ሴራ በመፍረክረክ ላይ ያለው የተራማጆች አንድነት መልሶ እንዲያንሰራራ በቅድሚያ ለሚያስፈልገው መተማመን፣ መተሳሰብ እና በጋራ ጠላት ፊት በአንድነት የመቆም ስሜት እንዲያዳብር ማድረጉ ስለሆነ ጓድን ወይንም ጓዲትን ከማዳን እጅግ አልፎ የሚሄድ ወደር የሌለው አስተዋጽኦ አደረገ ማለት ነው።

በዚህ የተነሳ ነው ዛሬ መኢሶን ለተራማጆች ህብረት መሰረት ለመጣል ይህ የመተማመን፣ የመተባበር፣ የወንድማማችነት መንፈስ በመሀከላችን እንዲሰፍን ከሁሉ አስቀድሞ ይህ የጥቆማ መርዝ፣ ይህ በኢትዮጵያ ግራ ጨቅላነት የተነሳ ስፍር ቁጥር የሌላቸው ጓዶች መስዋዕትነት የጠየቀን መርዝ ከማሃከላችን ጨርሶ መነቀል አለበት የሚለው። ለዚህ ነው ለፀረ ሕዝቦች መሳሪያነት ይብቃ! ብሎ የሚያስተጋባው።

ከዚህ ጋር የተያያዘ ሌላም የመላ ኢትዮጵያ ተራማጆች ተግባር መሆን ያለበት ጉዳይ አለ። ዛሬ በደርግ እስር ቤቶች በመሰቃየት ላይ የሚገኙት በሺ የሚቆጠሩት የመኢሶን አባላትም ሆኑ የሌሎች ማርክሲስት ሌኒኒስት ድርጅቶች አባላት፣ እንደዚሁም ስፍር ቁጥር የሌላቸው ዲሞክራቶችና አገር ወዳዶች በሙሉ በብሔራዊ ዴሞክራሲያዊ አብዮት መድረክ ላይ የቆሙ የአብዮቱ ኃይሎች ስለሆኑ ባስቸኳይ እንዲፈቱና አብዮታዊ ትግላቸውን እንዲቀጥሉ ተራማጆች ሁሉ ትግላቸውን ማስተባበር አለባቸው።

  1. በልዩነቶቻችን ላይ እንወያይ!

ይህ ጥሪ “እንደ አጣዳፊ ተግባር” ተብሎ መቅረቡ ራሱ አድሃሪዎች በኢትዮጵያ ተራማጆች መሃከል የነዙት የጥላቻና ያለመተማመን መርዝ ምን ያህል ፍሬ እንደሰጠ የሚያሳይ ነው። የኢትዮጵያ ተራማጆች ጨቅላነትን የሚለካበት መሳሪያ ነው። በተራማጆች ሰፈር በተለይ ከሁለት ዓመት ወዲህ ፀረ ሕዝቦች ሆን ብለው ያስፋፉት ይህ መርዝ በልዩነቶች ላይ እንኳን በጥሞናና በርጋታ መካሄድ ያለበትን ውይይት አፍኖት ይገኛል። ፀረ ሕዝቦች ከውይይት መግባባት፣ ከመግባባት፣ አንድነት፣ ከአንድነት ደግሞ ድል እንደሚገኝ ያውቃሉ። ስለዚህ ይህ ውይይት እንዳይካሄድ ባገኙት ተንኮል ሁሉ ይጠቀማሉ። ዲሞክራሲያዊ መብቶችን አፍነው መያዛቸው አንዱ ምክንያት በዲሞክራሲያዊ ውይይት ከሚደርስባቸው መጋለጥና ለመዳንና በተራማጆች ሰፈርና በሃቀኛ መስመር ላይ የተመረኮዘ አንድነት እንዳይኖር ለማድረግ እንደሆነ ግልጽ ነው። አብዮታዊያን ግን “ዲሞክራሲ የለምና ምን ያደርጋል ውይይት አይቻልም” ብለው ዝም አይሉም። በልዩነቶች ላይ መወያየት ለአብዮቱ ሂደት ምን ያህል ጠቃሚ እንደሆነ በመረዳት ይህ ውይይት እንዲኖር ያለማቋረጥ መታገል አለባቸው።

