የመላ ኢትዮጵያ ሶሻሊስት ንቅናቄ (መኢሶን) ማኅደር
ይህ «ተራማጅ» ድረ-ገጽ የመላ ኢትዮጵያ ሶሻሊስት ንቅናቄ (መኢሶን)፣ በምሥጢር ከተመሠረተበት ከነሐሴ 1960 ዓ.ም. በህቡዕና በይፋ የታተሙ ጽሑፎች፣ ጋዜጣዎች፣ ሰነዶች፣ ፎቶዎችና የሰማዕታት ዝክሮችን ለአንባቢያን አሰባስቦ ያቀረበ ማኅደር ነው።
ይህ ማኅደር የመኢሶንን ታሪክ በሰነዶች አስደግፎ ለማቅረብና ድርጅቱ በኢትዮጵያ ሕዝቦች የነጻነት፣ የእኩልነትና የፍትህ ትግል ውስጥ ያበረከተውን አስተውጽኦ ለአንባቢያን እውቀት እንዲሁም ለታሪክ ተመራማሪዎችና ጸሐፊዎች ማጣቀሻ ምንጭ እንዲሆን የተዘጋጀ ነው።
«ተራማጅ» የሚለው ስም ወደፊት መገስገስን፣ እውቀትንና ስር ነቀል ለውጥን የሚያመለክት ሲሆን፣ የአንጋፋ ተራማጆች የንባብ፣ የድርጅት፣ የመጠይቅና የምርምር እሴቶች በዘመናዊው የዲጂታል መድረክ ላይ ህያው በማድረግ አሁንም የማህበረሰባዊ እድገትና ታሪካዊ እውቀት ፍሰት መሸጋገሪያ ድልድይ ሆኖ እንዲያገለግል ታስቦ የተመረጠ ነው።
ይህ ድረ-ገጽ «ተራማጅ» በሚል ስም የተሰየመበት ሌላው ምክንያት በ1967 ዓ.ም. (1975 እ.ኤ.አ.) መኢሶን ፣ በአዲስ አበባ ከተማ አራት ኪሎ የከፈተውንና በኢትዮጵያ ታሪክ መጀመሪያ የሆነውን “ተራማጅ የመጽሐፍ መደብር”ን ለመዘከር እንዲሁም በህቡዕና በይፋ የተካሄደውን የኢትዮጵያ ተራማጆች ረጅም የፖለቲካዊ እና ማኅበራዊ አብዮታዊ ትግል ውርስ ለማክበር ነው።
ይህንን ድረ-ገጽ በግል ፈቃደኝነት ተነሳስተንና አደራጅተን ማኅደሩን ለአንባቢያን የምናስተናግድው፤ ቀደም ባሉት አመታት የመኢሶን አባሎች የነበርን ግለሰቦች ነን።