ልዩ እትም 1 1969

የሰፊው ሕዝብ ድምፅ

ልዩ እትም፣    ጥር 24፣ 1969 

የፅሁፉ ፍሬ ሀሳብ

ደርጉ ውስጥ የኢህአፓ አባል የነበሩት የመቶ አለቃ አለማየሁና ሻምበል ሞገስ ቡድን በመንግሥት የዜና ማሰራጫዎች ኢሕአፓ ላይ የሚደረገው ውግዘት እንዲቆም ትዕዛዝ አስተላለፉ። ጥር 21፣ 1969 ዓ.ም. የድርጉ ሊቀመንበር የነበሩት ጄኔራል ተፈሪ በንቲ፣ ኢህአፓን ሳይጨምር “ኢዲዩንና የኤርትራ ግንባሮችን” ብቻ የሚያወግዝ ንግግር አደረጉ። የዜና ማሰራጫዎች በማግስቱ ጥር 22 የሊቀመንበሩን ንግግር በመደገፍ ሕዝቡ ሰልፍ እንደሚወጣ ተናገሩ። በማግስቱ የሊቀመንበሩን ንግግር የሚደግፍ ሳይሆን፣ ኢህአፓንና ቢሮክራሲውን የሚያወግዝ የተቃውሞ ሰልፍ ተካሄደ።

ከጥር 22ቱ ሰላማዊ ሰልፍ በኋላ የወጣው ይህ የመኢሶን ልዩ እትም፣ በሰልፉ ላይ የታዩትን “ኢህአፓን ሰፊው ሕዝብ ተፍቶታል፤ አድሃሪው አቅፎታል” የሚሉና ሰሌዳዎችን እና ሌሎችንም ሰሞኑን የነበሩ እንቅስቃሴዎችን በመተንተን በደርጉ ውስጥ የነበሩ የኢህአፓ አባላትና የኢህአፓን የራሱን የሰሞኑን እንቅስቃሴ ይተነትናል። መኢሶን፣ ኢህአፓ የተሳሳቱ ተራማጆች ቡድን ነው ብሎ በማመን ለመቀራረብና ለመከራከር ሙከራዎች አድርጎ እንደነበረ ያስታውሳል። ከዚያም ኢህአፓ በየጊዜው የሚወስዳቸው አቋሞቹ እንዴት ከኢትዮጵያ አብዮት ጠላቶች ጋር እንደተሰልፈ፣ ለዚህም በሶማሌ፣ በኤርትራ ጥያቂዎች ላይ ያለውን አቋም እንደ ምሳሌ ያቀርባል። በገጠር ከኢዲዩና አድሃሪ ኃይሎች ጋር አብሮ መሰለፉን፣ በከተሞች ውስጥ በሽብር ላይ መሰማራቱን ይጠቅሳል።

ዛሬ ቢሮክራሲው ‘ኢሕአፓን እንቀፈው ‘ ሲል ወይንም ‘ኢድዩ የዴሞክራሲ እንጂ የዘውድ አገዛዝን አይፈልግም፣ ስለዚህ ከርሱ ጋር ተባብረን የውጪ ጠላት እንመክት’ በማለት የሚያቀርበው ጥሪ የኢትዮጵያን አብዮት ለመቀልበስ ከሚደረገው ሙከራ ለይተን አናየውም በማለት ያጠቃልላል።

የሰፊው ሕዝብ ድምፅ

ለሰፊው ሕዝብ ሰራተኛ ገበሬ፣ ነጋዴ፣ ወታደር፣ ምሁር መብትና ጥቅም የሚታገል ጋዜጣ

የኢትዮጵያ ሰፊ ሕዝብ ይቅደም

 
ልዩ እትም                                                                    ቀን 24/05/69

 

የሞተ ኢህአፓን ለመቀስቀስ የሚደክሙ ቀልባሾች ናቸው!!

የአዲስ አበባ ከተማ ሠርቶአደሮች፣ የአካባቢው ወዛደሮችና አርሶአደሮች ጥር 22 ቀን 69 ከ300 ሺህ በላይ በቁጥር ወጥተው ታላቅ ሰላማዊ ሰልፍ አድርገው ውለዋል። የአብዮት አደባባይ ከአፍ እስከ ገዳፉ ሞልቶ፣ ቦታ የጠበበው ሰልፈኛ ውጪ ወጪውን በመኪና መንገዶች ላይ መቆየት ነበረበት።

ይህ ታላቅ ሰላማዊ ሰልፍ የአዲስ አበባና የአካባቢዋ ጭቆኖችና ተራማጅ ኃይሎች በውስጥና በውጭ ጠላቶቻቸው ላይ ያላቸውን ተቃውሞ ለመግለጽ እና በተባበረ ክንዳቸው እነዚህን አድሀሪዎች ለመደምሰስ ቁርጠኞች መሆናቸውን ለማሳየት ራሳቸው በራሳቸው ለረዥም ጊዜ ተዘጋጅተው ያደረጉት ነበር። በዚህ ዕለት፣ የተያዙት መፈክሮች፣ ይዘመሩ የነበሩት መዝሙሮች እነዚህ ጭቁኖች ወዳጅና ጠላታቸውን ለይተው ማወቃቸውን፣ የውጭውን ጠላት ለመቋቋም የውስጥ አድሃሪዎችን ለመደምሰስ መነሳታቸውን የሚያሳዩ ነበሩ። የጐረቤት አገር ገዥ መደቦችን እንጂ የእነዚህ ሀገር ጭቁን መደቦች ወንድሞቻቸው እንደሆኑ ደጋግመው ይገልፁ ነበር። በስመ ኢትዮጵያዊ ዛሬ ሁሉም እናት አገሩን ለመጠበቅ እንደማይነሳ፣ ኢዲዩን፣ ኢህአፓን፣ ኢኤልኤፍን የመሳሰሉት ምንደኞች ሰልፋቸው፣ ሴራቸውና ትብብራቸው ከነዚሁ የውጭ ጠላቶች ጋር መሆኑን ያሰሙ ነበር። ይህንን የውጭ ጠላቶች ሴራ ለማክሸፍ ዋና ምሸጋቸውና መሰረታቸውን ጎረቤት አገሮች ውስጥ አድርገው አብዮታችንን ከውስጥ የሚቦረቡረትን የውስጥ አርበኞች ማለትም፣ ኢዲዩን፣ ኢህአፓንና ኢኤልኤፍን መደምሰስ እንደሚያስፈልግ ያስተጋቡ ነበር።

በዚህ ታላቅ ሰላማዊ ሰልፍ ላይ ሰፊ ሕዝብ  እንደጠላት እያጋለጠ ካወገዛቸው ድርጅቶች አንዱ የግልገል ፋሺስቶች ጥርቃሞ የሆነው ኢህአፓ ነበር። “ኢህአፓን ሰፊው ሕዝብ ተፍቶታል፣ አደሃሪዉ አቅፎታል” የሚለው መፈክር በብዛት ከተያዙት አንዱ ሲሆን ሰልፈኛም እየደጋገመ የሚያስተጋባው መፈክር ነበር። የዚህ የግልገል ፋሽስቶች ቡድን ምልምሎች ሰርገው ገብተው ሰልፉን ለመበጥበጥ ያደረጉትን ሙከራ በሰልፉ ላይ የተገኘው ሰፊው ሕዝብ እራሱ በንቃት ማክሸፉ የዚህን መፈክር እውነትነት በሚገባ ያረጋግጣል። ሰርጎ ገብነቱ የተነቃበት የግልገል ፋሺስቶቹ ቅጥረኛ ልክ ቤተክርስቲያን እንደገባችው ውሻ ነበር የሆነው። አብዮታዊ ሰልፈኞችን ከወዲያ ወዴት እያዋከቡ ተገቢውን ቅጣት ይሰጡት ነበር። ያ ሌሊት እያደባ የጭቆኖችን ወገን የሚገልና በዚህም ብዙ ህጻናት ያለአባት የሚያስቀረ አረመኔ መሆኑን በመረዳት የተቆጣው ሰፊው ሕዝብ ሰልፉ ላይ ሰርጎ ለመግባት ሲንቀዠቀዥ በነበረው አናርኪስት ላይ ራሱ አፀፋውን ለመመለስ ሞክሯል። መለዩ ለባሾች አንድ አናርኪስት ከነፈንጂ ወይንም ከነመሳሪያ እጅ ከፈንድ ይዘው ሲወስዱት ሰልፈኞቹ “ለኛ ስጡን፣ ለኛ ስጡን፣ እኛ ተገቢውን ቅጣት እንፈምበት” እያሉ ይጮሁ ነበር። በእውነቱ፣ በዚህ ዕለት ሰልፉ ላይ ኢህአፓ በሰፊው ሕዝብ ስትወገዝ ብቻ ሳይሆን ስትገረፍም ጭምር ነበር የዋለችው።