ነገር ግን ይህንን ውይይት የሚፈሩ የለየላቸው ፀረ ሕዝቦች ብቻ አይደሉም። የአድርባይ ድርጅቶች መሪዎች በዚህም በኩል አሳፋሪ የሆነ ተልኳቸውን ሲያካሂዱ ቆይተዋል። ካለፈው ስህተታቸው ምንም ትምህርት ያልቀሰሙ አንዳንድ የ“ግራ” አድርባዩ ኢህአፓ ቅሪቶች ወጣቱ በሀቀኛ አብዮት መስመር ላይ እንዳይሰለፍ ውይይትን ለማፈን ቀድሞ በመሳሪያ የተሰለፉትን ያህል ዛሬ ደግሞ በወጣቱ ጨቅላነት በመጠቀም፣ የቆየ ጥላቻና መጠራጠር እንዳይጠፋ ለማድረግ እየሞከሩ ናቸው። ቀደም ሲልም ቢሆን የኢህአፓ መሪዎች ሀቀኛ ተከታያቸው ነገሩ ገብቶት ወደ አብዮቱ ሰፈር እንዳይደባለቅባቸው ሲሉ ውይይትን ለማፈን “አታንብቡ አትመራመሩ” ብቻ ሳይሆን “ከፊዲስቶች” ጋር አትወያዩ እነሱ አይቻሉም ያወናብዷችኋል” ይሉ እንደነበር አንረሳውም። ዛሬም ቢሆን የቀኝ ኃይሎች ህብረትና አድሃሪ ቱልቱላዎቹ “ከመኢሶን ጋር ያለን ልዩነት በውይይት ሊፈታ የሚችል አይደለም” ብለው ሲዘባርቁ የሚያሳዩት ቀድሞ ኢህአፓ ያሳየው የነበረውን የአብዮታዊ ምስመር ፍራቻ ብቻ ሳይሆን ዲሞክራሲን አፍነው በደረቅና አሰልቺ ቅስቀሳቸው ሕዝቡን አደንቁረው በጠመንጃ አፈሙዝ ለዘላለም ለመግዛት ያላቸውን ምኞትም ነው። ይህ ፖለቲካቸው በኢትዮጵያ ተራማጆች መካካል ስላሉት ልዩነቶች ከ“ከግራ” አድርባዮች ጋር የተደረገውን ያህል እንኳን ምንም አይነት የረባ ውይይት እንዳይካሄድ አድርጓል። በዚህም የተነሣ የአብዮቱ ሰፈር አባል የሆኑት ኃይሎች ተራ በተራ እንዲመቱና እንዲዳከሙ ተደርጓል።

ከዚህ አሳዛኝ ሁኔታ ለመውጣት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ዲሞክራሲያዊ አብዮት በተሰለፉ ኃይሎች መካከል ካመቸ በይፋ፣ ካላመቸ ደግሞ በህቡዕ ውይይት ያስፈልጋል ስንል የውይይት ነጥቦች ምን ምን መሆን አለባቸው?

የመጀመሪያው የውይይት ነጥብ ዛሬ ለፀረ ሕዝቦች አመፅ ተጋልጠው በየእስር ቤቱ የሚማቀቁት የመኢሶን፣ የኢጭአት፣ የወዝአደር ሊግ፣ የአብዮታዊ ሰደድ፣ የማሌሪድ አባላት፣ ሌሎች ዲሞክራቶችና አገር ወዳዶች፣ እንዲሁም በኢሕአፓ ውስጥ አብዮታዊ መስመር ይከተሉ የነበሩ የጀብደኛ አመራራቸውን ውድቀትና የቀልባሽ መስመራቸውን ኪሳራነት በእርግጥ የተረዱ ተወናብደው የነበሩ ሀቀኞች ጭምር-እንደ አብዮቱ ጠላቶች የሚቆጠሩ ኃይሎች ናቸው ወይስ አይደሉም የሚለው ጥያቄ ነው። መኢሶን እነዚህ ጓዶች የአብዮት ጠላት አይደሉም እንዲያውም ዛሬ በፀረ ሕዝብ ኃይሎች እጅ ግፍና መከራ በመቀበል ላይ ያሉት በሃቅ ለብሔራዊ ዲሞክራሲያዊ አብዮት የቆሙና ሊቆሙ የሚችሉ ወገኖች በመሆናቸው ነው ይላል።

