የሰፊው ሕዝብ ድምፅ
ልዩ እትም፣ ሚያዝያ 23፣ 1969
የፅሁፉ ፍሬ ሀሳብ
በዚህ እትም መኢሶን የአብዮቱ ኃይሎቸ ወደ ኋላ ዞር ብለው የት ደርሰናል ብለው ብርቱ ወገናቸውንና ድካማቸውን መመርመር የወደፊት ትግላቸው ለመቀየስ የማይታለፍ ተግባር እንደሆነ አብክሮ ያስገነዝባል። በዚህ ረገድ ወዛደሩ አምና በቀኝ ክንፍ ንዑስ ከበርቴው ወኪል በኢህአፓ ተወናብደው እንደነበረ፣ ከዚያም በሃቀኛ አብዮታዊያንና በአውናባጆች መካከል በተደረገው ትግል የኢትዮጵያ ወዛደሮች በአሸናፊነት መውጣታቸውን ያበስራል። ነገር ግን አሁንም የወዛደሩ ድል የሚሰምረው በማርክሲዝም ሌኒኒዝም የታነጸ የራሱ የሆነ ግንባር ቀደም ፓርቲ ሲኖረውና አለማቀፋዊውን የወዛደሩን ርዕዮተ አለም ከኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ጋር ማገናዙብ ሲችል ብቻ መሆኑን አጥብቆ ያሳስባል።መኢሶንም ለወዛደሩ ፓርቲ መፈጠር፣ ለሕዝባዊ አብዮታዊ ግንባር ፣ ለብሄራዊ ነጻነት፣ለሶሺያሊዝምና ለአለም አቀፋዊነት እስከ መጨረሻ እንደሚታግል ቃል ይገባል።
አንድን አብዮታዊ እንቅስቃሴ የሚመራ ወይንም ለመምራት የሚታገል አብዮታዊ ድርጅት ወይንም አብዮታዊ መደብ በየጊዜው ወደ ኋላ ዞር ብሎ እንቅስቃሴው ያለፈበትን ጉዳና ካላስተዋለ፣ ካለፉት ጥሩ ውጤቶቹ፣ ከስህተቶቹ ወይንም ከጉድለቶቹ ተገቢውን ትምህርት ካልቀሰመ፣ ዛሬ የደረሰበትን ደረጃ በትክክል ለማወቅና የወደፊቱንም ጎዳና በቆራጥነትና በራሱ በመተማመን ለመቀየስ አይችልም። የኢትዮጵያን ብሄራዊ ዴሞክራሲያዊ አብዮት መርቶ ከግቡ የማድረስና ከዚያም የራሱን አምባገነንነት የመመስረት ታሪካዊ ኃላፊነት ያለበት የኢትዮጵያ ወዛደር መደብ ባለፈው ዓመት በዚህን ጊዜ ከምን ሁኔታ ላይ ነበር? ዛሬን ከምን ደረጃ ላይ ደርሷል? ወደፊት የሚጠብቀውስ ተግባር ምንድነው?
ባለፈው ዓመት የወዛደር ቀን በተከበረበት ሰሞን ይበልጡ የኢትዮጵያ ወዛደር በማህበር አልተደራጀም ነበር። የቀኝ ክንፍ ንኡስ ከበርቴው ድርጅት ኢህአፓ “የኢትዮጵያ ላብአደር በፋሽታዊ የሠራተኛ አዋጅ ስር አይደራጅም!” በማለት ሰፊ ፀረአብዮታዊና ፀረወዛደር ቅስቀሳን አካሂዶ ስለነበር፣ በሰርቶ አደሩ ሕዝብ ውስጥ ኃይለኛ ውዥንብር ሰፍኖ ነበር። “ጊዜያዊ ሕዝባዊ መንግሥት” የሚለው አድሃሪ መፈክር ሰፋ ያለ የአርሶአደሩን ክፍል ከማወናበዱም በላይ በወዛደር ቀን ሰልፍ ላይ በመጠኑ ይታይ ነበር። እንደሚታወሰውም፤ የዚያን ዕለት ዲሞዎች ቦዘኔዎችን ሰብስበው በመለዮለባሹ ላይ ድንጋይ በመወርወር ጠብ ከጫሩ በኋላ የንፁሃን ደም በከንቱ አንዲፈስ አድርገዋል።
ግን ደግሞ ያለፈው ዓመት የወዛደር ቀን ሃቀኛ አብዮታውያንና የዲሞ ቀልባሾች በይፋ የተፋጠጡበትና ወዛደሩን በጠቅላላው በሁለት ሰፈሮች መካከል በመምረጥ ላይ እንዳለ የታየበት ቀን ነበር። “ጊዜያዊ ሕዝባዊ መንግሥት የቀልባሾች መፈክር ነው!” የሚሉም በርከት ያሉ ሰሌዳዎች ነበሩ። በሁለቱ ወገኖች መካከል ግልጽ ጦርነት ከተጀመረበት ከግንቦት 67 በኋላ፣ ሚዛኑ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደሃቀኛ አብዮታዊያን ያዘነበለበት ቀን ነበር።