ታዲያ ነገሩ በእርግጥም “ኢህአፓን ሰፊው ሕዝብ ተፍቶታል፣ አድሃሪው አቅፎታል” ነውና፣ ጭቁኖዎች ከታች እንደዚያ ሲረግጡት እና ሲያወግዙት ከላይ ደግሞ ኢህአፓን አትንኩብን የሚሉ ቢሮክራቶችና አደሃሪ መኮንኖች ነበሩ። ሰፊው ሕዝብ አንቅሮ የተፋውን እነሱ ፊት ለፊት “ኢህአፓ ወዳጅ ነውና አትንኩት” ሲሉ ስለሚነቃባቸው፣ ኢህአፓን ሊያድኑ የሞከሩት ከሰፊው ሕዝብ ጀርባ ስልጣናቸውን በመጠቀም ነበር።

የማስታወቂያ ሚኒስቴሩ ቋሚ ተጠሪ፣ የመሳፍንቶቹ አማች ተስፋዬ ታደሰ በአድሃሪ መኮንኖች እየታገዘ ለኢትዮጵያ ሬዲዮ ሠራተኞች “ኢህአፓ የተወገዘበት ዜና እንዳታስተላልፉ” የሚል ትዕዛዝ ስጠ። ከዚህም በላይ፣ ሰልፍኛው ከያዛቸው ብዙ መቶ መፈክሮች 150 ያህሉን የያዘ ሊስት ወስዶ ኢህአፓን የሚያወግዙትን በሙሉ ሰረዘና “የተሠረዙትን ትታችሁ የቀሩትን ብቻ አስተላልፉ” የሚል ተጨማሪ ትዕዛዝ ሰጠ። የንግግር ፕሮግራሙ ከመጀመሩ በፊት ሰፊው ሕዝብ በውጭ አድሃሪዎች ላይ፣ በኢዲዩ፣ በኢህአፓ እና በኢኤልኤፍ ላይ የሚያሰማው የተቃውሞ ጩኸት በቀጥታ እንዳይተላለፍ ከሰልፈኛው ጋር የሚያገናኝ የድምጽ ማጉያ እንዳይኖር ከልክሎ የቴፕ ዘፈኖች ብቻ እንዲተላለፉ አደረገ። ሰልፈኛው ኢህአፓ የተባለውን የጠላት ድርጅት ሲያጋልጥ ቢሮክራቶዎች ድምጹን ሊያፍኑት እንደሚሞክሩ ለመረዳት ብዙ ጊዜ ያልፈጀበትም። “የኢህአፓ ተገን የሆኑ ቢሮክራቶዎችና አድሃሪ መኮንኖች ይውደሙ”፣ “ማስታወቂያ ሚኒስቴር የኢዲዩ እና የኢህአፓ ዋሻ ነው”፣’“የአብዮት አደባባዩ ሰልፍ በቀጥታ በሬድዮ ይተላለፍ”፣ “ተስፋዬ ታደሰና የኢትዮጵያ ሬዲዮ ድምፃችን አያፍኑ”፣ እና ሌሎችም የተቃውሞ ጩኸቶችን ሕዝብ ባንድ ላይ አስተጋባ። ከዚያ በኋላ ነው እነ ተስፋዬ ማፈግፈግ ግድ የሆነባቸው እና አንዳንድ የሰፊውን ሕዝብ ፀረኢህአፓ መፈክሮች መተላለፍ የጀመሩት።

የአድሃሪ ቢሮክራቶችና የአንዳንድ አድሃሪ መኮንኖች ኢህአፓን ከሞት ለማዳን መፍጨርጨር በዚህ ዕለቱ ሰልፍ ላይ የተጀመረ ነገር አይደለም። ቆይቷል። ዝቅ ብላን እንደምናሳየው ኢሕአፓ በስህተተኛ የፖለቲካ መስመር ጀምሮ እየከሰረ ከሰፊው ሕዝብ መሃል እየወጣ በሄደ መጠን በአድሃሪዎች እጅ ወድቋል። እነ ተስፋዬ ታደሰና መሰሎቹ ዛሬ ለኢህአፓ መከታ ለመሆን የሚፈልጉት በመሰረቱ ኢዲዩ በግልጽ የመሳፍንት ድርጅት ስለሆነባቸውና ዘመኑ ‘ከፍቶ’ ተራማጅ ሳይመስል ብዙም ተዝናንቶ ሊኖር ስለማይቻል የኢህአፓን ተራማጅ ካባ ፍለጋ እንጂ ኢህአፓ የተራማጆች ድርጅት እንዳልሆነ ሳያውቁት ቀርተው አይደለም። እንግዲህ፣ ይህ የቢሮክራሲውና ያድሃሪ መኮንኖች የኢህአፓ ተገንነት የቆየ ነገር ቢሆንም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተለየ መልክ የያዘው በደርጉም ውስጥ ያሉ አድሃሪዎችና አድርባዎች ተመሳሳይ አቋም ይዘው በግልጽ ስለወጡ ነው።

በመሠረቱ ስለ ኢህአፓ አነሳስና ምንነት የዛሬ አሽቃባጮቹ ከሆኑት ቢሮክራቶችና አድሃሪ መኮንኖች የበለጠ እናውቃለን። በሰፊው ሕዝብ ድምጽ ቁጥር 48 ላይ እንደገለጽነው፣ በኋላ ኢህአፓ ብሎ እራሱን ከሰየመው ቡድን ጋር አብረን ለመስራት ውይይቶቹ ሁሉ አድርገን ነበር። 1967 ውስጥ በወጡት የሰፊው ሕዝብ ድምፅ ቁጥሮች ላይ የዲሞክራሲያ “ጓዶችን” እንደ ተሳሳቱ ተራማጆች እንቆጥር ስለ ነበረ ደጋግመን ለፖለቲካ መስመር ክርክር እንደጋበዝናቸው እነዚህን ቁጥሮች መለስ ብሎ የተመለከተ ሊረዳ ይችላል። በተለይ ከሚያዝያ/68 ጀምሮ ግን እንደ ጠላት ድርጅት ስናጋለጠውና ስንታገለው መጥተናል። ይህ የሆነው ለምንድነው?