እንኳን የሌላ ድርጅት አባላትን፣ እንኳን ያልተደራጁ ዲሞክራትና አገር ወዳድ ግለሰቦችን ቀርቶ በአንድ ድርጅታዊ መዋቅር ተሳስረው አብረዋቸው የተዋደቁትን ጓደኞቻቸውን የከዱና ለጠላት አጋልጠው የሰጡ አንዳንድ አድርባይ “መሪዎች” በርግጥ ለዚህ መልሳቸው ይኽ ሁሉ በሺ የሚቆጠር ታጋይ አብዮቱን ከድቷል፣ ታጋይ የኢትዮጵያ ልጆች እኛ አተላዎቹ ብቻ ነን! እንደሚሆን ግልጽ ነው። ከዚህም “አስተሳሰብ” ተነስተው በጠቅላላ በኢትዮጵያ ተራማጆች ላይ (ድርጅቶቻቸውም ውስጥ ባሉ ሀቀኞች ጭምር) እሥራቱ፣ ጭፍጨፋው፣ ርሸናው እንዲቀጥል እንደሚገፋፉ የታውቀ ነው። በዚህ ነጥብ ላይ እርስ በእርሱም ይወያይ፣ ራሱን ይጠይቅ፣ ከሌሎች አብዮታዊያንም ጋር ሀሳብ ይለዋወጥ የምንለው በድርጅቶች ውስጥ ያለውን ሀቀኛ አብዮታዊና ገና ያልተደራጀውን ማርክሲስት፣ ዲሞክራትና አገር ወዳዱን ነው። ከማንኛውም የንኡስ ከበርቴ እልህ፣ ከማንኛውም የቡድን ስሜት በራቀ መንፈስ፣ ከሁሉም በላይ ለኢትዮጵያ አብዮትና ለብሔራዊ ነፃነቷ በሚቆረቆር መንፈስ የሚካሄድ ውይይት መኢሶን ከሁለት ዓመት ጀምሮ የሚጠቁመውን ዛሬ በተጨባጭ በሀገሪቱ የፖለቲካ መድረክ ላይ የተመሰከረውን ሀቅ አጎልቶ ያሳያል። ይህ ሃቅ ሌላ ምንም ነገር ሳይሆን በብሔራዊ ዲሞክራሲያዊ አብዮት መድረክ ላይ ቆመው በሚታገሉ ኃይሎች መካከል ያሉት ልዩነቶች በሁለተኛ ደረጃ የሚታዩ ልዩነቶች ናቸው የሚለው ሀቅ ነው። ከዚህች መሰረታዊ ሀቅ ላይ መድረስ ሲቻል ለመላ ኢትዮጵያ ተራማጆች አንድ ትልቅ የትግል አንድነት መድረክ ተከፈተ ለማለት ይቻላል። ልዩነቶች በውይይት እንዲፈቱ፣ መጠቆም፣ ማሳደድ፣ ማሰር፣ መረሸን፣ እንዲቆም የኢትዮጵያ ተራማጆች በሙሉ በአንድነት የሚታገሉበትን የአብዮቱ ባለቤት የሆነውን ሰፊ ሕዝብ በአንድ ቋንቋ የሚቀሰቅሱበትና የሚታገሉበት የጋራ መድረክ አገኙ ማለት ነው። ለአዲሱ የቀኝ ኃይሎች ህብረትና ለጠቅላላው የፀረ አብዮት ኃይሎች “የከፋፍለህ ግዛ” ሴራ አንድ ማርከሻ ተገኘ ማለት ነው።

ሌላ የውይይት ነጥብ ዛሬም እንደ ዛሬ አመቱ የዲሞክራሲ መብቶች ጥያቄ ለኢትዮጵያ አብዮት እንገብጋቤ ጥያቄ ነው ወይ? የሚለው ነጥብ ነው። እዚህም ላይ የመኢሶንና የተቀሩት ሀቀኛ አብዮታዊያን መልስ ግልጽ ነው። እንዲያውም ባለፉት ሁለት አመታት በአብዮታችን ላይ ለደረሰው ውድቀት ሁሉ ለሕዝባዊ ድርጅቶች መፈራረስም ሆነ ለቢሮክራሲው መንገስ፣ ለተራማጆች ህብረትም ምንሽርሽሩ መውጣትም ሆነ ለእያንዳንዱ አብዮታዊ ድርጅት መዳከም፣ ለብሔረሰቦች የዕኩልነት መብት መረገጥ ሆነ ለኢትዮጵያ ሕዝቦች ዲሞክራሲያዊ አንድነት ከፍተኛ አደጋ ላይ መውደቅ፣ የአብዮታችን እድል በውጭ ሃይሎች ቁጥጥር ስር መውደቅም ሆነ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ነፃነት

መደፈር፣ ለዚህ ሁሉ አንዱ ምክንያት ይህ አንገብጋቢ ጥያቄ በወቅቱ ተገቢ መልሱን አለማግኘቱ ነው እንላለን። በየድርጅቶቹ ቁንጮ ላይ ፊጥ ብለው በነበሩ አድርባዮች የተነሳ ተወናብዶ “በቂ ዴሞክራሲ አለ” ሲል የነበረው ሀቀኛ ዛሬስ በሀገራችን የንገሠውን ፀረ ዴሞክራሲ ሲመለከት፣ በየድርጅቱ ውስጥም ሆነ ከዚያ ውጪ ባለው ሃቀኛ ዴሞክራትና ሃገር ወዳድ ላይ የሚደርሰው ግፍ በራሱ ላይ ሲሰማው ከተጨባጩ ሁኔታ የቀሰመው ትምህርት ምንድነው? እጅ ለእጅ ተያይዞ ለዴሞክራሲያዊ መብቶች መታገል፣ ለዚህም ዓላማ የአብዮቱ ባለቤት የሆነውን ሰፊ ሕዝብ በይፋም ሆነ በህቡዕ ማታገል ያስፈልጋል ወይስ አስፈልግም? ይህም አንድ ሌላ እና ከፍተኛ የውይይት ነጥብ ነው።

