የሰፊው ሕዝብ ድምፅ
ልዩ እትም፣ መስከረም 16፣ 1968 ዓ.ም.
የፅሁፉ ፍሬ ሀሳብ
በ1968 መጀመሪያ ወራት ኢሠአማ (የኢትዮጵያ ሠራተኞች አንድነት ማኅበር) ከመስከረም 8 – 12 ባደረገው ጉባኤው የዴሞክራሲያዊ መብቶችን ጥያቄ አቀረበ። መልስ ካላገኘ ሠራተኛው የሥራ ማቆም አድማ እንደሚደረግ አስታወቀ። መስከረም 14 ቀን ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ሠራተኞች ጋር በነበረ ግርግር የደርጉ የጸጥታ ኃይሎች 7 ሠራተኞች ገደሉ። 30 ያህል አቆሰሉ። በዚህ ልዩ እትም፣ መኢሶን የደርግን እርምጃዎች አውግዞ የለውጡ ምሰሶ የሆነው ወዛደርና ሰፊው ሕዝብ በአንድነት እንዲታገሉ ያሳስባል። እንዲሁም ተራማጆች ልዩነቶቻቸውን አስወግደው በአንድነት መታገል እንዳለባቸውና መኢሶንም የትግሉ ተባባሪ እንደሚሆን ይገልጻል።
ለኢትዮጵያ ሕዝብ ሰብዓዊ መብቶችና ለአብዮቱም መግፋት ዋስትና የሚሰጡ ጥያቄዎችን የሚጠይቅ አብዮታዊ ውሳኔ የመላ ኢትዮጵያ ወዝአደር ወኪሎች ባደረጉት ጉባኤ አሳልፈው ነበር። ይህ ጽሑፍ በእርግጥ ፀረ-ደርግ ነበር። ነገር ግን በምንም አይነት ፀረ አብዮት አልነበረም።
ዛሬ ‘አብዮቱን ለማደናቀፍ’ የሚጥረው የኢትዮጵያ ወዛደር አይደለም። የአብዮቱ ባለቤት ማን ሆነና! የአብዮቱ ምሰሶ ማን ሆነና ነው የኢትዮጵያን ወዛደሮች ውሳኔ ‘አብዮቱን የሚያደናቅፍ’ የሚባለው? ይኸ መቼስ እነኃይለሥላሴ ትላንት ሰፊውን የኢትዮጵያ ሕዝብ እስከ አጥንቱ እየሰረሰሩ ሲግጡት ‘ካንተ ይበልጥ እናስብልሃለን’ ይሉት እንደነበረው ነው፣ ከእናት ትሻል ሞግዚት እንደሚሉት ተረት ነው። አድሃሪዎች ከወዛደሩ ይልቅ ለአብዮቱ ተቆርቋሪዎች ሊሆኑ! ከወዛደሩ ይልቅ ለአብዮቱ መደናቀፍ ሊጨነቁ! በመደብ ትግል ይሉኝታ የለምና ገና ብዙ እንሰማለን።
ለአብዮቱ እቆረቆራለሁ የሚለው ደርግ የትናንት በስቲያውን ዓይነት ፀረ ወዛደር ድርጊት መሥራት ከጀመረ ውሎ አድሯል። አምና ሰርተን እንብላ በማለት ሥራና እንጀራ ለመጠየቅ በሰላም በተነሳሱ ሥራ አጥ ኢትዮጵያዊያን ላይ ‘እንጀራ ለጠየቀ ጥይት’ በሚባለው የአድሃዎች መፈክር ሥራአጦችን እንደረሸነ ማን ይረሳል? ያኔ የተሰጠው ሐሰተኛ ምክንያት ‘ፀጥታ ነሱ ……በፀጥታ ጠባቂዎች ላይ ድንጋይ ወረወሩ’ ነበር። አሁን ደግሞ የአየር መንገድ ሠራተኞችን በጥይት ሲቆላ ‘ፀጥታ አወኩ፣…. ሽጉጥ ተኮሱ…’ የሚል ተልካሻ ቅጥፈቱን በፕሮፓጋንዳ መሳሪያዎቹ ነፋ። ኧረ ለመሆኑ የልመና መሳሪያና ጥይት የግድ የኢትዮጵያን ሕዝብ መጨፍጨፍ አለበት? ደግሞስ የኃይለሥላሴ ፀረ ሕዝብ መንግሥት በወታደራዊ ፀረ ሕዝብ መንግሥት የግድ መተካት አለበት?