የኢትዮጵያን ግራ እንቅስቃሴ በመጠኑም የሚያውቅ የመኢሶንም የኢህአፓም ምንጭ በኃይለሥላሴ አረመኔ አገዛዝ ስር ይካሄድ የነበረው የኢትዮጵያ ወጣቶችን እንቅስቃሴ እንደሆነ ይረዳል። በዚያን ወቅት በዚህ ታጋይ ትውልድ ውስጥ የተሳተፉ ኃይሎች በመሃላቸው የመስመር ልዩነት ነበር። የኋለኛው ኢህአፓ መስራቾች በዚህ የወጣት ታጋዮች ትውልድ ውስጥ “የጠመንጃ ትግል ዛሬ” በሚል ጀብደኛ መስመር ስር የተሰለፉ፣ ከማርክሲዝም ሌኒኒዝም እውቀታቸው ይልቅ በጥራዝ ነጠቅነታቸውና በደንፊነታቸው የታወቁ ነበሩ። ጀብደኛም ሆኑ ደንፊ፣ በዚያን የጨለማ ዘመን ውስጥ ጠመንጃ ላንሳ የሚል ጀብደኛ ይቅርና ከኃይለሥላሴ ጋር የግል ጠብ የነበራቸው እነብርሃኑ ድንቄ ሳይቀሩ ተራማጅነት ነበራቸው። ስለሆነም፣ በዚህ ወጣት ትውልድ ውስጥ ትክክለኛ መስመር ይዘው ይታገሉ የነበሩ ተራማጅ ወጣቶች በእነርሱና በጀብደኞቹ መሃል ያለውን ቅራኔ እንደ ሁለተኛ ደረጃ ቅራኔ ወስደውት ነበር። ከጀብደኞቹ ጋር አብሮ ለመስራትም ትልቅ ትዕግስት የጠየቀ ትግል አድርገዋል።

የየካቲት እንቅስቃሴ እንደተነሳ፣ ይህ ጀብደኛና ደንፊ ቡድን በተሳሳተ መስመሩ ቢቀጥልም የትግሉ ዒላማ የኢትዮጵያ ሰፊ ሕዝብ መሰረታዊ ጠላቶቹ ነበሩ። በአብዛኛው አቅፎ የነበረውም መንገዱን ጠንቅቀው ያልተረዱ ሆነው ነው እንጂ የኢትዮጵያ ጭቁኖች ቀን እንዲያልፍላቸው የሚፈልጉ ወጣቶችን ነበር። ስለሆነም፣ በየካቲት እንቅስቃሴ አፍላ ላይም ቢሆን፣ በጀብደኞቹና በትክክለኛው መስመር ተከታዮች መሃል የነበረው ቅራኔ የሁለተኛ ደረጃ ቅራኔ ነበር። አብሮ ለመስራት መሞከሩም የተገባ ነበር።የየካቲት እንቅስቃሴ ገፍቶ የቀድሞ ገዥ መደቦችን ከስልጣን በማውረዱ ጊዜያዊ ወታደራዊ መንግሥት እንደተተካ በኢትዮጵያ ውስጥ ፍጹም ልዩ ሁኔታ ተፈጥሮ ነበር። ጊዜያዊ ወታደራዊ መንግሥት በመጀመሪያዎቹ አራት ወራት ከህዝቡ መሰረታዊ ጥያቄዎች አንዱንም አለመመለሱ እና ሁለተኛም የአሜሪካኖች ሰው በነበረው በኣማን አንዶም መመራቱ የደርጉን ጠባይ ለመረዳት አዳጋች የሚያደርጉ ሁኔታዎች ነበሩ። በነዚህም ምክንያቶች ሀቀኛ ተራማጆችም ቢሆኑ የተሳሳተ መስመራቸውን ለማስተካከል እጅግም የማያመች አዝማሚያ ስለነበረ ደንፊዎቹም “የተሳሳቱ ተራማጆች” ክልል ውስጥ የሚገቡ ነበሩ።

በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ውስጥ የልዩ ሁኔታ መፈጠር፣ በተለይም ደግሞ የደርጉ ተራማጅ እርመጃዎችን መውሰድ መጀመር፣ በአንድ በኩል ሀቀኛ ተራማጆች አቋማቸውን እንዲያስተካክሉ ሲረዳና ሰያስገድድ በሌላ በኩል ደግሞ፣ የተሳሳተ መስመር ይዞ መቀጠል ከጠላቶች ጋር የሚያሰለፍ ሆነ። የኢህአፓ መስራቾች በተሳሳተ መስመራቸው በመቀጠላቸው እጃቸው የሚወድቀው ኃይል ቀስ በቀስ እንደድሮ የተሳሳተው ተራማጅ ሳይሆን የነቃው አድሃሪ እየሆነ ሄደ። ይህ ሂደት ዛሬ የዲሞን ሰዎች የት እንዳደረሳቸው ሳናመለክት በፊት ይህንኑ ሀቅ በአንዳንድ ምሳሌዎች ለማስረዳት እንሞክር።

የኃይለሥላሴ መንግሥት እንደወደቀና ጊዜያዊ ወታደራዊ መንግሥት ስልጣን ላይ እንደመጣ የደርጉ ተቃዋሚዎች ሁለት ኃይሎች ነበሩ። በአንድ በኩል ጥያቄዎቹ መልስ ያላገኙለት ሰፊ ሕዝብ፣ በሌላ በኩል ከስልጣን የተወገዱት የቀድሞ ገዥ መደቦችና አሽከሮቻቸው። ስለሆነም ያኔ ደርግም ተቃውሞ ለመነሳት አብሮ ማን እንደሚነሳ ማወቅ ያስፈልግ ነበር። የበኋለኛው ኢህአፓ መስራችና ገና ከድሮውም ጥንቃቄን እንደ “ዳተኝነት”፣ አዙሮ ማየትን እንደ “ደብተራነት” የሚያዩ ችኩሎች ነበሩና በደርጉ አገዛዝ ትግል ሲጀምሩ የደርግን ተቃዋሚ ሁሉ “ለመጠቀም” ተነሱ። ለዚህም ምሳሌ እንዲሆነን የበየነ ሰለሞንና የበኋለኛው ኢህአፓ መስራቾችን ግንኙነት እንውሰድ።

በየነ ሰለሞን፣ የኃይለሥላሴ መንግሥትና የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም ሃቀኛውን የኢሠማ አመራር አስወግደው በኢትዮጵያ ሰርቶ አደሮች ጫንቃ ላይ ያስቀመጡት አሽከራቸው ነበር። ይህ ሰው ከኢሠማ አመራር ላይ እንዲነሳ የኢትዮጵያ ሠርቶ አደሮች ብዙ ታግለዋል። በየካቲት እንቅስቃሴ መጀመሪያ ግድም በኢሠማ አመራር ላይ ለመውጣት ደርዳር ይል የነበረው የበኋለኛው ኢሕአፓ መስራች ቡድን ከአድርባይነትም ቢሆን ይሄን ሰው ተቃውሞ ታግሎ ነበር።ከመስከረም 2/67 በኋላ ግን እነዚህ ሁለት ጠበኞች ታረቁ። በየነ ሰለሞን ደርጉ የድሮ ጌቶቹን ከስልጣን ስለወረደበት ጸረደርግ ነበር። የበኋለኛው ኢህአፓ መስራቾች ደግሞ በደርግ ሥልጣን መያዝ ምክንያት የተቀየረውን የመደቦች አሰላለፍ ባለመረዳት “የደርግ ተቃዋሚዎችን” ሰብሳቢ ነበሩ። ስለሆነም፣ የቀድሞ ጠበኞች፣ ማለትም በየነ ሰለሞንና የበኋለኛው ኢህአፓ መስራቾች፣ አንድ ጠረጴዛ ላይ ቁጭ ብለው” ጊዜያዊ ወታደራዊ መንግሥት ይውደም፣ ጊዜያዊ ሕዝባዊ መንግሥት አሁኑኑ” በሚሉ ውሳኔ ላይ ተስማሙ። ከዚህ በኋላማ ምን ቅጡ!! ደርግ ተራመጅ እርምጃዎች መውሰድ ከጀመረ በኋላ ከሰፊው ሕዝብ ጋር የነበረው ቅራኔ እየቀነሰ ሲሄድ በሌላ ወገን ደግሞ ደርግ ላይ የሚያኮርፈው በዛ። የደርግ ተቃዋሚዎች ሰብሳቢ ለሆነችው ኢህአፓ የደራ ገበያ ተከፈተ። የተሳሳቱት ተራማጆች በአድሃሪ የደርግ ተቃዋሚዎች ተጥለቀለቁ። አድሃሪውን እጠቅማለሁ ብላ የተነሳችው ኢህአፓ ራስዋ የአድሃሪዎች መጠቀሚያ ሆና አረፈችው። ያኔ በኃይለሥላሴ ጊዜ፣ በሥርዓቱ ላይ የነበረንን ተቃውሞ ለመግለጽ አውቶቡስ ስንሰባብር ቡና ቤት ቁጭ ብሎ የሚስቅብን የመሳፍንት ልጅ ሁሉ ዛሬ “ኢህአፓ ያቸንፋል” እያለ አውቶቡስ ሰባሪ ሆነ።