ሦስተኛ፣ መላ የኢትዮጵያ ተረማጆች ሊወያዩበት የሚገባው ነጥብ የብሔራዊ ነፃነታችንንና የሀገራችንን ክብር የሚመለከት ነጥብ ነው። ከሰፊው ሕዝብ እየራቀና እሱን እየተቃረነ የተጠናከረው የቀኝ ኃይሎች ህብረት በሰፊው ሕዝብ ላይ መተማመን በመፍራቱ፣ እምነቱን በውጭ ኃይሎች ላይ መጣሉና በቀኝ ኃይሎችም ህብረት ግብዣ በሺ የሚቆጠሩ የባእድ ወታደሮች ሃገራችን መጥተው መስፈራቸው አብዮታችንን አራምዶታል? ወይስ ወደኃላ ጎትቶታል? ለኢትዮጵያችንስ በአፍሪካ ሆነ በሌሎች የአለም ሕዝቦች ፊት የነበራትን ዝናና ስም ጨምሮላታል ወይስ ሰሟንና ታሪኳን አጉድፎባታል? ራሷን የቻለች ኩሩ አገር አድርጓታል ወይስ የባእድ ኃይሎች ተቀጢላ ሆናለች? መኢሶንና ሌሎች የኢትዮጵያ አብዮታዊያንና አገር ወዳዶች የቀኝ ኃይሎች ህብረት በውጭ ኃይሎች ተማምኖና በነሱ ድጋፍ ተጠናክሮ አብዮታችንን አሁን የሚገኝበት አስቸጋሪ ሁኔታ ላይ ጥሎታል፣ የውድ እናት ሃገራችንንም ክብር አዋርዶታል ይላሉ። በአድርባይ የድርጅት መሪዎች አሉባልታ ተወናብዶና በጊዜው በኢትዮጵያ አብዮትና በሀገራችንና ሕልውና ላይ አፍጥጠው በነበሩት ከባድ ፈተናዎች ተማርኮ የመኢሶንን “ራስን በራስ መቻል” “እርዳታን በሁለተኛ ደረጃ መመልከት” “ለብሔራዊ ነፃነት ቀናተኛ መሆን” “እምነትን በ28 ሚሊዮን የኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ መጣል” የሚሉ መፈክሮች መረዳት አቅቶት የነበረው ሀቀኛ ታጋይ ዛሬ በሀገራችን ከሚያየውና ከሚሰማው ሁሉ ምን ተጨባጭ ትምህርት አግኝቷል? ዛሬ ካለንበት ማጥ ውስጥ ለመውጣት በእነዚህ መፈክሮች ስር ተሰልፎ ለአብዮታችንና ለእናት ሀገራችን ክብር የኢትዮጵያ ተራማጀችና አገር ወዳጆች ሁሉ እጅ ለእጅ ተያይዘን ማንኛውንም የውጭ ተፅዕኖ መቋቋም አለብን። ሰፊውንና በሀገር ፍቅር ስሜቱ ዓለም ያደነቀውን የኢትዮጵያ ሕዝብ ትግሉን እንዲያፋፍም መቀስቀስ አለብን ወይስ የለብንም? ይህም ሌላ የውይይት ነጥብ ነው።