የለም የለበትም። የኢትዮጵያ ወዛደርና ጠቅላላው ሰፊ ሕዝብ ማናቸውንም ፀረ ሕዝብ መንግሥት አይፈልግም። የዛሬው ደርግ ትላንት ኃይለሥላሴ ባላሳየው ድፍረት ኢሰአማን ለማፍረስና ለመዝጋት ሞክሯል፣ የወዛደሩን መሪዎች እረሽናለሁ እያለ በግልጽ እና በስውር ተንኮሎች ኢሰአማንና በጠቅላላው የኢትዮጵያን ወዝአደሮች ትግል ለማኮላሸት ታጥቆ ተነስቷል። በአፉ ያለውን ቢል በተግባር የሰፊው ሕዝብ ትግል ግቡን እንዳይመታ ለማደናቀፍ ቆርጦ መነሳቱን አስመስክሯል። ስለዚህ ለመብቱ ሲል፣ ለጥቅሙ ሲል፣ ለአብዮቱ ሲል ወዛደሩና ጠቅላላው ሰፊ ሕዝብ ይህንን ፀረ ሕዝብ መንግሥት ይቋቋሟል፣ ይታገለዋል።
የኢትዮጵያ ወዛደር አብዮቱ ተስፋ፡ የኢትዮጵያችን ግስጋሴና ብልጽግና ምሰሶ እሱው መሆኑን ተገንዝቦ የነፃነቱን ተጋድሎ ያህል ቁምነገር በአፍ ወዳጆቹ፣ በጥቂት ፀረሕዝብ አፈጻድቆች ትከሻ ላይ ጥሎ እንደማይተኛ በተደጋገመ ትግሉ አስመስክሯል። እያስመሰከረም ነው። በእርግጥ ፀረአብዮት ኃይሎች በሙሉ ከሀገራችን ገጽ ድምጥማጣቸው ጠፍቶ አዲሲቱ ሕዝባዊት ኢትዮጵያ እስከምትመሰረትበት ጊዜ ድረስ የተጋድሎ እየተፋፈመ ይሄዳል እንጂ በምንም አይነት አይገታም።
ይህንን ለመግታት በወዛደሩ ወኪሎች፣ በአስተማሪዎች፣ በገበሬዎች፣ በተማሪዎች ላይ የሚዘንበውን ፀረ ሕዝብ አመፅ ለመቋቋም የኢትዮጵያ ተራማጆች ወዳጅን ከጠላት በለየ በትክክለኛ ፖለቲካ ተመስርተው አንድነታቸውን ለማጠናከር በትጋት መሥራት አለባቸው። የአድሃሪዎችን ሴራ ሊገታና ሊበትን የሚችለው ተራማጆች ጥቃቅን ልዩነቶቻቸውን አስወግደው በአንድነት ሲታገሉ ነውና?
በነዚህ ከትናንት በስትያ በተገደሉት ወገኖቻችን ጉዳይ ጠቅላላው ተራማጅ ወገን ሙሉ ተቃውሞውን በገቢር እንዲገልጽ እየጠየቀ ለሚወሰደው እርምጃ ሁሉ ‘የሰፊው ሕዝብ ድምጽ’ ተባባሪ እንደሚሆን ይገልፃል።
ፋሽስታዊ ግፍ አብዮቱን አይገታም!
[የማይነበብ– አዘጋጆቹ]