ከላይ የጠቀስነው በኢህአፓ ላይ የተደረገው የአቋም ለውጥ ከዚህ የኢህአፓ አረማመድ ጋር የተያያዘ ነው። ኢህአፓ በአብዛኛው የተሳሳቱ ተራማጆች ቡድን የነበረ ጊዜ እንደሁለተኛ ደረጃ ቅራኔ በመውሰድ ለ“ጓዳዊ” ክርክር እንጋብዝ ነበር። ኢህአፓ የአድሃሪዎች መጠቀሚያ ከሆነ በኋላ እንደ ጠላት ድርጅት እንታገለው ገባን።

ይህንን የኢሕአፓን ቦታ መቀየር የሚያሳየው የመኢሶን አቋም በኢህአፓ ላይ መቀየር ብቻ አይደለም። በውስጡ የነበረው የተሳሳቱ ተራማጆች የወሰዱዋቸዉ እርምጃዎች ተጨማሪ ማረጋገጫዎች ናቸው። ለዚሁም፣ ከኢህአፓ መስራቾች መሃል ጫካ ድረስ ገብተው የመሬቱ አዋጅ እንደታወጀ “ተው ጓዶች፣ እኛም ጫካ፣ የመሬት ከበርቴውም ጫካ ይህ ነገር አይሆንምና እቋማችንን እናስተካከል የሚል ክርክር አንስተው በኢህአፓ ቡድን አመራር አምባገነንነት ምክንያት የአቋም ክርክር ስላልተቻለ ጥለውት ወጥተው ዛሬ በግልጽ ከሰፊው ሕዝብ ጎን የሚታገሉት ተራማጆች ምስክር ናቸው። አቋማቸውን አስተካክለው ከሀቀኛ ተራማጆች ጋር በመታገል ላይ እያሉ በነሱ ጥይት የወደቁት ጓድ ደመቀ እና ጓድ ብርሃኔ (ጥቂቶቹን ለመጥቀስ ያህል) ሌላኛዎቹ ምስክሮች ናቸው። ዛሬ በቅጥር ነፍሰ ገዳይነት ከተሰማሩት ውስጥ እንኳ፣ በአቃቂ አካባቢ የወዛደር መሪዎችን እንዲገድል ተመድቦ፣ “የግድያ ቡድን ጓዶቼ የመሳፍንት ልጆች፣ ግደል የተባልኩት ጭቁን ወዛደሮችን ይህ ነገር እንዴት ነው?” ብሎ ራሱን በመጠየቅ ተጸጸቶ እጁን ለመንግሥት የሰጠው ግርማ እንደዚሁ ሌላ ማረጋገጫ ነው። እንግዲህ፣ በኢህአፓ ውስጥ የነበሩ የተሳሳቱ ተራማጆች በየጊዜው ድርጅቱ አቋም አላስተካክል ስላላቸው ጥለውት ወጥተዋል። አሁንም እየወጡ ናቸው። ሌላው ቀርቶ፣ የኢህአፓ አባል የነበሩ፣ አቋማቸውን ያስተካከሉ አያሌ ጓደኞች ዛሬ በመኢሶን ውስጥ ይገኛሉ። አሁንም፣ የንቃተ ህሊና ዝቅተኛነት፣ የፊውዳል ይሉኝታ ይዞአቸው እንጂ ከሕዝቡ ጎን ሊቆሙ የሚችሉ ሰዎች እንደሚገኙ ሳይታለም የተፈታ ነው። ይህ ደግሞ ደጋግመን የገለጽነው ሀቅ ነው። እነዚህም ከጊዜ ብዛት ራሳቸውን እየነቁ፣ እኛ ሀቀኛ አብዮታዊያን በምናካሄደው ትግል እየሳብናቸው አቋማቸውን እንደሚያስተካክሉ የታወቀ ነው።

ግን ዛሬ ኢህአፓ የተሳሳቱ ተራማጆች ድርጅት አይደለም። እነዚህ የተሳሳቱ ተራማጆች ድምጻቸውን ማሰማት የማይችሉበት የአድሃዎች ድርጅት ነው። ዛሬ የኢህአፓ መከታዎች እነዚህ በየጊዜው ቁጥራቸው እያነሰ የሄደ የተሳሳቱ ተራማጅ አባሎቹ አይደሉም። የኢህአፓን የተራማጅ ካባ ፍለጋ ያጥለቀለቃት ምድረ አድሃሪ ቢሮክራሲው እንዲሁም ሲአይኤና የጎረቤት አድሃሪዎች በሙሉ ናቸው እንጂ። ለዚህም አንዳንድ ምሳሌዎችን እንጥቀስ።

ለምሳሌ፣ ኢህአፓ አንድ ምሳሌ በተነፈሰች ቁጥር የአሜሪካን ሬዲዮ፣ የእንግሊዝ ሬዲዮ እንደመአት አጋኖ ያስተጋባላታል። በቅርቡ እንኳ ከሃዲ ወጣቶች ባለፈው አርብ ያደረጉትን ውርውር ቮይስ ኦፍ አሜሪካና ቢቢሲ ልክ መሬት ያናወጠ የተቃውም ሰልፍ አድርገው ሲያቀርቡት፣ ባለፈው እሁድ ከ3000 ሺህ በላይ የሆነ ጭቁን ወጥቶ ያደረገውን ታላቅ ሰላማዊ ሰልፍ በአንድ አረፍተ ነገር ሸኝተውታል። የኢትዮጵያን ጭቆናዎች የረዥም ጊዜ ትግል ሲያፍኑ የኖሩ፣ ዛሬም አብዮታችንን በማጥላላት ላይ ያሉ የኢምፔሪያሊስቶች የዜና ማሰራጫዎች ለምን ይሆን ታዲየ ኢህአፓን እንደዚያ የሚያሞጋግሱት? ነገሩ ምንም ሚስጢረ ሥላሴ የለበትም። በስፔን ፋሺዝምን የሚታገለው የወዛደር ፓርቲ ላይ የማጥላላት ዘመቻ ኢምፔሪያሊስቶች በኢትዮጵያ “የላበደሩን ፓርቲ” የሚያሞግሱበት ምንም ምክንያት የላቸውም። ዋናው ምክንያት ኢህአፓ የአድሃሪዎች ድርጅትና ፀረወዛደር በመሆኑ ብቻ ነው።