አራተኛው የውይይት ነጥብ ሀቀኛውን የተራማጆች ህብረት የሚመለከት ነጥብ ነው። ለሃቅኛ የተራማጆች ህብረት ዋናው እንቅፋት የአድሃሪዎችና የየሰርጎገቦቻቸው የመከፋፈል ሴራ፣ የአብዮታዊ ሰደድም ሆነ የሌሎች አድርባይ ድርጅቶች መሪዎች የስልጣን ጥም መሆኑ እየታወቀ ይህ ችግር መኢሶን “አብጦ ራሱ ወደፓርቲ ለመለወጥ ፍላጎት” ሲለጠፍ ቆይቶ ነበር። ዛሬ ይህ ሁሉ በደልና ግፍ ደርሶበት አሁንም ለሀቀኛ ተራማጆች የህብረት ጥሪ የሚያደርገው ማን ነው? ሲያሻቸው ድርጅቶችን እንዳለ በ“አዋጅ” ከተራማጆች ህብረት የሚሠረዙት ሲያሻቸው በሌሎች ድርጅቶች ውስጥ ገብተው “ሹምሽር” የሚያካሄዱት፣ ዞሮ ዞሮ ደግሞ አብጠውና ከአድሃሪው ቢሮክራሲ ተዋህደው ራሳቸውን ወደ “ወዛደር ፓርቲነት” ለመለወጥ ደርዳር የሚሉት የኢትዮጵያ አብዮታዊያን ሃቀኛ ሕብረት እንቅፋት እነማን ናቸው? የአብዮታዊ ሰደድ መሪዎች ወይስ መኢሶን? መኢሶን አሁንም ራሱን ብቻውን ወደ ፓርቲ የመለወጥ ሀሳብ የለውም፣ አሀንም ሀቀኛ ከሆኑ ማርክሲስት ሌኒኒስቶች ጋር ለመወያየት የአብዮቱን ሰፈር ከመበታተን ይልቅ ለመሰብሰብ ይታገላል። የኢትዮጵያን አብዮታዊያን አንድነት የሚሻው ሀቀኛ ታጋይ ባለፈው አንድ ዓመት ተኩል ካየውና ከቀሰመው ተጨባጭ ትምህርት ተነስቶ የሚከተለው የትግል አቅጣጫ ምንድነው? እንደኛ ለጠንካራና ለዲሞክራሲያዊ አንድነት፣ እንደኛ ለሀቀኛ ዴሞክራሲያዊ ውይይት ይታገላል ወይስ አይታገልም? ከአድሃሪው ቢሮክራሲና ንዑስ ከበርቴው ተጠራርተው በኢትዮጵያ ሕዝብ ትከሻ ላይ ጸረ ወዝአደር የሆነ የዚያድ ባሬው ዓይነት “የወዛደር ፓርቲ” ሲጭኑ ዝም ብሎ ይመለከታል ወይንስ ከሀቀኛ ማርክሲስት ሌኒኒስቶች ጋር ተባብሮ በወዛደሩ፣ በአርሶአደሩ፣ በመለዩ ለባሹና በአብዮታዊው ምሁር አካባቢ ባመቸው መንገድ ሁሉ የሃቀኛውን የወዛደር ፓርቲ መሰረት ለመጣል በትጋትና በቆራጥነት፣ በዲሲፕሊንና በትዕግስት ይሠራል? ይህም አንድ የውይይት ነጥብ ነው።

በዚህ መልክ ብዙ የውይይት ነጥቦች እንደ መንደርደሪያ ሆኖ ሊቀርቡ ይችላሉ። ዋናው ነጥብ አሁን እነዚህን ዘርዝሮ መጨረሱ ላይ አይደለም። ዋናው ነጥብ የኢትዮጵያ ተራማጆች ካለፉት ስህተቶቻቸው አስፈላጊውን ትምህርት ተምረው ከጨቅላነት በሽታ ተላቀው ለፀረ ሕዝቦች መሳሪያነታቸውን ዛሬውኑ ማቆማቸውና በልዩነታቸው ላይ በጥሞና ለመወያየት መወሰናቸው ነው። ይህ እርምጃ ከተወሰደ ከእነዚህ የመንደርደሪያ ነጥቦች ሌሎች ለኢትዮጵያ አብዮት መሰረታዊ የሆኑ ጥያቄዎች ይኖራሉ። በየጊዜው ደግሞ ከተለዋዋጩ ሁኔታ ጋር አብረው የሚፈልቁ የመወያያ ነጥቦች ይኖራሉ።