ከዚያ በኋላ ነበር፣ በየፋብሪካውና በየድርጅቱ ብዙ ትግል ተደርጎ ብዙዎቹ ማህበራት ሊቋቋሙ የቻሉት። ከዚያ በኋላ ነበር ዲሞዎችና እነ ሲሳይ ሀብቴ ለፀረ አብዮታዊ ቅበሳቸው ወዛደሩ ጠቅላላ የሥራ ማቆም እርምጃን እንዲወስድ ጠይቀውት ወዝአደሩ ዞር በሉ ያላቸው። ከዚያ በኋላ ነበር መኢሰማ በስንት ትግል ሊቋቋም የቻለውና ዲሞዎችም ከክስረት ወደ ክስረት እየተሸጋገሩ ወደ ነፍስ ግደያ የተዛወሩት።
የኢትዮጵያ ወዛደር መደብ በዚህ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ያገኛቸው ድሎችና በጠቅላላው ያተረፈው የንቃተ ህሊና እርምጃ በጣም ከፍተኛ ነው። የኢትዮጵያ ወዛደር መደብ በአሁኑ ወቅት በነማርክስ ቋንቋ ከ“መደብ በራሱ” ወደ “መደብ ለራሱ” በመሸጋገር ላይ ይገኛል። ማለትም ከተበታተነና ቅርጽ ከሌለዉ አካል፣ በስሜትና በግንፍልነት በየቦታውና በየሁኔታው የተናጠል ትግልን ከሚያካሂድ መደብ፣ የቀኝ ክንፍ ንዑስ ከበርቴውና የሌሎችም አድሃሪዎችንና አወናባጆች መሳሪያ ከሆነ መደብ ወደ ተሰበሰበ፣ የራሱን ጉልበትና ታሪካዊ ሚና ወደ ተገነዘበ መደብ፣ ራሱን ወደ ቻለ የህብረተሰብ ኃይል በመሸጋገር ላይ ይገኛል። ሆኖም ግን፣ ያለፉት ድሎቹ ከሚመጡት ትግሎቹ ጋር ሲመዛዘኑ አሁንም ገና ብዙ መንገድ መጓዝ እንዳለበት እርሱ ራሱ ይገነዘበዋል።
ሌላው ቀርቶ፣ አሁን በስንት ትግል የተመሰረተው የሙያ ድርጅቱ በእርግጥ የራሱ መገልገያ እንዲሆን ገና መታገል ይኖርበታል። የኢትዮጵያ ወዛደር ገና የዓለም ወዛሮችን የትግል ልምድ ቀስሞ ከራሱ ትግል ጋር ማዋሃድ ይኖርበታል። ገና የመደቦችን ሁሉ አቋሞችና ድርጊቶች፣ የየመደቡን የጥቅም መጠበቂያ ዘዴዎች እና ሸሮች ለይቶ ማወቅ ይኖርበታል። ገና የራሱን ነፃና ታሪካዊ ድርጊቶችን የሚያከናውኑበትን ጥበብ ከትግሎቹ ሁሉ መቅሰም ይኖርበታል።
የኢትዮጵያ ወዛደር ከ“መደብ በራሱ” ወደ “መደብ ለራሱ” ሙሉ በሙሉ ተሸጋገረ የምንለው ከላይ የተጠቀሱትን ነገሮች እንዲያሟላ የሚያደርገውን በማርክሲዝም-ሌኒኒዝም የታጠቀውን የራሱን ፓርቲ ሲያገኝ ነው። ስለዚህም ነው የዛሬው ቀን የድሎች ማስታወሻና የመደሰቻ ቀን ሳይሆን የትግል የወደፊት እቅድ ማሰቢያ ቀን መሆን የሚኖርበት።
መኢሶን ለዚህ ዓይነቱ ፓርቲ መፈጠር ያልተቆጠበ ጥረትን እንዳካሄደ ነው። መኢሶን ከግንቦት 67 ጀምሮ የኢትዮጵያን ወዛደር ከቀኝ ክንፍ ንዑስ ከበርቴው ፀረ አብዮታዊ አስተሳሰብ ለማላቀቅ ሲታገል የቆየው የዚህ ዓይነቱ እውነተኛ የወዛደር ፓርቲ በተቻለ ፍጥነት እንዲመሠረት ለማድረግም ጭምር ነው።
የኢትዮጵያ ወዛደር ግንባር ቀደም ክፍል የሚሆነው ፓርቲው የሚፈጥረው አብዮታዊያን ከወዝአደሩና ከደሃው አርሶ አደር ጋር ሲዋሃዱ፣ በጠቅላላውም ከሰፊው ሕዝብ ጋር በጥብቅ ሲተሳሰሩና አለማቀፋዊ የሆነውን የወዛደሩን ርአዮተዓለም ከኢትዮጵያ አብዮት ተጨባጭ ሁኔታዎች ጋር ለማገናዘብ ሲችሉ ብቻ ነው። በዚህ ሌላ አማራጭ በሌለው መንገድ ፓርቲው እንዲፈጠር ለማድረግ ሕይወታቸውን የሰውትና በመሰዋትም ላይ የሚገኙትን የመኢሶንን፣ የማሌሪድንናና የሌሎችንም ድርጅቶች ጓዶች የኢትዮጵያ ወዛደር ለዘላለም ሲያስታውሳቸው ይኖራል። ድርጅታችን ከእነዚህ ጓዶች እጅ የወደቀውን ቀይ ባንዲራ አንስቶ ለወዛደር ፓርቲና ለሕዝባዊ አብዮታዊ ግንባሩ መፈጠር፣ ለብሔራዊ ዴሞክራሲያዊ አብዮትና ለሶሻሊዝም፣ ለብሔራዊ ነፃነትና ለአለም አቀፋዊነት እስከመጨረሻው ይታገላል።
ዲሞክራሲያዊ መብቶች አሁኑኑ!
የተራማጆች ህብረት ይጠንክር!
እውነተኛ የወዛደር ፓርቲ እንፍጠር!
የዓለም ወዛደሮች አንድነት ለዘላለም የኑር!