ኢትዮጵያስ ውስጥ? ኢትዮጵያም ውስጥ ዛሬ ኢህአፓን አቅፈው ደግፈው የያዙት ተስፋ ለዘውድ ቢሮክራቶችና ቀኝ ክንፍ ንኡስ ከበርቴዎች ናቸው። ይህንን ከሙሉ ማረጋገጫዎች ጋር በዝርዝር ለማቅረብ መጽሃፎች መድረስ ያስፈልጋል። ስለሆነም በአንድ ምሳሌ እንወሰናለን። ከላይ አማቾቹ የተደራጁበትን ኢዲዩን በይፋ እንዳይደግፍ ፈርቶ የኢህአፓ ተራማጅ ካባ ስር መሸሸግ የሚፈልገውን የማስታወቂያ ሚኒስቴሩን የተስፋዬ ታደሰን ጉዳይ አንስተን ነበር። በማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የተሰገሰጉት አድሃሪዎችም አያሌ የተመሳሳይ ድርጊቶችን ፈጽመዋል። በግንቦት/68 የፋብሪካ ወታደሮች ስብሰባ ላይ ለኢህአፓ ሰርጎገቦች የማይገባቸው መታወቂያ እየሰጡ ጉባዔውን የበከሉ አድሃሪ ቢሮክራሲያችን እናስታውሳለን። አሁን በቅርቡ፣ የኢህአፓ ምልምሎችና አድሃሪ ቢሮክራቶች ተባብሮ በሃቀኛ ወዛደሮች ላይ የሚፈጽሙትን ሴራ ለማሳየት የአዲስ አበባን ሰሚንቶ ፋብሪካ ጉዳይ ባጭሩ እንመልከት።

በአዲስ አበባ ሲሚንቶ ፋብሪካ ውስጥ በአጠቃላይ የወዛደሩ መደብ ሰርጎገብ አናርኪሰቶች ያስገቡት ውዥንብር ውስጥ ይዋኝ በነበረ ጊዜ የሞያ ማህበሩን አመራር ይዘው የነበሩት የኢህአፓ ምልምሎች ነበሩ። ኢህአፓ በወዛደሩ ላይ ያሰፈረው ውዥንብር እየበነነ ሲጠፋ፣ የኢህአፓም ሰርጎ ገቦች በወዛደሩ ፊት እየተጋለጡ ሲተፉ፣ የሲሚንቶ ፋብሪካም ተመሳሳይ አረማመድ ነበረው። የኢህአፓ ሰርጎገቦች የተሸነፉ፣ በአብዮታዊ መስመር ስር የተሰለፉ ሀቀኛ ወዛደሮች እያሸነፉ መጡ። የዚህ ድል ማረጋገጫው፣ የቀድሞ የሙያ ማህበር አመራር አይወክለንም በማለት ብዙሃኑ ወዛደሮች ለመስከረም/69 የፋብሪካ ወዛደሮች ጉባዔ ጊዜያዊ ኮሚቴ መርጠው መላካቸው ነው። የቀድሞ አመራር የብዙሃን ድጋፍ ባይኖረው ከአሰሪ ጋር የጀመረውን ድርድር እስኪጨርስ ለተወሰነ ጊዜ ተተወ። በወዛደሩ ጫንቃ ላይ ለመቆየት የፈለገው ይህ አሮጌ አመራር ግን ከፋብሪካው ስራ አስኪያጆች ጋር በመተባበር ድርድሩን በሆነ ባልሆነ አራዘመ። በመጨረሻ፣ ብዙሀኑ ወዛደር ትግስቱ አለቀ አዲስ አመራር መረጠ። ይህም አዲስ አመራር ህጋዊ ሰውነት ለመማግኘት አመልክቶ ነበር። የማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ቢሮክራቶች ግን በአጠቃላይ የኢህአፓ መደምስ ለ“ዳግማይ ትንሳኤያችን” ይሆናል ያሉትን መሳሪያ እንደሚሰጣቸው የነቁ አድሃርያን ስለሆኑ፣ አናርኪስቶችን የተካውን አዲስ አመራር /የብዙሃን ወዛደሮች ድጋፍ ቢኖረውም/ ሕጋዊ ሰውነት ለመስጠት ፈቃደኛ አልሆኑም። በዚህ መሀል፣ እንዲሁም የኢህአፓ ተሟጋች የሆነው ፋብሪካው ስራ አስኪያጅ የነቁ ወዛደሮች የሰርጎገብ አድሃሪዎች የነበረውን አመራር በመተካታቸው ብቻ በዚህ ፋብሪካ ኢህአፓን ከውድቀት ለማዳን ከታጋይ ወዛደሮች ውስጥ ሃያ ያክሉን ወደ አሰብና ምጽዋ በመላክ ሊበታትናቸው እያቀደ ነው።

አንዱን ቦታ ለምሳሌ ያህል ጠቀስን እንጂ የኢትዮጵያ ቢሮክራሲ ከላይ እስከ ታች ለኢሕአፓ  ጋሻና መከታ ሆኖ ይሰራል። ከዚህም ሌላ ደግሞ በእነዚህ አድሃሪያን መሣሪያነት በምታካሂደው የግድያ ተግባር ውስጥ በተባባሪነት እጅ ከፍንጅ የተገኙ ቢሮክራቶችና የንኡስ ከበርቴው ቀኝ ክንፍ አባሎች ብዙ ናቸው።

ይህ እንዲያው የትግል መደጋገፉን ለማሳየት ያህል ነው። በአቋም ደረጃ ኢዲዩ፣ ሲአይኤና ኢህአፓ ምንም ልዩነት እንደሌላቸው መኢሶንና ሌሎች የሀቀኛ ተራማጅ ድርጅቶች እያጋልጡ መጥተዋል። በዕድገት በህብረት ዘመቻ ጥያቄ ላይ፣ በደርግ ጥያቄ ላይ፣ በመሬት ጥያቄ ላይ….. ሦስቱም ተመሳሳይ አቋም እንዳላቸው ዛሬ ሁሉም የሚያውቀው ነው። ለምሳሌ፣ በየካቲት/67 የመሬት አዋጅ ላይ ኢዲዩም ለምን መሬቴ የተወሰደ ብሎ በግልጽ አልተቃወመም። ኢህአፓም ደርግ ለምን ይህን አዋጅ አወጣ ብሎ ፊት ለፊት አልፃፍም። ግን ሁለቱም በዚህ አብዮታዊ የመሬት አዋጅ ቦታ መሬትን ወደ ግል ንብረትነት የሚመለስ ቀልባሽ ፕሮግራም ይዘው ወጥተዋል።….. ኢህአፓ በተከታታይ የወሰደችው አቋም እያቀፏት በሄዱት አድሃሪዎች ዘንድ ጥገኝነት ፍለጋ እንደሆነ፣ በኋላም የነዚሁ አድሃሪያን አቋም ማስፋፊያ መሳሪያ ወደ መሆን እንደተቀየረች ብዙ ማረጋገጫዎች መስጠት ይቻላል። ከነዚህ አንዳንዶቹን ለመጥቀስ ያህል፡-

የኢትዮጵያ መንግሥት የአፋርና ኢሳ ግዛት ራሱን በራሱ ለማስተዳደር ያለውን ሙሉ መብት ያውቃል። ይህንን በርከት ባሉ ዓለም አቀፋዊ ስብሰባዎች ላይ ደጋግሞ ገልጿል። ሶማሌ ፊት ለፊት ይሄንን መብት እንደማትደግፍ ትናገራለች። ከኢትዮጵያ ግዛት የተወሰነ ክፍልና ጅቡቲ ይጋቡኛል ባይ ነች። ታዲያ ኢህአፓ የሱማሌ ጥገኛ በመሆኑ፣ አንደኛ የኢትዮጵያ መንግሥት ያለውን ትክክለኛ አቋም እያጥላላ ያወግዝና ስለ ሶማሌ አቋም አንዲት ቃል አይተነፍስም። ሁለተኛም፣ የሱማሌ መንግሥት ያለውን የመስፋፋት አላማ “ኢትዮጵያ ልትወረኝ ነው” በሚል ሰበብ ስራ ላይ ሊያውል ሲነሳ፣ ኢህአፓም “ደርጉ ሱማሌን ለመውረር በኦጋዴን ለአሜሪካን የጦር ሰፈር ሰጠ” የሚል በሬ ወለደ ፕሮፓጋንዳ ይነዛለታል።