ውይይቱ እንዴት ይካሄድ? ፀረ ሕዝብ ኃይሎች ይህ ውይይት እና የሚያስከትለው መግባባት እንዳይኖር ዲሞክራሲያዊ መብቶችን አፍነው ይዘዋል። በአብዮቱ አንገብጋቢ ጥያቄዎች ላይ ለየት ያለ አቋም ያለውን ሁሉ “ቀኝ መንገደኛ” “የቀኝ ክንፍ” “የመኢሶን ሰርጎገብ” እያሉ ያሥራሉ፣ ይረሽናሉ። ከዚህም በረቀቀ ዘዴ በተራማጆች መካከል ሊኖረው የሚገባው መተማመን እንዳይኖር፣ ጥላቻ፣ ጥርጣሬ እና መከፋፈል እንዲነግስ ሌት ተቀን ይሰራሉ። እዚህኛው ወጥመዳቸው ውስጥ ካልወደቅን የዲሞክራሲያዊ መብቶች መታፈን የተራማጆችን መወያያትና መቀራረብ ያጓትቱ እንደሆን እንጂ ጨርሰው አያፍኑም። ስለሆነም የሚተማመኑና የሚተዋወቁ ተራማጆች ዛሬ ነገ ሳይሉ ከላይ በጠቀስናቸውና በሌሎች አንገብጋቢ ብለው በሚቆጥሯቸው አርዕስቶች ላይ በህቡዕና በዲስፕሊን የሚካሄድ ውይይት ይጀምሩ እንላለን። በገበሬ ማህበራት፣ በወዛደሩ አካባቢ፣ በቀበሌዎች፣ በወጣቶች፣ በሴቶች፣ በመለዮ ለባሹ ውስጥ፣ ምሁራን፣ በአገር ወዳዱና ዲሞክራት የጦርና የፖሊስ መኮንኖች አካባቢ በሀቀኛነታቸው፣ በቁም ነገረኛነታቸው፣ በሚስጥረኛነታቸው፣ በሀገር ፍቅራቸው የሚተዋወቁ ኢትዮጵያን ሁሉ በያሉበት አካባቢ እነዚህን የአብዮታችንን እና የሀገራችንን ዕድል የሚመለከቱ ጥያቄዎች እያነሱ በጥንቃቄ መወያየት ይጀመሩ። የመኢሶን አባላት በሙሉ ለዚህ ውይይት ዝግጁ ናቸው።

ከዚህ ከሀቀኞችና በሚተማመኑ ኢትዮጵያን መካከል ከሚካሄድ የመጀመሪያ ደረጃ ውይይት አልፈን ለመሄድ መዘጋጀት አለብን። ይኸውም ድርጅት ለድርጅት መካሄድ ያለበት ውይይት ነው። እርግጥ ከላይ እንዳልነው ዛሬ ቀደም ሲል የነበሩት ተራማጅ ድርጅቶች አመራሮቻቸው በተከተሉት የከሰረ ፖለቲካ የተነሳ መበታተን ላይ ናቸው። የከዳውም ከድቷል። ከሃቀኛ ብዙ እየታፈሰ በየእስር ቤቱ ነው። ቢሆንም ምንም እንኳን አመራሮቻቸው ቢክዱ ቅሉ የእነዚህ ድርጅቶች ሃቀኛ አባላት በቅድሚያ አስፈላጊውን ውይይት በውስጣቸው አካሂደው ኃይላቸውን ሰብስበውና አደራጅተው በአድሃሪው ቢሮክራሲ የተካነባቸውን አመራር ወድያ ትተው ከሃቀኛ አብዮታውያን ጋር ከግለሰብ ውይይት አልፎ በሚሄድ ደረጃ ውይይት ሊከፍቱ ይችላሉ። በዚህ ውስጣዊ ውይይት የሚደርሱባቸውን ሊያቀርቧቸውና ውይይት ሊጋብዙባቸው ይችላሉ። በዚህም ደረጃ ቢሆን መኢሶን ከተራማጆች አካባቢ በሚቀርቡ ትንተናዎች ላይ ተመርኩዞ ሀሳቡን ይገልፃል። ይህ በየድርጅቱ ውስጥ የቀሩት ሀቀኞች በውስጣቸው የሚያካሄዱት ውይይት ከሌሎች ተራማጆች ጋር ከላይ በጠቀስነው መልክ በግለሰብ ደረጃ ከሚካሄደው ውይይት ጋር አይፃረርም። እንዲያውም ተጋግዘውና አብረው ሊሄዱ የሚችሉ ናቸው።