በኢትዮጵያ ውስጥ ጣልቃ ለመግባት የሚያስቡ አድሃሪ የጎረቤት ሀገር መሪዎች ጣልቃ ገብነት “ በኢትዮጵያ ወረራ ለመዳን” በሚል ቅጥፈት ሊሸፍኑት እንደሚሞክሩ በሰሕድ ቁጥር 49 ላይ ጠቅሰን ነበር። በሱዳን ጉዳይ የኤልኑሜሪና የኢህአፓ አቋም ሁለት ጠብታ ውሃ ተመሳሳይ ነው። ኢህአፓ “አብዮት” በተባለው ውጭ አገር በእንግሊዘኛ ቋንቋ የሚታተም ልሳኑ ላይ የሚወጡት አቋሞቹን ትተን፣ ዲሞክራሲያ ላይ ከጥቂት ወራት በፊት ያሰፈረውን እንውሰድ። እንደ ፋሺስቱ ሂትለር ፋሽስት ደርግም ጎረቤት አገሮችን ለማውረር ይዘጋጃል ይላል ኢህአፓ። ኑሜሪም ከዚህ የተለየ ነገር አላለም። ወደ ኢትዮጵያ ወሰን ተጠግቶና ኢትዮጵያን አመልክቶ “ተጠንቀቁ፣ ከዚህ ወሰን ባሻገር እኛን የሚወር ሰራዊት እየተቋቋመ ነው” ብሏል። ታዲያ ኢሕአፓ የነዚህ አድሃሪ መንግሥታት ቱልቱላ ለመሆኗ አንድ እና ሁለት አለው??

በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ውስጥ ካሉት ከፍተኛ የፖለቲካ ጥያቄዎች አንዱ የኤርትራ ጉዳይ እንደ መሆኑ ማንኛውም ቡድን በዚህ ጉዳይ አቋም መውሰድ አለበት። ከፍተኛ የፖለቲካ ጉዳይ እንደመሆኑ በዚህ ላይ የሚወሰደው አቋምም፣ የተራማጅነት የአድሃሪነት መለኪያም ጭምር ነው። ከግንቦት ስምንቱ /66ቱ የፖሊሲ ውሳኔ በፊት ደርግ የኤርትራን ችግር እንደ ፖለቲካ ጥያቄ ወስዶ ሰላማዊ መፍትሄ ባለመፈለጉ በኤርትራ ላይ ብዙ አድሃሪ እርምጃዎችን መውሰዱ የታወቀ ነው። በዚያው መጠን ደግሞ፣ የኤርትራ ግንባሮች  አመራር ከጊዜ ወደ ጊዜ ከኢትዮጵ አብዮት ወገኖች ይልቅ ከጠላቶች ጋር እየተመሳጠረ መምጣቱ የታወቀ ነው። ስለሆነም፣ ሃቀኛ ተራማጆች ያለምንም አድርባይነት የደርጉን አድሃሪ እርምጃዎች እያወገዙ ሰላማዊ መፍትሄ እንዲፈለግ ይታገሉ ነበር። የኤርትራ ግንባሮች አመራር ያለውን አድሃሪ ግንኙነት እያጋለጡ ይህ የኢትዮጵያን አብዮት የሚያስቀለብስ ግንኙነት እንጂ የኤርትራን ሰፊ የሕዝብ ነጻነት የሚያስገኝ አለመሆኑን እያሳዩ ያወግዙ ነበር። ኢሕአፓ፣ እነ ኢኤልኤፍ ከነመንገሻ ስዩምና አሊ ሚራህ ጋር በጅዳ ተሰብስበው የትግል አንድነት ሲመሰረቱ አንዲት ቃል አልተናገረም። ይህንን ግልጽ ፀረአብዮት አድማ እየካደ ደርግ ላይ ብቻ ቡራ ከረዩ ይል ነበር።

የግንቦት ስምንቱ ውሳኔ ደርጉ በኤርትራ ላይ ትክክለኛ አቋም የወሰደበት ውሳኔ ነበር። የኤርትራን ችግር በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት፣ የኤርትራንና የኢትዮጵያን ጭቆኖች አንድነት ለመመስረት የሚያስችል ውሳኔ ነው። የኢትዮጵያ ተራማጆች፣ የኤርትራ ተራማጆች ጭምርና የዓለም ተራማጅ ኃይሎች ሁሉ የደገፉት ውሳኔ ነው። አላማቸው የኤርትራ ጭቆናዎች ነፃነት ሳይሆን የራሳቸውን አድሃሪኝ መንግሥት ማቋቋም የሆነው የኤርትራ ግንባሮች አመራርና ጌቶቻቸው የሆኑት የጎረቤት አድሃሪዎች ይህን የፖሊሲ ዉሳኔ እንደማይደግፉት የታወቀ ነው። ኢህአፓ በግልጽ ይህንን የፖሊሲ ዉሳኔ ደጋግሞ ተቃውሟል። እንዲያውም ዛሬ የኤርተራ ግንባሮች እራሳቸው የማይክዱትን ከነመንገሻ ስዩምና ከአድሃሪ የአረብ ሀገሮች ጋር ያላቸውን ግንኙነት ይክድላቸዋል። ደርግ እና የኢትዮጵያን ተራማጆች የኤርትራን ግንባሮች ስም ለማጥፋት ሆን ብለው የፈጠሩት ግንኙነት ለማስመሰል ይጥራል። በግልጽም እነዚህን አድሃሪዎ የኤርትራ ጭቆና ሕዝቦች አርነት አምጪዎች አድርጎ በማቅረብ፣ የኤርትራን ግንባሮች አድሃሪ አመራር በማውገዝ ከኢትዮጵያ ተራማጆች ጋር የትግል አንድነት ለመመስረት የተነሱትን እነ ሳራ መኮንንን ከ“ሃዲዎች” ይላቸዋል። ከዚህ የበለጠ የኤርትራ አድሃሪዎች ተቀጥላነት ምን አለ??

እነዚህ ከላይ በአጭሩ እየጠቀስናቸው ምሳሌዎች ኢህአፓ ከመሳፍንቱ ጋር ተመሳሳይ አቋም እንዳለው ያረጋግጣሉ። የመሳፍንቱና የጎረቤት አድሃሪዎች እንዲሁም የነኢኤልኤፍ ፕሮፓጋንዳ አሰራጭ መሆኑን ያሳያሉ። ይህም ብቻ አይደለም። በየቀኑ በአብዮትና በፀረአብዮት መሃል በሚደረገው ትግል ኢህአፓ በየት በኩል ሆኖ እንደምትታገል ማየቱ በጣም ቀላል ነው። በነ ተስፋዬ ታደሰ ቁጥጥር ስር የሆነው የኢትዮጵያ ሬዲዮ ሺ ጊዜ ቢደብቅላት፣ ኢህአፓ እንዳቅሟ ያሰለፈችው “ሠራዊት” ከማን ጋር ሆኖ ማንን እንደሚወጋ የትግራይንና የቤጌምድርን ምሳሌ መጥቀሱ ብቻ ይበቃል። በትግራይ፣ የኢኤልኤፍ፣የነመንገሻ ስዩምና የኢህአፓ “ወታደሮች” አንድ ላይ ሆነው በትግራይ አርሶአደሮችና ዛሬ የአብዮቱ ኃይል በሆነው መለዮ ለባሽ ላይ በመተኮስ ላይ ናቸው። በጌምድር ባለው ሁኔታ፣ ጸረአብዮት ያየለባቸው አራት አውራጃዎች ብንወስድ፣ ሦስቱ የኢዲዩ ሲሆኑ “አንደኛው” የኢህአፓ ነው።

በከተሞችስ ውስጥ ቢሆን የኢህአፓ የግልገል ፋሽስቶች ቡድን ጥይት ያተኮረው እነማን ላይ ነው?? ሀቀኛ ተራማጆች ላይ፣ የጭቁኖች ተወካዮች ላይ አይደለምን?? ኢህአፓ “አብዮት” በተባለው የውጭ ልሳን ቅጽ 1 ቁጥር 8 ህዳር/1969 ባወጣው እትሙ ላይ እንዳመነው የካቲት/66ን የፖለቲካዊ ትምህርት ቤት አቃጥሎ ብዙ የሳይንሳዊ ሶሻሊዝምን መጽሐፍት ማውደም አይደለምን?? ደግሞስ የዚህ ተራ ውንብድና ተባባሪዎቹ እነሲአይኤ እና ተስፋ ለዘውድ ቢሮክራቶች አይደሉምን?? ታድያ ኢህአፓ ከቀልባሾች ጋር እየጣመረ ትግል እንደምታካሂድ የሚያጠያይቀው ምኑ ላይ ነው??

እንግዲህ፣ እስካሁን ካልነው ግልጽ እንደሚሆነው፣ ኢህአፓ የተሳሳቱ ተራማጆች ድርጅት መሆኑ አክትሞ የአድሃሪዎች መጠቀሚያ ድርጅት መሆኑ ምንም የሚያጠራጥር አይደለም። ይህንን ደግሞ የኢትዮጵያ ሰፊ የሕዝብ ከራሱ ትግልና ከሃቀኛ ተራማጆች የማጋለጥ ዘመቻ በሚገባ ተረድቶታል።

ዛሬ  ጭቁን  መለዩ ለባሾችና ተራማጅ መኮንኖችን የሚገድሉት፣ የጭቁንን ሕዝብ ልጆችን እየፈጁ ያሉት፣ ተራማጅ ዜጎችን የሚቀጥፉት የኢህአፓ ግልገል ፋሽስቶች እንደሆኑ በሚገባ አውቆታል። ስለሆነም ኢህአፓን አክ እንትፍ ብሎታል። እነዚህ ኢህአፓን ከሞት አፋፍ ለመመለስ  የሚፈጨረጨሩ አድሃሪ መኮንኖችና ቢሮክራቶች ፊት ለፊት መጥተው “ኢህአፓ የእናንተው ነውና እቀፉት” ለማለት አልደፈሩም። ይሞክሩት። ሰፊው ሕዝብ እንደሆነ የተፋውን እክታ መልሶ አይውጥም። “ኢህአፓ” የናንተ እንጂ የኛ አይደለም ብሎ እነዚህን አድሃሪዎች አቋም እስከመጨረሻው ይታገለዋል። ድሮውንስ የነፍሰ ገዳዮች ጠበቃ መሆናቸውን ሰፊው ሕዝብ እንዳያውቅባቸው አይደል እነርሱስ ስልጣን መከታ በማድረግ ከጀርባው የሚያሴሩት?

ዛሬ እንግዲህ፣ ኢህአፓ ላይ የሚወሰድ አቋም በአብዮትና በፀረአብዮት ላይ ከሚወሰድ አቋም ተለይቶ አይታይም። ኢህአፓ የተሳሳቱ ተራማጆች ድርጅት ነው የሚል ሰበብ ሰጥተው እንደገና እንዲያንሰራራ የሚደክሙ ኃይሎች ቀልባሾች ናቸው። ኢህአፓ የተሳሳቱ ተራማጆች ድርጅት መሆኑ አክትሞ የጠላቶች በተለይም የቢሮክራሲውና የሌሎችም አድሃሪዎች መጠቀሚያ፣ የውጭ አድሃሪዎች ላይ የሆነ ድርጅት ነው የሚሉት ደግሞ አብዮታዊያን ናቸው። ይህንን በመጠኑ እናብራራ።

የተሳሳቱ ተራማጆች አቋማቸውን የማርክሲስት ሌኒኒስት መርህ በሆነው ሂስና ግለ ሂስ አስተካክለው ወደ አብዮት ሰፈር ካልተመለሱ፣ አድሃሪው እየገፋቸው፣ እያጥለቀለቃቸውና እየዋጣቸው በውስጥ አርበኝነት /5ኛ ኮሎመን፣ ረድፍ፣ የሚባለው/ እንደሚያከትሙ ታሪክ ደጋግሞ አሳይቷል። በብዙ የአውሮፓ አገሮች ለፋሽስቱ ሂትለር ወረራ ድሎች ጥርጊያውን የሰሩት እነዚህ አይነቶቹ የውስጥ አርበኞች ናቸው። በሩሲያ፣ በስፔን….. የነበረውን የውስጥ አርበኞች ሚና ማወቅ ለኢትዮጵያ አብዮት እጅግ ትምህርታዊ ነው። ለጊዜው የሶቪዬት ህብረትን ምሳሌ እንጥቀስ።

ትሮትስኪ፣ በፀረቦልሽቪክነቱ ለረዥም ጊዜ የታወቀ ቢሆንም በተለይ ከየካቲት 1917 እንቅስቃሴ በኋላ ቦልሽቪኮች ጋር መደባለቁ ይታወሳል። ቡካሪን፣ ካሜኔቭ፣ ሲኖቭየቭ የተባሉትም የረዥም ጊዜ የቦልሽቪክ ፓርቲ አባሎችና መሪዎች ነበሩ። በየጊዜው ስህተተኛ አቋም ወስደው በሌኒንን ታርመዋል። ታላቁ ሌኒንን ሞቶ ስታሊን እንደተተካ፣ ከነዚህ የጠቀስናቸው ሰዎች አንዴ ከቀኝ አንዴ ከ“ግራ” የስታሊንና የቦልሽቪክ ፓርቲን መስመር ይቃወሙ ነበር። በፓርቲው ውስጥ በነርሱ አቋምና በነስታሊን አቋም ላይ ሰፊ ውይይት እየተካሄደ ለነሱ የግለሂሰ ማድረጊያ ሰፊ እድል ተሰጣቸው። አልተጠቀሙበትም። በስህተታቸው ገፉበት። በዚህ ሁኔታ ቀጥለውም፣ በመጨረሻ የነሂትለር መጠቀሚያ ሆነው አረፉት። በሶቪየት ህብረት ውስጥ፣ የስታሊንን አመራርና ውስጥ ውስጡን አዳክሞ ለሂትለር ድል ጥርጊያ መንገድ እንዲከፍት የታቀደውን 5ኛ ረድፍ በመባል የታወቀውን የውስጥ አርበኞች ቡድን አቋቋሙ። ታላቁን ስታሊን ለመግደል ያደረጉት ብዙ ሙከራ ቢከሽፍም እነኪሮቭን፣ እነጎርኪን የመሳሰሉ መሪ ቦልሽቪኮችን ገድለዋል። በወታደሩ ውስጥ ክፍፍል እንዲመጣ ብዙ ጥረዋል፣ የኢኮኖሚ ውድቀት እንዲደርስ ከፍተኛ አሻጥሮችን አደራጅተዋል።…. ታሪኩ ብዙ ነው።

ዛሬም፣ ኢህአፓ የመላ አድሃሪዎች “5ኛ ረድፍ” በመሆን በማገልገል ላይ ነው። መላው አደሃሪም እንድታንሰረራ የሚፍጨረጨርላት የቀልባሾችና የፋሽቶች የውስጥ አርበኛ በመሆኗ ነው። ቢሮክራሲና አድሃሪ መኮንኖች ለዚህ የውስጥ አርበኝነት ሚና ኢዲዩን ለምን እንዳልመረጡ ግልጽ ነው። ሰፊው ሕዝብ በመሳፋንቱ ላይ ያለው ጥላቻ ከፍተኛ ነው።  ኢዲዩ የመሳፍንት ድርጅት መሆኑን ተነቅቶበታል። ከላይ እንዳልነው ዘመኑ “ከፍቶ” የተራማጅ ካባ ሳይለበስ አድሃሪ ትግል ማካሄድ አይቻልምና እነ መንገሻ ስዩም ራሳቸው እንኳ “የምን ዘውድ፣ ዴሞክራሲ እንጂ” ብለው ነው የተሰለፉት። ግን እንደ መንገሻ እንደተደራጁ ቢኳኳሉም ስማቸው ብቻ ሲጠራ የሚዘገንነው ብዙ ስለሆነ ኢዲዩ ለነቁት አድሃሪዎ ለነተስፋዬ ታደሰና ለአድሃሪ መኮንኖች ብዙ የማያደምቅ የተራማጅ ካባ ስለሆነባቸው ሊያጠልቁት አልፈለጉም። የተመኙት ደመቅ ያለ የተራማጅ ካባ ያላትን ኢህአፓን ነው። ስለሆነም፣ ኢህአፓ ውስጥ ያሉትን የተሳሳቱ ተራማጆች ለመመለስ ሳይሆን ኢህአፓን መሳሪያ አድርገው አብዮታችንን ለመቀልስ ተነስተዋል።