በሌላ ደረጃ ደግሞ በውጭ አገር ያሉ የተራማጅ ድርጅቶች አካሎች የጭቁን ብሄረሰብ እንቅስቃሴዎች አካሎች፣ የተበታተኑ ተራማጆች፣ ዲሞክራቶችና አገር ወዳዶች እንዲሁም የ“ግራ”ና የቀኝ ድርጅቶች ደጋፊዎች የነበሩና ሀቀኛ ወገኖች፣ በተማሪዎች ንቅናቄ አማካኝነትም ሆነ ድርጅቶቻቸው በሚከፍቱላቸው መድረክ ሁሉ ሊያካሂዱት የሚችሉት ጠቃሚ ውይይት አለ። እርግጥ አዲሱ የቀኝ ኃይሎች ህብረት በተለይ የኢትዮጵያ ወጣቶች የትግል ስሜት በአፈሙዝ ኃይል ያንበረከከ ከመሰለው በኋላ በውጭ ያለውንም ወጣትና አብዮታዊ ኃይል ሁሉ በልዩ ልዩ ተጽእኖ ለመበታተንና ለማዳከም እየተሯሯጠ መሆኑን እናውቃለን። ይሁንና በልዩ ልዩ ድርጅቶች ደጋፊዎችም ሆነ በጠቅላላው ለኢትዮጵያ አብዮት፣ ብሔራዊ ነፃነት በቆሙ ኃይሎች መካከል ውይይት ለማካሄድ በአገር ውስጥ ታፈኖ በመታገል ላይ ካለው ኃይል በውጭ አገር የሚገኙት የኢትዮጵያ ተራማጆች የተሻለ እድል አላቸው። ይህ የተለየ ሁኔታቸው በሰጣቸው እድል ተጠቅመው ከማንኛውም ቡድን ስሜት በላይ ለዚች እናት አገራችን ክብርና ነፃነት በመቆርቆር መንፈስ ተነሳስተው፣ የተማሪ ማህበሮቻቸውም ሆኑ ድርጅቶቻቸው በሚከፍቱላቸው መድረክ አማካይነት ነፃና ዲሞክራሲያዊ ውይይት እያካሄዱ፣ ለተራማጆች የትግል አንድነት ምሳሌነት ያለው አስተዋጽኦ ሊያደርጉ ይችላሉ ብለን እንገምታለን። በዚያም ያሉ የመኢሶን አባላትና ድርጅታዊ አካሎች ለእንዲህ አይነቱ አብዮታዊ ተልዕኮ ዝግጁ መሆን አለባቸው። ናቸውም።

ውድ ጓዶችና ጓዲቶች፣ ወንድሞችና እህቶች!

ለኢትዮጵያ ተራማጆች ህብረት ጥሪ ሲደረግ ከዚህ “ለጠላት መሣሪያነት ይብቃ” “ተራማጆች እንወያይ” ከሚል ጥሪ አልፈን ለመሄድ ብንችል ኖሮ ምንኛ ደስ ባለን ነበር! ነገር ግን ዛሬ ቀደም ሲል የነበሩት ተራማጅ ድርጅቶች ሁሉ ያሉበት የመፈራረስ ደረጃ፣ በተራማጆች መካከል አድሃሪዎች የነዙት የጥርጣሬና ያለመተማመን ሁኔታ ሲታይ ዛሬ ጥሪያችን ከእነዚህ “የመጀመሪያ ደረጃ” ጥሪዎች አልፎ ሊሄድ ይችላል ወይ?? ዛሬ ባለንበት ሁኔታ በነዚህ ሁለት ዝቅተኛ ነጥቦች ላይ አስቀድመን ሳንስማማ፣ እነዚህን በሃቅ ከሥራ ላይ ለማዋል ሳንታገል፣ “ተራማጆች እንዲህ እንሥራ፣ እንዲያ እናድርግ” እያልን ከፍተኛ መተማመንን ድርጅታዊ ቅንብርን የሚጠይቁ የጋራ ተግባሮችን እንዘርዝር ብንል ሆድ ሲያውቅ ዶሮ ማታ አይሆንም ወይ?? ራስን ማታለል አይሆንም ወይ?? እኛ ይሆናል እንላለን። ስለዚህ ነው ይህ “እንደገና ለተራማጆች አንድነት ጥሪ” ብለን የሰነዘርነው ጥሪያችን ከነዚህ ሁለት መሰረታዊ ነገሮች

አልፎ ሌላ “ተግባር” ውስጥ ዝርዝር መግባት ያልታየን። አሁን ካለንበት ደረጃ ተነስተን እስኪ ለጠላት መሳሪያነት ይቁም፣ እስቲ በአብዮት ጥያቄዎች ላይ ሁኔታው እንደሚፈቅደው በየደረጃ ውይይት ይጀመር! ይህ ከሆነ በኋላ መኢሶን አስፈላጊ ሆኖ ሲያገኘው ከዚህ አልፎ የሚሄድ ሌላ መርሃ ግብር፣ ሌላ የድርጊት ፕሮግራም ያቀርባል። እንደሁኔታው፣ እንደተራማጆች አንድነት ስር መስደድ ታይቶ ይህ የጋራ መርሃ ግብር ወይም የድርጊት ፕሮግራም እርግጥ መኢሶን ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያ ተራማጆች ተወያይተው የሚሰነዝሩት መርሃ ግብር ሊሆን የማይችልበት ምንም ምክንያት የለም!

ለማጠቃለል፣ ከላይ በሰፊው እንዳብራራነው ዛሬ በአገራችን ምንም ያህል ግፍ እና ጭፍጨፋ በተራማጆች ላይ ቢወርድም ቅሉ ተጨባጩ ሁኔታ የአብዮታውያንን አቋም ትክክለኝነት ከዕለት ዕለት እያጎላ እያሳየ፣ የቀኝ ኃይሎች ሕብረት ኪሳራና ክህደት ደግሞ እንደዚሁ እያጋለጠ የሚሄድ አመቺ የፖለቲካ ሁኔታ አለ። በዚህ አንጻር አዲሱ የቀኝ ኃይሎች ህብረትና የበላይ አዛዦች የኢትዮጵያ አብዮትም ሆነ ብሔራዊ ክብር ለሚያቀርቧቸው አንገብጋቢ ጥያቄዎች ለአንዳቸውም ተገቢ መልስ ሊሰጡ ስለማይችሉ ከኪሳራ ኪሳራ፣ ከመጋለጥ መጋለጥ እንጂ ካሁኑ የተሻለ እድል እንደማይገጥማቸው ሳይታለም የተፈታ ጉዳይ ነው። በዚህ ልክ ደግሞ ማንኛውንም መሰዋእትነት እየከፈሉ በሀቅ ለአብዮትና ለእናት ሀገር ክብር ለቆሙ ኃይሎች ጊዜው ይበልጥ እያመቸ የሄዳል።

ቢሆንም ኪሳራቸውን ለመሸፈን የተራማጁን ሰፈር ለማድከም ፀረ ሕዝቦች በአብዮታዊያን ላይ ያወረዱት በታሪካችን ምንም አይነት ተወዳዳሪ የሌለው ግፍ የተነሳ ከዚህ በፖለቲካው አንፃር እጅግ አመችነት ጋር የሚነፃፀር ድርጅታዊ ጥንካሬም ሆነ የተራማጆች አንድነት አለ ለማለት አይቻልም። ግን ይህ ዘላቂነት የለውም። በተለያዩ አድርባይ አመራሮች ክስረት የተነሳ እርግጥ ዛሬ ብዙ ሀቀኞች ተስፋ በመቁረጥ፣ በመበታተን፣ ተደራጅተው መታገልን እርም ብለው በመተው ላይ ይገኛሉ። ሳይወድቅ ሳይነሳ፣ ተስፋ መቁረጥና እንደገና ማንሠራራት ሳይዘበራረቁበት የመጨረሻውን ግቡን የመታ አብዮት በየትም አገር ታሪክ ታይቶ አይታወቅም። ይህ ሁኔታ ለእኛ አዲስ ቢመስለንም በብዙ አብዮቶች ታሪክ ተደጋግሞ የታየ ሁኔታ ነው። ስለሆነም ዛሬ አድርባይ መሪዎቻቸው በተከተሉት የከሰረ ፖለቲካ መስመር የተነሳ ሕዝቡ የተፋቸው ግን ደግሞ በሀቀኝነታቸው የተነሣ በአድሃሪው ቢሮክራሲ ሙሉ ቁጥጥር ስር የወደቀው የቀኝ ኃይሎች ህብረት የሚያሳድዳቸው ስፍር ቁጥር የሌላቸው ግራ የተጋቡ ጓዶቻችን አሉ። እነዚህ ወገኖቻችን አንድ ነገር ማወቅ ይኖርባቸዋል። ለፍርፋሪ ተሸጠው ሰፊውን የኢትዮጵያ ሕዝብ የከዱት አድርባይ መሪዎቻቸው ለተከተሉት ፖለቲካ ዘለአለማቸውን ሲሳቀቁ መኖር የለባቸውም። በሃቅ ለሰፊ ሕዝብ የቆሙ ከሆኑ ለኢትዮጵያ አብዮትና ብሔራዊ ክብር የሚደረገው ትግል ገና ከፊታችን ነው። ያለፈውን ሁኔታ በጥሞና መርምረው ከተፈፀሙ ስህተቶች አስፈላጊውን ትምህርት ቀስመው ወደፊት ለመራመድ ከተነሱ አሁን የተያዘውን ተስፋ መቁረጥና መበታተን ተወጥተው ለመጪው ትግል የሚፈለግባቸውን አስተዋጽኦ ሊያደርጉ ይችላሉ። ማድረግም አለባቸው። በዚህ ጥረታቸውም የመላ ኢትዮጵያ ሶሻሊስት ንቅናቄ ምንጊዜም እንዳደረገው ሁሉ ዛሬም ነገም ከጎናቸው ተሰልፎ ለኢትዮጵያ ተራማጆች የትግል አንድነት፣ ለአብዮታችን ድልና ለእናት አገራችን ክብር እየተሰዋ ወደፊት ለመራመድ ዝግጁ መሆኑን ያረጋግጠላቸዋል።

ተስፋ መቁረጥና መበታተን ይብቃ!
የኢትዮጵያ ተራማጆች ሁሉ በአንድነት ወደፊት እንግፋ!
የነቃ፣ የተደረጀ፣ የታጠቀ ሕዝብ ትግል ያሸንፋል!
Scroll to Top