እኛ አብዮታዊያን፣ ኢህአፓ የአድሃሪዎች ሁሉ የውስጥ አርበኛ ሆናለች ስንል በውስጧ ዛሬም የተሳሳቱ ተራማጆች እንዳሉ እነርሱንም ለመሳብ መሞከር እንደሚያስፈልግ በመካድ አይደለም። ከላይ ደጋግመን እንዳነሳነው፣ ኢህአፓ

ዛሬ የተሳሳቱ ተራማጅ አባሎችዋ ድምጻቸውን ማሰማት የማይችሉባት፣ የኢህአፓን ግንኙነቶች ሊረዱ የማይችሉባት ድርጅት ሆናለች የሚል አቋም ስላለን ነው። በኢህአፓ ውስጥ ዛሬም ያሉ የተሳሳቱ ተራማጆች ወደ አብዮቱ ሰፈር እንዲመለሱ ከኢትዮጵያ አብዮታዊያን የበለጠ የሚፈልግና ለዚህም የሚታገል የለም። እንዲያውም፣ ለነዚህ አይነቶቹ የኢህአፓ አባሎች መሳሳት አብዮታዊያን የራሳቸውን ስህተቶችና ዳተኝነት ተጠያቂ እንደሚያደርጓቸው አይክዱም። ስለሆነም፣ ኢህአፓ የአድሃሪ መሳሪያ መሆኗን በማጋለጥ፣ ከእንግዲህ ይህ ድርጅት ለጸረአብዮት እንጂ ለአብዮት የማያገለግል ድርጅት መሆኑን በማሳየት የተሳሳቱት ተራማጆችን ይህንኑ ተረድተው ተገቢ ግለሂስ በማድረግ ወደ አብዮቱ ሰፈር እንዲመለሱ ይታገላሉ። ይህ ደግሞ በአያሌ ቦታዎች በየቀኑ እየተደረገ ነው።

ከላይ ስለ ፋሽስቶች አምስተኛ ረድፍ አንስተን ነበር። እነስታሊን፣ እነትሮትስኪ “ጓዶች” የነበሩ ጊዜ በፖለቲካ መስመር ተከራክረው ሊመልሷቸው ብዙ ጥረዋል። ከዚያ ይህንን የቀልባሾችና የፋሽስቶች የውስጥ አርበኝነታቸውን ከተገነዘቡትና ከደረሱበት በኋላ በነትሮትስኪ እና በነቡካሪን ቡድን ላይ ተገቢውን አብዮታዊ እርምጃ  ወሰዱ። በዚህም የቀልባሾችና የፋሽስቱን “አምስተኛ ረድፍ” በሶቪየት ህብረት ውስጥ ደመሰሱ። በ1941 በሶቪየት ህብረት የአሜሪካን አምባሳደር የነበረው ሰው ለአሜሪካን መንግሥት በላከው ራፖር “ሂትለር እንደነ ኖርዌይ ሶቭየት ህብረትን ሊያሸንፍ አይችልም። ምክንያቱም በሶቪየህብረት ውስጥ “አምስተኛው ረድፍ” ቀደም ብሎ ተደምስሷልና ብሎ ነበር። በታላቁ ስታሊን መሪነት የሶቪየት ሕብረት ሰፊ ሕዝብን ወረራ ከመታበት ምክንያቶች አንዱ የእነትሮትስኪና የነቡካሪን የውስጥ አርበኞች ቡድን አስቀድሞ በመደምሰሱ ነበር።

አዎ ቀልባሾችም ተራማጆችም ከታሪክ ይማራሉ። የኢትዮጵያ ቀልባሾች፣ አድሃሪ መኮኖችና ቢሮክራቶች፣ ሂትለር ለነትሮትስኪ ቡድን ሲያደርገው እንደነበረው ሁሉ፣ ኢህአፓ እንዳይደመሰስና እንዲያንሰራራ ይፍጨረጨራሉ። የኢትዮጵያ አብዮታዊያን ደግሞ፣ ስታሊን እንዳደረገው ሁሉ፣ ኢህአፓ የተባለውን የውስጥ አርበኛ ደምስሰን አብዮታችንን ከውጭ ጠላት እንከላከል ብለን ተሰልፈናል።

በመጨረሻ፣ ለነቁ አድሃሪ መኮንኖችና ቢሮክራቶች ሳይሆን፣ ኢህአፓ ‘የተሳሳቱ ተራማጆች ድርጅት ነው’ ብለው ለሚያምኑ አድርባዮችና በዚህ ድርጅት ውስጥ ላሉ የተሳሳቱ ግለሰቦች አንድ ነገር ግልጽ ማድረግ እንወዳለን። ኢህአፓ በተለይ ከዓመት ወዲህ በምድረ አድሃሪ ተጥለቅልቃ ጸረ አብዮት ኃይሎች እጅ ገብታለች። እነዚህ ፀረ አብዮት ኃይሎች የሚያሞግሷት በቃላት ብቻ አይደለም። በድርጅትም ተሳስራቸዋለች። ከእንግዲህ እርሷን ጎትቼ ወደ አብዮት ሰፈር አመልሳለሁ የሚል አድርባይ እራሱ ተጎትቶ ፀረ አብዮት ሰፈር መግባት የፈለገ እንደሆነ ብቻ ነው። እርሷ እንደሆነ ዳግም ላትመለስ ከአብዮት ሰፈር ወጥታ ፀረ አብዮት ሰፈር ተደላድላለች።የነቁ አድሃሪዎችን፣ አድሃሪ መኮንኖችንና ቢሮክራቶች ደግሞ አንድ ግልጽ ነገር እንንገራቸው። ዛሬ በኢህአፓ የጀመራችሁት በግልጽ አድሃሪ ድርጅቶችን እንቀፍ የሚል ጥሪ ለነገ ኢዲዩ ግብዣ መንደርደሪያ ነው። ዛሬ በኢህአፓ ከቀናችሁ፣ ነገ ደግሞ “ኢዲዩ እኮ የዘውድ አገዛዝ የሚፈልግ አይደለም። ፕሮግራሙን ተመልከቱ፣ ከእርሱም ጋር ተባብረን ‘የውጭ ጠላት’ እንመልከት ልትሉን እንደምትዘጋጁ ለእኛ ገልጽ ነው። ስለሆነም፣ ኢህአፓ እንዲያንሰራራ የምታደርጉትን ትግል ሁሉ የኢትዮጵያን አብዮት ለመቀልበስ ከታደርጉት ትግል ነጥለን አናየውም። እንደማንኛውም የቅልበሳ ትግል ሁሉ እንቋቋመዋለን። ኢህአፓን አንቅሮ ከተፋው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጋርም እናከሽፈዋለን።

ኢህአፓ እንዲያንሰራራ የሚደክሙ ቀልባሾች ይውደሙ!!
የጭቁኖችና የተራማጆች ህብረት ይጠንክር!!
የነቃ፣ የተደራጀና የታጠቀ ሰፊ ሕዝብ ቀልባሾችን ይደመስሳል!!
Scroll to Top